Administrator

Administrator

    አቃቤ ህግ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል
    ከአንድ አመት በፊት በሽብር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 10 ተከሳሾች መካከል  የቀድሞ የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌውን ጨምሮ አራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አንድ ሌላ ግለሰብ በቀረበባቸው ክስ ላይ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱ ከትናንት በስቲያ በይኗል፡፡ ቀሪዎቹን 5 ተከሳሾች ይከላከሉ ብሏል - ፍ/ቤቱ፡፡ አቃቤ ህግ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል፡፡
ፍ/ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹን፡- ሀብታሙ አያሌው፣ የሸዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም አብርሃም ሰለሞን የተባለውን ግለሰብ ነው በነፃ ያሰናበተው፡፡ ዘላለም ወ/አገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ሰለሞን ግርማ፣ ባህሩ ደጉና ተስፋዬ ተፈሪ የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ ተከላከሉ ተብለዋል፡፡
አቃቤ ህግ፤ ግለሰቦቹ ከ2000 ጀምሮ ግንቦት 7 ከተባለ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች መረጃ በመለዋወጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአረቡ ዓለም የተከሰተውን አመፅ ለመተግበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረጋቸውንና ከሽብር ድርጅቱ የሚላክላቸውን ገንዘብ እስከመቀበል መድረሳቸውን በመጥቀስ ነው በአራት የሽብር ወንጀሎች ክስ የመሰረተባቸው፡፡የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ሀብታሙ አያሌው ላይ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ አንድ ሳምሰንግ
ሞባይል ስልክና ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተገኙ የተባሉ ተከሳሹ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፋቸው መልዕክቶችና የስልክ ልውውጦች ሲሆኑ የአቃቤ ህግ ምስክሩም በፍተሻ ወቅት ሳምሰንግ ሞባይል በቤቱ እንደተገኘና በስልኩ ውስጥ ምን እንዳለ እንደማያውቅ ለፍ/ቤት አስረድቷል፡፡ ፍ/ቤቱም ማስረጃዎቹንና ምስክሩን መርምሮ በሰጠው ብይን፤ ግለሰቡ ሳምሰንግ ሞባይል ብቻ መያዙ ሽብርተኛ አያስብልም ብሏል፡፡
በማስረጃነት የቀረቡትን ሰነዶችም የመረመረው ፍ/ቤቱ፤ ንግግር አድርጓል በሚል የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስረዱት የአንድነት ድርጅት የመረጃ ኃላፊ መሆኑን ብቻ ነው በማለት ክሱ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ በነፃ እንዲሰናበት በይኗል፡፡ ሌላው ተከሳሽ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺም ሁለት ሳምሰንግ ሞባይል እንደተገኘበትና በሞባይሉ ውስጥ ምን እንዳለ አለማየታቸውን የአቃቤ ህግ ምስክሮች ማስረዳታቸውን የጠቀሰው ፍ/ቤቱ፤ ከብሔራዊ ደህንነት መረጃ የተገኘው ሰነድም
ክሱን በበቂ የሚያስረዳ አይደለም ሲል ግለሰቡን በነፃ አሰናብቷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሸዋስ አሰፋና የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታም በተመሳሳይ ሁኔታ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን፤ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በተጨማሪ ሌላው ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞንንም ፍ/ቤቱ በነፃ አሰናብቷል፡፡ በነፃ ከተሰናበቱት ተከሳሾች መካከል ሀብታሙ አያሌውና አብርሃም ሰለሞን በሌላ ጉዳይ የማይፈለጉ ከሆነ ከሐሙስ ጀምሮ ከማረሚያ ቤት እንዲለቀቁ ፍ/ቤቱ ያዘዘ ሲሆን የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሺ ከዚህ ቀደም ፍ/ቤት በመዳፈር  እስከ 1 ዓመት ከ4 ወር በሚደርስ  እስራት የተቀጡ በመሆኑ ቅጣታቸውን ሲጨርሱ እንዲፈቱ በይኗል፡፡ ተከላከሉ በተባሉት 5 ተከሳሾች ላይ ፍ/ቤት ምስክሮቻቸውን ለመስማት ለህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡ የፍርድ ቤቱን ብይን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ፈይሣ፤ የፓርቲያቸው አመራር
አባል አቶ የሺዋስን ጨምሮ ፖለቲከኞቹ ነፃ መባላቸው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ “አስቀድሞም እነዚህ ሰዎች ሽብርተኞች አልነበሩም፤ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ሰላማዊ ታጋዮች ናቸው” ብለዋል፡፡
በእነ የሸዋስ ላይ ምንም ማስረጃ አልተገኘም መባሉ የተፈረደባቸው ሌሎቹ እስረኞች ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ማለት እንዳልሆነ አቶ ስለሺ አክለው ተናግረዋል፡፡ በነፃ ከተሰናበቱት የአንድነት አመራሮች ጋር በአንድ ካቢኔ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት የፓርላማ አባሉ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በሰጡት
አስተያየት፤ በፍ/ቤቱ ውሳኔ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እንዲህ ያሉ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  መንግሥት በጀመረው መንገድ ሌሎች የህሊና እስረኞችንም መፍታት አለበት ብለዋል - አቶ ግርማ፡፡

      የግብጽ የአቅርቦትና የንግድ ሚኒስትር ካሊድ ሃናፊ፤ የኢትዮጵያን የስጋ ምርት አሁን ከሚሸጥበት ባነሰ ቅናሽ ዋጋ ለመግዛትና ለዜጎች ለማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት  እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን ዘ ካይሮ ፖስት ዘገበ፡፡ግብጽ የኢትዮጵያን የስጋ ምርት በቅናሽ ዋጋ በመግዛት በቶጎና በሌሎች የምዕራብ አገራት ለሚገኙ ግብጻውያን ማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር ከሆኑት አቡ በከር አል ሃናፊ እና በቶጎ የግብጽ አምባሳደር ከሆኑት ሞሃመድ ከሪም ሸሪፍ ጋር መወያየታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ግብጽ ከኢትዮጵያ ስጋ ለመግዛት ያሰበችበትን አዲሱን የቅናሽ ዋጋ በተመለከተ ሚኒስትሩ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ በአገሪቱ ወቅታዊ ገበያ አንድ ኪሎ ስጋ ከ9.58 እስከ 11.1 ዶላር እየተሸጠ እንደሚገኝ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በሁለቱ አገራት ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውንና በወቅቱም የግብጽ ባለሃብቶች በአገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኙ ለአገራቱ መሪዎች መግለጻቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለሃብቶቹ የኢንዱስትሪ ዞን እንዲቋቋም ወይም የትራንስፖርት ወጪን የሚቀንሱና የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰዱ መጠየቃቸውንም
አክሎ ገልጧል፡፡

     በዘንድሮው ክረምት ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ 14 ሰዎች በውሃ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ባለፈው ዓመት ክረምት ከደረሰው አደጋ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠር ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ኪዳነ አብርሃ ለአዲስ አድማስ
እንደገለፁት፤ ክረምቱ ከገባበት ሰኔ 1 ጀምሮ እስከ ትናንት በስቲያ 15 የውሃ አደጋዎች ደርሰው የ14 ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡ አብዛኞቹ በኩሬና በወንዞች ውስጥ ለመዋኘት ሲሞክሩ ሰጥመው መሞታቸውን አቶ ኪዳነ ገልፀዋል፡፡ አደጋዎቹ በብዛት ያጋጠሙት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማሪያም አካባቢ በሚገኙ ሁለት ኩሬዎች ውስጥ ሲሆን በእነዚህ ኩሬዎች 6 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል፡፡ በጀሞ የኮንዶሚኒየም ሳይት ለቤቶች ግንባታ ለሚውል ጠጠር ማምረቻ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ በተጠራቀመ የኩሬ ውሃ ደግሞ 3 ሴት ህፃናት ገብተው መሞታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት 21 የውሃ አደጋዎች አጋጥመው የ8 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ፣ ዘንድሮ 15 አደጋዎች አጋጥመው የ14 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡  ዓምና ክረምት ላይ መንገድ ዳር በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ የሞተ ሰው እንደሌለ የጠቆመው የባለስልጣኑ ሪፖርት፤ ዘንድሮ በዓለም ባንክና በቱሉ ዲምቱ አካባቢ የ60 እና የ65 ዓመት አዛውንቶችን ጨምሮ 3 ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን ገልጿል፡፡ ክረምት ት/ቤት የሚዘጋበት ወቅት በመሆኑ ህፃናትና ታዳጊዎች ዋና ለመለማመድ በሚል ወንዝና ኩሬ ውስጥ እየሰመጡ የሚሞቱ ሲሆን ወንዝ ይዞ የሚመጣን ቁሳቁስ ለመለቃቀም ሲሞክሩም በውሃ የመወሰድ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ አቶ ኪዳነ ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ በተለይ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ወደነዚህ ቦታዎች እንዳይጠጉ በማድረግ አደጋውን መከላከል ያሻል ያሉት አቶ ኪዳነ፤ ጎርፍ አቅጣጫውን ስቶ ወደ መኖሪያ ቤቶች እንዳይገባም ቱቦዎችን  ከደረቅ ቆሻሻ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ማናቸውም የመንግስት አካላትም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ለተለያዩ ዓላማዎች የቆፈሩትን ጉድጓድ መልሰው እንዲደፍኑ ያሳሰቡት
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ፤ ሁሉም ሃላፊነቱን በመወጣት አደጋውን መቀነስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡  





     በመጪው ጥቅምት የ70ኛ አመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ኢትዮጵያና የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በድርጅቱ መስራች አባልነት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክርና የበዓሉ አካል የሆነ ልዩ ፕሮግራም ማካሄዱን ታዲያስ መጽሄት ዘገበ፡፡
ኒውዮርክ ሲቲ ውስጥ በሚገኘው የተመድ ዋና ጽህፈት ቤት ከትናንት በስቲያ በተከናወነው በዚህ ልዩ ፕሮግራም ላይ አለማቀፍ እውቅና ያላቸው የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ጸሃፊያንና በተመድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ልኡክ ዶክተር ግርማ አበበ፤ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ በተመድ የነበራቸውን ሚና በተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልምና ንጉሱ እ.ኤ.አ በ1963 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በዋይት ሃውስና በሌሎች መድረኮች ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ለታዳሚው ቀርበዋል፡፡በተመድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ልኡክና የተመድ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ጉዳዮች ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ግርማ አበበ ባደረጉት ንግግር፤ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባዎች ላይ ያደረጓቸውን በሰላም፣ በጸጥታና በሰብዓዊ
መብቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ንግግሮችን ዳስሰዋል፡፡

“በካህናትና ሠራተኞች ስም የሚደረግ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም”

    በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት፣ ዘረፋ እና ምዝበራ ጥፋታቸው የተረጋገጠባቸው የአድባራት እና የሀገረ ስብከት ሙሰኛ ሓላፊዎች ለሕግ ተጠያቂነት ተላልፈው እንደሚሰጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ፓትርያርኩ ይህን የማረጋገጫ ቃል የተናገሩት፣ ስለ አድባራቱ የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመን በተካሔደው ጥናታዊ ሪፖርት ላይ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤ ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ ‹‹አድሏዊ እና ግለሰቦችን ለማጥቃት የተደረገ ነው›› በሚል በአንዳንድ አድባራት ተቃውሞ ማስነሣቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለፓትርያርኩ ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ የጥናታዊ ሪፖርቱን የመፍትሔ ሐሳቦች በሙሉ ድምፅ በመቀበል፣ የአድባራቱ ሓላፊዎች ጥፋት በሕግ አግባብ እንዲታይና ክሥ እንዲመሠረትባቸው ያሳለፈው ውሳኔም ሌላ አማራጭ
እንዲፈለግለት ፓትርያርኩን ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ ጥናቱ፣ ራሳቸው በሰጡት ትእዛዝ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ ባቋቋመው ኮሚቴ በይፋ መካሄዱን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ሪፖርቱን ለመቃወም በሚል ካህናትንና ልዩ ልዩ ሠራተኞችን በማደራጀት በጎን የሚቀርብላቸውን አቤቱታ እንደማይቀበሉት ለዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡‹‹ለማንም ሰው ከለላ መኾን አልፈልግም፤ ሽፋንም አልሰጥም፤ ለአንተም ጨምሮ፤›› በማለት አቋማቸውን ያረጋገጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ‹‹በዚኽ አጸያፊ የዘረፋና የምዝበራ ሥራ ውስጥ እጁ የተገኘበትን ሰው ኹሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሳልፋ ትሰጣለች፤ ይኼ የመጨረሻ አቋሜ ነው፤›› ሲሉ የሕግ ተጠያቂነቱ አይቀሬ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡በፓትርያርኩ ጠንካራ አቋም መደናገጥ ታይቶባቸዋል የተባሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በሀገረ ስብከቱ ተከማችተው ለቆዩትና በየአድባራቱ እየተባባሱ ለመጡት የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግሮች የአሠራር ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ በማስረዳት፣ ጥናታዊ ሪፖርቱን እንደሚቀበሉትና እንደሚደግፉት ለፓትርያርኩ እንደገለፀላቸው ታውቋል፡፡
ላለፉት ስድስት ወራት በ58 አድባራት ላይ ሲካሔድ የቆየው ጥናት፣ ከሓላፊዎቹ ጋር የጥቅም ትስስር ለፈጠሩ ግለሰቦች በሚያደሉ ውሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ መሬት፣ ሕንጻዎች፣ ሱቆች እና ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ላይ የተጧጧፈ ዘረፋና ምዝበራ መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረቷን ከብክነት ለመታደግ ያወጣችውን የቃለ ዐዋዲ ደንብ ማስከበር የሚገባው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፤ ከድንጋጌው ውጭ ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት የሕግ ጥሰቱ አካል እንጂ የሕግ አስፈጻሚ መኾን
አለመቻሉ የችግሩ ባለቤት እንደሚያደርገው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ከ400 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ተሣታፊዎች የሚካፈሉበትና ከ500ሺ በላይ ሰዎች ይጐበኙታል ተብሎ የሚጠበቀው “አበሻ አዲስ አመት ኤክስፖ 2008” ዛሬ ይከፈታል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት በእንግድነት ይገኙበታል በተባለው በዚህ የአዲስ አመት ኤክስፖ ላይ ከ100 በላይ የአገሪቱ ታላላቅ ድምፃውያንና ኮሜዲያን ሥራዎቻቸውን ለጐብኚዎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
ለሃያ አንድ ቀናት በሚቆየው በዚህ ኤክስፖ፤ የአለማችንን ትልቁ የሻማ ዛፍ የማብራት ሥነስርዓት እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡

Saturday, 15 August 2015 16:20

የየአገሩ ምሳሌያዊ አባባል

ከተጠበሰ እንቁላል ጫጩት ማስፈልፈል አትችልም፡፡
የደች አባባል
 መደነቅ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡
የግሪካውያን አባባል
እግዚአብሔር ምድር ላይ ቢኖር ኖሮ ሰዎች መስኮቱን ይሰብሩት ነበር፡፡
የአይሁዳውያን አባባል
ዝምታ ፈፅሞ ተፅፎ አያውቅም፡፡
የጣልያውያን አባባል
ፖለሪካ የበሰበሰ እንቁላል ነው፤ ከተሰበረ ይገማል።
የሩሳያውያን አባባል
ከተራመድክ መደነስ ትችላለህ፤ ከተናገርክ መዝፈን ትችላለህ፡፡
የዚምባቡዌ አባባል
እንደ ንፁህ ህሎሊና ለስላሳ ትራስ የለም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
ዝም ብለህ ተቀመጥ፤ ሰዎች እንደፈላስፋ ይቆጥሩሃል፡፡
የላቲን አባባል
የእግዚአብሔር እርሳስ ላጲስ የለውም፡፡
የሃይቲዎች አባባል
የማትናከስ ከሆነ ጥርስህን አታሳይ፡፡
የስፔናውያን አባባል
የጤናማነት መጀመሪያ በሽታውን ማወቅ ነው፡፡
የስፔናውያን አባባል
የስኳርን ጣዕም የምታደንቀው ሎሚን ስትቀምስ ብቻ ነው፡፡
የዩክሬናውያን አባባል
የቱንም ያህል ብትደክም ኮርማ ወተት አይሰጥህም፡፡
የዩክሬናውያን አባባል
ብቻውን የተጓዘ ያሻውን ማውራት ይችላል፡፡
የሩዋንዳውያን አባባል
ሚስትህን በአበባም እንኳ አትምታት፡፡
የሂንዱ አባባል
ማንም የራሱን አይብ ኮምጣጣ ነው አይልም፡፡
የአፍጋኒስታውያን አባባል
ሁሉም ሰው እንዲራመድብህ ከፈቀድክ ምንጣፍ ትሆናለህ፡፡
የቡልጋሪያውያን አባባል
የውሃውን ጥልቀት በሁለት እግሮቹ የሚለካ ጅል ብቻ ነው፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
መንገዶች ሁሉ ወደሮም አያደርሱም፡፡
የስሎቬንያውያን አባባል
ድልድዩን ከሰበርክ ዋና መቻልህን እርግጠኛ ሁን፡፡
የስዋሂሊ አባባል

Saturday, 15 August 2015 16:12

የኪነት ጥግ

(ስለ ራፕ ሙዚቃ)
አንዳንድ ጊዜ ዘረኝነትን ለማስቆም ቁልፉ ራፕ ሙዚቃ ይመስለኛል፡፡
ኤሚነም  
ሂፕ-ሆፕን መጀመሪያ ስሰማው እንቶ ፈንቶ መስሎኝ ነበር፤ ምክንያቱም ስለሰዎች በሙዚቃ የመነጋገር ፅንሰ ሀሳብ አልተረዳሁም ነበር፡፡
ኤኮን
መዝፈን በማይችሉ ሰዎች የተቀነቀነ መጥፎ ግጥም ነው፡፡ ይሄ ነው የእኔ የራፕ ብያኔ፡፡
ፒተር ስትሊ
የራፕ አማካይ ዕድሜ ሁለት ወይም ሦስት አልበሞች ነው፡፡ በራፕ ሙዚቃ ለሁለተኛ አልበምህ ከደረስክ ዕድለኛ ነህ፡፡
ጄይ - ዚ
በጣም ታዋቂ የራፕ ከያኒዎች ስለ ችስታነት ማቀንቀን የለባቸውም፡፡
ዳኒ ብራውን
በምንም ነገር እደንሳለሁ፡- በቦብማርሊም ሆነ በራፕ፡፡
ፍራንቼስካ አኒስ
ስለራፕ ስታወሩ፣ ራፕ የሂፕ-ሆፕ ባህል አካል መሆኑን መረዳት አለባችሁ፡፡
አፍሪካ ባምባታ
ወደ ራፕ ሙዚቃ መጀመሪያ ስገባ፣ ራፐሮችን የማስተሳሰር ቀዳሚ ህልም ነበረኝ፡፡
አይስ ቲ
ሰዎች እንደ አስተማሪ ሊመለከቱኝ ይችላሉ። እኔ ግን ራሴን እንደሂፕ - ሆፕ ተማሪ  ነው የምቆጥረው፡፡
ዲግ ኢ.ፍሬሽ
ራፕ የምትሰራው ነገር ሲሆን ሂፕ - ሆፕ የምትኖረው ነገር ነው፡፡
KRS - One
ሂፕ - ሆፕ የመጨረሻው እውነተኛ የሃገረሰብ ጥበብ ነው፡፡
ሞስ ዴፍ
ሂፕ - ሆፕ ተሰሚነት ለሌላቸው ድሃ ህዝቦች ድምፅ ነው፡፡
ራስል ሳይሞንስ

 በወርቅአፈራሁ አሰፋ የተዘጋጀው “ISIS ከሶሪያ እስከ አቢሲኒያ” የተሰኘ አዲስ መጽሃፍ ለንባብ መብቃቱን ደራሲው አስታወቀ፡፡ በመጽሃፉ ውስጥ ከተካተቱት አበይት ጉዳዮች መካከል  አይሲስና አርማጌዶን ፣የአይሲስ አፈጣጠርና የሲአይኤ አሻጥር፣ ኢትዮጵያ የአይሲስ ቀጣይ ዒላማ ትሆን?----የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የመጽሃፉ ማስታወሻነት በሊቢያ ትሪፖሊ፣ በስጋት ህይወት ውስጥ ለምትገኘው ታናሽ እህቱ መሠረት አሰፋና ያለሃጢያታቸው ለታረዱትና በእሳት ለተቃጠሉት የሰይጣናዊ ቡድኑ ሰለባዎች በሙሉ ይሁንልኝ ብሏል - ደራሲው፡፡
በ160 ገጾች የተቀነበበው መጽሃፉ፤በዴርቶጋዳ ማተሚያ ድርጅት ታትሞ በሊትማን መጻህፍት እየተከፋፈለ ሲሆን ዋጋው 46 ብር ከ65 ነው፡፡

 በቅርቡ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አዶት ሲኒማ፣ “ማጅራ” የተሰኘ አዲስ የህፃናት ቲያትር ነገ ከጠዋቱ 4 ሠዓት ለእይታ እንደሚያቀርብ ገለጸ፡፡ በሰለሞን መንግስቴ ተፅፎ በማስረሻ ገ/ማርያም የተዘጋጀው ይኸው ቲያትር፤በሲኒማ ቤቱ ፕሮዱዩስ እንደተደረገ ታውቋል፡፡
ሲኒማ ቤቱ በመደበኛነት የአገር ውስጥ ፊልሞችን ሲያሳይ የቆየ ሲሆን ባለፈው ወር “ከራስ በላይ እራስ” እና “እያዩ ፈንገስ” የተባሉ ሁለት የአዋቂ ትያትሮችን ማሳየት ጀምሯል፡፡ ከነገ ጀምሮ ደግሞ የህፃናት ቲያትር በየሳምንቱ እሁድ በ4 ሰዓት በመደበኛነት እንደሚያሳይ ተጠቁሟል፡