Administrator

Administrator

የትርዒቱ ርዕስ፡ የአዲሳባ ልጅ
    ሠዓሊ፡ መዝገቡ ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር)
      የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች
ብዛት፡ ሃያ ስራዎች
      የቀረበበት ቦታ፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ፡ አዲስ አበባ
     ጊዜ፡ ግንቦት 05-ሰኔ 03: 2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
እንደ መሻገሪያ
ይህ ዳሰሳና ትችት ‘ወቅቱን ያልጠበቀ’ ወይም ‘ያለፈበት’ ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያት? ትርዒቱ የዕይታ ጊዜው አልፎበታል፡፡ ሆኖም፡ ’የአዲሳባ ልጅ’ የተሰኘው የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሥዕል ትርዒት በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ በተለይም በያዝነው ዓመት ከቀረቡ የሥዕል ትርዒቶች መሃከል በይዘትም ሆነ በቅርጽ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ የዕይታ ጊዜው ቢያልፍበትም ባያልፍበትም ለመዳሰስና ሂስ ለመስጠት አይነተኛ ነው፡፡ እንቀጥል?
1. ‘ቢስ!’ ፡ ‘ይደገም!’  
ረዳት ፕሮፌሰር መዝገቡ ተሰማ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ‘ንግስ’ በሚል ስያሜ በብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ ለዕይታ ያቀረበው ትርዒት በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ የሠዓሊውንም ሆነ የትርዒቱን ልዩ አሻራ ትቶ ያለፈ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እውነታን ከምጡቅ ምናብ አሰናኝቶ በተለይም ሠዓሊው ከልጅነት እስከ እውቀት፣ በእዝነ-ልቦናው ግዘፍ ነስተው የተቀመጡ የተፈጥሮና የመልክዓ ምድር ቅርጾችን፣ ለዕይታችን እጅግ ገዝፈውና እጅግ ደቅቀው የሚገኙ አካላት ከሰው ልጅና እንስሳት አንጻር፣ የሶስት አውታረ መጠንነትን  በሁለት አውታረ መጠን ሥዕል መተግበር መቻሉን በስራዎቹ አሳይቶ ነበር። ታዲያ ይህ ትርዒት  ‘ቢስ!’ ወይም ‘ይደገም!’ የሚል ጥያቄ ከተመልካች እንደቀረበለት ይነገራል፡፡ ‘ንግስ’ ታላቅ ነበረና ጥያቄው መቅረቡ የሚያስገርም አይመስለኝም! የአቅም ጉዳይ ሆኖ እንጂ በሙዝየሙ ብቻ ሳይሆን ‘ንግስ’ በመላው ሃገሪቱም ተዟዙሮ መታየት ነበረበት፡፡ አሊያም አሁንም የአቅም ጉዳይ ሆኖ ይመስለኛል እንጂ የ’ንግስ’ ትርዒት ሙሉ በሙሉ በሙዝየሙ ቋሚ ስብስብ መካተት ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ምናልባት ወደፊት ይሆናል፡፡ የ’ንግስ’ የ’ይደገም!’ ጥያቄ እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልሆንም ረዳት ፕሮፌሰር መዝገቡ ተሰማ  ባሳለፍነው ወር ‘የአዲሳባ ልጅ’ የተሰኘ ሰፊ የተመልካች ዓይነት፡ እጅግ በርካታ ምናልባትም በጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ የሆነ፡ የተመልካቹን ቀልብና ተመስጦ የገዛ ትርዒት ለሕዝብ ዕይታ አቅርቦ ነበር፡፡ ‘የአዲሳባ ልጅ’፤ የ’ንግስ’ ‘ቢስ!’ ወይም ‘ይደገም!’ ከሆነ ምክንያታዊ መሰረቱ በ’የአዲሳባ ልጅ’ ትርዒት ከቀረቡት ስራዎች ጋር ይጣረሳል፡፡ ‘ቢስ!’ ካልሆነና ራሱን ችሎ የቀረበ ከሆነም ቀጥሎ የማቀርበው ነጥብ ይጎድለዋል፡፡
2. ‘የአዲሳባ ልጅ’ ፡ የትርዒቱ ማንነት(The Identity of the Exhibition)
የትርዒት ማንነትና ምንነት የሚገለጸው ባካተታቸው የስራዎች የአሳሳል ዘዬ(style)፣ ይዘት (content)፣ ቅርጽ (form)፣ ዓይነ-ግብ (subject matter)፣ አቀራረብ (presentation)  እንዲሁም እኒህ ሁሉ ሲጣመሩ የሚሰጡት የትርዒቱ አንድምታዎች ነው። ከነዚህ አኳያም ‘የአዲሳባ ልጅ’ የራሱ የሆነ የትርዒት ማንነቱን የተሟላ ለማድረግ እምብዛም የተጨነቀ አይመስልም። እያንዳንዱን የትርዒቱ አናስራት(elements) ነጥለን ስንመለከት የጎደለው ነገር እንዳለ አይሰማንም፡፡ በዚህ ረገድ ከሠዓሊው የዳበረ ልምድ፡ ከገነባው ሥነ-ጥበባዊ ግለሰባዊነትና ከዘለቀበት ከፍታ አንጻር እንዲያው በደፈናው (by default) የሚጠበቅ ነው፡፡ በርግጥም ምሉዕ ሥነ-ጥበባዊ ሰብዕናውን በእያንዳንዱ ስራው ላይ እናያለን፡፡ ሆኖም፡ አንድ ትርዒት የመታያ ጊዜው ካበቃ በኋላ በተመልካቹም ሆነ በሠዓሊው እዝነ-ልቦና የሚቀረው ትርዒቱ ትቶለት ያለፈው ወጥ ምስልና እሳቤ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ግን ‘የአዲሳባ ልጅ’ ጠንካራና ሁለንተናዊ ምስል እንዲሁም የተገራ የትኩረት አቅጣጫ ትቶልን ያለፈ ትርዒት እንዳልነበረ ምክንያቶቼን በመደርደር እተቸዋለሁ። ጠንከር ያለ ትችት ማቅረብ ከማይቻልበት አንደኛው ነጥብ ብጀምር፣ ‘ከብርሃን ተቃራኒ’ የተሰኘው ስራው በዘዬ፣ በይዘትና በዓይነ-ግብ ከሌሎች ተነጥሎ ለብቻው የሚታይ እንጂ በአንድ ትርዒት ለመቅረብ አጥጋቢ ምክንያት የለውም። በእርግጥ ይህ የብርሃንን አቅጣጫ ለማጥናትና ሌሎች ስራዎቹ ላይ የሚጠቀምበትን ቴክኒክ ማሳያ ሊሆነው ይችላል። ነገር ግን፡ ይህ ከስያሜም የሚልቅ ‘የአዲሳባ ልጅ’ በሚል ርዕስ በቀረበ ትርዒት ውስጥ (እንደ ሟሟያ) መካተቱ ለትርዒቱ አውራ ትኩረት መነፈጉን ያሳያል፡፡
ለትርዒቱ ተብሎ በተዘጋጀው ካታሎግ ውስጥ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ስራዎቹን የሰራበትን መነሾዎችና መደንግጉን (artist statement) ከማቅረብ ይልቅ ትምህርታዊ ጽሁፍ ነው ያቀረበው፡፡ ሙሉ መብቱ የሠዓሊው ነው፡፡ ይህ አይነቱ አቀራረብ በራሱ ጥልቅ ምሁራዊ እይታና ምርምር ይጠይቃል፡፡ በመምህርነት የአንድ ትውልድ እድሜ የሚሆን ጊዜ በአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ላሳለፈው ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ይህ የሚቻለው በመሆኑም ነው ያደረገው።  የመደንግጉ (artist statement) አለመኖር የሚያመላክተው ክፍተት ግን ለትርዒቱ ማንነትና ምንነት የሰጠው ቦታ አለመኖሩን ነው፡፡ በተለይ በይዘት ከሌሎቹ ስራዎች ጋር ለማይደጋገፉትና የትርዒቱን ስያሜ ለተሸከሙት ከቁጥር 1-3 ላሉት፣ ‘የአዲሳባ ልጅ’ ለተሰኙት ስራዎች ማብራሪያ እንኳን ባይሆን የዓይነ-ግብና የይዘት ለውጥ ያሳየበትን አመክንዮ ጠቆም አለማድረጉ፣ ትርዒቱን እንደ ትርዒት ማንነት የሚያሳጣው ነጥብ ነው፡፡ እነዚህ ስራዎች ከሌሎቹ ጋር ያላቸውን የሃሳብ ዝምድና ለማየት የሞከርን እንደሆነም ትርዒቱን አንድምታ ያሳጣዋል፡፡
ተመልካች ስለ ትርዒቱ ወጥ እሳቤ እንዳይኖረው ተደናቅፏል ባይ ነኝ፡ ይልቅስ በተለይ ዓይኑና የዕይታ ባሕሉ ያልሰለጠነው ተመልካች፤ እንደ ሠዓሊው ፍላጎት፣ ቅርጽና እይታዊ መስህብ እንዲሁም ‘የቀለም ቅብ ምትሃታዊ እንቅስቃሴ’ ላይ እንዲደመም ሆኗል፡፡ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ስለ ስራዎቹ ከሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡና ከአድናቂዎቹ ጋር ባደረገው ውይይትም፤ ’የሥነ-ጥበብ እድገት ሊረጋገጥ የሚቻለው ለቅርጽ በሚሰጥ ትኩረት’ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ሥነ-ጥበብን ከነባራዊው የሃገራችን ዓውድ አንጻር ስንመለከተው፣ ሰዓሊው የሚሞግተው ነጥብ አግባብነት ያለው ይሆናል።  ሠዓሊው የሚጠቀማቸው ዓይነ-ግቦች ቀጥተኛ መረዳት፡ ግንኙነትና እይታዊ መስህብ ሊፈጥርላቸው ለሚችልላቸው ተመልካቾች ወይም የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለስራዎቼ ይስማማልኛል ለሚላቸው የቅርጽ አትኩሮቶች አጽንኦት መስጠቱ ብልህነት ነው፡፡
ለይዘት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለመስጠት አሁንም በሠዓሊው ፈቃድና ነጻነት ስር የሚያልፍ መሆኑን ሳልዘነጋ፤ ሥነ-ጥበብ ለምንኖረው ሕይወት የሰላ እይታ እንዲኖረን እሴት ከመጨመር አንጻር የሚኖረውን ፋይዳ እንደ ‘የአዲሳባ ልጅ’ የትርዒት አርዕስትነትና እንደ ሰዓሊ  መዝገቡ ተሰማ ባለ ታላቅ ሠዓሊነት ከመዳሰስም አልፎ፣ ረገጥ ተደርጎ መወያያ መሆን ነበረበት የሚል ነው አቋሜ፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ከትርዒት ማንነት ባሻገር የሥነ-ጥበብን ህላዌ እንድንፈትሽ ያስችለናል፡ ስለ ትርዒት ማንነትና ምንነት ማንሳት የፈለግኩትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
3. ‘የአዲሳባ ልጅ’ - ውይይት
በሃገራችን የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ በሥዕል ትርዒት ዙሪያ ውይይት ሲደረግ በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች ያውም ከከያንያኑ የዘለለ ተሳታፊዎችን ማየት ብርቅ ነገር ነው፡፡ ‘የአዲሳባ ልጅ’ በርካታ የሥነ-ጥበብ ቤተሰቦችን ያፈራ እንደነበር ውይይቱ ላይ የተገኙት ከሶስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች የትርዒቱን ስኬታማነት ያመላክታሉ፡፡ ይሄ ያስደስታልም፡ ያኮራልም፡፡ የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ የግል ጥንካሬ በመሆኑም መመስገን ይገባዋል፡፡
በሥነ-ጥበብ ዙሪያ ትንታኔዎችን በማቅረብና የሥዕል መሳያ ቀለሞችን በሃገራችን በማምረት የሚታወቀው ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ፤ ስለ ትርዒቱ፡ ስለቀረቡት ስራዎች በተለይም ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ  አሜሪካ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ስራዎቹ ስለመቀየራቸው ባቀረበው ጽሁፍ ነበር ውይይቱ የተጀመረው፡፡ ሠዓሊ  መዝገቡ ተሰማ  ስለዚህ ጉዳይ አስተያየትም ሆነ ማብራሪያ አለመስጠቱ፣ተሳታፊው ራሱ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ የፈቀደ ይመስላል፡፡ ሆኖም ይህ አይነቱ ገለጻ፤ ከሠዓሊው የአሰራር ልምድ፡ ሂደትና ለውጥ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ፣ የሠዓሊው አተያይ ይጠቅም ነበር ባይ ነኝ፡፡ ቀጥሎ ከመድረክ የቀረበው ጽሁፍ የጋዜጠኛ ይትባረክ ዋለልኝ ሲሆን የአቶ ሰለሞን ተሰማን ጥናታዊ ጽሁፍ መሰረት ያደረገና የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ  መዝገቡ ተሰማ’ን ስራዎች፣ሃገረሰባዊ ማንነት በማላበስ የሚያትት ነበር፡፡ ከታዳሚው ወደ ቀረቡ አስተያየቶች ስንመጣ፡  ሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ፤ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ባዳበረው አሳሳል ተከታዮች እያፈራ በመሆኑ ‘መዝገብኛ’ ተብሎ ሊሰየም የሚችል አሳሳል መምጣቱን በመጠቆም አስተያየት የሰጡ ሲሆን ከረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የተሰጠ ምላሽ  አልነበረም፡፡
በሥነ-ጥበብ ታሪክ ግለሰቦችና ቡድኖች ያዳበሩትንና የሚከተሉትን ዘዬም ሆነ ፍልስፍና በManifesto አስደግፈው ያውጃሉ፡፡ የሥነ-ጥበብ ታሪክ አጥኚዎችና ተመራማሪዎችም ስለ ሠዓሊዎች ስራ፡ አሰራርና ፍልስፍናም ጥናትና ምርምር በማድረግ ስም ያወጡላቸዋል፡፡ የሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ ግላዊ አስተያየት፣ ምን ያህል በጥናት የተደገፈ እንደሆነ ባላውቅም ‘መዝገብኛ’ የሚለው ስያሜ አሁንም የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ’ን ሥነ-ጥበባዊ ጉዞ መሰረት ያደረገ በመሆኑ፣ የሠዓሊው ይሁንታ ወይም አሉታ አሊያም ማብራሪያ ያስፈልግ ነበር ባይ ነኝ፡፡ ውይይቱ ካስተናገዳቸው አዝናኝ አስተያየቶች መሃከል ፤’ጥበብ በፍቅር ቃላት ብቻ ነው የምትዳብረው’ በሚል ከዚህ ውጪ ትችት አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚሰብከው አስተያየት አንዱ ነበር፡፡ የፍቅር ቃላት ብቻ ሳይሆን ጥበብና ፍቅር የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ሆኖም፡ ያለ ትችትና ያለ ሂስ የሥነ-ጥበብ አካሄድ ሊቃና አይችልም፡፡ ቸር ይግጠመን!





Saturday, 11 June 2016 13:27

የውለታ ቀስተደመና

(ከአለማየሁ ገላጋይ “ኩርቢት” የተወሰደ)
አጣሁት፣ አጣሁት፣ እንጂ እንደ ችግሬስ ፈጣሪዬን ለሰላሳ ብር እሸጠው ነበር፡፡ ይሄን አድርጌው ቢሆን ይሄን ጊዜ እንደ ከንቱው ገበሬ “እንዲህ ልጠግብ በሬዬን አረድኩት” እል ነበር፡፡ ምክንያቱም ትናንት ሎተሪ እንደደረሰኝ አረጋግጫለሁና ነው፡፡
ግን ይሁዳ እግዚሃርን ለሰላሳ ብር ሲሸጥ የነበረበት ችግር ለምን አልተፃፈም? እንደኔ እርቦት የነበረ ቢሆንስ? እንደኔ ወይም ሚስቱ  ወልዳበት ቢሆንስ? እንደ እኔ እናቱ ታመውበት ቢሆንስ? እንደኔ ከሥራ ተባሮ ቢሆንስ? እሺ ያኔ ሥራ የለም ነበር እንበል፤ የሚያርስበት በሬ ገደል ገብቶበት እንደሆንስ? ይህን ሁሉ አራቱም ወንጌሎች አሟልተው አልገለጡም። እንዳውም ይሁዳን ያስመሰሉት ለመክዳት ሲል ብቻ መድኃኒዓለምን እንደሸጠው ነው፡፡ ከሐዲነት እኮ ያለ ገንዘብ አሳልፎ በመስጠትም ብቻ ይረካል፡፡ ታዲያ ሠላሳ ብሩ…
ኤዲያ! የኔ ነገር፡፡ የፈለኩትን ትቼ ሌላ ስዘበዝብ እገኛለሁ፡፡ ትናንት ሎተሪ ደረሰኝ፡፡
እስከ ዛሬ ከቤቴ አልወጣሁም፡፡
ኧረ እንዳውም ካልጋዬ አልወረድኩም፡፡
እንደ ሚስቴ የደስታ አራስ ሆኛለሁ፡፡ እንደ ሚስቴ ጨቅላውን ደስታ ታቅፌ፣ ያጋተ የምኞቴን ጡት አጠባዋለሁ፡፡ እንደ ሚስቴ ሁሉ ከዘመድ አዝማድ ለአራስ ጥሪ የመጣውን እየቀማመስኩ መጋደም፤ ጐጇችን የሁለት አራስ ቤት ሆኗል፡፡ ሚስቴ የታቀፈችው ጨቅላ የጋራችን ነው፡፡ የኔ ደስታ ግን የግሌ፤ አልነገርኳትማ!
ምነው አለመንገሬ? እኔን የመታኝ የደስታ ፍላፃ፣ እርሷ ላይ ቢያርፍ አትተረተርም፡፡ እርግጠኛ ነኝ እሁለት ትከፈላለች፡፡ ሎተሪ ሻጩን ጠርቼ፣ በሻካራ እጄ ሳሻሻት የምትመስጠኝን የሳምንት ወዳጄን ያቺን ሎተሪ ከማውጫው ጋር አመሳከርኩ፡፡ መጀመሪያ እግዚሃር ሲያላግጥብኝ መሰለኝ፡፡ መቼም መተከዣው አድርጐኛል…
ግን እውነት ነበር፡፡ ይሄን ላረጋግጥ አንድ ስል፣ ስሜት ከደመና በላይ ተወርውሮ የአናቴን እኩሌታ ከፍሎ፣ ወደ ልቤ በማድላት እየተረተረኝ ወረደና ሙሐሊቴን አቋርጦ አለፈ፡፡ አልፎም እንደ መብረቅ ክንድ መሬት ሰንጥቆ ገባ፡፡ ግራ አካሌና ቀኝ አካሌ ተፋትተው ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ በየፊናቸው የወደቁ መሰለኝ፡፡
ሎተሪውን ዳግም ያመሳከርኩት ማውጫውን ከሎተሪ ሻጩ ላይ በሃያ ሳንቲም ገዝቼ አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ ነበር፡፡ ጉደኛው ደስታ በተረጋጋ ስለት በለመደው አኳኋን ዳግም አካሌን ጐበኘው፡፡
እነሆ እስካሁን አልተነሣሁም፡፡
ደስታ ስለት ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ማር ያለ ጣፋጭ ነው፡፡
ከመጠኑ ሲያልፍ ለሃጭ ያዝረበርባል፡፡
ተዝረበረብኩ፡፡
እንደ አራሷ ሚስቴ ወገብ ያልጠናው በራችን እየተልመጠመጠ ተከፍቶ እማማ አስላኩን አስተናገደ፡፡ ከገቡም በኋላ በራችን ልምጥምጡን ለሰላሳ ሴኮንድ ያህል መቀጠሉ አበሳጨኝ። እርግጥ ያበሳጨኝ በሩ ብቻ አልነበረም፡፡ የእማማ አስላኩ በትርና ጐድጓዳ ሰሃን ግራና ቀኝ እጆቻቸው ላይ ውለው፣ እኔ እቀድም እኔ እቀድም እየተፎካከሩ ሲመጡ አበሳጩኝ፡፡ ለወትሮው በትሩንም ባይሆን ጐድጓዳ ሰሃኑን እናፍቅ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በውለታ ሥም እንጀራ ተሸክሞ የሚመጣው የእማማ አስላኩ ጐድጓዳ ሰሐን ከሎተሪው ብር ካልተሞላ እንደማይወጣ ሆኖ ተሰማኝ፡፡
“ጐድጓዳ ሰሐን ምግብ፣ በጐድጓዳ ሰሐን ብር!” መጮህ ከጀለኝ፡፡
“እንኪ እስቲ ይቺን ቅመሺ… የማሪያም አራስ” አሉ እማማ አስላኩ፡፡
ገብቶኛል፡፡ እኚህ ቀበኛ አሮጊት ውለታቸውን ለማሪያም ያስተላለፉት ቤተሰቡ ምንም እንደሌለው ስላወቁ ነው፡፡ ሎተሪ እንደደረሰኝ ሲሰሙ ግን ባለውለታ ጐድጓዳ ሰሐናቸውን በብር የመሙላት ዕዳ ይጭኑብኛል፡፡
ዘለግ አድርጌ ተነፈስኩ፡፡
ብዙዎቹ ጐረቤቶቼ የአራስ ጥሪ ያመጡበትን ዕቃ ይዘው ከእማማ አስላኩ ኋላ ይሰለፋሉ። ፔርሙስ፣ ብረት ድስት፣ ሰፌድ፣ እንቅብ፣ ደንበጃን…ውሃ የቀዱልን ሁሉ ባሊያቸውን ይዘው ሰልፉን ከአድማስ ያሻግሩታል፡፡
እንግዲህ ምን ተረፈኝ? ስም፣ ስም ብቻ!! የውለታ ቀስተ ደመና የህይወቴን ሰማይ ከቦታል።
“እዳዬን እንድከፍል ኑሯል ሎተሪ ያወጣህልኝ?” ስል እግዚሃርን ተደናቆልኩት፡፡
እንደውም በደንብ ሳሰላው ስራ የፈታው ህይወቴ፣ በጐረቤቶቼ ዳቦ የቆየበት ሦስት ዓመት በደረሰን ሎተሪ አይሸፈንም፡፡ ገንዘቡን ማከፋፈል ሳያንስ ያልተወራረደ ውለታ ያላቸው ጐረቤቶቹ፤ የውለታ ዕቃቸውን እንደያዙ የወቀሳ ኮረት እየለቀሙ ቤቴን፣ እኔ፣ ቤተሰቤን፣ ነፍሴን…ይደበድባሉ፡፡
ምን ፈረድብኝ?
ሆዴ ከጐረቤቶቼ ጋር አድሞ እሱም የውለታ ዕቃውን ይዞ አጉረመረመ፡፡
ምን አልኩህ፤ ፈጣሪዬ? ስለምን በስምህ የተዳፈነውን የውለታ ሰደድ በሎተሪ ስም ቆሰቆስከው? ስለምንስ በፅድቅ ስም ያሸለበውን የሶስት ዓመት ውለታ እንደ አላአዛር ከጥልቅ ሞት አስነሳኸው?
ዕዳዬ ውለታ ብቻ እንዳልሆነ አውቀዋለሁ፡፡
“መድፉ ሎተሪ ደረሰው” ሲባል የሰማ የስራ - ፈት ጅጊ ተውረግራጊ ቤቴን ይከባታል፡፡ ከቦም ያስጨንቃታል፡፡ ያኔ ደሜ በራሴ ላይ ነው፡፡
ምን ፈረደብኝ?
የሚወተውተኝን ሆዴን ለማስታገስ ወደ መፀዳጃ ቤት ሄድኩ፡፡ ለእኔ ከማበሻነት በላይ ጥቅም የሌላት ዕድሌን በቀኝ እጄ እንደጨመደድሁ፡፡  

ባለፈው ቅዳሜ ድንገት ባደረበት ህመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን አንጋፋውን የሥነ ፅሁፍ ሃያሲ አብደላ እዝራን የሚዘክር የኪነ ጥበብ ምሽት ከነገ ወዲያ ሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ በ“ዝክረ አብደላ” የኪነ ጥበብ ምሽት፣ ሃያሲ አብደላ
እዝራ ለአማርኛ ስነ ፅሁፍ ያበረከተው አስተዋፅኦ የሚዳስስ ሲሆን “አብደላና ሂስ”፣ “አብደላና ህይወቱ” በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሥነ ፅሁፍ ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
የቅርብ ወዳጆቹም ስለ አብደላ የሚያወቁትን ይመሰክራሉ፤ አብደላን የሚያወድሱ፣ ስራውንና
ሰብዕናውን የሚያወሱ ግጥሞችና ወጎችም ለታዳሚያን ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
ይህን የ“ዝክረ - አብደላ” የኪነ ጥበብ ምሽት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ያዘጋጀው ሲሆን፣ በምሽቱ አንጋፋና ወጣት ፀሐፍትና ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ከእነዚህም መካከል ነቢይ መኮንን፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ ደረጀ በላይነህ፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ደምሰው መርሻ፣ ምስራቅ ተረፈ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

Saturday, 11 June 2016 12:36

ፀሐፍት ጥግ

(ስለ እናት አገር)
- እናት አገር ላይ ክህደት ለፈፀሙ በሰዎች
የተፃፉ መፃህፍትን አላነብም፡፡
ቭላድሚር ፑቲን
- እኔ የምፈልገው ወደ እናት አገሬ ባንግላዲሽ
ወይም ወደ ጉዲፈቻ አገሬ ህንድ መመለስ
ነው፡፡
ታስሊማ ናስሪን
- ለጀግና ሰው፤ ዓለም በሙሉ እናት አገሩ
ናት፡፡
አቪድ
- ለሰው ልጅ እውነተኛ ፍቅር የሌለው፤
ለእናት አገር እውነተኛ ፍቅር አይኖረውም፡፡
አናቶሌ ፍራንስ
- የእናት አገርህ ዜጋ ብትሆንም ሁሉንም
አገራትና ሁሉንም ሃይማኖቶች በእኩል
አክብር፡፡
ሳዝያ ባባ
- በእናት አገርህ ክብር ይሰማህ፡፡ እናትህ
እንደወለደችህ ሁሉ እናት አገርህም
ወልዳሃለች፡፡
ሳዝያ ባባ
- አገር ወዳድነት ግሩም ነገር ነው፡፡ ግን
ለምንድን ነው ፍቅር በድንበር ላይ
የሚቆመው?
ፓብሎ ካሳልስ
- የአገር ፍቅር በማይረቡ ምክንያቶች
ለመግደልና ለመገደል ፈቃደኛ ነው፡፡
በርትራንድ ራስል
- ሰዎች አገራቸውን የሚወዱት ታላቅ
ስለሆነች አይደለም፤ የራሳቸው ስለሆነች
እንጂ፡፡
ሴኔካ
- የሰው አገሩ የተወሰነ መሬት፣ ተራሮች፣
ወንዞችና ደኖች አይደሉም፤ ይልቁንም
መርህ ነው፤ አገር ወዳድነት (አርበኝነት)
ለዚያ መርህ ታማኝ መሆን ነው፡፡
ጆርጅ ዊሊያም ኩርቲስ
- የአቴንስ ወይም የግሪክ ተወላጅ
አይደለሁም፤ እኔ የዓለም ዜጋ ነኝ፡፡
ሶቅራጠስ
- አገር ወዳድነት የሃይማኖት ዓይነት ነው፤
ጦርነቶች የሚፈለፈሉበት እንቁላል ነው፡፡
ጊዴ ሞፓሳ

Saturday, 11 June 2016 12:27

የዘላለም ጥግ

በራስ ስለመተማመን)
- በራስ መተማመን ከሌለህ በህይወት ውድድር
ሁለቴ ተረተሃል፡፡
ማርከስ ጋርቬይ
- እውነቱን ለመናገር የሰዎች በራስ መተማመን
ከገንዘብ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡
ካርተር ጂ.ውድሰን
- የ4 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወንድምና እህቶቼ
በረሃብ አለቁ፡፡ እናም ስኬትን የተቀዳጀሁት
በልበ ሙሉነት፣ ራስን በማነሳሳትና ተግቶ
በመስራት ነው፡፡
ቼን ጊዋንግብያኦ
- ተሰጥኦን ልታስተምር አትችልም፡፡
እግዚአብሔር ያጎደለውን አንተ አትሞላውም።
በራስ መተማመንን ግን ልታስተምር
ትችላለህ፡፡
ግሎርያ ናይለር
- በራስህ ተማመን፡፡ የሰው ልጅ እጅግ ማራኪው
ክፍል በራስ መተማመን ይመስለኛል፡፡
ኩርቲስ ጃክሰን
- በራስ መተማመን የሚመነጨው ከሰዓታት፣
ከቀናት፣ ከሳምንታትና ከዓመታት የማያቋርጥ
ሥራና ታታሪነት ነው፡፡
ሮጀር ስታውባች
- ህዝቦች በመሪዎች ላይ ያላቸው እምነት፣
መሪዎች በህዝቦች ላይ ያላቸውን ልበ ሙሉነት
ያንፀባርቃል፡፡
ፓውሎ ፍሬይሬ
- ውበት ብዙ መልኮች አሉት፡፡ እጅግ ውቡ
ነገር በራስ መተማመንና ራስህን ማፍቀር
ይመስለኛል፡፡
ኪስዛ
- በራስ መተማመን ካለህ ከመጀመርህ በፊት
ድል አድርገሃል፡፡
ማርከስ ጋርቬይ
- በራስ መተማመን የሚመጣው ከብስለት ጋር
ነው፤ ራስን ይበልጥ በመቀበል፡፡
ኒኮሎ ሼርዚንገር
- ሳንሱር፤ የህብረተሰብን በራስ የመተማመን
ስሜት ማጣት ያንፀባርቃል፡፡
ፖተር ስቲዋርት
- በራስ መተማመን የሚመነጨው ከዲሲፕሊንና
ከልምምድ ነው፡፡
ሮበርት ኪዩሳኪ
- ሁልጊዜ አንባቢዎቼ በእኔ ላይ በሚያሳድሩት
ልበ ሙሉነት እደነቃለሁ፡፡
ሜሪ ካር


5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል
     የመምህራንን ደሞዝ ለማሻሻል በመንግስት የተመደበው የ5 ቢሊዮን ብር በጀት፣ የመምህራኑን ደሞዝ በእጥፍ ሊያሳድግ የሚችል ከፍተኛ ጭማሪ ነው፡፡ ለአስተማሪዎች “ትርጉም ያለው የደሞዝ ጭማሪ ይደረጋል” በማለት መንግስት በደፈናው መግለጫ ቢሰጥም፤ እስካሁን ዝርዝር መረጃ አላቀረበም፡፡ ጭማሪውም በዝርዝር ተሰልቶ ለትምህርት ተቋማት ገና አልተደላደለም፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት፣ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ለመጨመር ውሳኔ ተላልፎ፣ ልዩ በጀት ተመድቦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ለመምህራን የደሞዝ ማሻሻያ፣ የ5 ቢ. ብር ልዩ በጀት ተመድቧል፡፡ ያኔ ለሁሉም የመንግስት ሰራተኞች፣ ለደሞዝ ማሻሻያ ተብሎ የተመደበው ልዩ በጀት 7 ቢ ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በአማካይ የሰላሳ በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ውሏል፡፡
ከዚህ ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ ለመምህራን ብቻ የተመደበው የደሞዝ ጭማሪ በጀት 5 ቢሊዮን ብር መሆኑ ጭማሪው ከፍተኛ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ የአገሪቱ የመምህራን ብዛት ሩብ ሚሊዮን እንደሚሆን የሚገመት ሲሆን፣ የወር ደሞዝ ጭማሪው በአማካይ 2500 ብር ገደማ ነው፡፡ ይህም የመምህራንን ደሞዝ በእጥፍ ለማሳደግ ያስችላል፡፡

• “በአመት 1 ቢ.ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል”
• ግድቡ የአፄ ኃይለስላሴ ህልም ነበረ - ታይም መጽሔት

ህዳሴ ግድብ ከአመት በኋላ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንደሚጀምር የዘገበው ታይም መጽሔት፣ ግንባታው፣ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጅ ቢሆንም፣ በየዓመቱ 1. ቢ ዶላር ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ገለፀ፡፡
የአገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የህዳሴ ግድብ ሲጨመርበት፣ አራት እጥፍ እንደሚሆን መጽሔቱ ጠቅሶ፤ የአገር ውስጥን የኤሌክትሪክ እጥረት ያቃልላል፤ ከሱዳንና ከግብጽ ማሰራጫ መስመሮች ጋር ሲገናኝም፣ በየዓመቱ 1 ቢ.ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ የኤምአይቲ ጥናት ያሳያል ብሏል፡፡
አፄ ኃይለስላሴ፣ ግድቡን የመገንባት ህልም እንደነበራቸውና የዛሬ ሃምሳ ዓመት ግንባታውን ለማካሄድ ወስነው እንደነበር አስታውሷል - መጽሔቱ፡፡ የገንዘብ እጥረት፤ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከባድ የድርቅ አደጋ፣ የደርግ መፈንቅለ መንግስት…ሌሎችም በርካታ ችግሮች ተደራርበው፣ የግድቡ ዕቅድ ለግማሽ ምዕተዓመት ዘግይቷል፡፡
በ2003 ዓ.ም በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ይፋ የተደረገው የግድብ ግንባታ፣ አሁን እንደተጋመሰና በግዙፍነቱ በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሆነ መጽሔቱ ጠቅሶ፤ በግድቡ የሚፈጠረው ሃይቅ የወንዙን ውሃ ሙሉ ለሙሉ የማጠራቀም አቅም አለው ብሏል። በሚቀጥለው አመት ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንደሚጀምርም መጽሔቱ በሰሞኑ እትሙ ገልጿል።

በግንባታ ስራ ላይ መሰማራት ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ ከፌደራል በጀት ውስጥ 75 ቢ. ብር ለግንባታ የተመደበ ነው፡፡
በትልቅ በጀት ቀዳሚነቱን የያዘው፣ የመንገድ ግንባታና ጥገና ነው - 46 ቢ. ብር፡፡
38 ቢ. ብር የተመደበላቸው ዩኒቨርስቲዎች፣ ሁለተኛ ደረጀ ላይ ተቀምጠዋል - በገንዘብ ብክነትና በዝርክርክነት ግን አንደኛ ሆነዋል፡፡
26 ቢ. ብር - መጠባበቂያ እህል ለማከማቸት ይውላል ተብሏል፡፡
14 ቢ. ብር ለእዳ ክፍያ (10 ቢ. ብሩ ለወለድ ክፍያ ነው)
11 ቢ. ብር ለመከላከያ፣ 2.3 ቢ. ብር ለፌደራል ፖሊስ፣ 1.2 ቢ. ብር ለብሔራዊና ለመረጃ ደህንነት
የእርሻ በጀት 8.6 ቢ ብር ቢሆንም፣ እንደ ድሮው ለምርት እድገት ሳይሆን፣ በአብዛኛው ለችግረኞች ድጐማ ተመድቧል፡፡
8.8 ቢ. ብር ለውሃ የተመደበ ነው፡፡ ግን በሃብት ብክነቱም ቀላል አይደለም፡፡ ከአስር ዓመት በፊት ይጠናቀቃሉ የተባሉ፣ ግድቦች ዘንድሮም ብዙ መቶ ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል
ለጤና አገልግሎት የሚውለው ገንዘብ 8.2 ቢሊዮን ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ 6 ቢ. ብር በውጭ አገር እርዳታ የሚሸፈን ነው - በአብዛኛውም በአሜሪካ መንግስት እርዳታ፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በፓርላማ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠቀበቀው የ274 ቢሊዮን ብር በጀት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ እየገዘፈ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ የእቅድ ትኩረቶችንና ስራዎችን ይዘረዝራል፤ የሃብት ብክነት አደጋዎችንም ይጠቁማል፡፡ ፌደራል መንግስት ከሚያንቀሳቅሰው ሃብት ውስጥ 40% ያህሉ ለግንባታ የሚውል በመሆኑ፤ የመንግስት የእቅድ ትኩረት፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ሰራተኞችና ኢንቨስተሮች በግንባታ መስክ እንዲሰማሩ የሚገፋፉ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በሌላ በኩልም፤ በሃብት ብክነት ኦዲተርን ያማረሩ  ዩኒቨርሲቲዎች፣ ብዙ ገንዘብ የሚመደብላቸው ተቋማት ስለሆኑ፣ የብክነትና የሙስና አደጋው ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታል - በጀቱ፡፡
በእርግጥ፣ ትልቅ በጀት ከተመደበ፣ ብዙ ሃብት ይባክናል ማለት አይደለም፡፡ ከሌሎች ስራዎች ጋር ሲነፃፀር፣ ለመንገድ ግንባታ የሚውለው ሃብት በአመዛኙ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በበጀት ትልቅነት ደግሞ የመንገድ ግንባታን የሚስተካከል የለም - 46 ቢ. ብር ነው የተመደበለት፡፡ በዚህ መስክ ብዙ ብክነት የማይታየውና የአገሪቱ የአስፋልት መንገድ የተሻሻለው አለምክንያት አይደለም፡፡
ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ፤ የመንገድ ግንባታ በደህና ሙያዊ መሰረት ላይ መዋቀሩ፣ እንዲሁም ዋና ዋናዎቹ የመንገድ ግንባታዎች በአለማቀፍ የጨረታ አሰራር ለተለያዩ ኩባንያዎች በኮንትራት የሚሰጡ መሆናቸው፤ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌደራልና በክልል ደረጃ፣ መንግስታዊ ድርጅቶች ወደ መንገድ ግንባታ እንዲገቡ መደረጋቸው ግን፣ ለወደፊት አሳሳቢ መሆኑ አይቀርም። የሃብት ብክነትን ያስከትላሉ፡፡ በፌደራልና በክልል መንግስታዊ ድርጅቶች አማካኝነት ላለፉት 12 ዓመታት ሲካሄዱ የቆዩ የግድብ እና የመስኖ ፕሮጀክቶችም፣ አደጋውን አጉልተው ያሳያሉ፡፡
ባለፉት ዓመታት፤ በርካታ ቢሊዮን ብር የፈሰሰባቸው የተንዳሆ፣ ከሰምና የረብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች፣ የዛሬ አስር ዓመት እንዲጠናቀቁ ነበር የታሰበው፡፡ ነገር ግን ዘንድሮም 500 ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡
ለአስር ዓመት በተጓተቱት ስራዎች ብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት ባክኗል፡፡
ነገር ግን በሃብት ብክነትና በዝርክርክ አሰራር፣ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚፎካከር አልተገኘም፡፡ ከአመት አመት የዩኒቨርስቲዎቹ አሰራር ከመስተካከል ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ የተማረሩት የፌደራል ዋና ኦዲተር፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ በቀጥታ ሃብት እንዳያንቀሳቅሱ መከልከልና፣… በተለይ የእቃ ገዢዎችን በበላይነት የሚመራ ሌላ ተቋም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ኦዲተርን ያማረሩት 34 ዩኒቨርስቲዎች ናቸው - በዓመት ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር የሚመደብላቸው። የሃብት ብክነቱና የሙስና አደጋውም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን፣ የዋና ኦዲተሩ ተደጋጋሚ ሪፖርት ይመሰክራል፡፡
የመጠባበቂያ እህል ለማከማቸት የተመደበው የ26 ቢሊዮን ብር በጀት፣ በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን፤ ከዚህ ቀጥሎ ከፍተኛ ድርሻ የወሰደው የብድር ክፍያ ነው፡፡ መንግስት ብድር ለመክፈል ከሚያውለው 14 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 10 ቢ. ብር ያህሉ የብድር ወለድ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በመንግስት በጀት ውስጥ የማይካተቱ ሌሎች ከባድ ብድሮች አሉ፡- የቴሌ፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የኤልፓ፡፡ እነዚህ ሲጨመሩበት፣ መንግስት የውጭ ብድር ለመክፈል በዓመት ከሃያ ቢሊዮን ብር በላይ ያወጣል፡፡
ነገር ግን፣ አሁንም የበጀት ጉድለት ለመሙላትና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን፣ ተጨማሪ ብድር መከማቸቱ አይቀርም፡፡ በተለይ ውጤታማ ያልሆኑ ፕሮጀክቶችና ምርታማነትን የማያሳድጉ ዕቅዶችን ለማስፈፀም የሚመጡ ብድሮች ለወደፊት አደጋ ናቸው፡፡ ከአስር ዓመት በፊት አብዛኛው የእርሻ በጀት፣ ለምርጥ ዘር ምርምር፣ ለቴክኒክ ስልጠና፣ ለማዳበሪያና ለመሳሰሉ ጉዳዮች ነበር የሚመደበው - ምርታማነትን ያሳድጋሉ በሚል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ችግረኛ ገበሬዎችን ለመደጐም የሚውለው የእርሻ በጀት እየገነነ መጥቷል። ነገር ግን፣ ድጐማ የሚደረግላቸው ገበሬዎች፤ ወደ ምርታማነት ሲያድጉ አይታይም፡፡ እናም ድጐማው እየተስፋፋ ዘንድሮ 6 ቢሊዮን ብር ደርሷል - ከጠቅላላው 8.2 ቢ. ብር የእርሻ በጀት፡፡

    በዩኔስኮ የዓለም አስደናቂ ቅርሶች ከተመዘገቡትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አካል የኾኑት የቤተ ሩፋኤልና ቤተ ገብርኤል አብያተ መቅደሶች፤ በረጅም ጊዜ አገልግሎትና በተፈጥሮ በደረሰባቸው የመሠንጠቅና የማፍሰስ ጉዳት የተነሣ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የነበሩ ሲኾን፤ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ ውጤታማ ጥገና እንደተደረገላቸው ተገለጸ፡፡
ከዩኔስኮ፣ ከዓለም ቅርስ ፈንድ(World Monument Fund) እና ከአሜሪካ መንግሥት(American Ambassador’s Fund) በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተካሔደውን የጥገና ፕሮጀክት በሓላፊነት ያሠራው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቅርስ ጥበቃ መምሪያም፤ ከፕሮጀክቱ ጥናት እስከ ፍጻሜው ድረስ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በባለቤትነት መሳተፏ ታውቋል፡፡
አምስት ዓመት በወሰደው የፕሮጀክቱ ጥናት መሠረት፣ ኦልሚ ኦሊንዶ የተባለ አገር በቀል ደረጃ አንድ ኮንትራክተር የአብያተ መቅደሶቹን ጥገና ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሲያካሔድ የቆየ ሲኾን፤ የፌደራል ሳይንቲፊክ ኮሚቴ ያስተባበራቸው ኢትዮጵያውያን አርክቴክቸሮችና ጂኦሎጂስቶች ከታዋቂ የእንግሊዝና የጣሊያን ባለሞያዎች ጋር መሳተፋቸው ተጠቅሷል፡፡
የውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን አካባቢ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያቀፈ ኮሚቴም ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንደተወጡና፤ የደብሩ አስተዳደርና ማኅበረ ካህናት ጸሎትም እገዛ እንዳደረገ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በስፍራው በተካሔደ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡
በዓለም ቅርስነት የሰፈሩት የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከ800 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩና ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሠሩ 11 ውቅር አብያተ መቅደሶች ያሉት ሲኾን፣ የቱሪስት ፍሰቱን ያጠናክራል የተባለ አስጎብኚ ቢሮ በአዲስ አበባ ለመክፈትና ሕንፃ ለማስገንባት የደብሩ አስተዳደር መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የአብያተ መቅደሶቹን ጥገና በቴክኒክና በገንዘብ የደገፈው የዓለም ቅርስ ፈንድ፣ በተመሳሳይ ጉዳት ላይ ለሚገኘው የይምርሐ ክርስቶስ ቤተ መቅደስ የቅድመ ጥገና ጥናት፤ 150 ሺሕ ዶላር መለገሡንና የጥናት ስምምነቱም፣ በፈንዱ የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተርና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መካከል ከኹለት ወራት በፊት መፈረሙ ተገልጿል፡፡

      ሰው በሀገር ይወለዳል ይባላል። ግን ደግሞ ሀገርን የሚወልዱ ሰዎች አሉ።  
አብደላ እዝራ ጥበብና ፍቅር የተቃቀፉበት ሀገር በውስጡ ተሸክሟል።አብሮም ኖሯል።  የምናውቀው በተባ ብዕሩ፣በሰላ ሂሱ፣ስለ ጥበብ ሲል ሁሉንም በሚተው ኪናዊ ፍቅሩ ነው።  የአንጋፋ ደራስያንን ሥራ ፈትኗል፤የረገበውን የሀገር ጥበብ ቆንጠጥ አድርጎ በከፍታ አጉልቶ ለማሳየት።  ጠቢባን የሚያደንቁ ውብ ዓረፍተ ነገሮችን ዘክሯል። እምቡጥ አበቦቹን ወጣት ደራሲያንን በሚሳሳ እጁ ኮትኩቷል።  ቸርነቱ በጥበብም በቁስም ነው።   አብደላ እዝራ ጭው ባለ በረሃ ውስጥ ዕድሜውን ሙሉ ለጥበብ ንጽህና እንደ ምንጭ
የፈሰሰ ጅረት ነበር!   በፈረሰው  ቅጥር -----     የቆመ የጥበብ ዘብ!!
                                   *********   
        አንጋፋው የጥበብ ሃያሲና የአዲስ አድማስ ጸሐፊ እዝራ አብደላ፣ ቅዳሜ ግንቦት 28  ቀን 2008  ከዚህ ዓለም በሞት  ተለይቶናል። የቀብር ሥርዓቱ እሁድ ተፈጽሟል።  ለቤተሰቡ፣ለወዳጆቹ፣ለአድናቂዎቹና ለጥበብ አፍቃሪያን መጽናናትን እንመኛለን።