Administrator

Administrator

     የርሃብ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ከውጭ አገራት የተገዛ 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ስንዴ በጅቡቲ ወደብ በተፈጠረ የመርከቦች መጨናነቅና ወረፋ ሳቢያ በወቅቱ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ለተረጂዎች ሊከፋፈል አለመቻሉን ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት የምትገዛው ስንዴ መጠን እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በጅቡቲ ወደብ ከፍተኛ መጨናነቅ ተፈጥሯል ያለው ዘገባው፣ የእርዳታ እህሉን የጫኑ አስር ያህል መርከቦች ጭነታቸውን ለማራገፍ ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙ ከጅቡቲ ወደብ አስተዳደር ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ገልጧል፡፡
“ሴቭ ዘ ችልድረን” የእርዳታ እህሉን ከመርከቦቹ ለማራገፍ 40 ቀናት ያህል ጊዜ ይፈጃል ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በኢትዮጵያ የ“ሴቭ ዘ ችልድረን” ዳይሬክተር ጆን ግርሃምም፣ የእርዳታ እህል የጫኑ በርካታ መርከቦች በጅቡቲ ወደብ ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙና እህሉን ለማራገፍ በቂ ሁኔታዎች አለመመቻቸታቸውን እንደተናገሩ አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም በጅቡቲ ወደብ መጨናነቅ መኖሩን አምኖ፣ ለማዳበሪያና ለስንዴ ቅድሚያ ተሰጥቶ የማራገፍ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ መግለፁን ዘገባው አመልክቷል፡፡

     የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅማለች በሚል ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ከውድድር እንድትታገድ የተወሰነባት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ኢቫን አቢይ ለገሰ  ውሳኔው የተላለፈብኝ ያለአግባብ ነው በሚል አለማቀፉን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኞች ማህበር መክሰሷን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ለቱርክ የምትሮጠው አትሌቷ እ.ኤ.አ በ2005 እና 2007 በተከናወኑት የአለም ሻምፒዎናዎች በተደረጉላት የሽንት ምርመራዎች የተከለከለ ንጥረ ነገር መገኘቱን ተከትሎ፣ በቱርክ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከውድድር መታገዷን ያስታወሰው ዘገባው፣ በምርመራዎቹ ላይ የቴክኒክ ስህተቶች ተፈጽመዋል በሚል በሞናኮ የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቷን ጠቁሟል፡፡
የአትሌቷ ወኪል ኦንዴር ኦዝባይለን በበኩላቸው፤ በአለማቀፉ የጸረ አበረታች እጽ ተቋም እውቅና በተሰጠው አንድ የምርመራ ላቦራቶሪ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጧቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ፣ ክሱን እንደመሰረቱና በምርመራው ወቅት ዘጠኝ ያህል የቴክኒክ ስህተቶች መፈጸማቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ለተባለ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ስህተቶቹ መፈጸማቸውን ካረጋገጠ፣ የአለማቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በአትሊቷ ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ውድቅ እንደሚደረጉም ወኪሉ ገልጸዋል።
አትሌቷ ባለፈው አመት የተባለውን አበረታች ንጥረ ነገር አለመጠቀሟንና እንዲህ አይነት ህገወጥ ተግባር ለመፈጸም አስባ እንደማታውቅ መናገሯን የጠቆመው ዘገባው፣ ኦሳካ ላይ በተካሄደው የ2007 የአለም ሻምፒዮና በአስር ሺህ ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያ ማግኘቷንም አስታውሷል፡፡

     የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ለልጃቸው ሕክምና
የገንዘብ ርዳታ የወሰኑላቸውን የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ገዳም 10 የአስተዳደር ኮሚቴ አባላትን
ከሥራና ከደሞዝ ያገዱ ቢሆንም ፓትርያርኩ እግዱን ሽረውታል፡፡ ሥራ አስኪያጁ፣ “ለታማሚ ልጃቸው ማሳከሚያ” በሚል ገንዘብ በማሠባሰብ ላይ እንደነበሩ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ ከእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ገዳም ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ብር በገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ እንዲሰጣቸው ቢወስንም፤ የገዳሙ ሒሳብ ሹም ክፍያውን አልፈጽምም በማለታቸው ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከትላንት በስቲያ በሥራ አስኪያጁ  እግድ ተላልፎባቸው ከነበሩት የአስተዳደር ኮሚቴ አባላት አንዱ፣ ሥራ አስኪያጁ በፅ/ቤታቸው ጠርተዋቸው ሁሉንም የአስተዳደር አካላት “ስሜን ለማስጠፋት ሆን ብላችሁ ሳላዛችሁ የሰራችሁት ነው፤” በሚል ቃለ ጉባኤውን በቃለ ጉባኤ ካልሻራችሁ፤” በሚል ሁሉንም ማገዳቸውን እንዳሳወቋቸው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ “ሥራ አስኪያጁ እገዳውን ካስተላለፉብን በኋላ የታገድንበትን ደብዳቤና የገንዘብ ርዳታውን የወሰንበትን ቃለ ጉባኤ ይዘን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመግባት አስረዳናቸው፤” ያሉት የአስተዳደር ኮሚቴው አባላት፤ በሌሎች አድባራትና ገዳማት እንደተደረገው ሁሉ እርዳታውን የሰጡት ለዚሁ ዓላማ ተዋቅሮ በተላከ ኮሚቴ በተጠየቁት መሠረት መሆኑን ለፓትርያርኩ ማሳወቃቸውን
ገልጸዋል፡፡ አቤቱታውን ያዳመጡት ፓትርያርኩ፤ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና የገንዘብ ርዳታ የወሰኑትን አቤቱታ አቅራቢዎች ገሥጸው፣ የሥራ አስኪያጁን እገዳ በማንሳት የገዳሙ የአስተዳደር ኮሚቴ
አባላት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በላኩት ደብዳቤ ማዘዛቸው
ታውቋል፡፡  

      በኢትዮጵያዊቷ የሙዚቃ ቀማሪና የክላሲካል ፒያኖ ተጫዋች እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የህይወት ታሪክና የሙዚቃ ስራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን አዲስ ፊልም እየተሰራ እንደሚገኝ “ኪክስታርተር” የተባለው ድረገጽ ዘገበ፡፡ በእማሆይ ጽጌ ማርያም የሙዚቃ ፋውንዴሽን እየተሰራ የሚገኘው ይህ ፊልም፣ የ93 አመት የዕድሜ ባለፀጋዋን ያላቸውን የሙዚቀኛ የህይወት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን በሙዚቃው ዘርፍ ያላቸውን ተሞክሮና የሙያ ስኬት የሚዳስስ ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በእየሩሳሌም በሚገኝ ገዳም ውስጥ የሚኖሩትን የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩን ታሪክ የሚተርከው የዚህ ፊልም የቅድመ ፕሮዳክሽን ስራ መከናወኑን የገለጸው ድረገጹ፤ የፕሮዳክሽን ስራውም በቅርቡ በእየሩሳሌምና ሙዚቀኛዋ በኖሩባቸው የኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚካሄድ ገልጿል፡፡
የፊልሙ የድህረ ፕሮዳክሽን ስራ በመጪው ሃምሌ ወር ላይ እንደሚጀመር የተነገረ ሲሆን፣ ፊልሙን በተሳካ ሁኔታ ሰርቶ ለእይታ ለማብቃት ፋውንዴሽኑ ለለጋሾችና ለአጋሮች የገንዘብ እርዳታ ጥሪ ማስተላለፉንም ድረገጹ ባወጣው ዘገባ አስረድቷል፡፡

የሰሜን ጐንደር ዞን አሣ አስጋሪዎችና ነጋዴዎች ወደ ሱዳን የደረቀ የአሣ ቋንጣ እየላኩ ሲሆን በዘንድሮ አመት በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
አሣ አስጋሪዎቹና ነጋዴዎቹ ከጣና ሃይቅ የሚያሰግሩት እርጥብ አሣ በአካባቢው ባለው የገበያ ችግር ውሎ ሲያድር ይበላሽባቸው እንደነበር ገልፀው ለሱዳን ገበያ አሣውን አድርቀው በቋንጣ መልክ ማቅረብ መጀመራቸው ከኪሣራ አላቆ ትርፍ በትርፍ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል፡፡
በሰሜን ጐንደር ዞን በጣቁሣ ወረዳ ዶልጊ ከተማ የሚገኙት አስጋሪዎችና ነጋዴዎቹ ምርታቸው በሱዳን ገበያ በእጅጉ ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ወደ 200 የሚሆኑት አስጋሪዎቹና ነጋዴዎቹ በግማሽ አመቱ 4 መቶ ሺህ ኪሎ ግራም የአሣ ቋንጣ አዘጋጅተው በመተማ በኩል ለሱዳን ማቅረባቸውም ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ጠቁሟል፡፡  

Saturday, 19 March 2016 11:19

የዘላለም ጥግ

(ይቅርታ ስለመጠየቅ)
- ይቅርታ መ ጠየቅ ግ ሩም ነ ው፤ ነ ገር ግ ን ም ንም
የሚለውጠው ነገር የለም፡፡ ለውጥ የሚያመጣው
ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ተግባር!
ስቴላ ያንግ
- ደስታ ለሚሰጥህ ማንኛውም ነገር ፈፅሞ ይቅርታ
መጠየቅ የለብህም፡፡
ጄሲ ጄ.
- ተኝተህ እንኳን እኔን ለማሸነፍ አልመህ ከሆነ፣
ተነስተህ ይቅርታ ብትጠይቅ ይሻልሃል፡፡
ሙሃመድ አሊ
- ለማስፈራራት የሚሞክሩ ሰዎችን ይቅርታ
አልጠይቅም፡፡
ኪንኪ ፍሪድማን
- ስህተት ስሰራ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ዶናልድ ትረምፕ
- ለቀልድ ይቅርታ አንጠይቅም፡፡ እኛ ኮማኪዎች
ነን፡፡ እዚህ ያለነው እናንተን ለማሳቅ ነው፡፡ ቀልዱ
የማይገባችሁ ከሆነ አትመልከቱን፡፡
ጆአን ሪቨርስ
- ጌታው፤ ፈፅሞ ይቅርታ አትጠይቅ፤ የደካማነት
ምልክት ነው፡፡
ጆን ዋይኔ
- ይቅር ስትል ነፍስህን ነፃ ታደርጋለህ፤ ይቅርታ
ስትጠይቅ ግን ሁለት ነፍሶችን ነፃ ታወጣለህ፡፡
ዶናልድ ኤል ሂክስ
- ማንኛውም ጥሩ የይቅርታ ጥያቄ ሦስት ክፍሎች
አሉት፡- 1) ለተከሰተው አዝናለሁ 2) ጥፋቱ የእኔ
ነው 3) የተበላሸውን ለማስተካከል ምን ላደርግ
እችላለሁ፡፡
አብዛኛው ሰው ሦስተኛውን ክፍል ይዘነጋዋል፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
- ደካማ ሰው ፈፅሞ ይቅርታ ማድረግ አይችልም፤
ይቅር ባይነት የጠንካራ ሰው ባህርይ ነው፡፡
The Fresh quotes
- ያልተጠየከውን ይቅርታ መቀበል ስትማር
ህይወት ቀላል ይሆናል፡፡
ሮበርት ብራውልት
- ደግመህ የምትፈፅመው ከሆነ ይቅርታ
አትጠይቅ።
ምንጩ ያልታወቀ
- በንግግሬ ለተቀ የሙኝ ሁሉ ልባዊ ይቅርታ
እጠይቃለሁ፡፡
ዊሊያም ቦይኪን

Saturday, 19 March 2016 11:12

የፀሐፍት ጥግ

- ረዥም ልብወለድ ስፅፍ እያንዳንዱ ቃል የራሴ
ነው፡፡ ከአርታኢዬ ሃሳቦች እቀበላለሁ፤ የመጨረሻ
ውሳኔዎቹ ግን የእኔ ናቸው፡፡
ሉዊስ ሳቻር
- ሁልጊዜ መፃፍ የምጀምረው በንፁህ ብጣሽ
ወረቀትና በቆሻሸ አዕምሮ ነው፡፡
ፓትሪክ ዴኒስ
- ፀሃፍት ሁለቴ ነው የሚኖሩት፡፡
ናታሊ ኮልድበርግ
- ለፃፍከው ነገር ጥብቅና መቆም በህይወት
ለመኖርህ ምልክት ነው፡፡
ዊሊያም ዚንሴር፣ ደብሊውዲ
- አንድ ሺህ መፃህፍትን አንብብ፤ ያኔ ቃላቶች እንደ
ወንዝ ይፈሱልሃል፡፡
ሊሳ ሲ
- ፀሃፊ የሰው ልጅ ነፍስ መሃንዲስ ነው፡፡
ጆሴፍ ስታሊን
- አርታኢ፤ ስንዴውን ከገለባ የሚለይና ከዚያም
ገለባውን የሚያትም ሰው ነው፡፡
አድላይ ኢ.ስቲቨንሰን
- አርታኢ ወይም ጋዜጠኛ መሆን ነበር የምፈልገው፤
ነጋዴ የመሆን ፍላጎት አልነበረኝም፤ ነገር ግን
መፅሄቴን በህትመት ለማቆየት ነጋዴ መሆን
እንዳለብኝ ተረዳሁ፡፡
ሪቻርድ ብራንሰን
- ፀሃፊ ወይም ካርቱኒስት በትክክል ምን
እንደሚሰማው ለማወቅ ከፈለግህ ሥራውን
ተመልከት፡፡ ያ በቂ ነው፡፡
ሼል ሲልቨርስቴይን
- ለምንድነው የምፅፈው? ሰዎች ጎበዝ እንዲሉኝ
ወይም ግ ሩም ፀ ሐፊ ስ ለሆንኩ አ ይደለም፡፡
የምፅፈው ብቸኝነቴን ለመግታት ስለምፈልግ
ነው፡፡
ጆናታን ሳፍራን ፎኧር
- ፃፊ ፃፊ እስኪለኝ ብጠብቅ ኖሮ፣ ከእነአካቴው
ምንም ነገር አልፅፍም ነበር፡፡
አኔ ታይለር

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ንጉሥ የሆነው አያ አንበሶ በጉልበት፣ በማን አለብኝና በገዢነት ስሜቱ መዋጡን ትቶ፣ ከሁሉም አራዊት ጋር አብሮ መኖርና ተጋግዞ በጋራ ፍሬ ማፍራትን በመፈለጉ፣ የዱሮው አያ አንበሶ መሆኑን ለመተው ማሰቡን ይፋ ለማድረግ አሻ፡፡
ስለሆነም ዋና መርሆው፡-
“ከሌሎች የዱር እንስሳት ጋር ተባብሮ መኖር ነው!” አለ
ይህንኑ በተግባር ለመተርጐም አያ ጅቦ ጋ ሄደና፤
“አያ ጅቦ የወትሮ ጠብና የገዢና ተገዢ ነገር ያብቃና በጋራ ተሳስበን እንኑር ብዬ አስቤያለሁ”፤
“መልካም ሀሳብ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል” አለ፡፡
አያ አንበሶ ቀጥሎ ወደ አያ ነብሮ ሄደና፤
“አያ ነብሮ፤ የወትሮ ጠብና የገዢና ተገዢ ነገር ያብቃና በጋራ ተሳስበን የምንኖርበት ሥርዓት እንፍጠር” አለው፡፡
አያ ነብሮ፤
“እጅግ ቀና ሃሳብ ነው - ይህን የተቀደሰ ሃሳብ ማን እምቢ ይላል?” አለና መለሰ፡፡
ቀጥሎ ተኩላ ጋ ሄደ፡፡
ተባብሮ አብሮ የመሥራትን ሥርዓት ጉዳይ አነሳበት፡፡
ተኩላ፤
“ይሄማ እሰየው ነው፡፡ ምን ሆኜ እቃወመዋለሁ?” አለ፡፡
የሦስቱም መልስ እጅግ ያስደስተዋል፡፡
“እንግዲያው የተስማማንበትን በተግባር ማየት አለብን” አለ ተኩላ፡፡
ተስማሙና ታላቁ አደን ላይ ተሰማሩ፡፡
ሄደው ሄደው አርፍደው አንዳች የሚያህል ጐሽ ፊታቸው ድቅን አለ፤ ተረባረቡና ጐሹን መሬት ላይ ጣሉት፡፡ ከዚያ ተካፍለው ድርሻ ድርሻቸውን መውሰድ ነበረባቸው፡፡ አሁን ጉድ ፈላ
አንበሳ ዋና ደልዳይና አከፋፋይ ሆነ፡፡ አራቱም የምግብ አጠቃቀም ዘዬአቸው የተለያየ ነው። አብረው መብላት የማይታሰብ ነው፡፡
አያ አንበሶ፤ “መብላት አለብን፤ ተካፍለን እንመገብ” አለ፡፡
ሌሎቹ ልባቸው ባያምንበትም “በጄ” አሉ፡፡ አንበሳ የጐሹን ሥጋ አራት ላይ ከፈለው፡፡
የመጀመሪያውን የቅርጫ መደብ፤
“ይሄ መደብ የእኔ ነው፡፡ የአራዊት ንጉሥ በመሆኔ የማገኘው ድርሻዬ ነው”
ቀጠለና፤ “ሁለተኛወን መደብ የሚያገኘው
“አደኑ ላይ ትልቅ ሚና የተጫወተው ነው ያ ደግሞ እኔ ራሴ ነኝ፡፡”
“ሦስተኛው መደብ፤ እኔ ራሴ በአንበሳነቴ ልክ እንደናንተው ድርሻዬ ነው” አለ፡፡
አያ አንበሶ፤ አራተኛውን ቅርጫ ወደ ወለሉ ገፋና
“ይሄን የቅርጫ መደብ የሚነካ ወዮለት!” አለ፡፡
*   *   *
“የባህርይ ነገር አይለወጥም፡፡ በበጐ ፈቃድ አይሻርም፡፡ ጅብ ማንከሱን፣ አዞ ማልቀሱን፣ እባብ መላሱን በፍላጐታቸው ሊተውት አይቻላቸውም” ይባላል፡፡
የአንበሳውን ድርሻ አንበሳው ብቻውን እንደሚወስድ በሚታወቅበት አካባቢ፣ ዲሞክራሲያዊነት በዋዛ የሚገኝ ነገር አይሆንም፡፡ “ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ ይላል” እንደሚለው ተረት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡
በራስ ወዳድነት ላይ ብቃት - አልባነት ሲጨመር ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ራዕይ ይደበዝዛል። የታቀደው ነገር ሁሉ የአፈፃፀም፣ ሰለባ ይሆናል፡፡ የበለጠ አሰቃቂው ነገር ደግሞ ስህተትን መድገም እንጂ ከስህተት መማር አይኖርም፡፡ ደጋግመን ስለአንድ ችግር የምናወራው ለዚህ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና፣ ኢ - ፍትኃዊነት፣ የደላሎች ስርዓት፣ ኔትዎርክ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የአቋም መሸርሸር፣ የአፈፃፀም ችግር፣ የተቋማት አለመጠንከር፣ ብቁ አመራር አለመኖር ወዘተ … እነዚህን ሐረጋት ስንቴ ደገምናቸው? ወይ ማረም አሊያም በተሸናፊነት ከጨዋታው መውጣታችንን ማመን ነው፡፡ ለዚህም ቢሆን ውስጠ - ማንነታችንን መፈተሸ ይበጃል፡፡ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ አብሮ መብላት ለማይችሉ ሰዎች፤ የትብብር ባህል ምን ያህል ዕሙናዊ ነው? ምን ያህልስ ረዥም መንገድ አብሮ መጓዝ ይቻላል? ራሳችንን በራሳችን እንድንሸረሽር የሚያደርጉ ኃይሎች ይኖሩ ይሆን? ለምንድን ነው ጉዟችን ውሃ ወቀጣ የሚመስለው? የመብራት … የውሃ ችግር ነጋ ጠባ የምናነሳው ለምንድነው? የህዝብ ብዛታችን በተለይ በዋና ከተሞች ጭንቅንቅ ደረጃ መድረሱን እያጤንን ነውን? ጥያቄዎች እየበዙ መልሶች እያነሱ መምጣታቸውን ልብ እንበል፡፡ የታክሲን ሰልፍ ርዝመት መጨመር እያስተዋል ነው? በአንድ አገር ላይ ዋና ለውጥ ሊያስከትል የሚችለው የአስተሳሰብ ለውጥ ወይስ የህንፃዎች ብዛትና የዓይነታቸው መበራከት ነው? የህንፃዎች መበራከት፣ የመንገዶች መሰራት በራሱ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ይሄ ግን የብዙሃኑን ተገልጋይ ህዝብ ኑሮ ፈቀቅ የሚያደርግ መሆን አለበት። ህዝባዊ ኑሮ፣ ዕድገትም ሲታይ የዜጎች ተስፋ ይለመልማል፡፡ የበለጠ የህይወት ዕሳቤ ይመጣል፡፡ የሥነ-ልቡናና የአመለካከት ለውጥ ተጨባጭ ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ መደላደሉም አስተማማኝ ይሆናል፡፡
ግምገማዎች ከእከክልኝ ልከክልህ መውጣት አለባቸው፡፡ ይህ ችግር የሚወገደው ድክመቶች እየበዙና እየተሳሰሩ ሲመጡ አይደለም፡፡ የአንዱን ድክመት አንዱ የሚሸፍንለት ራሱን ማዳን ስላለበት ነው፡፡ የነግ - በኔ ሥጋትም ስላለበት ነው፡፡ አብረው የገቡበትን ሌብነት መደበቅ ግድ ስለሚሆን ነው፡፡ “ግምገማ ድሮ ቀረ” እያሉ በፀፀት የሚናገሩ ሰዎች አልጠፉም፡፡ ሆኖም አንድ እፍኝ ጨው ውቂያኖስን አያሰማ ሆኖባቸዋል፡፡ ከልብ ስለሀገር የማሰብና የመወያየት ነገር የተመናመነው ለዚህ ነው፡፡ በየስብሰባው ላይ ሲፋጠጡ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ የልብ አውቃው፤ “መብላት ያስለመድከው ሲያይህ ያዛጋል” የሚለው ይሄኔ ነው!   

እስካሁን የተደረገው እርዳታ በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል

   ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ በድርቁ ለተጎዱ ዜጎች ተጨማሪ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲያደርጉ ለአለማቀፉ ማህበረሰብና ለለጋሽ ተቋማት ከትናንት በስቲያ ጥሪ ማቅረባቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እስካሁን ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የተደረገው እርዳታ በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው በአብዛኛው ዘግይቶ ነው ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዩኒሴፍን የመሳሰሉ አለማቀፍ ተቋማት በአፋጣኝ ተጨማሪ እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ገልጿል፡፡ በሌሎች የአለማችን አካባቢዎች የተከሰቱት ቀውሶች እንዳሉ ሆነው አለማቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ችላ ማለት የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፣ አገሪቱ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 750 ሺህ ያህል የጎረቤት አገራት ስደተኞችን እንደማስጠለሏ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ድጋፍ ሊያደርግላት ይገባል ብለዋል - ለአሶሼትድ ፕሬስ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ለጋሾች ከ10 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል መባሉንም አስረድቷል፡፡
ከፍተኛውን የእርዳታ ያደረገቺው አገር አሜሪካ መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፤ አሜሪካ ከጥቅምት ወር 2014 አንስቶ ለኢትዮጵያ ከ532 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሰብአዊ ቀውስ ድጋፍ እርዳታ መለገሷንና የኢትዮጵያ መንግስትም ችግሩን ለመቆጣጠር ከ380 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን አክሎ ገልጿል፡፡


- በዩኒቨርሲቲው ጀኔሬተር ፈንድቶ በተነሳ ቃጠሎ ትምህርት ተቋርጧል
- ህገወጥ ተብለው 250 ቤቶች ሲፈርሱ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተከስቷል

    አዳማ (ናዝሬት) ከተማ ላይ፣ የስጋት መንፈስ ሲያንዣብብባት ሰንብቷል፤ የዩኒቨርስቲ ትምህርት ተቋርጦ በርካቶች ወደየትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡ በከተማዋ አንድ ዳርቻ ህገወጥ ናቸው የተባሉ ቤቶች ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻም ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት ደርሷል፡፡
በከተማዋ በተፈጠረው አለመረጋጋት ስጋት እንዳደረባቸው የገለፁልን ነዋሪዎች፤ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በርካታ አመታት ሲያገለግል የነበረ ጀኔሬተር ፈንድቶ የእሳት ቃጠሎ እንደተነሳና በተለያዩ ክፍሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ተደናግጠው አለመረጋጋት በመፈጠሩ ትምህርት እንደተቋረጠ ምንጮች ጠቅሰው፣ አንዳንዶቹ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወደየመጡበት አካባቢ መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ኩሽነን እና ቀበሌ 03 በተሰኙ ቦታዎች፣ ህገወጥ ናቸው የተባሉ የጨረቃ ቤቶችን ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻ፣ ከነዋሪዎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ከ250 በላይ ቤቶች እንደፈረሱ ምንጮች የገለፁ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ከፖሊስና ከአፍራሽ ግብረ ሃይል አባላት ጋር ተጋጭተው ጉዳት የደረሰ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ ክስተቶች ሳቢያ አለመረጋጋትና ስጋት ቢፈጠርም፣ ከዚሁ ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኘው 10 ቀበሌ ተጨማሪ ህገ ወጥ ቤቶችን ለማፍረስ ተወስኗል ብለዋል ምንጮቹ፡፡ በሰባት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የተናገሩ ነዋሪዎች፤ በሰባተኛው ቀን አፍራሽ ግብረ ሃይል መጥቶ ቤቶችን እንደሚያፈርስ ተነግሮናል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ  ሳይሳካ ቀርቷል፡፡