Administrator

Administrator

Saturday, 06 February 2016 11:11

የስኬት ጥግ

- ስኬት ምስጢር የለውም፡፡ የዝግጅት፣ ተግቶ
የመስራትና ከውድቀት የመማር ውጤት ነው፡፡
ኮሊን ፖል
- ከገንዘብ በቀር ምንም የማይፈጥር ቢዝነስ ደካማ
ቢዝነስ ነው፡፡
ሔነሪ ፎርድ
- አንተ አንድ ግሩም ሃሳብ ካለህ ሰዎች ሌላ 20
ያቀርቡልሃል፡፡
ሜሪ ቮን ኢብነር - ኢሼንባች
- ታላላቅ ኩባንያዎች የሚገነቡት በታላላቅ
ምርቶች ላይ ነው፡፡
ኢሎን ሙስክ
- መሸጥ የማይችል ከሆነ ፈጠራ አይደለም፡፡
ዴቪድ ኦጊልቪ
- ሌሎች ሰዎች ሲሸጡ እኔ እገዛለሁ፡፡
ጄ.ፓል ጌቲ
- ገንዘብ መስራት ቀላል ነው፡፡ በጣም የሚከብደው
ልዩነት መፍጠር ነው፡፡
ቶም ብሮካው
- ሁሉም ዘላቂ ቢዝነሶች የሚገነቡት በወዳጅነት
ላይ ነው፡፡
አልፍሬድ ኤ. ሞንታፔርት
- ቢዝነስ በራሱ ኃይል ነው፡፡
ጋሬት ጋሬት
- የሥራ ኃላፊ የውደሳ ጭብጨባዎችን አይሰማም።
አልቪን ዳርክ
- ስኬታማ ለመሆን ልብህን ቢዝነስህ ውስጥ፣
ቢዝነስህን ልብህ ውስጥ ማድረግ አለብህ፡፡
ቶማስ ጄ. ዋትሶን

Saturday, 06 February 2016 11:13

የዘላለም ጥግ

- እውነተኛ እጣ ፈንታችን ፍቅር ነው፡
፡ የህይወትን ትርጉም ለብቻችን ፈልገን
አናገኘውም - ከሌሎች ጋር ሆነን እንጂ፡፡
ቶማስ ሜርቶን
- እጣ ፈንታህ ቅርፅ የሚይዘው ውሳኔዎችን
በምታሳልፍባቸው በምትወሰንበት ቅፅበቶች
ነው፡፡
ቶኒ ሮቢንስ
- እያንዳንዱ ሰው የራሱን እጣ ፈንታ የመወሰን
መብት አለው፡፡
ቦብ ማርሊ
- እጣ ፈንታ የዕድል ጉዳይ አይደለም፡፡ የምርጫ
ጉዳይ ነው፡፡ ቁጭ ብለን የምንጠብቀው ነገር
አይደለም፤ የምናሳካው እንጂ፡፡
ዊሊያም ጄኒንግስ ብርያን
- ሰዎች እጣ ፈንታን አይቀርፁትም፡፡ ዕጣ ፈንታ
ለጊዜው የሚሆን ሰው ይፈጥራል፡፡
ፊደል ካስትሮ
- የአንተ እጣፈንታ የእኔ እጣፈንታ ነው፡፡ የአንተ
ደስታ የእኔ ደስታ ነው፡፡
አይስሎም ካሪሞቭ
- ሁላችንም ከእጣ ፈንታችን ጋር የታሰርን ነን፤
ራሳችንን ነፃ የምናወጣበት መንገድ የለም፡፡
ሪታ ሃይዎርዝ
- ሁሉም ሰው የየራሱ እጣ ፈንታ ፈጣሪ መሆን
አለበት፡፡
ማርቲን ዴላኒ
- እጣ ፈንታህን ተቆጣጠር፤ ያለበለዚያ ሌላ
ሰው ይቆጣጠረዋል፡፡
ጃክ ዌልሽ
- በእጣፈንታ፣ በእግዚአብሔር ጣልቃገብነትና
ተግቶ በመስራት አምናለሁ፡፡
ካትሪና ካይፍ
- ሁሌም ዲ ሞክራሲ ፍ ፁም እ ንዳልሆነ
ለማስረዳት ከመሞከር ወደ ኋላ ብዬ
አላውቅም፡፡ ነገር ግን ዕጣ ፈንታህን ለመቅረፅ
ዕድል ይሰጥሃል፡፡
ኤዩንግ ሳን ሱ ኬዩ
- ሁልጊዜ የሰውን ልጅ ለመብረር የሚያስችለው
ማሽን መስራት እጣ ፈንታዬ ነው አስብ ነበር፡፡
ሊኦናርዶ ዳቬንቺ
- የምትንቀውን ሥራ እየሰራህ እጣ ፈንታህን
እውን አታደርግም፡፡
ጆን ሲ. ማክስዌል
- ታሪካችን እጣ ፈንታችን አይደለም፡፡
አላን ኮኸን፡፡

አቤል በ6፣ ጀስቲን ቢበር በ5 ዘርፎች ታጭተዋል

   ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአር ኤንድ ቢ ሙዚቃ አቀንቃኝ አቤል ተስፋዬ ወይም ዘ ዊክንድ እና ታዋቂው ድምጻዊ ጀስቲን ቢበር የካናዳውያን የግራሚ ሽልማት ተብሎ በሚታወቀው የዘንድሮው የጁኖ የሙዚቃ ሽልማት በበርካታ ዘርፎች በመታጨት መሪነቱን መያዛቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘገበ፡፡
የ25 አመቱ ኢትዮ-ካናዳዊ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ በዘንድሮው 45ኛው የጁኖ አመታዊ ሽልማት በስድስት ዘርፎች መታጨቱን የገለጸው ዘገባው፣ አምናም በአመቱ ምርጥ አርቲስት እና በአመቱ የአር ኤንድ ቢ ሶል ሪከርዲንግ ዘርፎች ተሸላሚ እንደነበር አስታውሷል፡፡
አቤል በዘንድሮው የጁኖ ሽልማት በዕጩነት ከቀረበባቸው ስድስት ዘርፎች፣ የአድናቂዎች ምርጫ፣ የአመቱ ምርጥ አልበምና የአመቱ ምርጥ የዘፈን ደራሲ... ይገኙባቸዋል ተብሏል፡፡
ጀስቲን ቢበርና ሌላው ታዋቂ ካናዳዊ ድምጻዊ ድሬክም በ2016 የጁኖ አለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማት በአምስት ዘርፎች ለሽልማት መታጨታቸውን ያመለከተው ዘገባው፣ የሽልማት ስነስርዓቱ በመጪው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በካልጋሪ እንደሚካሄድም አክሎ ገልጿል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ወደጎረቤት አካባቢ ያለችን አንዲትን ለአቅመ - ሔዋን የደረሰች ኮረዳ ለወንድ ልጃቸው ፈለጓትና ሽማግሌዎች ወደልጅቷ ቤተሰቦች ተላኩ።
ሽማግሌዎቹ የልጅቱ ቤተሰቦች ዘንድ ሲደርሱ፣ ቤት ገብተው ቆሙ፡፡ የልጅቱ ቤተሰቦችና ዘመድ - አዝማድ ሁሉ በአንድ ተርታ ተሰድረዋል፡፡
አባት፤
“እህስ፤ ምን አግር ጣላችሁ ጎበዝ?”
ከሽማግሌዎቹ አንዱ፤
“ምን የመሰለ ለአቅመ - አዳም የደረሰ ጎበዝ ወንድ ልጅ አለን፡፡ ልጃችሁን ለልጃችን ትሰጡን ዘንድ ይኸው ከወዲያኛው አምባ መጥተናል” ሲሉ መለሱ፡፡
አባት፤
እንደዚህ ከሆነማ፣ እኛ እምቢ የምንልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ግን አንድ ቅድመ - ሁኔታ ማሟላት አለባችሁ”
“ምን?”
የልጅቷ ወላጆችም፤ “እንግዲያው በጥሞና አዳምጡን፡፡ ልጃችንን የምንሰጣችሁ ሃምሳ ሰው ይዛችሁ መጥታችሁ 1ኛ/ ሃምሳ በግ ቀርቦላችሁ የምትበሉ ከሆነ
         2ኛ/ ሃምሳ ጋን ጠላ የምትጠጡ ከሆነ
     3ኛ/ መላ የሚያውቅ ሰው፣ ግን መላጣ ያልሆነ ሰው ይዛችሁ ከመጣችሁ  ነው፤” አሉ
 የወንዱ ልጅ ወገኖች፤
“ሀሳቡን እንቀበላለን፡፡ ያላችሁትን 50 ሰው ይዘን እንመጣለን” ሲሉ ሀሳቡን መቀበላቸውን አረጋገጡ።
“እንግዲህ ከቆረጣችሁ የዛሬ 15 ቀን ኑ” አሉና ቀጠሯቸው፡፡
በቀጠሮው ቀን ሽማግሌዎቹ 50 ሆነው መጡ፡፡ 50 በጎች ቀረቡላቸው፡፡ እንዳጋጣሚ ይዘውት የመጡት መላ አዋቂ ሰው መላጣ ነው፡፡ “እንዴት እናድርግ መላጣ አይግባብን ብለዋል?” ብለው ጠየቁት፡፡
“ጥምጥም አምጡ፡፡ ቄስ ሆኜ እገባለሁ፡፡ ቄስ አይግባ አላሉ!” አለ፡፡
“የቀረቡትን በጎች እንዴት እንብላቸው?” አሉት፡፡
“አንድ በአንድ እየተረከባችሁ ለ50 ሰው ጥሬውን መቀራመት ነው” አላቸው፡፡
መላ አዋቂው እንዳለው አንድ አንድ በግ እየተቀበሉ ከጋኖቹ ጠላ እየቀዱ እያማጉ ጥብስቅ አድርገው በሉና ጠላውን ግጥም አድርገው ጠጡ፡፡
የሙሽሪት ቤተሰቦች አይሆንም ያሉት ነገር ሆነና ተሸነፉ፡፡ የግዳቸውን ልጃቸውን ለማስረከብ ተስማሙ፡፡ የወንድ ወገን “ሃይ ሎጋ!” አለ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሴት ወገን በኩል ለወንድ ወገን አካባቢ ሰዎች ስም ወጣላቸው፡፡ ለምን ቢሉ፣ ልብ ብሎ ላያቸው ጥሬውን ሲበሉ ነው የታዩት፡፡ ቢጠብሱት ኖሮ ቅባቱ ይዘጋቸው ነበር፡፡ ይሄን ተመርኩዞ፤
“አይጠብሴ” የሚል የቅፅል ስም ወጣላቸው፡፡
*          *         *
ሌሎችን አሸንፍበታለሁ ያልነው ዘዴ አንዳንዴ መሸነፊያችን ሊሆን ይችላል፡፡ በርካታ ህዝብ ዘክሮ መክሮ የሚያመጣው ብልሃት አይታወቅም፡፡ ዋናው ነገር የሚዘክር የሚመክረውን ህዝብ መሰባሰብ፣ መምረጥና ማደራጀት መቻል ነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የተበታተነ የህዝብ ሐተታ እንጂ የሰከነ ዕምነት ማፍራት አንችልም፡፡ የአስተሳሰብ አንድነት የዛሬ የሀገር ጥሪ ነው!
በጋራ አስቦ፣ በጋራ ተስማምቶ የጋራ ዓላማ መያዝ እጅግ ከባድ ተልዕኮ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ጠጣት ሰናይ ተግባር ስም የሚያስጠራ ምግባር ያስፈልጋል፡፡ ፀሐፍት፤ “ያለጥርጥር መልካም ሥራህ ካንተ ቀድሞ ይታወቃል፡፡ ክብርን ያመለካተ ከሆነ አንተ ወደ መድረኩ ትርዒት ሳትደርስ በፊት ብዙው ሥራህ ተከናውኖ ጠበቀህ ማለት ነው፡፡ አንዲት ቃል ሳትተነፍስ ጉዳይህ አለቀ” ይላሉ፡፡
ስለመልካምም ሆነ እኩይ ምግባር የማሳወቅ ታላቅ ኃላፊነት ያለባቸው ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ምንም ዋጋ ያስከፍላቸው የፈጠጠውን እውነት መራቅ የለባቸውም፡፡ በእርግጥ መንግሥትም ይህን ሀቅ ተገንዝቦ ሊያግዛቸው እንጂ ሊያስፈራራቸው አይገባም፡፡ እንደ ሙስና ያሉት መያዣ መጨበጫ ያጡ ድርጊቶች በሁሎች ርብርብ የሚጋለጡ መሆናቸውን አለመርሳት ነው፡፡
በሀገራችን የሚታየውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስናይ ኃምሌት ይከሰታል፡-
“…ኋላ ምን ሊታየኝ ኖሯል፣ ጊዜ ከፈተነው ሌላ
ምድር ዕፅዋት ብቻ አታበቅል፣ ያለሾህ ያላሜከላ
ወይንም የተፈጥሮ መልክ፣ ሲካበት ሞልቶ ድርጅቶ ብቻውን አደለም ከቶ
ግን እንደዚሁ እንደ ህንፃ፣ ላዩ በሰም አንፀባርቆ
አካባቢው በጌጥ ደምቆ
መሰረቱ ግን በግድፈት፣ በአገም ጠቀም ተደባብቆ
በመሀንዲስ ጥበብ ጉድለት፣ ወይ ባጉል መራቀቅ ዘፍቆ
ከስህተቱም፣ ከጥራቱም፣ ተቻችሎ፣ አለ ተጣብቆ”
ህንፃው ብቻውን ባዶ ነው፡፡ መሰረቱ የተዛባ ነው፡፡ መሀንዲሱ ስራውን በአገም - ጠቀም ሰርቶ አሳቡን ከወሰደ ቆይቷል፡፡ አካባቢያችን ጌጥ ብቻ ነው! እሾህና አሜከላ ዙሪያችንን ከቦናል፡፡ ይሄ የሀገራችን ሀቅ ነው፡፡ ማማር ያለበት መንገድ፣ ህንፃው፣ ሪል ኢስቴቱ ብቻ አይደለም፡፡ ዋናውና ዋነኛው የህዝባችን ኑሮ ነው፡፡ ተመችቶኛል፣ ደልቶኛል ማለት ያበት ነዋሪው ህዝብ ነው! በግፍ ተበልቻለሁ፣ ተመዝብሬአለሁ ማለትም ያለበት ነዋሪው ህዝብ ነው፡፡ በሹመት ስም፣ በሀገር ሰላም ስም፣ በትራንስፎርሜሽን ስም፣ በኢንቬስተሮች ማበረታታት ስም፣ ዘራፊዎችን በማሳደድ ስም፣ … የሚካሄዱ ምዝበራዎችን አውቆ፣ ነቅቶ፣ ከሥር መሰረቱ አብጠልጥሎ ተረድቶ፣ ማጋለጥና ዕውነቱን ይፋ ማድረግም የነዋሪው ህዝብ ደንታ ነው፡፡ በፋይናንስ፣ በገቢ አሰባሰብና የመሬት ቁጥጥር ጉዳይ ላይ ህዝብ የመናገር መብት ሊኖረው ይገባል!! የመክሰስ መብቱን ሊጠቀም ይገባል!
በሥልጣን ብልግናም ይገለጥ፣ በመሬት ዘረፋም ይገለጥ፣ በታክስ ማጭበርበርም ይገለጥ፣ በኮንስትራክሽን ግዢም ይገለጥ፣ በሚዲያ ኢንዱስትሪ ሀሳዊ - ስብከትም ይገለጥ፣ የቦርድ አባልነትን ተገን በማድረግም ይገለጥ፣ በሙልሙል ቢሮክራት መልክም ይገለጥ … “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው” በሚለው ተረት በሚገባ የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ይህንን ልብ ለማለት ልብ ይስጠን!!

በአመት 82ሺ ኢትዮጵያውያን የመን ገብተዋል። 11ሺ ያህሉ ሴቶች ናቸው።
20ሺ የመናዊያን በጦርነት ወደ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ ተሰደዋል።

    ለሥራ ወደ አረብ አገራት መጓዝ የተከለከለው፣ ጉዳት ይደርስባቸዋል በሚል ነበር። በእርግጥም በየጊዜው፣ ለአደጋ የሚጋለጡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም። ነገር ግን፣ እገዳው፣ በጎ ውጤት አላስገኘም። አደጋንና ጉዳትን ከመቀነስ ይልቅ እንዲባባስ አድርጓል።
አይኦኤም ሰሞኑን ባሰራጨው መረጃ እንደጠቆመው፤ እስከ ጥር ወር ድረስ፣ ወደ የመን ለመግባት ከተጓዙት ስደተኞች መካከል 340 ያህሉ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ደብዛቸው ጠፍቷል። አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው - 280 ያህሉ። በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት መሄድ፣ የዛሬ ሁለት አመት ከመታገዱ በፊት፣ እንዲህ አይነት እልቂት አይከሰትም ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም። ቀደም ሲል፣ አብዛኞቹ ሴቶች ወደ አረብ አገራት የሚሄዱት በህጋዊ ምዝገባ በአውሮፕላን በረራ እንጂ፣ በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አደገኛዋ አገር ወደ የመን የመሄድ ብዙም ፍላጎት አልነበራቸውም። አሁን ግን፣ በህጋዊ ምዝገባ የመሄድ እድል በእገዳ ስለተዘጋ፣ አማራጭ በማጣት፤ በየመን በኩል የሚጓዙ ሴቶች ቁጥር ጨምሯል - 11ሺ።
የዛሬ አራት አምስት ዓመት፣ ወደ አረብ አገራት የሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ ሲደርስ የነበረው ጉዳት ቀላል አይደለም። የሚያስቆጭ የሚያንገበግብ ነው። ነገር ግን፣ ያንን ጉዳት ለመቀነስ በትጋት ከመስራት ይልቅ፣ ጉዞዎቹን ማገድ አቋራጭ መፍትሄ ሆኗል። ተቆርቋሪነትም ይመስላል። ተቆርቋሪነት ግን አይደለም። ጭካኔ ነው - የአምስት የአስር ሰዎች መሞት የሚቆረቁረው ሰው፤ መቶ፣ ሁለት መቶ፣ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ እገዳ ማወጅ።

- በፊናቸው ጠቅላላ ጉባኤ እናካሂዳለን ብለዋል
- አንዱ ሌላውን “ከሃላፊነት አግጃለሁ” ሲሉ ወስነዋል

   የመኢአድ ላዕላይ ምክር ቤት፤ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪን የከሰሰ ሲሆን፤ ፍ/ቤት አቶ አበባውን ለጊዜው በማገድ፣ የክስ መልስ እንዲያዘጋጁ የአንድ ወር ቀጠሮ ሰጠ፡፡  
ለአመታት ከተለያዩ ውዝግቦች እፎይታ ያላገኘው መኢአድ፣ ዘንድሮም የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የምክትላቸው በተቀናቃኝ ጐራ የተሰለፉበት የተካረረ ውዝግብ ገጥሞታል፡፡
መኢአድ፤ መጋቢት 24 ቀን ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ወስኗል ቢባልም፤ የፓርቲው  ም/ሬዚዳንት ተቃውመዋል፡፡ አቶ አበባው ከአመራር እንዲታገዱ ስለተወሰነ ጉባኤውን የመጥራት ስልጣን የላቸውም ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አንድሪያስ ኤሮ፤ እኛ በስድስት ወር ጠቅላላ ጉባኤ እናካሂዳለን ብለዋል፡፡
በአቶ እንድሪያስ ኤሮ አስተባባሪነት፤ ከ50 በመቶ በላይ የፓርቲው ላዕላይ ም/ቤት አባላት ተሰብስበው፤ አቶ አበባው መሃሪን ከፕሬዚዳንትነት አግደዋል፡፡ ክስም አቅርበዋል፡፡
አቶ አበባው በበኩላቸው ሌላ ስብሰባ በማካሄድ፤ የአቶ እንድሪያስን ቡድን አግጃለሁ ብለዋል፡፡ በፊናቸው ክስ እንደሚያቀርቡ በመጥቀስ፡፡

• ከመቶ ሺሕ በላይ ተመልካቾች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል
• ኦርቶዶክሳዊ ክውን ጥበባት ልዩ ገጽታዎቹ ይኾናሉ ተብሏል
• ለአጠቃላይ ዝግጅቱ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፋዊነት፣ ነባራዊ ሁኔታና ተግዳሮቶች ተረድተው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያስችላል የተባለ ልዩ ዐውደ ርእይ በመጪው መጋቢት ወር አጋማሽ እንደሚያካሒድ ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ፣ ከመጋቢት 15 - 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚያካሒደው ዐውደ ርእይ፣ ለአምስተኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው ሲሆን፣ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፡ አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” የሚል መርሕ እንዳለው የዝግጅቱ ዐቢይ ኮሚቴ ገልጧል፡፡
በዘንድሮው ዐውደ ርእይ፥ ቤተ ክርስቲያን በአደረጃጀቷ የካህናትና የምእመናን ኅብረት መሆኗን በማስገንዘብ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ድርሻቸውን ዐውቀው ሓላፊነታቸውን የሚወጡበትን መንገድ የሚያስገነዝቡ፤ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነትና አንድነት የሚያስረዱ፣ በአራት ሰፋፊ አርእስተ ጉዳዮች የተከፈሉ ትዕይንቶች ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመታገዝ እንደሚቀርቡ ተጠቅሷል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማንነት፤ በዓለም፣ በአፍሪቃ እና በኢትዮጵያ ያላትን ሐዋርያዊ ተልእኮ፤ ወቅታዊ ተግዳሮቶቿንና መፍትሔውን በመለየት ምን መደረግ እንዳለበትና ከምእመናን ምን እንደሚጠበቅ በስፋትና በዝርዝር ከተካተቱበት ዐውደ ርእይ ጎን ለጎን፣ ጭብጦቹ በጥናታዊ ጽሑፍ የሚዳሰሱበት ዐውደ ጉባኤ እንደሚካሔድም ታውቋል፡፡
ዐውደ ርእዩ ለእይታ ክፍት ኾኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥንታዊ ሥርዐተ ትምህርት የመማር ማስተማር ሒደት በደቀ መዛሙርቱና በመምህራኑ እንቅስቃሴ በተግባር የሚታይበት “የአብነት ት/ቤቶች መንደር” የሚገነባ ሲሆን በየዕለቱ ከ10 ሰዓት በኋላም ያሬዳዊ ዜማና ቅኔ ከትውፊታዊ ዕሴቶቻቸው ጋር የሚቀርቡበት መሰናዶ እንደሚኖር ተገልጧል፡፡ ኮሚቴው፣ “ኦርቶዶክሳዊ ክውን ጥበባት”/performance arts/ ሲል የገለጻቸው መሰናዶዎቹ፥ የጥበባቱን ሕያውነት፣ ገቢራዊነትና አሳታፊነት በማስገንዘብ ተመልካቾችን ለዕውቀት በማነሣሣት ረገድ ጉልሕ ድርሻ| ይኖራቸዋል፤ ብሏል፡፡
ለዐውደ ርእዩና ተጓዳኝ መሰናዶዎች አስፈላጊው ፈቃድና የድጋፍ ደብዳቤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ተገኝቶ ከኤግዚቢሽን ማእከሉ ጋር ስምምነት መፈጸሙን ዐቢይ ኮሚቴው ገልጦ፤ ከአንድ ሺሕ አባላቱ በዝግጅትና በቴክኒክ ምድቦች ተከፋፍለው ቅድመ ዝግጅታቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉና በሒደትም የሰንበት ት/ቤቶችንና ሌሎች መንፈሳውያን ማኅበራትን በአጋርነት በመያዝ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡
ለአጠቃላይ ዝግጅቱ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ  ወጪ የተያዘለት ሲሆን፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ተቋማት ጨምሮ የተለያዩ አጋር አካላት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለግብይት በማቅረብ እንደሚያስተዋውቁበት ተመልክቷል፡፡
ከመክፈቻው ዕለት ጀምሮ ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 12፡00 ለእይታ ክፍት የሚሆነው ዐውደ ርእዩ፣ ከመቶ ሺሕ በላይ ተመልካቾች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን የመግቢያ ቲኬት ሽያጭም ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ በመካሔድ ላይ ነው፡፡ ዓላማውን የሚደግፉ አካላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ የጠየቀው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ወዳጅ ዘመዶችን ወደ ዐውደ ርእዩ በመጋበዝ ስለ ቤተ ክርስቲያን እንዲያውቅና እንዲያሳውቀው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱና በምእመኑ መካከል ያለውን መስተጋብር ለማዳበር፣ ማኅበሩ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ከዘረጋቸውና በስፋት ከተገበራቸው ሰፊ የማስተማሪያና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች መካከል ዐውደ ርእይ አንዱ መሆኑን ያስረዳው ዐቢይ ኮሚቴው፤ ያለፉት አራት ዙር ዝግጅቶች፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ፣ ታሪክ፣ የቅርስ ባለቤትነትና ባለአደራነት፤ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ለሀገሪቱ ዕድገት ላበረከተችው አስተዋፅኦ ሰፊ ሽፋን የሰጡ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡

አሜሪካ፣ ደ/ ኮርያና ቻይና የሰ/ ኮርያን ዕቅድ አውግዘዋል
    ሰሜን ኮርያ ለምርምር ተግባር የሚውል ያለችውን ሳተላይት ወደ ጠፈር ለማምጠቅ መዘጋጀቷን ባለፈው ማክሰኞ በይፋ ማስታወቋ በአካባቢው አገራት ውጥረት የፈጠረ ሲሆን ጃፓን፤ ሰሜን ኮርያ ይህንን እቅዷን እንድታቋርጥ መክራ፣ ካልሆነ ግን ሮኬቱን መትታ ለመጣል የጦር ሃይሏን ዝግጁ እንዳደረገች ማስታወቋን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ናካታኒ፤ የሰሜን ኮርያ ሚሳየል የአየር ክልሏን ጥሶ የሚገባ ከሆነ፣ የባህር ሃይሏ በሮኬቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቱን ያስታወቁ ሲሆን፣ በጃፓን ባህር ላይ የጦር መርከቦች መሰማራታቸውና የባላስቲክ ሚሳኤል መከላከያዋም በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሰሜን ኮርያ ለምርምር ተግባር አውለዋለሁ ያለችውን ሮኬት በመጪዎቹ ሳምንታት ወደ ጠፈር እንደምትልክ ለተመድ ማስታወቋን ተከትሎ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ቻይናና ደቡብ ኮርያ የአገሪቱን እቅድ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል ለመሞከር የታቀደ ስውር ደባ ነው በማለት እንደተቃወሙት ተነግሯል፡፡
የደቡብ ኮርያ መንግስት ሰሜን ኮርያ ዕቅዷን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ትልቅ ዋጋ ትከፍላለች ያለ ሲሆን፣ ቻይናም ጉዳዩ እንደሚያሳስባት በመግለጽ ሰሜን ኮርያ ከድርጊቷ እንድትታቀብ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኮርያ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
አገራቱ ሰሜን ኮርያን ከድርጊቷ እንድትታቀብ ቢያስጠነቅቁም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን ሮኬት በማምጠቅ የጠፈር ምርምር ማድረግ ሉአላዊ መብቷ እንደሆነ በመግለጽ ነቀፋውን አጣጥላዋለች ተብሏል፡፡

   ሆላንድ በጸረ-ሰላም ድሮኖች ላይ ንስሮችን ልታዘምት ነው
    እስራኤል ለስለላ ተግባር አሰማርታዋለች በሚል ተጠርጥሮ ከአስር ቀናት በፊት በሊባኖስ በቁጥጥር ስር የዋለው አሞራ፣ ከቀናት ቆይታ በኋላ ከእስር ተፈትቶ ወደ አገሩ መመለሱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
1.9 ሜትር የሚረዝም ክንፍ ያለው ይህ የእስራኤል አሞራ፤ ከሊባኖስ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ጥሶ ሲገባ በአካባቢው ነዋሪዎች መያዙን ያስታወሰው ዘገባው፣ ነዋሪዎቹ ከአሞራው ላባ ላይ የታሰረ የክትትል መሳሪያ ተገጥሞ ማየታቸው ለጥርጣሬያቸው መነሻ እንደሆናቸው ጠቁሟል፡፡
የእስራኤል ባለስልጣናት አሞራው ከእስር ሊፈታ የቻለው፣ የስለላ ተልዕኮ እንደሌለው በሚመለከተው አካል በመረጋገጡና በሊባኖስ የሚገኙ የተመድ የሰላም አስከባሪዎች በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ባደረጉት ግልግል ነው ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የእስራኤል የአእዋፍት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች፤ አሞራው ባለፈው አመት ከስፔን እንደመጣና ከአንድ ወር በፊትም በእስራኤል ቁጥጥር ሥር  በሚገኙት የጎላን ኮረብቶች ውስጥ በሚገኝ ጋምላ የተባለ የተፈጥሮ ክልል  ውስጥ እንዲኖር መለቀቁን ተናግረዋል፡፡
እስራኤል አሞሮችን ለስለላ ተግባር ታሰማራለች በሚል በተደጋጋሚ ስትጠረጠር እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሆላንድ እየተበራከቱ የመጡት ህጋዊነት የሌላቸው ድሮን የተባሉ ሰው አልባ በራሪዎች ለዜጎች ደህንነት ስጋት መፍጠራቸው ያሳሰበው የአገሪቱ ፖሊስ፣ መሰል ድሮኖችን በሰለጠኑ ንስሮችና ሌሎች አእዋፍት በቁጥጥር ስር ለማዋል ማቀዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፍቃድ የሌላቸውና እውቀት በሌላቸው ግለሰቦች የሚንቀሳቀሱ መሰል ድሮኖች ከተፈቀደላቸው የበረራ ክልል በማለፍ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎችና ባለስልጣናት የታደሙባቸው ህዝባዊ ስነስርዓቶች ወደሚካሄዱባቸው ስፍራዎች ዘልቀው መብረራቸው ያሳሰበው የአገሪቱ ፖሊስ ነው እቅዱን ያወጣው፡፡  
የአገሪቱ ፖሊስና የጸረ-ሽብር ተቋም በጋራ በዘየዱት በዚህ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘን የደህንነት ስጋት በተፈጥሮ የመመከት  መላ፣ ንስሮችና አእዋፋት ሌሎች ታዳኞችን በሚያጠቁበት ዘዴ የደህንነት ስጋት የሆኑ ድሮኖችን በመሞጭለፍ ከአካባቢው የማራቅ ተልዕኮን እንዲወጡ ለማድረግ ታስቧል፡፡
የንስሮቹ አሰልጣኝ የሆኑት የአምስተርዳም ፖሊስ ባልደረባ፣ አእዋፋቱ ድሮኖችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከአደጋ ክልል ውጭ ለማድረግ በሚሞክሩበት ወቅት፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከሳይንቲስቶች ጋር በመተባበር እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ለዚህ የጸረ ድሮን ዘመቻ ከሰለጠኑት ንስሮች አንዱ፣ ከሰሞኑ በተደረገ ሙከራ አንድን በመብረር ላይ ያለ ድሮን ተከታትሎ በጥፍሮቹ በመያዝ ወደ መሬት እንዳወረደው የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የተለያዩ የአለማችን አገራት አይሲስን ለመደምሰስ በኢራቅና በሶርያ የሚፈጽሙት የአየር ጥቃት ያሰጋቸው በርካታ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ የጦር መሪዎች ከጥቃቱ ሸሽተው ወደ ሊቢያ እየገቡ ነው ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ሊቢያ ለሽብር ቡድኑ አመራሮች ምቹ አገር በመሆኗ፣ በርካታ የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው የአይሲስ ከፍተኛ የጦር አበጋዞች ሲርት ወደ ተባለችውና በቡድኑ ቁጥጥር ስር ወደምትገኘው የአገሪቱ ከተማ እየገቡ እንደሚገኙ የሊቢያ የስለላ ተቋም ሃላፊ ኢስማኤል ሹክሪ መናገራቸው ተገልጿል፡፡
ከተማዋ ካለፈው አመት ጀምሮ በአይሲስ ቁጥጥር ስር እንደምትገኝ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከኢራቅና ከሶርያ ሸሽተው ወደ ሲርት የሚገቡ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ የጦር መሪዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
በሽሽት ወደ ከተማዋ ከገቡት የቡድኑ አባላት አብዛኞቹ የቱኒዝያ፣ የግብጽና፣ የሱዳን ዜግነት ያላቸው ናቸው ያለው ዘገባው፣ አልጀሪያውያን፣ ኢራቃውያንና ሶርያውያንም እንደሚገኙባቸው የተነገረ ሲሆን፣ በተለይም ለቡድኑ የረጂም ጊዜ የሽብር ተልዕኮ ስኬታማነት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ የቡድኑ አባላት ወደ ሊቢያ መሸሻቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡