Administrator

Administrator

የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ የአማዞኑ ባለቤት ጄፍ ቤዞስ እና የቻይናው አሊባባ ኩባንያ መስራች ጃክ ማ ከሰሞኑ ተጧጡፎ በቀጠለውየአሜሪካና የሰሜን የቃላት ጦርነት ሳቢያ በአንድ ቀን ውስጥ በድምሩ 16 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንዳጡ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የቃላት ጦርነቱ መጧጧፉንና የሰሜን ኮርያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በአሜሪካ ላይ ጥቃትእንደምትሰነዝር ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣የአለማቀፍ ኢንቨስተሮች የግጭት ስጋት ማየሉንና ብዛት ያለው አክሲዮናቸውን መሸጣቸውንየጠቆመው ዘገባው፤በዚህም ሳቢያ ባለፈው ሰኞ በዓለማቀፍ የአክስዮን ገበያዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን አመልክቷል፡፡በዕለቱ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣የኩባንያው የተጣራ ሃብት በ3.2 ቢሊዮን ዶላር እንደቀነሰበት የጠቆመው ዘገባው፤የአሊባባውባለቤት ጃክ ማ፤ 1.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ፤ 1.2 ቢሊዮን ዶላር በተመሳሳይ ሁኔታ መክሰራቸውንም አስረድቷል፡፡

ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ፊሎዘፈርስ ስቶን የተሰኘው የእንግሊዛዊቷ ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ መጽሐፍ የመጀመሪያ ዕትም አንድ ኮፒ፣ ሰሞኑን አሜሪካ
ውስጥ ከመደበኛ ዋጋው በ5 ሺህ እጥፍ መሸጡን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ በ1991 ለመጀመሪያ ጊዜ ለህትመት ከበቁትና በ10.99 ፓውንድ ለገበያ ከቀረቡት 500 ኮፒዎች አንዱ የሆነው ይህ መጽሐፍ፤ ከሰሞኑ ለገበያ ቀርቦ፣በ60,186 ፓውንድ በመሸጥ፣ ዓለማቀፍ ክብረ
ወሰን ማስመዝገቡን ዘገባው አመልክቷል፡፡ከሃሪ ፖተር ሰባት ተከታታይ ክፍሎች የመጀመሪያው የሆነው መጽሐፉ፤ላለፉት ሃያ አመታት ገደማ በአንድ አንግሊዛዊ ግለሰብ እጅውስጥ መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ሄሪቴጅ ኦክሽንስ በተባለና በገበያ ላይ የሌሉ መጽሐፍትን እያደነ በሚያቀርብ ኩባንያ አማካይነት ዳላስ ውስጥ በተካሄደ ጨረታ መሸጡን ጠቁሟል፡፡

አስትራዜንካ  በመላው ዓለም የሚከበረውን ‹‹የዓለም የልብ ቀን›› ምክንያት በማድረግ ነፃ የደም ግፊት ምርመራዎች እና የምክር ድጋፎችን በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች አከናወነ፡፡
‹‹ሄልዚ ሃርት  አፍሪካ” በተሰኘው ፕሮግራሙ   አስትራዜንካ ነፃ የደም ግፊት ምርመራዎች እና የምክር ድጋፎችን  ያከናወነው በአዲስ አበባ ከተማ በሜክሲኮ፤ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ በሾላ ገበያ እና ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኙ አውራ ጎዳናዎች አደባባዮች እንዲሁም በክልሎች በጅማ፣ ሃዋሳ፣ ሆሳዕና ፤መቀሌ፣ ሃረር እና ድሬደዋ ከተሞች  በመሰማራት ነው፡፡ የዓለም ልብ ቀን ከ2012 እኤአ ጀምሮ በመላው ዓለም በተለያዩ ዘመቻዎች ሲከናወን የቆየ ሲሆን ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የሞት አደጋ እስከ 2025 እኤአ በ25 በመቶ ለመቀነስ በተያዘ ዓላማ ዘንደሮ ተከብሯል፡፡ አስትራዜንካ የደም ግፊት ምርመራዎች በማከናወን የልብ ጤናን ለመጠበቅ  መደረግ ስለሚችሉ ቅድመ ጥንቃቄዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል፡፡  
“በደም ግፊት ማንም ሰው መሞት የለበትም” በሚል መርህ የሚንቀሳቀሰው አስትራዜንካ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስተር ጋር በአጋርነት ለመስራት ስምምነት ያደረገው  ከዓመት በፊት ሲሆን፤ በሔልዚ ሃርት አፍሪካ ፕሮግራሙ የደም ግፊት በሽታን ለመዋጋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማገዝ እንዲሁም በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ የአሰራር መዋቅሮችን ከአገሪቱ የጤና አስተዳደር ጋር አጣጥሞ ለማከናወን ድጋፍ በመስጠት ኢትዮጵያውያን የነፃ ደም ግፊት ምርመራዎች እና የምክር አገልግሎቶችን እንዲያገኙ  እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
አስትራዜንካ  ባለፈው 1 ዓመት ለ900 የጤና ባለሙያዎች እና የህክምና ድጋፍ ሰጪዎች ስልጠና የሰጠ ሲሆን በሰባት የአገሪቱ ክልሎች በሚገኙ 12 ሆስፒታሎች እና 36 የጤና ማዕከላት የተቀናጀ የአሰራር መዋቅርን ዘርግቷል፡፡ የህክምና ተቋሙ ባለፈው 1 ዓመት ነፃ የደም ግፊት ምርመራዎችን ከ200ሺ በላይ ለሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ያከናወነ ሲሆን ፤ በሄልዚ ሃርት አፍሪካ ፕሮግራሙ ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ደረጃውን የጠበቀ ህክምና፤ እንክብካቤ እና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ ቆይቷል፡፡






   የላቲን አሜሪካው ጎሬላ መሪና አብዮታዊ ንድፈ - ሀሳብ ቀማሪ፣ ቼ ጉቬራ ዕውነተኛ ስሙ ኤርኔስቶ ጉቬራ ነው፡፡ የ1960ዎቹ አዲስ የግራ - ሥር - ነቀል ኃይሎች ጀግና ነው፡፡ በፊደል ካስትሮ በሚመራው የኩባ አብዮት ዋና ከሚባሉት ሰዎች አንዱ ነው፤ ቼ፡፡ ቼ ጉቬራ የአርጀንቲና ተወላጅ ይሁን እንጂ በየትም ሀገር ሄዶ፣ ትግል ለማገዝ ወደ ኋላ የማይል ዓለም - አቀፋዊ ታጋይ ነው፡፡ እንደ እሱ ዕምነት የላቲን አሜሪካን ድህነት፣ በሽታና ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ኢ-ፍትሃዊነት ለመላቀቅ፣ ብቸኛው መፍትሄ/መድሕን አብዮት ነው ብሎ ያምናል። የካስትሮ ዋንኛ አማካሪ የሆነ ሲሆን ካስትሮ ከኪውባው አምባገነንና ሙሰኛ መሪ ከፉልጄንቺዮ ባቲስታ ጋር ባደረገው የጎሬላ ውጊያ፤ ቼ ጉቬራ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቼ በኋላ የቦሊቪያን ወታደራዊ መንግስት ሲዋጋ ተገደለ፡፡ የተቀበረው ኪዩባ ውስጥ ነው።
ከላይ በተጠቀሰው የካስትሮና የቼ ጉቬራ ትግል ላይ በመመስረት፣ በወቅቱ ይጠቀስ የነበረ ቀልድ የሚመስል አንድ ታሪክ አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ቼ ጉቬራ፣ ካስትሮና አንድ ተራ ወታደር ኪውባ ውስጥ አምባገነኑን ወታደራዊ መሪ ባቲስታን እየተዋጉ ሳሉ አንድ ቃል ይገባባሉ፡፡
ካስትሮ ነው ነገሩን ያመጣው፡፡
“እንግዲህ” አለ ካስትሮ፤ “መቼም ሽምቅ ውጊያ ላይ ነንና ድንገት ጠላት እጅ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ጠላትም የሚሰጠን ቅጣት እኛ እሱ ላይ ባደረስንበት ጥቃት ያህል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም”
ቼ፤ በጉዳዩ መስማማቱን ሲገልፅ፤
“ዕውነት ነው፤ ጠላታችን ብዙ ጉዳት ያደረሰበት ሰው ላይ የመጨረሻውን አሰቃቂ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድበት ከዓለም ታሪክ የተረዳነው ነገር ነው፡፡ አይመስልህም ወዳጄ?” አለው፤ ወደ ወታደሩ ዘወር ብሎ።
ወታደሩም፤
“የእኔም ዕምነት እንደዚያው ነው!” አለ፡፡
ቀጠለ ካስትሮ፤
“እንግዲያው ጓዶች እንዳንከዳዳ! ጠላት ላይ የጥቃት እርምጃ ስንወስድ አናወላውል፡፡ የማያዳግም ጥቃት እናድርስ!”
ቼ፤ “በትክክል! ወሳኝ ጥቃት ነው መሰንዘር ያለብን!” አለ፡፡
ወታደሩም፤
“በበኩሌ የተማርኩትን የጎሬላ ጥበብ ሁሉ ልጠቀም ቃል እገባለሁ!”
ካስትሮ፤
“እኔም ቃል እገባለሁ!”
ቼም፤
“እኔ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፤ ቃሌ ቃል ነው!” አለ፡፡ ሲዋጉ ከርመው የተባለው አልቀረም፣ ሶስቱም ጠላት እጅ ወደቁ! ይባላል! ቅጣታቸውም እንደየበደላቸው መጠን በቁማቸው መሬት መቀበር ሆነ፡፡
ያ ተራ ወታደር እስከ አንገቱ ድረስ መሬት ተቀብሯል፡፡ ካስትሮ ግን እጉልበቱ ድረስ ብቻ ነው መሬት የገባው፡፡
ይሄኔ ያ ወታደር፤
“ካስትሮ፤ የገባነው ቃል እንዲህ ነበር? ጠላት ላይ ምንም ጉዳት አላደረስክም ማለት’ኮ ነው አንተ?” አለው፡፡
ካስትሮም፤
“አይ፤ ቼ ጉቬራ ጭንቅላት ላይ አቁመውኝ እኮ ነው!” አለ፡፡ (I am just standing on the head of Che Guevara) ቼ ሙሉ ለሙሉ ከመሬት በታች ተቀብሯል ማለት ነው!
*            *            *
አንድም በቼ ጭንቅላት ነው እዚህ የደረስከው ማለት ነው፤ ነገሩ፡፡ ቼ ያልተገነዘበው፤ “የሰው ቤት የሰው ነው” የሚለውን አማርኛ ተረት ነው! ያም ሆኖ መኖሪያው ያልሆነ ኩባ፣ መቀበሪያው ሆነ! የእንቅስቃሴዎች ሁሉ መዘውር ዕምነትን መካድ፣ ማተብን መበጠስ፣ አድር - ባይነት፣ ፅናት፣ ቆራጥነት፣ አይበገሬነት ነበር፤ ነውም፡፡
ጠንካራ ሰው ጥንካሬን ለዘለዓለም ማቆየት አይችልም፡፡ ጉልበትን ወደ መብት፣ ታዛዥነትን ወደ ሥራ ግዴታ ካልለወጠ በስተቀር፤ ይላሉ ፀሐፍት፡፡
ቼ ማርክሲስት ነው፡፡ የ60ዎቹ ዘመን ኢትዮጵያውያንም ማርክሲስቶች ነበሩ፡፡ እስከ ዛሬም አባዜው ያልለቀቃቸው፤ ልክ ይሁኑም አይሁኑም፤ አሉ፡፡
“ማርክሲዝምን ማግኘት፤ ጫካ ውስጥ ካርታ እንደ ማግኘት ነው” የሚል ሰው ነበር፡፡ የዚያን ዘመኑ ማርክሲዝም የፖለቲከኝነት መገለጫ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም እንደዚሁ የፖለቲካው መገለጫ የሶሻሊስቱ አካሄድ ሲሆን መጠንጠኛው ይኼው ማርክሲዝም ነበር፡፡ ዛሬ በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት ወገኖች የማርክሲዝም አቀንቃኞች ነበሩ፡፡ እስካሁን ያልለቀቃቸው አሉ ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡
ቶማስ ፔይን፤ “አንድ ትክክለኛ ሰው፤ ዘውድ ካጠለቀ አጭበርባሪ ይልቅ ብዙ ከበሬታ ይገባዋል” ይለናል። ዘውድ ያጠለቀ እንግዲህ ባለስልጣን ሁሉ ማለት ነው፡፡ ሹመኛ ማለት ነው፡፡ ሊቀመንበር ማለት ነው፡፡ የማህበርም፣ የፓርቲም መሪ ነው፡፡ የቢሮ ኃላፊ ነው፡፡
ካስትሮ እንዲህ ይለናል፡-
“የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ፣ ለችግርቿም የሚሰጠው መፍትሔ በጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች ትከሻ ላይ አሊያም ከደርዘን የማይበልጡ፣ አየር-ማረጋጊያ በተገጠመለት ነፋሻ ቢሮ የተቀመጡ፣ ወሳኝ ሰዎች፤ ቀዝቃዛ የትርፍ ሂሳብ ስሌት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ሊቀጥል አይችለም፡፡ … ችግራችን የሚፈታው አባቶቻችን ባወረሱን ኃይል፣ ታማኝነት/ለአገር መታመን፤ ጀግንነት… ራሳችንን አሳልፈን ከሰጠን ነው፡፡ “የኢንተርፕራይዞች ፍጹም ነፃነት”፣ “ካፒታላቸውን ለሚያፈሱ ኢንቨሰትሮች ዋስትና መስጠት”፣ “የአቅርቦትና ፍላጎት ሕግ” እያልን ያማሩ ቃላት በመደርደር አይደለም ችግራችን የሚፈታው! በሙስና የተዘፈቁ ተቋሞቻችንን ስናፀዳና በዘርፉ የተጨማለቁ ባለሥልጣናትን ስናስወግድ ነው! ትክክለኛ ያልሆኑ ህግጋትን ተቀብሎ የሚኖር፣ አገርን የሚጨፈልቅና የተወለደባትን አገር የሚበድል ሰው እያየ ዝም የሚል ግለሰብ፤ እሱ የተከበረ ሰው አይደለም፡፡… በዓለም ላይ የተወሰነ ብርሃን ያለውን ያህል፣ የተወሰነ የክብር ደረጃ መኖር አለበት፡፡ ክብረ-ቢስ የሆኑ ሰዎች በኖሩ ቁጥር፤ የብዙ ሰዎችን ክብር ይዘው የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችም ይኖራሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች፤ የህዝቡን ነፃነት የሚሰርቁ ሰዎች ለማስወገድ በኃይል የሚነሱቱ ናቸው፡፡ ያም ማለት ክብርን ራሱን የሚዘርፉ ሰዎችን የሚቃወሙ ማለት ነው! በእንደዚህ ያሉ ሰዎች ልብ ውስጥ  በሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች አሉ፡፡ የሰው ልጅ ክብር ታፍሮ ይኖራል!...” የሀገራችንን ነገር ከኩባ ጋር አነፃፅሮ ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
 ሼክስፒር በሎሬት ፀጋዬ ብዕር ውስጥ ይሄን ይለናል፡-
“ገንዘቤን የሰረቀ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር
 ዋጋ አለው ግን ከንቱም ነው፣ የእኔም የእሱም የእሷም ነበር፤
ግና ስሜን የሰረቀኝ
የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ”
ጆን ሚልተን፤ “የፖለቲካ ሥልጣን ያለው ለንጉሦች ዘውድ መጫንም፣ ዘውድ መንጠቅም፣ ጨቋኞችን የመጣል ግዴታም ባለው ህዝብ እጅ ውስጥ ነው!” ይለናል፡፡ ችግሩ የሚከሰተው የተባለው ህዝብ ይሄንን ያላወቀ እንደሆነ ነው፡፡
እዚህ ላይ የካስትሮን “ታሪክ ነፃ ያደርገኛል” የሚለው የፍርድ ቤት መከላከያ ንግግር መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ “ህልመኛ ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ የማርቲን ንግግር እጠቅሰላቸዋለሁ፡፡ “ዕውነተኛ ሰው ጥቅም ያለበትን ቦታ አይደለም የሚሻው፡፡ ይልቁንም ተግባር ያለበትን ቦታ እንጂ፡፡ ዕውነተኛ የተግባር ሰው ይሄ ነው- የዛሬ ህልሙ የነገ ህግ የሚሆን! ምክንያቱም፤ የታሪክን ሂደት ዞር ብሎ ለተመለከተና እንደ እሳት የሚንበለቦሉና በዘመናት ሰታቴ ድስት ውስጥ እየተፍለቀለቁ የደሙ ህዝቦችን ላየ፣ ነገ ሥራን በሚያከብሩ ሰዎች እጅ ውስጥ መሆኑን ይገነዘባል” ስለዚህ ዕውነተኛ ሰዎችን በዙሪያችን መያዝ ተገቢ ነው፡፡ የሰው ኃይል፣ የተደራጀ የሰው ኃይል፣ ራሱን የሚያውቅ የሰው ኃይል ማፍራት ዋና ነገር ነው፡፡ “ከእሾህ አጥር፣ የሰው አጥር ይጠነክራል” የሚለው የትግርኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡

    ላለፉት 38 አመታት በጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ስትመራ የቆየቺውና ዜጎቿ የነዳጅ ሃብቷ ተጠቃሚ ሳይሆኑ የከፋ ኑሮን እንደሚገፉ የሚነገርላት አንጎላ፤ የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትሯን ጃኦ ሎሬንኮን በሳምንቱ መጀመሪያ ቃለ መሃላ አስፈጽማ በፕሬዝዳንትነት ሾማለች፡፡አንጎላ ከአራት አስርት ዓመታት ገደማ በኋላ መሪዋን ብትቀይርም ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንደማይጠበቅ የዘገበው ቢቢሲ፤ ለዚህ በምክንያትነት
ያስቀመጠውም፣አዲሱ ፕሬዚዳንት በእነዚህ አመታት በብቸኝነት ስልጣኑን ተቆናጥጦ የዘለቀው የገዢው ፓርቲ ኤምፒኤልኤ ቁልፍ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ፣ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ቢያስረክቡም፣ በፓርቲው ውስጥ ያላቸውን የአገሪቱን የፖሊስ አዛዥና የጦር ሃይል አዛዥ የመሾም ስልጣን ይዘው እንደሚቆዩ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ሰውዬው ከወንበራቸው ቢነሱም አሁንም ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ እድሉን እንደሚሰጣቸው አመልክቷል፡፡በነዳጅ ሃብት በበለጸገቺው አንጎላ፣ የሃብት ክፍፍል ልዩነቱ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ መዝለቁን የጠቆመው ዘገባው፤ አዲሱ ፕሬዚዳንት በነባሩ የፖለቲካ ስርዓት ላይ ለውጥ ለማምጣት ቢያቅዱም ብዙ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡ አንጎላ ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት ከ1975 አንስቶ በገዢ ፓርቲነት የዘለቀው የኤምፒኤልኤ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ለረጅም አመታት ስልጣንን የሙጥኝ ብለው የዘለቁት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ከፍተኛ ነቀፋ ሲሰነዘርባቸው እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፤
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆነቺው ልጃቸው ኤልሳቤጥ ዶስ ሳንቶስም አባቷን መከታ በማድረግ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥራዋለች በሚል እንደምትተች አስረድቷል፡፡

   በህፃናት አመጋገብ ዙሪያ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያዘጋጃቸውን ማኑዋሎች ሰሞኑን ለባለድርሻ አካላት ይፋ ያደረገው  ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፤ በስልጠና ማኑዋሎቹ አማካኝነት ሰፊ ለውጥ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። በተለይ ህፃናት ተወልደው 1 ሺህ ቀናት ድረስ ባሉት ጊዜያት ያለው አመጋገባቸው ለእድገታቸው ወሳኝ መሆኑን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል ሁለት ወረዳዎች በወላጆችና ህፃናት ላይ ውጤታማነቱን ማረጋገጥ እንደተቻለ የጠቆመው ወርልድ ቪዥን፤ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካዮችና በህፃናት ላይ ለሚሰሩ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ከትላንት በስቲያ በሳርማሪያ ሆቴል  ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ፤ በሁለቱ ወረዳዎች በተለይ የህፃናት አመጋገብን አስመልክቶ በቤተሰብ ግንዛቤ ላይ በተሰራ ስራ፣ አመርቂ ውጤቶች መምጣታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህንን የግንዛቤ ስራ ወደ አገር አቀፍ ደረጃ በማሳደግ፣ ህፃናትን ከመቀንጨር በመከላከል፣ በቂ ክብደት ኖሯቸው እንዲያድጉ በማድረግ፣ ምርታማ ዜጋን ለማፍራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል - በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፣ የፕሮግራም ውጤታማነትና የማስተማር ስትራቴጂ ዳይሬክተር አቶ በየነ ገለታ፡፡ አዲሱ የስልጠና ማንዋል በተለይ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግብአት በመሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 55 በሚጠጉ ወረዳዎች በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚሰራ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ትኩረቱንም በጤና፤ በትምህርት፣ በማህበረሰብ ልማትና በምግብ ዋስትና ላይ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የኒዩትሪሽን ዲፓርትመንት ቴክኒካል ሀላፊ አቶ በኩረፅዮን አሳሳኸኝ በበኩላቸው፤ ይህንን የህፃናት አመጋገብ በማስተካክል በኩል ዋናው ተዋናይ መንግስት ቢሆንም ወርልድ ቪዥን የጥናት ውጤቶችን ለመንግስት በማቅረብ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች በምግብ እጥረት፣በሌላ አካባቢ በግንዛቤ እጥረት፣ ልጆች ከህፃንነታቸው ጀምሮ ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ባለው ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኙ ጥናቱ በተደረገባቸው ሁለት ወረዳዎች መረጋገጡን የጠቆሙት አቶ በኩረፅዮን፤ በጥናቱ ወቅት ግንዛቤ ያገኙ ወላጆች፣ አመጋገብ ላይ በሠሩት ስራ አመርቂ ውጤት መምጣቱንና በስልጠና ማኑዋሎቹ በስፋት ለውጥ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከእያንዳንዱ ጠርሙስ ውሃ፣ 1ሣንቲም፣ ለችግረኞች ድጋፍ ይውላል

ዋው የማዕድን ውሃ ፋብሪካ ምርት ከጀመረበት ቀን አንስቶ ከሸጣቸው ከእያንዳንዱ ጠርሙስ የማዕድን ውሃ ላይ አንድ ሳንቲም፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ድጋፍ አደረገ፡፡ ድርጅቱ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ፤ ቀጣይነት ያለውና ቋሚ
መሆኑን የፋብሪካው ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጠንክር በቀለ ገልፀዋል፡፡ ሰሞኑን በጉራጌ ዞን ቸአ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው
የፋብሪካው ቅፅር ግቢ በተከናወነ ሥነሥርዓት፣ድርጅቱ 60 ለሚሆኑ አረጋውያንና ችግረኛ ህፃናት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በአረጋውያኑና በህፃናቱ ስም በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተከፈተ የቁጠባ ሂሳብ፣ ለእያንዳንዳቸው 1500 ብር ገቢ የተደረገላቸው ሲሆን ችግረኞቹን በዘላቂነት ለመደገፍ ድርጅቱ ቃል ገብቷል። ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ባደረጉት ንግግርም፤የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ድርጅቱ የገባውን ቃል
የሚያረጋግጥበትና ሃገራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴውን የሚያሳይበት ነው ብለዋል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው አረጋውያንና ወላጅ
የሌላቸው ህፃናት በበኩላቸው፤ ባገኙት ድጋፍ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፣ ድርጅቱ በቀጣይነት በሚያደርግላቸው ድጋፍ፣ ህይወታቸውን ለማስተካከል የሚችሉበትን ሥራ ለመስራት እንደሚጥሩ ተናግረዋል። በዕለቱ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኙ በርካታ
የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብቶችም፣ለችግርኛ ህፃናቱና አረጋውያኑ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡ በ”የካብዲ አግሮፕሮሰሲንግ” ኃ.የተ.የግ.ማ ሥር
የተቋቋመው ዋው የማዕድን ውሃ ፋብሪካ፤ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ሌሎች አገር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በማስገኘት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት የፋብሪካው ባለቤት፤ ከዚህ ባሻገር ችግረኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በቋሚነት ለመደገፍ ዕቅድ ነድፎ በስፋት እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል፡፡ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተቋቋመው ድርጅቱ፤ በቀጣይ በወተትና የወተት ተዋፅኦ፣ በፍራፍሬ ጭማቂዎችና በሌሎች የምግብና የመጠጥ አግሮፕሮሰሲንግ ሥራዎች ላይ በስፋት እንደሚሰማራ አቶ ጠንክር ገልፀዋል፡፡

“የተሻለ ኮንስትራክሽን፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ”


የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው “ኢትዮ ኮን” ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተ ሲሆን ነገ አመሻሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሏል። “የተሻለ ኮንስትራክሽን፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በተከፈተው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ከ100 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን ከውጭዎቹ ሀገራት፡- ቻይና ቱርክ፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያና ሌሎችም ተሳታፊ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ የኮንስትራክሽን እቃ አምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ ዲዛይንና ስፔስፊኬሽን አዘጋጆች፣ ስራ ተቋራጮች፣ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ ኤጀንቶች፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ የአገር ውስጥ አምራቾች፣ አስመጭና አከፋፋዮች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢ/ር አበራ በቀለ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ እድገቱ ጤናማና ትክክለኛ እንዲሆን ለማድረግ፣ ሀላፊነቱ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ቢሆንም በዋናነት ከዘርፉ ባለቤት ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑ ምርትና አገልግሎትን ለጎብኚ በማቅረብ ብቻ ሳይወሰን የውይይት መድረክም አዘጋጅቷል፡፡ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በኢሲኤ አዳራሽ፤ “ወቅታዊ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ተግዳሮቶችና የእድገት ማነቆዎች”፣ “የቴክኖሎጂ ሽግግር በካፒታል ኢንተንሲቭ፣ በኮንስትራክሽን ዘዴ”፣ “የኮንስትራክሽን ግዢና የኮንስትራክሽን አስተዳደር”፣ “ብክነትና ሊን ኮንስትራክሽን” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው  ውይይት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አዲስ አበባ የጤናና የቢዝነስ ኮሌጅ፣ ለ13ኛ ጊዜ በዲግሪና በደረጃ አራት ያሰለጠናቸውን 429 ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ አስመረቀ።ተመራቂዎቹ በነርሲንግ፣ በጤና መኮንን፣ በክሊኒካል ነርሲንግና በላብራቶሪ ቴክኒሺያን የትምህርት ዘርፍ
የሰለጠኑ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ኮሌጁ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሶማሌ ላንድ ሀርጌሳ የሚገኘውን ካምፓስ ጨምሮ
በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ባሉት ካምፓሶቹ፣ከ47ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ በጤናው ዘርፍ ያለውን የባለሙያ ክፍተት ሲሞላ መቆየቱን የኮሌጁ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡ ከተመረቁ 47 ሺህ ባለሙያዎች መካከል
ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት በኮሌጁ ነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤
በየካምፓሶቹ በዓመት ለ20 ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል እንደሚሰጥና በተለይ መክፈል ባለመቻል መማር ላልቻሉ ሴት ልጆች ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደቆዩ አክለው ገልፀዋል፡፡ተማሪዎች እዚህ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለከፍተኛ ትምህርት አሜሪካ በሚሄዱበት ወቅት ተቀባይነት የሚያስገኝ፣ በአሜሪካ እውቅና ያለው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ኮሌጅ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ በምርቃቱ ዕለት አስታውቀዋል

በብርሀኑ ደጀኔ የተሰናዳውና በእውነተኛ ታሪኮች ላይ ያጠነጥናል የተባለው፣ “በራስ እይታ የእማዬ ውለታ” መፅሀፍ ለንባብ በቃ።መፅሀፉ፤ የልጅነት፣ የስራ፣ የት/ቤትና ተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎችን ያስቃኛል፤ ተብሏል። በ74 ገጽ የተመጠነው መፅሀፉ፣ በ70 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡