Administrator

Administrator

    በቅርቡ ስልጣን የያዙት የሲሪላንካው ፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃፓካሳ፣ ከትናንት በስቲያ ታላቅ ወንድማቸውን ማሂንዳ ራጃፓካሳን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ራኒል ዊክሬሚሴን ባለፈው ሐሙስ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ ፕሬዚዳንቱ በመዲናዋ ኮሎምቦ በተካሄደ ስነስርዓት፣ የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የ74 አመቱን ታላቅ ወንድማቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሃላ አስፈጽመው ወደ ስልጣን ማምጣታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሲሪላንካ ታሪክ ሁለት ዘመዳሞች ከፍተኛ ስልጣን ሲይዙ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቱ ወንድማቸውን መሾማቸው በአንዳንዶች ቢያስተቻቸውም፣ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ስልጣን እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ሹመቱ እምብዛም እንዳላስደነቃቸው የሚናገሩ መኖራቸውንም አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉት የ70 አመቱ ጎታባያ፣ ታላቅ ወንድማቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት ከ2005 እስከ 2015 በነበሩት አመታት የመከላከያ አማካሪ ሆነው ያገለግሉ እንደነበርና የ185 ሚሊዮን ብር የሙስና ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ወንድማቸውን በሾሙበት እለት ክሱ እንደተሰረዘላቸውም አክሎ ገልጧል፡፡  በቻይና ከአህዮች ቆዳ የሚሰራ መድሃኒት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ፣ በአሁኑ ወቅት በመላው አለም ከሚገኙ 45.8 ሚሊዮን አህዮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለዚሁ አገልግሎት ይታረዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
በቻይና ኢጃኦ ተብሎ የሚጠራውንና ከጉንፋን ጀምሮ የተለያዩ አይነት በሽታዎችን እንደሚያድንና እርጅናን እንደሚከላከል የተነገረለትን መድሃኒት ለማምረት በየአመቱ አምስት ሚሊዮን ያህል አህዮች እንደሚታረዱ የጠቆመው ዘገባው፤ የመድሃኒቱ ምርት ከ2013 እስከ 2016 በነበሩት አመታት ብቻ በ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
በቻይና ከ1992 አንስቶ በነበሩት አመታት የአህዮች ቁጥር በ76 በመቶ መቀነሱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህን ተከትሎም አገሪቱ ከሌሎች የደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካና እስያ አገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው አህዮችን ለመግዛት መገደዷንና በዚህም በአገራቱ ውስጥ ህገ ወጥ የአህዮች ንግድና እርድ ሊስፋፋ መቻሉን አመልክቷል፡፡
በቻይና እያደገ የመጣው የአህዮች ፍላጎት በሌሎች በርካታ አገራት የአህዮች ዝርፊያን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አህዮችን ለእርሻና ማጓጓዣ በመጠቀም ኑሯቸውን የሚገፉ በአለማችን የሚገኙ ከ500 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህልውናን አደጋ ላይ እንደጣለው ገልጧል፡፡
ቦትስዋና፣ ማሊና ሴኔጋልን የመሳሰሉ በርካታ የአለማችን አገራት፣ ህገ ወጥ የአህዮች ንግድና እርድን ለመከላከል ጥብቅ ህጎችንና መመሪያዎችን አውጥተው እየተገበሩ እንደሚገኙ ያመለከተው ዘገባው፤ ባለፉት 12 አመታት ገደማ የአህዮች ቁጥር በኪርጌዚስታን በ53 በመቶ፣ በብራዚል በ28 በመቶ፣ በቦትሱዋና በ37 በመቶ መቀነሱንም ጠቁሟል፡፡

  በሩዋንዳ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ መደበኛ የጽንሰት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ባልተለመደ ሁኔታ በ5 ወራቸው የተወለዱት መንትዮች፤ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በተረገዙ በ24 ሳምንታቸው በቅርቡ ኪጋሊ ውስጥ በሚገኘው ኪንግ ፈይሰል ሆስፒታል የተወለዱት እነዚሁ ሴትና ወንድ መንትዮች፣ ምንም እንኳን ሲወለዱ ክብደታቸው እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ ያለ አንዳች የጤና ችግር እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተወለዱበት ጊዜ ወንዱ 660 ግራም፣ ሴቷ 620 ግራም ክብደት እንደነበራቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ ትክክለኛው ክብደት ግን ከ2600 ግራም እስከ 4500 ግራም እንደሆነና በዚህ አነስተኛ ክብደት የተወለዱት መንትዮቹ በህይወት መቀጠላቸው እንዳስደነቃቸው የሆስፒታሉ ሃኪሞች በግርምት መናገራቸውን አመልክቷል፡፡ መንትዮቹ ያለ ጊዜያቸው ሊወለዱ የቻሉት እናታቸው ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት ስለተፈጠረባት መሆኑን የተናገሩት ሃኪሞቹ፤ ህጻናቱ ያለ ጊዜያቸው መወለዳቸው አስጊ በመሆኑ በልዩ ክፍል ክትትል ሲደረግላቸው እንደቆየና በአሁኑ ወቅትም በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
መንትዮቹ ከተወለዱ ሶስት ወራት ያህል እንደሆናቸውና ወንዱ 2 ኪሎ ግራም ከ90 ግራም፣ ሴቷ አንድ ኪሎ ግራም ከ500 ግራም ክብደት እንዳላቸው፤ እድገታቸውም ጥሩ የሚባል እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

  ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ አዳኝ እጅግ ወርቃማ የሆነች አንዲት ወፍ ያጠምዳል፡፡
ወፊቱም፤
‹‹ከምታርደኝም ከምትገለኝም ሦስት ዋና ዋና ምክሮችን ልስጥህ - አለችው፡፡
‹‹እስቲ የመጀመሪያውን ልስማ›› አላት፡፡
አንደኛው፡- ‹‹የሰውን ንብረት አትመኝ››
ሁለተኛው፡- ‹‹የሰው ንብረት ተወሰደብኝ ብለህ አትቆጭ››
ሦስተኛ፡-  ‹‹ሁሉን ነገር በጊዜው ሥራው››
አለችው፡፡
የወፏን ምክር ያዳመጠው ይህ ወጣት፤ ሕይወቱ ተለወጠ፡፡
ቤት ሰራ፡፡
መኪና ገዛ፡፡
ልጅ ወለደ፡፡
የሚቀጥለው የሕይወቱ ግብ የቱ ጋ  ነው ያለው?
እሱንስ ለማትጋት ምን እናድርግ?
ዛሬም፤
‹‹ስንት እልፍ አበው ናቸው አርግዘው የሞቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ››
***
መቀናናትማ መች ሳይቀናን ኖረ? ይህን ታሪክ ሽረን መኖር ምን ቸገረ? ብለን መጠየቅስ ማን ምን ከለከለን? ማንስ እንዳንግባባ ገራን?
‹‹በምናውቀው ስንሰቃይ የማናውቀውንም ፈርተን፣ በህሊናችንም ማቅማማት ወኔያችንንም ባህላችንም ማቅማማት ወኔያችንንም ተሰልበን
የተራመድንበት ጉልበት የመንቀሳወስ አቅሙ እያደረ ከህሊናችን ይደመሰሳል
ትርጉሙ
‹‹እፍ አንቺ መብራት ጨልሚ
ጥፊ ጨልሚ ጨልሚ
አንቺ የብርሃን ጭላንጭል
    እኔ እፍ ብዬሽ ብትወድሚ
ጭሬ ላለማሽ እችላለሁ ከቶም እንዳሻኝ ነው ስሚ››
ብሏል አቴሎ አንበሳው
ብሏል ጥቁሩ ሙር ግስላ
ማሸነፍ ነበረበትና ስሜን ደቡብ
 ደጋ ቆላ
እስከ ዛሬ አገራችን ያለባትን የአገር እዳ፤
የሚቆጣጠረው ማነው?
  ስንትስ እንደሆነ እናውቃለን ወይ? ብንጠያየቅ ምን ይመስላችኋል? ወቅቱ ዛሬ ነው! ብለን እናስብ፡፡
ዝም ብንል ብናደባ… ዘመን ስንቱን አሸንፎን
የጅልነት እኮ አይደለም፣
  እንድንቻቻል ነው
ገብቶን!
***
አገራችን የወርቃማዋ ወፍ ፍቅርና ምክር ያሻታል፡፡ ሰዓቱ አሁን ነው - መላ መላችንን እንምታ፣ አካባቢያችን እናስላ! የወደፊት መንገዳችን ይሳካ ዘንድ በየትኛውም እግር - መንገድ እንጓዝ፡፡ የቀረችን ጉዞ አጭር ናት፡፡ እንደምንም  እንጓዛት!
‹‹ማሸነፋችን በጭራሽ አጠራጣሪ አይደለም!›› ብለው የሚያምኑ አያሌ ናቸው! ኳስ ሜዳው ግን የዕምነታቸው ከቶም አጋዥ አልነበረም! ለረዥም ጊዜ ሲዳክር የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን፤ ማንቺስተርና ሲቲን ተመልካች እንጂ የራሱን ሜዳ ወዳሽና ቀዳሽ ወይም አጣኝ መሆን አልቻለም::
ቢቀናን ሜዳችን ቢታጠን፣ ለተመልካቾቻችን ውዳሴና ሕዳሴ፣ መልክና ገጽታ መድመቂያ ይሆኑ በሆነ ነበር!
1ኛ/ የሰውን ንብረት ላለመሻት
2ኛ/ የሰው ንብረት የራስህ አልነበረምና ተወሰደብኝ ብለህ ላለመቆጨት
3ኛ/ ሁሉን ነገር በጊዜ መሥራት
እነዚህን ህግጋት ሊፈጽም ተፈጠመ!!
ሰው መሆን ያለበት ይሄንን ነው!  

         - በውጭ ሀገራት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ይኖሩታል
                - ፓርቲው “ብልፅግና” የተሰኘ ልሣን ይኖረዋል


           የኢህአዴግ ም/ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የብልጽግና ፓርቲ መመስረትን በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን የፓርቲው ፕሮግራም “መደመር” እንዲሆን ወስኗል፡፡
ሐሙስ ባካሄደው ስብሰባው የብልጽግና ፓርቲ ሊከተለው ባቀደው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ዝርዝር ውይይት መካሄዱ ታውቋል፡፡
ስምንት የገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የመሠረቱት ፓርቲ በ37 ገፆች 54 አንቀፆችን የያዘ መተዳደሪያ ደንብም አጽድቋል::
አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ውህደት ለማካሄድ የወሰኑት አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴን እንዲሁም የአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪና የሱማሌ ገዥ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ ኢህአዴግን የመሰረተው ህወኃት ከውህደቱ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡
በቀጣይ ውህደቱን የሚፈጽሙት ፓርቲዎች በየራሳቸው የውህደት መሸጋገሪያ ጉባዔ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ይህን የመሸጋገሪያ ጉባኤ በአስቸኳይ ለማከናወን ከወሰኑ ፓርቲዎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ተጠቃሽ ሲሆን ከነገ በስቲያ ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2012 የመሸጋገሪያ ጉባኤውን እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የመሸጋገሪያ ጉባኤያቸውን ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከፓርቲዎቹ የመሸጋገሪያ ጉባኤ በኋላም አዲሱ ውህድ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ውህደቱን ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለውህደቱ ሂደት ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡
የፓርቲ ውህደቱን በተመለከተ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “ውህደቱ የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ተሠሚነት ላልነበራቸው አጋር ድርጅቶች እኩል ድምጽ የሚሰጥ ህብረ ብሔራዊነትን የሚያፀና፣ አካታችነትንና ፍትሃዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሁነኛ አቅጣጫ ነው” ብለዋል፡፡ የፓርቲው ውህደት ሀገራዊ አንድነትን ከህብረ ብሔራዊነት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ሊቀ መንበሩ ጠቁመዋል፡፡
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ኢሕአዴግ መዋሃዱ ለአገሪቱ ብሔራዊ መግባባትና ሰላም እንዲሁም የተጠናከረ ፌዴራሊዝም ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢሕአዴግን ውህደት ከደገፉት መካከል ኢዜማ እና የአረና መሪዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ውህደቱ የፌደራል ሥርዓቱን ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
45 የህወኃት ተወካዮች ባልተገኙበት በተካሄደው የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባም የፓርቲው ፕሮግራምና ህገ ደንብ በጥልቀት ተገምግመው በሙሉ ድምፅ መጽደቃቸው ታውቋል፡፡
የፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም የመደመር እሣቤ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን ዝርዝር መተዳደሪያ ደንቡም በህግ ባለሙያዎችና ምሁራን ሰፊ ጥናት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ ላይ ፓርቲው ሊያሳካቸው ያለማቸው ግቦች የተቀመጡ ሲሆን  አዲስ ራዕይና አዲስ ሀገራዊ ትርክትን በመያዝ የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሠፈነባት፤ የግለሰብና የቡድን መብቶች በሚዛኑ የሚከበሩባት፣ የበለፀገች፣ ህብረ ብሔራዊ ማንነቷ የዳበረና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን የመገንባት አላማ እንዳለው አስቀምጧል፡፡
ፓርቲው ለሁሉም የሀገሪቱ ቋንቋዎች ሙሉ እውቅና እንደሚሰጥ ነገር ግን አሁን የፓርቲው የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ሱማሊኛ፣ ትግርኛና አፋርኛ የተመረጡ ሲሆን ክልሎችና የአካባቢ የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሣቢ በማድረግ ቢያንስ አንድ የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተጨማሪነት መጠቀም እንዳለባቸው በህገ ደንቡ ተደንግጓል፡፡
አዲሱ ፓርቲ “ብልጽግና” የተሰኘ የራሱ ልሣን የሚኖረው ሲሆን ልሣኑም በፓርቲው ሁሉም የስራ ቋንቋዎች ይዘጋጃል ይላል፡፡ የቀድሞ የኢህአዴግ ልሣን “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” እንደነበር ይታወሳል፡፡
የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት አዲስ አበባ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በየክልሎቹ ዋና ከተማዎች እንዲሁም በዞንና በወረዳ የሚኖሩ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በውጭ ሀገራትም እንደሚኖሩት ደንቡ ይደነግጋል፡፡
ማንኛውም ፍላጐቱ ያለው ግለሰብ የፓርቲው አባል መሆን እንደሚችል የሚደነግገው መተዳደሪያ ደንቡ፤ በህብረ ብሔራዊነትና በሀገራዊ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም ያለውና ዋልታ ረገጥ አመለካከትና ተግባሮችን በጽናት የሚታገል የሚለው ከመስፈርቶቹ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካል ሲሆን ፓርቲው በፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንት እንዲመራ እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ ስልጣን በጊዜ ገደብ እንዲገደብ ደንቡ ይደነግጋል፡፡ ዝርዝር መመሪያውም በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል፡፡
አዲሱ “ብልጽግና” ፓርቲን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሔራዊ ጉባኤ አድርጐ በምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግና በቀጣዩ ምርጫ ፓርቲው እንዲወዳደር መታቀዱም ታውቋል፡፡
ከዚህ ውህደት ራስን ያገለለው ህወኃት፤ ከዚህ በኋላ በምን መልኩ እንደሚጓዝ እስካሁን የጠቆመው ነገር የሌለ ሲሆን፤ የኢህአዴግም ሆነ አጋር ድርጅቶች አመራሮችም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡     

   በአለማችን በእያንዳንዱ ቀን 2 ሺህ 200 ያህል ህጻናት በሳምባ ምች ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በአለማችን 800 ሺህ ያህል ከ5 አመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ህጻናት፣ በዚሁ በሽታ ሰበብ መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የሳንባ ምች ሊከላከሉትና ሊያድኑት የሚችል በሽታ ቢሆንም ያን ያህል ትኩረት ስላልተሰጠው በተለይ ህጻናትን በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት እንደሚዳርግ የጠቆመው ድርጅቱ፣ በአመቱ ከሌሎች በሽታዎች በበለጠ መጠን በርካታ ህጻናት በሳንባ ምች ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
በአመቱ ከሳምባ ምች ጋር በተያያዘ ለሞት ከተዳረጉት የአለማችን ህጻናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአምስት የአለማችን አገራት ህጻናት መሆናቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፣ 162 ሺህ ህጻናት የሞቱባት ናይጀሪያ ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንና በአገሪቱ በየቀኑ ከ440 በላይ ህጻናት ከሳምባ ምች ጋር በተያያዘ ለሞት እንደተዳረጉ ገልጧል፡፡
ከሳንባ ምች ጋር በተያያዘ ብዙ ህጻናት ለሞት የተዳረጉባት ሁለተኛዋ አገር ህንድ ስትሆን በአገሪቱ 127 ሺህ ህጻናት በበሽታው ለሞት መዳረጋቸው ተነግሯል፡፡ ፓኪስታን በ58 ሺህ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ40 ሺህ፣ ኢትዮጵያ በ32 ሺህ ከሳምባ ምች ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች ለሞት የተዳረጉ ህጻናት እንደቅደም ተከተላቸው፣ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ድርጅቱ አመልክቷል፡፡

   ኡጋንዳውያን ከሶስት አስርት አመታት በላይ አገሪቱን ያስተዳደሩትን ዮሪ ሙሴቬኒን፣ ዘ ሄግ በሚገኘው አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመክሰስ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውንና እስካሁንም ከ800 በላይ ዜጎች ፊርማቸውን ማስፈራቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
“ፎረም ፎር ዲሞክራቲክ ፓርቲ” የተሰኘው የአገሪቱ ፓርቲ የቀድሞ መሪ በነበሩት ዶክተር ኪዛ ቢሴጅ አስተባባሪነት የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ሙሴቪኒንና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትን ለፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ የወንጀል ድርጊት በአለማቀፉ ፍርድ ቤት አቅርቦ የማስቀጣት ግብ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፤ ግቡን ለማሳካት ቢያንስ የሁለት ሚሊዮን ሰዎች ፊርማ ማሰባሰብ እንደሚጠበቅባቸው  አመልክቷል፡፡
የዘመቻው አስተባባሪዎች፣ ዮሪ ሙሴቪኒ፣ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና በሌሎች ዜጎች ላይ እጅግ የከፋ የሰብዓዊ ወንጀሎችን እንደፈጸሙ የገለጹ ሲሆን ኡጋንዳውያንን በማሳመን ያሰባሰቡትን ፊርማ ለአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በማቅረብ ክስ እንዲመሰረትባቸው ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቪኒን በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማስቀጣት ፊርማ ሲሰባሰብ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ከሁለት አመታት በፊት በተመሳሳይ መልኩ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ተጀምሮ ከስኬት ሳይደርስ መቅረቱንም አስታውሷል፡፡


   የናይጀሪያ ምክር ቤት ግጭትና ሞት የሚያስከትሉ የጥላቻ ንግግሮችንና መልዕክቶችን እንዲሁም ሃሰተኛ መረጃዎችን ያሰራጩ የአገሪቱ ዜጎች በስቅላት እንዲቀጡ ለማድረግ ያቀረበው ረቂቅ ህግ ከመብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው ተዘግቧል፡፡
ረቂቅ ህጉ ባለፈው ማክሰኞ ለአገሪቱ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት መቅረቡን ተከትሎ፣ በርካታ ናይጀሪያውያን ህገ መንግስቱን የሚጋፋ ነው በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ የምክር ቤቱ ምክትል ሊቀ መንበር ህጉ የናይጀሪያውያንን መብት የሚጋፋና ችግር የሚፈጥር ከሆነ እንደማይጸድቅ በመጠቆም፣ ዜጎች የምክር ቤቱን ውሳኔ በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን አመልክቷል፡፡
ዜጎችን በስቅላት እስከ ማስቀጣት የሚደርሰው አዲሱ ህግ፤ ብሔርና ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሚፈጽሙ ዜጎች ከአምስት አመት ባላነሰ እስርና ከ10 ሚሊዮን የአገሪቱ ገንዘብ ባላነሰ እንዲቀጡ የሚደነግግ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ግጭትና ሞት የሚያስከትሉ የጥላቻ ንግግሮችን በተመለከተ የማጣራትና ወንጀሉን የፈጸሙትን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ስራ የሚያከናውን ገለልተኛ ብሔራዊ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠይቅ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ረቂቅ ህጉ ተቃዋሚዎችንና የመብት ተሟጋቾችን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጭምር ማስቆጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ህጉ ተግባራዊ መደረግ የለበትም በሚል በግልጽ ከተቃወሙት ባለስልጣናት መካከልም የአገሪቱ የነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ ጌሚሶላ ሳራኪ እንደሚገኙበትም አስታውቋል፡፡
ባለፈው አመትም ለምክር ቤቱ ተመሳሳይ ረቂቅ ህግ ቀርቦ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ምክር ቤቱ ግን  ውድቅ አድርጎት እንደነበር አክሎ ገልጧል፡፡


     ጂሚ ካርተር ሆስፒታል ገብተዋል

             ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራቶችን ወክለው የተወዳደሩትና በሽንፈት የተሰናበቱት ሂላሪ ክሊንተን፤ በቀጣዩ ምርጫ ከትራምፕ ጋር ዳግም እንዲፎካከሩ ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሚገኝና እሳቸው ግን በፍጹም እንደማይወዳደሩ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ72 አመቷ ሂላሪ ክሊንተን፣ ከቢቢሲ ሬዲዮ 5 ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦችና ፖለቲከኞች በምርጫው እንዲወዳደሩ ከፍተኛ ጫና ቢያደርጉባቸውም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባለፈው ወር ላይ ሄላሪን ወደ ምርጫው እንዲገቡ የሚገፋፋ ንግግር ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለቤታቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንም፣ ሂላሪ በቀጣዩ ምርጫ ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው እንደነበር አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር፣ ባጋጠማቸው የጭንቅላት ህመም ሳቢያ ሰሞኑን ሆስፒታል መግባታቸውን ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡ የ95 አመቱ ካርተር፣ ድንገት ባጋጠማቸው የመውደቅ አደጋ የጭንቅላት መቁሰል እንደተከሰተባቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህን ተከትሎ ከሚሰማቸው ከፍተኛ ህመም እንዲያገግሙ  ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን አመልክቷል፡፡


• ፈረንሳይኛ፤ ከ600 ዓመታት በላይ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል፡፡
• ኤልቪስ ፕሪስሊ 8ኛ ክፍል ሳለ፣ በሙዚቃ ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት “C” ነበር ያገኘው፡፡
• አንድ አማካይ የ4 ዓመት ሕጻን፣ በቀን ከ400 በላይ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡
• ቀንድ አውጣ ለሦስት ዓመታት እንቅልፉን ሊለጥጥ ይችላል፡፡
• ዝሆኖች መዝለል የማይችሉ ብቸኛ እንስሳት ናቸው፡፡
• አንዳንድ ድመቶች ለሰዎች አለርጂክ ናቸው፡፡
• አብርሃም ሊንከን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከመሆኑ በፊት የአገሩ የነፃ ትግል ሻምፒዮና ነበር፡፡ በ300 ገደማ የነፃ ትግል ግጥምዎት ላይ ተሳትፎ በአንዱ ብቻ ነው
የተሸነፈው፡፡
• እ.ኤ.አ በ1930 በሚያዝያ ወር አንደኛው ቀን ላይ ቢቢሲ ‹‹ዜና የለም›› ሲል አስታውቆ ነበር፡፡ በምትኩም የፒያኖ ሙዚቃ ለቋል፡፡
• እንደ ጣት አሻራ ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ሰው የምላስ አሻራ የተለያየ ነው፡፡
• በ16ኛውና በ17ኛው ክ/ዘመን፣ ቱርክ ውስጥ ቡና ሲጠጣ የተያዘ ማንኛውም ሰው ለሞት ይዳረግ ነበር፡፡
• የዛሬ 3ሺ ዓመት ገደማ፣ አብዛኞቹ ግብፃውያን የሚሞቱት በ30 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር፡፡
• ኮካኮላ መጀመሪያ ላይ ሲፈጠር ቀለሙ አረንጓዴ ነበር፡፡
• በዓለም ላይ ከአምስት ሰዎች አንዱ (1.1 ቢሊዮን ሕዝብ) የቀን ገቢው ከ1 ዶላር በታች ነው፡፡
• ሕጻናት ቢያንስ አንድ ወር እስኪሆናቸው ድረስ እንባ አያነቡም፡፡
• ማር የማይበላሽ ብቸኛ ምግብ ነው፡፡ 3 ሺ ዓመት ያስቆጠረ ያለችግር ሊበላ ይችላል:: ማር ይበላል፡፡

Page 9 of 461