Administrator

Administrator

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የአገሪቱ ፖሊስ በከተሞች እየተስፋፋ ያለውን የወንጀል ድርጊት በ2 ቀናት ውስጥ እንዲያጠፋ መመሪያ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ግድያና ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎች መስፋፋታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒም፣ ፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች በጋራ በመምከር በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ወንጀሎቹን ማስቆም የሚችሉበትን እቅድ በአፋጣኝ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አመልክቷል፡፡
ወንጀለኞችን በሙሉ በሁለት ቀናት ውስጥ ማጥፋት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ሙሴቬኒ፤ ዜጎች በወንጀለኞች ሲዘረፉና ሲገደሉ እያዩ ዝም የሚሉበት ጊዜ እንዳበቃ ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ መኖሪያ ቤቶችንና ድርጅቶችን ሰብረው እየገቡ በገጀራና በሌሎች መሳሪያዎች እያስፈራሩ ዝርፊያ የሚፈጽሙ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ እጅግ በርካታ ዜጎች በወንጀለኞቹ ቢዘረፉና ቢገደሉም የአገሪቱ ፖሊስ ይህ ነው የሚባል እርምጃ ሳይወስድ በመቆየቱ ሲወቀስ እንደነበርም አስታውሷል፡፡


 ከአሜሪካ መንግስት የተጣለበት ማዕቀብ ክፉኛ ያንኮታኩተዋል ተብሎ ተሰግቶለት የነበረው የቻይናው የሞባይል አምራች ኩባንያ ሁዋዌ፣ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ገቢው በ24 በመቶ ማደጉን አስታውቋል፡፡
ሁዋዌ ኩባንያ ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ብሉምበርግ እንደዘገበው፣ ኩባንያው እስካለፈው መስከረም ወር በነበሩት ያለፉት ዘጠኝ ወራት 185 ሚሊዮን የሞባይል ስልኮቹን ለአለማቀፍ ገበያ በማቅረብ 86.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡
ሁዋዌ ከሞባይል ሽያጭ በተጨማሪ እጅግ ፈጣኑን የ5ጂ ኔትወርክ በስራ ላይ ለማዋል የሚያግዙ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ለመሸጥ 60 ያህል የሽያጭ ስምምነቶችን በአለም ዙሪያ ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር መፈጸሙን የጠቆመው ዘገባው፤ ያም ሆኖ ግን የአሜሪካ ማዕቀብ የኩባንያውን አጠቃላይ አመታዊ ገቢ ክፉኛ ይጎዳዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ሁዋዌ ባለፈው አመት የአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የሞባይል አምራችነት ስፍራን ከአሜሪካው አፕል ኩባንያ መረከቡን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተግቶ በመስራት የሳምሰንግን ቦታ በመረከብ የአለም ቁጥር አንድ የሞባይል አምራች ኩባንያ የመሆን ግብ ቢያስቀምጥም፣ የአሜሪካ ማዕቀብ ግቡን እንዳይመታ እንቅፋት ይፈጥርበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክሎ ገልጧል፡፡

Saturday, 19 October 2019 13:20

በተስፋ የተሞላ ማነቃቂያ

 ‹‹ትችላላችሁ፤ እንደምትችሉ አምናለሁ››


            እኔ ከአባቴና ከእናቴ ቤት ስወጣ 13 ዓመቴ ነው፡፡ ያሳደገኝ እግዚአብሔር ነው፡፡ እናንተንም እግዚአብሔር ያሳድጋችኋል፡፡ (አሜን ይላሉ ልጆቹ) ግን የእምነት ሰው መሆን አለባችሁ:: እንደምታድጉ እንደምትለወጡ ካመናችሁ… በጣም ብዙ ወጣቶች በጣም ብዙ ታዳጊዎች አላችሁ መለወጥ ማደግ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ሃይስኩል የጨረስኩት፣ መጨረስ ከሚገባኝ ጊዜ በስድስት በሰባት ዓመት ዘግይቼ ነው:: ይቻላል ከወሰናችሁ፡፡ ዋናው የናንተ ውሳኔ ነው፡፡ በኛ በኩል ዛሬ እንድትመጡና እንድታዩ የፈለግነው በኋላ በክፍያ ሲሆን፣ ፕሮቶኮል ሲበዛ፣ እንደናንተ ዓይነት ሰዎች፣ እውነተኛ አገር የሚወዱ፣ አገር የሚጠብቁ፣ ለጊዜው ብቻ እጅ ያጠራቸው ሰዎች የማይገቡበት ሥፍራ እንዳይሆን ነው፡፡ እናንተን ካላካተተ የኢትዮጵያ ሃብት መሆን አይችልም፡፡ እናንተም ኢትዮጵያው ናችሁ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚያማምሩ የሃብታሞች ብቻ ሳይሆን የሌላቸውም ጭምር ስለሆነች…፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ቢያንስ ከ4ሺ እስከ 5ሺ የሚጠጉ የጐዳና ልጆችን ከጐዳና በማንሳት ማደሪያ ቦታ እንዲኖራቸው እየሰራን እንገኛለን፡፡ እስካሁን ተናግረን አናውቅም፤ ምክንየቱም ሁሉም ሲያልቅ ስለሚያምር ነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ እንጨርሳለነ:: አልጋ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ የሚያግዙን ሰዎች ካገኘን በኋላ በዚህ ዓመት ከ4ሺ -5ሺ የጐዳና ልጆች እናነሳለን፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እያልን ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ብዙ አይደላችሁም፡፡ 30ሺ -40ሺ የሚሆን ነው አዲስ አበባ ያለው:: ማደሪያ ካገኛችሁ ትናንሽ ሥራ ሰርታችሁ፤ ራሳችሁን የምትመግቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እናንተ አካባቢ ክሊኒክ ኖሮ፣ ቢያማችሁ እንኳን የምትታከሙበት ቢያንስ ማታ ማታም ቢሆን የምትማሩበት ነገር እንዲመቻች የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ እናንተ ግን በመደራጀት አሁን ከተማ ውስጥ አበባ ዛፍ እየተከልን ስለሆነ ያንን በመንከባከብ ብቻ… ውሃ በማጠጣት… በመኮትኮት የዕለት ምግባችሁን የምትሸፍኑበትን መንገድ ማመቻቸት የከተማውም የመንግስትም ሥራ ይሆናል፡፡ ከናንተ የሚፈለገው ሱስን መጠየፍ፣ ሌብነትን መጠየፍ፣ ጥላቻን መጠየፍ… ወስኖ መቀየርና ለአገር ኩራት መሆን ነው፡፡ ያንን ደግሞ ትችላላችሁ፡፡ እኛ ከጐናችሁ ነን፡፡ ትችላላችሁ… አምናለሁ እንደምትችሉ!!...››
(ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት የጎዳና ልጆች አንድነት ፓርክን በጎበኙበት ወቅት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)  


 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እየተንቀሳቀሰ ያለው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ ሒደታዊ መግለጫ፤

              በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በየጊዜው የሚኖረውን የውይይት ሒደት እና ውጤት፣ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ለማሳወቅ በገባው ቃል መሠረት የመጀመሪያውን መግለጫ መስጠቱም ይታወሳል። ኮሚቴው ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል፡-
ከየክልሉ ርእሳነ መስተዳድሮች ጋር የተደረጉ ውይይቶችን በመከታተል የተገቡ ቃሎች እንዲፈጸሙ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ የመስጠት ሂደቱ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተገቡ ቃሎች ትግበራ በተቻለ ፍጥነት እንዲሔድና ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩና ክልሉ እያደረጓቸው ያሉ ጥረቶች አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል:: በዚህ አጋጣሚ የክልሉንና የከተማ መስተዳድሮች ከፍተኛ አመራሮችን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ሳናመሰግን አናልፍም። የእነዚህን ያህል ባይሆንም ከኦሮሚያ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎችም ተስፋ ሰጪ ጅምሮችና እንቅስቃሴዎች አሉ።  
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ለዘብተኝነት እያሳየ ነው። ኮሚቴው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በችግሮች ላይ በተወያየበት ወቅት “በክልላችን መዋቅራዊ ጥቃቶች አሉ ብለን ባናምንም በግለሰቦች የሚፈጠሩ ችግሮች ስለሚኖሩ፣ እነዚህን ችግሮች በማጣራት መፍትሔ እንሰጣለን” ብሎ ቃል ቢገባም እስካሁን ምንም ተጨባጭ ውጤት ሊያመጣ እንዳልቻለ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጽ ለማሳወቅ እንወዳለን።
ከመስቀል በዓል ጋር በተያያዘ የፌደራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ምክንያት የታሠሩ ኦርቶዶክሳውያን እንዲፈቱ ተደርጓል። ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋርም በተደረገው ውይይት በመስቀል በዓል አከባበር ላይ በአንዳንድ የጸጥታ ኃይሎችና ሕገ ወጥ ቡድኖች ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ከክልሎች የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥና አስፈላጊውን እርምት ለመውሰድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በክልሎች ደረጃ የተደረጉ ውይይቶችን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተልና ቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት ለመሥራት ከመንግሥት እና ከየአህጉረ ስብከቱ የተውጣጡ አካላት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ በየዞኖች ተቋቁመው በክልሎቹ በተቋቋሙት የጋራ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት፣ በየዞኖቹ በመንግሥት እና በቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መካከል ውይይቶች መካሔድ ጀምረዋል። በአንዳንድ ዞኖች የትግበራ ዕቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በዚህ አጋጣሚ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዞኖቹ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ፣ መረጃዎችን እንዲሰጥ እና ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ፡-
የፌደራል ፖሊስ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ በዋዜማው ዕለት የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና መግለጫውን ተከትሎ በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ቀለማት የተዋቡ አልባሳትን በለበሱ ምእመናን ላይ ፖሊስ ይፈጽመው የነበረው የማንገላታትና የማመናጨቅ ተግባር አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል። መግለጫው ብዙ ምእመናን ወደ ደመራ በዓሉ እንዳይወጡ፣ የወጡትም በስጋት እንዲያሳልፉ ከማድረጉም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች በዓሉ በሰላም እንዳይከበርና ሁከት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ቃል በገባው መሠረት ገምግሞ አስፈላጊውን እርምት እንዲወሰድ እንጠይቃለን።
የመስቀል በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበር የዐደባባይ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በዓል ሆኖ ሳለ በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝበ ክርስቲያኑን ለግጭት በሚያነሣሣ መልኩ በጸጥታ አካላት አላስፈላጊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ተስተውለዋል። እንዲህ ዐይነት ድርጊቶች ወዳልተፈለገ ግጭት የሚያመሩና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት የአገር ገጽታን የሚያበላሹ ከመሆናቸውም በላይ የሕዝበ ክርስቲያኑ ትዕግሥትና ማስተዋል ታክሎበት እንጂ የከፉ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚጋብዙ ስለሆኑ በአስቸኳይ እርምት እንዲደረግባቸው እንላለን።
በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አከባቢዎች ከመስቀል በዓል አከባባር ጋር በተያያዘ በዝምታ ሊታለፉ የማይችሉ ችግሮች ተፈጥረዋል። በደብረ ዘይት ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የለበሳችሁትን ዩኒፎርም አውልቁ መባላቸው፣ በዚሁም ምክንያት የመስቀል ደመራ በዓል ሳይከበር መቅረቱና ደመራው ሌሊት በሕገ ወጥ ቡድኖች መቃጠሉ፣ በጅማ ከተማ ለመስቀል ደመራ በዓል የወጡ ምእመናን መደብደባቸው፣ በሻምቡ ከተማ በዓሉ ሲከበርበት ከነበረው መስቀል ዐደባባይ ውጪ ሌላ ቦታ አክብሩ ተብለው መከልከላቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘኑ ታሪካዊ ስሕተቶች ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች ምእመናን በዓሉን በሰላም እንዳያከብሩ ክልከላዎችን ያደረጉ፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ድብደባ የፈጸሙ እና ምእመናንንና አስተባባሪዎችን በማሰርና በማንገላታት የበዓሉን ድባብ ሰላማዊ እንዳይሆን ያደረጉ የመንግሥት አካላት ሊታረሙና አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። በተጨማሪም ከግሸን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓል የሚመለሱ ምእመናን በየመንገዱ በተደራጁ ወጣቶች እብሪት የተሞላበት የጥቃት ተግባር ተፈጽሞባቸዋል። የክልሉ መንግሥትም ይህን ነውረኛ ድርጊት በዝምታ በመመልከት መንግሥታዊ ሚናውን ሳይወጣ ቀርቷል:: አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ጫናዎች እና ማንገላታቶች ቀጥለዋል። የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን መውረር፣ መጋፋት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን እና የኦርቶዶክሳውያን ቤቶችና ሱቆች ማፍረስ ተባብሶ ቀጥሏል። መንግሥት በእነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ አለመውሰዱ ጥፋቱን እንዲባበስ አስተዋጽኦ አድርጓል። የክልሉ መንግሥት ይህን እያደረጉ ባሉ ቡድኖችና የመንግሥት አካላት ላይ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮችም በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
በአንዳንድ ሚዲያዎችና ግለሰቦች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጸያፍና ከፋፋይ የሐሰት ትርክቶች፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የማጉደፍና የማጣጣል ድርጊቶች እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ባልዋለችበት በማዋል የከበረ ስሟን በሐሰት የማጥፋት ዘመቻዎችን እያወገዝን በሕግ ለመጠየቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ እንገኛለን፡፡
በቀጣይም መላው ሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነቱን የበለጠ እንዲያጠናክር፣ የቤተ ክርስቲያንን መብት በተገቢው ሰላማዊ መንገድ እንዲያስከብር እና በኮሚቴው የሚሰጡትን ቀጣይ አቅጣጫዎች በንቃት እና በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ


 የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ፍቃዱ ማህተም ወርቅ ከ6 ዓመት በፊት ያሳትመው ከነበረው እንቁ መጽሔት ጋር በተያያዘ በቀረበበት የወንጀል ክስ ጉዳይ ማክሰኞ ለፍርድ ተቀጥሯል፡፡ በ2006 ዓ.ም ነሐሴ ወር መንግስት ሕገ መንግስቱን በሃይል የመናድ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል በሚል ክስ ከመሰረተባቸው 5 መጽሔቶች እና 1 ጋዜጣ መካከል አንዱ የነበረው የእንቁ መጽሔት በወቅቱ ከግብር ጋር በተያያዘም ተጨማሪ ክስ ቀርቦበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ክስ ቀርቦባቸው ከነበሩ መጽሔቶች ጋዜጦች በርካቶቹ በፍ/ቤት ውሳኔ የተዘጉ ሲሆን ይህን ተከትሎም ከ40 በላይ ጋዜጠኞች በወቅቱ
ከአገር መሰደዳቸውም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከአገር እንዳይወጣ እግድ ተጥሎበት የነበረው የእንቁ መጽሔት ተወካይ የነበረው ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ ላለፉት አመታት በገቢዎች የቀረበበትን ክስ ሲከታተል መቆየቱን ለአዲስ አድማስ አስታውቆ ለመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ከ6 ዓመት በኋላ ለማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 እንደሰጠው ቀጠሮ እንደተሰጠው አስታውቋል፡፡ በአገሪቱ ለውጥ ከመጣ በኋላ ክሱ አግባብነት የሌለው መሆኑን ለማስረዳት ላለፈው 1 ኣመት ለጠቅላይ አቃቤ ሕግና ለሚመከታቸው ሁሉ ለማስረዳት መሞከሩን የገለፀው ፍቃዱ ነገር ግን እስከ ዛሬ ቀና ምላሽ አለማግኘቱን አስረድቷል፡፡ እንቁ መጽሔት በወንጀልና ከታክስ ጋር በተያያዘ በተከፈተበት ክስና መዋከብ ህትመቷ እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ ፍቃዱ ማህተም ወርቅ ‹‹ጊዮን›› ሳምንታዊ መጽሔትን መስርቶ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል፡፡

Saturday, 19 October 2019 12:37

ቅምሻ ከድረገፅ ዘገባ

 በኦሮሚያ እጅግ ተስፋ ሰጪ የፖለቲካ መስተጋብር እየታየ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ እየተሸረበ ያለው የፖለቲካ ቁማር አስቀድሞ ወላፈኑ የሚገርፈው የኦሮሞን ሕዝብ በተለይም ወጣቶችን እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። አቶ ገመቹ ደንደና እንደሚሉት ግን ሳይገባቸው እንደ አቦሸማኔ የሚጋልቡት መብዛታቸው ከስጋትም በላይ ነው። ምልክቶችም እየታዩ ነው።
በተለያዩ መድረኮች በቃል ደረጃ ከሚሰማው በቀር በኦሮሚያ “ተስፋ ሰጪ” የሚባለው የፖለቲካ መስተጋብር በገቢር የሚታይ እንዳልሆነ “ተስፋ ሰንቀናል” የሚሉት ራሳቸው የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች፤ ከጥቅም ባሻገር ልዩነታቸውን አስወግደውና አቻችለው በሰላማዊ መንገድ ለመፎካከር መስማማት አለመቻላቸውን እነዚሁ ወገኖች በሃፍረት የሚገልጹት ነው። ልዩነት ቢኖርም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ አለመቻልና ነፍጥ ይዞ እስከ መገዳደል መድረሳቸው የመጨረሻው መጀመሪያ ማሳያ አድርገውም ይወስዱታል።
ሕዝብን በማይወክል ደረጃ የሚራገቡ አጀንዳዎችና ፕሮፓጋንዳዎች አየሩን መሙላታቸው ዛሬ ላይ ድል ቢመስልም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ልብ የሚያደርስ መረጋጋት እንዳይፈጠር ምክንያት እንደሆነ አቋም ይዘው የሚወተውቱ አሉ። ጥፋቶችን የማረም ሥራ ከተሠራ “ተስፋ ሰጪ” የሚሰኘው የፖለቲካ ጅማሮ፣ ከተስፋ እንደሚዘል በተስፋ ላይ ተስፋ ደርበው ያምናሉ።
“ቁማር እየተቆመረ ነው” የሚሉት ወገኖች በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ ክልል ምን እየተደረገ እንደሆነ ለመረዳት የሚያዳግቱ አጋጣሚዎች እየበረከቱ መሆናቸውን ያወሳሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ ከራሳቸው ጉዳይ አልፈው የኦሮሞን ጥቅም እናስከብራለን የሚሉ ወገኖች፤ በሲዳማ፣ በቅማንት፣ በአገውና በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መነከራቸው የማንን አጀንዳ እያስፈጸሙ እንደሆነ ይጠይቃሉ።
በኦሮሞ ህዝብ ስም ቅማንት ውስጥ ገብቶ እሳት መቆስቆስ፣ አገው ምድር ገብቶ ረመጥ ማራገብ፣ ሲዳማ ውስጥ ገብቶ ሕዝብ እንዲጫረስ አቅጣጫ ማስቀመጥና በሚዲያ ማራገብ፣ በራያና መሰል ጉዳዮች መነካካት ፍጹም እንደማይጠቅም የሚናገሩ ወገኖች፤ “አጀንዳ ተሸካሚዎች” ለኦሮሞ ሕዝብ ጠላት እየገዙለት ነው ይላሉ።
ይህ አካሄድ የሰሜኑ ፖለቲካ ውጥረት የተነፈሰ ዕለት የኦሮሞን ሕዝብ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። እነዚህ ወገኖች ወደ ኋላ ሄደው “በእኔ ስም አይደረግም” በሚል ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም የሚፈጽመውን በደል እንዲያቆም ሲጠየቅ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬም የኦሮሞ ሕዝብ፣ በተለይም ልሂቃኑ በኦሮሞ ስም የሚያከናወኑትን አስከፊና ነገ ዋጋ የሚያስከፍሉ አካሄዶችን “በስማችን እንዲደረግ አንፈቅድም” ሊሉ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ለውጡን ወዳልሆነ አቅጣጫ በመግፋት ለውጡ እንዲጨናገፍ ሌት ተቀን ለሚታትሩ ቀበኞች አሳልፎ ለመስጠት የሚሰሩ የኦሮሞ ልሂቃን፤ ለውጡ የተከፈለበትን የደም ዋጋ፣ ዋጋ ቢስ እንዳያደርጉት ከሚሰጉት መካከል አንዱ አቶ ገመቹ ደንደና ናቸው።
ምንጭ፡- (“ጉልጉል” ጋዜጣ)

 የማያውቋቸውን የተቸገሩ ሰዎች በመርዳት፣ ለበጎ ምግባር ገንዘብ በመለገስና በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉት ኬንያውያን፤በልግስና ከአፍሪካ የአንደኛ፣ ከአለም አገራት ደግሞ የ11ኛ ደረጃን መያዛቸውን ሰሞኑን የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
ቻሪቲስ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም በ128 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከአለማችን አገራት መካከል በልግስና ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው አሜሪካ ስትሆን በርማና ኒውዚላንድ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አውስትራሊያ፣ አየርላንድ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ፣ ሲሪላንካና ኢንዶኔዥያ በተቋሙ የ2019 እጅግ ለጋስ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል በልግስና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችው አገር ቻይና ስትሆን፣ ግሪክና የመን በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ቻሪቲስ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም፤ ዜጎች የማያውቁትን ሰው በመርዳት፣ ለበጎ ምግባር ገንዘብ በመለገስ ወይም በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍና ሌሎች መልካም ተግባራትን በመፈጸም ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ በመገምገም፣ የአገራቱን የልግስና ደረጃ እንደሚያወጣ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ኢንዶኔዢያ በልግስና ከፍተኛ መሻሻል ያሳየችዋ ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ናት ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ ኬንያን በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

Saturday, 19 October 2019 12:32

የኖቤል ሽልማት ታሪክ

 በአስራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ላይ አሜሪካ መልክዓ-ምድሯን የሚከፋፍሉትን ተራሮች ቦርቡራ፣ ህዝቦቿን በመንገድ በማገናኘት ወደ አንድነት ለማምጣት ፈለገች:: ችግሩ እነዚህን የአለት ተራራ ግርዶሾች ለመቦርቦር ወይም ለመናድ ይውል የነበረው በፍንዳታ ከፍተኛ ሃይል ማመንጨት የሚችለው ናይትሮግሊስሪን የተባለ ፈሻሽ ፈንጅ ነበረ፡፡ ይህ ፈሳሽ ውሁድ እጅግ ያልተረጋጋና በድንገተኛ ቅጽበታዊ እንቅስቃሴ ፈንድቶ ከፍተኛ አደጋ ማድረስ የሚችል ፈንጅ ነው፡፡
ናይትሮግሊስሪን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁፋሮ ሠራተኞች በወራት ድካም ሊሠሩት የሚገባን አድካሚ የቁፋሮ ሥራ በቀላሉና በፍጥነት እንዲሳካ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የወርቅ ማዕድን አውጪዎች፣ የነዳጅ ጉድጓድ ቆፋሪዎች እንዲሁም ተራሮችን በመቦርቦር መንገዶችን የሚገነቡ ባለሙያዎች ሁሉ ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ፈሳሽ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፡፡ በነዚያ ጭለማ፣ እርጥብና የሚያዳልጡ ጉድጓዶች፣ ፈንጂውን ፈሳሽ የያዘው ባለሙያ የከተንገዳገደ እንደሆነ ዘግናኝ ዜና መሰማቱ አይቀርም ነበረ፡፡
በማዕድን ማውጫ ጉድጓዶች አካባቢ፣ ናይትሮግሊስሪን ያለ ዕቅድ በድንገት የፈነዳ እንደሆነ ጉዳቱ እስከ አጐራባች መንደሮች ይዘልቃል፡፡ በ1866 እ.ኤ.አ ዌልስ ፋርጐ በሚባል የጭነት አመላላሽ (አሁን ከፍተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ድርጅት) ይጓጓዝ የነበረ የናይትሮግሊስሪን ፈሳሽ በጉዞ ላይ እያለ መንጠባጠብ መጀመሩን የተመለከቱት የትራንስፖርቱ ሰራተኞች የመያዣ ዕቃውን ከፍተው ለመመልከት በሚል እሽግ በርሜሉን በመዶሻና በመሮ መቀጥቀጥ በጀመሩበት ቅጽበት ፈንድቶ 15 ሰዎች ሰቅጣጭ አሟሟት ሞቱ፤ በኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ሕንፃዎች መስታዎቶቻቸው ከመሰባበራቸው በላይ የፍንዳታው በድምጽ ከስልሳ ኪሎሜትር ርቀት በላይ የተሰማ ነበረ፡፡ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ነበረ የመሰላቸው፡፡ በፍንዳታው የሞቱ ሰዎች አካላት ከአንድ ኪሎ ሜትር የበለጠ ርቀት ላይ ተበታትነው ተገኙ፡፡
በ1864 ታናሽ ወንድሙን በተመሳሳይ ፍንዳታ ያጣው አልፍሬድ ኖብል የተባለ ሳይንቲስት፤ ይህን ናይትሮግሊስሪን የተባለ ህይወትንም ሞትንም አስተሳስሮ ያዘለ ፈሳሽ ፈንጅ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንዳይኖረው ለማድረግ ይታትር ገባ፤ እናም ተሳካለት፡፡
አቶ ኖቤል (እንዲህ በአማርኛ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ፈረንጆች ስም ሲጠራ ሥራዎቻቸው የኛ ይመስሉኝና ደስ ይለኛል አርስቶትል አርጣጣሊስ፣ ፕሌቶ ጲላጦስ፣ ፒተር ጴጥሮስ…) ናይትሮግሊስሪንን ከሆነ የአፈር ዓይነት ጋር አደባልቆ ፈሳሹን ሊጥ በማድረግ ሆን ተብሎ ካልታዘዘ በቀር በድንገት እንዳይፈነዳ በማድረግ ዳይናማይት ብሎ ሰየመው፡፡
የዳይናማት ሊጥ እየተድቦለቦለ እንዲፈረካክሱ በሚፈለጉ የቋጥኝ ተራሮች ውስጥ በመወሸቅ እንዲፈነዱ ሲታዘዙ መፈንዳትና ጥቅም ላይ ብቻ መዋል ጀመሩ፡፡ እንደ ልብ ሊጓጓዙ ከመቻላቸውም በላይ ከሠራተኞች እጅ ላይ አምልጠው ቢወድቁ እንኳ ድንገተኛ ፍንዳታን የማያስከትሉ ሆኑ፡፡
ዳይናማይት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ማዳን በቻሉና ጉዳት አልባ በመሆናቸው አቶ ኖብልን ሃብታም አደረጉት፡፡ አቶ ኖብልም ዕውቀቱን ለዓለም ጥቅም ማዋል በመቻሉ ሲደሰት፣ ታላቅ ወንድሙን በህመም ምክንያት በሞት አጣ፡፡ በዚህ ጊዜም አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ወንድማማቾቹን በማምታታት፣ “የሞት ነጋዴው ሞተ” የሚል ዜና ይዞ ወጣ፡፡ አቶ ኖብልም በጋዜጣው በርካታ ሰዎችን በመግደል፣ ሃብት ስለማካበቱ የተፃፈውን ዝርዝር ዜና ሲሰማ፣ ከርሱ ሃሳብ እውነታ ጋር የሚፃረር በመሆኑ እጅግ ከመደንገጡም በላይ ማመን አቃተው፡፡
አቶ ኖብል በዓለም ታሪክ ጋዜጦቹ ባመኑበት መሰሪ ሁኔታ መታወሱን ፍፁም ባለመፈለጉ አንደ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ይህም ለዓለም ጥቅም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች በየዓመቱ ሽልማት የሚሰጥ ድርጅት በገዛ ገንዘቡ አቋቋመ:: በየዓመቱም ለሳይንስ (ኋላም ለፊዚክስ) ለኬሚስትሪ፣ ለህክምና፣ ለሥነ-ጽሑፍ፣ በልዩ ሁኔታ የኖብል የሠላም ሽልማት በሚል በተዘረዘሩት ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረበቱ ሰዎች መሸለም ጀመረ፡፡ ይህ የአቶ ኖብልን ስም የያዘው ሽልማትም የማንኛውም ሳይንቲስትና የሀገር መሪዎችን ጨምሮ የሁሉም ሰው የመጨረሻና እጅግ የተከበረ የስኬት ግብ ምኞት መሆን ቻለ፡፡ እናም አቶ ኖብል በመጨረሻ በዓለም ታሪክ እንደ ጋዜጠኞቹ ያልተጣሩ “የሞት ነጋዴ” የሚሉ አሉባልታዎች ሳይሆን እንደ እውነተኛው ንፁህ ልባቸው መሻትና ዕቅድ መታወስ ቻሉ፡፡
እነሆ የአቶ ኖብል ታላቅ ትሩፋትም ቅንና ፀዓዳ ሰብዕና ባላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት ለእኛም ደረሰን!!
የኖብል ሽልማት የግለሰብ ሽልማት አይደለም፤ እንኳንስ ለተሸላሚው ሰውና ለሀገሩ ቀርቶ ለአህጉሩም ጭምር የኩራትና (በተገቢው መንገድ ከተጠቀሙበት) የህብት ምንጭ ነው:: መላው ኢትዮጵያውያንና መላው አፍሪካውያን እንኳን ደስ አለን!!!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን እንኳን ደስ አልዎት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ክብር ስላበቁን ላመሰግንዎት እወዳለሁ፡፡  


 ሴቶች ቅርብ በሆነ ጉዋደኛ ወይንም የትዳር አጋር የሚደርስባቸው ጥቃት ከጤናቸው መጉዋ ደል ጋር እንደሚገናኝ የአለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ 29 November 2017 ባወጣው መረጃ ጠቅሶአል፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተውም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሴቶች በመሆናቸው ብቻ የሚደርስባቸው ሲሆን ውጤቱም በአካል፤በሞራል፤እና በወሲብ የሚደርስ ጉዳት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደዚህ ያሉ ማስፈራራትን የጨመሩ ድርጊቶች ወይንም ኃይልን፤በማንኛውም ጊዜ በድንገት በግልም ይሁን ህብረተሰቡ ባለበት የሚፈጸሙ ነጻነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ናቸው፡፡
በቅርብ ያለ ኑሮን የሚጋራ ጉዋደኛ ወይንም ባል የሚያደርሰው ጉዳት አካላዊ ጥቃት እና በጉልበት ወይንም በኃይል ወሲብ መፈጸም፤እንዲሁም በስነልቡና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ወሲባዊ ጥቃት በማንኛውም መንገድ ከግለሰብ ፈቃደኝነት ውጭ በጉልበት ወይንም በኃይል አስገድዶ መፈጸምን የሚመለከት ሲሆን ይህ በቅርብ ሰው ወይንም ኑሮን በሚጋራ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰው ሲፈጸም የሚገለጽበት ነው፡፡ ይላል የአለም የጤና ድርጅት የተባበሩት መንግ ስታትን መረጃ በመጥቀስ፡፡
ሴቶች በቅርባቸው ባለ ወንድ ሲጎዱ ማየት በአለም ላይ ምን ያህል የተተስፋፋ ችግር መሆኑን የሚያሳየው መረጃ በለንደን የሚገኘው(London School of Hygiene and Tropical Medi- cine እና በደቡብ አፍሪካ  (the South Africa Medical Research Council) ጠቅሶ በ80 ሀገራት ላይ መረጃ በመሰብሰብ ውጤቱም በአለም አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሴቶች አንድዋ ማለትም ከአለም ሴቶች ወደ 35 % የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው በቅርብ በሚገኝ ወይንም በማንኛ ውም ሰው ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ይጠቁማል (እ.ኤ.አ 2013 WHO)፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው በአለም ላይ ካሉት ሴቶች አንድዋ በሕይወት ዘመንዋ በቅርብዋ በሚገኝ ወይንም በማንኛውም ሰው አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባታል ሲባል ወደ 23.2% የሚሆነው ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የደረሰ ሲሆን ወደ 24.6% የሚሆነው ደግሞ በምእ ራብ የፓሲፊክ አገራት እንዲሁም 37% በምስራቅ ሜዲትሬንያን አካባቢ እና 37.7 % የሚሆነው ደግሞ በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት እንደሆነ የአለም የጤና ድርጅት ይገምታል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 38%የሚሆኑት ግድያዎች ሴቶች በቅርባቸው ባለ ሰው የደረሰባቸው መሆኑ እና ምንም እንኩዋን ቅርበት ከሌላቸው ሰዎች የደረሱ ጉዳቶችን በግልጽ የሚያሳይ መረጃ ባይኖርም ወደ 7% የሚሆኑ ሴቶች ተገደው የተደፈሩ መሆናቸውን ሪፖርት ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ሴቶች በቅርባቸው ባሉ ወንዶች የሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ለጉዳታቸው ከፍ ያለ ድርሻን እንደሚይዝ መረጃው ይጠቁማል፡፡
ለጉዳቱ ቁልፍ መረጃዎች ያላቸውን WHO እንደሚከተለው ዘርዝሮታል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጉዳት በተለይም በቅርብ አብሮ በሚኖር ወይንም በሚያገኛቸው ሰው የሚፈጸመው ከፍተኛውን የጤና ችግር የሚያስከትልና የሰብአዊ መብታቸውንም የሚጥስ ነው፡፡
በአለም እንደሚገመተው ከሶስት ሴቶች አንድዋ (30%) በሕይወት ዘመንዋ አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጉዳት ከቅርብ ወይንም አብሮአት ከሚኖር ሰው እንደሚደርስባት ተመዝግቦአል፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ግድያዎች 38% የሚሆኑት የሚፈጸሙት በወንድ የቅርብ ጉዋደኛ ወይንም የትዳር አጋር ነው፡፡
ጥቃት ሴቶችን አካላቸውን፤ ስነልቡናቸውን፤ ወሲባዊ ድርጊትን እና የስነተዋልዶ ጤናቸ ውን ሊጎዳ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለኤችአይቪ ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡
ወንዶች በሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱት በትምህርታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወይንም በልጅነታቸው ጥቃት እየደረሰባቸው ካደጉ፤በቤት ውስጥ ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ካደጉ፤ ጎጂ በሆነ መንገድ አልኮሆል የሚወስዱ ከሆነ፤ የተዛባ የስነጾታ ልምድ ካላቸውና ዝንባሌያቸው ጥቃት ማድረስን የሚገፋፋ ከሆነ እና የሴቶች የበላይ ነኝ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ድርጊቱን ይፈጽሙታል፡፡
ሴቶችም ጉዳት የሚደርስባቸው በትምህርታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከሆነ  እና እናቶቻቸው ቅርብ በሆነው ወንድ ሲደበደቡ ወይንም ሲጎዱ እያዩ ካደጉ እንዲሁም በሕጻንነ ታቸው ጉዳት እየደረሰባቸው ካደጉ እና በወንድ መጠቃት ወይንም መደብደብ ትክክል ነው ብለው የሚቀበሉ ከሆነ፤ ለወንዶች የተለየ ክብር ከመስጠት፤እና ሴቶች በወንዶች ላይ ጥገኛ ከሆኑ ጉዳት ሲፈጸምባቸው እንደትክክለኛ ነገር ይወስዱታል፡፡
ስለዚህም ሴቶች ድጋፍ ከተደረገላቸው እና አቅማቸውን ለማጠናከር እርምጃ ከተወሰደ እና የምክር አገልግሎት ከተሰጣቸው እንዲሁም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ኑሮአቸውን የሚጎበኝላቸው ወይንም ቃል የሚገባላቸው ካገኙ ግንዛቤያቸው ስለሚያድግ ጥቃቱን ለማስቆም እንደሚተባበሩ እሙን ነው፡፡
አንዳንድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶች ወይንም ቀደም ሲል በደረሰ ጥቃት ምክንያት የተከሰተ መፈናቀል የመሳሰሉት ነገሮች በድጋሚ ለጉዳቱ እንዲዳረጉ የሚያስገድድበት ምክንያት ይኖራል:: እንደዚህ ያሉት ክስተቶች በቅርብ ሰዎች ወይንም በቅርብ በማይገኙ ሰዎችም ቢሆን በአዲስ መልክ በሴቶች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳቶች ናቸው፡፡
የሴቶችን በቅርብ ሰው መጠቃት ሁኔታ በአፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ የሚጠቀስ መሆኑን የ Arch Public Health. ይጠቁመናል:: በእርግጥ በጥቃቱ ምክን ያት የሚጎዱት ሴቶች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ የሚደርስባቸውም የጤና እክል በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምሳሌም በእርግዝና ወቅት የሚደርስ ጉዳት እንዲሁም በግብረስጋ ግንኙነት ምክ ንያት በሚተላለፉ በሽታዎች ሳቢያ የወሲብ ፍላጎትን ማጣት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሴቶች ላይ በቅርብ ሰው የሚደርሱ ጥቃቶች በየትኛውም ቦታ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ቢሆ ንም ደረጃውና መጠኑ ግን ሁኔታውን አሜን ብለው በሚቀበሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንደሚጨምር እና ከቦታ ቦታ ከሀገር ሀገር በመላው አለም እንደሚለያይ እሙን ነው፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የሴቶች መጠቃት በከፍተኛ ሁኔታ የተመዘገበ ሲሆን በአለም ከተመዘገበው 30% ጉዳት 36% ድርሻ ይይዛል፡፡ በአፍሪካ ብዙ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው አብሮአቸው በሚኖር ወይንም ቅርብ በሆነ ሰው የሚደርስባቸው ጉዳት 45.6% ሲሆን የሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ደግሞ በየትኛውም የአለም ክፍል ከሚኖሩ ሴቶች 11.9% ይሆናሉ፡፡ በሴቶች ላይ ቅርብ ባለ ሰው የሚደርስ ጥቃት በጤና ላይ አስቸጋሪ ሲሆን ይህም የሚገለጽበት ደረጃ በተለይም ልጅን በመውለድ በኩል ከስነልቡና ጤና ችግር እስከ ስነተዋልዶ ጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው ይታያል፡፡
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ሴቶች በቅርባቸው ባለ ሰው በሚደርስ ጉዳት ወይንም ጥቃት ምክንያት ምንም እንኩዋን በውጤቱ ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ የአካል ጉዳት ደር ሶባቸው ቢታይ ሴቶቹ ለወንዶቹ የሚሰጡት ምላሽ የስነልቦና መዛባት ወይንም አስከፊ የሆነ እንጂ ወንዶቹም ተጎድተዋል የሚል አስተሳሰብ አይታይባቸውም፡፡ ይህም በችግሩ ምን ያህል እንደተጎዱ ወይንም እንደተበሳጩ የሚመሰክር ነው፡፡ መረጃው እንደሚጠቁመው በቅርብ ባሉ ሰዎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና በእርግዝና ወቅት የሚታዩ ችግሮች በጥብቅ ግንኙነት አላቸው፡፡
በቅርባቸው ባሉ ሰዎች በአካል ወይንም በወሲብ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃ ያቀረቡ ሴቶች በብዛት ላልታቀደ ወይንም ላልተፈለገ እርግዝና ይጋለጣሉ፡፡
በሕይወት ዘመናቸው በቅርብ ባለ ሰው ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ሕይወት የሌለው ልጅ መውለድ ወይንም እርግዝናው ካለቀኑ እና ሕይወት አልባ ሆኖ የመወገድ ወይንም ጽንስ መቋረጥ፤ የመሳሰሉት ችግሮች ይደርስባቸዋል፡፡
የተጎዱት ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ችግር በተለያዩ መንገዶች ሊገጥሙአቸው ይችላል፡፡ በግብ ረስጋ ግንኙነት ወቅት በሚተላለፉ በሽታዎች ከመያዝ እስከ እርግዝናን በጸጋ አለመቀበል በሚያደርስ ስጋት ውስጥ ሊጥላቸው ይችላል፡፡
በቅርብ ሰው በሴት ላይ የሚደርስ ጥቃት ኤች አይቪን ጨምሮ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ሊዳርግ ይችላል::
ከሌሎች የአለም ክፍሎች በተለየ በአፍሪካ ውስጥ በቅርብ ሰው በሴት ላይ የሚደርስ ጥቃት ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል ከፍተኛ ለሆነ የመጠጥ ሱስ የመጋለጥ ፤ወይንም በልጅነት ጊዜ የሚደርስ ጥቃት፤ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማለትም ስራ አጥነት እና መጨረሻ የሌለው በወንድ ቁጥጥር ስር የመሆን ልማድ ይታያል፡፡    

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዕብድና አንድ ለማኝ በጓደኝነት ይኖሩ ነበር፡፡ መተሳሰባቸው፣ መተጋገዛቸው እጅግ ያስቀና ነበር፡፡
መሀላቸው፣ ‹‹አደራ እንዳንከዳዳ›› የሚል ነበር፡፡
ሰንብቶ ሰንብቶ ለማኙ በብርድ በሽታ ታሞ ሞተ፡፡ ዕብዱ የለማኙን አስከሬን በሰሌን ጠቅልሎ ወደ መቃብር ቦታው ይዞት ሄደ። እንዳጋጣሚ ወደ አሥራ ስድስት የሚጠጉ የሸዋ መኳንንት በመኪና የመገልበጥ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ያ ዕብድ ለለማኙ እንዲህ አለው ሲሰናበተው፡-
‹‹እንግዲህ ወዳጄ ከደህና ሰዎች አገናኝቼሃለሁ፤ ብታውቅ እወቅበት›› ብሎ አስቀምጦት ሄደ፡፡
* * *
የአዕምሮ ጤና የጎደለው ሰው መላ ነገሩን እስከሚያስተካክል ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ የተማረም የተማረውን እስኪተገብር ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ ያልተማረውም የተማረው ቦታ ለመድረስ ጊዜ ይፈጃል፡፡ አገር የተማረውን ቦታ ለመስጠትና ያልተማረውን ለማስተማር ትጨናነቃለች፡፡ መሯሯጥ ይጠበቅባታል። ሼክስፒር በፀጋዬ አንደበት፡-
‹‹…በምናውቀው ስንሰቃይ
    የማናውቀውንም ፈርተን በህሊናችን ማቅማማት
    ወኔያችንንም ተሰልበን
    ሕይወት የምንለው ውጥንቅጥ እንቅልፍ ላይ ነው ህመሙ
በየዕለቱ መስለምለሙ
እያደር ከህሊናችን ይደመሰሳል ትርጉሙ!
የዱሮ ፀሐፍት፤
‹‹እኛማ ብለናል
እኛማ ታግለናል
እኛማ አምፀናል
ጥንትም ወርቅ በእሳት
እኛም በትግላችን
እየተፈተንን እናቸንፋለን››
ለዘመን መልካም ምኞትና፣ መልካም ምስክርነት  መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ህልውናችን የተሰራው ከመልካምነታችን ልቡና መሆን አለበት፡፡ መንገዳችን ቀና የሚሆነው በዚህ ጎዳና ብቻ ነው፡፡
‹‹እንጫወት እንጂ
እንጫወት በጣም
ከእንግዲህ ልጅነት
ተመልሶ አይመጣም፡፡
(ከዱሮ ማስታወሻ)
ከፀጋዬ ጋር ስናስብ ደግሞ (ለኢትዮጵያ ይበለው አይበለው ባናውቅም፤
‹‹አልወድሽም ያልኩት ውሸቴ ውሸቴ
ሳይሽ እርር ኩምትር ይላል ሆድ አንጀቴ››
ኢትዮጵያን ከአንጀቱ የሚወድ ኢትዮጵያዊ፤
‹‹እናትሽን አትውደጅ ለዘጠኝ ወር ዕድሜ
ተሸክሜሻለሁ እስከ ዘላለሜ››
ቢል… አይገርምምና፣ ለሁላችንም እንደዚያው - መልካም አዲስ ዘመን!