Administrator

Administrator

ሁለተኛ አልበምህን ለማውጣት ለምን ከ10 ዓመት በላይ ፈጀብህ ?
ከ10 ዓመት በፊት “ስጦታዬ ነሽ” በሚል የመጀመርያ አልበሜን ለአድማጭ አቅርቤአለሁ። “ስጦታዬ ነሽ” ሲወጣ ልጅም ነበርኩ፤ስለ ፕሮሞሽንም ብዙ አላውቅም፡፡ እንደዚያም ሆኖ በወቅቱ ጥሩ ምላሽ አግኝቼበታለሁ፡፡ በተለይ “ስጦታዬ ነሽ” እና “ሳቅሽ ነው ያንቺ ደስታ” የተሰኙት ዘፈኖች በጣም ከመወደዳቸው የተነሳ ሰዎች እነዚህን ነጠላ ዜማዎች የለቀቅኩ ብቻ ነበር የሚመስላቸው። በዚህ ሂደት ብዙ ልምድ፣ ብዙ እውቀቶችን ቀስሜበታለሁ። አልበም ሳላወጣ ብዙ የቆየሁት ደግሞ ጥሩ ስራ ይዤ ለመምጣት ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት መሀል ግን ቁጭ አላልኩም፡፡
ምን ትሰራ ነበር ?
የኪነ-ጥበብ ፍላጎቴ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ግጥምና ዜማ ሰብስቤ እስክጨርስ፣ በአጠቃላይ የአልበሙ ስራ እስኪሳካ ድረስ “አባሮሽ” እና “ባለ ቁልፉ” የተሰኙ ሁለት ፊልሞችን ፅፌ በማዘጋጀት መሪ ተዋናይ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ በተለይ በመጀመሪያው ፊልሜ “አባሮሽ”፣ በጣም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቼ ነበር፡፡ ሁለተኛው ፊልሜ፣ፕሮዲዩሰሩ አንዳንድ የግል ችግሮች አጋጥመውት ለወንድሙ አስረክቦት ነበር፤ ፊልሙ ተቆራርጦ በሰራሁት መልኩ አልሆነልኝም። ብዙ እውቅ ተዋንያን ተካተውበት ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ ለእይታ የበቃው እኔ በፃፍኩት መልክ አልነበረም፡፡ ያም  ሆኖ ብዙ ተመልካች ነበረው፡፡
“መንገስ ከፈለግክ ሙት” የተሰኘው የግጥም መፅሀፍህ በዚሁ ጊዜ ነው የታተመው?
አዎ ነገር ግን ታትሞ ቁጭ ብሏል፤ለአንባቢ አልደረሰም፡፡
ለምን?
ያላሰራጨሁት የአልበሙና የፊልሙ ስራ ወጥሮ ይዞኝ ስለነበር ነው፡፡ የታተመው በ2005 ዓ.ም ነው፤ ይሄው ሶስት ዓመት ሞላው ታትሞ ከተቀመጠ። አልበሙ ራሱን ችሎ አምስት ዓመት ወስዷል፡፡ መፅሀፉን ለማከፋፈል የተለያዩ የመጻህፍት መደብር ባለቤቶችን አነጋግሬ ነበር፤ ምላሽ ሳይሰጡኝ ሲቀሩ ፊቴን ሙሉ በሙሉ ወደ አልበሙ አዞርኩኝ፡፡ ፅፌ ያስቀመጥኩት የፊልም ስክሪፕትም አለ፡፡  
“መንገስ ከፈለግክ ሙት” የሚለውን ርእስ ለምን መረጥከው?
ርዕሱን በተመለከተ “መንገስ ከፈለግክ ሙት” ያልኩት በተለይ በእኛ አገር በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ክብር የሚገባቸው ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ የስነ ፅሁፍ ሰዎች ---- በህይወት እያሉ ክብር አይሰጣቸውም፤ከሞቱ በኋላ ግን ስለነሱ የሚነገረው፣ ሙገሳው፣ አድናቆቱ ይዥጎደጎዳል፤ ግን ያ ምን ይጠቅማል፤ ይሄ ያበሳጨኛል፤ በህይወት እያሉ ቢያዩት ነው ትርጉም የሚኖረው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህን ቁጭቴን ለመግለፅ ነው ርዕሱን የመረጥኩት፤ ግን ሽሙጥ ነው፡፡    
እርግጠኛ ባልሆንም የፊልም ትምህርት መማርህን የሰማሁ መሰለኝ፡፡ እውነት ነው?
አዎ ተምሬያለሁ፡፡ ትምህርቱን በተግባር ለማሳየት ነው ፊልሞችን የሰራኋቸው፡፡ በእርግጥ “አባሮሽ” ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ መሆን አልፈለግኩም ነበር፡፡ የተመለመሉት መሪ ተዋናዮች ከመሪ ሴት ተዋናይዋ ጋር ሊሄዱልኝ ስላልቻሉ፣ ሀሳቤንም ስላልገለፁልኝ ነው የገባሁበት። ብቻ ተሰጥኦዬን በትምህርት አግዣለሁ፡፡ በፊልም ብቻ ሳይሆን በቴአትር ስክሪፕት፣ በዳይሬክቲንግና አክቲንግም በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር ውስጥ ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ በሁሉም መልኩ ፍላጎቴን ለማውጣት እየጣርኩ ነው ያለሁት፡፡
ሁለተኛ አልበምህ ከዘገየባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ግጥምና ዜማ ለመሰብሰብ ጊዜ በመፍጀቱ እንደሆነ ነግረኸኛል፡፡ ግን በአልበሙ ውስጥ አብዛኛውን ግጥምና ዜማ የሰራኸው ራስህ ነህ ---
አዎ መጀመሪያ ሰብስቤ ነበር፤ግን መጨረሻ ላይ ከአንዳንዶቹ በስተቀር ስላላረኩኝ የራሴን ግጥምና ዜማ ለመስራት ተገድጃለሁ፡፡ ያው አሪፍ አሪፍ ሀሳቦችን ለማንሳት ሞክሬያለሁ፤ ከአድማጭም ጥሩ ምላሽ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በተለይ “መከልከል መፍቀድ ነው” የሚለው ዘፈንህ ለእኔ ተመችቶኛል፡፡ ስለ ዘፈኑ ንገረኝ…
አልበሙ የደቡቡንም፣ ሬጌውንም፣ ባህሉንም፣ ዘመናዊውንም አካትቶ ይዟል፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ተሰራ ቢባልም ጊታር ለሚያስፈልገው ጊታር፣ ሳክስ ለሚያስፈልገው ሳክስፎን፣ የተለየ መሳሪያም ሲያስፈልግ፣ ማሲንቆም---- ሁሉ አካትተን በሙሉ ባንድ ነው የተሰራው ማለት ይቻላል፡፡ ከአቀናባሪው ሙሉጌታና ከሌሎችም የአራት ዘፈኖችን ግጥምና ዜማ ወስጃለሁ፡፡ መላኩ ገብሩ ከተባለ ጎበዝ ወጣትም፣ግጥምና ዜማ ተጠቅሜአለሁ፡፡ ብቻ ለየት ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ “መከልከል መፍቀድ ነው” የሚለውን ዘፈን ብዙ ሰው ወዶታል፤ መጀመሪያ ግጥም ነበር የፃፍኩት፤ ለዘፈን አላሰብኩትም ነበር። ለሙዚቃ ስራ ስቱዲዮ ሄጄ ግጥሙን ሳነብ አቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ፤ “ይሄማ ግጥም ብቻ ሆኖ አይቀርም፤ እኔ ዜማ እሰራለታለሁ” አለና ሰራለት፡፡ አሪፍ ሆነ፡፡
ስለከለከልኩሽ መጥፎው ጥሩ መስሎሽ
አታርጊ ያልኩሽን ደግመሽ ደግመሽ አረግሽ
የፊቱን ስዘጋ ሄድሽ በጀርባው
ለካንስ ለሰው ልጅ መከልከል መፍቀድ ነው
ሙሉውን ጥለሽው ወደባዶው እሮጥሽ
የሰጠሁሽ መሮሽ ተይ ያልኩሽ ጣፈጠሽ
ለራስሽ አስቤ እንዲያምር ህይወትሽ
አንዱን ተይ ስላልኩሽ ስንቱ በር ተከፍቶ
የተዘጋ ሰብረሽ
ክብርሽን ጥለሽ ሄድሽ ስለተከለከልሽ -----
እያለ ይቀጥላል፡፡ ሁላችንም ያለፍንበት የኖርነው ነው፡፡ ሰው ተው ሲባል፣ ሲከለከል፣ ያንን ነገር ማድረግ በጣም ይፈልጋል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡
ከአልበሙ ምን ዓይነት ውጤት ወይም ምላሽ ትጠብቃለህ?
እንግዲህ ጊዜዬን፣ ገንዘቤን፣ ጉልበቴን፣ እውቀቴን እስከ ጥግ ተጠቅሜ ለአድማጭ ይመጥናል ያልኩትን ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ በስልትም ደረጃ ሬጌ፣ ዳንሶል፣ ደቡብ፣ ወሎ ሪትም አለው፤ ብቻ በሁሉም መልኩ አድማጭን ለማስደሰት ደፋ ቀና ብያለሁ። እናም ጥሩ ምላሽ እንደሚኖር እጠብቃለሁ፡፡ አልበሙ 10 ዘፈኖችን ነው የያዘው፡፡ ከመጀመሪያው አልበሜ “ስጦታዬ ነሽ” የሚለውን ሚክስ አድርገን ለማስታወሻነት አብሬ አካትቼዋለሁ፡፡ ሌሎቹ ዘጠኙ አዲስ ናቸው፡፡ አራት ዘፈኖች እኔን ስላላረኩኝ ከተሰሩ በኋላ ትቼአቸዋለሁ፡፡ ጥሩ ጥሩ ዘፈኖች ስለሆኑ አስሩ በቂ ናቸው ብለን አቅርበናል፡፡ ሙዚቃ ማድመጥን ይጠይቃል፤ ሰዎች ሥራዬን አድምጠው በየትኛውም መንገድ አስተያየት ቢሰጡኝ፣ አድናቆት ብቻ ሳይሆን ደካማ ጎኔንም ጭምር ባውቅ ለወደፊት ስለሚረዳኝ ይሄንን በጉጉት የምጠብቀው ነው፡፡  
ብዙ ጊዜ ኪነ-ጥበብ አካባቢ እንቅስቃሴ ያላቸው ሰዎች ነጠላ ዜማ ሞክረው ሳይሳካ ወደ ፊልም፣ ይህም ካልተሳካ ወደ ሌላ የጥበብ ዘርፍ ያመራሉ አንተ ሁሉንም ጎን ለጎን እያስኩድክ ነው እንዴት ነው?
አንዳንድ ሰው ኪነ-ጥበቡን እንደ ገንዘብ ማግኛ ከወሰዱት እዛም እዚህም ሊሞክሩ ይችላሉ፤ ስጦታው ካለሽ ግን ትርፍ አታስቢም፤ በቃ ስሜትሽን መወጣት ሀሳብሽን መግለፅ ነው፡፡ እኔ አልበሙ እስኪሳካ ብዬ ቁጭ አላልኩም፤ ግጥም ፊልም ሰርቻለሁ። ከ“አባሮሽ” ፊልም በገንዘብም በእውቅናም ደረጃ ጥሩ ምላሽ ሳገኝ፣ “ባለቁልፏ” የሚለውን ቀጠልኩ፤ በእርግጥ ይሄኛው ትንሽ ተቆራርጦ ጥሩ አልነበረም። የግጥም መፅሀፉም አልተበተነም፤ ገንዘብ አላገኘሁበትም ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ የምፈልገውን አድርጌያለሁ፡፡ ይህን ደግሞ ከልጅነቴ ሳደርገውና መስዋዕትነት ስከፍል ነው ያደግሁት፡፡
የግጥሙ መፅሀፍ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው?
ሰሞኑን አልበሙ ወጥቷል፤ ትኩረቴ በሙሉ በዚህ አልበም ላይ ነው፡፡ ትንሽ ከተደመጠ በኋላ የአልበም ምርቃት አዘጋጃለሁ፡፡ ያንን ካጠናቀቅኩ በኋላ የግጥም መፅሀፉን አስመርቄ እንደ አዲስ አሰራጨዋለሁ፤ 70 ምን የመሳሰሉ ሀሳቦች የያዙ ግጥሞች፣መጋዘን ውስጥ ተቆልፎባቸው አይቀሩም፡፡
ከመሰናበታችን በፊት ቀረኝ የምትለው ካለ -----
 በስራዬ ሁሉ ከጐኔ የነበሩትን ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን፣ በሙዚቃ ስራው የተሳተፉትን ሙሉጌታ አባተን፣ መሀመድ ኑሩሁሴንን፣ ኢዮብ ካሳሁንን፤ ድጋፍ ያደረገልኝን ቢጂአይ ኢትዮጵያን፣ እንግዳ ያደረገኝን አዲስ አድማስን አመሰግናለሁ። ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤በዓሉ የሰላምና የጤና ይሁንላችሁ --- እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እጅግ ሀብታም ሰው ወደ ገበያ ሄዶ ዕቃ እየገዛ ሳለ አንዲት በቀቀን (Parrot) ያያል፡፡ በቀቀኗ አንድ ጊዜ ጠዋት የነገራትን ነገር በቃሏ ይዛ ቀኑን ሙሉ የመድገም ችሎታ ያላት ናት፡፡ ነጋዴው በዚህ ችሎታዋ በጣም ተደስቶ ሻጩ የጠየቀውን ገንዘብ ሰጥቶ ለመግዛት ይወስናል፡፡
“ስንት ነው ዋጋዋ?” ሲልም ይጠይቃል፡፡
ያ ነጋዴም፤
“ጌታዬ ይቺን በቀቀን ለመሸጥ አደለም ይዣት የመጣሁት፡፡ እቤት ያደገች በመሆንዋ ሁሌም እጐኔ ሆና ታጫውተኛለች፡፡ እኔ የምነግደው ሌላ ሌላ ነገር ነው” አለው፡፡
ሀብታሙ ሰው፤
“ግዴለህም፤ ያልከውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አንተ ቤት ከምትቀመጥ እኔ ቤት ብትሆን ብዙ ሰው ያያታል፡፡ እኔን ብዙ ትላልቅ ሰዎች ሊጠይቁኝ ስለሚመጡ በቀቀኗ የመጐብኘትም ዕድል ታገኛለች” ይለዋል፡፡
ነጋዴው፤
“ጌታዬ፤ እንደልጄ የማያትን በቀቀን በገንዘብ አልለውጣትም፡፡ ሰው የነገራትን ደግማ የመናገር ችሎታ እንድታዳብር ዕድሜ ልኬን ደክሜያለሁ፡፡ ስለዚህም በጭራሽ ለሰው አሳልፌ አልሰጣትም” ብሎ ግትር አለ፡፡
ሀብታሙ ሰውም ተስፋ ቆርጦ ወደሌላ ገበያው ዞረ፡፡ ሆኖም በቀቀኗ ከአዕምሮው ልትወጣ አለቻለችም፡፡ ስለሆነም፤ አንድ ሰው ቀጥሮ፣ የዚያን ነጋዴ ቤት አስጠንቶ፣ ጥሩ አጋጣሚ ሲገኝ በቀቀኗን ሊያሰርቃት ዕቅድ አወጣ፡፡ ዕቅዱ ተሳካና በቀቀኗ ተሰርቃ መጣችለት፡፡
በዚያን ዕለት ሀብታሙ ሰው ቤት ቅልጥ ያለ ግብዣ ተደርጐ ትላልቅ ሰዎችም ጥተዋል፡፡ ከተበላ ከተጠጣ በኋላ ሀብታሙ ሰው አስገራሚዋን በቀቀን እንግዶቹ እንዲያዩለት ጋበዘ፡፡ ተራ በተራ ሳይሆን አንድ ላይ እንዲመጡም አደረገ፡፡
እንግዶቹ ወደበቀቀኗ ቀርበው የምትለውን ለመስማት ጓጉተዋል፡፡
“በይ የፈለግሺውን ተናገሪ” አላት ሀብታሙ ሰው፡፡
በቀቀኗም፤
“ሰርቀህ ነው ያመጣኸኝ፤ አንድ ቀን ትጠየቅበታለህ!” አለችው፡፡
ለካ ይህንን ቃል ጠዋት ያስጠናት ሰርቆ ያመጣት ቅጥረኛ ኖሯል!
“ለክፉና ለአመንዝራ ትውልድ ምልክት አላሳየውም፡፡ እንዲሁ አጠፋዋለሁ!” ይላል ፍካሬ - ኢየሱስ፡፡ ያለምልክት እንዳንጠፋ ያሰጋናል፡፡ የክፉ ዘመን ሌብነት እጅግ ያፈጠጠ ይሆናል፡፡ ሌብነት ለጊዜው ያስደስት ይሆናል፡፡ ውሎ አድሮ ግን መጠየቅ የግድ ይሆናልና የአገርም የህዝብም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የሚሊዮኖች ዐይን ከገባንበት ገብቶ ፈልፍሎ ያወጣናልና!
ሀብትን በንፁህ ታታሪነት ማግኘት ንፁህ እንቅልፍ እንድንተኛ ያደርገናል፡፡ በአንፃሩ ለአንዲት ቤሣ ማትረፊያ እንኳን የተጠቀምንበት ዘዴ፣ “ቢዝነስም ይሁን አራዳነት” ፣ ሌብነት ያለበት ከሆነ፣ ይዋል ይደር እንጂ እንቅልፍ መንሳቴ አይቀርም፡፡ “ማክቤት እንቅልፍን ገደላት፣ በእኩለ-ሌሊት አፍኖ” እንዳለው ነው ሼክስፒር፤ በፀጋዬ ቃል-ቀመር፡፡ “የሰው ሚስት ይዞ የተኛ ኮሽ ሲል ይደነብራል” እንደሚባለው እንቅልፍ ያሳጣል - በማደንዘዣ ካልተኛን በስተቀር! በቃኝን አለማወቅም ትልቅ በሽታ ነው፡፡ ይብቃኝ፤ ማለትም ለከት ማበጀት ነው! አንድ ቀን መያዜ አይቀርም ማለትም ያባት ነው!
ሀገራችን በንፁህ የሥራ ጥረት ሀብት የሚፈራባት ሀገር መሆኗ ካቆመ ቆይቷል። ወደ ሙስና ሀገርነት ከተሸጋገረች ሰንብታለች! ምዝበራ የዕለት የሰርክ-እንጀራ ሆኗል። የኢኮኖሚ አቅማችን ደካማ ስለመሆኑ ጧት-ማታ እያወሳን፤ ዝርፊያው ላይ አለመስነፋችን አስደናቂ ግርምቢጦሽ (Irony) ነው፡፡ ጥንት “የቢሮክራሲ አሻጥር” ሲባል የነበረው ዛሬ በይፋ መጥቷል፡፡ “ክራይ-ሰብሳቢም” ይባል “ደላላ” ድልብ ድልብ ሙሰኛ እያየን ነው፡፡ ጥንት “አሻጥረኛ ነጋዴ” ይባል የነበረው ዛሬ ህጋዊ ህገ-ወጥ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ጥንት “አቀባባይ ከበርቴ” የተባለውን ዛሬ “ደላላ” ብለን ስሙን አኮሰስነው እንጂ በተቋማዊም፣ በቡድናዊም፣ በግላዊም መልኩ ፈጦ ይታያል፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ የቢሮክራቱ ነው፡፡ አንድ ቦታ ያስቸገረን ሰው ከማስወገድ ይልቅ ሌላ ቦታ ኃላፊነት መስጠት አስገራሚ ልማድ ሆኗል፡፡ “በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል” እንደማለት መሆኑ ነው፡፡ “በአዲስ መልክ ምዝበራ ጀምረናል” ለማለት እየተንደረደርን ነው! መታወቅ ያለበት በግልፅ ፈጠው የወጡ አሻጥሮች እንዳሉ ሁሉ ረቂቅ የሆኑ አሻጥሮችም እንዳሉ ነው፡፡ የስልጣን ሽፋን፣ የወገን ሽፋን የፖለቲካ ሽፋን፣ የሀብት ሽፋን፣ የማዕረግ ሽፋን፣ የኔትወርኩ ሽፋን … ምኑ ቅጡ፣ የረቂቅ አሻጥር ግብዓቶች ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ የሌብነት ሽፋኖች ናቸው! መፈተሽ ያለባቸው ሽፋኖች ጥልቅ ዐይን ይፈልጋሉ፡፡ መርማሪ ዐይን ይፈልጋሉ፡፡ ሀገርን አስቀድሞ ማየትን ይጠይቃሉ፡፡ የራስ ንፁህ ልቡናን ይፈልጋሉ፡፡ በዚያው ልክ በመረጃና በዕውቀት መታገዝን ይሻሉ፡፡ “ሳይቃጠል በቅጠል”፣ “ዕባብን መቅጨት በእንጭጩ” የሚሉን አበው፣ የሚያቆጠቁጠውን የሥልጣን ብልግናና ሙስና እንድንገታ ነው፡፡ ልብና ልቡና ይስጠን!!

Monday, 11 January 2016 11:25

የዘላለም ጥግ

(ስለትውልድ)
- እየተናገርኩ ያለሁት ለሁላችንም ነው፡፡ እኔ
የትውልዱ ቃል አቀባይ ነኝ፡፡
ቦብ ዳይላን
- እያንዳንዱ ትውልድ አዳዲስ አርአያዎች፣
አዳዲስ ሰዎች፣ አዳዲስ ስሞች ይፈልጋል።
ራሱን ከቀድሞው ትውልድ ለማፋታትም
ይሻል፡፡
ጂም ሞሪሶን
- ህፃናት የትውልድን መስመር ከትውልድ
የሚያገናኙ ነቁጦች ናቸው፡፡
ሎይስ ዊሴ
- ለቀጣዩ ትውልድ ድልድይ ለመሆን እሻለሁ፡፡
ማይክል ጆርዳን
- የእኔ ትውልድ የመካከለኛ ዕድሜ ቀውስ
እያጋጠመው ያለው በ20ዎቹ ዕድሜው ላይ
ነው፡፡
ኢድዋርድ ኖርተን
- ትኩረትህን በመጪው ትውልድ ላይ
ካላደረግህ አገርህን እያጠፋህ ነው፡፡
ማላላ ዮሶፍዛይ
- በዚህ ዘመን እምብዛም የትውልድ ክፍተት
የለም፡፡
ክሪስ ፍራንትዝ
- የእያንዳንዱ ትውልድ ሳይንቲስቶች
የሚቆሙት በቀድሞዎቹ ትከሻ ላይ ነው፡፡
ኦዌን ቻምበርሌይን
- አባቴ ብሉይ ኪዳን ነበር፡፡ እኔ አዲስ ኪዳን
ነኝ፡፡ እኔ የአዲሱ ትውልድ አካል ነኝ፡፡ ሰዎች
ይሄን በጊዜ ሂደት ይገነዘባሉ፡፡
ዚጊ ማርሊ
- እያንዳንዱ ትውልድ አዲስ አብዮት
ይፈልጋል፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶሪዮ
- የህይወት ዘመን ደስታ ከፈለግህ … ቀጣዩን
ትውልድ እርዳ፡፡
የቻይናውያን አባባል
- አንዱ ትውልድ እንደቅንጦት የሚመለከተውን
ቀጣዩ ትውልድ እንደ መሰረታዊ ፍላጎት
ይመለከተዋል፡፡
አንቶኒ ክሮስላንድ

- ባለፉት 10 አመታት የተገደሉ ጋዜጠኞች 787 ደርሰዋል
በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2015 በአለማችን 100 የተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች በስራቸው  ምክንያት ወይም ባልታወቀ ሰበብ መገደላቸውን ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው አለማቀፍ የጋዜጠኞች
መብት ተሟጋች ተቋም ባለፈው ማክሰኞ አስታወቀ፡፡ በአመቱ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት ጋዜጠኞች መካከል ስድሳ ሰባቱ በስራቸው ላይ እያሉ  ተገድለዋል ያለው ተቋሙ፤
ይህም ባለፉት አስር አመታት ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የተገደሉ ጋዜጠኞችን ብዛት 787 እንዳደረሰው ጠቁሞ ሌሎችበሰላማዊ አገራት የሚንቀሳቀሱ በርካቶችም በስራቸው ምክንያት የግድያ ኢላማ መሆናቸውን
አስታውቋል፡፡ በአመቱ 43 ጋዜጠኞች የግድያ ሁኔታቸው ወይም የመገደላቸው ሰበብ ሳይታወቅ መገደላቸውን
የገለጸው ተቋሙ፣ በሙያቸው ጋዜጠኛ ባይሆኑም በዘርፉ የተሰማሩ 27 ግለሰቦችና በሌሎች ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ 7  ሰራተኞች መገደላቸውንም ጠቁሟል፡፡
በአብዛኞቹ ጋዜጠኞች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ናቸው ያለው ተቋሙ፣
ለጋዜጠኞች የሚደረገው ከለላ አናሳ መሆኑን ጠቁሞ፣ የተባበሩት መንግስታት በሟቾቹ ላይ ለተወሰደው እርምጃ  የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ በ2014 በተለያዩ የአለማችን አገራት ከሞቱት ጋዜጠኞች መካከል ሁለት ሶስተኛ ያህሉ ጦርነት
ባለባቸው አካባቢዎች የተገደሉ እንደነበሩ ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በተቃራኒው በ2015 ከሞቱት ጋዜጠኞች መካከል ሁለት ሶስተኛ ያህሉ ሰላማዊ ተብለው በሚታወቁ አካባቢዎችና አገራት የተገደሉ መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል፡፡ በአመቱ 11 ጋዜጠኞች የተገደሉባት ኢራቅ፣ለጋዜጠኞች አደገኛ የሆነች የአለማችን ቀዳሚዋ አገር  መሆኗን የጠቀሰው ተቋሙ፤10 ጋዜጠኞች የተገደሉባት ሶርያ በሁለተኛነት መቀመጧን፣ በቻርሊ ሄቢዶ መጽሄት ዝግጅት  ክፍል ላይ ሽብርተኞች በፈጸሙት ጥቃት 8 ጋዜጠኞች የተገደሉባት ፈረንሳይም ሶስተኛ ደረጃን መያዟን  ገልጧል፡፡
አይሲስና አልቃይዳን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች በአመቱ 28 ጋዜጠኞችን መግደላቸው የተነገረ
ሲሆን በተለያዩ አገራት የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥርም 153 ደርሷል፡፡

- ከ6 አመታት ወዲህ ዝቅተኛው ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል
በዋና ዋናዎቹ የአለማችን የበለጸጉ አገራት የተከሰተው የተቀዛቀዘ የኢኮኖሚ እድገትና ሌሎች አለማቀፍ ኔታዎች በሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ሳቢያ በ2016 የአለም ኢኮኖሚ እድገት በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ
እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ የ2006
የአለማችን የኢኮኖሚ እድገት እ.ኤ.አ በ2009 ከተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ወዲህ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ይደርሳል  ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱ በ2014 አመት ከተመዘገበው 3.4 በመቶ እድገት በታች ይሆናል ያሉት  ዳይሬክተሯ፤ በ2015 በአለማቀፍ ንግድ እድገት ላይ ከፍተኛ ቅናሽ መታየቱን ጠቁመው በሸቀጦች ዋጋ ላይ የታየው  ቅናሽም ሃብትን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ባላቸው አገራት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ሩስያና ብራዚልን የመሳሰሉ አገራት የከፋ የኢኮኖሚ ችግር
እንደሚገጥማቸውም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ የምርታማነት መቀነስ፣ የአምራች ዜጎች ቁጥር ማሽቆልቆል፣ ከፍተኛ ብድር፣ አነስተኛ  ኢንቨስትመንትና የመሳሰሉት ጉዳዮች በአውሮፓና በሌሎች አገራት ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

- የአልቃይዳው መሪ ስሜት ቀስቃሽ ግጥም ለሰልጣኞች ታድሏል
አልቃይዳን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች ግጥምን ተጠቅመው የግለሰቦችን ልብ በማማለል አዳዲስ  አባላትን እየመለመሉ እንደሚገኙና የፕሮጋንዳ መሳሪያ እንዳደረጉት ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ያወጣውን የጥናት
ውጤት ጠቅሶ ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡ ታጣቂ ቡድኖቹ የግለሰቦችን ስነ ልቦና ለመቀየርና ስሜታቸውን ለመግዛት ግጥምን በመሳሪያነት  እየተጠቀሙ ነው ያለው ዘገባው፤ ይህም አላማቸውን ለማስረጽና አዳዲስ አባላትን ለማፍራት ሁነኛ መሳሪያና ስልት  እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ አልቃይዳ በየመን ግጥምን እንደ አንድ ሃይለኛ የጂሃድ መሳሪያ እየተጠቀመ ነው ያለው  ዘገባው፤የሽብር ቡድኑ የግለሰቦችን ቀልብ የሚስቡ አማላይ ግጥሞችን በማሰራጨት ሰፊ የፕሮፓጋንዳና የቅስቀሳ ስራ  እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡ ኦሳማ ቢን ላደን በ2000 ዓ.ም በተፈጸመ ጥፋትና በሌሎች የአልቃይዳ አንቅስቃሴዎችና አላማዎች  ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ግጥሞችን እንደጻፉ ያስታወሰው ዘገባው፣ ሌላ የቀድሞ የቡድኑ መሪ የጻፋቸው ስሜት  ቀስቃሽ ግጥሞችም፣ በቡድኑ ለሽብር ተመልምለው ሲሰለጥኑ የነበሩ ጂሃዲስቶችን ለጥቃት ለማነሳሳት በስፋት  ተሰራጭተው እንደነበር አመልክቷል፡፡

- አዲሱ ቴክኖሎጂ በአይን ይከፈታል ተብሏል
   ታዋቂው የሞባይል አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ፣ ጋላክሲ ኤስ በሚል መለያ ሲያቀርባቸው የቆዩት
የስማርት ፎን ምርቶቹቀጣይ የሆነውን ጋላክሲ ኤስ 7 በየካቲት ወር አጋማሽ በገበያ ላይ ያውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሲኒውስ ድረገጽ ዘግቧል፡፡ ጋላክሲ ኤስ 7 እና ጋላክሲ ኤስ 7 ኢጅ ተብለው የሚጠሩት አዲሶቹ የኩባንያው ምርቶች፣ በ5.2  እና በ5.5 ኢንች መጠን ለገበያ እንደሚቀርቡ ታውቋል ያለው ዘገባው፤ ሞባይሎቹ ለአጠቃቀም ምቹና የተለየ ዲዛይን ያላቸው እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡ኩባንያው አዳዲሶቹን የሞባይል ምርቶቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስመርቅበት ወቅት 3.3 ሚሊዮን  ያህል ጋላክሲ ኤስ 7 እንዲሁም 1.7 ሚሊዮን ጋላክሲ ኤስ 7 ኢጅ ሞባይሎችን በገበያ ላይ የማዋል እቅድ እንዳለው  ተነግሯል፡፡
አዳዲሶቹ ሞባይሎች ተጠቃሚው በአይኑ በማየት ሊከፍታቸው የሚችላቸው እንደሆኑ ሲወራ መቆየቱንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

Saturday, 02 January 2016 12:04

ኪነት ጥግ

(ስለትወና)
ትወና ምትሃታዊ ነው፡፡ ገፅታህንና አመለካከትህን ይለውጠዋል፡፡ እናም ማንኛውንም ዓይነት ሰው ልትሆን ትችላለህ።
አሊሺያ ዊት
ሞዴሊንግ በዝምታ የሚከወን ትወና ነው፡፡
አሪዞና ሙሴ፡፡
ትወና ለብቸኝነቴ ያገኘሁለት ግሩም መልስ ነው፡፡
ክሌይር ዴንስ
ትወና ደስ የሚል ስቃይ ነው፡፡
ዣን ፖል ሳርተር
ሙዚቃ ህይወቴ ነው - ትወና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዬ ነው፡፡
ስቲቭ በርንስ
ሙዚቃ ሚስቴ ስትሆን ትወና ፍቅረኛዬ ናት።
ማርክ ሳሊንግ
ትወና ዝነኛ የመሆን ጉዳይ አይደለም፤ የሰውን ልጅ ነፍስ የመፈተሸር ጉዳይ ነው፡፡
አኔቴ ቤኒንግ
ለትወና አጋሮችህ በጣም ግልፅና በታሪኩ የምታምን መሆን አለብህ፡፡
ራሄል ማክ አዳምስ
ትወና በጣም ጥበባዊ ሙያ ነው፤ ራሳቸውን ተዋናይ አድርገው የሚያስቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ፤ እውነተኛ ተሰጥኦ ያላቸው ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
ዎልፍጋንግ ፑክ
በቴሌቪዥን ትወናዬ ትልቁ እርካታዬ ከዓለም ጋር የመገናኘት ዕድል ማግኘቴ ነው።
ራይሞንድ ቡር
ጥቂት ፊልሞችን እስክሰራ ድረስ ከትወና ጋር በፍቅር አልወደቅሁም ነበር፡፡ አሁን ግን ያለ እሱ መኖር አልችልም፡፡
ጌራልዲን ቻፕሊን
በሚዲያ ሙሉ በሙሉ  የመረሳትን ዋጋ ከፍዬ ኮሌጅ በመግባት ከትወና ጋር ግንኙነት የሌለውን ፍቅሬን ተወጣሁት የሂሳብ ትምህርት ተማርኩ፡፡
ዳኒካ ማክኬላር
ወላጆቼ ወደ ትወና እንዳልገባ ከመምከር ውጭ ፈፅሞ ጫና አላደረጉብኝም፡፡
ኢሚልያ ፎክስ

መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ለሚያስገነባው ህንፃ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ባደረጉት ንግግር፤ ባንካቸው የማዕከሉ ግንባታ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ተጠናቆ ሲቀርብ የበለጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ በጉብኝቱ ወቅት በተመለከቱት ስሜታቸው በመነካቱ በግላቸው የ10ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል፡፡
በመቄዶንያ ስም የዕርዳታ ቼኩን የተረከቡት የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሪት ኤልሳቤጥ ንጉሤ፣ በአረጋውን ስም ምስጋና በማቅረብ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶችና የግል ድርጅቶች ለማዕከሉ ግንባታ የኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መቄዶንያ፣ መንግሥት ለማዕከሉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በአዲስ አበባ ከተማ አያት ዋና መንገድ ላይ ከሊዝ ነፃ በሰጠው 30ሺህ ካ.ሜ ቦታ የአረጋውያን ማዕከል ለመገንባት እየተዘጋጀ ሲሆን ለማዕከሉ ግንባታ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል፤ በአሁኑ ወቅት ከ850 የሚበልጡ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን እየተንከባከበ ሲሆን የተረጂዎቹን ቁጥር 3ሺ ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡


… የቡዳ ጉዳይ በሀገራችን ባሕል ውስጥ የታወቀ ስለሆነ ለማስረዳት ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ ቡዳና ፖለቲካችንን ምን አገናኛቸው ለሚለው ጥያቄ ግን ተገቢ መልስ መስጠት ስለአለብኝ አንዳንድ ጭብጦችን ላስቀምጥ፡፡ ተረቱ እንደሚለው፣ አንድ ቡዶችን ለይቶ የማያውቅ ሰው፣ የቡዶች መንደር ይደርስና፣ “እዚህ አካባቢ የቡዶች መንደር አለ ይባላል፣ የትኛው ነው” ብሎ ራሱን፤ ቡዳውን ይጠይቀዋል፡፡ ቡዳው ሰው፣ “ቡዶች የምንባለው እኛው ነን” ለማለት ድፍረት ስላጣ፣ “እኛ እዛ ማዶ ያሉት ናቸው እንላለን፣ እነሱ ደግሞ እኛን ይሉናል” አለ ይባላል፡፡
ላለፉት አርባ ዓመታት ለውጥ ለመምጣት ከአንድ ትውልድ በላይ ቀላል ያልሆነ መስዋእትነት ተከፍሎዋል። የሀገራችን ፖለቲካ ባለህበት እርገጥ ከመሆን፣ አንዳንዴ ደግሞ የኋሊት ከመሄድ አላለፈም፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ለፀረ - ቅኝ አገዛዝ ትግል ከከፈሉት በላይ ሀገራችን ውድ ዋጋ ከፍላለች፣ የታሰበው ለውጥ ግን አልመጣም፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ጥያቄ ለሀገራችን ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ኃላፊነቱን የሚወስደው ማነው? የሚለው ነው። ቢያንስ አንዱ በሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር አልፎ የየድርሻችንን እንኳ እንውሰድ ሲባል አይታይም፡፡ እንደቡዳው፤ ስህተት የሠራሁት እኔ ነኝ ከማለት ይልቅ፤ አጥፊዎች እነዛ ናቸው ማለት ይቀላል፡፡ የአንድ ትውልድ ምርጦችን ያለርህራሄ የጨፈጨፈው መንግሥቱ ኃይለማርያም እንኳ “ሰው ይቅርና ዝንብ አልገደልኩም” ነበር ያለው፡፡ ተባባሪዎቹ የነበሩ የደርግ ባለሥልጣናትም ያንን አስከፊ ግፍ የፈጸምነው “የሀገር ፍቅር ያንገበገበን ወታደሮች ነበርን” እያሉ መጽሐፍ እየጻፉ ነው፡፡ የጥፋት ኃላፊነቱንም በሌሎች ላይ እየደፈደፉ ነው፡፡ ቢያንስ ብዙዎቹ በድንቁርና ለጨፈጨፉዋቸው ዜጐች ኃላፊነቱን ለመውሰድ አልተዘጋጁም፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔም ባለፈው ጊዜ በጻፍኩት መጽሐፌ ላይ የነገሮችን ሚዛን ለመጠበቅ በጣም አስቸግሮኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ለአብነት፤ የቀድሞ የመኢሶን ጓዶቼ ከኢሕአፓ ጋር አመሳሰልከን የሚል ቅሬታ እንዳላቸው ነግረውኛል። ታሪክ ፀሐፊዎች ስለ አንድ ድርጊት እርግጠኛ ሆነው መጻፍ ያለባቸው የድርጊቱ ተሳታፊዎች ሲሞቱ ነው የሚሉት የገባኝ አሁን ነው፡፡
አንድ ቀን ከቀድሞ የሕወሓት አመራር አባል ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስናወራ ለተሠሩት ስህተቶች የኃላፊነት ደረጃ ለድርጅቶች ስጥ ብትለኝ ደርግ አንደኛ፣ ሕወሓት ሁለተኛ፣ ኢሕአፓ ያንተ ድርጅት ስለሆነ ነው ወንጀሉን ያስነሳከው” አለኝ፡፡ የቀልድም ይሁን፤ የምር አስተያየቱ ቢያናድደኝም፣ ገርሞኛል፡፡
በእኛ ትውልድ ስላየናቸው የአፄ ኃይለሥላሴ፣ የደርግና የኢሕአዴግ መንግሥታት የትኛውን ትመርጣለህ ቢባል፣ የየዘመኑ ተጠቃሚ ያለምንም ጭንቀት እራሱ ተጠቃሚ  የነበረበትን ሊመርጥ እንደሚችል ይገመታል። በሕዝብ ደረጃ ሲታሰብ ግን፤ እንደጊዜው ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ከቀይ ሽብር በኋላ፣ አብዮቱ የደርግ መንግሥት ጭፍጨፋ እየመረረው ሲመጣ ብዙ ወጣቶች፤ “ተፈሪ ማረኝ፣ የደርጉ ነገር ምንም አላማረኝ” ሲሉ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ምርጫ እንደየ ማህበረሰቡም ሊለያይ ይችላል፡፡ ኦሮሚያና ደቡብ ውስጥ፣ ከዝንጀሮ ቆንጆ…ቢሆንም የደርግ መንግሥት ሊመረጥ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውለታ ይሁን፣ የደርግ መንግሥት፣ የመሬት አዋጅ በእነዚህ አካባቢዎች እስከ ዛሬም ድረስ እጅግ በጣም ሰፊ ድጋፍ አለው፡፡
የቡዳ ፖለቲካችንን ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሁሌም ጥፋተኞች እኛ ሳንሆን እነዛ ናቸው ብለን ስለምንደርቅ ነው፡፡ እዚህ ላይ ፈረንጆች የሚበልጡን በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው፡፡ አንደኛው፣ ለነሱ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ጥፋት መቀበልን እንደሞት አያዩትም፡፡ ሁለተኛ፤ ሥልጣንን የሙጥኝ በማለት አጥፍቶ መጥፋትን ከባህላቸው አስወግደዋል ወይም የኋላቀሮች አስተሳሰብ አድርገውታል፡፡ ቢያንስ ከሂትለር ወዲህ የአብዛኞቹ ጉዞ በዚህ አቅጣጫ ነው፡፡ ሦስተኛው፣ ፖለቲካቸው ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሁሉንም አግኝ ወይንም ሁሉንም እጣ (Zero –sum-game) የሚባለውን ፖለቲካ ከልብ እየተው መጥተዋል፡፡ ይበልጥ ደግሞ ከሥልጣን በኋላ፣ ጥሩ ኑሮ መኖርም፣ ክብር ማግኘትም እንደሚቻል አውቀዋል፡፡ እንደውም ከሥልጣን በኋላ ያለጭንቀት የተደላደለ ኑሮ መኖር እንደሚቻል ያውቃሉ፡፡ ኦባማ በአፍሪካ ኅብረት ንግግሩ የአፍሪካ መሪዎችን ለማስተማር የሞከረው ይህንኑ ነው፡፡ ትምህርቱ ገብቶት ይሁን፤ በተለመደው የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የማስመሰል ፖለቲካ፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሲያጨበጭብ አይቻለሁ፡፡ …
(“የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚል ርዕስ አንጋፋው ፖለቲከኛና የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰሞኑን ለንባብ ካበቁት ሁለተኛ መጽሐፋቸው የተቀነጨበ