Administrator

Administrator

 እናትነት …ሁሉም ነገር፡፡
እናት ካለች ቤተሰብ አለ፡፡ ቤተሰብ ሲኖር አካበቢ ወይንም መንደር ከዚያም አገር ይኖራል፡፡ አገር ካለ አለም እውን ይሆናል፡፡ እናት ደህና ካልሆነች ግን ሁሉም ነገር ይበላሻል፡፡
ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው
በውጭው አቆጣጠር ከጃኑዋሪ 9/ እስከ ፌብረዋሪ 7/ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ድረስ ለአንድ ወር የሚቆይ የእናቶችን ደህንነት የሚመለከት Campaign ወይንም የተለያዩ ስራዎች የሚሰሩበት እቅድ ተነድፎአል፡፡
በርእስነት የተቀመጠው አባባል በእንግሊዝኛው <<…NO MOTHERHOOD…DURING CHILD HOOD…>> የሚለውን የዘንድሮው አገር አቀፍ የእናቶች ደህንነት የአንድ ወር ዘመቻ ካተኮ ረባቸው ነጥቦች አንዱ ነው፡፡ በዚህ አመት ሌላው በአጠቃላይ የእናቶች ደህንነትን በሚመለከት ለጉዳት ከሚዳርጉዋቸው ውስጥ የፊስቱላ ሕመም እንዲሁም የደም መፍሰስ እና በልጅነት በእርግዝና ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶች ምን እንደሆኑ ጎልተው እንዲወጡ እና የሚመለከተው ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከላከላቸው የሚል እሳቤ የያዘ ነው። ይህንኑ መሰረት በማድረግም መልእክቶቹን ከተለያዩ ባለሙያዎችና የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከሆኑት በማሰባሰብ ለአንባቢ እነሆ ብለናል፡፡
ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስትና በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት በእርግጥ በአገር ውስጥ ያሉ የፌስቱላ ታካሚዎች ምን ያህል ናቸው የሚለውን ለመለየት ወደሁዋላ በመመለስ የተደረጉ ጥናቶችን ማየት አስፈላጊ ቢሆንም የፌስቱላ ሕመም አሁንም ድረስ መኖሩን ግን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቁጥር ከፍ ዝቅ ቢልም ባሁኑ ወቅት ግን ከ5-7/ሺህ/ድረስ የሚሆኑ ኢትዮያውያን ሴቶች በዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው የሚል ግምት አለ፡፡ ስለዚህም ፊስቱላ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶአል የማይባል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት መስራት የሚያስችል አደረጃጀት ስላለ የተሸለ ነገር ይታያል፡፡ መንግስትም ፊስቱላን ለማጥፋት የሚል ፕሮግራም ነድፎ ሐም ሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያም በግብረኃይሉ የሚሳተፍ ሲሆን የዚህ እቅድም በ5/አመት ጊዜ ውስጥ ፊስቱላ እንደዋነኛ የህብረተሰብ ጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ እንዲፈጠርና ለአዳዲስ ተጎጂ ዎችም አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ በተገቢው መንገድ ማዳረስ ይገባል የሚል ነው፡፡
ዶ/ር ዋሲሁን አለማየሁ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት እና በአሰላ Referral & teaching ሆስፒታል የፊስቱላ ሕክምና ክፍል አስተባባሪና ኃላፊ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ፊስቱላ የሚከሰተው በዋናነት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሲሆን በተለይም በተራዘመ ምጥ ምክንያት ነው፡፡ አንዲት ሴት በምጥ ከ24/ሰአት በላይ ከቆየች በእራስዋም እንዲሁም በልጅዋ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡  ከዚህም በተጨማሪ በቤታቸው በተራዘመ ምጥ ቆይተው ለእርዳታ ወደሆስፒታሉ የመጡ እናቶችን የማዋለድ ስራ በሚሰራበት ወቅት በተለያዩ መሳሪያዎች መጠቀምና ኦፕራሲዮን ማድረግ ስለሚኖር በዚያ ምክንያትም ለፊስቱላ የሚጋለጡ እናቶች እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በሌሎች ምክንያቶች ማለትም ለምሳሌ ለካንሰር ሕክምና በሚደረጉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሳቢያ ፊስቱላ ሊከሰት ይችላል፡፡
በዚህ በእናቶች ደህንነት ምክንያት የሚነሳው ፊስቱላ ከማህጸንና ዙሪያውን ካሉ አካላት ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ቀዳዳ ሲፈጠር የሚታየውን ሲሆን ቃሉ ግን በማንኛውም የሰውነት ክፍል አላስፈላጊ ቀዳዳ ተፈጥሮ ሲታይ የምንጠቀምበት ነው፡፡ በእናቶች ላይ ስንመለከተው በማህጸንና በሽንት መሽኛ አካባቢ ወይንም በማህጸንና በሰገራ መውጫ አካባቢ የሚፈጠር ቀዳዳ ፊስቱላ ይባላል። ይህም በኢትዮጵያ ፊስቱላ የሚባለውን የጤና ችግር ከ90/በመቶ በላይ ድርሻ ይይዛል፡፡ በወሊድ ሰአት ልጁ በሚያልፍበት መንገድ ላይ እና በሽንት ፊኛው መሐል ላይ ለረጅም ሰአት ሲቆይ የደም ዝውውር ይዛባል፡፡ የደም ዝውውር ሲዛባ የሽንት ፊኛውና የወሊድ አካል ለረጅም ጊዜ ደም ስለሚያጣ ይጎዳል፡፡ ያ ክፍል ደም በማጣቱ ምክንያትም ስለሚሞት ይረግፋል፡፡ በሚረግፍበት ጊዜ በፊት ያልነበረ ክፍተት በሁለቱ መካከል ይፈጠራል። ያ ክፍተት ደግሞ ሽንት በማንኛውም ጊዜ ሴትየዋ ልትቆጣጠር በማትችልበት መንገድ ይፈሳል፡፡
ፊስቱላ መከላከል የምንችለው ነገር ነው፡፡ መከላል የሚቻል ነገር በመሆኑም ሁሉም ባለሙያውም ሆነ ህብረተሰቡ በቀበሌ ደረጃ ካሉት ጀምሮ የሚችለውን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሐኪሞቹ ችግሩ የገጠማቸው ሴቶች ሲመጡ ሕክምናውን ከመስጠት ባሻገር ያቺ የታከመች ሴት ከእራስዋ አልፋ ሌላዋን እናት ማስተማር እንድትችል አቅም ፈጥሮ ወደቤተሰብዋ መቀላቀል ተገቢ ነው፡፡ እየሰራን ያለነውም በዚህ መንገድ ነው፡፡
ጤና መኮንን ብርቄ ግርማ
ጤና መኮንን ብርቄ ግርማ እንደገለጹት በአሰላ ሆስፒታል የፌስቱላ ታካሚዎች የሚረዱት በአንድ ክፍል ውስጥ የነበረ ሲሆን ከማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል ጋር በተያያዘ ሕክምናው ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ክፍል እራሱን ችሎ ባለሙያዎችም ለብቻ ተቀጥረው በማገልገል ላይ እንገኛለን፡፡ የፌስቱላ ሕክምና ክፍሉ የራሱ የሆነ 15/አስራ አምስት አልጋ ያለው ሲሆን በወር ውስጥ በአማካይ ከ6-10/ታካሚዎችን ያስተናግዳል፡፡ የታካሚዎች ሁኔታ እንደማንኛውም ታካሚ ከወቅት ጋር የሚያያዝ ሲሆን በክረምት እና በበጋው ወቅት ከፍና ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በክረምት ወቅት እነዚህ ታማሚዎች ያሉበትን አካባቢ አቋርጠው ወደጤና ተቋሙ ለመምጣት ስለሚቸገሩ ባሉበት የሚቆዩ ሲሆን የቅስቀሳ ወይንም ትምህርት የመስጠቱን ነገር ተከትሎም ታካሚዎች ቁጥራቸው ከፍና ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ከጤና ጣቢያዎች ጋር በመሆን ከአሰላ ሆስፒታል የፊስቱላ ሕክምና ክፍልም እየሄድን አብረን ትምህርት እንሰጣለን፡፡ ፊስቱላ የተባለው የጤና ችግር የሚገጥማቸው በተራዘመ ምጥ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንገድ እርቀት፣ የገንዘብ እጥረት ወይንም ቀደም ሲል ከነበሩ ቤተሰቦች የህይወት ልምድ በመነሳት እቤት መውለድ ትክክለኛው ነገር ነው ብሎ በማሰብ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም አለመሄድ ለችግሩ መንስኤ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ እቤት ውስጥ በተራዘመው ምጥ ቆይታ በአቅራቢያ ወደሚገኘው ጤና ጣቢያ ብትሄድም በማዋለድ ሂደቱ ላይ ፊስቱላ የሚከሰትበት አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ደግሞ ፊስቱላ የሚከሰተው በአብዛኛው በመጀመሪያ ልጅ መውለድ ጊዜ ሲሆን እነዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ እርጉዝ የሚሆኑት በአብዛኛው በልጅነት እድሜያቸው የተዳሩና ያረገዙ ሴት ልጆች ናቸው፡፡ ፊስቱላ ብዙ ምክንያ ቶች ቢኖሩትም ቀደም ሲል የጠቀስናቸው በግልጽ የሚታዩ ናቸው፡፡
‹‹…እኔ የመጣሁት ከወላይታ ነው፡፡ ዛሬ 22/አመቴ ነው። ትዳር ከያዝኩ ወደ 7/አመት ይሆነኛል፡፡ ትዳር በያዝኩ ወቅት ወዲያው በአመት ጊዜ ውስጥ ነው ያረገዝኩት፡፡ ምጥ የመጣ ጊዜ ግን በጣም ተቸገርኩ፡፡ ወደጤና ጣቢያ እንዳይወስዱኝ ሩቅ ስለሆነ ይበል ጡኑ ትጎዳለች ብለው እቤት አስቀመጡኝ፡፡ ነገር ግን በአምስተኛው ቀን ትሞታለች ብለው በቃሬዛ ተሸክመው ወሰዱኝ፡፡ ጤና ጣብያ ስደርስ ልጄ ሞቶ ነበር፡፡ እኔም ሳልሞት ለጥቂት ነው የተረፍኩት። ከዚያም ወደቤቴ መለሱኝ፡፡ ሌላ ችግር ደግሞ ተከሰተ። ሽንቴን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ከሶስት አመት በላይ ሽንቴ ሲፈስ ይህ የእግዜር ቁጣ ነው ብለው ዝም ብለውኝ ነበር፡፡ በሁዋላ ግን ትምህርት የሚያስተምሩ ሐኪሞች ሲመጡ ጉዋደኛዬ የሆነች የጎረቤት ልጅ ጠቁማ ካለሁበት ድረስ መጥተው አዩኝ፡፡ ከዚያም በቀጥታ ወደሐምሊን ፊስቱል ሐኪም ቤት እንድመጣ ተደረገ፡፡ አሁን ሕክምና ተደርጎልኝ ድኛለሁ፡፡ በጊዜው ግን እንዴት አድርጌ እራሴን እንደማጠፋ ነበር የማስበው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን …ስንት አመት ከተሰቃየሁ በሁዋላ አሁን ድኛለሁ፡፡››
በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮፕያ ታካሚ  
አንዲት ሴት ቅድመ እርግዝና ምርመራ አድርጋ …በእርግዝናዋ ጊዜ ክትትል ሳታቋርጥ ወደሕክምና ተቋም ሄዳ በሰለጠነ ባለሙያ የምትወልድ ከሆነ …ፊስቱላ አይከሰትም። በየትኛውም አቅጣጫ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ በተጉዋዳኝ የፊስቱላ መኖርንም እየቀነሱት ይመጣሉ፡፡
ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው

በአለማችን የተለያዩ አገራት የሚከሰቱ የመኪና አደጋዎች በየአመቱ 1.25 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት፣ 50 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ ለከፋ የመቁሰል አደጋ አየዳረጉ እንደሚገኙ የአለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአለማችን በመኪና አደጋዎች ሳቢያ ከሚከሰቱ የመቁሰል አደጋዎች መካከል 90 በመቶ ያህሉ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚከሰቱ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤የመኪና አደጋ በአገራቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
የአለም ባንክ ከ135 የአለማችን አገራት ለ24 አመታት ያህል የሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው፣ የመኪና አደጋ ከ15 እስከ 29 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አምራች ሃይል የሆኑ ዜጎችን ለሞትና ለአካል ጉዳተኝነት በመዳረግ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፡፡ ይህም የመኪና አደጋ በአገራት ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳያል ተብሏል፡፡
አገራት በመኪና አደጋ ሳቢያ የሚከሰቱ የሞትና የመቁሰል አደጋዎችን በግማሽ ያህል መቀነስ ከቻሉና ችግሩን በዘላቂነት ማቃለል ከቻሉ፣ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርታቸውን እስከ 24 አመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ከ7 እስከ 22 በመቶ ማሳደግ ይችላሉ ብሏል ሪፖርቱ፡፡

 ሳንዲስክ የተባለው የኮምፒውተር መረጃ መያዣ መሳሪያዎች አምራች ኩባንያ፣ በአለማችን በመጠኑ እጅግ ትንሹ እንደሆነ የተነገረለትንና 1 ቴራባይት መጠን የሚደርስ መረጃ የመያዝ አቅም ያለውን አዲሱን የፍላሽ ዲስክ ምርቱን ከሰሞኑ ለእይታ አቅርቧል፡፡
ኮንሲዩመርስ ኤሌክትሮኒክ ሾው በሚባለውና በላስቬጋስ እየተከናወነ የሚገኘው አመታዊው የአዳዲስ ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደርዕይ ላይ ለእይታ የበቃው የሳንዲስክ አዲሱ ፍላሽ፣ ከዚህ ቀደም ከተሰሩት መሰል ባለ ብዙ አቅም ፍላሾች ለየት የሚያደርገው መጠኑ አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከላፕቶፕና ከዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች በተጨማሪ ከአንድሮይድ ስልኮች ጋር የሚገናኝ መሆኑ ጭምር ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ የሳንዲስክ ፍላሽ የመሸጫ ዋጋው ምን ያህል እንደሚሆንና መቼ በገበያ ላይ እንደሚውል ኩባንያው በይፋ ያስታወቀው ነገር እንደሌለ ዘ ቴክኖሎጂ ኢንኳየረር ድረ-ገጽ ዘግቧል፡፡

ዩኒቨርሲቲ በገቡ በወራት ጊዜ ውስጥ ዶክትሬቱ እንደተሰጣቸው ተነግሯል

    የዚምባቡዌ የጸረ-ሙስና ኮሚሽን፣የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበት ሙጋቤ ባለቤት የሆኑት ግሬስ ሙጋቤ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዚምባቡዌ ተቀብዬዋለሁ የሚሉት የዶክትሬት ዲግሪ ህገ-ወጥ ነው በሚል ጥርጣሬ ጉዳዩን መመርመር መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን፣ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት በአግባቡ መሆንና አለመሆኑን ለማጣራት ምርመራ የጀመረው፣ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዚምባቡዌ መምህራን፣ ጉዳዩን እንዲያጣራላቸው ፊርማ በማሰባሰብ ባለፈው ሳምንት ያቀረቡለትን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ነው ተብሏል፡፡
ግሬስ ሙጋቤ ምንም እንኳን በ2014 ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተው እንደነበር ቢነገርም፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸው የተሰጣቸው ግን እንደ ሌሎች ተማሪዎች አመታትን የፈጀ ምርምር ካደረጉና ብቃታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ሳይሆን ወደ ዩኒቨርሲቲው በገቡ በወራት ጊዜ ውስጥ ነው መባሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው መምህራን ግሬስ ሙጋቤ፣ ምርምር ሳያደርጉና በመዛኞች ብቃታቸው ሳይረጋገጥላቸው ዶክትሬታቸውን ማግኘታቸውን ለኮሚሽኑ ባቀረቡት ማመልከቻ ጠቁመዋል ያለው ዘገባው፤ ግሬስ ከዚህ ቀደም የትምህርት ማስረጃቸውን ትክክለኛነት በተመለከተ ለሚቀርቡባቸው ጥርጣሬዎች መሰረተ ቢስ ናቸው የሚል ምላሽ ይሰጡ እንደነበርም አስታውሷል፡፡

የሩሲያው ፑቲንና የግብጹ አልሲሲም ለሽልማት ታጭተው ነበር

   አለማቀፉ የፕሬስ ነጻነት መብቶች ተሟጋች ተቋም ሲፒጄ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ባደረገው “የአለማችን ቀንደኛ የፕሬስ ነጻነት ጨቋኝ መሪዎች”  ልዩ ምጸት አዘል ሽልማት፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የቱርኩ አቻቸው ጠይብ ኤርዶጋን በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ “የአመቱ ምርጥ ውሸታም ሚዲያዎች ሽልማት” የተሰኘና በአይነቱ ልዩ የሆነ ሽልማት በማዘጋጀት በመጪው ሳምንት አሸናፊዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ ባለፈው ሰኞ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው ሲፒጄ፤ ዶናልድ ትራምፕ ከጋዜጠኞች የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶች እየተከታተሉ በማፈንና የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች በመጣስ፣ ከአለማችን መሪዎች ሁሉ አቻ ስለሌላቸው ሸልሜያቸዋለሁ ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2017፣ በተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ላይ እከስሳችኋለሁ ወይም የሥራ ፈቃዳችሁን እነጥቃችኋለሁ በሚል በተደጋጋሚ ዝተዋል ያለው ተቋሙ፤ ትራምፕ ባለፉት ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ በትዊተር ባስተላለፏቸው ከ1 ሺህ በላይ መልዕክቶች፣ መገናኛ ብዙሃንን መዝለፋቸውንና ማስፈራራታቸውን አስታውሷል፡፡ ጋዜጠኞችን ከስራ ትባረራላችሁ ሲሉ በይፋ አስፈራርተዋል፤ ተመልካቾች አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንን እንዳይከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል፤ ለዚህ ሁሉ ድርጊታቸው ሸልሜያቸዋለሁ ብሏል ሲፒጄ፡፡
የጸረ-ሽብር ህጎችን በመጠቀም የፕሬስ ነጻነትን በማፈን ዘርፍ፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋን የተሸለሙ ሲሆን በዚሁ ዘርፍ ታጭተው የነበሩት የግብጹ አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለጥቂት ተሸንፈዋል ያለው ሲፒጄ፤ በግብጽ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ ከ20 በላይ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አመልክቷል፡፡
በሚዲያ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ሲሸለሙ፣ የሩሲያው ፑቲን ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል፡፡ ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሚገደሉ፣ የሚታሰሩና ጥቃት የሚደርስባቸው የሩሲያ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ የአገሪቱ ነጻ ሚዲያም እየቀጨጨ መሄዱን ቀጥሏል ያለው ተቋሙ፤በአለማችን ላይ ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ቁጥር በ2017 ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ በአመቱ በአለማችን የተለያዩ አገራት 262 ጋዜጠኞች በእስር ላይ ነበሩ ብሏል - ሲፒጄ፡፡

 የቱኒዝያ መንግስት ግብር ለመጨመር ከያዘው አዲስ እቅድ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሰኞ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ብቻ ከ330 በላይ ዜጎች ለእስር መዳረጋቸውንና ባለፉት ቀናት የታሰሩት ሰዎች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሱፍ ቻሄድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዜጎችን ለከፋ ጥፋት እያነሳሱ መሆናቸውን በማውገዝ፣ ዜጎች ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ካሊፋ ቺባኒ በበኩላቸው፤ረቡዕ ምሽት በቁጥጥር ስር የዋሉት 330 ሰዎች ተቃውሞውን ያቀናበሩና ግርግሩን ሽፋን በማድረግ የዝርፊያ ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ ናቸው ማለታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ዜጎች በዋጋ መናርና እየከፋ በመጣ የስራ አጥነት በተማረሩበት ወቅት መንግስት በዜጎች ላይ የግብር ጫና ለማድረግ ማሰቡ ብዙዎችን ማስቆጣቱንና በመዲናይቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሳምንቱን ሙሉ በመቀጠል ወደ ሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን፣ የአገሪቱ መንግስትም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች አሰማርቶ፣ ተቃውሞውን ለማብረድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ተቃዋሚዎች በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የደህንነት ቢሮ ህንጻዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ተቋማትን ማቃጠላቸውንና ወደተለያዩ ከተሞች የተስፋፋውና ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጭምር ያጥለቀለቀው ተቃውሞ ተባብሶ በመቀጠሉ መንግስት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በመላ አገሪቱ ማሰማራቱንም ገልጧል፡፡
በቱኒዝያ በ2011 እና በ2015 የተካሄዱ ተቃውሞዎችና ጥቃቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ስምንት በመቶ ድርሻ የሚሸፍኑትን የውጭ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፎችን በከፍተኛ ሁኔታ ማውደማቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በኢራን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄዱ ጸረ-መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተሳትፋችኋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ዜጎች ቁጥር 3 ሺህ 700 እንደሚደርስ፣ አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የህግ ባለሙያ ማስታወቃቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
በኢራን በተቃውሞ ተሳትፋችኋል በሚል ከተያዙት ዜጎች መካከል አምስቱ በእስር ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል ያለው አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢራን መንግስት ያሰራቸውን ዜጎች በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥያቄ ማቅረቡን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በእስር ላይ በሚገኙ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ እየደረሰ ነው፣ እስር ቤቶቹ የሚገኙበት ሁኔታም እጅግ አስቸጋሪና ስቃይ የሞላበት ነው የሚለው  አምነስቲ፤ ጉዳዩ በአፋጣኝ በገለልተኛ ወገን  እንዲጣራና በእስረኞች ላይ ግፍ የሚፈጽሙ አካላትም ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡

 ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከፃፏቸው አጫጭር ትርክቶች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ፈረሰኛ ተራራ እየወጣ ሳለ፤ አንድ፣ አንድ እግሩ ቆራጣ የሆነ ሰው ያንን መንዲስ የሚያክልና ጫፉ ሩቅ የሆነ ተራራ፤ እየተንፏቀቀ ለመውጣት ሲፍጨረጨር ያገኘዋል፡፡ ያም እግሩ የተቆረጠ ሰው፡-
“ጌታዬ እባክህ የተወሰነ መንገድ ድረስ አፈናጠኝና ውሰደኝ?” ሲል ይለምነዋል፡፡
ፈረሰኛውም ልቡ በጣም ይራራና፤ “እሺ ወዳጄ፤ ፈረሱ የቻለው ርቀት ያህል አብረንእንሄዳለን፡፡ ና ውጣ” ብሎ፤ ወርዶ፣ አቅፎ ያፈናጥጠዋል፡፡
ትንሽ መንገድ አብረው ከተጓዙ በኋላ፤ እግረ ቆራጣው ሰውዬ፤
“ጌታዬ፤ ብዙ ምቾት አልተሰማኝም፡፡ አካል-ጉዳተኛ በመሆኔ አንደኛው እግሬን እጅግ ህመም ተሰማኝ!” አለው፡፡
ፈረሰኛው፤
“ታዲያ እንዴት ብናደርግ ይመችሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡
አካል-ጉዳተኛውም፤
“ትንሽ መንገድ እኔ ልሂድ፣ አንተ እግርህ ጤነኛ ስለሆነ ተከተለኝ” አለው፡፡
ፈረሰኛው በሁኔታው አዝኖ ልቡ ራራና፤
“መልካም፤ እኔ ልውረድ አንተ ሂድ፡፡ ሲደክመኝ ትጠብቀኝና ደሞ አብረን እንጓዛለን” አለውና ወረደ፡፡
የተወሰነ ርቀት፤ አካል-ጉዳተኛው በፈረስ፣ ባለፈረሱ በእግሩ ተጓዙ፡፡
ፈረሰኛው “ደክሞኛል ጠብቀኝ” አለው፡፡
እንደገና ተፈናጠጡና መንገድ ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ፣ ፈረሰኛው ወረደለትና አካል ጉዳተኛው በፈረስ ቀጠለ፡፡ አሁን ግን ያ አካል-ጉዳተኛ ፈረሱን ኮልኩሎ ለዐይን ተሰወረ፡፡ ፈረሰኛው ቢሮጥ፣ ቢሮጥ ሊደርስበት አልቻለም፡፡
ባለፈረሱ  ጮክ  ብሎ፣ “እባክህ ሌላ ምንም አልፈልግም፣ የምነግርህን ብቻ አንዴ አዳምጠኝ?” አለው፡፡
ፈረስ ነጣቂው ባለቤቱ የማይደርስበት አስተማማኝ ቦታ ሲደርስ፤
“እሺ ምን ልትል ነው የፈለከው? እሰማሃለሁ ተናገር!” አለው በዕብሪት፡፡
ባለፈረሱም፤
“ወንድሜ ሆይ! አደራህን ይሄን እኔን ያደረከኝን ነገር ለማንም ሰው እንዳትነግር፡፡ ወደፊት በዓለም ደግ የሚያደርግ ሰው ይጠፋል!” አለው፡፡
*   *   *
ደግነት የብዙ ህይወታችን መሰረት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ቀናነት ካልተጨመረበት ዲሞክራሲም፣ ፍትሃዊነትም፣ ልማትም፣ አስተማማኝነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ደግ ያደረጉን ለመካስ ዝግጁ መሆን እንጂ ለክፉ ማጋለጥ አይገባም፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገሩ ጉዳይ ያገባዋል፡፡ መምህራን የልጆችን ተስፋ አለምላሚ ናቸው፡፡ ወታደሮች የሀገር ህልውና ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ገበሬዎች የኢኮኖሚ ገንቢዎች ናቸው፡፡
የጥበብ ሰዎች የዘመን ዜማዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋዳሾች ናቸው፡፡  
“ሀብት ሲበዛ ዲሞክራሲ ይረጋገጣል ያለው ማነው?” ብሏል አንድ አዋቂ፤ ምን ያህል ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንደሚተሳሰሩ ሲያጠይቅ! ያለው ይናገራል፣ የሌለው ያፈጣል ወይም ሁሉን “እሺ” ይላል፤ የሚባል ነገር አለና አስተውለን ብናስብ ታላቅ ነገር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ፤ እየተሳሰቡ መጓዝን የመሰለ ነገር የለም፡፡ መከራችን፤ የሀገራችን የችግር ቁልል ተራራ አካል ነውና ለብቻ አይገፋም፡፡
ከረዥም ጊዜው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል አንፃር ስንመለከት ወጣቶች ልዩ ባህሪ እንዳላቸው እናስተውላለን - ታሪክን ዋቤ ቆጥረን፡፡ ባህሪያቸው፤ ቁርጠኝነትና ራስ - ወዳድ አለመሆን፣ ፍትሐዊነት፣ ጭቦኛ አለመሆን፣ የሴቶችን እኩልነት ማመን እና ትሁትነት የሚያካትቱ ልዩ ምልክቶቹ ነበሩ፤ ለማለት ያስደፍራል፡፡ እኒህ ምልክቶቹ ዛሬ ወዴት አሉ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው! እንጠያየቅ፡፡ ወጣቱን ያላቀፈ ጉዞ፣ ጉዞ አይደለምና!
አንጋረ ፈላስፋ፤
“ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ-ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይለናል፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ የልማት፣ የኢኮኖሚ ድርና ማግ ናቸው እንደማለትም ነው፡፡ ባህልን ማክበር፣ አዋቂን ማድመጥ፣ ለዕውቀት መሪ ቦታ መስጠት፣ ጎረኝነትን ማስወገድና የጋራ መድረክ፣ የጋራ ሸንጎ መሻት፣ ዋና ጉዳይ መሆናቸውን መቼም አንዘንጋ፡፡
“የአያቴ ብስክሌት መንዳት አሪፍ መሆን እኔን ከመውደቅ አያድነኝም” ይላል ገጣሚ ሰለሞን ደሬሣ (ልጅነት)፡፡ በትላንት አበው ታሪክ መመካት ብቻውን ወደ ፊት አያራምደንም ሲል ነው፡፡ አንድም ነገን ዛሬ እንፍጠረው እንደ ማለት ነው፡፡ ለሁሉም እኩል የሆነች አገር አጠንክሮ ለመጨበጥ እንዘጋጅ ሲልም ነው፡፡ እርስ በርስ የማንፈራራባት፣ የማንጠራጠርባት፣ ነጋችንን ጨለማ አድርገን የማናይባት አገር ነው መገንባት ያለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ አለመተማመን ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ነው፡፡ “ስንት ሰዓት ነው?” ቢሉ ከተሜው፤ “የዘመኑ ሰዓትና የዘመኑ ሰው ውሸታም ነው፡፡ ዝም ብለው ጥላዎትን አይተው ይሂዱ!” አለ ባላገር፤ የሚለው ቁም ነገር፣ ነገን እንድናስተውል ልብ በሉ የሚለን ነው!

 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፤ የዓለም ሃገራትን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው የደረጃ ሰንጠረዥ፤ ኢትዮጵያን በጉዞ ወቅት የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ከሚያስፈልግባቸው ሃገራት ተርታ መድቧታል፡፡
በደረጃ አንድ የተመደቡ ሀገራት የተለመደው ጥንቃቄ ተደርጎ ጉዞ ሊደረግባቸው የሚችሉ ሲሆን ኢትዮጵያ የተመደበችበት ደግሞ የፀጥታ ሁኔታቸው የሚያሰጋና በጣም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ከሚገቡ ሀገራት ተርታ ነው ብሏል- የአሜሪካ ድምፅ ባቀረበው ዘገባ፡፡
የግጭቶች የመከሰት እድሉ ከፍተኛ መሆኑንና  መንግስት ኢንተርኔት በተደጋጋሚ መዝጋቱ ሀገሪቱን በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ከሚያስፈልጋቸው ሀገራት እንድትመደብ ዋና ምክንያት ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲም በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ዜጎቹን በመረጃ መድረስ እንደማይችል ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካውያን በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንዲከታተሉና ለመረጃዎች ንቁ እንዲሆኑ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የጉብኝትና የጉዞ አካባቢዎችንም በ4 ደረጃዎች መድቦ፣ ዜጎቹ ጉዟቸውን በጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰበው መግለጫው፤ በአንደኛ ደረጃ የተመደቡት የተለመደ ጉዞ ማድረግ የሚቻልባቸው ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌና አፋር ክልል የደናክል አካባቢ በ3ኛ ደረጃ የተመደቡ መሆኑ ታውቋል፡፡ በ3ኛ ደረጃ የተመደቡ አካባቢዎች የሚደረጉ ጉዞዎችን ደጋግሞ በማሰብ፣ እስከመሰረዝ የሚገቡ ናቸው ይላል ሪፖርቱ፡፡
ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ያለባቸው የምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ ግጭቶች ሊያገረሹ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡
ደህንነታቸው ፍፁም የተጠበቀ አይደለም ተብለው በ4ኛ ደረጃ ከተመደቡት መካከል ደግሞ የሶማሌ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡ የጉዞ ማስጠንቀቂያው በ4ኛ ደረጃ ወደተመደቡ አካባቢዎች የሚደረግን ጉዞ ይከለክላል፡፡
ሁኔታዎች በተሻሻሉ ቁጥር በሪፖርቱ ላይ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከ4 ዓመት በላይ አነጋጋሪና አከራካሪ ሆኖ በቆየው የውጭ ሃገር የህፃናት ጉዲፈቻ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ህፃናት በጉዲፈቻ ለውጭ ሀገራት ዜጎች እንዳይሰጡ የሚከለክለውን አዋጅ ሰሞኑን አፅድቋል፡፡
የምክር ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ቢቢሲ እና ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን ሁነኛ መነጋገሪያ ያደረጉት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው እ.ኤ.አ በ2013 አሜሪካዊያን ጥንዶች ለማሳደግ የወሰዷትን ህፃን፣ በጭካኔ ከገደሉ በኋላ በተፈጠረ ቁጣ ነው ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፀደቀው አዋጁ፤ ህፃናትን ከእንግዲህ ለውጭ ሀገር ዜጎች በማደጎነት መስጠት እንደማይቻል የሚደነግግ ሲሆን ህጉን በሚጥሱት ላይ  ቅጣት ማስቀመጡም ታውቋል፡፡
ይህን አዋጅ ለመደንገግ ያስፈለገበት ምክንያት በማደጎነት ለውጭ ሀገር እየተሰጡ ባሉ ህፃናት ላይ የሚደርሱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተባባሱ በመምጣታቸው መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ከእንግዲህ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ህፃናት በተወለዱበት ሀገር ቋንቋውን፣ ባህሉን እየተማሩ ብቻ ነው ማደግ የሚችሉት የተባለ ሲሆን ወላጅ አልባ ህፃናትም በሃገር ውስጥ የማሳደጊያ ማዕከል የሚያድጉበት እድል እንደሚፈጠር ተጠቁሟል፡፡ የሃገር ውስጥ የጉዲፈቻ ባህልም እንዲስፋፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በአዋጁ ላይ ሰፊ ሃተታ ያቀረቡት ቢቢሲ እና ፎክስ ኒውስ፤ ኢትዮጵያውያን ህፃናትን በማደጎነት በመውሰድ ጉልህ ድርሻ ባላት አሜሪካ ዘንድ ውሳኔው ቅሬታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ የማደጎ ልጆችን ከሚያሳድጉ አሜሪካውያን መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ልጆች እንዳሏቸው የተመለከተ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ1999 እስከ 2017 ባሉት 18 ዓመታት ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ህጻናት  በማደጎነት ወደ አሜሪካ ተወስደዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናት ደግሞ በዋናነት ወደ ስፔን፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በማደጎነት ሲወሰዱ ነበር ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ህፃናትን ለውጭ አገራት ዜጎች በማደጎነት በመስጠት ከሚታወቁ  አስር የዓለም አገሮች አንዷ እንደነበረችም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡   

    - የቀድሞው መሪ ሳኒ አባቻ 4 ቢ. ዶላር ያህል መዝረፋቸው ተነግሯል

    የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ ዘርፈውታል የተባለውና የሙስና ምርመራ ለማድረግ በአሜሪካ የተያዘው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እንዲመለስ፣ የናይጀሪያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶች የተባለው የአገሪቱ የመብቶች ተከራካሪ ቡድን ለትራምፕ አስተዳደር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ፣ በስልጣን ዘመናቸው በድምሩ 4 ቢሊዮን ዶላር ያህል የህዝብ ሃብት መዝብረዋል መባላቸውን ያስታወሰው የሲኤንኤን ዘገባ፤ቡድኑም ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በአሜሪካ እጅ ውስጥ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝና ገንዘቡ ለህዝቡ እንዲመልስ ለትራምፕ አስተዳደር በደብዳቤ መጠየቁን አመልክቷል፡፡ ናይጀሪያ በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ላይ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በአሜሪካ እጅ ላይ የሚገኘው የህዝብ ገንዘብ በአፋጣኝ መመለሱ አግባብ ነው፤ ትራምፕ ገንዘቡን ይመልሱና ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ስራዎች ላይ ይዋል ብሏል፤ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ፡፡
የናይጀሪያው ፕሬዚደንት መሃመድ ቡሃሪ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውንና ገንዘቡን ለመመለስ መስማማታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአንዳንድ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች ምክንያት ገንዘቡ ሳይመለስ የትራምፕ አስተዳደር ወደ ስልጣን መምጣቱን አስረድቷል፡፡እ.ኤ.አ በ1998 ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሳኒ ኣባቻ፣ በተለያዩ አገራት የነበሯቸው ገንዘቦችና ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ስዊዘርላንድ 700 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ለናይጀሪያ መንግስት መመለሷን ገልጧል፡፡