Administrator

Administrator

 በተሰናበተው የ2011 ዓ.ም በርካታ ትኩረትን የሳቡ ነጠላ ዜማዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተመለከቷቸውንና ተወዳጆቹን እናስቃኛችሁ::
ከነዚህ መካከል በ“የኛ” የሙዚቃ ቡድን ውስጥ አድጋ “እንደኛ” ወደሚባለው ደረጃ ከተሸጋገሩት አምስት እንስት ድምፃዊያን አንዷና “ምን ልታዘዝ” ተከታታይ ድራማ ላይ ትተውን የነበረችው ድምፃዊት ዘቢባ ግርማ “ገራገር” ነጠላ ዜማ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ በተለቀቀ እለት ብቻ 500ሺህ ሰው ያየው ሲሆን፤ እነሆ በአንድ ወሩ ላይ 4.4 ሚሊዮን ሰው ተመልክቶታል:: የሙዚቃ አቀናባሪው ጊልዶ ካሳ ከሁለት ሳምንት በፊት የለቀቀው “ላገባ ነው” አዲስ ነጠላ ዜማ በሁለት ሳምንት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ሰው የመለተው ሲሆን፤ የራሄል ጌቱ “ጥሎብኝ” በ6 ወር አይቶታል፡፡ 10 ሚ. ተመልካች አይቶታል፡፡
በትግርኛ ቋንቋ የተዘፈነው የኤፍሬም አማረ “እሰይ አሰዬ” ነጠላ ዜማም በአንድ ዓመት ውስጥ 18 ሚሊዮን ሰው ሲመለከተው፣ የያሬድ ነጉ “አዲ መራ” በ9 ወር ውስጥ 8.7 ሚሊዮን ተመልካች አግኝቷል:: አሰጌ ዳንዳሾ ከሚካኤል መላኩ (ማይኮ) ጋር በጋራ የተጫወቱት “አኩኩሉ” ነጠላ ዜማ በ3 ወር ውስጥ 3 ሚሊዮን ህዝብ የተመለከተው ሲሆን፤ የሳንቾ “ታናሞ” ዜማ በ5 ወር 2.5 ሚሊዮን ሰው ተመልክቶታል:: የሳራቲ አንድ ነጠላ ዜማ በ10 ወር ውስጥ 3.6 ሚ ተመልካች ያገኘ ሲሆን፤ የዳጊ ዳንኤል “የባሌዋ ቆንጆ” ዘፈን በ4 ወራት ውስጥ 690ሺህ ተመልካች አግኝቷል፡፡ ሮፍናን “ልንገርሽማ” በተሰኘ ዜማው 226ሺ ተመልካች ሲያገኝ ይሁን የተባለው ድምፃዊ በቅርቡ የለቀቀው “ጀማሪ ጀማሪ ነኝ” ዘፈን በሁለት ወር ውስጥ 189 ሺህ ሰው አይቶታል፡፡
በሌላ በኩል፤ በዘንድሮ 10ኛው ዙር “አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” ላይ የኤፍሬም አማረ “እሰይ አሰዬ”፣ የያሬድ ነጉ “አዲመራ እና የራሄል ጌቱ “ጥሎብኝ” ነጠላ ዜማ በምርጥ ነጠላ ዜማ አምስት ውስጥ ዕጩ ሆነዋል፡፡


(ጌታቸው ዓለሙ፤ የ“ሰምና ወርቅ” ምሽት አዘጋጅ)


           “ሰምና ወርቅ” እስካሁን 21 ምሽቶችን አዘጋጅቷል፡፡ እኔ በመመስረት ደረጃ ሶስተኛ ነኝ:: አንደኛ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” ነው:: ሁለተኛ “ሀዋዝ” የኪነጥበብ ምሽት ነው፡፡ ከሁለት ዐመት በላይ ሆኖታል፡፡ ሦስተኛው “ሰምና ወርቅ” ነው፡፡ እንግዲህ ከኔ በኋላ እንኳን 10 የኪነጥበብ ምሽቶች ተፈጥረዋል:: በድምሩ እኔ እንኳን የማውቃቸው 13 የኪነ ጥበብ ምሽቶች አሉ፡፡ መብዛታቸው ምንም ጥያቄ የለውም:: የስነ ጽሑፉን ዘርፍ በማሳደግም ሆነ ሃሳቦችን በማስተናገድ በኩል ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል:: ከኪነ ጥበብ ውጭ አብረው እየተሰሩ ያሉትንም ዘርፎች  ከፍ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ፍልስፍና፣ ባህልና መሰል ዘርፎች ራሳቸውን ችለው ካልሆነ በስተቀር አይነሱም ነበር፡፡ ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች  ግጥሙን፣ ሙዚቃውን፣ ስዕሉን ብቻ ማዕከል ያደረጉ ነበሩ፡፡ አሁን በተለያየ ሃሳብ ላይ ብዙ ምሁራን ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት፣ እኛም እነሱን የምናገኝበት መድረክ ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል፤ በአንድ ተሰጥኦ ብቻ የምናውቃቸው ባለሙያዎች፣ ሌላ አስደናቂና ወደ መድረክ ሳያወጡት የቆዩትን ችሎታ የምናይበት እድል ፈጥሮልናል፡፡ ለምሳሌ አርቲስት ፍቃዱ ከበደን የምናውቀው በትወናው ብቻ ነበር፡፡ ግን አስገራሚ ወጐችን ይጽፋል፣ መጽሐፍም አሳትሟል:: ስፔሻሊስት ሀኪም ሆነው የበቁ የግጥም ፀሐፊዎች፣ ዲስኩር አቅራቢዎች… እነዚህን መድረኮች እያገኙና እያስተዋወቁን ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምሽቶች፤ ኪነ ጥበብ ከምንለው አጥር ወጥተው በሀገር፣ በታሪክ፣ በአኗኗርና ባህል ላይ ሁሉ  እንድንወያይ… ሃሳብ እንድንጋራ እያደረጉ ስለሆነ፣ መብዛታቸው መጥፎ ጐኑ አይታየኝም፡፡ በርግጥ በየመድረኩ በተደጋጋሚ የሚታዩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በተለያዩ መድረኮች ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀርባሉ ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ በተለይ አንባቢዎቹ  ሃሳብ አያልቅባቸውም፤ ባለምናብ ሰዎች፣ አስር ቦታም ቢጋበዙ… አስር የተለያየ ግን ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳዮቹን ያነሳሉ፡፡ አያሰለቹም፡፡ በሌላ በኩል፤ በኪነ-ጥበብ አዘጋጆች መካከል ፉክክር የሚመስል ነገር አለ፡፡ እከሌ ምሽት ላይ መጥቶማ እኔ ምሽት ላይ መቅረት የለበትም አይነት ፉክክር ማለቴ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ተመሳሳይ ፊቶች የሚቀርቡት፤ በከተማችንም ሆነ በአገራችን እጅግ የጠለቀ ሃሳብ ያላቸው፣ ተቆጥረው የማያልቁ  ከያኒያን ሞልተዋል፡፡  
እኛ በ2010 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ነው “ሰምና ወርቅ”ን ማቅረብ የጀመርነው፡፡ እስካሁን በተለያዩ ሃሳቦች ላይ 21 ምሽቶችን አካሂደናል:: ታዳሚያንን በተመለከተ ትንሹ ታዳሚያችን 300 ሰው ነው፤ ትልቁ ከ1200 ሰው በላይ ነው::
አንዳንዴ አዳራሽ ሞልቶ ሰው የሚመለስበት ሁኔታም አለ፡፡ ለምሳሌ “ያልታመመ አዕምሮን እንዴት ማከም ይቻላል” በሚል ርዕስ ከዶ/ር ወንድሙ ነጋሽ ጋር ባዘጋጀንበት ጊዜ ብሔራዊ ቴአትር ሞልቶ ሰው ተመልሶ ነበር፡፡ 1400 ሰው ገብቶ ነው ቀሪው የተመለሰው፡፡
በአጠቃላይ የኪነጥበብ ምሽት በነዚህ ሁሉ ነገሮች መካከል እየተሽከረከረ ያለ ስራ ሆኗል ለማለት ነው:: ሌላው እኔ ምሽት ላይ ቆንጆ ሃሳብ ያቀረበን ሰው፣ ሌላው አዘጋጅ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዲያቀርብ ቢጋብዘው ችግር የለውም፡፡ ይሄ በቅንነት ቢታይ መልካም ነው፡፡ በፉክክር የሚመስለው ነገርና በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማዘጋጀቱ ግን  ኪሳራ ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ ዋና ዓላማው፤ ማዝናናት፣ ማስተማርና ማሳቅ ነው ባይ ነኝ፡፡    ‹‹ንባብ የተነቃቃበት ዓመት ነው››
                             (ሰይፈዲን ሙሳ፤ በጃፋር መፃሕፍት መደብር የማርኬቲንግ ባለሙያ)

             በዓመቱ በርካታ መጻህፍት ለገበያ ቀርበዋል:: ከሌሎቹ አንፃር የግጥም መጽሐፍት በርከት ብለው ይወጡ ነበር፡፡ በአሁኑ አመት ግን በተለየ መልኩ የታሪክና የፖለቲካ መጽሐፍት ገበያውን በደንብ ተቆጣጥረውታል፡፡ ተነባቢም ነበሩ፡፡ የአንዳርጋቸው ጽጌ “እኛም እንናገር ትውልድ አይደናገር”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌላው የመምህር ታዬ ቦጋለ ‹‹መራራ እውነት›› ሲሆን በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ነው፡፡ በልቦለድ ዘርፍ በተለየ አቀራረብ የመጣው የደራሲ አለማየሁ ገላጋይ “ውልብታ“ በደንብ የተሸጠና የተነበበ መጽሐፍ ነው፡፡ ሌላው በኤርሚያስ አመልጋ የህይወትና የሥራ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው “የማይሰበረው- ኤርሚያስ አመልጋ”፤ ተነባቢ ነበር፡፡ የዶ/ር ኤርሲዶ ለንዶቦ “ኑሮ ማፕ” እንዲሁ  በደንብ ተሸጧል፡፡
በቅጂ በኩል የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍን ስንወስድ፣ 30 ሺ ኮፒ ታትሞ ነበር፤ በሙሉ ተሸጦ አልቋል፡፡ የታዬ ቦጋለ “መራራ እውነትም” 30ሺ ኮፒ ታትሞ፣ ተሸጦ እየተጠናቀቀ ነው:: “ኑሮ ማፕ” ህይወትን እንዴት መምራትና መለወጥ እንደሚቻል መንገድ የሚያሳይ አነቃቂ መጽሐፍ ነው፡፡ 10 ሺህ ኮፒ ታትሞ በአንድ ሳምንት ውስጥ አልቋል፡፡ የአለማየሁ ገላጋይ “ውልብታ”ም በአንድ ሳምንት 10 ሺህ ኮፒ አልቋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከቀድሞው በተለየ መልኩ የህትመት ቁጥር እንዴት ጨመረ ከተባለ፣ ከዚህ ቀደም ያለው ልምድ፣ አንድ መጽሐፍ ሲታተም ፍራቻ ስለሚኖር፣ በተለይ ታዋቂ ፀሐፊ ካልሆነ፣ 3ሺህ፣ ቢበዛ 5ሺህ ኮፒ ነበር፡፡ አሁን ግን አሳታሚም ፀሐፊም እየደፈረ፣ እስከ 30ሺ ኮፒ እያሳተመ ነው:: ያ ማለት የንባብ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ የንባብ መነቃቃቱ ከምን የመጣ ነው ከተባለ፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ሲለዋወጥ፣ አዲስ መሪ ሲመጣ፣ አይዲዮሎጂ ሲቀየር፣ አዳዲስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲመጡ፣ አዳዲስ አመራሮች ሲለወጡ…በአጠቃላይ የፖለቲካ ትኩሳቱ ከፍና ዝቅ ሲል፣ የህብረተሰቡን መረጃ የማግኘትና የማወቅ ጉጉት ስለሚጨምሩት ወደ ንባብ ያዘነብላል፡፡
ፖለቲከኞችም ስለ አገር ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ጉዳይ ይጽፋሉ፡፡ የህይወት ታሪካቸውን  ጭምር ሲጽፉ ሰው ያነባል:: ለዚህ ነው ዘንድሮ የንባብ መነቃቃትም፣ የመጽሐፍት ህትመት ቅጂም መጨመር የታየው፡፡ ከላይ የጠቀስኩልሽ ፀሐፊዎችም፣ የታሪክ ባለቤቶችም ተጽእኖ በመፍጠር ረገድ ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ዘመኑም እንድታነቢ ያስገድድሻል፡፡ ምክንያቱም ካላነበብሽ ከመረጃ ወደ ኋላ እንደምትቀሪ፤ ከሌላው እኩል በእውቀት እንደማትራመጂ ታውቂያለሽ፡፡ ስለዚህ የግድ ማንበብ አለብሽ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቀውን የሃሳብ ውሽንፍር ለመለየት፣ የግድ መጽሐፍትን ወደ ማጣቀስ ትመጫለሽ፡፡ ይሄ ሁሉ ንባቡን አነቃቅቶታል:: ግን በቂ አይደለም፡፡ በአገራችን ላይ ያለው የህዝብ ብዛትና የሚታተመው የመጽሐፍት ቁጥር ምንም አይቀራረቡም፡፡ አሁን የልጆች መጽሐፍት የሉም በሚያስብል ደረጃ ያለ ነው፤ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በልቦለድ በኩል፤ የዓለማየሁ ገላጋይ “ውልብታ” እና የሀብታሙ አለባቸው “አንፋሮ” ጐላ ብለው ወጥተዋል፡፡ የገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)፣“ኢህአፓና ስፖርት” ከታተመ ቆይቶ ነበር፡፡ ግን በዚህ ዓመት በድጋሚ ታትሞ  በደንብ ተሸጧል፡፡ የወጐች ስብስብ ነው፡፡ የግጥም መጽሐፍት በብዛት ቢታተሙም አንባቢ ፊት ይነሳቸዋል፡፡ ዘንድሮ ግን አንባቢያን የግጥም መጽሐፍ ርዕስ ጠርተው መግዛት መጀመራቸው አስደምሞናል፡፡ ለምሳሌ የመዘክር ግርማ “ወደ መንገድ” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ በደንብ ተሸጧል፡፡ በቅርብ ከወጡት ውስጥ የዮናስ ኪዳኔ “የነፋስ መሰላል”ም ተሸጧል፡፡ “የሽልንግ ተሳፋሪዎች” የተሰኘውም እንዲሁ በደንብ ተሸጧል:: ከበፊቱ አንፃር ያስደንቀናል፡፡
የንባብ ባሕል እንዳይዳብር ማነቆ ሆኗል ብዬ የማምነው የወረቀት ዋጋ መወደድ ነው:: የወረቀት ዋጋ መወደዱም ብቻ ሳይሆን ወረቀት የሚያስመጡትም ነጋዴዎች በቁጥር ማነስም ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ከፈለጉ ያስወድዱታል፡፡ ከፈለጉ ደግሞ እጥረት እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ የቀረጡ ከፍተኛ መሆንም ተደማምሮና እነዛ ጥቂት አስመጪዎች ገበያውን በግል መቆጣጠራቸው ተጨማምሮበት፣ የመጽሐፍን ዋጋ አንረውታል፡፡ የንባብ ባህል እንዲዳብር በጥብቅ አለመሰራቱም፣ ሌላው የንባብ ማነቆ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ከመንግሥት፣ ከግለሰቦችና ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ስራ ይመስለኛል፡፡ ንባብ በመሰረታዊነት እንደ ልብስ መጠለያና ምግብ አስፈላጊ ሆኖ እንዲወሰድ መደረግ አለበት፡፡
ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ 5 ሚሊዮን ህዝብ ይኖራል እንበል፡፡ አንድ ሚሊዮን ያህሉ የተማረ፣ የሚያነብ፣ የሚመራመር ነው ብለን ብንወስድ፣ አንድ መጽሐፍ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ 3ሺ ኮፒ ብቻ ነው የሚታተመው፡፡ በአማካይ ስናስበው ከኔጌቲቭ በታች ነው፡፡ ለ1 ሚሊዮን ህዝብ ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን መጽሐፍ መታተም አለበት:: መጽሐፍም በብዛት ሲታተም ዋጋው ይቀንሳል፡፡ 3ሺ ኮፒ ሲታተምና 40ሺ ኮፒ ሲታተም፣ የመጽሐፍ ዋጋ እኩል አይደለም፤ 40ሺ ሲሆን ዋጋው ይቀንሳል፡፡
የንባብ ባህል እንዲዳብር፣ አዳዲስ ፀሐፍት እንዲበረታቱ፣ ውይይቶች እንዲዳብሩ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት፡፡ የአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ብቻ ሀላፊነት አይደለም ባይ ነኝ:: በእናት ማስታወቂያና በሚዩዚክ ሜይዴይ የሚሰናዱ ውይይቶች መበረታታት አለባቸው:: የሽልማት ድርጅቶችም መስፋፋት አለባቸው እላለሁ፡፡ በንባብ ለውጥ ያመጡ ሰዎችን ወደ አደባባይ እያመጡ መሸለምና ማወደስም ሌሎች አንባቢዎችን ያፈራል:: ይህም መጠናከር አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ እናንብ እላለሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት እመኛለሁ!!  


                          - የዘንድሮ የሽልማት ሥነስርዓት ጥቅምት 11 ይካሄዳል
                           - የትምህርትና የምርምር መጻሕፍት በሽልማቱ ውስጥ ተካትተዋል

          በልጆች መጻሕፍት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የንባብ ባህልን ለማዳበርና ሥነ ጽሑፍን ለማበረታታት ታልሞ የተቋቋመው ‹‹ሆሄ›› የሽልማት ድርጅት፤ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አወዳድሮ ይሸልማል። በዚህ ዓመት በኦሮምኛና ትግርኛ ቋንቋ የተጻፉ የህፃናት መጻሕፍትን
እንዲሁም የትምህርትና የምርምር ሥራዎችን በሽልማቱ ውስጥ መካተታቸውን ከ‹‹ሆሄ ሽልማት” ዋና አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ ለመሆኑ የ‹‹ሆሄ›› የሦስት ዓመት ጉዞ ምን ይመስላል? ስኬቶቹና ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው? የአዲስ አድማሱ ደረጀ በላይነህ ከ“ሆሄ ሽልማት” ዋና
አስተባባሪ ጋር በሽልማት ድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ እንደሚከተለው አውግተዋል፡፡ ፡-

         የሽልማ-ት መርሀ ግብሩ እንዴትና በምን ሁኔታ ተጀመረ?
የ“ሆሄ ሽልማት” የተጀመረው በ2009 ዓ.ም ነው:: ዋና ዓላማው ሥነ ጽሑፍን ማበረታታትና የንባብ ባህልን ማዳበር ነው፡፡ በተለይ የልጆች የንባብ ልማድ እንዲዳብር ለማድረግ በሚል የተጀመረ ነው፡፡ ይህንን የሽልማት ድርጅት ስንመሰርት፣ ከዚህ በፊት በአገራችን የነበሩ የሽልማት ፕሮግራሞችን ለመቃኘት ሞክረናል:: የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት፤ ከዚያም በ1990ዎቹ የነበረ የኪነ ጥበብ ሽልማት ድርጅት አሰራርን አይተናል፡፡ የዳኞቹን ሁኔታ፣ መስፈርቶቹንና የሽልማቱን ዓይነት በመቃኘት ራሳችንን ለማዘጋጀት ብዙ ተጠቅመንበታል፡፡
እንግዲህ እነዚህንና የመሳሰሉትን ልምዶች ገምግመንና ቀስመን ነው የሆሄ ሽልማት ፕሮግራምን ለማዘጋጀት እየጣርን ያለነው:: ለጊዜው ይህንን ሽልማት ሀላፊነቱን ወስዶ የሚያካሂደው ‹‹ኖርዝ ኢስት ማርኬቲንግ››  የተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቢሆንም ያንድ ድርጅት ፍላጎት ማንፀባረቂያ እንዳይሆን አስራ አምስት አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የሽልማት ዝግጅቱን የሚመራው፣ ዘርፎቹን የሚመርጠው፣ ዳኞቹን የሚሰይመውና አጠቃላይ የፕሮግራሙን ይዘት የሚያቀናጀው ይኼ  ኮሚቴ ነው፡፡ ይህም  የሽልማት ፕሮግራሙ ነፃነቱን ጠብቆ በተዓማኒነት እንዲሰራ አድርጎታል:: ከዚህም ባሻገር የመጻሕፍቱ ዘርፍ ሦስት ሦስት ዳኞች እንዲኖሩት፣ ዳኞቹ ደግሞ በተሰማሩበት ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ፣ ልምድና ዕውቀት ያላቸው እንዲሆኑ ተመርጠው፤ ምክንያታዊና አሳማኝ በሆነ መንገድ እንዲሰራ አድርገናል፡፡ ሥራው ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ ባሰብነው አይነት እየሄደ ነው፡፡ በሥነ ጽሑፍ ቤተሰቡ ዘንድ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ‹‹ለምን የኔ መጽሐፍ ከአምስቱ ምርጥ ውስጥ አልተካተተም?... ዳኞቹ እነማን ናቸው? መጻሕፍቱ በምን መንገድ ተመረጡ? መመዘኛው ምንድነው?›› ከሚለው ማጉተምተም ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ ተቀባይነትና ተዓማኒነት እያገኘ መጥቷል:: በዚህ መሰረት ይኸው ዘንድሮ ሦስተኛውን ዙር የሽልማት ፕሮግራም እያዘጋጀን ነው፡፡
በዚህ የሽልማት ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላችሁ ግንኙነት በምን ላይ የተመሰረተ ነው?
የሽልማቱ ፕሮግራም በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ፍሬያማ ይሆን ዘንድ፣ ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ፣ ከትምህርትና ተዛማጅነት ካላቸው ተቋማት ጋር መስራት የተሻለ ውጤት ይኖረዋል የሚል ሀሳብ ስላለን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና መጽሐፍት ኤጀንሲ ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሉ የሥነ ጽሑፍ ምሁራንም ባቋቋምነው አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ታቅፈው ብዙ እገዛ ያደርጉልናል:: ከዚህም ባለፈ የተቋማቱ አብሮነት የሽልማቱን ከበሬታ ከፍ ያደርገዋል የሚል እምነት አለን፡፡
ከእነርሱ ሌላ የተለያዩ ትብብር የሚያደርጉልን ተቋማትም አሉ፡፡ ትምህርት ላይ ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል ‹‹ጄኔቫ ግሎባል›› የተሰኘው የአሜሪካ ድርጅትና የጀርመን የባህል ተቋም ይጠቀሳሉ:: በሚዲያም ተባባሪዎች አሉን፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ነው፡፡ ይህን ፕሮግራም በማስተዋወቅ በያመቱ የተመረጡትን መጻሕፍት ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፤ እያገዘን ነው፡፡ “ሪፖርተር” ጋዜጣና ኢቢኤስም ትብብር ያደርጉልናል፡፡ ሁሉንም እናመሰግናለን፡፡
ውድድሩን አዘጋጅታችሁ ሽልማት ከሰጣችሁ በኋላ መርሃግብሩ በደራሲውም ሆነ በሕብረተሰቡ ዘንድ  የሚፈጥረውን ስሜትና ተፅዕኖ ትገመግማላችሁ?
የሽልማቱ መርሀ ግብሩ ምን ለውጥ አምጥቷል? የሚለውን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ብዙም የማይታወቁ መጻሕፍት ወደ አደባባይ ወጥተው እንዲተዋወቁና እንዲነበቡ በማድረግ ረገድ ሽልማቱ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው:: ወጣት ፀሐፍት በመጀመሪያው ሥራቸው ከትላልቅ ደራስያን ጋር ተወዳድረው ያሸነፉበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ “የአመቱ ምርጥ አምስት መጻሕፍት” ዝርዝር ውስጥ የገቡ ጀማሪ ደራስያንም አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹ወሰብሳቤ›› የሚል መጽሐፍ ደራሲ ሲሆን ሁለተኛ መጽሐፉን ሲያሳትም፣ መግቢያው ላይ ስለ ሽልማት ፕሮግራማችን በዝርዝር ጽፏል፡፡
እንደዚህ አይነት ነገሮች እኛንም ያበረታቱናል:: በመጀመሪያው ዙር ተሸላሚ ከሆኑት ደራሲያን መካከል አንዱ አዳም ረታ ነው፡፡ አዳም ረታ የአገራችን ትልቅ ደራሲ ነው፡፡ እኛም ለርሱ ትልቅ ከበሬታ አለን፡፡ በመጽሐፍት ሽያጭ አካባቢ የሚሰሩ ሰዎች፣ ከሽልማቱ መርሀ ግብር በኋላ የመጽሐፉ ሽያጭ በተወሰነ ደረጃ መጨመሩን ገልፀውልናል፡፡ እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ውጤታችንን ለመገምገም ይረዱናል፡፡
የሽልማት መርሃ ግብሩን በማዘጋጀት ሂደት የሚገጥሟችሁ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ይህን መርሀ ግብር ስናዘጋጅ ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥሙናል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ  ከሥነ ጽሑፍና ከንባብ ጋር ያለው ልምምድ በጣም አናሳ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና አንድ መጽሐፍ ደራሲው ረቂቁን ካዘጋጀበት ጊዜ ጀምሮ መጽሐፍ ሆኖ ለገፀ ንባብ እስኪበቃ ድረስ የሚያልፍበት ብዙ ሂደት አለ፡፡ ከዚህም አልፎ ሥርጭቱ ሳይቀር የደራሲው ሸክም ነው:: በሌላው አለም የተደራጁ አሳታሚዎች ስላሉ ብዙውን ሥራ ያቃልሉለታል፡፡ እኛ አገር ግን ሁሉም እዳ በደራሲው ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑ ነገሩን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መጻሕፍት ወደ ተደራሲው እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡
እኛም በዚህ የሽልማት ሂደት ውስጥ በርካታ ሰዎች መጻሕፍት ጽፈው በእጃቸው እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ የመጀመሪያው ዙር የልጆች መጻሕፍት አሸናፊ የነበረው አስረስ በቀለም ጥቂት የማይባሉ የልጆች መጻሕፍት ጽፎ እንዳስቀመጠና የሕትመቱ ጉዳይ አስቸጋሪ እንደሆነበት ነግሮናል፡፡ እነዚህ ነገሮች የተሻሉና የተጠናከሩ ቢሆን የሽልማቱም ድርጅት የተጠናከረ እንዲሆን ያግዘው ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ችግር እያለም ቢሆን በየአመቱ በሚካሄደው የሽልማት መርሀ ግብር ውስጥ አንደኛ የሚወጡት፣ ምናልባትም ምርጥ አምስቱ ዝርዝር ውስጥ የሚገቡትም ሳይቀር አሳታሚ የማግኘት ዕድላቸውን ይጨምራል የሚል እምነት አለን:: በዚህ ጉዳይም ላይ የተሻለ ነገር ለመስራት ጥረት እያደረግን ነው:: በተለይ ከአሳታሚ ጋር ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የእኛም ዓላማ ንባብን ማበረታታት ስለሆነ በያመቱ ከመጻሕፍቱ ባሻገር ‹‹ለንባብ መዳበር አስተዋጽኦ ያደረጉ›› ግለሰቦችንና ተቋማትን እንሸልማለን፡፡ በዚህ ረገድ በየጋዜጦች ላይ መጻሕፍትን የሚገመግሙና ሂሳዊ ዳሰሳ የሚሰሩ፣ አዳዲስ መጻሕፍትን የሚያስተዋውቁ ግለሰቦችና ተቋማት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለን እናምናለን፡፡ አዳዲስ መጻሕፍት ላይ ውይይት የሚያካሂዱ ክበባት፣ የሬዲዮ ትረካና ፕሮግራም የሚያቀርቡ ተቋማትን እየመረጥን ሽልማት እንሰጣለን፡፡ ለአይነ ስውራን መጽሐፍትን ወደ ብሬል የሚቀይሩና በድምጽ የሚያዘጋጁትንም እንሸልማለን፡፡ የአሳታሚነት ሥራ እንዲበረታታና የሕትመት ዋጋ በጣም እንዳይወደድ በማድረግ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል የሚል እምነት አለን፡፡
የሽልማት ዝግጅቱን ወጪ እንዴት ነው የምትሸፍኑት?
ይህን ሥራ ለመሥራት አንዱና ከባዱ ችግር የስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ነው፡፡ ከስራው ጋር የተያያዙ ለማስቀረትና ለመቀነስ የማይቻሉ ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡ ሥራውን የምንጀምረው የአመቱ መግቢያ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ መጻሕፍቱን መሰብሰብ፣ ለየዘርፉ ዳኞች ማድረስ፣ የተመረጡት መጻሕፍት ድምፅ እንዲሰጥባቸው ማድረግ እንዲሁም፤ የራሳችንን የማህበራዊ ሚዲያ ማስተዳደር የመሳሰሉት ሥራዎች በጣም ከባድ ናቸው፡፡ እነዚህን ወጪዎች  የሚሸፍኑልን ስፖንሰሮች ለማግኘት በያመቱ ብዙ ጥረት ብናደርግም ብዙም የተሳካ አይደለም፡፡ ከመጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ እያገዘን ያለው ‹‹ሄንከን ቢራ›› ሲሆን፤ ዘንድሮም በ“ሶፊ ቡና›› ምርቱ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ የሽልማት ድርጅቱ እንዳይቋረጥ ባለው ቀናነት የተነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ተቋም ነው፡፡ ሌሎችም አነስተኛ ድጋፍ የሚያደርጉልን አሉ፡፡ አንዱ ‹‹ጄኔቫ ግሎባል›› የሚባል በልጆችና ጎልማሶች ንባብና ትምህርት ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው:: ‹‹ስቱዲዮ ኔት›› የተባለ ድርጅት የምናዘጋጃቸውን ፕሮግራሞችና ማቴሪያል ዲዛይን በማድረግ ያግዘናል:: በርካታ ግለሰቦችም ለዚህ ሥራ የራሳቸውን ጊዜ መስዋዕት አድርገው እየደገፉን ነው፤ ያለ እነርሱ ድጋፍ እዚህ ደረጃ መድረስም አንችልም ነበር፡፡
በሚቀጥሉት አመታት ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ሌሎች መንገዶችን ለመሞከር እያሰብን ነው፡፡ ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ድርጅቱ እንደ አካዳሚ ሆኖ እንዲዋቀር ለማድረግ ከሥነ ጽሑፍ ዘርፍ፣ ከአካዳሚክ ማህበረሰቡ፣ ከጋዜጠኞችና ደራስያን እንዲሁም ከንግዱ ሴክተር አባላትን በመመልመል የተወሰኑት የአባልነት መዋጮ የሚያደርጉበትን፣ ከዚያም ባሻገር ገንቢ ሀሳብ የሚያዋጡበትን ዕድል ለመፍጠር እንሰራለን፡፡ የአባላቱ ቁጥር በጨመረ መጠን ሽልማቱ ይበልጥ ተአማኒና ተቋሙም ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል ብለን እናምናለን፡፡ ከአባላት በሚገኙ መዋጮዎች አንዳንድ የሥራ ወጪዎችን መሸፈን የምንችልበትን መንገድ እያጠናን ነው፡፡
የመንግሥት ተቋማትስ አያግዟችሁም?
ከአዲስ አበባ የባህልና የኪነ ጥበብ ቢሮ ጋር አብረን እየሰራን ነው፡፡ በዚህ አመት አንዳንድ ድጋፍ እናደርግላችኋለን ብለውናል፡፡ ‹‹አብረን ብንሰራ ጥሩ ነው፤ ልትደግፉን ይገባል” እያልናቸው ነው:: የመንግስት ተቋማት ይህንን አገራዊ ፕሮግራም የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከተለያዩ ግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶች እየተለመነ መዝለቅ አይቻልም፡፡ መጻሕፍት ትውልድን ይቀርፃሉ:: ስለዚህ የደራስያን ገቢ የሚሻሻልበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ይህን የማሻሻል ኃላፊነት መንግሥትንም ይመለከታል፡፡
በዚህ አመት አዲስ የሸልማት ዘርፎች መጀመራችሁን ሰምቼአለሁ…
ትክክል ነው፡፡ ዘንድሮ በኦሮምኛና በትግርኛ የተጻፉ የልጆች መጻሕፍት አወዳድረን እንሸልማለን:: በሚቀጥሉት አመታትም በሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች ላይ በተለይ በሕጻናት መጻሕፍት አካባቢ የተሻለ መነሳሳት እንዲፈጠር እንፈልጋለን:: በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ የትምህርትና የጥናት ውጤቶችን ስለሚያሳትሙ፣ ይህንንም ዘርፍ በሽልማቱ መርሀ ግብር ለማካተት ሞክረናል። መስከረም የመጨረሻው ሳምንት ላይ ለፍጻሜ ውድድር የደረሱትን መጻሕፍት እናስተዋውቃለን:: ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም የሽልማት ሥነስርዓቱ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡ የዚህ አመቱ ፕሮግራም በተሻለና በተሳካ ሁኔታ ይካሄዳል ብለን እናምናለን፡፡


በአለማችን በግዙፍነቱ አቻ እንደማይገኝለት የተነገረውና 63 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የቻይናው ቤይጂንግ ዳክሲንግ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ  ባለፈው ረቡዕ በይፋ መመረቁን ፎርቹን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በተገኙበት በይፋ የተመረቀውና ከመዲናዋ ቤጂንግ በ40 ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ 18 ስኩየር ማይል ቦታ ላይ ያረፈው የአለማችን ግዙፉ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ግንባታው አምስት አመታትን ያህል እንደፈጀ ተነግሯል፡፡
98 የእግር ኳስ ሜዳዎችን ያህል ስፋት ያለው ቤይጂንግ ዳክሲንግ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በመጪዎቹ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 45 ሚሊዮን ያህል መንገደኞችን በማስተናገድ ከአለማችን አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች በመስተንግዶ የአንደኛ ደረጃን ለመያዝ ማቀዱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ እጅግ ፈጣኑን 5ጂ ኔትወርክ ጨምሮ በረቀቁ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች እንደተሟላ የተነገረለት አውሮፕላን ማረፊያው፤ በሚያስተናግዳቸው አውሮፕላኖች ቁጥርና በዘመናዊ መስተንግዶውም እጅግ የላቀ እንደሆነ ተገልጧል፡፡               የኢንዶኔዢያ ፓርላማ ከትዳር በፊት ወሲባዊ ግንኙነት ባደረጉና የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ባዋረዱ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ቅጣት በሚያስጥለው አዲስ ረቂቅ ህግ ላይ ውይይት መጀመሩን ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢንዶኔዢያውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
ትዳር ሳይመሰርቱ ወሲባዊ ግንኙነት ሲያደርጉ የተገኙ የአገሪቱ ዜጎችን በአንድ አመት እስራት ያስቀጣል በተባለው ረቂቅ ህግ ላይ ባለፈው ማክሰኞ ውይይት ያደረገው ፓርላማው ምንም እንኳን በዕለቱ ረቂቅ ህጉን ሳያጸድቀው ቢቀርም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአገሪቱ ዜጎች ግን  በፓርላማው ደጃፍ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አዲሱ ህግ ከዚህ በተጨማሪም ትዳር ሳይመሰርቱ አብረው የሚኖሩ ጥንዶችን በስድስት ወራት እስር፤ የጤና ችግር ወይም አስገድዶ መድፈር ካላጋጠመ በስተቀር የጽንስ ማቋረጥ የፈጸመን ደግሞ አራት አመት በሚደርስ እስር እንደሚያስቀጣ የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የመንግስት ተቋማትን፣ ሃይማኖትን፣ ሰንደቅ አላማንና ብሄራዊ መዝሙርን አለማክበርና ማዋረድም ህገወጥ ተግባር እንደሆነ የሚያትት ነው ብሏል፡፡
ፓርላማው ረቂቅ ህጉን የሚያጸድቅበትን ቀን ቢያራዝምም ኢንዶኔዢያኑ ግን መጽደቁ አይቀርም በሚል በመዲናዋ ጃካርታ አደባባይ ወጥተው ከፖሊስ ጋር እየተጋጩ መሆናቸውንና ተቃውሞው ወደሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በአለማችን ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያፈሩ 2 ሺህ 124 አዳዲስ እጅግ ባለጸጎች መፈጠራቸውንና በአለማችን የሚገኙ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው እጅግ ባለጸጎች ቁጥር 265 ሺህ 490 መድረሱን  ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ዌልዝ ኤክስ የተሰኘው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአለማችን የተለያዩ አገራት የሚኖሩት የእነዚህ 265 ሺህ 490 እጅግ ባለጸጎች ድምር ሃብት 32.3 ትሪሊዮን ዶላር ይጠጋል፡፡
ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ካፈሩት ከእነዚሁ የአለማችን እጅግ ባለጸጎች መካከል 31 በመቶ ያህሉ በአሜሪካ እንደሚኖሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ 9 በመቶው በቻይና፣ 7 በመቶ ያህሉ ደግሞ በጃፓን እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡ 8ሺህ 989 እጅግ ባለጸጎች የሚኖሩባት የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ከአለማችን ከተሞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባለጸጎች የሚገኙባት ቀዳሚዋ ከተማ ናት ያለው ሪፖርቱ፤ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ካፈሩት የአለማችን 265 ሺህ 490 እጅግ ባለጸጎች መካከል የሴቶች ድርሻ 14.6 በመቶ ብቻ መሆኑንም ገልጧል፡፡የአፍሪካ አገራት በ2018 የፈረንጆች አመት ብቻ በ67 ሚሊዮን ያህል አለማቀፍ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውንና አገራቱ በድምሩ 194.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን ሰሞኑን የወጣ አንድ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ጁሚያ የተባለው ተቋም ሆስፒታሊቲ ሪፖርት አፍሪካ በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው፣ በ2018 የአፍሪካ አገራትን የጎበኙ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር በ2017 ከነበረው የ7 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን፣ በአመቱ 11 ሚሊዮን ያህል አለማቀፍ ቱሪስቶች የጎበኙዋት ሞሮኮ ከአፍሪካ አገራት በርካታ ቁጥር ባላቸው ቱሪስቶች የተጎበኘች ቀዳሚዋ አገር ሆናለች፡፡
በአመቱ አፍሪካን ከጎበኙት አለማቀፍ ቱሪስቶች መካከል 71 በመቶ ያህሉ ለመዝናናት የመጡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ለንግድና ለስራ ጉዳይ አፍሪካን የረገጡ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
የአህጉሪቱ የጉዞና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ በአመቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለ24.3 ሚሊዮን አፍሪካውያን የስራ ዕድል መፍጠሩን የገለጸው ሪፖርቱ፣ ዘርፉ በአህጉሪቱ ከተፈጠረው አጠቃላይ የስራ ዕድል 6.7 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝም አመልክቷል፡፡


 የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የሚጠይቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመዲናዋ ካይሮ ጣህሪር አደባባይ ባለፈው አርብ የጀመሩት ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ፖለቲከኞችንና ታዋቂ ግለሰቦችን  ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በካይሮ የጀመረው ተቃውሞ በሌሎች ከተሞችም ባለፉት ቀናት ተባብሶ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህን ተከትሎም ፈቃድ ሳያገኙ ሰልፍ ወጥተዋል በሚል 1 ሺህ 200 ያህል ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል፡፡
ማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም ተቃውሞ አነሳስተዋል ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ተገናኝተዋል፣ ያለህጋዊ ፈቃድ ሰልፍ ወጥተዋል በሚል ከታሰሩት ግብጻውያን መካከል ሶስት ዝነኛ የፖለቲካ አክቲቪስቶች፣ እውቅ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደሚገኙበትም ተነግሯል፡፡
ግብጻውያኑ የሰሞኑን ተቃውሞ የጀመሩት ነዋሪነታቸው በስፔን የሆነው ታዋቂው ኮንትራክተርና የፊልም ተዋናይ ሞሃመድ አሊ በቅርቡ የፕሬዚዳንት አልሲሲን ወታደራዊ ሙስና የሚያጋልጡ በርካታ ቪዲዮዎችን በድረገጽ አማካይነት በስፋት ማሰራጨታቸውን ተከትሎ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Tuesday, 01 October 2019 10:48

የበዓለ መስቀል ታሪክ


           የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዐበይትና ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ በዓለ መስቀል ነው:: ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በወርኃ መስከረም ብቻ በዓለ መስቀልን አራት ጊዜ ታከብራለች፡፡ የመጀመሪያው ምክንያተ ክብረ በዓል፣ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ዓፄ ዳዊት ከግብፅ ንጉሥና ሊቃነጳጳሳት የተላከለትን በቅዱስ ሉቃስ እጅ የተሳለችውን ስዕለ ማርያምን፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የተሳለውን ኩርዓተ ርእሱን፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትንና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል የግብፅና ኢትዮጵያ ድንበር ከነበረችው አስዋን ከተባለችው ቦታ ተረክቧል፡፡
ንጉሡ የያዘውን በረከት ወደ ኢትዮጵያ ሳያደርስ ስናር በተባለው ቦታ ዐረፈ፡፡ ከጊዜ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የተባለው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ  ተቀብሎ በደብረ ብርሃን፣ በየረር፣ በመናገሻና በልዩ ልዩ ተራራማ ቦታዎች ሲዘዋወር ቆይቶ “መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር”  የሚል ራእይ ተገልጦለት፣ ቅዱስ መስቀሉን በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጦታል፡፡ መጋቢት ዐሥር ቀን ደብረ ብርሃን ሲገባ ብርሃን ስለወረደና ዐፄ ዳዊት ከግብፃውያን ጳጳሳትና ንጉሥ እጅ መስቀሉን የተረከቡበትን ቀን በማዘከር፣ የአድባራትና የገዳማት ሊቃውንት ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው የብር መቋሚያና ጸናጽል  ይዘው ወደ ነገሥታቱ ሔደው ተቀጸል ጽጌ እያሉ  እያሸበሸቡ ጸሎተ ወንጌል  ያደርሱ ስለነበር መስከረም ዐሥር ቀን የዓፄ መስቀል በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡
መስቀሉ እንዴት ተገኘ?
አይሁድ መድኃኔዓለም እውር አበራ፣ ለምጽ አነጻ፣ አጋንንት አወጣ፣ ሙታንን አስነሳ፣ በሽተኞችን ፈወሰ፣ ብለው በሰይጣናዊ ቅንዓት ሰቅለው ከገደሉት በኋላ ከሙታን ተለይቶ መነሳቱ ሲገርማቸው የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ዕውር ሲያበራ፣ ሙት ሲያስነሳ፣ ልዩ ልዩ ደዌያትን ሲፈውስ አይተው የክርስቶስ መስቀል እንዲቀበርና ደብዛው እንዲጠፋ 300 ዓመታት ያህል በከርሠ ምድር ቀበሩት:: አይሁድ የክርስቶስን መስቀል ለማጥፋት በጉድጓድ ጥለው የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሁሉ ጉድፍ እንዲጥሉበት አደረጉ፡፡ ማንኛውም ቤተሰብ የቤቱን ጥራጊ እያመጣ መቃብሩ ላይ እንዲቆለል ተደርጎ ጥራጊ ሲጣልበት በመኖሩ ቦታው ኮረብታ ሆኖ ነበር:: ምንም እንኳ ለማውጣት ባይችሉ ክርስቲያኖቹ ቦታውን ያውቁት ነበር:: ከጊዜ በኋላ ጀኔራሎች በአስቫስያንና ጥጦስ ወረራ በ70 ዓ.ም ክርስቲያኖቹ ኢየሩሳሌምን ለቀው ስለወጡ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ወዴት እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ዕሌኒ ንግሥት ልጇ ቆስጠንጢኖስ የክርስትና እምነት ፍቅርና ተቆርቋሪነቱ ቢኖረውም ገና አልተጠመቀም ነበርና አምኖ ተጠምቆ ወደ ክርስትና ሃይማኖት የገባልኝ እንደሆነ ወደ ኢየሩሳሌም ሄጄ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት አሳንፃለሁ፣ የተቀበረውን ቅዱስ መስቀሉን ፍለጋ አስፈላጊውን ሁሉ ራሴ አሟላለሁ ስትል ብፅዕት አድርጋ ስለነበር በአራተኛው መ/ክ/ዘ 337 ዓ.ም ከብዙ ሠራዊትና መኳንንት ጋር ሆና ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡
ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ቅዱስ መስቀልን ከተቀበረበት ለማውጣት አስቦ ስለነበር፣ እናቱ ከመንፈሳዊ ሃሳቡ ጋር በመተባበሩዋና ቅዱስ መስቀልን ለማስወጣት የነበሩትን ብፅዓት ለመፈጸም በማሰብ ተደሰቱ፡፡ አስቀድማ ሂዳ መስቀል ያለበትን ስፍራ እንድታጠና ሠራዊት ገንዘብ አሲዞ ላካት፤ ዕሌኒም ኢየሩሳሌም ደርሳ ኮረብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን ማግኘት አልቻለችም፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ የጎልጎታን ተራራ እንዲጠርጉ አዘዘች፡፡ በምንም ሁኔታ መስቀሉ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከነሐሴ ወር ጀምራ ምሕላ ያዘች፣ ሱባኤ ገባች፡፡ ጊዮርጊስ ወልድ አሚድ ዕሌኒ ንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስን አገኘችውና መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ ጠየቀችው፡፡ አባ መቃርስም፤ ከሃዲዎቹ በላይ ብዙ አፈር አፍሰውበታል፣ አፈሩም ትልቅ ተራራ አስከ መሆን ደርሷል ብሎ አስረዳት ይላል፡፡ ኪራኮስ የተባለም ሽማግሌ ወደ ንግሥቲቱ ቀርቦ መስቀሉ ያለበት ስፍራ ቀራንዮ መሆኑን አባቴ ነግሮኛል፣ ተራራው ያ ነው፡፡ ብሎ ጎልጎታን አመልክቷል:: በያዘችው ሱባኤ መልአከ እግዚአብሔር ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ መስቀሉን በእጣን ጢስ ታገኚዋለሽ ብሎ ነግሮአት ስለነበር ኅሊናዋ አልተጠራጠረም፡፡
የመላእኩንና የሽማግሌውን ቃል መሠረት አድርጋ በምድረ ይሁዳና ኢየሩሳሌም የነበሩትን ሕዝብ በጎልጎታ የሚደመር እንጨት እየያዛችሁ ኑ ብላ አዘዘቻቸው፡፡ መስከረም 16 ቀን ከየመንደራቸው እንጨት እየያዙ በጎለጎታ ተራራ ላይ ተደመሩ:: የተደመሩትንም እንጨቶች በእሳት አስለኮሰች፡፡ ብዙ ጊዜም የዕጣኑ ጢስ በተአምራት ከላይ ወደ ታች ተመልሶ መስቀሉ በተቀበረበት ሥፍራ ላይ ተተክሎ ታየ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፤ ዕጣን የመስቀልን ሥፍራ አመለከተ፣ ጢስም ለመስቀሉ ሰገደ እያለ የዘመረው ለዚህ ነው፡፡ /ምዕራፍ ዘአርያም/ ንግሥት ዕሌኒ የዕጣን ጢስ ያመለከተውን ስፍራ ወዲያው መስከረም 16 ቀን ማስቆፈር ጀመረች:: በብዙ ድካም በብዙ ጥረት በተፋጠነ ቁፋሮ መስቀሉ መጋቢት 10 ቀን ተገኘ፡፡
ንግሥት ዕሌኒ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና ሁለቱ ወንወበዴዎች ጥጦስና ዳክርስ የተሰቀሉባቸው መስቀሎች በተገኘ ጊዜ፣ ከእነዚህ ሁለቱ መስቀሎች ጌታችን የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀል በምን አውቀዋለሁ ብላ ለኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስን ጠየቀችው፡፡ አባ መቃርስም የጌታ መስቀል እንደ ልማዱ ሙት ላይ ሲያኖሩት ሙት ያስነሳልና በዚህ ለይተሽ ታውቂዋለሽ ብሎ ምልክት ነገራት፡፡ ወዲያው የጌታ መስቀል ሙት ላይ ቢያኖሩት ሙት ማስነሳቱ፣ ደዌ ቢያቀርቡለት ፈወሰ፡፡ ይህ የጌታችን የኢየሱስ መስቀል ነው ብለው አመኑ፡፡ መስቀል እንዲው ችቦ አብርተው አበባ ይዘው እንዲህ አበራ፣ እንዲህም አበበ አብቦም ፍሬ ክብርን አፈራ እያሉ አሸበሸቡ፡፡
የምስራችንም የቆስጠንጢኖስ ዙፋን እስከነበረበት ቆስጠንጢንያ ድረስ አስተላለፈ:: ከኢየሩሳሌም እስከ ቆስጠንጢኖስ ድረስ አስተላለፈ:: ከኢየሩሳሌም እስከ ቆስጠንጢኖስ ድረስ የነበሩ ሕዝቦች፣ ችቦ በማብራት በየደጁ ተሰብስቦ የደመራ እሳት ወጋገን በማሳየት አበባ ይዞ በመዘመር እልል በማለት ደስታውን በሕብረት ገለጡ፡፡
ዕሌኒ ንግሥት የጌታን መስቀል በማግኘቷ ስለተደሰተች፣ ጌታ በተወለደበት ቤቴልሔም፣ ጌታ በተቀበረበት ጎለጎታ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ማሳነጽ ጀመረች፡፡ በዕንቍ በወርቅ በብር አስጌጠች አሠራች፡፡ ቆስጠንጢኖስም በገንዘብና በንዋየ ቅድሳት ረዳት፡፡ ቅዳሴ ቤተክርስቲያኑ መስከረም 17 ቀን የእስክንድርያ፣ የአንጾኪያ፣ የቆስጥንጥንያ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጵስ ቆጶሳት መጥተው በዋዜማው መስቀል 16 ቀን ባረኩ፡፡ ቅዳሴ ቤቱንም አከበሩ:: መስቀል ጥንዓ ይዘው ቅዱሳት መካናት ሁሉ ዞሩ ሥርዓተ ዑደት አደረጉ፡፡ የዕጣን ጢስ አመልክቶ ቁፈራ የተጀመረበትና ቅዳሴ  ቤቱ የተከበረበት አንድ ዕለት ሆነ፤ በዚህም ዕለት ሆነ፤ በዚያም ዕለት የዓለም ሕዝብ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም እየተሰበሰቡ በዓሉን በድምቀት ያከብሩት ነበር:: ይህም መስቀል በኢየሩሳሌም ካስቀመጠችው በኋላ ዘረፋና ምርኮ አጋጥሟታል፡፡
ኢየሩሳሌም በየጊዜው ከጦርነት ከምርኮ ያላረፈች ሃገር በመሆኗ ቅዱስ መስቀልም በአሕዛብ እጅ እየተማረከ፣ ካንዱ ወዳንዱ መዘዋወሩ አልቀረም ነበር፡፡ የክርስቲያን ነገሥታትም በዚህ ነገር እየተናደዱ እየተቆጡ ጦራቸውን መስቀል ወደ ሔደበት ቦታ ሁሉ ከማዝመት አልተገዙም፡፡ ከዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የሮም ንጉሥ ሕርቃል ነው፡፡ ሕርቃል በተንባላት ተማርኮ ወደ ፋርስ /ኢራቅ/ የሔደውን መስቀል በጦርነት አስመልሷል:: የመስቀል ዘመቻና ጦርነት እየተባለ ብዙ ክርስቲያን ደም ፈሶበታል፡፡
ደመራ
ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትንና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል በማያምኑበት አይሁድ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል እንዳይገኝ ተደርጎ ከተቀበረ በኋላ በዕሌኒ ንግሥት ፍለጋ በደመራው የዕጣን ጢስ ስግደት የተደበቀበት ስፍራ ተለይቶ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን ከተቀበረበት ወጥቷል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ተቀምጦ መስከረም 16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፤ ስለሆነም ደመራ ዕንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡
(መስከረም 26, 2016
BY AMDETEWAHDO)