Administrator

Administrator

Saturday, 02 January 2016 11:51

የዘላለም ጥግ

ልዕልና ወደ ገፅ 11 ዞሯል
(ስለድንቁርና)
- ራስህን ከሀሰተኛ ዕውቀት ጠብቅ፤
ከድንቁርና የበለጠ አደገኛ ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
- ድንቁርና የእግዚአብሔር እርግማን ነው፤
ዕውቀት ወደ ገነት የምንበርበት ክንፍ ነው፡፡
ዊሊያም ሼክስፒር
- የራስን የመሃይምነት ልክ ለማወቅ ትልቅ
ዕውቀት ይጠይቃል፡፡
ቶማስ ሶዌል
- ዘረኝነት ከድንቁርና ይመነጫል፡፡
ማርዮ ባሎቴሊ
- ድንቁርና የሰው ልጅ ጭንቅላቱን
የሚያሳርፍበት ለስላሳው ትራስ ነው፡፡
ማይክል ዲ ሞንታ ግ
- ግጭት ከድንቁርናና ከጥርጣሬ ይወለዳል፡፡
ጎርዶን ቢ. ሂንክሌይ
- ድንቁርና የኃጢያቶች ሁሉ እናት ነው፡፡
ፍራንሶይስ ራቤላይስ
- ውይይት የዕውቀት ልውውጥ ሲሆን ክርክር
የድንቁርና ልውውጥ ነው፡፡
ሮበርት ኪውሌን
- በሰው ልጅ ታሪክ ድንቁርና ከዕውቀት ተሽሎ
የተገኘበትን ጊዜ አላውቅም፡፡
ኔይል ዲግራሴ ታይሰን
- ድንቁርና ሁልጊዜ ለውጥን ይፈራል፡፡
ጃዋሃርላል ኔህሩ
- የድንቁርና እውነተኛ ባህርያት፡- እብሪት፣
ኩራትና ትቢት ናቸው፡፡
ሳሙኤል በትለር
- ድንቁርና፣ ጥላቻና ስግብግብነት ተፈጥሮን
እየገደሏት ነው፡፡
ፓውል ሃሪስ
- ድንቁርና ፍርሃትን ይፈለፍላል፡፡
ማይክ ዊልሰን
- በድንቁርና አፈር ላይ ፍርሃት በቀላሉ ሊዘራ
ይችላል፡፡
ሂዘር ብሩክ

እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ያው እንደተለመደው ከተማችን “ታላቅ ቅናሽ” ‘Sale’ ምናምን የሚሉ ማባበያዎች በብዛት እየታዩ ነው፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… እዚሀ አገር መጀመሪያስ ነገር ብዙዎቹ ዕቃዎች፣ በተለየ ደግሞ አልባሳት፣ በድርድር አይደል እንዴ ሸመታ የሚካሄደው! እናማ…ከምኑ ላይ እንደቀነሱ ለማወቅም አስቸጋሪ ነው፡፡ መጀመሪያ የ‘እርግጡን ዋጋ’ ሳናውቀው…“ምናምን ፐርሰንት ቅናሽ…” የሚሉትን ባናምን አይፈረድብንም፡፡
ሌላ ደግሞ ‘Sale’ ማለት በሚጢጢው እንደሚመስለን ‘ማጣሪያ’ ሽያጭ ነው እንጂ ‘ታላቅ ቅናሽ’ ቅብርጥስዮ አይደለም፡፡ እናማ ‘Sale’ የምትሉ ሰዎች የመቶ ብሯን ዕቃ በአሥርና በአምስት ብር ምናምን መሸጥ ነው፡፡ ልክ ነዋ… ከ‘አማሪካን’ ሦስትና አራት ሻንጣ ልብስ በስጦታ የሚመጣው ምስጢሩ ‘Sale’ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እኔ የምለው፣ የባቡር ሀዲድና ቀላል ባቡር በየድራማው ላይ ብቅ፣ ብቅ ማለት ጀመሩ አይደል! ገና ወላ የዘፈን ክሊፕ፣ ወላ ምን በሉት…ሀዲድ በሀዲድ… ባቡር በባቡር ባይሆን! ደግነቱ እስካሁን ሀዲዱ ላይ መጨፈር አልተፈቀደም መሰለኝ፡፡
ያኔ ቀለበት መንገዱ ‘አዲስ’ የነበረ ጊዜ እንዲሁ ነበር፡፡ የትራፊክ ህግ የለ…‘አካፋዩን መዝለልና ላዩ ላይ ‘አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ’ አይነት ለአደጋ ያጋልጣል ማለት የለ…ብቻ ምን አለፋችሁ… ሲደነከርበት ከረመላችሁ፡፡
እናላችሁ… ከባቡር ሀዲዱ ጋር መክረማችን ካልቀረ ለምን የዘፈን የምናምን ግጥሞች በዛው አይጻፉልንም፡
ትመጫለሽ ብዬ ማዶ ማዶ ሳይ
ይሄ ቀላል ባቡር መቅረቱ ነው ወይ
አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ… ያውም በኤሌትሪክ መቋረጥ አንዳንዴ ቀጥ እያለ ነው እየተባለ ባለበት ጊዜ…በሰዓቱ ትድረስ፣ አትድረስ ማን ያውቃል!
ደግሞም ሌላ አለላችሁ…
በቀላሉ ባቡር መንሸርሸር ለምደሽ
ከእኔ ከድሀው ጋር መች ትሄጃለሽ
ልክ ነዋ! ዘንድሮ ልጄ…
“ድሀ የዋህ ነው…”
“ከጠገበ ሀብታም የተራበ ድሀ ይሻለኛል…”
ምናምን የሚባሉ ነገሮች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አብቅቷል፡፡ ተወደደም ተጠላም እንዲሉት አማርኛ…ተወደደም ተጠላም ፈረንካ ዘንድሮ ሁሉንም ነገር እያሽከረከረ ነው፡፡
እናማ…
“ከእሱ ጋር ቆሎ ቆርጥሜ እኖራለሁ…ከዕለታት አንድ ቀን ያልፍልናል…” ብሎ ነገር የለም፡፡
እናላችሁ ባቡርና ሀዲድ ድራማ ላይ መምጣታቸው ካልቀረ ውሀ ባይኖርም ነገ፣ ተነገ ወዲያ እንደ ‘ቢች’ ማገልገላቸው ካልቀረ ግጥሞች አሁኑኑ ይገጠሙልንማ፡፡
እንደ ባቡሩ ሀዲድ የተጠመጠመው
እንደ ባቡሩ ሀዲድ የተጠማዘዘው
ምን መስሎሽ ነበረ የእኔ ልብ እኮ ነው
ቂ…ቂ…ቂ…. የምር ግን እንዲህ ብሎ የሚገጥም ሰው መጀመሪያ ኤ.ኬ.ጂ. ነው ምናምን የሚሉትን ነገር ነው መታየት ያለበት፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ከተማችን ‘ህንጣ በህንጣ’ አይደል…ህንጻዎቹ አናት ላይ ሳይቀር ዘፈንና ምናምን ሁሉ ተጀምሯል፡፡ የምር ግን…በዚህ አይነት ነገር ከዓለም ከቀዳሚዎቹ መሀል ሳንሆን አንቀርም። ታዲያላችሁ…
 በህንጻው አናት ላይ የቆምኩት አሁን
 ከሺህ ሰው መካከል አይሽ እንደሆን
ምናምን ማለት አሪፍ አይደል! “ስንቱን አሳልፌው እዘልቀው ይሆን…” የሚለውን ‘አፕዴት’ እንደማድረግ ማለት ነው፡፡
የምር ግን ይሄ የኮፒራይት ነገር መልክ ሲይዝ የዘፈን ግጥም መሞከር አለብኝ፡፡
እንደ ባቡሩ ሀዲድ ልብሽ የረዘመው
አልጎተት አለኝ ብስበው፣ ባስበው
ይሄ አሁን ምን ይወጣለታል!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በየፊልሙና በየድራማው ላይ መአት ተዋንያን እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ ግን… አለ አይደል… “እንደው አሁን ከዚህኛው/ከዚችኛዋ ሻልየሚል  ሰው ጠፍቶ ነው!” እንላለን፡፡
በዛ ሰሞን… አንድ ሬድዮ ጣቢያ ላይ “እንዴት እንደማይተወን የሚያሳዩ ተዋንያን…” ምናምን ተብሎ የተጠቀሰው አይነት ማለት ነው፡፡ እኔ የምለው…እሱ ፕሮግራም ምነው ባለፈው ሳምንት ቄሱም ጭጭ፣ መጽሐፉም ጭጭ ሆነ! ‘ሰዎች አስቀየመ’ እንዴ!
እናማ…‘የማለዳ ኮከቦች’ ላይ የምናያቸው ልጆች የምርም ይቺ አገር የተዋንያን ችግር እንደሌለባት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዳኞቹ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሟትን ቃል ለመጠቀም “የሚገርም ችሎታ” ያላቸው መአት ልጆች አሉ፡፡ እናማ… የተዘጉ በሮች በበዙበት ዘመን የትወና ዓለምን ቶሎ እንዲቀላቀሉ አንድዬ በሩን ወለል አድርጎ ይክፈትላቸውማ!
ስሙኝማ… የድራማዎችን ነገር ካነሳን አይቀር…አሁን፣ አሁን አንዳንዴ ግራ የመጋባት ነገር እየገጠመን ስለሆነ ታሪኮቹን እያጠራችሁልን ሂዱማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ፡፡ እሷዬዋ ለጓደኛዋ ስለሆነ ሰው እየነገረቻት ነው፡፡
“ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ… ‘በጣም ታምሪያለሽ’ አለኝ፣” ትላታለች፡፡
ጓደኝዬዋ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው…
“ፍቅር እውር ነው የሚሉት እውነታቸውን ነው፣” ብላት አረፈች፡፡
የዘንድሮ ጓደኝነት! ያቺኛዋ እኮ በሆዷ… አለ አይደል… “ቆይ ብቻ፣ ቀላል ባቡር ሀዲድ ላይ ክሊፕ ሠርቼ ኮረንቲ ባላስጨብጣት!” ምናምን ልትል ትችላለች፡፡
እናማ ቀላል በባሩንና ሀዲዱን ታሳቢ ያደረጉ ግጥሞች አሁኑኑ ተዘጋጅተው ይቀመጡልንማ፡፡
እኔ እዚህ ታቹን ኮብልስቶን ላይ
አንቺ ከበላዬ በሀዲዱ ላይ
ምሰሶ ቧጥጬ ልመጣ ነው ወይ!
ይቺ የምር አሪፍ ነች፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉም ‘ስንኞች’ (“ተባለ!” የሚሉ አራዶች አንድ ዘመን ላይ ነበሩ፣) ለ‘ፍሪ ዳውንሎድ’ ዝግጁ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው፡፡
እስቲ ሸመታውም በልኩ ይሁን…
ሲፑም’ በልኩ ይሁን…
በሰው ሰው ላይ ‘ጆፌ መጣሉም’ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍና መልካም የበዓል ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ገንዘብ ካጠረ ‘ጥቆማ’…“ገንዘብ ስትበደር ከጨለምተኛ ሰው ተበደር…” የሚሏት ነገር አለች። ለምን መሰላችሁ… ጨለምተኛ ስለሆነ “ገንዘቤን ይመልስልኛል…” ብሎ አያስብማ፡ አሪፍ ስትራቴጂ አይደለች!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Saturday, 02 January 2016 11:50

የገና ዛፍ እውነታዎች!

• የተፈጥሮ ፅድ አሳድጐ ለገበያ ለማቅረብ ከ7-10
ዓመት ይፈጃል፡፡
• በአሜሪካ 98 በመቶ ያህሉ የገና ዛፍ የሚያድገው
በእርሻ ማሳ ነው፡፡
• በአሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ
የሚሆን መሬት ለገና ዛፍ እርሻ ይውላል፡፡
• በአሜሪካ 21 ሺህ የተፈጥሮ ፅድ አብቃይ ገበሬዎች
አሉ፡፡
• በአሜሪካ በገና ወቅት የተፈጥሮ ፅዶች ከተቆረጡ
በኋላ እንዳይበላሹ በግል በሄሊኮፕተሮች
ይሰበሰባሉ፡፡
• በአሜሪካ በየዓመቱ ከ34 እስከ 36 ሚሊዮን
የሚደርሱ የተፈጥሮ የገና ዛፎች የሚመረቱ ሲሆን
95 በመቶ የሚሆኑት ወደ ውጪ አገር የሚላኩ
ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የሚሸጡት
ማሳው ላይ እንዳሉ ነው፡፡
• በአሜሪካ “ብሔራዊ የገና ዛፍ ማህበር” በየዓመቱ
ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት የገና ዛፍ ስጦታ ይልካል፡፡
• ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የቆመውና በልዩ ልዩ
ጌጣጌጦች የተዋበው የገና ዛፍ የተሰራው እ.ኤ.አ
በ1510 ዓ.ም በላቲቪያ ነው፡፡
• በአሜሪካ አንድ መቶ ሺህ ያህል ግለሰቦች በገና
ዛፍ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ይሰራሉ።

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ አንድ ክፉ ሚስት ነበረችው፡፡
ጠዋት አልጋ ላይ እያለች፤
“ተነስ አቶ ባል፤ እሳት አያይዝና ቁርስ ሥራ!” ብላ በቁጣ ታዘዋለች፡፡
አቶ ባል፤
“ኧረ እሺ መቼ እምቢ አልኩና ትቆጪኛለሽ የእኔ እመቤት!” ይላታል፡፡
ሚስት፤
“ተነስ ብያለሁ ተነስ! የምን መልስ ነው ደሞ!”
ባል ፍንጥር ብሎ ካልጋ ወርዶ ወደ እሳት ማያያዙ ይገባል፡፡
እጇንና ፊቷን አስታጥቦ ሲያበቃ፤ ቁርሷን ያበላታል፡፡ ከዚያ ሞፈር ቀንበሩን ይዞ ወደ እርሻው ይሄዳል፡፡
ማታ ሲመለስ ደሞ “ና እግር እጠብና፤ እራት አቅርብ፣ ና ታጠብና ተኛ!” ትለዋለች፡፡
ከዚች ክፉ ሚስቱ ጋር ብዙ ዓመት ኖረው ባጋጣሚ ታመመችና ሞተች፡፡ ብዙ ዓመት ደግሞ ያለ ሚስት ኖረ፡፡ መንደሬው ሀዘን ይበቃሃል ብሎ ለሌላ ሚስት ዳረው፡፡
ይህችኛዋ ሚስት ደግሞ “ምን ሲደረግ ማዕድ ቤት ባል ይገባል? ምን ሲደረግ ሴት እያለች ባል ወጥ ቤት ይገባል? ምን ሲደረግስ ወንድ ሥራ ሲደክም ውሎ ቤት ሲገባ በሴት ሥራ ገብቶ ጉድ ጉድ ይላል?” የምትል ሆነች፡፡
ስለዚህም፤
ከአልጋ ሲወርድ ገንፎውን አዘጋጅታ፤ ባፍ በአፉ ታጐርሰው ጀመር፡፡
ከሥራ ሲመጣም፣ አግሩን ለማጠብ ውሃ አሙቃ አዘጋጅታ እግሩን አጥባ፣ ራቱን አብልታ፣ ገላውን በቅባት አሽታ ታስተኛዋለች፡፡
ይህ እንክብካቤ እጅግ አድርጐ አስደሰተው፡፡ ሆኖም የሰው ነገር ሁሌም የተሻለ መመኘትና የያዝኩት አይበቃኝም ማለት ነውና እንዲህ ሲል ፀለየ፡-
“ከዚች የተሻለች የማገባ ከሆነ
ምነው እቺም በሞተች?”  
*   *   *
የሰው ልጅ በቃኝን አያቅም፡፡ የኢኮኖሚ ምርምር አባት የሆነው አዳም ስሚዝ እንዳለው፤ “Human wants are unlimited” (የሰው ልጅ ፍላጐት ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም) ይህንን ፍላጐት ወደ ህብረተሰብ ፍላጐት ስንመነዝረው የአገር ጥያቄ ይሆናል፡፡ የመጠለያ ጥያቄ፣ የምግብ ጥያቄ፣ የአልባሳት ጥያቄ፣ ከዚያ ደግሞ የነፃነት ጥያቄ፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ፣ የፍትሕ ጥያቄ ይዥጐደጐዳል፡፡ አንዱ ቢሟላ ሌላው ይቀጥላል፡፡ ይህ የሰው መሠረታዊ ባህሪ ከጥንስሱ የማይቆምና አይቀሬ ሂደት ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ያሉት አካላት እነዚህን ፍላጐቶች አውቀው፣ ተረድተው፣ መልክና ቅጥ አበጅተው ኑሮን የሚያሳኩ ናቸው፡፡ ፍላጐት በመነጨ ቁጥር ሳይቆጡ፣ ሳያፈጡ፣ ዐይን ሳያጉረጠርጡ መፍትሔውን መሻት ግዴታ ነው፡፡ ኃላፊነት ነው፡፡ አሊያ ተጠያቂነት አይቀሬ ነው፡፡ የመጠለያ ችግር መሠረታዊ ነው፡፡ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ችግር መሠረታዊ ነው፡፡ አንገብጋቢም ነው፡፡ መፈታት አለበት፡፡ የህዝቡ ኑሮና የአገር ኢኮኖሚ መጣጣም አለባቸው፡፡ ያ ካልሆነ ብሶትና ምሬት ይወለዳሉ። እነዚህ በፈንታቸው እምቢተኝነትን፣ አመጽን ይፈለፍላሉ፡፡ ስለዚህ ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው፣ መላ ሊመታባቸው፣ መፍትሔ ሊያገኙ፣ በብስለት ሊቃኙ ይገባል፡፡ መልካም አስተዳደር እኒህን ሁሉ ይጠቀልላል፡፡
ስለመልካም አስተዳደር እያወራን ስለሙስናም ካላሰብን፣ ስለሙስና እያወራን ስለፍትህ ካላሰብን፣ ስለፍትህ እያወራን ስለዲሞክራሲያዊ መብቶች ካላሰብን፣ ስለዲሞክራሲ እያወራን ስለኢንቨስትመንት እንቅፋቶች ካላወሳን የምናውጀው መሬት አይረግጥም፡፡ አንዱን ቀዳዳ ደፈንን ብለን በሚዲያ ስንኩራራ፣ ሌላው ቀዳዳ የበለጠ አፉን ከፍቶ ይውጠናል፡፡ “አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?” ማለት አለብን፡፡ አሁንም የባለሀብትንና የቢሮክራሲውን ሽርብ አሻጥ መፈተሽ አለብን። ምክንና ውጤቱን (Cause and effect እንዲሉ) ማጤን አለብን፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ካፈጠጠው ሙስና ጋር ይጋጫል፡፡ መሬት ሸንሽኖ ከሸጠ፣ የኪራይ ቤቶችን ቤት በእጁ ካስገባ፣ በሥልጣኑ ያሻውን እያረገ በፍርደ ገምድልነት ህዝብን ካስለቀሰ በኋላ፤ እንደ ጨዋ ስለመልካም አስተዳደርና ስለህዝብ መበደል የሚለፍፈው እጅግ እየበረከተ መጥቷል፡፡ የኋላዬ አይፈተሽም፣ አይመረምርም በሚል በአደባባይ ኮርቶ የሚናገረው በዝቷል፡፡ ሁኔታው ቢያመች በለመደው ሌባ እጁ ያገኘውን ከመመዝበር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ምነው ቢሉ? ልቡ በአያ ጅቦ ፍልስፍና የተጠመቀ ነውና “እንብላም ካላችሁ እንብላ፡፡ አንብላም ካላችሁ እንብላ” ከማለት አይመለስም፡፡  

መግቢያ
ባሳለፍነው ዓመት ነሀሴ ወር በባህርዳር የተካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ዋነኛው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉ ተከታታይ መድረኮችም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሲወያዩና ህዝብን ሲያወያዩ ቆይተዋል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ መልካም አስተዳደር  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዴት ሊሰፍን ይችላል በሚል በዩኒቨርሲቲዎቹ ሲካሄድ ነበር፡፡ እኔ በማስተምርበት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲም በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ስላሉ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር ውይይት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ባለስልጣናት በመሩት ስብሰባ ተካሂዳል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተነሱ የተለያዩ ችግሮችና መፍትሄዎች ቢያንስ ከንድፈ ሃሳብ አንጻር የላቀ ዋጋ እንዳላቸው ባይካድም፣ በውይይቱም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ መድረኮች ላይ መልካም አስተዳደር በተግባር ይሰፍን ዘንድ በመሰረታዊነት ሊነሱ የሚገባቸው ነገሮች አልተነሱም ብዬ አምናለሁ፡፡
የዚህ መጣጥፍ ዓላማ በትምህርቱ ዘርፍ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ተግባራት ወሳኝ ሚና ያላቸው፣ ነገር ግን በእኔ ግምት ትኩረት የተነፈጋቸው በምላቸው ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ምልከታዬን ለመግለጽ ነው፡፡ በትምህርቱ ዘርፍ የመልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር መሰረታዊ ተብለው ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች እንደ የትምህርት እርከኑ፣ ማለትም በመጀመሪያና ሁለተኛ (መሰናዶንም ጨምሮ) ደረጃ፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች) ነባራዊ ሁኔታዎች ሊለያዩ የሚችሉበት ዕድል ስለሚኖር በመጣጥፉ የሚነሱት ሀሳቦች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንጻር እንደሆነ አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡
መልካም አስተዳደር ምንድነው?
አምስቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እሴቶች (values) ተብለው የሚነሱት፡ ተደራሽነት (access)፣ አካዳሚያዊ ነጻነት (academic freedom)፣ ተጠያቂነት( accountability)፣ ግልጸኝነት (transparency)፣ በህግ የተገደበ ስልጣን (autonomy) ናቸው፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የመልካም አስተዳደር የመስፈንና ያለመስፈን ሁኔታ ለእነዚህ እሴቶች በሚሰጠው ትኩረት ልክ ይወሰናል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የመልካም አስተዳደር አስፈላጊነት ተቋማቱ የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት አንጻር መታየት አለበት፤ምክንያቱም ተቋማቱ አካዳሚያዊ ዕውቀትን ለተማሪዎች ከማስጨበጥ ባለፈ በስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ የማፍራት ሃላፊነት ስላለባቸው ነው፡፡
መልካም አስተዳደር፤የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ተብለው የተቀመጡ መለኪያዎችን  ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ግብዓት በመሆን፣ለጥናትና ምርምር መደላደል በመፍጠር የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ ከዚህም በላይ መልካም አስተዳደር ለዴሞክራሲዊ ግንባታ መሰረት የሆነውን ዜጎች መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ በማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
ተማሪዎች የዲሞክራሲዊ እሴቶችን ማለትም ለህግና መመሪያዎች መገዛት፣መብትና ግዴታን አውቆ በዚያው ልክ መንቀሳቀስ፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት፣ ለመብትና ለጥቅም ተሟጋች መሆን፣ የሚማሩት በጽንሰ ሃሳብ ትምህርት ሳይሆን በሚማሩበት ተቋም በሚያገኙት አገልግሎት በተጨባጭ ባለው የመልካም አስተዳደር ልክ ነው፡፡ በአጠቃላይ የመልካም አስተደደር መስፈን የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና በማስፈኑ ረገድ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡
ለመልካም አስተዳደር መስፈን ቅድመ ሁኔታዎች
የትምህርት ባለድርሻ አካላት ዘርፉ የሚመራበትን ህግና መመሪያ እንዲገነዘቡ ማድረግ
መልካም አስተዳደር ይሰፍን ዘንድ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት፡ ተማሪዎች፣ መምህራንና ድጋፍ ሰጭ አካላት መብትና ግዴታቸውን ሊያውቁ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የመማር ማስተማርን እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ አገር አቀፍም ሆነ የየተቋማቱ ህጎችን ጠንቅቀው እንዲያውቁ መሰራት አለበት፡፡
የመምህራን የጥቅማ ጥቅም ሁኔታ
እኔ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ከሰባት ዓመታት በላይ በዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግያለሁ፣ እያገለገልሁም እገኛለሁ፡፡ እናም ስለ መማርም ሆነ ማስተማር መሰረታዊ ጉዳች ለመናገር እችላለሁ፡፡ በመሰረታዊነት ትምህርት (ለመማርም ሆነ ለማስተማር) ነጻ አዕምሮን ይሻል፡፡ ትምህርት የተለያዩ ገጽታዎች ቢኖሩትም የስነልቦናው ገጽታ የጎላውን ቦታ ይይዛል፡፡ የመምህራኑን የስነልቦናዊ ዝግጅት ከሚወስኑ ጉዳዮች ደግሞ ኢኮኖሚ ነክ ጉዳይ ዋናው ነው፡፡
መምህር እንደመሆኔ መምህሩ የተጋፈጠውን የኢኮኖሚ ችግር በተግባር አውቀዋለሁ፡፡ አንድም ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ፣ ሌላ ደግሞ በሚከፈላቸው አነስተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ምክንያት በአሁኑ ሰዓት መምህራን የሚመጥናቸውን ሳይሆን በዝቅተኛ ደረጃ እንኳ የምግብ፣ልብስና መጠለያ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችላቸውን የኢኮኖሚ ነጻነት (ወይም ኢኮኖሚስቶች starving wage እያሉ የሚጠሩት የክፍያ ደረጃ) እያጡ ነው፡፡
የኢኮኖሚ ነጻነት የሌለው መምህር፣ እንኳን በጥናትና ምርምር በመሳተፍ ዕውቀትን ለመፍጠርና ለማበልጸግ ይቅርና ቀድሞ የሚያውቀውን ለተማሪዎቹ በአግባቡ ለማስተላለፍ አይቻለውም፡፡ የኢኮኖሚ ችግሩን ለመቅረፍም ከማስተማርና ከምርምር ስራ በተጓዳኝ ሌሎች ስራዎችን መሥራቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ለተማሪዎች መስጠት የሚችለውን ያህል አገልግሎት እንዳይሰጥ ከማድረግ በዘለለለ ማስተማርና ለምርምር ስራዎች ማዋል የሚገባውን ጊዜ ጭምር ይሻማል፡፡ ፣ያውቁትንበአጠቃላይ መምህራን የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በሚያደርጉት ምላሽ በአግባቡ ተዘጋጅተው ወደ ክፍል እንዳይመጡ፣ ፈተናዎችን በጊዜ አርመው ለተማሪዎች መስጠት እንዳይችሉ፣ ለጥናትና ምርምር በቂ ጊዜ አንዳይሰጡ ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው የመምህራን የኢኮኖሚ ሁኔታ በትምህርቱ ዘርፍ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከምሁራን በኩል የሚጠይቀውን ትጋትና ቁርጠኝነት ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
የትምህርት አስተዳደር የራሱ የሆኑ ገጸታዎች እንዳሉት መገንዘብ
ትምህርት ከሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚለይበት ነገር ቢኖር ትርፉ የገንዘብ ወይም ሌላ ትርፍ ማግኘት ሳይሆን መንፈሳዊ ነው፡፡ ይህን ያላገናዘበ የትምህርት አስተዳደር ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ትምህርት የሚመራበት የአስተዳደር ሞዴል የመንግስት ቢሮክራሲ፣ ኢንዱስትሪ፣ የንግድ ተቋማት፣ ግብርና ከሚመራበት ሞዴል የተለየ መሆን እንደሚገባው የመምህራንና ምሁርነት እሴቶች በራሳቸው ያስገድዳሉ፡፡
በመሰረቱ ትዕዛዝ ጠብቆ ሳይሆን መብትና ግዴታውን አውቆ መስራት፣ ለህግና መመሪያ ከፍ ያለ ዋጋ መስጠት ዋነኛ የምሁራን እሴቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የትምህርት አመራር አካላት መምህራን ላይ ትዕዛዝና ቁጥጥር ማብዛት፣ ወዘተ…… ከመምህራን አሴቶች ጋር ስለማይሄዱ፣እንደዚህ ያለው የአስተዳደር ዘይቤ የትምህርት ከባቢውን ከማበላሸት ባለፈ ውጤታማ አይሆንም፡፡
ለዕውቀት ዋጋ የሚሰጥ ስርአት መኖር
የዕውቀትን ዋጋ በሁለት መልኩ መግለጽ ይቻላል። አንደኛው የተፈጥሮ ዋጋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የገበያ ዋጋ ነው፡፡ እውቀቱን የሚሸጥ ሰው (መምህር) በሁለቱም አንጻር ፍትሃዊ ክፍያ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ የእውቀት ተፈጥሯዊ ዋጋ ማሳያ ዕውቀት ሀይል ነው የሚለው መርህ ነው፡፡ በእርግጥ ዕውቀት ሀይል ነው ሲባል የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፉ ዕውቀት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ዕውቀት የችግሮች መፍቻ ቁልፍ የሚሆነው ደግሞ ለዕውቀት ዕውቅና ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ እናም ተፈጥራዊ የዕውቀት ዋጋ ለእውቀት ዋጋ መስጠት ነው፡፡
ለመሆኑ ለእውቀት ዋጋ መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው?› ለዕውቀት ዋጋ መስጠት ሌላ ሳይሆን የማያውቁትን ከመናገርና ለማድረግ ከመሞከር በጉዳዩ ዙሪያ የተሻለ የትምህርትም እና/ወይም የክህሎት ልምድ ላለው ቅድሚያ ለመስጠት ያለው ፍቃደኝነት ማለት ነው፡፡ ለዕውቀት ዋጋ መስጠት ማለት ስራው የሚጠይቀውን የአካዳሚክም ሆነ ተዛማጅ ዕውቀትና ክህሎት ለሚመጥኑ ቅድሚያ መስጠት፣በሌላ አባባል ሰዎች መመዘን ካለባቸው በእውቀታቸውና ክህሎታቸው መሆኑን መገንዘብና ለዚሁ መስራት ነው።
ሁለተኛው የገበያ ዋጋውን በተመለከተ ደግሞ ለተገቢው እውቀት ተመጣጣኝና ፍትሃዊ ክፍያ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ዕውቀት ሀይል እንደሆነ የሚገነዘቡ ቀጣሪዎች (መንግስትም ሆነ ግለሰቦች) በበዙበት የዕውቀት ገበያው የሚመራውና ዋጋው የሚተመነው በውድድር መርህ ሳይሆን ዕውቀት ሀይል ነው በሚለው መርህ ነው፤ማለትም የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በገበያው ላይ የደመወዝ መጠኑን ዝቅ ማድረግ አይኖርም ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ የመምህራን ደመወዝ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም መሆን አለበት፡፡ ዕውቀት ተገቢውን ዋጋ በሚያገኝበት ማህበረሰብ፤ መምህራን የሚገባቸውን ክብርና ቦታ ያገኛሉ፣ ካልሆነ ግን በተቃራኒው ነው፤እናም በትምህርት ተቋማት ውስጥ መልካም አስተዳደር ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች ዕውቀት ተገቢውን ዋጋና ክብር እንዲያገኝ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዙሪያቸው ካለው ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ የተጣጣመ የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ማድረግ
ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የየራሳቸው የሆነ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ነባራዊ ሁኔታዎች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም በህግ ከተቀመጠው የስልጣን ወሰናቸው በተጨማሪ የሚያስገድዳቸው ነባራዊ ሁኔታዊችን ለመጋፈጥ እንዲችሉ በህግ የተገደቡ መብቶች እንዲኖራቸው የሚያስችል አሰራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ይህም በትምህርቱ ዙሪያ የተለየ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ባለ ድርሻ አካላት የተለያዩ እገዛዎችና ድጋፎች አንዲመቻቹላቸው ስለሚያደርግ የስራ ከባቢውን ሚዛናዊ ከማድረግ ባለፈ መምህራን፣ ተማሪዎችና የትምህርት አስተዳደር ተግባራትን የሚወጡ ሁሉ ስራቸውን በጥራትና በትጋት (በተነሳሽነት) እንዲሰሩ ማበረታቻ ይፈጥርላቸዋል። ከዚሁ ጋር አብሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ሁኔታም ይሻሻላል፡፡
(ሀብታሙ ግርማ፤ በጂግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ በቀጣዩ የኢሜል አድራሻቸው - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. - ማግኘት ይቻላል)

ገንዘብ ማባከናቸውን አምነው ይቅርታ የጠየቁ አሉ
    የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት፣ በገንዘብ ምዝበራና በአሰራር ግድፈት የጠረጠራቸው አምስት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ክስ መመስረቱን የአዲስ አድማስ ምንጮች ገለፁ፡፡ ለፓርቲው ዲሲፕሊን ኮሚቴ ክስ የቀረበባቸው የስራ አስፈፃሚ አባላት፡- የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የቀድሞው የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፣የቀድሞው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ ወሮታው ዋሴ፣ የቀድሞው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና በኋላም የጥናትና ስትራቴጂ ሃላፊ የነበሩት ኢ/ር ጌታነህ ባልቻና የፋይናንስና የድርጅት ጉዳይ ፀሐፊና የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆኑት ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር መግቢያ ላይ በፓርቲው ውስጥ ስለገንዘብ ብክነትና አሰራር ብልሹነት መወራት ሲጀምር ብሔራዊ ም/ቤቱ ሶስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋሙን የጠቀሱት ምንጮች፤ ኮሚቴው ለ45 ቀናት ምርመራ በማካሄድ ባለ 48 ገፅ ሪፖርት ማቅረቡ ተጠቁሟል፡፡ ግለሰቦቹ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በክልል ጉዞዎች፣ በብድር መልክ፣ ደረሰኞችን ህጋዊ በማስመሰልና ከተለያዩ ቦታዎች ፓርቲውን ለመደገፍ ከሚገባ ገንዘብ ላይ ከ160 ሺህ ብር በላይ መዝብረዋል ያሉት ምንጮች፤ ብዙ ጽ/ቤቶች ለሌሉት አዲስ ፓርቲ ገንዘቡ በጣም ብዙ ቀዳዳ የሚሸፍን ነው ብለዋል፡፡
“ገንዘቡ ብዙ ባይሆን እንኳን ነገ አገርን እመራለሁ ብሎ በተነሳ ፓርቲ አመራሮቹ ይህን ያህል ማጭበርበር መፈፀሙ ያሳምማል” ብለዋል፤ አንድ አባል በሰጡት አስተያየት፡፡ አጣሪ ኮሚቴው ያወጣው ሪፖርት፣ ክስና ሰነድ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ግለሰቦች የደረሳቸው ሲሆን በምዝበራው ከተጠረጠሩት መካከል የጥናትና ስትራቴጂ ሃላፊ የነበሩት ኢ/ር ጌታነህ ባልቻ፤ የተባለው ገንዘብ መባከኑን አምነው፣ የሚደርስባቸውን ገንዘብ ለፓርቲው ለመመለስ ቃል እንደገቡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
“የግፍ ግፍ የሚሆነው ሲታገሉ ለታሰሩ የፓርቲው አመራሮች ከውጭ የተላከውን ገንዘብ ሳይቀር መመዝበራቸው ነው” ያሉት ምንጮቹ፤ የፓርቲው ሊቀመንበርም ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ለ18 ቀናት ከቢሮው ጠፍተው ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በየካፍቴሪያው ሲሰበሰቡ እንደነበር ተናግረዋል። ሰሞኑን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ በአስቸኳይ ይጠራ መባሉን በመስማታቸው መጥተው ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት፣ በስራ ላይ እንዳሉ ለማስመሰል ሞክረዋል ያሉት ምንጮች፤ “ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በጐንደርና ኦሮሚያ በተነሳው ሁከት ዙሪያ አንድም ቀን ለሚዲያ መግለጫ አለመስጠታቸው ስራቸው ላይ እንዳልነበሩ ያሳያል” ብለዋል፡፡
ስለገንዘብ ምዝበራው የጠየቅናቸው የቀድሞው የፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፤ ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮሚቴ መያዙን ጠቁመው፣ በግለሰቦች የእርስ በእርስ ግጭት የመጣ ስም ማጥፋት እንጂ እሳቸው በጉዳዩ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ወይንሸት ሞላ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ተራ አሉባልታ መሆኑን ጠቁመው የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚወስነውን እየጠበቁ እንደሆነ ገልፀዋል። ተናግረዋል፡፡ የቀድሞው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ ወረታው ዋሴም በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
የፓርቲው ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ እንደሻው እምሻው ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረናቸው በአጣሪ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት የገንዘብ ምዝበራው መፈፀሙን ያመለክታል ያሉ ሲሆን፤ ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ጥብቅ ክትትል የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

በዚህ አመት ማምረት እንደሚጀመር ይጠበቃል
     ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ግሩፕ የተባለው የቻይና የነዳጅ አምራች ኩባንያ በኦጋዴን አካባቢ የሚገኙ ሁለት የነዳጅ ጉድጓዶችን የቁፋሮ ስራ ማጠናቀቁንና በቅርቡም የጉድጓዶቹን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞታ መጠን ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
ኩባንያው የጉድጓዶቹን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞታ መጠን የማጥናት ስራ መጀመሩንና ውጤቱንም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ የገለጹት የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዋጋሪ ፉሪ፣ በዚህ አመት የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ልንጀምር እንችላለን ብለዋል ለሮይተርስ፡፡
እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የተፈጥሮ ጋዝ እንዳላቸው በጥናት ከተረጋገጠውና በካሉብ እና ሂላላ አካባቢዎች ከሚገኙት ሁለቱ ጉድጓዶች፣ 4.7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝና 13.6 ሚሊዮን በርሜል ጋዝነት ያላቸው ተያያዥ ፈሳሾች ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ኩባንያው በ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አምስት ጉድጓዶችን የመቆፈር እቅድ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሮጀክቱ አካባቢውን ከማልማት በተጨማሪ፣ በጅቡቲ የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ መገንባትንና ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ የሚዘልቅ የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋትን ያካትታል ብሏል፡፡
ኩባንያው የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት ስራውን እስከ 2018 መጨረሻ የመጀመር እቅድ እንዳለውና በአመት 3 ሚሊዮን ቶን በማምረት ጀምሮ፣ በሂደት አመታዊ የምርት መጠኑን ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር የማሳደግ ዕቅድ መያዙን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

ከ3 ሺህ በላይ ስደተኞች ባህር ሲያቋርጡ ሞተዋል


    ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ በቀሩት የፈረንጆች 2015 ዓ.ም ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ መግባታቸውንና 3 ሺህ 700 የሚሆኑትም ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸውን አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
እስካለፈው ሰኞ ድረስ በአመቱ ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር 1 ሚሊዮን 5ሺህ 54 መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ቁጥር ባለፈው አመት ከተመዘገበው ከአራት ዕጥፍ በላይ ማደጉን ያመለክታል ብሏል፡፡
በአመቱ ከ455 ሺህ በላይ ሶርያውያንና ከ186 ሺህ የሚልቁ አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞች ከቱርክ ወደ ግሪክ መግባታቸውን ያስታወቀው የአለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞችም ወደ አውሮፓ ለመግባት እየተቃረቡ ነው ብሏል፡፡
በጦርነት ሳቢያ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱና ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም በዘንድሮው አመት ከ60 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በመጀመሪያዎቹ የአመቱ ወራት ብቻ 839 ሺህ ሰዎች አለማቀፍ ድንበሮችን አቋርጠው ወደ ሌሎች አገራት መሰደዳቸውንና አንድ ሶስተኛ ያህሉም ሶርያውያን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
በዘንድሮው አመት በአለማችን ከ122 ሰዎች አንዱ በጦርነት ሳቢያ ከመኖሪያ አካባቢው እንደሚፈናቀል ወይም ወደ ሌሎች አገራት እንደሚሰደድ ድርጅቱ አክሎ ገልጧል፡፡

የአለማችን የመጀመሪያው ድረ-ገጽ አሁንም በስራ ላይ ነው


የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ከተጀመረ ተግባራዊ ከሆነና “ቲም በርነርስ ሊስ ወርልድ ዋይድ ዌብ” የተባለው የአለማችን የመጀመሪያው ድረ-ገጽ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በዚህ ሳምንት 25 አመት እንደሞላው ዘ ቴሌግራፍ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
ቲም በርነርስ ሊ የተባሉት እንግሊዛዊ የኮምፒዩተር ሳይንቲስት እ.ኤ.አ ታህሳስ 20 ቀን 1990 የአለማችንን የመጀመሪያ ድረ-ገጽ እንደፈጠሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ በዚያው አመት ነሃሴ ወር ላይ ስራ የጀመረው ድረ-ገጹ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
በወቅቱ የአውሮፓ የኒውክሌር ምርምር ተቋም (CERN) ተመራማሪ የነበሩት ሳይንቲስቱ፤ የፈጠሩት “ቲም በርነርስ ሊስ ወርልድ ዋይድ ዌብ” የተባለው ድረ-ገጽ info.cern.ch የሚል አድራሻ ያለው ሲሆን፣ ለተጠቃሚዎች ከድረ-ገጽ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ መረጃዎችን የሚሰጥ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለፉት 25 አመታት እጅግ እየተሻሻለና አሰራሩንም ሆነ አቅሙን እያሳደገ መቀጠሉን ዘገባው አስታውሶ፣ ሳይንቲስቱ አሁንም በዘርፉ እየሰሩ እንደሚገኙና የወርልድ ዋይድ ዌብ ማህበርን እየመሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በበርሜል ከ37 ዶላር በታች ደርሷል

የአለም የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ካለፉት 11 አመታት ወዲህ እጅግ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበውን የዋጋ ቅናሽ በማሳየት በበርሜል ከ37 ዶላር በታች መድረሱን የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ድርጅት ኦፔክ አስታወቀ፡፡
ባለፈው አመት በበርሜል ከ110 ዶላር በላይ ይሸጥ የነበረው ነዳጅ፣ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ሊያስመዘግብ የቻለው ከፍተኛ አቅርቦት በመኖሩና የአገራት የኢኮኖሚ እድገት እየተዳከመ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የነዳጅ ፍላጎት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው ሲል ኦፔክ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በነዳጅ ላይ የዋጋ ቅናሽ መፈጠሩ እንግሊዝን በመሳሰሉ አገራት ለተጠቃሚዎች በርካሽ ዋጋ ነዳጅ የማግኘት እድል መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየው የነዳጅ ዋጋው በአዲሱ አመት ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኦፔክ መግለጹን አስረድቷል፡፡
የአለም የህዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እድገት የሃይል ፍላጎትን እስከ 2040 በግማሽ ያህል ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ኦፔክ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም የነዳጅ ፍላጎት ጭማሪ እንደሚያሳይ ግምቱን አስቀምጧል፡፡