Administrator

Administrator

አደጋዎቹ 100 ያህል ሰዎችን ለሞት ዳርገዋል
ጎርፉ ተጨማሪ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊያፈናቅል ይችላል

   በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ከ20 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁንና መንግስትም 100 ያህል ዜጎች በአደጋዎቹ ለሞት ተዳርገዋል ማለቱን አልጀዚራ ዘገበ፡፡
በአገሪቱ በመከሰት ላይ ያሉት የጎርፍ አደጋዎች ዜጎችን ከማፈናቀል ባለፈ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች እርዳታን በማከፋፈል እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር የኢትዮጵያ ተወካይ ፖል ሀንድሊም የተፈጥሮ አደጋዎቹ በቀጣይ ሰብሎችንና እንስሳትን ከማውደም ባለፈ ዜጎችን ለከፋ ችግር ሊያጋልጡ ይችላሉ ማለታቸውን ገልጧል፡፡
የእርዳታ ድርጅቶችም የጎርፍ አደጋዎቹ ቀጣይ እንደሚሆኑና ሌሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊያፈናቅል እንደሚችል ግምታቸውን መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የተፈጥሮ አደጋዎቹ የተከሰቱባቸው አንዳንዶቹ አካባቢዎች የድርቅ ተጎጂ መሆናቸውንና ዜጎችን ለተጨማሪ ችግር መዳረጋቸውን አስረድቷል፡፡

የዘንድሮ የግንቦት 20፣ ሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዮ በአል - ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችንና ፈተናዎችን በመገምገም እንደሚከበር መንግስት የገለፀ ሲሆን አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች የግንቦት 20ን ትሩፋቶች በመተቸትና በማወደስ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በሰጡት አስተያየት፤ በ1983 ዓ.ም ለውጡ ሲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት አመራር ተፈጥሮ፤ ሀገሪቱ ለውጥ ታመጣለች የሚል ተስፋ ሰንቀው እንደነበር ጠቁመውና ዛሬ ላይ ሆነው ያለፈውን 25 አመት ሲገመግሙት ግን ያንን ተስፋቸውን በተግባር እንዳላዩት ይናገራሉ፡፡ የአንድ መንግስት ስኬታማነት በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ እድገት ብቻ አይመዘንም ያሉት አቶ ግርማ፤ ዋናው ስኬት የሰው ልጅ ሠብአዊ መብትና ነፃነት ሲከበር ነው ብለዋል፡፡ የኢኮኖሚው እድገትም ቢሆን ከሀገሪቱ ህዝብ 20 ሚሊዮን ያህሉን ከእለት ተረጅነት አላወጣም ሲሉ ተችተዋል- አቶ ግርማ፡፡
“ባለፉት 25 ዓመታት ቃልና ተግባር አልተገናኙም” ያሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ የግንቦተ 20 ትልቁ ትርፍ የደርግ መንግስት መወገዱ ነው ብለዋል፡፡ የመንግስት ለውጡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፤ ሆኖም ባለፉት 25 አመታት ይህ እንዳልተሳካ አስረድተዋል፡፡
“ግንቦት 20 በኢኮኖሚ እድገት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል” ያሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በዚያው ልክ የሀገሪቱን አንድነት እስከዛሬ ድረስ ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም በተጨማሪ ሀገሪቱን ወደብ አልባ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የአንድ ፓርቲ የስልጣን የበላይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረና ነፃ ሚዲያዎች እየደበዘዙ መምጣታቸውንም አቶ ልደቱ ተችተው ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ የቀድሞው ታጋይና አመራር የሆኑት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በ25 አመታት ውስጥ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊውና በፖለቲካዊው ዘርፍ በርካታ ድሎችና ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በአሁን ወቅት ዋነኛ አደጋ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም መንግስት በጠንካራ ትግል ላይ ነው ብለዋል፡፡   “ግንቦት 20 የመንግስት ሣይሆን የስርአት ለውጥ ነው ያመጣው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤  ስርአቱ እየተከተለ ያለው መሠረታዊ አቅጣጫ ትክክል መሆኑን ጠቁመው፤ የተገኙ ጠንካራ ድሎች የበለጠ የሚጠናከሩበትና ድክመቶች የሚታረሙበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል፡፡ ይሄን ስርአት ካለፉ ስርአቶች ጋር ማነፃፀር ተገቢ አለመሆኑን የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ “ይሄ መንግስት ነገ ከነገ ወዲያ ሊሄድ ይችላል፤ የስርአት ለውጡ ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡ 

• ከ2 ሺህ በላይ ቤቶች እየፈረሱ መሆኑ ታውቋል
• ግጭቱን ተከትሎ ለ3 ቀናት ት/ቤቶች ተዘግተዋል

    በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ገርጂ ወረገኑ በተባለ አካባቢ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ ተገንብተዋል የተባሉ ቤቶችን ለማፍረስ በተሰማራ የደንብ ማስከበር ግብረ ኃይልና በነዋሪዎች መካከል  ውዝግብ ተነስቶ ከፖሊስ ጋር በተከሰተ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በግርግሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ሲናገሩ የፖሊስ ምንጮች በበኩላቸው፤ 3 ፖሊሶችን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ከመድረሱ በቀር የሞተ ሰው ስለመኖሩ አልተረጋገጠም ብለዋል፡፡ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታልም ከግርግሩ ጋር በተገናኘ ያስተናገደው አስክሬን አለመኖሩን አስታውቋል፡፡ በቦታው ላይ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተሰሩ ናቸው ያላቸውን ከ2 ሺህ በላይ ቤቶች ለይቶ በማፍረስ ላይ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ኃላፊዎች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ “ከገበሬው ላይ በውድ ዋጋ የገዛነው መሬት ላይ ጥሪታችንን አሟጠን የሰራነው ቤታችን አማራጭ ሳይሰጠን በኃይል በመፍረሱ ሜዳ ላይ ተበትነናል” ሲሉ አማረዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ኃይሎች ከአፍራሽ ግብረ ኃይሉ ጋር በመሆን ቤቶቹን ማፍረስ መጀመራቸውን የሚገልፁት ተጎጂዎቹ፤ በኃይል እቃችንን እንድናወጣ ከተደረገ በኋላ በ7 የመቆፈሪያ ከባድ ማሽኖች (ስካቬተሮች) ቤቶቹን ማፍረስ ጀመሩ ይላሉ፡፡ እስከ ትናንት ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ የቤቶቹን ፍራሽ፣ ቆርቆሮዎችን ጨምሮ በደንብ ማስከበሮች ተጭኖ ተወስዷል ብለዋል፡፡ በነዋሪዎችና በፖሊስ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎም ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ በሚኖርበት በዚህ አካባቢ ከረቡዕ ጀምሮ መንቀሳቀስና ከቤት መውጣት የሚቻል ባለመሆኑ ለ3 ቀናት ት/ቤቶች መዘጋታቸውንና ትምህርት መቋረጡን ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ውዝግብ ከባድ የመሳሪያ ተኩስ እንደነበር የጠቀሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ አምቡላንሶች የተጎዱ ሰዎችን ሲያመላልሱ እንደዋሉ ያስታውሳሉ፡፡ ምንጮቻችን፤ ከቤት መውጣት ባለመቻላችን እስከ 12 ሰው መሞቱን ከመስማታችን በቀር ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉ ሲሆን የከተማዋ ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ም/ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተሰማ ነጋሽ በበኩላቸው፤ “ፖሊስ ላይ መጠነኛ ድንጋይ ከመወርወሩ በቀር የተባለውን ያህል ጉዳት አልደረሰም፣ ጉዳት ደረሰብኝ ያለ አካልም የለም” ብለዋል፡፡
ቤታቸው እየፈረሰባቸው መሆኑን ለአዲስ አድማስ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ አብዛኞቹ በቀን ሰራተኝነት የሚተዳደሩ ሲሆን ከገበሬው ላይ ከ50-100 ካሬ ሜትር ቦታ፣ አንዱን ካሬ ሜትር እስከ 1500 ብር ሂሳብ እየገዙ፣ ከ20-30 ቆርቆሮዎችን የፈጁ ቤቶችን ቀልሰው ሲኖሩ እንደ ነበር ገልፀዋል፡፡ አካባቢው መሰረተ ልማት ያልተሟላለት መሆኑን የሚጠቅሱት ነዋሪዎቹ፤ “ከዛሬ 6 እና 7 አመታት በፊት ቦታውን ገዝተን ቤት ስንሰራ ወረዳውም ሆነ ክ/ከተማው ህገወጥ ናችሁ አላሉንም ነበር” ሲሉ ያማርራሉ፡፡ የቀን ስራ ሠርተን ያጠራቀምነውን ገንዘባችንን በቦታ ግዢና በቤት ግንባታው ላይ ካዋልንና ተረጋግተን መኖር ከጀመርን በኋላ መንግስት ቤታችንን ማፍረሱ ተስፋ-ቢስ አድርጐናል የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ መውደቂያ አጥተን ከነቤተሰባችን ሜዳ ላይ ተበትነናል ብለዋል፡፡
የወረዳው የስራ ኃላፊዎች ባለፈው ሚያዚያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም በቦታው ተገኝተው ቤቶቹ ህገ - ወጥ መሆናቸውን ሲነግሩን እንዳያፈርሱብን ብንማፀንም አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡንም ነበር ያሉት ቅሩታ አቅራቢዎቹ፤ እንዳልሰጧቸውና ባለፈው ረቡዕ በድንገት ቤቶቹን ማፍረሣቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ቤቶቹ በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተገነቡ በመሆኑ ህጉን ተከትዬ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል፡፡ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ም/ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተሠማ፤ ከ2ሺህ በላይ ቤቶች በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተሠሩ ሆነው በመገኘታቸው እንደሚፈርሱና በቀጣይም ተጨማሪ ህገ-ወጥ ቤቶችን የመለየት ስራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በህገ መንግስቱ መሬት መሸጥ መለወጥ እንደማይቻል የጠቀሱት ኮማንደሩ፤ ግለሰቦቹ በየትኛውም ህግና ደንብ ህገ-ወጥ ናቸው ይላሉ፡፡ ህጋዊ መሆን የሚችሉበት መንገድም እንደሌለ አክለው ገልፀዋል፡፡  


ንብረትነቱ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበረውና ባለፈው ህዳር ወር ላይ በታዋቂው ዓለምአቀፍ አጫራች ኩባንያ ክርስቲ አማካይነት በጨረታ ሊሸጥ በዝግጅት ላይ ሳለ፣ የንጉሱ ቤተሰቦች ባሰሙት ተቃውሞ ሳቢያ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታግዶ የቆየው 1 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የወርቅ ሰዓት በቅርቡ ዳግም ለጨረታ ሊቀርብ እንደሚችል ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
ንጉሱ ከአንድ ጣሊያናዊ ባለሃብት በስጦታ እንዳገኙት የተነገረለትና ፓቴክ ፊሊፒ የሚል ስያሜ ያለው ይህ እጅግ ውድ የወርቅ ሰዓት፣ ጄኔቫ ውስጥ ለጨረታ ሊቀርብ ሲል የንጉሱ ቤተሰቦች “ሰዓቱ ከንጉሱ የተዘረፈ ነው፤ ሊመለስልን ይገባል” በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ የጄኔቫ ፍርድ ቤት ሽያጩ ለጊዜው እንዲሰረዝ በመወሰን ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም ሰዓቱ የንጉሱ ቤተሰቦች እንዳሉት ተዘርፎ የተወሰደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ አለማግኘቱንና በመጪዎቹ ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም ሰዓቱን ለሽያጭ እንዳያቀርብ በአጫራቹ ድርጅት ላይ የጣለውን ጊዚያዊ እግድ ያነሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ኦሊቨር ጆርኖት ተናግረዋል፡፡
ጊዚያዊ እግዱ የሚነሳ ከሆነ አጫራቹ ድርጅት ሰዓቱን ዳግም ለጨረታ ሊያቀርበው እንደሚችል የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም በንጉሱ ቤተሰቦች፣ በአጫራቹ ድርጅትና ሰዓቱን ከንጉሱ በስጦታ ያገኘነው ስለሆነ ባለቤትነቱ የኛ ነው በሚሉት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም አቡድ ቤተሰቦች መካከል ቀጣይ የባለቤትነት ውዝግብ ሊፈጥር እንደሚችል ገልጧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን አቪየሽንን የ2016 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማት ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደ ስነ-ስርዓት መቀበሉን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ በፋይናንስ እንቅስቃሴና ትርፋማነት፣ በረራን በማዘመን፣ የበረራ መስመር ትስስርን በማስፋፋት፣ በአጠቃላይ የደንበኞች እንክብካቤና በአህጉሪቱ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ልማት አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ በአመቱ ባስመዘገበው የላቀ ውጤት ለሽልማት መብቃቱ ተነግሯል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማቱን የተቀበሉት የአየር መንገዱ ቺፍ ኦፐሬቲንግ ኦፊሰር አቶ መስፍን ጣሰው፤ ሽልማቱ አየር መንገዱ ላለፉት 70 አመታት አፍሪካን አንድ ለማድረግና ከተቀረው አለም ጋር ለማቀራረብ በቁርጠኝነት መስራቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡ ሽልማቱን ያበረከቱት የአፍሪካን አቪየሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኒክ ፋዱግባ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ መሪነቱን ይዞ መቀጠሉንና ለአፍሪካ ትልቅ የኩራት ምንጭ መሆኑን በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

    የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፉ ዳኘው የሜቴክ
ፕሮጀክቶችን የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ከትናንት በስቲያ በተመረቀበት ወቅት ስኳር ፕሮጀክቶችን
አስመልክቶ በተለይ በአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ዘጋቢ ፊልም መስራት ያስፈለገበት ምክንያት መነሻው ምንድነው?
ጥናት ሰርቼ ነበር፡፡ የታገልኩለት ስለሆነ ጥናት ሰርቼ ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡ ጽሑፉ፣ ከጋዜጠኛዋ ፍፁም የሺጥላ የዘጋቢ ፊልም መነሻ ሀሳብ ጋር በጣም የተቀራረበ ስለነበር ጽሑፉን ሰጠኋት ያንን የማዳበር ስራ፤ ከመስራት በስተቀር ተነሳሽነቱ የጋዜጠኛዋ ነው፡፡ዘጋቢ ፊልሙ ለመስራት ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ ወሰደ? ፊ ልሙን ላይ፤ የብረታብረት ኮርፖሬሽን ስራዎች ሁሉውጤታማ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው ተብሏል፡፡ ግን በፓርላማ እና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ደግሞ፣ በተለይ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ አገሪቱ ለብዙ ወጪ ተዳርጋለች ተብላችሁ ተተችታችኋል፡፡ የመጀመሪያውን ጥያቄ ስንመለከት፣ ፊልሙን ያዘጋጁዜጐች፣ ከፊልሙ የጽሑፍ ዝግጅት ጀምሮ፣ በቀረፃ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ሲሰሩ ከሶስት  ወር በላይ ሳይወስድ አይቀርም፡፡ መነሻ ሃሳቦቹ ከዚያ ቀደም ይላሉ፡፡ ብዙም ደክመውበታል፡፡ሁለተኛ ጥያቄሽን በተመለከተ፣ በዋናነት ማለት የምፈልገው፣ ምንም ክስ ቢነሳም፣ ለእኔ ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውና የሚመራው የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ፣ የሚሳካ መሆኑ ነው፡፡ በአንዳንድ ሰዎች ክስ ቢነሳም፣ ድክመታችንን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በዚያው ልክ፣ ንካሬያችንንም የሚያሳይ አይደለም፡፡ዋናው ጉዳይ እኛ ድክመት ቢኖርብንም ባይኖርብንም፣ የልማታዊ ኢኮኖሚ አቅጣጫ አይቆምም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ያድጋሉ፡፡ እኔ ካጠፋሁ ልቀጣ እችላለሁ፡፡ ተቋማት ግን ይቀጥላሉ፤ መቀጠልም አለባችሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ፣ በግሌ አስተያየት፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ውድቀት
አለው ብዬ አላምንም፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን የወደቀበት ምክንያት በእንቶኔ ነው በእከሌ ነው
ቢባልም፣ አይገባኝም፡፡

አንጋፋው ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህና “ዘመናይ ማርዬ” በተሰኘው አልበሙ የሚታወቀው
ልጅ ሚካኤል የሚያቀነቅኑበት “አዲስ ኮንሰርት” የዛሬ ሳምንት ከሚሊኒየም አዳራሽ ጀርባ በሚገኘው ፋና ፓርክ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ የጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ታደሰ ታምራት አስታወቁ፡፡ ከሚካኤል በላይነህና ከልጅ ሚካኤል በተጨማሪ ያሬድ ነጉ (የመርካቶ አራዳ)፣ ዳዊት ነጋ (ባባ ኤለን)፣ አስገኘው አሸኮ (ዲንዴሾ) እና በሀይሉ ባዩ (በሃይሉ ማታ) ታዳሚውን እንደሚያዝናኑ የገለፁት አቶ ታደሰ፤ ዲጄ ኪንግስተን (ወዝወዝ አዲስ)፣ ዲጄ ሼሪ፣ ዲጄ የሚ እና ዲጄ ሮፊም መድረኩን ያደምቁታል ብለዋል፡፡ ኮንሰርቱ የፌስቲቫል ይዘት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን ሁለት እውቅ ስጋ ቤቶች፣ ስምንት ሬስቶራንቶችና ስድስት ባሮች ይሳተፉበታልም ተብሏል፡፡ የመግቢያ ዋጋ እስከ አርብ 12 ሰዓት ለሚገዙ መደበኛው 200 ብር፣ ቪአይፒ 500 ብር ሲሆን በዕለቱ ትኬት ለሚገዙ መደበኛው 300 ብር እንደሚሆንና ቪአይፒው ላይ ጭማሪ እንደማይደረግ ተነግሯል፡፡ ቦሌ የሚገኘው ፋና ፓርክ 10ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው የተገለፀ ሲሆን ይህም ህዝቡ ሳይጨናነቅ እንደ ልቡ እንዲዝናና ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያ የኮንሰርቱ የክብር ስፖንሰር እንደሆነ ታውቋል፡፡

      የገጣሚ ዮሐንስ ሞላ ሁለተኛ ስራ የሆነው “የብርሃን ሰበዞች” የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ከነገ
በስቲያ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ከምሽቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃል፡፡በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ውስጠ ወይራ የሆኑ ከሰባ በላይ ግጥሞችን ያካተተው መጽሐፉ፤ በ110 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ46 ብር፣ ለውጭ አገራት በ18 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ከመጽሐፉ የተመረጡ ግጥሞች የሚነበቡ ሲሆን ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያንም ግጥሞቻቸውን ለታዳሚው እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የግጥም መድበሉን ሊትማን መጽሐፍት መደብር ያከፋፍለዋል ተብሏል፡፡
ዮሐንስ ሞ ላ ከ ዚህ ቀ ደም በ 2005 ዓ .ም “የብርሃን ልክፍት” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ለአንባቢ ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን “ጠይም በረንዳ” በተሰኘው የራሱ ጦማር ላይ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በመፃፍ ይታወቃል፡፡ ገጣሚውበተጨማሪም የዘፈን ግጥሞችን የሚጽፍ ሲሆን ቀደም ሲ ል በ ግጥም የ ተሳተፈበት የ ፀደንያ ገ / ማርቆስ ዘፈን፤ ሁለት የአገር ውስጥ፣ አንድ አህጉር አቀፍ ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡

Saturday, 14 May 2016 13:44

የዘላለም ጥግ

ስለ አመራር)
• ድርጊትህ ሌሎችን የበለጠ እንዲያልሙ፣
የበለጠ እንዲማሩ፣ የበለጠ እንዲሰሩና
የበለጠ እንዲሆኑ ካነቃቃ አንተ መሪ ነህ፡፡
ጆን ኩይንሲ አዳምስ
• መሪ ማለት መንገዱን የሚያውቅ፣ በመንገዱ
የሚጓዝና መንገዱን የሚያሳይ ሰው ነው፡፡
ጆን ሲ.ማክስዌል
• በበግ የሚመራ የአንበሶች ሠራዊት
አያስፈራኝም፤ እኔን የሚያስፈራኝ በአንበሳ
የሚመራ የበጐች ሠራዊት ነው፡፡
ታላቁ እስክንድር
• ብርሃኑን ልታሳያቸው ካልቻልክ፣ ሙቀቱ
እንዲሰማቸው አድርግ፡፡
ሮናልድ ሬገን
• ስህተት ፈላጊ ሳይሆን መፍትሔ (መድሃኒት)
ፈላጊ ሁን፡፡
ሔነሪ ፎርድ
• ሰዎች በመሪና በአለቃ መካከል ያለውን
ልዩነት ይጠይቃሉ፡፡ መሪ ይመራል፤ አለቃ
ይነዳል፡፡
ቴዮዶር ሩዝቬልት
• እሴቶችህ ግልጽ ሲሆኑልህ ውሳኔዎችን
መወሰን ይቀልሃል፡፡
ሮይ ኢ ዲዝኒ
• ራዕይ ከሌለ ተስፋ የለም፡፡
ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
• መሪነት፤ ራዕይን ወደ እውነታ የመተርጐም
አቅም ነው፡፡
ዋረን ቤኒስ
• ለውጤት በቅጡ ከተጨነቅህ፣
በእርግጠኝነት ታሳካዋለህ፡፡
ዊሊያም ጄምስ
• ማሰብህ እንደሆነ አይቀርም፤ ስለዚህ ለምን
በትልቁ አታስብም?
ዶናልድ ትረምፕ
• ተነሳሽነት ከሌላቸው፣ መሪዎች በአመራር
ቦታ ላይ የተቀመጡ ተራ ሠራተኞች ናቸው።
ቦ ቤኔት
• የዛሬ አንባቢ፣ የነገ መሪ ይሆናል፡፡
ማርጋሬት ፉለር
• ኦርኬስትራን መምራት የሚሻ ሰው፣
ጀርባውን ለጀማው መስጠት አለበት፡፡
ማክስ ሉቻዶ

“ገዴ” እና “ቢሰጠኝ” በተሰኙ ቀደምት አልበሞቿ ተቀባይነትን ያገኘችው ዝነኛዋ ድምፃዊት ፀደንያ ገ/ማርቆስ፤ “የፍቅር ግርማ” የተሰኘ ሶስተኛ አዲስ አልበሟ ለአድማጭ ቀረበ፡፡ አልበሙ 11 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የተፈራ ደምሴ ግጥም የሆነው “ካምፕፋየር” የተሰኘ የእንግሊዝኛ ሙዚቃ እንደሆነ ድምፃዊቷ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ የአምስቱን ዘፈኖቿን ግጥም አንጋፋው ገጣሚ ይልማ ገ/አብ፣ አንዱን ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት ጌትነት እንየው፣ ሶስቱን ፋሲል ከበደ የተሰኘ አዲስ ገጣሚ፣አንዱን ደግሞ #ህመሜ” የተሰኘው ነጠላ ዜማዋ ገጣሚ አብዲ ራዋ የሰሩላት ሲሆን ዜማውን በአብዛኛው ራሷ ድምፃዊቷ እንደሰራችና አንዱን ሄኖክ መሀሪ እንደሰራላት ተናግራለች፡፡
“ካምፕፋየር” የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ሙዚቃ ቅንብር ኬሊ አለን የሰራላት ሲሆን  የሌሎቹን ቅንብር አቤል ጳውሎስ መስራቱንና አሳትሞ ያከፋፈለው ኤራ ኮሙዩኒኬሽንና ኤቨንት እንደሆነ ድምጻዊቷ ጠቁማለች፡፡  
 ጸደንያ በዘንድሮ ዓመት ብቻ የ“አፍሪካ ሚዩዚክ አዋርድ” (አፍሪማ)፣ የ“ለዛ አድማጮች” እና ለ“ሀሪየት” ፊልም በሰራችው የማጀቢያ ሙዚቃ የ#ጉማ አዋርድ” ሶስት ሽልማቶችን አሸናፊ ለመሆን የበቃች ሲሆን በአገራችን ብቸኛዋ የ“ኮራ አዋርድ” ተሸላሚ እንደሆነችም ይታወቃል፡፡