Administrator

Administrator

   በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው በመወዳደር ላይ የሚገኙት አወዛጋቢው ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ፤ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ፣ “ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ÷ የአሸባሪው ድርጅት አይሲስ መስራች ናቸው” ሲሉ መናገራቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘገበ፡፡ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በፍሎሪዳ ሰንራይዝ ከተማ ባካሄዱት የምረጡኝ ቅስቀሳ ንግግራቸው ላይ፣“አይሲስን የመሰረቱት ፕሬዚዳንት ኦባማ ናቸው” በማለት ሶስት ጊዜ ደጋግመው የተናገሩ ሲሆን “ከእሳቸው ጋር በመሆን አሸባሪውን ድርጅት የመሰረቱትም ተንኮለኛዋ ሄላሪ ክሊንተን ሳይሆኑ አይቀሩም” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል፡፡
አወዛጋቢው ትራምፕ፤በንግግራቸው ወቅት ኦባማን በሙሉ ስማቸው ባራክ ሁሴን ኦባማ ብለው መጥራታቸው፣ ፕሬዚዳንቱ የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸው የሚለውን ሃሜት ለማጉላት በማሰብ ነው ያለው ዘገባው፤ኦባማ ስለ ሽብርተኝነት ሲያወሩ አክራሪ እስላማዊ ሽብርተኝነት ብለው ለመናገር አይደፍሩም ሲሉ መንቀፋቸውንም ጠቁሟል፡፡ ፡፡
“ሂላሪ ክሊንተንም ፕሬዚዳንት ኦባማን ላለማስቀየም ሲሉ ይህንን አባባል በንግግራቸው ላይ ተጠቅመውት አያውቁም” ያሉት ትራምፕ፣ ይህም የሆነው ኦባማን ካስቀየምኩ የከፋ ነገር ይገጥመኝ ይሆናል በሚል ስጋት ነው ብለዋል፡፡ ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፤ትራምፕ የወቅቱን የአሜሪካ አስተዳደር ከአይሲስ ምስረታ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ሲያደርጉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ በመጠቆም፣ ባለፈው ሃምሌ ላይም አይሲስን የፈጠሩት ሄላሪ ክሊንተን ናቸው ማለታቸውን አስታውሷል፡፡

1- ዘንድሮ ኢህአዴግ ከየአቅጣጫው መጠነ-ሰፊ ህዝባዊ
ተቃውሞን እያስተናገደ ነው፡፡ ምናልባት በተቃውሞው
ተማርሮ፤ “ሥልጣን በቃኝ፤ አገሪቱን ተረከቡኝ” ቢል
ምን ይከሰታል?
ሀ) የተዓምር አገር ስለሆነች ምንም አይከሰትም!
ለ) ወላድ በድባብ ትሂድ፤ ደግሞ ስልጣን
ለመረከብ!
ሐ) የተቃዋሚዎች የሥልጣን ሽኩቻ ይቀጥላል!
መ) የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር!
ሠ) ባለቤቱ ሰፊው ህዝብ ይረከባላ!
2- የኢህአዴግ አመራሮች፤ ዱብዕዳ በሆነባቸው የህዝብ
ተቃውሞና የባህርይ ለውጥ የተነሳ (ከቻይነት ወደ
እምቢተኝነት!) ምን የሚያጉተመትሙ ይመስልዎታል?
ሀ) ለካስ መንግስቱ፤ “ይሄ ህዝብ ወርቅ ሲያነጥፉለት
ፋንድያ ነው ይላል” ያለው ወዶ አይደለም!!
ለ) በህዝብ ላይ እንደፈፀምነው በደል፣ተቃውሞ
ሲያንሰን ነው!
ሐ) ሥልጣን እንደሆነ ነፍጠኛ እጅ አይገባትም!
መ) ድምጹን ሰጥቶን፣ ፊት ነሳን!
ሠ) ከእንግዲህ ህዝብን ማመን አስሮ ነው!
3- ለወቅቱ ፖለቲካዊ ቀውስና አለመረጋጋት
መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ሀ) ጸሎትና ምህላ!
ለ) ኳሷ በመንግስት እግር ሥር ናት!
ሐ) ለተቃዋሚዎች ሥልጣን ማጋራት!
መ) ውይይትና እርቀ ሰላም!
ሠ) እንኳን እኔ መንግስትም አያውቀው!
4- በአገራችን የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ችግሮች የሰው
ህይወት ሳያልፍ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ
የማይፈቱት ለምንድን ነው?
ሀ) ዲሞክራሲ ሂደት ነው!
ለ) እልኸኝነታችንና ግትርነታችንስ!
ሐ) ይሄን ሊመልስ የሚችለው ኢህአዴግ ብቻ ነው!
መ) ሰዎች፤ የዘራነውን ነው የምናጭደው!
ሠ) እኔም ግራ የሚገባኝ እሱ ነው!
5- አገር በተቃውሞና ግጭት ስትታመስ፣ምሁራኑ
ድምጻቸውን ያጠፉት ለምንድን ነው?
ሀ) ድሮስ መች ድምጽ ነበራቸው!
ለ) እንዲተነፍሱ ማን ዕድል ሰጣቸው!
ሐ) ጎመን በጤና ብለው ይሆናል!
መ) አ ንድም ግ ዴለሽነት አ ሊያም አ ድርባይነት ነው!
ሠ) Boycott Politics ብለው ሊሆን ይችላል! (N.B- ከተሰጡት ምርጫዎች ውስጥ ለእርስዎ
የሚስማማ መልስ ከሌለ፣
የራስዎትን ምርጫ የማካተት መብትዎ የተጠበቀ ነው!!!)




ለትራምፕ ድምጻቸውን ላለመስጠት ተፈራርመዋል
   50 የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት ባለስልጣናት፣ አነጋጋሪው የአሜሪካ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በምርጫው በለስ ቀንቷቸው የሚመረጡ ከሆነ የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነትና ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ ማለታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የሪፐብሊካን አባላት የሆኑት እነዚሁ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ለኒውዮርክ ታይምስ በጻፉት ደብዳቤ፣ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የባህሪ፣ የእውቀትና የልምድ እጥረት እንዳለባቸውና ብቁ እንዳልሆኑ ገልጸው፣ በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የሚይዙ ከሆነ የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት የከፋ ችግር ላይ ይጥላሉ ብለዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫው የማሸነፍ ዕድል ካገኙ፣በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ግድየለሹና እንዝህላሉ መሪ ይሆናሉ ያሉት የደህንነት ባለስልጣናቱ፤ ሰውዬው የአገሪቱን ህገ መንግስት በቅጡ ስለማወቃቸውና በህገ መንግስቱ ስለማመናቸው እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉዳዮችን በቅጡ ስለመረዳታቸው እንጠራጠራለን ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
እነዚሁ የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያዎች በምርጫው ድምጻቸውን ለትራምፕ ላለመስጠት መወሰናቸውን በደብዳቤያቸው ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ከ100 በላይ የሪፐብሊካን የብሄራዊ ደህንነት ባለሙያዎች በተመሳሳይ መልኩ ትራምፕን በመቃወም የጋራ ደብዳቤ መጻፋቸውንም አስታውሷል፡፡

     የብራዚል ምክር ቤት አባላት ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ስብሰባ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ፤ከታክስና ህጋዊ ካልሆነ ወጪ ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው ውንጀላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንቷ ለፍርድ ይቅረቡ ወይስ አይቅረቡ የሚለውን ለመወሰን የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ድምጽ፣ 59 ያህሉ ለፍርድ ይቅረቡ ሲሉ፣ 21 ያህሉ ደግሞ አይቅረቡ በሚል ድምጻቸውን መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤  ጉዳዩ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በፍርድ ቤት መታየት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡
ሩሴፍ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ ከ1930ዎቹ ወዲህ ወደ ከፋ ዝቅጠት እያመሩት ነው በሚል ሲወነጀሉ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቷ የቀረቡባቸውን ክሶች በሙሉ ክደው በመከራከር ለፍርድ እንዲቀርቡ መወሰኑ እሳቸውን ከስልጣን ለማውረድ የሚፈልጉ ሃይሎች ሴራ ነው ማለታቸውን አስረድቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ሩሴፍ በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሙሉ ለሙሉ ከስልጣናቸው ይነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ተቀናቃኛቸው ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመር በጊዚያዊነት አገሪቱን መምራት ይቀጥላሉ መባሉን ገልጧል፡፡
የአሜሪካው ሴናተር በርኒ ሳንደርስ በበኩላቸው በድረገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ፕሬዚዳንቷ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መወሰኑን በመቃወም፣ጉዳዩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት ከስልጣን ለማስወገድ ታስቦ የተደረገ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ማለታቸውን ዘ ኢንኩዚተር ዘግቧል፡፡

በህይወት የቆዩት በግዳጅ በአፍንጫቸው በሚሰጣቸው ምግብ ነው
   የህንድ መንግስት ያወጣውን አንድ አነጋጋሪ ህግ በመቃወም ላለፉት 16 አመታት ምግብ ሳይመገቡ የዘለቁት ኢሮም ሻርሚላ የተባሉት ህንዳዊት፤ ባለፈው ማክሰኞ የረሃብ አድማቸውን አቁመው ምግም መመገብ መጀመራቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ።
ለአገሪቱ የጦር ሃይል በማኒፑር ግዛት የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ለመቆጣጠር ያልተገባ ስልጣን ይሰጣል የተባለውን ህግ የተቃወሙት ሻርሚላ፤ላለፉት 16 አመታት ምግብና ውሃ አልወስድም ብለው በረሃብ አድማቸው ጸንተው መዝለቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የመንግስት ሃይሎች በሴትየዋ አፍንጫ በተተከለ ቱቦ አስገድደው በሚሰጧቸው ምግብ ህይወታቸውን እንዳቆዩት ገልጧል፡፡
የማኒፑሯ ብረት የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው የ44 አመቷ ህንዳዊት፤ እ.ኤ.አ በ2000 የመንግስት ሃይሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸማቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ወታደሮች ዜጎችን ያለ እስር ትዕዛዝ ማሰር እንዲችሉና ሃይል እንዲጠቀሙ የሚፈቅደውን ህግ በመቃዎም የረሃብ አድማ መጀመራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡ ሴትዮዋ ለ16 አመታት የዘለቀውን የረሃብ አድማቸውን ለማቋረጥ የወሰኑት፣ ከረሃብ አድማው ይልቅ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ ህጉን ለማሰረዝ ያስችለኛል ብለው በማሰባቸው ነው ያለው ዘገባው፤አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን የህንዳዊቷን ውሳኔ መቃወማቸውን ጠቁሟል፡፡

ስራ ለመቀጠር የሚያስችለውን ከወንጀል ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲሰጠው ለመጠየቅ ወደ አንድ የአገሪቱ ፖሊስ ጣቢያ ያመራው ቻይናዊ÷ ከፖሊስ መኮንኖች “ምን ማለትህ ነው!?... አንተ እኮ ወንጀል ሰርተህ በመገኘትህ ከአስር አመታት በፊት በስቅላት የተገደልክ ሰው ነህ!... ሞተሃል!...” የሚል ምላሽ ተሰጠው ይላል ቢቢሲ፡፡
ቼን የተባለው የ45 አመት ቻይናዊ፣ በ2006 በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ በስቅላት እንደተገደለ የሚያረጋግጥ መረጃ እንዳገኙ በፖሊሶች እንደተነገረው የጠቆመው ዘገባው፤ ግለሰቡ ግን “እመኑኝ ወንጀል አልሰራሁም፣ በስቅላትም አልተገደልኩም፣ በህይወት አለሁ” ሲል አቤቱታ ማቅረቡን ገልጧል፡፡
የግለሰቡን የአልሞትኩም እመኑኝ አቤቱታ ተቀብሎ ሲመረምር የሰነበተው የዡሃንግዙ ፖሊስም፣ ጉዳዩ በስህተት የተፈጸመ እንደሆነና በተባለው ወንጀል የስቅላት ሞት የተፈረደበትና የተገደለው ሰው ሌላ ስመ ሞክሼ እንደሆነ መረጋገጡን አስታውቋል ብሏል ዘገባው፡፡
ወንጀል ሰርቶ በመገኘቱ ከአስር አመታት በፊት በስቅላት የተገደለው ትክክለኛው ቼን፣ ከዚህኛው ቼን ጋር ተመሳሳይ ስምና የነዋሪነት መታወቂያ ቁጥር እንዳለው መረጋገጡን ያስታወቀው ዘገባው፤በቻይና አንድ አይነት ስም ያላቸውና በስህተት አንድ ዓይነት የመታወቂያ ቁጥር የሚሰጣቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ችግር እንደሚገጥማቸውም አክሎ ገልጧል፡፡





50 ሺህ ሰዎች በመፈንቅለ መንግስቱ ተጠርጥረው ፓስፖርታቸውን ተነጥቀዋል

   በቅርቡ ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ በዜጎቹ ላይ መረር ያለ እርምጃ መውሰዱን የቀጠለው የቱርክ መንግስት፣ያሰራቸው ሰዎች ቁጥር ከ26 ሺህ በላይ መድረሱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአገሪቱን የፍትህ ሚኒስትር በኪር ቦዝዳግን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ጋር በተያያዘ 16 ሺህ ሰዎች በመደበኛ ሁኔታ ታስረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን ሌሎች 6 ሺህ ታሳሪዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ በሂደት ላይ ይገኛሉ፤8 ሺህ ያህል ታሳሪዎች ደግሞ ከእስር ቢፈቱም ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡
ሚኒስትሩ የቀሪዎቹን 4 ሺህ ያህል እስረኞች ጉዳይ በተመለከተ ያሉት ነገር እንደሌለ የጠቆመው ዘገባው፤ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው ከታሰሩት 26 ሺህ ያህል ሰዎች መካከል ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች ግለሰቦች እንደሚገኙበትና በሺዎች የሚቆጠሩትም ከስራቸው መባረራቸውን አመልክቷል፡፡
የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን መንግስት ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር በተያያዘ እየወሰደ ባለው እጅግ ከረር ያለ እርምጃ፣ ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ፓስፖርቶች መሰረዛቸውን፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን መታሰራቸውን፣ ከ130 በላይ መገናኛ ብዙኃን መዘጋታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
በቅርቡ በአገሪቱ መንግስት ላይ በተቃጣው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ፣ ከ246 በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውንና ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑትም የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ዘገባው አስታውሷል፡፡


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንሥር ጎጆ ቤቷን ትልቅ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ትሠራለች፡፡
አንዲት ድመት ደግሞ ከነልጆቿ የዛፍ ግንድ መካከል የተቦረቦረ ሥፍራ ትኖራለች፡፡
አንዲት የዱር አሣማ ደግሞ ከዛፉ ግርጌ በተቦረቦረው ግንድ ውስጥ ከነልጇቿ ትኖራለች፡፡
እነዚህ ሶስት እንስሳት እንደ ጎረቤታሞች ሁሉ በፍቅር ተሳስበው፣ በአንዱ ግንድ ላይ ሲኖሩ ያስቀኑ ነበር፡፡ በኋላ ግን ተንኮለኛዋ ድመት ያንን የመሰለ የፍቅር ህይወታቸውን ልታደፈርስ ተነሳች፡፡
ወደ ንስሩ ጎጆ ወጣች-ድመቲት፡፡
 እንዲምህ አለቻት፡-
‹‹እኔና አንቺ ከባድ አደጋ እያንዣበብን ነው››
‹‹እንዴት?›› አለች ንሥር››
‹‹አሣም ተንኮለኛ ናት፡፡ የእኛን ህይወት ለማበላሸት ሌት ተቀን ከመጣጣር አልታቀበችም››
ንሥርም፤
‹‹እኛ የምንኖረው የራሳችንን ኑሮ፡፡ አሣማም ልጇም የሚኖሩት የራሳቸውን ኑሮ፡፡ ለምን እንደራረሳለን?›› አለችና ጠየቀች፤ በሙሉ የዋህነት፡፡
ድመትም፤
‹‹አሣማ እንደኛ ቀና ብትሆን ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ልቧ ክፉ ነው፡፡ ስለሆነም የሁላችንም የጋራ መኖሪያ የሆነውን ግንድ ከሥሩ እየገዘገዘች ልትጥለው ነው፡፡ ከእንግዲህ መኖሪያ አይኖረንም። የአንቺም የእኔም ልጆች የእሷ ምግብ መሆናቸው ነው›› አለች፡፡ ንሥር በጣም ተረበሸች፡፡ ተሸበረች፡፡ ድመት ሆዬ፣ ከንሥር ጎጆ ወደዛፉ ግርጌ ወረደች፤ አሣማዋ ዘንድ መጣችና፤
‹‹እመት አሣማ፤ የእኔና አንቺ  ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን ታውቂያለሽ?›› ስትል አሣማን ጠየቀቻት፡፡
አሣማም፤
‹‹ለምን? እንዴት? እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም››፤ አለቻት፡፡
ድመትም፤
‹‹እዚያ፤ ዛፉ አናት ላይ ካለችው ንሥር መጠንቀቅ አለብሽ፡፡ አንድ ቀን ስትዘናጊላት ወደ ታች ወርዳ ግልገልሽን ይዛብሽ ትሄዳለች፡፡ ጊዜ እየጠበቀች ነው፡፡ ያንቺ ልጆች የንሥር ልጆች ቀለብ እንዳይሆኑ ብታስቢበት ይሻላል›› አለች፡፡
ልክ እንደ ንሥሩ ሁሉ አሣማም በጣም ደነገጠች፡፡ በጣም ተሸበረች፡፡ ድመት ሁለቱን ጎረቤቶቿን እጅግ አድርጋ ካስፈራራች በኋላ ወደ መኖሪዋ ተመለሰች፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ የፈራች ለማስመሰል ድመት ቀን ቀን መውጣቷን ተወች፡፡ ለልጆቿ ምግብ ለመፈለግ ማታ ማታ ብቻ ሆነ የምትወጣው፡፡
ንሥር ከጎጆዋ መውጣት ፈራችና ራሷን ዘግታ ቁጭ አለች፡፡
አሣማም ከፍርሃቷ የተነሳ ከዛፉ ግርጌ ካለው ሥር ንቅንቅ አልልም ብላ ከመኖሪያዋ ሳትወጣ ልጆቿን መጠበቅ ሆነ ሥራዋ፡፡ ቀን እየገፋ ሲመጣ የንሥርና የአሳማ ቤቴሰቦች በረሀብ አለቁ፡፡ ድመትም ለራሷና ለልጆቿ የሚሆን የተትረፈረፈ ምግብ አገኘች፡፡
የጋራ ቤታቸውን አስከብረው፣ በፍቅር እየተሰባሰቡ የሚኖሩ የታደሉ ናቸው፡፡ በተንኮል የሌሎችን ህይወት የሚያደፈርሱ እኩያን፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዋጋ መክፈላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለሁሉም በሚበቃ አገር፤ የሌላውን ህልውና በሚያጨልም መልኩ ግፍ መፈፀም የማታ ማታ ማስጠየቁ ሳታውቅ በስህተት፣ አውቀህ በድፍረት ባደረግኸው መጠየቅ አለና፤ የምታደርገውን በቅጡና በጥንቃቄ አድርግ! የሀገራችን ሰላም ማጣት ለማንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንጂ በኋይል ለመፍታት መሞክር ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ መላ አይሆንም፡፡ መንግሥት በየጊዜው የሚወስዳቸው አርምጃዎች እንድም ሶስትም ናቸው ከሚባሉት ከመልካም አስተዳደር፣ ከፍትሕና ከሙስና ችግሮ አኳያ፣ ያላንዳች ማንገራገር ራሱን ካልመረመረ ወደ ካንሰርነት በመለወጥ ላይ ያለ በሽታ ይዞ እንደመክረም መሆኑ አይካድም፡፡
የአገራችንን ጠቅላይ ስዕል (bigger picture) ማየት ተገቢ ነው፡፡ ገዢ የሚባሉትን ትላልቅ ችግሮች እንጂ እንደ ቀዶ ጥገና ሀኪም የተወሰኑ ብልቶን ብቻ ለይቶ ለማከም መጣር የተነካኩትን አካላት እንደ መዘንጋት ስለሚሆን አጠቃላይ ጤና ከመታወክ አይድንም፡፡ “የአብዬን እከክ ወደ ምዬ ልክክም” (Blame - Shifting) አያዋጣም፡፡ ነገ ተነገ - ወዲያ እናስተካክለዋለን ማለትም (procrastination) ችግሮችን ከማባባስና ቀንን ከማቅረብ በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። አድሮ ቅርንጫፍ አብቅሎ አፍጦ ይመጣብናልና፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ“ሐምሌት” ትርጉሙ እንዲህ ይለናል፡-
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል፤ ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል፡፡ ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል”
እንጠንቀቅ፡፡ ራሳችንን እንመርምር፡፡ የችግሮቻችንን አጠቃላይ ስዕል እንቃኝ፡፡ ነጋ - ጠባ እያወራናቸው ያልፈታናቸው ችግሮች የትየለሌ ናቸው! በግልፅ ችግሮቻችንን እንወያይባቸው፡፡ ልዩ ልዩ ታርጋ እሰጠን አንሽሻቸው፡፡ ፈረንጆች Denial የሚሉት ዓይነት፤ ያለውን ነገር እንደሌለ አድርገን መካድና መካካድ፤ የትም አያደርሰንም፡፡ መረጃ ባለመስጠት፣ አገር አናድንም፡፡ ጥቃቅኑን ነገር እየመነዘርን ፀጉር ስንጠቃም ያው ከቁንጫ መላላጫ ማውጣት ነውና ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ አንድም ደግሞ ከግጭት አዙሪት እንዴት እንውጣ ብሎ ራስን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። እንደ ሰሞኑ የውሃ ዋና ጭቅጭቅ አፍጥጠው ሚመጡ አያሌ ጅላጅል ሀሳቦች፣ የማመን ያለማን ግልፅነት የጎደለው ስፖርት፣ የዓለም መሳቂያ እንዳያደርጉን አሁንም ዐይናችንን መክፈት ተገቢ ነው፡፡ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን ከልብ እንፈትሽ፡፡
“የግጭት ቀለበለት ካሰርን ቆይተናል ሰርጉ ገና አልተደገሰም” እየተባለ ሲሾፍ፤ ውስጡ መራራ ዕውነት እንዳለ አለማስተዋል የዋህነት ነው፡፡ በበርካታ ስራ አጥ ወጣት የተወጠረች አገር ምንም አይነት ተንኮል ቢሸረብባት አይገርምም!! an idle mind is the devil’s workshop ይሏልና!! (ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ስራ - ቤት ይሆናል፤ እንደማለት ነው) እለት ሰርክ በተግባር የምናውን ነገር ስንክድ መፍትሄ መፈለግ ያባት ነው፡፡ ተግባር መስተውት ነው፡፡ ከተግባር ወዲ የምንቆጥረውም ስክር አይኖርም፡፡ “መስተዋት የምትነግርህን፣ የእናትህ ልጅ አትነግርህም” የሚባለው ተረትና ምሳሌ፣ በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሁኔታ መቃወስ በቅጢ እንድንፈትሽ፣ መስተዋቱን በጥንቃቄ እንድናይ፤ አመላካች ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት፣ በግማሽ ዓመት 670 ሚ.ዶላር ለእዳ ክፍያ አውጥቷል

የውጭ እዳ በፍጥነት እየተከማቸበት የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በ2006 ዓ.ም የብድር እዳ ከነወለዱ 570 ሚ. ዶላር መክፈሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ክፍያው በእጥፍ ጨምሮበታል። ዘንድሮ እስከ መጋቢት ድረስ፣ 670 ሚ.ዶላር እንደከፈለ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ገልጿል።
ከአራት አመት በፊት፣ የመንግስት ጠቅላላ የውጭ እዳ ወደ 9 ቢሊዮን ገደማ እንደነበረ የገንዘብ ሚኒስቴር ጠቅሶ፣ ዘንድሮ እስከ መጋቢት ወር ድረስ፣ የእዳው ክምችት 20.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል።
በተለይ፣ በባቡር መስመር ግንባታ፣ በቴሌኮም እና ለአመታት በተጓተቱት የስኳር ፕሮጀክቶች ሳቢያ በፍጥነት እየተከማቸ ከመጣው ብድር ጋር፣ ለእዳና ለወለድ ክፍያ የሚውለው የውጭ ምንዛሬም እየከበደ እንደመጣ የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያሳያል።
በ2004 እና በ2005 ዓ.ም፣ ለእዳና ለወለድ ክፍያ የሚውለው የውጭ ምንዛሬ ግማሽ ቢሊዮን ገደማ ነበር። አምና የክፍያው ሸክም ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል (980 ሚ.ዶላር)።
የወለድ ክፍያው ለብቻው ሲታይም እንዲሁ፣ ከአመት አመት እየጨመረ መጥቷል። ከአራት አመት በፊት፣ 100 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የወለድ ክፍያ፣ አምና ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። ዘንድሮም እስከ መጋቢት ድረስ፣ ለወለድ 210 ሚ.ዶላር እንደተከፈለ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ይገልፃል። እየከበደ የመጣውን የእዳና የወለድ ክፍያ ለማሟላት፣ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ በአምስት አመታት በእጥፍ ለማሳደግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ፣ የኤክስፖርት ገቢ እስካሁን አልጨመረም። ያኔ ከነበረበት፣ የ3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ፣ ብዙም አልተነቃነቀም።
ደግነቱ፣ ለነዳጅ ግዢ ይውል የነበረው የውጭ ምንዛሬ፣ ባለፉት ሁለት አመታት ቀንሷል። ከ2006 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር፣ የቤንዚን  የአለም ገበያ ዋጋ በ70% ቀንሷል። የናፍታ ደግሞ በ60% ቀንሷል። በዚህም፣ መንግስት በአመት ውስጥ፣ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ለማዳን እድል አግኝቷል።
ይህም ብቻ አይደለም። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ ወደ አገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ መምጣቱ፣ መንግስትን ጠቅሟል። ከአራት አመት በፊት፣ በአመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይልኩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ አሁን በአመት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይልካሉ - በኤክስፖርት ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሚበልጥ።

የምርምር ውጤቶች መድብል ነው ተብሏል
    በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካልና ኢንዱትሪያል ምህንድስና መምህር በሆኑት ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፣የተሰሩ የምርምር ውጤቶች የተሰባሰቡበት፤ ‹‹እንሆ መንገድ›› የተሰኘ መፅሐፍ ዛሬ ከጠዋቱ ከ3፡00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡
 መፅሃፉን ያዘጋጀው አንዷለም አባተ (የአፀደ ልጅ) እንደሆነ ታውቋል፡፡ የምርምር ውጤቶቹ በመፅሀፍ መልክ የታተመበት ዋና አላማ፣ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶች ማህበረሰቡ ዘንድ ደርሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማሰብ እንደሆነ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ተገልጿል፡፡ መፅሐፉ በ10 ክፍሎችና በበርካታ ንዑስ ርዕሶች ተከፋፍሎ፣በ188 ገፅዎች የተቀነበበ ሲሆን በ80 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡