Administrator

Administrator

Saturday, 28 December 2019 13:51

የግጥም ጥግ

        የኛ ፖለቲካ

ያኔ የልጅነቱን የምታስታውሱ
የሰፈሬ ልጆች ባካችሁ ተነሱ፡፡
ያ! የሰፈራችን
በልጅነታችን
ያልሾምነው መሪያችን
ያ! ጉልቤ አውራችን፡፡
“አለቃ ነኝ” ብሎ ራሱን የሰየመ
“ተቧቀሱ” ሚለን ትእዛዝ እየሰጠ
“ሆያ ሆዬ” ሲደርስ ገንዘብ ያዥ ሚሆነው
ከሱ የተረፈውን የሚያከፋፍለው
…ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡
ያ! የሰፈራችን
በልጅነታችን
ያ! ጉልቤ አውራችን፤
አሁን ልጆች ወልዶ ቤት ሰርቶ ይኖራል፤
ያደረሰውን “ግፍ” ረስቶትም ይሆናል፡፡
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ፤
ኑ! ቤቱን እናፍርስ ተነሱ እንነሳ፡፡
ስልጣኔ እና ፍቅር
እንደ ቀድሞ አይደለም
እንደጥንት አይደለም
እኩልነት መጥቷል፡፡
መናገር ማውራቱ
ለባል ብቻ አይደለም
ለሚስትም ተፈቅዷል፡፡
እንደ ቀድሞ አይደለም
እንደ ጥንት አይደለም
ስልጣኔ መጥቷል
እቤት ብቻ አይደለም
በስልክም ይወራል፡፡
እናም እኔና አንቺ
እቤት በእኩልነት
ስንርቅ በስልክ ቤት ብዙ እናወራለን
ግና ለመግባባት ምን ያህል ጠቀመን?
(የግጥም መድብል)
አንድነት ግርማ


Saturday, 28 December 2019 13:49

የዘላለም ጥግ

• እውነተኛ ጀግና ማለት የራሱን ንዴትና ጥላቻ የሚያሸንፍ ነው፡፡
   ዳላይ ላማ
• ለራስህ ብቻ የምትጨነቅ ከሆነ ጀግና ልትሆን አትችልም፡፡
   The Lego Batman (ፊልም)
• ጀግና፤ ሽሽትን የሚፈራ ሰው ነው፡፡
   የእንግሊዞች አባባል
• ጀግና ራሱን ይፈጥራል፤ ዝነኛ በሚዲያ ይፈጠራል፡፡
   ዳንኤል ጄ.ቡርስቲን
• ጀግኖችህን ንገረኝና ህይወትህ እንዴት እንደሚጠናቀቅ እነግርሃለሁ፡፡
   ዋረን በፌ
• ጀግና፤ ጀግና የሚሆነው በጀገነ ዓለም ውስጥ ነው፡፡
   ናትናኤል ሃውቶርን
• ሁላችንም የራሳችን ታሪክ ጀግኖች ነን፡፡
   ማይክል ፎክስ
• ሳይፈሩ ጀግና መሆን አይቻልም፡፡
   ጆርጅ በርናርድ
• በሕይወት ስትኖር የራስህ ጀግና መሆን አለብህ፡፡
   ዣኔት ዊንተርሰን
• ቀኑን ሙሉ የሚሰሩ እናቶች - እውነተኛ ጀግኖች ናቸው፡፡
   ኬቲ ዊንስሌት

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ በጣም ብርቱ ሰው ነበረ፡፡ ይህ ሰው ሃሳቡን ማጋራት ይወዳል:: ምግቡንም ብቻውን መመገብ አይወድም፡፡ መወያየትና የመጣላትን አዲስ ሃሳብ ማንሳትና ማዳበር ያዘወትራል፡፡ ነጋ ጠባ አስተውሎቱን የማሳደግና ልባዊ የብስለት ፀጋን የማጐልበት፣ የመወያየት፣ ተስፋና ምኞትን የማለምለም፣ ብርቱ ታታሪነትን የማፍካትና አዲስ መንገድን አለመፍራት፣ ለለውጥ አለመሸማቀቅ፣ ሁልጊዜም የሃሳብ በርን የመክፈት ባህል ተገቢ የጉዞ ጥንካሬ አለው፡፡ ይህ ሰው አዘውትሮ “አዝማሪና ውሃ ሙላት” የሚለውን የከበደ ሚካኤልን ግጥም ይጠቅሰዋል፡፡ እንደሚከተለው፡-
አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር እያለ ጐርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ
ምነው አቶ አዝማሪ ምን ትሠራለህ ብሎ ቢጠይቀው
ምን “ሁን ትላለህ”
አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ
አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩስ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ
መሄድ መሄድ አለኝ ጐዳና ጐዳና
አልግደረደርም ዘንድሮስ እንዳምና
እስቲ ላነሳሳው አንበርብር ጐሹን
በደሬ አደባባይ የወደቀውን
እሱስ ሆኖ አይደለም ታሪከ - ቅዱስ
መጽደቁንም እንጃ ያች ያንበርብር ነብስ
ሃዋርያው ሲናገር ወደምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ!!
ኧረ ስንቱ ስንቱ፣ ናቸው የሞቱቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ
እናትሽን አትውደጅ ለ9 ወር ዕድሜ
ተሸክሜሻለሁ እስከዘላለሜ!
እንደ ዐይን እንደ ጆሮ፣ እንደ እግር እንደ እጅ
ወዳጅ ማለት አብሮ፣ ሲባክን ነው እንጂ
***
ሀገራችን ከልቧ ምሁር ትፈልጋለች፤ አለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” እንደሚባለው ይሆናል፡፡ አሊያም በከርሞ ሰው መንፈስ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው፤
“ምኞቴ እንደ ጉም መንጥቃ
ተስፋዬ እንደ ጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ ለርስታቸው ሳላበቃ
የእኔ ነገር በቃ በቃ!”
ምንም ይሁን ምንም፤ ከመሆን የማይቀር አንድ አንድ ጉዳይ፤ ከመፈፀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ሲሆን አይተን ዳኝነት ከመስጠት በስተቀር እነ ገዳይ የሚረፍዱ አያሌ ናቸው፡፡ ከበደ ሚካኤል እንዳሉት፤
“ሂደቱን ስንቆጥር፣
አለ አንዳንድ ነገር
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር”
ይህን የዓለም ዕውነት መካድ አይቻልም
ለውጡ ዐይናችን ሥር ነው ውሉ እንዲለመልም
አገር እንደ ኮረዳ አካል ያለ ፍቅር ከቶ አትጠናም
አንጀት ካልቆረጠ ግና
የአንጀት ጥሪው አይሰማም
ሳይበስል ፍሬው አይጠናም
መንገድ ሳይጀምሩት አያልቅ
ምኞት ዳር -ዳር አያፈራም
ፈተናው ለትዕግሥት ነው፤ ለማይሞት የቁም አበሳ
እንደ አዳኝ በማነጣጠር፣ እንደ ዕውር በዳበሳ
ለዳኝነት አትቸኩል፣ ለቀና መፍትሔው ሳሳ
ከሁለት ነገር አንድ ላለማጣት ልፋ፡፡
ተረታችን እንደሚለው፤
እጅህን ወደ ውሃው አስገባ
ወይ አሳ ይዘህ ትወጣለህ፡፡
አሊያም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ፡፡   

    የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱና ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ባለፈው ረቡዕ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ፣ ትራምፕ በአገሪቱ ታሪክ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ሶስተኛው ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪን በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እና በልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲያደርጉ በመደለልና ጫና በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ባለመስጠትና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱ በቀረበባቸው የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ፣ ለአስር ሰዓታት ያህል ክርክር ያደረጉት የምክር ቤቱ አባላት፣ በስተመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ  እንዲከሰሱና ሴኔት ፊት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል::
ዩክሬን በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ዴሞክራቶችን ለመወከል እየተፎካከሩ ባሉት ጆ ባይደን ላይ ምርመራ እንድታደርግ ጫና ማሳደር በሚል የቀረበው ክስ፤ በ230 የኮንግረሱ አባላት ድጋፍና በ197 ተቃውሞ፣ የቀረበባቸውን ክስ ለማጣራት በተጀመረው ጥረት ምስክሮች ቃላቸውን እንዳይሰጡ በመከላከልና መረጃ በመከልከል የምክር ቤቱን ስራ ማደናቀፍ የሚለው ክስ ደግሞ በ229 ድጋፍና በ198 ተቃውሞ ሁለቱም በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኮንግረሱ አባላት በአፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ አነሳሽነት በቀረቡት ሁለት ክሶች ላይ የሚያደርጉትን የድምጽ ስነስርዓት ሚቺጋን ውስጥ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ፣ በቴሌቪዥን በቀጥታ የተከታተሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀረበባቸውን ክስ የአክራሪ ግራ ዘመሞች ነጭ ቅጥፈትና በሪፐብሊካን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሉ እንዳጣጣሉት ተነግሯል፡፡
ሴኔቱ ከሳምንታት በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ መክሮ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣናቸውን የሚለቅቁት ከሴኔቱ አባላት ሁለት ሶስተኛው የድጋፍ ድምጽ ከሰጡበት ብቻ እንደሆነና ያም ሆኖ ግን  ሴኔቱ ሪፐብሊካን የሚበዙበት እንደመሆኑ በፕሬዚዳንቱ ላይ ውሳኔው የመተላለፉ ዕድል አነስተኛ እንደሆነ መነገሩን አመልክቷል፡፡
ኮንግረሱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ቀጥሎ ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ፣ ሴኔቱ በትራምፕ ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ እንደሚያደርገውና በነጻ እንደሚያሰናብታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው ማለቱን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ዋይት ሃውስ እርግጠኛ እንደሆነውና ብዙዎች እንደገመቱት ሳይሆን ቀርቶ፣፣ ሴኔቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስልጣን እንዲሰናበቱ ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ምክትላቸው ማይክ ፔንስ መንበረ ስልጣኑን ተረክበው እስከ መጪው የ2021 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ አገሪቱን ማስተዳደር እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በመሰል የኮንግረስ ውሳኔ ሴነት ፊት ቀርበው ክስ እንዲመሰረትባቸው የተወሰነባቸው ሁለት የአገሪቱ መሪዎች አንድሪው ጆንሰንና ቢል ክሊንተን እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ሁለቱም ከስልጣን እንዲለቅቁ እንዳልተወሰነባቸው አክሎ ገልጧል፡፡የፓኪስታን መንግስት በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የጦር መሪ ጄኔራል ፔርቬዝ ሙሻራፍ ላይ ባለፈው ማክሰኞ የተላለፈውን የሞት ፍርድ ቅጣት እንደሚቃወምና ውሳኔውን ለማስቀየር እንደሚሰራ ማስታወቁን ዴይሊ መይል ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ልዩ ፍርድ ቤት በስልጣን ዘመናቸው ባልተገባ ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አገሪቱን ወደ ቀውስ አስገብተዋታል ተብለው በተከሰሱት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔርቬዝ ሙሻራፍ ላይ በሌሉበት የሞት ፍርድ መወሰኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ግን ተከሳሹ ምላሻቸውን ባልሰጡበትና በከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ በጥድፊያ የተላለፈው ፍርድ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ይግባኝ ለመጠየቅና ውሳኔውን ለማስቀየር መዘጋጀቱን እንዳስታወቀ አመልክቷል፡፡
በ2008 አገራቸውን ጥለው ወደ ዱባይ የተሰደዱትና በአሁኑ ወቅት በዱባይ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙት የ76 አመቱ ሙሻራፍ፤ በ2007 ባልተገባ ሁኔታ ጥለውታል በተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተባበሯቸው ባለስልጣናትና አጋሮች በክሱ አለመካተታቸውን እንደ አንድ መቃወሚያ የጠቀሱት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ “በዱባይ ህክምና የሚያደርጉላቸው ሃኪሞችም ሙሻራፍ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደማይችሉ ባረጋገጡበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉ አግባብነት የለውም” ሲሉ መቃወማቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1999 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን በመያዝ አገሪቱን ከ2001 እስከ 2008 በፕሬዚዳንትነት የመሩት ጄኔራል ፔርቬዝ ሙሻራፍ የሞት ፍርዱ ቢተላለፍባቸውም፣ ዱባይና ፓኪስታን ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ስለሌላቸው ዱባይ አሳልፋ አትሰጣቸውም ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ገልጧል፡፡ ሙሻራፍ፤ወደ አገራቸው ተመልሰው በፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ ቢሆኑም ሃኪሞቻቸው እንዳልፈቀዱላቸው ነግረውኛል ሲሉ የተናገሩት የሙሻራፍ ጠበቃ አክታር ሻፍ በበኩላቸው፣ ደምበኛቸው በዱባይ ከሚገኙበት ሆስፒታል በቪዲዮ መልዕክት ለፍርድ ቤቱ ምላሻቸውን እንዲሰጡ ቢጠይቁም፤ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበላቸውና በዚህ ሁኔታ የሞት ፍርዱ መተላለፉ አግባብ አለመሆኑን እንደገለጸ ዘገባው አመልክቷል፡፡ ሙሻራፍ ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤናዚር ቡቶ በተገደሉበት ሴራ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 አንጎላ በ2019 ብቻ ከመንግስት የተመዘበረ 5 ቢ. ዶላር ማስመለሷን ገልጻለች


            የናይጀሪያ የፍትህ ሚኒስትር አቡበከር ማላሚ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ 400 ቢሊዮን ዶላር ያህል የህዝብ ገንዘብ ዘርፈው ወደ ውጭ አገራት ማሸሻቸውን እንዳስታወቁ ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸረ ሙስና ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ባለስልጣናቱ በውጭ አገራት ከሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎችና አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር፣ አገሪቱን 400 ቢሊዮን ዶላር ያህል ዘርፈዋታል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ከውጭ ሃይሎች ጋር በመተባበር፣ የሚፈጽሙትን መሰል ዘረፋ ለመከላከል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተቀናጀ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ማስታወቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ አንጎላ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በባለስልጣናት የተዘረፈ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት እንዲመለስ ማድረጓን አልጀዚራ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ኩየሮዝ እንዳሉት፤ የአገሪቱ መንግስት በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ ከመንግስት ካዘና የተዘረፈ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ከሃገር ውስጥና ከውጭ ለማስመለስ የተቻለ ሲሆን፣ በተለይም ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎሬንሶ አገሪቱን ለ40 አመታት ያህል የመሩትንና ልጃቸውን ጨምሮ በሙስና እንደተጨማለቁ የሚነገርላቸውን ጆሴ ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስን ተክተው ስልጣን ከያዙ በኋላ ባለፉት 2 አመታት መሰል የህዝብ ሃብት ምዝበራንና ሙስናን ለመዋጋት እርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡


 የዚምባቡዌ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ባለቤት፣ ሜሪ ቺዌንጋ ባላቸውን በመግደል ሙከራና በከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር ክስ እንደተመሰረተባቸው ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሰኞ በመዲናዋ ሃራሪ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሜሪ ቺዌንጋ፤ ባለፈው ሃምሌ ወር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ባለቤታቸውን ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋን ወደ ህክምና እንዳይሄዱ በመከልከል አንዲሁም ሆስፒታል ከገቡ በኋላም የተተከለላቸውን የህክምና መሳሪያ በመንቀል ለሞት ለመዳረግ ሞክረዋል በሚል መከሰሳቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የ38 አመቷ ሜሪ ቺዌንጋ፣ ከዚህ በተጨማሪም፣ 1 ሚሊዮን ዶላር ያህል በማጭበርበር፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ አሸሽተዋል በሚል የከፍተኛ ገንዘብ ማጭበርበርና የሙስና ክሶች እንደተመሰረቱባቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ፍርድ ቤት በቅርቡ ውሳኔ ያስተላልፍባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

Saturday, 21 December 2019 13:21

የዝነኛ ሴቶች ጥግ

• ‹‹በአገሪቱ ድንቅ የጥበብ ታሪክ ውስጥ የራሴን አሻራ ማስቀመጥ በሚያስችለኝ የሙያ መስክ መሰማራት በመቻሌ፣ ራሴን እንደ ዕድለኛ ነው የምቆጥረው፡፡…››
   ሳራ አበራ (ፋሽን ዲዛይነር)
• ‹‹ለአገሬ ትልልቅ ህልሞች አሉኝ:: ዴሞክራሲ እንዲሁ ለአፍ ያህል ብቻ የ ምናወራለት ሳ ይሆን ት ርጉም ያለው የሕይወታችን ዘይቤ እንዲሆን እፈልጋለሁ::››
   ሶፊ ይልማ (ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ)
• ‹‹ለስኬቴ ምስጢሩ ለሥራዬ ያለኝ ከፍተኛ ፍቅር ነው፡፡ ሥራዬ ለእኔ ሕይወቴና በጋለ ውስጣዊ ፍቅር የምተጋለት ሁሉ ነገሬም ነው፡፡››
   ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ (አምባሳደር)
• ‹‹ከህክምና ዶክተሮች የላቀ ገቢ የሚያገኙ የጫማ ዲዛይን ሰሪዎች፣ ከባንክ ተቆጣጣሪዎች የበለጠ የሚከፈላቸው የስፌት ሠራተኞች በሶልሬብልስ ውስጥ
መኖራቸው ያኮራኛል፡፡ ብልፅግና ይሏል ይሄ ነው!››
   ቤተልሔም ጥላሁን (የሶልሬብልስ መሥራች)
• ‹‹ወደ ውስጣችሁ ተመልከቱ፤ በሕይወታችሁ ልትሰሩ ስለምትችሉት ታላቅ ነገር ራሳችሁን ጠይቁ፤ እናም አድርጉት!››
   ብሩክታዊት ጥጋቡ (የሕጻናት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ፈጣሪ)
• ‹‹እያንዳንዷን ነገር በጥልቀት እንደ መፈተሽና ውስጣዊ ባህርያቱን እንደማወቅ የሚያጓጓ ነገር የለም፡፡››
   ዶ/ር ታደለች አቶምሳ (የፊዚክስ ባለሙያ፤ ተመራማሪ)
• ‹‹በኢትዮጵያ የትኛዋም ሴት ከጥቃት ነፃ አይደለችም ብዬ አምናለሁ፡፡ የፆታ ጥቃት ባይሆን እንኳን የሞራል ጥቃት አይቀርላትም፡፡››
    ወንጌል ተስፋዬ (ረዳት ሳጂን፤ ወንጀል መርማሪ)
(ከ‹‹ተምሳሌት - ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች›› የተወሰደ

Sunday, 22 December 2019 00:00

የፖለቲካ ጥግ

• ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ ቢሆን ኖሮ፤ በአህያ ጀርባ ላይ አይጓዝም ነበር:: በአውሮፕላን ይበራል፤ በሚዲያ ይጠቀማል፡፡
   ጆኤል ኦስቲን
• በዲጂታል ሚዲያና በህትመት ሚዲያ መካከል ድንበር ያለ አይመስለኝም፡፡
   ያልታወቀ ሰው
• ትላንትና በእንግሊዝም በአሜሪካም የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም ድል ተደርጓል፡፡
   ፎክስ ኒውስ (በቅርቡ የእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ በዝረራ ሲሸነፍ)
• አብዛኛውን ጊዜ፣ መደበኛ ሚዲያዎች፣ አንድን ጉዳይ ላይ ሲዘግቡ፤ ሙሉ ታሪኩን አይናገሩም፡፡
   ሼንስሚዝ
• ዓይናችን እያየ የፖለቲካ ፓርቲ እየሞተ ነው፤ ዲሞክራቶችን ማለቴ አይደለም:: የማወራው፤ በተቃዋሚዎች እየጠፋ ስላለው መደበኛ ሚዲያው ነው፡፡
   ሆዋርድ ፊንማን
• እንጋፈጠው፡፡ ዊኪሊክስ የመጣው መደበኛ ሚዲያው ስራውን በቅጡ ባለመስራቱ ነው፡፡
   ጄሲ ቬንቱራ
• ጋዜጠኛ የሆንኩት፤ ለመረጃ በጋዜጦች ላይ እምነቴን እንዳልጥል ነው፡፡
   ክሪስቶፈር ሂችንስ
• መደበኛ ሚዲያው የሚያተኩርበትን ነገር ተጠንቀቅ፡፡ መደበኛ ሚዲያው ችላ ያለውን ጉዳይ ደግሞ አትኩርበት፡፡
   ሶቴሮሜ ሌፔዝ
• ሴቶች በአመራር ከወንዶች የተሻሉ ናቸው፡፡
   ባራክ ኦባማ

Page 7 of 464