Administrator

Administrator

Saturday, 02 November 2019 13:42

የዕውቀት ጥግ


• ዕውቀት፤ ፍቅር፣ ብርሃንና ርዕይ ነው፡፡
    ሄለን ከለር
• ዕውቀትን የመሰለ ሀብት የለም፤
ድንቁርናን የመሰለ ድህነትም የለም፡፡
   ቡድሃ
• ማንንም ም ንም ነ ገር ማ ስተማር አልችልም፤ እኔ እንዲያስቡ ብቻ ነው ማድረግ የምችለው፡፡
   ሶቅራጠስ
• ዕውቀት መጀመሪያ አለው፤ መጨረሻ ግን የለውም፡፡
    ጌታ ኤስ. ሊንገር
• ዕውቀት የሚጨምረው በማካፈል እንጂ በመቆጠብ አይደለም፡፡
     ካማሪ አካ ሊሪካል
• ሃሳባቸውን መለወጥ የማይችሉ ሰዎች፣ ምንም ነገር ሊለውጡ አይችሉም፡፡
    ጆርጅ በርናርድ ሾው
• በዕውቀት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የላቀ ትርፍ ያስገኛል፡፡
    ቤንጃሚን ፍራንክሊን
• መማር ፈጽሞ አታቁም፤ ዕውቀት በየአስራ አራት ወሩ በእጥፍ ያድጋል፡፡
   አንቶኒ ጄዲ’ አንጄሎ
• ዕውቀት ይናገራል፤ ጥበብ ግን ያደምጣል፡፡
   ጂሚ ሄንድሪክስ
• ሳይንስ ዕወቀት ይሰጠናል፤ ጥበብ የሚያጐናጽፈን ግን ፍልስፍና ብቻ ነው::
   ዊል ዱራንት
• ዕውቀት ያላቸው አይተነብዩም፡፡ የሚተነብዩ ደግሞ ዕውቀት የላቸውም፡፡
    ላኦ ትዙ

   ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም በስራዎቻቸው እጅግ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ የአለማችን ዝነኞችን ዝርዝር በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2019 ባለ ከፍተኛ ገቢ በህይወት የሌሉ ዝነኞችን ዝርዝር ባለፈው ረቡዕ ያወጣ ሲሆን ላለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት በመሪነት የዘለቀው ማይክል ጃክሰን ዘንድሮም በ60 ሚሊዮን ዶላር ቀዳሚነቱን ይዟል::
በወርሃ ሰኔ 2009 ከዚህ አለም በሞት የተለየው እውቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን፣ የሙዚቃ ስራዎች በአመቱ በአሜሪካ ውስጥ ብቻ በድረገጾች 2.1 ቢሊዮን ጊዜ መታየታቸውንና በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው የፎርብስ መረጃ፣ ምንም አንኳን ገቢው ካለፈው አመት በእጅጉ ቢቀንስም ዘንድሮም ከአንደኛ ደረጃ አለመውረዱን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1977 በልብ ድካም ህመም ይህቺን አለም የተሰናበተው ሌላኛው እውቅ ሙዚቀኛ ኤልቪስ ፕሪስሊ   በ39 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ከ19 አመታት በፊት በካንሰር ለሞት የተዳረገው ቻርለስ ሹልዝ በ38 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ሆኗል፡፡
ታዋቂው የጎልፍ ተጫዋች አርኖልድ ፓርመር በ30 ሚሊዮን ዶላር፣ የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ በ20 ሚሊዮን ዶላር፣ ዶክተር ሲዩስ በ19 ሚሊዮን ዶላር፣ ድምጸ መራው ጆን ሌነን በ14 ሚሊዮን ዶላር፣ ዘመን አይሽሬዋ ማርሊን ሞንሮ በ13 ሚሊዮን ዶላር፣ ፕሪንስ በ12 ሚሊዮን ዶላር፣ በቅርቡ በወሮበሎች የተኩስ እሩምታ ድንገት ህይወቱ ያለፈው ኤርትራዊው ድምጻዊ ኒፕሲ ሃስል በ11 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት ባለከፍተኛ ገቢ የአለማችን ሟች ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ታውቋል፡፡

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ዴንሴ ንኩሩንዚዛ፣ በሴቶች መብቶች መከበርና በጾታዊ ጥቃቶች ዙሪያ የሚያተኩርና ዜጎችን ለእኩልነት የሚቀሰቅስ አዲስ ነጠላ ዜማ መልቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
“ኡሞኬንዚ አሬንግዬ ኩቭየራ ጉሳ” ወይም ሴት ልጅ ከመውለድ በላይ ዋጋ አላት የሚል ትርጉም ያዘለ ርዕስ ያለውና የአገሪቱ ወንዶች ሴቶችን ዝቅ አድርገው መመልከታቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ የሚያስተላልፈው የቀዳማዊት እመቤቷ ነጠላ ዜማ፤ የቪዲዮ ክሊፕ ተሰርቶለት በሳምንቱ መጀመሪያ በዩቲዩብ የተለቀቀ ሲሆን በርካታ ተመልካቾችን ማግኘቱንና በማህበራዊ ድረገጾች መነጋገሪያ መሆኑን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ ጋር ባሳለፉት የ23 አመታት የትዳር ህይወታቸው አምስት ልጆችን ያፈሩት የ49 አመቷ ቀዳማዊት አመቤት ዴንሴ፤ አራት ደቂቃ እርዝማኔ ባለው የቪዲዮ ክሊፕ ላይ አንድ አባወራ ሚስቱን ሊደበድብ ሲሞክር ጣልቃ ገብተው ሲያስታርቋቸው ይታያሉ፡፡

  አፍሮባሮሜትር የተባለው የጥናት ተቋም፣ ከ28 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን፣ አንድ ባል አልፎ አልፎ ወይም በየዕለቱ ሚስቱን ቢደበድብ ጥሩ ነው ብለው እንደሚያምኑ በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ 34 የአፍሪካ አገራት የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ ምንም እንኳን በጥናቱ ከተካተቱት አፍሪካውያን መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ባሎች፣ በምንም አይነት ሁኔታ ሚስቶቻቸውን ሊደበድቡ አይገባም የሚል አቋም ቢይዙም፣ 28 በመቶ ያህሉ ግን ድብደባው ተገቢ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት 46 ሺህ ያህል የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መካከል ድብደባው ተገቢ ነው የሚል ምላሽ የሰጡት 24 በመቶ ሴቶች እና 31 በመቶ ወንዶች መሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት በጥናቱ ከተካተቱት ሰዎች መካከል እስከ 70 በመቶ የሚደርሱት ድብደባን ጨምሮ በባለትዳር ሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተገቢ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ መሰል አመለካከቶች ስር የሰደዱት ጋቦንና ላይቤሪያን በመሳሰሉ የመካከለኛውና ምዕራባዊ አፍሪካ አገራት ዜጎች ዘንድ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ተቋሙ ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በሰራው በዚህ ጥናት ከተካተቱትና ባሎች ሚስቶቻቸውን መደብደብ አለባቸው ብለው እንደሚያስቡ ከገለጹት ሰዎች መካከል 41 በመቶ ያህሉ ምንም አይነት መደበኛ ትምህርት ያልወሰዱ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

 ‹‹ታመመ ቢሏቸው አንበሳ ባለበት
ሊጠይቁት ሄዱ የምድር ሁሉ አራዊት
ይሄንኑ ሰምታ የጦጣ ብልጣ - ብልጥ
ሳትጠይቀው ቀረች ሳትገባ ወደ ውስጥ
ለምን ብለው ቢሏት መለሰች ጦጢቷ
የገቡት ሳይወጡ ጉዱ ሳይጣራ ቀኑም ሆነ ሌቱ
እንዴት ብዬ እጄን ልስጥ እስከ ማዕሌቱ
አራዊቱ ለአንበሳ ያላቸው ክብር እጅግ ድንቅ ነው፡፡ ሲታመም እጅግ አሳሰባቸው እንጂ ይሄ ጉልበተኛ በቃ እጁን ይሰጠናል ብለው አሰቡ፡፡ አያ አንበሶ ግን ይብሱን ጉልበት አፈራና ፈረጠመ፡፡ አራዊቱም በጣም ፈሩት፡፡
ከዚያም በሁለት ተከፈሉ፡፡
አንደኞቹ፡-
‹‹ምነው እንዳመመው በዛው በቀሩ››
ከፊሎቹ፡-
‹‹አይ የሚፈራ መሪ ወሳኝ ስለሆነ አያ አንበሶ ያስፈልገናል›› አሉ፡፡
በዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ ከብዙ ክርክር በኋላ ተግባቡ፡፡ አያ አንበሶም ሙሉ ለሙሉ አገገመና የዱር አራዊቱን እየተጎማለለ መጎብኘት ጀመረ!
‹‹ታምሜ በመንከባከባችሁ አመሰግናለሁ ትልቅ ውለታ ጥላችሁብኛል!›› አላቸው፡፡
***
አገራችን አንድ መንገድ አጥታለች ወይም ጠፍቶባታል፡፡ ብዙ ሆነን አንድ አገር ማቅናት ዳገት ሆኖብናል፡፡ ማሻሻል አቅቶናል። ለችግሮቿ መፍትሄ አጥተናል፡፡ መንገድም ጠፍቶብናል፡፡
‹‹እንግዲህ ለፍቅር መንገድ አልሰጠውም
ሲገኝ እየጠጣሁ እተኛለሁ የትም›› ማለት ይቀላል፡፡
‹‹ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ›› ማለትም ከሀምሌት ጋር ያዋጣናል፡፡
የሚሰማንን እንጻፍ፡፡ የምንጽፈውም ይሰማልን! በተቻለን ስሜቶቻችንን እንታዘዛቸው፡፡
ዕውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ምድር
እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር
እንነሳ!
እናብር!
እንተባበር!
እናልም!
እንመንብ!
ክፍተት አንተው!
እንንቀሳቀስ!
እንላወስ!!

  መቼም ለጤናዎት እንደምን አሉ ብዬ አልጀምር ነገር፣ የአካል ደህንነትዎን እያየሁት ነው፡፡ የመንፈስዎን ደግሞ መገመት ይቻላል:: ኢትዮጵያን የሚያህል ሀገር፣ ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ ጋር መምራት ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አይቸግርም፡፡
ክቡር ሆይ፤ እርስዎ ወደዚህ መንበር ከመጡ በኋላ ሀገራችን ብዙ ተስፋ የጫሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተውበት፣ የ2019 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በነገራችን ላይ እንኳን ደስ ያለዎት ብዬ መጀመር ነበረብኝ፡፡ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ሽልማቱ መቶ በመቶ ይገባዎታል ብዬ የማምን ዜጋ ነኝ፡፡  
በእኔ ምልከታ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፉም ቢሆን ብዙ ውጤቶችን በማስመዝገብዎት ትልቅ እውቅና እሰጣለሁ፡፡ በሀገራችን የህግ የበላይነት ባለመከበሩ ከዕለት ወደ ዕለት የዜጋው ሰላም ውሎ መግባት ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ማየት በእጅጉ የሚረብሽ ጉዳይ ነው፡፡ የዕለት ተዕለቱን ችግር ትተን እርስዎ ለሥራ ወደ ውጭ በወጡባቸው ጊዜያት እንኳን  የሚነሱ ችግሮች፣ የሰው ሕይወትን የሚያስገብሩ መሆናቸው በጣም አሳሳቢ ነው:: ሕዝቡም ያለብዎትን ጫና ለመረዳት እየሞከረ እንደሆነ የሚያመላክቱ ነገሮች ቢኖሩም፣ በተለይ ለውጡን ተከትሎ በሞት እያጣናቸው ያሉት ዜጎች ቁጥር መጨመር ስጋት እየፈጠረ ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ የተከሰተው አሳፋሪ ጭፍጨፋ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎቻችን ነገሮችን የምንመለከተው በተናጠል በመሆኑ መፍትሔው ቀልሎ ቢታየንም፣ ሀገር መምራት የብዙ ዘርፎች ድምር ውጤት ነውና ሊከብድ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
ለመሆኑ ሰሞኑን የተከሰተው ግጭትና የሰዎች ህልፈት መነሻው ከወዴት ይሆን? ወንጀል ፈፃሚዎቹስ እንዴት የልብ ልብ ተሰማቸው? የሚለውን ስናስብ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ጥቂቶቹን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ከለውጡ በኋላ የህግ የበላይነት ለማስከበር የተደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆን
ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ ለውጡ እጅግ መልካም የሆኑ አያሌ ገጸ በረከቶችን ይዞ የመምጣቱን ያህል፣ የመንግስት ሆደ ሰፊነት  ችግሮችን የሚያይበት መንገድ ጉድለት ያለበት በመሆኑ ነው እላለሁ፡፡ ለዚህም በእርስዎ ሲነሱ የነበሩ ምክንያቶች ታፍኖ የነበረ ማህበረሰብ በሩ ሲከፈት ለመውጣት የሚፈጠረው ግፊት ነው፣ የለውጥ ደንቡ ነው፣ በሃገራችን ታሪክ የማንግባባ ዜጎች በመሆናችን ታሪክን የምንመለከትበት እይታ የፈጠረው ችግር በመሆኑ ወደፊት እየተስተካከለ ይሄዳል ተብሎ መታሰቡና በመሪው ፓርቲ ውስጥ ያለው መከፋፈል የፈጠረው ችግር ነው እየተባለ የሚቀነቀነው ሁኔታ መዘናጋትን ፈጥሮ፣ አጥፊዎችን ለይቶና አጣርቶ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ፣ የምናየውን እንድናየው ሆኗል፡፡
በእርግጥ ለችግሩ መንግስትን ብቻ መኮንን አይቻልም፡፡  በማህበረሰቡም በኩል አሁን ለተከሰተው ግጭት መነሻ የሆነውን ግለሰብ ለመደገፍ ከሚሊዮን በላይ ህዝብ ተሰብስቦ፣ ጥቂቶች በሌላቸው የፈራጅነት ስልጣን እነሱው ወንጅለው፣ እነሱው በአደባባይ ሲሰቅሉ፣ ብዙዎቻችን ሃይማኖታችንን እንኳን ትተነው ለህሊናችንና ለሞራል እሴቶች መገዛት ባለመቻላችን፣ በካሜራ እየቀረፅን፣ አብረን ቁልቁል ከሰቀሉት እኩል መተባበራችን መንግስትዎ፣ እኔ ምን ላድርግ፤ ህዝቡስ እንዲል በር ከፍተንለታል፡፡
ከአፈናቃዮች ጋር አብረን አፈናቅለናል፡፡ የአጥፊዎችን ሃሳብ ገዝተን አከፋፍለናል፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት እንደ መንግስት በዚህ ሁሉ ጊዜ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የታሰበው ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን በማለት የህግ የበላይነትን በሙሉ ሀይሉ ለማስከበር የሚያቀርባቸውን የመቻቻልና ምህዳር የማስፋት እሳቤ እንደ አለመቻል የቆጠሩ አካላት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መስመራቸውን በመቀያየር፣ እያመሱንና እየገደሉን ይገኛል:: ለዚህም ዓላማቸው መሳካት የህዝቡ ረብሻን አልቀበልም ባይነት እሴት መሸርሸርና ወንጀለኞችን ከጥፋታቸው ይልቅ በዘራቸው በማየት፣ የእኛ ስለሆኑ አትንኩብን ማለቱ፣ ትልቅ መደበቂያ ዋሻ ሆኗቸው ፣በአደባባይ ፎክረው ይተኩሳሉ፤ ተኩሰው ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ይቀጥፋሉ:: መሳሪያ ባይኖራቸው ዓላማቸው መግደል ነውና፣ እንደ ሮማውያን ዘመን፣ በድንጋይ ወግረው ይገላሉ:: የተለያዩ ቤተ እምነቶችን ያቃጥላሉ፡፡ በሚዲያ ዘራፍ ያዙኝ ልቀቁኝ ባይነታቸው፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ እንደገባ ወረርሽኝ ከዳር ዳር እየተስተጋባ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ተው የሚል አካል ባለመኖሩ፣ ይኸው እሳቱ እየፈጀን ይገኛል፡፡ ስለዚህ መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻሉ፣ ሃገር እየታመሰች እንደሆነ አውቆ፣ ለነገ በማሰብ መንቀሳቀስ ዋና ሥራው እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የዚህ ችግር መፍትሔ በመራቁ አሁንም መንግስትንና ህዝብን ንቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት፣ በአራቱም ማዕዘናት ማየት የተለመደ ነው፡፡
የገዢው ፓርቲ መከፋፈል
ኢህአዴግ የሚባለው አካል ሀገሪቱን ሲመራት አሁን ለደረስንበት መከፋፈል መሰረቱን የቆፈረው እሱ በመሆኑ በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት ሃሳቡ ሁሉ ሲፈራርስ ማየታችን እሙን ቢሆንም፣ የማናውቃቸውን የሃገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች እንዲታወቁ የፈጠረው እድል እውቅና የሚያስቸረው ነው፡፡ በእርግጥ መንግስታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ለአገዛዛቸው የተሻለ ሆኖ ስለሚታያቸው፣ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ለህዝቡ ከማሳየት ይልቅ ከአንድነት የሚያስወጣ ልዩነት ላይ ብቻ በመሰራቱ አሁን ለደረስንበት ውድቀትም ኢህአዴግ  ተጠያቂ ነው:: ምንም እንኳን ለልማት ከወጣው ገንዘብ እኩል የግለሰቦችን ካዝና ያደለበ ከኢሕአዴግ ውጭ በዓለማችን  ሌላ መንግስት መኖሩን ባንሰማም፣ ከሙስና በተረፈው ገንዘብ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች መሥራቱ ቀልጣለች እንደተባለላት ቅንጥብጣቢ ሥጋ ሊያደርጋት ይችል ነበርና፣ ሳናመሰግነው አናልፍም፡፡
የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ ቢሆንም ታላላቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መገንባቱ ዛሬ ከመገንባት ይልቅ በተገነባው ላይ ሥለ ጥራት እንድናወራ በር ከፍቷልና እሠየው ቢባል አይበዛበትም ባይ ነኝ፡፡ በሌሎቹም ዘርፎችም እንዲሁ አዎንታዊነቱንና አሉታዊነቱን እያነሱ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ማለቴ ይህ ፓርቲ መንግስት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ለሰራው መልካም ውጤትም ይሁን ጥፋት ከመካከሉ የአንድ ፓርቲ የበላይነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎቹን ግንባር ድርጅቶች ለምስጋናውም ይሁን ለጥፋቱ ኃላፊነት ከመውሰድ አያድናቸውም፡፡ ለዚህም በየጊዜው የነበሩ የግንባር ድርጅት መሪዎች፣ ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው ማገልገል ሲገባቸውና ችግርም ካለ መስዋዕትነት ከፍለው አጀንዳውን ለህዝብ አለማቀበላቸው፣ የእነሱ ችግር በመሆኑ፣ ተጠያቂነቱ እኩል ሊያርፍባቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
ክቡር ሆይ፤ ታዲያ እርስዎን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ የመረጥዎት ድርጅት፣ የነበረበትን ድክመትም ይሁን ጥሩ ጎን እኩል መቋደስ ሲገባ፣ ስኬቱን በጋራ ወስዶ ጥፋቱን ወደ አንድ ወገን ብቻ መግፋቱ፣ በመርህ ደረጃ የማያስኬድ በመሆኑ፣ ይኸው እርስ በእርስ ተለያይታችሁ የምትወራውሯቸው መግለጫዎች፣ ሰላሳ ዓመት አብራችሁ የሰራችሁ መሆኑ ቀርቶ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ጠላት መሆናችሁን የሚያሳይ መሆን ከጀመረ ከራርሟል፡፡
በእርግጥ ይህ የፓርቲያችሁ ጉዳይ ነው ብለን እንዳንተወው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተከሰቱ ያሉ ጥፋቶች መነሻቸው የፓርቲዎቻችሁ ጎራ መለየት መሆኑ፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ትልቅ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ፓርቲዎች በህግ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፈን አንሰጥም ማለታቸው አሁንም ወንጀለኞች እንዲበራከቱ መንገድ ከፍቷል፡፡ ማህበረሰቡም የእነ እከሌ ወንጀለኛ ሳይጠየቅ የኛ ወንጀለኛ እንዴት ተደርጎ እንዲል የፈቀደ ሲሆን ክቡርነትዎ ቢቻል ሁላችሁም ተቀራርባችሁና ተነጋግራችሁ እንዳማረባችሁ፣ ከእነ ልማታችሁም ይሁን ከእነ ጥፋታችሁ አብራችሁ ብትቀጥሉ፤ ያ ካልሆነ ደግሞ በወጉ ተለያይታችሁ መስመር ለይታችሁ ብትሰሩ የተሻለ ነውና ቀላል የቤት ሥራ ባይሆንም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳዩ የእርስዎን ያላሰለሰ የሰላም ጥረትና ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በኋላ የሚደረግ ውሳኔ ይጠብቃል፡፡  
ሰዎችን ከሚገባቸው በላይ ማግነን
ክቡር ጠቅላያችን፤ ይህ ለውጥ የብዙሃን ደም የተከፈለበት፣ የብዙሃን ወጣትነት የተጨናገፈበት፣ ብዙዎች ህልማቸው በአጭር የተቀጨበትና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በወላጆቻቸው ቀብር እንኳን እንዳይገኙ መስዋዕት የከፈሉለት ነው፡፡ አሁንም ብዙዎች ሞተው ያመጡትን ለውጥ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ለውጡ የታሰበለትን ግብ እንዲመታ፣ የኑሮ ውድነቱ አደባባይ እንዲወጣ እየገፋው የዳቦ እጦት እያሰቃየው፣ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ስራ አጥ አድርጎት፣ በመኖርና ባለመኖር ውስጥ ሆኖ በተለይ  ለውጡ ገብቷቸው እርስዎን ለማገዝ ደፋ ቀና የሚሉ ባለስልጣናትን በመመልከት፣ የሆዱን በሆዱ አድርጎ በተስፋ እየጠበቅዎት ቢሆንም፣ የለውጡን ውጤት የተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ብቻ እንዳመጡት ተደርጎ በመወሰዱ፣ ህዝቡ በእነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች የህሊና ባርነት ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ እነዚህም ቡድኖች የሞቱለትን ዓላማ ዘንግተው፣ በተቃራኒው ጎራ በመቆም ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጥረት በድንጋይ ወግረው እስከ መግደል እየደረሱ ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ለተስፋ ሰጭ ለውጥ ዋጋ የከፈለው ሰፊው ህዝብ ተዘንግቶ -- ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዛርማ፣ ኤጄቶ….. እና ግለሰቦች ለውጡን እንዳመጡት ከበቂ በላይ በመቀንቀኑ፣ ይኸው እነዚህ አካላት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ክብር መሸከም ባለመቻላቸው፣ ለፍፁም አምባገነናዊ አመለካከት በቅተዋል፡፡
ሰሞኑን የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ድርጊቱን አለማውገዙና በጉዳዩ ላይ መንግስትዎን ማብራሪያ አለመጠየቁ ትንግርት ሆኖብናል:: ምክንያቱም ከለውጥ በፊት ቢሆን ግለሰቦች እንዲህ አይቀብጡም፤ ቢቀብጡም እኛም መፅናኛ ቃል አንጠብቅም፡፡ ግን አሁን የእርስዎ ዘመን ነውና  በሚዲያ ወጥቶ፣ የእንባ አድርቅ ቃላት የሚወረውር አንድ የፌደራል ባለሥልጣን መጥፋቱ ለምን ይሆን አስብሎናል፡፡
እንግዲህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሃሳቦች፤ የህግ የበላይነት እንዳይከበር ካደረጉት ምክንያቶች በጣም ጥቂቶቹ ናቸውና አሁንም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ፤ መልካም የሆነውን ኢትዮጵያዊ ራዕይዎትን ለመተግበር፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርና ህዝቧ ሊኖሩ የግድ ነውና፣ አውቀው አፍነው ይዘውት አንድ ቀን እሳቱ እርስዎንም በልቶዎት ከማየታችን በፊት አልፎ አልፎ በንግግር የሚያሳዩንን ቁርጠኝነት መሬት ላይ አውርደው፣ የሚመጣውን አብረን ዋጋ እንክፈልበት፡፡ ሀሳብዎት ገዢ በመሆኑ አለመደገፍ ባንችልም፣ ሃሳብዎትን ለማስፈፀም የሚችሉበትን ሜዳ እያጠበቡት መመልከታችን ያሳስበናል፤ከዚያም አልፎ ሀገራችን ነችና ያገባናል፡፡
መቼም እርስዎ የየቤተ ዕምነቱን አስተምህሮ የሚያውቁት በመሆኑ፣ ለታላቁ መጽሐፍ ቃል አዲስ ባይሆኑም “ለሰነፍ ሰው እራስህን ዝቅ አታድርግ…” ይላልና የእርስዎ ትህትናና ሆደ ሰፊነት፣ ሰነፎችን የልብ ልብ እየሰጠ በመሆኑ እባክዎት ሆደ ሰፊነትን ሊቀበለው ለማይፈልግ ጊዜ ማባከን ነውና በአንድ ወቅት “ብዙ ኮማንደሮች በተለያዩ ሀገራት እየሰለጠኑ ነውና መጥተው ሰው እንዳይፈጁ እሰጋለሁ” ያሏቸውን አስመጡና የህግ የበላይነትን አስከብሩልን:: ይህችን ወድ ሀገር ለመታደግ አብረንዎት ለመሰለፍ ቁርጠኛ ነንና “ልብ ያለው ልብ ይበል” እንደተባለው ልብ ያድርጉልን፡፡
ቸር ሰንብቱልኝ !     


  ባለፈው የፈረንጆች 2018 ብቻ በመላው አለም የሚገኙ 1.7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸውን ፖለቲኮ ድረገጽ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡
ባለፈው አመት ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር በተያያዘ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ከ770 ሺህ በላይ እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ የጠቆመው ዘገባው፣ በአለማችን በየሳምንቱ ከ15 እስከ 24 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 6ሺህ ያህል ሴቶች በቫይረሱ እንደሚጠቁም አመልክቷል፡፡ ባለፉት 8 አመታት በኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ የሚጠቁ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያደገባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ፊሊፒንስ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ በቫይረሱ የተያዙ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር በ203 በመቶ መጨመሩንም ገልጧል፡፡
ግብጽ በ196 በመቶ ጭማሪ የሁለተኛነት ደረጃን ስትይዝ፣ ማዳጋስካር በ193 በመቶ በሶስተኛነት እንደምትከተልም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰባት  ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ኮሞሮስ መሆኗንና በአገሪቱ የ67 በመቶ ቅናሽ መታየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡ በሲንጋፖር የ66 በመቶ፣ በቬትናም የ64 በመቶ፣ በካምቦዲያ የ62 በመቶ፣ በሩዋንዳ የ61 በመቶ፣ በታይላንድ የ59 በመቶ፣ በኔፓል የ57 በመቶ ቅናሽ መታየቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

የኬንያ መንግስት፤ የመንግስት ሰራተኞች በሳምንት አንድ ቀንና በህዝባዊ በዓላት በአገር ውስጥ የተመረቱ ልብሶችን ብቻ እንዲለብሱ መመሪያ ማስተላለፉን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን የማበረታታት ዓላማ ያለው ነው የተባለውን ይህንን መመሪያ ለሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ማሰራጨቱን የጠቆመው ዘገባው፤ መመሪያውን ባላከበሩ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ምን አይነት እርምጃ ይወሰዳል የሚለው በግልጽ አለመታወቁን አመልክቷል፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ባለፈው እሁድ በተከበረው የብሔራዊ ጀግኖች በዓል ላይ በአገር ውስጥ የተሰሩ አልባሳትን በመልበስ ለዜጎች ምሳሌ ሆነው ለመታየት መሞከራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡


            በዚምባቡዌ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይማሩ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል 61 በመቶ ያህሉ የትምህርት ቤት ክፍያቸውን መፈጸም ባለመቻላቸው ሳቢያ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸው ተዘግቧል፡፡
ምንም እንኳን የአገሪቱ ህግ እያንዳንዱ ዜጋ ትምህርት የማግኘት መብት እንዳለው ቢያረጋግጥም፣ ወላጆች እየናረ ያለውን የትምህርት ቤት ክፍያ ለመፈጸም ባለመቻላቸው፣ ልጆቻቸው ትምህርት ለማቋረጥ መገደዳቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በትምህርት ቤት ክፍያ መናር ሳቢያ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ህጻናት ከሚገኙባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል  ማታቤሌላንድ የተባለችው ግዛት አንዷ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፤ ሩብ ያህሉ የግዛቲቱ ህጻናት ትምህርት ማቋረጣቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ በትምህርት ቤት ክፍያ ሳቢያ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ከተገደዱት የዚምባቡዌ ህጻናት መካከል 55 በመቶው ወንዶች መሆናቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡

 የአለማችን ሚሊየነሮች ቁጥር በ2019 የፈረንጆች አመት፣ 46.8 ሚሊዮን መድረሱንና 18.61 ሚሊዮን ያህል ሚሊየነር ዜጎች የሚኖሩባት አሜሪካ፣ በሚሊየነሮች ብዛት ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን መያዟን አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ክሬዲት ሲዩሴ የተሰኘው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አመታዊው አለማቀፍ የሃብት ጥናት ሪፖርት፤የአሜሪካውያን ሚሊየነሮች ቁጥር አምና ከነበረበት የ675 ሺህ ጭማሪ በማሳየት ዘንድሮ 18.6 ሚሊዮን መድረሱንና ከአለማችን ሚሊየነሮች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በአሜሪካ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
4.45 ሚሊዮን ገደማ ሚሊየነሮችን ያፈራችው ቻይና፣ በሚሊየነሮች ብዛት ከአለማችን አገራት የሁለተኛነት ደረጃን መያዟን የጠቆመውና ተቋሙ ለ10ኛ ጊዜ ይፋ ያደረገው ሪፖርቱ፤ ጃፓን በ3.03 ሚሊዮን ያህል ሚሊየነሮች የሶስተኛ ደረጃን መያዟን አስታውቋል፡፡
በመላው አለም የሚገኙት 46.8 ሚሊዮን ያህል ሚሊየነሮች በድምሩ 158.3 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ሃብት ማፍራታቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፤ይህም ከአለማችን አጠቃላይ ሃብት ግማሽ ያህሉን እንደሚይዝ አመልክቷል፡፡

Page 12 of 461