Administrator

Administrator

“...ሁልጊዜ ጥሩ አስተያየት የሚሰጡኝን ሁለት ሰዎች በጣም እወዳቸዋለሁ፡፡ በሚያዩኝ ጊዜ ሁሉ ...ኦ...ዛሬ በጣም ጥሩ ነሽ፡፡ እርግዝናውም ቀለል ብሎሻል፡፡ ይሄ የሆድሽ ከፍታ እኮ ከትንሽ ጊዜ በሁዋላ ይቀላል፡፡ በተለይም ሊወለድ ሲል በጣም ይቀል ሻል፡፡ አይዞሽ የሚል አስተያየትን ከእነርሱ መስማት በጣም ያስደስተኛል ...ትላለች ፡፡በአሁኑ ወቅት እርግዝናዬ 34ኛ ሳምንቱን ይዞአል የምትለው ወይዘሮ፡ በተጨማሪም እንዲህ ትላለች፡፡ “… እኔ ለነገሩ በእርግዝናው ምክንያት በሚፈጠረው ሆርሞን ምክንያት ምንም ነገር ቢነገረኝ እንዳያናድደኝ ስለምጠነቀቅ ነው እንጂ እንኩዋንስ የማይሆን ነገር ተናግረ ውኝ ቀርቶ ደህናም ነገር ቢያወሩኝ በጥርጣሬ የምቀበል ሆኛለሁ፡፡ እስቲ በዚህ ጉዳይ የተለያዩ አባባሎችን ...ማለትም ከሰዎች የወሰድኩዋቸውን አንብቡ ብላለች አሊሰን ፋክለር...፡፡ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር ባለፈው እትም ስለ ማህጸን ውጭ እርግዝና ያብራሩትን ካስነ በብናችሁ በሁዋላ አሊሰን ፋክለር በእርግዝና ጊዜ መነገር የሌለባቸው ያለቻቸውንና ከአገር ውስጥም ልምዳቸውን ያካፈሉንን አካተን ለንባብ እንላለን፡፡

“.....እንደሚታወቀው እርግዝና የሚፈጠረው በወንዱ ዘርና በሴቷ ዘር ግንኙነት መንስኤነት ነው፡፡ይህ በጤናማ መልኩ የተፈጠረ ከሆነ የሚገኘው በዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ላይ ነው፡፡ በዚያም የተወሰነ ቀን ካሳለፈ በሁዋላ የተወሰነ የሰውነት ገንቢ ሕዋሳቶች ደረጃ ላይ ሲደርስ ወደ ዋናው የማህጸን ክፍል ውስጥ ይገባል፡፡ በማህጸን ውስጥም እርግዝናው እስኪጨርስ እና አድ ጎም ለመወለድ እስኪደርስ ድረስ ይቆያል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ይህ ሂደት ሊዛባ ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ጽንሱ ወደ ማህጸን ከመሄዱ ይልቅ የተለያየ ቦታ በመቅረት ባለበት ቦታ እድገቱን ይጀምራል፡፡ በተለይም በዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ጫፍ ወይንም መሃል አለበለዚያም ወደ ማህጸን ተጠግቶ ሊያድግ ይችላል፡፡ ከዚህም ውጭ ጽንሱ እንደተፈጠረ ዝም ብሎ ሆድ እቃ ውስጥ በመውደቅ ሞራ ላይ ወይንም አንጀት ላይ እና በመሳሰሉት አካላት በመጠጋት በዚያው እድገቱን ሊጀምርም ይችላል፡፡.. ከላይ ያስነበብናችሁ የማህጸን ውጭ እርግዝና እንዴት እንደሚፈጠር የሚያስረዳውን ባለፈው እትም ዶ/ር መብራቱ ጀምበር ያብራሩትን ነበር፡፡ በተለይም በሆድ እቃ ውስጥ ሰለሚኖረው ከማህጸን ውጭ እርግዝና ሲገልጹ፡- “...ከማህጸን ውጭ እርግዝና ከሁለት እስከ ሶስት ወር ድረስ አደጋ የሚከሰትበት ወቅት ነው፡፡

ነገር ግን በሆድ እቃ ውስጥ የሚያርፈው ከማህጸን ውጭ እርግዝና አልፎ አልፎ እስከመጨረሻው የእርግዝና ወቅት ድረስ ደርሰው በሰላም ልጆቻቸውን የተገላገሉ አሉ፡፡በእርግጥ እርግዝናው በማህጸን ውስጥ እንደሚኖረው እርግዝና ሳይሆን አስቸጋሪና ከበድ ያለ ነው፡፡ በሆድ እቃ ውስጥ ያሉ ሌሎች አካላት ጨጉዋራ፣ ጉበት...ወዘተእንዳሉ ሆነው እርግዝናው ግን ባገኘው ክፍት ቦታ ላይ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር የእንግዴ ልጁ የደም ስር ሊያገኝ እና ሊያድግ የሚችልበት ቦታ መሆን አለበት፡፡ እንግዴ ልጁ የሚመቸው ቦታ ላይ ካረፈ በሁዋላ ለልጁ ከእናቱ ደም ስቦ አጣርቶ በመመገብ እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡ እርግዝናው በማህጸን ውስጥ ባለመሆኑ መጥፎ አጋጣሚ ነው ተብሎ ቢፈረጅም ልጁን በሰላም እስከመጨረሻው ጠብቆ መገላገል ግን እድለኝነት ይባላል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ በቅርብ ጊዜ የተፈጸመ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ያሉ ክኖሎ ጂዎች ባልነበሩበት ወቅት የነበረ አጋጣሚ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ግን አስቀድሞውኑ ጽንሱ የተፈጠረበት ስፍራ በምርመራ ስለሚታወቅ አደጋ ከማስከተሉ በፊት እርምጃ ይወሰ ዳል፡፡ አስቀድሞ በነበረው የህክምና ዘዴ ግን በሆድ እቃ ውስጥ የሚፈጠረው እርግዝና እስኪወለድ ድረስ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ እንዳይደርስ ከመናፈቅ ባለፈ የሚደረግ ነገር አልነበረም፡፡ ጽንስ በማህጸን ውስጥም ሆነ በሆድ እቃ ውስጥ ሲረገዝ የራሱ የሆነ መሸፈኛ ይኖረዋል፡፡ ጽንስ በማህጸን ውስጥ ሲያድግ ላስቲክ መሰል በሆነ ስስ ሽፋን ውስጥ ሆኖ በሽፋኑ ውስጥ የሽርት ውሀ ከቦት ነው የሚያድገው፡፡ በእርግጥ ሽፋኑ እንደላስቲክ ስስ ሳይሆን ጠንከር ያለ እና ሞራ መሰል መልክ ያለው ነው፡፡ ይህ አፈጣጠር ጽንሱ በሆድ እቃ ውስጥም በሚፈጠ ርበት ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ ተሸፍኖ ስለሆነ ባለበት ቦታ ምንም ባእድ ነገር ሳያገኘው ሊያድግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እርግዝናው ምን ያህል እንደሚቀጥል ማወቅ ስለማይቻል ዝም ብሎ እስከመጨረሻው መጠበቅ ያስቸግራል፡፡

ከማህጸን ውጭ በሆድ እቃ ውስጥ የተረገዘ ጽንስ የሚወለደው ካለምንም ችግር በኦፕራሲዮን ይሆናል፡፡ በማህጸን ውስጥ የተረገዘን ልጅ በኦፕራሲዮን ለማዋለድ በመጀ መሪያ የሆድ እቃ ከዚያ በሁዋላ ደግሞ ማህጸን ተከፍቶ ሲሆን እርግዝናው በሆድ እቃ ውስጥ ከሆነ ግን እንዲያውም በቀላሉ ሆድ እቃን ብቻ በመክፈት ማገላገል ይቻላል፡፡ የማዋለዱን ተግባር ልዩ የሚያደርገው ግን እንግዴ ልጁ በዚያው መቅረት ስለሚገባው ነው፡፡ የእንግዴ ልጅን ለማውጣት ትግል ከተፈጠረ ደም የመፍሰስ ነገር ስለሚከሰት አደጋ ላይ መውደቅን ያስከትላል፡፡ ስለዚህም እትብቱን ቆርጦ ልጁን ከማውጣትና አንባቢውን ከማጽዳት ያለፈ ምንም አይደረግም፡፡ እንግዴ ልጁ በዚያው እንዲጠፋ ይተዋል ፡፡ በማህጸን የተረገዘ ልጅ ሲወለድ የእንግዴ ልጁ በጥንቃቄ የሚወገድ እና ይቅር ቢባልም አደጋን የሚያስከትል ሲሆን በሆድ እቃ ውስጥ ግን ምንም ችግር ሳያስከትል በራሱ ጊዜ እንዲጠፋ ይደረጋል፡፡

ከማህጸን ውጭ የተረገዘ ልጅ እንቅስቃሴው ፊት ለፊት በቀላሉ የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም በማህጸን ውስጥ እንዳለው ልጅ በሁለተኛ ደረጃ በማህጸን ግድግዳ ተሸፍኖ ስለማይገኝ ነው፡፡ በምጥ መውለድን በሚመለከትም በሆድ እቃ የሚኖር እርግዝና በትእግስት በሚጠበቅበት ዘመን በክሊኒክ በሚቆጠረው የጊዜ ቀመር በመመስረት በኦፕራሲዮን እንዲወለድ ይደረጋል እንጂ እንደ መደበኛው እርግዝና ምጥን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ከማህጸን ውጭ እርግዝና በዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥም ይሁን በሆድ እቃ ውስጥ ሲፈጠር አደጋ የሚያስከትልበት ሁኔታ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡ በተለይም ከሁለት እስከሶስት ወር ድረስ ባለው ጊዜ ከሚከሰተው አደጋ ዋናው የደም መፍሰስ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ጽንሱ ያለበት ቦታ እስከመጨረሻው ስለማያሳድገውና መቀደድ ስለሚጀምር ነው፡፡

ይህንን ሁኔታ የሚያባብሰውም እርግዝና በሚፈጠርበት ጊዜ እርግዝናው ባለበት አካባቢ እርግዝናውን ለማሳደግ የደም ስሮች በብዛት ስለሚፈጠሩ ጽንሱ ያለበት ቦታ ሲፈነዳ ደም በኃይል እንዲፈስ ስለሚያደርግ ነው ፡፡ይህ የደም መፍሰስም ሴትየዋን እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ ከማህጸን ውጭ እርግዝናን አስቀድሞ መወቅ የሚቻልባቸው ምልክቶች አሉ፡፡ እርግዝናው መኖሩ ከተረጋገጠ በሁዋላ ከማህጸን ደም መፍሰስ ሊጀምር ይችላል፡፡ ከእምብርት በታች ባለው የሰ ውነት ክፍል ሕመም ሊኖር ይችላል፡፡ እግርን የመያዝ አይነት ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡ እርግዝናው ውጥረቱ እየጨመረ ሲሄድ ከመፈንዳቱ በፊት የተገለጹት ስሜቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡በእርግጥ ሌሎች የጤና ሁኔታዎችም ተመሳሳይ የህመም ምልክቶችን ሊያሳዩ እንደሚችሉ መገመት ያስፈልጋል፡፡

ማንኛዋም ሴት የወር አበባዋ በሚቀርበት ጊዜ ገና ከጅምሩ ወደሐኪም ዘንድ ቀርባ ምርመራዋን ብትጀምር ሁኔታው አደጋ ከማስከተሉ በፊት እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል እንደ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ማብራሪያ፡፡ ለእርጉዝ ሴቶች ሊነገሩ የማይገባቸው ነገሮች፡- እርግጠኛ ነሽ ...መንታ ላለማርገዝሽ? አንቺ ...ሆድሽ ሊፈነዳ ደርሶአል እኮ...ከዚህ በላይ መቆየት የምትችይ ይመስልሻል? የእኔ ሚስት አኮ አምስት ልጅ ወልዳለች፡፡ ግን እንዳንቺ ሰውነቷ አልተበላሸም፡፡ ለመሆኑ ሐኪምሽ ምን ይልሻል? በእርግጥ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነሽ? አትናደጂ፡፡ ግን እርግዝና ነው ወይንስ ሌላ ነገር? መልክሽ እንዲህ የጠቆረው በጤና ነው? መልክሽ እንዲህ እስኪጠፋ ድረስ ያሳበጠሽ በእርግጥ እርግዝናው ብቻ ነው? አንቺ...ምን መሰልሽ? ምነው እርግዝናው ቢቀርስ? ...ወዘተ ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ነገሮችን ለእርጉዝ ሴቶች ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይም አርግዞ በመውለድ ዙሪያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ከመንገር ይልቅ ሴትየዋ በትክክል ወደሐኪም ሄዳ እርዳታ ማግኘት የምትችልበትን መንገድ መምከር ይገባል፡፡

  • ኳሷን ማሸነፍ ማለት ለእያንዳንዷ ኳስ ትኩረት መስጠት ነው
  • አጥቂዎች አንድ እድል ሲያገኙ አንድ ጎል ለማግባት ማሰብ አለባቸው
  • አጥቂዎች ወደ ጎል የሚሞክሯቸውን ኳሶች መሬት አስይዘው ይምቱ
  • ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ማለት የአገር ገጽታን ሊቀይር የሚችል ነው


ኳስ ተጨዋች ነበር፡፡ ከ16 ዓመት በፊት በአርሰናል ተጠባባቂ ቡድን ውስጥ ለ6 ወራት የሙከራና የልምምድ ጊዜ አሳልፏል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስም ተጨዋች ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያሬድ ተስፋዬ የተዋጣለት ነጋዴ ሆኗል፡፡ በመዝናኛ ዘርፉ ላይ የሚሰራው ያሬድ፤ የታዋቂው ፕላቲኒዬም የምሽት ክለብ ባለቤት ነው፡፡ ፕላቲኒዬም የፈርኒቸር ማምረቻ የሚባል ድርጅትም አለው፡፡ ቢቲ ትሬዲንግ በተሰኘ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አስመጭ ኩባንያ ውስጥም ከቤተሰቡ ጋር እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ አሁን ያሬድ ወደ ስፖርቱ ለመመለስ አስቧል፡፡ ይህን ሃሳቡን በመደገፍም አብሮት የተማረው ጋዜጠኛ አማን ከበደ እያበረታታው እንደሆነም ይናገራል፡፡ “ካሳለፍኩት የተጫዋችነት ህይወት፣ ከነበረኝ ልምድና ተሞክሮ በመነሳት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የለውጥ ምዕራፍ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት እፈልጋለሁ” ይላል፡፡ በክለብ ማኔጅመንት፣ በተጨዋች ወኪልነት፣ በስፖንሰርሺፕና ማርኬቲንግ እንቅስቃሴዎች የመስራት እቅዶች አሉት፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የደረሰበት የብቃት ደረጃ ለስፖርቱ ዕድገት የሚያግዙ ተግባራትን ለማከናወን መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን የሚገልፀው ያሬድ፤ በተጫዋችነት ዘመኑ ሊያሳካው ይሻው የነበረውን ህልም በመጪው ትውልድ እውን ሆኖ ማየት ይፈልጋል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት መገለጫ እንደሆነም ያምናል፡፡ እኔ ከያሬድ ተስፋዬ ጋር ሰሞኑን ጭውውት ሳደርግ ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ሁሉ ወሬያቸው ነገ ብሄራዊ ቡድናችን ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ እንደሚሆን ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ያሬድ ተስፋዬም ያወጋኝ ስለዚሁ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ብሄራዊ ቡድኑ አባላትና ስለእግር ኳስና ስለነገው ግጥሚያ የተጨዋወትነውን እነሆ፡፡
ነገ ዋልያዎቹ ከባፋና ባፋና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ምን ትጠብቃለህ?
ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ዋልያዎቹ በዚህ ግጥሚያ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሚገቡት ወደ ጦርነት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአገራቸውን ገፅታ የሚለውጡበት፣ የህዝባቸውን አንድነት የሚያጠናክሩበት፣ የኢትዮጵያውያን የዕድገት ተስፋ የሚያለመልሙበት ውጤት ነው የምጠብቀው፡፡
በነገው ጨዋታ የሚገኝ ውጤት እኮ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ያስችላል ማለት አይደለም፡፡ የነገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ቢወጣ እንኳን ቡድኑን ገና ሌላ ምእራፍ ይጠብቀዋል ፡፡ ከአፍሪካ 10 ሃያል ቡድኖች አንዱ ሆኖ ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው የደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ ውጤት ማምጣት የዋልያዎቹ ፈተና ይሆናል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ወሳኝነት ታዲያ ምኑ ላይ ነው?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን አሸንፎ፣ ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ውድድር ከሚበቁ የአፍሪካ 10 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን መብቃቱ ያጓጓል፡፡ ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያሳልፈው የ10 ብሄራዊ ቡድኖች የደርሶ መልስ ትንቅንቅ የነገውን ወሳኝ ፍልሚያ በድል በማጠናቀቅ የሚደረስበት ምእራፍ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የነገውን ጨዋታ በድል ለመወጣት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ስለነገው ነው ማሰብ ያለበት፡፡ ቀጣዩ ጨዋታ ከማን ጋር እንደሚሆን በማናውቀው ጉዳይ ላይ ማሰብ የለብንም፡፡ የነገውን ማሸነፍ ዓለም ዋንጫ እንደመግባት እንዲቆጥሩት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ ወሳኝ ምእራፍ አለ ብሎ መግባት ጥሩ አይሆንም፡፡ የነገውን ወሳኝ ጨዋታ አሸንፎ በማለፍ ነው ለመጨረሻው ምእራፍ የሚደረሰው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ተስፋ ተፈጥሮ መሸነፍ ማለት ለተጫዋቾቹም ሆነ ለስፖርት አፍቃሪው ሞራል የሚነካ ነው፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 ከሜዳው ውጭ አቻ ወጥቶ የተመለሰ ቡድን፣ እዚህ አገሩ ላይ የሚሸነፍበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡
ዋልያዎቹ ለዚሁ ወሳኝ ጨዋታ ምን ማድረግ አለባቸው? በእርግጥ በደጋፊያቸው ፊት እንደመጫወታቸው ማሸነፍ እንደሚችሉ ለመገመት አይከብድም፡፡ ይሁንና የጨዋታው ወሳኝነት የሚፈጥረው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ደቡብ አፍሪካ በዚሁ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በከፍተኛ ፍላጎት ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከሳምንት በፊት ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክን 3ለ0 ማሸነፏም ስጋት መፍጠሩ አይቀርም ፡፡ አንተ እንደ ስፖርት አፍቃሪ፤ እንደ ቀድሞ ኳስ ተጨዋችነትህ እና ከነበረህ ልምድ አንፃር ምን ትላለህ?
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች እና አባላት ከፍተኛ የሞራል መነቃቃት እና ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጨዋታው እያንዳንዷን ኳስ ለ90 ደቂቃዎች አሸንፈው መጫወት አለባቸው፡፡ ኳስ ከተነጠቁ መንጠቅ፣ ከነጠቁ ደግሞ ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው፡፡ እያንዳንዷን ኳስ ለማሸነፍ መፋለም አለባቸው፡፡ ኳሷን ማሸነፍ ማለት ለእያንዳንዷ ኳስ ትኩረት መስጠት ነው፡፡

በእያንዳንዷ ቅፅበት ያለውን ሁኔታ ሁሉም ተጨዋቾች እኩል ትኩረት በመስጠት ሙሉ 90 ደቂቃዎችን መጫወት አለባቸው፡፡ ዋልያዎቹ ጨዋታቸውን እዚህ አገራቸው እንደማድረጋቸው፤ ፊሽካ ከተነፋባት የመጀመርያዋ ደቂቃ አንስቶ ጫና ፈጥረው መጫወት አለባቸው፡፡ በሜዳቸው እየተጫወቱ መከላከል የለባቸውም፡፡ አገር ላይ መጫወት ያለው ጥቅም ለማግባት መጫወት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ቡድን ከኢትዮጵያ የምድቡን መሪነት ለመንጠቅ ከጅምሩ የሚጫወተው በማጥቃት ስለሚሆን፤ ያን በመከላከል ለማቆም መሞከር ለተደጋጋሚ ጥቃቶች ራስን ማጋለጥ ነው፡፡ ለማሸነፍ ማግባት አለብን፡፡ ለማግባት ደግሞ ማጥቃት አለብን፡፡ ዋልያዎቹ ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በምድቡ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ከሜዳው ውጭ ስለሚያደርገው ጨዋታ በፍፁም ማሰብ የለበትም፡፡ በነገው ጨዋታ ውጤቱን አሳምሮ ምድቡን በመሪነት ለመጨረስ መታሰብ አለበት፡፡ ማንም ተጨዋች ግጥሚያው የአገር ጉዳይ መሆኑን አምኖ መቶ በመቶ ብቃቱን ማሳየት አለበት፡፡ ይህን ለመወጣት የማይችል፤ በቂ እና የተሟላ ብቃት ለእለቱ ማበርከት እንደማይችል የሚያስብ ተጨዋች ካለ፣ ከእኔ ይልቅ እከሌ ቢገባ ይሻላል ብሎ በግልፅ ሃሳቡን ለአሰልጣኙ ማንፀባረቅ አለበት፡፡ ይህ ወሳኝ ምእራፍ የሙከራ ጊዜ አይደለም፡፡ ሜዳ የሚገቡ ተጨዋቾችም ያላቸውን ሙሉ ብቃት በመጠቀም፤ የላቀ የቡድን ስራ እና ቁርጠኝነት በማሳየት አስፈላጊውን ውጤት ለማስመዝገብ በልበሙሉነት መሰለፍ አለባቸው፡፡ ለብሔራዊ ቡድኑ ዋናው የስነልቦና ጥንካሬ የሚሆነው ለግጥሚያው በቂ ትኩረት ከማድረግ ባሻገር ለተጋጣሚው ቡድን ቀላል ግን ጠንቃቃ ግምት መስጠት ነው፡፡
ምንም አይነት ስህተት መሠራት የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካን በሜዳዋ ገጥሞ 1ለ1 አቻ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ በርግጥ በዚያ ጨዋታ የተገኘው ውጤት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስታድዬም ገብተው ለዋልያዎቹ የሰጡት ድጋፍ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ በነገው ጨዋታ ግን ዋልያዎቹ በሜዳቸው እንደመጫወታቸው የመላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ይበልጥ የጨመረ ይሆናል፡፡ ሌላው ለዋልያዎቹ የስነልቦና ጥንካሬ የሚሆነው የሚያስመዘግቡት ውጤት ትልቅ የታሪክ ምእራፍ መሆኑን ማሰብ ነው፡፡ ሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ከሰሞኑ ዝግጅታቸውም በላይ ዛሬ ልዩ ትኩረት እና በምክክር የተደገፈ የመጨረሻ ዝግጅት ያድርጉ፡፡ በቂ ልምምድ ሰርተውና ጥሩ እረፍት አድርገው ለነገው ፍልሚያ በተነቃቃ ስሜት፤ በጥሩ የአካል ብቃት እና ቅልጥፍና ተሳስበው በአገር ፍቅር ስሜት መስራት አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሸነፍ ይችል ዘንድ እንደ ተመልካች ምን አይነት ሃሳቦችን ትሰጣለህ?
ለማሸነፍ ከተፈለገ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን መተግበር አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ እነዚህ ተግባራዊ ሲደረጉ የማሸነፍ እድሉ 99 በመቶ ይሆናል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ማንኛውም ተጨዋች ያለበትን የስነልቦና ችግር ከአሰልጣኙ ጋር ከተወያየ እና በግልፅነት ከተመካከረ ለአገር የሚሆን ውጤት ያስገኛል፡፡ ሁለተኛ 90 ደቂቃዎቹን በሙሉ ትኩረት ሰጥቶ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጭ በመንቀሳቀስ ከተጫወተ ግጥሚያውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ይችላል፡፡ ሶስተኛ የቡድኑ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች የሚሰጧቸውን ያለቁ ኳሶች አማራጭ እንደሌለ በማሰብ ሌላ እድል አገኛለሁ በማለት ሳይዘናጉ፣ ከመጀመርያው ያገኟትን ኳስ ወደ ግብ መሬት አሲይዘው ከሞከሩ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አጥቂዎች ወደ ጎል የሚሞክሯቸውን ኳሶች መሬት አስይዘው ይምቱ የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡
ከመረብ የመዋሃድ እድል ያላቸው ኳሶች መሬት ለመሬት የሚመቱ ናቸው፡፡ ወደ ላይ የሚነሳ ኳስ የመግባት እድሉ ጠባብ ነው፡፡ አጥቂዎች አንድ እድል ሲያገኙ አንድ ጎል ለማግባት ማሰብ አለባቸው፡፡ ይህ አይነቱን ሙከራ ለሙሉ 90 ደቂቃዎች መቀጠል ደግሞ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካየኋቸው ለውጦች የመጀመሪያው የአጥቂዎች የአጨራረስ ብቃት ማደግ ነው፡፡ ዛሬ በብሔራዊ ቡድን ያሉ አጥቂዎች ጐል የማግባት ብቃታቸውና በቅጽበታዊ ውሳኔ ውጤት የማግኘት ክህሎታቸው ተለውጧል፡፡ በተለይ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አጥቂዎች ጐል የማስቆጠር ድፍረት ማዳበራቸው ጉልህ ለውጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውጤት እያማረ እና እየተለወጠ የመጣው የአጥቂዎች አጨራረስ ዕድገት በማሳየቱ ነው፡፡ ለዚህ የአጥቂዎች ውጤታማነት ፈር ቀዳጅነት ሚና የተጫወተው ሳላሃዲን ሰኢድ ነው፡፡ የእሱ የአጨራረስ ድፍረት እና በየግጥሚያዎቹ የሚያስቆጥራቸው ወሳኝ ጐሎች ብሔራዊ ቡድን አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሌሎች በሱ መስመር የሚሰለፉ የቡድኑ ተጨዋቾችን በማነቃቃትም አርአያ ሆኗል፡፡
የነገው ጨዋታ በድል ተጠናቀቀ እንበል፤ ቀጣዩ ወሳኝ ምእራፍ ከዚያ በኋላ ይመጣል፡፡ አሁን ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደሚገልፁት፣ የኢትዮጵያ ጊዜ ሆኖ ብሄራዊ ቡድኑ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፍ ስኬቱ ምን ትርጉም ይኖራዋል?
የማንም ተጨዋች፣ የየትኛውም እግር ኳስ ወዳድ ህዝብ አገር ህልምና ተስፋ የዓለም ዋንጫን መሳተፍ ነው፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ መቻል የእግር ኳሱን እድገት በአስደናቂ ሁኔታ የሚያፋጥነው ይሆናል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ሲያልፍ ለስፖርቱ ዕድገት በር ከፋች የሚሆኑ በርካታ እድሎች እና ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ካለፈ በኋላ በአገሪቱ በሚካሄደው የሊግ ውድድር ከፍተኛ የሆነ የፉክክር ደረጃ ይፈጠራል፡፡ ይህም ክለቦች በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው እና በተጨዋቾች ስብስብ ተጠናክረው ወደ ውድድር የሚገቡበትን ሁኔታ ያነቃቃል፡፡ በየክለቡ ያሉ ተጨዋቾች በዓለም ዋንጫ በሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ከፍተኛ ትጋትና ብቃት ማሳየታቸውም ሌላው ለውጥ ነው፡፡
ባለሀብቶች የአገሪቱ እግር ኳስ ለዓለም ዋንጫ በመብቃቱ በስፖርቱ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ፣ ክለቦችን በመግዛት እና በገንዘብ በመደገፍ ለመስራት በቀላሉ የሚነሳሱበትን ሁኔታም ይፈጥራል፡፡ ኩባንያዎች የተሰማሩባቸውን የኢንቨስትመንት መስኮች ለማስተዋወቅና ከስፖርቱ ለውጥ ጋር የንግድና የእድገት እንቅስቃሴያቸውን ለማስተሳሰር ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ ስታድዬሞችም በስፖርት አፍቃሪዎች መጥለቅለቃቸው አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል ህዝብ ወደ ስታድዬሞች የሚተመው በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ተጨዋቾችን ለመመልከት ስለሚሆን ነው፡፡ የዓለም ዋንጫው ስኬት የመንግስትንም ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በአፋጣኝ እንዲያልቁም ያበረታታል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ውጤቱ መንግስትና ህዝብን በማገናኘት ለአገር ልማት እና እድገት በጋራ መተሳሰብ እና በበጎ ስሜት እንዲሰሩ ተፅእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ማለት በውስጥም ሆነ በውጭ የአገርን ገጽታ ሊቀይር የሚችል ነው፡፡

“ዘፈኖቼ ህፃናትን የሚያሳድጉ ናቸው” - ጃ ሉድ

የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኙ ጃ ሉድ፤ በዳግማይ ትንሳኤ እለት በላፍቶ ሞል “ድግስ ቁጥር ሁለት” የተሰኘ ኮንሠርት ለማቅረብ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀና ትኬት ተሸጦ ካለቀ በኋላ ድንገተኛ የመውደቅ አደጋ ደርሶበት ኮንሰርቱ መሰረዙ ይታወሳል፡፡ መውደቁ ካደረሰበት የጤና መታወክ ካገገመ በኋላ ግን በተለያዩ የውጭ አገራት ተዘዋውሮ ኮንሰርቶችን በማቅረብ የዛሬ ሳምንት ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ምሽትም በተሰረዘው ኮንሰርት ምትክ “ድግስ ቁጥር ሁለት”ን በላፍቶ ሞል አቅርቧል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ድምፃዊውን ከኮንሰርቱ በፊት አግኝታው ስለውጭ አገር ኮንሰርቱ፣ ስለአዘፋፈን ስልቱ፣ በኮንሰርቱ መሠረዝ ስለደረሠው ኪሳራና ሌሎች ጉዳዮች አነጋግራዋለች፡፡ እንደ ዘፈኖቹ ዘና የሚያደርገውን ጭውውት እንድታነቡት ተጋብዛችኋል፡፡

 

የት የት ነበር የሙዚቃ ድግስ ስታቀርብ የቆየኸው?
ምን እባክሽ እኔ እኮ አላውቃቸውም… አንዱ ስዊዘርላንድ ነው፤ የመጨረሻውን አሪፍ እና የሚያምር የሙዚቃ ጊዜ ያሳለፍኩት ስዊዲን ነበር፡፡ ከዛ በፊት እንግሊዝ ነበርኩኝ፡፡ ለነገሩ እንግሊዝን ከበፊት ጀምሮ አውቃታለሁ፡፡ ግን ምን አለፋሽ… ስንገበገብ ሄጄ ስንገበገብ መጣሁ፡፡
እንዴት?
የዚህ አገር አየር እዚያ የለማ! እስካሁን የረገጥኩበት ቦታ የኢትዮጵያ አየር የለም፡፡
አየሩ ብቻ ነው ያልተመቸህ ወይስ ሌላም ነገር አለ?
አየሩ ነው፤ ብቻ ኢትዮጵያን ስለቃት የሆነ የሆነ ነገር እሆናለሁ፡፡ አይደላኝም፡፡ ነገር ግን ስራዬን በቆንጆ ሁኔታ ሰርቻለሁ፡፡
ኮንሠርትህን ያሳረግኸው ስውዲን ላይ ነው፡፡ የሠው አቀባበል እንዴት ነበር?
ኦ! የስውዲኑ በጣም ያምራል፤ ከምነግርሽ በላይ አሪፍ ነበር!
ስለተሠረዘው ኮንሠርትህ ብናወራስ?
ይቻላል! ምን ገዶኝ …
አወዳደቅህ እንዴት ነበር? ምን አጋጠመህ?
አወዳደቄ ትንሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ድንጋጤውን የበለጠ ያደረገው የኔ መውደቅና መታመም ሳይሆን የሠዎች መጉላላት አስጨንቆኝ ስለነበር ነው፡፡ ነገር ግን ችግሬ አሳማኝ ነበር፤ አሁን እንደምታይው እየደረቀልኝ ነው (ጉልበቱ ላይ ያለውን በመድረቅ ላይ ያለ ቁስል ሱሪውን ሰብስቦ እያሳየኝ) አወዳደቄ ከቤቴ ጋር ተጋጭቼ ነው፡፡ ቤቱ አዲስ ስለነበር ደረጃ የረገጥኩ መስሎኝ መሬት ረገጥኩ፡፡ እግሬና ጆሮዬ ጋ በጣም ተጐድቼ ነበር። በተለይ የጆሮዬ አናቴን አናጋብኝና አዕምሮህ ላይ ችግር ይፈጥራል ሲሉኝ በሲቲ ስካን ታይቼ ምንም ችግር እንደ ሌለው ተነገረኝ፤ ግን ምቱ ሀይለኛ ስለነበር ለኮንሰርቱ መድረስ አልቻልኩም፡፡ ሀይለኛ ህመም ስለነበረው ማለቴ ነው፡፡
ምናልባት ዓውደ ዓመት ስለነበረ ትንሽ መጠጥ ቀማምሰህ ይሆን እንዴ?
አ…ይ… ነው ብለሽ ነው?
በተሠረዘው ኮንሠርት ብዙ ኪሳራ መድረሱን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ነው?
ኪሣራው እኔ ነኝ፡፡ የእኔ መታመም ነው ኪሳራው፡፡ ባይሰረዝና ብጫወት ጥሩ ነበር፡፡ የእኔ ዘፈኖች ህፃናትን የሚያሳድጉ ናቸው፡፡ የህፃናትን አዕምሮ የሚያቆሽሽ ዘፈን አልሰራም፡፡ ህፃናትን አሳድጋለሁ፤ በዚህ ትርፋማ ነኝ፡፡ የእኔ መውደቅና መታመም እንጂ የብር ኪሳራ የለም፡፡
እንደሰማሁት ከሆነ ከኮንሰርቱ መሰረዝ ጋር በተያያዘ ወደ 700ሺህ ብር ኪሳራ ደርሷል፡፡ ይሄ እንደ ኪሳራ አይቆጠርም?
እሱ እኔን አያገባኝም …
የአንተ ብር የለበትም ማለት ነው?
እርግጥ የእኔም ብር አለበት፣ አዘጋጆቹ ከሚያወጡት ግማሹን አወጣለሁ፡፡ ቢጂአይም በርካታ ገንዘብ አውጥቷል፡፡ ነገር ግን ቢጂአይ ባወጣው ገንዘብ ሳይቆጭ፣ ፕሮሞሽናችንን በማድነቅ የዛሬውንም ኮንሠርት አጋራችን ሆኖ እየሠራ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ ስለ ኪሣራ ስናወራ አሁንም ኪሣራው እኔ ነበርኩኝ፡፡ አሁን ጤናዬ ተመልሶ ድኛለሁ፤ ስለዚህ ምንም ኪሣራ የሚባል ነገር የለም፡፡
ቅድም ህፃናትን አሳድጋለሁ ብለኸኛል… እስቲ አብራራልኝ?
ምን ማለት ነው… ሁሌም የህፃናትን አዕምሮ በበጐ መልኩ የሚያንፁና የሚያሳድጉ ነገሮችን ነው የምዘፍነው፡፡ ዘፈኖቼ ለበጐ ስራ የተሠጡ፣ አስታራቂና አቀራራቢ ናቸው፡፡ የምስራች አብሣሪም ናቸው፡፡ እናም ይሄ ነገር ወደፊት ለአርት ሥራ የሚዘጋጁ ህፃናትን የሚያሳድግና ጥሩ አመለካከት እንዲይዙ ይረዳቸዋል ለማለት ነው፡፡ አየሽ ህፃናት ሁልጊዜ “አንጀቴን በላሽው” የሚል ዘፈን እየሠሙ ከሚያድጉ ስለ ፍቅር፣ ስለ ባህል፣ ስለ ጤናማ ግንኙነት እየሠሙ ቢያድጉ መልካም ነው። ለምሣሌ እኔ ያደግሁበት አስተዳደግና አሁን ልጆች እያደጉ ያሉበት መንገድ አንድ አይደለም ብዬ ነው፡፡
አለባበስህን የተመለከተ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ጥለት ያላቸው ልብሶችን ራስህ ዲዛይን እያደረግህ እንጂ የተዘጋጁ ልብሶችን አትለብስም ይባላል፡፡ ይሄ ከምን የመጣ ነው? መቼ ነው የጀመርከው?
አሁንም የምታይው አለባበስ ያልሽው አይነት ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከማሸርጣቸው ልብሶች በሙሉ የአገሬ ልብሶች ናቸው፡፡ ይሄን መቼ ጀመርክ ላልሽው በጣም ቆይቷል ነው መልሴ፡፡ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡ አልበም ከማውጣቴ በፊት ማለቴ ነው፡፡
ነጭ የጠፍር ጫማና ነጭ ካልሲ ካልሆነ የትኛውንም አይነት ሽፍን ጫማ ቆዳም ይሁን ስኒከር አታደርግም። ቤትህ ውስጥ ጥልፍልፍ የጠፍር ጫማና ነጭ ካልሲ በገፍ ይገኛል ይባላል፡፡ ለምንድን ነው?
ደስ የሚለኝ እንደዛው ነው፤ ጐንበስ ስል ነጭ ሆኖ ሳየው ደስ ይለኛል፡፡ ሌሎቹን አይነት ጫማዎች አላውቃቸውም፤ ማወቅም አልፈልግም፡፡
የተለየ ምክንያት አለህ?
እኔ እንጃ! ይሄ ጫማ ልቤን ይዞብኛል (በዕለቱም ነጩን ጥልፍልፍ የጠፍር ጫማና ነጭ ካልሲ ተጫምቷል) ጐንበስ ስል ንፃቱ ለአይኔ ካልማረከኝ ትንሽ ጭንቅላቴን ይይዝብኛል፡፡ የእኔ ጭንቅላት ከተያዘ የሌላውም መያዙ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ሌላውን አልደፍረውም፡፡
ስለ አዲሶቹና በአልበምህ ውስጥ ስላልተካተቱት አምስት ዘፈኖችህ እናውራ?
እንዴ? አምስት ዘፈን ዘፍኛለሁ እንዴ? እኔ እኮ ዘፈኖቼን አላውቃቸውም፡፡
“ኩሉን ማንኳለሽ”፣ “ታዲያስ አዲስ”፣ “ድግስ” የተሠኙትን ዘፈኖች ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ አልበምህ ላይ የሉም…
ኦ! አዎ ልክ ነሽ “ዳጐስ”፣ “ድግስ”፣ “ታዲያስ አዲስ”፣ “ኩሉን ማንኳለሽ”፣ እና “ባቲ” የተሠኙ አዳዲስ እና የሚያማምሩ ሥራዎች ሠርቼያለሁ፡፡
ባህላዊና የሠርግ ዘፈኖችን ወደ ሬጌ ስልት ማምጣት አይከብድም?
በጣም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን የኔ ጭንቅላት ሙዚቃ ውስጥ ስለተነከረ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀለል እያለኝ መጥቷል። መጀመርያ አካባቢ ወደ ሬጌ ስልት መቀየር ትንሽ ያሰለቻል፤ ነገር ግን እኔ መሰልቸት ስለማላውቅ ስልቱን አገኘሁት፡፡ አሁን “እባክህ እንዲህ አይነት ሙዚቃ እፈልጋለሁ” ብዬ ልቤን እጠይቃለሁ፤ ልቤ ይሠጠኛል፡፡ በነገርሽ ላይ ሬጌ ላይ ግጥም ይከብዳል፡፡ ሬጌን ለመዝፈን ግጥም ነው ዋናው ነገር፡፡ ስለዚህ ግጥም ስፈልግ መንገድ ላይ ያገኘኋቸው ሀሳቦች ናቸው የሠርጉን የባህሉን ወደ ሬጌ እንዳመጣቸው ያደረገኝ፡፡ በፊት በፊት የሬጌ ግጥም የትግል ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ እናም ብዙ ጊዜ ድርቅ ያሉ ግጥሞች ይሆኑብኛል፡፡ አሁን ግን ቀስ በቀስ እየተፍታታልኝ፣ በአጫጭር ግጥሞች ሀሣብ መግለፅ ጀምሬያለሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ ከአስር ዓመት በኋላ የመጣ ነገር ነው፡፡
እንዳልከው ሬጌ አብዮተኛ የሙዚቃ ስልት ነው። ከደከሙበት ከጣሩበት ግን የፍቅርም የባህልም መግለጫ ይሆናል እያልክ ነው?
በሚገባ! እኔ አሁን ይህን እያደረግሁ ነው። ለምሣሌ “ታዲያስ አዲስ”፣ “ኩሉን ማን ኳለሽ” የተሠኙት ዘፈኖች ባህልንም ፍቅርንም የሚገልፁ ዘፈኖች ናቸው።
እስቲ ስለ ባህሪህ ንገረኝ… ቁጡ ነህ? ተጫዋች? ወይስ…
ስትቆጪኝ እቆጣለሁ፤ ስታጫውቺኝ እጫወታለሁ፡፡ እንደ አንቺ ተፈጥሮ የምጓዝ ነኝ፡፡ ተፈጥሮ እንደምትሆነው ነው የምሆነው ማለት ነው፡፡
እንደምሠማው ከሆነ ጃ ሉድ ትንሽ የባህሪ ችግር አለው፣ ከማናጀሮቹ ጋር እየተጣላ በተደጋጋሚ ማናጀር ቀይሯል፣ ከአቀናባሪው ከካሙዙና ከፕሮድዩሠሩ ታደለ ሮባም ጋር ሠላም አይደለም ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ከታደለም ከካሙዙም ጋር አልተጣላንም፡፡ ባለፈው አሜሪካ ስሄድም ሸኝተውኛል፡፡ ታደለ ሮባ አሁንም ወዳጄ ነው፡፡ እንዳልኩሽ ባለፈው አሜሪካ ስሄድ ከካሙዙ ጋር መጥተው ሸኝተውኛል፡፡ ከአሜሪካ ስመለስ ግን ታደለ ሮባ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም፡፡ ካሙዙም ቢሆን አሁን ወደ አሜሪካ ሊሄድ ነው፡፡ እኔም በቅርቡ ስለምሄድ እዛው እንገናኛለን፡፡ ሁለተኛ አልበማችንን እዛ ልንጀምር ነው፡፡
ረዘም ላለ ጊዜ ልትቆይ ነዋ?
እኔ እመላለሣለሁ እንጂ ከአንድ ወር በላይ በየትኛውም አለም ከኢትዮጵያ ውጭ መቆየት አልችልም፡፡ አሁን መመላለስ እችላለሁ፤ ዓለም የኔ ናት፡፡ እንደ በፊቱ አይቸግረኝም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ረጅም ጊዜ ስቆይ ጤንነት አይሰማኝም። በክርስቲያኑ ፋሲካም፣ በሙስሊሙ የረመዳን ፆም ፍቺ (ኢድአልፈጥር) ጊዜም ከኢትዮጵያ ውጭ መሆን አልችልም፡፡ በጣም ደስ አይለኝም፤ ስለዚህ እመላለሳለሁ፡፡
እንደ በፊቱ አይቸግረኝም ስትል ምን ማለትህ ነው?
በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ ዓለም ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡ አሁን መሄድ መምጣት ለምጃለሁ ለማለት ነው። እርግጥ አሁን አሜሪካ የምሄደው ለስራ ስለምጠራ ነው እንጂ እዛ ለመኖርና ሌላው ስለሄደ መሄድ አለብኝ ብዬ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ከማናጀር ጋር ተጣላ፣ ከአቀናባሪ ተጋጨ፣ ፕሮዱዩሠሩን አኩርፎታል የሚባል ነገር የለም፡፡ ከሁሉም ጋር ሠላም ነኝ፣ እንደዛም ከሆነ ተበዳይ እኔ ነኝ፡፡ ነገር ግን አልበደሉኝም አልበደልኳቸውም፤ በእኔ ላይ የሚወራው ውሸት ነው፤ እንግዲህ አሉባልታ የሚወራበት ሌላ ጃ ሉድ ካለ አላውቅም፡፡
ከሬጌ ሙዚቃ እና ከህይወት ዘይቤያቸው (Style) ጋር ተያይዞ የሚነሳው የአደንዛዥ ዕፅ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሠዎች ጃ ሉድን ከዕፅ ጋር አገናኝተው ሲያነሱት ይደመጣል፣ የባለፈውን ኮንሠርት ያሠረዘህን አወዳደቅም ሀሺሽ ከመውሠድ ጋር ያገናኙት አልጠፉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?
በፈጠረሽ ተይው፡፡ ምንም ነገር የለም! ይህንን ነገር ተይው፡፡ አሁን ህዝቡ በዚህ መልኩ እኔን መቃኘት የለበትም፡፡ እውነት ለመናገር ይህንን ነገር ላድርገው ብል አደርገዋለሁ፣ መብቴ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ነገር የለም፡፡ እውነቴን ነው የምልሽ የለሁበትም!
ሰዎች ቀጠን ማለትህንና የኪሎህን ነገር እያዩ ምግብ በደንብ አይበላም፣ ከምግብ ጋር ያለው ዝምድና የጠበቀ አይደለም ይላሉ፡፡ ለምንድን ነው በደንብ የማትመገበው?
እየውልሽ… ሰዎች ሁሉ ምግብ አይመገብም እያሉ ብዙ ሳልመገብ ቀረሁ፡፡ ይመገባል ቢሉኝ ኖሮ ብዙ እመገብ ነበር፡፡ ምክንያቱም “እሹ ይሰጣችኋል” ነው የሚለው መፅሀፉ፡፡ አሁን ብዙ ይመገባል እያሉ ቢያበረታቱኝና ብመገብ ደስ ይለኛል፡፡
ከ”መሀሪ ብራዘርስ” ባንድ ጋር ምን ያህል ተጣጥማችኋል?
“መሀሪ ብራዘርስ” በጣም ፍቅር የሆኑና ለሙያው ራሣቸውን የሠጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ አሜሪካም፣ አውሮፓም በአጠቃላይ እዚህም ያለውን ኮንሠርት ከእነሱ ጋር ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ለእኔ በጣም ተስማምተውኛል፡፡ እርግጥ አሜሪካ “ዛዮን” ባንዶች አሉ፡፡ እዚህ ያለውን ከመሀሪ ብራዘርስ ጋር ነው የምሠራው፡፡ አውሮፓና አፍሪካ አገር ካሉ ፕሮሞተሮች ጋር ትንሽ ጉዳዮች አሉኝ፡፡ እነሱን ካስማማሁኝ “መሀሪ ብራዘርስ” ከእኔ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ይቆያሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በጣም ጥሩ ልጆች ናቸው፤ ፍቅር የሆኑ ወንድማማቾች ናቸው። እንዲህ አይነት ወንድማማችነት ውስጥ ተካትቼ ለረጅም ጊዜ ብኖር ደስ ይለኛል፡፡

 

ትርጉም እያዛባ፣ቃል እያናናቀ፣
ፍቺ እያጣረሰ፤
ከበሽታ ሁሉ የደሃ ኩርፊያ ነው
ሃገር ያፈረሰ።
እናንተ ብልሆች!
ተስፋ−ተስፋ የሚሸት እቅድ ስታቅዱ፣
ንቁ−ፍኩ እንዲሆን የለውጥ መንገዱ፤
‘ካኮረፈ ደሃ’ ሃሳብ አትውሰዱ!

የለቅሶ ቤት አዝማች
ተዝካር፣
እዝን፣
ድንኳን፣
ንፍሮ፣
ሰልስት፤
12፣ 40፣ 80፣ ሙት−ዓመት፤
“ጐጂ ነው!” አትበሉን አቦ እናልቅስበት!
እናውቃለን እኮ!
አዛኞች፣ አጽናኞች በሞሉባት አምባ፤
‘ግማሽ ሳቅ’ ማለት ነው ሁሉ ያየው ዕንባ።

ዘ ሮክ ዘንድሮ በተወነባቸው ፊልሞች ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማስገኘት የሚስተካከለው አለመገኘቱን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገበ፡፡ ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርተኛ የሆነውና በሙሉ ስሙ ድዋይን ጆንሰን ተብሎ የሚታወቀው ዘ ሮክ፣ ላለፉት 16 ሳምንታት በቦክስ ኦፊስ የገቢ ደረጃ ከአንድ እስከ 10 ባለው ቦታ ባለመጥፋት ስኬታማነቱን አረጋግጧል፡፡ በ2013 ለእይታ የበቁት ዘ ሮክ የተወነባቸው ፊልሞች ‹ስኒች›፤ ‹ጂ.አይ. ጆ ሪታልዬሽን›፤ ‹ፔይን ኤንድ ጌይን› እና ሰሞኑን መታየት የጀመረው ‹ፋስት ኤንድ ፊርዬስ 6› ናቸው፡፡ በገቢ በጣም ስኬታማ የሆነባቸው ሁለቱ ፊልሞች በመላው ዓለም 365.53 ሚሊዮን ዶላር ያስገባው ‹ጂ.አይ. ጆ ሪታልዬሽን› እና 586.66 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው ‹ፋስት ኤንድ ፊርዬስ 6› ይጠቀሳሉ፡፡ በተወነባቸው ፊልሞች ገበያው ለምን እንደተሟሟቀለት የተጠየቀው ተዋናዩ በሰጠው ምላሽ ባለፉት 13 ዓመታት በትዋናው በመስራት ከፍተኛ ጥረት እና ትጋት እንደነበረው ገልፆ “ከፍተኛ ስኬት የማስመዝገብ ግብ ነበረኝ” ሲል ተናግሯል፡፡

ታዋቂው የፊልም ዲያሬክተር ጄ ጄ አብርሃምስ በ‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› ፊልም ባገኘው የገቢ ስኬት የጆርጅ ሉካስ ፊልም የነበረውን ስታርዋርስ 7ኛ ክፍል እንዲሰራ መዋዋሉን ዋሽንግተን ታይምስ ዘገበ፡፡ በጂን ሮደንበሪ በተደረሰው የስታር ትሬክ መፅሃፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራውና የስታር ትሬክ የተሰኘ ፊልሞች ፍራንቻይዝ 12ኛ ክፍል የሆነው ‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› በመላው ዓለም ያስገባው ገቢ 376.54 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የስታር ትሬክ ፊልሞች ፍራንቻይዝ መሰራት ከጀመሩ 38ኛውን ዓመት ሲሆናቸው፣ ዘንድሮ ለእይታ የበቃውን 12ኛውን ክፍል ጨምሮ ያስገኙት ገቢ ከ1.628 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡

‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› በ190 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራና በፓርማውንት ፒክቸርስ የሚከፋፈል ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በምድር አቅራቢያ ስለምትገኝና ጥንታዊ የዩኒቨርስ ስልጣኔ ያላት የኒብሩ ፕላኔት ፍጡራን በሰው ልጆች ላይ ስለሰነዘሩት የሽብር ጥቃት የሚተርክ ነው፡፡ ዲያሬክተር ጄጄ አብርሃምስ በ‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› ያገኘው ስኬት ነው የስታር ዋርስ ፊልሞች 7ኛ ክፍልን እንዲሰራና የገቢ ስኬቱን እንዲቀጥል ተመራጭ ያደረገው፡፡ የስታር ዋርስ 7ኛ ክፍል ቀረፃውንም በ2014 እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ የስታር ዋር ፊልሞች ፍራንቻይዝ በእውቁ ዲያሬክተር ጆርጅ ሉካስ የተሰሩ ሲሆን በመላው ዓለም ከ1.85 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስገኝተዋል፡፡

የሠአሊ አዳምሰገድ ሚካኤል የሥእል አውደርእይ ከትናንት በስቲያ ተከፈተ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የተከፈተው አውደርእይ እስከ መጪው ረቡዕ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

በምስጋና አጥናፉ ተጽፎ ዳይሬክት የተደረገውና በፓስፊክ ፊልም ፕሮዳክሽን የተዘጋጀው “ጥቁር እና ነጭ” ፊልም የፊታችን ሰኞ በብሔራዊ ትያትር ከቀኑ በ11 ሰዓት ይመረቃል፡፡ በዚህ የቤተሰብ ፊልም ላይ ሙሉአለም ታደሰ፣ እመቤት ወልደገብርኤል፣ ማክዳ አፈወርቅ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የሉሲ አካዳሚ ተማሪዎች በየክፍላቸው ንዑስ ቤተመፃሕፍት አቋቋሙ። የሕፃናትንና ታዳጊ ወጣቶችን የንባብ ባህል ለማዳበር የተቋቋሙትና ትላንት የተመረቁት የየክፍሉ አብያተ መጻሕፍት በዝነኛ ሰዎች ስም ተሰይመዋል። ከ1ኛ-5ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ያቋቋሙት ቤተመጻሕፍት በደራሲ ሜሪ ጃፋር ስም የተሰየመ ሲሆን ቤተመጻሕፍቱን ደራሲ ሜሪ ጃፋር መርቀውታል፡፡ በክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የተሰየመውን የ7ኛ ክፍል ቤተመፃህፍት ደግሞ ኢንጂነር ታደለ ብጡል ሲመርቁት በደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር የተሰየመውን የ11ኛ ክፍል ቤተመፃህፍት ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ መርቀውታል። ለ12ኛ ክፍል የሚያገለግሉት ሁለት አብያተ መጻሕፍት በክብርት ዶ/ር ስንዱ ገብሩ እና በደራሲ ፀሐይ መላኩ፣ የተሰየሙ ሲሆን አምባሳደር ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋና ደራሲ ፀሐይ መላኩ መርቀውታል፡፡ ትምሕርት ቤቱ ካሉት 18 መማርያ ክፍሎች ስድስቱ በዚህ መልኩ ቤተመጻሕፍት ያገኙ ሲሆን የሌሎችም እንደሚቀጥል ማወቅ ተችሏል፡፡

በጋዜጠኛ፣ ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የተዘጋጀው “ፍልስምና ፫” የተሰኘው መፅሃፍ ለንባብ በቃ፡፡ በቃለ ምልልስ መልክ በተዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ስምንት ባለሙያዎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ኬሚካል ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ፣ በቀለማት ፍልስፍናና ሥነ ልቦናዊ ማንነታቸው፣ ተፊሪ ንጉሤ በገዳ ሥርአት፣ በዋቂፈናና ኢሬቻ፣ ዶ/ር መስፍን አርአያ በማንነታችን ላይ የተናገሩት ይገኝበታል፡፡ 144 ገፆች ያሉት መጽሐፍ በ32 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

በሌላ በኩል በግዛው ዘውዱ የተዘጋጀው “ኢትዮጵያ፣ ታሪክ፣ ትርክትና ታሪካችን” መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በ285 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፍ በፋርኢስት ትሬዲንግ የታተመ ሲሆን በ60.70 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ መጽሐፉ በማጣቀሻነት ከተጠቀማቸው በርካታ ዋቢዎች መካከል የአለቃ ደስታ ተክለወልድ፣ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ የአሌክሳንደር ቡላቶቪችና የዶናልድ ሌቪን መጻሕፍትና ሌሎች ጽሑፎች ይገኙበታል፡፡