Administrator

Administrator

    ነዋሪነቱ በአሜሪካ የሆነ አንድ የቴሌኮም ኢንጂነር ከሰሜን ኮርያ ከፍተኛ የመረጃ ተቋም ባገኘው ድንገተኛ መረጃ፣ በአገሪቱ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ድረ-ገጾች 28 ብቻ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ዘ ጋርዲያን ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙት ከእነዚህ ድረ-ገጾች አብዛኞቹ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃን ናቸው ያለው ዘገባው፤ድረገጾቹ የመንግስት ፕሮፓጋንዳዎችን ከማሰራጨት ያለፈ ፋይዳ እንደሌላቸውም ገልጧል፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ፤ ሰሜን ኮርያ ዜጎቿ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳይጠቀሙ መከልከሏን በመጥቀስ፣ በአገልግሎት ላይ ከሚገኙት ከእነዚሁ የአገሪቱ 28 ድረ-ገጾች መካከል አብዛኞቹ ዘገምተኛ ፍጥነት ያላቸውና ይዘታቸው ወቅቱን ጠብቆ የማይስተካከል እንደሆኑ ዘግቧል፡፡
በስራ ላይ ከሚገኙት የአገሪቱ ድረ-ገጾች መካከል አብዛኞቹ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ትርኪ ምርኪ የእለት ውሎዎች የሚያስነብቡ እንደሆኑ የገለጸው ዘገባው፤ሌላኛው ድረ-ገጽ ደግሞ የሰሜን ኮርያን ባህላዊ ምግቦች አዘገጃጀት የተመለከቱ መረጃዎችን የያዘ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

 - ተቃውሞውን ያስነሳው መንግስት የክፍያ ጭማሪ ማድረጉ ነው

     የደቡብ አፍሪካ መንግስት በመጪው አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ክፍያ እንደሚጨምር ማስታወቁን ተከትሎ ባለፈው ማክሰኞ ተማሪዎች ባደረጉት ተቃውሞ ውድመት መድረሱንና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውንን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት መስጠት አቁመው መዘጋታቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
“መንግስት በክፍያ ላይ ጭማሪ ማድረጉ አግባብ አይደለም”፣ #ትምህርት በነጻ ሊሰጥ ይገባል” በሚል በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ተቃውሞ ማድረጋቸውንና ብጥብጥ መከሰቱን ተከትሎ በተፈጠረው የጸጥታ ስጋት ሳቢያ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውን፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዘ ዊትዋተርስራንድ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያን የመሳሰሉ ተቋማት መዘጋታቸው ተነግሯል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ሰኞ በቀጣዩ አመት በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ክፍያ ላይ የ8 በመቶ ጭማሪ እንደሚያደርግ ማስታወቁን ያስታወሰው ዘገባው፤ይህ መግለጫ ያስቆጣቸው የአገሪቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ከማሰማት ባለፈ የዩኒቨርሲቲዎችን ንብረቶች በከፍተኛ ሁኔታ ማውደማቸውን ጠቁሟል፡፡  

የብሩንዲ መንግስት በዜጎቹ ላይ ግድያና አሰቃቂ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ እንደሚገኝ የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ በአገሪቱ ዳግም የዘር ማጥፋትና እልቂት ሊከሰት እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መርማሪዎችን ሪፖርት ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ የአገሪቱ መንግስትና ተላላኪዎቹ በዜጎች ላይ የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እያደረሰ የሚገኝ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የግርፋት፣ የጾታዊ ጥቃትና የእስራት ሰለባ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ የብሩንዲ መንግስት በዜጎች ላይ በሚፈጽመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ካላደረገና አለማቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን ለመፍታት ካልሰራ አገሪቱ ወደማትወጣው የጥፋት አዘቅት መግባቷ አይቀሬ ነው ብለዋል፤የተመድ ባለሙያዎች፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በሚያዝያ ወር 2015 ለሶስተኛ ጊዜ በምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞና ብጥብጥ መከሰቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትም ባለፈው ወር በአገሪቱ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ቡድን ማሰማራቱን ጠቁሟል፡፡
ቡድኑ ከ277 የአገሪቱ ዜጎችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅና ማጣራት፣ ብጥብጡ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺህ በላይ የሚገመቱ የአገሪቱ ዜጎች መገደላቸውንና ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑትም አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል ብሏል ዘገባው፡፡ የብሩንዲ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ዊሊ ኒያሚትዌ በበኩላቸው፤ ተመድ ያወጣውን ሪፖርት ፖለቲካዊ አንድምታ ያለውና በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ያልተመሰረተ በማለት እንዳጣጣሉት ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 በተጠናቀቀው የብሩንዲ የእርስ በእርስ ጦርነት ከ300 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

     የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮ ማስተማርና ጥናትና ምርምር ማካሄድ ነው፡፡ ጥናትና ምርምር ካላካሄድን ከ2ኛ ደረጃ በምን እንሻላለን? ይላሉ የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሞላ ፀጋይ፡፡
አድማስ ዩኒቨርሲቲ የዛሬ ሳምንት ‹‹የትምህርት ጥራትና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር›› በሚል ርዕስ በሳሮ ማርያ ሆቴል 10ኛውን ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ አካሄዶ ነበር፡፡ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን 8 ጥናታዊና የምርምር ጽሑፎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሞላ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ዩኒቨርሲቲው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ እየመደበ፤ በየዓመቱ ጥናትና ምርምር እንደሚካሄድ ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ ዓመታዊ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶች፣ አንድ ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ፣ ስድስት የተማሪዎች የምርምር ሲምፖዚየም ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል፣ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱት በራዕይና ተልዕኮአቸው በግልጽ በመስፈሩ፣ በአገሪቷ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖሊስ ምርመር ማካሄድን ግዴታ በማድረጉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፈጠራ፣ የለውጥና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከላት እንዲሆኑ በተቆጣጣሪ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ስለ ተሰጠው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የዘንድሮውን የጥናትና ምርምር ርዕስ፤ ‹‹የትምህርት ጥራትና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር›› የሚል ርዕስ የያዘው ጉዳዩ የሕዝብና የመንግስት ከፍተኛ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለን ትስስር በአንፃራዊነት ጥሩ ነው፡፡ ተቋሙ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለው ትስስር ሲጎለብት ጠንከር ብሎ  ይታያል፤ ላላ ሲል ደግሞ ድክመቶች ይስተዋላል፤ ክፍተቶች ግን የሉም ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዋናነት የሚሰጣቸው ኮርሶች በቢዝነስ ላይ ያተኮሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አካውንቲንግ ፋይናንስ፣ ማኔጅመንት፣ ማርኬቲንግ፣ ሆቴል ማኔጅመንት፣ አይቲ፣ ኮምፒዩተር ሳይንስ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ኢንዱስትሪዎች በዚህ ሙያ ይህን ያህል ምሩቃን ላኩልን እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ የብዙዎችንም ጥያቄ እኔ ስለምፈርም፤ በአሁኑ ወቅት ሰልጥኖ ሥራ ያልተቀጠረ ተማሪ ይኖራል ብዬ አልወስድም ብለዋል፡፡
ብዙ ጊዜ የምርምር ግኝቶች የኅብረተሰቡን ችግሮች ሲፈቱ አይታዩም፡፡ ዕጣቸው መደርደሪያ ላይ ሆኖ አቧራ መልበስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የእናንተ ጥናትና ምርምር ምን ያህል ወደ ኅብረተሰቡ ወርዷል? በማለት ጋዜጠኞች ላቀረቡት ጥያቄ ዶ/ር ሞላ ሲመልሱ፤ ‹‹ብዙ አሉ፡፡ ለአብነት ያህል በአንድ ወቅት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸው ችግሮች ምንድናቸው? በማለት ጥናት አካሄድን፡፡ በውጤቱም የዕቅድና የአመለካከት ችግር እንዳለ አመለከተን፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማስታወቂያ ጠርተን ሥልጠና ሰጥተናል›› በማለት ገልጸዋል፡፡

 ቶታል ኢትዮጵያ ለ66 ዓመታት በአገሪቷ ሲሰጥ የቆየውን የኢነርጂ ንግድ ለማሳደግና ለማዘመን ባለው ፍላጎትና ባደረገው ጥረት በአገሪቷ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው እጅግ ዘመናዊ የነዳጅና የጋዝ ዴፖ አሰርቶ ከትናንት በስቲያ አስመረቀ፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ በስተደቡብ ዱከም አካባቢ በ5.5 ሄክታር መሬት ላይ የተሰራው ዴፖ፤ 270 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን 8 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅና 200ሺህ ሊትር ፈሳሽ ቤንዚን የመያዝ አቅም እንዳለው ታውቋል። ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራው ዴፖው፤ ዘመኑ ያፈራቸው እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተገጠሙለት ሲሆን በታንኩ ውስጥ ያለው ነዳጅ ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳየው መሳሪያ አውቶማቲክ ነው፡፡ የፈሳሽ ነዳጅ መያዣው ታንከር ድርብ ከመሆኑም በላይ ዴፖው አንዳች እክል ቢገጥመው የሚጠቁም (የሚጮህ) እጅግ ዘመናዊ አላርም ተገጥሞለታል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ኤሌክትሪክ ቢበላሽ፣ ጋዝ ቢፈስ፣ እሳት ቢነሳ፣ ጪስ ቢፈጠር፣ ፈሳሽ የሃይድሮጂንና ካቦርን (ሃይድሮካርቦን) ቢፈስ አደጋ ከማስከተሉ በፊት ወዲያውኑ የሚጠቁም የኤሌክትሪክ ሲስተም ስላለው ከአደጋ የተጠበቀ ነው፡፡
የአካባቢ ብክለትንና የአሰራሩን ደህንነት የሚያረጋግጥ የርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ አለው፡፡ ፕሮግራም ተደርጎ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር የዚህ ዴፖ ልዩ ባህሪው ሲሆን፣ ለአጠቃቀም ቀላልና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሆኑትን ደረሰኝ አጠቃቀም፣ ያለውን የክምችት መጠን፣ ወጪ የሆኑ ምርቶችን ለማወቅና የአደጋ ጊዜ ሁኔታን ምቹ መቆጣጠሪያ መሳሪያ መሆኑን ያመለክታል፡፡  
የእነዚህ በጣም ውድ የሆኑ የደህንነት መጠበቂያና መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች መገጠም፣ ቶታል ኢትዮጵያ ለደህንነትና አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚያመለክት ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

   ድምፃዊ ሙሉቀን ዳዊት፣ ቃቆ ጌታቸውና ብስራት ሱራፌል በጋራ ያቀነቀኑበት ‹‹መንገደኛ›› የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ቀረበ፡፡ ግጥምና ዜማው በዓለማየሁ ደመቀ፣ በሙሉቀን ዳዊት፣ በጃሉድና በብስራት ሱራፌል የተሰራ ሲሆን ሙዚቃውን ያቀናበረው ካሙዙ ካሳ ነው ተብሏል፡፡ ‹‹መንገደኛ››ን ጨምሮ 13 ዘፈኖች በአልበሙ መካተታቸውም ታውቋል፡፡ በፍቅርና በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ዘፈኖች የሚቀነቀኑበት ይኸው አልበም፤ ቴክሼል የተሰኘ ድርጅት ፕሮዱዩስ ያደረገው ሲሆን ቮካል ሪከርድስ እያከፋፈለው እንደሚገኝ ድምፃዊያኑ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

   የገጣሚ ሄኖክ ስጦታው ሶስተኛ ስራ የሆነውና ‹‹መንገድ›› የተሰኘው የግጥም መድበል ገበያ ላይ ዋለ፡፡ ገጣሚው የተለያዩ የህይወት ፍልስፍናዎቹን ያሳየባቸው 64 ያህል ግጥሞች የተካተቱ ሲሆን በመፅሀፉ ጀርባ ‹‹ጠፈጠፍ›› በሚል ርዕስ ገጣሚ አበባ ብርሃኑ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ግጥሞቿን በጋራ አሳትማለች፡፡ በመቶ ገፅ የተቀነበበው መፅሀፉ፤ ለአገር ውስጥ በ49 ብር ከ60 ሳንቲም፣ ለውጭ አገራት በ15 ዶላር ለገበያ የቀረበ ሲሆን አከፋፋዩ ጃፋር መፅሐፍት መደብር ነው፡፡ ገጣሚ ሄኖክ ስጦታው በ1994 ዓ.ም ‹‹ነቁጥ››፣ በ2005 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ሀ-ሞት›› የተሰኙ የግጥም መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

       ከ20 ዓመታት በላይ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት፣ በሬድዮ ድራማና ትረካዎች ስራ ላይ የሚታወቀው በድምፁ ብዙዎች የሚያደንቁት ጋዜጠኛ ቢኒያም ደረሰ ድንገት በደረሰበት ትንታ ባለፈው እሁድ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ሰኞ እለት በገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ጓደኞቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል። ጋዜጠኛ ቢኒያም ደረሰ በተለይም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቅዳሜ መዝናኛ ላይ የሬዲዮ ድራማዎችን፣ ጭውውቶችንና ትረካዎችን በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡  ጋዜጠኛው በባህሪው ጭምትና ሆደ ሰፊ እንደነበር የገለፀው ጓደኛው የፋና ሬዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ደረጀ አያሌው፤ለስራ እንኳን ተፈልጎ እንደሚገኝና ብዙ ልታይ ልታይ እንደማይል አስታውሶ ብዙ ትኩረትና እድል በማጣት ሳንጠቀምበት ያጣነው ድንቅ ባለሙያ ነው ሲል ምስክርነቱ ሰጥቷል፡፡ ጋዜጠኛ ቢኒያም ደረሰ ላለፉት ሶስት ዓመታት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ይተላለፍ በነበረው ‹‹መሀል ቤት›› የተሰኘ ድራማ በመሪ ተዋናይነት ሰርቶ ማጠናቀቁንና አሁንም በፋና በሚተላለፈው ‹‹እኛን ነው ማየት” የተሰኘ ድራማ ላይ መሪ ተዋናይ ሆኖ እየሰራ እንደነበር ደረጀ ገልጿል፡፡ ቢኒያም ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

     ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ንብረት ጠፍቶ ሌባውን ለመያዝ አውጫጪኝ ይደረግ ተብሎ፤ የመንደሩ ሰው ሁሉ ተጠርቶ አንድ ዛፍ ሥራ ተሰበሰበ፡፡
ሰብሳቢው- ‹‹ጎበዝ እንዴት አደራችሁ?››
ተሰብሳቢው- ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን›› አለ በአንድ ድምፅ
ሰብሳቢውም፤
‹‹ዛሬ እንግዲህ የተሰበሰብነው፤ አንድ ችግር ተፈጥሮ ነው፡፡ እንደምታውቁት በመንደራችን ማንኛውም ንብረት፣ ከብት፣ ገንዘብ ከጠፋ የእኛው መንደር ህዝብ ተሰብስቦ መላ መትቶ፣ አውጣጥቶ፣ ሌባውን እንዲጠቁም ይደረጋል፡፡ ከህዝብ ዐይንና ጆሮ ማንም አያመልጥም፡፡ ዘዴው ከጥንት ጀምረን የምንሠራበት ፍቱን ዘዴ ስለሆነ በቀላሉ የሌባ-ሻይ ጥበቡ ሥራ ላይ ይውላል፡፡
በሉ እንግዲህ ስለጠፋው ወይፈን ምልክት የሚሰጠን ሰው ካለ፤ እጁን አውጥቶ ይነሳና ይናገር?›› አለ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ አዛውንት እጃቸውን አወጡ፡፡
‹‹ይናገሩ›› ተባሉና ተፈቀደላቸው፡፡
‹‹ይሄ የጠፋው ወይፈን ቡሬ ነው፡፡ ቤቴ ጎረቤት ስለሆነ ሲወጣ ሲገባ አይቼዋለሁ››
 ሌላው ተነስተው፤
‹‹ዕውነት ነው፡፡ ዐይን የሚገባ፣ የሚያምር ኮርማ ነው፡፡›› አሉ፡፡
ሦስተኛው ሰው፤
‹‹መቼም ወይፈንን የሚያህል ነገር የሚሰርቅ የለመደ ሌባ መሆን አለበት›› ሲሉ፤ ህዝቡ ክፉኛ አገሩመረመ፡፡ ከፊሉ አዲስም የዱሮም ሌባ ሊሆን ይችላል አለ፡፡ ከዚያ ሰው በየተራ የዱሮም ጥርጣሬ፣ አዲስም ጥርጣሬ ያለውን ሰነዘረ፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ላይ ለማረፍ ችግር ሆነ፡፡
ሰብሳቢው-ደጋግመው፤
‹‹ጎበዝ! እዚሁ መዋላችን ነው፤ ብትናገሩ ይሻላል›› አሉ፡፡ የሚናገር ጠፋ፡፡ ምሽቱ እየገፋ ነው፡፡ ወደመበተኑ ሆነ፡፡ በመካከል ከተሰበሰበው ህዝብ ውስጥ አንዱ ጎኑ ላለው ወዳጁ፤
‹‹ወዳጄ፤ አደራህን ለማንም አትንገር፤ ወይፈኑን የወሰድኩት እኔ ነኝ›› ይለዋል፡፡
‹‹ወስደህ ምን አደረግኸው?››
‹‹ወዲያ ማዶ ላለው መንደር ሸጥኩት››
‹‹እንግዲያው አንድ መላ ታየኝ››
‹‹ምን ታየህ?››
እጁን አወጣ ባለመላው፡፡ ‹‹ተናገር›› ተባለ፡፡
‹ማዶም፤ ወዲያኛውም መንደር፤ ከዚያ ወዲያ ባለውም መንደር አውጫጪኝ መደረግ አለበት፡፡ በእኛ መንደር ብቻ አውጫጪኝ ተካሂዶ መቆም የለበትም፡፡ ለዛሬው ብንበተን ነው የሚሻለን›› አለ፡፡ ሰብሳቢውም፤
‹‹ጎበዝ! ወይፈናችን ተሻግሯል ማለት ነው! ለዛሬው አውጫጪኙ ያብቃ!›› ብለው በተኑት፡፡
ወይፈኑን የሰረቀው ሰው ግን በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ሚሥጥሩን የነገረውን ሰው እግር በእግር፣ የገባበት እየገባ ይናገር ይሆን አይናገር ይሆን እያለ ሚሥጥሩን የያዘውን ሰው ሲከታተል እስከ ዛሬ ይኖራል ይባላል፡፡
** ** **
ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሌብነት ቦቃ የለውም፡፡ የጥንቱ አውጫጪኝ የዛሬ ስሙ ግምገማ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሚሥጥሩን ለማውጣጣት ሀቀኝነት ይጠይቃል፡፡ የሆድን በሆድ ይዞ ተፋጦ መዋል ፍሬ ነገሩን ከማግኘት ያቅባል። ቂም በቀል ካለ ግምገማ ግቡን አይመታም፡፡ በቅጡ ብንሰራው ጥሩ ነበር፡፡ በበቂ ትኩረት አልሰጠነውም ነበር፡፡ በቀጣይ የምናስብበት ይሆናል…. እያሉ ሸፋፍኖ ማለፍ ድክመትን ተሸክሞ መጓዝ ነው፡፡ መልኩን ይቀያይር እንጂ ሌብነት አንድ ነው፡፡ ሌብነትን በሂደት ማጣራት ለበጣ ነው የሚመስለው!
ሌብነት ሲያስጨንቅ የሚኖር አባዜ ነው፡፡ ሣር ቅጠሉን ሲጠራጠሩ መኖር ነው፡፡ ይሰውረን! አንድ የማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት የዱሮ ባለስልጣን አንድ የተፈታ እስረኛ ውጪ አግኝተው ሦስት ምክሮችን ለገሡት ‹‹1ኛ/ ከፖለቲከኞች ጋር አለመገናኘት 2ኛ/ ፖለቲካ አለመናገር፤ 3ኛውና ዋናው ግን ማንም ፖለቲካ ሲናገር ቢያጋጥምህ አለመስማት፤ ምክንያቱም በእኛ ግምት መስማት አደገኛ ወንጀል ነው-ለምን ቢሉ የሰማኸውን የት አረግኸው? የሚል ጥያቄ ያስነሳልና! ሄደህ አንዱ ጋ መተንፈስህ አይቀርም ተብለህ ከመጠርጠር አታመልጣትም! ስለዚህ ከሁሉም ክፉ ወንጀል መስማት ነው! ጆሮህን ድፍን አድርገህ መቀመጥ ምን ይጎዳሃል?!›› አሉት፡፡ የምንሰማው ሁሉ ለጥፋት የሚዳርግ አደገኛ ነገር ነው ብሎ የሚያስብ ለጥርጣሬ እንደተዳረገ ይኖራል፡፡ ቁም ነገሩ ግን የሚሰማ ነገር አለ ወይ? ነው፡፡ በብዛት ተደጋግመው የሚነገሩ ነገሮች በጣም ከመለመዳቸው የተነሳ እንኳንስ ቁም ነገራቸው ጣዕማቸውም ይጠፋል፡፡  በዛሬው ዘመን የሁሉ ነገር መጠቅለያ፤ ‹‹ህዝቡ የሚለውን በወቅቱ በትክልል አላዳመጥነውም ወይም ከናካቴው ጆሮ አልሰጠነውም ነበር›› የሚል ነው፡፡ አሁን ድንገት ጆሮአችን ተከፈተ ዓይነት ይስሙላም ያለው ይመስላል፡፡
‹‹ካለአቅሟ ካፒታሊዝም አስታቅፈው ካልወለድሽ ብለው ሲያማምጧት ከነሶሻሊዝሙም አስወረዳት›› እንደተባለው ነው፡፡ አቅማችንን እንመርምር፡፡ ዘልማድ ትተን ጥናታዊ አካሄድን እንያዝ ጥናታዊ አካሄድን የያዘ ሥርዓት የመገምገሚያም ወግና ደንብ አብሮ ያስቀምጣልና እከክልኝ ልከክልህም፣ የአብዬን እከክ እምዬ ላይ ልክክም ሆነ ሀሳዊ- ተዋናይነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ፔትሮስ ጊዮርጊስ ለራስ አሉላ የፃፈውን ደብዳቤም አንርሳ፡-
‹‹ታሪክ አላነበቡም እንጂ ፈረንጅና ቁንቁን አንድ ነው፡፡ ቁንቁን ከትል ሁሉ ያንሳል፡፡ ነገር ግን ታላቁን ግንድ በልቶ፣ አድርቆ ይጥለዋል፡፡ እነዚህም መጀመሪያ በንግድ ስም ይመጡና ጥቂት በጥቂት እየገቡ የሰውን አገር ይወርሳሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ቶሎ ደብድቧቸው፤ ይለቁ፡፡ አለዚያ አገርም መጥፋቱ ነው፡፡… ዛፍ ሳያድግ በእግር ጣት  ይነጫል፡፡ ካደገ በኋላ ግን ብዙ መጋዝና መጥረቢያ ያስፈልገዋል፡፡ እንደዚሁ የሞራ ግልገል ክንፉ ሳያድግ የስድስት ዓመት ልጅ ከዛፍ አውርዶ ሲጫወትበት ይውላል፣ ክንፉ ካደገ በኋላ ግን ከሰው እጅ ሥጋ ነጥቆ እስከ አየር ይወጣልና የሚያገኘው የለም፡፡ እንደዚሁም እነዚህ ናቸውና ለአገርዎ፤ ለግዛትዎ፣ ለጠጅዎ፣ ለጮማዎ ከሁሉም ይልቅ ለታላቅ ክብርዎ ይሞክሩ›› (ባህሩ ዘውዴ)
ምሁራንም ሚናቸው አይናቄ ነው፡፡ ምሁራንን ማዳመጥ በጎ ነገር ነው፡፡ እንደ ሩሲያ ምሁራን ‹‹ማነው ባለ አባዜው?›› ፤ ‹‹ምን መደረግ አለበት?›› ወይም ‹‹የህዝቡ ወዳጆች እነማናቸው?›› የሚሉ ፀሀፍት ማስፈልጋቸውን እናስተውል!
ለሁሉ ጥያቄ አንድ መጠቅለያ (ፓኮ) ፍለጋ፤ ሁለንተናዊ መድህን (Panacea) አድርጎም ሙሉ በሙሉ መቀበል፤ ትንተናዊ አቅጣጫዎችን እንዳናይ ይገድበናል፡፡ ከተለመዱት መጠቅለያዎች እንደ ‹‹መልካም አስተዳደር››፤ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ወዘተ ብሎ አለማቆም ብልህነት ነው፡፡ ይሄው ዛሬ ብዙ ያልተመረመሩ የህዝብ ችግሮች ብቅ ማለታቸውን እያመንን ነው፡፡ ራስ-ፍተሻው ይቀጥል! የህዝብን ድምፅ እንደ ባህል መያዝ ዋና ነገር ሲሆን ብዙ ድካም የሌበት ነው፡፡ የሚጠይቀን አንድ ጉዳይ ብቻ ነው- ቀናነት! በቀናነት ጥፋታችንን ማመን! በቀናነት ወገናዊነታችንን ትተን መጓዝ፡፡ መነሳት ያለበትን ሹም ማንሳት፤ በቀናነት እዚህኛው ሥልጣን ላይ ድክመቱ በይፋ የታየውን  ሰው ሌላ ቦታ አለመሾም! በቀናነት ‹‹እንደተጠበቀው አይደለም›› የሚልን ሽባ ሰበብ (Lame excuse) መተው፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ፡- ግብርናው እንደተጠበቀው አይደለም፤ ኢንዱስትሪው እንደተጠበቀው አይደለም፣ ለወጣቱ የተሰጠው ትኩረት እንደጠበቀው አይደለም….›› ይሄ ሄዶ ሄዶ ‹‹እኛም እንደጠበቅነው አይደለንም›› እንዳይሆን መጨረሻውን ማስተዋል አለብን፡፡ ሲደጋገሙ ወደ ፌዝነት የሚለወጡ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ ‹‹ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት….›› ዓይነት፡፡ ‹‹የመልካም አስተዳደር›› አይነት … ወዘተ Stereotype እንደሚሉት ፈረንጆቹ፡፡ በውጥረትና በስጋት እርስ በርስ በመወጣጠር፣ በመወሻሸት፣ የተሳተ መረጃ በመስጠት፣ አላየንም አልሰማንም በማለት… ያለወቅቱ መፍትሔ እንፈጥራለን ብሎ መሯሯጥ ከንቱ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ሀገራችን የዛሬ ወቅታዊ ሁኔታ ዐይን-ከፋች ሁኔታ የለም፡፡ ይህን ሁኔታ በግልፅ የሚያፀኸልን ‹‹ዕንቁላሉን ስለሰበርከው ጫጩት አታገኝም፡፡ በራሱ ሙቀት መፈልፈል አለበት!›› የሚለው አባባል ነው፡፡ ልብ ያለን ልብ እንበል!!

‹‹የህዝቡ ጥያቄ የስርአትና የፖሊሲ ለውጥ ነው››

   በተሃድሶ ግምገማ ላይ ከሚገኙት አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ኦህዴድ ሊቀመናብርቱን ሰሞኑን ከሃላፊነት ያነሰ  ሲሆን  ተቃዋሚ ፓርቲዎች  በየትኛውም ደረጃ የሚደረጉ የአመራር ለውጦች ለህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ አይሆኑም ብለዋል፡፡
ህዝብ የጠየቀው የስርዓትና የፖሊሲ ለውጥ እንጂ የግለሰቦች መቀያየርን አይደለም፤ ይላሉ ተቃዋሚዎች፡፡
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የገዥውን ፓርቲ ተሃድሶ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አስተሳሰቦች የተካተቱበት የፖሊሲ ለውጦች ነው የጠየቅነው ብለው፡፡ አሁን  ባለው ፖሊሲ ላይ ግለሰቦችን መለዋወጥ ተሃድሶ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የህዝቡ ጥያቄም የአመራሮች መለዋወጥ›› አይደለም ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ተሃድሶው በዚህ መልኩ ከቀጠለ ምንም ለውጥ አያመጣም፤ የህዝቡንም ጥያቄ በዚህ መንገድ መመለስ አይቻልም ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ የኦህዴድ አመራሮች መቀያየራቸው ሌሎቹ ድርጅቶችም ከዚህ የተለየ አጀንዳ እንደሌላቸው ያሳያል፡፡ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢዴፓ እምነት ይህ አካሄድ የበለጠ የህዝበን ጥያቄ የማፈኛ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ አዴፓ አሁንም ብቸኛው መፍትሄ የብሄራዊ እርቅ መድረክ ማዘጋጀት ነው የሚል አቋም እንዳለውም ዶ/ር ጫኔ ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያም ቢሆን ህዝብ የአመራር ለውጥ አልጠየቀም ያሉት የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ ‹‹ጥያቄው አጠቃላይ የስርአት ለውጥ ነው›› ብለዋል፡፡ ‹‹ህዝቡ ድርጅቶቹና ፖሊሲያቸው አይወክለንም፤ አያስፈልገንም ነው ያለው፤ ግለሰቦች ይለወጡ አላለም›› ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ድርጅቶቹ በህዝብ ያልተጠየቁትን ነው መልስ እየሰጠን ነው የሚሉት ብለዋል፡፡
ህዝቡ ጉዳዩ ከግለሰቦች ሳይሆን ከስርአቱ ጋር ነው፤ የሚሉት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ የህዝቡን ጥያቄዎች ያላገናዘበ መፍትሄ ነው ለመስጠት እየተሞከረ ያለው ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከግለሰብ አመራሮች ጋር ችግር የለበትም፤ መሻሻል ያለበት የመንግስት ስርአትና መዋቅር ነው ሲሉ በአፅንኦት የገለፁት አቶ ሙላቱ፤ አሁን የተያዘው የመፍትሄ አቅጣጫ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይሆንም ብለዋል፡፡
ድርጅቶቹ ከመሰረታዊው የህዝብ ጥያቄ ለመሸሽ በሌላ ጉዳይ ላይ ጊዜያቸውን እያጠፉ ነው፤ ያሉት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፤ ማድረግ ያለባቸው ፖሊሲያቸውን መመርመርና መቀየር ነው ብለዋል፡፡
ለተፈጠሩት ችግሮች በሙሉ ተጠያቂው የመንግስት ፖሊሲ እንጂ የፖሊሲው አስፈፃሚ ግለሰቦች ሊሆኑ አይችሉም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች፡- ብአዴን፣ ህውሓት፣ ኦህዴድና  ደኢህዴን በየክልሎቻቸው የተሃድሶ ግምገማ ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን በግምገማው በርካታ የአመራር ለውጦች ይጠበቃሉ ተብሏል፡፡ ኦህዴድ የቀድሞ አመራሮቹን አቶ ሙክታር ከድርና ወ/ሮ አስቴር ማሞን ካሃላፊነት አንስቶ በምትካቸው አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን የተካ ሲሆን አቶ ለማ መገርሳ የክልሉ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
አዲሱ የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በተሾሙ ማግስት በአጭር የሞባይል መልዕክት ለህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ድርጅታቸው የሰፊውን ህዝብ ጥያቄ በየደረጃው ተሃድሶ በማድረግ እንደሚመልስ አስታውቀዋል፡፡ በመቀጠል በላኩት ሌላ የሞባይል መልዕክት ደግሞ፤ ኦህዴድ በህዝብ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ለማድረግ የወሰነው ጥልቅ ተሃድሶ ለሌላውም አርአያ የሚሆን እርምጃ ነው፤ ኦህዴድ ሁሌም ከህዝብ ጎን ይቆማል ብለዋል፡፡