Administrator

Administrator

 የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
ጋዜጠኛ መንግስቱ፤ የአዲስ አድማስ የንግድና ኢኮኖሚ አዘጋጅ በመሆን፣ ከ15 ዓመት በላይ በትጋትና በታታሪነት የሰራ ብርቱ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በጋዜጣው ላይ በሰራባቸው ዓመታት  ከ300 በላይ ታዋቂ የንግድ ሰዎችን የስኬት ታሪክ፣ ባማረ አቀራረብና በማራኪ ቋንቋ፣ ለአዲስ አድማስ አንባቢያን በማቅረብ፣ ሥራ ፈጣሪነትንና ኢንቨስትመንትን በማበረታት ረገድ ጉልህ አገራዊ ሚና ተጫውቷል፡፡ ጋዜጠኛው ለሙያውና ለሥራው ባለው ፍቅር፣  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ በህመም ላይ ሳለ ጭምር፣ ከሥራው አልተለየም ነበር፡፡
ጋዜጠኛ መንግስቱ፤ በአዲስ ዘመንና በዕለታዊ አዲስ ጋዜጦችም ላይ  ለበርካታ ዓመታት በጋዜጠኝነት ማገልገሉ ይታወቃል፡፡  
የጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ የቀብር ሥነ ሥርዓት በነገው ዕለት፣ ከቀኑ በ9 ሰዓት በቀጨኔ መድሃኒያለም ቤ/ክርስቲያን እንደሚከናወን ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍልና ማኔጅመንት፣ በጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ ዜና ዕረፍት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡
 ፈጣሪ  ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን፡፡     

Saturday, 23 November 2019 13:29

የእውነት ጥግ

• ሦስት ነገሮች ለረዥም ጊዜ ተደብቀው መቆየት አይችሉም፡- ፀሐይ፣ ጨረቃና እውነት፡፡
   ቡድሃ
• ጥበብ የምትገኘው በእውነት ውስጥ ብቻ ነው፡፡
   ጆሃን ዎልፍጋንግ ቮን ገተ
• በውሸት ከመፅናናት ይልቅ በእውነት መጎዳት ይሻላል፡፡
   ካሊድ ሆስኒ
• እውነት ብርቅዬ ከመሆኑ የተነሳ መናገሩ በእጅጉ ያረካል፡፡
   ኢሚሊ ዲከንሰን
• እውነት ምንም ነገር አያስወጣህም፤ ውሸት ግን ሁሉን ነገር ያሳጣሃል፡፡
   ኮትስ ጌት
• ጤናማ አዕምሮ እንዲኖርህ የምትሻ ከሆነ፣ አዕምሮህን እውነት መመገብ አለብህ፡፡
   ሪክ ዋረን
• የምትዋሸው ስትፈራ ብቻ ነው፡፡
   ጆን ጎቲ
• እውነቱን የምትናገር ከሆነ፣ ምንም ነገር ማስታወስ አይኖርብህም፡፡
   ማርክ ትዌይን
• ሁሉም እውነትን ይፈልጋል፤ ማንም ግን ሃቀኛ መሆን አይሻም፡፡
   አርኬጂ
• ሰዎች እውነትን መለወጥ አይችሉም፤ እውነት ግን ሰዎችን መለወጥ ይችላል፡፡
   ፒክቸር ኮትስ ዶት ኮም
• እውነት ይጎዳል፡፡ ውሸት ግን ሊገድል ይችላል፡፡
   ካሬን ሜሪ ሞኒንግ
• እውነት ጥቂት ወዳጆች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡
   ሁሴይን ኢብን አሊ
• እውነቱን ከሚናገር ሰው በላይ የሚጠላ የለም፡፡
   ፕሌቶ
• እውነት የማንም ሰው ንብረት አይደለም፤ የሁሉም ሃብት እንጂ፡፡
   ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
• በውሸት ከመሳም ይልቅ በእውነት በጥፊ መመታት ይሻላል፡፡

Saturday, 23 November 2019 13:28

የዘላለም ጥግ

 • ሰዎችን መጥላት፤ አይጥን ለማጥፋት የራስን ቤት እንደ ማቃጠል ነው፡፡
   ሔነሪ ኢመርሰን ፎስዲክ
• አንዳንድ ሰዎችን የምንጠላቸው ስለማናውቃቸው ነው፤ ወደፊትም አናውቃቸውም፤ ምክንያቱም እንጠላቸዋለንና፡፡
   ቻርለስ ካሌብ ኮልቶን
• ሌሎች ሊጠሉህ ይችላሉ። የሚጠሉህ ሰዎች የሚያሸንፉት ግን አንተም በተራህ ስትጠላቸው ነው፡፡
   ሪቻርድ ኒክሰን
• ጥላቻ የምናብ መጥፋት ነው፡፡
   ግራሃም ግሪኒ
• ጥላቻ የሲኦል ድባብ ነው፡፡
   ማርቲን ፋርኩሃር ቱፐር
• ጥላቻ ሁላችንንም አስቀያሚ ያደርገናል፡፡
   ሎውሬል ኬ.ሃሚልተን
• ጥላቻ፣ ዘረኝነትና አክራሪነት በዚህ አገር ውስጥ ቦታ የላቸውም፡፡
   አንጌላ መርኬል (የጀርመን ቻንስለር)
• ጥላቻ ፈፅሞ አያሸንፍም፡፡
   ስኩተር ብራዩን
• ጥላቻ ራስን በራስ መቅጣት ነው፡፡
   ሆሴ ባሎዩ
• ታሪክ ጥላቻ አይደለም፡፡
   ማልኮልም ኤክስ
• ጥላቻ መቼም ቢሆን በጥላቻ አይጠፋም፡፡ ጥላቻ የሚጠፋው በፍቅር ነው፡፡ ይሄ የማይለወጥ ሕግ ነው፡፡
   ቡድሃ
• እንዳለመታደል ሆኖ ዘረኝነት ድንበር የለውም፡፡ ልክ እንደ ጥላቻ፡፡
   አይሪስ ዋትስ
• ፈጣሪዬ፤ የሰላምህ መሳሪያ አድርገኝ፡፡ ጥላቻ ባለበት ፍቅር እንድዘራ ፍቀድልኝ::
   ፍራንሲስ ኦፍ አሲሲ
• ጥላቻ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ችግሮችን አምጥቷል፤እስካሁን ግን አንዱንም አልፈታም፡፡
   ማያ አንጄሎ
• እውነቱን ለመናገር፣ የሚጠሉኝን ሰዎች ለመጥላት ጊዜ የለኝም፤ ምክንያቱም  የሚወዱኝን ሰዎች በመውደድ ተጠምጃለሁ፡፡

Saturday, 23 November 2019 13:19

ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር

አሁን
አምስት
በአዳራሹ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ግትሩ ሎቂሬ አሁንም በማንገናኝበት መንገድ ላይ ቆሞ እየጠበቀን ነው፡፡ ሁናቴው በጣም አሰልቺ እየሆነ መጣ፡፡ ሎቂሬም ከኛ በላይ ተንገሽግሾ አረፈው፡፡
በጭንቀት ቁልጭ ቁልጭ ማለታቸውን ያላቋረጡ ዓይኖቹን እኛ ላይ እያንከራተተ “ንገሩኝ እኮ ነው የምላችሁ …እስከ መቼ ነው ትልቁንም ትንሹንም ነገር እኔ የማብራራላችሁ…?” የምትል ጥያቄ ወረወረወብን፡፡ “መቼ ነው ራሳችሁን ችላችሁ የስም ዓይጠሬውን ፕሬዝዳንታችንን ንግግር ለመረዳት እና ለማስረዳት የምትሞክሩት?... መቼ ነው እባክህ ሎቂሬ አብራራልን ከሚል ጥገኛ አስተሳሰብ የምትላቀቁት?...መቼ ነው የምትለወጡት?... እየተሽቀዳደማችሁ እኔም ላስረዳ…እኔም ላብራራ የምትሉት መቼ ነው?...” ሲል ደነፋ ሎቂሬ…
በ“መቼ ነው” ድንፋታው ብንን ያሉት እማማ ኩንዳሬም “መቼ ቢሆን ይሻላል?” ሲሉ አጉተመተሙ፡፡ በእንቅልፍ ጫና የተከደነ ዓይናቸውን ሳይገልጡ…
የኛ ሳቅ ሊገነፍል ደረሰ፡፡ የሎቂሬ ቁጣም እንደዚሁ ጨመረ፡፡
የግንባሩ ደም ስር ተገታተረ፡፡ የዕልህ ሳግም ይተናነቀው ጀመር፡፡ ካንጀቴ የገነፈለበትን እንባ ለመቆጣጠር እየሞከረ…
“በተለይ ወጣቶች ልብ ብላችሁ እንድትሰሙኝ እፈልጋለሁ፡፡ ስም አይጠሬው ፕሬዝዳንታችን እንደናንተ አልደላቸውም፡፡ የወጣትነት ዘመናቸውን ያሳለፉት ናይት ክለብ ሳይደንሱ…ፋሽን ሳይለብሱ…መጠጥ ሳይቀምሱ…ጫት ሳይቅሙ…ኮረዳ ሳይስሙ ነው፡፡”
ይህን ሲናገር ከከፍተኛ ሀዘን የመነጨ አንድ መንሰቅሰቅ ሰማሁ፤ መንሰቅሰቁን ተከትዬ ዘወር ስል ዋርሁም ፖፖን ተመለከትኩ፡፡ ይህን ለማመን ቢከብድም አፉን በመሀረብ ከልሎ በመንሰቅሰቅ ላይ የነበረው ራሱ ዋርሁም ነበር:: “ይሄ ትውልድ ከሀገሩ እና ከወገኑ ይልቅ ለፋሽን ለሴት፣ ለዳንስ፣ ለመጠጥ፣ ለጫት እና ለመሳሰሉት እርኩሰቶች ነው የሚጨነቀው” እያለ ሲያማርረን እንዳልኖረ ሁሉ---ይሄውና -- አሁን ስም አይጠሬው ፕሬዝዳንታችን በወጣትነታቸው ፋሽንና ሴት ባለማሳደዳቸው፣ ባለመደነሳቸው፣ ባለመጠጣታቸው እና ባለመቃማቸው ትልቅ ነገር እንደቀረባቸው የተረዳ መስሎ ሲያለቅስ ተመለከትኩ፡፡
ሌሎቹም ሆዳሞች ተከትለውት ከንፈራቸውን ይመጡ ጀመር፣ ሎቂሬም ይበልጥ በስሜት ገንፍሎ መናገሩን ቀጠለ፡፡ “አዎን…እንደናንተ ሴት ሳያማልሉ…ኳስ ሳይከታተሉ…ፒዛ ሳይበሉ…” አለና ዝም አለ፡፡
ዓይኖቹን ባዶው አየር ላይ አፍጥጦ ዝም አለ:: ሌሎቹም በ“ሉ” የሚያልቁ ቃላትን በመፈለግ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “ምነው ደህና ዋሉ…” ብሎ ይሄን ስብሰባ በገላገለን እያልኩ በማሰላሰል ላይ ሳለሁም “ነገር ግን እሳቸው በወጣትነት ነፃ መብታቸውን እንደናንተ ሳይጠቀሙበት…የተሟላ ቤታቸውን ሳይኖሩበት …የወጣትነት እድሜያቸውን ሀሩር እየጠበሳቸው …ቁር እያንዘፈዘፋቸው …የቀይ ጥቁር ሆነው …ከሰውነት ተራ ወጥተው ወጣትነታቸውን በየበረሃው የፈጁት እናንተ በምቾት እንድትኖሩ እና በነፃነት እንድትናገሩ ነበር፡፡
ይሄ ያሁኑ ዝምታችሁ በርሳቸው ተጋድሎ እና በጓደኞቻቸው መስዋእትነት በተገኘው የመናገር ነፃነት ላይ እንደማላገጥ ይቆጠራል” እያለ የ“መልስ ስጡኝ” ጥሪውን አጠናክሮ እና አክርሮ አዳራሹን ከሞሉት የመስሪያ ቤታች ሠራተኞች ላይ ዓይኑን ቢያንከራትትም እስካሁን ጥሪውን ተቀብሎ እጁን ያወጣ ሰው አልነበረም፡፡ ወደፊትም ለመንጠራራት ካልሆነ በቀር ብስጦን ለማብራራት ማንም እጁን እንደማያወጣ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
መሳሳቴን ያወቅኩት ሎቂሬ እጁን ወደ አንድ አቅጣጫ ወርወር አድርጐ “እሺ እዚያ ጋ” ሲል ነው፡፡ የሁላችሁንም ዓይኖች የሎቂሬ እጅ ወደተወረወረበት አቅጣጫ ተወረወሩ፡፡ ፍልጥ ፍልጥ ጥርሶቹን ከጢሙ መሀል ፍልጥጥ አድርጐ “አመሰግናለሁ የድካው ልጅ…” ሲል ሰማን፡፡ ከዚያም “ሁሉም ነገር የተጀመረው ቅዳሜ ምሽት ነው…” ሲል ጀመረ ጅባካ…
“ያው እንደሰማችሁት ቅዳሜ ምሽት ስም አይጠሬው ፕሬዚዳንታችን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አስደናቂ እና አነቃቂ የሆነ ታሪካዊ ቃል ተናግረዋል፡፡ ቃሉም --ብስጦሽቁዋጭቁዋጣሽ..ነው፡፡ በዚያ ምሽት ያንን እንግዳ ቃል በተናገሩበት ቅጽበት መጀመሪያ ፊቴ ድቅን ያላችሁት እናንተ ናችሁ፡፡
ለመሆኑ ስም አይጠሬነታቸው በዚያ እንግዳ ቃል በኩል ያስተላለፉት ሚስጥራዊ መልዕክት ምን ያህል ይገባቸው ይሆን ስል አሰብኩ” ብሎ እንደመመሰጥ አለ፡፡ ፍልጥ ፍልጥ ጥርሶቹን ፍልጥጥ አድርጐ…
እኔም እንደዚህ ያለ ግልጽ ኤረር ውስጥ ምን ዓይነት ሚስጥራዊ ፍቺ ሊያወጣ ይሆን እያልኩ…ያንንም ሚስጥራዊ ፍቺ ካሁኑ እየፈራሁ ጥርስ ጥርሱን በስጋት በመመልከት ላይ ሳለሁም “የዚህን እንግዳ ቃል ትርጉም ከብስጦ እጀምራለሁ” አለ፡፡
“ስም አይጠሬው ፕሬዚዳንታችን ብስጦ ሲሉ በአንድ በኩል በኛ ተጋድሎ የተደመሰሰው ወታደራዊ መንግስት ሩቅላዋን አከብራለሁ…ሙኢኛንም እናገራለሁ…ያሉትን ሁሉ እየረሸነ እና እየጨፈጨፈ ሚስቶችን ያለ ባል…ልጆችን ያለ አሳዳጊ…እና ወላጆችን ያለ ጧሪ ባስቀረበት አሰቃቂ ዘመን የነበረውን ንኩን ብስጦን ማስታወሳቸው ነው፡፡  
ምንጭ፡- (ከደራሲና ገጣሚ ታገል ሰይፉ “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር” የተሰኘ አዲስ ልብ ወለድ መጽሐፍ ላይ የተቀነጨበ፤ ጥቅምት 2012 ዓ.ም)


                 - ሊዞ በ8 ዘርፎች በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛለች
                  - ሚሼል ኦባማ ለሽልማት ታጭተዋል

           በአለማችን ታላቁ የሙዚቃ ሽልማት እንደሆነ የሚነገርለት የግራሚ ሽልማት የ2020 ዕጩዎች ዝርዝር፣ ባለፈው ረቡዕ ይፋ የተደረገ ሲሆን በስምንት ዘርፎች ዕጩ ሆና የቀረበችው ዝነኛዋ ድምጻዊት ሊዞ፣ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡
“ኮዝ አ ላቭ ዩ” በተሰኘው ተወዳጅ አልበሟ የአመቱ ምርጥ አልበምና የአመቱ ምርጥ ሙዚቃ ዘርፎችን ጨምሮ በድምሩ በስምንት ዘርፎች ከታጨችው የ31 አመቷ አሜሪካዊት ድምጻዊት ሊዞ በመቀጠል በብዛት የታጩት ሊል ናስ ኤክስ እና ቢሊ ኢሊሽ ሲሆኑ ሁለቱም በስድስት ዘርፎች ለሽልማት ታጭተዋል፡፡
በአምስት ዘርፎች ለሽልማት የታጨችው ሌላኛዋ ዝነኛ ድምጻዊት አርያና ግራንዴ፣ በብዛት በመታጨት የሶስተኛ ደረጃን በያዘችበት የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት፤ በአብዛኛው አዳዲስና ሴት ድምጻውያን በዕጩነት የቀረቡበት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለዘንድሮው የግራሚ ሽልማት በቀዳሚዎቹ አራት ዘርፎች በሙሉ የታጨችው የ17 አመቷ ድምጻዊት ቢሊ ኢሊሽ፤ በለጋ ዕድሜዋ ለግራሚ ሽልማት በመታጨት አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧ ታውቋል፡፡
የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በቅርቡ ለንባብ ባበቁት “ቢካሚንግ” የተሰኘ የግለ-ታሪክ መጽሐፋቸው የድምጽ ቅጂ “ዘ ቤስት ስፖክን ዎርድ አልበም” በሚለው ዘርፍ ለግራሚ መታጨታቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ባለቤታቸው ባራክ ኦባማም በዚሁ ዘርፍ ለሁለት ጊዜ የግራሚ አሸናፊ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡
ለ62ኛው የግራሚ ሽልማት በ84 የተለያዩ ዘርፎች በድምሩ ከ22 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች ቀርበው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በተከታታይ ዙሮች በተደረጉ ማጣሪያዎች የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች መመረጣቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
 በመጪው ጥር ወር መጨረሻ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ስቴፕልስ ሴንተር የሚከናወነውና በሲቢኤስ ቴሌቪዥን በቀጥታ የሚተላለፈውን የ2020 ግራሚ ሽልማት በመድረክ አጋፋሪነት የምትመራው ታዋቂዋ ድምጻዊት አሊሻ ኪስ እንደምትሆንም ተነግሯል፡፡

    በቅርቡ ስልጣን የያዙት የሲሪላንካው ፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃፓካሳ፣ ከትናንት በስቲያ ታላቅ ወንድማቸውን ማሂንዳ ራጃፓካሳን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ራኒል ዊክሬሚሴን ባለፈው ሐሙስ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ ፕሬዚዳንቱ በመዲናዋ ኮሎምቦ በተካሄደ ስነስርዓት፣ የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የ74 አመቱን ታላቅ ወንድማቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሃላ አስፈጽመው ወደ ስልጣን ማምጣታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሲሪላንካ ታሪክ ሁለት ዘመዳሞች ከፍተኛ ስልጣን ሲይዙ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቱ ወንድማቸውን መሾማቸው በአንዳንዶች ቢያስተቻቸውም፣ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ስልጣን እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ሹመቱ እምብዛም እንዳላስደነቃቸው የሚናገሩ መኖራቸውንም አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉት የ70 አመቱ ጎታባያ፣ ታላቅ ወንድማቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት ከ2005 እስከ 2015 በነበሩት አመታት የመከላከያ አማካሪ ሆነው ያገለግሉ እንደነበርና የ185 ሚሊዮን ብር የሙስና ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ወንድማቸውን በሾሙበት እለት ክሱ እንደተሰረዘላቸውም አክሎ ገልጧል፡፡  በቻይና ከአህዮች ቆዳ የሚሰራ መድሃኒት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ፣ በአሁኑ ወቅት በመላው አለም ከሚገኙ 45.8 ሚሊዮን አህዮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለዚሁ አገልግሎት ይታረዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
በቻይና ኢጃኦ ተብሎ የሚጠራውንና ከጉንፋን ጀምሮ የተለያዩ አይነት በሽታዎችን እንደሚያድንና እርጅናን እንደሚከላከል የተነገረለትን መድሃኒት ለማምረት በየአመቱ አምስት ሚሊዮን ያህል አህዮች እንደሚታረዱ የጠቆመው ዘገባው፤ የመድሃኒቱ ምርት ከ2013 እስከ 2016 በነበሩት አመታት ብቻ በ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
በቻይና ከ1992 አንስቶ በነበሩት አመታት የአህዮች ቁጥር በ76 በመቶ መቀነሱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህን ተከትሎም አገሪቱ ከሌሎች የደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካና እስያ አገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው አህዮችን ለመግዛት መገደዷንና በዚህም በአገራቱ ውስጥ ህገ ወጥ የአህዮች ንግድና እርድ ሊስፋፋ መቻሉን አመልክቷል፡፡
በቻይና እያደገ የመጣው የአህዮች ፍላጎት በሌሎች በርካታ አገራት የአህዮች ዝርፊያን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አህዮችን ለእርሻና ማጓጓዣ በመጠቀም ኑሯቸውን የሚገፉ በአለማችን የሚገኙ ከ500 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህልውናን አደጋ ላይ እንደጣለው ገልጧል፡፡
ቦትስዋና፣ ማሊና ሴኔጋልን የመሳሰሉ በርካታ የአለማችን አገራት፣ ህገ ወጥ የአህዮች ንግድና እርድን ለመከላከል ጥብቅ ህጎችንና መመሪያዎችን አውጥተው እየተገበሩ እንደሚገኙ ያመለከተው ዘገባው፤ ባለፉት 12 አመታት ገደማ የአህዮች ቁጥር በኪርጌዚስታን በ53 በመቶ፣ በብራዚል በ28 በመቶ፣ በቦትሱዋና በ37 በመቶ መቀነሱንም ጠቁሟል፡፡

  በሩዋንዳ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ መደበኛ የጽንሰት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ባልተለመደ ሁኔታ በ5 ወራቸው የተወለዱት መንትዮች፤ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በተረገዙ በ24 ሳምንታቸው በቅርቡ ኪጋሊ ውስጥ በሚገኘው ኪንግ ፈይሰል ሆስፒታል የተወለዱት እነዚሁ ሴትና ወንድ መንትዮች፣ ምንም እንኳን ሲወለዱ ክብደታቸው እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ ያለ አንዳች የጤና ችግር እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተወለዱበት ጊዜ ወንዱ 660 ግራም፣ ሴቷ 620 ግራም ክብደት እንደነበራቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ ትክክለኛው ክብደት ግን ከ2600 ግራም እስከ 4500 ግራም እንደሆነና በዚህ አነስተኛ ክብደት የተወለዱት መንትዮቹ በህይወት መቀጠላቸው እንዳስደነቃቸው የሆስፒታሉ ሃኪሞች በግርምት መናገራቸውን አመልክቷል፡፡ መንትዮቹ ያለ ጊዜያቸው ሊወለዱ የቻሉት እናታቸው ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት ስለተፈጠረባት መሆኑን የተናገሩት ሃኪሞቹ፤ ህጻናቱ ያለ ጊዜያቸው መወለዳቸው አስጊ በመሆኑ በልዩ ክፍል ክትትል ሲደረግላቸው እንደቆየና በአሁኑ ወቅትም በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መንትዮቹ ከተወለዱ ሶስት ወራት ያህል እንደሆናቸውና ወንዱ 2 ኪሎ ግራም ከ90 ግራም፣ ሴቷ አንድ ኪሎ ግራም ከ500 ግራም ክብደት እንዳላቸው፤ እድገታቸውም ጥሩ የሚባል እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

  ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ አዳኝ እጅግ ወርቃማ የሆነች አንዲት ወፍ ያጠምዳል፡፡
ወፊቱም፤
‹‹ከምታርደኝም ከምትገለኝም ሦስት ዋና ዋና ምክሮችን ልስጥህ - አለችው፡፡
‹‹እስቲ የመጀመሪያውን ልስማ›› አላት፡፡
አንደኛው፡- ‹‹የሰውን ንብረት አትመኝ››
ሁለተኛው፡- ‹‹የሰው ንብረት ተወሰደብኝ ብለህ አትቆጭ››
ሦስተኛ፡-  ‹‹ሁሉን ነገር በጊዜው ሥራው››
አለችው፡፡
የወፏን ምክር ያዳመጠው ይህ ወጣት፤ ሕይወቱ ተለወጠ፡፡
ቤት ሰራ፡፡
መኪና ገዛ፡፡
ልጅ ወለደ፡፡
የሚቀጥለው የሕይወቱ ግብ የቱ ጋ  ነው ያለው?
እሱንስ ለማትጋት ምን እናድርግ?
ዛሬም፤
‹‹ስንት እልፍ አበው ናቸው አርግዘው የሞቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ››
***
መቀናናትማ መች ሳይቀናን ኖረ? ይህን ታሪክ ሽረን መኖር ምን ቸገረ? ብለን መጠየቅስ ማን ምን ከለከለን? ማንስ እንዳንግባባ ገራን?
‹‹በምናውቀው ስንሰቃይ የማናውቀውንም ፈርተን፣ በህሊናችንም ማቅማማት ወኔያችንንም ባህላችንም ማቅማማት ወኔያችንንም ተሰልበን
የተራመድንበት ጉልበት የመንቀሳወስ አቅሙ እያደረ ከህሊናችን ይደመሰሳል
ትርጉሙ
‹‹እፍ አንቺ መብራት ጨልሚ
ጥፊ ጨልሚ ጨልሚ
አንቺ የብርሃን ጭላንጭል
    እኔ እፍ ብዬሽ ብትወድሚ
ጭሬ ላለማሽ እችላለሁ ከቶም እንዳሻኝ ነው ስሚ››
ብሏል አቴሎ አንበሳው
ብሏል ጥቁሩ ሙር ግስላ
ማሸነፍ ነበረበትና ስሜን ደቡብ
 ደጋ ቆላ
እስከ ዛሬ አገራችን ያለባትን የአገር እዳ፤
የሚቆጣጠረው ማነው?
  ስንትስ እንደሆነ እናውቃለን ወይ? ብንጠያየቅ ምን ይመስላችኋል? ወቅቱ ዛሬ ነው! ብለን እናስብ፡፡
ዝም ብንል ብናደባ… ዘመን ስንቱን አሸንፎን
የጅልነት እኮ አይደለም፣
  እንድንቻቻል ነው
ገብቶን!
***
አገራችን የወርቃማዋ ወፍ ፍቅርና ምክር ያሻታል፡፡ ሰዓቱ አሁን ነው - መላ መላችንን እንምታ፣ አካባቢያችን እናስላ! የወደፊት መንገዳችን ይሳካ ዘንድ በየትኛውም እግር - መንገድ እንጓዝ፡፡ የቀረችን ጉዞ አጭር ናት፡፡ እንደምንም  እንጓዛት!
‹‹ማሸነፋችን በጭራሽ አጠራጣሪ አይደለም!›› ብለው የሚያምኑ አያሌ ናቸው! ኳስ ሜዳው ግን የዕምነታቸው ከቶም አጋዥ አልነበረም! ለረዥም ጊዜ ሲዳክር የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን፤ ማንቺስተርና ሲቲን ተመልካች እንጂ የራሱን ሜዳ ወዳሽና ቀዳሽ ወይም አጣኝ መሆን አልቻለም::
ቢቀናን ሜዳችን ቢታጠን፣ ለተመልካቾቻችን ውዳሴና ሕዳሴ፣ መልክና ገጽታ መድመቂያ ይሆኑ በሆነ ነበር!
1ኛ/ የሰውን ንብረት ላለመሻት
2ኛ/ የሰው ንብረት የራስህ አልነበረምና ተወሰደብኝ ብለህ ላለመቆጨት
3ኛ/ ሁሉን ነገር በጊዜ መሥራት
እነዚህን ህግጋት ሊፈጽም ተፈጠመ!!
ሰው መሆን ያለበት ይሄንን ነው!  

         - በውጭ ሀገራት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ይኖሩታል
                - ፓርቲው “ብልፅግና” የተሰኘ ልሣን ይኖረዋል


           የኢህአዴግ ም/ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የብልጽግና ፓርቲ መመስረትን በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን የፓርቲው ፕሮግራም “መደመር” እንዲሆን ወስኗል፡፡
ሐሙስ ባካሄደው ስብሰባው የብልጽግና ፓርቲ ሊከተለው ባቀደው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ዝርዝር ውይይት መካሄዱ ታውቋል፡፡
ስምንት የገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የመሠረቱት ፓርቲ በ37 ገፆች 54 አንቀፆችን የያዘ መተዳደሪያ ደንብም አጽድቋል::
አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ውህደት ለማካሄድ የወሰኑት አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴን እንዲሁም የአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪና የሱማሌ ገዥ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ ኢህአዴግን የመሰረተው ህወኃት ከውህደቱ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡
በቀጣይ ውህደቱን የሚፈጽሙት ፓርቲዎች በየራሳቸው የውህደት መሸጋገሪያ ጉባዔ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ይህን የመሸጋገሪያ ጉባኤ በአስቸኳይ ለማከናወን ከወሰኑ ፓርቲዎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ተጠቃሽ ሲሆን ከነገ በስቲያ ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2012 የመሸጋገሪያ ጉባኤውን እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የመሸጋገሪያ ጉባኤያቸውን ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከፓርቲዎቹ የመሸጋገሪያ ጉባኤ በኋላም አዲሱ ውህድ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ውህደቱን ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለውህደቱ ሂደት ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡
የፓርቲ ውህደቱን በተመለከተ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “ውህደቱ የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ተሠሚነት ላልነበራቸው አጋር ድርጅቶች እኩል ድምጽ የሚሰጥ ህብረ ብሔራዊነትን የሚያፀና፣ አካታችነትንና ፍትሃዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሁነኛ አቅጣጫ ነው” ብለዋል፡፡ የፓርቲው ውህደት ሀገራዊ አንድነትን ከህብረ ብሔራዊነት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ሊቀ መንበሩ ጠቁመዋል፡፡
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ኢሕአዴግ መዋሃዱ ለአገሪቱ ብሔራዊ መግባባትና ሰላም እንዲሁም የተጠናከረ ፌዴራሊዝም ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢሕአዴግን ውህደት ከደገፉት መካከል ኢዜማ እና የአረና መሪዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ውህደቱ የፌደራል ሥርዓቱን ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
45 የህወኃት ተወካዮች ባልተገኙበት በተካሄደው የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባም የፓርቲው ፕሮግራምና ህገ ደንብ በጥልቀት ተገምግመው በሙሉ ድምፅ መጽደቃቸው ታውቋል፡፡
የፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም የመደመር እሣቤ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን ዝርዝር መተዳደሪያ ደንቡም በህግ ባለሙያዎችና ምሁራን ሰፊ ጥናት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ ላይ ፓርቲው ሊያሳካቸው ያለማቸው ግቦች የተቀመጡ ሲሆን  አዲስ ራዕይና አዲስ ሀገራዊ ትርክትን በመያዝ የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሠፈነባት፤ የግለሰብና የቡድን መብቶች በሚዛኑ የሚከበሩባት፣ የበለፀገች፣ ህብረ ብሔራዊ ማንነቷ የዳበረና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን የመገንባት አላማ እንዳለው አስቀምጧል፡፡
ፓርቲው ለሁሉም የሀገሪቱ ቋንቋዎች ሙሉ እውቅና እንደሚሰጥ ነገር ግን አሁን የፓርቲው የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ሱማሊኛ፣ ትግርኛና አፋርኛ የተመረጡ ሲሆን ክልሎችና የአካባቢ የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሣቢ በማድረግ ቢያንስ አንድ የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተጨማሪነት መጠቀም እንዳለባቸው በህገ ደንቡ ተደንግጓል፡፡
አዲሱ ፓርቲ “ብልጽግና” የተሰኘ የራሱ ልሣን የሚኖረው ሲሆን ልሣኑም በፓርቲው ሁሉም የስራ ቋንቋዎች ይዘጋጃል ይላል፡፡ የቀድሞ የኢህአዴግ ልሣን “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” እንደነበር ይታወሳል፡፡
የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት አዲስ አበባ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በየክልሎቹ ዋና ከተማዎች እንዲሁም በዞንና በወረዳ የሚኖሩ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በውጭ ሀገራትም እንደሚኖሩት ደንቡ ይደነግጋል፡፡
ማንኛውም ፍላጐቱ ያለው ግለሰብ የፓርቲው አባል መሆን እንደሚችል የሚደነግገው መተዳደሪያ ደንቡ፤ በህብረ ብሔራዊነትና በሀገራዊ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም ያለውና ዋልታ ረገጥ አመለካከትና ተግባሮችን በጽናት የሚታገል የሚለው ከመስፈርቶቹ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካል ሲሆን ፓርቲው በፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንት እንዲመራ እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ ስልጣን በጊዜ ገደብ እንዲገደብ ደንቡ ይደነግጋል፡፡ ዝርዝር መመሪያውም በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል፡፡
አዲሱ “ብልጽግና” ፓርቲን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሔራዊ ጉባኤ አድርጐ በምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግና በቀጣዩ ምርጫ ፓርቲው እንዲወዳደር መታቀዱም ታውቋል፡፡
ከዚህ ውህደት ራስን ያገለለው ህወኃት፤ ከዚህ በኋላ በምን መልኩ እንደሚጓዝ እስካሁን የጠቆመው ነገር የሌለ ሲሆን፤ የኢህአዴግም ሆነ አጋር ድርጅቶች አመራሮችም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡     

Page 11 of 464