Administrator

Administrator

Saturday, 12 October 2019 12:35

የሙዚቃ ጥግ

• ሙዚቃ የመላዕክት ቋንቋ ነው መባሉ ሲያንስበት ነው፡፡
    ቶማስ ካርሊሌ
• ሙዚቃ የፈውስ ሃይል አለው፡፡ ሰዎችን ለጥቂት ሰዓታት ከራሳቸው  ውስጥ መንጥቆ የማውጣት አቅም ተችሮታል፡፡
   ኢልቶን ጆን
• የምታደምጠውን ሙዚቃ ንገረኝና፣ ማንነትህን እነግርሃለሁ፡፡
   ቲፋኒ ዲባርቶሎ
• ሕይወቴን የምመለከተው ከሙዚቃ አንፃር ነው፡፡
   አልበርት አንስታይን
• ሙዚቀኞች ጡረታ አይወጡም፤ ሙዚቃ ከውስጣቸው ሲደርቅ ያቆማሉ እንጂ፡፡
   ሉዊስ አርምስትሮንግ
• ሙዚቃ የተፈጠረው የሰውን ልጅን ብቸኝነት ለማረጋገጥ ነው፡፡
  ሎውረንስ ዱሬል
• አንዳንድ ሰዎች ኑሮ አላቸው፤ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሙዚቃ፡፡
   ጆን ግሪን
• ፈጣሪ አያድርገውና ከሞትኩ፣ መቃብሬ ላይ እንዲህ ተብሎ ይፃፍልኝ፡- ‹‹እግዚአብሔር ለመኖሩ የሚፈልገው ብቸኛ ማረጋገጫ ሙዚቃ ነበር››
   ኩርት ቮኔገት
• ሙዚቃ በቃላት የማይነገረውንና በዝምታ ሊታለፍ የማይችለውን ይገልጻል፡፡
   ቪክቶር ሁጎ
• ብቸኛው የዓለማችን እውነት ሙዚቃ ነው፡፡
   ጃክ ኬሮዋክ
• የሙዚቃን ፍሰት ማስቆም ማለት ጊዜን ራሱን እንደ ማስቆም ነው፤  ሊሆንና ሊታሰብ አይችልም፡፡
   አሮን ኮፕላንድ
• ‹ሁሉንም ዓይነት ሙዚቃ› እንወዳለን የሚሉ ሰዎች ታውቃላችሁ? እነሱ ምንም ዓይነት ሙዚቃ የማይወዱ ናቸው፡፡
   ቹክ ክሎስተ

Saturday, 12 October 2019 12:33

የዘላለም ጥግ

(ስለ ትዕግስት)

 • በፍቅርና በትዕግስት ምንም የማይቻል ነገር የለም፡፡
   ዳይሳኩ አይኬዳ
• ትዕግስት ለስኬት ቁልፍ ሚና አለው፡፡
  ቢል ጌትስ
• ትዕግስት የችግሮች ሁሉ መፍቺያ ቁልፍ ነው፡፡
  የሱዳናውያን አባባል
• ትዕግስት ተስፋ የማድረግ ጥበብ ነው፡፡
  ሉክዲ ክላፒርስ
• ትዕግስት የገነት ቁልፍ ነው፡፡
  የቱርካውያን አባባል
• እግዚአብሔር ሁልጊዜም ታጋሽ ነው፡፡
  ፖፕ ፍራንሲስ
• ትዕግስት የጥበብ አጋር ነው፡፡
   ቅዱስ ኦጉስቲን
• የማንኛውም ጥበብ መሠረቱ ትዕግስት ነው፡፡
   ፕሌቶ
• የአንድ ደቂቃ ትዕግስት፣ የአስር ዓመት ሰላም ያጎናጽፋል፡፡
   የግሪኮች አባባል
• ከዛሬ እንቁላል ይልቅ የነገ ዶሮ ይሻላል፡፡
    ቶማስ ፉለር
• ትዕግስት ማጣት ጦርነትን መረታት ነው፡፡
   ማሃትማ ጋንዲ
• ሁሉም ታላላቅ ስኬቶች ጊዜ ይወስዳሉ፡፡
   ማያ አንጄሎ
• ትዕግስት ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡
   ጆን ፍሎርዮ
• ትዕግስት ገደብ አለው፡፡ ሲበዛ ፍራቻ ነው፡፡
   ጆርጅ ጃክሰን

Saturday, 12 October 2019 12:26

ዝክረ - ኤልያስ መልካ

  አንፀባራቂው የሙዚቃ አቀናባሪ


           እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ፣ የዛሬ 19 ዓመት ከ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ጋር ለሁለት ሳምንት የዘለቀ ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር- ነሐሴ 5 እና 12፤ 1993 ዓ.ም፡፡ ያኔ የ23 ዓመት ወጣት የነበረው ኤልያስ መልካ፤ ከተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ጋር ከመስራቱም ባሻገር በአንጋፋዋ ድምፃዊ በአስቴር አወቀ ኮንሰርት ላይ በጊታሪስትነት ተመርጦ፤ ከሚሊኒየም ባንድ ጋር መጫወቱ ተጠቅሷል - በቃል ምልልሱ፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ላስታ ባንድን መስርቶም በንቃት እየሰራ ነበር፡፡ የሙዚቃ አብዮቱን ያቀጣጠለበትን ‹‹አቤን›› የተሰኘ ዘመናዊ የሪኮርዲንግ ስቱዲዮ ያቋቋመውም ያኔ ነው፡፡
በዚህ ስቱዲዮው ያቀናበረው የመጀመሪያ ሥራው ደግሞ የዕውቁ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮን ‹‹አቡጊዳ›› የሚል አልበም ነበር:: ከጋዜጣው ጋር ላደረገው ቃለ ምልልስ ሰበብ የሆነው፣ ከቴዲ አፍሮ ጋር ከሰሩት ካሴትና የሙዚቃ ኮንሰርት ጋር በተያያዘ በመሃላቸው የተፈጠረው ቅሬታና እሰጥ አገባ ነበር፡፡ የሚገርመው ታዲያ ኤልያስ መልካ ‹‹ተጣልተናል›› ብሎ የቀድሞ ጓደኛውንና የሙያ አጋሩን ቴዲ አፍሮን በሃሰት ወይም በማጋነን ለማጣጣልና ስም ለማጥፋት አልሞከረም፡፡ የተፈጠረውን ችግርና ቅሬታ በቀጥታና በጨዋነት ነበር ለአዲስ አድማስ ያብራራው፡፡ ከዚያም ባሻገር ለቴዲ አፍሮ የድምፅና የአዘፋፈን ችሎታ ሽንጡን ገትሮ ተከራክሯል - ከጠያቂው ጋዜጠኛ ጋር፡፡ በአገራችን እንደተለመደው፣ ውሸትም ጨምሮ ቢሆን ለማውገዝ ፈጽሞ አልዳዳውም፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በወቅቱ በአርቲስቶቹ መሃል የተፈጠረውን ውዝግብ ብቻ በማውጣት አልተወሰነም፡፡ የጋዜጣው መስራችና ባለቤት የነበረው አቶ አሰፋ ጎሳዬ፤ በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ ኤልያስ መልካንና ቴዲ አፍሮን በማስታረቅ፣ አብረው እንዲሰሩ ቃል አስገብቷቸው ነበር፡፡  በጋዜጣው ላይም የሁለቱ አርቲስቶች ፎቶ፣ ገጣሚ ነቢይ መኮንን  ‹‹ሽማግሌ ሊማር ልጆቹን እያየ›› በሚል ከቋጠረላቸው ግጥም ጋር ታጅቦ ወጥቷል:: የምስራቹን ለአንባቢያን ለማጋራት፡፡ እስቲ ከግጥሙ ላይ ጥቂት ስንኞችን መዝዘን እናስታውሳችሁ፡-
‹‹ዘመን ቢራቢሮ
ዘመን ቢራቢሮ
ይኸው በርሮ በርሮ
አደይ አበባ ሆይ
ቀስተ ዳመናው ህብር
እዩ ፈገግታ አምሮ
ናፋቂ መስቀል ወፍ
ጆሮሽን አቅኚና
ስሚ ቅኝት ሰምሮ
ልጅ አዋቂ ትውልድ ባንድ ተነባብሮ
ምን ይሆን ምልኪው ብላቴን ሊገዝፍ
ምን ይሆን ትርጉሙ ሕጻን ጀልባ ሲቀዝፍ
ምንድን ይሆን ፍቺው ፀደይ ሳቅ ሳቅ ሲለው?
መስከረም ፍርግርግ እስክስታ ሲቃጣው?...››
*  *  *  *
ዕውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ፣  የዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲ ኤልያስ መልካ፣ በወቅቱ ከአዲስ አድማስ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ውስጥ ውዝግቡን አስቀርተን፣ በሙዚቃና ማቀናበር ዙሪያ የሰጠውን ትንተና ለቅኝት ያህል እንዲህ አቅርበነዋል፡-
ሙዚቃን በኮምፒዩተር ማቀናበር
ዜማ ይመጣልሃል - ከዜማ ደራሲ፡፡ ለዜማው የሚስማማ ሪትም (ምት) ትመርጥለታለህ - ሬጌ፣ የአፍሪካ፣ ዲስኮ፣ ጃዝ፣ አማርኛ ምት ወዘተ፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ምን ምን እንደሚጫወቱ ትመርጣለህ፡፡ ጊታሪስቱ እንዴት እንደሚጫወት… ኪቦርድ፣ ሳክስፎን፣… በየቅደም ተከተልም ሆነ በህብረት… ለዜማውና ለምቱ የሚያስፈልግ ሙዚቃ ትመርጣለህ፣ ታስተካክላለህ፡፡ ሁሉንም ራስህ ልትጫወተውም ትችላለህ፤ በኮምፒውተር የማዋሃድና የማቀነባበር እገዛ፡፡ ሙሉ ባንድ የሚሰራውን ነገር ጊታር፣ ሳክስፎን፣ ባስ… ሳያስፈልግህ ብቻህን እያንዳንዱን መሳሪያ በኪቦርድ እየተጫወትክ በኮምፒውተር ታቀናብረዋለህ፡፡ አሁን ‹‹አቤን›› በሚል መጠሪያ አዲስ ስቱዲዮ እየከፈትኩ ነው፡፡ በውጭ አገር አገር ከሚሰራ የካሴት ህትመት (Recording) ጋር የሚስተካከል ጥራት የሚያስገኙ ዘመናዊ መሳሪያዎችን አስመጥቻለሁ፡፡
ጥሩና ተወዳጅ ሙዚቃ መስራት
… ስትሰማው የሚያስደስትህና ስትሰራው ከበድ የሚልህን ትመርጣለህ፡፡ ይሄ ከባድ ነው - ጥሩ ነው ትላለህ፡፡ አንድን ሙዚቃ ስትሰማ በውስጡ የምታገኘውን የፒያኖ ድምጽ ብቻ ትወደው ይሆናል፡፡ በሌላ ሙዚቃ ደግሞ ሳክስፎን ወዘተ፡፡ ሌላው ደግሞ አንድ ሙዚቃ ሲወጣ፣ ብዙ ሰው ከወደደውና ከተቀበለው ጥሩ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ግርግር፣ ቄንጥ ወዘተ ስለበዛበት ብቻ ጥሩ ሙዚቃ ነው ተብሎ ሊነገርለት ይችላል፤ ግን አድማጭ አይወደውም፡፡ እውነትም ጥሩ ሙዚቃ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጥንቃቄ፣ በከባድ ችሎታ የተሰሩ፣ በሙዚቃ ባለሙያዎች ዘንድም ጥሩ ሙዚቃ መሆናቸው የሚመሰከርላቸው ዘፈኖች፣ አብዛኛው አድማጭም ሲወዳቸው ታያለህ:: እንዲህ ስል ግን ጥሩ ሙዚቃ ሆኖ አድማጭ የሚያጣ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱንም ማጣጣም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ጥሩና ተወዳጅ ሙዚቃን መስራት፡፡
ድምፅና ልምምድ
… ካሴት ስትሰራ፣ ሁሉም ነገር ተቀርፆ ካለቀ በኋላ በካሴት ከመታተሙ በፊት የተቀረፀውን ዘፈን ትንሽ እንዲፈጥን ታደርገዋለህ፡፡ ቴፕ ሪኮርደር ተበላሽቶ ካሴት እያፈጠነ ሲጫወት ሰምተህ እንደሆነ ድምፁን ይቀይረዋል፡፡ በእርግጥ በጣም አታፈጥነውም፣ በትንሹ ነው፡፡ ያኔ የድምፁ ቅላፄ ይወጣል፡፡ ቀጠን ይላል፡፡ ግን ያን ያህል ጎልቶ የሚጋነን አይደለም፡፡ አንዳንድ ዘፋኞች ካሴት ሲያሳትሙ አያስፈጥኑም፡፡ ነገር ግን አፍጥነው የሚያሳትሙት ዘፋኞችም ቢሆኑ መድረክ ላይ የሚበላሽባቸው በሌላ ምክንያት ነው፡፡ እዚህ አገር፣ የድምፅ ቅላፄ እንደ ቋሚ ነገር ይቆጠራል፡፡ ድምፅ ግን የሚበላሽና የሚሻሻል ነው፡፡
ድምፃዊ ሁልጊዜ መለማመድ አለበት:: አንድ ጊዜ ዘፍነው ላይ ከወጡ በኋላ ችላ ይሉታል፤ አይለማመዱም፣ ራሳቸውን መጠበቅ ይተዋሉ፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ አስመስሎ መዝፈን ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አስመስለህ የምትዘፍነው የራስህን ድምጽ ለማሻሻል እንጂ አላማህ ማስመሰል ብቻ ከሆነ፣ ራስህ ለዘለቄታው ትበላሻለህ፡፡ ውጭ አገር ዘፋኞች ለድምፃቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ መለማመድ መደበኛና የሁልጊዜ ስራቸው ነው፡፡ ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ይማራሉ፡፡
የአዳዲስ ባለተሰጥኦዎች ጉዳይ…
… ከስር የሚመጡ በጣም በጣም ሀይለኛ ልጆች አሉ፡፡ በየቦታው የሚጫወቱ፣ በትያትር ቤት የሚሰሩም ብዙ ጎበዝ ልጆችን አውቃለሁ:: አሁን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የተሻሉ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡
ሙዚቀኞች ኢንፎርሜሽን ያገኛሉ፤ የተለያዩ የሙዚቃ አይነቶችን፣ ዘፈኖችን፣ ስልቶችን፣ አሰራሮችን ያውቃሉ፡፡ ድሮ የተወሰኑ ነገሮች ብቻ ነበር የሚገኘው፤ ያውም ከውጭ ካሴት ለሚላክላቸው ጥቂት ሰዎች:: ዛሬ ግን ብዙ አማራጭ አለ፡፡ ከየአቅጣጫው እውቀትና ልምድህን የሚጨምርልህ ነገር በብዛት ታገኛለህ፡፡ እና ለሙዚቃ ትልቅ እድገት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡…


አህያና ውሻ አንድ ቀን ተገናኝተው፣ ስለ አሳለፉት ሕይወት ይወያያሉ፡፡
አህያው - ‹‹የእኔ ሕይወት፣ ዘለዓለም ዓለሙን ጀርባን የሚያጎብጥ የሸክምና የልፋት መከራ ነበር›› አለ፡፡
ውሻም -  “የእኔ ሕይወት ደግሞ ሁሌ ሌሊቱን ያለ እንቅልፍ መጮህ ነው፡፡ ባለቤቶቹ ተኝተው፣ ‘ይሄ ውሻ እኮ ተኝቶ ያዘርፈኛል’ እያሉ እያሙኝ መሳቀቅ፣ እጣ ፈንታዬ ነበር፡፡ የት እሄዳለሁ ብዬ በጭንቀት ተጎሳቁዬ ነበር የምኖረው፡፡`
አህያ - “አሁን ግን አረጀንና አባረሩን፡፡”
ውሻ - “ታዲያ፣… አሁን ለምን አንድ አዲስ ሥራ አንጀምርም?”
አህያ - ‹‹ይሻለናል፡፡ የራስን ሥራ የመሰለ ነገር የለም፡፡ ግን፣ የዚህን አገር ነገር እንተውና ወደ ሌላ አገር እንሂድ፡፡ አንተም ዘበኝነትህን እኔም ሸክሜን በነፃነትና በምቾት እንሥራ አለው፡፡
በዚህ ውይይት መሰረት፣ ውሻና አህያ፣ ተይይዘው ወደ ሌላ አገር ተሰደዱ፡፡
እዚያ አገር እንደ ደረሱ፣ ጊዜ ሳያጠፉ፣ ብዙ ቦታ ሥራ ጠየቁ፡፡ ያገኙት ምላሽ ግን፣ እንደ ቀድሞው ነው፡፡ ያው ዘበኝነትና ያው ሸክም ነው፡፡ አዘኑ፡፡ ‹‹ወደ ዱሮ ጌቶቻችን ሄደን፣ ወደ ሥራችን እንዲመልሱን እንጠይቃቸው›› አለ አንዱ፡፡
‹‹መልካም ሀሳብ ነው፤ ወደነሱ ብንመለስ ይበጀናል›› አለ ሌላኛው፡፡
ተያይዘው ወደ ዱሮ ጌቶቻቸው ሄዱ፡፡
የዱሮ ጌቶቻቸው ግን፣ እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፡- ‹‹አይ ዘገያችሁ፡፡ ሌሎች ሥራ የራባቸው እንስሳት፣ በቦታችሁ ገቡባችሁ፡፡ እናም ሌላ ቦታ ሄዳችሁ ሞክሩ›› በሚል ምላሽ ተሰናበቱ፡፡ አዝነው ጎዳና ወጡ፡፡
* * *
አገርክን አትልቀቅ፡፡ የባሰ አገር አለ፡፡ ጠላ አለ ቢሉህ - ውሃ ረግጠህ አትሂድ፡፡ ይህ እውነት፣ ባህል ያጠመቀው፣ ታሪክ ያቆየው ሀቅ ነው፡፡ የምንጊዜም ችግራችን፣ የቆየውን አጠንክሮ አለመያዝና አዲሱን በአግባቡ መርምሮ አለመያዝ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ሁለቱንም አጣጥሞ መጓዝ፣ ወድደን የምንዳክርበት ግዴታችን ነው፡፡ ግን እጣፈንታ አይደለም፡፡ አማራጭ መንገዶችን ማጤን ወግ ነው፡፡ ወደፊት ለመሄድ፣ የኋላችንን ማስተዋል ግድ ይለናል፡፡ አገራችን፣ አሁንም በስደትና በመፈናቀል የተያዘች ናት፡፡ በሚገርም ሁኔታ፣ አገራችን መስቀለኛ መንገዷ ላይ፣ አበሳዋን እያየች ናት፡፡
በክፉ ዘመን ደግሞ፣ የሰው ሁሉ ስሙ አበስኩ ገበርኩ ነው፡፡
‹‹እውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ምድር፣
እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር››
ዞሮ ዞሮ፤
‹‹በእንጉሥ ፍርፋሪ የፋፋን ትል፣
አሳ አገኘችና፣ ቅርጥፍ!
አሳ አጥማጆች እሷን ቅርጥፍ!
ሆድን ሞልቶ እንደ ስልቻ፣
በልቶ ለመበላት ብቻ››
ይለናል ሐምሌት፡፡
ጉዞህ ለከርሞ ከሆነ፣ ጤፍ ዝራ፡፡
ጉዞህ የአምስት ዓመት ከሆነ፣ ባህር ዛፍ ትከል፡፡
ጉዞህ የዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር!

ኢትዮጵያ፣ ብርቅና ትልቅ አገር ናት፡፡ ትንሽ ሰው አንሁን፡፡


             የኖቤል ሽልማት፣ እንደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ሁለት መልክ አለው፡፡ በአንድ ፊት፣ ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ደረጃ የተመዘገበ፣ የድንቅና ብርቅ ታሪክ ባለቤት ናት፡፡ የኖቤል ሽልማትም፣ እንደ ልብ የማይገኝ ብርቅ ሽልማት ነው፡፡ በልባም ጥረት ግሩም ውጤቶችን በማስመዝገብ፣ በዓለማቀፍ መድረክ ጐልቶ የሚታይ ታሪክ በመስራት የሚመጣ ነው፡፡
በሌላ ፊት ግን፣ ኢትዮጵያ የተስፋ አገር ናት፡፡ ኖቤልም፣ የተስፋ ሽልማት፡፡ ኢትዮጵያ ከቀድሞ ታላቅነቷ የሚበልጥ ሌላ አዲስ ታሪክ ለመስራት፣ ወደ ላቀ ከፍታ ለመመንደግ፣ ልዩና እምቅ አቅም እንዳላት የሚታመንባት አገር ናት፡፡ ከግሪክ የጥንት ታሪክ ፀሐፊ ከሄሮዶትስ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች ድረስ፣ ከእስራኤል ከግብጽና ከሮም ነገስታት፣ የአይሁድና የክርስትና መሪዎች እንዲሁም ከነብዩ መሐመድ መልእክተኞች ጀምሮ፣ እስከ መካከለኛው ዘመን ሰባኪያንና አሳሾች ድረስ፣ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የስልጣኔ፣ የብልጽግና ምንጭ እንድትሆን፣ በብዙዎች ዘንድ የምትጠበቅ፣ የሚመኙላትና የሚተነብዩላት አገር ነበረች:: ይህ ልዩ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በአስደናቂው የአድዋ ድል ታድሶ ነው፣ ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን የተሻገረው፡፡
የአፍሪካ የነፃነት አርአያና ፋና እንድትሆን ብቻ ሳይሆን፣ በዓለማቀፍ ደረጃ - በሊግ ኦፍ ኔሽንስና በዩኤን በኩል ጭምር፣ ለዓለም ሰላም አለኝታ እንድትሆን ተስፋ የተጣለባት አገር ናት:: ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የኖቤል ሽልማት እጩ ሆነው መቅረባቸውም፣ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ተስፋ ይመሰክራል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ መቁረጥ የለም፡፡ ከቀድሞ ታሪኳ በተጨማሪ፣ አዲስ የላቀ ታሪክ እንደምታስመዘግብ፣ ለእልፍና እልፍ አመታት፣ በየዘመኑ የሚነገርላት የተስፋ አገር ናት - ኢትዮጵያ፡፡
የኖቤል ሽልማትም፣ የተስፋ ሽልማት ነው፡፡ በጥረት ለተመዘገበ ውጤትና በጽናት ለተሰራ ታሪክ፣ በአክብሮት የሚቀርብ ሽልማት እንደመሆኑ መጠን፣ በዚያው ልክ ‹‹የተስፋ እዳም›› ነው - የኖቤል ሽልማት፡፡ አድናቆትም፣ ማበረታቻም ነው፡፡
ድንቅ ውጤትን እያሞገሰ፣ ለላቀ አዲስ ውጤት፣ ከባድ የኃላፊነት ስሜትን ያሸክማል - ወደፊት የላቀ አዲስ ታሪክ የመስራት ኃላፊነትን በአደራ እየሰጠ፣ ለትጋት እምነት ይጥልብሃል፣ ስኬትን ተስፋ በማድረግ፡፡
- “በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ” እየተናቀ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ፀጋ ናት፡፡ ሰርተን  የፈጠርናት ሳትሆን፣ በመታደል ያገኘናት ድንቅ ስጦታ መሆኗን አለመገንዘባችን ጐዳን፡፡
- በዓለም ዙሪያ፣ በየዘመኑ፣ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች፣ “አገር” ለመፍጠር መከራ ያያሉ፡፡ የፈጠሯት አገር ገና በእግሯ ሳትቆም እየፈረሰች፣ በወረራና በጦርነት፣ በስርዓት አልበኝነትና በትርምስ - ሚሊዮኖች ያልቃሉ፡፡ ይሰደዳሉ:: ኑሮ አልባ ከርታታ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ አይነት አገር - አጦች ናቸው “ሚስኪን” የሚል ስያሜ የነበራቸው (ከኢትዮጵያ እስከ ፐርሺያ፣ ከአስራኤል እስከ ባቢሎን፣ ሚስኪን የሚለው ቃል ተመሳሳይ ትርጉም ነበረው - መጠለያ ያጣ አድራሻ ቢስ፣ መድረሻ ቢስ ማለት ነው፡፡)
በአለም ዙሪያ፣ ከጥቂት ጀግኖችና እድለኞች በስተቀር፣ አብዛኛው የሰው ልጅ፣ አገር የለሽ ነበር፡፡ አንድም በስርዓት አልበኝነት ኑሮው ተመሳቅሎ በአጭር እየተቀጨ ይረግፋል:: አንድም፣ ከስርዓት አልበኞችና ወረበሎች እየሸሸ፣ የተራራ እናት ላይ፣ ገደል ጫፍ ላይ ተንጠልጥሎ፣ ጐስቋላ አጭር እድሜውን ይገፋል፡፡ ጨለማ ዱር ውስጥ የአራዊት መጫወቻ ሆኖ ይቀራል፣ በሚያጥወለውል በረሃ በውሃ ጥም እየደረቀ፣ በየዋሻው በእልፍ የበሽታ ዓይነት እየወደቀ ያልቃል፡፡
አልያም፣ መጠጊያና መጠልያ ፍለጋ፣ “አገር እና ስርዓት ተፈጥሯል” ወደተባለበት አቅጣጫ ይሰደዳል፡፡ ነገር ግን፣ “አገርና ስርዓት” እንደልብ አይገኝም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ ብርቅዬ ነበር::
አገር ሆኖ ለረዥም ዓመታት መዝለቅ፣ እንደልብ አይገኝም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ:: ብርቅዬ ነበር፡፡ አገር ሆኖ ለረዥም ዓመታት መዝለቅ፣ እንደ ተዓምር ነው ተፈልጐ የማይገኝ አይነት፡፡
ለሺ ዓመታት በህልውና የሚቀጥል አገርማ፣ ምናለፋችሁ፣ በጣት የሚቆጠሩ ስሞች ብቻ ናቸው የሚጠቀሱት፡፡ ብዙዎቹ አንጋፋና አውራ አገራት ፈራርሰዋል፡፡ ስማቸው ጭምር ተረስቷል፡፡ አንዳንዶቹም፣ በአሸዋ ስር ተቀብረው፣ ምልክታቸው እንኳ ጠፍቶ፣ እንደ ተረት ብቻ የሚወራላቸው ሆነው ቆይተዋል - እንደነባቢሎን፡፡
በህልውና ከዘለቁት ጥቂት አገራት መካከል ናት ኢትዮጵያ፡፡  ከሞላ ጐደል፣ በወረራ ስትንበረከክ፣ በነፃነት፣ ሺ ዓመታትን ያስቆጠረች እስከዛሬም የዘለቀች አገር ማን ነው ቢባል፣ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሌላ አገር የለም - ኢትዮጵያ ናት፡፡   
ይሄ፣ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ፣ አገር ለመፍጠር፣ በህልውና ለማቆየት ሲሉ ብዙዎች ተሰቃይተዋል፡፡
ለተወሰነ ጊዜ ሲሳካላቸው፣ የዚያኑ ያህል ተደስተዋል ሲፈርስ እንደገና ሀ ብለው እየገነቡ:: ከዘመን ዘመን፣ ለህልውና መከራ ያያሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን፣ አገር ለመፍጠር ሳይሰቃዩ፣ ገና ድሮ ተፈጥራ በህልውና የቆየች ትልቅ አገር ይዘው፣ አገርን ይበልጥ በማሻሻል ላይ የማተኮር ሰፊ እድል አግኝተዋል፡፡ ወደተሻለ ከፍታ፤ በስልጣኔ ጐዳና እየተሻሻለች እንድትገሰግስ የማድረግ በቂ ጊዜና አቅም ይኖራቸዋል (ሌላው ዓለም፣ አቅምና ጊዜውን ሁሉ የሚያውለው አገርን በመመስረት ላይ በነበረበት ወቅት ማለት ነው)
ታዲያ፣ ኢትዮጵያ ትልቅና ብርቅ ፀጋ አይደለችምን? የከበረች ስጦታ ናት፡፡ አንደኛው ስህተት፣ የከበረች ድንቅ ፀጋ መሆኗ አለመገንዘብ ነው፡፡ የአላዋቂነት ነገር ከዚያም የባሰ የማጣጣልና የማጥላላት ክፋት አለ፡፡
ሁለተኛው ስህተት፣ ትልቅና ብርቅ ፀጋነቷን ከማክበርና ከማድነቅ ይልቅ፣ ስጦታነቷን በምስጋናና በፍቅር ተቀብሎ፣ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር ለመስራትና ለመጨመር ኃላፊነት ከመውሰድና በትጋት ከመጣር ይልቅ፣ ዛሬ አገሪቱን የፈጠሯት ያቆሟት ይመስል፣ የኩራት ባለቤት ለመሆን፣ የክብር መንፈስ ለማግኘት፣ ይራኮታል - ያልነበረበትንና የማያውቀውን ታሪክ በሽሚያ የራሱ ማድረግ የሚችል ይመስለዋል - “እኛ” የሚል ቃል በመደጋገም ብቻ ወይም በሃይማኖት ተከታይነትና በዘር ቆጠራ አማካኝነት ተጠግቶ “ብጋራ” ለማለት፣ የጥንት ሰዎች የሰሩትን ታሪክ፣ “በርቀት ለመውረስ”፣ “በጊዜ መዘውር” የኋሊት ተመልሶ፣ ስሙን በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለማስገባት ያምረዋል፡፡
ከመቶ እና ከሺ ዓመታት በፊት በሕይወት ከነበሩ ሰዎች እንኳ፣ “በአውቶማቲክ” የታሪክ ባለቤት አይሆኑም፡፡ ከወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል፤ አንዱ አዋቂ፣ ሌላኛው አላዋቂ፣ አንዲ ጥበበኛ፣ ሌላኛዋ ነገረኛ፣ ታላቅየው ሃኬተኛ፣ ታናሽየዋ ሰነፍና ገልቱ ትሆናለች፡፡
በቤተሰብ ውስጥ እንኳ፣ አንዱ የሌላውን ብቃት፣ አንዱ የሌላኛዋን ትጋትና ስኬት አየር ባየር መጋራትና መውረስ አይቻልም፡፡
ትክክለኛውና ቀናው መንገድ፣ አገርን ፈጥረው አንቅንተውና ጠብቀው ለማቆየት በትጋት የጣሩ፣ በጥበብ የሰሩ፣ በብቃት ስኬትን ያስመዘገቡ ሰዎችን (በስም ብናውቃቸውም ባናውቃቸውም፣ ታሪካቸው ቢመዘገብም ባይመዘገብም)፣ አኩሪ ስራቸውን በአድናቆት ማክበር፣ በምስጋና ስጦታቸውን መቀበል በዚህም የመንፈስ ልጆቻቸው መሆን፣ በተራችንም፣ እያንዳንዳችን፣ ፋይዳ ያለው ነገር ለመስራት፣ አዲስ ትልቅ ታሪክ ለመጨመር፣ በእውቀትና በጥበብ መትጋት ነው!


             የፔሩ ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራ ባለፈው ሰኞ የአገሪቱን ምክር ቤት መበተናቸውን ተከትሎ፣ ላቲን አሜሪካዊቷን አገር በጊዜያዊነት እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት ሜርሴድስ አራኦዝ ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣን ከተረከቡ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሜርሴድስ አራኦዝ ሰኞ የያዙትን የምክትል ፕሬዚዳንትነት ስልጣን፣ ማክሰኞ ለመልቀቅ የወሰኑት ሹመቱ የተከናወነው ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ በመሆኑ ህገ መንግስቱን የሚጥስ ነው የሚል ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ አራኦዝም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ፈርሷል የሚል አቋም በመያዛቸው ስልጣናቸውን በፈቃደኝነት መልቀቃቸውን በመግለጽ በአፋጣኝ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረባቸውን አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራ ምክር ቤቱን የበተኑት ተቃዋሚዎች አብላጫ ወንበር የያዙበት ምክር ቤት በመሆኑና ምክር ቤቱ የጸረ ሙስና ጥረታቸውን እያደናቀፈባቸው ወራትን በመዝለቁ እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፤ ተቃዋሚዎች ግን ወዲያውኑ ሜርሴድስ አራኦዝን በጊዜያዊነት አገሪቱን እንዲመሩ መሾሙን ጠቁሟል፡፡ አራኦዝ ከተሾሙ ከሰዓታት በኋላ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የፕሬዚዳንት ቪዛርካ ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን የገለጸው ዘገባው፤ የፖሊስና የጦር ሃይሉን ድጋፍ የያዙት ቪዛርካ በመጪው ጥር አዲስ የፓርላማ ምርጫ እንዲካሄድ ሃሳብ ቢያቀርቡም ምክር ቤቱ ግን ሰሞኑን አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ፣ ፕሬዚዳንት ቪዛርካን እስከ መጨረሻው ከስልጣን ለማባረር ድምጽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

 234 ሜ. ቁመት ያለው ህንጻው 203 ሚ. ዶላር ፈጅቷል


          በአፍሪካ አህጉር እጅግ ረጅሙ ህንጻ እንደሆነ የተነገረለትና 234 ሜትር ቁመት እንዲሁም 55 ወለሎች ያለው የደቡብ አፍሪካው ሊዎናርዶ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ከሳምንታት በኋላ በይፋ ተመርቆ ስራ እንደሚጀምር ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሌጋሲ ግሩፕና ኔድባንክ የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች በደቡብ አፍሪካዋ ጁሃንስበርግ ሳንድተን ሲቲ ውስጥ ከተማ በጋራ ያስገነቡትና ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት የሚውለው ሊዎናርዶ 203 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የጠቆመው ዘገባው፤ ህንጻው 254 አፓርትመንቶች፣ አምስት ወለል ቢሮዎችና ሱቆች፣ ሬስቶራንቶች፣ ጂም፣ ትምህርት ቤትና አረንጓዴ ስፍራ እንዳለውም አመልክቷል፡፡
ይህንን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ዲዛይን ያደረገው ኮአርክ ኢንተርናሽናል አርክቴክትስ የተባለ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ከኩባንያው 11 ባለሙያዎች መካከል ዘጠኙ ሴቶች መሆናቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
እስካሁን በአፍሪካ በቁመቱ ረጅም ተብሎ ሲጠቀስ የቆየው ህንጻ በዚያው በጆሃንስበርግ የሚገኘውና 222 ሜትር ቁመት ያለው ካርልተን ሴንተር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በአፍሪካ በቁመታቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ከያዙት ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች መካከል አራቱ በደቡብ አፍሪካዋ ጁሃንስበርግ፣ ሶስቱ በታንዛኒያዋ ዳሬ ሰላም፣ ሁለቱ በኬንያ መዲና ናይሮቢ አንዱ ደግሞ በናይጀሪያዋ ከተማ ሌጎስ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡              ህንድ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ በውጭ አገራት የሚኖሩባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗንና አገሪቷ በመላው አለም የሚገኙ ህንዳውያን ዲያስፖራዎች ቁጥር በ2019 የፈረንጆች አመት 18 ሚሊዮን ያህል መድረሱን ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራ ህንዳውያን የሚኖሩባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር አሜሪካ ናት ያለው መረጃው፤ በ2017 የፈረንጆች አመት ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ ብዛት 1.3 በመቶው የህንድ ዝርያ ያላቸው እንደሆኑ አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ የላቀ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ካቋቋሙት መካከል 8 በመቶ ያህሉ ህንዳውያን ዲያስፖራዎች እንደሆኑ የጠቆመው መረጃው፤ ጎግልና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ በርካታ ህንዳውያን በታላላቅ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዉስጥ በሃላፊነት እየሰሩ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡
በዲያስፖራ ብዛት ከአለማችን አገራት የሁለተኛነት ደረጃን የያዘችው ሜክሲኮ መሆኗን ያመለከተው  ተቋሙ፣ 11.8 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች በተለያዩ የአለማችን አገራት ውስጥ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡ ቻይና በ10.7 ሚሊዮን፣ ሩስያ በ10.5 ሚሊዮን፣ ሶርያ በ8.2 ሚሊዮን፣ ባንግላዴሽ በ7.8 ሚሊዮን፣ ፓኪስታን በ6.3 ሚሊዮን፣ ዩክሬን በ5.9 ሚሊዮን፣ ፊሊፒንስ በ5.4 ሚሊዮን እንዲሁም አፍጋኒስታን በ5.1 ሚሊዮን ዲያስፖራ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሶስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ እንደያዙም መረጃው ይጠቁሟል::
በአለማችን ከሚገኙ አጠቃላይ አለማቀፍ ስደተኞች መካከል ግማሽ ያህሉ በአስር አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ ያስታወቀው መረጃው፤ 19 በመቶው ወይም 51 ሚሊዮን ያህሉ በአሜሪካ እንደሚኖሩም ገልጧል፡፡
ጀርመንና ሳኡዲ አረቢያ 13 ሚሊዮን ያህል የሌሎች አገራት ዜጎች የሚኖሩባቸው ሲሆን ሩስያ 12 ሚሊዮን፣ እንግሊዝ 10 ሚሊዮን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ 9 ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳና አውስትራሊያ እያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን፣ እንዲሁም ጣሊያን 6 ሚሊዮን የሌሎች አገራት ዜጎች ይኖሩባቸዋል፡፡

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር አሰድ ሃሪሪ ከአንዲት ደቡብ አፍሪካዊት ሞዴል ጋር የድብቅ የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸውንና ከ16 ሚሊዮን ዶላር በላይ በስጦታ መልክ ሰጥተዋል መባሉን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካንዲስ ቫን ደር ሜርዌ ከተባለችው ታዋቂ ደቡብ አፍሪካዊት ሞዴል ጋር ከስድስት አመታት በፊት በሲሸልስ በሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ መተዋወቃቸውንና በወቅቱ የ20 አመት ወጣት እንደነበረች ያስታወሰው ዘገባው፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶም በድምሩ 16 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ እንደላኩላት መረጋገጡን አመልክቷል፡፡
በፋይናንስና ኢኮኖሚ ቀውስ እየተሰቃየች የምትገኘውን ሊባኖስ በመምራት ላይ የሚገኙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይሄን ያህል ገንዘብ ለግለሰቧ በስጦታ መልክ ማበርከታቸው ሊደረስበት የቻለው የደቡብ አፍሪካ የግብር መስሪያ ቤት በግለሰቧ ገቢ ላይ ባደረገው ምርመራ ከሊባኖስ ባንክ 16 ሚሊዮን ዶላር እንደተላከላት ማረጋገጡን ተከትሎ እንደሆነም ዘገባው አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገንዘቡ በተጨማሪ እያንዳንዳቸው 250 ሺ ዶላር የሚያወጡ ሁለት የቅንጦት መኪኖችን ለሞዴሏ በስጦታ መልክ ማበርከታቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

በአሜሪካ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሮቦቶች ሰዎችን በመተካት የሚያከናውኑት ስራ እያደገ መምጣቱንና በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ 200 ሺህ ያህል የባንክ ሰራተኞች ስራ በሮቦቶች ይነጠቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ዌልስ ፋርጎ የተባለ ተቋም የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአሜሪካ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ ለማዘመንና ለሰራተኞች የሚከፍሉትን ወጪ ለመቀነስ በአመት 150 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እያደረጉ ሲሆን ይህም ስራቸውን በሮቦቶች የሚነጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞች ስራዎቻቸውን በሮቦቶች ይነጠቁባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ የባንክ ክፍሎች መካከል ቅርንጫፍ ባንኮችና የጥሪ ማዕከሎች ይገኙበታል ያለው ተቋሙ፤ በእነዚህ ክፍሎች ከሚሰሩት ሰራተኞች መካከል 30 በመቶ ያህሉ ስራቸውን እንደሚያጡ አመልክቷል፡፡