Administrator

Administrator

 በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰዋ የመን የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ1ሺህ 600 በላይ የመናውያንን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ ወረርሽኙ በስፋት በመሰራጨት ሁሉንም የአገሪቱ ግዛቶች ማዳረሱን ያስታወቀው ተመድ፣ ከ270 ሺህ ያህል ዜጎችም የኮሌራ ተጠቂ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ መገመቱን ገልጧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመግታትና
ታማሚዎችን በአግባቡ ለማከም ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ጃሪክ፣ ባለፈው ማክሰኞ 400 ቶን ያህል የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በኮሌራ የተጠቁ የመናውያንን ለማከም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 600 ያህል ጊዚያዊ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙም አመልክተዋል፡፡

  አሜሪካ ሰሜን ኮርያ በሳምንቱ መጀመሪያ ለፈጸመቺው የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ የከፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ ያደረገቺው ሰሜን ኮርያ እጅግ አደገኛ አካሄድ እየተከተለች ነው፤ ለዚህ ድርጊቷ ጠንከር ያለ ምላሽ ያስፈልጋታል ብለዋል ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ዋርሶ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብ ሰሜን ኮርያ ከዚህ አጥፊ ድርጊቷ እንድትታቀብ ማድረግ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የሰሜን ኮርያ ሚሳኤል ረጅም ርቀት በመጓዝ የአሜሪካዋን የአላስካ ግዛት የመምታት አቅም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሊ በበኩላቸው የሚሳኤል ሙከራውን ተከትሎ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ መጠነኛ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስታወቃቸውን አስታውሷል፡፡ ሰሜን ኮርያ የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለባትን ማዕቀብ በሚጥስ መልኩ የሚሳኤል ሙከራውን ማድረጓን ተከትሎ፣ የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን ድርጊቱን በጽኑ አውግዞታል፡፡ ደቡብ ኮርያን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መንግስታት ድርጊቱን ማውገዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር በሰሜን ኮርያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል፡፡
ሩስያና ቻይና በበኩላቸው ድርጊቱን ቢኮንኑም፣ እነ አሜሪካ የያዙትን ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ አማራጭ ለሌላ የከፋ ቀውስ የሚዳርግ አደገኛ አካሄድ በሚል እንደማይደግፉት አስታውቀዋል፡፡

 በሀዋሳ፣ የእኛው ለእኛ በጎ አድራጎት ማኅበር አባላት በበዓላት ወቅት ዶሮም ሆነ በሬ አርደው አረጋውያን አብረዋቸው በልተውና ጠጥተው ተደስተው ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ከእንብራ የማኅበር ሱቅ ዘይት፣ ዱቄት፣ ሳሙና፣… ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ገዝተው ለአረጋውን ይሰጣሉ፡፡ ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸውና በዝናብ ወቅት የሚያፈስ ቤት ክፍለ ከተማውን አስፈቅደው፣ ለጥገና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን የከተማው ባለፀጎች እንዲደግፏቸው ለምነው እነሱው አናጢ፣ እነሱው መራጊ፣ እነሱው ሁሉን ነገር ሆነው ቤታቸውን ይጠግኑላቸዋል፡፡
በየሳምንቱ እሁድ የአረጋውያን ቤት ይፀዳል፣ ልብሳቸው ይታጠባል፡፡ ሴት የማኅበሩ አባላት፤ እሁድ እሁድ ቡና አፍልተው በማጠጣት፣ ፀሐይ ሞቀውና ፈታ ብለው ወደ የቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ልብስ ከከተማው ማኅበረሰብ ሰብስበው (ለምነው) አረጋውያኑን ያለብሷቸዋል፡፡ የተሰበሰበው ልብስ ልካቸው ካልሆነ ተሽጦ በገንዘቡ በልካቸው ልብስ ይገዛላቸዋል፡፡ አንሶላ፣ ትራስ፣ ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣… እየገዙ ለአረጋውያኑ እንደሚሰጡ ወጣት አገኘሁ ወርቁ ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት ባለፈው ሳምንት የማኅበረሰብ ምሥርት ተቋማት የመልካም ተሞክሮ ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ለ3ኛ ጊዜ ባከበረበት ወቅት ተናግሯል፡፡
በባህርዳርም ከተማም ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዳለ፣ ለቀድሞ ባለውለታ አረጋውያን ክብር እየተሰጠ መሆኑን የባህርዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ተስፉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳኛቸው ከጥምረቱ ውጭ ፋና የሕፃናትና ማኅበረሰብ ልማት ማኅበር አስተባባሪ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን ለመደገፍ በከተማዋ ብዙ ተግባራት እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ፋና ማኅበር፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው፣ መሥራት ለማይችሉ፣ አልጋ ላይ ለወደቁ፣ ወጥተው መለመን እንኳ ለማይችሉና ለተረሱ 98 አረጋውያን ክብር በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው  ጠቅሰው፣ በራሳቸው መፀዳዳት የማይችሉትን የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር እንዲያፀዳዷቸውና ቤታቸውን በተራ እንዲያፀዱ፣ አረጋውያን ወደ ውጭ ወጥተው ፀሐይ የሚሞቁበት ተሸከርካሪ ወንበር የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር እንዲለግሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢሕማልድ) የዛሬ 32 ዓመት በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ለመታደግ የተቋቋመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ናቸው፡፡
በድርቁ ወቅት ድርጅቱ 6 የሕፃናት ማሳደጊያ ከፍቶ፣ ከ1000 በላይ ሕፃናትን ከተለያዩ አካባቢዎች ሰብስቦ ሲያሳድግ እንደነበረ የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ አንድ ሕፃን ኅብረተሰቡ ውስጥ አድጎ የኅብረተሰቡን እሴቶች ማወቅ፣ ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር ማግኘት ስላለበት ኅብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራ ውስጥ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን የልማት ሥራዎች ድርጅቱ ከዚያ ቢወጣ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? በማለት አንድ ማኅበር መስርተው 7 ዓመት አብረው ሰርተው ቢወጡም ምስርት ማኅበራትንና ዕድሮችን በማጎልበት ድርጅቱ ሲሰራ የነበረውን እነሱ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢሕማልድ በአሁኑ ወቅት እያከናውናቸው ያሉት 3 ፕሮግራሞች 1ኛ፡- በማኅበራዊ አገልግሎት በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ከቤተሰብ ጋር እያሉ መደገፍ፣ 2ኛው፡- የኑሮ ማሻሻያና የአካባቢ ጥበቃ፣ 3ኛው፡- የምስርት ተቋማትን አቅም ማጎልበትና ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የውጭ እጅ ከማየት ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አገር ውስጥ ያለን ሀብት በመጠቀም፣ ሀብቱ ውጤት እንዲያመጣ እየሠራን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤በዚህ ረገድ አንድ የስብሰባና የማሠልጠኛ ተቋም በቢሾፍቱ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ማሠራታቸውንና ይህ አሠራር ወደ ምስርት ማኅበራትም እየወረደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕንፃናትን በተቋም ከማሳደግ ይልቅ ማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ያለውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በመገንዘብ በ1996 ዓ.ም ከማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ጋር በሙከራ የተጀመረው የልማት ሥራ፤በአሁኑ ወቅት አድጎ በ22 የተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከ142 ማኅበራትና  ዕድሮች ጋር ዘላቂ የልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት የኢሕማልድ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ ቅጣው፤ቀደም ሲል አባላትን በማስተዛዘን ሥራ ላይ ብቻ ተጠምደው የነበሩ ዕድሮች የአሰራር ስልታቸውን በመቀየር ሕዝቡ የራሱን ችግር በራሱ ለመፍታት ኅብረተሰብ አቀፍ ልማት ውስጥ መግባታቸው ምርጥ ተሞክሮና ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡
በሐዋሳ ከተማ ከኢሕልማድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተው የእንብራ ራስ አገዝ ማኅበር ወጣት ቡድን አባል የሆነው አገኘሁ ወርቁ፣ አባቱን በሞት የተነጠቀው በኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ከእሱ ጋር የ3 ልጆች እናት የሆነችው እናቱ፤ምንም የሌላት የቤት እመቤት ነበረች። እቤት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ስለነበረባቸው አገኘሁ ወደ ጎዳና ወጣ፡፡ እየለመነና ትንንሽ ዕቃዎች በመሸከም የሚያገኘው መጠነኛ ገቢ፣ ጎዳና ከወጣ በኋላ ለለመደው ሱስ አልበቃ አለው፡፡ ስለዚህ እሱና ጓደኞቹ ጨለማን ተገን አድርገው ሞባይል መቀማትና ኪስ መበርበር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እሱ ከሌሎች ጓደኞቹ ፈርጠም ያለ ስለነበር ሰዎችን አንቆ ሲይዝ፣ ሌሎቹ ኪስ ገብተው ይበረብሩ ነበር፡፡ አሁን የእሱና የጓደኞቹ ሕይወት ተለውጧል፡፡
እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር አቅርቧቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክርና ስልጠና ሰጣቸው፡፡ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶላቸው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት ከቤት ወጥተው እንዲሰሩ አደረጋቸው፡፡ ፎቶ ኮፒ፣ መጠረዣና ማሸጊያ መሳሪያ ገዝቶ የሥራ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ከአገኘሁ ጋር ሲቀሙ ከነበሩት ጓደኞቹ አንደኛው አሁን 5ኛ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ፣ ወላይታ ሶዶ ውስጥ ሲኖትራክ እያሽከረከረ መሆኑን፣ አገኘሁ ደግሞ ሐዋሳ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ 2ኛ ዓመት ተማሪ መሆኑን ገልጾ፣ ሕይወቱ እንዲለወጥ ያደረገውን ኢሕማልድን ከልቡ አመስግኗል፡፡
በማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ምርጥ ተሞክሮ ቀን የተገኙ በርካታ ማኅበራትና ዕድሮች ኢሕማልድ ቢወጣ የራሳቸው ገቢ ማግኛ ፕሮጀክት ስላላቸው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንደማያቋርጡ ተናግረዋል፡፡  
የባህር ዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ሰይፉ ቤትና መጋዘን ሰርቶ በማከራየት፣ ሥጋ ቤት ከፍቶ በመነገድ፣ … በአጠቃላይ በተለያዩ የገቢ ማግኛ ፕሮጀክቶች በመሰማራት በዓመት ከ650 ሺህ ብር በላይ ስለሚያገኙ፣ ወላጅ አልባና የቤተሰባቸው የገቢ አቅም አነስተኛ የሆኑትን ሕፃናት አስፈላጊ ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ት/ቤት ልከው እያስተማሩ መሆኑን፣ ለቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ብድር በመስጠት የገቢ አቅም እንደፈጠሩላቸው፣ ለአረጋውያን የፈረሰባቸውን ቤት በመጠገን፣ በዓመት በዓል ጊዜ ከብት አርደው በማብላትና የተወሰነውን ወደ ቤታቸው ይዘው እንዲሄዱ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የተለያየ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሐዋሳና አካባቢው (ሻሸመኔና አቼቡራን ያጠቃልላል) ምስርት ማኅበራት ጥምረት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ከበደ የአቶ ዳኛቸውን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ጥምረታቸው 41 ዕድሮችና ማኅበራትን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢሕማልድ የሚያደርግላቸውን ድጋፍ ቢያቋርጥ ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን ማህበራዊ አገልግሎት ላለማቋረጥና ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ በ3,170,200 ብር ካፒታል አቋቁመው፣ 1,869,621 ብር ትርፍ ማግኘታቸው ገልጸዋል፡፡
ባገኙት ትርፍ፣ በማኅበሩ ውስጥ ላሉና ለሌሎች ችግረኛ ሕፃናት ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ወደ ጎዳና ለመውጣት እያኮበኮቡ እያሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው፣ ለወጣቶች 2500 ብር ተዘዋዋሪ ብድር በመስጠት የተለያየ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ ለችግረኛ ልጆች ቤተሰቦች 4000 ብር ብድር በመስጠት ነግደው የብድሩን 60 በመቶ ለራሳቸው ተጠቅመው፣ 40 በመቶውን እንዲመልሱ ይደረጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለገቢ ማግኛ በዕድሮችና ማኅበራት የሚተዳደሩ 15 ባጃጆች አሉ፡፡ እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር 3፣ የዕድሮች ኅብረት 4፣ 03 ቀበሌ መረዳጃ ማኅበር ዕድር 2፣ ሐረር ሰፈር መረዳጃ ዕድር 4 ባጃጆች፣ እንዳሏቸው የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ባጃጆቹ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ሲሠሩ ቆይተው ሌሊት ለሕሙማን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡   

   - 30 ተማሪዎችን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አስመርቋል
                          - የዛሬ ሳምንት 100 እናቶችን በተለያየ ሙያ አስመርቋል
                          - በአሁኑ ወቅት ከ950 በላይ ሰዎች በቀን 3 ጊዜ ምግብ ያቀርባል
                       
     የአብስራ፣ እጆቿ ደረቷ ላይ ሆነው እግሮቿ ተጠላልፈው ነበር ከእናቷ ማህፀን የወጣችው፡፡ ስለዚህ እጅና እግሯን ማንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች በኋላ ወ/ሮ ሙዳይ ተቀብላ እያሳከመች፣ ልዩ መቀመጫ ወንበር አሰርታላት፣ ዩኒፎርም አልብሳት፣ የትምህርት መሳሪያ አሟልታላትና እየመገበች እያስተማረቻት ትገኛለች፡፡ የአብስራ እጆቿ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ የምትጽፈው በጥርሷ ነው፡፡ በጥርሷ የሚያምር ጽሑፍ እየጻፈች ዘንድሮ በ11 ዓመቷ ከመዋለ ህፃናት ትመረቃለች፡፡
“ድሃ ስለሆንኩ እሷን የግል ት/ቤት ከፍዬ ማስተማር አልችልም፡፡ ብችልም የሚቀበላት ት/ቤት የለም” ትላለች፤ እናትና ሞግዚቷ ወ/ሮ ገነት አዱኛ። “ያለኝ አማራጭ ልጅቷን ወደ መንግስት ት/ቤት መውሰድ ነበር፡፡ እዚያም ብወስዳት ለእሷ የሚሆን አስተማሪና ልዩ መቀመጫ የለንም፡፡ በአጠቃላይ ለእሷ የሚሆን የልዩ ፍላጎት ማስተማሪያ ስለሌለን አንቀበላትም” ብለው መለሷት፡፡ ስለዚህ እቤት መልሰናት በር ዘግተንባት ነበር ወደ ስራ የምንሄደው በማለት የልጇን ችግር ገልጻለች፡፡
ወ/ሮ ገነት አዱኛ አዲስ አበባ ውስጥ አንቆርጫ በሚባል አካባቢ ነዋሪ ነበረች፡፡ አብስራን የወለደችው የካቲት ሆስፒታል ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ሲያዩዋት ሪፈራል ብለው ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጻፉልኝ፡፡ እዚያም ከአንድ ወር በኋላ አምጫት ብለው መለሷት። ጊዜው ሲደርስ ወሰድኳት፡፡ 15 ቀን አስተኝተው ኦፕራሲዮን አደረጓት፡፡ ከዚያም ጄሶ ታሰረላት፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ለ3 ወር 24 ሰዓት የሚደረግ ጫማ አሰሩላት፡፡ እሱም ምንም አላሻላትም፡፡ በመጨረሻ ሙከራችን ምንም ተስፋ የለውም” በማለት እንዳሰናበቷት በሀዘን ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር፤ ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ በልመና የተሰማሩና በሴተኛ አዳሪነት ሕይወታቸውን ሲገፉ የነበሩትን እናቶች፣ ከእነልጆቻቸው ከዚያ አረንቋ ውስጥ አውጥቶ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ ደርጅት ነው። እናቶችን ከነበሩበት አስከፊ ህይወት አውጥቶ መጠለያ በመከራየት፣ ሙሉ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው፣ በተለያዩ ሙያዎች፣ በሽመና፣ በሸክላ ስራ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ስፌት፣ በዕደ ጥበብ ስራዎች አሰልጥኖ ከተመጽዋችነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
ልጆቻቸው ሙሉ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው፣ ዩኒፎርም ተሰፍቶላቸው፣ የትምህርት መሳሪያዎች እየተሰጣቸው፣ ቁርስ፣ ምሳና እራት እያበሉ እንደየትምህርት ደረጃቸው ሙሉ ወጪያቸው ችሎ፣ በነፃ ከመዋለ ህፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ግቢው ውስጥ በሚገኘው “ፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ” እያስተማረ ነው፡፡ ከ9ኛ ክፍል እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በአቅራቢያው ባሉ ት/ቤቶች እንዲሁም በተመደቡባቸው የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ወጪያቸውን በመሸፈን እንዲማሩ ያደርጋል፡፡
ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ለ430 እናቶች፣ ለ50 አካል ጉዳተኞች፣ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ህፃናትና ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ በቀን ሶስት ጊዜ ቁርስ ምሳና ራት እንዲበሉም እያደረገ ነው፡፡ ማኅበሩ ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በተለያዩ ሙያዎች፡- በሸክላ፣ በሽመና፣ በዕደ ጥበብ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ስፌት ያሰለጠናቸውን 100 እናቶችን ያስመረቀ ሲሆን በድጋፍ ስራ ላይ በቆየባቸው 17 ዓመታት ከ1000 በላይ ለሆኑ እናቶች የተለያየ ሥልጠና ሰጥቶና ራሳቸውን ችለው ከማኅበሩ እንዲወጡ አድርጓል። 30 ተማሪዎችን ወጪያቸውን ችሎ በማስተማር፣ ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አስመርቋል። ለ1500 ሰዎች የትራስፖርትና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎችን ሸፍኖ፣ ወደመጡበት የመኖሪያ አካባቢ እንዲመለሱ ማድረጉም ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል 100 እናቶች በተመረቁበት ወቅት ጥቂቶቹን አነጋግረን ነበር። ዘሪቱ ራፍዬ በወሎ ክፍለ ሀገር የአማራ ሳይንት አካባቢ የቤት እመቤት ነበረች፡፡ አንድ ወንድ ልጅ እንደወለደች ባሏ ይሞትባታል፡፡ ቸግሯት አዲሳባ ወዳሉት ዘመዶቿ ዘንድ ከመጣች 16 ዓመት ሆኗታል፡፡ ገቢዋ በየሰው ቤቱ ልብስ እያጠበችና እንጀራ እየጋገረች የምታገኘው ትንሽ ገንዘብ ነበር። በዚህ መኸል ሌላ ወንድ ተዋውቃ ሴት ልጅ ወለደች። ሁለት ልጆች ማብላቱ ማጠጣቱ ማልበሱ፣ ማስተማሩ በአጠቃላይ ተንከባክቦ ማሳደጉ ትልቅ ፈተና ሆነባትና በጣም ተቸገረች፡፡
ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡ አመጣጧም ሰው ጠቁሟት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ሰዎች “ኮተቤ አካባቢ ሙዳይ በጎ አድራጎት የሚባል አለ፡፡ እንኳን አንቺን እንዲህ የተቸገርሽውን ቀርቶ ሌላውንም ይቀበላሉ፡፡ ሄደሽ ጠይቂ” አሏት፡፡ ሄዳ ጠየቀች፡፡ ወ/ሮ ሙዳይም ልታግዛት ፈቃደኛ ሆና ተቀበለቻት፡፡ እሷና ሁለቱ ልጆቿ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
“እዚህ ከመጣሁ አንስቶ ድጋፍ የሚደረግ ነገር ሁሉ ምንም የቀረብኝ የለም፡፡ በጣም ታምሜ ነበር። አሳክማ ለልጆቼ እንድተርፍላቸው አድርጋኛለች። ልብስ በዓመት ሁለቴ ይሰጠናል። በቀን ሶስቴ እንበላለን፤ ቤት ተከራይታልኛለች፡፡ እዚሁ እሰራለሁ፣ በሽመና ሰልጥኜ ባለፈው ሳምንት በሻርፕ ስራ ተመርቄያለሁ፡፡ ሁለቱም ልጆቼ ጫማና ዩኒፎርም ተገዝቶላቸው፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው፣ በቀን ሦስቴ እየተመገቡ፣ 6ኛና 4ኛ ክፍል እየተማሩ ነው፡፡ ተመስጌን ነው የምለው” በማለት ገልጻለች፡፡
የ27 ዓመቷ ራሄል ሽፈራው ትውልዷ ጅማ ነው። ወደ አዲስ አበባ የመጣችው አክስቷ ጋ ሆና ለመማር ነው። አክስቷም እያሳደገች አስተማረቻት። 10ኛ ክፍል ደርሳ ስትፈተን ውጤት ሳይመጣላት ቀረ፡፡ ይኼኔ ከአክስቷ ተጣልታ ከቤት ወጣች፡፡ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ መስተንግዶ እየሰራች ስትኖር፣ ከአንድ ወንድ ጋር ተዋውቃ፣ በጓደኝነት አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ አረገዘችና ልጅ ወለደች፡፡ ልጅ ተወልዶ ዓመት ሲሞላው ባል ጥሏት ጠፋ፡፡
ያለ አባት ለብቻልጅ ማሳደግ ከባድ ፈተና ነው ትላለች ራሄል፡ “ትልቅ ስቃይና ችግር ነው ያየሁት። ለልጁ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሁሉ ማድረግ አቅቶኝ ትልቅ ችግር ውስጥ ገባሁ፡፡ አሰሪዬ የቤት ኪራይ ትከፍልልኝ ነበር፡፡ እኔ ገንዘብ ለማግኘት ልብስ አጥብ ነበር፡፡ የማገኘው ገንዘብ ትንሽ ስለነበረ ከአቅሜ በላይ ሆነብኝና ልጄን ማሳደግ አቃተኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች “የተቸገሩ የሚረዳ እንዲህ የሚባል ድርጅት አለ፡፡ እዚያ ሄደሽ ሞክሪ” አሉኝ፡፡
“ይኼ የሆነው በ2005 ነበር፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት መጥቼ ችግሬን ነግሬ፣ እንድትረዳኝ ወ/ሮ ሙዳይን ጠየኳት፡፡ እሷም ቤቴን ሄዳ አይታ፣ ስለ አኗኗሬ ሰዎች ጠይቃ ተቀበለችኝ፡፡ ልጄ አሁን 4 ዓመቱ ነው፣ መዋለ ህፃናት ገብቷል። እኔን እያሰለጠነች ቤት ተከራየችልኝ፤ ቀለቤንና ወጪዬን የምትችለው እሷ ናት፡፡ ባለፈው ሳምንት የተመረቅሁት በአበባ ማስቀመጫ ስራ ነው፡፡ ሌሎች ሙያዎችም ለማወቅ እጥራለሁ፡፡ ትልቁ ሙያዬ ግን የተመረቅሁበት ነው” በማለት ታሪኳን ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ቋሚ ገቢ የለውም፡፡ የገቢው ምንጮች የተለያዩ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያደርጉለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ከመንግስትና ከግል ተቋማት የሚወሰድ ብድር ነው፡፡ እናቶች የሚሰሯቸው የተለያዩ የእጅ ስራዎች ተሸጠው አነስተኛ ገቢ ያስገኛሉ። ከምንም በላይ ከማኅበሩ ጎን በመሆን በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ታዋቂ ሰዎችና ግለሰቦች ሚና ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ ስለዚህ “የግል ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ የመንግስት መ/ቤቶች፣ … አቅማችሁ በቻለው ሁሉ ድጋፍ እንድታደርጉልን በተረጂዎቹ ስም እጠይቃለሁ” በማለት ተማፅናለች፤ የማኅበሩ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፡፡    

     የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን ሰሞኑን  በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ እየጣለ ያለው አዲሱ የግምት የገቢ ግብር ተመን ከፍተኛ መደናገጥን የፈጠረ ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ ከዚሁ የቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የተጣለባቸውን የቀን ገቢ ግምት ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮባቸው በድንገት ወድቀው ህይወታቸው ያለፈው አቶ አጎናፍር፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በሰፈር ውስጥ በከፈቷት የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፤ ሰሞኑን በተጀመረው የቀን ገቢ ግመታ፣ ሃምሳ ብር የማይሞላ የቀን ገቢ እንኳን በሌላት አነስተኛ ሱቃቸው ላይ የተጣለው የ5ሺ ብር የቀን ገቢ ግምት በፈጠረባቸው ድንጋጤ ራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ፤ በወቅቱ በሥፍራው የነበሩ ሰዎችም አቶ አጎናፍርን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ወደ አዲስ ህይወት ሆስፒታል የወሰዷቸው ቢሆንም ህይወታቸውን ለማትረፍ አልቻሉም፡፡ የሟች ባለቤት ደግሞ ሸንኮራ ዮሐንስ ለንግስ በዓል ሄደው ነበር ተብሏል፡፡  
የከተማዋ ገቢዎች ባለስልጣን በቁርጥ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ላይ ሰሞኑን የጀመረው የቀን ገቢ ግምት ፍትሃዊ ያልሆነና ጥናት ያልተደረገበት መሆኑን የሚገልጹት  ነጋዴዎች፤ የንግዱን ማህበረሰብ ለምሬት የሚዳርግና ተስፋ የሚያስቆርጥ አሰራር ነው ይላሉ፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሴራሚክ ሥራ ላይ የተሰማራ ረሻድ አወል የተባለ ግለሰብ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ በቀን ገቢ ግምቱ በቀን 10 ሺህ ብር ገቢ አለህ መባሉ በእጅጉ አስደንግጦታል። አምባሳደር አካባቢ የጀበና ቡና በመሸጥ ንግድ ላይ የተሰማራችው  ሌላዋ ወጣት ደግሞ የቀን ገቢሽ 3500 ብር ነው መባሏን ትናገራለች፡፡ “ከጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ በአንድ ቅፅበት ወደ መካከለኛ ግብር ከፋይ መዛወሬ አስደንጋጭም አስቂኝም ሆኖብኛል” ያለችው ወጣቷ፤” ለመሆኑ በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ካፒታል የሚባለው ነገር አይታይም? የእኔ ካፒታል እኮ 100 ብር እንኳን የማያወጣ ጀበና እና ስኒ ነው፡፡ ሰዎቹ ግን እንዴት ነው የሚያስቡት? ይህን ያህል የቀን ገቢ ቢኖረኝ ፀሐይ ላይ ምን እሰራለሁ?” ስትል ደጋግማ ትጠይቃለች፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሳሪስ አካባቢ በአነስተኛ የወንዶች ፀጉር ማስተካከል ሥራ ላይ የተሰማራው  ግብር ከፋይ፤የቀን ገቢ ግምቱ ሰሞኑን በደብዳቤ እንደደረሰው ጠቁሞ፤በቀን 5 ሺህ ብር ገቢ አለህ መባሉ ድንጋጤ እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡ ቀደም ሲል በዓመት ከ8ሺህ ብር በላይ ከፍሎ የማያውቅ መሆኑንና በወር 2ሺ ብር የማይደርስ ገቢ እያገኘ የቀን ገቢህ 5 ሺህ ብር ነው መባሉ ፍትሃዊ አለመሆኑን ገልጿል።
በዚሁ ክፍለ ከተማ በፎቶ ኮፒና ፅህፈት ሥራ ላይ የተሰማራ ሌላ ወጣት የቀን ገቢህ ነው ተብሎ 6 ሺ ብር ግምት የመጣበት መሆኑን ገልፆ፤ ይህን ያህል ገቢ እንኳንስ በቀን በወር አግኝቶ ማወቁን እንደሚጠራጠር ተናግሯል። ሁኔታው ሰርቶ ለመለወጥ ያለኝን ተስፋ በእጅጉ ያጨለመብኝ ነው ብሏል፡፡ የቀን ገቢ ግምቱን በሰማበት ወቅት የተሰማውን ሲገልፅም፤”ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፤ ለሁለት ቀናት ያህል ምግብ መብላት እንኳን አልቻልኩም” ብሏል፡፡ ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር አቤቱታ ለማቅረብ ጥረት ማድረጉን የሚገልፀው ወጣቱ፤ ‹‹ከ500 በላይ ቅሬታ አቅራቢዎች ተሰባስበን ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ፅ/ቤት ሄደን ጥያቄ ብናቀርብም፣ የሚያናግረን የመንግስት አካል እንኳን አጥተን ተመልሰናል” ይላል፡፡
በማግስቱም ከ2 ሺ በላይ አቤቱታ አቅራቢዎች ተሰባስበው ወደ ክፍለ ከተማው ፅ/ቤት በማምራት አቤቱታቸውን ለማሰማት ጥረት ቢያደርጉም ምላሽ በማጣታቸው ጩኸታቸውን እያሰሙ በጎዳና ላይ መጓዛቸውንና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መሞከራቸውን የተናገረው ወጣቱ፤ ”ድምፃችን  ይሰማ” ፣ ”መብታችን ይከበር” ለሚለው መፈክራችንና ጩኸታችን የተሰጠን ምላሽ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል፤ ህገወጥ ተቃውሞ እያደረጋችሁ ነው፤ መብታችሁን መጠየቅና ቅሬታ ማቅረብ ከፈለጋችሁ ኮሚቴ ምረጡና በኮሚቴ ጠይቁ” የሚል ነው ብሏል፡፡ “ኮሚቴ አንመርጥም፤ ለጥቃት ይዳረጉብናል” ብለን ለመከላከል ብንሞክርም፣” ይህ ካልሆነ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ተበተኑ” ተብለን ተበትነናል፤ አቤቱታችን ሰሚ አጥቶ እንዲሁ የሚመጣውን ለማየት ቁጭ ብለናል ብሏል - ወጣቱ፡፡
ወ/ሮ ሂክመት በቦሌ ክ/ከተማ በተለምዶ 17/17 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የልብስ መሸጫ ሱቅ አላቸው፡፡ ሰሞኑን በተጣለባቸው “የግብር እዳ” ጤናቸው መቃወሱን ይናገራሉ፡፡ “ቡቲክ ውስጥ የምውለው እቤት ከመዋል ይሻላል በሚል እንጂ እንኳን በቀን 3700 ብር ልሸጥ አንድም ቲ-ሸርትና አንድም ሱሪ ሳልሸጥ የምውልበት ቀን’ኮ ብዙ ነው” ይላሉ፤ተገምቶ የተነገራቸውን የቀን ገቢ አስመልክተው ሲያስረዱ፡፡  “በቀን 3700 ብር ከሸጥኩ በዓመት 1.4 ሚ. ብር እሸጣለሁ እንደ ማለት ነው፤ ይሄን ሁሉ የምሸጥና ገቢ የማገኝ ከሆነ ላለፉት አራት ዓመታት ባገኘሁት ገቢ እንደ ባለ ሀብቶቹ ፎቅ እገነባ ነበር” ብለዋል፤ ወ/ሮ ሂክመት፡፡
“የሱቅ ኪራይ መክፈል እያቃተኝ አንዳንዴ ባለቤቴን አስጨንቄ እከፍላለሁ” ያሉት ወይዘሮዋ፤ “እንዲህ ዓይነት እዳ ከመሸከምና በሽታ ላይ ከመውደቅ ለምን ከርችሜው ቤቴ ቁጭ ብዬ ልጆቼን አላሳድግም?” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር በመሆን ሲጨቃጨቁ መሰንበታቸውን ጠቁመው፤ በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ ለዛሬ ቀጥረውናል ብለዋል፡፡
የ32 ዓመቷ ፍቅርተ ገድሉ፤ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ ለ6 ዓመታት በኩዌት ስትሰራ ቆይታ ከተመለሰች አራት ዓመቷ ነው፡፡ የራሷን ስራ ለመስራት በማቀድ፣ ፀጉር ቤትና ሽሮ ቤት ከፍታ ስትሰራ እንደነበር ያወሳችው ፍቅርተ፤ ለኪሳራ በመዳረጓ የካፌ አስተናጋጅ ሆኗ መቀጠሯን ትናገራለች፡፡ ይህም የልቧን አላደርስ ስላላት፣ ቡና የምታፈላበትን በረንዳ በወር ሁለት ሺህ ብር ተከራይታ የጀበና ቡና እያፈላች መሸጥ መጀመሯን ትናገራለች፡፡ ምንም እንኳን የጀበና ቡና ሥራው ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በቀን 2500 ብር ገቢ ታገኛለች መባሏ አገሯ ላይ የመስራት ተስፋዋን እንደ ጉም እንዳተነነው ፍቅርተ በምሬት ትናገራለች። “እውነት የጀበና ቡና ሸጣ በቀን 2500 ብር ታገኛለች ብለው ሳይሆን ለመለወጥ ያለኝን ተስፋ ለማሟጠጥ ነው” የምትለው ወጣቷ፤ ”እዚህ ያለው እንደዚህ የሚማረር ከሆነ የተሰደደውስ ምን ተስፋ ኖሮት ይመለሳል?” በማለት ትጠይቃለች፡፡
 የጀበና ቡና ገበያዋን በተመለከተ ስታስረዳም፤”በቀን  መቶና 150 ብር ብሸጥም ስኳር፣ ከሰል፣ ቡና፣ የራሴ ጉልበት አለበት፤ ለዚያውም 150 ብር የሸጥኩበት ቀን በጣም በቁጥር ነው፤ በተለይ ክረምቱ ከገባ በኋላ በረንዳው ስለሚያፈስ ገበያ ቀዝቅዟል፤በዚህ የተነሳ ክረምቱ እስኪያልፍ ስራውን ለማቆም እያሰብኩ ነበር” ብላለች፡፡ “እንዴት የጀበና ቡና እየሸጥኩ በቀን 2500 ብር ትሸጫለሽ ትላላችሁ? ከየትስ አምጥቼ እከፍላለሁ?” ብዬ ብጠይቃቸው፣ ‹‹በቀን ከምትሸጭው ላይ ለምን እቁብ እየጣልሽ አጠራቅመሽ አትከፍይም” ሲሉ ተሳለቁብኝ ያለችው ፍቅርተ፤አሁን እንደገና  ልቤ ለስደት ተነሳስቷል ብላለች፡፡  
ወጣት ባልና ሚስት ናቸው፤ እሱ ታዋቂ የፀጉር ስታይሊስት ነው፡፡ ባለቤቱም በሹሩባና በፀጉር ስፌት የተካነች ናት፡፡  ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም በተለያየ የውበት ሳሎን ተቀጥረው ይሰሩ  እንደነበር ይናገራሉ። “የራሳችንን የውበት ሳሎን የመክፈት ሀሳብ ስለነበረን እቁብ እንጥል ነበር፤ከረጅም ጊዜ ትግል በኋላ እቁብ አሰባስበን አራዳ ክ/ከተማ በተለምዶ ገዳም ሰፈር በሚባለው አካባቢ አንዲት ጠባብ ቤት በወር 5 ሺህ ብር ተከራይተን፣ ግማሹን የውበት መሳሪያ ገዝተን፣ ግማሹን በኪራይ አሟልተን፣ የውበት ሳሎን ከፈትን” ይላሉ፤ጥንዶቹ፡፡  ‹‹እርግጥ ነው የራሳችንን የውበት ሳሎን ከከፈትን በኋላ ተቀጥረን እንሰራባቸው ከነበሩ የውበት ሳሎኖች ደንበኞቻችን ተከትለውን መጥተዋል፤ የማደግና የመለወጥ ተስፋ ነበረን›› የሚሉት ባልና ሚስቱ፤ሰሞኑን በቀን 2800 ብር ታስገባላችሁ ሲባሉ በድንጋጤ ክው ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ግን እኮ እዚህ እኛው አካባቢ በቀን 10 እና 25 ሺህ ብር ያስገባል የሚባለው ሬስቶራንት የተገመተለትን ብትሰሙ  በሳቅ ትሞታላችሁ፤በቀን 1800 ብር ነው” ያለው ወጣቱ የውበት ሳሎን ባለቤት፤”አሁን ከተማዋ ላይ ትንሽ አብዶ የማሳበድ ስራ እየተሰራ ይመስላል” ብሏል፤የተሰማውን ሲገልጽ፡፡
 በቀን ትሰራለህ የተባልኩት በዓመት ሲባዛ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ነው ያለው ወጣቱ፤ ግብሩ የዚህ 20 በመቶ ሲሆን ስንት ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ራሱ ያሳብዳል ይላል፡፡ “ለመሆኑ የሚገምቱት አካላት በምን መስፈርት እንደሚገምቱ፣ መነሻቸው ምን እንደሆነ፣ መንግስት ለነጋዴው ግልፅ አድርጓል ወይስ ስራው በአቦ ሰጡኝ ነው የሚሰራው?” ሲል ይጠይቃል፤ወጣቱ፡፡ ቀጣይ ዕቅዳቸውን በተመለከተ ጥንዶቹ ሲናገሩ፤”ለጉዳዩ መንግስት መፍትሄ ካልሰጠና እልባት ካልተገኘ ወደተቀጣሪነታችን እንመለሳለን” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ፤በግመታው ላይ የግንዛቤ ችግር መኖሩንና ህብረተሰቡን ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ተገቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ የታክስ ፕሮግራምና ልማት ሥራዎች ዘርፍ ም/ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የዕለት ገቢ ግምት መነሻ ግብር ከፋዩ ራሱ ያቀረበው መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ቅሬታ አለኝ የሚል አካል ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል በአግባቡ የማቅረብ መብት አለው ብለዋል፡፡ የንግድ ሥራው ባለበት አካባቢ ያለው የንግድ እንቅስቃሴና አማካይ የዕለት ገቢ ታሳቢ ተደርጎ ግምቱ መሰራቱንም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቅሬታዎች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን የጠቆሙት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች፤ ማንኛውም ግብር ከፋይ ቅሬታውን ከወረዳ ጀምሮ ላሉ ማዕከላት ማቅረብ እንደሚችልና ቅሬታውን ሲያቀርብ ግን በግል ብቻ መሆን እንዳለበት፣ በቡድን ተደራጅቶ  ቅሬታ ማቅረብ እንደማይቻልም አክለው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሰጥና የሚያስረዳ ኮሚቴ መቋቋሙንም  ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡





     መንግስት በአጠቃላይ ከ725 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ሰርቻቸዋለሁ ያላቸው 972 የ40/60 መኖሪያ ቤቶች  እጣ ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የሚወጣ ሲሆን ዕድለኞች በወር ውስጥ ቤታቸውን ይረከባሉ ተብሏል፡፡  
ዛሬ ለእጣ ከተዘጋጁት 972 ቤቶች የሚጠበቅባቸውን የቤት ዋጋ ሙሉ ለሙሉ የከፈሉ 11 ሺህ 88 ቤት ፈላጊዎች የሚወዳደሩ ሲሆን ከነዚህ እድለኞች ውስጥ 20 በመቶ ለመንግስት ሰራተኞች፣ 3 በመቶ (29 ቤቶች) ለዳያስፖራዎች ቅድሚያ እድል የሚሰጥባቸው ይሆናሉ፡፡
የቤቶቹን እጣ አወጣጥ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ቤቶች ልማት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ለእነዚህ ግንባታቸው ከተጀመረ ከ4 ዓመት በኋላ ለተጠናቀቁ 972 ቤቶች አጠቃላይ ወጪ፣ ቤት ፈላጊዎች ከቆጠቡት በተጨማሪ መንግስት ከ725 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድርጎባቸዋል ተብሏል፡፡
የ40/60 የቤት ፕሮግራም ከ4 ዓመት በፊት 44 ሲደረግ ባለ 1 መኝታ ቤት 55 ካሬ ሜትር፣ ባለ 2 መኝታ 75 ካ.ሜ እንዲሁም ባለ 3 መኝታ 100 ካ.ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ በተደረገ የዲዛይን ማሻሻያ ባለ 1 መኝታ ቤት እንዳይኖር ተደርጎ፣ ባለ 1 የነበረው ወደ ባለ 2 መኝታ ቤት 125 ካ.ሜትር ስፋት፣ ባለ 2 የነበረው ወደ ባለ 3 መኝታ ከፍ ተደርጎ፣ በ150 ካ.ሜትር ላይ እንዲሁም ባለ 3 የነበረው ወደ ባለ 4 መኝታ ቤት ከፍ ተደርጎ፣ 168 ካ.ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው መደረጉ ተገልጿል፡፡  
የቤቶቹ ዋጋም ቀደም ሲል በካሬ ሜትር በ3200 ብር ታስቦ የነበረው ወደ 5680 ብር ከፍ ማለቱን፣ መንግስት በእያንዳንዱ ካሬ ሜትር ላይ የ720 ብር ድጎማ አድርጎ፣ እድለኞች ቤቱን በካሬ ሜትር 4918 ብር ሂሳብ እንዲረከቡ ማመቻቸቱን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት፤ ዛሬ እጣ የሚወጣባቸው መኖሪያ ቤቶች ላይ እያንዳንዱ ባለ እድለኛ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ ላይ በካሬ ሜትር 1718 ብር ጭማሪ እንደሚከፍል ታውቋል፡፡
በቤቶቹ ዋጋ ላይ በጠቅላላው 170 ሚሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን እንዲሁም አስተዳደሩ ፓርኪንግ ለመሳሰሉ ወጪዎች 140 ሚሊዮን፣ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ 97 ሚሊዮን እና ለቫት 168 ሚሊዮን የከፈለውን ጨምሮ 725 ሚሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
ለመኖሪያ ቤትነት እጣ ከሚወጣባቸው ቤቶች በተጨማሪ 320 የንግድ ቤቶችም በእለቱ በመነሻ ዋጋ በካሬ ሜትር 172 ሺህ ብር ለጨረታ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ከ40/60 ቤቶች የተወሰኑት ለመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እንዲሰጥ ጥያቄ መቅረቡን የጠቆሙት የአስተዳደሩ ም/ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው፤ዕድለኞች ክፍያ ፈፅሞ ቤቶቹን ለመውሰድ የሚከብዳቸው ከሆነ መንግስት ራሱ ቤቱን ይገዛዋል፤ዋጋው አሁን በዝቶብኛል ያሉ በቀጣይ በሚወጡ እጣዎች የመካተት እድል ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡  
የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ዛሬ እጣ የሚወጣባቸው የክራውንና የሠንጋ ተራ ሳይት ቤቶች መሠረተ ልማት እንደተሟላላቸውና በጥራት መሰራታቸውን ሙሉ ለሙ አረጋግጦ ባንኩ መረከቡን አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም በ2005 ዓ.ም 164 ሺህ ያህል ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 140 ሺህ ቤት ፈላጊዎች ቁጠባቸውን ሳያቋርጡ አድላቸውን እየተጠባበቁ ነው ተብሏል፡፡ በቀጣይ ዓመትም 20 ሺህ ቤቶችን ለተመዝጋቢዎች ለማስተላለፍ እቅድ መያዙን የስራ ሃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡

  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለማስወገድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል የተከሰሱት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ የምስክሮችን ዝርዝር የማወቅ መብትን” በተመለከተ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት የህግ ትርጉም እንዲሰጥበት ፍ/ቤቱ ብይን ሰጠ፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ለፍ/ቤቱ ካቀረቧቸው የክስ መቃወሚያዎች መካከል ‹‹ክሱ የተሟላ አይደለም፤ ክሱ ፖለቲካዊ ነው፤ በሽብር ክስ ሳልከሰስ የሽብር ክስ ማስረጃ ሊጠቀስብኝ አይገባም›› የሚሉና ሌሎች የክስ መቃወሚያ በጠበቆቻቸው በኩል ያቀረቡ ቢሆንም ከአንዱ በስተቀር ቀሪዎቹን መቃወሚያዎች ፍ/ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት እንዳልተቀበላቸው አስታውቋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና የተከሰሱት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማስፈፀሚያ ደንብና በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ ነው፡፡ የማስረጃ ዝርዝሩ የቀረበበባቸው ደግሞ በፀረ ሽብር አዋጁ መሰረት መሆኑን የዶ/ር መረራ የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሣ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በሽብር የተከሰሰ ሰው፤ የሰው ምስክሮች ላይገለጡለት እንደሚችል በህግ ተደንግጓል፡፡
ተከሳሹ በሽብር ወንጀል አለመከሰሳቸውን በመጥቀስ የሰው ማስረጃ ዝርዝሮች እንዲገለጥላቸው ጥያቄ በማቅረባቸው ፍ/ቤቱ የህግ ትርጉም ያስፈልገዋል ሲል ፌዴሬሽን ም/ቤት የህግ ትርጉም እንዲሰጥበት ብይን ሊሰጥ መቻሉን አቶ ወንድሙ አብራርተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤትን የህግ ትርጉም ለመጠባበቅ ጉዳዩ ለሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡
ዶ/ር መረራ ፍ/ቤት የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ባደረጉት ንግግር፤ “የኔ ክስ የፖለቲካዊ ክስ ነው፣ ለኦሮሞ ህዝብ መብት በመታገሌ ነው የተከሰስኩት፣ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ነፃነት በመቆሜ ነው፤ ለሃቀኛ ፌደራል ስርአት መገንባትና ነፃ ፍ/ቤት፣ ነፃ የዳኝነትና የፍትህ ስርአት እንዲፈጠር ስለታገልኩ ነው የተከሰስኩት፡፡
ይሄን ትግል እኔ ብቻ አይደለሁም የታገልኩት፤ ቀደም ሲል አቤ ጉበኛ የሚባል ደራሲ “አልወለድም” የሚል መፅሃፍ ፅፎ ለንጉሡ ማስጠንቀቂያ ነግሮ፣ ንጉሡ ሳይሰማቸው መጨረሻው እንደዛ ሆነ፤ በደርግ ስርአት ደግሞ በአሉ ግርማ “ኦሮማይ” የሚል መፅሐፍ ፅፎ ለደርግ መንግስት ምክር ቢሰጥ ሳይሰማ ቀርቶ የሆነውን ታሪክም ፍ/ቤቱም ያውቃል፤ እኔ ደግሞ “የተራበ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል” ብዬ መፅሓፍ ፅፌያለሁ፤ እባካችሁ ዳኞች ለታሪክ ስትሉ እነዚህን ሶስት መፅሃፎች አንብቡ …. የሰራሁት ወንጀል የለም፡፡ ለሁላችንም የምትሆን ህግና የህግ የበላይነት የሰፈነባት ሰው ሁሉ በእኩል የሚኖርባትን ሀገር እንመስርት ብዬ አንድ ለሆዱ ከሚያስብ ምሁር በላይ ዋጋ በመክፈሌ ነው የተከሰስኩት” ማለታቸው ታውቋል፡፡






 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአህጉራዊ ደረጃ ለሚደረጉ ውድድሮች በሚኖረው  የማጣርያ ግጥሚያዎች ተሳትፎ  በቂ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸው ከሁለት ሳምንት በፊት በአክራ ከተማ 5ለ0 ከባድ ሽንፈት የገጠማቸው ዋልያዎቹ ይህ ደካማ አጀማመራቸው ብዙዎችን አላስደሰተም፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ የሚመለሰው ከ8 ወራት በኋላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል በ2018 እ.ኤ.አ ኬንያ ለምታዘጋጀው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን 2ኛ ዙር ማጣርያ ሰሞኑን ዝግጅታቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ በቻን 2ኛ ዙር ማጣርያ የመጀመሪያው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሜዳ ውጭ የሚገናኘው ከጅቡቲ አቻው ጋር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና  አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቻን  ከጅቡቲ ጋር ከሜዳ ውጭ ለሚገናኙበት  የ2ኛ ዙር ማጣርያ ጨዋታ  ዝግጅት   አዳዲስ ተጫዋቾችን ጠርተዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ በአገር ውስጥ የሊግ ተጨዋቾች የተደራጀ ስብስባቸውን ይዘው  ለዝግጅት   ወደ ድሬዳዋ እንደሚያመሩ ይጠበቃል፡፡በ2018 እ.ኤ.አ ኬንያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ኮታ ለ3 አገራት ነው። ኬንያ በአዘጋጅነቷ በቀጥታ ማለፋን ያረጋገጠች ሲሆን ሌሎች 2 ብሔራዊ ቡድኖች በ2ኛ እና 3ኛ ዙር በሚካሄድ ቅድመ ማጣሪያዎች የሚወሰኑ ይሆናል፡፡ ከ2 ሳምንታት በኋላ በሚቀጥለው የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ደቡብ ሱዳን ከኡጋንዳ፤ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ ከሩዋንዳ እንዲሁም ብሩንዲ ከሱዳን ይገናኛሉ፡፡
ለቻን 2018 ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተጫዋቾች ዝርዝር
ግብ ጠባቂዎች
ጀማል ጣሰው (ጅማ አባ ቡና)፣ ሳምሶን አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ) ፣ ለአለም ብርሃኑ (ሲዳማ ቡና)
ተከላካዮች
አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ሳላዲን በርጌቾ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አብዱልከሪም መሃመድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)፣ ሙጂብ ቃሲም (አዳማ ከተማ)፣ ስዩም ተስፋዬ (ደደቢት) ፣ ደስታ ዮሀንስ (ሀዋሳ ከተማ)፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ)
አማካዮች
ሽመክት ጉግሳ (ደደቢት)፣ ሙሉአለም መስፍን (ሲዳማ ቡና)፣ ጋዲሳ መብራቴ (ሃዋሳ ከተማ) ፣ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ናትናኤል ዘለቀ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
አጥቂዎች
ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አብዱልራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከተማ)፣ ሳላዲን ሰዒድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
በ2019 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ  በተጀመረው የምድብ ማጣርያ በምድብ 6 ጋና በአክራ ኢትዮጵያን 5ለ0 ስታሸንፍ ሴራሊዮን በሜዳዋ ኬንያን 2ለ1 ረታለች፡፡
ሴራሊዮን በዋና ከተማዋ ፍሪታውን በሚገኘው ብሄራዊ ስታድዬም ኬንያን 2ለ1 ስታሸንፍ ዋሌይ በ22ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም አምበሉ ባንጉራ በ69ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ጎሎች ነው፡፡ የኬንያን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ኦሉንጋ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ ሴራሊዮን ኬንያን በሜዳዋ በማሸነፍ ያሳየችው ጅማሮ ለብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሮላቸዋል፡፡ ሎን ስታርስ የሚባለው ብሄራዊ ቡድኑን በአምበልነት የሚመራው ባንጉራ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት ለማንም የማንመለስ ጠንካራ ቡድን ነን ሲል ተናግሯል፡፡ ሴራሊዮን በአፍሪካ ዋንጫ ለ2 ጊዜያት የተሳተፈችው በ1994 እና 1996 እኤአ ላይ ነበር፡፡ በሰኔ ወር የፊፋ ወርሃዊ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ309 ነጥብ 113ኛ ላይ ትገኛለች፡፡  የተጨዋቾች ስብስቧ በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 3.63 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በተያያዘ የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  በሴራሊዮን ለደረሰው ሽንፈት ምቹ ባልሆነ ስታድዬም ጨዋታ መደረጉ እንዲሁም የዳኝነት በደል መብዛቱን ምክንያት አድርገዋል፡፡ ይህን አስመልክቶም ለአፍሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የክስ ማመልከቻ ማስገባታቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያውን የሃራምቤ ኮከቦች በሽንፈት መጀመራቸው በፌደሬሽኑ አካባቢ የነበረው የአስተዳደር ቀውስ ቆስቁሶታል፡፡ በተለይ ከ2018 የቻን ውድድር አዘጋጅነት በተያያዘ ነው፡፡ የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከመንግስት ሙሉ ድጋፍ ባለማግኘቱ መስተንግዶው ማቀላጠፍ አልቻልኩም በሚል እያማረረ ነው፡፡ የካፍ ኮሚቴ ሰሞኑን በናይሮቢ በነበረው ጉብኝት በ2018 እኤአ የሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ሊጀመር 6 ወራት ቢቀሩትም ኬንያ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ አለመሆኗን በመጥቀስ፤ ሌላ አስተናጋጅ በሚመርጥበት ሁለተኛ ዕቅድ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በ2020 እኤአ 6ኛውን ቻን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ኢትዮጵያ፤ እንዲሁም ሞሮኮና ኮትዲቯር በምትክነት መስተንግዶውን ለመረከብ ፍላጎት አላቸው። ኬንያ በአፍሪካ ዋንጫ ለአምስት ጊዜያት የተሳተፈችው በ1972፤ በ1988፤ በ1990፤ በ1992 እና በ2004 እኤአ ላይ ነበር፡፡ በሰኔ ወር የፊፋ ወርሃዊ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ463 ነጥብ 74ኛ ላይ የምትገኝ ሲሆን ስብስቧ በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 17.06 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
ከምድብ 6 የምድብ ማጣርያውን ለማለፍ ቅድሚያ ግምት የተሰጣት ጋና በአክራ ከተማ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ ኢትዮጵያን 5ለ0 ማሸነፏ ብዙዎችን አላስደነቀም። ለጥቋቁሮቹ ክዋክብቶች ጎሎቹን በ10ኛው ደቂቃ ላይ አሳሞሃ ጊያን፤ በ15ኛው ደቂቃ ቦዬ፤ በ35ኛው ደቂቃ ኦፍሪ እንዲሁም ድዋሜና በ48ኛው እና በ70ኛው ደቂቃዎች ላይ አስመዘግበዋል፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኩዋሲህ አፒያህ በራስ መተማመን እንደሚያሳድግ የአገሪቱ ሚዲያዎች አውስተዋል፡፡ ጋና ከኢትዮጵያ በኋላ ለዓለም ዋንጫ የምታደርገውን ዝግጅት ቀጥላለች ሰሞኑን ከሜኬሲኮ ጋር ተገናኝታ 1ለ0 የተሸነፈች ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የምትጫወት ይሆናል፡፡  የአፍሪካ ዋንጫ ለ4 ጊዜያት ያሸነፈችው ጋና በሰኔ ወር የፊፋ ወርሃዊ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ678 ነጥብ 49ኛ ላይ የምትገኝ ሲሆን የተጨዋቾች ስብስቧ በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 55.17  ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋ በጋና ባጋጠመው የመጀመርያ ጨዋታ ከባድ ሽንፈት የሚያበረታታ አልሆነም፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን 10 ጊዜ በመሳተፍ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ በሰኔ ወር የፊፋ ወርሃዊ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ265 ነጥብ 125ኛ ላይ የምትገኘ ሲሆን፤ የተጨዋቾች ስብስቧ በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 723ሺ ዩሮ ነው፡፡
ከመጀመርያው ዙር ጨዋታ በኋላ ምድብ 6ን ጋና በ3 ነጥብ እና በ5 የግብ ክፍያ ስትመራው ሴራሊዮን በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ 2ኛ ሆናለች፡፡ ኬንያ በ1 የግብ እዳ ሶስተኛ ደረጃን ስትይዝ ኢትዮጵያ በ5 የግብ እዳ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች፡፡ የምድብ ማጣርያው 2ኛ ዙር ጨዋታዎች ከ8 ወራት በኋላ ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን እንዲሁም ኬንያ ከጋና ይገናኛሉ፡፡ ከ14 ወራት በኋላ  ደግሞ የ3ኛና የ4ኛ ዙር ጨዋታዎች በሁለት ሳምንት የደርሶ መልስ ትንቅንቅ  ሲቀጥሉ በመጀመርያ ጋና ከሴራሊዮን እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኬንያ እንዲሁም ከ1 ሳምንት በኋላ በመልስ ጨዋታ ሴራሊዮን ከጋና እንዲሁም ኬንያ ከሴራሊዮን ይጫወታሉ፡፡ ከ15 ወራት በኋላ በ5ኛ ዙር ጨዋታ ኢትዮጵያ ከጋና እንዲሁም ኬንያ ከሴራሊዮን እንዲሁም በ6ኛ ዙር ጨዋታ ሴራሊዮን ከኢትዮጵያ ጋና ከኬንያ ይገናኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሁለት ሳምንት በፊት አክራ ከተማ ላይ ከገጠመው የ5ለ0 ሽንፈት በኋላ ብዙ የትችት ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ ዋልያዎች በቂ ዝግጅት እያደረጉ አይደለም፡፡ በፌደሬሽኑ በኩል ተገቢውን ትኩረት ያጡም ይመስላል፡፡  ቀደምት ዋልያዎችም በየክለቦቻቸው ስኬታማ ቢሆኑም በብሄራዊ ቡድኑ ያላቸው ሚና መዳከሙ ብዙዎችን ያስገረመ ነው፡፡   ከደቡብ አፍሪካ መልስ ፕሪሚዬር ሊጉን በኮከብ ግብ አግቢነት ሪከርድ አስመዝግቦ ያሸነፈው ጌታነህ ከበደ፤ በግብፅ ሊግ ሁለት ክለቦች በግብ አዳኝነት እና በኮከብ ተጨዋችነት የተሳካላቸው ኡመድ እና ሽመልስ፤ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላዲን እንዲሁም ሰሞኑን የሩስያውን ክለብ ለመቀላቀል የበቃው ጋቶች ፓኖም የዋልያዎቹ አባላት ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ለወደፊቱ ብዙ ተግባራ መሰራት ይኖርባቸዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ስኬታማ እንዲሆን የፋይናንስ አቅሙ ማሟላት፤ ለተጨዋቾች የማበረታቻ ክፍያዎች ማዘጋጀት፤  የወዳጅነት ጨዋታ እና በቂ የዝግጅት መስጠት ተገቢ ነው፡፡

      የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ተጨዋችና አምበል ሆኖ ያገለገለው ጋቶች ፓኖም የራሽያውን ታዋቂ ክለብ አንዚ ማካችካላ ተቀላቀለ፡፡ የ23 ዓመቱ ጋቶች ይህን በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዝውውር ያሳካው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረው የቅጥር ውል ካበቃ በኋላ ነው፡፡  ባለፈው ሰሞን ለሙከራ ወደ ራሽያ ተጉዞ የነበረው ተጨዋቹ በሙከራ ጨዋታ ላይ ጎል ካገባ በኋላ የክለቡን ሃላፊዎች እና አሰልጣኞች ስለማረካቸው፤ የዝውውሩን ሂደት ስኬታማ አድርጎታል በማለት የተጨዋቹ ወኪል  ሆኖ የሰራው ትውልደ ጀርመናዊው ዴቪድ በሻህ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ጋቶች በራሽያ ፕሪሚያራ ሊግ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች ዋንኛ ተጠቃሽ  የሆነውን አንዚ ማካችካላ በመቀላቀል መጫወት የሚጀምረው ከ2017 -18 እኤአ የውድድር ዘመን ጀምሮ ሲሆን የውል ስምምነቱ ለ3 ዓመታት የሚቆይ   ነው፡፡  
በተከላካይ አማካይ እና በመሃል አማካይ መስመሮች የሚጫወተው ጋቶች  ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ቀጥሎ በሚመደበው ራሽያ ፕሪሚዬራ ሊግ በመጫወት የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ የስኬት ደረጃ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።    አንዚ ማካችካላ  ለ2017-18 ዘመን ለሚያደርገው ዝግጅት ጋቶች ፓኖምን ጨምሮ    ሌሎች 10 ተጨዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን ከታዋቂዎቹ ሲኤስኬ እና ዳይናሞ ሞስኮ ያዛወራቸው ይገኙበታል፡፡ በተጨዋቾ ስብስቡ ከ6 የተለያዩ  አገራት ፕሮፌሽናሎች ጨምሮ 29 ተጨዋቾችን ያስመዘገበው የሩሲያው ክለብ  የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 18.4 ሚሊዮን ዮሮ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከጋቶች ፓኖም የራሽያ ዝውውር በኋላ የተሰሙ አንዳንድ መረጃዎች በአንዚ ማካች ካላ በሳምንት 5ሺ ዩሮ እንደሚከፈለው የገለፁ ሲሆን  በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ ከግማሽ ሚሊዮን ዩሮ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውዱ ተጨዋች ሊያደርገው ይችላል፡፡
ከጋቶች ፓኖም ሻገር የሌሎቹ ዋልያዎች የዝውውር ገበያ ግምትና ወቅታዊ ውጤታማነት
ሽመልስ በቀለ በወቅቱ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 400ሺ ዩሮ ነው፡፡ የግብፅ ክለብ ፔትሮጄት የሚገኘውና በቀኝ እና ግራ አማካይ መስመሮች የሚጫወተው ሽመልስ  ባለፈው 1 ዓመት በግብፅ ሊግ እና ካፕ ላይ በ22 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን አስመዝገቧል፡፡
የ28 ዓመቱ ሳላዲን ሰኢድ በወቅቱ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 300ሺ ዩሮ ነው፡፡ ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከቅድማጣርያው አንስቶ በ7 ጨዋታዎች በመሰለፍ 4 ጎሎች አስመዝግቧል፡፡
ኡመድ ኡክሪ በወቅቱ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 200ሺ ዩሮ ነው፡፡ በ2014 15 የውድድር ዘመን በአልኢትሃድ፤ በ2015 በኤንፒፒአይ እየተጫወተ ከፍተኛ ልምድ ያካበተው ኡመድ ከ2016 በጀምሮ በግብፁ ኤል ኤንታግ ኤልሃረቢ እየተጫወተ ሲሆን በግብፅ ሊግ እና ካፕ ላይ በ29 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን አስመዝገቧል፡፡
ጌታነህ ከበደ አሁን በሚጫወትበት የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በወቅቱ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 150ሺ ዩሮ ነው፡፡ ከዓመት በደቡብ አፍሪካ ሁለት ክለቦች ቢድቬስት ዊትስ እና በፕሪቶርያ ሲጫወት በ56 ጨዋታዎች በመሰለፍ 13 ጎሎች ያስመዘገበው ጌታነህ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት ጨርሷል፡፡

 - አሁን የምናመርተው እስራኤል 70 ኣመት ከተጠበበችበት ምርት ይበልጣል
                 - እኛ ፋብሪካ ውስጥ ፈተና ወድቆ መምጣት ነውር ነው
                 - ፋብሪካው ትንሽ ገቢ ሲያገኝ ለሰራተኞችም ጭማሪ ይደረጋል

          በ1978 ዓ.ም ነው አራት ህፃናት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ እስራኤል የተሻገሩት፡፡ የሄዱበት ምክንያት ደግሞ ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው ነበር፡፡ ደሴ ከተማ ውስጥ ተወልደው ያደጉት አቶ አሰፋ አስናቀ መንገሻ፤ በወጣትነት እድሜያቸው በአየር ኃይል፣ በግብርና ሚኒስቴርና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሰሩ ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ የህብረት ስራ ማህበራት አደራጆች አንደኛው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በጠቅላላው ወደ 10 ዓመታት ያህል ከሰሩ በኋላ በ1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ አሰፋ፤ በዓመቱ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው፣ አራት ህፃናት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ እስራኤል መጓዛቸውን ይገልፃሉ፡፡ በእስራኤልም “ሰርቲፋይድ አካውንቲንግ” ካጠኑ በኋላ በአካውንታንትነት ሙያ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከቅጥር ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት በመክፈት ለተለያዩ ኩባንያዎች የአካውንቲንግ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር የሚናገሩት አቶ አሰፋ፤ ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን “አፍሮ አምክሰላር ኢነርጂ ቴክ” የተሰኘ በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ የውሃ ጋኖችንና የፀሐይ ሀይል የሚሰበስቡ ፓኔሎችን የሚያመርት ፋብሪካ አቋቁመው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ አሰፋ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

    ከኢትዮጵያ ከወጡ ከ22 ዓመታት በኋላ እንዴት ነው ወደ አገርዎ የተመለሱት?
ከኢትዮጵያ ከወጣሁ በኋላ በአንድ ወቅት አንድ ሁለት ጊዜ መጥቼ ነበር፡፡ ብቅ ብዬ ነው የተመለስኩት። በመጣሁበት ወቅት ገና ለውጥ መጀመሩ ነበር፤ የመጣሁትም አባቴ አርፎ ለለቅሶ ነበር፡፡ ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ ገና ልማት አልተጀመረም ነበር፡፡ ወደ እስራኤል ተመልሼ ከሄድኩ በኋላ ለ22 ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ አልመጣሁም፡፡ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንድመጣ ያበረታታችኝ ባለቤቴ ናት፡፡
እንዴት?
ባለቤቴ በእስራኤል አገር የትምህርት ዲቪዥን ኃላፊ ናት፡፡ በአንድ ወቅት ከእስራኤል አገር ለስራ ትልልቅ እንግዶችን ይዛ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ የተወለድንበትን አካባቢ ጎብኝታ፣ የተለያዩ አካባቢዎችን አይታ፣ ያለውን ለውጥ እንድመለከት ነገረችኝ፡፡ ከዚያም አብረን መጥተን፣ ሁሉንም ተዘዋውረን አየን፡፡ እንደገና ተመልሼ ብቻዬን መጣሁና ሁሉን ነገር በሚገባ ተመለከትኩኝ፡፡ እኔ ኢትዮጵያ በነበርኩበት ጊዜ ከአዲስ አበባ እስከ ገጠር ስለሰራሁ፣ ያን ጊዜ የነበረውን የመሰረተ ልማት ችግሮች አውቅ ነበር፡፡ አሁን እነዚያ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በጥሩ ሁኔታ ተለውጠው አየሁኝ፡፡ ይህን ስመለከት እኔስ እዚህ መጥቼ ለአገሬ ምን ላድርግ፣ የሚለውን ጥያቄ ራሴን ጠየኩኝ፡፡ ይህን ያሰብኩት እ.ኤ.አ በ2011 ነበር፡፡ ከዚያም እስራኤል የምሰራውን ስራ ትቼ ወደ ኢንዱስትሪ ለመግባት ወሰንኩ፡፡ የተለያዩ ቢዝነሶችንም ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ እውነት ለመናገር እኔ ለአገሬ ቀናተኛ ሰው ነኝ፡፡ እዚያ የለሙ ነገሮችን ሳይ፣ የሆነ ነገር ተለውጦ ስመለከት፣ ምን ነበር አገሬ ላይ ቢሆን እላለሁ፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው ሳጠና የሶላር ኢነርጂው ጉዳይ የመጣልኝ፡፡
በዘርፉ ለመሰማራት የመረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
የኖርኩባት አገር እስራኤል ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በፀሐይ ኃይል በኩል ከፍተኛ ተጠቃሚ ናት፡፡ በተለይ በፀሐይ ኀይል የምታለማው የመስኖ ስራ ከፍተኛ ነው፡፡ እኔም ሶስት አራት ዘርፎችን ግምት ውስጥ ካስገባሁ በኋላ በተለይ ዓለም በአሁኑ ሰዓት በኃይል እጥረት በተወጠረበትና የኢትዮጵያ መንግስት በታዳሽ ሀይልና በአረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ባደረገበት በዚህ ዘመን፣ የፀሐይ ሀይልን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ከማዳንና የኤሌክትሪክ ሀይል ብክነትን ከመታደግ እንዲሁም የስራ እድል ከመፍጠርም አኳያ አቻ የማይገኝለት ስራ ነው በሚል ነው “አፍሮ አምክሶላር ኢነርጂቴክ” የተሰኘውን ፋብሪካ በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የከፈትኩት፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ፀሐይ ሀይል ካለው ግንዛቤ፣ ዘርፉ ለአገራችን አዲስ ከመሆኑ አኳያ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሙኝ ባውቅም ኃላፊነቱን ወስጄ ነው ያቋቋምኩት፡፡
ፋብሪካውን በማቋቋም ሂደት የገጠምዎት ተግዳሮቶች አሉ?
ፈተናው የጀመረው ሀሳቡን ለዘመድ ወዳጅ ማማከር በጀመርኩበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ እኔም ባለቤቴም በውጭ ስንኖር፣ በስራችን ባህሪ ምክንያት ከህዝቡ ጋር ብዙ ትውውቅና ቅርርብ ነበረን፡፡ ብዙ ፈረንጅ ጓደኞቻችን ሀሳቡን ስንነግራቸው፣ እንደ እብደት ነበር ያዩት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያውም ሶስተኛ ዓለም ላይ እንዴት ይህን ታስባለህ በማለት፣ እኔ እንዳልበረታታ ብዙ ግፊቶች ነበሩ፡፡ አንዱ ፈተና ይሄ ነበር፡፡ ያንን ፈተና ማለፍ ቻልኩኝ፡፡ ኢትዮጵያ በህዝቧ ጥረትና ብዛት፣ ባላት የተፈጥሮ ሀብትና ባለሙያዎች፣ ወደፊት ተስፋ ያላት አገር መሆኗን ስለማውቅ፣ ዛሬ ባይሳካ ነገ ይሳካል በሚል፣ የጓደኞቼን ምክርና ተግሳፅ ወደ ጎን ትቼ፣ በሀሳቤ ገፋሁ፡፡ በኋላ ደግሞ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ያሉ ዲፕሎማቶች ሀሳቤን ሲሰሙ፣ ከእኛ ጋር በአጋርነት ለምን አትሰራም የሚል አማላይ ሀሳብ አቀረቡና ትንሽ ግራ መጋባት ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ ይህንንም ከራሴ ጋር መክሬ ተውኩት፡፡ በምንም ሚዛን የአገሬን ያህል አይሆኑም፡፡
ይህን ካለፉ በኋላ የፋብሪካው ግንባታ ምን ይመስል ነበር?
እኔ በሀሳቤ ከፀናሁ በኋላ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ህላዌ ዮሴፍ በጉዳዩ ገብተውበት፣ የአቶ ታደሰ ኃይሌ ድጋፍ ተጨምሮበት፣ በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን በመረጥነው ቦታ ላይ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ወሰድኩኝ፡፡ ቦታውን ለማግኘት ብዙ አልተቸገርኩም። ከዚያ በኋላ በራሴ ገንዘብ ግንባታ ጀመርኩና ብድር ጥየቃ ወደ ባንክ ሄድኩኝ፣ ይሄ ቴክኖሎጂ በብዙ ዘርፍ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነውና ብድር ስጡኝ ስል፣ ገንዘብ የለንም አሉኝ፡፡ ቴክኖሎጂው ጠቃሚ ስለመሆኑ ሚኒስትሮቹና ባለሙያዎች እየመሰከሩ፣ እኔም ትልቅ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳለኝ ለማሳየት ከሚደግፉኝ ሰዎች ጋር ሆኜ፣ በራሴ ገንዘብ እየገነባሁ፣ ፈፅሞ ብድሩን ለማግኘት አልቻልኩም።
ከባንክ ምን ያህል ነበር የጠየቁት ብድር?
በወቅቱ ፋብሪካውን ለማቋቋም ከ16 ሚ. ብር በላይ ያስፈልግ ነበር፡፡ እኔም የጠየኩት 16 ሚ. ብር ነው። ነገር ግን ይህን ብድር ለማግኘት ከ2 ዓመት በላይ ተጉላልቻለሁ፡፡ ሆኖም ግንባታው ቀጥሎ ነበር፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ ብድር ፈቃጆች የፕሮጀክቱ ጥቅም ላይ ግንዛቤ ስላልነበራቸው አልፈርድባቸውም፡፡ ሆኖም ጉዳዩን ከልብ አዳምጠው መረዳት ይችሉ ነበር፤ ግን ትኩረት አልሰጡትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትልልቆቹ ኃላፊዎች ጉዳዩን ጠንቅቀው ያውቁት ነበር፡፡ በኋላ ከስር ያሉት ሰዎች፤ “ይሄ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ፕሮጀክት አይደለም” የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡
ከዚያስ?
ያንን ውሳኔ ሲወስኑ የኢነርጂ ሚኒስትር ወደነበሩት ወደ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ሄድኩና የተከለከልኩበትን ደብዳቤ ሰጠኋቸው፡፡ በወቅቱ ተበሳጩ፡፡ ስልክ ደውለው ይሄን ቴክኖሎጂ እንዴት ትገፋላችሁ ብለው ተናገሩ። ከዚያ እንደገና ጉዳዩ ይታይ ተባለና፣ በባለስልጣኖቹ ድጋፍ ከሞላ ጎደል ብደሩ ተፈቀደ፡፡
ከሞላ ጎደል ሲሉ ከጠየቁት ብድር ምን ያህሉን አገኙ?
አልወሰኑም እንዳይባሉ ከጠየኩት 16 ሚ. ብር 11 ሚ. ብር ፈቀዱ፡፡ ትንሽ ቆዩና ፕሮጀክቱን በተግባር ሲመለከቱ እንደገና 1.3 ሚ. ፈቀዱና ብድሩ በጠቅላላ 12.3 ሚሊዮን ብር ሆነ፤ ያንን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ፈጀ፤ ያንን አልፈን ምርት ተጀመረ፡፡
መቼ ነው ማምረት የጀመራችሁት?
ባለፈው ዓመት ነሀሴ ላይ ማምረት ጀመርን። አሁን በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆቴሎች፣ በሻወር ቤቶች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ምርታችን በተፈለገበት ቦታ እየሄድን እንገጥማለን፡፡ በብዙ ኮንቴይነር ከሌላ ቦታ የሚገባውንና ለዚያ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ችለናል፡፡ ያለማጋነን ምርታችን እስራኤል አገር ካሉ ምርቶች በጥራት ይበልጣል፤ ይሄንን እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡
በፀሐይ ሃይል ውሃ ለማሞቅ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ምን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይልስ ይቆጥባል?
ይሄ በጣም ጥሩና አስፈላጊ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከውጭ አገር የሚገቡት በፀሐይ ኃይል ውሃ የሚያሞቁ በርሜሎች አብዛኞቹ 200 ሊትር ናቸው፡፡ እኛ ግን አማራጮችን አስቀምጠናል፡፡ ለምሳሌ ባልና ሚስት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩ ከሆነ፣ 200 ሊትር ውሃ ምን ያደርግላቸዋል? 80 ሊትር በቂ ነው፡፡ ወጥ ቤትም ውስጥ ሙቅ ውሃ መጠቀም እፈልጋለሁ ካልሽ፣ 150 ሊትር ከበቂ በላይ ነው፤ የግድ 200 ሊትር ስላለ ብቻ ሰውን ያንን ግጠም ብሎ ማስገደድ አግባብ አይደለም። አንዱ ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው በፀሐይ ኃይል ለመሞቅ የሚወስደው ጊዜ እንደየወቅቱና አካባቢው ቢለያይም፣ በአማካይ ግን የሁለት ሰዓት የፀሐይ ሙቀት 200 ሊትር ውሃ በደንብ ያሞቃል፡፡ በ80 እና በ150 ሊትር ግን በበርሜል ውስጥ የፈላ ውሃ ታገኛለሽ፡፡ እኛ አገር በጣም ክረምት በሚባለው በሐምሌና ነሐሴ ወር እንኳን ዝናብ ከመዝነቡ ከአንድና ሁለት ሰዓት በፊት ፀሐይ ይወጣል፤ ያኔ ሙቅ ውሃ አለ፤ ፀሐይ ጭራሹኑ በማይኖር ጊዜ ማሞቂያችን በኤሌክትሪክ ሲስተምም ስለሚሰራ፣ ያኔ ግድ ከሆነ ኤሌክትሪክ መጠቀም ይቻላል፡፡ የኛ የፀሐይ ኃይል ሲስተም ከፍተኛ ኢንሱሌሽን ያለው ነው፤ አንዴ ከሞቀ ለረጅም ጊዜ ሙቀት አፍኖ የመያዝ አቅም ስላለው ቶሎ አለመቀዝቀዙ ከሌላው ይለየናል፡፡
ምን ያህል የኤሌክትሪክ ሀይል ይቆጥባል የሚለውን አልመለሱልኝም …
በጣም ጥሩ! በእያንዳንዱ 200 ሊትር የፀሐይ ኃይል ውሃ የሚያሞቅ በርሜል 7 ኪሎ ዋት ኢነርጂ እንቆጥባለን። በ150 ሊትርም ቢሆን 7 ኪሎ ዋት ትቆጥቢያለሽ፡፡ ይሄን ሀይል መንግስት ለሌላ በርካታ ስራ ያውለዋል፡፡ እኛ ይህንን የምንለው በኪሎ ካሎሪ ነው፤ ያንን ወደ ኢነርጂ ስንለውጠው የምንቆጥበውን ኃይል እናውቀዋለን፡፡ ይሄ የእስራኤል ሳይንቲስቶች ቀመርና የ70 ዓመት ልምድ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ከፍ አድርገን እንመልከተው፡፡ ለምሳሌ እኛ 1 ሺህ ማሞቂያዎችን ብንገጥም፣ ከ7 እስከ 10 ሜጋ ዋት ኃይል በቀን ለመንግስት ይቆጠብለታል፡፡ ይሄ ማለት የቆቃ ሀይል ማለት ነው፡፡ ቆቃ እስከ 90 ሜጋ ዋት ነው ያመርታል የሚባለው፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ክቡር አለማየሁ ተገኑ ፋብሪካውን መጥተው ጎብኝተው፤ “መቼ ነው ማስፋፊያ የምትጀምረው?” ብለው ጠይቀውኛል። ከስራቸውም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ እርሳቸው ባይደግፉኝ ህልሜ እውን አይሆንም ነበር፡፡ “ይህንን ስራ አስፋፍተህ የአዲስ አበባን የኤሌክትሪክ ውሃ ማሞቂያ ጠራርገህ አውጣልኝ” ነው ያሉት፡፡ ይሄ የሚያመለክተው መንግስት ምን ያህል የኃይል እጥረት እንዳለበትና ተጨማሪ አጋዥ ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልገው ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀን ወደ 400 ሜጋ ዋት ሀይል ያስፈልግ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 700 ሜጋ ዋት አድጓል። እኛ እድሉንና ድጋፉን ካገኘን ይህንን ሀይል መቆጠብ እንችላለን፡፡ ይህን የምናደርገው የህዝቡን ግንዛቤ አሳድገን፣ ፋብሪካችን ተስፋፍቶና ገበያውን ሰብረን ስንገባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አሁንም ከመንግስት ብዙ ድጋፍ እንፈልጋለን፡፡
በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ እየተስፋፋ ከመጣው የፋብሪካ ብዛትና የኃይል አቅርቦት አለመመጣጠን አንፃር ከውሃ ማሞቂያ ይልቅ የሚያስፈልገው መብራት ይመስለኛል፡፡ መንግስትም ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከውጭ በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ መብራቶችን ቢያስገባም፣ አብዛኞቹ ለብልሽት እንደተዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እርስዎ ከመብራት ይልቅ እንዴት ለውሃ ማሞቂያዎች ቅድሚያ ሰጡ? ወደፊትስ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ መብራቶችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ያሰቡት ነገር የለም?
ከጥያቄሽ በመነሳት ሁለት ነገሮችን ልመልስ … ሰው በሀይል እጥረት መብራት ይቆራረጥበታል፤ አዎ እውነት ነው፡፡ ግን በተወሰነ የሰዓት ገደብ መብራት ያገኛል። መታጠቢያን ስትመለከቺ፣ አብዛኛው ሰው በሙቅ ውሃ የመታጠብ እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይሄን ከኢኮኖሚ አለማደግ ጋር እናያይዘዋለን፡፡ ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ኃይል እንጀራ ለመጋገር፣ ውሃ አሙቆ ለመታጠብ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸው የማይፈቅድ ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ ግን አንዴ ማሞቂያ ፓኔሉን ካስገቡ በነፃ ነው የሚጠቀሙት። ቆጣሪ የለውም፤ ክፍያ የለውም፤ ተፈጥሮን ብቻ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ሁለተኛው ነገር ወደ ገጠሩ ወጣ ብለን እንዳየነው ከሆነ፤ አሁን አሁን ሰዎች ሻወር ቤት እየገነቡ፣ በፀሐይ ሀይል ውሃ የሚያሞቅ በርሜልና ፓኔል እየገጠምንላቸው፣ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እየሰጡና እነሱም እየተጠቀሙ ነው፡፡ በሀይል ቁጠባም በኩል ካየሽው፣ ከመብራት (ከአምፖል ይልቅ) የውሃ ማሞቂያው ብዙ ሀይል ስለሚፈጅ፣ ለውሃ ማሞቂያው ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡ የውጭ ምንዛሬንም ማስቀረት ችለናል፡፡
ይሁን እንጂ በፀሐይ ሀይል ብርሃን የሚሰጥ መብራት የመስራትም እቅድ አለን ግን አሁንም ከፍተኛ ገንዘብ፣ ትልቅ ፋብሪካ ይፈልጋል፡፡ እኛ መንግስት ድጋፍ ካደረገልን፣ በዚህም በኩል ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ ምርት የማምረት እውቀቱም ብቃቱም አለን፡፡ ከተማውንም ሆነ ገጠሩን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ እንችላለን፡፡ መንግስት ፋይናንሱን ከሰጠን ከ6-8 ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት እንችላለን። በሰራተኞቻችን እውቀትና የስልጠና አቀባበልም እንተማመናለን፡፡
በፀሐይ ኃይል የሚሰራ መብራት ለማምረት ብድር ጠይቃችሁ ነበር?
ሁልጊዜ እንጠይቃለን፤ ከውጭ አይምጣ፤ ጥራት ያለው የፀሐይ መሰብሰቢያና ለመብራት የሚውል እቃ ላምርት ብዬ ብዙ ጊዜ ብጠይቅም ፋይናንስ የለም ነው መልሳቸው፡፡ በቃ በዚህኛው ተገድቤ እየሰራሁ ነው፡፡
እስኪ በፋብሪካችሁ ስለሚሰሩ ሰራተኞቻችሁ ይንገሩኝ፡፡ የትምህርት ደረጃቸው እንዴት ነው? የሠራተኛ አያያዛችሁ ምን ይመስላል?
በነገራችን ላይ እኔ መንግስትን ከማደንቅበት አንዱ የቴክኒክና ሙያ ት/ቤቶችን አስፋፍቶ፣ ወጣቶች በተለያዩ ደረጃዎች ሰልጥነው፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉ ነው፡፡ እርግጥ ነው ቀደም ሲልም እንደነ ፖሊቴክኒክ፣ ተግባረ ዕድ ያሉ የስልጠና ተቋማት ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ በከፍተኛ ደረጃ ነው ስልጠና የሚሰጡት። አሁን መንግስት ያስፋፋቸው የቴክኒክና ሙያ ት/ቤቶች በርካታ ዕድል ላላገኙ ወጣቶች እድል ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ እድል ያላገኙ የነበሩት ደግሞ በጣም ጥሩ ጥሩ ጭንቅላት ያላቸው ልጆች ናቸው፡፡ የእኛን ፋብሪካ ቀጥ አድርገው የያዙትም ከትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች በኤሌክትሪካል ወይም በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የተመረቁ እንዳይመስሉሽ፤ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የመጡ ብቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከፍተኛ ስልጠና እንዲያገኙ ከውጭ አገር ኤክስፐርቶችን ለሳምንት ለ10 ቀን እናመጣለን። እነሱ በ3 ቀን ስልጠና ሁሉን አውቀው ያጠናቅቁና በቃ ፈረንጁን ወደ አገሩ መልሰው ይላሉ፡፡ አሁን እየሰሩ ያሉት በትልቅ ብቃት ነው፡፡ አያያዝንና እንክብካቤን በተመለከተ፣ እኔ ከምናገር እነሱ ቢጠየቁ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ውጤታማ ስራ ለመስራት ከፈለገ፣ ሰራተኞቹን መንከባከብ፣ እንደ ቤተሰብ ቀርቦ ችግራቸውን መረዳት፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ እውቀታቸው እንዲያድግ፣ ጥሩ የስራ ከባቢ እንዲኖራቸው ማድረግ የግድ ይመስለኛል፡፡ እኛ ይህን እናደርጋለን፡፡ እኛ ጋ እየሰሩ የትምህርት ደረጃቸውን እያሳደጉ የሚገኙ አሉ። የፈተናና የጥናት ሰዓታቸው ይከበራል፡፡ እኛ ፋብሪካ ውስጥ ፈተና ወድቆ መምጣት ነውር ነው፡፡ በጣም ታማኝና ቅን ሰራተኞች ናቸው፡፡ ነገ በስራቸው ሌሎችን አሰልጥነው ተክተው፤ እነሱ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ የማድረግ እቅድ አለኝ፡፡ በሌላው ፋብሪካ እንደምታዘበው፣ ለስልጠናና ለአቅም ግንባታ ሰራተኞቻቸው ላይ ብዙ ብር አፍስሰው ሲያበቁ ጥለዋቸው ይሄዳሉ፡፡ እኔን እስካሁን ጥሎኝ የሄደ ሰራተኛ የለም፤ ቢሄዱም ከኔ የተሻለ እንክብካቤና ደሞዝ አግኝተው ከሆነ ቅር ሊለኝ አይገባም፡፡ እስካሁን ያለው ይሄን ይመስላል፡፡ እኛ አሁን ከሌቭል አንድ የወሰድናቸው ነበሩ፡፡ እዚህ እየሰሩ ሌቭል ሁለትና ሶስትን ተምረው፣ ሲኦሲ አልፈው፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት የሚያስቡ አሉ፡፡ ክፍያን በተመለከተ ተመጣጣኝ ክፍያ እንከፍላለን፡፡ ፋብሪካው ትንሽ ገቢ ሲያገኝ ለእነሱም ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ከደሞዛቸው ውጭም ሲስተም ለመትከል ስንሄድ የሚያገኙት ገንዘብ አለ፤ ለተከሉበት ማለት ነው፡፡ እኔም ሲስተም እንዲገጥሙ ስወስዳቸው የውሎ አበል እከፍላለሁ፡፡ ሁሉም የተሻለ ክፍያ እንደምከፍላቸው ያውቃል፡፡ አንድ ስራ ከያዙና ካልጨረሱ ምሳ ለመብላት እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ እንዲህ ዓይነት ታማኝና ጠንካራ ሰራተኞች አለመንከባከብ ውድቀት ነው፡፡ እነዚህ ልጆች ከቴክኒክና ሙያ ነው የመጡት፤ ግን ሰውን መፍጠር ይቻላል፡፡
የውሃ ማሞቂያዎችን በምን ያህል ዋጋ ነው የምትሸጡት? ሲስተሙን ለመግጠም ተጨማሪ ክፍያ ትጠይቃላችሁ?
ዋጋን በተመለከተ 80 ሊትሩን የውሃ ማሞቂያ ቫትን ጨምሮ በ13, ሺህ 500 ብር፣ 150 ሊትር ቫትን ጨምሮ በ17 ሺህ ብር፣ 200 ሊትሩን ደግሞ 22 ሺህ 500 ብር እንሸጣለን፡፡ ሄደን በምንገጥምበት ጊዜ ለባለሙያዎች 700 ብር ገዢው ይከፍላል፤ ያ 700 ብር ወደ እኛ አይመጣም፤ ወደ ገጣሚዎቹ ነው የሚሄደው፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅሙ ምን ያህል ነው? የፈላጊውስ መጠን?
 ፋብሪካው አሁን ባለበት ሁኔታ በወር 3 ሺህ በርሜሎችንና የፀሐይ ኃይል የሚሰበስቡ ፓኔሎችን የማምረት አቅም አለው፡፡ ፈላጊው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ሆቴሎች፣ ግለሰቦች፣ ባለ ሻወር ቤቶችች፣ ጤና ጣቢያዎች እየጠየቁን፣ በክልልም በአዲስ አበባም ምርታችንን እያቀረብን እንገኛለን፡፡ አሁን ህዝቡ ግንዛቤ እያገኘ ነው፡፡ ወደፊት ገበያውን ሰብረን እንገባለን፤ ያኔ አሁን ከምናቀርብበት ዋጋ በጣም ባነሰ ለማቅረብ ያስችለናል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ባመረትንና በሸጥን ቁጥር ከውጭ የሚመጡ መሳሪያዎችን እዚህ ማምረት እንጀምራለን፡፡ በተጨማሪም ከውጭ በተዘዋዋሪ የምናስገባቸውን የፋብሪካ ግብአቶች ቀጥታ ከአምራቾች የምንረካከብበትን ሁኔታ የመፍጠር አቅም ይኖረናል፣ ይሄ ይሄ ወጪያችንን ስለሚቀንስልን አሁን ከምናቀርብበት ዋጋ በጣም በመቀነስ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
ምን ያህል ሰራተኞች አሏችሁ?
በአሁኑ ወቅት ከ19 እስከ 22 የሚደርሱ ሰራተኞች አሉን፡፡ ስንጀምር የፋብሪካው መነሻ ካፒታል 16 ሚ. ብር ነበር፤ ሲሆን አሁን ከ30 ሚ. ብር በላይ ካፒታል ያንቀሳቅሳል፡፡
የወደፊት ዕቅድዎ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ኖሮት፣ መንግስትም ዋነኛ አጋዥ ኃይል መሆኑን በመገንዘብ ይበልጥ አግዞን፣ ሁሉም ህብረተሰብ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው አላማዬ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ህዝቡም አውቆት የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሎ፣ ካደግን በአጎራባች አገሮች ያለውን ገበያ መያዝና የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ ኢትዮጵያ በሶላር ኢነርጂ ከሌላው ዓለም የተሻለች መሆኗን ማሳየት ሌላውና ትልቁ አላማችን ነው፡፡ ምክንያቱም 13 ወር ሙሉ የፀሐይ ፀጋ ያላት በተፈጥሮ የታደለች አገር ናት፡፡ ሌላው ለውጭ ገበያ ደረጃውን የጠበቀ የዘርፉን ምርቶች ማቅረብና ሁሉንም መስራት እንደምንችል ለሌላው ዓለም ማሳየትም የአፍሮአምክ ሌላው ራዕይ ነው ይህን ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁንም የምናመርታቸው ምርቶች እስራኤል 70 ዓመት ከተጠበበችበት ምርት ይበልጣል፡፤
ከዚያ ቀጥሎ ዋናው ዓላማችን የኤሌክትሪክ መፍጠሪያውን መሳሪያ አገራችን ላይ አምርተን ማሳየት ነው፡፡ ይሄ እንደውም በቅርቡ ቢሆን ትልቅ ምኞት አለን፡፡ ለዚህ ዋና እንቅፋት የሆነብን ፋይናንስ እንጂ እውቀትና ብቃት አለን፡፡ ቢሮክራሲው እስከለቀቀንና ፋይናንስ እስካገኘን ድረስ መስራት እንችላለን፡፡ ፈረንጅ ላይ ጥገኛ መሆን አያስፈልገንም፡፡ በቃ በአገራችን ልጆች እውቀት እንመን፤ መልዕክቴ ነው፡፡ በተረፈ እዚህ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙኝም ያንን እንዳልፍ የረዱኝን ቤተሰቦቼን፣ የመንግስት ኃላፊዎችንና ጓደኞቼን እንዲሁም ዓላማዬን ራዕዬን ተረድታችሁ፣ ፍላጎቴንና ስራዬን ለህብረተሰቡ እንድናገር እድል የሰጣችሁኝን የጋዜጣችሁን ዝግጅት ክፍል ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡