Administrator

Administrator

 የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ፍቃዱ ማህተም ወርቅ ከ6 ዓመት በፊት ያሳትመው ከነበረው እንቁ መጽሔት ጋር በተያያዘ በቀረበበት የወንጀል ክስ ጉዳይ ማክሰኞ ለፍርድ ተቀጥሯል፡፡ በ2006 ዓ.ም ነሐሴ ወር መንግስት ሕገ መንግስቱን በሃይል የመናድ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል በሚል ክስ ከመሰረተባቸው 5 መጽሔቶች እና 1 ጋዜጣ መካከል አንዱ የነበረው የእንቁ መጽሔት በወቅቱ ከግብር ጋር በተያያዘም ተጨማሪ ክስ ቀርቦበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ክስ ቀርቦባቸው ከነበሩ መጽሔቶች ጋዜጦች በርካቶቹ በፍ/ቤት ውሳኔ የተዘጉ ሲሆን ይህን ተከትሎም ከ40 በላይ ጋዜጠኞች በወቅቱ
ከአገር መሰደዳቸውም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከአገር እንዳይወጣ እግድ ተጥሎበት የነበረው የእንቁ መጽሔት ተወካይ የነበረው ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ ላለፉት አመታት በገቢዎች የቀረበበትን ክስ ሲከታተል መቆየቱን ለአዲስ አድማስ አስታውቆ ለመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ከ6 ዓመት በኋላ ለማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 እንደሰጠው ቀጠሮ እንደተሰጠው አስታውቋል፡፡ በአገሪቱ ለውጥ ከመጣ በኋላ ክሱ አግባብነት የሌለው መሆኑን ለማስረዳት ላለፈው 1 ኣመት ለጠቅላይ አቃቤ ሕግና ለሚመከታቸው ሁሉ ለማስረዳት መሞከሩን የገለፀው ፍቃዱ ነገር ግን እስከ ዛሬ ቀና ምላሽ አለማግኘቱን አስረድቷል፡፡ እንቁ መጽሔት በወንጀልና ከታክስ ጋር በተያያዘ በተከፈተበት ክስና መዋከብ ህትመቷ እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ ፍቃዱ ማህተም ወርቅ ‹‹ጊዮን›› ሳምንታዊ መጽሔትን መስርቶ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል፡፡

Saturday, 19 October 2019 12:37

ቅምሻ ከድረገፅ ዘገባ

 በኦሮሚያ እጅግ ተስፋ ሰጪ የፖለቲካ መስተጋብር እየታየ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ እየተሸረበ ያለው የፖለቲካ ቁማር አስቀድሞ ወላፈኑ የሚገርፈው የኦሮሞን ሕዝብ በተለይም ወጣቶችን እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። አቶ ገመቹ ደንደና እንደሚሉት ግን ሳይገባቸው እንደ አቦሸማኔ የሚጋልቡት መብዛታቸው ከስጋትም በላይ ነው። ምልክቶችም እየታዩ ነው።
በተለያዩ መድረኮች በቃል ደረጃ ከሚሰማው በቀር በኦሮሚያ “ተስፋ ሰጪ” የሚባለው የፖለቲካ መስተጋብር በገቢር የሚታይ እንዳልሆነ “ተስፋ ሰንቀናል” የሚሉት ራሳቸው የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች፤ ከጥቅም ባሻገር ልዩነታቸውን አስወግደውና አቻችለው በሰላማዊ መንገድ ለመፎካከር መስማማት አለመቻላቸውን እነዚሁ ወገኖች በሃፍረት የሚገልጹት ነው። ልዩነት ቢኖርም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ አለመቻልና ነፍጥ ይዞ እስከ መገዳደል መድረሳቸው የመጨረሻው መጀመሪያ ማሳያ አድርገውም ይወስዱታል።
ሕዝብን በማይወክል ደረጃ የሚራገቡ አጀንዳዎችና ፕሮፓጋንዳዎች አየሩን መሙላታቸው ዛሬ ላይ ድል ቢመስልም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ልብ የሚያደርስ መረጋጋት እንዳይፈጠር ምክንያት እንደሆነ አቋም ይዘው የሚወተውቱ አሉ። ጥፋቶችን የማረም ሥራ ከተሠራ “ተስፋ ሰጪ” የሚሰኘው የፖለቲካ ጅማሮ፣ ከተስፋ እንደሚዘል በተስፋ ላይ ተስፋ ደርበው ያምናሉ።
“ቁማር እየተቆመረ ነው” የሚሉት ወገኖች በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ ክልል ምን እየተደረገ እንደሆነ ለመረዳት የሚያዳግቱ አጋጣሚዎች እየበረከቱ መሆናቸውን ያወሳሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ ከራሳቸው ጉዳይ አልፈው የኦሮሞን ጥቅም እናስከብራለን የሚሉ ወገኖች፤ በሲዳማ፣ በቅማንት፣ በአገውና በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መነከራቸው የማንን አጀንዳ እያስፈጸሙ እንደሆነ ይጠይቃሉ።
በኦሮሞ ህዝብ ስም ቅማንት ውስጥ ገብቶ እሳት መቆስቆስ፣ አገው ምድር ገብቶ ረመጥ ማራገብ፣ ሲዳማ ውስጥ ገብቶ ሕዝብ እንዲጫረስ አቅጣጫ ማስቀመጥና በሚዲያ ማራገብ፣ በራያና መሰል ጉዳዮች መነካካት ፍጹም እንደማይጠቅም የሚናገሩ ወገኖች፤ “አጀንዳ ተሸካሚዎች” ለኦሮሞ ሕዝብ ጠላት እየገዙለት ነው ይላሉ።
ይህ አካሄድ የሰሜኑ ፖለቲካ ውጥረት የተነፈሰ ዕለት የኦሮሞን ሕዝብ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። እነዚህ ወገኖች ወደ ኋላ ሄደው “በእኔ ስም አይደረግም” በሚል ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም የሚፈጽመውን በደል እንዲያቆም ሲጠየቅ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬም የኦሮሞ ሕዝብ፣ በተለይም ልሂቃኑ በኦሮሞ ስም የሚያከናወኑትን አስከፊና ነገ ዋጋ የሚያስከፍሉ አካሄዶችን “በስማችን እንዲደረግ አንፈቅድም” ሊሉ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ለውጡን ወዳልሆነ አቅጣጫ በመግፋት ለውጡ እንዲጨናገፍ ሌት ተቀን ለሚታትሩ ቀበኞች አሳልፎ ለመስጠት የሚሰሩ የኦሮሞ ልሂቃን፤ ለውጡ የተከፈለበትን የደም ዋጋ፣ ዋጋ ቢስ እንዳያደርጉት ከሚሰጉት መካከል አንዱ አቶ ገመቹ ደንደና ናቸው።
ምንጭ፡- (“ጉልጉል” ጋዜጣ)

 የማያውቋቸውን የተቸገሩ ሰዎች በመርዳት፣ ለበጎ ምግባር ገንዘብ በመለገስና በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉት ኬንያውያን፤በልግስና ከአፍሪካ የአንደኛ፣ ከአለም አገራት ደግሞ የ11ኛ ደረጃን መያዛቸውን ሰሞኑን የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
ቻሪቲስ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም በ128 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከአለማችን አገራት መካከል በልግስና ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው አሜሪካ ስትሆን በርማና ኒውዚላንድ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አውስትራሊያ፣ አየርላንድ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ፣ ሲሪላንካና ኢንዶኔዥያ በተቋሙ የ2019 እጅግ ለጋስ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል በልግስና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችው አገር ቻይና ስትሆን፣ ግሪክና የመን በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ቻሪቲስ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም፤ ዜጎች የማያውቁትን ሰው በመርዳት፣ ለበጎ ምግባር ገንዘብ በመለገስ ወይም በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍና ሌሎች መልካም ተግባራትን በመፈጸም ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ በመገምገም፣ የአገራቱን የልግስና ደረጃ እንደሚያወጣ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ኢንዶኔዢያ በልግስና ከፍተኛ መሻሻል ያሳየችዋ ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ናት ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ ኬንያን በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

Saturday, 19 October 2019 12:32

የኖቤል ሽልማት ታሪክ

 በአስራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ላይ አሜሪካ መልክዓ-ምድሯን የሚከፋፍሉትን ተራሮች ቦርቡራ፣ ህዝቦቿን በመንገድ በማገናኘት ወደ አንድነት ለማምጣት ፈለገች:: ችግሩ እነዚህን የአለት ተራራ ግርዶሾች ለመቦርቦር ወይም ለመናድ ይውል የነበረው በፍንዳታ ከፍተኛ ሃይል ማመንጨት የሚችለው ናይትሮግሊስሪን የተባለ ፈሻሽ ፈንጅ ነበረ፡፡ ይህ ፈሳሽ ውሁድ እጅግ ያልተረጋጋና በድንገተኛ ቅጽበታዊ እንቅስቃሴ ፈንድቶ ከፍተኛ አደጋ ማድረስ የሚችል ፈንጅ ነው፡፡
ናይትሮግሊስሪን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁፋሮ ሠራተኞች በወራት ድካም ሊሠሩት የሚገባን አድካሚ የቁፋሮ ሥራ በቀላሉና በፍጥነት እንዲሳካ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የወርቅ ማዕድን አውጪዎች፣ የነዳጅ ጉድጓድ ቆፋሪዎች እንዲሁም ተራሮችን በመቦርቦር መንገዶችን የሚገነቡ ባለሙያዎች ሁሉ ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ፈሳሽ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፡፡ በነዚያ ጭለማ፣ እርጥብና የሚያዳልጡ ጉድጓዶች፣ ፈንጂውን ፈሳሽ የያዘው ባለሙያ የከተንገዳገደ እንደሆነ ዘግናኝ ዜና መሰማቱ አይቀርም ነበረ፡፡
በማዕድን ማውጫ ጉድጓዶች አካባቢ፣ ናይትሮግሊስሪን ያለ ዕቅድ በድንገት የፈነዳ እንደሆነ ጉዳቱ እስከ አጐራባች መንደሮች ይዘልቃል፡፡ በ1866 እ.ኤ.አ ዌልስ ፋርጐ በሚባል የጭነት አመላላሽ (አሁን ከፍተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ድርጅት) ይጓጓዝ የነበረ የናይትሮግሊስሪን ፈሳሽ በጉዞ ላይ እያለ መንጠባጠብ መጀመሩን የተመለከቱት የትራንስፖርቱ ሰራተኞች የመያዣ ዕቃውን ከፍተው ለመመልከት በሚል እሽግ በርሜሉን በመዶሻና በመሮ መቀጥቀጥ በጀመሩበት ቅጽበት ፈንድቶ 15 ሰዎች ሰቅጣጭ አሟሟት ሞቱ፤ በኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ሕንፃዎች መስታዎቶቻቸው ከመሰባበራቸው በላይ የፍንዳታው በድምጽ ከስልሳ ኪሎሜትር ርቀት በላይ የተሰማ ነበረ፡፡ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ነበረ የመሰላቸው፡፡ በፍንዳታው የሞቱ ሰዎች አካላት ከአንድ ኪሎ ሜትር የበለጠ ርቀት ላይ ተበታትነው ተገኙ፡፡
በ1864 ታናሽ ወንድሙን በተመሳሳይ ፍንዳታ ያጣው አልፍሬድ ኖብል የተባለ ሳይንቲስት፤ ይህን ናይትሮግሊስሪን የተባለ ህይወትንም ሞትንም አስተሳስሮ ያዘለ ፈሳሽ ፈንጅ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንዳይኖረው ለማድረግ ይታትር ገባ፤ እናም ተሳካለት፡፡
አቶ ኖቤል (እንዲህ በአማርኛ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ፈረንጆች ስም ሲጠራ ሥራዎቻቸው የኛ ይመስሉኝና ደስ ይለኛል አርስቶትል አርጣጣሊስ፣ ፕሌቶ ጲላጦስ፣ ፒተር ጴጥሮስ…) ናይትሮግሊስሪንን ከሆነ የአፈር ዓይነት ጋር አደባልቆ ፈሳሹን ሊጥ በማድረግ ሆን ተብሎ ካልታዘዘ በቀር በድንገት እንዳይፈነዳ በማድረግ ዳይናማይት ብሎ ሰየመው፡፡
የዳይናማት ሊጥ እየተድቦለቦለ እንዲፈረካክሱ በሚፈለጉ የቋጥኝ ተራሮች ውስጥ በመወሸቅ እንዲፈነዱ ሲታዘዙ መፈንዳትና ጥቅም ላይ ብቻ መዋል ጀመሩ፡፡ እንደ ልብ ሊጓጓዙ ከመቻላቸውም በላይ ከሠራተኞች እጅ ላይ አምልጠው ቢወድቁ እንኳ ድንገተኛ ፍንዳታን የማያስከትሉ ሆኑ፡፡
ዳይናማይት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ማዳን በቻሉና ጉዳት አልባ በመሆናቸው አቶ ኖብልን ሃብታም አደረጉት፡፡ አቶ ኖብልም ዕውቀቱን ለዓለም ጥቅም ማዋል በመቻሉ ሲደሰት፣ ታላቅ ወንድሙን በህመም ምክንያት በሞት አጣ፡፡ በዚህ ጊዜም አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ወንድማማቾቹን በማምታታት፣ “የሞት ነጋዴው ሞተ” የሚል ዜና ይዞ ወጣ፡፡ አቶ ኖብልም በጋዜጣው በርካታ ሰዎችን በመግደል፣ ሃብት ስለማካበቱ የተፃፈውን ዝርዝር ዜና ሲሰማ፣ ከርሱ ሃሳብ እውነታ ጋር የሚፃረር በመሆኑ እጅግ ከመደንገጡም በላይ ማመን አቃተው፡፡
አቶ ኖብል በዓለም ታሪክ ጋዜጦቹ ባመኑበት መሰሪ ሁኔታ መታወሱን ፍፁም ባለመፈለጉ አንደ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ይህም ለዓለም ጥቅም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች በየዓመቱ ሽልማት የሚሰጥ ድርጅት በገዛ ገንዘቡ አቋቋመ:: በየዓመቱም ለሳይንስ (ኋላም ለፊዚክስ) ለኬሚስትሪ፣ ለህክምና፣ ለሥነ-ጽሑፍ፣ በልዩ ሁኔታ የኖብል የሠላም ሽልማት በሚል በተዘረዘሩት ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረበቱ ሰዎች መሸለም ጀመረ፡፡ ይህ የአቶ ኖብልን ስም የያዘው ሽልማትም የማንኛውም ሳይንቲስትና የሀገር መሪዎችን ጨምሮ የሁሉም ሰው የመጨረሻና እጅግ የተከበረ የስኬት ግብ ምኞት መሆን ቻለ፡፡ እናም አቶ ኖብል በመጨረሻ በዓለም ታሪክ እንደ ጋዜጠኞቹ ያልተጣሩ “የሞት ነጋዴ” የሚሉ አሉባልታዎች ሳይሆን እንደ እውነተኛው ንፁህ ልባቸው መሻትና ዕቅድ መታወስ ቻሉ፡፡
እነሆ የአቶ ኖብል ታላቅ ትሩፋትም ቅንና ፀዓዳ ሰብዕና ባላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት ለእኛም ደረሰን!!
የኖብል ሽልማት የግለሰብ ሽልማት አይደለም፤ እንኳንስ ለተሸላሚው ሰውና ለሀገሩ ቀርቶ ለአህጉሩም ጭምር የኩራትና (በተገቢው መንገድ ከተጠቀሙበት) የህብት ምንጭ ነው:: መላው ኢትዮጵያውያንና መላው አፍሪካውያን እንኳን ደስ አለን!!!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን እንኳን ደስ አልዎት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ክብር ስላበቁን ላመሰግንዎት እወዳለሁ፡፡  


 ሴቶች ቅርብ በሆነ ጉዋደኛ ወይንም የትዳር አጋር የሚደርስባቸው ጥቃት ከጤናቸው መጉዋ ደል ጋር እንደሚገናኝ የአለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ 29 November 2017 ባወጣው መረጃ ጠቅሶአል፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተውም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሴቶች በመሆናቸው ብቻ የሚደርስባቸው ሲሆን ውጤቱም በአካል፤በሞራል፤እና በወሲብ የሚደርስ ጉዳት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደዚህ ያሉ ማስፈራራትን የጨመሩ ድርጊቶች ወይንም ኃይልን፤በማንኛውም ጊዜ በድንገት በግልም ይሁን ህብረተሰቡ ባለበት የሚፈጸሙ ነጻነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ናቸው፡፡
በቅርብ ያለ ኑሮን የሚጋራ ጉዋደኛ ወይንም ባል የሚያደርሰው ጉዳት አካላዊ ጥቃት እና በጉልበት ወይንም በኃይል ወሲብ መፈጸም፤እንዲሁም በስነልቡና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ወሲባዊ ጥቃት በማንኛውም መንገድ ከግለሰብ ፈቃደኝነት ውጭ በጉልበት ወይንም በኃይል አስገድዶ መፈጸምን የሚመለከት ሲሆን ይህ በቅርብ ሰው ወይንም ኑሮን በሚጋራ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰው ሲፈጸም የሚገለጽበት ነው፡፡ ይላል የአለም የጤና ድርጅት የተባበሩት መንግ ስታትን መረጃ በመጥቀስ፡፡
ሴቶች በቅርባቸው ባለ ወንድ ሲጎዱ ማየት በአለም ላይ ምን ያህል የተተስፋፋ ችግር መሆኑን የሚያሳየው መረጃ በለንደን የሚገኘው(London School of Hygiene and Tropical Medi- cine እና በደቡብ አፍሪካ  (the South Africa Medical Research Council) ጠቅሶ በ80 ሀገራት ላይ መረጃ በመሰብሰብ ውጤቱም በአለም አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሴቶች አንድዋ ማለትም ከአለም ሴቶች ወደ 35 % የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው በቅርብ በሚገኝ ወይንም በማንኛ ውም ሰው ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ይጠቁማል (እ.ኤ.አ 2013 WHO)፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው በአለም ላይ ካሉት ሴቶች አንድዋ በሕይወት ዘመንዋ በቅርብዋ በሚገኝ ወይንም በማንኛውም ሰው አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባታል ሲባል ወደ 23.2% የሚሆነው ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የደረሰ ሲሆን ወደ 24.6% የሚሆነው ደግሞ በምእ ራብ የፓሲፊክ አገራት እንዲሁም 37% በምስራቅ ሜዲትሬንያን አካባቢ እና 37.7 % የሚሆነው ደግሞ በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት እንደሆነ የአለም የጤና ድርጅት ይገምታል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 38%የሚሆኑት ግድያዎች ሴቶች በቅርባቸው ባለ ሰው የደረሰባቸው መሆኑ እና ምንም እንኩዋን ቅርበት ከሌላቸው ሰዎች የደረሱ ጉዳቶችን በግልጽ የሚያሳይ መረጃ ባይኖርም ወደ 7% የሚሆኑ ሴቶች ተገደው የተደፈሩ መሆናቸውን ሪፖርት ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ሴቶች በቅርባቸው ባሉ ወንዶች የሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ለጉዳታቸው ከፍ ያለ ድርሻን እንደሚይዝ መረጃው ይጠቁማል፡፡
ለጉዳቱ ቁልፍ መረጃዎች ያላቸውን WHO እንደሚከተለው ዘርዝሮታል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጉዳት በተለይም በቅርብ አብሮ በሚኖር ወይንም በሚያገኛቸው ሰው የሚፈጸመው ከፍተኛውን የጤና ችግር የሚያስከትልና የሰብአዊ መብታቸውንም የሚጥስ ነው፡፡
በአለም እንደሚገመተው ከሶስት ሴቶች አንድዋ (30%) በሕይወት ዘመንዋ አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጉዳት ከቅርብ ወይንም አብሮአት ከሚኖር ሰው እንደሚደርስባት ተመዝግቦአል፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ግድያዎች 38% የሚሆኑት የሚፈጸሙት በወንድ የቅርብ ጉዋደኛ ወይንም የትዳር አጋር ነው፡፡
ጥቃት ሴቶችን አካላቸውን፤ ስነልቡናቸውን፤ ወሲባዊ ድርጊትን እና የስነተዋልዶ ጤናቸ ውን ሊጎዳ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለኤችአይቪ ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡
ወንዶች በሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱት በትምህርታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወይንም በልጅነታቸው ጥቃት እየደረሰባቸው ካደጉ፤በቤት ውስጥ ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ካደጉ፤ ጎጂ በሆነ መንገድ አልኮሆል የሚወስዱ ከሆነ፤ የተዛባ የስነጾታ ልምድ ካላቸውና ዝንባሌያቸው ጥቃት ማድረስን የሚገፋፋ ከሆነ እና የሴቶች የበላይ ነኝ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ድርጊቱን ይፈጽሙታል፡፡
ሴቶችም ጉዳት የሚደርስባቸው በትምህርታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከሆነ  እና እናቶቻቸው ቅርብ በሆነው ወንድ ሲደበደቡ ወይንም ሲጎዱ እያዩ ካደጉ እንዲሁም በሕጻንነ ታቸው ጉዳት እየደረሰባቸው ካደጉ እና በወንድ መጠቃት ወይንም መደብደብ ትክክል ነው ብለው የሚቀበሉ ከሆነ፤ ለወንዶች የተለየ ክብር ከመስጠት፤እና ሴቶች በወንዶች ላይ ጥገኛ ከሆኑ ጉዳት ሲፈጸምባቸው እንደትክክለኛ ነገር ይወስዱታል፡፡
ስለዚህም ሴቶች ድጋፍ ከተደረገላቸው እና አቅማቸውን ለማጠናከር እርምጃ ከተወሰደ እና የምክር አገልግሎት ከተሰጣቸው እንዲሁም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ኑሮአቸውን የሚጎበኝላቸው ወይንም ቃል የሚገባላቸው ካገኙ ግንዛቤያቸው ስለሚያድግ ጥቃቱን ለማስቆም እንደሚተባበሩ እሙን ነው፡፡
አንዳንድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶች ወይንም ቀደም ሲል በደረሰ ጥቃት ምክንያት የተከሰተ መፈናቀል የመሳሰሉት ነገሮች በድጋሚ ለጉዳቱ እንዲዳረጉ የሚያስገድድበት ምክንያት ይኖራል:: እንደዚህ ያሉት ክስተቶች በቅርብ ሰዎች ወይንም በቅርብ በማይገኙ ሰዎችም ቢሆን በአዲስ መልክ በሴቶች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳቶች ናቸው፡፡
የሴቶችን በቅርብ ሰው መጠቃት ሁኔታ በአፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ የሚጠቀስ መሆኑን የ Arch Public Health. ይጠቁመናል:: በእርግጥ በጥቃቱ ምክን ያት የሚጎዱት ሴቶች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ የሚደርስባቸውም የጤና እክል በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምሳሌም በእርግዝና ወቅት የሚደርስ ጉዳት እንዲሁም በግብረስጋ ግንኙነት ምክ ንያት በሚተላለፉ በሽታዎች ሳቢያ የወሲብ ፍላጎትን ማጣት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሴቶች ላይ በቅርብ ሰው የሚደርሱ ጥቃቶች በየትኛውም ቦታ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ቢሆ ንም ደረጃውና መጠኑ ግን ሁኔታውን አሜን ብለው በሚቀበሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንደሚጨምር እና ከቦታ ቦታ ከሀገር ሀገር በመላው አለም እንደሚለያይ እሙን ነው፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የሴቶች መጠቃት በከፍተኛ ሁኔታ የተመዘገበ ሲሆን በአለም ከተመዘገበው 30% ጉዳት 36% ድርሻ ይይዛል፡፡ በአፍሪካ ብዙ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው አብሮአቸው በሚኖር ወይንም ቅርብ በሆነ ሰው የሚደርስባቸው ጉዳት 45.6% ሲሆን የሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ደግሞ በየትኛውም የአለም ክፍል ከሚኖሩ ሴቶች 11.9% ይሆናሉ፡፡ በሴቶች ላይ ቅርብ ባለ ሰው የሚደርስ ጥቃት በጤና ላይ አስቸጋሪ ሲሆን ይህም የሚገለጽበት ደረጃ በተለይም ልጅን በመውለድ በኩል ከስነልቡና ጤና ችግር እስከ ስነተዋልዶ ጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው ይታያል፡፡
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ሴቶች በቅርባቸው ባለ ሰው በሚደርስ ጉዳት ወይንም ጥቃት ምክንያት ምንም እንኩዋን በውጤቱ ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ የአካል ጉዳት ደር ሶባቸው ቢታይ ሴቶቹ ለወንዶቹ የሚሰጡት ምላሽ የስነልቦና መዛባት ወይንም አስከፊ የሆነ እንጂ ወንዶቹም ተጎድተዋል የሚል አስተሳሰብ አይታይባቸውም፡፡ ይህም በችግሩ ምን ያህል እንደተጎዱ ወይንም እንደተበሳጩ የሚመሰክር ነው፡፡ መረጃው እንደሚጠቁመው በቅርብ ባሉ ሰዎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና በእርግዝና ወቅት የሚታዩ ችግሮች በጥብቅ ግንኙነት አላቸው፡፡
በቅርባቸው ባሉ ሰዎች በአካል ወይንም በወሲብ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃ ያቀረቡ ሴቶች በብዛት ላልታቀደ ወይንም ላልተፈለገ እርግዝና ይጋለጣሉ፡፡
በሕይወት ዘመናቸው በቅርብ ባለ ሰው ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ሕይወት የሌለው ልጅ መውለድ ወይንም እርግዝናው ካለቀኑ እና ሕይወት አልባ ሆኖ የመወገድ ወይንም ጽንስ መቋረጥ፤ የመሳሰሉት ችግሮች ይደርስባቸዋል፡፡
የተጎዱት ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ችግር በተለያዩ መንገዶች ሊገጥሙአቸው ይችላል፡፡ በግብ ረስጋ ግንኙነት ወቅት በሚተላለፉ በሽታዎች ከመያዝ እስከ እርግዝናን በጸጋ አለመቀበል በሚያደርስ ስጋት ውስጥ ሊጥላቸው ይችላል፡፡
በቅርብ ሰው በሴት ላይ የሚደርስ ጥቃት ኤች አይቪን ጨምሮ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ሊዳርግ ይችላል::
ከሌሎች የአለም ክፍሎች በተለየ በአፍሪካ ውስጥ በቅርብ ሰው በሴት ላይ የሚደርስ ጥቃት ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል ከፍተኛ ለሆነ የመጠጥ ሱስ የመጋለጥ ፤ወይንም በልጅነት ጊዜ የሚደርስ ጥቃት፤ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማለትም ስራ አጥነት እና መጨረሻ የሌለው በወንድ ቁጥጥር ስር የመሆን ልማድ ይታያል፡፡    

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዕብድና አንድ ለማኝ በጓደኝነት ይኖሩ ነበር፡፡ መተሳሰባቸው፣ መተጋገዛቸው እጅግ ያስቀና ነበር፡፡
መሀላቸው፣ ‹‹አደራ እንዳንከዳዳ›› የሚል ነበር፡፡
ሰንብቶ ሰንብቶ ለማኙ በብርድ በሽታ ታሞ ሞተ፡፡ ዕብዱ የለማኙን አስከሬን በሰሌን ጠቅልሎ ወደ መቃብር ቦታው ይዞት ሄደ። እንዳጋጣሚ ወደ አሥራ ስድስት የሚጠጉ የሸዋ መኳንንት በመኪና የመገልበጥ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ያ ዕብድ ለለማኙ እንዲህ አለው ሲሰናበተው፡-
‹‹እንግዲህ ወዳጄ ከደህና ሰዎች አገናኝቼሃለሁ፤ ብታውቅ እወቅበት›› ብሎ አስቀምጦት ሄደ፡፡
* * *
የአዕምሮ ጤና የጎደለው ሰው መላ ነገሩን እስከሚያስተካክል ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ የተማረም የተማረውን እስኪተገብር ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ ያልተማረውም የተማረው ቦታ ለመድረስ ጊዜ ይፈጃል፡፡ አገር የተማረውን ቦታ ለመስጠትና ያልተማረውን ለማስተማር ትጨናነቃለች፡፡ መሯሯጥ ይጠበቅባታል። ሼክስፒር በፀጋዬ አንደበት፡-
‹‹…በምናውቀው ስንሰቃይ
    የማናውቀውንም ፈርተን በህሊናችን ማቅማማት
    ወኔያችንንም ተሰልበን
    ሕይወት የምንለው ውጥንቅጥ እንቅልፍ ላይ ነው ህመሙ
በየዕለቱ መስለምለሙ
እያደር ከህሊናችን ይደመሰሳል ትርጉሙ!
የዱሮ ፀሐፍት፤
‹‹እኛማ ብለናል
እኛማ ታግለናል
እኛማ አምፀናል
ጥንትም ወርቅ በእሳት
እኛም በትግላችን
እየተፈተንን እናቸንፋለን››
ለዘመን መልካም ምኞትና፣ መልካም ምስክርነት  መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ህልውናችን የተሰራው ከመልካምነታችን ልቡና መሆን አለበት፡፡ መንገዳችን ቀና የሚሆነው በዚህ ጎዳና ብቻ ነው፡፡
‹‹እንጫወት እንጂ
እንጫወት በጣም
ከእንግዲህ ልጅነት
ተመልሶ አይመጣም፡፡
(ከዱሮ ማስታወሻ)
ከፀጋዬ ጋር ስናስብ ደግሞ (ለኢትዮጵያ ይበለው አይበለው ባናውቅም፤
‹‹አልወድሽም ያልኩት ውሸቴ ውሸቴ
ሳይሽ እርር ኩምትር ይላል ሆድ አንጀቴ››
ኢትዮጵያን ከአንጀቱ የሚወድ ኢትዮጵያዊ፤
‹‹እናትሽን አትውደጅ ለዘጠኝ ወር ዕድሜ
ተሸክሜሻለሁ እስከ ዘላለሜ››
ቢል… አይገርምምና፣ ለሁላችንም እንደዚያው - መልካም አዲስ ዘመን!

Saturday, 12 October 2019 12:38

የግጥም ጥግ

ከአዘጋጁ፡- ሰሞኑን በዩቲዩብ አንድ ነጠላ ዜማ ተለቋል፡፡ ቴዲ XL በተባለ ድምፃዊ “ሀኪሙ” በሚል ርዕስ የሚቀነቀነው አዲስ ዘፈን፣ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን የሚያወድስ ነው፡፡ በሬጌ ሥልት የተቀናበረው ይሄ ሙዚቃ፣ የግጥም ይዘቱ ምን እንደሚመስል ለመፈተሽና ግንዛቤ ለመጨበጥ ያህል ጥቂት ስንኞችን መዝዘን አቅርበናል፡፡ አንዳንዴ መሪዎቻችንን እያደነቅንና እያወደስን ብናቀነቅን ምን ይለናል!
(ቢያንስ ለለውጥ ያህል!)


***

                ሀኪሙ

በዘመናት በአንዱ ዘመን
ለእኛ ሲባል ይህ ይሆናል
ከዓመታት ድካም ጀርባ
የተድላ ዛፍ በቅሎ ይፀናል
የፈረሰው ተገንብቶ
የጠመመውም ይቃናል
የተጎዳው አገግሞ
ሰባራውም ይጠገናል
ሀኪሙ
የእውነት ኢትዮጵያ አለች በደሙ
ሀኪሙ
ይመራናል ትልቅ ነው አቅሙ
ሀኪሙ
ፈውስ መድሃኒት አለው ለታመሙ
ሀኪሙ
ረዳት አጋዥ ነው ለደከሙ
(ይስሙ)
ከጨለማው ደግሞ አሁን ነግቷል
ለአዲሱ ቀን አዲስ ጀግና መጥቷል
ከጅማሬው ብሩህ ፀሐይ ታይቷል
ለኛ ከላይ ሙሴ ተዘጋጅቷል ---
         (ይቀጥላል)

Saturday, 12 October 2019 12:35

የሙዚቃ ጥግ

• ሙዚቃ የመላዕክት ቋንቋ ነው መባሉ ሲያንስበት ነው፡፡
    ቶማስ ካርሊሌ
• ሙዚቃ የፈውስ ሃይል አለው፡፡ ሰዎችን ለጥቂት ሰዓታት ከራሳቸው  ውስጥ መንጥቆ የማውጣት አቅም ተችሮታል፡፡
   ኢልቶን ጆን
• የምታደምጠውን ሙዚቃ ንገረኝና፣ ማንነትህን እነግርሃለሁ፡፡
   ቲፋኒ ዲባርቶሎ
• ሕይወቴን የምመለከተው ከሙዚቃ አንፃር ነው፡፡
   አልበርት አንስታይን
• ሙዚቀኞች ጡረታ አይወጡም፤ ሙዚቃ ከውስጣቸው ሲደርቅ ያቆማሉ እንጂ፡፡
   ሉዊስ አርምስትሮንግ
• ሙዚቃ የተፈጠረው የሰውን ልጅን ብቸኝነት ለማረጋገጥ ነው፡፡
  ሎውረንስ ዱሬል
• አንዳንድ ሰዎች ኑሮ አላቸው፤ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሙዚቃ፡፡
   ጆን ግሪን
• ፈጣሪ አያድርገውና ከሞትኩ፣ መቃብሬ ላይ እንዲህ ተብሎ ይፃፍልኝ፡- ‹‹እግዚአብሔር ለመኖሩ የሚፈልገው ብቸኛ ማረጋገጫ ሙዚቃ ነበር››
   ኩርት ቮኔገት
• ሙዚቃ በቃላት የማይነገረውንና በዝምታ ሊታለፍ የማይችለውን ይገልጻል፡፡
   ቪክቶር ሁጎ
• ብቸኛው የዓለማችን እውነት ሙዚቃ ነው፡፡
   ጃክ ኬሮዋክ
• የሙዚቃን ፍሰት ማስቆም ማለት ጊዜን ራሱን እንደ ማስቆም ነው፤  ሊሆንና ሊታሰብ አይችልም፡፡
   አሮን ኮፕላንድ
• ‹ሁሉንም ዓይነት ሙዚቃ› እንወዳለን የሚሉ ሰዎች ታውቃላችሁ? እነሱ ምንም ዓይነት ሙዚቃ የማይወዱ ናቸው፡፡
   ቹክ ክሎስተ

Saturday, 12 October 2019 12:33

የዘላለም ጥግ

(ስለ ትዕግስት)

 • በፍቅርና በትዕግስት ምንም የማይቻል ነገር የለም፡፡
   ዳይሳኩ አይኬዳ
• ትዕግስት ለስኬት ቁልፍ ሚና አለው፡፡
  ቢል ጌትስ
• ትዕግስት የችግሮች ሁሉ መፍቺያ ቁልፍ ነው፡፡
  የሱዳናውያን አባባል
• ትዕግስት ተስፋ የማድረግ ጥበብ ነው፡፡
  ሉክዲ ክላፒርስ
• ትዕግስት የገነት ቁልፍ ነው፡፡
  የቱርካውያን አባባል
• እግዚአብሔር ሁልጊዜም ታጋሽ ነው፡፡
  ፖፕ ፍራንሲስ
• ትዕግስት የጥበብ አጋር ነው፡፡
   ቅዱስ ኦጉስቲን
• የማንኛውም ጥበብ መሠረቱ ትዕግስት ነው፡፡
   ፕሌቶ
• የአንድ ደቂቃ ትዕግስት፣ የአስር ዓመት ሰላም ያጎናጽፋል፡፡
   የግሪኮች አባባል
• ከዛሬ እንቁላል ይልቅ የነገ ዶሮ ይሻላል፡፡
    ቶማስ ፉለር
• ትዕግስት ማጣት ጦርነትን መረታት ነው፡፡
   ማሃትማ ጋንዲ
• ሁሉም ታላላቅ ስኬቶች ጊዜ ይወስዳሉ፡፡
   ማያ አንጄሎ
• ትዕግስት ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡
   ጆን ፍሎርዮ
• ትዕግስት ገደብ አለው፡፡ ሲበዛ ፍራቻ ነው፡፡
   ጆርጅ ጃክሰን

Saturday, 12 October 2019 12:26

ዝክረ - ኤልያስ መልካ

  አንፀባራቂው የሙዚቃ አቀናባሪ


           እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ፣ የዛሬ 19 ዓመት ከ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ጋር ለሁለት ሳምንት የዘለቀ ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር- ነሐሴ 5 እና 12፤ 1993 ዓ.ም፡፡ ያኔ የ23 ዓመት ወጣት የነበረው ኤልያስ መልካ፤ ከተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ጋር ከመስራቱም ባሻገር በአንጋፋዋ ድምፃዊ በአስቴር አወቀ ኮንሰርት ላይ በጊታሪስትነት ተመርጦ፤ ከሚሊኒየም ባንድ ጋር መጫወቱ ተጠቅሷል - በቃል ምልልሱ፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ላስታ ባንድን መስርቶም በንቃት እየሰራ ነበር፡፡ የሙዚቃ አብዮቱን ያቀጣጠለበትን ‹‹አቤን›› የተሰኘ ዘመናዊ የሪኮርዲንግ ስቱዲዮ ያቋቋመውም ያኔ ነው፡፡
በዚህ ስቱዲዮው ያቀናበረው የመጀመሪያ ሥራው ደግሞ የዕውቁ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮን ‹‹አቡጊዳ›› የሚል አልበም ነበር:: ከጋዜጣው ጋር ላደረገው ቃለ ምልልስ ሰበብ የሆነው፣ ከቴዲ አፍሮ ጋር ከሰሩት ካሴትና የሙዚቃ ኮንሰርት ጋር በተያያዘ በመሃላቸው የተፈጠረው ቅሬታና እሰጥ አገባ ነበር፡፡ የሚገርመው ታዲያ ኤልያስ መልካ ‹‹ተጣልተናል›› ብሎ የቀድሞ ጓደኛውንና የሙያ አጋሩን ቴዲ አፍሮን በሃሰት ወይም በማጋነን ለማጣጣልና ስም ለማጥፋት አልሞከረም፡፡ የተፈጠረውን ችግርና ቅሬታ በቀጥታና በጨዋነት ነበር ለአዲስ አድማስ ያብራራው፡፡ ከዚያም ባሻገር ለቴዲ አፍሮ የድምፅና የአዘፋፈን ችሎታ ሽንጡን ገትሮ ተከራክሯል - ከጠያቂው ጋዜጠኛ ጋር፡፡ በአገራችን እንደተለመደው፣ ውሸትም ጨምሮ ቢሆን ለማውገዝ ፈጽሞ አልዳዳውም፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በወቅቱ በአርቲስቶቹ መሃል የተፈጠረውን ውዝግብ ብቻ በማውጣት አልተወሰነም፡፡ የጋዜጣው መስራችና ባለቤት የነበረው አቶ አሰፋ ጎሳዬ፤ በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ ኤልያስ መልካንና ቴዲ አፍሮን በማስታረቅ፣ አብረው እንዲሰሩ ቃል አስገብቷቸው ነበር፡፡  በጋዜጣው ላይም የሁለቱ አርቲስቶች ፎቶ፣ ገጣሚ ነቢይ መኮንን  ‹‹ሽማግሌ ሊማር ልጆቹን እያየ›› በሚል ከቋጠረላቸው ግጥም ጋር ታጅቦ ወጥቷል:: የምስራቹን ለአንባቢያን ለማጋራት፡፡ እስቲ ከግጥሙ ላይ ጥቂት ስንኞችን መዝዘን እናስታውሳችሁ፡-
‹‹ዘመን ቢራቢሮ
ዘመን ቢራቢሮ
ይኸው በርሮ በርሮ
አደይ አበባ ሆይ
ቀስተ ዳመናው ህብር
እዩ ፈገግታ አምሮ
ናፋቂ መስቀል ወፍ
ጆሮሽን አቅኚና
ስሚ ቅኝት ሰምሮ
ልጅ አዋቂ ትውልድ ባንድ ተነባብሮ
ምን ይሆን ምልኪው ብላቴን ሊገዝፍ
ምን ይሆን ትርጉሙ ሕጻን ጀልባ ሲቀዝፍ
ምንድን ይሆን ፍቺው ፀደይ ሳቅ ሳቅ ሲለው?
መስከረም ፍርግርግ እስክስታ ሲቃጣው?...››
*  *  *  *
ዕውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ፣  የዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲ ኤልያስ መልካ፣ በወቅቱ ከአዲስ አድማስ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ውስጥ ውዝግቡን አስቀርተን፣ በሙዚቃና ማቀናበር ዙሪያ የሰጠውን ትንተና ለቅኝት ያህል እንዲህ አቅርበነዋል፡-
ሙዚቃን በኮምፒዩተር ማቀናበር
ዜማ ይመጣልሃል - ከዜማ ደራሲ፡፡ ለዜማው የሚስማማ ሪትም (ምት) ትመርጥለታለህ - ሬጌ፣ የአፍሪካ፣ ዲስኮ፣ ጃዝ፣ አማርኛ ምት ወዘተ፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ምን ምን እንደሚጫወቱ ትመርጣለህ፡፡ ጊታሪስቱ እንዴት እንደሚጫወት… ኪቦርድ፣ ሳክስፎን፣… በየቅደም ተከተልም ሆነ በህብረት… ለዜማውና ለምቱ የሚያስፈልግ ሙዚቃ ትመርጣለህ፣ ታስተካክላለህ፡፡ ሁሉንም ራስህ ልትጫወተውም ትችላለህ፤ በኮምፒውተር የማዋሃድና የማቀነባበር እገዛ፡፡ ሙሉ ባንድ የሚሰራውን ነገር ጊታር፣ ሳክስፎን፣ ባስ… ሳያስፈልግህ ብቻህን እያንዳንዱን መሳሪያ በኪቦርድ እየተጫወትክ በኮምፒውተር ታቀናብረዋለህ፡፡ አሁን ‹‹አቤን›› በሚል መጠሪያ አዲስ ስቱዲዮ እየከፈትኩ ነው፡፡ በውጭ አገር አገር ከሚሰራ የካሴት ህትመት (Recording) ጋር የሚስተካከል ጥራት የሚያስገኙ ዘመናዊ መሳሪያዎችን አስመጥቻለሁ፡፡
ጥሩና ተወዳጅ ሙዚቃ መስራት
… ስትሰማው የሚያስደስትህና ስትሰራው ከበድ የሚልህን ትመርጣለህ፡፡ ይሄ ከባድ ነው - ጥሩ ነው ትላለህ፡፡ አንድን ሙዚቃ ስትሰማ በውስጡ የምታገኘውን የፒያኖ ድምጽ ብቻ ትወደው ይሆናል፡፡ በሌላ ሙዚቃ ደግሞ ሳክስፎን ወዘተ፡፡ ሌላው ደግሞ አንድ ሙዚቃ ሲወጣ፣ ብዙ ሰው ከወደደውና ከተቀበለው ጥሩ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ግርግር፣ ቄንጥ ወዘተ ስለበዛበት ብቻ ጥሩ ሙዚቃ ነው ተብሎ ሊነገርለት ይችላል፤ ግን አድማጭ አይወደውም፡፡ እውነትም ጥሩ ሙዚቃ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጥንቃቄ፣ በከባድ ችሎታ የተሰሩ፣ በሙዚቃ ባለሙያዎች ዘንድም ጥሩ ሙዚቃ መሆናቸው የሚመሰከርላቸው ዘፈኖች፣ አብዛኛው አድማጭም ሲወዳቸው ታያለህ:: እንዲህ ስል ግን ጥሩ ሙዚቃ ሆኖ አድማጭ የሚያጣ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱንም ማጣጣም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ጥሩና ተወዳጅ ሙዚቃን መስራት፡፡
ድምፅና ልምምድ
… ካሴት ስትሰራ፣ ሁሉም ነገር ተቀርፆ ካለቀ በኋላ በካሴት ከመታተሙ በፊት የተቀረፀውን ዘፈን ትንሽ እንዲፈጥን ታደርገዋለህ፡፡ ቴፕ ሪኮርደር ተበላሽቶ ካሴት እያፈጠነ ሲጫወት ሰምተህ እንደሆነ ድምፁን ይቀይረዋል፡፡ በእርግጥ በጣም አታፈጥነውም፣ በትንሹ ነው፡፡ ያኔ የድምፁ ቅላፄ ይወጣል፡፡ ቀጠን ይላል፡፡ ግን ያን ያህል ጎልቶ የሚጋነን አይደለም፡፡ አንዳንድ ዘፋኞች ካሴት ሲያሳትሙ አያስፈጥኑም፡፡ ነገር ግን አፍጥነው የሚያሳትሙት ዘፋኞችም ቢሆኑ መድረክ ላይ የሚበላሽባቸው በሌላ ምክንያት ነው፡፡ እዚህ አገር፣ የድምፅ ቅላፄ እንደ ቋሚ ነገር ይቆጠራል፡፡ ድምፅ ግን የሚበላሽና የሚሻሻል ነው፡፡
ድምፃዊ ሁልጊዜ መለማመድ አለበት:: አንድ ጊዜ ዘፍነው ላይ ከወጡ በኋላ ችላ ይሉታል፤ አይለማመዱም፣ ራሳቸውን መጠበቅ ይተዋሉ፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ አስመስሎ መዝፈን ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አስመስለህ የምትዘፍነው የራስህን ድምጽ ለማሻሻል እንጂ አላማህ ማስመሰል ብቻ ከሆነ፣ ራስህ ለዘለቄታው ትበላሻለህ፡፡ ውጭ አገር ዘፋኞች ለድምፃቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ መለማመድ መደበኛና የሁልጊዜ ስራቸው ነው፡፡ ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ይማራሉ፡፡
የአዳዲስ ባለተሰጥኦዎች ጉዳይ…
… ከስር የሚመጡ በጣም በጣም ሀይለኛ ልጆች አሉ፡፡ በየቦታው የሚጫወቱ፣ በትያትር ቤት የሚሰሩም ብዙ ጎበዝ ልጆችን አውቃለሁ:: አሁን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የተሻሉ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡
ሙዚቀኞች ኢንፎርሜሽን ያገኛሉ፤ የተለያዩ የሙዚቃ አይነቶችን፣ ዘፈኖችን፣ ስልቶችን፣ አሰራሮችን ያውቃሉ፡፡ ድሮ የተወሰኑ ነገሮች ብቻ ነበር የሚገኘው፤ ያውም ከውጭ ካሴት ለሚላክላቸው ጥቂት ሰዎች:: ዛሬ ግን ብዙ አማራጭ አለ፡፡ ከየአቅጣጫው እውቀትና ልምድህን የሚጨምርልህ ነገር በብዛት ታገኛለህ፡፡ እና ለሙዚቃ ትልቅ እድገት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡…