Administrator

Administrator

      የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ፣ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች 128 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ የሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት መወሰኑን ከትናንት በስቲያ አስታወቀ፡፡
በዩኤስኤአይዲ የዲሞክራሲ፣ የግጭትና የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪ ቶማስ ኤህ ስታል፣ ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍ እርዳታው ምግብ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የስነምግብ አገልግሎቶችና ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖችን የሚያጠቃልል መሆኑንና ለአርሶ አደሮችም የተለያዩ የእህል ዘሮች እንደሚከፋፈሉ ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ እርዳታው አሜሪካ ድርቁ አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል ለመከላከል ስታደርገው የቆየቺውን ጥረት አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉት ስታል፣ አሜሪካ ከጥቅምት ወር 2014 አንስቶ፣ ለኢትዮጵያ 705 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡

       በደቡብ አፍሪካ ምስራቃዊ ኬፕታውን በሚገኘው ሴንት ፍራንሲስ ቤይ የተባለ አካባቢ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ባለፈው ሳምንት በዘራፊዎች መገደሉንና ይህን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኙ የውጭ አገራት ዜጎች መደብሮች በአገሬው በመዘረፍ ላይ እንደሚገኙ ተዘገበ፡፡
ኢዮብ ማዴሞ የተባለው ኢትዮጵያዊ የ27 አመት ወጣት ከ9 ቀናት በፊት ክዋኖምዛሞ በተባለው አካባቢ በሚገኘው መደብሩ ውስጥ እያለ በአንድ ዘራፊ መገደሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ ወጣቱን በመግደል የተጠረጠረው ዘራፊ የሌላን ኢትዮጵያዊ መደብር ዘርፎ ካመለጠ በኋላ፣ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያውያን ናቸው በተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በደረሰበት ድብደባ ህይወቱ ማለፉን ገልጧል፡፡
ይህም በአካባቢው በሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ቁጣ መቀስቀሱንና የተደራጁ ዘራፊዎች ሲ ቪስታ በተባለው አካባቢ የሚገኙ የውጭ አገራት ዜጎችን መደብሮች መዝረፍ መጀመራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የአካባቢው የፖሊስ ቃል አቀባይም ስምንት ያህል የውጭ አገራት መደብሮች መዘረፋቸውን እንዳረጋገጡ ገልጧል፡፡
ፖሊስ ዝርፊያውን ለማስቆም በአካባቢው መሰማራቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በዘረፋው ላይ ተሰማርተዋል በሚል የተጠረጠሩ ሶስት ደቡብ አፍሪካውያንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ከትናንት በስቲያ በሁማንስ ድሮፕ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስታውቋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የሉዋንግዋ ፍርድ ቤት በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ወደ ዛምቢያ ገብተዋል በሚል በተከሰሱ 41 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉን ሉሳካ ታይምስ የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘግቧል፡፡ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች፤ የገንዘብ ወይም የሶስት ወራት እስር እንደሚጠብቃቸው የገለጸው ዘገባው፣ ስደተኞች ዕድሜያቸው ከ30 አመት በታች መሆኑን አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ሉዋንግዋ ተብሎ በሚጠራው የድንበር አካባቢ አቋርጠው ወደ ዚምባቡዌ ሊያመሩ ሲሉ በዛምቢያ ፖሊስና የደህንነት አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተነግሯል፡፡
ባለፈው ወርም በተመሳሳይ ሁኔታ ይህን ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ 16 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአገሪቱ የደህንነት ሃይሎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም ዘገባው አስታውሷል፡፡

          በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ ገርባ ከተማ፣ ከሑዳዴ ጾም እና የፋሲካ እርድ ጋር በተያያዘ ከበዓሉ ቀን ጀምሮ ሁከት ተፈጥሮ እንደነበር የተገለጸ ሲኾን፤ በቡድን ተደራጅታችሁ ሁከት ፈጥራችኋል በሚል የታሰሩ ከኻያ ያላነሱ ሰዎችም ፍ/ቤት ቀርበው በነፃ እና በዋስ ተለቀዋል፡፡
በጾም ወቅት የከተማዋ ሉካንዳ ቤቶች እንዳይዘጉ ሲከላከሉ ነበር በተባሉ ግለሰቦች ስጋት ተፈጥሮ መቆየቱን የተናገሩ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ በበዓሉ ዕለት በተከፈተ አንድ ሉካንዳ ቤት ደግሞ ሕገ ወጥ እርድ ተካሒዷል በሚል ሁከቱ መቀስቀሱን ጠቁመዋል፡፡
በሁከቱ በሉካንዳው ላይ ጉዳት የደረሰ ሲኾን ባለቤቱን ጨምሮ የከብቱን ቆዳ ገዝቷል የተባለ ነዋሪና ሥጋም ለመሸመት ሞክሯል የተባለ ሌላ ሰው በማዘጋጃ ቤቱ ታስረው መዋላቸው ተገልጧል፡፡
በበዓሉ ማግሥት፣ የሉካንዳው ባለቤት ይቅርታ ጠይቆ የከብቱ ሥጋ ከተወገደ በኋላ ሉካንዳው ሥራውን ቀጥሎ የዋለ ሲኾን፤ ከቀትር በኋላም የከተማው አስተዳደር ሓላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በጉዳዩ የምክክር ስብሰባ ተካሒዶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ስብሰባው ምሽቱን መጠናቀቁን ተከትሎ ግን፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች የወረዳውን ሊቀ ካህናት እና በከተማው የሚገኘውን የገርባ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ አባላት በድንጋይ እሩምታ ሲያሳድዱ፣ መኖርያ ቤቶቻቸውንም እየለዩ በመደብደብ ጉዳት አድርሰዋል፤ ተብሏል፡፡ የከተማዋ ፖሊስ ኹኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ በነበረበትም ወቅት፣ ግለሰቦቹ የቤተ ክርስቲያኑን ክልል በመክበባቸውና ደወልም በመሰማቱ ለሁከቱ መባባስ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በቀጣዩ ቀን በወረዳው ባለሥልጣናት በተጠራውና የሁከቱን መንሥኤ በመለየት ላይ ያተኮረ ነበር በተባለው ስብሰባ፤ ፖሊስ በቡድን ተደራጅተው ሁከት ፈጥረዋል ያላቸውን ተጨማሪ ሰዎች ማሰሩን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከበዓሉ ማግሥት ጀምሮ በወረዳዋ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ከኻያ የማያንሱ ግለሰቦች ማክሰኞ እና ኃሙስ በቡሌ ሆራ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲኾን፤ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ አላገኘሁባቸውም በማለታቸው በነፃ እና በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ሁከቱ የዓመት በዓሉን የሉካንዳ ንግድ መነሻ ያደረገ ይኾናል ብለው እንደሚገምቱ የተናገሩ አንድ የሃይማኖት አባት፤ “ጉዳዩ የሃይማኖት ግጭትም አይደለም፤ የብሔረሰብ ግጭትም አይደለም፤ ችግሩ የተወሰኑ ሰዎች ስሜትና አጀንዳ ነው፤” ብለዋል፡፡
“ሕዝቡ አብሮ የኖረ ነው፤ ነገም አብሮ የሚኖር ነው፤” ያሉት እኚሁ አባት፤ በግለሰብ ደረጃ ያሉ ጠብ አጫሪዎችና በሕዝቡ ወይም በሃይማኖት ተቋማት ሽፋን በመጠቀም የብጥብጥ ሙከራ የሚያደርጉ በየመሥሪያ ቤቱም ኾነ በየሃይማኖት ተቋማት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ከመጠየቅ ጀምሮ የከተማችንን ችግር እኛው በራሳችን ተነጋግረን መፍታት አለብን፤ የሚሉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ግን፣ የማረጋጋት ዓላማ ያላቸውን ስብሰባዎች እንደቀጠሉ መኾናቸውን ተናግረዋል፤ መንሥኤውንና ተጠያቂውን አካል በትክክል ለይቶ መፍትሔ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ባለመቋጨቱም እንዲህ ነው የሚል መረጃ ለመስጠት እንደሚያስቸግር አስታውቀዋል፡፡
የከተማዋን ፖሊስ እና የአስተዳደር ሓላፊዎች በስልክ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ጥሪው ስለማይመልስ አስተያየታቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡






ሼክ መሀመድ አሊ አላሙዲ ለመቄዶኒያ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ 16 ሚ. ብር ለገሱ፡፡ እርዳታውን ለማዕከሉ ያስረከቡት የሞሀ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ቢርቦ ሲሆኑ የተረከቡት ደግሞ የማዕከሉ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ከርክክብ ስነስርዓቱ በኋላ የመቄዶኒያ መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ ባደረጉት ንግግር፤ ሼክ አሊ አላሙዲ ከዚህ ቀደም እንደነ ደርባ ሲሚንቶ፣ ኒያላ ሞተርስ፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ አዲስ ፓርክ፣ አዲስ ጐማ፣ ኤልፎራ፣ ኩዊንስ ሱፐር ማርኬትና ሚድሮክ አንሊሚትድ ፓኪንግ ፋክተሪ በመሳሰሉ ድርጅቶቻቸው በኩል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሳቸውን አስታውሰው፤ በሼኩ የተለገሱት አምቡላንሶችም ከ800 በላይ ተጨማሪ እርዳታ የሚፈልጉ ደካሞችን ከየጐዳናው ለማንሳት እንዳገዟቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ቢኒያም አክለውም መቄዶኒያ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ከአንድ ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን እየረዳ መሆኑን ጠቅሰው ለዕለት ፍጆታ ብቻ በየወሩ ከ1ሚ. ብር እንደሚያወጣ ገልፀዋል። ከ300 ሚ.ብር በላይ ለሚያስፈልገው ማዕከል ግንባታ ማህበረሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተማፀኑት መስራቹ፤ ሼክ አላሙዲ የለገሱት 16 ሚ. ብርም ለማዕከሉ ግንባታ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
የሞሃ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ቢርቦ ባደረጉት ንግግርም፤ መቄዶኒያ እያከናወነ የሚገኘውን በጐ ተግባር አላሙዲን እንደሚያደንቁ ገልፀው ወደፊትም እርዳታቸው ከማዕከሉ እንደማይለይ ጠቁመዋል፡፡

Saturday, 07 May 2016 13:37

ይበለኝ በገዛ እጄ!

    ያዕቆብ ይባላል፡፡ ሙሉ ቀን መለሰ “ሰንደቅ ያሰቅላል”ን ለሴት ቢያዜመውም ያዕቆብን በሚገባ ይገልፀዋል፡፡ የአርባዎቹን አጋማሽ እየተሻገረ ቢሆንም ግርማ ሞገሱ፣ቅልጥፍናውና ሽንቅጥቅጥ ማለቱ ገና በሰላሳዎቹ ማለዳ ላይ ያለ ያስመስለዋል፡፡ ተምሯል፤የገንዘብም የዲግሪዎችም ሀብታም ነው፡፡ በአንድ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በሚንቀሳቀስ ትልቅ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ ይሰራል፡፡ ዘወትር ሙሉ ልብስ ግዴታው ነው፡፡ እንደሱ የሚያምርበትም አላየሁም፡፡ ታዲያ በዕረፍት ቀኖቹ ቀለል ያለ ልብስ ሲለብስ ሌላ ሰው ይመስላል፡፡ ልውጥ ይላል፡፡ባሌ ነው፤ የምወደው ባሌ፡፡ ምን ዋጋ አለው? ጥሎኝ ሄዷል፡፡ ሁለት ሳምንቱ … በገዛ እጄ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጥሎኝ መሄዱን እንጂ ጠልቶኝ መሄዱን አላምንም፡፡ ጠልቶኝ ካልሆነ ደሞ ክዶኝ ሊሆን አይችልም፡፡ የጋብቻችንን ዘጠነኛ ዓመት ለማክበር የቀረንም ሁለት ሳምንት ብቻ ነበር … ዝግጅታችንን በጋራ አቅደን ጨርሰንም ነበር፡፡
“ካልሆነልን ለምን እንጨነቃለን አቡቲዬ” ውይ ቁልምጫው ሲጥመኝ….አበባ ብሎ ጠርቶኝ  አያውቅም፡፡
“ምንም አይሰማህም?”
“አልዋሽሽም … በቃ ማመን ካለብን ማመን ወይም ተማክረን አማራጭ …”
ቀለል ሲያደርገው ማን አክብጂው አለኝ … በገዛ እጄ!
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ወደ ምሰራበት ግብረሰናይ ድርጅት ቢሮ መጣ፡፡ የኛን ድርጅት የሚረዱ … የውጭ ተቋማት ከነሱም ጋር ይሰራሉ፤ ተመሳሳይ ዓላማዎች ሲገጥሙን አብረን እንሰራለን፡፡ እኔ ደሞ የድርጅታችን ዋና ኃላፊ ነኝ፡፡ ወደ ቢሮዬ ሲገባ ዓይኖቼ ከቁጥጥሬ ወጥተው አጠር ያለች ቁመቴ ረዝማብኝ እየሳብኳት ብድግ ብዬ ተቀበልኩት፡፡ ዘንጣፋ ሰውነቱን እጥፍ አርጎ በአክብሮት ጨብጦኝ ተቀመጠ፡፡ ቢሮዬን እንደሱ የሞላው ሰው አልገጠመኝም፡፡ በግርማው ተጥለቀለቀች፡፡ ለስንትና ስንት ጥላ ቢሶች የሚተርፍ ግርማ፣ የቀልቤን መዝረክረክ ይወቅብኝ አይወቅብኝ እንጃ፡፡ እንደ ምንም የመጣበትን ጉዳይ ተነጋግረን ሄደ፡፡ ለሱ ነው የሄደው፤ ለኔ ቢሮዬ ነበር የዋለው፡፡
ጉዳዮች አመላለሱት፤ቀጥሎም እኔ ጉዳዩ ሆንኩና … ልቤ ላይ በድብቅ ስትንፈራፈር የነበረችውን የፍቅር ፅንስ ነፍስ ዘራባት፡፡
እኔን ድንገት ላየኝ ሰው፣ ክልስ ልመስለው እችላለሁ፡፡ “ቀይ ሰው መልክ አይፈጅም” ቢባልም ሳይጋነን ፈጅቻለሁ፡፡ ከ27 ወደ 28ኛ ዓመቴ በመሸጋገር ላይ ነበርኩ፡፡ አስጨናቂ የዕድሜ ዳገት ነው ለኛ ለሴቶች፡፡ ብዙ ወንዶች እንዳዩኝ ቢሸነፉም እኔ በቀላሉ አልሸነፍም፡፡ እየፈለግሁ እንኳን አይሆንልኝም፡፡ ዕውቀት፤ ስራ፤ ጥሩ ደሞዝ፤ ጥሩ ኑሮ አለኝ፡፡ ለእህቶቼ ተርፌያለሁ፡፡ በየመንገዳቸው ሄደው ርቀዋል … የእናቴን ድህነት ታሪክ አድርጌ ቀብሬዋለሁ፡፡
 ጎድሎኝ የነበረውን ያቆብ ሞላው … ስንላመድ እንደ ልጅ ያደርገን ጀመር፡፡ ያልኖርነውን እንደ መኖር … በኋላም ምርጫ አጣን፤ ከመጋባት በቀር፡፡ … በቃ አደረግነው፡፡ ተጋባን፡፡  በቅርብ ጓደኞቻችንና ወላጆቻችን ብቻ ታጅበን … በእማዬ “እልልታ” ደምቀን፣ “በወልዳችሁ ሳሙ” ምርቃት እየሰፈፍን ወደ ያቆቤ የሪል ስቴት ቪላ ገባን፡፡ ኑሮ ደመቀ … ጣፈጠ … ግን አልሞላም … ሁሉም ላይሞላ ቢችልም ደርበብ የሚያደርገው የእማዬ ምርቃት ሰሚ አጣ፡፡ በየወሩ ጠባዬን … ሆድ ሆዴን ትከታተላለች፡፡ ያቆቤም ይጠብቃል፡፡ ሁለት ጊዜ እያሳየ ነሳኝ፡፡ ደስታችንን ሳናጣጥም ጨንግፎ አጨነገፈን … ከዚያ በቃ ዝም ሆነ፡፡ እናቴም “ፈጣሪ ያልፈቀደውን እሷን ምን አርጊ እላታለሁ?” ብላ ነው መሰል ዝም …. እምምምም ብላ ቀረች፡፡ ያቆብም አመነ፡፡ ከዕውነቱ ጋር ታረቀ፡፡ እኔ ግን ጭንቀት የውስጥ ልብሴ ሆነ፤ከላይ ድምቅ ፅድት ውስጤ ግን …
ሰሞኑን ሃዘን ላይ ነኝ፤ ከፍራሽ ላይ ሳልወርድ እንባዬን ደብቄ አወርደዋለሁ፡፡ የሰርጋችንን ቪዲዮ ማየት የዘወትር ስራዬ ሆኗል፡፡ ያቺን ብርቅ ቀን፣ ያንን ድንቅ የፍቅር ሰው እያሰብኩ እንባዬ ሊያልቅ ነው፤ ሚዚዬ ሔዋንም የለችም፤ አብሮ አደጌ፣ ከራሴ እኩል ከማያቸው ሰዎች አንዷ ናት፡፡ ያሉኝም እነዚሁ ናቸው፡፡  እናቴ --- ያቆብ --- ሔዋን!!
… እናቴ የያቆቤን መጥፋት ማወቅ የለባትም፤ሌላ ህመም ይሆንባታል፡፡ በገዛ እጄ ራሴን ክፉኛ ቀጣሁት፡፡
“አቡቲ”
“ወዬ..”
“ራስሽን እያስጨነቅሽ ነው”
“ደህና ነኝ”
“እያየሁሽ …. ለምን በጉዲፈቻ አናሳድግም” ለስሜቴ እየተጠነቀቀ
“ከስራሽም ጋር ስለሚያያዝ….”
“እስኪ … አንድ የማሰላስለው ነገር አለ … እሱን …”
“ምንድነው አቡቲዬ?”
“ሰሞኑን እነግርሃለሁ”
ቢሮ ገባሁ አልገባሁ ለውጥ አልነበረውም፡፡ የስራ መንፈሴ ሸሽቶኛል፤ የአዕምሮዬም አቅም ተዳክሟል፡፡ ስልኩ ላይ መደወል መደወል … ዝግ ነው፤ ቢዚ ነው፤ ሊገኝ አይችልም …ይለኛል፡፡ አንዴ በመሃል ላይ ድምጹን ሰማሁት፡-
“ሃሎ አቡቲ” ጥሎኝ ሄዶም አቡቲ ማለቱ ገረመኝ፡፡
“ያቆቤ” ሳግ እየተናነቀኝ አወራሁት …
“ኬንያ ነኝ … ስመለስ እደውላለሁ” አጣድፎኝ ሥልኩን ዘጋው፡፡ ስራው ከሀገር ሀገር እንደሚወስደው አውቃለሁ፡፡ ሳይነግረኝ ግን የትም ሄዶ አያውቅም፡፡ ወደ ቢሮው ስሄድ መውጣቱን ይነግሩኛል፡፡ ዝም ብዬ ግራ ስጋባ ሰነበትኩ፡፡
ከጉዲፈቻው አማራጭ በፊት ያሰብኩትን ይዤ ሔዋን ጋ ሄጄ ነበር፡፡ እኩያዬ … ከወዲያኛው ጫፌ እስካለሁበት የምታውቀኝ፡፡ ቆንጆ ነች፤ደስ የምትል ቆንጆ፡፡ ትምህርት ዕጣ ክፍሌ አይደለም ብላ ሁለተኛ ደረጃን ጀምራ ትታዋለች፡፡ በማያዛልቁ ስራዎች ወጣ ገባ ስትል ወንዶች አዩዋት፡፡ ሁሉንም ነገር ቀድማን ነው ያደረገችው፡፡ ቸኩላ አገባች፤ ሁለት ወለደች፤ ሳይቆይ ባሏ በሞት ተለያት፡፡ ብዙም አላዘነችም፤ ኑሮዋንም አለስልሶላት ነበር ያለፈው፡፡ ወጣ ገባዋን ቀጠለች፡፡ የባሏ ዘመዶች በቅርብ ርቀት አዩዋት፤ ገመገሟት፡፡ በመጨረሻ “አንቺ ጥሩ ወላጅ እንጂ ጥሩ እናት አይደለሽም” ብለው ልጆቿን ወሰዱባት፡፡ ጭራሽ ተመቻት አማረባት፤ ተስማማት፤ ያለውን ወንድ የመረቧ ሲሳይ ማድረግ ሆነ ስራዋ፡፡
“ሔዊ ምን ይሻለኛል?” ስላት … እየሳቀች፤ “ወልጄ ልስጥሽ እንዴ?” አለችኝ፡፡ ደንታ የሌላት ናት፡፡ በላች ጠጣች፤ ይዛ ወደቀች .. በቃ ኖረች…
“እኔም ያሰብኩት …”
“አትቀልጅ …”
“ተመሳሳይ ነው ---” ልጅነታችንን … መወለድ ቋንቋ እንደሆነ ያየንባቸውን ዓመታት … ፍቅራችንን እያሰብኩ አማከርኳት …
የዛኑ ቀን … ማታ … መኝታ ክፍላችን ውስጥ … ክንዱን አንተርሶኝ ከሔዋን ጋር የተመካከርነውን ስነግረው … እመር ብሎ ተነሳና አየኝ፡፡ መቆጣት አይችልበትም፡፡ ሄዋንን  እንዳገኛት አይፈልግም ነበር፡፡ “አብሮ ማደግ አብሮ ማርጀት መሆን አለበት” ይለኛል … ሌላ ጊዜ ደሞ “ያኔ እኩል ነበራችሁ … አሁን ግን አይደላችሁም” እያለ ግንኙነታችንን ይቃወም ነበር፡፡
 እኔ ግን ሔዋንን እንደሱ ላያት አልቻልኩም፡፡ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ በማግባባት--- በመለመን --- ረታሁት፡፡
“የግድ ካልሽ … ይሁና” አለና ዞሮ ተኛ፡፡ በግድ ሳዞረው የቀይ ዳማ ፊቱ ላይ ጭንቀት፤ ፍርሃት፣ ግርምት … በየተራ እየበሩ ሲጠፉ አየሁ
ዛሬ አስራ ሰባተኛ ቀኑ ከጠፋ፡፡ አቅሜ ተዳክሟል፡፡ ስልኩ አይመልስም፤ ቢሮዬን ትቼ ወጣሁ፡፡ ባልደረቦቼ የሚያደርጉልኝ ጠፍቷቸው እንጂ ጭንቀቴ አስጨንቋቸዋል፡፡ መኪናዬ ራሷ ትምራኝ ደመነፍሴ እንጃ … ብቻ እየበረረች ነው፡፡ ያለ ቀልቤ መኪናዬን ዳር አውጥቼ ሳቆማት፣ ከፊቴ የማውቃትን መኪና ያየሁ መሰለኝ፡፡ ወረድኩ፡፡ አዎ የማውቃት መኪና ናት … ሰውነቴ ባንዳፍታ አልታዘዝ አለኝ፡፡
እግሬ እየመራኝ ጥቂት ተራመድኩ፡፡ የልጅነት ጓደኛዬ፣ሚዜዬ ቤት በራፍ ላይ ደረስኩ፡፡
ሳላንኳኳ በሩን ገፍቼው ገባሁ፡፡ ከደፉ ግን ማለፍ አልቻልኩም፡፡ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ እውትና ቅዠት ተምታታብኝ፡፡ ቅዠት ቢሆንልኝ ተመኘሁ፡፡ ምኞቴ ግን አልሰመረም፡፡
የማፈቅረው ባሌ ያቆቤ----ከራሴ እኩል የማያት የልጅነት ጓደኛዬ ሔዋን---- አንድ ላይ የተሰፉ መስለዋል፡፡ ጠፍተዋል፡፡ አንጎሌ ለአፍታ ማሰብ ያቆመ መሰለኝ፡፡ ሁሉነገሬ ዝም አለ፤ጭጭ፡፡ “ሔዊ ለአንድ ቀን ከያቆቤ ጋር …” ብላት … የልጅነቴን ፀጋ … በረከቴን ሁሉ ነጠቀችኝ፡፡ በአንዲት ቀን ጦስ ባሌን በሞገደኛዋ ሔዋን ጭን ስር አስቀረሁት፡፡ ጓደኛዬንም ባለቤቴንም አጣኋቸው፡፡ ፊቴን አዙሬ ወደ መኪናዬ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ያየሁት አስክሮኛል፤ አፌም አይኔም ደርቀዋል፡፡ እነሱ ግን ምን አጠፉ? የራሴ ጠላት ራሴ ነኝ፤ ሁሉም የሆነው በገዛ እጄ ነው፡፡ መኪናዬ ውስጥ ከገባሁ በኋላ እንዲህ የሚል ሃሳብ በግድ መጣብኝ፡- “ያንን ሁሉ ዓመት በኔ ደስተኛ አልነበረም ወይስ ከሁሉም ሾራ የምታሾረው ሔዋን ሌላ ተዓምር አሳየችው ?!”
ይበለኝ፤በገዛ እጄ ነው! የራሴ ጠላት ራሴ ነኝ !!







ዓለማቀፍ የፕሬስ ቀን ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 25 በሀገራችን የተከበረ ሲሆን በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት በፍሬንድሺፕ ሆቴል የግማሽ ቀን
የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በፓናል ውይይቱ ወቅት የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን ሁኔታ የሚዳስሱ ሶስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሠፊው ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡
“የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር - ኢትዮጵያ” የሚል መሪ ቃል የተሰየመለትን የዘንድሮ የፕሬስ ቀን መነሻ በማድረግ፣ በተለይ በአገራችን ያለውን ተጨባጭ እውነታ
በተመለከተ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የጋዜጠኝነት መምህራንን፣ የጋዜጠኛ ማህበራት አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችንና ምሁራንን አነጋግሯል፡፡
ሃገሪቱ በመሪ ቃሉ ላይ እንደተጠቀሰው በእርግጥም የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር ናት? አስተያየት ሰጪዎቹ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውንና ዕይታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

“ብዝሃነት መሬት ላይ ያለን ሃቅ
ለመደፍጠጥ የዋለ ቃል ነው”
በ1920 እና 30ዎቹ ጆርጅ ኦዌል “1984” የተሰኘ መፅሃፍ ነበረው፡፡ በዚህ መፅሃፍ ውስጥ “ፖለቲካና ቋንቋ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ፅሁፍ፤ “መሬት ላይ ያለን የፖለቲካ ችግር በቋንቋ ለመሻገር መሞከር” ይለዋል፡፡ ቋንቋን በመጠቀም የተወሰነ ርዕዮተ ዓለማዊ ግብን መምታት ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የሚዲያ ሁኔታ ገምግም ከተባልኩ በሁለት መንገድ ነው የማየው፡፡ አንደኛው ክፍል ራስን ሳንሱር በማድረግ (ሰልፍ ሴንሰርሺፕ) ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሰልፍ ሴንሰርሺፑ አንዳንዴ ከመንግስት ጫና በላይም ሊሻገር ይችላል፡፡ አሁን እያየነው ያለው ያንን ነው፡፡ ደርግና ኢህአዴግ የሚለያዩት እዚህ ላይ ነው፡፡ ደርግ በግልፅ አታድርግ ይልሃል፡፡ ኢህአዴግ የሴንሰርሺፕ ተቋም አላቋቋመም፤ ነገር ግን “ይሄን ካደረግህ ዋ ኮንትራት አንሰጥህም” ይላሉ፡፡ “ብዝሃነት” የሚለው ቃል እንግዲህ ቋንቋ ሰርቆ መሬት ላይ ያለን ሃቅ ለመደፍጠጥ የዋለ ቃል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም አይገልፀውም፡፡ ይሄን ካልን ብዙም “ብዝሃነት አለ፣ የለም” የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አይጠበቅብንም፡፡

              ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
(የፍልስፍና ምሁር)

=========================================

“ሚዲያው የሃሣብ ብዝሃነትን
የሚፈራ ነው”

ኤልያስ ገብሩ
(የ“አዲስ ገፅ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ)

የፕሬስ ብዝሃነት ማለት የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበት ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግን ደግፎም ሆነ ነቅፎ መፃፍ መቻል ማለት ነው፡፡ ብዝሃነት ቃሉን እንዲሁ ለፕሮፓጋንዳ ተጠቀሙት እንጂ አሁን መሬት ላይ ካለው ሃቅ ጋር ፈጽሞ የማይሄድ ነው፡፡ እስከ ዛሬ እንደውም ሚዲያው የሃሣብ ብዝሃነትን የሚፈራ ሆኖ ነው የሚታየው፡፡ ኢቢሲን ብንመለከተው ለአንድ ወገን ወግኖ የሚሠራ ነው፡፡ የተለያዩ ሃሳቦችን የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ በምርጫ ክርክር እንኳ ተቃዋሚዎች በጣት የምትቆጠር ደቂቃ ነበር የተሰጣቸው፡፡ ይሄ ኢህአዴግን በሃሳብ የበላይነት አሸንፈን ስልጣን እንይዛለን ለሚሉ ተቃዋሚዎች ምን ይጠቅማቸዋል? ራሳቸውን እንኳ ለማስተዋወቅ የማይበቃ ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የሚዲያ ብዝሃነት ተፈጥሯል ልንል የምንችለው? መንግስት ብዝሃነትን አስቦ ቢንቀሳቀስ ኖሮ፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ ውብሸት ታዬ፣ እነ ተመስገን ደሣለኝና የመሳሰሉ ጋዜጠኞች አይታሠሩም ነበር፡፡ በሃሳብ ብዝሃነት የሚያምን መንግስት ቢኖር ኖሮ፣ ፖለቲከኞች በየጊዜው እየታሠሩ ባልተፈቱ ነበር፡፡
አለማቀፍ ተቋማት የሀገሪቱን የፕሬስ ሁኔታ አስመልክቶ የሚያወጡት ሪፖርት መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የሚገልጽ ነው፡፡ እኛም ሪፖርት እንስራ ብንል ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ በሚዲያ ጉዳይ ጥናት የሚያደርግ የሀገር ውስጥ ተቋም ቢኖር፣ ከእነሱ የከፋ ሪፖርት ሊያወጣ እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ ዛሬ ጋዜጠኝነት የአደጋ ቀጠና ሆኗል፡፡ በሙያው ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች እንኳ ወደ ሙያው መቀላቀል አደገኛ መሆኑን እያዩ እየሸሹ ነው፡፡

================================

“ሚዲያዎች በሞኖፖሊ ስር ነው ያሉት”
አቶ ወንድወሰን ተሾመ
(የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት)

  በየአመቱ የሚከበረውን የፕሬስ ቀን በፊት ያከብር የነበረው የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) ነበር፡፡ እለቱ ታሣቢ የሚያደርገው የታሠሩትን የተሰደዱትን፣ በሙያቸው ጫና እያረፈባቸው ያሉትን ነው፤ መከበር ያለበትም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አሁን ሞኖፖሊ የሠፈነበት ጊዜ ላይ ነው ያለው፡፡ የግል ፕሬስ አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ ሞኖፖሊ ሲበዛ የሚዲያ ብዝሃነት የምንለው ነገር ይጠፋል፡፡ የግል ፕሬሶች በወረቀት ዋጋ መናርና በሌሎች ምክንያቶች እየተዳከሙ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በግል የተያዙ ያሉ ቢሆንም ብዝሃነት ያለው ሃሣብ የማንሸራሸር አቅም ሲፈጥሩ አልታዩም፡፡ በሞኖፖሊ ስር ነው ያሉት፡፡ በሙያቸው ጋዜጠኛ ሆነው የምናቃቸው ሰዎች፤ መንግስት በሌላ ጉዳይ ወንጀለኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ በማለቱ አሁን በእስር ቤት የሚገኙ አሉ፡፡ መንግስት በዚህ ቀን እነዚህን ሙያተኞች ቢለቃቸው ምን ይጐዳል? እንደውም ክብር ያገኝበታል፡፡ የተከሰሱት በሌላ ቢሆንም እኛ የምናውቃቸው በጋዜጠኝነታቸው ነው፤ ቢለቀቁ በሙያው ላይ የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ የመንግስትን ገጽታ በአለማቀፍ ደረጃ የሚያበላሸውና የተለያዩ ሪፖርቶች ላይ የሚንፀባረቀውም ይኼው ነው፡፡

==================================

“ሁሉም አመለካከቶችና ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት እድል አልተፈጠረም”

አቶ አንተነህ አብርሃም
(የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚደንት)
   የፕሬስ ቀን አከባበሩ ላይ እንድንገኝ ተጠርተን ነበር፤አልተገኘንም፡፡ ያልተገኘነው ክብር ስለነፈጉንና ስላዋረዱን ነው፡፡ አንደኛ፤ ተገቢውን እውቅና ነስተውናል፡፡ በበአሉ ላይ መጥታችሁ ቁጭ ትላላችሁ፤ከዚያ ሲያልቅ ትሄዳላችሁ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ነው የተውነው፡፡ እኛ ተሳታፊዎች ብቻ መሆን አይገባንም፤ ባለድርሻዎች ነን፤ ንግግር ለማድረግ አስበን ነበር፡፡ እነሱ ግን እንደ ማንኛውም ሰው ትመጣላችሁ፤ የሚባለውን ሰምታችሁ ትሄዳላችሁ ነው ያሉን፡፡ እኛ ደግሞ ይሄ አምባገነንነት ነው፤አምባገነንነትን መሸከም አንችልም ብለናቸዋል፡፡ እኛ እስከ ዛሬ ከመንግስት ጋር በጋራ ስንሰራ ነበር፡፡ አሁን እኛን ከስርአቱ ጋር የማጋጨት ሥራ ነው የተሰራው፡፡ መንግስት በፊት ያደርግልን የነበረውን ድጋፍም አሁን እየነፈገን ነው፡፡ ድጋፍ ማድረግ አቁሟል፡፡ ለምን አቆመ? መንግስት ራሱ ነው የሚያውቀው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን አከባበር ላይም አያገባችሁም ተብለን ተገፍተናል፡፡  
ይሄ መገፋት ግን እኛን ለሀገራችን ከምናደርገው አስተዋፅኦ አያግደንም፡፡
አንዳንድ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የመንግስትን አቋም አይደለም እያንፀባረቁ ያሉት፤ የራሳቸውን ነው፡፡ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ ስመለስ፤ “የሚዲያ ብዝሃነት” ማለት የተለያዩ ሃሳቦችና አመለካከቶች የሚንሸራሸሩበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው፡፡
በዚህም ሁሉም እኩል የመናገር፣ የመደመጥና ሃሳቡን የማንፀባረቅ መብት ያገኛል ማለት ነው፡፡
 ከዚህ አንፃር ካየነው አሁን ላይ ሁሉም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆኗል ብዬ አላምንም፡፡ ሁሉም አመለካከቶችና ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት እድል አልተፈጠረም፡፡ ይሄን ስል ክልከላ አለ ማለቴ አይደለም፤ ክልከላው ባይኖርም የበለጠ ሙሉ የሆነ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ አሁን ጭራሽ ያለውና የነበረው ነገር እየኮሰመነ ነው፡፡
በተወሰኑ የመንግስት ኃላፊዎች የሚፈለገው፣የጋዜጠኞች ማህበራት እንዲዘጉ ነው፡፡ ይሄ የመንግስት አቋም አይደለም፤የግለሰቦች ነው፡፡ ውይይት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
 ውይይት እናድርግ ስንል ደግሞ ፍቃደኛ አይደሉም፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች የአምባገነንነት አዝማሚያ ፍንጮች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ደግሞ እኛ ልንሸከማቸው አንችልም፡፡

================================

“ብዝሃነት ያለው ሚዲያ ቢኖርማ እኛም ባልተከራከርን”
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
(የመድረክ ሊቀመንበር)

  እኛም ከተያያዝናቸው የትግል አጀንዳዎች አንዱና ዋነኛው ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ጉዳይ ነው፡፡ ባለፉት የፖለቲካ ትግላችንም ለዚህ ስንከራከር ቆይተናል፡፡ ብዝሃነት ያለው ሚዲያ ቢኖርማ እኛም ባልተከራከርን፤ በዚህ ላይ ጊዜያችንን ባላጠፋን ነበር፡፡ ህገመንግስቱ የሚዲያ ነፃነት እንደሚከበር ደንግጓል፡፡ ነገር ግን ስርአቱ በጉልበት ህገ-መንግስታዊ መብቱን ገድቦታል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ዝም ብሎ የሚታይ አይደለም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ መሬት ላይ ያለው ሃቅና በመንግስት የሚነገረው የተለያየ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ አለማቀፍ ሪፖርቶችም በየጊዜው የሃገሪቱ የፕሬስ ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንዳለ እንጂ በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን አያንፀባርቁም፡፡ ጋዜጠኞች ጠንከር ብለው መንግስትን ሲተቹ፣ ሽብርተኛ ተብለው እንደሚታሠሩ እናውቃለን፡፡
ይሄን ሽሽት ጋዜጠኞች ያልተሰደዱበት የአለም ሃገርም የለም፡፡ ይሄ እንዲህ ባለበት ሁኔታ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር” ማለት የህዝብ ንቀት ነው፡፡

==============================

“በሌላው ሀገር መንግስት በፕሮፓጋንዳ አይፎክርም”

በፍቃዱ ኃይሉ (የዞን 9 ብሎገርና
የ“ውይይት” መፅሄት ዋና አዘጋጅ)

   በአገሪቱ የሚዲያ ምህዳር ውስጥ እየኖርኩበት ነው፤ዋጋም የከፈልኩበት ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ከአለማቀፍ ሪፖርት ሳይሆን በዚህ መንገድ የሀገሪቱን የሚዲያ ምህዳር አውቀዋለሁ፡፡ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር - ኢትዮጵያ” የሚለውን መፈክር ስሰማ እንደ ስላቅ ነው የወሰድኩት፡፡ ፀሐፊዎቹ ራሳቸው አምነውበት የፃፉት አይመስለኝም፡፡ መፈክር ራሱ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው፡፡ በሌላው ሀገር መንግስት እንደዚህ በፕሮፓጋንዳ አይፎክርም፡፡ እኔ ከምኖርበት አንፃር ይሄን መፈክር ከስላቅ ለይቼ አላየውም፡፡ በምርጫ ማግስትና በምርጫ ዋዜማ ላይ የሚዲያዎች ቁጥር እኩል አይደለም፡፡ በምርጫ ዋዜማ ላይ ጠንካራ ፕሬሶች ይዘጋሉ፣ ይከሰሳሉ፣ ጋዜጠኞች ይሰደዳሉ፡፡ ይሄን በ2007 ምርጫ አይተነዋል፡፡ የፕሬሱ አስተዋፅኦ አስፈላጊ በሚሆንበት ሰአት ላይ በፍጥነት እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡ ተፅዕኖ መፍጠር በማይችሉበት ወቅት ደግሞ ዝም ይባላሉ፡፡ በሀገሪቱ ያለው የሚዲያ ሃቅ ይሄ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬ ከ10 ሺህ በላይ ኮፒ ያለው ጋዜጣ የለም፡፡ በየቀኑ የሚወጣ ጋዜጣ የለም፡፡ ሬዲዮ ጣቢያዎችም የግል ቢኖሩም ራስን በራስ በመመርመር የሀሳብ ተአቅቦ ያደርጋሉ፡፡ ፖለቲካ ሽሽት መዝናኛና ስፖርት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሚዲያ ብዝሃነት ፅንሰ ሀሳብን ራሱ መንግስት በቅጡ የተረዳው አይመስለኝም፡፡


===============================

“የሚዲያ ብዝሃነት አለመኖር ለመንግስት ውድቀት ነው”

እንግዳወርቅ ታደሰ
(በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋዜጠኝነት መምህር)

ባለፉት 25 ዓመታት ፕሬሶች ቁጥራቸው አንዴ ይጨምራል፣ ሌላ ጊዜ ይቀንሳል፡፡ የመንግስት ሚዲያዎችን ካየን በቁጥር እየጨመሩ ነው፡፡ የብሮድካስት ዘርፍ በቁጥር ደረጃ ከፕሬሱ የተሻለ እየተስፋፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለኛ ሀገር የሚያስፈልገን የሃሳብ ብዝሃነትን ሊያመጣ የሚችል ሚዲያ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የግል ፕሬስ በቁጥር ሊያድግ ይገባዋል፡፡ በብሮድካስቱ ከሚገኙ የግል ጣቢያዎች ውስጥ እንኳ መረጃ ከማግኘት አንፃር ግልፅ ልዩነት ይታይባቸዋል፡፡ ፋና ከመንግስት የሚያገኘውን መረጃ ያህል ሌሎቹ አያገኙም፡፡ ያሉትን ውስን የግል ጋዜጦችም ብንመለከት መረጃ አያገኙም፤ራሳቸውን በራሳቸው ሳንሱር የማድረግ ችግርም አለባቸው፡፡ የሃሳብ ልዩነት በሰፊው የሚያንሸራሽሩ ጋዜጦች እድሜያቸው አጭር ሲሆን አይተናል፡፡
በብሮድካስት በኩል እየበዛ ያለው በቁጥር እንጂ የተለያዩ አስተሳሰቦችን በማንፀባረቅ ደረጃ አይደለም፡፡ በየክልሉ የተመሰረቱ ብሮድካስት ሚዲያዎች ከኢቢሲ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ነው ያላቸው፡፡ እንደኔ በቁጥር መስፋፋታቸው ጥሩ መስሎ የሚታየኝ፣ ስቱዲዮዎች ከመገንባታቸውና መሰረተ ሚዲያው ከመዋቀሩ አንጻር ነው፡፡ ኢቢሲን ነጥለን ብንመለከት ብሮድካስት ኮርፖሬት ሲሆን ራሱን እያስተዳደረ መንግስትን ሳይሆን ህዝብን እንዲያገለግል ተብሎ የተዋቀረ ነው፡፡ ግን አሁን ይሄን በተግባር እየሰራ ነው ወይ? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ከህትመት ሚዲያው፣ጠንካራ ጉዳዮችን የሚዘግቡት ከሁለት አይበልጡም፡፡ ይሄን ስናይ በቁጥርም በይዘትም ብዝሃነት አለው ለማለት እንቸገራለን፡፡ የሚዲያ ብዝሃነት ከሌለ ደግሞ መንግስት ድክመቶቹን መረዳት የሚችልበት አማራጭ አያገኝም፡፡ ይሄ ለመንግስት ውድቀት ነው፡፡ ብዝሃነት ስንል የሃሳብ ብዝሃነት እንጂ ቁጥር ላይ ካተኮርን ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በአሁን ሰአት ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት አማራጭ የላቸውም፡፡ ፕሬሱም የሚገባውን ያህል ቦታ እየሰጣቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ በጥቂቱ የማየው አንዳንድ ጋዜጦች በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሲያወያዩዋቸው ብቻ ነው፡፡ ይሄ ጥቂትም ቢሆን የነሱን ሀሳብ ማግኘት ለሚፈልግ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ መንግስት አቋማቸውን በተዘዋዋሪ እንዲረዳና ምክራቸውን የሚቀበል ከሆነ እንዲቀበል ይረዳዋል፡፡ በዚህ መንገድ ውስጥ ያሉ ፕሬሶች የሃሳብ ብዝሃነት ትርጉሙ የገባቸው ይመስለኛል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤የሚዲያ ፖሊሲውን ልማታዊ ብሎ ጠቅልሎ ጨርሶታል፡፡


===============================


“ራስን በራስ ሳንሱር የማድረግ ችግር አለ”

ዶ/ር ነገረ ሌንጮ
(በአ.አ.ዩ.የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ት/ት ክፍል ዲን)

የአንድ ሚዲያ እድገት የሚለካው አንደኛ የተቋሙ ብቃት፣ የህግ ማዕቀፉ አሠሪነት ምን ያህል አሳታፊ ነው የሚሉት መታየት አለባቸው፡፡ የባለሙያ ደረጃውስ ምን ይመስላል የሚለውንም ማየት አለብን፡፡ ከፕሬስ ነፃነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የፖለቲካል ኢኮኖሚው ለሚዲያ የሚሰጠው ግምት ምንድን ነው የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አኳያ የኛን ሀገር ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሚዲያ ነፃነት መናገር ከጀመርን ሁለት አስርት አመታት ብቻ ነው ያስቆጠርነው፡፡
ስርአቱ ራሱ የሚዲያ ጉዳይን ህጋዊ አድርጓል፡፡ በህገመንግስቱም፣ በሚዲያ ህጐችም የሚዲያ ነፃነት ተደንግጓል፡፡ መረጃ ማግኘት የዜጐች መብት እንደሆነ፣ መንግስት ደግሞ ስልጣኑን የሚያገኘው ከህዝብ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ይሄ እንዴት ነው ተግባር ላይ እየዋለ ያለው ስንል፣ የጋዜጠኞች ብቃትንና የሚዲያ ተቋማትን ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡ በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ የማይካድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሁሉም ሃላፊነት ተሠምቷቸው በትክክል ይሠራሉ ብለን ብንጠይቅ፣ የሚሠሩም አሉ የማይሰሩም አሉ፡፡ ከመንግስት ባለስልጣናትም ህጉን በተገቢው የማያስፈጽሙ ይኖራሉ፡፡ በአለማቀፍ ሪፖርቶች፣መንግስት ሚዲያን ያፍናል የሚል ሪፖርት ይወጣል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በትክክል የጋዜጠኝነትን ሙያዊ መሠረቱን ጠንቅቀው አውቀው የሚሠሩት ናቸው የሚታሠሩት? የሚሰደዱት? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እንደኔ ጋዜጠኞቹም መንግስትም ጋ ችግር አለ፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞችም ራሣቸውን በራሳቸው አላስፈላጊ ሳንሱር ያደርጋሉ፡፡ ይሄ ሲሆን ለህዝብ የተሰጠው መረጃን የማግኘት መብት ይጨፈለቃል፡፡ እኔ ችግር ያለው ከህገ-መንግስታዊ ስርአቱ አይመስለኝም፤የግለሰቦች ችግር ነው፡፡ ባለፉት 20 አመታት በእነዚህ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ የመጣ ፕሬስ እየተገነባ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
“የሚዲያ ብዝሃነትን በእርግጥስ ያከበረች ሀገር ነች ወይ” የሚለው ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ይቅርና አደጉ በተባሉ ሃገሮች እንኳ “አዎ” እና “አይደለም” በሚል የሚመለስ አይደለም፡፡ ለምሣሌ መጽሐፍት የፈለጋቸውን ሃሳብ እያንፀባረቁ ይታተማሉ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ገደብ የሚጣልበት ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ ተገቢ አይሆንም፡፡ የህዝብ ሚዲያዎች ላይ ሃሳብ ምን ያህል ብዝሃነት አለው የሚለውን ስናይ፣ ትንሽ ችግር አለ፤ተከልክለው አይደለም፡፡ የግለሰቦች ራስን በራስ ሳንሱር የማድረግ ችግር ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ብዝሃነት ይኑር የሚል አመለካከት አለ፤ ይሄን ወደፊት በተግባር ማምጣት አለብን፡፡



በጥበባዊ ዝግጅት የታጀበ ነበር

    የዛሬ ሁለት ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የአንጋፋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር 80ኛ ዓመት የልደት በአል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድህረ ምረቃ አዳራሽ ከትናንት በስቲያ በድምቀት የተከበረ ሲሆን በእለቱ ደራሲውን የሚዘክሩ ሰፋ ያሉ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡
“ሌቱም አይነጋልኝ”፣ “ትኩሳት”፣ “7ኛው መልአክ”፣ “5፣6፣7” በተሰኙ ድርሰቶችና አዲስ አድማስን ጨምሮ በበርካታ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በመፃፍ የሚታወቀው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔርን የሚዘክረውን ዝግጅት ያስተባበረው ኢጋ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሲሆን የሃሳቡ አመንጪ አቶ ደምሰው ኃይለሚካኤል ነው ተብሏል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ስብሃት ለመጨረሻ ጊዜ ከፃፋቸው “እሴት ያለው ህይወት ኑር” የሚለውን ደራሲ እንዳለጌታ ከበደና ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ከአብዮቱ በፊት ምን ይመስል ነበር የሚለውንና ከወዳጆቹ ጋር ያለውን ግንኙነት የተመለከተ ፅሁፍ ፕ/ር ሽብሩ ተድላ ያቀረቡ ሲሆን ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በበኩሉ፤ ስብሃት ከአብዮቱ በኋላ ምን ያስብ ነበር የሚለውንና የስብሃት አንዳንድ እውነታዎች በሚል አቅርቧል፡፡
የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ መሰረት አበጀ በስብሃት ስራዎች ላይ በተለይ በ“ሰባተኛው መልአክ” ላይ ዳሰሳዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን አቶ ሄኖክ በሪሁን ደግሞ “5፣6፣7”ን  በመድረክ ላይ ተውኖታል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ከዳር አገር ወደ ዋናው ከተማ የመጡ አዛውንት ለንጉሱ አቤቱታቸውን ለማቅረብ ከዙፋን ችሎቱ ዘንድ ተቀምጠው ተራቸውን ይጠብቃሉ፡፡
ባለሟሎች ስነ-ስርዓት እያስከበሩ ሁሉን በወግ በወግ ያስተናግዳሉ፡፡ አንዱ ሲጨርስ ሌላው ግባ ይባላል፡፡ በዚሁ ደንብ እኒያ የዳር-አገር መኳንንት ተራቸው ይደርስና ይቀርባሉ፡፡ ንጉሱ ገና ከሩቁ አውቀዋቸዋል፡፡ ጃንሆይ፤
“እህስ ምን ችግር ገጠመህና ከሩቅ አገር ድረስ ወደ እኛ መጣህ?”
አዛውንቱም፤
“ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ከንጉሱ ከተማ እኛ ወዳለንበት ዳር-አገር ከሚመጡ ሹማምንት መካከል አንዱ ከብቶቹን በግፍ ነድተውብኛል … ያላግባብ ሰብሌን ወስደውብኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለዘር ያወጣሁትን እህል እንኳ አልተውም፤ መዝብረውታል፡፡ እኔ ከላይም እግዚሃርን፣ ከታችም እርስዎን አምኜ የተቀመጥኩ አንድ ደሀዎ፣ በአገር አማን ይሄ ሁሉ በደል እንደምን ይደርስብኛል?”
ጃንሆይ፤
“ዕውን ይሄ ሁሉ በደል ደርሶብሃል? ለዚህ ዕማኝ አለህ?”
አዛውንቱ፤
“አዎን ጃንሆይ፤ አገር ይመሰክርልኛል፡፡ አገሩ ሁሉ ለእኔ ሲል አልቅሷል፡፡ “ነግ በኔ” እያለም ስጋት አድሮበታል፡፡
ጃንሆይ፤
“ይህ የሚለው ዕውነት ከሆነ በእርግጥ ተበዳይ ነውና ተጣርቶ ካሣ ይከፈለው፡፡ ግምቱ ተሰልቶ እህል ይሰጠው” አሉ፡፡
አዛውንቱ፤ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው፣ እየተደሰቱ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ በቀጠሮአቸው መሰረት ወደ ንጉሱ አገር ተመለሱና ችሎት ቀረቡ፡፡ ባለሟሉ የአዛውንቱን የተጣራ ውጤት ለንጉሴ አቅርቧል፡፡
ጃንሆይ ተጣርቶ የቀረበላቸውን በጥንቃቄ ካዩ፣ ካስተዋሉ በኋላ፤
“ይህ ሰው በደል ደርሶበታል፡፡ ለመሆኑ ይሄን ያህል በደል ሲፈፀምብህ እስከዛሬ ለምን ዝም አልክ?” ሲሉ አዛውንቱን ጠየቁ፡፡
አዛውንቱም፤
“እኔማ ንጉሥ ሆይ! ‹ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተጣልቶ› አይሆንም ብዬ ነው፡፡ ሲብስብኝ በቀጥታ ወደ እርስዎ የመጣሁት፣ በየደረጃው መጎሳቆሉን ፈርቼ ነው፡፡ እርስዎ ባይደርሱበት ነው እንጂ ሹማምንቱን ያስደሰተ እየመሰለው እኛን ሱሪ ባንገት የሚያስወልቅ ስንት አዛዥ ናዛዥ አለ መሰለዎ?”
ጃንሆይ፤
“መልካም፤ ባለፈው እንዳልኩት በደሉ ተገምቶ ተመጣጣኝ እህል ይዞ አገሩ ይግባ” ብለው ፈረዱላቸው፡፡
ይህ በሆነ በሁለተኛውም፣ በሶስተኛውም ሳምንት አዛውንቱ ምንም ያገኙት ነገር የለም፡፡ የተፈረደላቸው ፍርድ አልተፈፀመላቸውም፡፡ ይቀርባሉ፡፡
ጃንሆይ፤
“ዛሬስ ምን ሆነህ መጣህ?” ይሏቸዋል፡፡
አዛውንቱ፤
“ዛሬም አልተፈፀመልኝም ጃንሆይ”
ንጉሡ ደግመው ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡
ታዛዦቹ ሹማምንት “እሺ ጃንሆይ እናስፈጽማለን” ይላሉ፡፡ በተግባር ግን ምንም አይታይም፡፡
አዛውንቱ በመጨረሻ ንጉሱ ዘንድ ይቀርባሉ፡፡

ጃንሆይ፤
“እህ ምን ችግር ገጠመህ?” አሏቸው፡፡
አዛውንቱም፤
“ንጉሥ ሆይ! ዛሬስ አጋሰስ ልጠይቅ ነው የመጣሁት፡፡ ሁሉ ቀርቶብኝ፤ አንድ አሥራ አምስት ያህል አጋሰሶች ይሰጡኝ!”
ጃንሆይ፤
“ለምንህ ነው አጋሰስ የፈለግኸው?”
አዛውንቱ፤
“የሸዋን መኳንንት “እሺታ” ልጭንበት!” አሉ፡፡
***
የሀገራችን የአፈፃፀም ችግር የጥንት የጠዋት ነው፡፡ ህግጋት ይደነገጋሉ፡፡ መመሪያዎች ይወጣሉ፡፡ ማዘዝ ቁልቁለት ነውና ትዕዛዛት ይፈስሳሉ፡፡ ግን በተግባር ሥራ ላይ ውለው አይገኙም፡፡ በየእርከኑ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት፤ ወይ ነገሩን ከጉዳይ አይጥፉትም፤ ወይ በግላቸው እንዳይፈፀም ይሻሉ፤ አሊያም ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ምክንያቶች እየደረደሩ ባለጉዳይ ማጉላላታቸውን ይያያዙታል፡፡
ስብሰባዎች የኑሮ ዘዴ እስኪመስሉ ድረስ በተደጋጋሚ “ስብሰባ ላይ ናቸው”ን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ ጉዳይ የያዘ ፋይል ሲንፏቀቅ ይከርማል፡፡ ዳር የደረሰው ፋይል ደግሞ “ይሄ ይሄ አልተሟላም” ተብሎ ጉዳዩ መልሶ ጥሬ ይሆናል፡፡ የደከመው ባለጉዳይ እርም ብሎ ከነጭርሱ ነገሩን ይተወዋል፡፡ ያልታከተው ባለጉዳይ ሥራ ያቀላጥፍልኛል ወዳለው ሹም በአማላጅ ለመሄድ ይጥራል፡፡ ይሄ የባለጉዳይ መጉላላት እጅግ ሲደጋገም “ጉዳይ አስፈፃሚ” የሚል ታርጋ ያለው፤ በውል በ “ቢ ፒ አር” የማይታወቅ ማዕረግ ያነገበ፣ ሠራተኛ ፈጥሮ ቁጭ ይላል፡፡ ዛሬ በማናቸውም መሥሪያ ቤት ያለ ሥራ፣ ከተቋሙ ውጪ በሚኖር “ጉዳይ አስፈፃሚ” የሚተዳደር ይመስላል፡፡ የቢሮክራሲውን ቀይ ጥብጣብ (bureaucratic red tape) የሚበጥሱ ጉዳይ አስፈፃሚዎች” ናቸው፡፡ “ከእያንዳንዱ አሸናፊ ወንድ ጀርባ አንድ ሴት አለች” ይባል የነበረው፤ በዛሬው የአገራችን ሁኔታ፤ “ከእያንዳንዱ ስኬት ጀርባ አንድ ጉዳይ አስፈፃሚ አለ” የሚባልበት ወቅት ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት፤ በስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች እርስ በርስ ሥራውን ለማሳካት “ጉዳይ አስፈፃሚ” ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡
“ገንዘብ የደም ሥር ነው” የሚለው የጥንት አባባል፣ ዛሬ ዐይን ባወጣ መልኩ እንደ ዱላ ቅብብል ሥራ ማስኬጃ መሆኑ የአደባባይ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነወ፡፡
ከአንድ ቢሮ ጉዳይ ለማንቀሳቀስ ህጉ፣ ባለጉዳዩ የያዘው ገንዘብ ነው፡፡ ፀሐፊዋ ያለገንዘብ፣ ፋይል ለአለቃ አታቀርብም፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚ በፈገግታ “ጉዳይህ ምንድነው” ለማለት ገንዘብ ትሻለች፡፡ አለቃዋ፤ አሉ የሉም፤ ለማለትም ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ጉዳይ ከተፈፀመ በኋላም ገንዘብ እንደማህተም የሚያገለግል የፋይሉ አካል ነው፡፡ ይሄን እንደምሳሌ ጠቀስን እንጂ ከተላላኪ እስከ ሥራ አስኪያጅ፣ ከዚያም እስከ ቦርድ ሰብሳቢ ድረስ፤ መላው ይሄ ሆኗል፡፡ እንግዲህ ይሄ አካሄድ “እየተሻሻለ መጥቷል” በተባለው የመልካም አስተዳደር ዘይቤ ውስጥ ያለ ነው፡፡ “ፍትሐዊ አሠራር እየሰፈነ ነው” በሚባልበት አገር ነው፡፡ “እጅህን እኩሬው ውስጥ ክተት፡፡ ወይ አሣ ታገኛለህ፤ ካልሆነም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ” ነው የትም ቦታ ያለው ሙስናዊ መርህ፡፡ አንዳንድ ሰፈር፤ “አለዛ (ያለገንዘብ) እንዴት ሥራ ይሠራል?” የሚለው አነጋገር የመጽሐፍ ቃል ይመስላል፡፡
አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “የአፍሪቃ አማፂያን ድል ባደረጉ ማግስት ገንዘብ ማርባት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያም ራሳቸው ይሰባሉ፡፡ በመጨረሻም ዕውነተኛው ግብ ራስን ማድለብ ይሆናል”፡፡ (At the end, the real goal becomes fattening oneself) ስለፈጣን ልማት እያወራን ፈጣን ስባት ውስጥ ከገባን፣ ልማቱን ወደ ፈጣን ጥፋት ለወጥነው ማለት ነው፡፡ በቪላዎች፣ በፎቆች፣ በመሬት ብዛት፣ በባንክ ደብተሮች ቁጥር ብዛት፣ በልጅ በዘመድ አዝማድ ውክልና ብዛት ወዘተ… በአጠቃላይ በግል ልማት፤ የአገርን ልማት ተክተን የምንንቀሳቀስ ከሆነ፤ ወሰን-የለሽ መንኮታኮት ገና ይጠብቀናል፡፡ እስር ቤቶች ያለጥርጥር ሞልተው ይትረፈረፋሉ፡፡ የሚገርመው፤ የሚሞሉት በጉቦ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን በጉቦ-ሰጪም ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ፤ ጉቦ-ተቀባዩ በምን መልክ መቀበል እንዳለበት ተጨንቆ ተጠቦ መላ የሚዘይድለት ራሱ ጉቦ-ሰጪው የሆነበት ደረጃ በመድረሱ ወደ ባህልነት ተሸጋግሯ፡፡ ጉዳይ አስፈፃሚው እንደ ህግ አማካሪ ማገልገሉም አይገርምም - የልምድ አዋላጅነት ፈጣን ገቢ የማከማቻ አቋራጭ ሆኗልና! በአቋራጭም ሆነ በረዥሙ መንገድ መንጋ በላተኛ ፈጥረናል፡፡ ደላሎቹ እንደሚሉት፤ “የሥራው ፀባይ ነው” ማለት በሙስናም ረገድ የማያሳፍር አባባል ነው፡፡ ትላልቅ ውሸቶች የጥቃቅንና አነስተኛ ውሸቶች መድብል ናቸው፡፡ አያሳፍሩም፡፡ ገንዘብህን የበላ፣ መሬትህን የበላ፣ ንብረትህን የበላ፤ አንተን ከመብላት ወደ ኋላ አይልም - “መብላት የለመደ ሲያይህ ያዛጋል” የሚባለው ለዚህ ነው!!

      ታዋቂው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሰራቸው ትልልቅና አዳዲስ ስዕሎች፣ “የአዲስ አባ ልጅ” በሚል ስያሜ፣ ሐሙስ  በብሔራዊ ሙዚየም ለተመልካቾች ይታያሉ፡፡ምናባዊ ፈጠራንና ተዓማኒነትን ባጣጣመ ድንቅ የስዕል እውቀትና ክህሎት የላቀ የጥበብ ደረጃ ያሳየ አርቲስት እንደሆነ የሚነገርለት ሰዓሊ መዝገቡ፤ “ንግስ” በተሰጥኦ ትርኢት ያቀረባቸው  ስዕሎች ከፍተኛ አድናቆት አትርፈውለታል፡፡ በታሪክ ተጠቃሽ የሆኑ የስዕል ስራዎቹንና ምርጥ ችሎታውን ማሳየት የጀመረው ከ20 ዓመታት በፊት ቢሆንም፤ በየጊዜው የፈጠራና የችሎታ ምጥቀትን የሚመሰክሩ ስራዎች በማበርከት ይታወቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት “ንግስ” በሚል ስያሜ ያቀረባቸው ስዕሎች በበርካታ የሚዲያ ተቋማት መነጋገሪያ  ርዕስ ለመሆን የበቁትም፤ ስዕሎቹ በፈጠራ ሃሳብና በስዕል ችሎታ አዲስ ደረጃን ያሳያሉ በሚል ነበር፡፡ በርካታ ተመልካቾችን የማረከው ይሄው “ንግስ” የስዕል ትርዒት፣ እንደገና ለእይታ እንዲከፈት በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የነበረ ሲሆን፤ የተወሰኑት ስዕሎች በአሁኑ ትርዒት እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ “የአዲስ አባ ልጅ” ለተሰኘው ትርዒት የተሰሩ  አዳዲስ የመዝገቡ ስዕሎች፤ ከወትሮው የተለዩ አይደሉም፤ እንደ ወትሮው በአዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችና በጥበብ ክህሎት  የተሰሩ ስዕሎች ናቸው፡፡ የፊታችን ረቡዕ ምሽት ተመርቆ ሐሙስ ለተመልካች የሚከፈተው ትርኢት 20 ስዕሎችን የያዘ ነው፡፡


“የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒትና ሕክምና የምዕተ ዓመት ጉዞ” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በዐይነቱም ሆነ በጥልቀቱና በይዘቱ የተለየና የመጀመሪያው ነው የተባለ ሲሆን ለረጅም ጊዜ ተዘንግቶ የኖረውን የሀገረሰብ ህክምና ታሪክ በማጐልበት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተገልጿል፡፡ አዘጋጁ ዶክተር ባልቻ አሰፋ ከተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በርካታ የቃልና የጽሑፍ ማስረጃዎችን፣ 63 ያህል የሀገረሰብ ህክምና ባለመያዎችን ቃለ ምልልሶችና ሌሎች በርካታ ግብአቶችንም ተጠቅመዋል፡፡ በ10 ምዕራፍ የተከፋፈለውና በ377 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፣ በ150 ብር ዋጋ ለገበያ ቀርቧል፡፡