Administrator

Administrator

የቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ግለ-ታሪክ ሲመረቅ በልጃቸው ጥያቄ መሰረት ተጋብዘው የነበሩ አንድ አንጋፋ የሀገራችን ምሁር ይሄን በማለት የሰውዬው የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ለሌሎችም አብነት መሆን እንደሚገባው ለማስረዳት ሞክሩ፤… [አበሾች ዘንድ ስለ ግለታሪክ ህይወታችን የመጻፍ ልምድ ባለመኖሩ ታሪክ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ፈረንጅ ለአንድ ትንሽ ነገር ትልቅ መጽሐፍ ይጽፋል፤ ሀበሻ ተራራ የሚያህል ታሪክ ይዞ መቃብር ይወርዳል፡፡]
የኛ ታላላቆች ያለፉበትን ታሪክ ለመጻፍ የመቸገር ጣጣ እዚህች አጭር አረፍተ ነገር ውስጥ ተጠቃሎ በምልአት ተገልጧል ማለት ይቻላል፡፡ አዎን! ታሪክ ውቅያኖስ ነው፡፡ ባህር አይለይም፣ ገባር ኩሬዎችን አይመርጥም፡፡ ባደጉ ሀገሮች ደግ የሰራ ሰው ብቻ ሳይሆን ክፉ የሰራ ግለሰብም ቢሆን ታሪኩ ይጻፋል፡፡ አዶልፍ ሄክማን ይቆየንና፤ ሂትለር ሁለተኛ የአለም ጦርነትን ከመቀስቀሱም ባለፈ ብዙ ሚሊዮኖችን በግፍ ገድሏል፡፡ ይሁንና በሱ ላይ አያሌ የታሪክ መጻሕፍት ከትላንት እስከ ዛሬ ተከትቧል፡፡ በሀገራችንም በተመሳሳይ ባይሆንም እንኳን በግፍ ግብራቸው የንጹሀንን እንባ ያፈሰሱ፤ አያሌ ባለቱባ ታሪክ ባንዳዎችን በዝርዝር መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር የነሱ ታሪክ ታስሶ መፃፍ አልነበረበትምን? ሌላው ቀርቶ የደርጉን ሳዲስት፣ (ሳዲሰቶች ሌሎች ላይ በሚፈጽሙአቸው የጭካኔ ድርጊቶች ደስታን የሚያገኙ ሰዎች ናቸው፡፡) ‹‹አብዮታዊ ውሳኔ›› በሚል ስም የስንት ምስኪንና ንጹሃን የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ህይወት የቀጠፈው ግርማ ከበደ፣ ታሪኩን በቁንጽል ካልሆነ በስተቀር በዝርዝር ሰንዶ ማን አቆየልን! መቼ አነበብነው - የት ተማርንበት - ማንንስ አስተማርንበት - ትውልድ ለመቀጣጫ እንዲያውቀውስ ለምን አላደረግነውም? በወቅቱ ሰዎች ከፍርድ ቤት ውጭ በደርግ ውሳኔ፤ በቀበሌ ፍርድ ሸንጎ ውሳኔ፣ በአብዮትና በዘመቻ ኮሚቴ ፍርድ እንደ ቀልድ ይገደሉ ነበር፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ የሚወሰኑት፣ የሚወሰዱት የእስራትና የግድያ እርምጃዎች ደግሞ አብዮታዊ ውሳኔ ይባሉ ነበር፡፡ እንግዲህ ግርማ ከበደ ሰዎችን የገቡበት ገብቶ አድኖ የሚገድል ሊቀመንበርና የደርግ ካድሬ ነበር፡፡ የጭካኔውን ደረጃ ቃላት የሚገልጹት አይደሉም፡፡ ሰውዬው እንኳን በግንባር ታይቶ ስሙም ሲጠራ ያስፈራል፣ ያስበረግጋል፡፡ የቅርብ ጓደኞቹንና በትምህርት ቤት ወይንም በስራ ቦታ የሚያውቃቸውን ነገር ግን በራሱ ምክንያት የማይወዳቸውን ሰዎች አጋጣሚውን ተጠቅሞ እንደገደላቸው፣ አብዮታዊ እርምጃ እንደወሰደባቸው ይነገራል፡፡ በሚያውቃቸው ላይ ሰይፉ በዚህ ልክ መበርታቱ የቅናት ይሁን የምቀኝነት የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ በቀይ ሽብርም ይሁን በነፃ እርምጃ እስራቱን፣ ሰቆቃውን፣ ግድያውን ሁሉ የሚፈጽሙት በአዋጅ ህጋዊ ካባ በማልበስ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በግርማ አማካኝነት የደርግ ሰይፍ ካረፈባቸው ሰዎች መካከል ዳሮ ነጋሽ የተባለች የስምንት ልጆች እናትና የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር አንዷ ነበረች፡፡ ካለችበት ቦታ በድንገት ወስዶ ነብሰ ጡር እንደሆነች እያወቀ ነው የገደላት፡፡ ይህን የሰማ የአራት ኪሎ ህዝብ ሁሉ በንዴት ያብዳል፡፡ እናቶች በሰልፍ እየጮሁ ወደ ቤተ መንግስት ይሄዳሉ፡፡ ድርጊቱ እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝም ጭምር ስለነበረ የደርግ አመራሮች ይደነግጣሉ፡፡ ወዲያው ግርማ ከበደና ግብረ አበሮቹ እንዲያዙ ይደረጋል፡፡ በተያዘበት ጊዜ በቀጣይ የሚገድላቸውን ሰዎች ስም ዝርዘር የያዘ ሰነድ በእጁ ተገኝቶ ነበር፡፡ ከስሞቹ መካከል አንዱ አስራት ወልዴ የተባሉ የፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም አጎት ይገኙበት ሁሉ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ የዳሮ ነጋሽ ግድያ ይሁን፣ የአጎታቸው በስም ዝርዝር ውስጥ መገኘት አሊያም ደግሞ የእናቶች ጩኸት ተሰምቷቸው አይታወቅም… ግርማ በሞት እንዲቀጣ ፈረዱበት፡፡ ግርማ የመጀመሪያ ዲግሪ ነበረው፡፡ በባህሪው ትምህርት የገራው ሰው ግን አልነበረም፡፡ ትምህርት አንዳንድ ሰዎችን ከመጥፎ ባህሪያቸው እንደማይመልሳቸው ማሳያ ሞዴል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የተማሩና የተመራመሩ፣ ሀገርና ህዝብን ከፊት ሆነው የሚመሩ ሆነው ነገር ግን አስተሳሰባቸው ከራሳቸው ፍላጎት የማያልፍ፣ ድርጊታቸው የእንስሳና የአራዊት፣ የሚያደርጉት ሁሉ ለታይታ፣ ለክብርና ለዝና ብቻ የሆነ፣ ለጥቅማቸው ምንም ከማድረግ የማይቆጠቡ፣ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ባዮች ትላንት እንደ ነበሩ ሁሉ ዛሬም እንዳሉና ነገም እንደሚኖሩ ግልጽ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የሰው ልጅ የተማረም ይሁን ያልተማረ፣ ሰው በመሆኑ ብቻ ክፉን ከደግ የመለየት ፀጋ ከፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ መማር ደግሞ ይህንን ፀጋ የበለጠ እንዲያድግና እንዲበለጽግ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለሁሉም ግን አይደለም፤ ትምህርት አንዳንድ ሰዎች ዘንድ በተለይም ጨካኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮልና ሴራ፣ ምቀኝነት፣ ንፉግነትና ራስ ወዳድነት የተጠናወታቸው ላይ ሲደርስ አይደለም ማበልጸግ እስከናካቴው ያመክንዋል፡፡ የነዚህ ሰዎች የሀሳባቸውና የድርጊታቸው መነሻ ምንጭ አእምሮአቸው ሳይሆን በደመ ነፍሳቸው የሚመራ የግል ጉዳያቸው ምኞታቸውና ተራ የለት-ተለት ፍላጎታቸው ብቻ እንደሆነ በልሂቃን ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ልክ ትምህርትን የታከኩት አለምክንያት አይደለም፡፡ በቆቆ ቀበሌ እስከ ስልሳዎቹ አጋማሽ ድረስ በዩኒቨርስቲ ደረጃ የተማረ የአንድ ታላቅ ግለሰብ ህይወቱን፣ የተማሪነትና የትምህርት ጉዞውን፣ የፖለቲካ ተሳትፎውን፣ የእስር ዘመኑን ጨምሮ ለመመልከት ስለወደድኩ ነው፡፡…የመጀመሪያው የሀገራችን የትምህርት ስርአት እንዴት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ እንደሄደ እና አሁን ያለበትንም ተጨባጭ ደረጃ፣ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በይበልጥ ደግሞ የቅርብ ጊዜው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት የዚህን ማሽቆልቆል ጥግ በይፋ አሳይቶናል ሊባል ይችላል፡፡ ያ ትውልድ በዚህ ረገድ እድለኛ ነበር፡፡ ብዛትን የሚያጅበው የጥራት መጓደል ሰለባ አልነበረምና! መምህራኖቹ በሙያቸው ብቃት የነበራቸው ከመሆናቸው ባሻገር ተማሪዎቻቸውን (ከቤተሰብ ጥብቅ ክትትል ባልተናነሰ መልኩ) በቅርበት የሚከታተሉም ነበሩ፡፡ በንጉሱና በደርጉ ዘመን ከስልሳዎቹ መጀመሪያ እስከ ሰባዎቹ መጨረሻ ስርዓቶቹ ትውልዱን ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ከአማርኛ በስተቀር ሁሉንም ትምህርት በእንግሊዘኛ በማስተማራቸው፣ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት በቅተዋል፣ ችለዋልም፡፡ በተለይም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በርካታ ተማሪ ቤቶችን የምዕራቡ አለም ትምህርት ይቀሰምባቸው ዘንድ አመቻቹ፡፡ የድህረ አብዮቱ ቀንደኛ ተሳታፊና ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የእነ ዶ/ር መላኩ ተገኝ ትውልድ (ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳምን ልብ ይሏል) እራሱን በንባብ ያስታጠቀ በመሆኑ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባለመማራቸው አልተጎዳንም፣ አላጎደለንምም እሚሉ አባላቶቹ ጥቂት አይደሉም፡፡ ዛሬ-ዛሬ ትግላቸውን መለስ ብለው በመቃኘት ትዝታቸውን ያኖሩልን እንደነ ተድላ ድረሴ ያሉ፣ ያ የትምህርት ስርዓትና አስተሳሰብ ያፈራቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነጽሑፍ መምህር የሆነው ባዩልኝ አያሌው፤ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በዘመናዊ ትምህርት ዙሪያ ባዘጋጀው ጥናታዊ መጣጥፉ እንዳስነበበን፤ ”ሀገራችን የምዕራቡን አለም ስርዓተ ትምህርት ከእነ ቋንቋው የተቀበለችው ተማሪ ቤት አቁማ በመሆኑ በዚያው ቅጽበት ለዘመናት ማህበረሰብን በህግና በስርዓት፣ ከእውቀት ማዕድ ገሸሽ አደረገችው፡፡ ይሁንና የዘመናዊ ትምህርትን ያህል የሞራልና የስነምግባር እሴቶቻችንን በመጠበቅ ድርሻ ያለው ሌላ ያለ አይመስልም›› ሲል የደረሰበትን ድምዳሜ አስቀምጧል፡፡ (ቁጥር 1265.ሚያዚያ 5/2016)
ያ ትውልዶች በምዕራባውያን በአሜሪካና በሌሎችም ሀገሮች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተሉ እንጂ፣ ከጥልቅ ንባብ ባሻገር የተወያዩ፣ የተከራከሩ፣ የሞገቱና የተሞገቱ ምሁራን ነበሩ፡፡ በርግጥ ሀገር በቀሉን የህብረተሰብ ተጨባጭ የእውቀት ክፍተት ለማካካስና ለመሙላት ሲሉ ደግሞ በወቅቱ በእናት ቋንቋቸው በአማርኛ የተጻፉና የተሰነዱ ድርሰቶችን ከዳር እስከ ዳር በማገላበጥ ይተጋሉ፡፡ የታሪክ ተማራማሪ የሆኑት ባህሩ ዘውዴ በ‹ኅብር ህይወቴ› ግለታሪካቸው፣ የእስር ዘመናቸውን ባወሱበት ምዕራፍ ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፉ፤ ”በባእድ ቋንቋ ከተማርን በኋላ ለማጠናከር ዋና መንገድ ብዙ መጽሐፍ ማንበብ ነው!”…ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለው…‹‹በዚህ ረገድ በተለይ ልብ ወለድ መጽሐፍት ይመረጣሉ፡፡ ምክንያቱም የነሱ ስነቃል የሰፋ፣ አገላለፃቸውም የዳበረ ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህ በጣም የምንጠቀምባቸው ልብ አንጠልጣይ ልብወለዶችን ነበር፡፡ ከተፈታን በኋላ ትውስታ ስንለዋወጥ እኔ አንድ ቋንቋ ለማወቅ የሚያስፈልጉህ ሶስት ነገሮች ናቸው፤ እነሱም አንድ ጥሩ መዝገበ ቃላት፤ እና ብዙ የልብ ወለድ መጻሕፍት ስል እሸቱ ‹‹አንድ እስር ቤት ጨምርበት›› አለ፡፡ ( ገጽ.158 ) መምህር ተድላ ድረሴ ከነዚህ የቀለም ቀንድ ከሆኑ ከነባር የ-ያ ትውልድ ጉምቱ ምሁራን አባላት መካከል ግለህይወት ታሪካቸውን በቀላል ቋንቋ ሰንደውና አሰናድተው ያገኘናቸው፤ ከመጀመሪያዎቹም ረድፍ በጉልህ የሚጠቀሱ ግለሰብ ናቸው፡፡ የተማሪነትና የመምህርነት ረጅም ጉዞዋቸው የተዋቀረበት መጽሐፋቸው ለዚህ የዘመናዊ የቀለም ትምህርት ግስጋሴ ሁነኛ አስረጂ ነው፡፡ ባለታሪካችን ተድላ ከደብረ ብርሃን እና ጣርማበር አካባቢ፣ ከመንዝ ከምትጎራበተውና ጥቂት ኪሎ ሜትሮችንም እርቃ በምትገኘው ‹ቆቆ› በተባለች አነስተኛ መንደር ውስጥ ተወልደውና ተምረው ያደጉ ናቸው፡፡ ደብረሲና፣ ሰላድንጋይ…ሌሎችም አያሌ የተድላ ከልጅነት እስከ እውቀት የተከናወኑ የታሪክ ኩነቶች መነሻ ቦታዎች ናቸው፡፡ ቺቸሮ የተባለ ሮማዊ ተናጋሪና ደራሲ ‹ትምህርት›ን ከግሪክኛ ወደ ላቲን ሲተረጉም “(cultural animi) ትምህርት ህሊናን የማለዘብ፣ የማለስለስ የመንፈስ እርሻ ነው!” ብሎ ሰይሞታል፡፡ ተድላ መምህር ከመሆናቸው ቀድሞ በርሳቸው የልጅነት እድሜ ትምህርት ለማግኘት በልጆች ላይ ይደርስ የነበረውን የኑሮ ውጣ ውረድና እንግልት በስፋት ይዳስሳሉ፡፡ ከመንዝ ወደ ደብረብርሃን ልብስና ስንቅን ተሸክሞ ሁለት ቀን ያህልም ተጉዞ መማር፣ ከቁርና ከሀሩር፣ ከረሃብና ከህመም…ከሌሎችም ስቃዮች ጋር እየታገሉ ፊደልን መለየት ጠንቅቆ የሚያውቀው የቀመሰው ተድላ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዴ በሌሊት፣ በጨለማም ጭምር ጉዞ መጀመር ግድ ሆኖ በመሸበት ማደርም አለ፡፡ አዳሩ ደግሞ በየሰው ቤት ‹የመሸበት መንገደኛ አሳድሩኝ!› በማለት ተለምኖም ጭምር ነው፡፡ ቤት ለእንግዳ ብለው የሚያስተናግዱት ሰዎች ኑሮ እንደነገሩ ከሆነ የሚላስ የሚቀመስ ይጠፋና ጦም ማደርም ይኖራል፡፡ ለመተኛ የሚጎዘጎዝ ሳር ይቀርናም መሬት ላይ መተኛት ይከተላል፡፡ ቀኑን ሙሉ በመጓዝ ሰውነት ዝሎ፣ ረሃብ ሆድን እየሞረሞረ ማደር ይመጣል፡፡ ቆላና ወይና ደጋው ላይ ትኋኑና ቁንጫው አይጣል ነው፡፡ በዚያ ላይ የሚታደረው ብርዳማ አውራጃ ስለሆነ ውርጩ ይነጫል፡፡ ያልታሰበ ነገርም ሊያጋጥም ሁሉ ይችላል፡፡…
“ተማር አትማርም ወይ፤ እረኛ መሆን ይሻልሀል ወይ?፤ አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፤ የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል” … በርግጥ በዘመኑ የትምህርት ጠቃሚነትን፣መልካም ስነምግባርን የሚነግሩና ህብረተሰቡ ውስጥም የሚያሰርጹ እንዲህ ያሉ መዝሙሮች በተለያየ ዜማ የሚዘመሩበት፣ ተማሪው ከፍ ያለ ዋጋ ከፍሎ እንዲማር የሚያነቃቁበት፣ ሰልፍና መዝሙሮችም ለዚሁ ቅስቀሳ ሲባል በስፋት የሚደረጉበትም ነበር፡፡ ይሁንና ግን ችግሩ ት/ቤት በቅርብ አለመኖሩ፣ ህዝቡም ስለትምህርት አስፈላጊነት በቂውን ያህል ግንዛቤ ማጣቱ ብቻም አልነበረም፡፡ ማህበረሰቡ ልጁ ከብት ቢጠብቅለት፣ ሴት ከሆነች ደግሞ ብትዳርለት ነበር እሚወድደው፡፡ የድሃ ልጅ እንዳይማር የሚገድብና ትውልዱን ባጭር የሚቀጩ ደንቦች እንዳይኖሩ ጥቂት ቀለም የቀመሱ መምህራን ድምጻቸውን የሚያሰሙበት፣ መፈክራቸውን እያዘመሩ ሰልፍ የሚያስወጡበት፣ የሚያስነግሩበትም ነበር - እንዲህ… ‹‹ደሃ ደሃ ደሃ ምን ታየበት እንዳይማር የሆነበት››፡፡ ተድላም እናቱ ተምሮ ትልቅ ቦታ እንዲደርስላት ኑሮዋን ሰውታለች፣ የሞቀ ቤትዋን አፍርሳለች፡፡ ‹‹ትምህርት እና ቤተሰብ›› ሲል በሰየመው ንዑስ ርዕስ ስር እንዳሰፈረው፤ እናቱ የመኖርዋ ሰበብና እርካታ እሱ በትምህርት የሚደርስበት ትልቅ ደረጃ ብቻ ነበር፡፡ እንግዲህ ሰውዬው ተድላ በዚህ በተከፈለለት ከፍ ያለ ዋጋ፣ በግሉም ባደረገው ትንቅንቅ ውስጥ አልፎ ነው ቀለም ቀመስ ለመሆን የበቃው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከማስተማር ጎን ለጎን ከሰራቸው ስራዎች ሁሉ መምህርነቱን በፍቅር የሚወድደው፤…‹‹እኔ በመንፈሴ ምንጊዜም መምህር ነኝ፡፡ መምህር የነበርነው ሁሉ ስንገናኝ የምናወራው ስለ መምህርነት ህይወት ነው፡፡ ሌላ መስሪያ ቤትም እየሰራሁ በነበርኩበት ጊዜ ሁሉ የሚሰማኝ መምህርነቴ ነው፡፡ ትዝ ይለኛል በአንድ ስልጠና ላይ በዋናነት ለምን መምህር ለመሆን እንደፈለግን ሲጠይቁን ለዚህ የሰጠሁት መልስ፣ መምህርነት የተቀደሰ ሙያ ስለሆነ ነው አስተማሪ ለመሆን የፈለግሁት በማለት (“teaching is a very profession”)
ሲባልና እኛም ስንል ነው ከልጅነታችን ጀምሮ የምናውቀው፡፡ አስተማሪዎቻችን እንዲህ እያሉን ነው መምህርነታችንን የወደድነው፡፡ (ገጽ.153)
ተድላም በተራው ያልተማረ ወገኑን መልሶ በእውቀት ነፃ ሊያወጣው ታጥቆ የተነሳው፣ ማልዶ የዘመተው እምብዛም ሳያረፋፍድ…ትምህርቱን ዳር ለማድረስ ብዙ ሳይገፋበት ነበር፡፡ ቀደም ብሎም የመንዝ ህዝብ በትምህርት ወደ ኋላ መቅረት ሲያሳዝነውና፣ ሲያስቆጨውም ኖሯል፡፡ ወደ መንደሩ በመዝመት በህዝቡ ልብ ውስጥ የእውቀትን ብርሀን በመለኮስ ሊያቀጣጥል ሲጥር በመጽሐፉ ምንባቦች ተዘግቦ ያጋጥመናል፡፡ በወቅቱ የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ተምረው የደረሱ ወጣቶችን መንግስት አስተማሪ ለመሆን መብቃታቸውን ተምሳሌት በማድረግ የአካባቢው ታዳጊዎችም ይሄን በማየት እንዲነቃቁ ለማስቻል ወደመጡበት ቀዬ በመመደብ በሞያቸው እንዲያገለግሉ ያደርጋቸውም ነበር፡፡ በዘመኑ አስተማሪ መሆን ቀርቶ ያስተማሪ ቤተሰብ፣ ያስተማሪ ዘመድ፣ ጎረቤትም መሆን ያስቀና ሁሉ ነበር፡፡ አስተማሪ በማንኛውም ስፍራ ጠርቶ ያናገረው ተማሪ እንደ እድለኛ ይቆጠራል፡፡ አስተማሪ ይከበራል፣ ከማንም በላይ በትልቅነት ይታያል፡፡ ከወላጅ በላይ ሁሉ ሳይታይ ይቀራል?! ሌላው ቢቀር የኛ ሙሽራ ባለድሪ ወሰዳት አስተማሪ›! ተብሎ ይዘፈን የነበረውን ያልሰማና ያላነበበስ ማነው?፡ ሰውዬው በቀለም ትምህርት እውቀታቸው የገፉ ጠቢብ ይሁኑ እንጂ መጽሐፋቸውን ስንመለከት ግን አካዳሚ ነክ ጉዳዮችን በሚዛንና በተገቢው ቦታቸው ላይ እንጂ አላግባብ በአወቅሁ ባይነት እያነሱ አያቸኩንም፡፡ በቲዎሪና በተራ ንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ የሰው ልጆችን ሁሉ በሚያቅፍ አስተምህሮት፣ በተግባራዊ ሳይንስ የተደገፈ የልምድ ችሎታ በመታገዝ ተሞክሮአቸውን እያዋዙ ያካፍሉናል፡፡ መልካሙንና ክፉውን ከሚያሳውቀው እውቀቶቻቸው፣ ከእውቀት ዛፍ ላይ እንግዳና ልዩ-ልዩ ፍሬዎችን እየቀጠፉ ያቀብሉናል፡፡
ከኢህአፓ ግንባር ቀደም አመራር አባላት መካከል አንዱ የሆኑትና የፖለቲካ እስረኛም የነበሩት ተድላ፣ ከካበተ የህይወት ልምዳቸው የሀገሪቱን ነባራዊም ሆነ ተጨባጩን አስተዳደራዊ ሁኔታና ክስተት በሚገባ በማጤናቸው ጠንቅቀውም እንደሚያውቁ ከሚያነሱዋቸውና ከሚሰነዝሯቸው አጥጋቢ አስተያየቶችና ግላዊ ምልከታዎቻቸው በቅጡ መረዳታቸውን እንገነዘባለን፡፡ የስነልቦና ውቅራቸው እንደዘመነኞቻቸው ትላንትናቸው ላይ ብቻ ያልተገታ፣ ለአሁናዊ ሀገራዊ ጉዳዮች በሩን ገርበብ አድርጎ ለመፍረድ የመቆም ጭምር ነው፡፡ መንዜው ተድላ የነገር ብልት በብቃት የሚያወጣ ሀሳቡን አፍታቶም፣ ሲያሰኘው አብራርቶም በአጭሩ መግለጥ የሚሆንለትና በቃላትም ቢሆን በቦታው ያልነበርነውን፣ ሁነቱና ድርጊቱ በተከናወነበት ጊዜ የሌለነውን አንባቢያን የማሳመንና የማግባባት አቅምና ልዩ ክህሎታቸውን በዚህ ህይወት ታሪክ ንባቤ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ መጽሐፉ በጥናት ላይ የተመረኮዙና በበቂ ማስረጃዎች የተደገፉ ተአማኒነት ያላቸው አያሌ የግለሰብ እውነተኛ ገጠመኞችን በውስጡ አካቷል፡፡ ቁም ነገር የሰሩ ነገር ግን ያልተነገረላቸውና ያልተዘመረላቸው ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን የዘመን ተጋሪ ጓዶቻቸውን እሚችሉትን እና እሚያውቁትን ያህል ሊመሰክሩላቸውም ጥረዋል፡፡ በጥቂት ዋና-ዋና አንኳር ርእሶች፣ በአያሌ ንዑስ ርዕሶች ተደልድሎ የተሰናኘ ተነባቢ ስራ ነው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ግለታሪክ እንደ ፖስት ካርድ እስቶሪ በአጫጭር፣ ቅልብጭና ቁልጭ ባለ አተራክና ውብ አቀራረብ ታትሞ ሳነብ ለኔ በግል ይሄ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
ያ ትውልድ በመባል የሚፈረጀው ወገን የሚታወቅበትና የሚለይበት አብዮታዊ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ተድላም ‹‹ፍፁም ነው እምነቴ የትግሉ ነው ህይወቴ፣ ብዝበዛና ጭቆና እስኪጠፋ ረሀብ ችግር አይፈታንም፣ የህዝቡ ታማኝ አገልጋይ የሰርቶ አደሩ ወታደር ነኝ››…መሰል የኢህአፓ የቃል ኪዳን የመዝሙር ስንኞች እየዘመሩ ማልደው ከተነሱ ጓዶቹ መሀል አንዱ ነበር፡፡ በእርግጥ ተድላና መሰሎቹ የህዝቡ ባለእዳ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለመሞት ቆርጠው ትግሉን የተቀላቀሉት ጦሙን እያደረ ያስተማራቸውን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት፣ ገበሬው የሚያርሰው መሬት ባለቤት እንዲሆን፣ ህብረተሰቡ ያለቆቹና የገዢዎቹ አሽከር ከመሆን ነፃ እንዲወጣ ለማስቻል በማሰብ ነበር፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ለራሳቸው የጎደላቸው ነገር የለም፡፡ በቂውን ያህል ተምረዋል፣ ነገም ደግሞ የፈለጉትን ስራ ሰርተው መኖር ይችሉ ነበር፡፡ ለዚህም ሲሉ ነው በፖሊቲካ ጀልባ ተሳፍረው፣ በፖለቲካ ባህር ላይ እየቀዘፉ... በዚህ የደርግን አገዛዝ ለመነቅነቅ፣ በዚያ ደግሞ ከመኢሶኖች ጋር በመተናነቅ፣ ብሎም አድሀሪያንን በመዋጋት ብዙ ፍዳ ያዩት፣ ብዙ ዋጋም የከፈሉት፡፡ በኢህአፓ አመራር ውስጥ በተፈጠረ መከፋፈል ሳቢያ እስከ ታች ድረስ ወዳሉት መዋቅሮች በመውረዱ ለእስር ከርቸሌ መውረዱ ይቅርና ለሞት የመዳረጉ አደጋ ሲበዛ የሰፋ ነበር፡፡ በእያንዳንዳቸው አባላት ላይ እያንዣበበና እየተጋረጠም መምጣቱ ገሀድ ነበር፡፡ ተድላም የዚህ ሰለባ ከመሆን አላመለጠም፡፡ እጁን በውዴታ በመስጠት ለመታሰር እንደማይፈቅድ ቀድሞ ለራሱ ቃል ገብቷል፡፡ ለነገሩ እሱ ብቻ አይደለም፤ ያ የኢህአፓ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበረው ትንታግ ትውልድ ጓዶቹ ከፊሉ ታስረው፣ ገሚሱም ደግሞ ሞተው ቀሪው ምንም ሳይሆን ሲኖር ሰላም እሚነሳቸውና እሚጸጽታቸው፣ የመንፈስ እረፍት እንደማይሰጣቸው እነሱም ደግሞ ከሁለቱ በአንዱ እስኪቀላቀሏቸው እንቅልፍ የሌላቸው የማይረጋጉ ትውልዶች እንደነበሩ ካገላበጥናቸው የትውልዱ ታሪካዊ መዝገቦችና ማስታወሻዎች አስረግጠው የሚነግሩን ሀቅ ነው፡፡ ተድላም በመጨረሻ ተይዞ ከማእከላዊ ምርመራ ወደ ከርቸሌ ሲጋዝ በዚያ ያሳለፈውንና የተሰማውን ሲተርክ የሚያረጋግጥልን ከላይ ያለውን እውነት ነው፡፡ ከእስር ቤት ውጭ ባለው አለም ውስጥ እንደሚታዩት ልዩ-ልዩ ነገሮች ሁሉ በከርቸሌም በየ‘እለቱ የሚታይ ክስተት አለ፡፡ ደግና ክፉ፣ የሚያስቅና የሚያስለቅስ፣ የሚያስደስትም ሆነ የሚያሳዝን፣ የሚያስደንቅና የሚያሳፍር…ሌሎችም፡፡ ተድላ በዚያ የተከናወኑና ፍንትው ብለው የታዩትን አይረሴ የሚላቸውን ገጠመኞች፣ ታሪካዊ ክስተቶች ለዛ ባለው መልኩ ተርኳል፡፡ በተለይ ይሄ የመጽሐፉ ክፍል ሲበዛ መሳጭ ነው፡፡ ራሱን የቻለ መጽሐፍ መሆን የሚችል አቅምም አለው፡፡
ስህተቶቻቸው
በተለምዶ ያ ትውልድን እርስ በእርሱ የተገዳደለ፣ በትንንሽ ነገሮች ላይ እንኳን የማይግባባ፣ ችግሮችን በውይይት የማይፈታ፣ በሀይል የሚያምን ወዘተ… በማለት በዚህ ትውልድ አባላት ይብጠለጠላል፣ የሰላ ትችትም ይሰነዘርበታል፡፡ ከተድላ ሊነቀስ የሚችል አንድ ድክመት ወይንም ስህተት ቢኖር በዚህና በአንዳንድ የሀገሪቱ ነባር የታሪክ ውዝግቦችና የትውልዱ አሉታዊ ምልከታዎች ላይ በእማኝነት ለምስክርነት ብለው የሚታደሙባቸው አላስፈላጊና አታካች የሆኑ ችሎቶች ናቸው፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴውም ሆነ ስለ ያ ትውልድ ከእውነት የራቀና ፈሩን የለቀቀ ነው በሚሉት አስተያየቶች ላይ ሚዛኑን ያልጠበቀና ስሜት ያጠላበት ጠንከርና ጠጠር ባሉ ቃላት፣ ጠልቀውም ከርዕሰ ጉዳዮቻቸው እርቀውም ይሄን ትውልድ ይወቅሳሉ፣ ጨከን ብለውም ይገስጻሉ፡፡ ሌላው ቢቀር ለዚህ ሁሉ ንትርክ እሳቸው የጻፉልን መጽሐፍ በቂና አጥጋቢ ምላሽ መሆኑን በተደጋጋሚ ይጠቅሳሉ፡፡ በሁሉም ትውልዶች ውስጥ የተዛባ ትርክት እንዳለና እሱን የማጥራት ስራ ደግሞ የታሪክ ተመራማሪዎች መሆኑን እንዴት ልብ ሳይሉ ቀሩም ያስብላል፡፡
ማጠቃለያ
እጓለ ገ/ዮሀንስ ”የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተሰኘ ተወዳጅ መጽሐፋቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ከታሪካዊ እድሉ ለመድረስ ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ትልቅነት በእጁ ለማድረግ በተምኔት እየተመራ ወደ ፊት ይጓዛል፤ ከዚህ አላማው ከሚያደርሱት መሳሪያዎች አንደኛው ትምህርት ነው፤ ሁለተኛው ትምህርት ነው፤ ሶስተኛውም ትምህርት ነው”...ይላሉ፡፡ መምህር ተድላ ድረሴም ከእድል ፈንታቸው ለመድረስ ያበቃቸው ብቸኛው መሳሪያ ከአንድ እስከ ሶስት ሳንቆጥር ትምህርት መሆኑን ግለታሪካቸው በዝርዝር ያስረዳል፡፡ የዚያን ዘመን መምህራን በሄዱበት ቦታ ሁሉ አካባቢውን እንደተወለዱበት’ ህዝቡን ደግሞ እንደ ቤተሰብ በመቁጠር ተመሳስለው እየኖሩ እውቀታቸውንና ችሎታቸውን አቅም በፊደላቸው መጠን ሁሉ አንዳች ሳይቆጥቡ እንዳገለገሉ ድርሳኑ በአፅንኦት ይተርካል፡፡ ያ ትውልድ ላገሩና ለወገኑ ሲል በቀለም ትምህርት ረገድ በከተማና በገጠር ያደረገውን አበርክቶና ተጋድሎም እንዲሁ በጥልቀት ይቃኛል፡፡
በዚህች ባላደገችና ባልተመነደገች’ የዪንቨርስቲዎቿን ቁጥር ማብዛት ላይ እንጂ ትምህርትን ተደራሽ አድርጋ ገና ለሁሉም ዜጎችዋ በቅጡ ባላዳረሰች፣ ዛሬም በቁጥር እሚበዙት ዜጎችዋ ገና ከመሀይምነትና ፊደል ካለመለየት ድንቁርና ባልተላቀቁባት ሀገር፣ የተከተልነው የዘመናዊ ትምህርት ተሞክሮን ጨምሮ ከመነሻው እስከ መዳረሻው’ ከጥንስሱ እስከ ድግሱ እንዴት ያለ’ እንደነበረ ለመረዳት የተድላ መጽሐፍ በምርኩዝነት ያግዛል፡፡ የኔታ ተድላ ትውልድን በእውቀታቸው ሲመግቡ ኖረው በዚህ የእድሜ አመሻሻቸው ወቅት ደግሞ በመጽሐፋቸው እኛኑ ተደራሲያኑን የዘመን ልምዳቸውን ከሀ እስከ ፐ እያስቆጠሩ አካፍለውናልና ላቅ ያለ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የብራሰልስ/የቤልጂየምን ብርድ ለመቋቋም ሬስቶራንት ፍለጋ ዞረን፣ አንዲት መካከለኛ ሬስቶራንት አግኝተን እየተረጋጋን ሳለን ነበር ጽሁፌን ያቆምኩት። ከዚያው እንቀጥላለን።
በነገራችን ላይ ከዛ በፊት ስላጋጠሙኝ ሁለት ነገሮች ልንገራችሁ።
1ኛው/ አንድ ወጣት ሚኒባስ ላይ አግኝቶኝ ተዋወቀንና፣ “የኛ ሰው በአሜሪካ አልቆ ነወይ፤ የኛ ሰው በብራሰልስ የጀመርከው?” ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “አይደለም ባለኝ የውጪ ማስታወሻ ላይ ተጨማሪ ስላገኘሁ ነው። ከዚህ ቀደም የሄድኩበትን ማስታወሻዬ ላይ ስላሰፈርኩት የት ይሄድብናል? ዕድሜውን ይስጠን እንጂ እናነበዋለን” አልኩት። “እንዲህ ከሆነማ ሁልጊዜ በየአገሩ በወሰዱህ አሪፍ ይሆንልን ነበር” አለ።
“ኢትዮጵያዊ የሌለበት ቦታ ከወሰዱኝ ነው ጉዱ!”
“ኢትዮጵያዊ የሌለበት ቦታ ፈጽሞ የለም! ጨረቃ ላይም አለ” አለኝ ኮስተር ብሎ፤ ነገር -ዓለሙ ገርሞኛል።
“እዛስ በምንም መንገድ ለመሄድ የምችል አይመስለኝም” ስለው፤
በጣም ፍርጥም ብሎና በተመስጦ፤ “ግዴለህም ነቢይ፤ አንድ ቀን ዲቪ ይደርስሃል!” አለኝና የመጨረሻ አሳቀኝ። ወጣቱ ከታክሲው ወርዶ ሲሄድ በማያዩ አይኖች እያየሁት ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄው ዲቪ መሆኑ ገረመኝ። የሐሳባችን ውሱንነት ሀሳብ ውስጥ ከተተኝ። ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን መንፈሴ ውስጥ ገባ- በከርሞ ሰው በኩል።
“… ምኞቴ እንደ ጉም መንጥቃ
ተስፋዬ እንደ ጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ ለርስታቸው ሳላበቃ
የኔ ነገር በቃ በቃ!!”
2ኛው/ አጋጣሚ
እንደዚሁ ታክሲ ውስጥ ነው። ልጆች ሲጨዋወቱ፤
አንደኛው “አይዞህ እኔ አሜሪካ ስሄድ፣ እኔ ነኝ ያለ ስኒከር፣ እልክልሃለሁ!!” ደሞ ትንሽ ተጫውተው፣
“እኔ አሜሪካ ስሄድ የቀወጠ ጃኬት እልክልሃለሁ!!” ይለዋል። እንዲሁ እያለ “እኔ አሜሪካ ስሄድ”ን ቀጠለ። “እኔ አሜሪካ ስሄድ…” ብሎ እንደገና ሊጀምር ሲል ጓደኝዬው አቋረጠውና፤
“ቆይ ኧረ፤ እኔ አሜሪካ ስሄድ፣ ይህን እልክልሃለሁ፣ ይሄን እሰድልሃለሁ የምትለው፣ እኔ ዋሊያ ነኝ፤ ቀይ ቀበሮ ነኝ… ወይስ መለስ ነኝ፤ ወደ አሜሪካ የማልሄደው?”
“አይ!! አንተ እንኳን ወደ አሜሪካ የምትሄደው ወይ “ከቦሌ ዲሲ” የሚሠራ ሚኒባስ ጀምሮ ወያላው “ዲሲ! ዲሲ!” እያለ ሲጠራ ካጋጠመህ፤ አለበለዚያ ኢትዮጵያ ራሷ ዲቪ ሲደርሳት ነው!” አለውና ተሳሳቁ።
ሦስት ነገር ገረመኝ። አንደኛው ሚኒባስ ላይ ሆነው የሚኒባስን እድገት አስበው ከቦሌ ዲሲ ስለሚለው ሚኒባስ ማሰባቸው ነው። ሁለተኛው መለስን እንደ ብርቅዬ እንስሳ ሲጠቅሰው፤ እንኳን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ መሥሪያ ቤት ዘበኛም የሚያወራ አለመምሰሉ ነው። ሦስተኛው ለኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ዲቪ መመኘታቸው ነው።
***
የሬስቶራንቱ ዋጋ አስፈሪ አይደለም። ሁለት ትላልቅ ሳንድዊች መጣልን። እርቦን ስለነበር እየተስገበገብን ሳንበላ አልቀረንም። ሁለታችንም የምንበላው አትክልቱንም፣ ስጋውንም ከውስጥ እየቦጠቦጥን ነው። ገርበብ ብለን ቀና ስንል አብሮኝ የሚመገበው ተጓዥ ወዳጄ፡-
“እኔ የምልህ?” አለ
“እ!”
“ይሄ ምግብ በሁለት ሳህን ለምን መጣ?”
“እንዴት በሁለት ሣህን?”
“ይሄው አንደኛው ሳህን” አለና ምግቡ የቀረበበትን ሳህን አሳየኝ።
ቀጥሎ ደግሞ!
“ይሄው ሌላው ሳህን” ብሎ ሁለተኛውን ሳህን አሳየኝ። ሁለተኛው ሳህን ብሎ ያሳየኝ አንድ ጥርብ እንጨት ሁለት ላይ ተሰንጥቆ ማህሉ ስጋና አትክልት የተደረገበት የሚመስለውን ትላልቅ ዳቦ ነው ለካ። ዕውነትም ሁለታችንም ዳቦውን እንደ ዳቦ ሳይሆን እንደ ምግብ ማስቀመጫ ነው ያየነው- ሳናውቀው።
በጣም ተሳሳቅን።
ለማንኛውም ከርሃብ እፎይ ብለን ቢራችንን መጠጣት ቀጠልን። “እስቲ እንግዲህ ደግሞ ሌላ ቢራ ቤት ዘወር ዘወር ብለን እንመልከት” አለኝ ጓደኛዬ። ከፈለና ወጣን። እዚያው የብርድ ግግር ውስጥ ጥልቅ አልን። ጀመረን ብርዱ። ግን እንደ መጀመሪያው አይደለም። “ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል” ወደሚለው አንድረስ እንጂ ብርዱን የመልመድን፤ መንገድ መንገዱን ጀምረነዋል።
የዚያን ዕለት በቤልጂየም አንድ ያስገረመን ነገር ፀጥታው ነው። ሰው ወዲያ ወዲህ አይልም። ቀኑ ቅዳሜ ነው። መቼም ሰው በቅዳሜ ምድር እቤቱ ክትት አይልም የሚለው የኢትዮጵያ አዋዋል ግምታችን እዚህም ተከትሎን መጥቶ ነው መሰለኝ። ብቻ ጭር ጭው ብሏል። ያ ስንመጣ ነው።
አሁን ግን ቢራ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ማለት ስንጀምር ሰው ማየት ጀመርን።
“ምናልባት የምሳ ሰዓት ቢሆን ነው ጭር ያለው” አልኩት ለጓደኛዬ።
ጓደኛዬም- “ነው ብለህ ነው? ሁሉም፣ እንዲህ ክትት እስከሚል ድረስ deserted (ሰው የት ይሄዳል) ይሆናል ብለህ ነው ታዲያ?”
እናም- “ይመስለኛል። ሌላ ምን ምክንያት ትሰጠዋለህ ታዲያ? በብራሰልሱ የስብሰባ ፕሮግራማችን ላይ እንኳ በደምብ ብታስተውለው ቅዳሜና እሁድን በጥንቃቄ ነው የዘለሏቸው። ስለዚህ የእረፍት ቀንነቱን ኮስተር ብለው ቢያምኑበት ነው”
“እስቲ እናያለን” አለ ጓደኛዬ።
አንድ ሬስቶራንት ገባን። ቤቱ ከቅድሙ ተለቅ ያለና ግርማ-ሞገሱም ገዘፍ ያለ ነው።
“ቢራ” አልኩኝ።
“ምን ዓይነት ቢራ?” አለ አስተናጋጁ።
“እንግዲህ ገና በስም አናውቀውም- ቅድም የጠጣነው “ሜዝ” ይሁን “ሜስ” በደንብ አላወቅነውም እንጂ እሱን ብናዝ ጥሩ ነው” አልኩኝ።
“Do you have some light beer?” አለ ጓደኛዬ። (ቀለል ያለ ቢራ አላችሁ እንዴ? እንደ ማለት ነው)
“We have many types of birr! Something like 400 what do you want?...”
(ብዙ ነው ያለን! 400 ገደማ የተለያዩ ዓይነት ቢራዎች አሉን፤ የትኛውን ፈለጋችሁ?)
“የሰማያቱ ያለህ!” አልኩኝ በሆዴ። 400 ዓይነት ቢራ?!
ጥቂት ቆየት አለና ጠየቀን። “Shall I bring you maes?” (ሜስ የሚባለውን ላምጣላችሁ? ማለቱ ነው)
እንግድነታችን ገብቶታል።
“አዎን” አልኩኝ ወዲያውኑ!
“ይቺ ከላፍቶ ክፍለ ከተማ የማትበልጥ ከተማ እንዲህ ትጫወትብን?” አለ ጓደኛዬ። ተሳሳቅን።
“ምን ታደርገዋለህ? ሁሉም ነገር እንዳገሩ እንድትሆን ይወስንሃል”
“This is maes!” (ይኸው “ሜስ”!) አለ አስተናጋጁ። ድምፁ ውስጥ ያለው ልበ-ሙሉነት ሲታይ፤ ራሱ የጠመቀው ነው የሚመስለው።
“ራሱ ነው!” አልኩኝ አንዴ ተጎንጭቼ። እየተጎነጨን ጨዋታ ያዝን።
ተጨዋውተን፣ ጠጣጥተን ስናበቃ ወደ ሆቴላችን ሄደን አራተኛውን ጓደኛችንን፤ከፍራንክፈርት ዘግይቶ የሚመጣውን ማለት ነው፤ ልናገኘው አስበን መንገድ ጀመርን።
እኔ ሁሌ የምከራከርበት “ሁሉ አገር አዙሪት አለው” የሚል ሙግት አለኝ። አንዳንድ ወዳጆቼ አይቀበሉኝም። እኔ የናዝሬት ልጅ ነኝ። የናዝሬት ልጆች፣ ናዝሬት አዙሪት አለ ብለን እናምናለን። አዙሪት ማለት እንዲህ ነው።
ወደ አንድ ምንም ከዚህ ቀደም አይታችሁት ወደማታውቁበት ቦታ ሄዳችኋል እንበል። ባንዱ ቅያስ ሄዳችሁ ስታበቁ ተመልሼ ያንኑ ቅያስ አገኛለሁ ብላችሁ ስትመጡ፣ ምኑም ምኑም ያንን ቅያስ የሚመስል አንድ መንገድ ታገኛላችሁ። በእርግጠኝነት “ጎሽ አገኘሁት!” ብላችሁ ትገቡበታላችሁ። ትንሽ እንደሄዳችሁ ፍፁም ያንኑ ቅያስና መንገድ የሚመስል ታገኛላችሁ። ሊዞርባችሁ ይጀምራል። ትመለሳላችሁ። በቃ የአዙሪቱ ቀለበት ውስጥ ገባችሁ ማለት ነው። ያደረጋችሁት ምልክት የጠፋችሁ ይመስላችኋል። ሰው ልጠይቅ ብላችሁ አላፊ- አግዳሚ መማተር ትጀምራላችሁ። አንዱን አግኝታችሁ፡-
“እባክህ አንድ ነገር እርዳኝ?” ትሉታላችሁ። ደግ ሰው ከሆነ “ምን ልርዳህ? ምን ፈለግህ?” ይላል።
“እንዲህ እንዲህ የሚባል ቦታ ነበር የምፈልገው። ከዚህ ምን ያህል ይርቅ ይሆን?”
“ It is right behind you…or it is right in front of you there, across the road” ይላችኋል።
(ይኸው ከጀርባህ’ኮ ነው ያለው…ወይ ያው ፊት ለፊትህ መንገዱን ተሻግሮ’ኮ ነው)
ብሎ ወጣቱ ይጠቁማችኋል። ይሄ ዐይናችሁ ስር እያለ የሚጋርድባችሁ፤ ሲያዞር ሲያንቀዋልላችሁ የሚውለው ነገር ነው እንግዲህ “አዙሪት” የሚባለው። ቅድም እንዳልኩት በናዝሬት ልጅነት የማውቀው አዙሪት የቅያሶቹ መመሳሰል፣ የቤቶቹ ቅርፅና ዕድሜ አንድ መሆን፣ ከጠራራዋ የናዝሬት ጸሐይ ጋር ተደምሮ ናላ ይነካል፤ ብዥ-ድንብር ያደርጋል። ብዙ ሰው ይዞርበታል። ያ ነው እንግዲህ አዙሪት የሚሆነው። በተጨማሪም እንደ አገሬው እምነት “ቆሌዋ ሳትወድድህ ስትቀር ነው” የሚባለውም አለው። ያ በመጠኑ ወደ ዕምነታዊው አቅጣጫ ያመራናልና ለሌላ ጊዜ ልተወው።
ከሬስቶራንቱ ተመልሰን ወደ ሆቴላችን በሰላም እንዳንገባ የቤልጅንግ አዙሪት በዬት በኩል! ዞረን እዛው! ሄደን ሄደን እዛው! ብዙ ከተንገላታን በኋላ
“ያው ሆቴላችን!” አለ ወዳጄ።
በራሳችን ሳቅን። ልክ ወደ ሆቴላችን ልንገባ ስንል ከኋላችን አንድ ድምጽ ጓደኛዬን ጠራው።
ጓደኛዬ ዘወር አለ። የሚያውቀውን ሰው አግኝቶ ነው ብዬ እኔ በቀስታ ወደፊት ሳመራ ጓደኛዬ ጠራኝና፤ “ና እንጂ አትተዋወቁም እንዴ?” ብሎ መተዋወቅ ወደ አለብኝ ሰው በአይኖቼ አመላከተኝ።
ሰውዬውን በአካል አግኝቼው ባላውቅም ብዙ ቦታ አይቼዋለሁ። በቴሌቪዥንማ ሁሌ አለ።
ተጨባበጥን። ከሀገራችን የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች አንዱ ነው! ከጓደኛው ጋር ነው።
ጓደኛዬ በመገረም፤ “እንዴ እዚህ ነው እንዴ ያላችሁት?” አለና ጠየቀው።
“አዎ እዚሁ ሰንብተናል፤ ለስብሰባ መጥተን ነው” አለ መሪው
“ትቆያላችሁ?”
“የለም ዛሬ ማታ ወደ እንግሊዝ እሄዳለሁ። እዚያ አንድ ቀን አድርና ለአንድ ሳምንት አሜሪካ እሄዳለሁ”
“ምን ለመስራት ነው የምትሄዱት?”
“ያው lobby ለማድረግ ነዋ!” (ለመቀስቀስ ማለቱ ነው።)
ከተለያየን በኋላ ጓደኛዬ፤ “የዓለም ጠባብነት አይገርምህም። ከእነዚህ ሰዎች ጋር እዚህ እንገናኛለን ብለህ ታስባለህ አሁን?!” እውነትም እኛ ኢትዮጵያ ጥለናቸው የመጣን መስሎን ነበር፤ ለካ እነሱ ናቸው ጥለውን የመጡት።
“The world is a village nowadays man!`”
(ዛሬ ጊዜ ዓለም እንደ መንደር ጠባለች ወዳጄ!) የነገ ፕሮግራማችን ብራሰልስን በአስጎብኚ እየዞሩ ማየት ነው። የነገ ሰው ይበለን።
***
(አዲስ አድማስ፤ ሚያዝያ 1 ቀን 1997 ዓ.ም)

አንድ በሠፈር ውስጥ በጀግንነቱ የታወቀ ሰው አለ። አንድ ጠዋት የሠፈሩ ሰው ተሰብስቦ ቤቱ ይመጣል።
“ምነው በጠዋት ምን እግር ጣላችሁ ጎበዝ?” ሲል ጠየቀ።
የሠፈሩ ሰዎች ተወካይ፤
“ምን መሰለህ ጀግና ሆይ! በአካባቢያችን ያሉ ጠላቶቻችን መንደራችንን ዙሪያዋን ሊያቃጥሉ እያደቡ ነው። ነጋ ጠባ ስብሰባ የሚያካሂዱት በእኛው ላይ ነው። ሰላይ እየላክን የሚመጣው ወሬ በጣም ግራ የሚያጋባ፣ የሚያሰጋ ነው። እንዲያው ምን ይሻላል ልንልህ ነው የመጣነው?” ሲሉ አስረዱ።
ጀግናውም፤
“እስቲ ጊዜ ወስጄ ላስብበት ይላቸዋል”
ሰዎቹ አመስግነውት ሄዱ።
በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሰው ወደ ጀግናው ይሄዳሉ።
“እነዚህ ጎረቤቶቻችን እየተዘጋጁ ነው። እንዴት እያደረግህልን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ።
“እያሰብኩበት ነው። አንድ ቀን እንዋጋለን። በለስ የቀናን ዕለት እናሸንፋለን አይዟችሁ” ብሎ ይመልስላቸዋል።
ሰዎቹ በየሳምንቱ እየተመላለሱ “ዝግጅትህ ምን ደረሰ? ተሳካልህ ወይ?” ይላሉ። እሱም “እየተዘጋጀሁ ነው፤ አይዟችሁ” ይላል።
እንዲህ እንዲህ ሲባል ስድስት ወራት ያህል እንዳለፈ፤ አንድ ማለዳ ሰዎቹ ከመምጣታቸው በፊት ጀግናው ወደ ቤታቸው ይመጣል። ሁሉም ተደናገጡ። ስንቅም አዘጋጁ ሳይለን፣ ወደ ጦርነት እንሂድ ሊለን ነው እንዴ፤ በሚል ክፉኛ ስለሰጉ ሁሉ ነገራቸው ተረባብሿል።
“ምነው ጌቶቼ የተደናገጣችሁ ትመስላላችሁ? ስትመኙት የነበረው ጦርነት  ሲቃረብ ትሸበራላችሁን?” ሲል ጠየቀ።
ተወካዩ አዛውንትም፤
“ኧረ የለም። ያስደነገጠን ጦርነቱ አይደለም። አለመዘጋጀታችን ነው።”
“እኔን ተዘጋጀህ ወይ ስትሉኝ አልነበረም?”
“መሪያችን በመሆንህ፤ ይህን አድርጉ፣ በዚህ በዚህ ተዘጋጁ ትለናለህ ብለን ስንጠብቅ ነበር”
“አሁን የመጣሁት እሱን ልነግራችሁ ነው”
“እሺ የምትሰጠንን መመሪያ ሁሉ እንፈጽማለን”
“እንግዲያው ወደ ጎረቤታችን ሂዱና እንዴት ልታስተዳድሯቸው እንደምትፈልጉ ንገሯቸው”
ሁሉም አነጋገሩ ግራ ገብቷቸው፤
“ይህን እንዴት ለማድረግ እንችላለን። ጠላቶቻችን ሆነው ከመሬት ተነስተን እንግዛችሁ ብንላቸው ይቀበሉናል?”
ጀግናውም፤
“ከሦስት ቀን በፊት ጀምሮ ከጠላቶቻችን ጋር ስዋጋ ነበር። ድንገት ሄጄ ባላሰቡት ቀንና  ሰዓት ድምጥማጣቸውን አጥፍቻቸዋለሁ። አሁን ሁሉም ለኔ ገብረዋል። መመሪያ ስጠን ስላሉኝ ሰዎች እልካለሁ ብያቸዋለሁና ቶሎ ሂዱ”አላቸው።
“ለኛም የማትገመት ሆንክብንኮ? ነገርህ ሁሉ ያልታሰበ ሆነ?” ብለው በመገረም ጠየቁት።
“መሪ በተጠበቀበት መንገድ አለመምጣቱ የተለመደ ነው- ተገቢም ነው ለማንም ቢሆን። ድሉ የሚጀምረውም ከዚያ ነው” አላቸው።
***
ሮበርት ግሪን የተባለ ጸሐፊ “አርባ ስምንቱ የስልጣን ህግጋት” በተባለው መጽሐፉ፤ “ሌሎችን ምንጊዜም ልብ የሚያንጠለጥል ሽብር ውስጥ ክተታቸው። በተጠበቅኸው መንገድ የአለመሄድህን ዘዴ በየልባቸው ዝራ። ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ድርጊት የማወቅ የማይነካ ጥምና ሱስ ያለባቸው ፍጡራን ናቸው። በተጠበቅኸው መንገድ ከሄድክላቸው ድርጊትህን በቀላሉ ይቆጣጠሩታል። ስለዚህ ሁኔታውን ገልብጠህ አስቀምጠው። ሆነ ብለህ በተጠበቀው መንገድ የማትሄድ ሰው ሁን። ነገረ-ሥራህ የማይታወቅ፤ ተለዋዋጭ ጠባይ የምታሳይ ከሆንክ፤ ሰዎች ግራ-ይጋባሉ። ሚዛናቸውን ይስታሉ። ሲጨነቁ ይውላሉ። ድርጊትህ ምን እንደሆነ ሲመራመሩ ራሳቸውን ይጨርሳሉ። እያደርም ሽብር ይፈጥርባቸዋል” ይላል። በኢትዮጵያ የአመራር መድረኮች ይህን ፈሊጥ የሚጠቀሙ አያሌ መሪዎች፣ ኃላፊዎች፣ ሥራ-አስኪያጆች ወዘተ  አይተናል። መሪውም ተመሪውም በዚህ ሰንሰለት ተሳስረው ይኖራሉ። ሰብሳቢና ተሰብሳቢ በዚህ መንገድ ተቆልፈው ይገኛሉ። ድንገተኛ እርምጃና ያልተጠበቀ መንገድን መጠቀም ሌላውን ግራ ያጋባል። ጥንት “የመወቃቀስ  ጉባዔ” “የመመካከሪያ ሸንጎ” የነበረው፤ ቆይቶ ወደ “ሂስና ግለ-ሂስ”፤ እጅግ ሰነባብቶ ደግሞ “ግምገማ” ወደተባለ ደረጃ ተሸጋገረ። የስብሰባ አውጫጪኝ፤ በተጠበቀው መንገድ አለመሄድን እንደ ሁነኛ ዘዴ ሥራ ላይ ሲያውል ተመልክተናል። በተሰብሳቢው ላይ የፈጠረውን ሽብር ግን ቤቱ ወይም ልቡ ይቁጠረው። “ቅርበት ከቀረጥ አያድንም” እንዲሉ አውጫጭኙ ወገንንም አይምርም። ስለዚህ ሥጋትና-ሽብር-ተኮርነቱ ከሰብሳቢዎቹ በስተቀር የሁሉም የጋራ ሀብት ነው።
ከሞላ ጎደል መሪዎች እንደ ናፖሊዮን ቦናፓርት፤ “የመጨረሻው ከፍተኛ አደጋ የሚደርሰው በድል ወቅት ነው” የሚለውን አባባል ሳያምኑበት አይቀሩም። ስለዚህ አንድ ድል በተጎናፀፉ ቁጥር መንታ ስጋት ይወርራቸዋል። አንድም ከባላንጣ፣ አንድም ከወገን። ስለዚህም እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ጅራፋቸውን ያጮሁበታል። አንዳንዴም ጅራፉ ለህዝቡ ይተርፋል። ምነው ቢሉ፤ የጅራፉን ጩኸት የሰሙ ትናንሽ አለቆችና ባለሥልጣናት በየጉያቸው የያዙዋትን ትናንሽ አለንጋ እያወጡ ወደ ህዝቡ (ዜጋው) ይሰነዝራሉና ነው። ይሄኔ ሥጋቱ ለአገር ይሆናል።
ተገዥዎች ከገዢዎች የሚማሩት ብዙ ነገር ነው። ከዚህ ውስጥ በድንገት አቅጣጫ መቀየር፣ ያልታቀደ የሚመስል ንግግር መናገር፤ ሰው በታቀደ መንገድ ሲሄድ እነሱ ባልታቀደ መንገድ መሄዳቸውና የመሳሰሉት ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው።
ታዋቂው የቼዝ ተጫዋች ቦቢ ፊሸር ከዓመታት በፊት ተጋጣሚውን ሩሲያዊ ስፖስኪን ባልተጠበቀ መንገድ ሲረታው፤
“የፊሸር ልዩ ማሸነፊያ ዘዴ ምርጥ የሚባለውን መንገድ መፈለጉ ብቻ ሳይሆን፤ አብሮት የሚጫወተውን ሰው የሚረብሽና የሚያሸብረውን ጠጠር ማንቀሳቀሱ ነው” ተብሎለት ነበር።
ጥበቡ ይሄው ነው። ይሄ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ማህበራትና በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊያስተውሉት የሚገባ ጥበብ ነው። ብልህ ከአሸናፊም ከተሸናፊም ይማራል፤ እንዲል!
አለቆቹ አሳቻ መንገድ በመረጡ ቁጥርና ኃላፊዎቹ ያልተጠበቀ ዘዴ በተጠቀሙ ቁጥር ግራ እሚጋባው ህዝብ ሚሥጥሩና ጉዳዩ ላይ የሚደርሰው ከመሸ ነው። የነቃ ሲቪል ማህበረሰብ የመሪዎቹን አካሄድ ያስተውላል። የነቃ ሲቪል ማህበረሰብ የአለቆቹን አካሄድ ለመቆጣጠር የፈጠነ እይታና ንቃትን በየጊዜው ያዳብራል። የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ሙስናን ያስተውላል፤ ይዋጋል። ጊዜያዊ ዘዴን ከዘላቂ እስትራቴጂ ለይቶ ያያል። ከሁኔታዎች ፍጥነት ጋር ይራመዳል። አለበለዚያ “ሌባ ሀሙስ ጨፍሮ፣ ውሻ አርብ ይጮሃል” እንደሚባለው ይሆናል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ፣ አልሸባብና አይኤስ ኢትዮጵያውያንን መመልመላቸው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ተናገሩ፡፡ ቃል አቀባዩ ይህንን የተናገሩት ለቪኦኤ ሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው።  
“ኢትዮጵያ ጠንካራ የመረጃ አሰባሰብና የቡድኖቹን እንቅስቃሴ የማክሸፍ ብቃት ስላላት፣ ቡድኖቹ ድንበር ዘለል ጥቃት ይፈጽሙብኛል ወይም የጸጥታ ስጋት ይፈጥሩብኛል” የሚል ስጋት እንደሌላት ነቢዩ መናገራቸው በዘገባው ተገልጿል። በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቅንጅት በሚቆጣጠሯቸው የሶማሊያ አካባቢዎች ከአልሸባብ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የኢትዮጵያ የጸጥታ መዋቅር ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በሶማሊያ የፑንትላንድ ግዛት ባለስልጣናት፣ ተራራማ በሆነው አል ሚስካድ አካባቢ ከአይኤስ ጋር ወግነው የሚዋጉ ኢትዮጵያውያንን መማረካቸውንና መግደላቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡  
በሃምሌ ወር የፑንትላንድ የጸጥታ ሃይሎች፤ “ከኢትዮጵያ፣ ከማላዊና የመን ታጣቂዎች ጋር አብሬ በመሆን ተዋግቻለሁ” በማለት የተናገረ፣ አንድ ዛንዚባራዊ የአይኤስ ታጣቂ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም አስታውቀው ነበር።
የፑንትላንድ የቀድሞ የስለላና የፖሊስ አዛዥ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል አብዲ ሀሰን ሁሴን፤ ከአይኤስ ጋር የሚዋጉ የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር ከ500 እስከ 600 እንደሚገመት ለሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ጠቁመዋል፡፡ ይህ አሃዝ በይፋ ያልተረጋገጠ ቢሆንም፣ “ከተዋጊዎቹ መካከል ኢትዮጵያውያን ግን ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል” ብለዋል፤ ብርጋዲየር ጄኔራል አብዲ።
የቀድሞ የአልሸባብ አባል የነበረው ኦማር መሐመድ አቡ አያን፤ ወጣቶችን ለመሳብ የቡድኑን ፕሮፓጋንዳ ወደ አማርኛ የሚተረጎም አንድ ኢትዮጵያዊ ሰባኪ ከእርሱ ጋር ይሰራ እንደነበር ተናግሯል።
ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለመመልመል የሚያደርጓቸውን ሙከራዎች በጥብቅ እንደሚከታተል መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡


ዶላር ከአዲስ አበባ ገበያዎች ጠፍቷል

መንግስት መዋቅራዊ ችግሮችን ካልፈታ በስተቀር የብር የመግዛት አቅምን ማዳከም ዘላቂ ለውጥ እንደማያመጣ ተገለጸ፡፡ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ አንድ የምጣኔ ሃብት ምሁር፣ ከሰሞኑ የወጡት የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ “የሚጣረሱ ነገሮች አሉ” ብለዋል።
የምጣኔ ሃብት ምሁርና በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ማሕበር ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር)፣ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን አስመልክተው ሲናገሩ፤ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ጥንካሬን መፍጠር ዋነኛው ዓላማ ሲሆን፤ በተጓዳኝም ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚ በመገንባት ኢንቨስትመንትን ማዘመንና የንግድ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ፣ ምርት፤ ምርታማነትና የምርት አቅምን መጨመር፣ የመንግስት ተቋማትን አቅም ማሻሻል ተጨማሪ ዓላማዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ብዙ ነገር ተነካክቷል ያሉት ምሁሩ፤ “ማሻሻያው በተለይ ትኩረቱ ያጠነጠነው በምንዛሬ ማሻሻያ ላይ ነው።” ብለዋል፡፡
“እስካሁን ማኔጅድ ፍሎቲንግ ሬት (ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ የሚገባበት የውጭ ምንዛሬ ስርዓት) ነበር። ሰዎች በፈለጉት መጠን ከባንክ በነጻነት ምንዛሬ አያገኙም ነበር። አሁን ግን ገበያ መር የምንዛሬ ስርዓት (ፍሎቲንግ ኤክስቼንጅ ሬት) እንዲሆን ተደርጓል። ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ጣልቃ ገብነት ይቀራል” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን በወጡት የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ የሚጣረሱ ነገሮች እንዳሉ ጣሰው (ዶ/ር) ያመለክታሉ። “አንደኛ ጠንካራ የፊስካል ፖሊሲ ይኖረናል። መንግስት የራሱን አቅም ያጠናክራል፤ገቢውን ያሻሽላል እያለ ነው። እነዚህ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ነገሮች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
 ሌሎቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ‘የማሻሻያ ማዕቀፍ’ ተባሉ እንጂ በአንድም በሌላም መልክ ይህንን ለውጥ ለማጠናከር የወጡ መሆናቸውን ምሁሩ  ይጠቁማሉ። “መንግሥት ራሱ ፈቅዶ ያወጣው ነው? ወይስ በጫና የመጣበት ነው? የሚለው በአንድ በኩል የሚታይ ነው” ሲሉ የሚሞግቱት እኚሁ ምሁር፤ መንግስት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ረዥምና ሰፊ ጊዜ የወሰደ ድርድር ስለማድረጉ አውስተው፤ “መንግስት በተወሰነ መልኩ አሁን የወሰዳቸውን እርምጃዎች ላለመውሰድ ፈራ ተባ ሲል ቆይቶ፣ በመጨረሻም ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እጁን ሰጥቷል -- በግልጽ ባይናገረውም።” ብለዋል።
አክለውም፤ “መንግሥት በራሴ ማሻሻያ ‘አደረግሁ’ ይበል እንጂ አብዛኛዎቹ ማሻሻያዎች በተለምዶ የአይኤምኤፍ ‘የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ’ (Washington Consensus) ተብለው የሚታወቁ የፖሊሲ እርምጃዎችን ነው፣ መንግስት እንዲቀበላቸው የተደረጉት። ከፖሊሲዎቹ መካከል፣ ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት መምጣት አንደኛው ነው። ሁለተኛው የማዕከላዊ መንግስት የታክስና የወጪ ፖሊሲ ለውጥ (fiscal policy reform) ነው። ሦስተኛው በወለድ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ አስተዳደር (interest rate based monetary framework) ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ሦስት ጊዜ ከዶላር አንጻር የብር የመግዛት አቅምን እንዳዳከመች የሚያወሱት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፤ የመጀመሪያው በደርግ የሚመራው መንግስት ወድቆ ኢሕአዴግ መንበረ ስልጣኑን ሲቆጣጠር፣ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ “Structural Adjustment Program (SAP)” በተባለው መርህ መሰረት፣ ኢትዮጵያ የንግድ ሚዛኗን ለማስተካከል፣ የወጪ ንግዷንም ፈር ለማስያዝ የብር የመግዛት አቅምን አውርዳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  
እ.ኤ.አ. በ2010 በተወሰነ ፐርሰንት እንዲቀንስ ለማድረግ ተመሳሳይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ በ2010 ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ይህ እርምጃ መቀጠሉን ምሁሩ በአንክሮ ያብራራሉ። እርምጃው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ አካል በመሆን፣ የምንዛሬ ስርዓቱ በገበያ እስከሚወሰን ድረስ ተብሎ ቀስ በቀስ የመግዛት አቅሙ እንዲወርድ ተደርጎ እንደነበር ጣሰው (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
“እነዚህን እርምጃዎች ተከትሎ ኤክስፖርታችን አመርቂ ለውጥ አላመጣም። የምንልከው የግብርና ውጤቶችን  ነው። እነዚህ ምርቶች ደግሞ የገንዘብ የመግዛት አቅምን በማውረድ የሚያድጉ አይደሉም። ዋጋቸውም በዓለም አቀፍ ገበያ ነው የሚወሰነው። ለዋጋ ወጥ አለመሆን (price volatility) የተጋለጡ ናቸው” የሚሉት ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር)፤ “ምርቶቻችን የተሻሉ ተወዳዳሪዎች ሆነው የዓለም አቀፍ ገበያ ላይ አልተገኙም። በዚያ ምክንያት የኤክስፖርት ገቢያችን አልጨመረም። ጭማሪም ካለ፣ የአገር ውስጥ ምርታችን ጥሩ በሆነበት፤ በዓለም አቀፍ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ በሚንርበት ጊዜ ነው እንጂ ያን ያህል በተደረጉ የማዳከም እርምጃዎች ጠንከር ያሉ ለውጦች አይታዩም” ብለዋል።
አክለውም፤ “እ.ኤ.አ. 2018 ላይ ኤክስፖርታችን ከGDP (አገራዊ ጥቅል ምርት) አንጻር ያለው ድርሻ 8 ነጥብ 2 በመቶ ነበር። እ.ኤ.አ. 2022/2023 አካባቢ ወደ 6 ነጥብ 7 አሽቆልቁሏል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ የአገሪቱ የገቢ ንግድ መጠን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። ኤክስፖርት የጨመረው ግን በ590 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ከእነዚህ ቁጥሮች በመነሳት የንግድ ሚዛን ጉድለቱ “ጠብቧል፣ አልጠበበም?” የሚለውን መረዳት ይቻላል፤ አልጠበበም። እንዲያውም እየሰፋ ሄዷል።” ሲሉ ያስረዳሉ።
 “በኢኮኖሚው ያለው አብዛኛው ችግር መዋቅራዊ ችግር ነው፤ እርሱን ማስተካከል እንጂ የብር የመግዛት አቅምን በማዳከም የሚመጣ ለውጥ ለጊዜው አይታየኝም።” የሚሉት  የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ያገኘውን ድጋፍና ብድር የያዘ ተጨማሪ በጀት፣ በቅርቡ ለፓርላማ አቅርቦ እንደሚያስጸድቅ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፈው ረቡዕ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸውን በማሳያነት ጠቅሰው “ማባበያ ነው፤ ብለዋል።
“በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት 2018 ላይ የተደረገው የመግዛት አቅምን ማዳከም፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ነው ያመጣው። የሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ እየጨመረ መጥቷል፤ምክንያቱም እኛ አምራች አይደለንም፤ለብዙ ዕቃዎች በገቢ ንግድ ላይ ጥገኛ ነን። አሁንም ይህ የማዳከም ሂደት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋና የኑሮ ውድነት መናርን ይዞ ይመጣል።” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ሚኒስትሩ “ይጸድቃል” ያሉት ተጨማሪ በጀት ለዝቅተኛ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች ለሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ እንዲሁም ለነዳጅ፣ ዘይት፣ ማዳበሪያና መድኃኒት ድጎማ እንደሚውል ተነግሯል። ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር) ግን የድጎማውን ዘላቂነት በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት፡፡
“ብዙ ጊዜ እነ አይኤምኤፍ ድጎማን ትኩረት አድርገው ድጋፍ አይሰጡም። የሚመጣውን ቀውስ የመንግስት ባለስልጣናት ያውቁታል። በሰው ዘንድ ያለውን ድንጋጤ ለማርገብ ካልሆነ በስተቀር፣ አንደኛ ድጎማ ቢሰጥም አብዛኛው ሰው የኑሮ ውድነትን መቋቋም አይችልም። የኑሮ ውድነቱ ጫፍ ላይ ደርሷል። ድጎማው እስከ መቼ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ፖሊሲውም ግልጽ አይደለም። በአንድ ሌሊት የተሰራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ይመስላል። ድጎማውም ጊዜያዊ ‘ነው’ ነው የሚለው። በተወሰኑ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ድጎማ ‘እንሰጣለን’ ይላል። መሰረታዊ በሚባሉት ላይ ማለት ነው። በቅርብ ወራት ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሲፈጠር ያንን ለማስታገስ እንደ ነዳጅ፣ መድሐኒት፣ ማዳበሪያና የመሳሰሉ አስፈላጊ ምርቶች ላይ ድጎማ እንደሚደረግ ተገልጿል። አነስተኛ ገቢ ላላቸው መንግስት የደመወዝ ጭማሪ ያደርጋል። መንግስት በሴፍቲኔት ለታቀፉ ሰዎች ድጋፍ ‘አደርጋለሁ’ ነው ያለው። ምን ያህል በመቶ ድጎማ ይደረጋል? ስለሚለው በዝርዝር አልወጣም። ሁለተኛው ‘ጊዜያዊ’ ማለቱ ግልጽ አይደለም። ድፍን ነው። እስከ መቼ እንደሆነ አልገለጸም። የዋጋ ንረቱ ለብዙ ዓመታት እየቀጠለ ከሄደ፣ የመንግስት አቅጣጫ ምን ይሆናል? በዘላቂነት ድጎማ ለመስጠት አቅም አለው ወይ? አቅምም ስለሌለው ነው ‘ጊዜያዊ’ ተብሎ የተቀመጠው።” በማለት አብራርተዋል።
በሌላ በኩል፣ ዶላር ከአዲስ አበባ ገበያዎች መጥፋቱን ብሉምበርግ የዜና አውታር ዘግቧል። በውጭ ምንዛሬ ግብይቶች የዶላር ዕጥረት የተፈጠረው፣ “የብር ምንዛሬ ይበልጥ ሊዳከም ይችላል በሚል ግምት ሰዎች ዶላር መደበቅ በመጀመራቸው” መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች አንድ ዶላር በ115 ብር ለመግዛት ዝግጁ መሆናቸውን እንደተረዳ የጠቀሰው ብሉምበርግ፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ መንዛሪዎች ዶላር የሚመነዝር ሰው እንዳጡ መናገራቸውን ጠቁሟል።
ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2027 እስከ 2028 ባለው ጊዜ ውስጥ ከውጭ ዕዳ ሽግሽግ የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የብድር እፎይታ ያስፈልጋታል ብሏል። ድርጅቱ ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ጉድለት እንደሚኖርባትም አስታውቋል። ይሁን እንጂ የመንግስት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወርና የብድር መክፈያ ጊዜን የማራዘም ሁኔታዎች፣ የገንዘብ ጉድለቱን ወደ 10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወርደው ድርጅቱ አመልክቷል።
መንግስት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ያስታወቀው ባለፈው እሁድ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲሆን፤ ከዚያ ቀደም ብሎ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በወለድ ተመን ላይ ወደተመሰረተ የገንዘብ ስርዓት እንደሚሸጋገር ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

....ስንወለድ የሚበጠሰው ከእናታችን ጋር የተያያዝንበት እትብት ውጪ ከአባታችን የተያያዝንበት  ሁለተኛ እትብት አለ የሚል ፍልስፍና ነው የመጽሐፌ አዕማድ።

በሦስት መንገድ ለማየት ሞክሬአለሁ። አባት ማጣት፤ አባት ማምለክ እና አባት መጥላት በሚሉ ምዕራፎች። ከዱር እንስሳ አንበሳን አጠናሁ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይስሀቅ ያቆብን ትቶ ኤሳውን መባረኩን አመጣሁ ከዛ...

...ሦስተኛ ፊልሞችን እንደ ዋቢ መጻሕፍት ተጠቅሜ በትንታኔ ደገፍኩት። ወጥ ልቦለድ ነው። 215 ገጽ ይረዝማል። postmodern ሲሆን፤ ስነ-ልቦና ከልብ-ወለድ ጋር ዝምድና እንዳለው ያሳየሁበትም ስራዬ ነው።

 ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ጥበቃ፣ ቅርስ፣ ታሪክ እና ባህል ዙሪያ ሲሰራ የቆየ ኢትዮጵያዊ የጉዞና ጉብኝት ጋዜጠኛ ነው። ከዚህ ቀደም "የመንገድ በረከት"፣ "ጎንደርን ፍለጋ"፣ "ሀገሬን" እና "ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች" የተባሉ መጻሕፍትን አሳትሞ ለአንባቢያን አድርሷል።

የተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም "መንገድ ዐይኑ ይፍሰስ..." የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ የተለያዩ አካባቢዎችን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ትረካዎች ይዟል።

Wednesday, 31 July 2024 07:05

የዘላለም ጥግ

 የህይወታችን ዓላማ ደስተኛ መሆን
ነው።
ዳላይ ላማ
 የምትኖረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤
በትክክል ከኖርከው ግን አንዱ በቂ ነው።
ማ ዌስት
 ገንዘብና ስኬት ሰዎችን አይለውጡም፤
የነበረውን ብቻ ነው የሚያጎሉት።
ዊል ስሚዝ
 ስለ ህይወት ለመጻፍ መጀመሪያ አንተ
ራስህ መኖር አለብህ።
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
 እኔ ትችት እወዳለሁ። ጠንካራ
ያደርግሃል።
ሌብሮን ጄምስ
 በእውነቱ እራስህ የምትናገረውን
ከመስማት ብዙም አትማርም።
ጆርጅ ክሉኒ
 ህይወት ብስክሌት እንደ መጋለብ ነው።
ሚዛንህን ለመጠበቅ መጓዝህን መቀጠል
አለብህ።
አልበርት አንስታይን
 ለህይወት በጣም ጤናማው ምላሽ
ደስተኝነት ነው።
ዴፓክ ቾፕራ
 እያንዳንዱ ቅፅበት አዲስ ጅማሮ ነው።
ቲ.ኤስ.ኢሊዮት
 ማለም ስታቆም መኖር ታቆማለህ።
ማልኮልም ፎርብስ


የተለያዩ ወጎችንና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ የምትታወቀው ደራሲ ሕይወት እምሻው፤ ‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ›› የተሰኘ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ መጽሐፍ ለተደራሲያን ልታቀርብ ነው።

መጽሐፉ የፊታችን  ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. አራት ኪሎ በሚገኘው ኢክላስ ሕንፃ፣ ዋልያ መጽሐፍ መደብር ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ የጥበብ አፍቃሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል፡፡

‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ››፤ 27 አጫጭር ታሪኮች የተካተቱበትና በ208 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤  በ300 ብር ለገበያ  እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

ደራሲዋ ከዚህ ቀደም ‹‹ባርቾ›› ፣ ‹‹ፍቅፋቂ›› እና ‹‹ማታ ማታ›› የተሰኙ የወግና የአጫጭር ታሪኮች መጽሐፍትን ለተደራሲያን ማቅረቧም ይታወሳል፡፡

Page 7 of 722