Administrator

Administrator

በማህበራዊ ሚዲያ ጸሃፊነቱ የሚታወቀው ገጣሚ አደም ሁሴን፤“እሳት ያልገባው ሀረግ” በሚል ርዕስ ያሳተመው የግጥም መድበል ለገበያ የቀረበ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በፑሽኪን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ  ግጥሞችን ያካተተው መጽሀፉ፤በብር 29፡90 እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡  

Saturday, 15 August 2015 16:08

“ከእለታት” ፊልም ተመረቀ

በቅድስት ይልማ የተደረሰውና ዳይሬክት የተደረገው #ከእለታት; ፊልም ባለፈው እሁድ ተመረቀ፡፡ የ1፡35 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 6 ወር እንደፈጀ ታውቋል፡፡  ፊልሙ፣ሁለት በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ተፈጥሮ በአጋጣሚ የሰጠቻቸውን ስጦታ እንዴት እንደሚጠቀሙበት የሚያሳይ የቤተሰብ ድራማ ነው ተብሏል፡፡
በ123 ስቱዲዮ ተዘጋጅቶ፣በአለን ኢንተርቴይመንት በቀረበው #ከእለታት; ፊልም ላይ እፀህይወት አበባና ሩታ መንግስታብን ጨምሮ በርካታ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

 ክፍል አንድ
15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሳምንት በኋላ በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ይጀመራል፡፡ 29ኛው ኦሎምፒያድን ከ7 ዓመት በፊት በድምቀት ባስተናገደው  ታላቁ የወፍ ጎጆ ስታድዬም ለሁለት ሳምንታት የሚካሄድ ነው፡፡ የወፍ ጎጆ የተባለው ዘመናዊ ስታድዬም ኦሎምፒክን  ያስተናገደው እስከ 80ሺ ተመልካች በመያዝ ነበር፡፡ ለዓለም ሻምፒዮናው ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር ሲባል  54000 ተመልካች ብቻ እንዲያስተናግድ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ተወስኗል። ብዙዎቹ ውድድሮች በምሽት መካሄዳቸው የውድድሩን ድምቀት ይጨምረዋል ተብሏል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው በአጭር ርቀት አሜሪካና ጃማይካ፤ በረጅም ርቀት ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ይደምቃል፡፡
በተለያዩ የውድድር መደቦችን ሚኒማዎችን ያሟሉ፤ ከ2 ዓመት በፊት ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱ፤ የ2014 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች፤ የየአህጉሩ ሻምፒዮኖች መሳተፋቸው ሻምፒዮናው ያለበትን ከፍተኛ ደረጃ ያመለክታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የሚገኝ ስኬት ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ውጤታማነት አመልካች ሲሆን በየውድድር መደቡ ሻምፒዮን ሆነው የወርቅ ሜዳልያ የሚያገኙት የሪዮዲጄኔሮ ትኬታቸውን በቀጥታ የሚቆርጡበት ይሆናል፡፡
ከ200 አገራት በላይ እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው የዓለም ሻምፒዮናው በ47 የውድድር መደቦች (24 በወንድ እና 23 በሴት)  ከ2000 በላይ አትሌቶች ይወዳደራሉ። በየሻምፒዮናው አጠቃላይ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በመሪነት የመቆጣጠር ልምድ ያላቸው አሜሪካ፤ ጃማይካና ራሽያ ሙሉ ቡድናቸውን ሰሞኑን አሳውቀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አሜሪካ 6፤ ጃማይካ 6፤ ኬንያ 5፤ ጀርመን 4 እንዲሁም ኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከ1 እስከ 6 ያለውን ደረጃ ይዘው መጨረሳቸው ይታወሳል፡፡በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ1 እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት እንዲሁም ለሌሎች የቡድን ውድድሮች የገንዘብ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግብ አትሌቶች የ100ሺ ብር ቦነስ ተዘጋጅቷል፡፡ ለወርቅ ሜዳልያ 60 ሺ ዶላር፤ ለብር ሜዳልያ 30ሺ ዶላር፤ ለነሐስ ሜዳልያ 20ሺ ዶላር ሲበረከት፤ ከ4 እስከ 8 ደረጃ ለሚያገኙት 15ሺህ፤ 10ሺህ ፤6ሺህ፤ 5ሺ እና 4ሺ ዶላር እንደቅደመተከተላቸው ይሸለማል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን ኬንያ እና ሌሎች
ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን 33 አትሌቶች ያሉበትን ቡድን የምታሰልፈው ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች ከአራት በላይ የወርቅ እንዲሁም በድምሩ እስከ 12 ሜዳልያዎች እንደምትሰበስብ ተገምቷል።  የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ካለፈው የዓለም ሻምፒዮና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚቻል ተስፋ ማድረጉን የገለፀ ሲሆን፤ ብሔራዊ ቡድኑን  ላለፈው 1 ወር በአራራት ሆቴል አስቀምጦ ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርግ አስችሏል፡፡ አትሌቶች የቤጅንግ አየር ንብረትን ለመቋቋም እንዲያስላቸው ተግባራዊ በሆነው የልምምድ መርሃ ግብር ሰርተዋል፡፡ ከቃሊቲ እስከ ሶደሬ በሚገኙ የአገሪቱ ሞቃታማ አካባቢዎች በመዘዋወር ዝግጅታቸውን ሲያከናውኑ ከርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታዎች በ6 የውድድር መደቦች ተካፋይ ትሆናለች፡፡ በ800፤ በ1500፤በ5ሺ በ10ሺ፤ በ3ሺ መሰናክል እና በማራቶን ማለት ነው፡፡ ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ካስመዘገቡት በ10ሺ  የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ጥሩነሽ ዲባባ በወሊድ እረፍት  እንዲሁም በ5ሺ የወርቅ ሜዳልያ ያገኘችው መሰረት ደፋር ባልታወቀ ምክንያት አለመሳተፋቸው ታውቋል፡፡ ከእነሱ ባሻገር የኢትዮጵያ ቡድን የዓለም ሻምፒዮና ፤ የዳይመንድ ሊግ እንዲሁም የትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ልምድ ባካበቱ አትሌቶች፤ በወጣት እና ተተኪ አትሌቶች የተሞላ ነው፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል በ800 ሜትር ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ከ2 ዓመት በፊት ያገኘው መሃመድ አማን ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው። በሴቶች ደግሞ የዓለም ሻምፒዮና ኮከብ አትሌት ሆኗ ተሳትፎዋ በጉጉት የሚጠበቀው ገንዘቤ ዲባባ ትነሳለች። በ1500 ሜትር ዘንድሮ የዓለም ሪከርድ ያስመዘገበችው ገንዘቤ ዲባባ በ5ሺ ሜትር እንድትወዳደር ፌደሬሽኑ ቢመርጣትም ገንዘቤ በ1500 ሜትር እና በ5000 ሜትር ደርባ መወዳደር ብትችል የብዙዎች ፍላጎት ነበር፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በ3 የዓለም ሻምፒዮናዎች የመሳተፍ እድል የነበራት ገንዘቤ የወርቅ ሆነ የሜዳልያ ውጤት ለማስመዝገብ  ብዙም አልሆነላትም ነበር።  በ5000 ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስትሳተፍ በ2009 ላይ 9ኛ እንዲሁም በ2011 8ኛ ደረጃ አግኝታ የነበረ ሲሆን  በ2013 እኤአ ደግሞ በ1500 በመካፈል ስምንተኛ ነበረች፡፡ በተጨማሪም ከ2 ዓመት በፊት በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ የብር ሜዳልያ ያገኘችው አልማዝ አያና፤ በ10ሺ የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው በላይነሽ ኦልጅራ፤ በ5ሺ የብር ሜዳልያ ያገኘው ሐጎስ ገብረህይወት፤ በ3ሺ መሰናክል የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው ሶፍያ አህመድ ልምዳቸውን በመጠቀም ውጤታማ እንደሚሆኑ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው፡፡ በ10ሺ ለወርቅ ሜዳልያ የሚጠበቁት በሆላንድ በተደረገው የማጣርያ ውድድር አስደናቂ ውጤት ያስመዘገቡት ሙክታር ኢድሪስ እና ገለቴ ቡርቃ ይሆናሉ። ከወጣት ተተኪ አትሌቶች ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ የተደረገው በ5000 ሜትር ወንዶች የሚጠበቀው ወጣቱ ዮሚፍ ቀጀልቻ ነው፡፡  በኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ያለው ደጀን ገብረመስቀል ደግሞ በ10ሺ ሜትር በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ከኢትዮጵያ የራቀውን የወርቅ ሜዳልያ ድል እንደሚመልስ ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ 47 አትሌቶችን በማስመዝገብ ትሳትፋለች፡፡ ለኢትዮጵያ እና ለኬንያ ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ባሉ ውድድሮች የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ እና የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች እየተጠቀሱ ናቸው፡፡ በረጅም ርቀት በተለይ በወንዶች ለእንግሊዙ ሞፋራህ  ከፍተኛ ግምት ሲሰጥ፤ በ800 ሜትር የቦትስዋናው ኒጄል አሞስ፤ የአሜሪካዎቹ ጋለን ሩፕና ራያን ሂል በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የሜዳልያ ተስፋ ፉክክር እንደሚፈጥሩ ተነግሮላቸዋል፡፡ ኬንያ በ200 በወንዶች፤ በ400ሜ በሁለቱም ፆታዎች እና በ400 መሰናክል በወንዶች፤ በጦር ውርወራ በወንዶች በ5 የውድድር መደቦች ከኢትዮጵያ የተሻለ ተሳትፎ ይኖራታል፡፡ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ባሻገር የደቡብ አፍሪካው ዋይዴ ቫን በ200 ሜትር፤ ናይጄርያ በ400 ሜትር  ሌሎች የአጭር ርቀት ውድድሮች ኡጋንዳ እና ኤርትራ ደግሞ በረጅም ርቀት የአፍሪካን ተሳትፎ ያጠናክሩታል ተብሏል፡፡

  ፕሬዚዳንቱ ያስገደሏቸው ባለስልጣናት 70 ደርሰዋል ተብሏል
   አምና በሰኔ ወር ስልጣን ላይ የወጡት የሰሜን ኮርያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቾ ዮንግ ጎን በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን ትዕዛዝ ባለፈው ግንቦት ላይ እንደተገደሉ መነገሩንና ደቡብ ኮርያም ጉዳዩን እያጣራች እንደሆነ መግለጧን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ዮንሃፕ ኒውስ የተባለ የዜና ምንጭ የስለላ ተቋማትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ባወጣው ዘገባ፣ የ63 አመቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን የምከተለውን የደን ልማት ፖሊሲ ተችተዋል በሚል አስገድለዋቸዋል፡፡
የግንባታና የግንባታ መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች ምክትል ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉትና ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ያደጉት ቾ ዮንግ ጎን ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ከህዝብ እይታም ተሰውረው መቆየታቸውና እሳቸውን በተመለከተ ምንም አይነት የዜና ሽፋን ተሰጥቶ አያውቅም ብሏል ዘገባው፡፡
ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን ስልጣን ከያዙ በኋላ በእሳቸው ትዕዛዝ የተገደሉና የገቡበት ጠፍቶ የቀሩ የሰሜን ኮርያ ባለስልጣናት ቁጥር 70 ያህል ደርሷል ያለው ዘገባው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቾ ዮንግ ጎንም የፕሬዚዳንቱን አስተዳደር በመተቸታቸው እንዲገደሉ ተደርገዋል የሚል ዘገባ መውጣቱን ገልጧል፡፡
የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ አንድነት ኢንስቲቲዩት ባለፈው ወር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በሰሜን ኮርያ በ2012 ብቻ 21 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን በ2013 የገዛ አጎታቸውን ማስገደላቸውንና በዚህ አመትም የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮን ያንግ ቾልን በአሰቃቂ ሁኔታ በሞርታር ማስረሸናቸውን አስታውሷል፡፡

  የስዊድን ፍርድ ቤት አቃቤ ህጎች ዊኪሊክስ የተባለው አለማቀፍ ሚስጥር ጎልጓይ ድረገጽ መስራች በሆነው ጁሊያን አሳንጄ ላይ ከቀረቡት የተለያዩ የወንጀል ድርጊት ክሶች መካከል ሶስቱን ውድቅ ማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የስዊድን ፍርድ ቤት አቃቤ ህጎች ሃሙስ እለት እንዳስታወቁት፤ በአሳንጄ ላይ ከቀረቡት ውንጀላዎች ሶስቱ ክስ መመስረት ከሚገባው ጊዜ አልፎ የቀረቡ በመሆናቸው ውድቅ የተደረጉ ሲሆን፣ በ2010 የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሟል በሚል የቀረበበት ክስ ግን መታየቱን ይቀጥላል፡፡ አሳንጄ በስዊድን ከተላለፈበት የእስራት ትዕዛዝ በማምለጥ ከሰኔ ወር 2012 ጀምሮ ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ጥገኝነት አግኝቶ እየኖረ እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፤ውድቅ የተደረጉለት ወንጀሎች ክስ መመስረት ከሚገባቸው የአምስት አመት የጊዜ ገደብ አልፈዋል መባሉን ጠቁሟል፡
የ44 አመቱ አውስትራሊዊ አሳንጄ የቀረቡበትን የወንጀል ክሶች በሙሉ መካዱን  ያስታወሰው ዘገባው፣ በሺህ ዎች የሚቆጠሩ አሜሪካን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ይፋ በማውጣቱ ሳቢያ እየተደረገበት ካለው ምርመራ ጋር በተያያዘ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ በመስጋት ወደ ስዊድን እንደማይመለስ መናገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

በእዳ ጫና አስከፊ ቀውስ ውስጥ ገብቶ የከረመው የግሪክ ኢኮኖሚ በዘንድሮው ሁለተኛ ሩብ አመት የዜሮ ነጥብ ስምንት በመቶ ያልተጠበቀ እድገት ማሳየቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ብሄራዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣በዚህ አመት ከ2.1 በመቶ እስከ 2.3 በመቶ ገደማ ይቀንሳል ተብሎ የተገመተው የግሪክ ኢኮኖሚ ባልተጠበቀ ሁኔታ በሁለተኛው ሩብ አመት የ0.8 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡
በግሪክ ብሄራዊ ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ኒኮስ ማጊናስ እንደገለጹት፤ በሁለተኛው ሩብ አመት የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት፣ ቀደም ብሎ የተተነበየውን የኢኮኖሚ ውድቀት ከ2 በመቶ በታች ማድረስ እንደሚቻል ያመላከተ ሲሆን ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ1.4 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
ላልተጠበቀው የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ካበረከቱት ዘርፎች መካከል የፍጆታ፣ የኢንዱስትሪ ምርትና የቱሪዝም መስኮች መነቃቃት ማሳየታቸው እንደሚገኝበት የጠቆሙት ማጊናስ፣ ኢኮኖሚው በመጀመሪያው ሩብ አመት እድገትም ሆነ ውድቀት አለማስመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡
የግሪክ አጠቃላይ አገራዊ ምርት ካለፈው ሚያዝያ ወር እስከ ሰኔ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የ0.8 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ ሰው ብዙ ከብቶች ወዳሉበት አንድ በረት ገብቶ አንድ ላም ሰርቆ ሲወጣ፤ አንድ መንገደኛ ሰው ያየዋል፡፡ ያም ሌባ ጣቱን አፉ ላይ አድርጐ “ዝም በል አትንገርብኝ ባክህ!” ይለዋል፡፡
ያም መንገደኛ ለማንም እንደማይናገርበት ራሱን በአዎንታ ነቀነቀለት፡፡
ሌላ ጊዜ ሌባውና መንገደኛው አንድ ሆቴል ቤት ተገናኙ፡፡ መንገደኛው ምግቡን በልቶ ሌባውን ክፈልልኝ አለው፡፡
“ለምንድነው የምከፍለው?” አለው ሌባው፡፡
መንገደኛው፤
“ዋ! የላሟን ነገር ለመንደሩ አለቃ እነግርልሃለሁ!” አለው፡፡
ሌባው ተሽቆጥቁጦ ከፈለ፡፡
ሌላ ቀን አንድ የገበያ አዳራሽ ውስጥ ይገናኛሉ፡፡ መንገደኛው የሚችለውን ዕቃ ወስዶ ሲያበቃ ለባለሱቁ፤
“ያ ሰውዬ ይከፍላል” ብሎ ወደ ሌባው ጠቆመ፡፡
ሌባው አሁንም፤
“ለምንድነው የምከፍለው?” አለ፡፡
መንገደኛውም፤
“ዋ! የላሟን ነገር!” አለው፡፡
ሌባው የግዱን ከፈለ፡፡
በሌላ ቦታ መንገደኛው ሌባውን አገኘውና፤
“ገንዘብ ቸግሮኛልና ስጠኝ?” አለው፡፡
ሌባው፤ “ለምንድን ነው የምሰጥህ?” አለ፡፡
“ዋ! የላሟን ነገር!” ሲል ገና፤ ገንዘብ አውጥቶ ሰጠው፡፡
ሆኖም አሁን ቆም ብሎ ማሰብ ጀመረ፡፡
“ለምን ሄጄ ለመንደሩ አለቃ ላም መስረቄን ነግሬ፣ ይቀጣኝም እንደሆን አልቀጣም?” ብሎ አሰበ፡፡ ወሰነ፡፡
ቀጥ ብሎ ወደ መንደሩ አለቃ ሄደና፤
“ጌታዬ፤ ቸግሮኝ ከመንደሩ በረት አንድ ላም ሰርቄያለሁ፡፡ በህጉ መሠረት የምትቀጣኝን ቅጣኝ” ሲል ጠየቀው፡፡ (“የምታፋፍምብኝን አፋፍምብኝና ልሂድ!” እንዳለው ሰው በቀይ ሽብር ዘመን)
አለቅየውም፤ አውጥቶ አውርዶ፤ “ዋናው ይቅርታ መጠየቅህ ነው” ብሎ በምህረት ሸኘው፡፡
ሌባው በደስታ እየፈነጠዘ ሄደ፡፡
ሌላ ቀን መንገደኛው እንደልማዱ “ገንዘብ አምጣ” አለው፤ ሌባውን፡፡ “አልሰጥም” አለ ሌባው።
“ዋ! የላሟን ነገር!” ሲለው፤
“የፈለከው ቦታ ድረስ!” ብሎት ሄደ፡፡
መንገደኛው ተናዶ፤ ወደ መንደሩ አለቃ እየበረረ ሄደና፤ “እገሌ ላም ሰርቋል” ሲል ተናገረ፡፡
አለቃውም “እሱስ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አንተ ነህ ሌባ!”
“ለምን?” አለ መንገደኛው፡፡
“እስካሁን በልብህ ላሟን ይዘህ የምትዞር አንተ ነህ!” አለው፡፡
*   *   *
በአካል የሠረቀው ሌባ ሲባንን ይኖራል፡፡ በልቡ ስርቆቱን የያዘው የባሰ ሌባ፣ ከሌባ እየተሻረከ ሳይነቃበት ይኖራል፡፡ ይህ የሚሆንበት አገር ለከፍተኛ ጥፋት የተጋለጠ ነው፡፡ ቀና የሚመስለው መንገድ ሁሉ ዕውን ቀና ነወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የምንገለገልባቸውን ቃላት እንመርምር።
እንደ “ነፃነት”፣ “አማራጭ” እና “ዕድሎች” ያሉ ቃላት ከሚሰጡት ዕሙናዊ ጥቅም የበለጠ ቀስቃሽ ኃይል አላቸው፡፡ በተግባር ግን ገበያ ቦታ፣ በምርጫ ጊዜ እና በሥራ ቦታ አማራጭ ያለን የሚመስሉን “ሀ” እና “ለ”፤ ሌሎቹን ሆህያት ተትተው የተሰጡን ናቸው፤” ይላል ሮበርት ግሪን፡፡
አንድ መሠረታዊ የገዢዎች መርህ አለ፡-
“የመጨረሻው ምርጥ የማጭበርበሪያ ዘዴ፤ ለባላንጣህ አማራጭ የሰጠኸው ማስመሰል ነው። ያኔ ያንተ ሰለባዎች ጉዳዩን የተቆጣጠሩ እየመሰላቸው አሻንጉሊትህ ይሆናሉ፡፡ ከሁለት እኩይ ነገሮች አንዱን እንዲመርጡ አድርጋቸው፡፡ (Choosing between two evils) ሆኖም ሁለቱም አንተን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ዋናው ጥበብ፡፡” (ሮበርት ግሪን)
አማራጮችን አስፍቶ ያለማየት ድህነት፣ አንዱ የድህነታችን ምንጭ ነው፡፡ ይሄ አንድም ከዕውቀትና አቅም ማነስ፣ አንድም አርቆ የማስተዋል ባህል ከማጣት፣ አንድም ደግሞ በአፍንጫ ሥር ዕይታ ከመወጠር ሊከሰት ይችላል፡፡ ከታጠርንበት አጥር ባሻገር ማየት መልካም ነገር ነው። “ይቺን ያቀድኳትን በስኬት ከተወጣሁ” አመቱን እሰየው ብዬ ጨረስኩ፤” ማለት ሌላ እንዳናይ ሊገድበን የሚችል አካሄድ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ በአጭር ርዕይ ታቅበን ጊዜ ያመልጣል፡፡ በጀማ ጉዞ ከጀማው ጋር ከማዝገም በላቀ ንቃተ ህሊና መፈትለክ የሚያሻበት ጊዜ ነው፡፡
አንድ ህፃን ልጅ፤ “ወደፊት ምን ለመሆን ታስባለህ?” ተባለ አሉ ዘንድሮ፡፡
ልጁም፤ “ዲያስፖራ!” አለ፡፡ (ስለዲያስፖራ ስንናገር ትውልድን እናስብ!)
ዳያስፖራ ማለት፤ አንድ ተሰብስቦ፣ በአንድ ቦታ ተቀምጦ የነበረ ህዝብ ወይም ቋንቋ አሊያም ባህል፤ ሲበተን ወይም ወደሌላ ሲሰራጭ የሚሰጠው መጠሪያ ነው፡፡ አይሁዳውያን ከእሥራኤል ውጪ የተበተኑበትንም ሁኔታ የሚያመላክት ነውም ይላሉ፡፡ እንግዲህ ለኢትዮጵያውያንም እንደዚያው ነው፡፡
ኢትዮጵያ የውጪውን ዓለም ኢትዮጵያውያን መሰብሰቧ ደግ ነገር ነው፡፡ አያያዟ ምን ያህል ከኢኮኖሚዋ፣ ከፖለቲካዋ፣ ከዲፕሎማሲዋና ከባህሏ ጋር መስተጋብር ይኖረዋል? ዳያስፖራውያኑስ ምን ያህል ከልባቸው መጥተዋል? ተስፋቸው፣ ምኞታቸው፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ምን ያህል የጠለቀ፣ ምን ያህልስ ከጥቅም ባሻገር አገርና ህዝብን ያግዛል? የሚለው የነገ ጥያቄ ነው፡፡ እግረ መንገዳችንን፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ “ሰው ሆኖ ካሹት (ከፈተጉት) ጥቅም የማይሰጥ የለም” ያለውን ልብ ማለት ይጠቅማል፡፡
እንግዲህ መንገዱ ረጅም ነው፡፡ ከካሬ ሜትር እስከ ልብ ሜትር የሚያለካካ ነው! ማናቸውም ነገር አልጋ በአልጋ አለመሆኑን መገንዘብ ደግ ነው፡፡ ህጋዊውን፣ ቢሮክራሲያዊውንና ሰዋዊውን መንገድ በቀቢፀ - ተስፋ ለማያይ ሰው፣ ሁነኛና ቀና ብርሃን ሊያስተውልበት የሚችል ሁኔታ አለ። በተወሰነ ደረጃ ግን ሂደቱን ሊያሰናክሉ፣ ሊያቀጭጩና ሊያሟሽሹ የሚችሉ እንከኖች ይኖራሉ? ብሎ አለመጠበቅ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ “ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል፤ ተሸከም ያለው ታሥሮ ይጠብቀዋል” የሚለው ተረት መሠረታዊ፣ አገራዊ ፋይዳ የሚኖረው እዚህ ላይ ነው!  

Saturday, 15 August 2015 15:46

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ንባብ)
- የአዳዲስ መፃህፍት ክፉ ነገራቸው አሮጌዎቹን
እንዳናነብ ማድረጋቸው ነው፡፡
ጆን ውድን
- ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው በማንበብ ነው፡፡
ቢል ጌትስ
- ንባብ የአዕምሮ ባትሪዬን ለመሙላት
ያስችለኛል፡፡
ራሁል ድራቪድ
- እንደ ንባብ ርካሽና ዘላቂ ደስታ የሚያጐናፅፍ
መዝናኛ የለም፡፡
ሜሪ ዎርትሌይ ሞንታጉ
- ንባብ ለህፃናት መቅረብ ያለበት እንደ ግዴታ
ሳይሆን፤ እንደ ስጦታ ነው፡፡
ኬት ዲካሚሎ
- ንባብ ደስታ እንጂ ሥራ መሆን የለበትም፡፡
ጆአን ሪቨርስ
- ንባብ የማይታወቁ ወዳጆችን ያመጣልናል፡፡
ሆኖሬ ዲ ባልዛክ
- ያለ መፃህፍት መኖር አልችልም፡፡
ቶማስ ጃፈርሰን
- የመፃህፍት ገፆች ነፍስ የሚዘሩት ሲገለጡ
ብቻ ነው፡፡
ኤል.ጄ.ዴቬት
- ግሩም አንባቢ ዓለምን የመነቅነቅ ኃይል
አለው፡፡
አማን ጃሳል
- ጊዜህን በማሰብ ለማጥፋት የማትፈልግ ከሆነ
ማንበብ ጀምር፡፡
አማን ጃሳል
- ከንባብ ጋር ፍቅር ይዞኛል፡፡
ላይላህ ጊፍቲ አኪታ
- አንድ ሺ መፃህፍትን አንብብ፡፡ ያኔ ቃላት
ከአንደበትህ እንደ ወንዝ ይፈሳሉ፡፡
ሊሳ ሲ
- አንባቢ ከመሞቱ በፊት አንድ ሺ ህይወቶችን
ይኖራል፡፡ ጨርሶ የማያነብ ሰው ግን አንድ
ህይወት ብቻ ይኖራል፡፡
ጆርጅ አር.አር.ማርቲን

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ነው ተብሏል

   ከአዲስ አበባው ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ስዊድን ስቶክሆልም በመብረር ትናንት ማለዳ አርላንዳ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የእቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ተደብቆ የተጓዘው ኢትዮጵያዊ ጥገኝነት መጠየቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ እንደሆነ የተነገረለትና በሃያዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ የተገለጸው ወጣቱ፣ አውሮፕላኑ ማረፉን ተከትሎ ሰራተኞቹ ጭነት ሊያራግፉ በሩን ሲከፍቱ ክፍሉ ውስጥ ተደብቆ እንደተገኘ የጠቆመው ዘገባው፣ ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በተደረገለት የጤና ምርመራ ምንም አይነት የጤና ችግር እንደሌለበት መረጋገጡን ገልጿል፡፡
ለስምንት ሰዓት ያህል በርሮ አርላንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በደረሰው አውሮፕላን ተደብቆ የተገኘው ወጣቱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ መሆኑን የሚያሳይ የደረት ላይ መታወቂያ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሶ፣ ወደ ስቶክሆልም ኢሚግሬሽን ቢሮ ተወስዶ ጥገኝነት መጠየቁንም አመልክቷል፡፡
የአርላንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ምክትል መኮንን የሆኑት ስቴፋን ፋርዲክስ፤ ወጣቱ ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ እንደማይጠረጠር ገልጸው፣ በስዊድን አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች መሰል ድርጊት ተፈጽሞ እንደማያውቅና የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ማንኛውንም ከብት ያለ ንግድ ፈቃድ መሸጥ አይቻልም

በአዲስ አበባ የዳልጋ ከብት ግብይት ከትላንት ጀምሮ በደረሰኝ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ማንኛውም የቁም እንስሳት የንግድ ግብይት ያለ ንግድ ፈቃድ ማከናወን እንደማይቻልም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የከብት ግብይቱ የሚካሄደው በ5 የገበያ ማእከላት፡- በጉለሌ፣ የካ ካራሎ፣ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂና ኮልፌ ቀራኒዮ መሆኑን የገለፀው ቢሮው፤ ከእነዚህ ማእከላት ውጪ ምንም አይነት የቁም እንስሳት ንግድ ማካሄድ እንደማይቻል አስጠንቅቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺሳ መላኩ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ለጊዜው የደረሰኝ ግብይት ሥርዓቱ የሚመለከተው የዳልጋ ከብት (በሬና ላም) ብቻ ቢሆንም ወደፊት የበግና ፍየል ንግድም በደረሰኝ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
የልኳንዳ ማህበር ከግብር ጋር በተያያዘ ሂሳብ ማወራረድ በመቸገሩ ግብይቱ በደረሰኝ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ መጠየቁን ኃላፊው ጠቁመው፣ የደረሰኝ ግብይቱ የማህበሩን ችግር እንደሚፈታ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የደረሰኝ  ግብይቱ ህገወጥ እርድን፣ የቤት ለቤት ማደለብንና መሰል ህገወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችልና የህብረተሰቡን ጤናም ለመጠበቅ እንደሚያግዝ የተገለፀ ሲሆን የቁም እንስሳት ንግድ ግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንም ዓይነተኛ መፍትሄ ነው ተብሏል፡፡
እስካሁን በ5ቱ የገበያ ማእከላት የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ ፍቃድ እንዲያወጡ የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውንና አብዛኞቹም የንግድ ፍቃድ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ገመቺስ፤ ፈቃድ ሳያወጡ ተቀላቅለው እየሰሩ ያሉ ነጋዴዎችም ፍቃድ አውጥተው ወደ ህጋዊ ስርአት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የደረሰኝ ቁጥጥር ስርዓቱንም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንደሚከታተለው ታውቋል፡፡