Administrator

Administrator

Saturday, 30 May 2015 12:44

የሰውነታችን እውነታዎች

 

 

 

- ጨጓራችን የላም ወተትን ለማብላላት አንድ

ሰዓት ይፈጅበታል

- የሴቶች አይን ከወንዶች ይልቅ በእጥፉ

ይርገበገባል

- አንድ ሰው በአማካይ 2 ሚሊዮን የላብ

እጢዎች ይኖሩታል

- ህፃናት ሲወለዱ የጉልበት ሎሚ

አይኖራቸውም፤ ይህ ሰውነት ክፍል

የሚወጣው ከ2-6 ዓመት ባለው የህፃናቱ

እድሜ ውስጥ ጊዜ ነው

- በፀደይ ወራት የህፃናት እድገት ፈጣን ነው

 

 

 

 

Saturday, 30 May 2015 12:40

የግጥም ጥግ

እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞገጉ

“ሥጋችን የት ሄደ” ብለው ሲፈልጉ

በየሸንተረሩ በየጥጋጥጉ

አስሰው አስሰው በምድር በሰማይ

አገኙት ቦርጭ ሆኖ አንድ ሰው ገላ ላይ፡፡

(“ኗሪ አልባ ጎጆዎች”፤ በዕውቀቱ ስዩም)

Saturday, 30 May 2015 12:39

የፍቅር ጥግ

 

 

 

* ፍቅር በፈገግታ ይጀምራል፤በመሳሳም ያድጋል፤በእንባ ይቋጫል፡፡

            ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር እንደ ነፋስ ነው፤አታየውም ግን ይሰማሃል፡፡

            ኒኮላስ ስፓርክስ

* ምክንያት የሌለው ፍቅር ዕድሜው ረዥም ነው፡፡

            ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር አብሮን የተፈጠረ ሲሆን ፍርሃት እዚህ የምንማረው ነው፡፡

            ማሪያኔ ዊላምሰን

* የሚወደን ሰው ከሌለ፣ ራሳችንን መውደድ ትተናል ማለት ነው፡፡

      ማዳም ዲ ስቴል

* ራሳችሁን ማፍቀር እንዳትረሱ፡፡

      ሶረን ኪርክጋርድ-

* ሰውን መውደድ የእግዜርን ፊት ማየት ነው፡፡

      ሌስ ሚዘረብልስ

* ፍቅር ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከባድ ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ይጎዳል፡፡

      ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር ሲይዘን በጣም የምናምነውን ነገር እንጠራጠራለን፡፡

      ላ ሮቼፎካልድ

* ስለፍቅር የምናውቀውን ብዙውን ነገር የምንማረው ከቤት ነው፡፡

      ያልታወቀ ሰው

* ፍቅር ከምንም በላይ የራስ ስጦታ ነው፡፡

      ጄን አኖይልህ

* በፍቅር መውደቅ ቀላል ነው፤ከባዱ የሚያነሳህ ሰው ማግኘቱ ነው፡፡

      በርትራንድ ራሴል

* ልብህን ለከፈትክላቸው ሰዎች አንደበትህን አትዝጋባቸው፡፡

      ቻርልስ ዲከንስ

* ፍቅር፤የሌላው ሰው ደስታ ለራስህ ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ ነው፡፡

      ሮበርት ሄይንሊን

ሰው ሊደብቃቸው የማይችላቸው ሁለት ነገሮች፡ ስካር እና ፍቅር፡፡

አንቲፋንስ

* ሰዎችን የምትተች ከሆነ ለመውደድ ጊዜ አይኖርህም፡፡

ማዘር ቴሬዛ

 

 

 

 

 

 

 

ኢትዮጵያዊ ፊልሞችን የሚሰራው “ካም ግሎባል ፒክቸርስ” የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፈው ረቡዕ ለስድስት እውቅ ተዋንያን የክብር ሽልማት ሰጠ፡፡ ተሸላሚዎቹ አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ግሩም ኤርሚያስ፣ ማህደር አሰፋ፣ አማኑኤል ሀብታሙ እና የትናየት ታምራት ሲሆኑ ሁሉም ተዋናዮች ባለፉት ዓመታት ”ካም ግሎባል ፒክቸርስ” በሰራቸው ፊልሞች ላይ መተወናቸው ታውቋል፡፡ ድርጅቱ ከሰራቸው ፊልሞች መካከል “ስውሩ እስረኛ”፣ “በራሪ ልቦች”፣ “አማላዩ”፣ “ሼፉ” (ቁጥር 1 እና 2)፣ “ወደ ገደለው” እና “አማረኝ” ይገኙበታል፡፡

 

 

 

 

“እስኪ ተጠየቁ” የተሰኘው የዮሐንስ አድማሱ የግጥም መድበል ነገ በ8 ሰዓት በብሄራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት ይደረግበታል፡፡ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት አርክቴክትና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው እንደሆኑ ታውቋል፡፡ውይይቱን ያዘጋጁት እናት የማስታወቂያ ድርጅት፣ ጀርመን የባህል ማዕከልና ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ በጋራ ሲሆን የሥነፅሁፍ ቤተሰቦች በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

 

     የገጣሚ ኃይሌ ተስፋዬ ቸኮል የግጥም ስብስቦች የተካተቱበት “የራዕይ እግሮች” የተሰኘ የግጥም መድበል ነገ ከጧቱ 3፡00 ጀምሮ በፍፁም ሲኒማ ይመረቃል፡፡ የግጥሙ ይዘት ማህበራዊ፣ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ትዝብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን የግዕዝን ቋንቋ በመቀላቀል በጠንካራ አገላለፅ የታጀበ ነው ተብሏል፡፡

ገጣሚው ግጥም ወደመፃፍ የተሳበበትን ምክንያት በመድበሉ መግቢያ ላይ ሲያስረዳ፤ “ገና በ11 ዓመቴ አካባቢ ቤተክርስቲያን ስማር የእነሙሴን፣ ዳዊትን … ረዣዥም ግጥሞች ከመፅሀፍ ቅዱስ ቃል በቃል እገለብጥ ነበር፡፡ ይህ የህይወት ልምምድም እድሜዬ እየጨመረ በመጣ ጊዜ ትልቅ ዕርዳታ አድርጎልኛል” ብሏል ገጣሚው፡፡ በ110 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤ 73 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን ለአገር ውስጥ በብር 35.50፣ ለውጭ ደግሞ በ15 ዶላር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡ 

 

 

 

 

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በምቹ ወንበሮችና ከውጭ አገራት በገቡ የተለያዩ መሳሪያዎች የተደራጀው “ሶሎዳ ቪአይፒ ሲኒማ” በከተማዋ እምብርት አራት ኪሎ፣ ዴንቨር ታዎር ላይ ከትላንት በስቲያ ተመርቆ ተከፈተ፡፡በቪአይፒ ደረጃ የታነፀው ሲኒማ ቤቱ፤ በአንድ ጊዜ ውስን የተመልካች ቁጥር እንደሚያስተናግድ ተገልጿል፡፡

ሲኒማ ቤቱ የተከፈተበትን ምክንያት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ያብራራው ድርጅቱ፤ በሃገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲኒማ ኢንዱስትሪ ላይ እየታየ ያለውን መነቃቃት ከግምት ውስጥ በማስገባትና የማህበረሰባችንን አፍቅሮተ ጥበብ በመገንዘብ መሆኑን አስታውቋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

        በ2003 በከፍተኛ ሙቀት ከ3ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል

     በህንድ ሰሜናዊና ማዕከላዊ አካባቢዎች የተከሰተውን ያልተለመደ ሃይለኛ ሙቀት መቋቋም አቅቷቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ በላይ መድረሱን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ዘገበ፡በያዝነው ሳምንት በተጠቀሱት አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ የአገሪቱ የሜቲዮሮሎጂ ባለስልጣንም የሙቀት መጠኑ መጨመር በታየባቸው የአገሪቱ ግዛቶች የከፋ ጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቁን ገልጿል፡፡በአብዛኞቹ የህንድ ግዛቶች የሳምንቱ አማካይ የሙቀት መጠን 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ የሙቀት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የሰዎችን ተፈጥሯዊ አደጋን የመከላከል የሰውነት ስርዓት እንደሚያዛባና ለድካምና ለሞት እንደሚዳርግ ሃኪሞች መናገራቸውን ዘገባው አብራርቷል፡፡

የአገሪቱ መንግስት ዜጎች በከፍተኛው ሙቀት እንዳይጠቁ ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማቀዝቀዣ ውሃና ድርቀትን የመከላከያ ፈሳሾች እየተሰራጩ ነው ብሏል፡፡ ለሞት የተዳረጉት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ አረጋውያን እንደሆኑም ታውቋል፡፡ላልተለመደው የሙቀት መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከፓኪስታን አቅጣጫ ወደ ህንድ የሚነፍሰው ሞቃት ንፋስ እንደሚገኝበት ዘገባው ጠቁሟል፡፡ህንድ በእነዚህ ወራት ሞቃት አየር እንደሚኖራት ቢታወቅም የዘንድሮው ሙቀት ግን ከተለመደው በ6 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚበልጥ የዘገበው ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ፣ አንድራ ፕራዴሽ በተባለችው የህንድ ግዛት ባለፈው እሁድ የተመዘገበው 48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ባለፉት 68 አመታት በግዛቲቱ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ገልጿል፡፡

የህንድ የሳይንስ ኢንስቲቲዩት ጥናት እንደሚለው፤ ባለፉት 15 አመታት ከሙቀት መጨመር ጋር በቀጥታ በተያያዘ ሰበብ፤ በአገሪቱ በየአመቱ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች አማካይ ቁጥር 153 የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜ ሂደት ግን ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል ተብሏል፡፡

ከአምስት አመታት በፊት አህመዳባድ በተባለው የህንድ አካባቢ የተከሰተውና 112 ዲግሪ ፋራናይት የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን 1ሺህ 300 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስታወሰው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ፣ እ.ኤ.አ በ2003 በአንድራ ፕራዴሽ ግዛት የተከሰተ ከፍተኛ ሙቀትም ከ3ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሉን አክሎ ገልጿል፡፡

የሙቀት መጠኑ እስከ ወሩ መጨረሻ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ የህንድ የሜቲዮሮሎጂ ባለስልጣን ሃላፊ ዴቬንድራ ሻርማም፤ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡና ብዙ ውሃ እንዲጠጡ ጥሪ ማቅረባቸውንና በሙቀት መጠኑ መጨመር የተነሳ በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ መስተጓጐሉን ጠቁሟል፡፡

 

 

 

 

 

 

     የባንክ ሒሳብ ደብተር ቁጥር ይፋ አድርገዋል

    የአገሪቱ ህገ መንግስት ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው ከፍተኛ ተቃውሞና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያደረሰባቸው የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ ህዝቡ ምርጫውን በገንዘብ እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረባቸውን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡

ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚደርስባቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ጫና አልሰማም ብለው ለመወዳደር የቆረጡት ፕሬዚዳንቱ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለምርጫው ማስፈጸሚያ ቃል የገባውን የገንዘብ ድጋፍ ላለመስጠት በመወሰኑ ህዝቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ በፌስቡክ ገጻቸው ጥሪ አድርገዋል፡፡

“የኔን በምርጫ መወዳደር የደገፍክ የአገሬ ህዝብ ሆይ!... ለምርጫው ስኬታማነት በፈቃድህ የቻልከውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ አድርግ” ያሉት ፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ፣ ህዝባቸው ለምርጫው የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበትን የባንክ የሒሳብ ቁጥርም ይፋ አድርገዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ በምርጫ የመወዳደር ውሳኔ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት ያሰጋቸው ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ የተወሰነ መረጋጋት ቢፈጠርም ተቃውሞው እንደቀጠለ መሆኑንና ፕሬዚዳንቱም ምርጫውን በመጪው ሰኔ መጨረሻ ለማካሄድ መወሰናቸውን አክሎ ገልጿል፡፡

 

 

 

 

 

 

      በ2000 የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 400 ሚ. ብቻ ነበሩ

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለማቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት፤ ከዓለማችን ህዝብ ግማሽ ያህሉ እስከያዝነው የፈረንጆች 2015 አመት መጨረሻ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡ህብረቱ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፤ እስከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ በአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 3.2 ቢሊዮን እንደሚደርስና ከዚህ ውስጥም 2 ቢሊዮን ያህሉ ያደጉ አገራት ዜጎች እንደሚሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የሞባይል ብሮድባንድ አገልግሎት መስፋፋቱ በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ለማደጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ያለው ሪፖርቱ፣ በአሁኑ ወቅት በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት ቻይና፣ አሜሪካና ህንድ መሪነቱን ይዘው እንደሚገኙና በአመቱ መጨረሻ ግን ህንድ ሁለተኛ ትሆናለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡

የአለማችን ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ባለፉት 15 አመታት ከ6.5 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማደጉን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በቤታቸው የኢንተርኔት አቅርቦት ያላቸው ሰዎች ቁጥርም በ2005 ከነበረበት 18 በመቶ፣ ዘንድሮ 46 በመቶ ደርሷል ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2000 በአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 400 ሚሊዮን ብቻ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በአሁኑ ወቅት የአለማችን 69 በመቶ የሚሆነው አካባቢ የ3ጂ ኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁሞ፣ ይሄም ሆኖ ግን 29 በመቶ የሚሆኑ የገጠር አካባቢዎች ብቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል፡፡በሞባይል ብሮድባንድ ሽፋን ከአለማችን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አፍሪካ ስትሆን፣ በዘርፉ አህጉሪቱ ያላት ሽፋን 17.4 በመቶ ብቻ ነው ብሏል ሪፖርቱ፡፡