Administrator

Administrator

በሀገራችን እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መጓደልና የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ተከትሎ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ታስቦ የተመሰረተው “ዩቶፒያስ ስቱደንትስ” አጋዥ የትምህርት መተግበሪያ አገልግሎት ላይ መዋሉን የድርጅቱ ባለቤቶች ገለፁ። የድርጅቱ ባለቤቶች ይህን የገለፁት ትላንት ረፋድ ላይ በዓለም ሲኒማ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።በ2015 ዓ.ም የተመሰረተው “ዩቶፒያስ ስቱደንትስ”፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀላል፣ ምቹና ቀልጣፋ የሚያደርጉ አሰራሮችን እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን፣ በይፋ የተዋወቀው መተግበሪያም ከ9ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚያገለግል እንደሆነ ተገልጿል።
መተግበሪው የስድስት ዓመት (ከ2017-2022 ያሉ) የ12ኛ ክፍል የመግቢያ ጥያቄዎችን ከእነመልሶቻቸው፣ ለጥናት የሚያገለግሉ ከ9-12ኛ ክፍል ያሉ አጋዥ መፅሐፍትን፣ 24 ሰዓት ማናቸውንም ጥያቄዎችን የሚመልስ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚዘጋጁ ሽልማት የሚያስገኙ ውድድሮችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን፣ መተግበሪያውን ከጉግል ፕሌይ ስቶር በማውረድና  ለአገልግሎቱ በዓመት አንድ ብር በመክፈል መጠቀም እንደሚቻል ተገልጿል።
መተግበሪያው በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና በኢንፎሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ተገምግሞ ያለፈና ለተማሪዎች አጋዥ እንደሚሆን ታምኖበት አገልግሎት ላይ የዋለ መሆኑም ታውቋል።

ካፒታሉን ወደ 1 ቢሊዮን ብር አሳድጓል

ብሬክስሩ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር ባለፉት አራት ዓመታት ከ41 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሰብዕና ለውጥ ሥልጠና መስጠቱንና በስልጠናው በርካታ በኢኮኖሚ ራሳቸውን የለወጡ ዜጎች ማብቃቱን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ይህንን የገለፀው ባለፈው ረቡዕ ጥር 15 ከሰዓት በኋላ በሸራተን አዲስ ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ የተመሰረተበትን 4ኛ ዓመት በዓል  ባከበረበት ወቅት ነው፡፡ብሬክ ስሩ ትሬዲንግ በ2012 ዓ.ም “ቅን” (Genuine) በተሰኘ 17 ባለ ራእይ ሰዎች ጥምረት የተቋቋመ ሲሆን፣ አላማውም ባለ ራዕይ፣ ቅን፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድን መፍጠር እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱል ፈታህ ሁሴን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ በአራት ዓመት ጉዞው ዜጎች በአዎንታዊ መልኩ ሰብዕናቸውን በመገንባት በኢኮኖሚ ያደጉና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ እየተጋ እንደሚገኙ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ብሬክስሩ በ2.4 ሚ ብር ካፒታል ተነስቶ በአራት ዓመታት ውስጥ ካፒታልን ወደ 1 ቢሊዮን ማሳደጉንና አሁንም አክሲዮን በመሸጥ ላይ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ ከሰብዕና ግንባታ በተጨማሪም ወደ ተለያዩ ቢዝነሶች እየተሰማራ መሆኑንና በቅርቡ አንድ ት/ቤት መክፈቱን እንዲሁም “የኔ” የተሰኘ የሰብዕና ግንባታ ስልጠና ፕሮጀክት ማቅረቡንና በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ እንደሚሰማራም ተናግረዋል፡፡
በብሬክስሩ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር አራተኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የድርጅቱ ከፍተኛ ሀላፊዎችና አባላትን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡

ይህ አልበም ቆየት ያሉ የሙዚቃ ስራዎች ድጋሚ የተሰሩበት እንደሆነ ባለፈው ቅዳሜ "የቅዳሜ ጨዋታ " ፕሮግራም ላይ መናገሩ ይታወሳል።
ሙዚቃቸው ድጋሚ ከተሰራላቸው አንጋፋ ድምፃዊያን መካከል ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ ፣ ድምጻዊ እሳቱ ተሰማን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል ተብሏል።

"ህልም ነበረኝ፤ ሁለት አልበም በአንድ ቀን ማውጣት"

ሙዚቀኛ ሮፍናን ኑሪ፤ በአንድ ቀን "ሀራንቤ" እና "ኖር" የተሰኙ ሁለት አልበሞችን፣ "ዘጠኝ" በሚል አብይ ርዕስ ውስጥ ለአድማጮች እንደሚያደርስ ተጠቆመ፡፡

"ይህ አልበም ማሳረጊያ ፕሮጀክቴ ነው። በጣም ደክሜበታለሁ። ቴክኒካል ጉዳዮችን ጨምሮ ብዙ የተለፋበት ነው። የኔን እድገት የምታዩበት አልበም  ነው" ብሏል፤ድምጻዊው።

አክሎም ሲናገር፤ "ህልም ነበረኝ፤ ሁለት አልበም በአንድ ቀን ማውጣት" ብሏል፡፡

በ"ዘጠኝ" አብይ ርዕስ ውስጥ ያሉት ሁለቱ አልበሞች፣ በአጠቃላይ ሃያ አንድ ሙዚቃዎችን ይዘዋል ተብሏል።

በአልበሞቹ ላይ ሀይሌ ሩት፣ ሸዊት መዝገቡ፣ የልጅ ተመስገን ልጆችን ጨምሮ የሀገር ውስጥና የውጪ የሙዚቃ ባለሞያዎች ተሳትፈዋል።

"ሀራንቤ" እና "ኖር" አልበሞች ከሦስት ሳምንት በኋላ ለሙዚቃ አድማጮች እንደሚደርሱ ታውቋል፡፡

አልበሞቹ በሮፍናን ዩቲዩብ ቻናልና በሁሉም የሙዚቃ ማሰራጫ መተግበሪያዎች በኩል ይለቀቃሉ።

ከአልበሙ ውስጥ ለሁለቱ Yሙዚቃ ቪዲዮዎች የተሰራ ሲሆን፤ ከአልበሙ የተወሰደ አንድ የሙዚቃ ቪዲዮ ዛሬ ማታ ለአድማጮች ይደርሳል ተብሏል።

Tuesday, 23 January 2024 20:11

ኢህአፓና ስፖርት part 6

https://youtu.be/k-llnz_sfro?si=Sr1-RWyz4-25MfPi

ይህ ሰው ሁሌም በመረጃ አሰባሰብ፣ በዝግጅት አቀራረቡና በሌሎች ነገሮቹ  ድንቅ ከሚሉኝ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው።
 ሁለገቡ ሰው ገነነ መኩሪያ( ሊብሮ)።
 ሊብሮ የምትለውን ስያሜ ያወጣለት በአብዛኛው የእግር ኳስ አፍቃሪ በአዝናኝነቱ፣ በእግር ኳስ ወዳድነቱ የሚታወቀው የኳስ ሜዳው ሰው ሀይሌ ካሴ ነው። በወቅቱ ጊዮርጊስ ከሜታ አቦ በተጫወቱበት ጊዜ አምስት ተጫዋቾችን አልፎ ግብ  ባስቆጠረበት ጊዜ ነበር የተቀፅላው መነሻ።
ሊብሮ የተወለደው ይርጋለም ከተማ ቢሆንም፣ እድገቱ ግን ሻሸመኔ ቀበሌ 09 ነው ።
በልጅነት ወቅትም እግርኳስ ይወድ የነበረው ገነነ፤ በጊዜው በየ15 ቀኑ አዲስ አበባ  የሚመጡት የሆቴላቸው  ሾፌር አብሮቸው ያቀና ነበር፤ በነበራቸው ቆይታም ካምቦሎጆ ገብተው እግር ኳስ ተመልክተው ይመጡ  ነበር፤ በዚያ  በአፍላነት ጊዜው መሆኑ ነው።
ሌላው የሚገርመው ገኔ ሻሸመኔ ውስጥ ላለ ቡድን  ለAም፣ ለBም፣ ለCም ይጫወት ነበር፤ በአንድ ቀን ውስጥ።
የቀበሌ 09 ቡድንም በወቅቱ የአቶ ሙኩሪያ ቀበሌ ቡድን ይባል ነበር። በጊዜው እሱን ጨምሮ ስድስት ወንድሞቹ እዛ ቡድኑ ውስጥ ይጫወቱ  ነበሩ። እንደዚህ እያለ ነው ወደ እግር ኳስ ተጫዋችነት ያመራው።  ወደ ክለብ ደረጃም መጀመሪያ የመጣው በ1975 ዓ.ም አካባቢ፣ የትምህርት ቤት ውደድሮች ላይ በመታየት ከእነ ታሪኩ መንጀታ፣ አስቻለው ጋር በመሆን ነበር፤ ወደ ሜታ ቢራ የተቀላቀለው።
እዚህ ጋ  በወቅቱ በአጨዋወትና በሌሎች ተዛማጅ ነገሮች  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከአሰልጣኞች ጋር ሙግት ይገጥም ነበር። በጊዜው ሜታን ያሰለጥን ከነበረው ስዩም ጋር ይጋጩ እንደነበር ይጠቀሳል። በእግር ኳስ ተጫዋችነቱ ወቅት እረፍት ሰአቱን በማንበብ ማሰለፍ ይወድ እንደነበር አብረውት የተጫወቱት ይመሰክራሉ።
የሊብሮ ጋዜጣው መነሻ
ከዛ በፊት በበጎ ፍቃደኝነት በተለያየ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ይሰራ ነበር። ከሰራባቸው የህትመት ሚዲያ ውስጥም መረሀ ስፖርት፣ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ውስጥ ይጠቀሳል።
በመቀጠል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ማለትም አበበ ወልደ ፃዲቅ፣ ሁሴን አብድልቀኒ ጋር በመሆን ሻምፕዮን የምትባል የስፖርት ጋዜጣ መስርተው ሰርተዋል።
በማስከተልም የራሱ የሆነችውን ሊብሮ ጋዜጣ አቋቋመ።  የዚህች ጋዜጣ አመሰራረት የሚገርም ነው፤ በተለይ በወቅቱ የነበሩቱ የቦሌ ማተሚያ ስራ አስኪያጂ አሰፋ ከበደ ሊመሰገኑበት የሚገባ ድርጊት ነው። በጊዜው ገነነ የሚያሳትምበት ገንዘብ እጥረት ያጋጥመዋል፤ ሁሉን ነገር ጨርሶ ከሰራ በኋላ ግን እጁን አጣጥፎ ከሰማይ መና አልጠበቀም፤ ወደ ቦሌ ማተሚያ ቤት  ሄዶ ስራ አስኪያጁን ያለበትን ነገር ሁሉ አስረድቶ  በእሳቸው ቀና ትብብር አማካኝነት ጋዜጣዋ ለመጀመሪያ ጊዜ  ለህትመት በቃች። በጊዜውም በጣም ተወዳጅ ጋዜጣ እንደነበረች በጊዜው የነበሩ ሰዎች ያስታውሳሉ፡፡ አብዛኛውን ትኩረት የምታደርገው የሀገር ውስጥ ዜናዎች ላይ ነበር። ለነገሩ አብዛኛዎቹ የዚያን ዘመን ጋዜጦች ትኩረታቸው የሀገር ውስጥ እንደነበር መመልከት ይቻላል።
በህትመት ግን ለ13 አመታት ከብዙ ችግሮች ጋር እየተጋፈጠች ለህዝብ ተደራሽ መሆን ችላ ነበር ። አብዛኛውን ስራ እራሱ  ገነነ ነበር የሚሰራው። የጋዜጣ ስራ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ  የሚያውቀው ያውቀዋል።
ነገር ግን ጋዜጣዋ ከተቋረጠች በኋላ ለአጭር ጊዜ በድረ ገፁ በኩል ጀምሮት ነበር። ቢሆንም ግን  ሊዘልቅ አልቻለም።  ሁሉን ነገር ገታ አድርጎ  በመተው  በመፅሐፍና ሌሎች ተዛማጅ መስኮች ላይ በመስራት በተከታታይ በእግር ኳስ ዙሪያና ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥኑ መፅሀፎችን አበረከተለን፡፡  ለመጥቀስ ያህል፡-
*የአሸናፊ ግርማ የህይወት ታሪክ፤ ከአሸዋ ሜዳ እስከ አርጀንቲና
*የእግር ኳስ ወጎች
*ኢህአፓና ስፖርት 1 እና 2 እዚህ ጋ በቅርብ ለእይታ የቀረበው የነገን አልወልድም የታሪኩ መነሻ ከ ኢህአፓና ስፖርት 1 የተወሰደ ነው)
እና ሌሎች በህትመት ደረጃ ያልወጡ በሙዚቃና በሌሎች ጉዳዮች ያተኮሩ መፅሐፍት ሲያሰናዳ ነበር፡፡
ሌላው በ90ዎቹ አጋማሽ ላይ በስፋት ይወራ ስለነበረው የኢትዮጵያዊ ስልጠና ሀሳብ አመንጪ ሰው ነው፡፡ በተለምዶ  Gk የሚባለውን  የስልጠና ፍልስፍና በኋላ በካሳዬ አራጌ  ዳብሮ ለአጭር ጊዜ የተሞከረው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ዙሪያ ላይ በ1994 ዓ.ም ኢትዮጵያ ስልጠና መፅሀፍ ማውጣቱ አይዘነጋም። እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ደብዳቤ ፅፏል በስልጠናው ዙሪያ ላይ።
*****
ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ ) ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ማረፉ ተሰምቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል፣ በታላቁ የስፖርት ሰው ገነነ መኩሪያ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቹ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርለት፡፡

 

 

ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ገነነ መኩሪያ ባደረበት ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ዛሬ ንጋት ላይ ማለፉን ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ "ንባብ እና አገር" የተሰኘ የንባብ ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ "ንባብና አገር" የተሰኘ የንባብ ፌስቲቫል ከጥር 16 እስከ 23ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
የባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አስፋው ኩማ እንዳሉት፤ የንባብ ፌስቲቫሉ ዓላማ የከተማው ማህበረሰብን የንባብ ባህል ለማሻሻልና ግንዛቤ ለመስጠት ነው።
ባለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ በራሪ ጽሁፎች በማዘጋጀት የስርፀት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የገለፁት ሃላፊው፤ በዚሁ ዝግጅት በህትመት ታሪክ ውስጥ በርካታ አስተዋፅኦ ያደረጉ ድርጅቶችና ደራሲያን ታሪካቸው ይወሳል ብለዋል።
የንባብ ፌስቲቫሉ ለ8ኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን ዝግጅቱ በአዲስ አበባ ሙዚየም ይደረጋል።

የአንጋፋው ጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈፀመ

ጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ ባደረበት ህመም በአሜሪካ ሕክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ሕይወቱ ማለፉ ይታወቃል፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽም የስንብት መርሐግብር ከተካሄደ በኋላ በመንበረ ጸባኦት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ፣ የሙያ አድናቂዎቹ፣ የስራ ባልደረቦቹ በተገኙበት የፍትሃት እና የቀብር ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በአንጋፋው የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ አስፋው መሸሻ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለስራ ባልደረቦቹና ለወዳጆቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል። ፈጣሪ ነፍሱን በአፀደ ገነት ያኑርለት።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Page 6 of 690