Administrator

Administrator

ከደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ወደ የሚገኘው የኦሊቨርታምቦ አየር ማረፊያ የደረስነው ባለፈው ሃሙስ 9 ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ በበደሌ ስፔሻል የጉዟችን ሙሉ ወጭ ተሸፍኖ የቻን ውድድርን ለመዘገብ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናነው ጋዜጠኞች ከላይ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ለብሻለሁ፡፡ ከውስጥ የለበስኩት ቲሸርት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ማልያ ነው፡፡ የመግቢያ ቪዛዬን የመረመረው የኢምግሬሽን መኮንን አለባበሴን ሲያይ ዝም ማለት አልቻለም፡፡ ለምን ማሊያ እንዳቀላቀልኩ ሲጠይቀኝ፤ የሁለቱም አገራት ደጋፊ ነኝ አልኩት፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ ማጣርያው ካልቀናትና ከተሰናበተች፤ በሁለተኛ ደረጃ የምደግፈው አገር ደቡብ አፍሪካ ነው አልኩት፡፡

የኢምግሬሽን መኮንኑ ፓስፖርቴን እየመረመረ ደቡብ አፍሪካ ናይጄርያን ካሸነፈች ለዋንጫ ትደርሳለች አለኝ፡፡ እኔም፤ ኢትዮጵያ በሁለተኛው ጨዋታዋ ኮንጎ ብራዛቪልን ካሸነፈች ከምድብ የማለፍ እድል ይኖራታል አልኩት፡፡ የመልካም እድል ምኞት ተለዋውጠን ተለያየን፡፡ የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ ወሳኝ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ትናንት እና ዛሬ ነበር የተደረጉት፡፡ ዋልያዎቹ በምድብ የመክፈቻ ጨዋታ በደረሰባቸው የ2ለ0 ሽንፈት ምክንያት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መከፈታቸውን ለመረዳት ብዙ አያስቸግርም፡፡ በዋና ከተማዋ ጆሃንስበርግ ውስጥ፣ ጄፒ ስትሪት አካባቢ የሚገኘው የጆበርግ መርካቶ ላይ ያጠላውን ድባብ መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በንግድ ስራ ተሰማርተው የሚንቀሳቀሱበት እና ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች በመምጣት እንደ መናሐርያ የሚገናኙበት የጆበርግ መርካቶ፤ ባለፈው ሃሙስ ከ10 ሰዓት በኋላ እንደልማዱ ጭር ሲል በአካባቢው ተዘዋውሬ የተመለከትኩት ሁኔታ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ባለሸንተረሩን፤ ወይንም ቢጫውን ካልሆነም አረንጓዴውን የዋልያዎቹ ማልያ የለበሰ ኢትዮጵያዊ እንደ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሰሞን አልነበረም፡፡ እንደውም በጆበርግ መርካቶ አካባቢ የሚታየው ከብሄራዊ ቡድን ጋር የተያያዘ ድባብ የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ርዝራዥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህን የዋልያዎቹ ማልያ በጆሃንስበርግ እስከ 140ራንድ መሸጡን ያሰታወሰው አንድ ነጋዴ ሰሞኑን በከተማዋ ለኢትዮጵያ እና ለደጋጋፊዎቿ ሲሸጥ የነበረው ማልያ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለገበያ ቀርቦ ከነበረው የተረፈ መሆኑን ይናገራል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በ2010 እኤአ ላይ በዚያው አገር በተካሄደው19ኛው ዓለም ዋንጫ ወቅት ለውድድሩ ትኩረት የነበረውን የቩቩዜላ ጥሩንባ በማምረት እና በመቸርቸር እንዲሁም በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ማልያ በመሸጥ ከፍተኛ ገበያ ነበራቸው፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ መሳተፏን በድምቀት ያከበሩት እነዚህ ኢትዮጵያውን፤ በወቅቱ የዋልያን ማልያ በደቡብ አፍሪካ ስታድዬሞች በተለይም ብሄራዊ ቡድኑ በተጫወተባቸው ሁለት ከተሞች ሩስተንበርግ እና ኔልስፕሪት እንዲሁም በመናሐሪያቸው ጆሃንስበርግ ከተማ በመቸብቸብ እና በመልበስ የማልያውን ተወዳጅነት ጨምረውታል፡፡ ይሄው በደቡብ አፍሪካ ተመርቶ እና ለገበያ የቀረበው የዋሊያዎቹ ማልያ፤ ወደ ኢትዮጵያ፤ ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ወደ አውሮፓ ተልኮም ከፍተኛ ገበያ እንዳገኘ ተገልጿል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሰኞ እለት ዋልያዎቹ ከሊቢያ አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ የገጠማቸው የ2ለ0 ሽንፈት ያበሳጫቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ሲገባ ያደረግነው አቀባበል ከአፍሪካ ዋንጫው በተለየ የደመቀ ነበር ያለው ብሩክ የተባለ ወጣት፤ ያን ጊዜ እንበላዋለን ብለን ጨፈርን፤ አሁን ለቻን ሲመጡ ደግሞ ሁላችንም እናስብ የነበረው በሊቢያ እንዲሸነፉ ሳይሆን ለዋንጫ እንዲደርሱ ነው ብሏል፡፡ ያነጋገርኳቸው የጆሃን ስበርግ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በቻን የመክፈቻ ጨዋታ ዋልያዎቹ የነበራቸውን ብቃት አንገት ያስደፋል ብለው ገልፀውታል፡፡ አንዱ ወጣት ነጋዴ እንደውም ቡድኑ ከሊቢያ ጋር ባደረገው ጨዋታ የነበረው ሁኔታ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን ያስመስለው ነበር ብሏል፡፡ ለሰላሣ አመታት ርቆን ስንመኘው ወደነበረው የአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ለመግባት መብቃታችን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ዋሊያዎቹ ለአህጉሪቱን የእግር ኳስ ዋንጫ ከሚፎካከሩ 16 ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን በመቻላቸው የህዝቡ ስሜት የቱን ያህል እንደተጠቀለለ አይተናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

ነገሩ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል አይደለም፡፡ በእንግድነት የረገጥነው አህጉራዊ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆንን ነው፡፡ አለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከ መጨረሻው ዙር በስኬት በመጓዝ ከአስሩ ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን ችለናል፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ በአህጉራዊው የቻን ውድድር ውስጥ ገብተናል፡፡ አሁን ተራ ነገር ቢመስልም ለብዙ አመታት ስንናፍቀው የነበረ ነው አህጉራዊው የእግር ኳስ መድረክ፡፡ ነገር ግን ባዕድ ሆኖብን በነበረው መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆንን ብንመጣም በቂ አይደለም፡፡ በአህጉራዊው መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ የመሆን ምኞታችን ገና አልተነካም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ባለፈው 2 ዓመት ውስጥ ካደረጋቸው ጨዋታዎች አንዱንም አላሸነፈም፡፡ ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 አቻ ከወጡ በኋላ ፤ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከዛምቢያ ጋር አንድ ለአንድ አቻ፤ በቡርኪናፋሶ 4ለ0 እና በናይጄርያ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሁለት ሽንፈት አስተናግደው ከውድድሩ ውጭ ሆነዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ ልምዱ ተነስቶ በቻን ውድድር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል የሚል ከፍተኛ እምነት ነበራቸው፡፡ - እስካሁን አልተሳካም እንጂ፡፡

በሊቢያው ጨዋታ አንዳንድ ደጋፊዎች አምበሉን ደጉ ደበበን ተበሳጭተውበት እንደነበር የገለፀው ታሪኩ የተባለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ፤ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የተጫዋቹን ወቅታዊ አቋም በመረዳት ማሰለፍ እንዳልነበረበት እና በሱ ምትክ ሳላዲን በርጌቾን በማጫወት በቡድኑ ላይ የደረሰውን ሽንፈት እና በተጨዋቹ ላይ ያለ አግባብ የተፈጠረውን ትችት መከላከል ይችል ነበር ብሏል፡፡ ብሩክ የተባለው ኢትዮጵያዊ የደቡብ አፍሪካ ነዋሪ በበኩሉ በጨዋታው ላይ አዳነ ግርማ ከፍተኛ ድካም የገጠመው ያለቦታው በመሰለፉ ነው የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሩክ፤ ከሜዳ ውጭ ረዳት አሰልጣኝ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት እንዲህ አድርግ እዚያ ጋር ሸፍን በሚል በሚያዥጐደጉዱበት ትዕዛዝም ያደክማል በማለት ወቅሷል፡፡ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከሃዘናቸው ባሻገር ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ወደፊት ብሄራዊ ቡድኑ በስብስቡ በወጣት ተጨዋቾች ተጠናክሮ ውጤት እንደሚያገኝ ስለሚያምኑ በደስታ መደገፋቸውን እንደማያቋርጡ ይገልጻሉ፡፡ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን እንደገለፁት የሊቢያውን ጨዋታ ለመመልከት ስራቸውን ትተው ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ወደ ፍሪስቴት ስታድዬም በመጓዝ ጨዋታውን የታደሙ ቢሆንም በዋልያዎቹ ያስመዘገቡት ውጤት አሳዝኖቸዋል፡፡ በምድብ 3 የተደለደሉት ዋልያዎቹ የመክፈቻ ጨዋታቸውን በፍሪ ስቴት ስቴድዬም ሲያደርጉ፤ ድጋፋችንን ለመስጠት እስከ 10 አውቶብስ ያህል ሆነን መጥተናል ብሏል - በደቡብ አፍሪካ አምስት አመት የሆነው ኢትዮጵያዊ በአጠቃላይ ለጨዋታው እስከ 8ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስታድዬም መግባታቸውን፤ የገለፀው ይሄው ኢትዮጵያዊ፤ የትኬት ዋጋ ከ50 እስከ 70 ራንድ መክፈላቸውን ተናግሯል፡፡ ከ100 እስከ 140 ብር ገደማ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ድጋፍ የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ሃይሎች ሳይቀሩ ተደስተዋል፡፡ የቻን ውድድር ድምቀት እናንተው ናችሁ በማለት የፀጥታ ጥበቃ ሃይሎች ኢትዮጵያውያን ሲያበረታቱ እንደነበሩና እንዳይ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው እና በነፃ ስታድዬምም እንዲገቡ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡድን በመሸነፉ የብዙዎቹ ስሜት ቢቀዘቅዝም ተስፋ ሳይቆርጡ ሁለተኛውን ጨዋታ ለመመልከት መጠባበቃቸው አልቀረም፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፍ መስጠታቸውም አያጠራጥርም፡፡ ዋልያዎቹ ኮንጎ ብራዛቪልን ማሸነፍ ከቻሉ ግን፤ የኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች ስሜት እንደገና ይሟሟቃሉ፡፡

ዋሊያዎቹ የፊታችን ሰኞ የምድባቸውን የመጨረሻ ጨዋታ ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ሲያደርጉ በርካታ ደጋፊዎች ስታድዬም እንደሚገቡም ይገመታል፡፡ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ የነበረውን ጉዞ በንቃት መከታተላቸውን የሚናገሩት ኢትዮጵያውያን፤ ዋልያዎቹ ደቡብ አፍሪካን በሜዳቸው ሁለት ለአንድ ባሸነፉበት ጊዜ በጆሃንስበርግ መርካቶ የነበረው ደስታ ወደር እንዳልነበረው ያስታውሳሉ፡፡ እዚህ በሰው አገር ከደስታችን ብዛት መንገድ ሁሉ ተዘግቶ በጭፈራ ደምቆ እንደነበር፤ ደቡብ አፍሪካውያኑን በማብሸቅ ከፍተኛ ድራማ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ታልፋለች በሚል ተስፋ ከናይጄርያ ጋር የተደረጉ የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን እንደተከታተሉ ገልፀው፤ ኢትዮጵያ በመጀመርያው ጨዋታ በሜዳዋ መሸነፏን ሲያዩ ማዘናቸውንና የካላባሩ ጨዋታ ብዙም እንዳልሳባቸው ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ እለት በጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኘው እና ኢስትጌት በተባለው የገበያ ማዕከል ስንዘዋወር ቆይተን አንድ የስፖርት ትጥቆች ሱቅ ውስጥ ገባን፡፡

የተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ማልያዎች እየተመለከትኩ በነበረበት ጊዜ ነው አረንጓዴ ቱታ የለበሱ ተጨዋቾች ወደሱቁ የገቡት፡፡ የኮንጎው ብራዛቪል ክለብ ኤሲ ሊዮፓርድስ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ አንዱን ወጣት ተጨዋች ንናግረው ስሞክር እኔ በእንግሊዝኛ እሱ በፈረንሳይኛ አልተግባባንም፡፡ በሬዲዮ የስፖርት 365 አዘጋጅና በኢንተርስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ዲያሬክተር ሁሴን አብዱልቀኒ ነው በፈረንሳይኛ ያግባባን፡፡ ኤሲ ሊዮፓርድስ በኮንጎ ብራዛቪል ትልቅ ክለብ እንደሆነ ወጣቱ ተጫዋች ገልፆ፤ በክለቡ የወጣቶች አካዳሚ ውስጥ እግር ኳስን ሰልጥኖ ዋናውን ቡድን በ21 ዓመቱ እንደተቀላቀለ ነገረኝ፡፡ ለኮንጎ ብሄራዊ ቡድን ባለመመረጡ ቢያዝንም፤ ውድድሩን በጉጉት እየተከታተለው ነው፡፡ ከምድብ 3 የሚያልፉት እነማን ይሆናሉ ተብሎ ሲጠየቅ በሰጠን መልስ፤ ኢትዮጵያ እና ሊቢያ ጠንካራ ቡድኖች በመሆናቸው ከጋና ይልቅ እንፈራቸዋለን ብሏል፡፡ የኤሲ ሊዮፓርድሱ ተጨዋች ለስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ መጫወት እንደሚፈልግ ሲነግረኝ፤ የሚያስደንቅ ህልም አለህ ብዬ እንደሚያሳካው በመመኘት ተሰናበትኩት፡፡

‹‹ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት የተረቀቀው ሕግ ወደ ኋላ አይመለስም፤ መሥመሩን አይለቅም›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመዋቅርና አሠራር ለውጥ በባለሞያ ያካሔደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት እንቃወማለን የሚሉ ውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች አይወክሉንም ሲሉ የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ልዩ ልዩ አገልጋዮችና ምእመናን ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡ ለዘመናት የቆየው የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና የሥራ ሒደት ከነበረው ተስፋፍቶ፣ የወቅቱን አሠራርና ሥልጣኔ የዋጀ ኾኖ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔና በፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በባለሞያዎች መዘጋጀቱንና ረቂቁ ወደ ታች ለግምገማ ወርዶ እንደተወያዩበት አስተዳዳሪዎቹና አገልጋዮቹ ጠቅሰዋል፡፡

የግምገማው ሪፖርት በሀ/ስብከቱ ተጠናቅሮ የሚቀርብለት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ሳይታወቅ በሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት ስም ‹‹በውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች›› በጥናቱ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞና በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ የሚሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ÷ ‹‹ከመሥመር የዘለለ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ አንድነትና ጥቅም እየደከሙ ያሉትን ብፁዓን አባቶች በመድፈር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰድቦ ለሰዳቢ አጋልጧታል፤›› ብለዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በአምስት ሺሕ የአስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ፊርማ አስደግፈው ማቅረባቸውን የገለጹት በመቶዎች የሚቆጠሩ እኒህ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች፣ ሀ/ስብከቱ እያካሔደው በሚገኘው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አቡነ እስጢፋኖስ ‹‹ወሳኝ አባት›› እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ውጭ በኾኑ፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና ጠባየ ብልሹነት ባለባቸው ውስን ሰዎች ሳቢያ ምእመኑ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዲያመራ እየተደረገ በመኾኑ ጉዳዩ አንገብጋቢ መኾኑን በመጠቆም፣ ‹‹በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ የሚደረግ የስም ማጥፋት ዘመቻና ሰድቦ ለሰዳቢ የመስጠት ሕገ ወጥ ተግባር›› መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከማስጠበቅ ጋራ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአባቶችን ክብር ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ የሚችል ጠበቅ ያለ ሕግ ማውጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡ የጥያቄ አቅራቢዎቹን አቤቱታ ያዳመጡት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ ኹሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመኾናቸው የኹሉንም ሐሳብ የመስማት ሓላፊነት ቢኖርባቸውም በተቃዋሚዎቹ በኩል የተሰማው ሕገ ወጥና ግብረ ገብነት የጎደለው ንግግር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰዋል፤ አኹን ደግሞ በተረጋጋ መንገድ ስለቀረበው የአስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ጥያቄ አመስግነዋል፡፡

በባለሞያዎች የቀረበው የሀ/ስብከቱ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቅ ወደኋላ የሚመለስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ፓትርያርኩ ገልጸው፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና፣ ለሃይማኖት መጽናት የሚጠቅመውን ሐሳብ ኹሉ ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የዘመኑ ምሁራን የተካተቱበት በቁጥር ከ9 - 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ረቂቁን ዳግመኛ እንዲያዩት መቋቋሙን ለጥያቄ አቅራቢዎቹ ያስታወቁት አቡነ ማትያስ፣ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲኖራት የተዘረጋው ሕግ ረቂቅ መሥመሩን እንደማይለቅ አረጋግጠውላቸዋል፡፡

በወጣት እና አንጋፋ ከያንያን እየቀረበ ያለው “ግጥም በጃዝ” 30ኛ ወርሐዊ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ በሚቀርበው ዝግጅት፤ አበባው መላኩ፣ ምንተስኖት ማሞ፣ ምስራቅ ተረፈ እና ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ግጥም፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወግ እንዲሁም መምህር እሸቱ አለማየሁ ዲስኩር የሚያቀርቡ ሲሆን የመግቢያ ዋጋው 50ብር ነው፡፡

ለአጭር ጊዜ ታምሞ ባለፈው ረቡዕ በተወለደ በ44 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አርቲስት ፈለቀ ጣሴ፤ከትላንት በስቲያ በደብረሊባኖስ ገዳም፣ ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት የቀብር ሥነሥርዓቱ ተፈፅሟል፡፡ በአዲስ ከተማ ት/ቤት ለመጀመርያ ጊዜ ከትያትር ጋር የተዋወቀው አርቲስት ፈለቀ፤ በኋላም የአርቲስት ተስፋዬ አበበ ትያትር ክበብን ተቀላቅሏል፡፡ አርቲስቱ በሀገር ፍቅር ትያትር - የጣር ሳቅ፣ የቀለጠው መንደር፣ ጥምዝ፣ የወፍ ጎጆ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ እንዲሁም በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ - ቀስተ ደመና፣ የክፉ ቀን ደራሽ፣ የደም ቀለበት፣ ማዶ ለማዶ፣ ፍለጋ፣ ጣይቱ፣ ምርጫው፣ ሶስና እና የታፈኑ ጩኸቶች በተባሉ ትያትሮች ላይ ተውኗል፡፡ ሰርፕራይዝ እና ጥቁር ነጥብ በተሰኙ ፊልሞችም ላይ መስራቱ ይታወቃል፡፡

በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማና አካባቢዋ የሥነጽሑፍ አፍቃሪያን የተቋቋመው “ሆራቡላ ሥነጽሑፍ ማሕበር” 20ኛ የስነጽሑፍ ዝግጅቱን የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 7፡30 በከተማው ሕይወት ሲኒማ ትንሿ አዳራሽ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ “የብዕር አዝመራ” በሚል ርእስ በሚቀርበው ዝግጅት፤ የማሕበሩ አባላት የግጥም፣ መነባንብ፣ ጭውውት እና ሌሎች ኪነጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዝነኛው የፊልም ተዋናይ ግሩም ኤርምያስ፤የህይወትና የሙያ ተመክሮውን ለማህበሩ አባላት እንደሚያካፍል ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ1940ዎቹ የተመሠረተው ጐንደር ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን የ60ኛ አመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ለአንድ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርስቲው ዘንድሮ ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በተጨማሪ በዓሉን ምክንያት በማድረግ 3ሺ የቀድሞ ተማሪዎችንም በድጋሚ ያስመርቃል ተብሏል፡፡ ዩኒቨርስቲው በማስገንባት ላይ ያለውን ሆስፒታልም በሰኔ ወር እንደሚያስመርቅ ታውቋል፡፡ በታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም በይፋ የተከፈተው የዩኒቨርስቲው ክብረ በአል የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡበት ሲሆን ክብረ በአሉ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡ ዩኒቨርስቲው ባካሄደው የ6 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር ላይ ከ2000 በላይ የተሳተፉ ሲሆን የሆቴልና ቱሪዝም ተማሪዎች ለቡርባክስ ህዝቦች መታሰቢያ ያደረጉትን የአዝማሪ ቅኝት አቅርበዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው ከመንግስት ጋር በመሆን በማስገንባት ላይ ያለው ባለ አንድ ሺ መኝታ ሪፈራል ሆስፒታል በሰኔ ወር እንደሚመረቅ ተነግሯል፡፡

The secret በተሰኘው የመጀመሪያ መጽሐፏ ከፍተኛ ዝናን የተቀዳጀችው አውስትራሊያዊ ደራሲ ርሆንዳ ባይርኔ The hero በሚል ያወጣችው ሦስተኛ መጽሐፏ “ጀግና” ተብሎ ወደ አማርኛ ተተረጐመ፡፡ መጽሐፉን የተረጐመው ብርሃኑ በላቸው ነው፡፡ “እያንዳንዳችን ወደዚህች ምድር የመጣነው በየራሳችን መንገድ ራሳችንንና ዓለምን የማበልጸግ ዓላማ ይዘን ነው” የሚለው መጽሐፉ፤ “አንተም ልዩ ነህና ለስኬት ተዘጋጅ” ይላል፡፡ 182 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ በ40.50 እየተሸጠ ነው፡፡

በገጣሚ ሲሳይ ታደሰ /ዘ-ለገሐሬ/ የተፃፉ የግጥም ስብስቦችን የያዘው ‹‹ለፍቅራችሁ›› የተሰኘ የግጥም መድብል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ 106 ግጥሞችን ያካተተው መድበሉ፤ “ለፍቅራችሁ” የሚል ርዕስ የተሰጠው መጽሐፉ ለህትመት እንዲበቃ ያገዙትን ሁሉ ለማመስገን እንደሆነ ገጣሚው ገልጿል፡፡ የግጥሙ መድበል ለአገር ውስጥ በ30 ብር፤ ለውጭ ደግሞ በ15 ዶላር ይሸጣል፡፡

በአስፋው መኮንን የተፃፈውና አስቂኝ፣ ቀልዶችና ቁምነገሮች የተካተቱበት መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በአገራችን በቃል የሚነገሩ በርካታ አዝናኝና ቁም ነገር አስተማሪ ቀልዶች ቢኖሩም ብዙዎቹ በመፃህፍት ተፅፈው ስለማይቀመጡ የሚረሱና የሚደበዝዙ ይሆናሉ፤ ስለዚህም መመዝገብ አለባቸው ብሏል አዘጋጁ፡፡ በ158 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

Saturday, 11 January 2014 12:11

“አለሁ ---- አልሞትኩም”

ረቡዕ ማታ በዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ላይ “አርቲስት ፈለቀ አበበ አረፈ” በሚል በስህተት በተነበበ ዜና እረፍት

ምክንያት አርቲስቱ፣ ቤተሰቦቹ፣ጓደኞቹና አድናቂዎቹ እስከ ሀሙስ እለት ተረብሸው ነበር፡፡ በርካቶች ዜናውን ባለማመን

ነገሩን ለማረጋገጥ አርቲስት ፈለቀ አበበ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ሲደውሉ ማምሸታቸውንና መዋላቸውን አርቲስቱ

ገልጿል፡፡ በስህተት ከተሰራጨው ዜና እረፍት በኋላ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ ስለተፈጠረበት ስሜትና አጠቃላይ

ሁኔታ ከጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር  አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

የሞትህን ዜና በምን ሁኔታ ሰማህ?
ረቡዕ ወደ ማታ ቤት ቁጭ ብዬ እየሰራሁ ሳለሁ፣ ባልተለመደ መልኩ ስልኮች በተከታታይ መደወል ጀመሩ፡፡ አስደንጋጭ

ነበር፡፡ ብቻ የሆነ ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡
ዜና እረፍትህን ሰምተው መደወላቸውን እንዴት አወቅህ?
አንዱን ጓደኛዬን በድፍረት ጠየቅሁት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፍጥነት በተከታታይ ሲደወል ለእኔ የተለመደ አይደለም፡፡

“ምንድን ነው ነገሩ? አካባቢው ላይ የተፈጠረ ነገር አለ እንዴ? ብዙ ሰው በተከታታይ እየደወለልኝ ነው” ብዬ

ስጠይቅ፤“አይ ሞተሀል ተብሎ በሬዲዮ ተነግሮ ነው” ሲለኝ ክው ብዬ ደነገጥኩኝ፡፡ ደግሞ ያስታውቃል፤ አንዳንዶቹ ልክ

ስልኬን አንስቼ “ሀሎ” ስላቸው ቶሎ ይዘጉታል። ብቻ መኖሬን ነው ማወቅ የሚፈልጉት፡፡ እንደዚህ ካደረጉት ውስጥ

ጓደኛዬ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ አንዱ ነው፡፡ አማኑኤል መሀሪ እንዲሁም ቤተሰቦቼም ድምፄን ሰምተው ብቻ ስልክ

ዘግተዋል፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤተሰቦቼም ይደወል ነበር፡፡ ከውጭ አገር ሁሉ የስልክ ጋጋታው ሊያቆም አልቻለም፡፡
ሲደውሉልህ የሰዎች ስሜት እንዴት ነበር?
በጣም ህመም የሆነብኝ እሱ ነው፤ በጣም የሚያለቅሱና ኡኡ የሚሉ ነበሩ (ለቅሶ…) በጣም ያሳዝናሉ፤ እኔም አብሬያቸው

አለቅስ ነበር (ረጅም ለቅሶ)…
ሬዲዮ ጣቢያው ጋ አልደወልክም ?
ትንሽ ቆይቶ--- ከዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ደወሉልኝ፡፡ “በስህተት ነው ፈለቀ አበበ ሞተ ያልነው፤ የሞተው ግን አርቲስት

ፈለቀ ጣሴ ነው፤ አንተ በጣም ታዋቂ ስለሆንክ ፈለቀ ስንል አፋችን ላይ የገባው የአንተ አባት ስም ነው” አሉኝ፡፡ ነገር

ግን ሰው በጣም ያለቅሳል፤ በጣም ያሳዝናል፡፡
ይቅርታ ጠየቁ ወይስ----
እኔን በግሌ ይቅርታ ጠይቀውኛል፡፡ አድማጮችን ይቅርታ ይጠይቁ አይጠይቁ አላውቅሁም፡፡ ነገር ግን በነገሩ በጣም

አዝኛለሁ፡፡ ማንም ከሞት አይቀርም ግን እንዲህ ቀላል የሚመስሉ ስህተቶች ከባድ ጉዳት ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ በድንጋጤ

ልቡ ቀጥ የሚል ቤተሰብ፤ ወዳጅ ዘመድ ይኖራል፤ መሞት አለ --- ስንት ነገር አለ፡፡
በዚህ ድንገተኛ ክስተት ምን ተረዳህ?
እንዴ… በጣም በጣም ተገረምኩ እንጂ! ይህን ያህል ሰው ይወደኛል ወይ ነው ያልኩት፡፡ በጣም ደነቀኝ፡፡
ዜና እረፍትህ ከተነገረ ጀምሮ ምን ያህል ሰው ደውሎልሀል?
ከ500 በላይ ስልክ ተደውሏል፤ በግምት ወደ 600 ሳይጠጋ አይቀርም፡፡
ከዚህ በስህተት ከተሰራጨ ዜና እረፍት መልካም አጋጣሚ የምትለው ነገር አለ?
 እንደውም በጣም እድለኛ ነኝ አልኩኝ፡፡ በቁሜ ይህን ያህል ሰው እንደሚወደኝ ማየት ችያለሁ፡፡ ግርምቴ እስካሁን

አልቆመም፡፡
ከዚህ በፊት ያልሞተ ሰው ሞተ ተብሎ የተነገረበትን አጋጣሚ ታውቅ ነበር?
ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹን የሰማኋቸው ዛሬ (ሐሙስ ማለቱ ነው) ነው፡፡ ለምሳሌ ጥላሁን ጉግሳ የሚባል

ሌላ አርቲስት ሲሞት፣ በስም መመሳሰል በህይወት ያለው ጥላሁን የመሰለበት አጋጣሚ  ትዝ ይለኛል፡፡ ሌላ ጊዜ

በቴሌቪዥን አርቲስት ሲራክ ታደሰ ሲሞት፣ የአርቲስት አለሙ ገ/አብን ፎቶ ማሳየታቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ያጋጥማል ነገር

ግን ሰው የሚያለቅሰው… መንገድ ላይ ሲያዩኝ የሚሆኑት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል፡፡
አሁን እንዴት ነው ስልኩ ቀነሰ? አንተስ ተረጋጋህ?
ያው እየተረጋጋሁ ነው፡፡ አንድ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፡፡ የህይወት እስትንፋስን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡

የምንኖረውም እግዚአብሔር የፈቀደልንን ያህል ነው፡፡ ማናችንም ከተቆረጠልን ቀን አናልፍም፡፡ ግን እዛው ቤቴ ውስጥ

ቁጭ ብዬ፤ “አሁንስ ለመኖሬ ምን ማረጋገጫ አለ” ብዬ መፈላሰፍ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ “ኦኬ በቃ አለሁ ማለት ነው…”

ማለት ጀመርኩኝ፡፡ አንዳንዶች እኮ “እርግጠኛ ነህ ፈለቀ ነህ የምታናግረኝ” ብለውኛል፡፡ ስለሞት ብዙ ነገር ነው

ያሰብኩት፡፡ ከምንወለድበት ቀን ይልቅ የሞት ቀን ይሻላል የሚለውንም አሰብኩኝ፡፡ እንደውም የአዲስ አድማስ ባለቤትና

መሥራች አሰፋ ጎሳዬ  ሲሞት አዲስ አድማስ ግቢ ሆኜ  የፃፍኩት ግጥም ነበር፡፡
ትዝ ይልሃል ---ምን የሚል ነው?
ቢርቅም አይጠፋም ይልቃል ከሽቶ
በሰው ልብ ይኖራል ከመቃብር ሸሽቶ፡፡   የሚል ነበር፡፡ አየሽ --- በዚህ አጋጣሚ ያየሁት የሰው ፍቅር፤ የበለጠ

የምሰራበትና መልካም ያልሆኑ ነገሮች ካሉኝም ለማሻሻልና ጥሩ ለማድረግ የምተጋበት ነገር ተፈጥሯል፡፡ የበለጠ መልካም

ሆኜ እንዳልፍ የሚያደርግ ጥሪም ነው፡፡ ደጋግሜ የምነግርሽ… ሰው ለእኔ የሆነው ነገር ገርሞኛል… እንዲህ ነው ወይ

የምትወዱኝ ነው ያልኩት፡፡
አንዳንዴ ሞት የሚያናድደው ከሞትክ በኋላ ሰው ለአንተ ያለውን ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ማየት ባለመቻሉ  ነው አይደለ?
እውነት ነው፡፡ እህቴም እንደዚህ ነው ያለችው፡፡ እህቴ ምስጢር ደምሴ ስትነግረኝ፤ መንግስቱ የተባለ ደራሲ “ሞቻለሁ”

ብሎ ቀጨኔ መድሀኒዓለም ሰው ተሰብስቦ ዋይ ዋይ ሲል፣ እሱ ተደብቆ ማን ቀብር እንደመጣና እንዳልመጣ፣ ማን ከልቡ

እንዳዘነና እንዳላዘነ ይመለከት ነበር፡፡ ይሄ ይገርማል። እሱ አስቦበትና ተዘጋጅቶ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው

ሌሎች በፈጠሩት ስህተት፣ የህዝቡን ፍቅር አይቼበታለሁ፡፡ እኔ ልሳቀቅ፣ እኔ ልደንግጥላቸው (ለቅሶ…)
የሞትህ ዜና ሲነገር ስራ ላይ እንደነበርክ ነግረኸኛል፡፡ ምን እየሰራህ ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱሱን ዮሐንስ ራዕይን በትረካ መልክ ለማቅረብ  እየተረጐምኩ ነበር፡፡ በመተርጐም ላይ ሳለሁ ነው ስልኩ

በተደጋጋሚ መደወል የጀመረው። ሀሙስ ጠዋት ከቤት ስወጣ ገርጂ አካባቢ “ዊሽ ስቱዲዮ” የሚባል ፎቶ ቤት አለ፤ ፎቶ

ሲያነሱኝ አየሁ፡፡
ለምን እንደሆነ አልጠየቅሃቸውም?
አልጠየቅኳቸውም፡፡ እነሱ ማታ ሞቷል መባሉን ሰምተው አድረው ኖሮ፣ ፎቶ ካነሱኝ በኋላ “Fele this morning”

ብለው ፌስ ቡክ ላይ ፖስት አድርገውኝ አየሁ፡፡ ሌላም ሰው “Still alive” ብሎ ፖስት አድርጓል --- እና የሚገርም

ነው፡፡
እና አሁን ምን ትላለህ?
አለሁ አልሞትኩም፤ ፈጣሪ እስከፈቀደልኝ እኖራለሁ፡፡ የሞተውን ወዳጃችንን ፈለቀ ጣሴንም ነፍሱን ይማርልን፡፡ ማርክ

ትዌይን  ያለውን እናስታውስና እንጨርስ፤ “ሞቴን በተመለከተ የወጣው ዘገባ ያለቅጥ  ተጋንኗል” እናም አልሞትኩም።

በዚህ አጋጣሚ አንዱ ጓደኛዬ መኪና እየነዳ “ፈለቀ አበበ ሞተ” ሲባል በድንጋጤ መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት

ከመስመር ወጥቶ ሊጋጭ ለትንሽ ነው የተረፈው፡፡ እህቴም ቀድማ አልሰማችም እንጂ በልብ ድካም ትሞት ነበር፡፡

ስለዚህ ጋዜጠኝነት ትልቅና የተከበረ ሞያ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊያዝና ሊከበር ይገባል እንጂ በቸልታ የሚሰራበት

አለመሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እኔም እወዳችኋለሁ፤ ስለተጨነቃችሁ

ስላዘናችሁልኝ አከብራችኋለሁ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡