Administrator

Administrator

Saturday, 16 April 2016 11:09

የቢዝነስ ጥግ

 (ስለ ደንበኞች)
የቢዝነስ ዓላማ ደንበኞችን የሚፈጥር ደንበኛ መፍጠር ነው፡፡
ፒተር ድራከር
ትክክልም ይሁን ስህተት፣ ሁልጊዜም ደንበኛ  ትክክል ነው፡፡
ማርሻል ፊልድ
ደሞዝ የሚከፍለው ቀጣሪው አይደለም። ቀጣሪዎች የሚያደርጉት ገንዘቡን ማስተዳደር ብቻ ነው፡፡ ደሞዝ የሚከፍለው ደንበኛው ነው፡፡
ሔነሪ ፎርድ
ደንበኞች ፍፁም እንድትሆን አይጠብቁህም። እነሱ የሚጠብቁት ነገሮች ሲበላሹ እንድታቀናቸው ነው፡፡
ዶናልድ ፖርተር
ደንበኛህን የታሪክህ ጀግና አድርገው፡፡
አን ሃንድሌይ
አንድ አለቃ ብቻ ነው ያለው፡፡ ደንበኛችን። ገንዘቡን ሌላ ቦታ በማጥፋት ብቻ በኩባንያው ውስጥ ያሉትን ሠራተኞች በሙሉ ከዋና ሥራ አስፈፃሚው እስከ ዝቅተኛው ተቀጣሪ ድረስ ከሥራ ሊያባርር ይችላል፡፡
ሳም ዋልተን
ደንበኞችህን ካልተንከባከብካቸው ሌላው ይንከባከባቸዋል፡፡
ያልታወቀ ሰው
ሁሉም ነገር ከደንበኛ ይጀምራል፡፡
ሎዩ ገርስትነር
ትህትና የተመላበት አያያዝ ደንበኛውን ተጓዥ ማስታወቂያ ያደርገዋል፡፡
ጄ.ሲ.ፔኒ
የደንበኛ አገልግሎት አንድ ዲፓርትመንት አይደለም፡፡ አመለካከት ነው፡፡
ያልታወቀ ሰው
አንድን ደንበኛ ለማግኘት ወራት ይፈጃል፤ ለማጣት ግን ሰኮንዶች ይበቃሉ፡፡
ክላንትጌሪችዜይድ
የደንበኛ አገልግሎት ብቸኛ ዓላማው ስሜትን መለወጥ ነው፡፡
ሴዝ ጐኮን    

Saturday, 16 April 2016 11:02

የፀሃፍት ጥግ

(ስለ ትርጉም)
ፀሃፍት በቋንቋቸው አገር አቀፍ ሥነ ፅሁፍፉን ይፈጥራሉ፤ የዓለም ሥነ ፅሁፍ የሚፃፈው ግን በተርጓሚዎች ነው፡፡
ጆሴ ሳራማጎ
ትርጉም ባይኖር በአገሬ ድንበር ተወስኜ እቀር ነበር፡፡ ተርጓሚ በጣም አስፈላጊ አጋሬ ነው፡፡ ለዓለም ያስተዋውቀኛል፡፡
ኢታሎ ካልቪኖ
ተርጓሚ እንደሚተረጉመው ደራሲ መሆን አለበት፤ ከደራሲው መላቅ የእሱ ስራ አይደለም፡፡
ሳሙኤል ጆንሰን
ትርጉም የውድቀት ጥበብ ነው፡፡
ዩምቤርቶ ኢኮ
ትርጉም የዓለም ሥነ ፅሁፍ የዝውውር ሥርዓት ነው፡፡
ሱሳን ሶንታግ
ትርጉም የቃላት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ አንድን ሙሉ ባህል አንባቢው እንዲረዳው የማድረግ ጉዳይም ጭምር ነው፡፡
አንቶኒ በርጌስ
የትርጉም ጥበብ፤ ታሪክንና የሰው ልጅ አዕምሮን የመመልከቺያ መስኮት ይከፍታል፡፡
“ፋውንድ ኢን ትራንስሌሽን”
ተርጓሚዎች እንደ ወይን ጠጅ ናቸው፤ አሪፍ ለመሆን ጊዜ ይፈልጋሉ፤ ከእርካሾቹ የምታተርፉት ራስ ምታት ብቻ ነው፡፡
ትርጉም ባይኖር ኖሮ በዝምታ በተከለሉ ግዛቶች ነበር የምንኖረው፡፡
ጆርጅ ስቴይነር
ትርጉም እንደ ሴት ነው፡፡ ውብ ከሆነ ታማኝ አይደለም፡፡ ታማኝ ከሆነ በእርግጠኝነት ውብ አይደለም፡፡
ይቭጌኒ ይቭቱሼንኮ
ትርጉም ለእኔ እንደዘበት የምሰራው ነገር ነው፤ ምክንያቱም በልጅነቴ ከጀርመንኛ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሜአለሁ፡፡
ማይክል ሃምቡርገር

Saturday, 16 April 2016 10:59

የዘላለም ጥግ

(ስለ ዕውቀት)
• እውቀት ምን እንደሚናገሩ ማወቅ ሲሆን
ጥበብ መቼ እንደሚናገሩ ማወቅ ነው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
• ግሩም ውሳኔ በዕውቀት ላይ እንጂ በቁጥር
ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡
ብሬይኒ
• በዕውቀት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት
እጅግ የላቀውን ወለድ ያስከፍላል፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን
• ለዕውቀት ባለህ ጥማት በመረጃዎች
አለመስመጥህን እርግጠኛ ሁን፡፡
አንቶኒ ጄ.ዲ አንጄሎ
• ሳይንስ የተደራጀ ዕውቀት ነው፡፡ ጥበብ
የተደራጀ ህይወት ነው፡፡
አማኑኤል ካንት
• በመረጃ ውስጥ እየሰጠምን ነው፡፡ ነገር ግን
ዕውቀትን ተርበናል፡፡
Quotesaday.com
• መረጃ ዕውቀት አይደለም፤ ዕውቀት ጥበብ
አይደለም፤ ጥበብ እውነት አይደለም፤
እውነት ውበት አይደለም፤ ውበት ፍቅር
አይደለም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
• እውቀት ከመማር ይመጣል፡፡ ብልህነት ከኑሮ
ይገኛል፡፡
አንቶኒ ዳግላስ ዊሊያምስ
• የእውቀት ብቸኛ ምንጭ የህይወት ልምድ
ነው፡፡
አልበርት አንስታይን
• ከሃሰተኛ ዕውቀት ተጠንቀቅ፤ ከድንቁርና
የበለጠ አደገኛ ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
• ጥርጣሬ የዕውቀት ቁልፉ ነው፡፡
ምሳሌያዊ አባባል
• እውቀት ለብልህ ሰው ሃብቱ ነው፡፡
ዊሊያም ፔን
• እውቀት መሳሪያ ነው፡፡ ጦርነት ከመጀመርህ
በፊት ራስህን በቅጡ አስታጥቅ፡፡
ጆርጅ አር. አር. ማርቲን
• መማር ዕውቀት የመሰብሰብ ጉዳይ ነው፤
ጠቢብነት ያንን ዕውቀት መጠቀም ነው፡፡
ሩፕሊን


Saturday, 16 April 2016 10:52

ማራኪ አንቀጽ

    ባለብዙ ቀለምዋ ሕይወት ብዙ ጠብታዎች አሏት - እንደ ሻማ ቀልጠው ብርሃናቸው ካበቃ በኋላ በዘመን ሰም ተወልውለው የሚቀመጡ። … ብርሃን የአንድ ጊዜ ፍንደቃ፣ ጨለማም የአንድ ጊዜ ድብርት ይሁን እንጂ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የመቆየትና እየተፍለቀለቁ ወይም እየሰቀቁ የመኖር ዐቅማቸው ብዙ ነው። ሕይወት በአንድ ትከሻ ጎመን የነሰነሰ ጎጆ፣ በሌላው ደግሞ ጮማ የተንተራሰ ቪላ አዝላ ስትሄድ በዚያ መንገዳገድ ውስጥ  ለሚያልፈው አዳም በልቡ  የምትጽፋቸው ውሎች አሉ። … ውበትና ፉንጋነት!
እኔም በልጅ ልብ የሚኖሩ … በወጣትነት ዘመን እንደ እሳተ ገሞራ እየተንፈቀፈቁ የሚወጡ ግንፍል ስሜቶች የሚታፈኑበትን፣ ማኅበረ-ፖለቲካዊ፣ … ማኅበረ-ባህላዊና ማኅበረ-ታሪካዊ ቀውሶች የነበሩበትን ትውልድና ምጡን፣ ደመና የዋጠው ድምፁንና ሣቁን፣ ደረቅ ሳሉንና አልደርቅ ያለ እንባውን ለማሰብና ለማስታወስ ነፍሴ ግድ ብላኛለች። ምናልባትም ታላቁ አሜሪካዊ ደራሲ፣መምህርና ሃያሲ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን -በእግሮቻችን እንሄዳለን፤በእጆቻችን እንሰራለን፤የአእምሯችንን እንናገራለን” እንደሚል ውስጤ ያለውን ማውጣት ግድ ብሎኛል፡፡  
… ከፊል ዘመነኞቼን ያሰብኩበት ብሔራዊ ውትድርናና የብላቴውን የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን ሕይወትና የሀገሪቱን ምስቅልቅል፣ … በሌላ በኩል ደግሞ የቀዳሚዎቹን ዘመነኞች ጡንቻማ ፍልሚያ ወላፈን ከሕፃናት ሕይወት ጋር እጅ ለእጅ ለማጨባበጥና ለማስታወስ ፈዛዛ ምስሎች በትንሷ ኪሴ ወሽቄያለሁ። የማላውቀውን ዘመን ነፋስ ስሜት በሩቁ እንጂ እጄን በመስደድ እልፍኙን አልደፈርኩም።
… ግን ደግሞ የክብር ዘውድ ሊደፋባቸው የሚገባ ጭንቅላቶች ላይ የተጎነጎነውን የሾህ አክሊል አለማሰብ አልተቻለኝምና ጥላሸት በለበሰው የትዝታ ፋኖሴ ትንሽ ጭላንጭል ለኩሻለሁ።
ከሁሉ  ይልቅ አበባነት ውስጥ ያሉ ትንንሽ የሕይወት እንጎቻዎች በትንሷ ምጣድ ላይ ተጋግረው፣ በመዓዛቸው ድንበር ዐልፈው እንዲመጡ፣ አጥር ዘልለው እንዲያፏጩ … ቅጥሩን ዝቅ አድርጌላቸዋለሁ ብዬ አምናለሁ። … በዚህም በጾታዊ ፍቅር የሚንከባለሉ ከረሜላ ልቦች … ሰማይ የሚቧጭሩ ሀገራዊ ምኞቶች … ክንፍ ሳያወጡ በእንቁላልነታቸው እቅፍ ሥር ለባከኑ ሕልሞች … እንባ ያነቃቸው ሣቆች በታሪኩ ተራራ ላይ እንደ ሰንደቅ  ተተክለዋል።
(ከደረጀ በላይነህ “የደመና ሳቆች” የተሰኘ አዲስ ረዥም ልብወለድ መግቢያ ላይ የተቀነጨበ)

     በኩዌት በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ የምትሰራ ስሟ ያልተጠቀሰ ኢትዮጵያዊት፣ የአሰሪዎቿን  ቤተሰቦች የሰው ስጋ ይበላሉ ስትል መክሰሷን ገልፍ ዲጂታል ኒውስ የተባለው ድረገጽ ዘገበ፡፡ሳላዋ በተባለው የአገሪቱ አውራጃ በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ የምትሰራው ኢትዮጵያዊቷ፣ በአሰሪዎቿ   መኖሪያ ቤት ውስጥ የሰው ራስ ቅል ተደብቆ ማየቷን በመጥቀስ ለፖሊስ አቤቱታዋን ያቀረበች ሲሆን፣ የአካባቢው ፖሊስም ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አሰሪዎቹ በሄደበት ወቅት፣ የቤቱን በር የሚከፍትለት ሰው ማጣቱን ዘገባው ገልጧል፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን በመመርመር ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ የምርመራ ቡድኑ ምናልባትም ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ ከአሰሪዎቿ የደረሰባትን በደል ለመበቀል ያደረገቺው ድርጊት ሊሆን ይችላል፣ አልያም የአእምሮ ጤንነቷ የተዛባ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት መያዙን አስታውቋል፡፡

ይድረስ ለኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር
ሰሞኑን ሥርጭቱን በጀመረው “ቃና ቲቪ” ይዘት እና አሰራር ላይ ለመወያየት በደብዳቤ
ባሳወቅናችሁ መሰረት ተወካያችሁን መላካችሁ ይታወቃል፡፡  የኪነ ጥበብ ሞያ ማኅበር ተወካዮቹ (የእናንተም ባሉበት) በተጠቀሰው ጉዳይ ለሁለት የተለያዩ  ቀናት የጋራ ውይይት አካሂደው የጋራ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ የጋራ  አቋም በፅሁፍና በንባብ ለሚዲያ ከመቅረቡ በፊት የእናንተ ሁለት ተወካዮችን ጨምሮ የሁሉም   የሞያ ማኅበር ተወካዮች መስመር በመስመር በጥንቃቄ ተመልክተው ማሻሻያና ማረሚያ ካደረጉ  በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ መግለጫ ከመሰጠቱ አንድ ቀን ቀደም  ብሎ (በ20/07/2008) የደራስያን ማኅበር ልሳን በሆነውና ዘወትር ማክሰኞ ምሽት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚቀርበው ፕሮግራም ላይ የመግለጫውን ፍሬ ሃሳብ ለህዝብ በመግለፅ ሚዲያዎች እንዲገኙ መረጃ ስታደርሱ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ይህ ጥሬ ሀቅ ባለበት ሁኔታ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 1 ቀን 2003 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ  ጋዜጣ ላይ የደራስያን ማኅበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ የሰጡት ከእውነት የራቀና የተዛባ  መግለጫ እጅግ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የመላው የደራስያን ማኅበር አመራርና አባላት እምነት እንዳልሆነም እናምናለን፡፡ የእሳቸው ማኅበር ተወካይና ሌሎች የጥበብ ማኅበራት በጋራ ተወያይተው ያወጡትን መግለጫ በምን ምክንያትና መነሳሳት ለመካድ እንዳነሳሳቸው ለጊዜው ያወቅነው ነገር የለም፡፡ በሂደቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሲሳተፍ የነበረውን የማኅበራቸውን ተወካይ፤ “መግለጫውን ለመከታተል የተገኘ ነው” በማለት ከደራሲያን ማኅበር ተወካይነት ወደ ሚዲያ ተወካይነት ለውጠው፣ ለጋዜጣው ለመግለፅ ለምን እንደተገደዱም አልተረዳንም፡፡ ከዚህም በላይ ማህበራቱ የቴሌቪዥን ጣቢያውን በሚመለከት እያቀረቡት ካለው አመክንዮና ለህዝብ ከገለፁት አቋም ፈፅሞ የራቀና የማናውቀውን ጉዳይ በመናገር አንባቢን ግራ ከማጋባታቸውም በላይ የማኅበራቱን ጥያቄ ያልተገባ ለማስመሰል መሞከራቸው ከምን በመነጨ አስተሳሰብና ዓላማ እንደሆነ ለጊዜው አልደረስንበትም፡፡ በእሳቸውና በመላው የጋዜጣዊ መግለጫው ተሳታፊ በነበሩ የሚዲያ አካላት እጅ በሚገኘው ባለ አምስት ገፁ የሞያ ማኅበራቱ የአቋም መግለጫ በየትኛው አንቀፅ ላይ ይሆን የሳንሱር ጉዳይ የተነሳው!? የኢትዮጵያ ደራስያንን እወክላለሁ የሚል
የማኅበር ፕሬዚደንት የተፃፈን ፅሑፍ አንብቦ መረዳት ተሳነው ቢባልስ ማን ያምን ይሆን!? የሆነስ
ሆነና “እነ በዓሉ ግርማን የመሳሰሉ ፀሐፍት በሳንሱር ምክንያት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል”
ማለታቸውስ የደራስያን ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብሎ የፕሬዚደንትነት ሥልጣን ከተቆናጠጠ ግለሰብ ይጠበቃል ወይ!? ሌላው ቢቀር የደራስያን ማኅበር የአመራር አባል በነበረው ደራሲ እንዳለጌታ  ከበደ ጥልቅ ጥናትና ምርምር የታተሙትን “ማዕቀብ” እና “የበዓሉ ግርማ ሕይወትና ሥራዎች” የተሰኙ በብዙዎች የተነበቡ መፃሕፍትን ቢያነቡ ኖሮ በዓሉ ግርማን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በሳንሱር ምክንያት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈለ (የተገደለ) አንድም ደራሲ እንደሌለ በተረዱ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የኪነ ጥበብ ሞያ ማኅበራቱ በመግለጫቸው ያሉት ዋና ፍሬ ሀሳብ ዶ/ር ሙሴ በስህተት አልያም በችኮላ ተረድተው እንዳሉት ሳይሆን “ቃና” ቴሌቪዥን ለውጭ ሀገር ፕሮግራሞች የሰጠው (70%) ተገቢ አይደለም የሚል ነው፡፡ ይህ ሀሳብ የሳንሱር ሳይሆን በሀገር ውስጥ፣ በሀገር አቅም በሚሰሩ ፊልሞች ላይ ጫና ፈጥሮ ፍትሀዊ ተወዳዳሪነት እንዳይኖር በማድረግ፣ ዳዴ በማለት ላይ ያለውንና የብዙ ዓይነት ጥበቦችና ባለሙያዎች ውህደት ውጤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሲኒማ አቀጭጮ ያጠፋል፣ አዲስ ለሚከፈቱ ጣቢያዎች በቀላሉና በውስን ሰዎች ሳይለፉ ገንዘብ እንደሚሰራ በማሳየት በመስኩ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ዜጎች በሀገራቸው ስለ ሀገራቸው ጉዳይ የሚተርክ ፊልም በመስራት እንዳይጠቀሙና ሞያውን እንዳያሳድጉ እንቅፋት ይሆናል፣ ህዝብን የሚያረካ ሥራን የሰሩና ይሁንታን በማግኘት የተደነቁ ባለሙያዎችም ዝናቸውን በመጠቀም የደሀ
ህዝባቸውን ችግር ለመቅረፍ በሚደረጉ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚያደርጉትን በጎ እንቅስቃሴና ቅስቀሳ ተፅዕኖ አልባ በማድረግ ያዳፍነዋል የሚል ነው፡፡ በእግረ መንገድም ፊልሞቹ በአብዛኛው ከምዕራባውያን የሚመጡ እንደመሆናቸውና የሚተላለፈው ለቤተሰብ ቅርብ በሆነው የቴሌቪዥን ሚዲያ በኩል ከመሆኑ አንፃር አጉል ባህል በቀላሉ ታዳጊ ህፃናትና ልጆች ላይ እንዳይሰርፅ ሥጋታችንን የገለፅንበት ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ሞያ ማኅበራቱ በጋራ ባካሄዱት ውይይት ዶ/ር ሙሴ የእሳቸውን ማኅበር በመወከል በተገኘው ግለሰብ እምነት ከሌላቸው፣ ከቢሮአቸው በአራት እርምጃ ከሚርቀው የጋራ ማኅበራቱ
መሰብሰቢያ ቢሮ በመምጣት ጉዳዩን ማጣራት ይችሉ ነበር፡፡ አልያም በአሁን ሰዓት የደራስያን አመራር አባል የሆኑት የሥራ ባልደረባቸው በዚሁ ጋዜጣ ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም የፃፉትን ጥልቅና ለብዙዎች ስለ ጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ ያስጨበጠ ፅሑፍ ቢቻል አንብበው ካልሆነም ካነበበ ሰምተው አስተያየታቸውን ቢሰጡ ኖሮ ትዝብት ላይ የሚጥል ስህተት ባልሰሩ፣ መልካም ሥም የነበረውን ማኅበራቸውንም ባላቀለሉ ነበር እንላለን፡፡
(ተፃፈ፡- ከ “የኢትዮጵያ  የኪነ ጥበብ ማኅበራት
ጊዜያዊ አስተባባሪ”)

• ፓርቲው የውስጥ ችግሩን መፍታት ለምን ተሳነው?
• ለፓርቲው ቀውስ ተጠያቂው ማን ነው?
• የመበታተን አደጋ ያሰጋው ይሆን ?
ሰማያዊ ፓርቲ በተለይ ሊቀመንበሩና ሌሎች አመራሮች መዝብረዋል የተባለውን ገንዘብ መነሻ በማድረግ በአጋጅ ታጋጅ ድራማ ታጅቦ በቀውስ
እየተናጠ ይገኛል፡፡ በፓርቲው ችግሮች፣ በመፍትሄዎቹ፣ በፓርቲው የወደፊት እጣ ፈንታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጋር ጥልቀት ያለው ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

     ሰማያዊ ፓርቲን ----- ከምርጫ 2007 ዓ.ም በፊትና በኋላ እንዴት ይገልጹታል?
አሁን ባለው ሁኔታ ሰማያዊ ፓርቲ ስራ እየሰራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ነው ያለው፡፡ የተፈጠሩ ችግሮች ከእለት እለት ፓርቲውን እንደሚጎዳ ሁሉ፣ የህዝቡንም የደጋፊውንም ስነ ልቦና እየጎዳ ነው፡፡ በተለይ ዲሲፒሊንና ኦዲትና ኢንስፔክሽን የሚባሉት በመካሰስና በፍረጃ የተሞላ ስራ እየሰሩ በመሆኑ፣ በአሁን ሰአት አባላት በንቃት እየተሳተፉ አይደለም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
ፓርቲው አሁን ከገባበት ችግር አንፃር እየተዳከመ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…
ፓርቲው ተዳክሟል ማለት አልችልም፡፡ ሊቀመንበሩ እኔ ነኝ፤ አሁን ያሉት ስራ አስፈጻሚዎች በትምህርት ደረጃቸውም የተሻሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ሰማያዊ ውስጥ ስራ የሚያሰራ ሁኔታ የለም። ወደ ስራ እንዳንገባ ልዩ ተልዕኮና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች፣ እለት በእለት ትጉህ አባላትን በመክሰስ፣ በመደብደብ፣ የማይሆን ስም እየሰጡ በመፈረጅ ተጠምደዋል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ከመስከረም ጀምሮ ስራ መስራት አልተቻለም፡፡ በእስር ቤት ያሉ የፓርቲው አባላትን ጭምር አባረናል የሚል ውሳኔ ሁሉ ተወስኗል፡፡ ቀደም ሲል አራት አባላት ተባረዋል ተባለ፡፡ ከዚያ አይባረሩም ተባለ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ አባረናል የሚል ውሳኔ እየሰማን ነው። ከዚያም አልፎ እኔንም አባረንሃል እየተባለ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ስራ መስራት የሚቻለው?
የዲሲፕሊን ኮሚቴው በፓርቲው ውስጥ ያለው ስልጣን ምን ድረስ ነው?
እኔም ግራ የገባኝ ይሄው ነገር ነው፡፡ ብዙዎቹ በኮሚቴው ውስጥ ያሉት የአቅም ችግር አለባቸው። የህግ ትምህርት ያለው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ እሱም በብዙዎች ውሳኔ የሚዋጥ ነው፡፡ መስራት አልቻለም፡፡ ሌሎቹ ግን የትምህርት ደረጃቸውም ሆነ እውቀታቸው የሚያወላዳ አይደለም፡፡ ከዚያም ባለፈ ሆን ብሎ አባላትን ለመጉዳት የመንቀሳቀስ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ “የለሁበትም፤ውሳኔ አልሰጠሁም” እያለ ሰዎች በሌሉበት ነው ወሰንን የሚሉት፤ ህገ ወጥ ውሳኔዎች ናቸው የሚደረጉት፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች የአባላትና የደጋፊዎቻችንን ስነ ልቦና እየጎዱ ነው፡፡
የኮሚቴው ስልጣን ምን ድረስ ነው?
እኔ በጠቅላላ ጉባኤ ነው የተመረጥኩት፡፡ ውሳኔያቸው ላይ ካየኸው “ተባሯል ግን ለጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ይቀርባል” ነው የሚለው፡፡ ሊቀ መንበር ከሆንኩ ይሄ ነገር ለምን አስፈለገ፡፡ ተባሯል የሚለውን ማለቴ ነው፡፡ ይሄ ሆን ተብሎ የእኔን ሰብዕና ለማጉደፍ የሚደረግ ነው፡፡ ሆን ብለው የህዝቡን ልብ ለመስበር የሚደረግ ጥረት ነው እንጂ ይሄን ያህል የተሰጠው ስልጣን የለም፡፡ እኔን የመረጠኝ ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
የሁሉም መነሻ እርስዎን ጨምሮ ለምርጫ የተመደበን ገንዘብ መዝብራችኋል የሚል ክስ ነው … በእርግጥ የተባለው ድርጊት ተፈፅሟል ?
አንድ በግልፅ የምነግርህ ጉዳይ ይሄ ነገር ሆነ የተባለው በ2005 ዓ.ም ነው፡፡ አሁን 2008 ላይ ነው ያለነው፡፡ በ2007 ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ገቢና ወጪ ላይ የጠፋ ገንዘብ እንደሌለ ተማምነን፣ ያ ሰነድ ፀድቆ ለምርጫ ቦርድ ገብቷል፡፡ አሁን ታዲያ የ2005 ክስ ለምን መጣ? ሲባል ምክንያቱ ግራ ያጋባል፡፡ አጠፋን የተባለው የገንዘብ ልክ እንኳ አልተጠቀሰም፡፡ እነዚህ ሰዎች ያለ ማስረጃ በሃሜት ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ እኛ በፍ/ቤት ልንከሳቸው እንችላለን፡፡ መጨረሻ ላይ መረጃ ሲያጡ፣ ባልታወቀ የገንዘብ መጠን ምዝበራ ተባራችኋል ነው ያሉት፡፡
165 ሺህ ብር ተብሎ የተጠቀሰውስ ?
ኧረ ምንም ነገር የለም፡፡ የቅጣት ውሳኔያቸው ላይ “ገና በኦዲት ሪፖርት ሲደረግ የሚወሰንባችሁን በሁለት ወር ውስጥ ትከፍላላችሁ” ነው የሚለው፡፡
እርስዎ ያጠፋሁት ምንም ገንዘብ የለም እያሉ ነው?
አዎ እኔ ምንም ያጠፋሁት ገንዘብ የለም፤ክስም አልቀረበብኝም፡፡ ከሳሽ ነው የተባለው አቶ ይድነቃቸው ከሰሞኑ በፌስቡክ ገፁ ላይ “እኔ አልከሰስኩም፤ ክሱንም አልተከታተልኩም” ብሏል። ታዲያ ክስ ሳይኖር ፍርድ አለ? ምስክር ከየት መጣ? ዳኛውም ከሳሹም የዲሲፒሊን ኮሚቴው ነው ማለት ነው? ከሳሽ የተባለው ሰው አልከሰስኩም እያለ ክሱ ከየት መጣ? እንደውም “ይሄን ነውረኛ ተግባር ሊቀመንበራችን መናገር ያለበት አሁን ነው” ብሎ ነው የጻፈው፡፡ ታዲያ ከሳሽ ሳይኖር ፍርድ አለ?
የዲሲፒሊን ኮሚቴው ይሄን ሁሉ ግድፈት ሰርቶ ፓርቲውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚል እምነት ካላችሁ፣ የፓርቲው ማዕከላዊ ም/ቤት ለምን ዝምታን መረጠ?
እንግዲህ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚባለውን እኔ አላቋቋምኩም፡፡ ኦዲትና ኢንስፔክሽን የሚባለው ነው ያቋቋመው፡፡ እኛ አናውቀውም፡፡ ይሄን ሁሉ ስህተት ሲሰሩ ዝም ያላቸው እሱ ነው፡፡ መቆጣጠርና መከታተል ያለበት እሱ ነው፡፡ ትልቁ ስህተት የኦዲትና ኢንስፔክሽኑ ነው፡፡  የሚመለከተው እሱን ነው፡፡
ሌላው ሊቀመንበሩ በቢሮ ተገኝቶ አያውቅም፣ ስራ አስፈፃሚውንም ስብሰባ ጠርቶ አያውቅም፣ በአጠቃላይ ፓርቲውን ትቶታል የሚል ክስም ይቀርባል?
ይሄ ውሸት ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚው በየጊዜው ይሰበሰባል፣ ስራውን ይሰራል፡፡ ነገር ግን ፅ/ቤት ውስጥ አንድ ችግር አለ፡፡ የፅ/ቤት አገልግሎት ኃላፊው ማህተሙን ይዞ አለቅም ብሎ ቁጭ ብሏል። ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ የፓርቲውን ንብረት አስረክብ ተብሎ አሻፈረኝ ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ሰውዬ ደሞዝተኛ ነው፡፡ ለፅ/ቤት ሰራተኞች ደሞዝ ይከፍላል፣ ቼክ ላይ ይፈርማል፣ ከ10 ሺህ ብር በታች የሆኑ ወጪዎችን ያንቀሳቅሳል፣ የስራ አስፈፃሚውን ቃለ ጉባኤ ይይዛል፡፡ ይሄ ነው የሱ ስራ። አሁን እነዚህን ሁሉ ስራዎች እየሰራ አይደለም። ቢሮውንም አለቅም፤ማህተሙንም አልሰጥም ብሎ ቁጭ ብሏል፡፡ ፅ/ቤቱን የምመራው እኔ ነኝ፤ በሌላ አነጋገር ይሄ ሰውዬ ለኔ አይታዘዝም ማለት ነው፡፡ እንደውም አምባጓሮ በመፍጠር ሰዎችን ይዞ እየመጣ ድብድብ መፍጠር ጀመረ፤ ስለዚህ እኔ እንዲህ ያለውን ነገር አልፈልግም፣ቢሮ ባልገባም ባለሁበት ሆኜ የፓርቲዬን ስራ እሰራለሁ፤ ስራ አስፈፃሚውን እሰበስባለሁ፤ ለሚዲያ መግለጫ እሰጣለሁ፤ በአጠቃላይ ፓርቲዬን ወክዬ እየሰራሁ ነው፡፡ ፅ/ቤት ግን መግባት አያስፈልገኝም፡፡
አንድ የፅ/ቤት ሰራተኛ ማህተም አላስረክብም ሲል አመራሩ እንዴት ማስቆም ይከብደዋል?
አመራሩ ምን ያድርግ?!
በህግ ጠይቆ ማህተሙን ማስመለስ አይችልም?
እሱ እንግዲህ ወደ ህግ እንሂድ ቢባል ይቻላል፤ ነገር ግን ወደ እነዚህ ተቋማት ብንሄድ ችግሩን የበለጠ ነው የምናሰፋው፡፡ የህግ አስከባሪ የሚባሉት ተቋማት ደግሞ እንደማይረዱን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በፊት በተለያዩ ፓርቲዎች ላይ የተፈጠረውን አይተነዋል፡፡ ይሄ ሰውዬ ይሄን ያደረገበት የራሱ ምክንያትና አላማ ይኖረዋል፡፡
ለምንድነው ከኃላፊነት እንዲነሳ የተወሰነው?
በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ተወዳድሮ የፓርቲው የምክር ቤት አባል ሆኗል፤ በደንባችን መሰረት ደግሞ የም/ቤት አባል የሆነ ሰው የፅ/ቤት ኃላፊ ሆኖ መስራት አይችልም፡፡ ስለዚህ ይሄ ሰውዬ በራሱ ጊዜ ነው የፅ/ቤት ኃላፊነቱን የለቀቀው፡፡ እኔ አይደለሁም ልቀቅ ያልኩት፤ የፓርቲው ደንብ ነው እንዲለቅ ያስገደደው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የፓርቲው ማህተም ህገ ወጥ ስራ ቢሰራበትስ?
እንግዲህ ምን እናድርግ እኛ! ወይ ፍርድ ቤት ወይ ምርጫ ቦርድ መሄድ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሚሆን አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብቶ ፓርቲዎችን ለብዙ  ችግር ሲዳርግ ነው የምናውቀው፡፡ ስለዚህ ያለኝ አማራጭ ------ ድብድብ ከመፍጠር በውጭ እየሰራሁ ፓርቲው ወደነበረበት የሚመለስበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ እኔ ፓርቲው ውስጥ የገባሁት ለግብግብና በጠመንጃ ጉልበት ለመታገል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ነገሩን ለመሸሽ በውጪ የምሰራው፡፡
ችግር ፈጥረውብናል የምትሏቸው ሰዎች አላማቸው ምንድን ነው ትላላችሁ?  
እኔ የደረስኩበት ድምዳሜ፣ የእነዚህ ሰዎች አላማ ፓርቲውን ማዳከም ነው፡፡ ፓርቲው ስራውን እንዳይሰራ በማድረግ፣ የነበረውን ጠንካራ እንቅስቃሴ መግታት ነው፡፡
ፓርቲው ከመዳከሙ የተነሳ ለቢሮ ኪራይ የሚከፍለው በወር 18 ሺህ ብር አጥቷል እየተባለ ነው፡፡ ይሄስ እውነት ነው?
ሰማያዊ በብዛት በውጭ ሀገር በህጋዊነት የተመዘገቡ የድጋፍ ሰጪ ማህበራት አሉት፡፡ እነዚህ በድጋፍ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው፤ነገር ግን በአደባባይ አባላት እየተዘላለፉ፣ ንቁ አባላት እየተባረሩ ----- በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለሰማያዊ ገንዘብ ለማሰባሰብና ለመርዳት እንቸገራለን ብለው ያለቻቸውን ገንዘብ ከ3 ወር በፊት ላኩ፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር ነች፡፡ ከዚያ በኋላ አልላኩም፡፡ የማይረዱበትን ምክንያት፣ ፓርቲው እርስ በእርሱ እየተወነጃጀለና ስም እየተጠፋፋ በመሆኑ ነው ብለው በግልፅ ተናግረዋል፡፡ እውነትም ነው! ሰው ገንዘቡን የሚሰጠው ትግሉ እንዲሳካ፣ በአንድ አላማ ተሰልፈን እንድንታገል ነው፡፡ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች የሚፈልጉት ደግሞ ይሄ እንዳይሳካ ነው፡፡
ፓርቲው በእንዲህ ያለ ቀውስ ውስጥ መግባቱ አባላቶቻችሁንና ደጋፊዎቻችሁን ተስፋ እያስቆረጠ አይመስልዎትም?
አይ፤ አባላትን በተመለከተ አሁንም ቢሆን ስራ ለመስራትና በንቀት ለመሳተፍ ፍላጎታቸው እንዳለ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለቅቄያለሁ የሚል ሰው አላየሁም፡፡ ዮናታንም ቢሆን ከኃላፊነቱ ነው እንጂ የለቀቀው ከፓርቲው አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን በእስር ላይ እያለ ከፓርቲው ተባረዋል የተባሉት 4 የፓርቲው አባላት መጀመሪያ የተወሰነው ውሳኔ ችግር አለበት ተብሎ በፓርቲው ይቀጥሉ ተብሎ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በድጋሚ አባረናቸዋል ተብሏል፡፡ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ሰው ሞራሉ ቢነካ ምን ይገርማል፡፡ እኔን ጨምሮ ቢሮዬን መጠቀም እስከማልችልበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ ነገሮችን እስካሁን ይፋ ሳናደርግ የቆየነው ለህዝብ ካለን ክብር የተነሳ ነው፤አባላትና ደጋፊዎቻችን በስነ ልቦና እንዳይጎዱ በማሰብ ነበር፡፡ ይሄ ነገር አሁንም ቢሆን መፍታት ካልተቻለ፣ ፓርቲውም አስፈላጊ የማይሆንበት ደረጃ ይደርሳል ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየጊዜው እርስ በርስ እየተጠላለፋችሁ ስትፈርሱ፣ ይደግፈናል የምትሉትን ህዝብ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይመስልዎትም?…
በተለይ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ እንደዚህ መሆን-
አሁን እኮ ችግሩ “የእናንተ እንዲህ መሆን ---” የሚለው ነገር ነው፡፡ እኔና የስራ አስፈፃሚ አባላት በሙሉ ልብና በሙሉ አቅም ነው እየሰራን ያለነው። ችግሩ ያለው ዲሲፒሊን ኮሚቴ የሚባለው ጋ ነው፡፡
የእኔ ጥያቄ የውስጠ ፓርቲ ችግራችሁን እንዴት በተረጋጋ መንገድ መፍታት አትችሉም ነው? የዲሲፒሊን ኮሚቴ ነው ችግር ፈጣሪ ካላችሁ ለምን አታስተካክሉትም?
ዲሲፒሊን ኮሚቴውን እንዲያስተካክል ለፈጠረው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እነዚህ ሁሉ አወዛጋቢ ውሳኔዎች ከመምጣታቸው በፊት ደብዳቤ  ፅፌያለሁ፡፡ እስከዛሬ የነበሩትን ድክመቶች አመላክቼ ጠንካራ ደብዳቤ ፅፌላቸዋለሁ፡፡ እንግዲህ ያንን ተመልክተው የእርምት እርምጃ ይወስዳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በሰማያዊ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በማንኛውም ፓርቲ ውስጥ የሚያጋጥም ተራ ግጭት ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል?
አይቻልም፤ ምክንያቱም ይሄ ሆን ተብሎ ታስቦና ታቅዶ እየተሰራ ያለ ሴራ ነው፡፡
የቢሮአችሁ ቀጣይ እጣ ፈንታስ ምንድን ነው?
በኔ እምነት ገንዘብ አይጠፋም ብዬ አስባለሁ፤ ፓርቲው ከጠነከረ ብር ያገኛል፡፡ ነገር ግን በዚህ ችግር ከዘለቀ ገንዘብ ማግኘት አይችልም፤ያኔ ቢሮ አልባ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ፓርቲው የመፍረስ አደጋ ላይ ነው ማለት ይቻላል?
ህጋዊ ሰውነቱን የሚያጣ አይመስለኝም፡፡ እዚህ ሀገር የማይፈጠር ነገር የለም፡፡ ጉዳዩ ምርጫ ቦርድ ዘንድ ቢሄድ የሚፈጠረውን መገመት ቀላል ነው፡፡ ፓርቲዬን ከመፍረስ ለመታደግ  በምንችለው አቅም ጥንቃቄ እያደረግን ነው፡፡
ላለመበታተን ምን ዋስትና አላችሁ?
ምንም ዋስትና የለንም፡፡ እዚህ ሀገር ህግ ዋስትና አይደለም፤ ኢህአዴግ የፈለገውን ነገር ማድረግ የሚችልበት ሀገር ነው፡፡ እኛ ግን ለህሊናችን ተጠንቅቀን የምንችለውን ሁሉ እንሰራለን፡፡
በቀጣይ እንግዲህ ኦዲትና ምርመራ፣ እጣ ፈንታችሁን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል … እንዴት ትቀበሉታላችሁ?
ኦዲት ከዚህ በኋላ በእኛ ላይ መወሰን የሚችለው ነገር የለውም፡፡ ምክንያቱም ከሳሽ የተባለው ግለሰብ አልከሰስኩም ባለበት ሁኔታ ምን ውሳኔ ይመጣል? ክስ በሌለበት የምን ውሳኔ ነው የሚጠበቀው፡፡ ማን ከሶኝ ነው የሚፈረድብኝ? ኦዲት አሁን ላይ ምንም የሚመረምረው ጉዳይም ሆነ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የለም፡፡ ከነሱ የሚጠበቅ ምንም ውሳኔ የለም፡፡
ፓርቲያችሁን ከቀውስ ለማዳን የምትወስዱት የመጨረሻ እርምጃ ምንድን ነው?
እንግዲህ የመጨረሻው መፍትሄ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ፣ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ እየፈጠረ ያለውን ችግር አስረድቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ነው። ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን ችግሩን የፈጠረው አካል እንዲሻር ማስደረግ ብቻ ነው መፍትሄው፡፡
ጉባኤውን ለመጥራት ታዲያ ለምን ዘገያችሁ?
ጉባኤያችንን ያደረግነው በቅርቡ ነው፡፡ በድጋሚ መጥራት ከአቅም አንፃር አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡ አሁን ግን ችግሮቹ እያፈጠጡ ስለሆነ ጉባኤ መጥራቱ የግድ ይሆናል፡፡
ጉባኤው መቼ ይደረጋል?
ችግሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሆናል፡፡
በዚህ ዓመት ይሆናል?
አዎ የግድ ነው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የወደፊት እጣ ፈንታ ምንድነው?
እርግጥ ነው ፓርቲያችን ችግር አጋጥሞታል፤ግን የፓርቲውን መሰረታዊ ነገር የሚጎዳ ነው ብዬ አላምንም፤ሆኖም የፓርቲውን ስራ እንዳንሰራ ተሰነካክለናል፡፡ ፓርቲው ጉባኤ ካደረገ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናከራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከተቃዋሚዎች ጋር በተወያዩበት መድረክ ላይ ያልተገኛችሁት ለምንድን ነው?
አልተጠራንም፡፡ የሚጠሯቸው ከኢህአዴግ ቀለብ የሚቆረጥላቸውን ነው፡፡ በአለም ታሪክ ተቃዋሚ ከገዢ ፓርቲ ቀለብ የሚቆረጥለት በኛ ሀገር ብቻ ነው፡፡


አንድ አርሶ አደር በአጥር ግቢው ውስጥ አንድ የፍሬ ዛፍ ነበረው፡፡ ሆኖም ይሄ ዛፍ ፍሬ አላፈራም፡፡ ስለዚህም አርሶ አደሩ፣
“አንተ ዛፍ፤ስንት ዓመት ሙሉ ደጃፌ ቆመህ አንዲት ፍሬ እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፡፡ አሁን መቆረጫህ ሰዓት ደርሷል - ተዘጋጅ!” አለው፡፡
በዛፉ ላይ በየቅርንጫፉ ውስጥ የሚኖሩና በጥላው የሚጠቀሙ ድንቢጥ ወፎችና አንበጣዎች አሉ፡፡ እነሱ ማረፊያቸው ሊፈርስባቸው ስለሆነ፤
“እባክህ ይሄንን ዛፍ አትቁረጥብን፡፡ መጠጊያ ታሳጣናለህ፡፡ ዛፉ የኛ መኖሪያ ከመሆኑም በተጨማሪ ለአካባቢው ጥላ ይሆናል፡፡ ነፋሻ አየርም ያመጣል” እያሉ ለመኑት፡፡
አርሶ አደሩ ግን “ምንም የማያፈራ ዛፍ ተሸክሜ አልኖርም” ብሎ መጥረቢያ ሊፈልግ ሄደ፡፡ ከልቡ ሊቆርጠው ወስኗል፡፡ መጥረቢያውን አግኝቶ መጣ፡፡ አንበጦቹና ድንቢጦቹ ደግመው ለመኑት፤
“እባክህ አያ አርሶ አደር፣ ዛፉን በመቁረጥ ምንም አትጠቀምም፡፡ ይልቁንም አያሌ ነብሳት ማደሪያ ያጣሉ፡፡ በጠዋት የሚዘምሩ ወፎች አትክልትህን ስትኮተኩት እያጀቡ ህይወትህን ያለመልሙልሃል” ሲሉ አወጉት፡፡
አጅሬ አንደኛውን ጨክኗልና ምክራቸውን አልሰማ አለ፡፡ የዛፉን ግንድም በመጥረቢያው ይመታው ጀመር፡፡ ደግሞ፣ ሰልሶ ሃይ - በል ካለው በኋላ፣ የዛፉ ውስጡ ይታይ ጀመር፡፡ በራሱ ባዶ ነው፡፡ ቀፎ ነው፡፡ ሆኖም ውስጡ ግን የንብ መንጋ ይኖር ኖሯል፡፡ በንቦቹ ዙሪያ ከባድ የማር ክምችት አለ፡፡ የዚያ ዛፍ ሆድ ዕቃ ለካ ከባድ የማር መጋዘን ኖሯል፡፡ አርሶ አደሩ በደስታ መጥረቢያውን ጥሎ ማሩን ተመለከተ፡፡ ነገር ግን ወዲያው ሀዘን ገባው፡፡
“ወይኔ! ወይኔ!” አለ፡፡ “ይህን ግንድ በህይወት ማቆየት ነበረብኝ፡፡ ውስጡ ምን እንዳለ ሳላውቅ፣ ለስንት ዘመን ማር የሚያጠራቅምልኝን ዛፍ ቆረጥኩት፡፡ ትልቅ ሀብት አፈረስኩኝ!” አለ፡፡
*        *          *
ታላላቅ ያገር ይዞታዎችን፣ የጥንት ታሪካዊ ቅርሶችን፣ በችኮላ ካፈረስን ለከባድ ፀፀት ሊዳርገን ይችላል፡፡ ውስጡ ያለውን እንመርምር፡፡ ብዙ ቅርሶቻችን የዘመናት ፍሬዎቻችን ናቸው፡፡ አንድ ነባር ዋርካ ሲወድቅ፣ በዙሪያው ያሉ የንፍቀ ክበቡ ነዋሪዎች ጥቅም ጭምር ይወድቃል፡፡ ሳናውቀው የብዙ ማህበረሰብም ኑሮ ሊናጋ ይችላል፡፡ ግንባታን ስናስብ ፍርሳታውን፣ አልፎም ልማታዊ ግቡን አበክረን ካላየን ጉዳቱ ሊበዛ ይችላል፡፡ በጥናት፣ በብልህነትና በጥንቃቄ መሰራት ያለባቸውን ነገሮች አስተውሎ ማየት ዋና ነገር ነው፡፡ ሌላው መሰረታዊ ነገር የቅርሶች አጠባበቅ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አስጊው ነገር ደሞ መዘረፋቸው ነው፡፡ ዘረፋ ደግሞ ባህል ሆኗል፡፡ “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለው የድሮ ተረት፣ ዛሬ የዕለት - ሰርክ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ጥንቃቄ የሚሻው ይህ ጉዳይ ነው፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል! የአየር ጠባይ መለዋወጡን አለመዘንጋት እጅግ ብልህነት ነው፡፡ ትላልቅ እርሻዎቻችንን መጪው የአየር ንብረት ለውጥ ምን አደጋ ላይ እንደሚጥላቸው ከወዲሁ በንሥር - ዐይን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ለሁሉም ነገር በሁሉም አቅጣጫ “መረጃም ማስረጃም ይኑረን” የተባለው እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ፍሬ ነገር በእጃችን ያለ እየመሰለ በአፍታ ከእጃችን ያመልጣል፡፡ ተቋሞቻችን የማይናዱ ግንቦች ይመስሉንና ውስጣቸው እየተሸረሸረ አንድ ቀን ባዶ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ዲሞክራሲ ጠንካራ ተቋማት ላይ ካልቆመ አብሮ ፈራሽ ነው፡፡ እንኳን እንደኛ አገር በአዲሱ ወለል ላይ መሰረት የሚቸክል ቀርቶ የበለፀጉትም አገሮች ስንቴ ወድቀው ስንቴ ተነስተው፣ ልብ - አድርስ የሚባል የዲሞክራሲ ዋንጫ አልጨበጡም፡፡ እነሱም ጋ ዛሬም ሙስና አለ፡፡ እነሱም ጋ ዘረኝነት አለ፡፡ እነሱም ጋ የኢኮኖሚ ድቀት (Economic Crisis) አለ፡፡ ይሄ የሚያሳየን የእኛን ዲሞክራሲና ኢኮኖሚ በቀላል ሊወድቅ መቻል ብቻ ሳይሆን፤ የእነሱንም ትኩሱን እፍ - እፍ ሳንል እንዳናጋብስና መሸፈኛውን ገልጠን እንድናይ ነው፡፡
የጥንት ታዋቂ ፖለቲከኞች፤ “ፖለቲካ የኢኮኖሚው ጥርቅም መገለጫ ነው” ይላሉና እያንዳንዷን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አጥርተን ካላየን፣ በፖለቲካ መልክ ብቅ ስትል ማህበራዊ ቀውስን ጭምር አመላካች ትሆናለች፡፡ ለህዝብ የምንገባውን ቃል ተጠንቅቀን ካልሆነ ያስተዛዝባል፡፡ አገርን በሰላም መምራት “እራሱን ያልገዛ፣ አገር አይገዛ” ከሚለው ብሂል ጋር በእጅጉ የተሳሰረ በመሆኑ የራስን ጥንካሬ በየጊዜው መመርመር የግድ ያስፈልጋል፡፡
“ቃል የእምነት ዕዳ” ነው ይላልና ገጣሚው ቃላችንን እንጠብቅ፡፡ የህግ የበላይነት ካልን ከሱ በላይ ምንም እንደሌለ እናረጋግጥ፡፡ በወገን አንሰራም ካልን ዘር፣ ሃይማኖት፣ አብሮ አደግ አናፈላልግ፡፡ የትግሪኛው ተረትና ምሳሌ ይሄንን በአፅንዖት ይገልፀዋል፡፡ እንዲህ ሲል፡-
“እወድሃለሁ እያለ የሚጠላ፣
እፆማለሁ እያለ የሚበላ፣
እሰጣለሁ እያለ የሚነሳ፣
እነዚህን አምላክ ይጠላ”፡፡
በአደባባይ ቃል መግባት በአደባባይ መጠየቅን ነው የሚያመለክት፡፡ በየሚዲያው ለውዳሴም ሆነ ለቅዳሴ ብለን የምንገባውን ቃልና ኋላም አፈፃፀም በጥንቃቄ እናስተውል፡፡

 - ባለፈው አመት በቻይና ከ1ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል
              - የሞት ቅጣት የሚፈጸምባቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል
     አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ባለፈው የፈረንጆች አመት 2015፣ ዜጎችን በሞት በመቅጣት ቻይና ከአለማችን አገራት ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘችና አገሪቱ በአመቱ የሞት ቅጣት የተጣለባቸውን ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሏን ገለጸ፡፡
ባለፈው አመት 2015 የሞት ፍርዶችን በማስተላለፍና ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል ያለው ተቋሙ፣ ቻይናን ሳይጨምር በአመቱ በአለማችን ከ1ሺህ 634 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ በግማሽ መጨመሩን መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በአመቱ በኢራን 977 ያህል ሰዎች መገደላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ አብዛኞቹ ሰዎች የተገደሉትም ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ በተመሰረተባቸው ክስ በተላለፈባቸው የሞት ፍርድ ውሳኔ ነው ብሏል፡፡
በ2015 አመት ብቻ በፓኪስታን 326፣ በሳኡዲ አረቢያ 158፣ በአሜሪካ 28፣ በኢራቅ 26፣ በሶማሊያ 25፣ በግብጽ 22፣ በኢንዶኔዢያ 14 እና በቻድ 10 ሰዎች በተለያዩ የወንጀል ክሶች ሳቢያ በሞት መቀጣታቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ ታውቋል
     ታዋቂው የሞባይልና የኮምፒውተር አምራች ኩባንያ አፕል፣ በ5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የዓለማችንን ምርጥ የቢሮ ህንጻ በካሊፎርኒያ እየገነባ መሆኑን ዘ ዴይሊ ሜይል ዘገበ፡፡ ግንባታው በመገባደድ ላይ የሚገኘው የአፕል ዋና መስሪያ ቤት የግንባታ ስምምነት የተፈጸመው ከ6 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ህንጻው በ260 ሺህ ስኩዌር ሜትር ቦታ ላይ ማረፉንና 13 ሺህ ያህል ሰራተኞችን መያዝ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
በክብ ቅርጽ ለተሰራውና የዙሪያ መጠኑ 1.6 ኪሎሜትር እርዝማኔ ላለው ለዚህ ግዙፍ ህንጻ የሚገጠሙት መስኮቶች በአለማችን በግዙፍነታቸው ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ የተነገረ ሲሆን የግንባታው ወጪ 3 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ቢጀመርም ወጪው እየጨመረ መጥቶ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ዘገባው ገልጧል፡፡
1 ሺህ መኪኖችን የማስተናገድ አቅም ያለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በሚኖረው በዚህ ህንጻ ግቢ ውስጥ 7 ሺህ ያህል ዛፎች መተከላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ግንባታው በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡