Administrator

Administrator

Saturday, 11 February 2017 12:54

የዘላለም ጥግ

(ታላላቅ ሰዎች
በመሞቻቸው ሰዓት)
- “ማምለጫ ሰበብ እየፈለግሁ ነው”
ደብሊው ሲ. ፊልድስ
(አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይና ኮሜዲያን)
- “በእግዚአብሔር እ መኑ እ ናም ም ንም
የሚያስፈራችሁ ነገር አይኖርም”
ጆናታን ኤድዋርድስ
(የክርስቲያን ሰባኪና የስነ-መለኮት ልሂቅ)
- “ምድር ወደ ኋላ ስትሸሽ፣ መንግስተ ሰማያት
ሲከፈት ይታየኛል፡፡ እግዚአብሔር እየጠራኝ
ነው”
ዲ.ኤል.ሙዲ
(አሜሪካዊ ወንጌላዊና ደራሲ)
- “ሞት፤ የዘላለማዊነትን ቤተ መንግስት
የሚከፍት ታላቅ ቁልፍ ነው”
ጆን ሚልተን
(የብሪቲሽ ገጣሚ)
- “በአስር ደቂቃ ዘግይቻለሁ፡፡ እኔ ማርፈድ
አልወድም፡፡ ፀሎቱ ጋ ልክ በ11 ሰዓት መገኘት
እፈልጋለሁ፡፡”
ማሃትማ ጋንዲ
(የህንድ የነፃነት ንቅናቄ መሪ)
- “ዛሬ በጣም ሞቃት ነው”
ጄሲ ጄምስ
(አሜሪካዊ የባቡር ላይ ዘራፊ)
- “ሁልጊዜም ጋደም ስል የተሻለ እናገራለሁ”
ጄምስ ማዲሰን
(የአሜሪካ 4ኛ ፕሬዚዳንት)
- “በቃ ተይኝ!”
(ነርሷ የእግር እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ስትጠይቀው)
ጎሬ ቪዳል
(አሜሪካዊ ደራሲ)
- “እስቲ ወደ አባታችን ቤት ልሂድ”
ጆን ፖል (ዳግማዊ)
(የሮማን ካቶሊክ ቤ/ክርስቲያን ጳጳስ)
- “ለብቻዬ ተይኝ፤ ደህና ነኝ”
(ለነርሱ የተናገረው)
ባሪ ዋይት
(አሜሪካዊ ሙዚቀኛ)
- “እና ሞት ይሄ ነው - ይሁና”
ቶማስ ካርሊሌ
(የስኮትላንድ ፈላስፋና የታሪክ ምሁር)
- “የሰሙኝ እንኳን አይመስለኝም”
(ራሱን ከማጥፋቱ በፊት የተናገረው)
ዩክዮ ሚሺማ
(ጃፓናዊ ደራሲ)

Sunday, 12 February 2017 00:00

ገራገሩን -ስለ አገረ ሩሲያ!

- አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1867 የአላስካ ግዛትን ከሩሲያ ላይ የገዛችው በ7.2 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡
- በሩሲያ በታላቁ ፒተር የአገዛዝ ዘመን፣ጺም ያላቸው ወንዶች በሙሉ ለመንግስት ግብር እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር - “የፂም ግብር”በሚል፡፡
- እ.ኤ.አ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በሩሲያ ቢራ እንደ አልኮል መጠጥ አይቆጠርም ነበር፡፡
- ሩሲያ በኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች ብዛት በዓለም ላይ ቀዳሚ ናት፡፡ ከ8400 በላይ የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች አሏት፡፡
- እ.ኤ.አ ከ1959 አንስቶ የሩሲያ ሳይንቲስቶች፣ቀበሮዎችን ልክ እንደ ውሻ ለማዳ አድርገዋቸዋል - የቤት እንስሳት፡፡
- የሩሲያ 20 ባለፀጎች አጠቃላይ ድምር ሀብት ከ227 ቢ. ዶላር በላይ ሲሆን ይሄም ከፓኪስታን ጠቅላላ አመታዊ ምርት ይበልጣል፡፡
- እያንዳንዱ ሩሲያዊ በዓመት 18 ሊትር አልኮል ይጠጣል፡፡
- በሩሲያ አማካይ በህይወት የመቆየት ጣሪያ ለወንዶች 59 ዓመት ሲሆን ለሴቶች 73 ዓመት ነው፡፡
- ስታሊን ስደተኛ ነበር፤8 ዓመት እስኪሞላው ድረስ የሩሲያ ቋንቋ መማር አልጀመረም፡፡ አፉን የፈታው በጆርጂያን ቋንቋ ነው፡፡
- ሩሲያ ቢያንስ 15 ምስጢራዊ ከተሞች እንዳሏት ይታመናል፡፡ የእነዚህ ከተሞች ስምም ሆነ ስፍራ የማይታወቅ ሲሆን የውጭ ዜጎች ወደነዚህ

ሥፍራዎች እንዲጠጉ አይፈቀድላቸውም፡፡
- ሞስኮ በዓለም ላይ ትልቁ የማክዶናልድ ሬስቶራንት አላት፡፡

   የዚያድ ባሬን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ እንደ አገር መቆም ተስኗት አሳር መከራዋን ስትቆጥር የዘለቀቺው፣ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የጽንፈኛ ቡድኖች ጥቃት፣ ድርቅና ርሃብ እየተፈራረቁ ያደቀቋት ሶማሊያ፤ ከ25 አመታት በኋላ ሰሞኑን ታሪካዊ የተባለውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አከናውናለች፡፡በሙስና የታማው፣ በሽብር ስጋት የታጀበው፣ ተስፋ የተጣለበትና ለወራት የዘለቀው የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት፣ ባለፈው ረቡዕ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡የተረጋጋች አገር፣ የተሻለ ኑሮ፣ ዘላቂነት ያለው ሰላም፣ ብልህና አዋቂ መንግስት፣ ከትናንት የተሻለ ነገ የናፈቀው የሶማሊያ ህዝብ፣ ነገውን የሚወስንለትን ወሳኝ ሰው፣ ቀጣዩን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ለማወቅ ጓጓ፡፡“ማን ይሆን ተረኛው?...” ሲል ጠየቀ፡፡
“ፎርማጆ ነው!...” አለ የምርጫ ውጤቱ፡፡
የሶማሊያ ዘጠነኛው ፕሬዚዳንት በመሆን መንበረ ስልጣኑን ለመረከብ የተመረጠው ወሳኙ ሰው፣ ፎርማጆ ነው፡፡
“ሶማ-አሜሪካዊ”ው ፎርማጆየምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በርካታ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን፣ ምርጫውን በተመለከተ ያወጧቸው ዘገባዎች ርዕሶች ተመሳሳይና ስላቅ ቢጤ ያዘሉ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ዘገባዎች ከአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ስም ጋር፣ የጥምር ዜግነት ባለቤትነታቸውንም ጭምር በማጉላት የተቀናበሩ ናቸው፡፡እርግጥ ነው...
ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው ያልተለመደ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ህግ ግን የሌላ አገር ዜግነት ያለው ሶማሊያዊ በፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደር የማያግድ ነውና፣ ጉዳዩ ከጊዜያዊ ግርምት አልፎ ፖለቲካዊ ጥያቄ አላስከተለም፡፡ በምርጫው ያሸነፉት የሶማሊያና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የ55 አመቱ ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2011 በነበሩት ስምንት ወራት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ፎርማጆ፣ በ1993 በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲያገኙ፣ በ2009 ደግሞ ከስቴት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክ፣ በፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡በዋሽንግተን የሶማሊያ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉትና የአራት ልጆች አባት የሆኑት ፎርማጆ፤ እ.ኤ.አ ከ1985 አንስቶ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ
ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም አሁንም ድረስ በአሜሪካ ነው የሚገኙት፡፡
“አዲሲቷን ሶማሊያ እፈጥራለሁ፣ በጽንፈኛው ቡድን አልሻባብ ላይ እዘምታለሁ፣ ከአለም አንደኛ አድርጎ ስማችንን በአጉል የሚያስጠራውን ሙስናን በቁርጠኝነት እዋጋለሁ!...” ሲሉ ቃል ገብተዋል፤ ፎርማጆ ድላቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፡፡ድምጽ 100 ሺህ ዶላር ይሸጣል!...
የሶማሊያ ምርጫ ስርዓት በአንዳንድ አገራት ቢሰራበትም፣ ከተለመዱት የምርጫ ስርዓቶች ወጣ ያለ ነው፡፡
በመጀመሪያ የአገሪቱ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች፤ የፓርላማ አባላትንና ሴናተሮችን ይመርጣሉ፡፡ እነዚሁ ተመራጮች በተራቸው፣ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት ለቀረቡ ተወዳዳሪዎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ፡፡ በሶስት ዙር በሚሰጥ ድምጽ በሚደረግ ማጣሪያም
አሸናፊው ፕሬዚዳንት ይለያል፡፡በዚህ መልኩ በተከናወነው የዘንድሮው ምርጫም 14 ሺህ ያህል የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የመረጧቸው 329 የፓርላማ አባላትና ሴናተሮች፣ በተወዳዳሪነት ለቀረቡት 21 ዕጩዎች ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡በስተመጨረሻም...
በስልጣን ላይ የቆዩትና ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ይቀጥላሉ የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ሃሰን ሼክ ሙሃሙድ 97 ድምጽ በማግኘት ሽንፈትን ሲያስተናግዱ፣ ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ ፎርማጆ 184 ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡ይህም ሆኖ ግን...
ታሪካዊ የተባለው ምርጫ በሙስና መታማቱ አልቀረም፡፡ተቀማጭነቱ በሞቃዲሾ የሆነው ማርካቲ የተባለ የጸረ ሙስና ተቋም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት፤ በምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ፣ መራጮች በገንዘብ ተደልለው ድምጻቸውን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብሏል፡፡በዚህ መልኩ በሙስና ድምጻቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ የህዝብ ተወካዮች፣ የመራጭነት መብታቸውን ከመገፈፍ አንስቶ እስከ ግድያ የሚደርስ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው እንደተዛተባቸውም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡አንዳንድ የህዝብ ተወካዮች ለአንድ የፓርላማ አባል ድምጻቸውን ለመስጠት፣ እስከ 30 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በሙስና መልክ እንደተሰጣቸውና፣ በፕሬዚደንትነት ለመወዳደር የቀረቡ አንዳንድ ዕጩዎች በበኩላቸው፤ የፓርላማ አባላቱ እንዲመርጧቸው  እስከ 100 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ መደለያ (ጉቦ) እንደሰጡም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ አውሮፕላን ጣቢያ - ምርጫ ጣቢያበአለማችን የምርጫ ታሪክ በአውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ የተከናወነ የመጀመሪያው ምርጫ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል - የሰሞኑ የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፡፡የአገሪቱን አንድ ሶስተኛ ግዛት ያህል ተቆጣጥሮ የሚገኘው ጽንፈኛው ቡድን አልሻባብ፣ የሽብር ጥቃት በመፈጸም ምርጫውን ሊያስተጓጉል ይችላል ተብሎ በመሰጋቱ ሳቢያ፣ የምርጫ ስነስርዓቱ በሞቃዲሾ በሚገኝ የፖሊስ አካዳሚ ቅጽር ግቢ ውስጥ እንዲደረግ ነበር የታሰበው፡፡ በኋላ ላይ ግን፣ የተሻለ የጸጥታ ሁኔታና የተጠናከረ ጥበቃ ያለበት ስፍራ መፈለግ እንዳለበት ተወሰነ፡፡ በዚህም መሰረት ምርጫው በአገሪቱ እጅግ የተጠናከረ ጥበቃ ያለበት ስፍራ እንደሆነ በተነገረለት የሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ እንዲከናወን ተደርጓል፡፡አልሻባብ የምርጫ ሂደቱን ለማወክ መሞከሩ አይቀርም የሚለው ስጋት እንቅልፍ የነሳው የአገሪቱ መንግስት፣ በሞቃዲሾ የትራፊክ እንቅስቃሴ ለ8 ሰዓት ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጋ ከማድረግ ባለፈ፣ የሞቃዲሾ አውሮፕላን ጣቢያም መጪም ሆነ ሂያጅ አውሮፕላንን ላያስተናግድ ተዘግቶ ነው የዋለው፡፡ህዝቡ ፈንድቋል...
የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን በመዲናዋ ሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት በደስታ ሲፈነጥዙ ታይተዋል፡፡ በፎርማጆ ማሸነፍ የፈነደቁ ወታደሮችም በደስታ ተኩስ፣ ሞቃዲሾን ሲያደምቋት አምሽተዋል ተብሏል፡፡ሰውዬው ምንም እንኳን የዳሮድ ጎሳ አባል ቢሆኑም፣ የተሻለች አገርን ተስፋ ያደረጉ ሶማሊያውያን ግን፣ ጎሳ ሳይለዩ አደባባይ በመውጣት ለፕሬዚዳንቱ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡ በኬንያ ዳባብ የስደተኞች ካምፕ የሚገኙ በርካታ ሶማሊያውያንም ደስታቸውን እንደገለጹ ተዘግቧል፡፡



አንዳንድ ተረት ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ወይ ስለማይገባ፣ አሊያም ቸል ስለሚባል እንደገና መደገሙ ግዴታ ይሆናል፡፡ የዛሬውም
ከዓመታት በፊት ያልነው ነው፡፡ (አንድ የፈረንጅ ጸሐፊ “As no one listens we should say it again…” ይላል፡፡ የሚሰማ ስለሌለ እንደገና
መናገር አለብን፤ ማለቱ ነው።)
እኛም እንድገመው፤ አሻሽለን፡-
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ የእርሻ ስራውን አጠናቆ ወደ ቤቱ እየመጣ ነበር፡፡
ጦጢት ደግሞ እንደ ልማዷ ዛፉ ላይ ሆና ገበሬው ሲመጣ ታየዋለች፡፡ ገበሬው ከዘር ዝሪ እንደሚመጣ ታውቋታል፡፡ ወቅቱ የዘር መዝሪያ ጊዜ
መሆኑን ተገንዝባለች፡፡ ስለሆነም የዘራው ዘር እሷ የምትበላው ዓይነት ከሆነ፣ ሄዳ እየፈለፈለች እያወጣች ልትበላ ነውና መረጃ ፈልጋለች፡፡
ስለዚህ ገበሬውን ለማወጣጣት በትህትና ትጠይቀዋለች፡፡
“ገበሬ ሆይ! እርሻ ምን መሳይ ነው?”
ገበሬ፤
“ሁሉ አማን፣ ሁሉ ሰላም ነው!”
ጦጢት፤
“ዛሬ የዘር ጊዜ ነው አይደል?”
ገበሬ፤
“አዎ የዘር ጊዜ ነው፡፡ በየዓይነቱ ዘር ይዘራል”
ጦጢት፤
“ዘንድሮ ምን ተዘራ?”
ገበሬ፤
“ምን ያልተዘራ አለ፡፡ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄ፣ … ምኑ ቅጡ? ሁሉም የየአቅሙን ይዘራል፡፡ መሬቱ፤ መሬት ነውና

ሁሉንም ይቀበላል”
ጦጢት፤
“እንደው ደፈርሺኝ አትበለኝና አንድ ጥያቄ እንድጠይቅህ ትፈቅድልኛለህ?”
ገበሬ፤
“እስካሁን የፈለግሺውን እንድትናገሪ ፈቅጄልሽ የለ?”
ጦጢት፤
“አይ ይሄኛው ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ልጠይቅህ?”
ገበሬ፤
“ኧረ ጠይቂ፤ ምንም ችግር የለም”
ጦጢት፤
“አመሰግናለሁ፡፡ እንደው ዘንድሮ አንተ ምን ዘራህ?” አለችው
ገበሬ፤ ጦጢት ሄዳ እንደምትቦጠቡጠው ያውቃልና እሷ የማትፈለፍለውን እህል አስቦ መናገር አለበት፡፡ አሰላ አሰላና፤ በትህትና፡-
“ጦጢት ሆይ፤ እኔ ዘንድሮ የዘራሁት ተልባ ነው” አላት፡፡
(ጦጣ ለመፈርፈር በጣም የሚያስቸግራት ተልባ ነው)
ጦጢት፤
“በጣም ግሩም! በቃ ወርደን እናየዋለና! ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
*         *       *
ጦጢት የእኛ አገር ነገር የገባት ነው የምትመስለው፡፡ ከላይ የተነገረውን መሬት ወርዶ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ዲሞክራሲ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! ፍትህ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! (Justice delayed Justice
denied የዘገየ ፍትህ እንደሌለ ይቆራል - ዕውነት ነው?)
የሕግ የበላይነት አለ ተብለናል፡፡ “ፍትህ የተዘጋጀ ዳቦ አይደለም” የሚለው አባባል ነው ተግባራዊ? ታች ወርደን እናረጋግጥ! ማንም የበላይ
የበታቹን እንዳሻው አይበድልም? እናጣራ!
“ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግዴለም” እያልን አንዘልቀውም፡፡ ወርደን እንየው!
ትምህርት፤ በወላጅ፤ በመምህርና በተማሪ ሶስት - ማዕዘን (Triangular) ግንኙነት እያማረ ነው ተብለናል፡፡ እስቲ መሬት ወርደን እንየው፡፡
ጤና፤ በየጣቢያዎቹ ለህዝቡ በሚያመች ዘዴ ተሰልቶ ዝግጁ ሆኗል ተብለናል፡፡ መዳኒት አለ? የበቃ ህክምና አለ? ጤና ኬላ በቂ ነው? እስቲ
ጦጢት እንዳለችው፤ ይዋጥልን እንደሆን ወርደን እንየው! የመንገድ ሥራ ተሳክቶ ተጠናቋል፤ ተብለናል፡፡ ዘላቂ ናቸው አይደሉም? ወርደን
እናጣራ! አገራችን ሰላም ሆናለች፤ ተብለናል፡፡ ወደ ሰሜን፣ ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ደቡብ ምዕራብ ወርደን እንታዘብ፡፡ መሬት የያዘውን አይለቅምና
ወርደን እንየው፡፡ በሀቅ እንዘግበው!
ሀብት፤ በፍትሐዊ መልክ ይከፋፈላል ተብለናል፡፡ እኩልነት ቤት - ደጁን ሞልቶታል ተብሏል፡፡ እስቲ ወርደን ኢወገናዊ መሬት መኖሩን አይተን
እንርካ! የትራፊክ አደጋ ቀንሷል እንባላለን፡፡ መሻሻል አለመሻሻሉን፣ ትራፊክ ሜዳው ላይ ወርደን እንየው! የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር
ተብለናል፡፡ ዛሬስ? ወርደን ማየት ነው!
አገራችን የአሸባሪዎች ኮሪደር ናት ተብለናል፡፡ ዕውነት የሽብር ድልድይ ነን? ወርደን ማየት የአባት ነው! የአገራችን ፌደራሊዝም እና ክልላዊ
መስተዳድሮች አካሄድ የተቀናጀና የሰመረ ግንኙነት ያለው ነው ተብለናል፡፡ ወርደን እንየው! ባቄላ፣ በቆሎ ወይስ ተልባ? እናጣራ፡፡ እንናበባለን?
በፓርቲ አባላት መካከል ልባዊ መግባባት፣ ወቅታዊ መናበብ አለ? ተቃዋሚዎች ከአሉታዊ ፅንፍ ወጥተዋል ወይ? ወርደን እንየው!
መንግሥት በግል ሚዲያዎች ላይ ያለው ዕምነት ምን ይመስላል? ዛሬም “በሬ ወለደ ይላሉ” ነው? ዛሬም “የሌሎች አፍ ናቸው” ነው? ዛሬም
“ፀረ-መንግሥት” ናቸው ነው? ዛሬም መታሰራቸው ልክ ነው? ዛሬም የሚታኑና የማይታመኑ ሚዲያዎች አሉ? ወርደን እንያቸው!
በአገራችን ሙስና ጉዳይ የማንስማማበት ምክንያት ያለ አይመስልም፡፡ ይሰረቃል፡፡ ይዘረፋል፡፡ ችግሩ ግን የማይደፈሩ ሰራቂዎችና ዘራፊዎች አሉ
የሉም? ነው፡፡ ጥያቄው ግልፅ ነው!፡፡ ስለዚህ ወርደን እንየው!
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከውጪ ያለውን አጋር ወይም ሐሳዊ ወዳጅ መንግስት የምናምነው ምን ያህል ነው? ሴትዮዋ ጓሮ ለሚጠብቃትና
እያስነጠሰ ምልክት ለሚሰጣት ውሽማዋ፣ የባሏን ቤት ውስጥ መኖር ለመንገር፣
“አንት የጓሮ ድመት፣ ምንም ብታነጥስ ዛሬ በዓል (ባል) ነውና፣ ቅጠልም አልበጥስ” እንዳለችው ያንን እየደጋገምን የምንጓዝበት ዲፕሎማሲ
ያስኬደናል ወይ?
ከገዛ ህዝባችን መግባባትና መስማማት እንጂ ከሌሎች በምናገኘው ገቢ (fund) ወይም ድጎማ መተማመን ብዙ አያራምደንም፡፡ የሚያዛልቀን
የህዝብ ሀብት ነው! መቼም ቢሆን ነባርም መፃኢም ህልውናችን የሚወሰነው በህዝባችን ፍቅር ነው!
“አገባሽ ያለ ላያገባሽ
ከባልሽ፣ ሆድ አትባባሽ”
የሚለውን ተረት ሳንታክት ማሰብ ለሀገር ልማትና ዕድገት መሰረት ይሆነናል! አንርሳው!

    በአፍሪካ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ህፃናት የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው የጠቆመው “ወርልድ ቪዥን” የተሰኘው አለማቀፉ ግብረ ሰናይ ድርጅት፤ የአህጉሪቱ መሪዎች ህፃናትን ከጥቃት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ወርልድ ቪዥን በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም
አገራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለመጠቆምና ለመቀስቀስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት ፕሮግራም ላይ በአህጉሪቱ የሚገኙ ህፃናት ከፍተኛ በደል እንደሚፈፀምባቸው በዝርዝር ተገልጿል፡፡ የጉልበት ብዝበዛ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲሁም ህፃናትን ያለ እድሜያቸው ለጦርነት የማዋልና በቀጥታ የግጭት ሰለባ የመሆን አደጋዎች እንደተበራከቱ ተመልክቷል፡፡ ከ200 በላይ የሚሆኑ
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ አመራሮች በሂልተኑ ውይይት ላይ ተገኝተው የአህጉሪቱ ህፃናት ፍዳ በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን “የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ፣ ከዚህ በኋላ ለድርጊቱ ምንም ትዕግስት የለንም” በሚል መርህ ሁሉም ወገን ድርጊቱን እንዲቃወምና የአህጉሪቱ ሴት ህፃናት ከግርዛት እንዲድኑ ጥሪ ተላልፏል፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከኡጋንዳና ከደቡብ ሱዳን የተውጣጡ የህፃናት ተወካዮችም
በአቻዎቻቸው ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

Sunday, 12 February 2017 00:00

“ጉዛራ ዛሬ” ይመረቃል

     በኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል የአደን ባለሙያ የተሰራውና ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል የተባለው “ጉዛራ ሆቴል” ዛሬ ይመረቃል፡፡በአደን ሙያ ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ሙሉ ፈቃድ ተሰጥቶአቸው ለረዥም አመታት በሙያው ሲሰሩየቆዩት አቶ ተሾመ አደም፤ በቱሪዝም ዘርፉ ለዓመታት ያዳበሩትን ዕውቀትና ልምድ ተጠቅመው፣ የቱሪስቱን ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል መልኩ ሆቴሉን መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ሲኤምሲ ስዓሊተ ምህረት አካባቢ የተሰራውና ከ20 ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል የተባለውይኸው ሆቴል፤ ዛሬ ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት በሚገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡

     ‹‹ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ማለት ሐሳብንና ገንዘብን አቀናጅቶ ሥራ መፍጠር ነው፡፡ ሰዎች እዚህ ተምረው ወጥተው እንዴት የራሳቸውን ሥራ መፍጠር እንደሚችሉ ነው የምናስተምረው፡፡ ሐሳብና ገንዘብ እንዴት እንደሚቀናጁ መንገድ እናሳያለን፡፡ ከፊዚቢሊቲ ጥናት አንስቶ ማርኬቲንግና ፋይናንሻል ስትራቴጂ እንዴት እንደሚቀረጽ እናስተምራለን፡፡ ምክንያቱም ያለ ፋይናንስ (ገንዘብ) ሐሳብ ብቻውን ውጤታማ አይሆንም፡፡ ድሮ በአገራችን ገንዘብ ያለው ሰው ነጋዴ፣ ነጋድራስ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ ሐሳብ ሆኗል ገንዘብ፡፡ እነ ጎግል፣ እነ ፌስቡክ የሐሳብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሐሳብ ነው ብር እየሆነ የመጣው፡፡ እኛ የምናስተምረው ሐሳብን ከገንዘብ ጋር አቀናጅቶ እንዴት ወደ ሥራ መተርጎም እንደሚቻል ነው፡፡‹‹በዚች አገር አንድ ሰው ሐሳብ ይዞ ሲነሳ፣ ብዙም ተቀባይነት የለውም፡፡ ባንኮች እንዴት ገንዘብ ሊያበድሩት እንደሚችሉ፣ ብር ያላቸው ሰዎች እንዴት ገንዘባቸውን ሊሰጡት እንደሚችሉ እንዲቀምር ነው የምናስተምረው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች ደግሞ እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ፣ ከአራትና አምስት ዓመት ገቢያቸው ጋር እንዲያስተያዩት፤ እንዴት የበለጠ ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ፣ ገንዘባቸውን ባንክ ከሚያስቀምጡ ኢንቨስት ቢያደርጉ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ ማሳመን መቻልን ነው የምናስተምረው ‹‹ከአንድ ቢዝነስ ወጥቶ እንዴት ሌላ የተሻለ ቢዝነስ መጀመር እንዳለበትም እናስተምራለን፡፡ ቀደም ሲል አያቱ ወይም አባቱ ቤንዚን ማደያ ካላቸው ልጃቸውም ቤንዚን ማደያ ነው የሚኖረው፡፡አሁን ግን ያ አይደለም ዘመናዊ ቢዝነስ፡፡ ቢዝነሱ በፊት ከነበረበት አድጎ ነው መገኘት ያለበት፤ ወደ ፈጠራ ነው መሸጋገር ያለበት፡፡ የቢዝነስ ሞዴል አስተዳደር ትምህርት ይህ ነው›› ብለዋል የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንትና የኤምቢ ኤ ፕሮግራም ሥራ አስፈጻሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤቱ መላኩ፡፡ ከተመሰረተ አንድ መቶ ዓመት ሊሆነው ሁለት ዓመት ብቻ የቀረው የሊንከን ዩኒቨርሲቲ አካል የሆነው ዌስተርን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባለፈው ሳምንት በሁለተኛ ዲግሪ በኤምቢኤ (Masters of Business Administration) ለ6ኛ ዙር፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (ቢኤ) ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት እዚህ አዲስ አበባ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በድምቀት አስመርቋል፡፡ ለመሆኑ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንዴት በአገራችን (Masters of Business Administration (ኤምቢኤ) ትምህርት መጀመር ቻለ? መቼ? መልሱን አቶ አቤቱ ይነግሩናል፡፡ ከተመሰረተ 98 ዓመታትን ያስቆጠረው፣ በአሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ከተማ የሚገኘው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ በአራት ወይም በአምስት
አገሮች በኤክስቴንሽን ያስተምራል፡፡ የአፍሪካ ተወካይ ናይጀሪያ ነበረች፡፡ ይህ ካምፓስ በፀጥታ ችግር መዘጋቱን አቶ አቤቱ በማስታወቂያ ሰሙ፡፡ እንዴት አፍሪካን የሚያህል አህጉር ያለ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ይቀራል? በማለት ጠየቁ እኛ ለደህንነታችን ነው ቅድሚያ
የምንሰጠው ተባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ አፍሪካን እንድትወክል ተመኙና ኢትዮጵያስ? በማለት ጠየቁ በኢትዮጵያ ሰላም አለ? ኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በርካታ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ድርጅቶች ያሉባት፣ ፈረንጆች በእኩለ ሌሊት የሚንሸራሸሩባት ናት በማለት መለሱ፡፡ “ለምን ፕሮፖዛል ጽፈህ ለባለ አደራ ቦርድ አቅርበህ አትሞክርም?” አሏቸው፡፡ ፕሮፖዛል ፅፈው አስገቡና ሰዎችም ረድተዋቸው ተቀባየነት አገኙ፡፡ የባለ አደራ ቦርዱ ሊቀ መንበር ግን ጥርጣሬ ገባቸው፡፡ ‹‹ይህ ሰው የተማረው ስለ ቢዝነስ ነው፡፡ የአካዳሚክ እውቀት የለውም፡፡ ታዲያ እንዴት ዩኒቨርሲቲውን መምራት ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ ቀደም ሲል አቶ አቤቱ ብሉናይል ኢንተርፕራይዝ  ኩባንያ አቋቁመው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አምቦ ውሃንና በደሌ ቢራን ወደ አሜሪካ ወስደው ለ5 ዓመት የሸጡና ያስተዋወቁ ሰው
ናቸው፡፡ እዚህ አገር ቤት በተፈጠረ ችግር ተቋረጠ እንጂ አምቦ ውሃው በአሜሪካ ገበያ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡  ለባለአደራ ቦርዱ ሊቀመንበር ጥያቄ፣ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሲመልሱ፣ ‹‹ከአፍሪካ (ኢትዮጵያ) ውሃ አምጥቶ በአሜሪካ ገበያ መሸጥ ከቻለ፣ ይህንን
ዩኒቨርሲቲ አገር ቤት ወስዶ እንዴት ነው መምራት የሚያቅተው?” በማለት ተሟገቱላቸው፡፡ በዚህ ዓይነት በሊንከን ዩኒቨርሲቲ ተወክለው ወደ ኢትዮጵያ ተላኩ፡፡
ሊንከን ዩኒቨርሲቲ… እዚህ (ኢትዮጵያ) ሲመጣ ድንበር ተሻጋሪ ስለሚባል ትምህርት ግልጽ መመሪያ አልነበረም፡፡ ‹‹ጥርጣሬውም ስለነበር ሊፈቅዱልኝ አልፈለጉም ነበር፡፡ ሦስት ወር ሙሉ ከወዲያ ወዲህ በመመላለስ ጫማዬን ጨርሼ ምንም ውጤት ስላላገኘሁ፣ ከፍተኛ ፍርሃትና
ስጋት ገብቶኝ ነበር›› ይላሉ አቶ አቤቱ ሊንከን ዩኒቨርሲቲን በኢትዮጵያ ለማቋቋም ገጥሟቸው የነበረውን ችግር ሲያስታውሱ፡፡ በመጨረሻም  ተስፋ ቆርጠው ወደ አሜሪካ ለመመለስ ሲነሱ፣ ቀደም ሲል ያውቋቸው የነበሩትን ወዳጃቸውን፤ ‹‹ሰላም ሁን›› ለማለት ቢሮአቸው
ደወሉላቸው፡፡ ወዳጃቸውም ‹መቼ መጣህ?›› በማለት ጠየቁ፡፡ አቶ አቤቱ ‹‹አይ፤ ሳላይህ ብሄድ ውቃቢህ ያየኛል ብዬ ነው የደወልኩት እንጂ መሄዴ ነው›› አሉ፡፡፡ ወዳጃቸውም ‹‹መቼ መጣህ›› አሉ፡፡ ‹‹ለዚህ ጉዳይ ነበር የመጣሁት፡፡ አሁን ስላልተሳካልኝ ተስፋ ቆርጨ መመለሴ ነው››
በማለት መለሱ፡፡ ‹‹ስልኩን ዝጋው፤ መጣሁ›› ብለው፤ አቶ አቤቱ ወደ ነበሩበት ሄደው በመኪና ወደ ቢሯቸው ወሰዷቸውቢሮ እንደደረሱ ለምን ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ፤ ያደረጉትን ጥረት፣ አልሳካ ቢላቸው ተስፋ ቆርጠው ለመመለስ እንደወሰኑ በዝርዝር
አጫወቷቸው፡፡ ወዳጃቸው በሰሙት ነገር በጣም ተገረሙ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የሚያውቋቸው ሰዎች ስለነበሩም እነሱን በስልክ አግኝተው ስለጉዳዩ አጫወቷቸውና፤ ‹‹እንዲህ ያለ ነገር እንዴት ይታለፋል? ያገር ጉዳይ’ኮ ነው›› በማለት ፋክስ አደረጉላቸው፡፡ ከዚያም አሪጂናል ዶክመንቶችን አገላብጠው ተመለከቱ፡፡ ‹‹ ይህን ይዘህ ማን ጋር ሞከርክ?›› በማለት ጠየቋቸውየ‹‹እገሌ የሚባል ያልሞከርኩበት ባለሥልጣን የለም፡፡ በማለት መለሱ፡፡ ‹‹ለምን አንድ ሦስት ቀን አትቆይም?›› አላቸው፡፡ አቶ አቤቱም፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ አያልቅም፡፡ ስለዚህ ተመልሼ መስራት አለብኝ፡፡ በጊዜ አልቀልድም፣ ስለ ጊዜ አጠቃቀም ነው የተማርኩት›› አላቸው  ሰዎቹም፤ ‹‹ግድ የለም፤ ተስፋ አትቁረጥ፤ እኛም እንረዳሃለን››አሏቸው፡፡
በዚህ ዓይነት ከሚመለከታቸው ቢሮዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ተጀምሮ ፈቃድ ተሰጣቸው፡፡ ፈቃዱን ሲያገኙም ብቻቸውን እንዲሠሩ ሳይሆን፣ አስተማማኝነቱ ከተረጋገጠ ተቋም ጋር ተዳብለው እንዲሰሩ ከኒው ጀኔሬሽን ዩነቨርሰቲ ኮሌጅ ጋር ተዳብለው በ2010 መሥራት ጀመሩ፡፡ ለአንድ ዓመት ከሰሩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ከኮሌጁ ጋር ተዳብሎ መስራቱን አስተዳደሩም ሆነ ተማሪዎች ስላልወደዱት፣ እንደገና
አመልክተው ፈቃድ ስላገኙ ነፃ ሆነው በራሳቸው መስራት መጀመራቸውን አቶ አቤቱ አስረድተዋል፡፡
 ዩኒቨርሲቲውን ለመክፈት ግን በጣም ፈታኝ ችግሮች ገጥሟቸው እንደነበር አቶ አቤቱ ይናገራሉ፡፡ ተስፋ ቆርጠው ሊመለሱ ሲነሱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በነበሩ ሰዎች ድጋፍ አግኝቶ (እ.ኤ.አ)፣ በ2010 ከኒውጀኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ጋር ተዳብሎ እንዲሠራ ፈቃድ እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚያስተምረው ስለቢዝነስ ነው፡፡ ዘመናዊ የቢዝነስ ጥበብ አስተምሮ በማስተርስ (ሁለተኛ) ዲግሪ ያስመርቃል፡፡ ዘንድሮ ግን ለማስተርስ ፕሮግራም ሥልጠና ብቁ የሆኑና ተገቢውን መመዘኛ የሚያሟሉ ተማሪዎችን ለመመልመል ያስችለው ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አስተምሮ 18 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል፡፡ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ፣ በዲያግኖስቲክ ኢ-ሜጂንግ (ስካኒንግ፣ ሲኖግራፊ፣) ስፔሻላይዝድ ያደረገ ስለሆነ በሚቀጥለው ዓመት በዚህ እውቀት
አስተምሮ በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስመረቅ አቅዷል፡፡ ነገር ግን አንድ ችግር አለበት፡፡ ይኼውም ተማሪዎች ወጥተው ልምምድ የሚያደርጉበት ሆስፒታል ያስፈልጋል ሁለተኛ፣ ለሆስፒታሉ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች መግባት አለባቸው፡፡ መሳሪያዎቹን ለማስገባት የጉምሩክ ፈቃድ
ይፈልጋል፡፡ ፈቃዱን ለማግኘት ደግሞ ዕቃዎች መሟላት አለባቸው የሚል ችግር ቢያጋጥማቸውም ይፈታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የእኛ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ኳሊቲው (ጥራቱ) የትምህርት አሰጣጡ ካሪኩሌም የሚቀረፀው በ1919 ዓ.ም በተመሠረተውና ዕድሜ ጠገብ በሆነው
ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት አቶ አቤቱ፣ ከሚያስተምራቸው 11 ኮርሶች ስምንቱን መምህራን ከአሜሪካ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ መጥተው እንደሚያስተምሩ፣ ሦስት ኮርሶች ብቻ እዚህ ባሉ መምህራን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ እኛ የምንደራደረው በጥራትና ጥራት ብቻ ነው፡፡
የምናስተምራቸውን ጥቂት ሰዎች በጥራት አውጥተን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እናደርጋለን ዩኒቨርሲቲው በትምህርት መረጃ መጻሕፍት የተሟላ መሆኑን አቶአቤቱ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ ቤተ መጽሐፍት የተጀመረው በእኛ ዩኒቨርሲቲን ነው፡፡ ዳታ ቤዙ አሜሪካ ሆኖ ተማሪዎች እዚህ ተቀምጠው የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ነው የሚጠቀሙት፡፡ መጽሔትና ጋዜጦችን  ጨምሮ የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት መጠቀም ይችላሉ፡፡ ከአሜሪካ የሚመጡ መምህራን በኢንተርኔት ከራሳቸው መጻሕፍት ነው የሚያስተምሩት፡፡ የእኛ
ዩኒቨርሲቲ መምህራን ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ትምህርታቸው እንደዚህ አገር መምህራን በንድፈ ሐሳብ (ቲዮሪ) ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ቢዝነስ ላይ ያሉና ሕይወታቸውን እየኖሩበት ያለውን ልምድ ነው የሚያስተምሩት፡፡ ለምሳሌ በምረቃው ላይ የተገኙት የባለአደራ ቦርዱ
ሊቀመንበር የህክምና ዶክተር (አንኮሎጂ- የካንሰር ስፔሻሊስት) ናቸው። ነገር ግን እዚህ ሲመጡ የሚያስተምሩት የ200 ሆስፒታሎች ኃላፊ ስለሆኑ ሊደርሺፕና ኮሙኒኬሽን ነው››  በማለት አብራርተዋል፡፡  ለአንድ አገር እድገትና ለውጥ ትምህርት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ቁጥር ሳይሆን በጥራት ሲሰጥ ነው የተፈለገው ራዕይ እውን የሚሆነው ይላሉ - አቶ አቤቱ፡፡ ‹‹ የእኛ የወደፊት ዕቅድ ከመዋዕለ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ዲግሪና ዶክትሬት ድረስ ከስር መሰረቱ ኮትኩቶ ማውጣት ነው፡፡
የእኛ ዕቅድ እንደ ሀርቫርድና እንደ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ከሥር ከመሰረቱ ኮትኩቶ ማውጣት ነው፡፡ ፐሮፖዛል አስገብተን የመሬት ጥያቄም አቅርበናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከአሜሪካ- ሳንፍራንስኪስኮ ከሪችሞንድ ከተማ ሳንቴ የተባለ ሬስቶራንት ባለቤት ወ/ሮ መንበረ አክሊሉ በሊንከን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኃላፊዎች ጋባዥነት ተገኝታ፣ የስኬት ታሪኳን ለተመራቂዎች ተናግራለች፡፡ በሌላ በኩል ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ተሰማርተው ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉት ለአቶ ብዙአየሁ ታደለ፣ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል፡፡ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ባሳለፋቸው ስድስት ዓመታት ብዙ ችግሮችን ቢያጋጥሙትም ዋናው ችግር ቢሮ ክራሲው መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ኤጀንሲ የሚባለው ድርጅት ገምጋሚ ብቻ ሳይሆን ተገምጋሚም ነው ለእኔ፡፡ በድንገት መጥተው የሚጠይቁት የዛሬ 30 እና 40 ዓመት የሚሠራበትን ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ በዋይ ፋይ ዘመን ላይ እያለን፣ የግድ ገመድ ያለው ኮምፒዩተር ማሳየት የለብንም፡፡ ኔትወርኩ የታለ? በማለት ይጠይቃሉ›› ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚጠይቀው ክፍያ ወደድ እንደሚል አቶ አቤቱ ያምናሉ፡፡ ‹‹እኛ የምናስተምረው የርቀት (non-distance) አይደለም፡፡ በክፍል ውስጥ ከተማሪዎች ጋር ፊት ለፊት (non-Distance) ነው፡፡ ስለዚህ መምህራኑ ከአሜሪካ ሲመጡ የአውሮፕላን ይከፈላል፣ ክፍል ገብተው የሚያስተምሩበት የአበል ብቻ 1400-1500 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ሌላው ክፍያውን የሚያንረው የማስተማሪያ ሕንፃው ኪራይ ነው፡፡ ለሕንፃው ኪራይ የሚከፈለው 85 ሺ ብር ቢቀር፣ በእርግጠኝነት የተማሪዎች ክፍያ ይቀንሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደሩ ይህን ችግር ተግዝቦ ሕንፃ መሥሪያ ቦታ ቢሰጠን፣ ወደፊት የተማሪዎች ቁጥር ስለሚጨምር፣ የትምህርት ክፍያውም ይቀንሳል›› በማለት አስረድተዋል፡፡

እነሆ መፅሐፍት መደብር፣ ሊትማን ቡክስ እና ክብሩ መፅሐፍት መደብር በመተባበር “መፅሐፍን እንደ መሰረታዊ ፍላጎት” በሚል መሪ ቃል፣ በየወሩ መጨረሻ በሚያካሂዱት የመፅሐፍት አውደ ርዕይና የሂስ ጉባኤ፣የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ፣ “አዙሪት” በተሰኘው የደራሲ ነገሪ ዘበርቲ ልብወለድ መፅሐፍ ላይ ሂስ ይቀርባል፡፡ ሥነ ጽሁፋዊ ሂሱንየሚያቀርበው ደራሲና የፊልም ባለሙያ ዳንኤል ወርቁ እንደሆነ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገልፀዋል፡፡“ትራኮን የመፅሐፍት አውደ ርዕይና የሂስ ጉባኤ” በየወሩ መጨረሻ ቅዳሜና እሁድ በትራኮን ታወር የሚካሄድ ሲሆን የመፅሐፍት እቁብን ጨምሮ ከገበያ የጠፉ መፅሐፍትንና አዳዲሶችን ከ20 እስከ 50 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለሽያጭ ይቀርቡበታል፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት አገራት ስደተኞች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ከሰሞኑ ያስተላለፉትን ውሳኔ በማውገዝ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተደረጉ ተቃውሞዎችን እንደሚደግፉ ማስታወቃቸውን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ኦባማ በቃል አቀባያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ መልኩ በህዝቦች ላይ የሚደረግን አድሎአዊ አሰራር እንደሚቃወሙ ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ትራምፕ ያስተላለፉትን ውሳኔ በመቃወም አደባባይ የወጡ ዜጎችን ድርጊት እንደሚደግፉ መግለጻቸውንም አብራርቷል፡፡ ኦባማ መንበረ ስልጣኑን ለትራምፕ ካስረከቡ ወዲህ በአዲሱ አገዛዝ ላይ ትችታቸውን ሲሰነዝሩ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የሰሞኑ የትራምፕ ውሳኔ ኦባማ ከአምስት አመታት በፊት ኢራቃውያን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጥለውት ከነበረው የእገዳ ውሳኔ ጋር መነጻጸር እንደሌለበት ቃል አቀባዩ ይፋ ያደረጉት መግለጫ ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
ፎክስ ኒውስ በበኩሉ፤ በአገራቱ ላይ የተወሰደው እርምጃ በኦባማ የስልጣን ዘመን የተጀመረና ህጋዊ እውቅና የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ፣ ሰባቱ አገራት ለአሜሪካ የደህንነት ስጋት መሆናቸው ተጠቅሶ፣ የአገራቱ ዜጎች ላይ የተለየ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚደነግጉ ህጎች በ2015 እና በ2016 መውጣታቸውን ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ አሜሪካ የወሰደቺው እርምጃ የተመድን መሰረታዊ መርሆዎች የጣሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ትራምፕ በሰባቱ አገራት ስደተኞች ላይ የጣሉትን እገዳ በአፋጣኝ እንዲያነሱ ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት መልእክት ጠይቀዋል፡፡ ሽብርተኞች ወደ አገራት ሰርገው ገብተው አደጋ የመፍጠር ዕድላቸው አሳሳቢ ስጋት መሆኑን የጠቆሙት ጉቴሬስ፤ ይሄም ሆኖ ግን ትራምፕ የወሰዱት እርምጃ አሜሪካንም ሆነ ሌሎች አገራትን ከመሰል ስጋት ለመጠበቅ የሚያስችል ሁነኛ አማራጭ አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት የአለማችን አገራት ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያሳለፉት የእገዳ ውሳኔ እንዳስደሰታቸው አይሲስ እና አልቃይዳን ጨምሮ የተለያዩ ጂሃዲስት ቡድኖች ማስታወቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
“ትራምፕ በአብዛኛው ሙስሊም ህዝብ ያላቸው የኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶርያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና የመን ዜጎች ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ፣ ከዚህ ቀደም እንደተናገርነው አሜሪካ ከእስልምና ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉ በተለያዩ ድረገጾች በኩል ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ማስታወቃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የትራምፕን የስደተኞች ውሳኔ የተቃወሙ 1.7 ሚሊዮን ያህል እንግሊዛውያን፣ በእንግሊዝ ሊያደርጉት ያቀዱት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ፊርማ ያሰባሰቡ ሲሆን በተቃራኒው የትራምፕን ጉብኝት በመደገፍ፣ ፊርማቸውን ያሰባሰቡ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥርም ከ200 ሺህ በላይ መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ይህን ተከትሎም የእንግሊዝ ፓርላማ በጉዳዩ ዙሪያ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለመከራከር ቀጠሮ መያዙንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ላለፉት 33 አመታት ከአፍሪካ ህብረት አባልነቷ ተገልላ የቆየቺው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው 39ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በተደረሰው ውሳኔ መሰረት ወደ አባልነቷ መመለሷን ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የህብረቱ አባል አገራት ከምዕራባዊ ሰሃራ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ ባለፈው ማክሰኞ ጠንከር ያለ ክርክር ካደረጉ በኋላ በደረሱት ስምምነት ሞሮኮ 55ኛዋ የህብረቱ አባል ሆና ዳግም እንድትቀላቀል ወስነዋል፡፡
“በስተመጨረሻም ወደ ቤታችን ተመልሰናል” ብለዋል የሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ ስድስተኛ፣ ህብረቱ አገሪቱ ወደ አባልነቷ እንድትመለስ መወሰኑን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፡፡ ሞሮኮ ዳግም የህብረቱ አባል ለመሆን ባለፈው አመት ሃምሌ ወር ላይ ባቀረበቺው ጥያቄ መሰረት፣ በህብረቱ አባል አገራት በተሰጠ ድምጽ ወደ አባልነቷ መመለሷ የተነገረ ሲሆን አገሪቱ ከሶስት አስርት አመታት በኋላ ወደ ህብረቱ አባልነቷ ለመመለስ ጥያቄ ማቅረቧ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማድረጓን ያሳያል ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ1984  የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሞሮኮ ስር ትተዳደር ለነበረቺው ምዕራባዊ ሰሃራ፣ ራሷን የቻለች አገር ሆና መቀጠል የምትችልበትን እውቅና መስጠቱን ተከትሎ፣ ሞሮኮ ከህብረቱ አባልነቷ መውጣቷንና ለ33 አመታት ያህል ብቸኛዋ የአፍሪካ ህብረት አባል ያልሆነች አፍሪካዊት አገር ሆና መቆየቷን ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውሷል፡፡