Administrator

Administrator

• ስለሜክሲኮ ግንብ እና ስለኦባማኬር ያሉት ነገር የለም
• ሄላሪን ወህኒ አስገባታለሁ የሚለውን ዛቻ እንደማይተገብሩት ተገልጧል

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባልተለመደ መልኩ ባለፈው ሰኞ በዩቲዩብ በኩል ባሰራጩት አጭር የቪዲዮ መልዕክት ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ቀዳሚነት ሰጥተው የሚያከናውኗቸውን ተግባራትና ዕቅዶቻቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡በመጀመሪያዎቹ 100 የስልጣን ቀናቴ ቀዳሚ ስራዎቼ ይሆናሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ያብራሩት ትራምፕ፣ ስልጣን በያዙ በመጀመሪያው ቀን የሚያከናውኑት የመጀመሪያው ነገር፣ ከትራንስ ፓሲፊክ የንግድ አጋርነት ስምምነቶች መውጣት እንደሆነ አስታውቀዋል ብሏል ሲኤንኤን፡፡ ትራምፕ ቀዳሚ ስራዎቼ ይሆናሉ ካሏቸው ጉዳዮች መካከልም፤ በፕሬዚዳንት ኦባማ የተቀመጡ
የአካባቢ ጥበቃ ክልከላዎችን ማስቀረትና የስራ ዕድሎችን መፍጠር የሚሉት ይገኙባቸዋል ብሏል ዘገባው፡፡
አሜሪካን ከተለያዩ ጥቃቶች መከላከል የሚያስችሉ እቅዶችን እንዲያወጡ ለሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች መመሪያ መስጠትም ከተቀዳሚ ስራዎቻቸው አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት ትራምፕ፣በሜክሲኮና በአሜሪካ ድንበር ላይ ግንብ ማስገባትንና
ኦባማ ኬር ተብሎ የሚታወቀውን የጤና መድህን ማስቆምን ጨምሮ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቧቸውን አነጋጋሪ ጉዳዮች በሰኞው መግለጫቸው አለማካተታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡ የስልጣን ሽግግር ቡድን አዲሱ መንግስታቸው በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች በማቀድና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመንደፍ ረገድ ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝና ዝርዝር መረጃዎችን ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርጉም ትራምፕ በቪዲዮ መልዕክታቸው አስታውቀዋል፡፡በተያያዘ ዜና ተቀናቃኛቸውን ሄላሪ ክሊንተንን በኢሜይል ቅሌታቸው ሳቢያ ወህኒ እንደሚያስገቧቸው ሲዝቱ የከረሙት ትራምፕ፣ሴትዮዋ በቅሌቱ ሰበብ ከገቡበት ቀውስ እንዲወጡ ድጋፍ ያድርጉላቸዋል እንጂ እንደዛቱት በኤሜይል
ሰርቨራቸው ላይ ምርመራ እንዲደረግ እንደማያዝዙ የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ አስታውቀዋል፡፡አማካሪዋን ኬልያኔ ኮንዌይን ጠቅሶ አይሪሽ ታይምስ እንደዘገበው፣ ትራምፕ ወደ ስልጣን ሲመጡ በሄላሪ የኢሜይል ቅሌት ዙሪያ ምርመራ በማስደረግ ለፍርድ የማቅረብ ሃሳብ የላቸውም፡፡

በ4 ወራት ጊዜ ከስራ የተባረሩ 125 ሺህ፣ የታሰሩ 36 ሺህ ደርሰዋል

ባለፈው ሃምሌ ወር ከተቃጣበት የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ በርካታ  ዜጎቹን በማሰርና ከስራ ገበታቸው በማፈናቀል ተጠምዶ የከረመው የቱርክ መንግስት፣ ተጨማሪ ከ15 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞችን ማባረሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ማክሰኞ በወሰደው እርምጃ ከስራ ገበታቸው የተፈናቀሉት እነዚሁ ቱርካውያን በውትድርና፣ በፖሊስ፣ በግብር ምርመራና በሌሎች የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ናቸው ያለው ዘገባው፣ ይህም ከሃምሌ ወዲህ ከስራ የተፈናቀሉና የታገዱ ዜጎችን ቁጥር ከ125 ሺህ በላይ እንዳደረሰው ገልጧል፡፡ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር ንክኪ አላችሁ በሚል
በአገሪቱ መንግስት የታሰሩ ዜጎች ቁጥር 36 ሺህ ያህል እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፣ መንግስት መሰልእርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ማስታወቁንም አብራርቷል፡፡ በተያያዘ ዜናም የቱርኩ መሪ ጠይብ ኤርዶጋን ተመራጩን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን አምባገነን ናቸው ሲሉ የሚተቹትን ጸረ- ዲሞክራሲ ናቸው በማለት ማውገዛቸው ተዘግቧል፡፡

የካዛኪስታን ርዕሰ መዲና አስታና ስያሜ እንዲቀየርና ከተማዋ በ76 አመቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኑርሱልጣን ናዛርባየቭ ስም እንድትጠራ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ በፓርላማ መውጣቱን ሮይተርስ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡ፓርላማው ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን በቅጡ በመምራት ላደገሩት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት በማሰብ ከተማዋን በስማቸው ለማስጠራት ያቀረበው እቅድ ስኬታማ የሚሆን ከሆነ፣ ወትሮም የግል ዝና በማካበት ሲታሙ የኖሩትንና ላለፉት 27 አመታት አገሪቱን ያስተዳደሩትን ፕሬዚዳንቱን የባሰ ሀሜትና ትዝብት ይጥላቸዋል ተብሏል፡፡የአገሪቱ ርዕሰ መዲና አስታና የሚለውን ስያሜ ላለፉት 18 አመታት ስትጠራበት እንደቆየችና ቃሉበካዛክ ቋንቋ ዋና ከተማ የሚል ትርጉም እንዳለው ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱ ፓርላማው ያቀረበውን የስያሜ ለውጥ እቅድ በተመለከተ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ምላሻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የፕሬዚዳንት ናዛርባየቭንፎቶ ግራፍ በመገበያያ ገንዘብ ላይ እንደሚያትምና ገንዘቡ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ በስራ ላይ እንደሚውል ባለፈው ሳምንት ማስታወቁንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

ታዋቂው የግል የኤሮስፔስ ኩባንያ ስፔስኤክስ መሰረቱን በህዋ ላይ ያደረገ አለማቀፍ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመዘርጋት የሚያስቸሉ ከ4 ሺህ በላይ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ማቀዱን አስታውቋል፡፡ ኩባንያው እቅዱን ለማሳካት የሚያስችሉትን 4
ሺህ 425 ሳተላይቶች የማምጠቅ ፈቃድ እንዲሰጠው ለአሜሪካ መንግስት ጥያቄ ማቅረቡን የዘገበው ዘ ዴይሊ ሚረር፣ የኩባንያው እቅድ የሚሳካ ከሆነ በየትኛውም የአለማችን ክፍል የሚገኝ ሰው የፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ገልጧል፡፡ የኩባንያው የህዋ የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት እስከ 23 ጊጋ ባይት በሰከንድ እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሮጀክቱ 10 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደሚደረግበት የኩባንያው ባለቤት ከዚህ ቀደም ማስታወቃቸውን አስታውሷል፡፡
ስፔስኤክስ የመጀመሪያውን ሳተላይት የሚያመጥቅበትን ትክክለኛ ጊዜ አለመግለጹን የገለጸው ዘገባው፣ ሳተላይቶቹ ወደ ጠፈር በተላኩ ከአምስት እስከ 7 ቸመታት ጊዜ በአገልግሎት ላይ እንደሚቆዩ አስረድቷል፡፡ በአሁኑ ሰአት ምድርን በመዞር ላይ የሚገኙ ስራ ያላቋረጡ ሳተላይቶች ቁጥር 1 ሺህ 419 ያህል እንደሆነም አክሎ ገልጧል፡፡

• አንድ ስዊዘርላንዳዊ በአማካይ 562 ሺህ ዶላር ሃብት አለው
• በአመቱ ጃፓን 20.1 ትሪሊዮን ዶላር ስታገኝ፣ እንግሊዝ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር አጥታለች

ክሬዲት ሲዩሴ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ሰሞኑን ባወጣው የ2016 አለማቀፍ የሃብት ስርጭት ሪፖርት፣ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ድሆች የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር ህንድ መሆኗንና በአገሪቱ 246 ሚሊዮን ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ አስታወቀ፡፡  
72 ሚሊዮን የከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የያዘቺው ቻይና በሪፖርቱ በሁለተኛነት ስትቀመጥ፣ ናይጀሪያ በ35 ሚሊዮን ከአለማችን አገራት ሶስተኛ ደረጃን መያዟንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በአለማችን በከፋ ድህነት ውስጥ ከሚገኙና ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ ቁጥር 20 በመቶ ያህሉን የሚሸፍኑት አንድ ቢሊዮን ያህል ሰዎች ውስጥ፣ ሶስት አራተኛ ያህሉ የሚኖሩት በእስያና በአፍሪካ አገራት ነው ያለው ሪፖርቱ፣ ሩስያና ዩክሬንም በርካታ ድሆች ያሉባቸው አገራት እንደሆኑ ገልጧል።
በአለማችን  33 ሚሊዮን ያህል የሚሆኑና ከአንድ ሚሊዮን እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ሃብት ያካበቱ የተለያዩ አገራት እጅግ ባለጸጋ ዜጎች እንዳሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከእነዚህም መካከል 45 በመቶው አሜሪካውያን መሆናቸውን አስታውቋል።
እጅግ እጅግ ባለጸጎች በሚለውና ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ያካበቱ የናጠጡ ሃብታሞች በሚካተቱበት መደብ ውስጥ የተቀመጡ የተለያዩ የአለማችን አገራት ዜጎች ቁጥር 140 ሺህ 900 ያህል ደርሷል ያለው ሪፖርቱ፣ ግማሽ ያህሉ አሜሪካውያን፣ 11 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ቻይናውያን ናቸው ብሏል፡፡
እያንዳንዱ አዋቂ ዜጋዋ በአማካይ 562 ሺህ ዶላር ያካበተባት ስዊዘርላንድ የአለማችን ቁጥር አንድ የሃብታሞች ሃገር ናት ያለው ሪፖርቱ፣ አውስራሊያ በ376 ሺህ ዶላር፣ አሜሪካ በ345 ሺህ ዶላር እንደሚከተሏት ያትታል፡፡
በአለማችን በአመቱ ከፍተኛውን የሃብት መጠን ጭማሪ ያሰመዘገበቺው አገር ጃፓን ስትሆን፣ የአገሪቱ የሃብት መጠን ከ3.9 ትሪሊዮን ዶላር ወደ 24 ትሪሊዮን ዶላር አድጓል ተብሏል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በአመቱ የከፋውን የሃብት ኪሳራ ያስተናገደቺው እንግሊዝ መሆኗንና፣ አገሪቱ አንድ እና አንዱ ባልለየለት የአውሮፓ ህብረት አባልነት ሪፈረንደም ሳቢያ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ማጣቷን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡





     ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻቸው የሆነውን ታላቁን የፕሬዚዳንቱ የነጻነት ሜዳይ ሽልማት ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በዋይት ሃውስ በተካሄደ ስነስርዓት ለ21 ታዋቂ አሜሪካውያን አበርክተዋል፡፡
ኦባማ የእኔ ጀግና ያሏቸውና ታላቁን የነጻነት ሜዳይ ያጠለቁላቸው 21 አሜሪካውያን በተለያዩ መስኮች ለአገራቸውና ለህዝባቸው የጎላ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆኑ  የፊልምና የመዝናኛ ዘርፍ ዝነኞች፣ ሳይንቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ በጎ አድራጊዎችና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ መሸለማቸው ታውቋል፡፡  
“ሁሉም የዕለቱ ተሸላሚዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በግሌ ተጽዕኖ የፈጠሩብኝ ናቸው” ሲሉ ተሸላሚዎችን አድንቀዋል፤ ኦባማ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
ኦባማ የአሜሪካን ትልቁ የሲቪል ሽልማት  በክብር ካበረከቱላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ አሜሪካውያን መካከል፣ ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ የፊልም ከዋክብቱ ቶም ሃንክስና ሮበርት ዲ ኔሮ፣ ከበጎ ምግባር ስራዎች ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ፣ ከስፖርት ካሬም አብዱል ጀባርና ማይክል ጆርዳን ይገኙበታል፡፡ ከዘንድሮ ተሸላሚዎች በእድሜ ትንሹ የ53 አመቱ የቀድሞው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን ሲሆን፣ በዕድሜ ትልቁ  ተሸላሚ ደግሞ የ91 አመት የእድሜ ባለጸጋዋ ተዋናይት ሲስሊ ታይሰን ናቸው፡፡

ናሁሰናይ በላይ
(በአ.አ.ዩ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፌደራሊዝም መምህር

ሹም ሽር መደረጉ፣ መንግስት የለውጥ ፍላጎት እንዳለው፣ ምልክት እንደማሳየት ነው፡፡ “የለውጥ ፍላጎት አለኝ፤ ፍላጎቴንም በዚህ በሹም ሽር እዩት” የሚል ምልክት ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን፣ ከገጠመን ችግር አንፃር ሲታይ የሚያስፈነጥዝ አይደለም፡፡
እርግጥ ነው፣ ያመጣው ነገር አለ፡፡ እውቀት እና ስራ መገናኘት አለባቸው የተባለ ይመስላል፡፡ እውቀትና ስልጣን ሲገናኙ፣ የተሻለ ነገር መስራት ይቻላል የሚል አቅጣጫ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ይሄ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን መጠንቀቅ አለብን፡፡
ኢትዮጵያ ላይ የተከሰተው ችግር፣ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ የመንግስት ቅቡልነት ቀውስ ውስጥ የገባበት ነው፡፡ በጣም ጉልህ የስራ አጥነት ችግር አለ፡፡ እንግዲህ ከገጠመን ችግር አንፃር፣ የመንግስት ጥረት በሹም ሽር የሚያበቃ ከሆነ፣ ሌላ ራሱን የቻለ ችግር ነው የሚሆነው፡፡ ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም፣ ከአገሪቱ ችግር አንፃር ትንሽ ነው፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶችን ግምገማ በተመለከተ፣ እኔ ከግምገማዎቹ ብዙ አልጠብቅም፡፡ ኢህአዴግ ችግሩን በቅጡ ያወቀው አልመሰለኝም፡፡ አሁን የችግሩን ምልክቶች ነው እያሯሯጠ ያለው፡፡ በሽታውን ሳይሆን የበሽታውን ምልክቶች ነው እያከመ ያለው፡፡
በዚህ ሁኔታ አሚካሄድ ግምገማና ብወዛ፣ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ አልጠብቅም፡፡ በእርግጥ፣ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ጥሩ የመሻሻል ምልክት ታይቷል፡፡ የተማረና አቅም ያለው፣ ወጣት አመራር ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በተቃራኒው በህውሓትና በብአዴን በኩል ሲታይ ደግሞ፣ ፍላጎቱ ያላቸው አይመስልም፡፡ ወንበሩን እንደርስት የያዙ ሰዎች፣ በዚያው እንዲቀጥሉ የሚያስቡ ይመስላል፡፡
ስለዚህ ኢህአዴግም መንግስትም፣ የችግሩን መሰረታዊ ባህሪ በቅጡ ሳይረዱ፣ ችግሩን ያክማል ብለው የሚያመጡት መድኃኒት፣ ችግሩን ከማከም ይልቅ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት አለኝ። ዋናው የኢህአዴግ ችግር የሚመስለኝ፣ ችግሩን አለማወቁ ነው፡፡ ወይ ለማወቅ አለመፈለግ፣ አሊያም ለማወቅ አለመቻል፡፡
የፌደራል ስርአቱም ሆነ ህገ መንግስቱ፣ ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ ፖለቲካው ህገ መንግስቱን መምሰል ስላልቻለ ይመስለኛል እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባነው፡፡ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ሊኖር የሚገባው ህግንና ህግን ብቻ መሰረት ያደረገ አሰራር፣ ገና አልተፈጠረም። ይሄ የእገሌ ወይም የእገሊት ድክመት አይደለም፡፡ ግን አሁን የተፈጠረውን ችግር ከግለሰቦች ባህሪ ጋር ያገናኙታል፡፡ ይሄ ተስፋን የሚያጨልም ነው፡፡
የፖለቲካ ስርአት ሊበላሽ የሚችለው፣ ከግለሰብ በመነጨ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ግለሰቦች ስልጣን ሲያገኙ አይበላሹም ማለቴ አይደለም፡፡ የሚበላሹ ግለሰቦች ሁሌም የትም አገር ይኖራሉ፡፡ ዋናው ነገር፣ የፖለቲካ ስርዓቱ፣ ባለስልጣናት እንዳይበላሹ የሚቆጣጠር መሆኑና አለመሆኑ ላይ ነው፡፡ ችግሩን በዚህ መንገድ አይቶ ሳይንሳዊ ጥናትና ትንታኔ መስራት ካልተቻለ፣ “እንታደሳለን፤ ቃል እንገባለን” ማለት ብዙም አያስኬድም፡፡

አንድ የቻይና ተረት የሚከተለውን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ልጆቻቸውን ሰብስበው፣
“ልጆቼ፤ እስከዛሬ መቼም በክፉም በደግም መንበሬ ላይ ሆኜ ሳስተዳድር ታውቁኛላችሁ፡፡ አሁን እርጅናም እየመጣ ነው፤ ሆኖም ለአንዳችሁ መንግሥቴን እንዳወርሳችሁ፤ በማስተዳድር ጊዜ የሰራሁት ጥፋት ካለ ንገሩኝ፡፡ ከእናንተ መካከል ለማን ማውረስ እንዳለብኝ እንዳመዛዝን ይጠቅመኛል” አሉ፡፡
ልጆቹ እርስ በርሳቸው መተያየት ጀመሩ፡፡ ሀሳባቸው ተከፋፈለ፡፡ ከፊሎቹ ንጉሱን በማወደስ ወንበሩን ለማግኘት ቋመጡ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ዕውነቱን ተናግረን ያሉትን ይበሉ አሉና ሀሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡
1ኛው/ “ንጉሥ” ሆይ! እንደርሶ ያለ መሪ በዓለም ታይቶ አይታወቅም፡፡ ሁሉን እኩል ያያሉ። ለሁሉም ፍትሐዊ ነዎት፡፡ ሰብዓዊ መብት እንዳይረገጥ ሌት ከቀን ሲለፉ ኖረዋል፡፡ ከላይ እግዚአብሔርን ከታችም እርስዎን የሚፈራ ህዝብ ፈጥረዋል፡፡ እኛ ልጆችዎ በእርስዎ እንድንወጣ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደኖሩ ማንም አይጠራጠርም፡፡ አምላክ ዕድሜዎን ያርዝምልን እንጂ ውርሱ አይጠቅመንም” አለ፡፡
2ኛ/ “እርሶን የመሰለ ንጉሥ ፈፅሞ እግር እስኪነቃ ቢኬድ አይገኝም፡፡ በተለይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ባለዎት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንፃር ወደር የለዎትም” አለ፡፡
3ኛ/ “በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ ሥራ፣ ያመጡልን የዕድገት ውጤት ከአህጉራችን አንደኛ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ፀሎታችን እድሜዎትን እንዲያረዝምልን ነው” አለ፡፡
በዚህ ዓይነት ስድስቱ ልጆቻቸው የንጉሡን ደግነትና ርህራሄ፣ በህዝብ ያላቸውን ተወዳጅነት እያሞገሱ ብዙ ተናገሩ፡፡ በመጨረሻ ግን ሰባተኛው ልጃቸው ተነስቶ መናገር ጀመረ፡-
“በበኩሌ ስልጣን አልፈልግም፡፡ ስለዚህ እውነትን መናገር እመርጣለሁ፡፡ ንጉሥ ሆይ! በመጀመሪያው የግዛት ዘመንዎ ደህና አስተዳደር ነበረዎ፡፡ ትዕግሥት ነበረዎ፡፡ ወገናዊነት አልተፈታተነዎትም ባይባልም፤ ከሞላ ጎደል ዲሞክራሲያዊና ለሰው አሳቢ ነበሩ፡፡ ፍርድ ቤቶቹም ቀናና ለተበደለ ፍትህን የሚሰጡ ነበሩ፡፡ መብቶች እንደሚከበሩና ሀብት በአግባቡ እንደሚዳረስም ቃል ገብተው ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመንዎ ሁሉም ነገር ፈሩን እየሳተ መጣ፡፡ በመጨረሻውና አሁን በደረስንበት የግዛት ወይም የግዝት ዘመንዎ ግን ነገሩ ሁሉ ተገለባበጠ፡፡ ሙስናና ጉቦ የዕለት ሁኔታ ሆነ፡፡ ቁጥጥር ጠፋ፡፡ እንዲያውም አመራሮችም ሳይቀሩ ተዘፈቁበት፡፡ “የአሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” የሚለው ምሳሌ በዐይን ታየ፡፡ እርሶም እጅዎን ሰብስበው ተቀመጡ፡፡ የአስተዳደር ብልግና የማያስጠይቅ መሰለ፡፡ ሹም ሽር ቢያካሂዱም ቦታ መለዋወጥ እንጂ ሥርዓትዎ ስላልተለወጠ ከድጡ ወደ ማጡ መኬድ ቀጠለ፡፡ እንደ እርሶ ዕድሜ ማርጀት ሁሉ ሥርዓቱም እያረጀ ነው፡፡ “አዲስ ወይን በአሮጌ ጋን” ከመሆኑ በስተቀር ለውጥ አልተጠመቀም፡፡ አልታየም፡፡ አሁንም ሳንዋሽ ዕውነቱን አውጥተን ካልተነጋገርን መሸፋፈኑ አይጠቅመንም፤ ንጉስ ሆይ!” አለ፡፡
ንጉሡም፤
“በመጀመሪያ የተናገራችሁት ልጆቼ፤ ያሞገሳችሁኝንም፣ ዕድሜ የተመኛችሁልኝንም አመሰግናችኋለሁ፡፡ ከእናንተ ጋር በተሰበሰብን ጊዜ ሁሉ ስሰማው የኖርኩት ነው፡፡ የመጨረሻው ልጄ የተናገርከው ነገር ግን፤ ዕውነተኛው መልካችን ነው፡፡ ከፍተኛው ምሥጋናም የሚገባህ ላንተ ነው። መንግስቴንም የማወርሰው ላንተ ነው! ምክንያቱም አገር ለመለወጥ የምትችል አንተ ነህ!” ብለው አሰናበቷቸው፡፡
*      *     *
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ!”
ይለናል ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፡፡ አስመሳዮችና አድር ባዮችን ተማምነን፤ መልካም የሰራንና የተሻለ አቋም ላይ ያለን ከመሰለን፤ ስህተታችን ከዚያ ይጀምራል፡፡ ከቶም መልካም አስተዳደር በሙገሳ እንደማይገኝ ያለፉት አመታት በማያወላዳ ሁኔታ አረጋግጠውልናል፡፡ መሸነጋገል እንደማያዋጣም ተገንዝበናል፡፡ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ የተጠያቂነት ስርዓት፣ ግልፅነት፣ የማንነትና የባለቤትነት ጥያቄ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የሲቪክ ማህበራት ማደራጀት፣ መመሪያዎችን በለበጣ ሳይሆን ከልብ የመተግበር አሰራር፣ ወዘተ ከአፍ አልፎ በስራ የሚገለጥበት፤ በተስፋና በዱቤ ሳይሆን “እጅ - በጅ ፍቅር እንዲደረጅ” የሚባልበት፣ እንዲሆን ከተፈለገ፤ ግምገማዎች ሀቅን የተንተራሱ፣ መሬት የነከሱ እንዲሆኑ፤ ከልብ ማመን ግድ ነው! መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒ የሚሆኑት የመንግሥት ደጃፎች መረጃ ለመስጠት ክፍት ሲሆኑ ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች እንዳይደመጡና እንዳይነበቡ የሚሆኑት … የማጋነኛ መድረኮች ሲሆኑና ዕውነት - ጠለቅ ሳይሆኑ፣ “የጌታዬ ቃል የእኔ ቃል” በሚል መርህ ስለሚጓዙ ነው፤ ለማለት ይቻላል፡፡
“ለመቶ አምሳ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ
አለቀ በላዬ”
ማለት የዱሮ ፈሊጥ ይምሰል እንጂ “የሆድ የሆዳችንን እንነጋገር” በሚለው ህዝብ፣ በምሁሩ፣ በነጋዴው፣ በተማሪው፣ በዜጋው ሁሉ የሚብሰለሰለው ሀሳብ ይሄንኑ ፈሊጥ የሚገልጥ ነው፡፡ ግምገማዎች ከመፈራራት፣ ከእከክልኝ ልከክልህ፣ ከአሞግሰኝ ላሞግስህ፣ ከሾሜሃለሁ ትሾመኛለህ/ትክሰኛለህ፣ ከ “ይሄን ተናግረህ ሰው አያረጉህም” አስተሳሰብ፣ ካልፀዱ ዋጋቸው አናሳ ነው፡፡ ወይም አክሳሪ ነው፡፡ በጥናትና በፅናት መካከል ገደል አከል ልዩነት አለ፡፡ አንዱ ዘዴ፣ አንዱ መስዋዕትነት ጠያቂ ነው፡፡ የህዝብ ብሶት አራምባ፣ የግምገማው መንፈስ ቆቦ ከሆነ ውጤቱ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ነው፡፡ ያልተዘራ አይታጨድምና እናስብበት፡፡ በየግምገማው አድርባዮች ዥዋዥዌያቸውን ከቀጠሉ፣ አመራሮች ከአንገት በላይ “ተሳስተን - ነበር” ማለቱን እንደ አዘቦት ሰላምታ ከለመዱት፣ የበታች ምንዝሩም “ይሄ ቃል ተገብቶልን አልተፈፀመልንም” ማለቱን የዕለት ፀሎት ያህል መደጋገሙን እንጂ ሰርንቆና ገትቶ ተግባራዊነቱን ካልተቆጣጠረ፣ ወጥሮም ካልታገለ፣ ከህዝብ እሮሮና በደል አንፃር ስናየው፣ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ይሆናል፡፡ እናስብበት፡፡ ግምገማዎች ወደ አደባባይ ተግባር ያምሩ እንጂ፤ የአዳራሽ ቴያትር ሆነው አይቅሩ!

 ጃኪ ቻን ከ56 አመታት በኋላ ኦስካር ተሸለመ፤
              ከ200 በላይ ፊልሞችን ለእይታ አብቅቷል
    የ2016 የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ጸሃፊ ቦብ ዳይላን፣ በመጪው ታህሳስ ወር መግቢያ በስቶክሆልም በሚከናወነው የኖቤል ሽልማት ስነስርዓት ላይ እንደማይገኝ ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
የ75 አመቱ ቦብ ዳይላን፣” በስነስርዓቱ ላይ ተገኝቼ ሽልማቱን ብቀበል ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖ ግን ሌሎች ፋታ የማይሰጡ ጉዳዮች ስላሉብኝና ስራ ስለበዛብኝ ልገኝ አልችልም” ሲል ለኖቤል አካዳሚ በላከው ደብዳቤ ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የሽልማት አካዳሚው የቦብ ዳይላንን ውሳኔ እንደሚያከብር ገልጾ፣ እንዲህ ያለው ውሳኔ ያልተለመደ ቢሆንም ሽልማቱን በአካል ተገኝቶ ባለመቀበል፣ ቦብ ዳይላን የመጀመሪያው ሰው አለመሆኑን ጠቁሞ፣ ድምጻዊውን በመወከል ሽልማቱን የሚቀበለው ሰው ማንነት ገና አለመታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
አካዳሚው የቦብ ዳይላንን ተሸላሚነት ይፋ ያደረገው ከአንድ ወር በፊት ቢሆንም፣ ተሸላሚውን ለማግኘት እጅግ ተቸግሮ መቆየቱና ዳይላንም ባልተለመደ መልኩ ሽልማቱን በተመለከተ ለሳምንታት ምንም አይነት አስተያየት አለመስጠቱ ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡ በተያያዘ ዜና ላለፉት 56 አመታት በፊልሙ ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆየውና አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፈው የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፣ ገቨርነርስ አዋርድ የተባለውን የኦስካር የክብር ሽልማት ባለፈው ሳምንት መቀበሉ ተዘግቧል፡፡ ጃኪ ቻን በየአመቱ በፊልሙ ኢንዱስትሪ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሙያተኞች የሚሰጠውን ገቨርነርስ አዋርድ የተባለውን የኦስካር የክብር ሽልማት ባለፈው ቅዳሜ በሎሳንጀለስ በተካሄደ ስነስርዓት መቀበሉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በረጅም አመታት የሙያ ቆይታው ከ200 በላይ ፊልሞችን በተዋናይነትና በዳይሬክተርነት ለእይታ ያበቃው የ62 አመቱ የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፣ አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸርስ አርትስ ኤንድ ሳይንስስ ባዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ተገኝቶ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ ጃኪ ቻን በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረገው ንግግር፤ በሽልማቱ መደሰቱን ገልጾ፣ ከ56 አመታት በላይ በዘለቀው የፊልም ስራ ቆይታው፣በርካታ ፈተናዎችን እንዳለፈ በማስታወስ፣ ለወደፊትም ሌሎች አዳዲስ ፊልሞችን መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

  ከታክስ በፊት ከ428 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ
       ሕብረት ባንክ ያለፈው ዓመት 2008 (ጁን 30 2016) የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገሪቱ ላሉ ባንኮች ፈታኝ ሆኖ ቢያልፍም፣ ባንኩ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 13.63 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከግል ባንኮች 4ኛ ደረጃ ሊይዝ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የባለ አክሲዮኖች 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ያደረገ ሲሆን የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ ዛፉ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከቀደመው ዓመት  ጋር ሲነፃፀር 25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱና፣ ከግብር በፊት የተኘው ትርፍም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 358.2 ሚሊዮን ብር ጋር ሲተያይ ወደ 428.5 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከቀደመው ዓመት (2007) ከነበረው 11.7 ቢሊዮን ብር 16.2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 13.63 ቢሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከቀደመው  ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ24.4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 8.53 ቢሊዮን ብር በመድረሱ የተገኘው ውጤት አመርቂ ነው ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአገሪቷ ወጪ ንግድ በመቀነሱ ከዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከካቻምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ቀንሷል፡፡ አምና ከዓለም አቀፍ ባንክ ዘርፍ የተገኘው ገቢ 2.98 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የበጀት ዓመቱ 4.71 በመቶ ቀንሶ 2.84 ቢሊዮን ዶላር ወይም 400.9 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም የባንኩን አጠቃላይ ገቢ 23 በመቶ እንደሚሸፍን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አያደር ሲብስበት እንጂ ሲሻሻል የማይታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሥራቸው እንቅስቃሴ ስጋት መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ዛፉ፤ ስጋቱን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ ከሁለት ዓለም አቀፍ የካርድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማለትም ከቪዛ ኢንተርናሽናልና ከቻይና ዩኒየን ፔይ ጋር መሥራት ጀምረናል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች የባንኩ አጋር መሆን ለንግድ ተጓዦችና ቱሪስቶች የምናቀርበውን አገልግሎት ምቹና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ባንኩ ጁን 30 2016 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ በተከፈለ አክሲዮን ላይ 25 በመቶ የትርፍ ክፍያ አንዲደረግ የዲሬክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 17.3 ቢሊዮን፤ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል 1.25 ቢሊዮን ብር ሲሆን ባንኩ 2,998 ባለአክሲዮኖች እንዳሉት ታውቋል፡፡
ተደራሽነትን ከማስፋፋት አኳያ ባንኩ 161 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ የሰው ኃይሉም 3,123 ደርሷል፡፡ በበጀት ዓመቱ 438 ሠራተኞ የተቀጠሩ ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ በ289 ሰራተኞች ብልጫ አለው፡፡ 149 ሠራተኞች ደግሞ ባንኩን ለቀዋል፡፡