Administrator

Administrator

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ተፈላሳፊ ሰው ታርኖፖል የሚባል ቦታ ይኖር ነበር፤ ይላል አንድ የአይሁዶች ተረት፡፡ ይህ ፈላስፋ እያነበበና እየተመራመረ ሳለ የሰፈር ወጣቶች መጥተው “ምክር ስጠን፣ አስተምረን፣ አንድ ታሪክ ንገረን” እያሉ አስቸገሩት፡፡ ፈላስፋውም “ለምን አንድ የውሸት ተንኮል ፈጥሬ አላባርራቸውም?” ሲል ያስብና፤ “ልጆች ወደዚያ አሮጌ የእምነት ቦታ፣ ወደ ምኩራቡ ሂዱ፡፡ እዛ አንድ ትልቅ የባህር ጭራቅ ታያላችሁ፡፡ አምስት እግር፣ ሶስት ዐይን እና እንደ ፍየል ያለ ጢም ያለው ሲሆን መልኩ አረንጓዴ ነው” አላቸው፡፡ ልጆቹ ወደተባለው ቦታ ሮጡ፡፡ ፈላስፋው ምርምሩን ይሠራ ጀመር፡፡ እነዚያን ደደብ ወጣቶች ተጫወትኩባቸው እያለ በሆዱ ፈገግ አለ፡፡ ሆኖም ጥቂት እንደቆየ የብዙ ሰዎች ዱካ ሰማ፡፡ በመስኮት ሲመለከት መአት አይሁዶች ሲሮጡ ተመለከተ፡፡ “ወዴት ነው የምትሮጡት?” ሲል ጠየቃቸው “ወደ አሮጌው የእምነት ቦታ” አሉት፡፡ “አልሰማህም እንዴ? አንድ አረንጓዴ፣ ባለአምስት እግር የባህር ጭራቅ ታየኮ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ ፈላስፋውም በሆዱ “ተንኮሌ ሠራ ማለት ነው!” ብሎ ተደሰተ፡፡

ጥናቱን ቀጠለ፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ግን ሌላ ግርግር ሰማ፡፡ በመስኮት ሲመለከት፤ ሴቱ፣ ህፃኑ፣ ሽማግሌው ሁሉ ይሮጣል፡፡ “ምን ተፈጠረ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ “አንተ ፈላስፋ አይደለህም እንዴ? ስለ ጭራቁ አላወቅህም? አንድ ትልቅ የባህር ጭራቅ ከእምነቱ ቦታ ፊት ለፊት አለ፡፡ እሱን ልናይ መሄዳችን ነው! እንደ ፍየል አይነት ጢም ያለው አረንጓዴ ጭራቅ!!” ፈላስፋው እየሳቀባቸው ሳለ ዋናው አይሁዳዊ ቄስ - የእምነቱ ቦታ ኃላፊ፤ ከህዝቡ ጋር ሲሮጡ አያቸው፡፡ “የሰማያቱ ያለህ! ዋናው የእምነት አባት ካሉበትማ አንድ የታየ ጭራቅ ቢኖር ነው፡፡ እሳት ከሌለ ጭስ አይታይም!” አለና ፈላስፋው ባርኔጣውን አድርጐ፤ ካፖርቱን ደርቦ፤ ከዘራውን ይዞ፤ “ማን ያውቃል የጭራቁ መታየት እውነት ቢሆንስ?” እያለ ከህዝቡ ጋር መሮጥ ጀመረ፡፡ *** “አካፋን አካፋ እንጂ ትልቅ ማንኪያ ነው አንበል” ይላሉ ኬንያውያን፡፡ ይህን አባባል ስለማንነታችን፣ ስለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን፣ ስለፓርቲያችን፣ ስለሀገራችን፣ ስለመከላከያችን፣ ስለሥልጣናችን፣ ስለልማታችንም ሆነ ስለዲሞክራሲያችን ስናወሳ ብናስታውሰው ይበጀናል፡፡

የመዋሸት መጥፎነቱ ልክ እንደፈላስፋው እኛኑ ተብትቦ መልሶ እውነት እንዲመስለን ማድረጉ ነው፡፡ ስለግልፅነት እያወራን የበለጠ ሚስጥራዊ የምንሆን ከሆነ ያው መዋሸት ነው፡፡ ዛሬ ያልነውን ነገ ካልደገምነው ያው መዋሸታችን ነው፡፡ ሰውን በሸራ ኳስ እያጫወትን እኛ በካፖርተኒ የምንጫወት ከሆነ ያው ማጭበርበራችን ነው፡፡ ያለአቅማችን ጉልበተኛ ነን ማለትም ሆነ ጉልበተኛ ሆነን ምስኪን ኮሳሳ ነን ማለትም ያው መዋሸት ነው፡፡ እያየን አላየንም፣ እየሰማን አልሰማንም፣ እያጠፋን አላጠፋንም ማለትም ያው መቅጠፍ ነው! “ያብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክም” ያው መዋሸት ነው! “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለትም ያው መዋሸት ነው! አስገድደን የምንፈፅመውም ሆነ ዋሽተን የምናሳምነው፣ አሊያም በገንዘብ የምንደልልው፤ የዘወትሩን ሰው ቢያስጨበጭብልንም የክቱን ሰው ያሳዝናል፡፡

በመዋሸት የተገነባ አመኔታ ከጥርጣሬ የፀዳ አይሆንም፡፡ አንድ ፀሀፊ እንዲህ ይለናል፤ “የመጠራጠር አዝማሚያችን፤ ከምክንያታዊነታችንና ከእውነታው እያራቀ እሚወስደን፤ በቡድናዊ አመለካከት ውስጥ ስንገባ ነው፡፡ ሁላችንም በየውስጣችን ያለውን ጥርጣሬ፤ የህዝብ ሞቅ-ሞቅና የመንገኝነት ባህል ያበረታታዋል፤ ያጋግለዋል፡፡ ዕምነተ-ሰብ (cultist) የሚያጠቃው ደጋፊ (ቲፎዞ) በቀላሉ ሥልጣን ይሰጣል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ተንኮለኛ አገዛዝን በፈለግህ ጊዜ፡- በሰዎች ያልተፈፀሙ ምኞቶች ላይ በመጫወት እነዚያን ህዝቦች እንደመንጋ ልትነዳቸውና ፍፁም ሠልጣን ልትጐናፀፍባቸው ትችላለህ፡፡ በፅኑ ማስታወስ የሚገባህ ነገር ደግሞ፤ እጅግ ስኬታማ የምትሆነው ሃይማኖትን ከሳይንስ ጋር ቀላቅለህ ስትጠቀም ነው፤ በጣም የረቀቀውን ቴክኖሎጂ ወስደህ፤ ከአንዳች ክቡር ዓላማ፣ ከማይጨበጥ እምነት ወይም አዲስ አይነት ፈውስ ጋር አጣብቀው፡፡ ያኔ መንጋው ህዝብ ይከተልሃል፡፡ አንተ ሳትሻ ልዩ ልዩ ትርጉም ይሰጥልሃል፡፡ አንተ የሌለህንና ያላሰብከውን ችሎታና ሥልጣንም ሰጥቶህ ቁጭ ይላል!” ይሄ እርግማን ነው፡፡ እርግማኑ በመንግሥትም፣ በተቃዋሚም፣ በሰባክያንም፣ በምዕመናንም አንፃር ብናሰላው ያው ነው፡፡ ህዝብን ማታለል ክፉ እርግማን ነው፡፡ የማታ ማታም ያስከፍላል፡፡

የሌለ ጀግና መፍጠርም ሆነ፤ ያለን ጀግና መካድ ሁለቱም ማታለል ነው፡፡ በከፋ መልኩ ሲታይ ራስንም ማታለል ነው፡፡ የሰው ዓላማ የኔ ነው ማለትና የሌላውን ስም የራስ ማድረግ፤ ከኢኮኖሚ ዘረፋም የከፋ ዘረፋ ነው፡- “ገንዘቤን የወሰደ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር የእኔም የእሱም የዚያም ነበር፡፡ ግና ስሜን የሰረቀኝ፤ የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ!” ይለናል እያጐ፤ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሳን፡፡ ውሸት እንደማግኔት መግነጢሳዊ ኃይል አለው፡፡ ማግኔት፤ በአንዳች የማይታይ ኃይል ባካባቢ ያሉ ነገሮችን ይስባል፡፡ እነዚያ ነገሮችም በፈንታቸው የመሳብ ኃይል ያበጃሉ - ባካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች በተራቸው ይስባሉ፡፡ ያንን ኃይል ይዘው ይቆያሉ፡፡

ሰዎችም በአንድ ውሸት ሲሳቡና ያንን ውሸት የራሳቸው ሲያደርጉ ከዚያ የሚለያቸው ኃይል አይኖርም፡፡ ኦርጅናሌ ዋሾውን እንደተአምረኛ ያዩታል፡፡ በዙሪያው ይከባሉ፡፡ እንደመንጋም ይነዳሉ፡፡ (ግሬት ዴ ፍራቼስኮ) በየፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳያችን አንፃር የሌለንን አለን፣ ያለንን የለንም ብለን ከዋሸንና ካሳመንን፤ ተከታያችን ሊደሰትበት፣ አልፎም ሊኮራበት ይችላል፡፡ ያም ሆኖ እንደማናቸውም ነገር ውሸትም ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት ጊዜ (expiry date) አለው፡፡ የዘንድሮ ካፒታሊዝማችን በሶሻሊዝማችን ላይ፤ ዲሞክራሲያችንም በፊውዳላዊ መሰረታችን ላይ፣ “ቫለንታይን ዴይም” በሌለ ፍቅራችን ላይ የተጣደ ከሆነ፤ በሽሮ ላይ ቅቤ ባናቱ ጠብ እንደማድረግ አይነት ነው፡፡ ሹሯችን ዛሬም ያችው ሹሯችን ናትና! ዋናው ነገር እውነቷን፣ እቅጯን አለመርሳት ነው፡፡ “ሸንጐ ተሰብስቦ ለሚስቱ እውነቱን የማያወራ ባል አያጋጥምሽ!” ነው ነገረ-ዓለማችን!

በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው የተፈረደባቸውና በማረሚያ ቤት የሚገኙት የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና የአንድነት ዋና ፀሐፊ የእነ አንዷለም አራጌ የይግባኝ ጉዳይ ለ40 ቀን ተራዘመ፡፡ ባለፈው ወር ክርክሩ ለውሳኔ ተቀጥሮ የነበረ ሲሆን የአንድነት ፓርቲ የባህር ዳር አመራሮች ሻምበል የሺዋስ ይሁንአለምና አንዷለም አያሌው ከእነ እስክንድር ነጋ ጋር በአንድ መዝገብ ቢከሰሱም ይግባኝ የጠየቁት ግን በተለያየ መዝገብ በመሆኑ መዝገቡን አንድ ላይ ለማየትና ውሳኔ ለመስጠት ለትናንትና ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

በትላንትናው ዕለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ዳኛ የሆኑት ዳኛ ብላቸው አንሶ የእነ እስክንድር የውሳኔ ቀጠሮ ለ40 ቀናት የተራዘመበትን ምክንያቶች ሲያስረዱ፤ አንደኛ:- የዕለቱ የመሀል ዳኛ ዳኜ መላኩ በሌላ ዕክል ምክንያት አለመገኘታቸውንና የእነ እስክንድር መዝገብም ሰፊ ውይይትና ጊዜን የሚፈልግ በመሆኑ ከሥር ፍርድ ቤት እንዲመጣ ታዝዞ፣ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት በመሆኑ ይህ ሁሉ ተጠናቆ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሠጠቱን ተናግረዋል፡፡

በእነ አንዱአለም አራጌ የክስ መዝገብ ሥር ያሉትና ተፈርዶባቸው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙት ሻምበል የሺዋስ ይሁንአለም፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ናትናኤል መኮንን እና ዮሐንስ ተረፈ ችሎቱ ከተበተነ በኋላ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሱ ቢሆንም ይህንኑ ውሳኔ በመስማት ወደ ማረሚያ ቤት ተመልሰዋል፡፡

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ፤ ካህናትና ምእመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል የሚሉትን ዕጩ እንዲጠቁሙ ያወጣው የስምንት ቀን መርሐ ግብር ትላንት፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ለፓትርያሪክነት የተጠቆሙት ዕጩዎች ዛሬ ይለያሉ፡ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ እንዲሰጥ፣ የወደደውንና የፈቀደውን በመንበረ ፕትርክናው እንዲያስቀምጥ ካህናትና ምእመናን አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ የታዘዘው የአንድ ሳምንት የጸሎት ሱባኤ እስከ ምርጫው ፍፃሜ የካቲት 21 ቀን 2005 ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት ተላልፏል፡፡ ዐዋጅም መፈጸሙ ተነግሯል፡፡ በምርጫው መሪ ዕቅድ መሠረት፣ በዛሬው ዕለት ካህናትና ምእመናን የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማ የሰጡበትን ቅጽ የያዘው የታሸገ ሣጥን ተከፍቶ ተጠቋሚዎቹን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

በዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማው ካህናት፣ ምእመናንና ገዳማውያን ሳይቀሩ በንቃት መሳተፋቸውን የተናገሩት ሓላፊው አቶ ባያብል ሙላቴ፤ ጥቆማውን ኮሚቴው በዕጩነት ለሚለያቸው አምስት አባቶች ዋነኛ ግብአት አድርጎ እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴው በዛሬው ዕለት ለጥቆማው አቀባበል በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ካህናትና ምእመናን የጠቆሟቸው አባቶች ለፓትርያሪክነት ለሚመረጡ ዕጩዎች የተቀመጡትን መመዘኛዎች ማሟላት አለማሟላታቸውን ከግል መረጃዎቻቸው ጋር እያነጻጸሩ የመለየትና የማጣራት ሥራዎች እንደሚሠራ አቶ ባያብል አስረድተዋል፡፡

ሓላፊው አያይዘውም በፓትርያሪክነት መመዘኛው መሠረት ተጠቋሚዎቹን የመለየትና ተጨማሪ የማወዳደር ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ፣ ኮሚቴው የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚቀርቡትን አምስት ዕጩዎች ለይቶ የካቲት 14 ያስታውቃል ብለዋል፡፡ 
‹‹በአንድ ሰውም ይኹን በአንድ ሺሕ ሰው የተጠቆሙ የተለያዩ አባቶች ቢኖሩ ኮሚቴው የሚወስደው ለዕጩነት መጠቆማቸውን ነው፤›› የሚሉት አቶ ባያብል፣ ተጠቋሚው በዕጩነት ሊያዝ የሚችለው፣ በምርጫ ሕገ ደንቡ የፓትርያሪክነት መመዘኛውን አሟልቶ ሲገኝ እንጂ በብዙ ሰው ስለተጠቆመ ብቻ ባለመኾኑ የዕጩ ጥቆማውን ጥያቄ ከመምረጥ ወይም ምርጫ ሂደት ጋር ማሳሳት ተገቢ አለመኾኑን ገልፀዋል፡፡
ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይ የተጠየቁትን የድጋፍ ደብዳቤዎች አሟልተው የቀረቡ ዕጩ ጠቋሚዎች የተስተናገዱት በግላቸው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ባያብል፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች እገሌን ለዕጩነት ጠቁመናል ወይም እገሌን መርጠናል በሚል በቡድን የቀረቡ ማመልከቻዎችን ሳይቀበሉ መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በዕጩ ፓትርያሪክነት በመጠቆም እንዳቀረቡት የተገለጸው ደብዳቤ ተቀባይነት የሚኖረው፣ ደቀ መዛሙርቱ በነፍስ ወከፍ የኮሌጅ ተማሪነታቸውን ከኮሌጁ አስተዳደር በተጻፈ ደብዳቤ አስደግፈው ለጥቆማ ሲቀርቡ እንደኾነ ሓላፊው አስረድተዋል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት መግለጫው፣ የካቲት 21 ቀን በሚካሄደው የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚሳተፉት የመራጮች ብዛት 800 እንደኾኑ ካስታወቀ በኋላ በሂደት እየተለዩና ዕውቅና እየተሰጣቸው የተጨመሩ መራጮች መኖራቸው ተመልክቷል፡


በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቷ በሀገር ውስጥ ካሏት 53 አህጉረ ስብከት መካከል 790 መራጮች ይሳተፋሉ፤ ከሀገር ውጭ ባሏት ስምንት አህጉረ ስብከት ከእያንዳንዳቸው አራት (ከሥራ አስኪያጁ ጋር ካህናትን፣ ምእመናንን፣ ሰንበት ት/ቤቶችን የሚወክሉ አንድ አንድ) መራጮች፣ ከግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ጋር ባለው የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት አራት መራጭ ተወካዮች በአጠቃላይ ማስተካከያው እስከተነገረበት ጊዜ ድረስ 826 መራጮች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

 

የሩሲያዊው ሐኪምና ደራሲ የአንቶን ቼሆቭ 153ኛ የልደት በዓል የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በፑሽኪን አዳራሽ በሙዚቃ ዝግጅት እንደሚከበር የሩስያ የሳይንስና የባህል ማዕከል አስታወቀ፡፡ በዕለቱ የሩስያ የፒያኖ እና የኦፔራ ሙዚቀኞች ናታሊያ ኮርሹኖቫ እና አሌክሲ ፓርፌኖቭ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚው  ያቀርባሉ ተብሏል፡፡“ሥነፅሁፍ ውሽማዬ ሕክምና የሕግ ሚስቴ” ይል የነበረው ሩስያዊው ሐኪምና ደራሲ አንቶን ቼሆቭ፣ ሩስያ ካፈራቻቸውና ሥራዎቻቸው በዓለም ዙርያ ከናኙ የአጭር ልቦለድ ፀሐፍት አንዱ ነው፡፡ የሰኞ አመሻሹ ዝግጅት በሩስያ የባህላዊ ሻይ አፈላል (ሳሞቫር) የሚታጀብ ሲሆን ለታዳሚዎች የሻይ ግብዣ እንደሚኖር የባህል ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ጐንደር ቅርንጫፍ ባለፈው ሳምንት አርብ መፅሐፍ ሲያስመርቅ የቀረበ አንድ የግጥም መፅሐፍ በስድስት ሺህ ብር ተጫርቶ ተሸጠ፡፡ “አፈርሳታ” የተሰኘው ይኸው መፅሐፍ በጐንደር ከተማ ሲመረቅ ጨረታውን አሸንፎ የገዛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነው፡፡ “አፈርሳታ” በከተማዋ ኗሪ ወጣት በሪሁን አሰፋ የተገጠሙ ማህበራዊ ጉዳዮችን ያካተተ የግጥም መፅሐፍ ነው፡፡

የ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ መስራች እና ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው ግርማ ተስፋው የገጠማቸው ግጥሞች የተካተቱበት “የጠፋችውን ከተማ ኅሰሳ” የግጥም መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ ገጣሚው በአራት የአለማችን ከተሞች ላይ ተመስርቶ የፃፋቸውን 69 ግጥሞች በአራት ክፍሎች ያቀረበ ሲሆን የመፅሐፉ ዋጋም 25 ብር ነው፡፡
ግርማ ተስፋው “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ከተዘጋ በኋላ በ”አዲስ ነገር ኦንላይን” እና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጦች ላይ ፅሁፎቹ የታተሙ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2011-12 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የናይት (Knight) ጆርናሊዝም ፌሎ ነበር፡፡

Saturday, 09 February 2013 12:41

“LIFE’S LIKE THAT” ለገበያ ቀረበ

የሥነፅሁፍ መምህር የሆኑት አቶ ገረመው ገብሬ ያዘጋጁአቸው አጫጭር የእንግሊዝኛ ልቦለዶች የተካተቱበት የምናብ ታሪኮች መድበል ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ LIFE’S LIKE THAT AND OTHER STORIES በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው ባለ 44 ገፆች መፅሃፍ ለሀገር ውስጥ ገበያ በ25 ብር፣ ለውጭ ሀገራት 1.33 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡
16 ታሪኮች የተካተቱበትን መፅሐፍ ሔሪቴጅ ፕሪንቲንግ ኤንድ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ነው ያሳተመው፡፡ አቶ ገረመው ካሁን ቀደም የንግግር እንግሊዝኛ (Spoken English) መፅሃፍ አሳትመዋል፡፡

የግጥም በጃዝ የግጥም እና የሙዚቃ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡30 እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ የሚቀርበው 19ኛ ወርሀዊ ዝግጅት የመግቢያ  ዋጋ በሰው 50 ብር ነው፡፡አርቲስት ሜሮን ጌትነት መድረኩን በምትመራበት ዝግጅት ላይ አቶ አብዱ አሊጅራ ዲስኩር የሚያቀርቡ ሲሆን አርቲስት ጌትነት እንየው፣አበባው መላኩ፣ ዮሐንስ ገብረመድህን እና አለማየሁ ታደሰ የ”አንቲገን” ትያትርን ቅንጭብ በጃዝ ሙዚቃ ታጅበው እንደሚጫወቱ ተገልጿል፡፡

የኢራን እስላማዊ አብዮት የተካሄደበትን 34ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኢራን ኤምባሲ‹‹የፍቅር ተዓምር›› የተሰኘ የግጥም ምሽት ትላንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል አቀረበ፡፡ የአምስት ታላላቅ ኢራናዊያን ገጣሚዎች ስራ በኢትዮጵያውያን ገጣሚዎች ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የቀረበበት የግጥም ምሽት፣መታሰቢያነቱ የኢራናውያን መንፈሳዊ መሪ ለነበሩት አያቶላ ኢማም ሆሚኒ እንደነበር ታውቋል፡፡
የኢራናዊያን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ኢማም ሆሚኒን ግጥም ጨምሮ የኦማር ኻያም፣ የሩሚ፣ የሳዒድና የባባጥህር ግጥሞች በአማርኛ ተተርጉመው የቀረቡ ሲሆን የዛሬ 34 ዓመት በኢራን የተካሄደው እስላማዊ አብዮት በየዓመቱ በኪነጥበባዊ ዝግጅት እንደሚዘከር ታውቋል፡፡

“ውቢት እንቅልፋሟ” የሚል የልጆች ትያትር ዛሬ ከጧቱ 3 ሰዓት በኤድናሞል ሲኒማ እንደሚያስመርቅ ናታን መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ ትያትሩን ፅፎ ያዘጋጀው አብነት ጌታቸው ሲሆን በትያትሩ ምረቃ ላይ አዱኛ የዳንስ ቡድን ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡በየትምህርት ቤቱ በመዞር የሚታየው ይኼው ትያትር፣ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩ ሕፃናትን በማለም የተሰራ ነው፡፡ ትያትሩ በናታን መልቲ ሚዲያ “የተራኪ ዳንሰኛና ድራማ ክለብ” መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡