Administrator

Administrator

Saturday, 23 April 2016 10:28

የዘላለም ጥግ

- ጥበብ አንድም ስርቆት ነው አሊያም አብዮት ነው።
ፓውል ጋውጉዪን
- የነፃነት ፍቅር ሌሎችን ማፍቀር ነው፤ የሥልጣን
ፍቅር ራሳችንን ማፍቀር ነው፡፡
ዊልያም ሃዝሊት
- ተንበርክከህ ከመኖር ቆመህ መሞት የተሻለ ነው፡፡
ዶሎሬስ ኢባሩሪ
- ኪነ - ህንፃ ቦታን እንዴት ማባከን እንደሚቻል
የማሳያ ጥበብ ነው፡፡
ፊሊፕ ጆንሰን
- ማውራትና አንደበተ - ርቱዕነት አንድ አይደሉም፤
መናገርና በቅጡ መናገር ሁለት የተለያዩ ነገሮች
ናቸው፡፡
ቤን ጆንሰን
- ጋዜጠኝነት ባዶ ቦታን የመሙላት ፈተናን
የመወጣት ችሎታ ነው፡፡
ሬቤካ
- ሰዎች ስለ ሥዕል እኔ የማውቀውን ያህል ቢያውቁ
ኖሮ ስዕሎቼን ፈፅሞ አይገዙኝም ነበር፡፡
ኢድዊን ላንድሲር
- ቀዝቃዛውን ጦርነት ያስቆመው ሰው ነበር … የጦር
መሳሪያ ወይም ቴክኖሎጂ፣ የጦር ሰራዊት ወይም
ዘመቻ አልነበረም፡፡ በቃ ሰው ነው፡፡
ጆን ሊካሬ
- ሰዎች ካልተቸገሩ በቀር ምንም ጥሩ ነገር
አይሰሩም፡፡
ኒኮሎ ማኪያቬሊ
- ሌሎችን የሚያስተዳድር ሰው በመጀመሪያ የራሱ
ጌታ መሆን አለበት፡፡
ፊሊፕ ማሲንገር
- ደስተኛ መሆን አለመሆንህን ራስህን ጠይቅ፤
ከዚያም ደስተኛ መሆንህን ታቆማለህ፡፡
ጆን ስተዋርት ሚል
- እያንዳንዱ ትውልድ በአባቶቹ ላይ ያምፅና
ከአያቶቹ ጋር ወዳጅነት ይፈጥራል፡፡
ሌዊስ ሙምፎርድ



“--- ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ አደርጎ ከንፈር መምጠጥ ብቻ በቂ አይደለም፡
ከሚቸረው የከንፈር መምጠጥና የሞራል ካሳ ጎን ለጎን፣ በኢኮኖሚያዊ
ካሳም የዜጎቻችንን እንባ ማበስ ያስፈልጋል፡፡----”
ሙሼ ሰሙ
     በቅድሚያ በግፍ ላለቁ ዜጎቻችን ጥልቅ ሃዘኔን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
ከደቡብ ሱዳን የተነሱ የሙርሌ ጎሳዎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በመሳርያ የታገዘ ጥቃት  በመሰንዘር በጋምቤላ ክልል በሚኖሩ ቁጥራቸው ከ200 ያላነሱ ዜጎቻችን ላይ እልቂት ፈጽመዋል፡፡ ድርጊታቸው በዚህ ሳያበቃም ቁጥራቸው ያልታወቁ ህጻናትና ሴቶችን አግተውና ከብቶች ዘርፈው  እየነዱ ወደ መጠቡት ተመልሰዋል፡፡
ይህ ድርጊት ለአዕምሮ የሚከብድ ከመሆኑ አንጻር እንኳን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሊፈጸም ይቅርና ሊታሰብ የማይችል ድርጊት መስሎ የሚታየን በርካታ ሰዎች እንኖራለን፡፡ በእኔ ግምት ግን ወደድነውም ጠላነው፣ አፍሪካውያን ገና ከዘመናዊ አኗኗር ጋር ያላዋሃድናቸው ብዙ ጎሳዎችና ብሔሮች ያሉት ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት በቀጣይ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡ በበርካታ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ከኋላ ቀርና ከአስከፊ ባህል ለመላቀቅ ብዙ ስራ የሚጠይቃቸው ሕዝቦች አሉን፡፡
ችግሩ ዘለቄታ ባለው መንገድ የማይፈታው ግን ስር ነቀል መፍትሔ ከመሻት ይልቅ አንደዚህ አይነት ድርጊት በተከሰተ ቁጥር እንዴት ተደፈርን የሚለው የበቀል ዛራችን እያገረሸ፣ በሕግ የበላይነት መንፈስ ሳይሆን ያስቆጣንና ያሳዘነን ሁሉ ለመፍጀት ከመነሳሳታችን ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ በታሪክ ፊት እንደ ሕዝብ የሚያስተዛዝበን ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ በጋምቤላ በተከሰተው እልቂትም ዙርያ እየተመለከትን ያለነው የመፍትሔ አቅጣጫ ይኸው ነው፡፡ ይህ ወሬሳ የመምታት ስነልቦና ቀድሞውን ቢሆን በኋላ ቀር ባህልና አስተሳሰብ ተተብትበው ወረራ ከሚያካሂዱትና እልቂት ከሚደግሱት ጎሳዎች የማንሻል ያደርገናል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሃሳቤ መቋጫ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
አሁን አወዛጋቢ ወደሆነው የተጠያቂነት ጉዳይ ልምጣ፡፡ ከቅድመ ዝግጅት መጓደልም ሆነ ከንህዝላልነት በመነጨ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው መጠየቅ የሚገባቸው የመንግስት ተቋማት፣ ባለስልጣናትና ግለሰቦች ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደዚህ አይነቱን ድርጊት ዝንተ ዓለማችንን ሰራዊት ዘብ በማቆም ወይ ድንበር በማጠር ብቻ የምንፈታውና ልንቋቋመው የምንችለው ጉዳይ እንዳልሆነ እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱን ላቅርብ፡፡
ይህ እልቂት የተከሰተው መንግስት በሁለት ምክንያት በአካባቢው ያለውን የኃይል ሚዛን የሚያናጋ ድርጊት በመፈጸሙ እንደሆነ መጠርጠር ይቻላል፡፡ አንደኛው በቅርቡ በጋምቤላ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የአካባቢው ነዋሪን ጨምሮ የክልሉ ታጣቂ ሃይሎች በሙሉ ትጥቅ በመፍታታቸው የሃይል ሚዛኑ ላይ ክፍተት በመፈጠሩ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ በኦሮሚያና በተለያዩ ክልሎች የተነሳውን ሕዝባዊ ቁጣ ለማብረድ መንግስት ሰራዊት ከየአካባቢው  በማንቀሳቀሱ በተፈጠረው የሃይል መሳሳት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በማንኛውም መንገድ ማለትም በቅድመ ዝግጅት ማነስም ሆነ በንዝላልነት ክፍተት ሲፈጠር ወረራው የሚከሰት ከሆነ፣ ዝንተ ዓለም ታጥቀንና ሰንቀን ጠላት በመጠበቅ ስራ ላይ መሰማራታችን ብቻ ለመፍትሔው በቂ  ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ያሳያል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ጥቃት የፈጸሙት የሙርሌ ጎሳ አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለምዶ በለሊት በር እያንኳኳን በልመና ስራ ካልተሰማራን አንቆመጣለን እንደሚሉት ዜጎቻችን ሁላ ወረራ ካላካሄድን መቅሰፍት ይደርስብናል የሚል እምነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። በዚህም ምክንያት ሙርሌዎቹን ከዚህ እምነታቸው ማላቀቅ ካልተቻለ በስተቀር እድል በሰጣቸውና ሁኔታው በፈቀደላቸው ጊዜና  መጠን ወረራ ከማድረግና እልቂት ከመፈጸም የሚመለሱ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ለምን ቢባል  በመንግሰት በኩል ዜጎችን ከእልቂት በመታደግ ረገድ ከታየው ንዝህላልነት ባልተናነሰ የሙርሌዎች የኋላቀር ባህል ቁራኛነት ሌሌው ችግር ነው፡፡
መንግስት ለችግሩ ወቅታዊ መፍትሔ ከመሻት ባሻገር ዘለቄታዊ አማራጭን ተደራድሮ ከማምጣት አኳያ ምን ያህል ድክመት እንደነበረበት ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ችግሩ ስር የሰደደ፣ ባሕላዊና ስነልቦናዊ መንስኤ ያለው  መሆኑ እስከታወቀ ድረስ ታጥቆና ሰንቆ ከመጠበቅ በተጨማሪ ቅድመ መከላከል እውን የሚያደርግ፤ ዙርያ ገብ የሆነና የድንበር ላይ እንቅስቃሴን የሚቆጣጣር በተለይ ደግሞ ሰርጎ ገብ ዜጎቹን ስርዓት የማስያዝ ኃላፊነትን በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ የሚጥል ስምምነት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር መደረስ ነበረበት፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ሙርሌ ዓይነት የወራሪነትና የዘራፊነት ባህላዊ ዝንባሌ ያለውን ጎሳ ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም በከፋ መልኩ ወራሪነት የተጠናወተው ባሕላቸው ጎጅነትና አደገኛነት ላይ ትምህርት በመስጠት ከዚህ ዓይነቱ ኋላ ቀር ባህል የማላቀቁ ስራ መሰራት ነበረበት፡፡ ይህ አልተደረገም፡፡ ቅድመ መከላከሉ መዘንጋቱ ሳያንስ ደግሞ በአናቱ ላይ ሕዝቡን ከእልቂት ለመከላከል የሚያስችል ሃይል ሳይተካ ነዋሪዎቹን፣ ሰራዊቱን፣ የፖሊስና የአካባቢ ጥበቃውን መሳሪያ ማስፈታቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ለእልቂቱ በር ከፋች ነበር፡፡
እግዚአብሔር ምድርን ከዘረጋ በኋላ በምድር ላይ ያሰፈነው ስርዓት እንደሆነ የሃይማኖት መጽኃፍት ይገልጻሉ፡፡ ስርዓት በተዘረጋበት ዓለምም ላይ ከፍጡራን ሁሉ እጅግ የላቀውን ክቡር የሆነው የሰው ልጅ በበላይነት እንዲኖርበት እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖአል፡፡ ኢ-አማኒ በሆኑ ሰዎችም ዘንድም ስለ ሰው ልጅ ክቡርነት ልዩነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ በሁላችንም ዘንድ የተከበረና የጋራ ስምምነት የተደረሰበት እምነት ግን ሁሌ ሲፈተን እንደማየት የሚከብድ ነገር የለም፡፡
ዛሬ ላይ ኢህአዴግ በቁሳዊ ብክነትና በሃብት ዘረፋ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ዘመቻ እያደረገ ነው፡፡ ሙስናን መታገል የሚያስመሰግን ስራ ነው፣ ነገር ግን ለነዚህ ሁሉ ዜጎች እልቂት ምክንያት የሆኑ ሹመኞችና ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት ያለባቸውን ተቋማት የሚመሩ ሃላፊዎች የተጠያቂነት ጉዳይ ላይ ግን ባለቤት ለማበጀት ፍላጎት አይታይም፡፡ የሙስና ትግሉና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ጥረቱ የሰው ልጅን ክቡርነት ለማረጋገጥና የሕልውናውን ልዕልና ለማስጠበቅ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን፣ የሙስና ትግሉም ሆነ የመልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ውጣ ውረዱ በስልጣን ለመቆየት ከሚደረግ ትግል ዘልቆ ሊሄድ አንደማይችል ግልጽ ነው። ከቁሳዊ ጉዳይ ይልቅ በኃይማኖት፣ በሞራልም ሆነ በሕገ መንግስቱ ቅድሚያ ለሚገባውና ለተሰጠው ከቁሳቁስም የሰው ልጅ ሕይወት ክብርና ቅድሚያ ይሰጥ፡፡
ወደ ሃሳቤ ማጠቃለያ አነሳዋለሁ ወደአልኩት ጉዳይ ልምጣ፡፡ ሰሞኑን ከግራም ከቀኝም የሚነሳውን ምሬትና ቂም ተበቃይነት ላጤነው፣ የሰው ልጅን ክቡርነት ከማስቀደምና የሰው ልጅን ልዕልና ማዕከል ከማድረግ የታላቅነት መንፈስ ይልቅ ደርሶ ተደፈርንና ተጠቃን በሚል የተሸናፊነት ስነልቦና  ዙርያ የሚያጠነጥን  የእልቂት ደጋሽነት አዙሪት ውስጥ መሆናችንን መረዳት አያዳግተውም፡፡  ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት የሚገባው አዕምሮአችን፣ ጦር ለመስበቅ የገነባው ፍላጎት ምን እየተፈታተነው በዚህ ደረጃ እንዳሽቆለቆለ ለመረዳት አዳጋች ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግስት ተወካዮች “እያሳደድን እንቀጣለን” ሲሉ እንደ መስማት አስፈሪ ነገር የለም፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ ድርጊት የአሁኑን አያህል  እንጂ በተደጋጋሚና በተለያየ ጊዜ ይፈጸም እንደነበረ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው እያስታወሱት ነው፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ እውነታው ይህ ከነበረ የመጀመርያው ጥያቄ መሆን ያለበት መንግስት ወይም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ለጉዳዩ እልባት ከመስጠት አኳያ እስከ ዛሬ የት ነበሩ የሚል መሆን ሲገባው፣ “አባረህ በለው” የሚለው የጦረኝነት ጥሪ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ስነልቦና አሳዛኝ ነው፡፡
እርግጥ ነው የታሰሩትን ዜጎቻችንን ማስለቀቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አሌ የምንለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በተሻለ ደረጃ የጦር መሳርያ የታጠቀ በመሆኑ ብቻ ሰራዊት አዝምቶ የታገቱትን ለማስመለስ በሚል እልህ፣ እልቂት መደገሱ ግን ህሊና ሊቀበለው የሚችል ጉዳይ አይደለም። ዓለም በዚህ መንገድ የምትመራ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ፣ ቻይን፣ ጃፓንና ፈረንሳይ ሌሎችንም ጨምሮ ዜጎቻቸው በታፈኑ ቁጥር ስንት አይነት ጦርነትና ወረራን ባሳዩን ነበር። የኢትዮጵያ መንግስትም የታገቱ ዜጎችን ለማስመለስ ማንኛውም የዓለም መንግስት እንደሚያደርገው፣ቅድሚያ ማድረግ ያለበት ከደቡቡ ሱዳን መንግስትና ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመተባበር መፍትሄ መሻት ነው፡፡
መንግስትና በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በተለይ ደግሞ የኢህአዴግ ደጋፊዎች  በተቃራኒው እየጋለቡት ያለው “ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት” የሚል ዓይነት በኋላቀር ስነልቦና የሚመራ የጦርነት ዘመቻ፣ በውጤቱ የበቀል ጥማቸውን ያረካ እንደሆነ እንጂ የሃገራችንን በጎ ታሪክ የሚያጎድፍና የእልቂትና የጨፍጫፊነት ምዕራፍ ከማከል የዘለለ ሚና እንደማይኖረው ማሳሰብ ያስፈልጋል የሚል አምነት አለኝ፡፡  ይህ ከኢህአዴግ ካድሬዎች እየሰማነውና እያየነው ያለው የመጣሁባችሁና አትችሉኝም አይነት ስነልቦና ሃገር ውስጥ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችም ላይ የለመድናቸው ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ኢህአዴግ እንደ መንግስት ወሳኝ ሕገ መንግስታዊ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶቹን በቅጡ መወጣት ሲያቅተው ወይም የደረሰውን ጥፋት ለማድበስበስ ሲፈልግ፣ “ያዙኝ ልቀቁኝ፤ አሳያችኋለሁ” ማለቱ ድርጅታዊ ባሕል ነው፡፡
ኢህአዴግ ዛሬ ላይ ደርሶ ድንበር አቋርጦ በመሄድ በግዢ ባሰባሰበው መሳርያ ተማምኖ በሌሎች ያውም እጅግ ኋላ ቀር  የሆኑ ሕዝቦችን በጀት፣ በመድፍና በታንክ እየታገዘ ሌላ ፍጅት መጋበዙ፣ በእኔ እምነት ዘመኑ የማይፈቅደው ሌላ ዓይነት ጭካኔ ነው፡፡ በመጀመርያ በዚህ ዘመቻ አማካኝነት የሚገኝ አንድም ለውጥ አይኖርም፡፡ ምናልባትም ታግተው የተወሰዱት ላይ ተጨማሪ እልቂትን ላለመጋበዙም ማረጋገጫ የለም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወረራውን የፈጸሙት ኃይሎች  ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከአካባቢው ሰላማዊ ሕዝብ ጋር መቀላቀላቸው ስለማይቀር ወረራው ሌላ ጭካኜ የተሞላበት የሰላማዊ ዜጎችን እልቂት ላለማስከተሉ እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል፡፡    
ሌለው አስገራሚ ጉዳይ እንደተለመደው የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ የማህበራዊ ድረገ-ጾች በተፈጠረው ንዝህላልነት የተከሰተው እልቂት በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር  በድጋሚ  እንዳይከሰት አስተማሪ በሆነ መልኩ አጥቂዎቹና ንዝህላሎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከማበረታታት፣ ገንቢ ተጽእኖ ከመፍጠር ወይም ወደፊት እልቂቱ የማይደገምበትን መንገድ ከመሻት ይልቅ ስለ በቀልና የሃዘን ቀን ትኩረት ሰጥተው በሰፊው ሲደሰኩሩ ነበር፡፡ አዎ፡፡ እራሳቸውን መከላከል ሳይችሉ የተፈጁት ዜጎቻችን ተገቢውን ሃዘኔታ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ በዘመናዊ መንገድ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ አደርጎ ከንፈር መምጠጥ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከሚቸረው የከንፈር መምጠጥና የሞራል ካሳ ጎን ለጎን በኢኮኖሚያዊ ካሳም የዜጎቻችንን እንባ ማበስ ይስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ ተገቢውን ካሳ ከመክፈል ባሻገር፣ እልቂቱ የተከሰተበትን ክፍተት አጣርቶ  ተጠያቂውን በመቅጣት፣ቀሪዎቻችንም ወይም ያልሞትነው ተረጋግተን ሕይወታችንን ለመምራት እንድንችል ለሁሉም ነገር ባለቤት ሊበጅለት ይገባል። ዜጎቻችንን ለዚህ አደጋ የዳረጉ ንህዝላሎች ወደፊትም ለዚህ አይነት አደጋ ወይም ከዚህ ለከፋ አደጋ ማለትም አንደ አልቃይዳና አይሲስ ላሉ ነፍሰ በላዎች አሳልፈው እንደማይሰጡን መተማመኛ ያስፈልገናል፡፡ መተማመኛው ደግሞ የሕግና የሞራል የበላይነት፣ መንግስት በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው፡፡
ዜጎቻችን በእልቂቱ የደረሰባቸው መከራ ቤተሰቦቻቸውን በሞት በመነጠቃቸው ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ለአቅም አዳም የደረሱና ሰርተው የሚደጉሟቸውን የኑሮአቸውን፣ የሕይወታቸውን ማገርና ወጋግራ አባወራዎቻቸውን የተነጠቁ በመሆኑ ለዘለቄታው የሚቆይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም በሕይወታቸው ላይ ደርሶባቸዋል፡፡
በዋነኛነት የሱዳን መንግስት በተጓዳኝ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ሕይወት ከአደጋ ለመከላከል ካለበት ሕገ-መንግስታዊ ግዴታ በመነሳት፣ ለተፈጠረው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ተገቢውን ካሳ በመክፈል ለሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ተገቢው ሁሉ ይደረግ፡፡ አሟሟታቸውም ከንቱ፣ ደማቸው ደመ ከልብ አይሁን ፡፡

ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል 3 ወረዳዎች ከደቡብ ሱዳን ድንበር ጥሰው የገቡ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት 208 ዜጎች ሲገደሉ፣ 108 ህፃናትና እናቶችም ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 20ሺ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ከ2ሺ በላይ ከብቶችም ተዘርፈዋል፡፡ ጥቃቱን ተከትሎም መከላከያ ሰራዊት ደቡብ ሱዳን ድረስ ገብቶ 60 ያህሉን ጥቃት ፈጻሚዎች መግደሉ ተነግሯል፡፡ ይህን አሰቃቂ ጥቃት
በተመለከተ አስተያየት የሰጡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የድንበር አካባቢ የደህንነት ጉዳዮች አስጊ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የሀገሪቱ የድንበር አጠባበቅ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ አለበት የሚሉት ተቃዋሚዎች፤ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት በሚገባ እየጠበቀ አይደለም ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

“ድንበር መጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት ነው”
(አቶ ነገሠ ተፋረደኝ -
የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)
በጋምቤላ ለሞቱት ንፁሃን መንግስት ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ ድንበር መጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ድንበሩ ይጠበቅ ነበር። ከድንበር ጥበቃ ጎን ለጎን ራሱን እንዲጠብቅ መንግስት ህብረተሰቡን ማደራጀት አለበት። ራሳቸውን የሚጠብቁበት የተመዘገበ ትጥቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡
መንግሥት ለሰራው ጥሩ ነገር እንደሚመሰገነው ሁሉ ለተከሰተው ጥፋትም ይወቀሳል፤ ለዚህም ጥፋት ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ መንግስት ታፍነው የተወሰዱ ዜጎችን ለማስመለስ የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የአለማቀፍ ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ፣ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በማስመለሱ ጥረት ተባባሪ መሆን አለባቸው፡፡
እኛ እንደ ማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት ይሰማናል፤አንድም ኢትዮጵያዊ በከንቱ ህይወቱ ማለፍ የለበትም፤ ታፍኖም ሊወሰድ አይገባም፡፡

“በየትኛውም ድንበር አካባቢ የደህንነት ስሜት የለም”
(አቶ ገብሩ አስራት - የአረና ፓርቲ አመራር)
መንግስት እንደ ሌላው ዜጋ ሁሉ ሃዘኑን ብቻ እየገለፀ ነው ያለው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው ልክ የእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ የመንግስት አንዱና ዋናው ተግባር የዜጎቹን ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ይሄ እየሆነ አይደለም፡፡ በኦሮሚያም በትግራይም፣ በአማራም፣ በጋምቤላም ሆነ በሌሎች ቦታዎች መንግስት ይሄን ኃላፊነቱን እንደዘነጋ እየታየ ነው፡፡ ዛሬ የተጨፈጨፉት ሰዎች፣ቀድሞ ታጣቂዎች ስለነበሩ ራሳቸውን በሚገባ ሲከላከሉ ነበር፡፡ መንግስት ነው ትጥቃቸውን ያስፈታው። መንግስት ይሄን ሲያደርግ በቂ ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባ ነበር፡፡
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንበሩ ሰፊ ስለሆነ ቦታ እየቀያየሩ ያጠቃሉ ያሉት መልስ አይሆንም፡፡ እነዚህ ሰዎች በ3 ወረዳዎች ላይ ነው ጥቃት የፈፀሙት፡፡ ድንበሩ ለምን አይጠበቅም? በሌላ ሀገር ወታደር ዋና ስራው ድንበር መጠበቅ ነው፡፡ እንደኔ በዚህ ጉዳይ መንግስት ዋንኛ ተጠያቂ ነው፡፡ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ሰው ካለቀ በኋላ እርምጃ መውሰዱ ላይ አይደለም፡፡ ዋናው አደጋው እንዳይከሰት መከላከሉ ነው፡፡
እንደ እኔ መንግሥት የሚገባውን ያህል እየሰራ አይደለም፡፡ የዜጎች ደህንነት በሚገባ እየተጠበቀ አይደለም፡፡ በየትኛውም ድንበር አካባቢ የደህንነት ስሜት የለም፡፡ “አልተዘጋጀንም ነበር፤ ድንገተኛ ነው” የሚል ነገር ፈፅሞ መልስ መሆን አይችልም፡፡ የእነዚህ ዜጎች ጭፍጨፋ እንዲህ በቀላሉ መታለፍ ያለበት ጉዳይም አይመስለኝም፡፡

“የውጪ ግንኙነት ፖሊሲያችን ሊፈተሽ ይገባል”
(ዶ/ር ጫኔ ከበደ - የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)
ኢዴፓ በአጠቃላይ በተፈጠረው አደጋ ሃዘኑ ጥልቅ ነው፡፡ መንግስት እየተከተለው ያለው የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ እንደገና ትኩረት ተሰጥቶት ሊፈተሽ የሚገባ ነው፡፡ ክልሎች ከአጎራባች ሃገሮች ጋር የሚዋሰኑ በመሆኑ በተለይ ታዳጊ ክልሎች ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበትን ስልት መቀየስ ያሻል፡፡ በክልሎቹ መንግስታት የሚመራ የሚሊሻና ታጣቂ ኃይል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የጋምቤላን ጉዳይ ስንመለከት፣ መንግስት የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታቱ ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ሌሎች ክልሎችም ራሳቸውን የሚከላከሉበት መንገድ እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ከአሁን በፊትም በየድንበር አካባቢው ግጭቶችና የከብት ዝርፊያ አለ። ይሄኛው ግን ከዚያም አልፎ ክቡሩን የሰው ህይወት የነጠቀ መሆኑ እንደ ማንቂያ ደውል ሊታይ ይገባዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ችግሮቹ አሉ፡፡ በኤርትራ ተዋሳኞች፣ በኬንያ፣ በሱዳን ድንበሮች ያለው ሁኔታ ደህንነቱ በደንብ የተረጋገጠ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በፊት የኤርትራ ታጣቂዎች ሰዎችን አፍነው ወስደዋል፡፡ በኛ በኩል ድንበሩ በሚገባ እየተጠበቀ ነው ብለን አናምንም፡፡ ሰፊ ድንበር ጠባቂ ኃይል ሊደራጅ ይገባዋል፡፡
ይሄ አደጋ ዘግናኝና አሳፋሪ ነው፡፡ የሀገራችንን ገፅታም የሚያበላሽ ነው፡፡ የምንከተለው የውጭ ፖሊሲ በተለይ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያለው የዜጎችን ደህንነት የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡ ድንበሮች ክፍት የሚሆኑት ለውጭ ሀገር ዜጋ እንጂ ለኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ ከጎረቤት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች እንዳሻቸው ሲሆኑ፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ከድንበር አልፈው በሰላም መሃል ሀገር ድረስ መኪኖቻቸውን ይዘው መጥተው እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ በኬንያ በኩል ኬንያውያን እስከ ያቤሎ ድረስ መጥተው ጨፍረው የሚሄዱበት ሁኔታ አለ። በአሶሳ በኩልም ሱዳኖች በተመሳሳይ እንዳሻቸው ይወጣሉ ይገባሉ፡፡ የኛ ዜጎች ግን ከድንበር 30 ኪ. ሜትር እንኳ ርቀው ከሄዱ ይታሰራሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የውጭ ፖሊሲያችን ውጤት ነው፡፡ እኔም የዚሁ ችግር ሰለባ የሆንኩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሞያሌ ላይ ወደ ኬንያ ድንበር ገብቼ እቃ ገዝቼ ስመለስ 12 ሰዓት ሆኗል ተብዬ ታስሬያለሁ፡፡ በአንፃሩ የነሱ ሰዎች ምሽቱን እንዳሻቸው ሆነው ከኢትዮጵያ ወደ ሃገራቸው ኬላ አቋርጠው ሲመለሱ በአይኔ አይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ረገድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነትና የዜጎቻችንን መብት የምናስጠብቅበት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ነው ያስተዋልኩት፡፡
ከሰሞኑ በጋምቤላ ለደረሰው አደጋ ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባ አካል መኖር አለበት፡፡ የሱዳን መንግስት ወይም የአማፂ ቡድን ወይም ሌላ ቡድን ካለ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡ እንደኔ ግን የደቡብ ሱዳን መንግስት ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል፡፡ ሰራዊታችን ድንበር ጥሶ ህፃናቱን ለማስመለስ ወደ ደቡብ ሱዳን ቢገባ፣ ሉአላዊነትን በመዳፈር ሊከሱን ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገሪቱ መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ ህፃናቱ እንዲመለሱ ማድረግ ያሻል፡፡ አልያም ወደ አለማቀፍ ህግ መሄድ ተገቢ ነው፡፡  

ድንበሬን በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠዋል በሚል ታንዛኒያ የእርስ ፍርድ ወስናባቸው የቅጣት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ 74 ኢትዮጵያውያንን በኬንያ ድንበር ላይ ማራገፏ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ መፍጠሩን “ዘ ስታንዳርድ” የተባለው የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡  
የታንዛኒያ መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች እስራቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ሲገባው በኬንያ ድንበር ላይ በሚገኝ በረሃ ላይ መጣሉ አግባብ አይደለም ሲል የወቀሰው የኬንያ መንግስት፤ ኢትዮጵያውያኑን ወደ ታንዛኒያ መልሶ እንደሚልክ አስታውቋል፡፡
“ኬንያ የታንዛኒያን ችግር የምትሸከምበት ምክንያት የለም፤ አለማቀፍ ህግም ይህን አይፈቅድም” ብሏል፤ የኬንያ መንግስት - “ዘ ስታንዳርድ” እንደዘገበው፡፡

“የሥራ ልምድ አፃፉ ማለት ሥራ ለቀቁ ማለት አይደለም
   የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በርካታ ሰራተኞች ከስራ ለመልቀቅ ማኮብኮባቸውን የአዲስ
አድማስ ምንጮች ገለፁ፡፡ በኢቢሲ 10ኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው የስራ ልምድ ማፃፊያ ክፍል ሰሞኑን የስራልምድ በሚያፅፉ ሰራተኞች ተወጥሮ እንደሰነበተ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኢቢሲ የሚከፍለው ደሞዝ መጠን፣ ለሰራተኞች እንደ ትራንስፖርትና የመኖሪያ ቤት አበል አለመክፈሉና አጠቃላይ ለሰራተኛው የሚደረገው እንክብካቤ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ሠራተኞቹ ከስራ ለመልቀቅ ምክንያት ሆኗቸዋል የሚሉት ምንጮች በአሁን ሰዓት የተሻለ ክፍያ የሚከፍሉ አማራጭ የሚዲያተቋማት እየተስፋፉ በመምጣታቸው የሰራተኛውልብ አኮብኩቧል ብለዋል፡፡ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የኢቢሲጋዜጠኛ በሰጠው አስተያየት፤ ኢቢሲ በአመራርላይ ላሉ የተቋሙ ሰራተኞች የነዳጅ፣ የትራንስፖርትየሃላፊነትና የህክምና አበል እንደሚከፍል ገልፆስራውን በአብዛኛው ደክመው ለሚሰሩትና ውጣውረድ ለሚበዛባቸው የበታች ሰራተኞች እነዚህ ጥቅማ ጥቅሞች አለመሰጠቱ ሰራተኛው ሌላአማራጮችን እንዲመለከት እንዳደረገው ተናግሯል።ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ፤ በተሰጠው የስራሃላፊነት ከሶስት አመት በፊት በተደረገለት ጥቂትየደሞዝ ጭማሪ ብቻ እስከዛሬ ድረስ እንደሚሰራጠቁሞ ያለ ጭማሪ፣ ያለ ጥቅማ ጥቅምና ያለእድገት በስራ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለውና ሌላቦታ ለመወዳደር የስራ ልምዱን በእጁ ማስገባቱን
ገልጿል፡፡ሌሎቹ አስተያየታቸውን በጋራ የሰጡን የተቋሙሰራተኞች በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተመረሰተበትን50ኛ ዓመት ሲያከብር 50ሚ. ብር በጀት ይዞለሰራተኞቹ መኖሪያ ቤት እንደሚያሰራ ቢገልፅምእስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉሌላው ሰራተኛው ተስፋ እንዲቆርጥና ከመስሪያቤቱ ለመልቀቅ እንዲነሳሳ ምክንያት እንደሆነተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተገኘው መረጃ ብቻ ከ35በላይ ሰራተኞች የስራ ልምድ ማፃፋቸውንምምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የእርከን እድገት አድርጉልን፣ጥቅማ ጥቅም ይታሰብልንና መሰል ጥያቄዎችንሰራተኛው በየጊዜው ቢጠይቅም ማኔጅመንቱምላሽ አለመስጠቱን ሰራተኞቹ ገልፀዋል፡፡ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የስራ ሃላፊ፤በዚህ መጠን ሰራተኛው የስራ ልምድ ስለማፃፉመረጃ እንደሌላቸው ጠቁመው፤ የስራ ልምድአፃፉ ማለት ስራ ለቀቁ ማለት እንዳልሆነ ገልፀዋል።ድርጅቱ የራሱ የሆነ የደሞዝ ስኬል፣ የደረጃእድገትና የደሞዝ እርከን ጭማሪ እንዳለውና ይህምበተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ መሆኑን የገለፁትሃላፊው፤ አንድ ሰራተኛ በድርጅቱ ስኬል መሰረትደሞዝ እየተከፈለው ከዚያ እጥፍ ክፍያ ቢያገኝናየተሻለ ፍለጋ ቢሄድ ጥፋተኛ የሚባልበት ምክንያትየለም ብለዋል፡፡ ሃላፊው፤ እስካሁን ደሞዝ አነሰኝ፤እንዲህ አይነት ችግር ደርሶብኛል ተበድያለሁ ብሎያመለከተ ሰራተኛ እንደሌለና ምንም አይነት ቅሬታእንዳልቀረበም ጨምረው ገልፀዋል፡፡



   በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የቶታል “ስታርት አፐር” የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ከ350 ሺ ብር እስከ 150 ሺ ብር የተሸለሙ ሲሆን ውድድሩም ሆነ ሽልማቱ ለበለጠ ፈጠራ እንዳነቃቃቸው ተሸላሚዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
 በወድድሩ በኢንተርኔት የማስጠናት አገልግሎት (tutor) የሚሰጥ ተቋም የፈጠሩት ዶክተር ሄኖክ ወንድይራድ አንደኛ ሲወጡ፣ በጸሃይ ሃይል የሚሰራ የሞባይል ስልክ ቻርጀር የሰሩት አቶ ቢኒያም ተስፋዬ ሁለተኛ ወጥተዋል። በጸሃይ ሃይል የሚሰራ የትራፊክ መብራት፣ የሞባይል ቻርጀር፣ የቤት ውስጥ መብራት፣ የሶላር ጄኔሬተርና እስከ መቶ ሃያ እንቁላል የሚፈለፍል የሶላር ኢንኩቤተር የፈጠሩት አቶ ቃለ ዳዊት እስመአለም ደግሞ የሶስተኛነት ደረጃን አግኝተዋል፡፡ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡት አሸናፊዎች፡- የ350 ሺ፣ የ200ሺ እና የ150ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።
የቶታል “ስታርት አፐር” ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ኢብራሂም ማማ፤አሸናፊዎቹ በቀጣይ ፈጠራቸውን እንዲያሳድጉ ተከታታይ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል። ውድድሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን በመግለጽም ወደፊት በየዓመቱ መሰል ውድድሮች በማካሄድ ቶታል ፈጠራን የማበረታታት እንቅስቃሴውን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አሸናፊዎቹ ከአገሪቱ የልማት አጀንዳ ጋር የተጣጣሙ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማምጣት ላይ ናቸው ያሉት ማናጀሩ፤የተሸላሚዎቹ ፈጠራዎች በትምህርት ጥራት፣ በትራፊክ ዘርፍና በሃይል አቅርቦት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አቅምን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤የቶታል ኢትዮጵያን ተግባርና መሰል ፈጠራን የሚያበረታቱ ድርጅቶችን አድንቀው፤መንግስት በተቻለው አቅም ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብተዋል።
“አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ያነገቡና የራሳቸውን ቢዝነስ ለማቋቋም የተነሳሱ ወጣቶች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተስፋዎች ናቸው” ብለዋል፤ ሚኒስትር ዴኤታው።
አንደኛ የወጣው የፈጠራ ሥራ በ34 የአፍሪካ አገራት በተካሄዱ የቶታል “ስታርት አፐር” ወድድሮች አንደኛ ከወጡ ሌሎች ፈጠራዎች ጋር እንደሚወዳደርም ተገልጿል።

- የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ተሸርቦብኛል፤ እስከመጨረሻው እታገላለሁ ብለዋል
በተለያዩ ውንጀላዎች የመከሰሳቸውና በስልጣን የመቆየታቸው ቀጣይ እጣ፣ ነገ በሚከናወን የምክር ቤቶች የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት የሚወሰንባቸው የብራዚል ፕሬዚዳንት ዲላማ ሩሴፍ፣ ከተጠያቂነት ነጻ ለመሆንና መንበራቸውን ላለማስነጠቅ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ተግተው እንደሚታገሉ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ላይ ያደረሱ በማስመሰል ሃሰተኛ መረጃ አውጥተዋል፣ በሙስና ተዘፍቀዋል፣ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የበጀት ህጎችን ጥሰዋል  በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ፕሬዚዳንቷ፤ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ተቀናቃኞቼ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ያለ አግባብ ስልጣኔን ለመቀማት የሸረቡብኝ ሴራ ነው፤ ድምጽ አሰጣጡ አግባብ ባለመሆኑ እስከመጨረሻው እታገለዋለሁ ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
65 አባላት ያለው የአገሪቱ የኮንግረስ ኮሚቴ ሰኞ ዕለት በአብላጫ ድምጽ ባሳለፈው ውሳኔ በስልጣን ቆይታቸው ላይ ድምጽ እንዲሰጥበት የተወሰነባቸው ፕሬዚዳንት ዲላማ ሩሴፍ፣ የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ሸርበውብኛል ብለው ከጠቀሷቸው ፖለቲከኞች መካከል ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሚሼል ቴምር እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ዲላማ ሩሴፍ ከሚመሩት ጥምር መንግስት ውስጥ ራሳቸውን ማግለላቸውን ማክሰኞ እለት ያስታወቁ ሁለት ፓርቲዎች፣ ነገ በሚደረገው ድምጽ አሰጣጥ ላይ ሴትዮዋ ስልጣን ይልቀቁ በሚል ድምጻቸውን እንደሚሰጡ መግለጻቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ከስልጣን እንዲለቁ የሚፈልጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ብራዚላውያን ውሳኔውን በደስታ መቀበላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ የፕሬዚዳንቷ ደጋፊዎች የሆኑ በርካቶችም ጉዳዩን የፖለቲካ ጠላቶች የፈጸሙት ህገወጥ የስልጣን ቅሚያ ነው በማለት አውግዘውታል ብሏል፡፡
በአመት 2015 ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ሸቀጦች ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ፣ የብራዚል ኢኮኖሚ ባለፉት ከ30 በላይ አመታት ታሪኩ በከፋ ቀውስ መመታቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ የዋጋ ግሽበት ባለፉት 12 አመታት ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱንና የስራ አጥነት በ9 በመቶ ማደጉን፣ ይህም የፕሪዚዳንቷን አስተዳደር ክፉኛ ማስተቸቱን ገልጧል፡፡
ነገ አመሻሽ ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው በአገሪቱ ምክር ቤቶች በየደረጃው የሚከናወኑ ድምጽ አሰጣጦች አጠቃላይ ውጤት፣ የፕሬዚዳንቷን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ይወስነዋል ተብሏል፡፡

 የአለማችን ረጅሙ ህንጻ የሆነውና 828 ሜትር ቁመት ያለው ቡርጂ ከሊፋ መገኛ የሆነቺው ዱባይ፣ በቁመቱ አዲስ የአለም ክብረወሰን እንደሚያስመዘግብ የተነገረለትን አዲስ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በ1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት ማቀዷን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ እጅግ ያማረ የስነ-ህንጻ ጥበብ የተገለጠበት ነው የተባለውን የዚህን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት የያዘው “ኢማር ፕሮፐርቲስ” የተባለው ተቋራጭ ኩባንያ ስለሚገነባው አዲስ ህንጻ ቁመት ባይገልጽም፣ ግንባታው በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
20 የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ወለሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የመኖሪያ ክፍሎች፣ ሆቴልና ሌሎችን ይይዛል የተባለውንና የዱባይን ገጽታ ሙሉ ለሙሉ ሊያሳይ የሚችል ማማ ያለውን ይህን ህንጻ ዲዛይን ያደረገው ስፔናዊው የኪነ-ህንፃ ባለሙያ ካልትራቫ ቫልስ ሲሆን፣ የሚገነባውም በዱባይ መካከለኛ ስፍራ ላይ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
በቁመቱ እርዝማኔ የአለማችንን ክብረወሰን ይዞ የሚገኘው የዱባዩ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ቡርጂ ከሊፋ፣ ለግንባታው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበትና በ2010 መጀመሪያ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 - የ8 አመት ህጻንን ለአጥፍቶ መጥፋት አሰማርቷል

     በምዕራብ አፍሪካ አገራት የሽብር ተግባራት መፈጸሙን አጠናክሮ የቀጠለው ጽንፈኛው ቡድን ቦኮ ሃራም፤ በተለያዩ አካባቢዎች ለአጥፍቶ መጥፋት ተግባር የሚያሰማራቸው ህጻናት ቁጥር ባለፈው አመት በ11 እጥፍ እንዳደገ ዩኒሴፍ መግለፁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ዩኒሴፍ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ እንዳለው፣ ቦኮ ሃራም ባለፉት ሁለት አመታት በናይጀሪያ፣ በካሜሩንና በቻድ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ላይ ካሰማራቸው አጥፍቶ ጠፊዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ አብዛኞቹም ሴቶች ናቸው፡፡ ቦኮ ሃራም ለሽብር ተግባሩ የሚመለምላቸውና ለጥቃት የሚያሰማራቸው ህጻናት ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በ2014 አራት ህጻናትን በአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ላይ ያሰማራው ቡድኑ፣ ድርጊቱን በማጠናከር ባለፈው አመት 44 ህጻናትን ለጥቃት ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡ ቡድኑ በአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ካሰማራው ህጻናት መካከል ዝቅተኛውን ዕድሜ የያዘው የ8 አመት ህጻን እንደሆነ ዩኒሴፍ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ቡድኑ በናይጀሪያ፣ ካሜሩን፣ ቻድ እና ኒጀር በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ሳቢያ 1.3 ሚሊዮን ህጻናት ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውንና 670 ሺህ ያህሉም ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን አመልክቷል፡፡

 - የአውሮፓ ታላላቅ ባንኮች የከፋ ችግር ውስጥ ገብተዋል
     - የእንግሊዝ ከህብረቱ አባልነት መውጣት፣ በአህጉሪቱ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ተብሏል

    አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ የአውሮፓ አህጉር በገንዘብ ቀውስ ልትመታ እንደምትችል ሰሞኑን ባወጣው የግማሽ አመት አለማቀፍ የገንዘብ ሁኔታ ሪፖርት፣ ማስጠንቀቁንና በአለማቀፉ የገንዘብ መረጋጋት ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ተባብሰዋል ማለቱን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡ በአውሮፓ አገራት ከሚገኙ ባንኮች አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ትርፋማ ሆነው እንዳይቀጥሉ በሚያግዷቸው የከፉ ችግሮች መተብተባቸውን ያስታወቀው ተቋሙ፣ በአገራቱ ባንኮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ በአህጉሪቱ በተከሰቱ የባንክ ቀውሶች ክፉኛ ከተጎዱት መካከል፣ የግሪክ፣ የጣሊያንና የፖርቹጋል ባንኮች እንደሚገኙባቸው ያስታወሰው ተቋሙ፣ እየተባባሰ የቀጠለው የገንዘብ ቀውሱ በመላ አህጉሪቱ የሚገኙ ባንኮችን ተጠቂ ሊያደርግ እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ባወጣው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ሪፖርት፣ ለረጅም ጊዚያት አዝጋሚ ሆኖ የዘለቀው የአለማችን ኢኮኖሚ እድገት ዘንድሮም 3.2 በመቶ ብቻ ሊያድግ እንደሚችል በመጥቀስ፣ የአለም ኢኮኖሚ ለአደጋ የበለጠ ተጋላጭ ሆኗል ማለቱን ዘግቧል፡፡
በዘንድሮው አመት ከአለማችን አገራት የኢኮኖሚ እድገቷ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ የምትጠበቀው ናይጀሪያ ናት ያለው ዘገባው፤ ብራዚል፣ ሩስያና ሌሎች በርካታ የአለማችን አገራትም ዘንድሮ ያስመዘግቡታል ተብሎ ከተገመተው የኢኮኖሚ እድገት ያነሰ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል መባሉንም ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መውጣቷ በአካባቢው አገራትና በአለማቀፍ ደረጃ የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ሲል አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ማስጠንቀቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የእንግሊዝ ከህብረቱ አባልነት መውጣት ለረጅም ጊዜ የዘለቁ የንግድ ግንኙነቶችን ከማቃወሱ በተጨማሪ ለእንግሊዝም ሆነ ለተቀሩት የአውሮፓ አገራት ፈታኝ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ያለው ተቋሙ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በኢንቨስተሮች ዘንድ ያለመተማመን ስሜት መፍጠሩንም ገልጧል፡፡