Administrator

Administrator

 አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባለፈው የአገሪቱ ምርጫ፣ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙ እንዲጣራ የሚያደርግ ትዕዛዝ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሁለት ግዛቶች በመራጭነት የተመዘገቡ አሉ፣ ህጋዊ ያልሆኑ መራጮች ተመዝግበዋል፣ በህይወት የሌሉ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል የሚሉትን ጨምሮ ከመራጮች ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ መጭበርበሮችን እንዲጣራ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በምርመራው የተገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም፣ የአገሪቱን የምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስርዓት የምናስተካክል ይሆናል ብለዋል ትራምፕ፡፡
ትራምፕ ተፈጽሟል የተባለውን መጭበርበር አጣራለሁ ይበሉ እንጂ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የምርጫ ሃላፊዎች በምርጫው ሂደት መጭበርበር መፈጸሙን የሚያመለክቱ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃዎች አለመቅረባቸውን ሲናገሩ መቆየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን መግለጫ ያወጡት ባለፈው ማክሰኞ በተደረገው የዋይት ሃውስ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቃል አቀባዩ ሻን ስፓይሰር፤” በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች በምርጫው ድምጻቸውን ሰጥተዋል” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ ትራምፕ የምርጫው ሰሞን ጀምሮ መጭበርበር መፈጸሙን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሲገልጹና “በምርጫው አምስት ሚሊዮን ያህል ህገ-ወጥ መራጮች ለሄላሪ ድምጻቸውን ሰጥተዋል” የሚል ክስ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሶ፣ ይህን ክሳቸውን የሚደግፍ ምንም አይነት ማረጋገጫ አለማቅረባቸውን ዘግቧል፡፡

   ኢትዮጵያ በሙስና ከ176 የአለማችን አገራት 68ኛ ደረጃን ይዛለች

     ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ አመታት በሙስና ክፉኛ በመዘፈቅ አለምን ስትመራ የዘለቀቺው ሶማሊያ፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016ም ቀዳሚነቷን ማስጠበቋን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም አስታውቋል፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የአመቱ የዓለማችን የሙስና ሁኔታ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ጥናቱ ከተሰራባቸው የአለማችን 176 አገራት በሙስና 68ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ጠቁሟል፡፡
ተቋሙ በአለማችን ከፍተኛ ሙስና የተንሰራፋባቸው አገራት በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፡- ደቡብ ሱዳንና ሰሜን ኮርያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ያገኙ ሲሆን  ሶርያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ጊኒ ቢሳኦ እና ቬንዙዌላ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የዓለማችን 176 አገራት መካከል ዴንማርክና ኒውዚላንድ እጅግ አነስተኛው ሙስና የሚታይባቸው ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ ፊንላንድና ስዊድን በሁለተኛና በሶስተኛነት መቀመጣቸውን ገልጧል። አነስተኛ ሙስና ያለባቸው የአለማችን አገራት ተብለው የተዘረዘሩት ቀሪዎቹ አገራት ደግሞ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ሲንጋፖር፣ ኒዘርላንድስ፣ ካናዳና ጀርመን ናቸው፡፡
ሙስና መጠንና ስፋቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም የአለማችን አገራት እንደሚታይ ያስታወሰው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፤ በርካታ የአለማችን አገራት ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በ2016 መሻሻል ከማሳየት ይልቅ የባሰ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

 የወቅቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ እና የማይክሮሶፍት መስራቹ አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ፣ በመጪዎቹ 25 አመታት ጊዜ ውስጥ የአለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ የጥናት ውጤት አመለከተ፡፡
የቢልጌትስ ሃብት በፍጥነት እያደገ መሄዱ ከቢሊየነርነት ወደ ትሪሊየነርነት ያሸጋግራቸዋል ቢባልም፣ በመዝገበ ቃላት ውስጥ ግን ትሪሊየነር የሚባል ቃል እስካሁን እንዳልሰፈረ ተዘግቧል። ኦክስፋም ኢንተርናሽናል ይፋ ያደረገው ይህ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ እ.ኤ.አ ከ2009 አንስቶ የሃብት መጠናቸው በአማካይ በ11 በመቶ እያደገ እዚህ የደረሰው ቢል ጌትስ፣ እድገቱ በዚሁ መጠን እየጨመረ ከቀጠለ እድሜያቸው 86 አመት ሲሞላቸው፣ የአለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 የቢል ጌትስ የሃብት መጠን 50 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የዘገበው ፎርብስ፤ በአስር አመታት ጊዜ ውስጥ የተጣራ ሃብታቸው ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016 ላይ 84.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም ገልጧል፡፡

  በተለያዩ ድረገጾች የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ዕቅድ አለው የሚል መረጃ በስፋት ሲሰራጭበት የከረመው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ መረጃው ሃሰተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ዙክበርግ በቅርቡ ባልተለመደ ሁኔታ ፖለቲካ ቀመስ አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ፣ ወደ ፖለቲካው አለም የመግባትና ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንዳለው የሚጠቁሙ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ መሰንበታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ግለሰቡ ግን ሰሞኑን ከአንድ ድረገጽ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ መረጃውን ማስተባበሉን ዘግቧል፡፡
“የሚወራው ነገር ሃሰት ነው፡፡ እኔ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ የለኝም፡፡ ሙሉ ትኩረቴን የማደርገው የፌስቡክን ማህበረሰብ በመገንባትና ከባለቤቴ ጋር ባቋቋምነው ቻን ዙክበርግ ኢኒሺየቲቭ የተሰኘ ድርጅት አማካይነት የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራት ላይ ነው” ብሏል ዙክበርግ፡፡
ዙክበርግ ለፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንደሌለው ያስታውቅ እንጂ፣ ወደ ፖለቲካ የመግባትም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የመስራት እቅድ ይኑረው አይኑረው በግልጽ ያለው ነገር እንደሌለ ዘገባው ገልጧል፡፡
ዙክበርግ ፕሬዚዳንት የመሆን እቅድ አለው የሚለውን ጭምጭምታ ያጠናከረው ደግሞ፣ የፌስቡክ ኩባንያ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በቅርቡ ባደረገው ማሻሻያ፣ ዋና ስራ አስፈጻሚው በፖለቲካዊ ምርጫ የመወዳደር መብት እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ ማስተካከሉ ነው ተብሏል፡፡

 አለማቀፉ ማህበረሰብ እየጨመረ ለመጣው የናይጀሪያ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ በመጪዎቹ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ 90 ሺህ ያህል የአገሪቱ ህጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል፡፡
በአገሪቱ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ተገቢውን ድጋፍ ባለማግኘት በአለማቀፍ ደረጃ ቀዳሚው እንደሆነ ያስታወቀው ተቋሙ፤አሸባሪው ቡድን ቦኮ ሃራም ከሚያደርሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ስደቶችና መፈናቀሎች የአገሪቱን 450 ሺህ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጠቂ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁሞ፣ ተገቢው ድጋፍ ካልተደረገ በመጪዎቹ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በየቀኑ በአማካይ 240 ህጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ቦኮ ሃራም በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው የሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰባት ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ከአነዚህ የአገሪቱ ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት እንደሆኑም አመልክቷል፡፡
የምግብና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችና ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ ቢሄድም፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ ተገቢ ምላሽ አልሰጠም ያለው ዩኒሴፍ፤መንግስታትና ለጋሾች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ በዓል ቀን፣ ባልና ሚስት አንድ እንግዳ ይመጣባቸዋል፡፡ የከበደ እንግዳ! ዶሮ ወጥ ተሰርቷል፡፡ በግ ታርዷል፡፡ ቤቱ በዓል በዓል ይሸታል፡፡ ስኒ ረከቦቱ ላይ ተደርድሯል፡፡ እጣኑ ቦለል ቦለል ይላል፡፡
እንግዳውና ቤተሰቡ ግብዣውን ለመብላት አኮብኩበዋል፡፡
ራቱ ተጀመረ፡፡ በመካከል “እ!እ!እ!” የሚል የትንሽ ልጅ የለቅሶ ድምፅ ይሰማል፡፡
እንግዳው፣
“ምንድን ነው ይሄ የሚሰማው ድምፅ?” ሲል ጠየቀ፡፡
አባት፤
“አይ፣ የእኛ ልጅ ነው ተወው” አለ፡፡
እንግዳውም፤
“እንዴት እተወዋለሁ? በዓመት በዓል እንዴት ከቤተሰቡ ይለያል? የት ነው ያለው አሳዩኝ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡
እንግዳው፤
“እንዲያውም አልበላም” አለ፡፡
“ና ላሳይህ” ብሎ ወደ ጓዳ ወሰደው፡፡
ልጁ፤ ቆጡ ላይ ታስሯል፡፡
እንግዳው በጣም አዘነ፡፡
“ምን አድርጎ ነው እንዲህ ዓይነት ቅጣት የፈፀማችሁበት?”
አባት፤
“ምንም አላደረገም፣ ግን ከልምድ እንደምናውቀው፣ ከእንግዳ ጋር ገበታ ከቀረበ እጁ ባለጌ ነው!
ከእንግዳ ፊት ብድግ ያደርጋል፡፡ ብትቆጣውም አይሰማም” አለ፡፡
እንግዳው፣
“ኧረ በጣም ነውር ነው፡፡ ግዴለም፤ ይምጣ፣ ይምጣ፡፡ እናስተምረዋለን፤ ሥነ ስርዓት፡፡” አለና አግባባቸው፡፡
ልጁ ተፈቀደለትና ከእስር ተፈታ፡፡ ከቆጡ ወረደና ገበታ ቀረበ፡፡
የዶሮ ብልት በፈርጅ በፈርጁ ይቀርብ ጀመር፡፡
ልጁ ዕውነትም አደገኛ ኖሯል፡፡
እንግዳው ፊት የቀረበውን ሁለት የዶሮ እግር በተከታታይ እያነሳ ነጨ! ከዚያ የአባቱን የፈረሰኛ ብልት አነሳ! ይሄኔ ግራ የተጋባችው እናት በቁጣ፤
“ይሄን እንዲች ብለህ እንዳትነካ፤ ነግሬሃለሁ!” ብላ ለእንግዳው ሌላ ብልት ስታቀርብ፤ ልጁ ይሄ ሊመልሰው ነው? እጁን ሰደደ፡፡ ይሄኔ እንግዳው የልጁን እጅ ቀብ አድርጎ፣ ፈጥኖ አጠንክሮ ያዘና፤ ወደ ባለቤቶቹ ዞሮ፤ “እንግዲህ፣ ሸብ አድርጉልኝ ይሄን ልጅ!” አለ፡፡ ልጁም ከሶስት የዶሮ ብልት በኋላ፣ ሸብ ተደርጎ፣ ተመልሶ ቆጡ ላይ ሰፈረ!
*          *        *
ልማድ የልጅነት አባዜ አለው፤ አድጎ ተመንድጎም ራሳችን ላይ ፎቅ ሊሰራብን ይችላል። መላቀቅ ያለብን ብዙ ልማድ አለ! ይሄ ከባህላችን፣ ከማህበራዊ ኑሯችን፣ ከፖለቲካችንና ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ ስነ ልቦናዊ ግንኙነቱም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ ይሄን ወደ አገር ጉዳይ መንዝሮ ማየት ጉዳዩን በሚገባ መሰረት ያበጅለታል፡፡ እየተዘወተሩና እየተለመዱ የሚመጡ የአገራችን ጉዳዮች ውለው አድረው፣ ጎልበተው መታየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ትናንሽ ዕቅዶች ወደ ትላልቅ ፈቅዶች የሚያድጉት ትናንሾቹ በአግባቡ ሲፈፀሙ ነው፡፡ ለዚያ የጊዜ ስሌት፣ የዝርዝር አያያዝና የቁጥጥርና ግምገማ ሥርዓት በአግባቡ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ይህን ፈፃሚውና አስፈፃሚው አካል፣ የራሱ አቅልና ብስለት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የራስ አመለካከት ከአገር አመለካከት ጋር ይራራቅና ጣጣ የሚያመጣው፡፡ እያንዳንዱን ሰው ቀርፆ፣ ሰው ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ይህን የሚሠሩ ተቋማት እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ለዚህ ብሩህ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የሲቪል ማህበራት ቁጥርም፣ አቅምም በጣም ውስን ነው፡፡ ይህ የሆነው ፋይዳቸውን ከልቡ ያመነበት ወገን ባለመኖሩ ነው፡፡ ጊዜም ባይኖር ጊዜ ወስዶ፣ ለጥያቄው መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አማካዩ መንገድ ይሄው ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚው ድርድር ባሻገር የህዝብን አስተሳሰብ የሚያሰባስብ፣ ወደ ተግባር እንዲያመራም የሚያግዝ ኃይል ያስፈልጋል፡፡
‹‹ከእናንተ ሌላ እኛም አለንኮ›› የሚል የህብረተሰብን ክፍል ማን ይታደገው ማለት አለብን፡፡ በጥቁርና በነጭ መካከል ያለውን ግራጫ መስመር፣ ስፋቱን ስለማንገነዘብ ጠቀሜታውም የዚያኑ ያህል ይሳሳብናል፡፡ ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ፣ ለአንድ ዓመት አይነግሥ›› የሚለው አባባል፣ አበው ያለ ነገር አላሉትም፡፡ ለአመራሩ፣ ለገዢው ክፍል፣አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ በእርግጥ አማካሪ ሲባል በዕውቀት የረቀቀ፤ በልምድ የበለፀገና  ጊዜ ያስተማረው ሊሆን ይገባል! መንግሥት ሲቸኩል የሚያለዝበውም፣ ሲጠጥር የሚያልመው፤ ግትር ሲል የሚያላላው፣ አይዞህ ባይም፣ ገሳጭም፣ ነው የሚያሻው፡፡ የጥንት የጠዋቱ ገጣሚ ገሞራው፤ እንዳለው፡- ‹‹…ነገሩ አልሆን ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
 ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…›› የሚሉ በሳሎች ያስፈልጋሉ፡፡ በመደራደር ብዙ መንገድ መሄድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንድ ዕውነት መረሳት የለበትም፡፡ ማናቸውም ወገን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ገና ሶስተኛም ወገን ተጨምሮ አይበቃም ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው። ጉዳዩን መሠረታዊ የሚያደርገው የሀገራችን ችግር ስፋት ነው፡፡ የፍትሕ መጓደል፣ የዲሞክራሲ አለመብሰል፣ የሀብት አለመደላደል፣ የተቋማት ሥርዓት አለመሻሻል፣ መልካም አስተዳደር አለመታደል፣ ያልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ አጥተው መንሳፈፍ፣ ወዘተ ምኑ ቅጡ! ለዚህ ነው አገር ሙሉ ድርጅት ቢፈጠር እንኳ የአገር ቋት አይሞላም የምንለው!
እነዚህ ሁሉ በቅጡ ቢሰባሰቡና ኢኮኖሚውን ካቀረቀረበት ቢያቀኑት ድንገት ፎቀቅ እንል እንደሁ እንጂ ነገረ-ሥራችን እንኳ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነብን መቸገራችን የዕለት የሠርክ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ተራው ዜጋ ‹‹የምበላው ሳጣ፣ ልጄ ጥርስ አወጣ›› ቢል አይፈረድበትም! ኑሮው ከሥረ-መሠረቱ እናሻሽልለት! በዓል በመጣ ቁጥር የሚሰቀቀው አያሌ ነው! የእኛን መጥገብ ብቻ አንይ!! ይህንን ተደራዳሪዎቹ ወገኖች፣ እነሆ ወቅቱ መጥቷልና በምን መቀነቻ አጥብቀን እንያዘው ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ፀፀታችንን ሳይሆን ነገርአችንን እናስብ! የመሪዎችን ጉባኤ ስናስብም የአገራችንን መረጋጋት እንፈይድ!! 

Sunday, 29 January 2017 00:00

የዘላለም ጥግ

(ዝነኞች በመሞቻቸው ሰዓት)
‹‹መጋረጃውን አውርዱት- ቧልቱ አብቅቷል››
ፍራንሶይስ ራቤላይስ (ፈረንሳዊ ፈላስፋና ኮሚክ)
“ዕድሜህን ሙሉ ሳትፀልይ በመጨረሻ ሰዓት መፀለይ ዋጋ የለውም!››
ኢታሎ ስቬቮ (አይሁዳዊ ደራሲ)
‹‹መኖር እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ልሰራቸው የምፈልጋቸው ጥቂት ነገሮች አሉ››
አኔዩሪን ቤቫን
 (በመጨረሻ የህመሙ ሰዓት የተናገረው)                      
‹‹እግዚአብሄር ይቅር ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ሥራው ነው››
ሔይንሪክ ሄይን
‹‹የደስታ ዘመኔ አክትሟል››
 (ጄምስ ዲን
የመኪና አደጋ ሊደርስበት ሲል የተናገረው)
‹‹ስንት ሰዓት ነው? ተዉት፡፡ አስፈላጊ አይደለም..››
ጃኖስ አራኒ  (ሃንጋሪያዊ ገጣሚ)
‹‹እንደ ፈላስፋ ኖሬአለሁ፤እናም እንደ ክርስትያን እሞታለሁ››
ኒያኮም ካሳኖቫ (ጣልያናዊ ጀብደኛና ደራሲ)
“ወደ ትውልድ ስፍራዬ ውሰዱኝ። የተወለድኩት ደቡብ ነው፡፡ መሞትና መቀበር የምሻውም ደቡብ ነው”
ቡከር ቲ. ዋሺንግተን
“ደህና ሁኚ … ከተገናኘን …”
ማርክ ትዌይን (ለሴት ልጁ ለክላራ የተናገረው)
(አሜሪካዊ ደራሲ)
“በመንግስተ ሰማያት ስዕል እንደሚኖር፣ በሙሉ ልቤ ተስፋ አደርጋለሁ”
ዣን-ባፕቲስቴ- ካሚሌ ኮሮት (ፈረንሳዊ ሰዓሊ)
“ቡና ስጡኝ፤ ልፅፍ ነው”
ኦላቮ ቢላክ (ብራዚላዊ ገጣሚ)
“ሚላን፡ ለመሞት እንዴት ያለ ውብ ሥፍራ ነው”
ጆን ካራዲን (አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ)
“ከእናንተ ውስጥ ለሰይጣን መልዕክት ያለው ካለ፣ ለእኔ ይስጠኝ፤ አሁን ላገኘው መሄዴ ነው”
ላቪና ፊሸር (በነፍስ ማጥፋት በስቅላት የተቀጣች)
“እዚህ ህመም ይሰማኛል”
ቻርልስ ደ ጎል (የፈረንሳይ መሪ)

ፍንዳታው ያስከተለው ክስተት ለጨው አምራቾች ስጋት፣ ለቱሪስቶች መስህብ ሆኗል
ከቀድሞው የበለጠ አዲስ የቀለጠ አለት ሃይቅ ተፈጥሯል

በኣፋር ክልል የሚገኘው የኤርታሌ የቀለጠ አለት ሃይቅ ባልተለመደ መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ በመንተክተክና ሃይለኛ ፍንዳታ አስከትሎ፣ ከቀድሞው የበለጠ አዲስ የቀለጠ አለት ሃይቅ በመፍጠር በሁሉም አቅጣጫ በፍጥነት መፍሰስ መጀመሩን “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ድረገጽ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ኤርታሌ ከዚህ በፊትም እየተንተከተከ መጠኑን በመጨመር፣ ለሁለትና ለሶስት ቀናት ከፍና ዝቅ ይል እንደበር፤ አልፎ አልፎም ከጉድጓዱ ወጥቶ በመፍሰስ፣ ተመልሶ ወደነባሩ ሁኔታው ይመለስ እንደነበር  ያስታወሰው ዘገባው፣ ከሰሞኑ ግን ያልተለመደ ከፍተኛ ፍንዳታና ፍሰት መፍጠሩን ገልጧል፡፡
“በኦሪጅንስ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል” የቱር የኦፕሬሽን ማናጀር የሆኑት የስነ-ምድር ባለሙያው አቶ እንቁ ሙሉጌታ በተለይ ለአዲስ አድማስ ትናንት እንደገለጹት፣ ከጥቅምት መጨረሻ አንስቶ ለተራዘመ ጊዜ ከነባሩ ጉድጓድ እስከ አስር ሜትር ከፍታ በመውጣትና በመውረድ፣ አልፎ አልፎም ከጉድጓዱ አልፎ ሲፈስ የቆየው ኤርታሌ፣ ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም ግን ባልተለመደ ሁኔታ ተፈጥሮውን ቀይሮ፣ ከፍተኛ ፍንዳታ በመፍጠር ብዛት ያለው የቀለጠ አለት በሁሉም አቅጣጫ መፍሰስ ጀምሯል፡፡
ይህ አዲስ ክስተት ከቀለጠ አለቱ የፍሰት ፍጥነት፣ መጠንና ከአለቱ የመረጨት ወሰን አንጻር እጅግ ያልተመለደና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት አቶ እንቁ፣ ኤርታሌ እስከ 20 ሜትር ከፍታ እየዘለለ በመረጨት፣ በሰከንድ 50 ሜትር ኪዩብ የቀለጠ አለት እያወጣ በሁሉም አቅጣጫ በሰዓት 55 ኪሎ ሜትር ፍጥነት መፍሰሱንና 3 ሜትር ውፍረት ያለው ይህ የአለት እሳት ወንዝ በአራት ቀናት ቆይታው ጉድጓዱ እስከ 700 ሜትር ርቆ መጓዙን ተናግረዋል፡፡
ክስተቱ ለአራት ቀናት ያህል በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በኋላ፣ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ደቡብ አቅጣጫ “አቶሚክ ኤክስፕሎሲቭ” የተባለ ሃይለኛ ፍንዳታ መፍጠሩን የጠቆሙት አቶ እንቁ፣ ይሄን ተከትሎም በኤርታሌ የነበሩት ሁለት የቀለጠ አለት ሃይቆች በመካከላቸው ሰፊ ስንጥቅ በማስከተል ሌላ አዲስ የቀለጠ አለት ሃይቅ ጉድጓድ መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
አዲስ የተፈጠረው ጉድጓድ ከነባሮቹ በስፋቱ የበለየና ብዛት ያለው የቀለጠ አለት የያዘ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፤ ከአዲሱ ጉድጓድ እየገነፈለ በየአቅጣጫው ለቀናት ሲፈስ የቆየው የቀለጠ አለት ከትናንት በስቲያ መብረድ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎች መሰል ተፈጥሯዊ ክስተቶች ከሚታዩባቸው አካባቢዎች ሰዎች በ150 ኪ.ሜትር ያህል መራቅ እንዳለባቸው ይመከራል ያሉት ባለሙያው፣ የአፍዴራ የጨው ማምረቻ ከኤርታሌ በ50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው፣ ተመሳሳይ ሁለት እና ሶስት ክስተቶች ቢከሰቱ በጨው አምራቾች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከኤርታሌ በሌላ አቅጣጫ እስከ 50 ኪ.ሜትሮች ርቀው በሚገኙ ትንንሽ የአፋር መንደሮች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም፣ የአደጋ ስጋት ክልል ውስጥ በመሆናቸው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
ይህ ክስተት ለጨው አምራቾችና ለአካባቢው ነዋሪዎች ደህንነት ስጋት ቢሆንም፣ ለቱሪዝሙ ግን አዲስ ተጨማሪ መስህብ መፍጠሩ ተነግሯል፡፡  በርካታ አለማቀፍ የቱሪዝምና የተፈጥሮ ክስተቶችና አደጋዎች ላይ የሚሰሩ ድረ-ገጾችና ተቋማት ያልተመለደውን የሰሞኑ የኤርታሌ ክስተት በስፋት መዘገባቸውን ተከትሎ፣ ወደ አካባቢው የሚያቀኑና ለመጎብኘት ያቀዱ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ የሆነውና በአብዛኛው ከመስከረም እስከ መጋቢት ባሉት ወራት በቱሪስቶች የሚጎበኘው  ኤርታሌ፣ በእነዚህ ወራት በቀን በአማካይ እስከ 40 በሚደርሱ ቱሪስቶች እንደሚጎበኝ ይገመታል፡፡

ከደረጃ ዝቅ የተደረጉ፤ ከሥራና ደመወዝ የታገዱና የተሰናበቱ ይገኙበታል
የዋና ሥራ አስኪያጁ አካሔድ የፓትርያርኩን መመሪያ የጣሰ ነው፤ ተብሏል
    ከሚገባቸው በላይ የሰው ኃይል ክምችት በመያዝ እየተጨናነቁ በሚገኙት የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት፣ የሚካሔደው የሓላፊዎችና የሠራተኞች ዝውውር እንዲሁም ከሥራ የማገድና የማሰናበት ርምጃ በአስቸኳይ እንዲጣራ፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አዘዙ፡፡
ፓትርያርኩ ትእዛዙን የሰጡት፣ በመ/ር ጎይትኦም ያይኑ ዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ከሕግና ሥነ ሥርዓት ውጭ የአስተዳደር በደል አድርሶብናል፤ የሚሉ የሃያ አመልካቾችን አቤቱታ፣ በአካልና በጽሑፍ ከተቀበሉ በኋላ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል በጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡
ከአስተዳዳሪነት ጀምሮ ባሉት የጽ/ቤት ሓላፊነቶች የሚሠሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፦ ደመወዝ፣ አበልና የሥራ ደረጃን በሚቀንስ እንዲሁም፣ የተዛወሩበትን የሥራ መደብ፣ ደመወዝና አበል በማይጠቅስ ውሳኔ ተገቢ ያልሆነ ዝውውር ተፈጽሞብናል፤ ባልተጣራና ባልተወሰነ የሥራ ግድፈት ከሥራና ደመወዝ እንድንታገድና እንድንሰናበት በማድረግ በደል ደርሶብናል፤ በሚል ማመልከታቸውንና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ልዩ ጽ/ቤቱ በደብዳቤው ገልጿል፡፡
ሠራተኞቹ፣ ከአንዱ አጥቢያ ወደ ሌላው እንዲዛወሩ፤ ከሥራና ደመወዝ እንዲሰናበቱ የተደረገበት ማስረጃ ተገቢነት፣ ካቀረቡት አቤቱታና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋት አንፃር እየተገናዘበ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ እንዲመረመር ፓትርያርኩ አዘዋል፤ አፈጻጸሙም፣ ሕጋዊውን አሠራር ያልተከተለ ኾኖ ሲገኝ፣ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር በምልዓተ ጉባኤ አስተካክሎና አርሞ አፋጣኝ ውሳኔ በመስጠት፣ ውጤቱ በአስቸኳይ እንዲገለጽላቸው በመመሪያቸው ማሳሰባቸውንም ልዩ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
አቤቱታው፣ ባለፈው ኅዳር ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ቀርቦ የታየና ሀገረ ስብከቱ በሕጉ መሠረት አስቸኳይ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ አስቀድሞ የታዘዘበት ከመሆኑም በላይ፤ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ለሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርም ደርሶ በሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲያገኝ ሲጠየቅ መቆየቱ ተወስቷል፡፡
አቤት ባዮቹ፣ በተለይ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በጻፉት ደብዳቤ፣ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፥ ከሕገ ወጥ ዝውውር በተጨማሪ፣ የሙስና ተግባራትን እንደሚፈጽሙና ያለምንም ጥፋት ከባድ ማስጠንቀቂያ የጻፉባቸውም ይህን በመቃወማቸውና የመብት ጥያቄ በማንሣታቸው እንደኾነ በቅሬታቸው ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ አቤቱታውን የሚያጣራ ስምንት አባላት ያሉት ቡድን ባለፈው ማክሰኞ በዋና ሥራ አስኪያጁ ተቋቁሞ ጉዳዩን የሚመለከት ሰነድ በማስቀረብ ሲያጠና መቆየቱን የጠቀሱ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች፤ የማጣራቱ ውጤትም፣ ከትላንት በስቲያ በተካሔደውና ዋና ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ 11 የዋና ክፍል ሓላፊዎች በተገኙበት የአስተዳደር ጉባኤ ታይቶ ውሳኔ ማግኘቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ምንጮቹ እንደተናገሩት፣ ከኻያዎቹ አቅራቢዎች መካከል፣ ሦስት የአድባራት ጸሐፊዎች፣ በዝውውሩ የተቀነሰባቸው ደመወዝ ካለ ባሉበት እንዲስተካከል፤ ታቦት ታቅፈው ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ድረስ ይዘው በመምጣት ከፍተኛ ድፍረትና የቀኖና ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ከሥራና ደመወዝ በተሰናበቱ አንድ አለቃና ሦስት ሠራተኞች ላይ የተወሰደው የማሰናበት ውሳኔ ባለበት እንዲጸና፤ የተቀሩት 13 ሠራተኞችም፣ ይቅርታ እየጠየቁ በተገኘው ቦታ እንዲመደቡ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
በበርካታ የሰነድ ማስረጃዎች የተደገፈውን አቤቱታ ማጣራት የሚገባው፣ 14 አባላት ያሉት የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ እንጂ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ በራሳቸው መርጠው ያቋቋሙት ቡድን አለመኾኑን የሚጠቅሱ ወገኖች በበኩላቸው፤ አካሔዱ፣ የፓትርያርኩን መመሪያ እንደሚፃረር፤ በጥቅማጥቅምና በአቅም ማነስ የተሠሩ የጽ/ቤቱን ስሕተቶች ለመሸፋፈን የተደረገ ሙከራ በመሆኑ እንደሚቃወሙት ገልጸዋል፡፡  
በሕገ ቤተ ክርስቲያን በሰፈረው የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ መሠረት፣ በፓትርያርኩ የበላይ ሓላፊነት የሚመራው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፤ በእገሌ ሥራና በጀት እየተባሉ መዋቅርን፣ ዕውቀትን፣ ልምድንና በጀትን ማዕከል ባላደረጉ የዝውውር፣ ቅጥርና ሽግሽግ አሠራሮች ጋራ ተያይዘው በሚነሡ ውዝግቦች እየታወከ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብለትና ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ጠንካራ መዋቅርና አደረጃጀት እንዲዘረጋለት የተላለፉ ውሳኔዎች አፈጻጸምም መጓተቱን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የዛምቢያ መንግስት በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቴ ገብተዋል በሚል አስሯቸው የነበሩና በቅርቡ ይቅርታ ያደረገላቸውን 147 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከትናንት በስቲያ ወደ አገራቸው መመለሱን አስታውቋል፡፡
እነዚሁ 145 ወንድ እና 2 ሴት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ድጋፍ ባለፈው ሃሙስ ተሲያት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን፣ የአገሪቱ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ማስታወቁን ዥንዋ ትናንት ዘግቧል፡፡