Administrator

Administrator

 ኩባንያችን መንግስት የገቢ ምርትን ለመተካት በሰጠው ትኩረት መሰረት፤ በአገሪቱ ቀዳሚውን የአልሙኒየም ማምረቻ ፋብሪካ በመገንባት ከ600 በላይ ለሚሆኑ ቋሚና ለበርካታ ሰራተኞች የስራ እድል በመፍጠር፣ የተለያዩ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የአልሙኒየም ተረፈ ምርቶች መልሶ በማቅለጥ ጥራታቸውን የጠበቁ የአልሙኒየም ፕሮፋይሎች በማምረት፣ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በማቅረብ የገቢ ምርትን በመተካት ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ያለ ሀገር በቀል ተቋም ነው፡፡
ሆኖም ጋዜጣችሁ የካቲት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው እትም፤ ለ40/60 ቤቶች አልሙኒየም አቅርቦት የወጣው ጨረታ ቅሬታ እንዳስነሳ ባወጣው ዘገባ ላይ “የጨረታው መስፈርት አንድን ድርጅት ታሳቢ ያደረገ ነው” የሚለው ሀሰተኛ መሆኑን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡
በዘገባው ላይ አንድን ድርጅት ታሳቢ ያደረገ ነው የሚል ስም ባይጠቅስም ጉዳዩ ቀጥታ ኩባንያችንን “B&C Aluminum PLC” ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፣
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አንድን ድርጅት የወገነና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያላገናዘበና በአጠቃላይ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ ነው፤ ጨረታው የአልሙኒየም ከምችትና ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርብ መጠየቁ የተጠቀሰው ሀሰት መሆኑን እየገለፅን፤ የጨረታ ሰነዱ ላይ የተዘጋጀው መስፈርት ለማናቸውም በአልሙኒየም ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶች የሚሆንና ሁሉም ድርጅቶች የአልሙኒየም ናሙና ለፍተሻ ለኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በማስገባት ደረሰኙን ብቻ ለአማራጩ ድርጅት እንዲያስገቡ ተጠይቋል፡፡ የውጪ ምንዛሬን በተመለከተ የጨረታ ሰነዱ ላይ የተገለፀ ነገር ባይኖርም፣ ኩባንያችን በሀገር ውስጥ በሚያመርተው ምርት አማካኝነት የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል የበኩሉን ሚና መጫወቱ ከሚያስመሰግነው በቀር የቅሬታ ነጥብ ሊሆን አይገባም፤
“ታሳቢ የተደረገው ድርጅት ከውጪ በሚመጣ አልሙኒየም ተረፈ ምርት ሪሳይክል እያደረገ የሚያመርት ነው” ተብሎ የተገለፀው ሀሰተኛ መሆኑን እየገለፅን ኩባንያችን ምርቱን የሚያመርተው የተለያዩ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የአልሙኒየም ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም እንደሆነ እንጠቁማለን፣
ከአምስት አመታት በፊት በክራውን እና በሰንጋ ተራ ለተገነቡ ቤቶች ተመሳሳይ የ1 ቢሊየን ብር ጨረታ መውጣቱንና ይኸው የተባለው ድርጅት አሸንፎ በጊዜው እንዳላጠናቀቀ ተገልጿል፡፡ ኩባንያችን በወቅቱ ከጨረታ እንዲወጣ የተደረገበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን ሆኖም ለፌደራል የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ በራሳችን ትግል በጨረታው ተሳትፈን ያገኘነው ፕሮጀክት ሲሆን የተጠቀሰው የገንዘብ መጠንም በፍፁም ከእውነት የራቀና ኩባንያችንም ስራውን እንዳላዘገየ እንገልፃለን፣
ቅሬታ አነሱ የተባሉ ግለሰቦች አንድ ጠንካራ የሚባል ድርጅት በቀን ከ30 ካ.ሜ በላይ መስራት እንደማይችል የተገለፀው በፍፁም ስህተትና የአፈፃፀም መጠን በኩባንያው የስራ ልምድ፤ የሰው ሀይል፤ የአመራር ብቃት፤ የማሽነሪዎች መኖርና በተለያዩ ነገሮች የሚወሰን ይሆናል፣
እንደሚታወቀው፤ የጨረታ ዋጋቸው የሚታወቁ የቴክኒካል ሰነድ ተገምግሞ ካበቃ በኋላ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ የጨረታ ሂደት ገና የቴክኒክ ግምገማው ያልተጠናቀቀ ስለሆነ ቅሬታ አቀረቡ የተባሉት ሰዎች የጠቀሱት የገንዘብ መጠን በተራ ግምት ላይ የተመሰረተ እንጂ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም፣
በአጠቃላይ ኩባንያችን ህግን ተከትሎ የገቢ ምርትን ለመተካት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ያለ ተቋምና ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪን በማዳን ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ ተቋም ሲሆን ከላይ የተዘረዘሩት ሙሉ በሙሉ የኩባንያችንን ስም የማጥፋት ዘመቻ መሆኑን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡
ከ B&C Aluminum PLC

በደቡብ ኮርያ በኮከብ ቆጠራና በጥንቆላ ተግባር ላይ የተሰማሩና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ ያስነበበው ኒውስዊክ፤ ከአጉል ልማዶቹ ጋር በተያያዘ በየአመቱ የሚንቀሳቀሰው አጠቃላይ ገንዘብ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
በደቡብ ኮርያ በየአደባባዩና በየቤቱ ጧት ማታ፣ የኮከብ ቆጠራና የጥንቆላ ተግባር የሚያከናውኑ ሰዎች እየተበራከቱ ነው ያለው ኒውስዊክ፤ የኮርያ ነቢያት ማህበርም በአገሪቱ ከ300 ሺ በላይ ኮከብ ቆጣሪዎችና 150 ሺ ገደማ ጠንቋዮች እንዳሉ መገመቱን ጠቅሷል፡፡ በመጫወቻ ካርዶች የሚከናወኑ የኮከብ ቆጠራና የእለት ዕጣ ፋንታ ትንቢቶች፣ በአገሪቱ ለረጅም አመታት የተለመዱ ድርጊቶች እንደሆኑ ያስታወሰው ዘገባው፤ አሁን አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዙ የሞባይል አፕሊኬሽን ጥንቆላዎችና ኮከብ ቆጠራዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጧል፡፡
ሃንዳሶፍት የተሰኘው ታዋቂ የአገሪቱ ሶፍትዌር አምራች ኩባንያ፣ ባለፉት አምስት አመታት ብቻ 13 ያህል የጥንቆላና የዕለት ውሎ ትንበያ ሶፍትዌሮችን አምርቶ በገበያ ላይ ማዋሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ ጂኦምሲን የተባለውና ከ2 አመታት በፊት ገበያ ላይ የዋለው ተወዳጅ የውሎ ትንበያ የሞባይል አፕሊኬሽን ሶፍትዌር፣ከ3 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ዳውንሎድ መደረጉን አውስቷል፡፡
ኮርያ ኢኮኖሚክ ደይሊ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ባለፈው አመት ያወጣው መረጃ በበኩሉ፤የአገሪቱ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው ኮከብ በማስቆጠርና በማስጠንቆል፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በከንቱ በማባከን ላይ እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ ኮርያን ኪዩንግሲን ፌዴሬሽንና የጥንቆላ ማህበር የተባሉት ሁለት የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራት ብቻ በድምሩ አንድ ሚሊዮን ያህል አባላት እንዳሏቸው አመልክቷል፡፡ በማህበር የታቀፉ አስጠንቋዮች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት በእጥፍ ማደጉንም ጋዜጣው አክሎ ገልጧል፡፡

በኬንያ ባለፈው ነሐሴ ወር ተግባራዊ የተደረገውንና ፌስታሎችን ጨምሮ ፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀምን የሚከለክለውን ህግ በመጣስ፣ ፌስታል ሲሸጡ ተገኝተዋል የተባሉ 19 ኬንያውያን፣ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ግብረሃይል ኪሲ፣ ኬሮካና ኔማ በተባሉት ከተሞች ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ምሽት ላይ ባደረገው ፍተሻ በቁጥጥር ስር የዋሉት 19 ኬንያውያን፣ ከሰሞኑ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኬንያው ኔሽን ዘግቧል፡፡ አገሪቱ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በማሰብ ተግባራዊ ያደረገቺውንና  የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረት፣ መሸጥና መጠቀምን የሚከለክለውን ህግ ጥሰው የተገኙ ዜጎች፤ በ4 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም በአራት አመታት እስር እንደሚቀጡ መደንገጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ኬንያውያን ከፕላስቲክ ከረጢቶች ይልቅ ወረቀትና ጨርቅን ከመሳሰሉ በቀላሉ የሚበሰብሱና አካባቢን የማይበክሉ ነገሮች የተሰሩ ከረጢቶችንና ቦርሳዎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ተወካይ፤መንግስት የተከለከሉ ከረጢቶችን ሲጠቀሙና ሲሸጡ የሚገኙ ህገወጥ ዜጎችን ቅንጣት ታህል እንደማይታገስና በቁጥጥር ስር አውሎ እንደሚቀጣ አስጠንቅቀዋል፡፡

ታላላቆቹ የአለማችን ኩባንያዎች የጀርመኑ ቮዳፎን፣ ኖኪያና አውዲ በመጪው አመት በጨረቃ ላይ ፈጣን የ4ጂ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ለመዘርጋት የሚያስችላቸውን ፈር-ቀዳጅ ፕሮጀክት በጋራ ስኬታማ ለማድረግ መነሳታቸውን ባለፈው ማክሰኞ አስታውቀዋል፡፡
የሰው ልጅ ወደ ጨረቃ በመጓዝ ድንቅ ታሪክ ከሰራ 50 አመታት ያህል መቆጠራቸውን ያስታወሰው ሮይተርስ፤ እነሆ አሁን ደግሞ የዘመናችን ሳይንቲስቶች፣ የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን ከምድር አልፈው ወደ ጨረቃ በማድረስ፣ ሌላ ታሪክ ሊሰሩ ነው ሲል ዘግቧል፡፡
ኩባንያዎቹ ተቀማጭነቱ በበርሊን ከሆነው ፒቲሳይንቲስትስ ከተባለው ኩባንያ ጋር በመተባበር በጨረቃ ላይ ሊዘረጉት ያቀዱትና በአይነቱ አዲስ የሆነው የሞባይል ስልክ ኔትወርክ፤ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የቪዲዮና የድምጽ መረጃዎችን በጨረቃና በመሬት መካከል ለመላላክ ያስችላል ተብሏል፡፡

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ እየተጠቀሙበት የሚገኘውን ኤርፎርስ ዋን የተሰኘ ልዩ ፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላን የሚተኩ 2 እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን፣ በ3.9 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት፣ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ባደረጉት ድርድር መስማማታቸው ተዘግቧል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ እጅግ ዘመናዊ እንደሆኑ የተነገረላቸውን ሁለት ቦይንግ 747 - 8 አውሮፕላኖች፣ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሸጥ ከዓመታት በፊት ለዋይትሃውስ ዋጋ አቅርቦ እንደነበር ያስታወሰው ኤንፒአር የዜና ወኪል፤ በቢዝነስ ድርድር የላቀ ችሎታ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ትራምፕ ግን ተደራድረው፣በ3.9 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት መስማማታቸውን የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ሆጋን ጌሊ፣ ባለፈው ረቡዕ እንዳስታወቁ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ በዋጋ ድርድር ብቃታቸው ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማዳናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ቦይንግ ኩባንያ አውሮፕላኖቹን ለዋይትሃውስ የሚያስረክብበት ትክክለኛ ጊዜ አለመታወቁን አመልክቷል፡፡
እጅግ የረቀቁ የደህንነት መሳሪያዎች የተተከሉላቸው እነዚህ እጅግ ዘመናዊ የቦይንግ አውሮፕላኖች፤ የሽብር ጥቃቶችን በብቃት የመመከት ችሎታ እንዳላቸውና የኒውክሌር ጦርነትን ጨምሮ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ያለ አንዳች ችግር ረጅም ርቀት መብረር እንደሚችሉ ገልጧል፡፡
ትራምፕ እና ቦይንግ ኩባንያ 1ሺህ ማይል ርቀት የመብረር አቅም እንዳላቸው የተነገረላቸውን አዲሶቹን ቦይንግ 747 - 8 አውሮፕላኖች፣ በተጠቀሰው ዋጋ ለመገበያየት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን በቀጣይም ህጋዊ የግዢ ውል ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

 ሰሜን ኮርያ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ400 በላይ ዜጎቿ በክሎሪን ጋዝ ጥቃት ለሞት ለተዳረጉባትና በእርስበርስ ጦርነት አሰቃቂ ውድመት እያስተናገደች ለምትገኘው ሶርያ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት 40 ጊዜያት ያህል፣ ለኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ምርት በጥሬ እቃነት የሚውሉ ቁሳቁሶችን መሸጧን ተመድ አስታውቋል፡፡
ሰሜን ኮርያ እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2017 በነበሩት ዓመታት፣ አለማቀፍ ማዕቀቦችን በመጣስ፣ ለኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ምርት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ሶርያ መላኳንና የአገሪቱ የሚሳኤል ባለሙያዎችም፣ በሶርያ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ማዕከላት ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ ማግኘቱን፣ተመድ ባወጣው መረጃ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሶርያ ከሰሜን ኮርያ ለገዛቻቸው ለእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች፣ “ሳይንቲፊክ ስተዲስ ኤንድ ሪሰርች ሴንተር” የተባለው የሶርያ መንግስት ተቋም፣ በሌሎች ኩባንያዎች ስም ክፍያ መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ያለው ተመድ፤ተቋሙ የተመሰረተው ለምርምር ቢሆንም በሶስት ማዕከላት ውስጥ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ሲያመርት እንደነበር መረጋገጡንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ኢንፌክሽን፣ የወሊድ ችግሮችና ካለወቅቱ መወለድን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በአለማችን በየአመቱ 2.6 ሚሊዮን ያህል ህጻናት በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚሞቱ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
በፈረንጆች 2016 በአለማችን አገራት የተከሰቱ መሰል የህጻናት ሞት ክስተቶችን በማጥናት የአገራቱን የችግሩ ተጠቂነት ደረጃ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ያወጣው ድርጅቱ፤ በከፋ ደረጃ ላይ በመገኘት ቀዳሚ በሆነቺው ፓኪስታን በአመቱ ከተወለዱ ህጻናት በአማካይ ከ22ቱ አንዱ ዕድሜው አንድ ወር ሳይሞላው መሞቱን አመልክቷል፡፡
ከጃፓን በመቀጠል በርካታ ህጻናት በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚሞቱባቸው የአለማችን አገራት ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና አፍጋኒስታን ሲሆኑ ሶማሊያ፣ ሌሴቶ፣ ጊኒቢሳኦ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኮትዲቯር፣ ማሊና ቻድ በቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከአለማችን አገራት ለመሰል ችግር በመጋለጥ የመጨረሻውን ደረጃ በያዘቺው ጃፓን፣ በአመቱ ከተወለዱ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 111 ጨቅላዎች በአማካይ አንዱ ብቻ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ከጃፓን በመቀጠል አይስላንድና ሲንጋፖር ዝቅተኛ የህጻናት ሞት ያለባቸው የአለማችን አገራት እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡
በቀዳሚዋ ፓኪስታንና በመጨረሻዋ ጃፓን መካከል ያለውን የችግሩ ተጠቂነት ደረጃ ያነጻጸረው ሪፖርቱ፤ በፓኪስታን የሚወለድ አንድ ህጻን በጃፓን ከሚወለድ ሌላ ህጻናት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ወር እድሜውን ሳይሞላ ለህልፈተ ህይወት የመዳረግ እድሉ በ50 እጥፍ ያህል የጨመረ እንደሆነ አብራርቷል፡፡

 የአፍሪካ አገራት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የነዳጅ ዝርፊያ፣ የአደንዛዥ እጽ ንግድና ኮንትሮባንድን በመሳሰሉ ተግባራት በሚፈጸሙ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሮች በየዓመቱ በድምሩ 50 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያጡ ተዘገበ፡፡
ተቀማጭነቱ በፓሪስ የሆነው አለማቀፉ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ተቋም ከሰሞኑ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ከሚከናወነው ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር 80 በመቶውን የሚይዘው ከተፈጥሮ ሃብት በተለይ ደግሞ ከነዳጅ ዝርፊያ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
በአፍሪካ አገራት በህገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ መሆኑ የአገራቱን ልማት እንዳይፋጠን ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፤በአውሮፓ አገራትም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስ አመልክቷል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተመርቆ የወጣውና አፍሪካዊ ፊልም ባህር የመሻገር ብቃት የለውም የሚለውን አመለካከት እንዳከሸፈ የተነገረለት “ብላክ ፓንተር” ፊልም፣ ገና ለእይታ በበቃ በአራት ቀናት ውስጥ ብቻ 241.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በዚህ ገቢውም ከ”ስታር ዎርስ” ቀጥሎ በመቀመጥ ታሪክ ሰርቷል፡፡
ወንጀልን ለመታገል ቆርጦ በተነሳ የአንዲት ምናባዊ የመካከለኛው አፍሪካ አገር መሪ የስኬት ጉዞ ላይ የሚያጠነጥነውና በጥቁሩ ዳይሬክተር ሪያን ኮግለር የተሰራው “ብላክ ፓንተር”፤ ለእይታ በበቃ በቀናት እድሜ ውስጥ በርካታ የቦክስ ኦፊስ ክብረ-ወሰኖችን መሰባበሩን ተያይዞታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ በትዊተር ማህበራዊ ድረገጽ ከ5 ሚሊዮን በላይ ፊልሙን የተመለከቱ ጽሁፎችና መልዕክቶች የተሰራጩለት ፊልሙ፤ በአለማችን ታሪክ በትዊተር እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጠቃሚዎችን  ያነጋገረ ቀዳሚው ፊልም ሆኗል፡፡
ፊልሙ ከአሜሪካ የቦክስ ኦፊስ የደረጃ ሰንጠረዥ በተጨማሪ በእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጃፓንና ሌሎች በርካታ የአለማችን አገራት የፊልሞች ገበያና የገቢ የደረጃ ሰንጠረዦች የሚደንቅ ክብረ ወሰን እየጨበጠ እንደሚገኝ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ በሆሊውድ መንደር ባልተለመደ ሁኔታ አፍሪካውያንን ባለስኬት ጀግኖች አድርጎ የሚያሳየው ይህ ፊልም፣ የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት አመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ አለማቀፍ ዝነኞች በአደባባይ አድናቆታቸውን እየቸሩት ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“ብላክ ፓንተር” 200 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ በታሪክ ከፍተኛው በጀት የተመደበለት በጥቁር ጀግኖች ዙሪያ የሚያጠነጥንና በአብዛኛው ጥቁር የፊልም ባለሙያዎችን ያሳተፈ ቀዳሚው ፊልም እንደሆነ አመልክቷል፡፡

 ለረጅም ዓመታት ልደታቸውን በብሄራዊ በዓልነት እጅግ በደመቀ ሁኔታ ከህዝባቸው ጋር በአደባባይ ሲያከብሩ የኖሩት የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ ባለፈው ረቡዕም የ94ኛ አመት ልደታቸውን ከወትሮው በፈዘዘ መልኩ እንደነገሩ አክብረዋል፡፡
ሙጋቤ ምንም አንኳን ስልጣን ከለቀቁ ወራትን ቢያስቆጥሩም፣ የልደት በዓላቸው ግን የዚምባቡዌ ወጣቶች ቀን በሚል ስያሜ በብሄራዊ ደረጃ ወጣቶችን ለበጎ ስራ በማሰማራት መከበሩን የዘገበው ኒውስ 24፤ እንደ ወትሮው በኬክና በሻምፓኝ፣ በክምር ስጦታና በደማቅ ሙዚቃ፣ በይፋ በአደባባይ  አለመከበሩን አመልክቷል፡፡
የሙጋቤ ልደት በየአመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር በጀት ተመድቦለት በሚገርም ፈንጠዝያና በግዙፍ ኬክ ይከበር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ፓርቲያቸው ዛኑ ፒኤፍ ግን ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የሙጋቤ ልደት ያለ ብዙ ወጪ ቀለል ብሎ እንደሚከበር ማስታወቁን ገልጧል፡፡