Administrator

Administrator

ዱቤ ባለመክፈላቸው ሆስፒታል ውስጥ የታሰሩ 258 ኬንያውያን ተፈቱ

         የኬንያ መንግስት በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አሸባሪው ቡድን አልሻባብ በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ስትል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መውቀሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሃፊ ማቻሪያ ካሙ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በሶማሊያ በአሸባሪ ቡድኖች በተያዙ አካባቢዎች እርዳታ ለመስጠት እንዲችል ቡድኖቹ መንገድ እንዲከፍቱለት ለማድረግ ለሰብዓዊ ድጋፍ ከታሰበው እርዳታ ውስጥ 10 በመቶ ያህሉን ለአሸባሪዎች ይሰጥ ነበር ሲሉ ትችታቸውን መሰንዘራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ተመድ በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አልሻባብ 12 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ በመደለያነት መስጠቱን የሚናገሩት ማቻሪያ፤ ተመድ ለአሸባሪ ቡድኖች በመደለያ መልክ ገንዘብ መክፈሉን እንዲያቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ማቻሪያ ያቀረቡት ውንጀላ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥመዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የህክምና አገልግሎት ክፍያቸውን አልፈጸሙም በሚል በኬንያታ ብሄራዊ ሆስፒታል ታስረው የቆዩ 258 ታማሚዎች ባለፈው ማክሰኞ ከእስር መፈታታቸውን ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡በሆስፒታሉ የተለያዩ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎቶችን በዱቤ ካገኙ ታካሚዎች መካከል 30 በመቶ ያህሉ ክፍያቸውን ባለመፈጸማቸው በሆስፒታሉ ውስጥ እስከ አራት ወራት ለሚደርስ ጊዜ ታስረው እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፣ የታካሚዎቹ ቤተሰቦችና የመብት ተሟጋቾች ድርጊቱን በስፋት መቃወማቸውንና ጫና ማሳደራቸውን ተከትሎ ሊፈቱ መቻላቸውንም አመልክቷል፡፡

 የአለማችን የሙዚቃ ሽያጭ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል


           ሳኡዲ አራማኮ የተባለው የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ኩባንያ በ2018 የፈረንጆች አመት በአለማችን ከፍተኛውን ትርፍ ያገኘ ቀዳሚው የንግድ ኩባንያ መሆኑን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፤ ኩባንያው በአመቱ 111.1 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉን አመልክቷል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ንብረት የሆነው ሳኡዲ አራማኮ በአመቱ በአማካይ 10.3 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማምረቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ አጠቃላይ አመታዊ ገቢውም 355.9 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጧል፡፡
ሞዲ ኢንቬስተርስ ሰርቪስስ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ባወጣው በ2018 ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገቡ የአለማችን ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው አፕል ሲሆን፣ ኩባንያው በአመቱ 59.5 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡በአመቱ 39.9 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያስመዘገበው የደቡብ ኮርያው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ የሶስተኛነት ደረጃን የያዘ ሲሆን፣ ጄፒ ሞርጋን በ32.5 ቢሊዮን ዶላር፣ አልፋቤት በ30.7 ቢሊዮን ዶላር አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአመቱ የአለማችን የሙዚቃ ሽያጭ ባለፉት አስር አመታት እጅግ ከፍተኛው ሆኖ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን የዘገበው ቢቢሲ፣ በአለማቀፍ ደረጃ 19 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሽያጭ መከናወኑን አመልክቷል፡፡በአመቱ በአለማችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በድረ-ገጽ የቀጥታ ሽያጭ፣ በሶፍት ኮፒና በአልበም የተከናወነው ሽያጭ በ9.7 በመቶ ያህል ዕድገት ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ 3.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው የግሬተስት ሾውማን አልበም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን አመልክቷል፡፡

 ከስምንት ወራት በፊት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአገሪቱ በሳምንት 75 ያህል አዳዲስ የኢቦላ ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና ይህም ከዚህ ቀደም ያልታየና ከፍተኛ መሆኑን ገልጧል፡፡
በአገሪቱ በአስከፊነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተነገረለትንና ከስምንት ወራት በፊት የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ያስታወሰው ድርጅቱ፣ የአዳዲስ ታማሚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ይህንን ጥረት እንዳያደናቅፈው ያሰጋል ብሏል፡፡
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰው ይህ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ 676 ያህል የአገሪቱ ዜጎችን ለሞት እንደዳረገ የጠቆመው ድርጅቱ፤ ኢቦላ እ.ኤ.አ ከ2013-16 በነበሩት አመታት በምዕራብ አፍሪካ አገራት በድምሩ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉንም አክሎ ገልጧል፡፡

 በከተማዋ ከ12,500 በላይ መጠጥ ቤቶች ይገኛሉ

          የኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በከተማዋ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ መጠጥ ቤቶችን ቁጥር ከ3 ሺህ እንዳይበልጥ የሚገድብ ህግ ልታወጣ መዘጋጀቷንና ይህ ህግ የሚጸድቅ ከሆነ በከተማዋ ከሚገኙት መጠጥ ቤቶች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት እንደሚዘጉኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የከተማዋ የአልኮል መጠጦች ፈቃድ ቦርድ፣በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የመጠጥ ሽያጭና ተጠቃሚነት ለመቀነስ በማሰብ የመጠጥ ቤቶችን ቁጥር የሚገድበውን ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሰኞ ለከተማዋ ምክር ቤት ማቅረቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ከአምስት አመታት በፊት በከተማዋ ውስጥ ከነበሩት 200 መጠጥ ቤቶች መካከል ፈቃድ ያላቸው ሰባቱ ብቻ እንደነበሩም አስታውሷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 የወጣ አንድ መረጃ በናይሮቢ ከተማ ውስጥ ከ12 ሺህ 500 በላይ መጠጥ ቤቶች እንደሚገኙና አብዛኞቹም ህገወጥ መሆናቸው መረጋገጡን ያስታወሰው ዘገባው፤ በከተማው በየሶስት ወሩ በአማካይ 50 አዳዲስ መጠጥ ቤቶች እንደሚከፈቱ አመልክቷል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት የተመዘገቡት 5 ዝነኞች ብቻ ናቸው
 
           ደቡብ ኮርያ እጅግ ፈጣኑን የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በማስጀመር በአለማችን ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ዘ ቨርጅ ድረገጽ አስነብቧል፡፡
ኤስኬ ቴሌኮም የተባለውና በአገሪቱ ግዙፉ የዘርፉ ኩባንያ ትናንት በይፋ ያስጀመረውን እጅግ ፈጣን የ5ጂ ኔትወርክ ሞባይል ኔትወርክ በጥሩ ሁኔታ መጠቀም የሚችሉት ግን የጋላክሲ ኤስ10 ሞባይል ተጠቃሚዎች ናቸው ብሏል ዘገባው፡፡  
ፎርብስ መጽሄት በበኩሉ፤ ኩባንያው የጀመረው የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ሰዎች አምስት የአገሪቱ ታዋቂ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡የዚህ ፈጣን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ከተመዘገቡት አምስት ሰዎች መካከል ዩን ሱንግ ሂዩክ እና ኪም ዩና የተባሉት ደቡብ ኮርያውያን ዝነኛ ስፖርተኞች እንደሚገኙበትም ዘገባው አመልክቷል፡፡


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ነገር የገባው ሰው አዳማ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡
ታሪኩ ሲጠቀስ ከንጉሳውያን ቤተሰብ አፈንግጦ፤ መጀመሪያ ወደ አርሲ፣ ቆይቶ ወደ ናዝሬት (አዳማ) የመጣ ሰው ነው!
ይሄው ሰው ምንም እንኳ በልጅነቱ ከንጉሳውያኑ አፈንግጦ፣ በአርሲ የአህያ ሌንጬጭ እየሳበ ሸክሙን ወደ ዚታዎው (መኪና) የማድረስ ሥራ ይሰራል፡፡ ለዚህ ልፋቱ ዋጋው አስር የኢትዮጵያ ሳንቲም ብቻ ነው!
ሆኖም፤ አስር ሳንቲሞቹ ተጠራቅመው የዛሬውን ባለ ዚታዎና፣ ባለ ጎተራ ሰው ፈጠሩ! ያገሩ ሀብታም፣ ያገሩ ዲታ እሱ ሆነ! በአዳማ!
ስለዚህ ስለ ዲታ ሰው ስንፅፍ በኩራት ነው፡፡ ምክንያቱም ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ቦታ መድረስ ዋና ጉዳይ ነው፡-
ከአዝራር መሸጥ ተነስተው “ባንኩ ደህና አደረ?” እስከ ማለት የደረሱት ኢንተረፕሩነር ታላቅ አስተማሪያችን የመርካቶ ሰው ናቸው! ብርን ከትራስ አውጥቶ ወደ ባንክ ማህደር ማስገባት ትልቅ የአዕምሮ ስልጣኔ ነው፡፡ የብሔራዊ ከበርቴውን ሚና ዛሬም ከ45 ዓመታት በኋላ እንጠቅሰዋለን፡፡ ባይሰማ፤ አውቆ - የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም ብለን እንተወዋለን!
***
ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያን ነባር የኢኮኖሚ መሰረቶች መርሳት ከቶም በሀገራችን ላይ ትልቅ ጥፋት ማድረስ ብቻ ሳይሆን፤ መሰረታችንን እየናድን ወዴት እንደርሳለን የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ፊታችን ላይ ድቅን እንዲል ማድረጉ አይቀሬ ከመሆን እንዳይዘለል ያደርጋል! ከቶውንም እኔ ተጎድቻለሁና የአገር ኢኮኖሚ ኖረም አልኖረም፤ ፈፅሞ አያገባኝም፤ (ለሚሉ ወገኖች) ብዙ የችግሮች መዳረሻዎች፣ የብዙ ፈተናዎችና እንቅፋቶች መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢረዱ መልካም ነው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ዲታ ሰውዬ ይህን ይላሉ፡- በጥንት በጃንሆይ ዘመን አዳማም ቤተ መንግስት ነበር፡፡ በኋላ ቤተ መንግስቱ ቀረና ወባ ማጥፊያ ሆነ፡፡ ቀጥሎ ወባ ማጥፊያው ቀረና የፖለቲካ ድርጅት ማጥፊያ ሆነ (ኢህአፓ፣ መኢሶን ወዘተ) ደሞ ቀጠለና የዘር ማጥፊያ ሆነ፡፡ ነገ ከናካቴው የትውልድ ማጥፊያ እንደማይሆን ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ጉዞው ከጥፋት ወደ ጥፋት ነው - ሁሌ ከድጡ ወደ ማጡ! አሊያም ዱሮ እንደተፃፈው ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ!
በተደጋጋሚ እንደገለፅነው ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ የተሳቱ አጋጣሚዎች መናኸሪያ ናት፡፡ 1966 ዓ.ም፣ 1969 ዓ.ም፣ 1997 ዓ.ም እንዲሁም ዛሬ፡፡ ዛሬን ሙሉ ለሙሉ አልሳትነውም፤ ለማለት ቢቻልም የዛኑ ያህል የህዝብ ንቃት ካልተጨመረበትና መሪዎቻችን ካልነቁ፣ የመቀልበስ አደጋ አለ፡፡ አልነቃንም ካሉ፤ “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይነቃም”ን እንተርታለን!!

በሰምና ወርቅ ኢንተርቴይንመንት በየወሩ የሚካሄደው “ሰምና ወርቅ” የኪነ ጥበብ ምሽት 16ኛው ዙር የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በቫምዳስ የመዝናኛ ማዕከል ይካሄዳል፡፡ በዕለቱም ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት፣ ዶ/ር አዲል አብደላ፣ ዶ/ር ሙላቱ በላይነህ፣ ኮ/ል አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አርቲስት ሀይሉ ፀጋዬ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ፍሬው፣ መምህር ኤፍሬም ለማ፣ መምህርት ዕፀገነት ከበደ፣ የፊልም መምህር ኤሊያስ ማዳ፣ ገጣሚዎቹ ቴዎድሮስ ነጋሽና አስታውሽኝ ረጋሳ በመሶብ ባህላዊ ባንድ ታጅበው ዝግጅታቸውን እንደሚያቀርቡ አዘጋጁ ጋዜጠኛ ጌታቸው አለሙ አስታውቋል፡፡

 ለመስዋዕት - ሻማ
ለውበት …አበባ
ለጀግኖች ….አንበሳ
ከመምሰል በቀር አዲስ ቃል ብርቅ ሆነ፤
አዲስ ያለው ሁሉ እየተኮነነ፣
ሻማው ከጨለማ ላይቀልጥ ተዳልቦ፣
አበባና ውበት በብር ተቸብችቦ፣
አንበሳው በጅቦች ጉልበቱ ተሰልቦ…
(እናት ፍቅር ሐገር፣ አሌክስ አብረሃም)
ጣጣችን  የማያልቅ፣ ታሪካችን እንባ ያጨቀየው፣ ደማችን ፍሬ አልባ እየሆነ ሺህ ዓመታት መኳተንና መበተን ዕጣችን ቢሆንም፣ ተያይዘን ለመውጣት ግን ውስጣችን ያደገው ሥነ ልቡናዊ ቁስል ሰንሰለት የሆነብን ይመስላል፡፡
ሰሞኑን እንደዋዛ ያገኘሁት አንድ ወዳጄ በቁዘማ ካወራኝ ብጀምር ደስ ይለኛል፡፡ ነገሩ ውስጤ ተቀምጦ እንደ እሣት ይለበልበኛል፡፡ ዐይኖቹ ውስጥ ይንቀለቀሉ የነበሩት የተስፋ ሻማዎች ቀልጠው፣ ዐመድ የታቀፉት ኳሶች ያስነበቡኝ፣ ጦርነትና ግጭት ገዳይ መሆናቸውን ነው፡፡ በሚኖርበት አካባቢ ጓደኞቹ ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አማቾቹ ተለያይተዋል፡፡ አጐቶቹ ጐራ ለይተዋል፡፡ ከዚህ በላይ እርግማን የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ከተነሣባቸው አካባቢዎች በአንዱ የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ አውቀዋለሁ፡፡ አስተሳሰቡም በሰል ያለ ነው። መጻሕፍት የሚያገላብጥ ስለሆነ ሲያወራም የሚደመጥ፣ ሲስቅና ሲያለቅስም እውነት ያለው ነው፡፡ አሁን ሥራውን ከሚሠራበት አካባቢ በዘውግ ግጭት ለቅቆ፣ ወደ ራሱ ዘውግ በመሸሽ ኑሮውን ጀምሯል፡፡ በግጭቱ ከሁለቱም ወገን የሞቱትን፣ ሀብታቸው የተቃጠለውንና የተዘረፈውን እያሰበ በእጅጉ ይቆዝማል፡፡
ዋናው አሳዛኝ ነገር ይህ ነው፡፡ ግጭቱ ደም እስኪያመጣ ለምን ይጠበቃል? የሠላሙ ዘንባባ በደም እስኪጨቀይ መንግሥት ለምን ዝም ይላል? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩን የክልሉ መሪዎች ያውቃሉ፡፡ ግን መፍትሔ አልሰጡትም፤ ሕዝቡን አላወያዩም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ዳኛ ሲያጣ ወደ መገዳደል ገባ፡፡ ችግሩም ጦዘ የሀገርና የሕዝብ ሀብት አፈር ጋጠ፡፡ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተሰነካከሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ የተዋለዱና አብረው የኖሩ ሰዎች ጐራዴ ተማዘዙ፣ ቁርሾ ከመሩ፤ ለትውልድ ቂም አስቀመጡ፡፡
እንግዲህ የዚህ ዓይነት ትዕይንቶችን ስንሰማ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ ይልቅስ የየሳምንቱ ወሬ ስለሆነ ለመድነው፡፡ አሁን መፈናቀል ብርቅ አይሆንብንም፤ መገዳደል ሱስ እየሆነብን ነው። የሚመከር፣ የሚቃና ሰው ጠፍቶ ሁሉም እሳቱ ላይ ቤንዚን ይረጫል፡፡ በዶክተር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ መንግሥትም ጉዞውን የጀመረው እሾሁን ሳይነቅል ስለነበር ዛሬም አንካሳነቱን ቀጥሏል፡፡ በአንድ ዐመት ውስጥ በርካታ አስደናቂና አነቃቂ ተግባራትን ያከናወነው መንግሥት፤ በትይዩው አሳዛኝና አሸማቃቂ አሣፋሪ ድርጊቶችም ያስመዘገበው በከፊል ከዚህ ጋር በተያያዘ ይመስለኛል፡፡
ገና ከጅማሬው በአደባባይ ላይ ቦንብ አፈንድቶ ጠቅላዩን ለመግደል ከመሞከር ጀምሮ፣ ሠራዊት ቤተ መንግሥት ድረስ በመላክ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስከማድረግ ተደረሰ፡፡ ይህም ሲሆን ዶክተሩ ተፈጥሯዊ ልስላሴያቸውን በቁጣ ቅኝት ቀይረው፣ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ አልቻሉም። ይልቁንም በፍቅር፣ በንግግርና በሰለጠነ መንገድ ሕዝቡንና ተቃዋሚዎችን ለሀገር በአንድ ልብ እንዲሠሩ መምከርና ሄድ ሲልም መውቀስ ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ለሃያ ሰባት ዓመታት ሥር ሰድዶ የቆየው ሕወሓት መራሹ መንግሥት ቅሪቶች፣ እግር በእግር እየተከተሉ የለውጡን እሳት ለማጥፋት፣ ውሃ ማፍሰስና ፀብ በተፈጠረባቸው ቦታዎች፣ እሳቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ቀጠሉ። እናም ብዙ ግጭት ስደትና መፈናቀል ዓለምን በሚያስደንቅ ሁኔታ ተከሰተ፡፡ ይህም በራሱ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ቅርጥፍ አድርጐ በላ፡፡ ሰውየው በአንድ በኩል ችግሩን ለማረጋጋት ላይ ታች ሲሉ፣ በሌላ በኩል የተረከቡትን ባዶ ካዝና ሳንቲም ለማጉረስ በሀገራቱ ተንከራተቱ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩትን ሽሙጦችና ዘለፋዎች ላለመስማት ጆሮ ዳባ ብለው ነው፡፡
በአንድ ወገን ለውጡ በእኛ መስዋዕትነት የተገኘ ነው ብለው የሚያምኑና የጫጉላ ቤት ይመስል “እስቲ እዩት የደሙን ሸማ” መዝሙር የሚዘምሩ፣ መጪውን ዘመን ሳይሆን ደጅ ላይ ያለውን ጥሪት ለመቀራመት የጐመዡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሲጮሁባቸው በሌላ በኩል ደግሞ ሃያ ሰባቱን ዐመታት በስደት፣ በግድያ፣ በዘር ማምከን ግፍ ተሠርቶብናል፣ ስለዚህ “ኢትዮጵያዊነት የሚለው መዝሙር ለእኛ ከሙሾ የተለየ ጣዕም አይሰጠንም” ያሉ ሰዎች በቡድን ተደራጅተው፣ ሀገሪቷን ሲንጡት እነሆ እስከ ዛሬ ዘልቀናል፡፡
ከዚህ ባለፈ ደግሞ “የክልል ጥያቄ አለን” የሚሉና አንዳንዴም በሰላማዊ ሠልፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሚያሥፈራ ጩኸትና መፈክር አካባቢያቸውን ሲያስበረግጉ፣ በሌላ በኩል፣ “የማንን ሀብት ማን ይዞ ይገነጠላል?” በሚል ውዝግብ የቦነነው አቧራ ዛሬም የሀገሪቱን የፖለቲካ ጉዞ አፍኖ ህዝቡን እያስነጠሰው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎችን ሁሉ ያነጋገረና መግለጫ እስከመስጠት ያደረሰ ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የለውጡ ፊታውራሪዎች የነበሩት ለማ መገርሣና ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን የተረዳላቸው የለም፡፡
በአንድ በኩል ለዐመታት ሲታገሉለት የነበረውና ለሃላፊነትም ያበቃቸው ሕዝብ ጥያቄ በጦዘ ዜማ ሲዘመርና የቁጣ መብረቅ ሲተፋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ የተቀበሉት ሀገራዊት ሃላፊነትና የህዝብ ጥያቄ እረፍት እየነሳቸው በእጅጉ መራራ በሆነ ምጥ ውስጥ ሊያልፉ ግድ ሆነ፡፡ እኛ ሁላችን ግን በየራሳችን ወገን እንዲቆሙልን ስንጎትታቸው መሀል ለመሆን፣ ሚዛን ለመጠበቅ ያዩት መከራ ቀላል የሚባል፣ ወይም ከምጥ የሚተናነስ አልነበረም።
አቶ ለማም ይሁኑ ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩና የመጨረሻ ግባቸው፣ ኢትዮጵያን ወደ ጥንቱ ክብሯ መመለስ መሆኑን ደጋግመው በአደባባይ በመናገራቸው፣ የሀገሩ ታላቅነት ጉጉት ያለው ሕዝብ በሙሉ ልብ እንደተከተላቸው እናስታውሳለን፡፡ ይሁንና በየጊዜው በሚፈጠሩ አጣብቂኞች ውስጥ በተነሱ ግጭቶች ህዝቡ እምነቱን እያጣና “እየተካድን ነው” ወደሚል መላምት ሄደ፡፡ መላምቱን የሚቀበሉት ሰዎች መነሻ የለገጣፎ ቤቶች መፍረስ፣ የሰዎች መፈናቀል፣ ስለጉዳዩ መግለጫ የሚሰጡት ባለስልጣናት የንግግር ድምፀትና የቃላት ምርጫ ጉዳይ ነበር። ከዚያም በኋላ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባና በሌላ መሰል ጉዳዮች የሰጠው መግለጫ፣ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ የነበረውን አመኔታ ነጠቀው፡፡
የዚህ መግለጫና ጊዜውን ያልጠበቀው ህገ ወጥ ቤቶችን የማፍረስ ስራ፣ “የረቀቀና በስልት የተሞላ የሌሎች ፓርቲዎች እጅ አለበት” የሚሉ ወገኖች ምናልባት፣ ለረጅም ዓመታት ለሥልጣን ሲባትት የነበረው ኦነግ፣ በተፈጠረለት የግርግር አጋጣሚ ኦዴፓ ውስጥ ገብቶ የዚህ ዓይነት የጥፋት ሥራዎችን ያስፈጽም ይሆናል ወደሚል ጥርጣሬ አመሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ የነአቶ ለማ መገርሳ የአሁን አካሄድ አውሎ ንፋስና ወጀቡን በተለያዩ ዘዴዎች አሳልፈው፣ የሀገሪቱን ዋነኛ ሥራ ሊሠሩ ይሆናል፤ በማለት የራሳቸውን ግምት እየሰጡ አለፉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አንዴ የተፈጠረውንና የጀርመንና የሩሲያን ግጭትና እርቅ እንዳስታውስ አደረገኝ። ዘመኑ የሌኒንና የቦልሺክ ዘመን ነበር። የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት (ሩሲያ) በጦርነት በመዳከሟ በርካታ መሬቶቿ በጀርመናውያን ተይዘው ነበር። በተለይ ደግሞ የበርካታ ማዕድናት ምንጭ የነበረችው ዩክሬን በጠላት ተይዛ ስለነበር ሁኔታው ከባድ ነበር፡፡ በሌኒን የሚመራው ፓርቲ ሁለት ነገር መምረጥ ተገደደ፡፡ ዩክሬንን ሰጥቶ ከጀርመን ጋር መደራደርና መታረቅ! አለዚያም ጦርነቱን መቀጠል፡፡ ይሁንና ሁለተኛው ምርጫ የሚያስኬድ አልነበረም። ምክንያቱም ሠራዊቱ ጦርነት ሰልችቶታል፡፡ ብዙ ነገሮች ተዳክመዋል፡፡
ስለዚህ ሌኒን ባለው ሁኔታ መታረቅና ጦርነቱ መቆም አለበት ሲል ጓዶቹ አልዋጥላቸው አለ። ሌኒን ግን በመከራ አሳመናቸው፡፡ ያ ብልሃት የተሞላ ውሳኔ ሀገሪቷን ውርደትም ከጥፋትም ያዳነ ነበር። ዩክሬንና ሌሎቹ መሬቶች ያለ ጦርነት በእጃቸው የገባው ጀርመን በጦርነት ስትዋከብ ስለበር ጥቅሙ ብዙ ነበር ዛሬም የአቶ ለማ መግለጫዎች ከጀርባቸው ምን እንደበርና እንዴት ከቀጣዩ ጥፋት እንዳዳኑን የምናውቀው ምናልባት ዘግይቶ ይሆናል። በተለይ እኛንና የሀገሪቱን ሁለመና ሊውጡ በተነሱ ጽንፈኞች መከበባቸውን በማሰብ ትንሽ የማርያም መንገድ ልንተውላቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ቸኩለን “ካዱን ሸነገሉን” ማለት ከጥርጣሬ ያለፈና፣ ከግጭት በስተቀር የሚያመጣው ፋይዳ ስለሌለ፣ ነገሮችን ሰከን ብሎ ማሰብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ በኮየ ፈጬ ኮንዶሚኒየም የተነሳ ጃዋርና ሠልፈኞቹ “ኮንዶሚኒየም ወይም ሞት” ባሉበት ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተጀመሩ ሠልፎች ቢቀጥሉ ኖሮ፣ አክራሪ ብሔርተኞች ዕድሉን ተጠቅመው፣ ኦሮሚያንና መላ ሀገሪቱን ቢያመሳቅሉስ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ የለማ መገርሳ መግለጫ ከሌኒን የጀርመን እርቅ ጋር አይመሳሰልም።
ይሁንና እኛ መቶ ሚሊየን ዕብዶች ሆነን፣ ለየጐጣችን በቆምንበትና መደማመጥ ባቆምንበት ሁኔታ እነዚህ ሰዎች ለምንጮኸው ስፍራውን ቢተውልን፣ ቀጣዩ ጉዳይ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበናል? አሁን ከብሔር ወጥተን፣ አማራውን ኦሮሞውን ሳይቀር በሠፈር ለመበታተን፣ የሚሰሩ የማህበራዊ ሚዲያ ክፍተቶች እንዳሉስ መገንዘብ የሚገባ አይመስላችሁም፡፡ ከዚህ ባለፈ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር፣ ዋቄ ፈታን፣ ከኦርቶዶክስና ፕሮቴስታንት ጋር ለማጋጨት የተጀመረው ዘመቻስ ግብ የት የሚያደርሰን ይመስላችኋል? ይህ ጊዜ ለሀገራችን በጣም ከባድ የፈተናና የምጥ ጊዜ ነው፡፡ ይሁንና ጽንሱ እንዳይነግፍ በጋራ ከሠራን ጤነኛ ልጅ መውለድ አይቀሬ ነው፡፡
ይህ የአንድ ዓመት የለውጡ ጉዞ ሂደትና አሁን ያለንበት ሁኔታ ነው፡፡ ትኩስ የሆነው የአዲስ አበባ/ፊንፊኔ ጉዳይ ግን እኛን ብቻ ሳይሆን የዶክተር ዐቢይን መንግሥትም ጥያቄ ውስጥ የሚከትት ነው፡፡
አዲስ አበባ ላይ በቅርቡ በተነሱት አለመግባባቶች እንደምናየው ከሆነ፣ የአንድ ብሔር መድልዎ አለ እየተባለ ነው፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛ ቅጥር ላይና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ለተሰማው ቅሬታ መንግሥት ምላሽ መስጠትና ነገሩ አሁንም እየተደረገ ከሆነ ማስቆም ሲገባው “ለምን ትጠይቃለህ?” ብሎ መቆጣት ትክክለኛ ነው ብዬ አላስብም፡፡ “ዶክተር ዐቢይ ተሳስተዋል” ብዬ የምልበት ቦታም ይህ ነው። ጋዜጠኛ እስክንድርን ከገሰፁ፣ ለምን አዲስ አበባ ላይ የሚሠራውን የመድልዎ ሥራስ በይፋ አይኮንኑም? ይህ አካሄድ ፍትህን ወደማዛባት የሚወስድ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ጋዜጠኛ እስክንድር አሁን በመታሠሩ የሚያገኘው ስምና ዝና የለም፡፡ እስክንድር በብዙ ነገሩ ኑሮ የሞላለት፣ ከዚያም ባለፈ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት መከራ በነበረበት እሥር ቤት ዘጠኝ ዓመታትን ያሳለፈና በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ ዶክተር ዐቢይ አደባባይ ላይ ይህን ከሚናገሩ ይልቅ እርሱንና መሠሎቹን ሰብስበው ቢያናግሩ ለሚያስቧት ኢትዮጵያ ጥሩና ቀላል መንገድ ይሆንላቸው ነበር፡፡ አለበለዚያ ንትርኩ እየቀጠለ ወደማንወጣው አደጋ ውስጥ የምንገባ ይመስለኛል፡፡
ከሁላችን ይልቅ ሃላፊነቱን የተሸከመው መንግሥት፣ ነገሮችን ከማባባስና በችግር ላይ ችግር ከመጨመር ይልቅ ችግር ቅነሳ መልመድ አለበት። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ችግሮች ተጧጡፈው ሳለ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችን ማፍረስ ምን የሚሉት ጠማማነት ነው? እውን ኢንጂነር ታከለ ይህን ነገር ሳያውቁት ቀርተው ነው? ካወቁትስ የሚያመጣው መዘዝ፣ በምሬት ላይ ምሬት አያመጣም?
እውነት ለመናገር አሁን በሚታየው ሁኔታ ከቀጠልን ሀገራችን ትፈርሳለች፤ ስትፈርስ ደግሞ በሚዘገንን ሁኔታ እኛም እንፈርሳለን፡፡ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ ወደማይታወቅ እልቂት እንገባለን፡፡ ካልተጠነቀቅንና ከእልህና ጥላቻ ካልወጣን፣ ከዚህ የሚታደገን ደግሞ ምንም የለም፡፡
በተለይ አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በእግዚአብሔር አደባባይ የሚቆሙ ሰዎች ዋና ዋና ዘረኞችና የጥላቻ ወንጌል ሰባኪዎች በሆኑበት ጊዜ ፀብን ማርገብ ቀላል አይሆንም፡፡ ዛሬ በጥላቻ የተሞሉ ጽንፈኛ ወጣቶችን የፈጠርን ሁሉ የምንፈርደው በነርሱ ላይ ሳይሆን በራሳችን ላይ ነው፡፡
ቃላት እየሰነጠቅን ወደ ዝቅጠት ባንወግድ ዝቅ ባንል፣ ለኛም ለሀገራችንም ክብር ነበር። ለማንኛውም በአንድ ዓመቱ የለውጥ ጉዞ በትዕግስት የመራችሁን እኛም ፍቅራችንን ገልጠን የተቀበልናችሁ መሪዎቻችን ማስተዋል ይብዛላችሁ! ከጥቂት ዕብዶች ጋር እንዳታብዱ! ተጠንቀቁ፡፡ አንበሶቻችንን የከበባችሁ ጅቦች በዚሁ አትቀጥሉም፡፡    


               ቃለ ምልልስ


 
                             የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ፤ ከየት ወዴት?

               · አዲስ አበባ የብሔርተኞች የሽኩቻ ማዕከል ሆናለች
              · ያልተገደበ ዲሞክራሲን የመሸከም ባህል የለንም

             ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው የአንድ አመት የለውጥ ጉዞ ግምገማ ላይ ሃሳባቸውን ከሰነዘሩ በርካታ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች መካከል ወጣቱ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ዮናታን ተስፋዬ ይገኝበታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከዮናታን ተስፋዬ ጋር ባለፈው አንድ ዓመት በተካሄደው የለውጥ ጉዞ ዙሪያ፣ በጎውንም ክፋውንም አንስተው ተወያይተዋል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ለአንድ ዓመት በዘለቀው የለውጥ ጉዞ ሂደት ላይ የተለያዩ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን እያንፀባረቀች ነው፡፡ ሃሳብን ማንሸራሸር አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው!!

                 ለብዙዎች ተስፋ ፈንጥቆ የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ምን ገጠመው?
አንደኛ፤ አሁን ነገሮች ሠከን ሲሉ ሁሉም፣ ዞር ብሎ የሚመለከተው ነገር አለ፡፡ ዞር ብለው ሲመለከቱ፣ ኢህአዴጐች ሪፎርም የሚሉት ብዙዎች ለነፃነት በሚደረገው ትግል፣ አንድ ላይ የቆሙበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይብዛም ይነስም የህዝብ ሁሉ ትግል አንድ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በፊት የነበረው አንድነት፣ ከለውጡ በኋላ ሰዎች የቱ ጋ እንደቆሙ እየለየ የመጣ ይመስላል። በተለይ ጠ/ሚኒስትሩ ለ6 ወር ያካሄዱት ፈጣን የሪፎርም ስራ ሁሉንም ያስደሰተ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስልጣን ላይ ሆነው ተጠቃሚ ከነበሩት በስተቀር፡፡ ስለዚህ በፊት የነበረው በትግል ሂደት የነበረ አንድነት ነው፡፡ አላማና ሃሳብ ቢለያይም፣ አፈናን ለማስወገድ ግን አንድነት ተፈጥሮ ነበር። ጠ/ሚኒስትሩ ከመጡ በኋላ ያለው 6 ወር ደግሞ አፍላ የሪፎርም ሂደት በመሆን ብዙዎችን ሲያስደስት ነበር። በሃሳብም በአላማም በፊት የማይስማሙ ሰዎች አንድ ላይ ቆመው እንድናይ አስችሎናል፡፡ ከ6 ወር በኋላ ግን የለውጡ አመራር አንዳንድ ለየት ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል ወይም ደግሞ ቸልተኛ እየሆነ መምጣቱን ያሳየበት አጋጣሚ አለ፡፡
ለምሣሌ የግንቦት 7 አመራሮች ወደ ሀገር ውስጥ ሲመለሱ፣ ደጋፊዎቻቸው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ አስፋልት ላይ እየቀቡ፣ በየመንገዱ እየሠቀሉ እየተደሰቱ ነበር። ይሄ ሲደረግ መንግስት ምንም አላለም፡፡ ነፃነት ሰጥቶ ሁሉንም ሰው በደስታ ተቀበለ፡፡ በኋላ ደግሞ የኦነግ መሪዎች እነ አቶ ዳውድ ኢብሣ ሲመጡ፣ ደጋፊዎቻቸው በተመሳሳይ መልኩ በድርጅታቸው አርማና ሰንደቅ አላማ፣ መንገዶችን መቀባት፣ አደባባዮችን ማስጌጥና ሠንደቃቸውን ለማውለብለብ ሙከራ ሲያደርጉ፣ ግጭት ተፈጠረ። “የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርዳችሁ የእናንተን አትሰቅሉም” የሚለው በአንድ ወገን፣ “አይ እናንተ ጊዜያችሁን ጨርሳችኋል፤ የኛም ባንዲራ አለ” የሚለው በሌላ በኩል ቆሞ፣ ከፍተኛ ግጭት ነው የፈጠረው፡፡ ሰዎች የትና የት እንደቆሙ፣ የመጀመሪያው ማሳያ ይሄ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሁሉም በአንድነት ነበር ለውጡን ሲያጣጥምና ሲደሰትበት የነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ቡራዩ ላይ በመንጋ ፍርድ፣ ብዙዎች አሠቃቂ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሷል። እንግዲህ ከዚህ የምናየው በ“ግንቦት 7” እና በ“ኦነግ” አቀባበል ላይ መንግስት ያሳየው ቸልተኝነት፣ የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የመንግስት ክፍተት፣ ሰዎች ቆም ብለው ነገሮችን እንዲያጠይቁ አድርጓል። በኋላም ከአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት ጋር፣ ከከተማዋ የይገባኛል ጥያቄ ጋር፣ በተለያዩ የክልል ከተሞች ከተከሰቱ ግጭቶችና መንግስት ከሚያሳየው ቸልተኝት፣ በኋላም የሠብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና የፈፀሙ እየተመረጡ ሲታሠሩ … ለምሣሌ እነ አቶ በረከት ስምኦን ሲታሠሩ፣ ጥረት ኮርፖሬትን በማክሠር የሚል ነው፡፡ በአንፃሩ ግን እኩያ የሚሆነውና ከፍተኛ ምዝበራ የተፈፀመበት የኦሮሚያውን ዴንሾ ያከሰሩ እነ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ባሉበት ነው የቀጠሉት። የሠብአዊ መብት ጥሰት በሚል ከትግራይ ሰዎች ሲታሠሩ፣ በ1997 ከምርጫ ጋር በተያያዘ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በሹመት ቀጠሉ፡፡ ይሄ ኢ-ፍትሐዊነትን ፈጠረ። የሰው ስሜትም ይሄን ተከትሎ የበለጠ እየዋለለ ነው የመጣው፡፡ ብዙ ልዩነቶች እየተፈጠሩ ሲመጡ፣ አጨብጭቦ ለተቀበለው የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርም ያለው ስሜት ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደመጣ ነው ያየነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ማዳከሚያ የሆነው የኢህአዴግ የውስጥ ግንኙነት መቀዛቀዝ ነው፡፡ “የህወኃት የበላይነት ነበረ” የሚል ግምገማ በኦዴፓም በአዴፓም በኩል ነበረ። ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን አዴፓ ውስጥ ያሉ ሰዎች በአንፃሩ፣ “የስልጣን ተጋሪ አልሆንም” የሚል ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ።
ለተፈጠረው የለውጥ ሂደት ምስቅልቅል ተጠያቂው ማነው?
ተጠያቂው በአጠቃላይ ያለፍንበት የፖለቲካ ታሪክ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ተጠራጣሪ አድርጐ እዚህ ያደረሰን የፖለቲካ ስርአት ነው የነበረን። ላለፉት 60 አመታት የገነባነው ፖለቲካ፣ ያለመተማመን ባህልና ተጠራጣሪነትን ያጐለበተ ነው፡፡ ስለዚህ ከነበረው አፈና ስንወጣና ያ ደስታ አልፎ መረጋጋት ሲመጣ፣ ያ የጥርጣሬ ባህሪ በድጋሚ ቦታውን የያዘ ይመስለኛል። አሁን የተጠራጣሪነት ባህሪያችን ፊት ለፊት ተገልጦ እያየነው ነው፡፡ ኦዴፓ ስልጣን ላይ ሲሆን አዴፓ ወይም ሌሎች የኦሮሞ የበላይነትን ለማምጣት እየሠራ ነው የሚል ጥርጣሬ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይሄ ጥርጣሬ በተለይ በአማራ ልሂቃን ውስጥ የነገሠ ሆኗል፡፡ ስለዚህ አሁን ለውጡን ለምስቅልቅል ያደረሰው ተጠራጣሪነታችን፣ ያለፍንበት ስርአት የተወልን ጠባሳ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግን መንግስት ራሱ ፍትህን ለማስፈን ወጥነት የጐደለው መሆኑ፣ አሁን ላለው ችግር አድርሶናል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን ያለው የፖለቲካ ሲስተም በራሱ ተፈጥሮ መታረቅ የማይችል መሆኑ ነው፡፡ አሁን ያለነው የሽግግር ወቅት ላይ ነን እንጂ ሠከን ብለን ተቀምጠን ተደራድረን፣ ችግሮችን ለመፍታት አቅም የለውም፡፡ ምክንያቱም ቀጣይ ምርጫ አለ፡፡
ይክፋም ይልማም አሁን በአመራር ያለው ፓርቲ ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን መያዝ ይፈልጋል። በዚህች አንድ አመት ውስጥ አነዚህን ሁሉ ችግሮች ወይም ፕ/ር መረራ እንዳሉት “የሚጋጩ ህልሞች”ን አስታርቆ፣ ምርጫውን አሸንፎ ስልጣን መያዝ የሚቻል አይሆንም። አንዱን አስታርቃለሁ ብሎ ሲያስብ ሌላው ያመልጣል፡፡ ያመለጠውን ለመሰብሰብ ሲሄድ ደግሞ የተሰበሰበው ያመልጣል፤ ይሄ ነው አሁን ያለንበት ሂደት፡፡ ይሄን የፈጠረው የፖለቲካ ፍላጐቶቻችን በጣም የተራራቁ መሆናቸው ነው፡፡ አሁን ላለንበት መዋለል ያበቁን እነዚህ ሁሉ ተጠራቅመው ነው፡፡
“ኦዴፓ የህዝብን እምነት በልቷል”፣ “የኢትዮጵያውያንን ትግል ክዷል” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የአንተ ሀሳብ ምንድን ነው?
እኔ ሶስት አይነት ነገር ነው የሚታየኝ። አንደኛ ዶ/ር ዐቢይ ኦዴፓን ወክለው ነው ጠ/ሚኒስትር የሆኑት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ይናገሯቸው የነበሩ ነገሮች፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ  የሚያሳዩ ነበሩ። ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ ለዘብተኛ ነው። ፍትህን ማስፈን ላይ ለዘብተኛ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ይሄ አካሄድ የፈጠረው የራሱ ክፍተት አለ። የዲሞክራሲ ባህልን ያላዳበረ ማህበረሰብ፣ እንዲህ ያለን ለዘብተኛ አመራር ደካማ እንደሆነ አድርጐ ነው የሚያስበው፡፡ በዚህ አይነት ስነልቦና ውስጥ ያደጉ ፖለቲከኞች፤ ዶ/ር ዐቢይን “መምራት ያልቻሉ ደካማ” አድርገው ያስባሉ። ዶ/ር ዐቢይ በአንፃሩ “አሁን ህግ እናስከብር ብለን ብናስር ተመልሰን ወደነበርንበት እንገባለን” የሚል ስጋት ያላቸው ይመስላል፡፡ በተለያዩ ንግግሮችም ያንጸባረቁት ጉዳይ ነው፡፡ የሃይል እርምጃ ልውሰድ ቢሉ ነገሩ ለእሣቸው ቀላል ነው፡፡ አሁንም የደህንነትና ፖሊስ ሃይሉ በኢህአዴግ ስር ነው ያለው፡፡ ግን እሣቸው ያንን መንገድ ባለመምረጣቸው፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ባህል ባለን ፖለቲካኞች ዘንድ እንደ ደካማ አመራር ነው ያየናቸው፡፡
ሁለተኛ ደግሞ ዶ/ር ዐቢይ በንግግሮቻቸው ስለ ኢትዮጵያ ሲናገሩ፣ ብዙዎቻችን የሠማናቸው በውስጣችን ያለችን ኢትዮጵያ ይዘን ነው እንጂ እሣቸው ስለሚያወሯት ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ሲሉን እኛ የምናስበው በውስጣችን ያለችውን ኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የተለያየ የብሔር ታሪክ ያላቸው፣ በየራሳቸው ነው የሚተረጉሙት፡፡ ብዙ አይነት አተያይ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር ዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያ ሲሉ የውስጣችንን ትርጉም ነው ይዘን የምንሄደው፡፡ ለዚህ ነው አሁን በተግባር ዶ/ር ዐቢይ የሚሏትን ኢትዮጵያ ማየት ስንጀምር ግራ መጋባት ውስጥ የነባነው። ሶስተኛው ግን የስልጣን ሽሚያ ጉዳይ ነው። ዶ/ር ዐቢይ ክስ በበዛባቸው ቁጥር ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። ለምሣሌ የኦሮሞ የበላይነትን ሊያመጡ ነው ሲባል፣ ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። በቅርቡ እንኳ አንድ መጽሔት በአዲስ አበባ የአስተዳደር ጉዳይ ላይ ይዞት በወጣው መረጃ፣ የኦሮሞ ተሿሚዎችን ዝርዝር ብቻ ይዞ ወጥቶ፣ የኦሮሞ የበላይነት ነግሷል የሚያስብል ነገር ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ግን ሙሉ የአስተዳደሩ አመራርና ሠራተኞችን ዝርዝር ብንመለከት እውነታው ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይሄ አካሄድ ደግሞ ግልጽ የስልጣን ሽሚያ እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡ በአዴፓም ይሁን በሌላ ሃይሎች ዶ/ር ዐቢይን ደካማ አድርጐ በመሣል ወይም የኦሮሞ የበላይነት አስከባሪ አድርጎ በመፈረጅና ተጠራጣሪ የሆነውን ስነ ልቦናችንን በመጠቀም፣ ዶ/ር ዐቢይን የማዳከም አካሄድንም እናያለን። ይሄን የሚያደርጉት ሃይሎች ዋነኛ ግባቸው፣ ስልጣኑን ከዶ/ር ዐቢይ በስልት መቀበል ነው። በዚህ አካሄድ ደግሞ በራሱ ላይ ትልቁን ዱላ የሚያቀብለው ኦዴፓ ነው፡፡
በኦዴፓ እና በአዴፓ መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
የስልጣን ፍላጎቶች መጋጨት ነው፡፡ ትልቁ ውጥረት ያለው ክልሎቹ ላይ ነው፡፡ ክልላቸው ላይ የሚፈጠርን የህዝብ ግፊትና ውጥረት ይዘው፣ ወደ ፌደራል ይመጣሉ፡፡ ክልላቸው ላይ ያለውን ውጥረት የሚያረግብላቸው የመሰላቸው የተለያየ የተቃረነ መግለጫ የሚሰጡትም ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦዴፓ ውስጥ ፅንፈኛ ብሔርተኝነትን የሚያራምዱ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ የህዝቡን ተቀባይነት ለማግኘት የሚሄዱበት ርቀት ስሜታዊ የሚያደርጉ አጀንዳዎች በማንሳት የሚለካ ነው። በሌላ በኩል፣ ኦዴፓ የክልሉን መቀመጫ ካላገኘ፣ የፌደራል መንግስት መቀመጫንም አያገኝም፡፡ ስለዚህ ይህን ሃሳብ መግፋት አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም የጠራ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ የለውም፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ድርጅት ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ የሚያወጣቸው መግለጫዎች እነዚህን ውጥረቶች ለማርገብ በማሰብ ነው፡፡ የፅንፈኛ ብሔርተኞች፣ የለዘብተኛውን ሃሳብ አማክሎ መግለጫ ለማውጣት ሲታገል ነው፤ የምናየው፡፡ በተመሳሳይ አዴፓም የዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የገባ ድርጅት ነው፡፡ የኦዴፓ ሎሌ ሆኗል የሚል ትችት ይሰነዘርበታል። ይሄ ከፍተኛ የስነ ልቦና ውጥረት ውስጥ ነው የከተተው፡፡ ይሄ በፅንፈኛ ብሔርተኞች የሚፈጠርን ጫና ለመቋቋምና ውጥረቱን ለማርገብ ነው፤ በተለይ ከማንነት ጋር በተገናኘ ከኦዴፓ ተቃራኒ የሆነ መግለጫ ለመስጠት የሚሞክረው፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ህወሓት የት ነው ያለው?
አሁንማ ህውሓት በሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ግን “አትድረሱብን አንደርስባችሁም” ያለ ይመስላል። በተለይ በኢዴፓ እና በኦዴፓ መካከል በተፈጠረው መቀዛቀዝ ሳቢያ ልሂቃኖቹ በሁለቱም ላይ ዱላ ሲሰነዝሩ ይታያል። ይሄ ለህውሓት ምቾት የሰጠው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አሁን ተፈላጊነትም ሊኖረኝ ይችላል ብሎ ይገምታል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ሶህዴፓ (የሶማሌ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ) በዚህ ጨዋታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሶህዴፓ በፓርላማ ከህውሓት እኩል ማለትም 36 መቀመጫ ነው ያለው፤ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ አመራሩም ወደ ፌደራል ፖለቲካው የበለጠ ለመሳተፍ አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ ህውሓት አሁን ከጎኑ ማድረግ የሚፈልግ ይኖራል፡፡ በቀጣይ ህውሓት ሚናው ምን ይሆናል የሚለውን ደግሞ በተግባር የምናየው ይሆናል፡፡ እስካሁን ግን ገለልተኛ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ፓርቲዎች ወደ ውህደት ሲሄዱ ግን የህውሓትን ተግባራዊ ሚና እናያለን። አሁንም ለወደፊትም ቢሆን ህውሓት ለዶ/ር ዐቢይ በጣም ፈተና የሚሆን ይመስለኛል፡፡
አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካ መካረር “አዴፓ” እና “ኦዴፓ” በቀላሉ ውህድ ፓርቲ መሆን ይችላሉ?
ለራሳቸው ሲሉ አንድ ውህድ ፓርቲ የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ሃገሪቷን ለማስተዳደር የሁለቱ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ያጡታል ብዬ አላስብም። ኦዴፓ የአጋር ፓርቲዎችን ሰብስቦ ውህድ የሚፈጥር ከሆነና አዴፓ ራሱን ካገለለ ጥሩ እንደማይመጣ ያውቁታል፡፡ ውህደቱን ይፈልገዋል፤ አዴፓም በተመሳሳይ፡፡ አዴፓ በዚህ ስብስብ አልካተትም ካለ፣ ህውሓትም ተመሳሳይ አቋም ከወሰደና ሁለቱ ብቻቸውን ከተጣመሩ ለእነሱ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ለመጣመርም በጣም ይከብዳቸዋል፡፡ ኦዴፓ እና አጋሮች ከተጣመሩ አብላጫ ወንበር ይዘው መንግስት ሆነው የመቀጠል እድል ይኖራቸዋል። አዴፓ እና ህውሓት ግን ቢጣመሩም አብላጫ ወንበር መያዝ አይችሉም። ስለዚህ ይህን ስሌት ከግምት አስገብተው፣ ሁለቱ አዴፓ እና ኦዴፓ ከመጣመር (መዋሃድ) ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ያውቃሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ እንዴት ነው ጤናማ ዲሞክራሲ የሚገነባው?
ይሄ ከባድ ነው፡፡ አሁን ጤናማ ዲሞክራሲን የምንገነባበት እድል የለም፡፡ አሁን መንግስት ሊያደርገው የሚችለው፣ የተገራ ‹ሊበራላይዤሽን› መተግበር ነው፡፡ ምናልባት እንደ ቱርክ ያሉ መንግስታትን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። በቱርኮች መንገድ ዲሞክራሲን ማስለመዱ የተሻለ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ዲሞክራሲን ልቅ ለማድረግ ቢሞከር የሚሸከም ባህል የለንም። ዲሞክራሲ ስትል ደካማ አድርጎ የሚያስብህ ሃይል ራሱ ጉልበት እያገኘ ይመጣል፡፡ ጉልበት ሲያመጣ ደግሞ ጠላት ነው የሚሆንብህ፡፡ ጠላት ሆኖ ሲመጣብህ ሳትወድ አምባገነን ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ሊያለማምደን በሚችል መልኩ የተቃኘ ነፃነት ነው የሚያስፈልገን እንጂ በአንድ ጊዜ ልቅ የሚሆንበት ስርአት ብዙ አያስኬድም፡፡ በሌላ በኩል፤ ዲሞክራሲ የግለሰቦችን በነፃነት የመወሰን መብት ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ስርአት ግን ቡድኖች ናቸው እንጂ ግለሰቦች አይወስኑም፡፡ ህገ መንግስቱ በራሱ ለግለሰቦች ዲሞክራሲ ማነቆ ነው። ለዚህ ዲሞክራሲን መሰረት ለማስያዝ ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። ያ ማለት ግን ዲሞክራሲ አይገባንም ማለት አይደለም፡፡ ግን ዲሞክራሲን የምንሸከምበት ሁኔታ በመጀመሪያ መፍጠር አለብን፡፡ ለምሳሌ፡- አንዱን አንዱ ሲያሸንፍ፣ ተሸናፊው መሸነፍን በፀጋ የማመን ባህል ማዳበር አለበት፡፡ ይሄ ገና አልጀመርነውም፡፡
አሁን ያለው ስርአት ይሄን ለመፍጠር ያስችላል?
አዎ በዚህ ስርአት ያንን ማምጣት ይቻላል። አንደኛ በተቻለ መጠን ተቋማትን ገለልተኛ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ፣ ጠቅላይ ፍ/ቤት የመሳሰሉትን ለመቀየር የሚደረገው ጥረት ሲታይ ተስፋ ይሰጣል። ሌሎች አፋኝ የሚባሉ ህጎችን ለማሻሻል የሚደረግ ጥረትም አለ፡፡ እነዚህን የለውጡን ኃይል ጥረቶች ስንመለከት ብዙ ተስፋ ማድረግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ተስፋው የፀና እንዲሆን የአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች መስተካከልና አንድ መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ግን አሁንም ጥሩ ዕድል አለ፡፡
አክራሪ ብሔርተኝነት ሃገሪቱን ወዴት ሊወስዳት  ይችላል?
አሁን ባለው መልኩ ከቀጠለ ሃገሪቷን አደጋ ውስጥ እንደሚከታት ምንም ጥርጥር የለውም። አደጋ ውስጥ ይከታታል ስል ግን ያፈርሳታል ማለቴ አይደለም፤ ወደ ተለያየ ግጭት ነው የሚከታት። ግጭቱ ውስጥ ደግሞ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ግጭቶች በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ከሆነ፣ ማዕከላዊ መንግስቱን የያዙት ኃይሎች ፍፁም አምባገነናዊ ይሆናሉ። ይሄ አካሄድ ሄዶ ሄዶ ወደ ወታደራዊ ስርአት ይወስደናል የሚል ስጋት ነው ያለኝ፡፡ ግን ይሄ ከመሆኑ በፊት ራሱ ኢህአዴግ ወደ አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ከመጣ፣ ይሄን ፅንፈኝነት ሊያረግበው ይችላል፡፡ ፅንፈኝነቱንና የስሜት ፖለቲካውን ወደ መሃል ሰብስቦ ያሰክነዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ የኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ መሆን አንዱ ከፅንፈኝነት የመውጫ መንገድ ይመስለኛል። ይሄ ካልሆነ ግን ሃገሪቱ አትፈርስም፤ ነገር ግን የከፋ አምባገነናዊ ወታደራዊ መንግስት ሊፈጠር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አዲስ አበባ የኔ ነው” … የሚል ስሜት ለምንድን ነው ያየለው?
ይሄ ስሜት በልሂቃኑ ውስጥ ካለው የመገንጠል እሣቤ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ነገ ስንገነጠል ይዘነው ልንገነጠል እንችላለን በሚልና ሲገነጠሉ ይዘውብን ይሄዳሉ ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ ውጥረት ነው። ይሄ እሣቤ ነው ይሄን ሁሉ ጥርጣሬ የሚፈጥረው፡፡ ነገ ለሚገነጠሉት እንዴት አዲስ አበባን እንለቃለን የሚለውም በመድረኩ አለ፡፡ ሌላው ብሔረሰቦች እንጂ የፖለቲካ ሃሳብ የስልጣን መፎካከሪያ ባለመሆኑ፣ አዲስ አበባን የስልጣን ተፎካካሪዎች እንደ መወዳደሪያ አድርገዋታል፡፡ አዲስ አበባ ነፃ ግዛት ነች፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ኢህአዴጐች እንደ ኢህአዴግ ነበር የሚወዳደሩት እንጂ ኦህዴድ እንደ ኦህዴድ፣ ብአዴን እንደ ብአዴን አልነበረም። በኮታ ነበር ስልጣን የሚከፋፈሉት። አሁን ግን ድጋፍ እያሠባሰቡ ያሉት እንደ ኢህአዴግ ሳይሆን በየራሣቸው ቆመው ነው፡፡ ይሄ በራሱ ሌላው ችግሩን አባባሽ ሁኔታ ነው፡፡ አዲስ አበባ የብሔርተኞች የሽኩቻ ማዕከል ነው የሆነችው። ግን አንዳቸውም ለከተማዋ የሚፈይዱላት ነገር የለም፡፡ ጃዋር መሐመድ በአንድ በኩል፣ እስክንድር በሌላ በኩል የቆሙበት ሁኔታ ከፖለቲካ ፍላጐት የሚመነጭ ነው፡፡ እስክንድር የሚያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው፤ “አዲስ አበባ የአዲስ አበባውያን ነች” ይላል፡፡ አዎ ነች፡፡ ጃዋር ባለቤት ነኝ ቢል አንሠማውም፡፡ እዚህ ጋ ግን ያለው ችግር ምንድን ነው? በእስክንድርና በእስክንድር ዙሪያ የተሰባሰቡ ሃይሎች የአማራ ብሔርተኞች መሆናቸው ነው፡፡ እስክንድር ራሱ የአማራ ብሔርተኛ እንደሆነ የሚጽፋቸው ጉዳዮችን በማስረጃ መጥቀስ ይችላል፡፡
ሀገሪቱ ከገባችበት ውጥረት እንዴት ነው የምትወጣው? እስቲ ሃሳብ አዋጣ …
በመነጋገር ነው ከዚያ ችግር መውጣት የሚቻለው፡፡ ውይይት በስፋት ያስፈልገናል፡፡ አሁን ባለው ስሜት ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ቢካሄድም አሁን ባለው ሁኔታ በምርጫ አሸናፊ የሚሆነው ብሔር እንጂ የፖለቲካ ሃሳብ አይሆንም፡፡ ብዙ ቁጥር ያለው ብሔር ያሸንፋል፡፡ አበቃ፡፡ በዚያ ደግሞ ግጭት ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሄን ሁሉ ለማርገብ ብዙ ፖለቲካዊ ውይይቶች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፣ አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሃይል አጋር ምናምን የሚለውን ትቶ፣ በመጀመሪያ ግንባር ሆኖ፣ በብዙ ነገሮች መግባባት አለበት። በመርህ ደረጃ አንድ ላይ መቆም አለባቸው። መደራደር፣ መነጋገር አለባቸው፡፡ በኋላ ወደ ውህደት መምጣት ይችላሉ፤ ከአጋሮቹ ጋር። በዚህ የእነሱ ስምምነት አንድ ውህድ ፓርቲ ከተፈጠረ፣ ትልቅ እፎይታ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እነሱ በዚህ መልኩ ሲደራጁ አብን፣ ኦፌኮ፣ አረና የመሳሰሉት ደግሞ በተመሳሳይ ተነጋግረው ወደ ግንባር፣ ጥምረት፣ ቅንጅት መቀየር መቻል አለባቸው፡፡
አለበለዚያ ኢህአዴግ ብቻውን አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ሲመሠርት፣ አማራ ክልል የሚያሸንፈው አብን ቢሆን ፌደራል መንግስቱ ላይ ተፅዕኖ እንኳ መፍጠር አይችልም፤ ሌላውም እንደዚያው። ፌደራል መንግስቱን የመምራት እድል አይኖረውም፡፡ ነገር ግን የስልጣን ሽኩቻው ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ኦፌኮም ተመሳሳይ ነው … ሶስተኛው ሃይል ደግሞ ግንቦት 7፣ ሠማያዊ፣ ኢዴፓ የመሳሰሉት … ወደ ውህደት ሲመጡ፣ ትልቅ ድጋፍ የሚኖራቸው ከተማ ላይ ነው፡፡


ፓርቲ ማቋቋም እንደ ነውር መታየት የለበትም

        የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪያቸውን ያገኙት በምጣኔ ሀብት ነው፡፡ በምጣኔ ሀብት ባለሙያነትና ተመራማሪነት በበርካታ ሀገር በቀል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ባለፉት 8 አመታትም ኑሮአቸውን በውጭ ሀገር አድርገው፣ የሀገሪቱን የፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከወዳጆቻቸው ጋር የፖለቲካ ድርጅት ለማቋቋም ካቀዱ 10 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ያኔ የተፀነሰው ሃሳብ በኢትዮጵያ ባለፈው 1 አመት ውስጥ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ዛሬ ተወልዷል ይላሉ - ዶ/ር ዐብዱል ቃድር አደም፡፡ አዲሱ ፓርቲያቸው ነፃነትና እኩልነትን በዋናነት ያቀነቅናል፡፡ ስያሜውም “ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ” ነው፡፡ ፓርቲውን ከመሠረቱት አንዱ የሆኑትና በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር አብዱል በፓርቲው አላማ፣ ግብና በፖለቲካ ፕሮግራሙ እንዲሁም በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር እንደሚከተለው ቆይታ አድርገዋል፡፡


              “ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ” እንዴት ተወጠነ?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ብሆንም፣ እኔ በግሌ ከድሮ ጀምሮ የፖለቲካ ፍላጐት ነበረኝ፡፡ ብዙ ጊዜዬንም በሀገራችን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አተኩሬ እንቀሳቀስ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ጊዜ በሀገራችን የነበረው ሁኔታ ለእውነተኛ ፖለቲካ ትግል የሚመች አልነበረም፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ብዬ በሲቪክ ማህበራት በኩል እንቅስቃሴ አደርግ ነበር፡፡ በተለይ አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ በአገልግሎትና ማህበረሰብን በማንቃት ስራዎች ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ያን ማድረጌ የሀገሪቷ አቅጣጫ ወዴት ነው መሄድ ያለበት? ያለንን አቅም ምን ላይ ነው ማዋል ያለብን? የሚለውን ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ስናጠና ቆይተናል፡፡ ውጪ ትምህርት ላይ እያለሁም ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር በዚህ ባለራዕይ ፓርቲ ምስረታ ላይ  ለረጅም ጊዜያት፣ ውይይትና ምክክር ስናደርግ ቆይተናል፡፡
ርዕዮተ አላማችሁ ምንድን ነው? የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጐትስ ያማከለ ነው ትላላችሁ?
በመጀመሪያ ደረጃ አሁን በሀገሪቷ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ለውጥ አለ፡፡ በአስተሳሰብም በተግባርም ለውጥ አለ፡፡ ይሄን እኔም ባልደረቦቼም ገምግመን ተረድተናል፡፡ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት ሠራተኞችም ጥሩ ድጋፍ ነበር ሲያደርጉልን የነበረው እኛ ፓርቲውን ለመመስረት ከተንቀሳቀስንበት ያለፉት 5 ዓመት ውስጥ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችናት ባለሙያዎች ከፍተኛ ድገፍ ነው ያደረጉልን፡፡ በተለያዩ ውይይቶች ላይ ስንሳተፍ ቆይተናል። በቅርብ ጊዜ በተዘጋጀወ የቃል ኪዳን ሰነድ ላይም ፈርመናል፡፡ ገና ሳንመሠረት እንድንፈርም ምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጐልናል። እኛ የተጀመረ የለውጥ በር ውስጥ ገብተን፣ ማስፋት አለብን የሚል አላማ ነው፣ ያለን፡፡ ስንቋቋም ሁለት ዋነኛ ጉዳዮች መነሻ አድርገን ነው፡፡ አንደኛ የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ ሀገራችን በጣም ድሃ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ ናት፡፡ ሁለተኛው ጊዜያዊ ችግሮች ናቸው፤ ሠላምና መረጋጋት ጠፍቷል፡፡
በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል አናውቅም። ስለዚህ ይሄን ሁኔታ ለአጋጣሚ ወይም ለእድል ከመተው እኛ የምንችለውን ያህል ተሳትፈንበት ማስተካከል አለብን ከሚል ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በሀገራችን ብዙ ያልተሞከሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አካሄዶች አሉ እነዚያን አውጥቶ ለህዝባችን አዲስ ነገር ለማበርከት ነው፡፡
ርዕዮተ አለማችንም ከዚህ ተነስቶ የተቀረፀው ነው፡፡ ለዘብተኛ ሊበራል አስተሳሰብ ነው፡፡ ለዘብተኛ ሊበራሊዝምን የመረጥነው ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይጣጣማል በሚል ነው። ጭልጥ ያለ ሊበራሊዝም አይጠቅመንም። ከሶሻል ዲሞክራሲም በጐ የሆነውን እንወስዳለን። መሀል ላይ ያለውን አስተሳሰብ ነው ይዞን የምንራመደው፡፡
ትግላችንም ሙሉ ለሙሉ ርዕዮተ አለምን መሠረት ያደረገ ነው የሚሆነው፡፡ የራሳችንን የኢኮኖሚ ፕሮግራምም ቀርፀናል፡፡ ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተም በዋናነት ባህላችንን መነሻ የሚያደርግ ይሆናል እንጂ ከአውሮፓ ሊበራሊዝም የሚቀዳ አይሆንም፡፡ ለዚህ ነው ለዘብተኛ ሊበራሊዝምን አማራጫችን ያደረግነው፡፡ በነገራችን ላይ ከሊበራሊዝም ብቻ ሳይሆን ከሶሻል ዲሞክራቶች ጠቃሚ ነገር ሲኖር እንወስዳለን፡፡ ርዕዮት አለማችን የማይለወጥ የማይቀየር ነው ብለን አናስቀምጥም፡፡
“ነፃነት እኩልነት” የሚለውን ስያሜ ስትመርጡ ምንን ታሳቢ በማድረግ ነው?
የፓርቲ ስያሜ ለማውጣት ብዙ ተጨንቀንበታል። ተግባራችንን በትክክል ሊገልጽ እንደሚገባ ስንነጋገር ነበር፡፡ አኛ በፖለቲካ ትግላችን አማካዩን ፍለጋ ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ኦሮሞነትን አማራነትን፣ ጉራጌነትን፣ ሲዳማነትን የማያኮስስ፣ ኢትዮጵያዊነትን የማያኮስስ፣ ሁለቱንም በእኩል የሚመለከት የፖለቲካ አካሄድ ነው የመረጥነው።
ስለዚህ ነፃነት ስንል፣ ሁሉን አቀፍ ነፃነት፡- የመደራጀት፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ ሠርቶ የመበልፀግ የመሳሰሉትን ማንሳት እንችላለን። እኩልነት ስንል በህዝቦች፣ በፆታ፣ በብሔር … ማንም ከማንም የማይበልጥ እንዲሆን ነው። ነፃነትና እኩልነት ሁለቱም የወቅቱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁለት አንኳር ጉዳዮች ማሳካት እንደተቀመጠው፤ ሀገሪቱን በሚገባ አስተማማኝ አድርጐ ያሻግራታል የሚል ጽኑ እምነት ነው ያለን። በሀገሪቱ የብዙ ችግሮች መነሻ፣ የእኩልነት ጉዳይ ነው፡፡ ኤርትራን ያሳጣን ስንመራመር ብንውል መጨረሻው የእኩልነት ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን። አሁንም ያለው የብሔር የግዛት ይገባኛል ጥያቄ መነሻው የእኩልነት ጉዳይ ነው፡፡
ፓርቲያችሁ ምን አይነት አባላትን ነው ያሰባሰበው?
ሁሉም መስራች አባላት ከዚህ ቀደም ቀጥተኛ የፓርቲ ፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው አዳዲሶች ናቸው፡፡ በመተዳደሪያ ደንባችን እንደተቀመጠው፤ በምስረታ ጉባኤያችን 50 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፡፡ ከእነዚያ 50 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል 11 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል። ሁሉም እኔን ጨምሮ ለፓርቲ ፖለቲካ አዲስ ነን፤ ግን እንዳልኩት ለረጅም አመታት ዝግጅት በማድረግ ሂደት ውስጥ ሠፋፊ ልምዶችን ለመቅሰም ሞክረናል፡፡ ፓርቲያችን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጥፎና እና ነገሮች ለይቶ ጠቃሚውን እየሰወደ ነው ወደፊት የሚጓዘው። ፓርቲው ተቋማዊ እንዲሆን ነው እየሠራን ያለነው፡፡
የሀገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካ እንደ ፓርቲ እንዴት ነው የምትረዱት?
ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ለውጥ አለ፡፡ ሠፊ የፖለቲካ ምህዳር አለ፡፡ አስቸኳይ ሁኔታዎች አሉ። መንግስት ጠንካራ ድጋፍ እያደረገልን ነው። ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ መደፍረስ ካልሆነ በስተቀር፣ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ አስቸኳይ ሁኔታ፣ አሁን በሀገሪቱ አለ፡፡ እርግጥ ነው የሽግግሩ ጊዜ በጣም ማጠር አለበት፤ በተራዘመ ቁጥር ብዙ ችግር ነው የሚፈጥረው። ግጭቶችና አለመግባባትን በአንድ ጊዜ ማስቆም ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ከመተቸት ይልቅ አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረቡ የተሻለ ይሆናል፡፡ የኛ ፓርቲ በፖለቲካ ትግሉም ከመተቸት ይልቅ አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ ያተኩራል። አሁን ጥሩ የሽግግር ጊዜ ላይ ነን፤ በዚያው ልክ የታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ እነዚህን በአማራጭ ሃሳቦችና ምክሮች ማቃናት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ከመረረ ትችት ወጥተን፣ መንገድና አቅጣጫ ማመላከት አለብን የምንለው፡፡
ለውጡ ወዴት ሊያመራ ይችላል? ተገማች ሁኔታዎች ይኖራሉ?
አሁን ብዙዎቻችን ያለን አስተሳሰብ ጥናት ላይ ያተኮረ አይደለም፡፡ ያለው አካሄድ ብሔር ላይ መሠረት ያደረገው በአንድ ጐራ፣ የዜግነት ፖለቲካ የሚባለው ደግሞ በሌላ ጐራ ነው። ብሔር ላይ የተመሠረተው ሀገሪቱ ወደ አሃዳዊነት እንዳትሄድ ነው የሚታገለው፡፡ በእነዚህ ሁለት አካሄዶች መሃል አማካይ ካለ፣ ጥሩ የለውጥ አካሄድ ይኖረናል፡፡ አሁን እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች እንዲበራከቱ ነው እኛም የምንሠራው፡፡
በፌደራሊዝሙና በብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ጉዳይ አቋማችሁ ምንድን ነው?
እኛ በምንም መመዘኛ የመገንጠል ጥያቄን አንደግፍም፡፡ ፌደራሊዝሙ ግን ከአለም ተሞክሮም አንፃር የተጠና መሆን አለበት። ፌደራሊዝም ጠንካራ ስርአት መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲተገበር ግን አንድን ብሔር ከሌላው ጋር እንዲጠራጠር፣ እንዲጋጭ በሚያደርግ የከፋፍለህ ግዛው አይነት ነው፡፡ ይሄ ለአገዛዝ እንዲመች የተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዴት ይምጣ የሚለው ምክክር ሊደረግበት ይገባል፡፡
የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የሌላውም ህዝብ በቋንቋው መናገር፣ ባህሉን የሚያሳድግበት መንገድ ተፈጥሮ እውነተኛው ፌደራሊዝም መተግበር አለበት ነው አቋማችን። የመንግስት ስልቱ ፕሬዚዳንታዊ ነው፡፡ ጽንፍ የሄደ ብሔርተኝነትንም ሆነ ጽንፍ የተረገጠ የአንድነት ንቅናቄን ወደ አማካይ ማምጣትን ታሣቢ አድርገን ነው የምንንቀሳቀሰው። ሁሉም ቦታ ኖሮት፣ ሳይከፋ፣ ሀገሩን እንዲወድ የሚያደርግን ስርአት ነው እውን ማድረግ ያለብን፡፡ እኛ እንደ ፓርቲ፣ እንድንፈጠር ያደረገን ይሄ ነው፡፡
አንድነቱንም ብዝሃነቱንም በእኩል ደረጃ እንፈልገዋለን፡፡ ይህ እውን እንዲሆንም እንታገላለን። መሀከለኛ ፖለቲካን ማለማመድ አለብን፡፡ ብሔር እና አንድነት የሚሉት፣ ሁለቱም ጋ ጥሩ ነገር አለ፡፡ ከሁለቱም የሚወሰድ አማካይ ነገር ደግሞ የበለጠ ለሀገራችን ፈውስ ይሆናል፡፡
“ፓርቲዎች ተሰባሰቡ” እየባበለ … እናንተ ተጨማሪ ፓርቲ መፍጠራችሁ ትችት አያስነሳም?
በመርህ ደረጃ መሠባሰብ አብሮ መስራት ተገቢ ነው፡፡ ይሄ መሆን ያለበት ግን ራሱን በቻለ ሂደት ነው፡፡ ሲሮጡ የታጠቁት አካሄድ፣ ህዝባችንን ያሰለቸ ነው፡፡ መንግስት “ተሰብሰቡና ልርዳችሁ” ስላለም መሠብሰብ አያስፈልልም። መንግስት ገንዘብ ይሠጠኛል ብሎ መሰብሰብ የትም አያደርስም። ሌሎች ሀገሮችም እኮ በርካታ ፓርቲ ነው፤ ያላቸው። ለምሣሌ አሜሪካ ሁላችንም የምናውቀው ሪፐብሊካኖችንና ዲሞክራቶችን ነው ነገር ግን ከ90 በላይ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ በሌላውም ሀገር እንደዚያው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደገሞ ብዙሃነት አገር ስለሆነች በርካቶች በፈለጉት መንገድ ቢደራጁ የሚደንቅ መሆን የለበትም፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት 27 አመታት ዝም በለው ለቁጥር ማሟላት የውሸት ፓርቲዎች ጭምር ሲቋቋሙ ነበር፡፡ አሁን ግን እውነተኛ ፓርቲዎችን ማቋቋም የሚቻልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ዋናው ፓርቲዎች ይዘውት የሚነሱት ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ በመድረኩ ቀርቦ አሸናፊ የሆነው ነጥሮ ይወጣል። ስለዚህ ሰዎች አሁንም በፈለጉት መንገድ ይደራጁ በኋላ ብዙሃኑ የተቀበሉት ሃሳብ ገዥ ይሆናል። ሌላው በወንፊት እየተንገዋለለ ወደ ኋላ ይቀራል፡፡ ይከስማል፡፡ እኛ ሀገር ገና ብዙ አይነት አደረጃጀቶች መፈጠር አለባቸው፡፡ አሜሪካ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሲቪክ ተቋማት አሉ፡፡ በኛ ሀገር ግን በመቶዎች ናቸው፡፡
አዲስ ፓርቲ ከመመስረት ለምን ሃሳባችሁን ከሚገራ የተቋቋመ ድርጅት ጋር አትጣመሩም ነበር ነው ጥያቄው?
ይሄ ተገቢ ጥያቄ አይደለም፡፡ አዲስ ሃሳብ አለን የምንል ሰዎች ለምን? አንደራጅም፡፡ ለምን ሃሳባችንን ሌሎች ይቀበላሉ አይቀበሉም ማለት አስፈለገ? ፓርቲ ማቋቋም እዚህ ሀገር ላይ እንደ ነውር መታየት የለበትም፡፡ የተቋቋመው ፓርቲ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ? የሚለው ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ያመጣው ሃሳብ ገዥ ከሆነ መደገፍ ይቻላል፡፡ ካልሆነ መተው፡፡ ይሄ ነው ተፈጥሮአዊ ሂደቱ፡፡ እውነተኛ አላማ ያለው፣ በህዝብ የተመረጡ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ሌላው በራሱ ጊዜ ይከስማል፡፡ አብሮ የመስራት ቅንጅት፣ ግንባር፣ ውህደት ግን በሂደት የሚመጣ  ነው እንጂ በአንድ ሰሞን ሆያ ሆዬ የሚሆን አይደለም፡፡ ተሰብሰቡ ስለተባለ መሰብሰብ መርህ አልባነት ነው፡፡
ፓርቲያችሁ ኢትዮጵያውያን እንዴት ነው የሚረዳት? ለሀገሪቱ ያላችሁ አላማስ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ነች፡፡ የነፃነት ምድር ነች፡፡ በሌላ መልኩ ስናይ ደግሞ ደሃ ነን። እኛ ትልቅና ገናና ሀገር እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ እርጥ ነው እስከ ዛሬ በታሪካችን አልተስማማንም፡፡ ሁላችንንም ያግባባ ጀግና የለንም፡፡ ከዚህ አንፃር ጥሩ ታሪኮችን እንቀበል መጥፎ ታሪኮችን እንማርባቸው የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ባለፈ ታሪክ መቆዘም አይገባም የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡
ስለዚህ “እኛ አፄ እገሌ በድሎናል” ከሚል ወጥተን፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ምንድን ነች? ከ25 አመት በኋላ ምን ትሁን የሚለው ላይ እናተኩራለን። የወደፊቱን ተመልካች ፓርቲ ነው የመሠረትነው። ከ25 አመት በኋላ ከአፍሪካ ስንተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ነው የምንገነባው? ስንት ሰው ከድህነት እናወጣለን? የሚለው ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ ያለፈ በደልን እየቆጠሩ መቆዘም የትም አያሻግረንም። ሩዋንዳ በዚህ ጥሩ ምሣሌ ነች፡፡ ሁቱም ቱትሲ የተጨፈጨፉት በቅርቡ ነው ግን ከዚያ ቁዘማ ወጥተው ዛሬ ታሪኩን እንደ መማሪያ እንጂ እንደ መበቀያ አያዩም። የወደፊታቸውን አሻግረው ነው የሚያዩት፡፡ ከብሶትና ቁዘማ ወጥተዋል፡፡ እኛም እንደዚህ ነው የምናስበው፡፡   


Page 13 of 435