Administrator

Administrator

  • ሥልጠናው 5G፤ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን--ያካትታል
       • ሴት መምህራንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሥልጠናው ተሳትፈዋል



           የትምህርት ሚኒስቴር ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር፤ “ሴቶችን በዲጂታል ክህሎት ማብቃትና የሴቶች አመራርን በቴክኖሎጂ መደገፍ” በሚል መሪ ቃል፣ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና ለሴት መምህራን መሰጠቱ ተገለጸ።
የመጀመሪው ዙር ስልጠና ከህዳር 12 እስከ ህዳር 14 ቀን 2015 የተካሄደ ሲሆን ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ሴት መምህራን በስልጠናው መሳተፋቸው ታውቋል። ሁለተኛው ዙር ስልጠና ህዳር 15 የተጀመረ ሲሆን ስልጠናው በዲጂታል ክህሎት (5G፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ክላውድ) እንዲሁም በሴቶች አመራር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ፣ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሁዋዌ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የሴቶችን የኑሮ ደህንነት በማሻሻል ረገድ  ዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለውን ፋይዳ እየመረመረ  ነው ብለዋል።
“ሴቶች በቴክኖሎጂ እንዲሳተፉ ለመርዳት እንዲሁም ዕምቅ አቅማቸውን እንዲያወጡና ህብረተሰባችንን ወደላቀ ብልፅግናና ፍትሃዊ መጪ ዘመን ይመሩ ዘንድ የበለጡ ዕድሎችንና መድረኮችን ለመክፈት ቁርጠኞች ነን” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ትምህርት ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ ዘላለም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ትምህርት ሚኒስቴር በICT ዘርፍ በሰው ሃብት ልማት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የትምህርት ዘርፉን የሚያግዝ ተግባራዊ ሥልጠና ለማግኘትም ሁዋዌን ከመሳሰሉ የግል ኩባንያዎች ጋር እንደሚሰሩ በአጽንኦት ተናግረዋል። ሁዋዌ ለሴቶች መምህራን ሥልጠና በመስጠት ላደረገው ትብብርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አንዳንድ ሰልጣኞች እንደተናገሩት፤ የክፍል ውስጥ የማስተማር ሂደቱ ይበልጡኑ ንድፈ-ሃሳባዊ በመሆኑ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ተግባራዊ ስልጠና ወሳኝ ነው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2008 አንስቶ ሁዋዌ በርካታ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ መርሃ ግብሮችንና ውድድሮችን በዓለማቀፍ፣ በክልላዊና አገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የጀመረ ሲሆን ከእነሱም መካከል፡ “የስኮላርሺፕ መርሃግብሮች፤ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር፤ ሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚ፤ ሁዋዌ ዴቨሎፐርስ ትሬይኒንግ፤ ሁዋዌ ክላውድ ዴቨሎፐር ኢንስቲቲዩት፤ ውመን ቴክ እና ቴክኖሎጂ ፎር ኢጁኬሽን” ይጠቀሳሉ፡፡
በተመሳሳይ ዜና፤ የ2022 “Seeds for the Future” መርሃ ግብር በኢትዮጵያ፣ ከህዳር 12 እስከ ህዳር 19 ቀን 2015 የተካሄደ ሲሆን፤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ60 በላይ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል።
መርሃ ግብሩ የ8 ቀናት የኦንላይን ስልጠና ሲሆን ከተማሪዎቹ የ15 ሰዓታት ሙሉ ትጋትን የሚጠይቅ እንደሆነ ተጠቁሟል። ሥልጠናው በቁልፍ ቴክኖሎጂዎች (5G፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ላይ መሰረታዊና ከፍተኛ ደረጃ ኮርሶችን የሚያካትት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

  ከዕለታት ከአንድ ቀን ዘጠኝ ጓደኛሞች ወደ አንድ ሩቅ አገር ለመሄድ መንገድ ይጀምራሉ። ብዙ ርቀት እንደሄዱ ይመሽባቸዋል።
አንደኛው፤
“ጎበዝ፤ ከዚህ ወዲያ ከቀጠልን ጨለማው ይበረታብናል። ስለዚህ እዚህ ተኝተን እንደር” አለ።
ሁለተኛው፤
“ጥሩ ሀሳብ ነው። ግን ደህንነታችን ለመጠበቁ ምን መተማመኛ ይኖረናል?”
ሦስተኛው፤
“በተራ በተራ የሚጠብቅ ሰው እንመድብና ተረኛው ሲደክመው ቀጣዩን ጠባቂ ቀስቅሶ ይተኛ” አለ።
ሁሉም በመጨረሻው ሀሳብ ተስማማና “ስለ አተኛኘት ቅደም ተከተል እጣ እናውጣ” ተባባሉ። በወጣባቸው እጣ መሰረትም ተኙ።
ሌሊት ላይ አንድ የመቆረጫጨም ድምጽ ተሰማ።
“የምንድን ነው የሚሰማው ድምጽ” ተባባሉ።
ከዳር የተኛው ሰው መለሰ፡-
“ጎበዝ ዝም ብላችሁ ተኙ፤ አያ ጅቦ እኔን እየበላ ነው!” አለ።
አያ ጅቦ ወደሚቀጥለው ተረኛ ተሸጋገረ።
በዚህ ሁኔታ ሁሉም “ዝም በሉ” እያሉ፤ ዐይናቸው እያየ ተበልተው አለቁ ይባላል!
***
በየአሮጌው መመሪያና ህግ፣ ያለ አንዳች ማሻሻያ እየተጎዳዱ መገዛት ከጀመርን ብዙ ሰነበትን። አዲስ አውጥተናል ብንልም፤”አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን” የሚባለውን አይነት  ነው (Old wine in a new bottle እንዲል ፈረንጅ)
መንግስትና መንግስት፤ በተቀያየረ ቁጥር ህዝብ ቢወድም ቢጠላም፣ ያንን ተቀብሎ መገዛት እጅግ ከመለመዱ የተነሳ እንደተፈጥሮ ህግ መወሰዱ፣ እንደ ፀሀይ  መውጣትና መጥለቅ ከሆነም ሰንብቷል።
በመካከል “ይሄኛው መንግስትና ህግ አይሻኝም” የሚል ግለሰብ ወይም ቡድን አሊያም ፓርቲ ቢወለድ፤ ወይ ይታሰራል፣ ወይ ይወገዳል አሊያም ስርዓተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል። ከታሪክ እስከ ዛሬ ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ ከባንዳ እስከ ዘመናዊ አድር-ባይ፣  አሸርጋጅና አቀንቃኞችን የፈሰፈልነው፣ በዚህ “ጥበብ” እና “ዘዴ” ነው። ሌላው ቢቀር በጉርሻ ወይ በንክሻ “የሚባለውን ፍልስፍና ማንም ጅል አይስተውም ( Carrot and stick እንዲሉ)። በዚህ መልኩ ሲታሰብ እያንዳንዱ መንግስት ሊፈተሽ ይገባዋል ማለት ነው።
በተለይም አሁን ከመደብ ፖለቲካ ይልቅ የብሔር ብሔረሰብና ሐይማኖት እንደ ዘመን አመጣሽ ዘፈን በሚቀነቀንበት ሰዓት፣ የፖለቲካው አካሄድ እጅግ እየተወሳሰበ መምጣቱን ከነትርፍና ኪሳራው ለማስላት ከባለኪዮስክ ትንተና (Shop-keeper’s analysis) የበለጠ ስሌት አይጠይቅም። “ማንኛውም መሪ እበልጥሃለሁ” በሚል እሳቤ ሲያምታታ፣ ቀላል የዓሳ መረብ ውስጥ ሲገባ ታገኘዋለህ ይላሉ ጸሐፍት። የእኛም አገር መሪዎች ታሪክ ይሄን የሚያጸኸይ ነው። ይሄንን ለማየት የፖለቲካ ሳይንቲስት ማማከርም፣ አዋቂ-ቤት ሄዶ መስገድም አይጠይቅም!
በኢትዮጵያ አገራችን ከተማሪና አስተማሪ ትግል ጋር መተዋወቅ ትምህርት ቤት መግባትን አይጠይቅም። እንዳሁኑ ጊዜ 13,000 ተማሪ የተንሳፈፈበት ዘመን ግን ኖሮ አያቅም። ሚኒስትሩም ያሳዝናሉ። የትምህርት ስርዓት ከተጀመረ ፊደል ከተቆጠረ ጀምሮ፣ ይህ ሁኔታ አብሮን የኖረ ነው። አንዳንድ መሪዎቻችንም “እጁን እኪሱ ከትቶ፣ ባዶ ኪስ የሚያገኝ መምህር ከእንግዲህ አይኖርም” ብለውም ነበር። ሆኖም ዛሬም ከደሞዝ ጥያቄ እስከ ሥራ ማቆም አድማ ድረስ ሲገፋ እየታዘብን ነው! የሚገርመው ይህንኑ መሰል ጥያቄ ለወቅቱ ትምህርት ሚኒስትር ቀርቦ እንደነበር መታወሱ ነው። የታሪክ አዙሪት! ጥናቱን ስጠን!
እውነቱን ለመናገር የአምባ-ገነን መሪዎች ዴማጎጂም ተለይቶን አያውቅም። እነ ሂትለርስ እንደ ጎብልስ ያሉ አማካሪዎች ነበሯቸው። የእኛስ እነማን ይሆኑ? ወጣ ወረደም ያለን አማራጭ ከዕለታት አንድ ቀን ስለ ኤች አይ ቪ እንዳስጠነቀቅነው፡-
“ክፉ ደጉን ያየን፣ ነንና ጎረቤት
ያንተ ቤት ሲንኳኳ፣ ይሰማል እኔ ቤት!”
የሚለውን ስንኝ እንደግመዋለን!
ነግ በእኔ ነው ጎበዝ!! ትምርታችንን ይግለጥልን!

 በመንግስት ምህሪት ከእስር ተለቀው የነበሩት የህውሃት መሥራችና አመራሩ አቶ ስብሐት ነጋ ለህክምና ወደ ውጪ አገር እንዳልሄድ ከህግ ውጪ በፌደራል ፖሊስ ተከለከልኩ ሲሉ ክስ አቀረቡ።
አቶ ስብሐት ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ መሰረታዊ መብቶች ጉዳዮች ችሎት ትናንት ባቀረቡት ክስ እንዳመለከቱት፤ “ለህክምና ወደ ውጪ አገር እንዳልሄድ በፌደራል ፖሊስ  ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከቦሌ አየር ማረፊያ እንድመለስ ተደርጌአለሁ” ብለዋል። አቶ ስብሐት ነጋ በጠበቃቸው አማካኝንነት ባቀረቡት ክስ ላይ እንዳመለከቱት፤ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመቻቸውን ህጎች ባልተከተለና በህገ-መንግስቱ የተቀመጠውን የዜጎችን በነፃነት መንቀሳቀስ መብት በሚጋፉ መልኩ ፍርድ ቤት ሳያዝ ፖሊስ ከስልጣኑ ውጪ የጉዞ እገዳ እንደጣለባቸው ተጠቁሟል።
የአቶ ስብሐት ነጋን ክስ የተቀብለው ፍ/ቤቱ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ፖሊስ መልስ ባለማቅረቡ ሳቢያ መልስ የመስጠት መብቱ እንዲታለፍ ብይን ሰጥቷል። በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠትም ለመጪው ረቡዕ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሥራ አመራር መስክ የካበተ ልምድ እንዳላቸው የተነገረላቸው  የ60 ዓመቱ ፈረንሳዊ  ሚስተር ሄርቬ ሚልሐድ፤ ከጥቅምት  2015 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በካስቴል ግሩፕ መሾማቸው ተገለጸ፡፡
ሚስተር ሚልሐድ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አህጉሮች በሚገኙ በርካታ አገራት  ከሚሠሩ ዳኖኔ ግሩፕን ከመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ያዳበሩ ሲሆን፤ በዳኖን ግሩፕ ብቻ ለሃያ ዓመታት የኦፕሬሽንስ  ም/ፕሬዚዳንት (WW VP Operations) እንዲሁም  ለአልጀሪያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡   
በመቀጠልም የl’Européenne d’Embouteillage ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ እንዲሁም የጃፓን መጠጦችና አልኮል ኩባንያ የሳንቶሪ (Suntory Group) አካል የሆነው የኦራጂና ሳንቶሪ ፈራንስ (Orangina Suntory France (OSF) የኦፕሬሽንስ ም/ፕሬዚዳንት (VP Operations) በመሆን  650 ሠራተኞችን ያቀፉ አራት ፋብሪካዎችን እንደመሩ፤  ኩባንያው ለአዲስ አድማስ የላከው መግለጫ ያመለክታል።
ሚስተር  ሚልሐድ የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን እንደ አዲስ ነድፈው የተገበሩ፣ ለስኬታማ ሥራ አፈፃፀም፣ የደንበኞች አገልግሎትና ወጪ ተገቢ ትኩረት የሚሰጡ፣ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ድርጅቶች የሥራ ቅልጥፍናን ከሠራተኞች ደህንነት  ጋር ባጣጣመ መልኩ አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የቻሉ የሥራ መሪ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
በሚያዝያ 2010 ዓ.ም ካስቴል ግሩፕን ከተቀላቀሉ በኋላም፣ ሶዲብራን (ኮትዲቯር)፣ ኤስኤቢሲን (ካሜሩን) እና የመካከለኛ አፍሪካውን (Centrafrique) MOCAF በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
በቅርቡ ሚስተር ሚልሃድ የካስቴል ማላዊ ሊሚትድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን ላለፉት አራት አመታት ያገለገሉ ሲሆን ለድርጅቱ ባከናወኑት ታላቅ ሥራ “ድርጅቱን ከመዘጋት ያዳነ ሥራ አስኪያጅ” የሚል ስያሜ መቀዳጀታቸው ታውቋል፡፡   
በተለያዩ ባህሎች ውስጥ አልፈው ካካበቱት ልምድና ለሠራተኞች ደህንነት እንዲሁም ለማኀበራዊ ኃላፊነት ሥራ ከሚሰጡት ትኩረት አንፃር፣ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፣ የቆየውን የቢጂአይ ኢትዮጵያ ስኬታማ የንግድ ሥራ ጉዞ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የማህበረሰብ ድጋፍን ባህል አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
“አዲሱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቢጂአይን የተቀላቀሉበት የአሁኑ ወቅት በንጽጽር እጅግ ምቹ ሊባል የሚችል ነው፤ ከምክንያቶቹም መካከል ዋነኛው በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማብቃቱን ተከተሎ፣ በአገር ደረጃ የሰላም ተስፋ ማንሰራራቱ ሲሆን እንደ ድርጅትም ለዓመታት ሥራ ፈትቶ የቆየው የራያ ቢራ ፋብሪካ ሥራ የሚጀምርበት ዕድል መገኘቱ፤ እንዲሁም  ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ ቢራ ፋብሪካን መግዛቱ፣ ተጠቃሽ ናቸው።” ብሏል ኩባንያው በመግለጫው፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሚስተር ሚልሃድን “እንኳን ደህና መጡ”  በማለት በደስታ መቀበሉን የጠቆመው መግለጫው፤ በዓለም አቀፍ መጠጥ ንግድ ካካበቱት  የረዥም ጊዜ  ዘርፈ-ብዙ ልምድ ለመጠቀም መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ላለፉት 25 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ የቆየ ደርጅት ሲሆን መቶ ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ብቁና የተገባ ወራሽ መሆኑ ይታወቃል።

Monday, 28 November 2022 16:53

‹‹የፈረንጅ ሚስት››

 ደራሲ፡- እስከዳር ግርማይ (የ‹‹ሰውነቷ›› ፊልም ደራሲ ተዋናዪትና ፕሮዱዩሰር እንዲሁም የ‹‹ጥቁር እንግዳ›› ፊልም ፕሮዱዩሰርና ተዋናዪት)
ሒሳዊ ዳሰሳ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ
ንቁ፣
……ብቁ፤
ቁጡ፣
…...ቅንጡ፤
ጥንቁቅ፣
……ምጡቅ፤
ድንብልቅ፣
……ፍልቅልቅ፤ (ለእስከዳር ግርማይ)
መነሻ፡-
ሪዛሙ ደራሲ በርናንድ ሾው ‹‹Major Barbara›› በሚል ድርሰቱ አንዲት ልባም ሴት አስተዋውቆናል። በበኩሌ የበዓሉ ግርማ ሴቶችም ለእኔ ጎምቱ ናቸው፤ እነ ሒሩት፣ ሉሊት፣ ፊያሜታ…
…ካለፈው ዓመት (2014 ዓ.ም.) አንስቶ የሴት ደራሲያን ቁጥር እየተበራከተ መምጣት ለሥነ-ጽሑፋችን ጉልህ አበክሮ ይኖረዋል፤ በጣም ደስ ተሰኝቼአለሁ፤ ለመሆኑ ሴት የሌለችበት ነገር ምኑ ይጥማል?...
….ከእነዚህ መካከል እስከዳር ግርማይ አንዷ ናት፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?›› በተነበበ በወራት ልዩነት ‹‹የፈረንጅ ሚስት››ን አስነበበችን፤ ለአሁን ስለ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› እናውጋ፡-
‹‹የፈረንጅ ሚስት›› በተሰኘ ድርሰት እስከዳር ግርማይ በፈረንጅ ሚስትነት - የእራስዋን ተመክሮዎች፣ ገጠመኞች አሳዛኝ ወላ አስደሳች ቀናት፣ ሞግታ የረታችባቸውን አጋጣሚዎች - ከሌሎች - ከወዳጅ ጓደኞችዋ (ከፈረንጅ ሚስቶች) ጋር እያጣቀሰች የተረከችበት ድርሰት ነው፤ ቋንቋው ግልጽ ግና ውብና ትረካው ፈጣን ድርሰት ነው፤ ሳነበው እንዲህ ሆነ፡-   
1ኛ. ነገረ መቃን/Frame-work - አንድን የድርሰት ወላ የጥናታዊ ጽሑፍ ሀሳብ ለማስኬድ መቃን ሁነኛ ዘዴ ነው፤ ፎቶ በመቃን ሲሆን ውበት ይኖረዋል። እስከዳር የታላቁን ባለቅኔ የጸጋዬ ገ/መድኅንን ‹‹አድባር›› የሚል ግጥምና ከቲያትሮቹ መካከል ደግሞ ‹‹ማነው ምንትስ?›› የሚል ሴቶችን የሚያበቃ ሀሳብ ላይ ተመርኩዛ፣ ወይም መቃን አድርጋ በመገልገል ሀሳቧን ትተርካለች። በእርግጥ ድርሰቱ በተለያዩ ገጠመኞች፣ ትንታኔዎች፣ መዘርዝሮችና ምሳሌዎች የተሞላ ቢሆንም ሲቋጭ ከመቃኑ ፈቅ አይልም፤ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ አበክሮ እንዳላቸው ይጠቁማል የሚል ዕምነት አለኝ። አልቆጨኝም፤ ረክቼአለሁ!!
2ኛ. ነገረ ጥናታዊ ጽሑፋዊነት - ድርሰቱ ለቀለም ትምህርት ብሎም ለዓለም-አቀፍ ንባብ መዋል የሚችል ጥናታዊ ጽሑፍ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ደራሲዋ ተሳታፊ ቀጂ እና የጥናቱ አካል በመሆን /participant observant/ በፈረንጅ ሚስትነት የገጠማትን ዕክል፣ መድሎ፣ ኢ-ፍትሕና ሌላም ነገር ትተርካለች፤ ትረካው ደግሞ በሁኔታዎችና በሰዎች አኳኋን ላይ መሠረት ያደረገ - interpretive analysis ነው (እመለስበታለሁ)። እናም ድርሰቱ ሴቶችን በተመለከተ ለሶሾሎጂ፣ ለሥነ-ልቡና፣ ለምጣኔ-ሀብትና ለሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ሁነኛ ምንጭ በመሆን ያገለግላል ብዬ አምናለሁ። ‹‹Challenges that Hampers Yeferenj Mist›› በሚል ርዕስ ለዓለም እንደምታስነብብ አልጠራጠርም።    
3ኛ. ነገረ ቁጣ - በወንዴ ጾታ በኩል ትክክል የሚመስሉ ግና መረንና መቀጮ የሆኑ ድርጊያዎች፤ በትንሹ አላስፈላጊ፣ ወይ፣ መናኛ፣ ወይ፣ ክብረ ነክ ቃላት አጣጣላችን ምን ያክል የሴትዋን መንፈስ እንደሚያስቆጣ፣ አልፎም ጫና እንደሚያሳድርባት የሚያስገነዝብ ድርሰት ነው፤ መረንና ፈር ከሳቱ አባባሎች እስካልተቆጠብን ድረስ የሴቶቹን ሥነ-ልቡና እንደምናለምሽ የሚያስጠነቅቅ ድርሰት ነው፤ ለምሳሌ፡-
በገጽ፡- 23፣ 34 እና በሌሎች የቀረቡ ተረኮችን ማየት ይቻላል።    
4ኛ. ነገረ ትንተና/interpretive analysis - በqualitative research መስክ ተመራጩን የትንተና ዘዴ (interpretive analysis) በመጠቀም፣ የሰዎችን ፊት በመፈተሽ ብሎም የቃላት አጣጣልን ከግምት በማስገባትና ከሁኔታው/ከጉዳዩ በማናበብ የሚከናወን ትንተና ማለት ነው፤ ለምሳሌ፡-
በገጽ 32፣ 33 ላይ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር የምታደርገውን ውይይት፣ ትንተና እና ሌሎችንም ማየት ይቻላል፤  
5ኛ. ነገረ ፍካሬ - እውነትን በሥነ-ውበት መፈከር የዚህ ድርሰት በጎ ጎኑ ነው፤ አንዳንድ ውበታም ቃላት፣ ገላጭ ሐረጋትና ዓረፍተ-ነገሮች በብዛት ይስተዋላሉ። የዓረፍተ ነገር አጀማመርዋም ቢሆን መሳጭና ሁሉን አቀፍ ነው።  
ማሳያ፡- ገጽ 36 ‹‹የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ከባለቤቴ ጋር ተፋትተን ንብረት ክፍፍል ውስጥ ብንገባ፣ ባለቤቴ መቀመጫዬን ከራሱ ድርሻ ንብረት ጋር ሳይደምረው አይቀርም….››
6ኛ. ነገረ ሚዲያ እና ክብረ-ነክ ጋዜጠኞች - በድርሰቱ አንዳንድ ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያዎች ክፍተት ተቃኝቷል፤ መረንና ለሙያቸው ክብርና ግንዛቤ የሌላቸው ጋዜጠኞች ምን ያክል የሴትዋን መንፈስ እንደሚያስቆጡ ያሳስባል፤ ለምሳሌ፡-
ከገጽ 32-41 ያለውን ውይይት መመልከት ተገቢ ነው።
7ኛ. ነገረ ተጽዕኖ - ድርሰቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ (በውጭም በአገር ውስጥም) በሚገባ ያስቃኛል፤ የሞራል፣ የአካል፣ የመንፈስ፣ ኢ-ፍትሐዊነት…ወዘተ ጫናዎች በፈረንጅ ሚስቶች ላይ ሲደርሱ እናያለን።
8ኛ. ነገረ ተራ ግምት/wild-guess - የውጭ አገር ብሎም የአገራችን ሰዎች ለፈረንጅ ሚስት ያላቸውን ተራና መናኛ ግምት ከዚህ ድርሰት መገንዘብ ይቻላል፤ የፈረንጅ ሚስት በራስዋ ጥረት እንደማትኖር አድርጎ መሳል አንዱ ክፍተት እንደሆነ በመረጃ አስደግፋ ትሞግታለች።
9ኛ. ነገረ ሙግት/discourse - በዚህ ድርሰት ያልተገባ ንግግርና ተራ ግምት ሲገጥማት ከተሳሳተው ግለሰብ ጋር ቀጥተኛና ግልጽ ውይይት በማድረግ የተሳሳተ ግንዛቤን መቀየር እንደሚቻል ያሳየችበት መጽሐፍ ነው፤ ሴቶች በምክንያታዊነት ላይ ተንተርሰው ክርክርና ሙግት ሲገጥሙ ታስቃኛለች፤ ሴቶችን ማብቃት ነው ይኼ! ለአብነት፡-
ገጽ 74 ላይ ደራሲዋ/ተራኪዋ ከአንድ የአረብ ሰው ጋር ስትሞግት ወላ ስታሳምን እናገኛለን!
10ኛ. ነገረ መሰናሰል እና የፍሰት ወጥነት - ድርሰቱ ከምዕራፍ ምዕራፍ የተያያዘና በቂ መዘርዝሮችን ያቀፈ ነው። በተጨማሪም ምሳሌዎችና ምዕራፎቹ ከዋናው ሀሳብ የማይጋጩ ናቸው፤ ረክቼአለሁ!!
11ኛ. ነገረ ምክረ-ሀሳብ/recommendations - ደራሲዋ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ክስተቶች ወ ገጠመኞች ተንትና ካቀረበች በኋላ፣ ‹ከእጄ ውጪ› ብላ አትገላገልም፤ ለጠቀሰቺው ችግር መፍትሔ ይሆናሉ ብላ ያሰበችውን (ሚዛን የሚደፉ) የምክር ሀሳቦችን ትለግሳለች። እንዲያ ይሻላል!!
መውጪያ፡-
በጥናታዊ ጽሑፍ አንድ የተለመደ አባባል አለ፤ ‹‹Publish or Perish›› ይሉት ብሒል ነው ታዲያ። የምርምር ወላ የድርሰት ሥራዎች ለውጥ እንዲያመጡ ከተቻለ ለኅትመት ማብቃት፤አሊያ ወዲያ መጠቅለል። በአጠቃላይ፣ አንድ ድርሰት ወላ ጥናታዊ ጽሑፍ በተደራሲው ወይም በተጠኚው ላይ ፈጣን አሉታዊ ጫና ማሳደር ከቻለና ትክክለኛውን መንገድና መፍትሄ እንዲመርጥ ካስቻለ ግቡን መቷል ማለት ይቻላል፤ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› በእራሴ ላይ ፈጣን እርምጃ እንድወስድ አድርጎኛል፤ ምናልባት ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ሚስቶች ወላ ለሴቶች የነበረኝን ተራና መናኛ ግምት እንድከልስና ትክክለኛውን እሳቤ እንድፈትሽ አስችሎኛል ብዬ ብናገር ከሕሊናዬ አልጋጭም!!   

በኬንያ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የተኛ ህፃን እየደነሰች ስታነቃቃ የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ በቲክቶክ መልቀቋን ተከትሎ፣ በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆናለች፤ የ22 ዓመቷ የነርሲንግ ተማሪ ሉክሬስያ ሮባይ፡፡
ቪዲዮው በኪታሌ ካንቲ ሪፈራል ሆስፒታል በሥራ ላይ ሳለች የተቀረፀ መሆኑን ተናግራለች- ሮባይ። በሆስፒታሉ ውስጥ ህመምተኞችን እየዞረች ስትጎበኝ አንድ የተከፋና የተደበተ ህፃን ማግኘቷን የምታስረዳው ወጣቷ ነርስ፤ በተወዳጅ የህጻናት ዘፈን እየደነሰች  ልታነቃቃውና ልታስደስተው መወሰኗን ትገልጻለች።
“ታማሚው  እግሩ ላይ ስብራት ደርሶበት ወደ ሆስፒታሉ የገባ ሲሆን የፈራ ይመስል ነበር። ወዲያው ሙዚቃውን ከሞባይል ስልኬ ላይ በማጫወት መደነስ ጀመርኩኝ፤በዚህም ህጻኑ ተነቃቃ። እንደ ነርስ ህመምተኞቼ ደህና መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብላለች፤ ሮባይ፡፡
ወጣቷ የጤና ባለሙያ  የዘየደችው መላ ሰርቶላታል። ግትር ብሎ ተቀምጦ የነበረው በሽተኛ ህፃን፤ እጆቹንና እግሮቹን ባለበት ሆኖ ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ፊቱም በፈገግታ ፈክቷል፤ ዕድሜ ለዳንሰኛዋ ነርስ፡፡  
በዚህም አስደማሚ ተግባሯ የአያሌ ኬንያውያንን ልብ አሙቃለች፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት በቲክቶክ የለቀቀችው ይኼ አጭር ቪዲዮ፤ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዕይታዎችንና  በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶችን አግኝቶላታል፡፡
ፎለፎሏ ነርስ፤ ዳንስ በጥልቅ ስሜት የምትወደውና በዙሪያዋ ለሚገኙ ሁሉ የተስፋ መልዕክት ለማስተላለፍ የምትጠቀምበት ጥበብ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡
“ለዳንስ ጥልቅ ፍቅር አለኝ። አብሮኝ የተፈጠረ ነው። በዚህ ህይወታችን  ድንቅ ነገሮችን የሚያበረታታ ህብረተሰብ ወይም ባህል አካል መሆን ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።” ብላለች ሉክሬስያ።
የሉክሬስያ አለቃ የሆነችው ቤቲ ናልያካ፣ እቺ ተማሪ ነርስ በልምምድ ጊዜያቶቿ  ላሳየችው ብቃትና ሰብአዊ  ተግባር አወድሳታለች፡፡
“ሮባይ ጎበዝ ተማሪ ናት። አንድ ስራ ስንሰጣት በቅጡ እንደምታጠናቅቀው እርግጠኞች ነን። ምንጊዜም ፈታኝ ጉዳይ ሲገጥማት ጥያቄ የምትጠይቀውና ከሠራተኞቹ ጋር የምትተባበረው እሷ ናት። ለእርሷ የወደፊቱ የነርሲንግ ሙያ ብሩህ ነው።” ስትል ናልያካ መስክራለች፡፡
ነርስነት የዕድሜ ዘመኗ ጥልቅ ፍላጎት እንደነበር የምትገልጸው ሉክሬስያ፤ ሁልጊዜም ሰዎችን መርዳትና ከስቃያቸው መገላገል ትሻ  እንደነበር ጠቁማለች፡፡
“ሁልጊዜም መስራት የምፈልገው ነገር ነው። ከውስጤ ነው ፈንቅሎ የወጣው፡፡  ከልጅነቴ ጀምሮ የህክምና ባለሙያ ለመሆን እፈልግ ነበር። የታመሙትን መንከባከብ እሻ ነበር። ሌላ ሙያ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም…አብሮኝ የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ” ብላለች።
ያለ ወላጅ ያደገችው ሉክሬስያ፤የትምህርት ጉዞዋ በብዙ ውጣውረዶች የተሞላ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ እዚህ ደረጃም የደረሰችው በነፃ የትምህርት ዕድልና በስፖንሰርሺፕ ነው፡፡
የትራንስ ንዞያ ካንቲ አስተዳደር የቀራትን የአምስት ወር የነርሲንግ ኮርስ ክፍያ ለመሸፈን ቃል የገባላት ሲሆን፤ ትምህርቷን ስታጠናቅቅም ለህመምተኞቿ በፍቅር በደነሰችበት ሆስፒታል ውስጥ እንደሚመድባትም አረጋግጦላታል። በዚህም የ22 ዓመቷ ወጣት ህልም እውን ይሆናል ብሏል፤የኬንያው ሲቲዝን ቴሌቪዥን።

Saturday, 26 November 2022 00:00

ደብዳቤ

 ከዳግማዊ ምኒልክ ለፕሬዚዳንት ሩዝቬልት የተጻፈ ደብዳቤ

      ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር፣ ንጉሠ-ነገሥት ዘኢትዮጵያ።
ይድረስ ለክቡር የዩናይትድ እስቴት መንግሥት ፕሬዚዳንት ሮዝቤል።
ሰላም ለእርስዎ ይሁን።
ባለሙሉ ስልጣን ሆኖ ለመጣው መልክተኛዎ ቆንስል ጀነራል እስኪነር የላኩት ደብዳቤ ደርሶኛል። እስካሁን በኔና በርስዎ መንግስት የፍቅር መላላክ አልነበረም እንጂ ከጥንት የሁለታችን አገር ነጋዴዎች እየተመላለሱ ይነግዱ ነበር። በፍቅርና በንግድ ውል ከተስማማን፣ የሁለታችን መንግስት ፍቅራችን እየበረታ ለዘላለም እንዲኖር ተስፋ አለን። ፎቶግራፍዎና ካገርዎ አዲስ የተሰራ ጠበንጃ፣ የጽፈት መኪና ደርሶኛል።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ። እኔም አዲስ ስለተጀመረው ፍቅራችን መታሰቢያ ሁለት የዝሆን ጥርስ፣ ሁለት አንበሶች ልኬአለሁ። ይህን ጥቂቱን ስለብዙ አድርገው ይቀበሉኝ። እርስዎንና የዩናይትድ እስቴት መንግሥት ሕዝብን እንዲጠብቅ እግዚአብሔርን እለምናሁ።
ታህሳስ 17 ቀን 1896 ዓመተ ምሕረት አዲስ አበባ ከተማ ተፃፈ።

  - አብን በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ጠይቋል
    - ኦፌኮ ለችግሮቹ መባባስ “አብን”ን ተጠያቂ አድርጓል
     
        በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችና በንፁሃን ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)እርስ በርስ እየተካሰሱ ነው፡፡
አብን  በክልሉ በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም መንግስት በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ጠይቋል። ኦፌኮ በበኩሉ፤ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ችሮች መባባስ ተጠያቂው አብን ነው ብሏል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ላለው ጥቃት ኦፌኮ እና ኦነግን ተጠያቂ ያደረገው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ በንፁሃን ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅና የመከላከያ ሠራዊቱን በስፍራው እንዲያሰማራ ጠይቋል።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ፣የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ጭምር በጥቃቱ ይሳተፋሉ ያለው አብን፤ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ብሏል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ በንፁሃን የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉንና ለዚህም የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የአብን ሥራ አስፈጻሚ አባልና የብሔራዊ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያምን ጠቅሶ ዶቼቬሌ ዘግቧል።
 ውንጀላውን የሚቃወመው ኦፌኮ በበኩሉ፤ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እያጋጠሙ ላሉት የፀጥታ ችግሮች አብንን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ “በአገሪቱ ውስጥ ሁልጊዜ ግጭት እንዲፈጠር የሚቀሰቅሱት የአብን አባላቶች ናቸው፤ ኦፌኮ ጦርነትን አይፈልግም።” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው፡፡
“ኦፌኮ የሰሜኑን ጦርነት ባወገዘበት ወቅት አብኖች በጦርነቱ ተካፍለዋል፤ ህገ-መንግስቱ እንዲፈርስም ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ግጭቱ እንዲባባስና እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት የሚያመላክት ነው” ሲልም አክሏል፤ ፓርቲው፡፡
አሁን በአካባቢው የተፈጠረውን ቀውስ ለማስቆም የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግስታትና ሁሉም በኦሮሞና በአማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሃላፊነት አለባቸው ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆም በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኦፌኮ በበኩሉ፤ በዚህ ዘመን ጠመንጃ ይዞ መገዳደል ተገቢ ባለመሆኑ ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይኖርብናል ሲል አሳስቧል።
በሌላ በኩል፤ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቃለምልልስ ያደረገው  ታዋቂው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ ሸኔ ሕዝብን እየገደለና እየዘረፈ የራሱን ምቾት ለመጠበቅ የሚንቀሳቀስ የዘራፊ ስብስብ ነው ሲል  ተናገረ።
“ሸኔ እንደ ሀገር በህዝብ ላይ ያደረሰው ተጽእኖ ከባድ ቢሆንም፤ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በተለይ በኦሮሞ አርሶ አደር ላይ የሚፈጽመው ዘግናኝ ግፍ ደግሞ ለመናገር እንኳ የሚከብድ ነው።” ብሏል፤አትሌቱ፡፡
የሕዝቡ ሰቆቃ እንዲያበቃ የሸኔ ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ እንዲያገኝ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም  አትሌቱ ጠቁሟል።
ቀደም ሲል የቡድኑ እንቅስቃሴና ግፉ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነበር ያለው አትሌት ፈይሳ፤ አሁን ላይ ግን ግፉም እንቅስቃሴውም በጣም ስለሰፋ ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት ካልተሰጠ መዘዙ ከአሁኑ የከፋ ይሆናል ብሏል።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመለካከቶች ሸኔን መስመር ለማስያዝ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ውስብስብ እንደሚያደርጉት የጠቆመው አትሌቱ፤ ሸኔን ለመዋጋት ባለው ጠንካራ አቋም ምክንያት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ አንዳንድ አካላት ጫና እንደሚደርስበትም አልሸሸገም።

  ከሽንብራ ዱቄትና ከተለያዩ የምግብ ግብአቶች የሚዘጋጅ ብስኩት መመረት ጀመረ

       በአገራችን የመቀንጨር አደጋ 37 በመቶ የደረሰ ምጣኔ ያለው ሲሆን ችግሩ በስፋት የሚታየው ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ እንደሆነ ተገለፀ። ይህ የተገለጸው ለህጻናት አካላዊና አዕምሮአዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል የተባለና ከሽንብራ ዱቄትና ከተለያዩ የምግብ ግብአቶች የሚዘጋጅ ብስኩት መመረት መጀመሩ ይፋ በተደረገበት መርሃግብር  ላይ ነው።
መሰረቱን በዴንማርክ ያደረገውና በልማትና እርዳታ ላይ አተኩሮ በአገራችን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በጋምቤላ ክልሎች ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀሰው “Dan Church Aid (DCA)” ህፃናትና እናቶች ላይ ትኩረት ባደረገውና “Sustianable Food partnership for better Nutrition through inclusive value chain in Ethiopia (SFP)” በተሰኘው ፕሮጀክቱ፣ በሞያ የምግብ ኮምፕሌክስ መመረት የጀመረው ሰኒ ብስኩት፤ ህፃናትን ለመቀንጨር ችግር የሚዳርጋቸውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።
ይህ ለህጻናት እድገት አስፈላጊ በሆኑ የምግብ ግብዓቶች ተመርቶ የቀረበው ብስኩት፤ በአገራችን በተለይም ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ በስፋት ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግም በዚሁ ዝግጅት ላይ ተገልጿል።

 በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረጉ

        ኢትዮ ቴሌኮም እና ሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ፣ የሲኔት ሶፍትዌር ተጠቃሚ አጋሮች ደንበኞቻቸው የአገልግሎትና የግብይት ክፍያቸውን በቴሌብር አማካኝነት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን አሰራር ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ተግባራዊ አደረጉ::
 ይህም አሰራር ቴሌብርንና ሲኔት ሶፍትዌርን በማስተሳሰር፣ የሲኔት ሶፍትዌር ተጠቃሚ አጋሮች ደንበኞቻቸው ግብይት ሲያከናውኑ፣ ቴሌብርን ተጠቅመው፣ ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
በተለይም ይህ አሰራር የሲኔት ሶፍትዌርን በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች፣ ፋርማሲዎች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ የመዝናኛና የመስተንግዶ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች መሰል ተቋማት፣ ደንበኞቻቸው ቴሌብርን በመጠቀም፣ በቀላሉ የተለያዩ የአገልግሎትና የግብይት ክፍያዎቻቸውን እንዲያከናወኑ እንደሚረዳቸው ተጠቁሟል፡፡
በዚህም መሰረት ደንበኞች ለአገልግሎት ወይም የግብይት ክፍያዎችን ለመፈጸም የአገልግሎት ሰጪውን ተቋም/ድርጅት ኪው አር ኮድ (QR code) በማንሳት (scan) እንዲሁም በቅድሚያ ክፍያቸውን በቴሌብር እንደሚከፍሉ በማሳወቅ፣ በሞባይል ስልካቸው በሚደርሳቸው የክፍያ የሚስጥር ቁጥር፣ ለሂሳብ ባለሙያው/ዋ በመናገር ክፍያቸውን በቴሌብር መተግበሪያ ወይም አጭር ቁጥር (USSD) ሲፈጽሙ፣ ከ127 የክፍያ ማረጋገጫ አጭር የጽሁፍ መልዕክት የሚደርሳቸው ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም  በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 25.85 ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 101 ዋና ወኪሎችን  (Master Agents) ፣ 87 ሺህ ወኪሎችን፣ 23 ሺህ ነጋዴዎችን /Merchants/ያፈራ  ሲሆን፤ ከ153 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገዱ ታውቋል፡፡
 በተጨማሪም ከ17 ባንኮች ጋር ትስስር  በማድረግ፣  ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን፣ ከ14 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ለደንበኞቻቸው እፎይታን ማጎናጸፉን ይገልጻል፡፡

Page 11 of 637