Administrator

Administrator

በምግብ ዝግጅት ባለሙያዋ አዝመራ ካሳሁን የተፃፈውና ከ6 ወር ህፃን፣ ት/ቤት እስከ ሚቋጠር የልጆች ምግብ አዘገጃጀት ያስተምራል የተባለው “ከቤት እስከ ት/ቤት” የተሰኘ የህፃናት ምግብ አዘገጃጀት መፅሐፍ ዛሬ በካሌብ ሆቴል ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ ይመረቃል፡፡
በ51 ገፆች የተቀነበበውና በ50 ብር ለገበያ የቀረበው መፅሀፉ፤ የትኛውም ወላጅ በአካባቢው በቀላሉ በሚገኙ የምግብ ጥሬ ዕቃዎች ለልጆቹ እንዴትና በምን ሁኔታ ምግብ በማዘጋጀት መመገብና ጤናማ ማድረግ እንደሚችል ያሳያል ተብሏል፡፡በምርቃት ስነ - ስርዓቱ ላይ ወላጆች፣ የት/ቤቶች ባለቤቶች ህፃናት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችና በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ የመፅሀፉ አዘጋጅ ወ/ሮ አዝመራ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

 አብርሀም ግዛው ኢንተርቴይመንትና የፕሬስ ስራዎች፣ ከጄቲቪ ጋር በመተባበር ‹‹መስቀልና ባህላዊ አከባበሩ›› የተሰኘ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ገለጸ፡፡
ፕሮግራሙ በካፒታል ሆቴል ነገ የሚቀረጽ ሲሆን የአገር ሽማግሌዎች ምርቃት፣ የእርድ ስነ-ስርዓት፣ የደመራ ማብራት ስነ- ስርዓት፣ ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ዝግጅቶች፣ ባህላዊ የጉራጌ አለባበስ የፋሺን ትርኢትና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ሰዎች ገጠመኞቻቸውን ለታዳሚው የሚያካፍሉ ሲሆን በጉራጌ ማህበረሰብ ለመስቀል በዓል የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ለዕይታ ይቀርባል ተብሏል፡፡ በመዝናኛ ፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንደሚታደሙ አዘጋጁ ጋዜጠኛ አብርሃም ግዛው ጨምሮ ገልጿል፡

ሚዩዚክ ሜይዴይ፤ ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር፣ ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ-መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ፣ ‹‹ምስክርነት›› በተሰኘው የሻምበል ተስፋዬ ርስቴ መፅሐፍ ላይ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት የ‹‹ጅቡቲ›› መፅሐፍ ደራሲ የሆኑት ዶ/ር በለጠ በላቸው ሲሆኑ፣ማንኛውም ፍላጎት ያለው ሰው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጋብዟል፡፡

   ከወራት በፊት የአሲድ ጥቃት ለደረሰባት ወጣት መሰረት ንጉሴ ህክምና የሚውል ገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ድግስ ጀክሮስ አካባቢ በሚገኘው ጋላኒ ኮፊ ውስጥ ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት እንደሚካሄድ አዘጋጁ ሴታዊት ንቅናቄ ገለፀ፡፡ በመዚቃ ድግሱ ላይ ፀደንያ ገ/ማርቆስ፣ ማርታ ታደሰና ቼሊና የሚያቀነቅኑ ሲሆን በድግሱ ላይ ለመታደም መግቢያ በነፃ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከሙዚቃ ድግሱ በተጨማሪ የስዕልና የፎቶግራፍ ሽያጭ የሚካሄድ ሲሆን ገቢው ሙሉ በሙሉ ለተጎጂዋ እንደሚሆን ከሴታዊት ንቅናቄ መስራቾች አንዷ የሆኑት  ዶ/ር ስሂን ተፈራ ገልጸዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ በጥቃት መከላከል ላይ የሚሰሩ የድርጅት ተወካዮች፣ የመንግስት ሃላፊዎች፣የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ተጎጂዋ በቦታው ተገኝታ ንግግር እንደምታደርግም ታውቋል፡፡ ማንኛውም ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚል አካል በፕሮግራሙ ላይ ተገኝቶ፣ለተጠቂዋ ወገናዊነቱን እንዲያሳይ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  - 20 ሺህ ዶላር ያህል እንደሚያወጣ ተገምቷል
    በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው በመወዳደር ላይ የሚገኙትን አነጋጋሪው ዕጩ የዶናልድ ትራምፕ እርቃን ተክለ ሰውነት የሚያሳየው ሃውልት ለጨረታ ሊቀርብ ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ሰውዬው አነጋጋሪ የሆነውና ዘ ኢምፐረር ሃዝ ኖ ቦልስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሃውልት፣ በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ጁሊንስ በተባለ አጫራች ኩባንያ አማካይነት በሎሳንጀለስ ለጨረታ እንደሚቀርብ የጠቆመው ዘገባው፤ሃውልቱ እስከ 20 ሺህ ዶላር ሊሸጥ እንደሚችል መገመቱን አስታውቋል፡፡
ኢንዲክላይን የተባለው የስነጥበብ ኩባንያ ንብረት የሆነውና የዶናልድ ትራምፕን ያልተሟላ ተክለ-ሰውነት በማሳየት በሰውየው ወንድነት ላይ ይሳለቃል የተባለው ሃውልት ተሸጦ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነው ለስደተኞች መብቶች ለሚሟገት አንድ ግብረ ሰናይ ተቋም እንደሚለገስ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የሚሳለቁ ሌሎች አምስት ሃውልቶች ከዚህ ቀደምም በአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰርተው ለእይታ እንደበቁ ዘገባው አስታውሷል፡፡

- በአገሪቱ የአህዮች ዋጋ በ3 እጥፍ አድጓል
      በኒጀር አህዮችን ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ የንግድ ተቋማት መበራከታቸውንና የአገሪቱ አህዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መመናመኑን ተከትሎ የኒጀር መንግስት ባለስልጣናት የአህያ ኤክስፖርትን የሚከለክል ህግ ማውጣታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የንግድ ተቋማት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አህዮችን ወደ ሌሎች አገራት በመላክ ከፍተኛ ትርፍ እያገኙ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የአገሪቱ አህዮች በብዛት የሚላኩት ወደ እስያ አገራት መሆኑንና ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘውም ቻይና እንደሆነች ገልጧል፡፡ ባለፈው አመት ለውጭ ገበያ የቀረቡ የኒጀር አህዮች ብዛት 27 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻም ከ80 ሺህ በላይ የአገሪቱ አህዮች ወደተለያዩ የአለማችን አገራት መላካቸውን ጠቁሟል፡፡
አህያ በተለይ በአገሪቱ የገጠር አካባቢ ማህበረሰብ ዋነኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ የኒጀር መንግስት ባለስልጣናትም አህዮችን በብዛት ለውጭ ገበያ ማቅረቡ በዚሁ ከቀጠለ አስጊ ሁኔታ ይፈጠራል በሚል የውጭ ንግዱን የሚከለክል ህግ ማውጣታቸውን አመልክቷል፡፡ የውጭ ንግዱ መስፋፋቱን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በአገሪቱ የአህዮች ዋጋ በሶስት እጥፍ ያደገ ሲሆን በኒጀር አንድ አህያ እስከ 150 ዶላር ዋጋ እንደሚያወጣ ዘገባው አስታውቋል፡፡

በአገረ ህንድ ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆኑት ህንዳዊው ቢሊየነር ሙኬሽ አምባኒ ለ1 ቢሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች ያለምንም ክፍያ መጠቀም የሚችሉበትን እጅግ ፈጣን የሆነ የ4ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ማቅረባቸውን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡ ቢሊየነሩ ያቋቋሙትና ሪሊያንስ ጂኦ የተሰኘው የኢንተርኔት አገልግሎት፤ከአገሪቱ 80 በመቶ ያህሉን አካባቢ የሚሸፍን ሲሆን ህንዳውያን ይህን እጅግ ፈጣን ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት እስከ 2016 መጨረሻ ያለ ምንም ክፍያ መጠቀም ይችላሉ ተብሏል፡፡
ተጠቃሚዎች የነጻ አገልግሎቱ የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላም እጅግ ርካሽ በሆነ ክፍያ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል የፈጠሩት ባለሃብቱ፣ ለዚህ አገልግሎት የሚከፍሉት 2.5 ዶላር ወርሃዊ ክፍያ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የባለሃብቱ የኢንተርኔት አገልግሎት እጅግ ፈጣን እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ በሰከንድ 21 ሜጋ ባይት ፍጥነት እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት እንዳስነበበው፤የነዳጅ ኩባንያዎችና የታላላቅ የንግድ ተቋማት ባለቤት የሆኑት ህንዳዊው ቢሊየነር ሙኬሽ አምባኒ፣ በዚህ አመት የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 36ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፣ ግለሰቡ የተጣራ 22 ቢሊዮን ዶላር ሃብት አላቸው፡፡

 - ቫይረሱ በ70 የአለማችን አገራት ተከስቷል

     ነፍሰጡር ሴቶችን በማጥቃት የራስ ቅላቸው የተዛባ ህጻናት እንዲወለዱ የሚያደርገው ዚካ ቫይረስ ወደተለያዩ የዓለም አገራት በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝና በአለማችን በድምሩ 2.5 ቢሊዮን ሰዎችን ሊያጠቃ እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ዚካ ቫይረስ አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ አለማቀፍ የጤና ችግር ሆኗል ያለው የአለም የጤና ድርጅት፤ቫይረሱ የስርጭት አድማሱን በማስፋት ከዚህ በፊት ተከስቶባቸው በማያውቁ የአለማችን አገራት መከሰት መጀመሩን በመጠቆም ስርጭቱን ለመግታት አለማቀፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የህክምና ባለሙያዎች ቡድን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባደረገው ስብሰባ፣ የዚካ ቫይረስን ስርጭት መግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን በተለይም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የአለማችን አገራት በቫይረሱ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
በዚካ ቫይረስ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው ከተባሉ የአለማችን አገራት መካከል ህንድ፣ ኢንዶኔዢያና ናይጀሪያ በቀዳሚነት እንደሚቀመጡም የባለሙያዎች ቡድኑ አስታውቋል፡፡ ሲንጋፖር በዚካ ቫይረስ የተጠቁባት ዜጎቿ ቁጥር 242 መድረሱን ከሰሞኑ ማስታወቋን የዘገበው ዘ ዴይሊ ሜይል ፤ማሌዢያም በሳምንቱ መጀመሪያ በቫይረሱ የተጠቃ የመጀመሪያ ዜጋዋን በተመለከተ መግለጫ መስጠቷን አስረድቷል፡፡ የዚካ ቫይረስ በግንቦት ወር 2015 በብራዚል ከተቀሰቀሰ ወዲህ ባሉት ጊዚያት በዚካ ቫይረሱ የተጠቁ የአለማችን አገራት 70 ያህል መድረሳቸውን የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ጌራ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ላለፉት ስድስት ወራት በጋዜጠኛንነት ሙያ ያሰለጠናቸውን ከ35 በላይ ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት ሳሪስ በሚኘው ‹‹ነጋ ቦንገር›› ሆቴል አስመርቋል፡፡ በ2003 ዓ.ም ተማሪዎችን በጋዜጠኝነት መሰረታውያን ማሰልጠን የጀመረው ተቋሙ፤ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ያስመረቀ ሲሆን እስካሁን ከ1ሺ በላይ ስልጣኞችን ማስመረቁን የተቋሙ ስራ አስኪያጅና የስድስት መዓዘን የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ አብርሀም ፀሀዬ፤ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡

Saturday, 10 September 2016 14:03

አመፀኛ ግጥሞች!

 የኛ ሀገር እረኞች
የኛ ሀገር እረኞች፣ ማማ የረገጡ.
ከወንጭፋቸው ጋር፣ ቆጥ ላይ እየወጡ፣
ከማሽላው መሃል፤
አሁንም አሁንም፤
ወፍ አረፈ ብለው፤ ወንጭፍ እያነሱ፤
የድንጋይ ውርጅብኝ፣ ከማሳው መሃከል እየነሰነሱ፤
በወፍ አመካኝተው፣
የስንቱን ማሽላ አንገት ቀነጠሱ፡፡
(በጃኖ መንግስቱ)
አትንኩታ
ድሃን አትንኩታ!
የምን ገፋ … የምንገፋ - ገፋ
ደሳሳ ጎጆውን … ያፈረሰ እንደሆን
የግራ በሬውን … የሸጠው እንደሆን
ዝናር ምንሽሩን … የታጠቀ እንደሆን
ኧረ ምድር ቀውጢ!
ምድር ቁና እንዳትሆን፡፡
አትንኩታ!
አታጨልሙታ!
የምን ገፋ ገፋ ገፋ …
ለምን ደፋ … ደፋ
እርፉን ከማረሻ … ሲወስደው ለያይቶ
አንካሴ ቀጥቅጦ … ሽመል አበጅቶ፣
አፈር እርም ብሎ …. ከወረደ ቆላ፤
ማጠፊያው እንዳያጥር … መመለሻው መላ፡፡
(ከወንድዬ አሊ)
የተጀመረ አንጀት
በደል ያሰለሰው
ጥቃት የበዛበት፣
የተገዘገዘ፤
የተጀመረ አንጀት፣ …
ባልጎደፈ ቃል፣
ባልገረጀፈ ጣት፣
በስሱ ካልነኩት፣
በፍቅር ካልዳሰሱት
በስስት ካልያዙት፣
በዕውቀት ካላከሙት …
በበደል፤ በጥቃት፣
ዳግም ከደፈቁት፣
ደፍቀው ከጎጡት፣
የተብሰከሰከ፤ የተጀመረ አንጀት፣
እንኳንስ ሊቀጥል፣
ጥቂት ይበቃዋል፤ ቆርጦ ለመለየት፡፡
(ከጌትነት እንየው “እውቀትን ፍለጋ”)
አዲስ ዓመት ብቻ!!
አበባየሁ ለምለም፣ አበባየሁ ለምለም
ኢትዮጵያዊ ከሆንክ …
አዲስ ዓመት እንጂ፣ አዲስ ነገር የለም!!
“አድገሃል” ይሉሃል፣ ታድጋለህ ባታድግም
ከዜና አበባ ላይ፣ ፍሬ አትፈልግም፡፡
(ከበላይ በቀለ ወያ)
ከንቱ ፍረጃ
“… አየሽ እዚህ ሀገር፣ ከንቱ ፍረጃ አለ፣
አማኝ ሁሉ አክራሪ፣
ሙስሊሙ አሸባሪ፣
ጉራጌ ቋጣሪ፣
ትግሬ ሁሉ ወያኔ፣
ወጣቱ ወመኔ፣
አማራው ነፍጠኛ፣
ደርግ ሁሉ ግፈኛ፣
ናቸው እያስባለ፣
ቁልቁል የሚነዳን፣ ጭፍን ጥላቻ አለ፡፡…”
(ከዮናስ አንገሶም ኪዳኔ)