Administrator

Administrator

Saturday, 03 October 2015 10:13

የባቡር ላይ ጥቅሶች

የታክሲዎን አመል እዛው
- ትዳርና ባቡር አንድ ናቸው
መሳፈሪያቸውን እንጂ
መውረጃቸውን ማወቅ አይቻልም
- ባቡር እና ሰውን ማመን ቀብሮ ነው
- ነገረኛ ተሳፋሪ ባቡርን ኮንትራት
ይጠይቃል
- ደግሞ እንደታክሲ በየቦታው ወራጅ
አለ በሉ አሏችሁ
- ብድር ባይኖር ኖሮ አዳሜ ይሄኔ
ለታከሲ ተሰልፈሽ ነበር
- አይደለም የባቡር ሐዲድ ወርቅ
ቢየነጥፉላችሁ አታመሰግኑም
- አፄ ምኒሊክ እንዴት ደስ ብሏቸው
ይሆን
- ባቡር እና ኑሮ ሞልቶ አያውቅም
- ሴት ረዳቶችን መልከፍ ክልክል ነው
- ሹፌሩን ማናገር የሚቻለው መብራት
ሲጠፋ ብቻ ነው፡፡ ለዚያውም
ቻይንኛ ከቻሉ
- መብራት ሲጠፋ አትደናገጡ
መብራት መጥፋት ብርቅ
ነው እንዴ?
- መቶ ብር እና ባቡር ሲገኙ ቀስ በለው
ሲሄዱ ደግሞ ፈጥነው ነው
- እንደ ታክሲ የረጋህ እንደ ባቡር
የፈጠንክ ሁን
- ቻይና በጫማዋ ስታቃጥለን ኖራ
ደግሞ በባቡር ልታቃጥለን መጣች
- ባቡር መብራት ሲጠፋ ጓደኛ ደግሞ
ገንዘብ ሲጠፋ ይከዳሉ
የባቡር ላይ
ጥቅሶች

“በአመራር ችግር ከ200 በላይ መምህራን ለቀዋል;
የተሳሳተ ገፅታ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው”

ባለ 10 ገጽ አቤቱታ ለትምህርት ሚኒስትሩ ቀርቧል

  ሰሞኑን በኢሜይል የደረሰን ደብዳቤ “ግልፅ አቤቱታ - ይድረስ ለክቡር የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ” ይላል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎች፤“የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክና አስተዳደር ሰራተኞች” መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መረር ያለ አቤቱታቸውና ትችታቸው ያነጣጠረው በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ ላይ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ለትምህርት ሚኒስቴር ቢሮ፣ ሁለት ጊዜ የድረሱልን ጥሪ አቤቱታ አስገብተው ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ አስታውሰዋል፡፡ ይህንን ግልፅ አቤቱታ ለክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ ለማቅረብ በሁለት ምክንያቶች መገደዳቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ “አንደኛው ምክንያታችን፤ በአምባገነኑ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ አማካኝነት ተቋም ብቻ ሳይሆን አገር ጭምር እየፈረሰ ስለሆነ የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ነው” ይላሉ፡፡ ሁለተኛውን ምክንያታቸውን ሲገልጹም፤“ከዚህ ቀደም በፃፍናቸው አቤቱታዎች ላይ አጥጋቢ ምላሽ የማይሰጠን ከሆነና አምባገነኑ መሪ ከእኩይ ሥራቸውና ሀገር ከማፍረስ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ ወደ ሚዲያው እንደምናወጣውና እስከመጨረሻ ድረስ ሄደን እንደምንታገል አስቀድመን በመናገራችን እንዲሁም የአምባገነኑ መሪ የመብት ረገጣ፣ ዛቻ፣ ጥላቻ፣ ስድብና የመብት ጥሰት በየቀኑ እየተባባሰ በመሄዱ ነው” ብለዋል - አቤቱታ አቅራቢዎቹ፡፡
በ10 ገፆች የቀረበው “የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክና አስተዳደር ሰራተኞች” አቤቱታ፤ በዋናነት በብልሹ የዩኒቨርሲቲው አመራር የተነሳ ሶስተኛ ድግሪ ያላቸው ነባር መምህራን ዩኒቨርሲቲውን ጥለው እየተሰደዱ መሆናቸውን ይገልጻል - በአንድ ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ሠራተኞች መውጣታቸውን በመጥቀስ፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ሌሎች በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ይፈጸማል ያሏቸውን፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም…ቤተዘመድን ሥራ መቅጠር----የዘረኝነትና ጠባብነት አስተሳሰብ እና ሌሎችንም ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በ16 ነጥቦች የተዘረዘሩትን አቤቱታዎች በተመለከተ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬን በስልክ አነጋግሮ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ (ፕሬዚዳንቱ ለሰጡን ፈጣን ምላሽና ማብራሪያ የዝግጅት ክፍላችን ምስጋናውን ይገልጻል፡፡)
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለትምህርት ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ተራ ቁጥር 1 ላይ የሰፈረው ቅሬታ በከፊል እንዲህ ይላል፡-
“…በአንድ እስክሪብቶ ጫፍ ስልጣንን ሁሉ ከህግ፣ መመሪያና አዋጅ ውጭ ተቆናጠው ይዘው በዩኒቨርስቲው ውስጥ 229 ሠራተኞችን ያለምንም ደንብና ሥርዓት፣ ያለመመሪያ፣ ያለ ውድድር ወይም በይስሙላ ውድድር ለካምፓስ ሆስፒታል ቀጥረውና አስቀጥረው ምንም እርምጃ ሳይወሰድባቸው መቅረቱ ወይም ደግሞ እርስዎ እንዲያጣራ ልከው መጥቶ ሄደ የተባለው ቡድን ሪፖርት የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ አሳዝኖናል…”
የፕሬዚዳንቱ ምላሽ፡-
በቅጥር ጉዳይ እኔ የምሰጠው ትዕዛዝ የለም፡፡ በተለይ የቀረበው ቅሬታ ከጽዳትና ከጥበቃ ሠራተኞች ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይሄን የሚመለከተው ራሱን የቻለ ኮሚቴ ነው፡፡ ተወዳድሬ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ እድል አላገኘሁም ብሎ ቅሬታ ያቀረበ የለም፡፡ በኔ ደረጃ ምንም ውሣኔ የተሠጠበት አይደለም፡፡ ትክክለኛ አሠራርን ተከትሎ የተተገበረ ነው፡፡ እኔ ጋ በዚህ ጉዳይ የቀረበ አንድም ቅሬታ የለም፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ቅሬታ የሚያቀርቡ ግለሰቦች አይታወቁም፡፡ በአካል ቀርበውም ቅሬታ አላቀረቡም፡፡ የሠራተኛ ዝውውር ስርአታችንን አድሏዊ ለማስመሰል ሁሉ ሲጥሩ ተመልክተናል፡፡ የአካባቢው ልጆች ብቻ የተለየ እድል ተጠቃሚ ለማስመሰል የሌሎችን ዝርዝር አውጥተው ነው እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ማንም ቢሮ መጥቶ ቢመለከት፣ አድሏዊነት በሌለው ሁኔታ ነው የዝውውር ስራዎች የሚሠሩት፡፡ የሌላ አካባቢ ሰዎችም ዝውውር ሲጠይቁ ይዘዋወራሉ፡፡ ተቀጠሩ የተባሉ ግለሰቦች ጉዳይም በሰው ሃብት አስተዳደር በኩል የሚያልቅ ነው፤ እኔ ጋ የሚመጣ አይደለም፡፡
 በብልሹ አመራርና በተለያዩ ጫናዎች የተነሳ፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰደዱ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሌክቸረሮች ዩኒቨርሲቲውን ለቀዋል፡፡ በስም ከጠቀሷቸው መካከል ዶ/ር አህመድ ሁሴን (ወደ አ.አ.ዩ በዝውውር ሂደት ላይ ያሉ) ዶ/ር ወንዳወቅ አበበ (ወደ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ3 ወራት በፊት የለቀቁ) ይገኙባቸዋል፡፡ የሠራተኞች ስደቱ እውነት ነው?
እንግዲህ ከዩኒቨርሲቲው ለቀዋል ከተባሉት መካከል ለምሣሌ ዶ/ር አህመድ አብረን፣ ማናጅመንት ውስጥ የምንሠራ፣ የምንግባባ ሰው ነን፡፡ ጊዜውንም በምርምር ስራ የሚያጠፋ፣ በዚህም የምርምር ስራዎችን እንዲሠራ የተደረገ ምሁር ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተማር እድል አግኝቶ ሲሄድም በሠላም የሸኘነው ሰው ነው፡፡ በግል አንድም ቀን በሃሳብ እንኳ ተጋጭተን አናውቅም፡፡ ዶ/ር ወንዳወቅም ቢሆን በጣም የምንግባባ ሰዎች ነን፡፡ አዋሣ ቤተሰቦቹ ስላሉ እድሉን ሲያገኝ፣ ከቤተሰቤ ጋር አንድ ላይ መሆን አለብኝ ብሎ የኮንትራት ውል ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ ነው የሄደው፡፡
በአጠቃላይ ለቀዋል የሚባሉት መምህራን እየሄዱ ያሉት ወደ ቤተሰባቸውና ወደተሻለ ስራ እንጂ “ዲላ ዩኒቨርሲቲ አልተመቸንም” በሚል አይደለም፡፡ በእርግጥ በጣም ልምድ ያላቸው መምህራን የኮንትራት ጊዜያቸውን እየጨረሱ መሄዳቸው አንዱ ስጋታችን እንደሆነና ትምህርት ሚኒስቴርም በዚህ በኩል ሊረዳን እንደሚገባ እያሳወቅን ነው፡፡
መምህራን የሚለቁት በአመራር ችግር አይደለም እያሉኝ ነው?
እኛ ለአንድም አስተማሪ ማስጠንቀቂያ እንኳ ሰጥተን አናውቅም፡፡ የስንብት ደብዳቤም ለአንድም መምህር ሰጥተን አናውቅም፡፡ በአሠራር ስርአታችንም ቢሆን ከአመራር ጋር እንጂ ከመምህራን ጋር ብዙም አንደራረስም፡፡ እኛ የምንወያየው ከአመራሮች ጋር ነው፡፡ በመምህር ደረጃ ከኛ ጋር የተነጋገሩት አንድ መምህር ብቻ ናቸው፡፡ የጂኦሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የነበሩ ግለሰብን አንድ ተማሪ ስለከሰሳቸው፣በዚያ ጉዳይ አነጋግረናቸዋል፡፡ ከዚያ ውጪ የመምህራን ጉዳይ በኮሌጅ ዲኖች ደረጃ የሚያልቅ ነው፡፡
በአንድ አመት ብቻ 200 ሠራተኞች  ለቀዋል የሚለው ትክክለኛ መረጃ አይደለም፡፡ አዎ! ሰዎች የተሻለ ነገር ሲያገኙ የስራ ዝውውር ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ እኛ ሠራተኞቻችን የተሻለ ስራ አግኝተው መልቀቂያ ሲጠይቁ፣ አስፈላጊውን ክሊራንስ አድርገን የሽኝት ስነስርዓት አዘጋጅተን ነው የምንሸኘው፡፡ እነሱም ምስጋና አቅርበውልን ነው የሚሄዱት፡፡ አሁንም ቢሆን “ዝውውር ፍቀዱልን፤ ወደ ቤተሰባችን እንጠጋ” የሚል ማመልከቻ ያስገቡ አሉ፡፡ ይሄ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡
ለምሣሌ ከኢነጂነሪንግ ዲፓርትመንት ብዙ ሰው ነው የሚለቀው፡፡ ወደ ስኳር ፕሮጀክቶች፣ ወደ ሜቴክ የተሻለ ስራ አግኝተው ይለቃሉ፡፡ ኢንጂነሪንግ አካባቢ በእርግጥም ሰው ብዙ አይቆይልንም፤ ይሄ ደግሞ ገበያው የፈጠረው ነው፡፡ በአመራሩ ምክንያት ሠራተኛ እየለቀቀ ነው የሚለው ስሞታ የተሳሳተ ገፅታ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
እርስዎ ለአንድም  መምህር ማስጠንቀቂያ ጽፈን አናውቅም፤የስንብት ደብዳቤም ለአንድም መምህር ሰጥተን አናውቅም፡፡ ብለዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ እርስዎን የሚገልፁት “አምባገነን” እያሉ ነው፡፡ ይሄ በምን ምክንያት ይመስልዎታል? ቁጡ ባህሪ አለዎት እንዴ? ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ያለዎት ግንኙነትስ?
ምናልባት እኔ ወደ ዲላ ስመደብ፣በደንብ ያልተያዙ ስራዎች ከመኖራቸው አንፃር በእልህና በቁጭት የሚሠሩ ትጉህ ሰራተኞችን ነው የምይዘው፡፡ ትክክል ነው አይደለም የሚሉ ውሣኔዎችን እየሠጠሁ ነው የምሄደው፡፡ ይሄ ደግሞ አልተለመደም መሠለኝ፡፡ ስራዎችን ጫን አድርጌ የመሄድ ነገር ነበር፤ ይሄ ደግሞ ከእልህ ጋር የተያያዘ እንስራ በሚል መንፈስ የማደርገው ነው፡፡ ጫና ፈጥሬ ስራ እንዲሠራ ስለማደርግ ነው፡፡ ለምን ቀስ አትልምም… ይሉኛል፡፡ የመንግስት መመሪያን ለመፈፀም ጫን ብለን እንሄዳለን፤ ከዚያ አንፃር ይመስለኛል፡፡ ግን ስራን ማዕከል ያደረገ ጫና ነው እንጂ ከስራ ውጪ ምንም ነገር የለም፡፡
ከስራ የለቀቁት መምህራን ምን ያህል ይሆናሉ?
በዝርዝር የተዘጋጀ ነገር የለም፡፡ ግን ብዙዎቹ በ2007 ብቻ አይደለም የለቀቁት፤ ከዚያ በፊትም ብዙ ለቀዋል፡፡ በስም ከተጠቀሱት መካከልም ከ2007 ዓ.ም በፊት የለቀቁ አሉ፡፡
  ፕሬዚዳንቱ ከዩኒቨርስቲው እንዲለቁ የሚፈልጓቸውን የአስተዳደር ሠራተኞችና ምሁራንን ያስደበድባሉ በማለት አቤቱታ ቀርቧል፡፡ ለምሳሌ የሶሻል ሳይንስ ዲን ዶ/ር፤ በመኪና ቁልፍ ተወርውሮ ተመቷል፡፡ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፤ስድብና ዛቻ በተደጋጋሚ ደርሶባቸዋል የሚል ተጠቅሷል፡፡  
ይሄ ጉዳይ በቀጥታ እኔ ላይ መለጠፉ ነው እንጂ ስነምግባር የጐደላቸው ሹፌሮች እንዳሉ አይተናል፡፡ ዶ/ር ቦጋለ በጣም ጥሩ ሰው፣ ተግባቢ ነበረ፡፡ ሹፌሮች ይሄን ድርጊት መፈፀም አልነበረባቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት የዩኒቨርሲቲው ትራንስፖርትና ስምሪት ክፍል ሃላፊዎች ሹፌሩን ከስራ አግደውታል፡፡ የሌሎች ሹፌሮችን የስነ ምግባር ጉድለት በማረቅ ረገድ በትክክል አልመራችሁም በሚል ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር በጥብቅ ተነጋግረናል፡፡ ችግሩ አለ ግን አመራሩ ላይ በቀጥታ መለጠፉ ተገቢ አልነበረም፡፡ እኛም እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡
ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ያለ ደንብና ስርአት ሠራተኛ መቅጠር፣ በሃላፊ ላይ ሃላፊ ደርቦ መሾም የሚል አቤቱታም ቀርቧል፡፡ ለ3ኛ ድግሪ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ የሄዱ ሰው፤ እዚያው በሚገኝ ቢሮ በዳይሬክተርነት ተመድበዋል - በሌላ ሃላፊ ላይ ተደርበው፡፡ ስለዚህስ የሚያውቁት ነገር አለ?
በደብዳቤው ላይ በስም የተጠቀሰችው መስከረም ጃራ ማለት በዩኒቨርሲቲው ፀሐፊ የነበረች ናት፡፡ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ ላይ የአገናኝ ቢሮ አለን፡፡ እሷ የዚያ ቢሮ ፀሐፊና አስተባባሪ ናት፡፡ አሁንም እዚያው አዲስ አበባ ሩዋንዳ አካባቢ በ10 ሚሊዮን ብር አዲስ ህንፃ ገዝተናል፡፡ እሱን ህንፃ ለማስተባበር አንድ ሠራተኛ ልከናል፡፡ በሌላ በኩል ብቻውን ጫና እንዳይበዛበት በደብዳቤው የተጠቀሰችውን ምስራቅ ጠና (የፒኤችዲ ተማሪ በአ.አ.ዩ) እገዛ እንድታደርግለት አድርገናል፡፡
ሌላው አቤቱታ፤የዶክትሬት ድግሪያቸውን ሳያገኙ “ዶክተር በሉኝ፣ ዶክተር ሆኛለሁ” በማለት ለ 1 አመት የዶክተር ደሞዝ በልተዋል የሚለው ነው
ይሄ ፍፁም ሃሰት ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርቴን መጨረሴን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ የፃፈልኝ በህዳር ወር ነው፡፡ ግን ምረቃው በአመቱ መጨረሻ ነበር፡፡ በዚህ መነሻ ዩኒቨርስቲው ፒኤችዲ መጨረሴን ጠቅሶ ነው ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ደብዳቤ የፃፈው፡፡ እኔም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር ውል ከገባሁ በኋላ ነው ወደዚህ ተመድቤ የመጣሁት፡፡ ደሞዜ የተስተካከለውም በዚያ መሠረት ነው፡፡
የ3ኛ ድግሪ ተማሪዎች የምርምር ገንዘብ ድጋፍ ሲሰጥ፣ ለኔም ይገባኛል ብለው ወስደዋል የሚል ወቀሳም አቅርበዋል፡፡ ይሄስ እንዴት ነው?
እኔም በወቅቱ እየተማርኩ ነበር፡፡ የ3ኛ ድግሪ ተማሪዎች ሲሄዱ፣በማናጅመንት ደረጃ የወሰነው የሚያገኙት ጥቅማጥቅም አለ፡፡ መጀመሪያ የሚሄድ ሰው ቤተሰቡንም ይዞ ሊሄድ ስለሚችል 10ሺህ ብር እንሠጣለን፡፡ ሁለተኛ ላይ ደግሞ ቶሎ ጨርሶ እንዲመጣ ለማበረታታት 10ሺህ ብር እንደገና ይሠጣል፡፡ እኔም ይሄን መብቴን ተጠቅሜ እንደ አንድ የ3ኛ ዲግሪውን እንደሚጨርስ ተማሪ፣በማመልከቻ ጠይቄ፣ይገባሃል ተብዬ፣ በመመሪያ መሠረት ነው የተሰጠኝ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ወጪ ጀርመን፣ ኦስትሪያና ቻይናን ጐብኝተዋል፤ እንዲሁም እሣቸውን ውጪ የጋበዟቸውን ሁለት ግለሰቦች እንደገና በዩኒቨርስቲው ወጪ ወደ ኢትዮጵያ ጋብዘዋል---- የተባለው አቤቱታስ?
የሄድኩት ለዩኒቨርስቲው ስራ ነው፡፡ ግንኙነት የምንፈጥርባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ት/ት ሚኒስቴር በደብዳቤ ተጠይቆ፣ ቦርድም አውቆት ተፈቅዶ ነው ወደ ኦስትሪያና ጀርመን የሄድኩት፡፡ ቻይና ደግሞ 13 ዩኒቨርስቲዎች ናቸው የጉብኝት ግብዣ ቀርቦላቸው የሄዱት፡፡ ከነዚያ አንዱ የኛ ዩኒቨርስቲ ስለነበር ሄጃለሁ፡፡ ለልምድ ልውውጥ ነው የተሄደው፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሃገራቱ የሄድኩት ለግል ጉዳይ ሳይሆን ለዩኒቨርሲቲው የስራ ጉዳይ ነበር፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንዲመጡ የተደረጉት የውጭ ሀገር ዜጐችም መልካም ግንኙነት ለመፍጠር፣ ለአጋርነትና የተሻለ ፈንድ ለማምጣት እንዲሁም የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ለማሳየት የሚያስፈልገውን ወጪ ሸፍነን አምጥተናቸዋል፡፡ ሌሎችም እንዲህ ይመጣሉ፡፡ ለኮንፈረንስ እንኳን የሚመጡና ወጪያቸውን የምንሸፍንላቸው ሰዎች አሉ፡፡
በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት እንዳለ … በሆነ ባልሆነ በጀቱ ቶሎ እንደሚያልቅ… በዚህም የተነሳ በዩኒቨርስቲው የሚተገበሩ የመስክ ትምህርቶችና ሌሎችም ወጪ የሚጠይቁ ትምህርት ነክ ጉዳዮች እንደቆሙ ተጠቅሷል፡፡ ለመሆኑ የወጪ ቁጥጥራችሁ ምን ይመስላል?
የገንዘብ ቁጥጥራችን ጠንካራ ነው፡፡ ገንዘብ ወጥቶ ለታለመለት አላማ መዋል አለመዋሉን በጥብቅ ነው የምንቆጣጠረው፡፡ ሰዎችን ለስልጠና ስንልክም በበቂ ጥናት ላይ ተመስርተን ሰዎቹ ተመልሰው የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ በዚህ በኩል ውስን በጀት ነው የምንጠቀመው፤ የሚባክን ገንዘብ የለም፡፡ የወጣው ብር ምን ላይ ዋለ? ምን አስገኘ የሚለውን በየጊዜው እንገመግማለን፡፡ እጥረት እንዳለብንም እንረዳለን፡፡ በየጊዜውም እያስተካከልን እንሄዳለን፡፡
“ማንኛውም የተቃውሞ ሃሳብ ሲነሳባቸው፣ቶሎ ብለው ድካማቸውንና የራሳቸውን ጠባብነት ከጌዴኦ ማህበረሰብ ጋር ለማገናኘት ይሞክራሉ፡፡ የጌዴኦ ጠላት ነው አጥፉት የሚል ዘመቻ በዩኒቨርሲቲውና ከግቢው ውጭ እንዲከፈትበት ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ መምህር ቤቱ በወረበሎች ተቃጥሎበታል-----” የሚል አቤቱታም በደብዳቤው ቀርቧል ------
 ሰው እኔ ላይ ተቃውሞውን ስላቀረበ አልፈርጅም፡፡ የራሱን ሃሳብ በፈለገው ልክ ማራመድ ይችላል፡፡ አንድ ግለሰብ ከተማ ውስጥ ችግር አጋጥሞኛል፣ የሆኑ ሙከራዎች ተደርገውብኛል ብሏል፡፡ ይሄን እንግዲህ በደንብ ማጣራት ይጠይቃል፡፡ እሱም ፍ/ቤት ከሶ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ ይችላል፡፡ በህግ አግባብ ተጣርቶ ምላሽ ያግኝ በሚል ተወስኗል፡፡  
እኔ የአካባቢው ተወላጅ ስለሆንኩ፣ “ለአካባቢው ህዝብ ይሳሳል፤ ይራራል” የሚሉ ነገሮች ቢኖሩ አይደንቅም፤በእውነትም የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲለወጥ እፈልጋለሁ፡፡ ግን በጠባብነት አይደለም፡፡ ዩኒቨርስቲው የብሔር ብሔረሰቦች ማዕከል ነው፡፡ በአካባቢው ያለውን ልማት እንደግፋለን፤ ብሔራዊ ፖሊሲውንም እንተገብራለን፡፡
በቅጥረኛ ሰዎች ስለላ ይደረግብናል፣ ዛቻና ማስፈራራት ይደርስብናል፣--- በሚል ስለቀረበው  አቤቱታስ-----?
እንደዚህ ያለ ነገር ተደርጐ አያውቅም፡፡ ምናልባት አስተዳደራዊ ውሣኔ በሚሹ ጉዳዮች ላይ መረጃ እናሰባስባለን፡፡ ጆሮ ጠቢ ሊኖረኝም አይችልም፤ አያስፈልገኝም፡፡ የተማሪዎች አገልግሎት መሟላት አለመሟላቱን ለማወቅ ግን መረጃ የግድ ያስፈልገናል፡፡ በአካባቢው ላይ ሺሻ ቤት እንዳለና እንደሌለ፣ በሴቶች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ስለመኖር አለመኖራቸው በየጊዜው የማጣራት ስራ እንሠራለን፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ሰዎችን አደራጅቼ አላሠልልም፡፡
በክልሉ መንግስት ስር ያሉ የተለያዩ ሴክተር መ/ቤቶችና ሌሎችም ተጠቃሚዎች በማስተርስ ድግሪ ደረጃ አማርኛ ቋንቋና ቅርስ ጥበቃ ጥናት ይከፈትልን ብለው ጠይቀው፣ አስፈላጊነቱም በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጦ እያለ እሳቸው፤ “እኔ የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሆኜ በህይወት እስካለሁ አማርኛና ታሪክ አይከፈትም” ብለዋል የሚል ስሞታ በደብዳቤው ቀርቧል…
አማርኛና ታሪክ መደበኛ የዲግሪ ፕሮግራም አለን፡፡ አሁን ጥያቄው የማስተርስ ፕሮግራምን በተመለከተ ነው፡፡ የማስተርስ ጥያቄዎች በብዛት ሲመጡ እንከፍታለን የሚል ሃሳብ ነው ያለን፡፡ አሁን በትምህርት አከፋፈት ላይ ያስቀመጥነው ስርአት አለ፡፡
በእሱ አሠራር ላይ በየደረጃው ተነጋግረን፣ ይሄኛው ፕሮግራም በኛ ተቋም ተጨባጭ ሁኔታ ወይም በሀገሪቱ ለማፍራት ከታቀደው የሰው ሃይል ቁጥር ጋር ይጣጣማል ወይ? ይሄ የትምህርት ክፍል ሌላ ቦታ የለም ወይ? የሚል ጥያቄና ውይይት አድርገናል፡፡ “ሰው እየተመረቀ ስራ ላይ የማይውል ከሆነ” በሚለው ጉዳይ ላይም በስፋት ተነጋግረናል፡፡ በአሁን ወቅት ኮሚቴዎች እንዲያጠኑት እያደረግን ነው፤ እነሱ በሚያመጡት ውጤት ላይ ተንተርሰን ወደ ቀጣይ ሂደት እንገባለን፡፡ ግን በዚህ ደረጃ የሚገለፅ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ቃል በቃል ተናግሯል ተብዬ የተጠቀሰብኝ ንግግርም አግባብ አይደለም፡፡ እኔ እንደዛ አይነት ነገር አልተናገርኩም፡፡  

ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የሸገር ኤፍ ኤም
102.1 የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ  የኪነጥበብ ሽልማት በፊልምና በሙዚቃ ዘርፍ
የአመቱ የአድማጭ ምርጦች ተሸልመዋል፡፡

• በአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ አሸናፊ የቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሣሁን) “ሠባ ደረጃ”
• በአመቱ ምርጥ የፊልም ማጀቢያ ዘርፍ ፀደንያ ገ/ ማርቆስ በ “ሃርየት” ፊልምማጀቢያ ሙዚቃ
• በአመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ ዘርፍ  ዳን አድማሱ
• በአመቱ ምርጥ አልበም
“አስታራቂ” የአብነት አጐናፍር
• በአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ
• በአመቱ ምርጥ ፊልም ሰኔ 30
• በአመቱ ምርጥ ሴት ተዋናይት አዚዛ አህመድ በሰኔ 30 ፊልም
• በአመቱ ምርጥ የወንድ ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ በላምባ ፊልም
• በአመቱ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በመሆን ተሸልመዋል
የለዛ ፕሮግራም ሽልማት ተካሄደ ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የሸገር ኤፍ ኤም
102.1 የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ የኪነጥበብ ሽልማት በፊልምና በሙዚቃ ዘርፍ
የአመቱ የአድማጭ ምርጦች ተሸልመዋል፡፡
በአመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ የማዲንጐ አፈወርቅ “ስወድላት” እና የአብነት አጐናፍር “አስታራቂ”
አልበም ከፍተኛ ፉክክር የታየባቸው ሲሆን አስታራቂ 0.9 በመቶ ልዩነት ብቻ አሸናፊ ሆኗል፡፡

  • በ7 ቀናት ከ100ሺህ በላይ የድጋፍ ፊርማዎች ተሰባሰቡ


  በኢትዮጵያን ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (EBS) ቴሌቪዥን በሚተላለፉት “ታዖሎጐስ” እና “ቃለ - አዋዲ” በተባሉት ፕሮግራሞች ላይ ሰሞኑን ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ ፕሮግራሞቹ እንዲዘጉና በኦርቶዶክስ ስም እንዳይጠቀሙ የሚያግዝ የድጋፍ ፊርማ እየተሰባሰበ ሲሆን በ7 ቀናትከ100ሺህ በላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መፈረማቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጐልማሶች ማህበራት ህብረት ሰብሳቢ ፌቨን ዘሪሁን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ህጋዊ ፈቃድ ለሌለው አካል ፈቃድ እየሰጠ ጥንታዊቱን እና የተከበረችውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና እንዲሁም ያሬዳዊ ዝማሬን እያንኳሰሱ ይገኛሉ” ያሉት ወ/ሮ ፌቨን፤ ይህ ትውልድን ከመተካትና ትክክለኛውን እምነት ከማስቀጠል አንፃር ትልቅ አደጋ አለው ብለዋል፡፡ የአገራችን ህገ - መንግስት ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልና የሀገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ማስተማርና ማስፋፋት እንደሚቻል ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፣ ነገር ግን የሌሎችን የእምነት ተቋማት ስም በማናለብኝነት በመዝለፍ በሃይማኖቱ ስም ስብከትም ሆነ ትምህርት በብዙሃን መገናኛ ማስተላለፍ ወንጀልም ሃጥያትም ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡ “ታዖሎጐስ” እና “ቃለ አዋዲ” የተባሉት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ደንብ የተዘጋጁ መሆናቸውን ቢገልፁም የሚተላለፉት ፕሮግራሞች ግን ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ፈጽሞ የሚቃረኑና የቤተክርስቲያኗን ክብር የሚጋፋ በመሆናቸው ፕሮግራሞቹን ለማዘጋት የድጋፍ ፊርማ እያሰባሰቡ መሆኑንና በተለያዩ የአምልኮ ቦታዎች በመዘዋወር ከመቶ ሺህ በላይ ምዕመናንን ማስፈረማቸውን ወ/ሪ ፌቨን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “በነዚህ መርሃ ግብሮች የሚራቀቁት ጥቂት የማይባሉ ሰባኪያንም ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ኑፋቄ ሲጽፉና ሲያስተላልፉ የነበሩ ውስጠ ሌላዎች መሆናቸው በግልጽ ይታወቃል” ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡
ከሀገረ ስብከትና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ግንኙነት አላችሁ ወይ ፊርማውንስ አስባስባችሁ ስትጨርሱ ለማን ነው የምታቀርቡት በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ወ/ሪት ፌቨን ሲመልሱም “ሀገረ ስብከቱና ጠቅላይ ቤተክህነት ባላቸው የስራ ጫና ምክንያት አሁን እንቅስቃሴውን የሚያደርጉት ከምዕመናን ጋር እንደሆነ ገልፀው፤ ውሳኔውን ግን ጠቅላይ ቤተክህነት እንዲሰጥ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ በታች በተዋረድ ካሉ ጽ/ቤቶች ጋር እንነጋገራለን ብለዋል፡፡
ለኢቢኤስ ቴሌቪዥን ቅሬታ አቅርበው እንደሆን የተጠየቁት ሰብሳቢዋ፤ “የጣቢያው ባለቤቶች ስህተት እንደሚሰራ በእርግጠኝነት ያውቃሉ” ካሉ በኋላ የድጋፍ ፊርማውን በ10 ቀን ቶሎ ቶሎ አጠናቀው ጥቅምት ላይ ስብሰባ ለሚቀመጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ እየተጣደፉ መሆኑን ጠቁመው ከዚያ በላይ ለጣቢያውም ጥያቄ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት በአዲስ አበባ ለሚገኘው የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ተወካይ ኢንኮም ትሬዲንግ ደውለን፤ እነዚህ ፕሮግራሞች ፈቃድ የሚያገኙት አሜሪካ ከሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት ስለሆነ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ነግረውናል፡፡ አሜሪካ ከሚገኙት የጣቢያ ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ፤ አቶ ነቢዩ ጥዑመ ልሳን፤ ለአዲስ አድማስ በስልክ እንደተናገሩት፤ ከሲኖዶሱም ሆነ ከሌሎች የቤተ-ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ተቋማት በይፋ የደረሳቸውና በአካልም ቀርቦ ያመለከተ ባይኖርም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ተረድተነዋል፤ ብለዋል፡፡ በማስረጃ ተደግፎ የሚቀርብ ነገር ካለም አስፈላጊውን እርምት እንደሚወስዱም አስታውቀዋል፡፡

• የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት እንዲያቀርብ በምእመናኑና በሰንበት ት/ቤቱ ተጠይቋል
• የታገደው የቅ/ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ሪፖርት ለማቅረብ የፓትርያርኩን አመራር ጠየቀ


በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ አስተዳዳሪ፣ ስለ ደብሩ የአስተዳደርና የገንዘብ አያያዝ ችግር በአዲስ አድማስ የወጣው ዘገባ፤ “በማስረጃ ተደግፎ ያልቀረበ የስም ማጥፋት አስተያየት ነው” ሲሉ አስተባበሉ፡፡
አስተዳዳሪው መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ኃይለ ማርያም፣ “በአዲስ አበባ: ሰበካ ጉባኤያት በአስተዳደር ሓላፊዎች መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኗል” በሚል ርእስ በተጠናቀረው ዘገባ፤ ስለ ደብሩ የተነሡት ጉዳዮች “ማንነታቸውን ባላወቅናቸው ግለሰቦች የቀረቡ ናቸው” በማለት  ዘገባውን ተቃውመዋል፡፡
በዘገባው፣ አስተዳዳሪው የሰበካ ጉባኤውን ውሳኔ አይተገብሩም የተባለው፣ “በግልጽ ተዘርዝሮ ያልቀረበና ፍጹም ሐሰት ነው፤” ያሉት አስተዳዳሪው፤ “በሰበካ ጉባኤው ተወስኖ ተግባራዊ ያልሆነ ምንም ዐይነት ውሳኔ የለም፤” ብለዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤውን ምክትል ሊቀ መንበር ጨምሮ ሌሎችም አባላት፣ አንሠራም በማለታቸው በፈቃዳቸው ሓላፊነታቸውን የለቀቁና በደብዳቤም ቢጠሩ ለመምጣት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንጂ አስተዳደሩ አንዳቸውንም እንዳላገደ ገልጸዋል፡፡
ደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ከመፈረም ውጭ፣ በቃለ ዐዋዲው በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት በውሳኔ ሰጪነት የማይሳተፉት÷ የደብሩን ገቢና ወጪ አጥብቀው በመቆጣጠራቸው፤ የሒሳብ ሪፖርትም በመጠየቃቸው ሳቢያ እንደሆነ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተካሔደ ማጣራት እንደተረጋገጠ የቀረበው ዘገባ “ሐሰት ነው” ያሉት አስተዳዳሪው፤ ስለጉዳዩ ለበላይ አካል ሪፖርት አቅርበው የሚሰጠውን ውሳኔና መመሪያ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የአስተዳዳሪውን አልታዘዝ ባይነት በመግለጽ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤትም ለሀገረ ስብከቱ አስተላልፎታል በሚል የቀረበውን ሪፖርትም በተመለከተ፤ “የደብሩ ጽ/ቤት የማያውቀው ነገር እንደሆነ” ገልፀዋል፡፡
የደብሩ የገቢና ወጪ ሒሳብ በዘመናዊ መልክ እንደሚሠራ በመጥቀስ የአሠራሩን ትክክለኛነት የገለፁት አስተዳዳሪው፣ የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ሒሳብ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተላኩ ኦዲተሮች ተመርምሮ ያለምንም ጉድለት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡ ሪፖርቱም በደብሩ መዝገብ የሚቀመጥ በመሆኑ የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ ጠይቀው የመረዳት መብት አላቸው፤ ብለዋል፡፡ በማንኛውም ደብር ስም የሚከፈት የባንክ ሒሳብ የሚከፈተው በሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር እንደሆነና የሚንቀሳቀሰውም በአስተዳዳሪውና በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር እንደሆነ ያስረዱት አስተዳዳሪው፣ ሳይፈቀድ እንደተፈለገ የሚንቀሳቀስ አልያም የሚወጣና የሚገባ ገንዘብ የለም፤ በሚል ይህንኑ ያስረዳልኛል ያሉትን ማስረጃ አቅርበዋል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ የሚገባው የሃያ በመቶ ድርሻ ፈሰስ ሳይደረግ፣ ደብሩ ለዕዳ ተዳርጓል መባሉን በተመለከተ አስተዳዳሪው በሰጡት ምላሽ፤ እርሳቸው ተመድበው ከመምጣቸው በፊት የብር 900‚000 ውዝፍ እንደነበረበትና ከተመደቡበት ካለፈው ዓመት መጋቢት 1 ቀን ጀምሮ ግን እንዲከፈል በማድረግ “ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትመሰገን አደረግሁ እንጂ ለዕዳ ዳርገዋታል መባሉ ሐሰት ነው፤” ብለዋል፡፡
“ካህናት ፍቅርን የሚሰብኩ የሰላም አባቶች እንደሆኑና ቤተ ክርስቲያኒቱም ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ልጆቿ ተሰባስበው በአንድነት የሚያገለግሉባት ነች፤” ያሉት አስተዳዳሪው፣ በተወላጅነት የተከፋፈለ አንድም ካህንና ሠራተኛ እንደሌለ በመጥቀስ፣ የሰበካ ጉባኤው አባላት በአስተዳደር ሠራተኞች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማኅበረ ካህናቱን በተወላጅነት ይከፋፍላሉ መባሉን አስተባብለዋል፡፡ ካህናትና ሠራተኞች ከደመወዝና ከሥራ እንዳልታገዱና ያጠፋ ቢኖር እንኳ በማገድ ሳይሆን በቃለ ዐዋዲው መሠረት፣ በቃል ምክርና በማስጠንቀቂያ የገንዘብ ቅጣት ሊቀጣ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡  
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የበላይ አካል ሳያውቀው ቅጥርም ሆነ ዝውውር ተደርጎ አያውቅም፤ ያሉት አስተዳዳሪው፣ ያለአግባብ የሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር እንደሚፈጽሙ በዘገባው የቀረበው፣ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ ውድቅ ሊሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፤ በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ሠራተኛ እንዳስፈላጊነቱ ከአንድ አጥቢያ ወደ ሌላ እየተዘዋወሩ የመሥራት ግዴታ ያለባቸው በመሆኑም ቅሬታው ይህንኑ ደንብና መመሪያ በጥልቀት ያልተረዳ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
አስተዳዳሪው የቤተ ክርስቲያንን መሬት ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ከሓላፊነታቸው ታግደው እንደነበር የተጠቀሰውን በተመለከተ፣ መልካም ስማቸውንና ዝናቸውን ለመጉዳት ሆነ ተብሎ የተሰነዘረባቸው “ፍጹም ሐሰትና አሳዛኝ ውንጀላ ነው” ሲሉ ተከላክለዋል፡፡ አለቃው ከሓላፊነታቸው ታግደው እንደነበር በማስተባበያቸው ቢያምኑም፤ በፍርድ ወንጀለኛ ተብለው ያልተቀጡበት እንደሆነና እገዳውም ሥልጣኑ በማይመለከተውና ደረጃው በማይፈቅድለት ሓላፊ የተላለፈ እንደነበር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መንፈሳዊ ፍ/ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. መረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡ ይኸው ውሳኔ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ታኅሣሥ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርቦ ያልተከፈላቸው ደመወዛቸው ተከፍሏቸው ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ እንደተወሰነላቸውም በመጥቀስ ክሡ፣ “ፈጽሜ በማላውቀውና ባልተደረገ” የቀረበብኝ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ከበርካታ አድባራት ሲቀርቡ በቆዩ አቤቱታዎች መነሻነት በአዲስ አድማስ በተጠናቀረው ዘገባ የተካተተው የደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ፤ የሰበካ ጉባኤው አባላትና ምእመናን ለሀገረ ስብከቱ ባቀረቧቸው የጽሑፍ አቤቱታዎችና የኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሀ/ስብከቱ ትእዛዝ አጣርቶ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ከሥራ ውጭ ኾኖ ባለበት በአሁኑ ወቅት አስተዳዳሪው፣ ያለሰበካ ጉባኤው ፈቃድ በሰበካ ጉባኤው ስምና ማኅተም የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣትና ሌሎች ደብዳቤዎችንም በመጻፍ አግባብነት የሌለው ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ይናገራሉ፡፡ ስለ ደብሩ ወቅታዊ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት እሑድ መወያየታቸውን ጠቅሰው፣ የሰበካ ጉባኤውና የአስተዳደር ጽ/ቤቱ በነገው ዕለት የሥራ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸው የሚጠይቅ ከ500 በላይ ፊርማ አሰባስበው ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የፓትርያርኩ መቀመጫ በሆነችው የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት በአስተዳደር ሓላፊዎች የታገደው ሰበካ ጉባኤ፣ ለመረጠው የማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ፣ እንደ ቃለ ዐዋዲው ደንብ የሥራ ሪፖርቱን ማቅረብ እንዲችል ፓትርያርኩ አመራር ይሰጡለት ዘንድ ጠይቋል፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም በደንቡ ድንጋጌዎች መሠረት ርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል፡፡
በገዳሙ ያለውን ዘረፋ በማስቆም ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ አሠራሮችን እንዲዘረጋ ከፓትርያርኩ በተቀበለው ትእዛዝ፣ መተዳደርያ ደንብና መመሪያዎችን አዘጋጅቶ በከፊል ወደ ሥራ ቢገባም አዎንታዊ እገዛም ሆነ አመራር አለማግኘቱን ጠቅሷል፡፡ ጉዳዩን በየጊዜው በተለያዩ መንገዶች ለፓትርያርኩ ሲያሳውቅ ቢቆይም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለችግር የዳረጓትን ኃይሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው እንዳለ በመጥቀስ “እናቱን በገጀራ የገደለ ጎራዴ ተሸለመ” በሚል ተችቷል፡፡
 “ሙስናን እንታገላለን፤ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን” በሚል ፓትርያርኩ በየመድረኩ የገቧቸው ቃሎች በተግባር ካልተተረጎሙም የማዘናጊያ መፈክር ከመሆን ስለማያልፉ፣ መልካም አስተዳደርን በተግባር ወደሚያሰፍን ርምጃ እንዲገባ ጠይቋል፤ በዚህ በኩልም ተስፋ ባለመቁረጥ ከፓትርያርኩ ጎን እንደሚቆምም የታገደው ሰበካ ጉባኤ ዝግጁነቱን አረጋግጧል፡፡   

የታዋቂው የቴሌቪዥን ሾው አቅራቢ ሠይፉ ፋንታሁን እና የባለቤቱ ወ/ሮ ቬሮኒካ ኑረዲን የሠርግ መልስ ስነስርአት በነገው ዕለት በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ይከናወናል፡፡ ሙሽሮቹ የመልስ ስነስርአቱን ከ550 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ  ህሙማን ጋር ከቀኑ 7 ሰአት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል ተብሏል፡፡ ባለፈው ጳጉሜ 1 ሰርጉን በሸራተን አዲስ በደማቅ ስነስርአት የፈፀመው ሰይፉ፤ለሠርጉ ሊያውለው አቅዶት የነበረውን 300ሺህ ብር ለመቄዶኒያና ለሙዳይ በጐ አድራጐት ድርጅት መለገሱ ይታወቃል፡፡ በመልሱ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና ከ5ሺህ በላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡  በሥነሥርዓቱ ላይ የመቄዶንያ አረጋውያን፤ ሙሽሮችን የሚመርቁ ሲሆን  ሙሽሮቹም ከነሚዜዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን እንዲሁም አልጋ ላይ የዋሉ ህሙማንን ይጐበኛሉ ተብሏል፡፡ ለአረጋውያን ስጦታ የመስጠትና ጋቢ የማልበስ ፕሮግራም እንደሚኖር ያመለከተው ማዕከሉ፤ አረጋውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ ግጥሞችና መነባንቦችን ያቀርባሉ ብሏል፡፡   
በማዕከሉ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሰዎች የሠርግ፣ የቀለበት፣ የልደት፣ የምረቃ ስነስርአት እንዲሁም የሙት አመት መታሰቢያዎች የማከናወን ልምድ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መንግስት በነፃ ባበረከተለት 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሰጪ ማዕከል ለመገንባትና የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 3ሺህ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ማዕከሉን ለመገንባትም 300 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መነገሩ ይታወሳል፡፡ 

  • ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ፣ የደመራ በዓልን በመስቀል ዐደባባይ ያከብራሉ
  • አክሱም ጽዮንን፣ ጎንደርን፣ ላሊበላንና የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ይጎበኛሉ


  የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶች፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ ተገለጸ፡፡
በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ከሚመራው ልኡክ ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የሚካሔደው ምክክር፤ የኹለቱን አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል ወደ ከፍተኛ መተማመን እንዲያመራ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡
በክርስትናው አስተምህሮ ባላቸው የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት፣ “እኅትማማች” የሚባሉት ኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጋራ ተልእኮዎቻቸውን በአንድነት በመፈጸም ጥንታዊውንና ታሪካዊውን ግንኙነታቸውን ለማዳበር የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት ጥር ባደረጉት የግብጽ ይፋዊ ጉብኝታቸው ወቅት ጠይቀዋል፡፡
የግብጹ አቻቸው ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም ጥያቄውን በመቀበል፤ በሃይማኖታዊ፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አብሮ የሚሠራና በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ኮሚቴ ለመሰየም ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀው እንደነበር ተወስቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈለገ ግዮን ተብሎ የሚታወቀውና ኹለቱ አገሮች በጋራ የሚጠቀሙበት ተፈጥሯዊው የዓባይ ውኃ የማኅበራዊ ትስስሩ መሠረት ሲኾን በዝግ በሚካሔደው የኹለቱ ቅዱሳት ሲኖዶሳት ምክክርም ዐቢይ ትኩረት እንደሚያገኝ ተጠቁሟል፡፡
የዓባይ ውኃን በመተማመን ከተጠቀሙበት ከኹለቱ አገሮች አልፎ ለመላው አፍሪካ የሚበቃ የአምላክ በረከት እንደኾነ ለግብጽ ባለሥልጣናት የተናገሩት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚኾኑት የእግዚአብሔር ጸጋ በኾነው በዓባይ ነው፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ደግሞ ሰው ሊለያየው አይችልም፤” ያሉ ሲኾን ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም፤ “እኛ የግብጽ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ አንድ ብርጭቆ ውኃ በጠጣን ቁጥር ኢትዮጵያን እናስታውሳታለን፤” ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በወቅቱ ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በ2008 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ እንዲገኙ ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው ግብዣ፣ ትላንት ሌሊቱን ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሃይማኖት አባቶች ልኡክ በማስከተል ዐዲስ አበባ የገቡ ሲኾን ከዛሬ ጀምሮ የአምስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡  ለጉብኝቱ የወጣው መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው ፓትርያርኩ፣ ትላንትና መስከረም 14 ቀን ሌሊት 9፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የፕሮቶኮል ባለድርሻ አካላት አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመንበረ ፓትርያርኩና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ የእንኳን ደኅና መጡ ፕሮግራም ይደረግላቸዋል፤ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም ይወያያሉ ተብሏል፡፡
ጠዋት በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተገኝተው ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራት፣ ሥርዐተ ቅዳሴውን የሚያከናውኑ ሲኾን ከቀትር በኋላም በመስቀል ዐደባባይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር የመስቀል ደመራ በዓልን ያከብራሉ፡፡
ከመስከረም 17 - 19 ቀን የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያምን፣ የጎንደርን፣ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ታሪካዊ ስፍራዎችን፣ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን እንዲኹም በአዲስ አበባ የሰበታ ጌቴሰማኔ ቤተ ደናግል ወጠባባት ገዳምንና የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመጎብኘት ጸሎት እንደሚያደርጉና እንደሚባርኩ ታውቋል፡፡ በግብፅና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ትብብር እንደ ድልድይ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ በ1951 ዓ.ም እስከሾመችበት ጊዜ ድረስ ለ1600 ዓመታት ከግብጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሾሙ ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች፡፡ በሀገራቱ መንግሥታት ምክክር ጭምር የመንበሩ ነጻነት ከተገኘም በኋላ የሚካሄዱ ፕትርክናዊ ጉብኝቶች ለውጭ ግንኙነታቸው መጠናከር አስተዋፀኦ እንዳለው ይታመናል፡፡

     ባለፈው ማክሰኞ 80ኛ የልደት በዓላቸውን ያከበሩት አንጋፋው ክላርኔት ተጫዋች መርአዊ ስጦት ተሸለሙ በዳኒ ሮጎ የማስታወቂያ ስራና ፊልም ፕሮዳክሽን ድርጅት አስተባባሪነት በሃርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው አርቲስቱን የማክበርና የማመስገን ስነ - ስርዓት ላይ ልጃቸው ኢትዮጵያ መርአዊ ላለፉት 60 ዓመታት የተጫወቱበትን ክላርኔት ያበረከተችላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርም ክብራቸውን የሚገልፅ የምስጋና የምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው ተገልጿል፡፡ በእለቱ አቶ አብነት ገብረመስቀል የ50 ሺህ ብር ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን የጃዝ አምባዎቹ ያሬድ ተፈራ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ግሩም መዝሙር፣ ሳምሶን ጃፋር፣ ፋሲል ዊሂር እና አክሊሉ ዘውዴ ለአርቲስቱ ክብር እያንዳንዳቸው ሙዚቃ ተጫውተውላቸዋል፡፡ አርቲስት ጌትነት እንየው፣ ፍቃዱ ተክለማርያምና ሙዚቀኛው ግርማ ይፍራሸዋም በየግላቸው ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን ጌትነት እንየው “ድንቅ” የተሰኘ ግጥም እንደገጠመላቸውም የዳኒ ሮጎ ስራ አስኪያጅ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ተናግሯል፡፡
 አቶ አብነት ገ/መስቀል አርቲስቱን እስከመጨረሻው ለመደገፍ ቃል የገቡ ሲሆን የላንድ ማርክ ሆስፒታል ባለቤት ፕ/ር ከበደ ወሌም በማንኛውም ሁኔታ ለህክምና ሲመጡ ሆስፒታላቸው በነፃ እንደሚያክማቸው ቃል ገብቷል፡፡ ቲሞኒየር ልብስ ስፌትም በእለቱ ሙሉ ልብሳቸውን በማልበስ ለአርቲስቱ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ 

ሳምሰንግ ምርቶቼ በስፋት መቸብቸባቸውን ይቀጥላሉ ብሏል

      በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚዎቹ ተፎካካሪዎች ሆነው ለአመታት የዘለቁት ሳምሰንግ እና አይፎን፣ ፉክክራቸው ከገበያ አልፎ ችሎት የደረሰ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባላንጣዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
“ሳምሰንግ የራሱን ፈጠራ እንደመስራት የእኔን እያየ ይኮርጃል” በሚል ሲማረርና ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ለመሰረተው ክስ፣ ተገቢ ውሳኔ የሚያገኝባትን ዕለት ለአመታት በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው አይፎን ከሰሞኑ በለስ ቀንቶታል፡፡
በዋሽንግተን የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተሰየመው ችሎት፣ “ከአሁን በኋላ ከአይፎን እያየህ መኮረጅህን እንድታቆም፤ ከዚህ በፊት የኮረጅካቸውን ሶፍትዌሮችም ዛሬ ነገ ሳትል መጠቀም እንድታቆም” ሲል ለሳምሰንግ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል - ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡
ሳምሰንግ በበኩሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በምርቶቹ ተወዳጅነት ላይ ይህ ነው የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር ገልጾ፣ ጋላክሲ በሚል መጠሪያ የሚያመርታቸው ስማርት ፎኖቹ በቀጣይም በአለም ዙሪያ በስፋት መቸብቸባቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
አይፎን ፈጠራዎቼን እየኮረጀ አስቸግሮኛል በሚል በሳምሰንግ ላይ ክስ የመሰረተው ከ3 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ወቅቱ ሳምሰንግ ኩባንያ ጋላክሲ ኤስ 2 የተሰኘውን ስማርት ፎን ለገበያ ያበቃበት እንደነበርና ከዚያ በኋላም፣ በዚህ አመት ለገበያ ያበቃውን ጋላክሲ ኤስ 6 ጨምሮ የተለያዩ አይነት የተሻሻሉ የጋላክሲ ምርቶቹን ማውጣቱን ጠቁሟል፡፡
አይፎን ክሱን የመሰረተው በጋላክሲ ኤስ 2 ላይ ሲሆን፣ ክሱ ሳምሰንግ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያመረታቸውን ስማርት ፎኖች የማይመለከት በመሆኑ የፍርድ ቤቱ  ውሳኔ ለአይፎን ያን ያህልም ተጠቃሚ እንደማያደርገው ተዘግቧል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በፈጠራ ባለቤትነት ጉዳይ መካሰስ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው የታወቀ ሲሆን በቅርቡም “ሳምሰንግ ከአይፎን ኮርጀሃል” በሚል 980 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበት እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

 መንግስት በበኩሉ፣ ከ700 ሚ ዶላር በላይ በመዝረፍ ከሷቸዋል
   ሩስያዊው ቢሊየነር ሰርጊ ፑጋቼቭ፣ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን እና ታማኞቻቸው በህገወጥ መንገድ በሸረቡብኝ ሴራ ግዙፉን የባንክ ኩባንያዬን ለኪሳራና ለውድቀት ዳርገውታል፣ የአገሪቱ መንግስት 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከታዋቂ የአገሪቱ ባንኮች አንዱ የነበረው ሜዝፕሮም ባንክ ድንገት ተንኮታኩቶ የወደቀባቸውና በባንኩ ዘርፍ ከሚታወቁ የአገሪቱ ባለጸጎች አንዱ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሰርጊ ፑጋቼቭ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንና ታማኞቻቸው ዋና ዋናዎቹን ንብረቶቼን ነጥቀው ኩባንያዬን ለውድቀት ዳርገውታል ሲሉ፣ ባለፈው ሰኞ ዘ ሄግ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ላይ ክስ መመስረታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የሩስያ መንግስት በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ2008 ተከስቶ የነበረውን የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ ሜዝፕሮም የተባለውን የግለሰቡን ባንክ ለመደጎም በማሰብ የመደበውን ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል፣ በስደት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙት ሰርጊ ፑጋቼቭ ላይ ክስ መመስረቱንና ግለሰቡ ተላልፈው እንዲሰጡት የእንግሊዝን መንግስት እንደጠየቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እያጣራ ባለበት ሁኔታ ላይ በመሃል ቢሊየነሩ ከእንግሊዝ መውጣታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሩስያን መንግስት ክስ ተከትሎ የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ የአለም አገራት ውስጥ የሚገኙና 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ የሰርጊ ፑጋቼቭ ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያዘዘ ሲሆን ቢሊየነሩ ግን ከሩስያ የተሰነዘረባቸውን ክስ፣ መሰረተ ቢስና ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ውንጀላ ነው ሲሉ ማጣጣላቸው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን እንዲወጡ በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ቢሊየነሩ ፑጋቼቭ፣ ከእንግሊዝ ከወጡ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሳይሄዱ እንዳልቀሩ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡