
Administrator
በስዊድን ለዳንስ ፈቃድ ማውጣት ሊቀር ነው
የዳንስ ፈቃድ ለማግኘት 4ሺህ ብር ይጠየቃል!
እንግዲህ የትኛውም መንግስት በተፈጥሮው የመከልከልና የመቆጣጠር አባዜ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ አምባገነን መንግስት ሲሆን ይብሳል፡፡ በዓለም ላይ የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣በርካታ መንግሥታት “የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት” በሚል ሰበብ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ፣ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ፣ ወደ መዝናኛ ተቋማት ድርሽ እንዳይሉ ጥብቅ ህግና መመሪያ አውጥተው ነበር - በገንዘብና በእስር የሚያስቀጣ፡፡ ቤተ አምልኮ ለመሄድ ሁሉ መንግስት ካልፈቀደ አይሞከርም ነበር፡፡
ከሰሞኑ ከወደ ስዊድን የተሰማው ዜና ያልተለመደ ነው፤ ግራ የሚያጋባ። “በስዊድን ለዳንስ ፈቃድ መጠየቅ ሊቀር ነው” ይላል። ለመሆኑ ለምንድን ነው ለዳንስ ፈቃድ የሚጠየቀው? ያውም በሰለጠነችውና በበለፀገችው አገረ ስዊድን!
አሶሼትድ ፕሬስ እንደ ዘገበው፤ በስዊድን ሬስቶራንቶች፣ የምሽት ክለቦችና ሌሎች የመዝናኛ ተቋማት ከመንግስት ፈቃድ ሳያገኙ የዳንስ ፕሮግራም ማዘጋጀት አይችሉም- ከባድ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ የመዝናኛ ተቋማት ደንበኞቻቸው እንዲደንሱ ከመፍቀዳቸው በፊት ራሳቸው ከመንግስት ፈቃድ ማግኘት አለባቸው - የዳንስ ፈቃድ! (አይገርምም!?)
አሁን ታዲያ የስዊድን ወግ አጥባቂ ጥምር መንግስት፣ ለዳንስ ፈቃድ ማውጣት የሚጠይቀውን ለአስርት ዓመታት የዘለቀ አሰራር ሊያስቀር መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተቀረጸው ፕሮፖዛል እንደሚለው፤ ለዳንስ ከመንግስት ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡ ለፖሊስ ማስመዝገብ በቂ ነው - ያውም በቃል! ለምዝገባው የሚከፈል ገንዘብም አይኖርም - በፕሮፖዛሉ መሰረት፡፡
እስካሁን ባለው አሰራር በስዊድን ማንኛውም ሬስቶራንት፣ የምሽት ክበብ፣ የመዝናኛ ተቋምና ሌሎችም የዳንስ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለማመልከት ቢያንስ 67 ዶላር (4ሺህ ብር ገደማ) መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
የዳንስ ፈቃድ ሳያወጡ ደንበኞቻቸውን ሲያስደንሱና ሲያስጨፍሩ የተያዙ የመዝናኛ ተቋማት ባለቤቶች የንግድ ፈቃዳቸውን ሊነጠቁ ሁሉ ይችላሉ፡፡
የስዊድን ፍትህ ሚኒስትር ጉናር ስትሮመር በሰጡት መግለጫ፤ “መንግስት የሰዎችን ዳንስ መቆጣጠሩ ተገቢ አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “የዳንስ ፈቃድ ማውጣት የሚጠይቀውን አሰራር በማስቀረት፣ ቢሮክራሲውን እንዲሁም የንግድ ተቋም ባለቤቶችን ወጪ እንቀንሳለን፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የስዊድን ሚዲያዎች ይህን “ጊዜ ያለፈበትና ሞራላዊ” ሲባል የቆየ የዳንስ ፈቃድ የመጠየቅ አሰራር ለማስቀረት የተወሰደውን እርምጃ በአዎንታዊነት እንደተቀበሉት ተጠቁሟል፡፡
መንግስት፤ አዲሱ አሰራር ከመጪው ጁላይ 1 ቀን 2023 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁሟል፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊት ረቂቅ ፕሮፖዛሉ በፓርላማው መጽደቅ ይኖርበታል። ያኔ በስዊድን ምድር ፈቃድ ሳይጠይቁ እንደ ልብ መደነስ ይቻላል፡፡ ዳንስም ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ ትወጣለች ማለት ነው፡፡
ጥሬ ስጋ እንደጉድ በሚበላበት አገር ይህን ዜና ሰምቶ ዝም ማለት ወንጀል ነው!
በአንጀት ካንሰር ተይዞ በሽታው ወደ ጉበቱ ተሰራጭቶ የነበረው የ42 ዓመቱ ጎልማሣ፣ የሕመም ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች በፍጥነት ሃኪም እንዲያዩ ይመክራል
በብሪታንያ ከ1980ዎቹ ወዲህ፣ በአንጀት ካንሰር የሚጠቁ ከ50 አመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው
በ40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ብሪታኒያዊ ጎልማሳ ባጋጠመው ተደጋጋሚ ሸርተቴ ምክንያት ሃኪም ዘንድ ሲቀርብ ነበር፣ የአንጀት ካንሰር ታማሚ መሆኑ የተነገረው፡፡
ቶም ማክኬና ለእንግሊዙ “ኢንሳይደር” ጋዜጣ በኢሜይል እንደገለፀው፤ እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም ለመፀዳጃ ከተጠቀመበት ወረቀት ላይ በተመለከተው ያልተለመደ ነገር ነበር ወደ ሃኪም ዘንድ ለመሄድ የተገደደው፡፡
ማክኬና የድካም ስሜት አዘውትሮ ቢሰማውም፤ ጉዳዩን ተደራራቢ ከሆነው ሥራውና በቂ እንቅልፍ ካለማግኘቱ ጋር ነበር በቀጥታ ያገናኘው፡፡
“ፍፁም ደህና ነበርኩ” ይላል ማክኬና፡፡
ተደጋጋሚው ሸርተቴ አሳስቦት ወደ ሆስፒታል በሄደ ጊዜ ሃኪሞቹ፤ የcolonoscopy (በካሜራ የአንጀትን የውስጥ ክፍል ማሣየት የሚችል የህክምና መሣሪያ) ምርመራ አደረጉለት፡፡ በምርመራ ውጤቱም፣ የአንጀት ካንሰር እንዳለበት አረጋገጡ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተደረገለት ቀጣይ ምርመራ፣ ካንሰሩ ወደ ጉበቱ የተሰራጨ መኾኑ ተነገረው፡፡ ይህም ማለት በሽታው “ደረጃ 4” ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡
ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ፤ በአሜሪካና በሌሎች ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት የአንጀት ካንሰር ስርጭት እንደ ብሪታኒያ ሁሉ በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ይኽም የኾነው በአሜሪካ ከ45 ዓመት በላይ፣ በብሪታኒያ ደግሞ ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ጎልማሶች፣ ቅድመ ምርመራ ስለሚያደርጉና በሽታው ሥር ሳይሰድ በፊት ስለሚደርሱበት ነው ተብሏል፡፡
ነገር ግን በፊንጢጣና በአንጀት ካንሰር የሚጠቁ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ1980 ወዲህ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
የሆድ እቃ መቆጣትን የሚፈጥረው ከፍተኛ የኾነ የቀይ ሥጋ ፍጆታ ለበሽታው መንስኤነት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡
የሚሰጠው ሕክምና ሕመሙ እንዳለበት ደረጃ ይወሰናል፡፡ በዚሁ መሠረት ኬሞቴራፒ፣ ሬዲዮቴራፒ እና ቀዶ ጥገና በጥምረት ወይንም በተናጠል ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡ ማክኬና የጉበቱ 60 በመቶ ያህሉ በመስከረምና የካቲት 2020 ዓ.ም በተደረጉለት ተከታታይ ቀዶ ሕክምናዎች ተወግዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ግማሽ ያህሉ የትልቁ አንጀቱ ክፍልና የሃሞት ከረጢቱ፣ በግንቦት 2021 ዓ.ም በተደረገለት ቀዶ ጥገና ተወግዷል፡፡
የቀዶ ጥገና ህክምናው የፈጠረው ጠባሳ አካባቢ፣ ሕመም እንደሚሰማው የሚናገረው ጎልማሳው፤ ቅባት ያላቸው ምግቦችና አልኮል መጠጥ እርግፍ አድርጎ መተዉን፤ እንዲሁም ፋይበር ያላቸው ምግቦችን እንደሚያዘወትር ገልጿል፡፡
በታህሳስ 2021 ዓ.ም በተደረገለት ምርመራ፣ ምንም ዓይነት ካንሰር በሰውነቱ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል እንዳልተገኘ የተረጋገጠ ሲኾን፤ በመጪው ግንቦት ወር ድጋሚ ምርመራ ይደረግለታል፡፡ ካንሰሩ ዳግም ላለማገርሸቱ እርግጠኛ ለመሆን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት፣ በየስድስት ወሩ ተመሳሳይ ምርመራ እንደሚያደርግም ለኢንሳይደር ጋዜጣ ጠቁሟል፡፡
የአሜሪካ የካንሰር ማህበር፤ በ2023 ዓ.ም 106,970 ገደማ ሰዎች በአንጀት ካንሰር ሊጠቁ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በአንጀት ካንሰር የተጠቃ ሰው ሕመሙ ከታወቀ በኋላ ከ5 ዓመት በላይ በሕይወት የመቆየት እድሉ የሚወሰነው እንደ በሽታው የስርጭት መጠን ነው፡፡
“የአንጀትና የፊንጢጣ ካንሰር ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል” የሚለው ማክኬና፤ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች ሳይዘገዩ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመክራል፡፡
ማክኬና ከተሰማው የሕመም ስሜት በተጨማሪ፤ በሽታው ከሚያሳያቸው የተለመዱ ምልክቶች መካከል፡ ከተፀዳዱ በኋላ የሆድ መክበድ፣ የክብደት መቀነስ፣ በሆድ አካባቢ የሕመም ስሜት ይገኙበታል፡፡ እኒህ ስሜቶች የሚሰማው ሰው፣ በፍጥነት ሃኪም ማንገር አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
እስካሁን ያለፍነው ሁሉ ወደዚህ የሚያመጣን ነበር ይሄኛውም ነገ ወደ ሚመጣው የሚወስደን ነው
ከዕለታት አንድ ቀን፣ በአንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የፈረሰ ግልቢያ ውድድር ይካሄድ ነበር፡፡
የውድድሩ ዓይነት ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ እንደተለመደው ፈጥኖ ቀድሞ በገባ ሳይሆን ተንቀርፍፎ ኋላ በመቅረት ነው፡፡ አራት ጋላቢዎች ነበሩ ለፍፃሜ የደረሱት፡፡
ጨዋታው አስደሳች ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን እንደተለመደው አስደናቂ አልሆነም፡፡ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነ!
ውድድሩ ከመቆም እኩል መስሎ ቀጭ አለ፡፡ ይሄኔ አንድ ጮሌ የአወዳዳሪው ኮሚቴ አባል አንድ ሀሳብ ሰነዘረ፡፡ ይሄውም፡-
“አራቱ ተወዳዳሪዎች ፈረሶቻቸውን ይቀያየሩ፡፡ ያኔ ሁላቸውም በሰው ፈረስ አንደኛ ለመውጣት መጭ ማለታቸው አይቀርም፤ ለየፈረሰኞቹም ቲፎዞው ህዝብ ጩኸቱን በእጅጉ ማስተጋባቱ አያጠያይቅም፡፡ ጃልሜዳ ሙሉ ህዝብ አለ! ሁሉም በሀሳቡ ተስማሙና ውድድሩ ሽምጥ ግልቢያ ሆነ፡፡ ፈረስ ከኮለኮሉት ሥራው መጋለብ ነው፡፡ መንቀርፈፍማ በምን ዕድሉ!
ቀጣዩ ስነሥርዓትም፣ የውጤትና የማዕረግ መንጋ ማወጃ ሆነ፡፡ የየፈረሱ ደጋፊ የሆኑ ሹማምንትም ጮኸው አይናገሩ እንጂ፣ ክቡር ትሪቡኑ ላይ ተሰይመዋል! የየራሳቸውን ድጋፍ በሆዳቸው ይዘዋል! ጋላቢው ሁሉ ከሰው ፈረስ ወርዶ የየራሱን ፈረስ ጋማ እያሻሸ ቆመ፡፡ ሁሉም ጋላቢ ፊት ላይ በፈረሱ የመኩራት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡
በውድድር ዓለም እንዲህም ዓይነት ውድድር አለ! ግጥሚያው የፈረሰኞቹ ብቻ ሳይሆን የፈረሶቹም ጭምር የሆነ፡፡ ውጤቱም የዚሁ ፍሬ ነው!
የእኛ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችስ፣ ፈረስ ቢለዋወጡ እንዴት ይሆኑ ይሆን? ብሎ ለመጠየቅ ይቻላል። በእውነት የተለያዩ ፈረሶች አሏቸውን? ፓርቲዎቹ ከአርማና ቀለም የተለየ ምን ልዩነት አላቸው? ጋላቢዎቹስ ምን ያህል የክህሎት፣ የልምድ ፣ የዕውቀት፣ የትግል ልምድ አላቸው? መንቀርፈፍን ትተው ዋናውን እሽቅድድም እንዴት ይወጡት ይሆን? የሚያቋርጥ ይኖር ይሆን? በመካከል ከፈረሱ የሚወርድ ይኖራል? በእሽቅድምድሙ መጠላለፍስ? ዳኞችስ አያዳሉም ? …ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ድምፅ መስጠት ቢኖር እጅግ አሳሳቢ በሆነ ነበር! ሳይደግስ አይጣላም ! በታሪክ በሀገራችን የተካሄዱ ምርጫዎች ሰርተው የሚሄዱት የድምፅ አሰጣጥን ሁኔታ ዞሮ መመልከት ይበቃል! ለየ ትውልዱ የሚበቃና የሚዳረስ መዝገብ ትተውልናል፤ አንብቦ መረዳት የየባለጉዳዩ ፋንታ ነው፡፡
ከልምዱ መማርም እንደዛው (የተቀደደና የጠፋ ሊኖር ቢችልም እንኳ!) ይሁን፤ ከታሪክ የማይማር ፈንጅ መርማሪ ብቻ ነው! ተብሏልና እንቀበለው፡፡
ተስፋ መቁረጥን ወደ ጎን በመተው፣ እረጅም እርቀት የሚጓዙ ንፁሀን ናቸው! በአጭር ጊዜ ድል የሚሹ ደግሞ ዘላቂ አይሆኑም፡፡ የትግል ውስብስብነትና ረቂቅነት፤ በአንድ በኩል ግልፅና የሚጨበጥ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህቡዕና ግራ ገቢ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ እንደጥንቱ አባባል “ረጅምና መራራ መሆን አለበት” በሚሉ ይብሱን ዝግጁነትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ያደርገዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የሁሉም መጠቅለያ ግን መሰዋዕትነትን መሻቱ ነው የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የንብረትና የህይወት ዋጋን ማስከፈሉ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደኛ አገር ምዝበራና ጦርነት የማይሰማው ሲሆን ደግሞ “ከእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” የሚባለውን ስዕል ያመጣል፡፡ የታሪካችን ድግግሞሽ ከላይ የጠቀስነውን መሰረተ ጉዳይ ሁሉ አሻራውን አሳርፎበታል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሁሌም ጀማሪዎች ሆነን እንገኛለን። ጥናቱን ይስጠን!
“ምንግዜም ስንል እንደኖርነው ዛሬም አረፈደም!” እንላለን፤ ምነው ቢሉ፤ (all that had gone before was a preparation to this, and this , only a preparation to what is this to come.) (እስካሁን ያሳለፍነው ሁሉ ወደዚህ የሚያመጣን ነበር፡፡ ይሄኛውም ነገ ወደ ሚመጣው የሚወስደን ነው)
ስለዚህ እኛም መንገድ እንድንጀምር አስበን እንዘጋጅ!
ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት ገለጸች
እየተጠናቀቀ በሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት፤ የግድቡንም ሆነ የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ በጋራ መግባባትና ንግግር መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ሱዳን አስታወቀች። አገሪቱ ይህንን ያስታወቀችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሱዳን ያደረጉትን የአንድ ቀን የስራ ጉብኝነት ተከትሎ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ነው።
የሱዳን ሽግግር ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብደልፋታህ አል ቡርሃ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉንና ሱዳንና ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ሁሉም ጉዳዮች ላይ እንደሚስማሙና እንደሚደጋገፉ አስታውቀዋል።
በዚሁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ማጠቃለያ ላይ በጋራ በወጣው መግለጫ፤ ሁለቱ አገራት የታላቁን ህዳሴ ግድብንም ሆነ የድንበር ጉዳይን በተመለከተ የህዝቦቻቸውን ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ በንግግርና በመግባባት መፍትሔ ለመስጠት መስማማታቸውን አመልክተዋል።
ይህ አሁን በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይትና የተደረሰበት ስምምነት ቀደም ሲል ሁለቱ አገራት ድንበራቸውን በአግባቡ ለመለያየት፣ ለአወዛጋቢ አካባቢዎች መፍት ለመፈለግ በጋራ አቁመውት የነበረውና ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነት ሲቀሰቀስ የሱዳን ሃይሎች በሃይል በመያዛቸው ሳቢያ የተቋረጠው የድንበር ኮሚሽን ስራውን እንዲጀምርና ለድንበር ይገባኛል ጥያቄ መፍትሄ ሊያበጅ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሱዳን ተቃውሞ እንደሌላትና ግድቡን በሚመለከት ሁሉም ጉዳዮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደጋገፍና በመግባባት ለመስራት እንደምትፈልግ ማሳወቋ ተቋርጦ የቆየው ንግግር እንዲጀመር ሊያደርግ የሚችልበት እድል እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
የአገር በቀልና የውጭ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቡድን በትግራይ ጉብኝት አደረገ
በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስተባባሪነት የተመራ የአገር በቀልና የውጭ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያካተተ ቡድን ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በመቀሌ የሥራ ጉብኝት ማድረጉ ተገለጸ።
ጉብኝቱ በትግራይ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና በቀጣይ ስለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋምና መሰል ተግባራት ላይ በክልሉ ከሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነበር ተብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተካሄደው የምክክር መርሃ ግብር ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ፤ “እውነተኛ ማህበረሰባዊ ሽግግር እና ዘለቄታዊ ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው ህዝብን በማዳመጥና ህዝብ ያለውን ሃብትና እሴት ከግንዛቤ ያስገቡ የችግር መፍቻ አካሄዶችን በመቀየስ ነው” ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “ግጭትና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት የማንችል ከሆነ ችግሮቹ እንዲቀጥሉ እድል ከመስጠት ባለፈ ለመጪውም ትውልድ እዳንና የተደራረቡ ችግሮችን የሚያወርስ መሆኑን ምክር ቤታችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ቆይቷል” በማለት ሰላማዊ የግጭት አፈታት አማራጭን መጠቀም አይተኬ ሚና እንዳለው በአጽንኦት ገልጸዋል።
የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ በርሄ በበኩላቸው፤ “ባለፉት ሁለት ዓመታት ለብዙ ህይወት መጥፋት፣ ከቤት ንብረት መፈናቀልና ሰቆቃ የተዳረጉ ወገኖችን የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ መታደግ ባይችልም፣ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥምረትን በመፍጠር ጉዳት ላይ ለወደቁ ዜጎች በአፋጣኝ ዕርዳታና ድጋፍ የሚደርስበትን ሁኔታ በመረባረብ ማሳካት ይጠበቅበታል” ብለዋል።
ቡድኑ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያን የጎበኘ ሲሆን፤ በጣቢያው ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃይ ዜጎች አሁንም ከፍተኛ ችግር ላይ ስለሚገኙ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ገ/እግዚአብሄር፤ "ስለደረሰብን ስብራት አብዝተን በማውራት የምንቀይረው ብዙ አይኖርም። በትንሹ ከተግባባን፣ በብዙ ከሰራን ለህዝባችን ልንደርስለት እንችላለን” ብለዋል። የጉብኝት መርሃ-ግብሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና በትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት የጋራ ትብብር መሆኑ ታውቋል፡፡
በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደረጃጀት ላይ በርካታ ክፍተቶች አሉ ተባለ
“ህዝበ ውሳኔው መንግስት እንደሚለው ህዝቡን ያሳተፈ አይደለም”
በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ የክልል አደረጃጀት ላይ በርካታ የህግ ክፍተቶች መኖራቸውን የገለፀው የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ መንግስት የህግ ጥሰቶችን በአስቸኳይ እንዲያስተካክል ጠየቀ፡፡
በ2015 ዓ.ም በህጋዊነት ተደራጅቶ ተግባሩን እየፈፀመ መሆኑን የገለፀው የጋራ ምክር ቤቱ፣ ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ገልፆ፤ በተለይ ግን ከቀድሞው ደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችንና አምስት ልዩ ወረዳዎችን አንድ ላይ በማድረግ፣ “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚል መጠሪያ ያለው አዲስ ክልል ለማደራጀት ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በሚደረገው ህዝበ ውሳኔ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ማየቱንና በውይይቱም ላይ በርካታ ክፍተቶች መታየታቸውን ነው የተገለፀው፡፡ የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የገለፀው ከህግ ክፍተቶችም አንዱ ህዝብ ውሳኔው ህዝቡ መምረጥ የሚፈልገውን አማራጭ ያላቀረበ በመሆኑ የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
ይህን ክፍተት ለመሸፈን ሲባል በበርካታ ምርጫ ጣቢያዎችና ምርጫ ክልሎች ለመራጮች ምዝገባ ሂደት ጀምሮ የህግ ጥሰቶች መፈፀማቸውን የገለፀው የጋራ ምክር ቤቱ፣ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ሳይመጡ በቀበሌ አመራሮችና በአካባቢው የህግ አስከባሪዎች በኩል የምርጫ ካርዶች ወጪ ከመደረጋቸውም በተጨማሪ መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ምርጫውን ለመዘወር የቀበሌ ህግ አስከባሪዎችና አመራሮች፣ የዜጎችን የምርጫ ካርድ በእጃቸው በመያዝ ህዝበ ውሳኔውን ቀን እየተጠባበቁ እንደሆነ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
በመሆኑም መንግስት በተለይም ምርጫ ቦርድ ይህን ህገ ወጥ አሰራር እንዲያስቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
“እስከ ዛሬ በአካባቢያችን ከተካሄዱትና ካሳለፍናቸው ምርጫዎች አንፃር ይህ የአዲሱ ክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ ለበርካታ አመታት የሚፀና በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ሀይሎች ፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና መንግስት በጋራ በመወያየት ሀሳባቸውን ማንፀባረቅ ሲገባቸው፣ ይህ ባለመደረጉ ህዝበ ውሳኔው በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው ብሏል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ይህንን መነሻ በማድረግ ጥር 6 ቀን በአስቸኳይ የተጠራው የጋራ ምክር ቤት፤ በዚሁ አጀንዳ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን ለአዲስ አድማስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
እየተካሄደ ያለው የህዝብ ውሳኔ ሂደት የዜጎችን የመምረጥ መብት ያላከበረና የመብት ጥሰትን ስለሚያመለክት በአስቸኳይ እንዲቆም ፣የህግ በላይነት እንዲከበር ብሎም በህዝበ ውሳኔው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት እንዲሳተፉ፣ የዚህ አዲስ ክልል አደረጃጀት ፅንሰ ሀሳብ ባለቤት መንግስትና ገዢው ፓርቲ ሆኖ ሳለ ህዝበ ውሳኔ ላይ የሚቀርቡት ምልክቶች ለማህበረሰቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ማስተዋወቅ ሲገባ አንዱን (የእርግቡን) ምልክት ብቻ የማስተዋወቅ ተግባር የምርጫን ሂደትና ሥነ ስርዓት የሚፃረር በመሆኑ መንግስት አካሄዱን በአስቸኳይ በማረም ተጨማሪ አማራጮችን ለመራጮች በማቅረብ እንዲያስተዋውቅ፣ ለህዝበ ውሳኔው የሚቀርበው አዲሱ “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ብዙ የክላስተር ማዕከላት ያሉት መሆኑ በመንግስት እየተገለፀ መሆኑ ይህ ጉዳይ በዜጎች ላይ ተጨማሪ አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚዩዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል የጋራ ምክር ቤቱን ስጋቱን ገልፆ፤ መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ እንዲሁም እንደ ወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሚደረገውን የአዲሱን ክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ በተመለከተ የአካባቢው ማህበረሰብ ያለው ፍላጎትና ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈፀም በመንግስት የተደረሰበት ሂደት አለመጣጣሙን መገንዘቡን የጋራ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ እነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበትን ህዝብ ውሳኔ ማድረግ ውጤቱ እንደማያምር በማሳሰብም፤ ህዝብና መንግስት ጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ በቅድሚያ ሀገራዊ ምክክር ተደርጎ ቀጥሎ ህዝበ ውሳኔው እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ኢዜማን፣ የወላይታ ህዝብ ዴሞክራቲክ ግንባር (ወህዴግ)፣ ህብረ ኢትዮጵያ ፖርቲን ፣ ነፃነትና እኩልነት፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ብልፅግና እና (ኢህአፓን) በአባልነት ያቀፈ የጋራ ምክር ቤት ነው፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ኮሚሽነር ምን ይላሉ?
-”የሽግግር ፍትህ እውነቱን ለማውጣት፣ ተጎጂዎችን ለመካስ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው”
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ ከእንግሊዝኛው “አዲስ ስታንዳርድ” ጋር ከሰሞኑ ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በአገሪቱ በሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ በስፋት አውግተዋል።
የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነትን በተመለከተ እንዲሁም በኮሚሽኑ የገለልተኛነት ጥያቄ ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዞች እንዴት ይሻሻሉ ለሚለውም መፍትሄ ጠቁመዋል፡፡ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በህግና በሰብአዊ መብት ያገኙ ሲሆን ለ25 ዓመታት በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በዲሞክራሲ እንዲሁም በሴቶችና ህጻናት መብቶች ላይ ሰርተዋል። ከቃለ-ምልልሱ መርጠን እንዲህ ተርጉመን አቅርበነዋል፡፡
በጦርነቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመሆን ያደረገው ምርመራና ያወጣው ሪፖርት በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አግኝቷል?
በሁለቱም ወገኖች እንኳን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ነገር ግን በሰነዱ ውስጥ የቀረቡት አብዛኞቹ ምክረሃሳቦች መከናወን ያለባቸው በገዢው መንግስት ነው። ብዙዎቹ ሥራዎች በአቃቢያነ- ህግ ነው መከናወን ያለባቸው፣ ለምሳሌ እንደ ወንጀል ምርመራና ክስ መመስረት ያሉት፡፡ ሪፖርቱን ተከትሎ የመንግስትን አፈፃፀም ተከታትለናል፣ እናም አንዳንዶቹ ምክረሃሳቦች ትኩረት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም በግጭቱ ሚና የነበራቸው ህውሓት እና የኤርትራ መንግስት ምክረ ሃሳቦቹን አልተቀበሏቸውም፡፡ ምክረሃሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ግፊት እያደረግን ነው፡፡ አሁን የሰላም ስምምነቱ ተፈርሟል፤ በስምምነቱ ላይም የሽግግር ፍትህ ተካቶበታል፡፡ እኛም ምክረሃሳቦቹን እንዲቀበሏቸው ግፊት ማድረጉን እንቀጥልበታለን፡፡
ምክረሃሳባችሁ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያላገኘበትን ምክንያት ለማወቅ ያደረጋችሁት ሙከራ አለ?
እንዳልኩት በሥልጣን ላይ ባለው መንግስት ተቀባይነት ማግኘቱ ለእኛ እንደ ትልቅ አዎንታዊ ሂደት የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹን ምክረ ሃሳቦች መተግበር ያለበት መንግስት ነው። ነገር ግን ከምክንያታቸው አንዱ የገለልተኝነት ጥያቄ ነው፡፡ ሪፖርቱ በገለልተኝነት እንዳልተሰራ ነው የሚያስቡት፤ እናም ምርመራው በሌላ አካል መከናወን አለበት ብለው ይሞግታሉ፡፡ አሁን ግን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ እየተከናወነ ሲሆን ይህም በዚያ ሪፖርት ውስጥ ካሉት ምክረ ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ምክረ ሃሳቡ እየተተገበረ ነው፤ የሽግግር ፍትህም በስምምነቱ ውስጥ ተካትቷል፡፡
እስካሁን ባደረጋችሁት ምርመራ በአገሪቱ የሚፈፀሙ ዋነኞቹ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምንድን ናቸው?
በአገሪቱ እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ፣ ውስብስብና ባለብዙ መልክ ናቸው፡፡ አንዱን ከሌላው ለመለየት ወይም አንዱ ከሌላኛው ይበልጣል ለማለት ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ከግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አስከፊ ናቸው፡፡ አያሌዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ የመሰረተ ልማት መፈራረስ፣ የመማር መብት መስተጓጎል፣ የጤናና አገልግሎት መቋረጥ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ፣ የኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ውድመት እንዲሁም በርካታ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ይፈጸማሉ፡፡ በተለይ በመላው ዓለም በአንደኝነት ያሰለፈን፣ የሰዎች የአገር ውስጥ መፈናቀል ነው፡፡
ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተጠለሉበት ሥፍራ ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተዳረጉ ናቸው፡፡ መፈናቀላቸው ሳያንስ፣ ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኙ ለተራዘሙ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ ሥፍራዎች በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ፡፡ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በስፋት የተነሳው ፆታዊ ጥቃት፣ በስፋት ተፈፅሟል፡፡፡ የጥቃት ተጎጂዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው የበለጠ እየተጎዱ ነው። በጦርነቱ ሳቢያ የአካል ጉዳተኞች ቁጥርም ጨምሯል። ሃቁን ለመናገር በአገሪቱ ያሉትን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በትክክል አናውቅም። አሁን ግን ተጨማሪ የአካል ጉዳተኞች ያሉን ሲሆን ከጉዳታቸው የሚያገግሙበት አገልግሎት እያገኙ አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፤ የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንቶችም ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተዳርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡
በኮሚሽኑ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ አንዳንዶች ኮሚሽኑ በመንግስት ላይ ጥገኛ በመሆኑ በገለልተኛነትና በሃላፊነት አይንቀሳቀስም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ለገለልተኛነት አንዱ እርምጃ የየትኛውም ፓርቲ አባላት ያልሆኑ መሪዎች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ኮሚሽነሮች ከፖለቲካ ትስስር ነፃ ናቸው፡፡ ይኼ በምርጫ ወቅት አንዱ መስፈርትም ነበር፡፡ ሁለተኛ፣ ኮሚሽነሮቹ የተመረጡት በልምድና ትምህርታቸው ላይ መሰረት ተደርጎ ነው፡፡ በሰብአዊ መብት መስክ በአመራርነት ልምድ አላቸው፡፡ በአመራር ደረጃ ላይ ያለነው በሙሉ በምርጫ ውሰጥ አልፈናል፣ እናም መነሻችንም ሆነ መድረሻችን የሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ ነው፡፡ በምርመራችንና በሪፖርታችን አንዱ ወገን ላይደሰት፣ ሌላው ደግሞ ሊደሰት ይችላል፡፡ እኛ ግን ወገንተኛ አይደለንም፡፡ ወገንተኛ ከሆንንም፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባዎችን ድምጽ እንዲሰማ ለማድረግ ነው- ጉዳታቸውንና ስቃያቸውን የሚያሳዩ ሰነዶች በማቅረብ። በተረፈ ግን ለማንም ወገንተኛ አይደለንም፡፡ ዋነኛ ሥራችን መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው፡፡ ሥራችንን የምናከናውነው መሬት ላይ ባለው መረጃና በዓለማቀፍ ግምገማ መሠረት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጉዳዩን እንደሰማን ሪፖርት የማናወጣው። ሥራችን የሚወሰነው መሬት ላይ ባለው እውነታ ነው፡፡
ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት ሪፖርት ታወጣላችሁ፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ደግሞ ትዘገያላችሁ የሚሉ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ፡፡ ለምንድነው እንደዚያ የሚሆነው?
በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ ነው አንድ ሪፖርትን በፍጥነት እንድናወጣና እንድናዘገይ የሚያደርገን። አብዛኛውን ጊዜ በግጭት አካባቢዎች ከሆነ መዘግየት ይኖራል፣ ምክንያቱም ቦታው ላይ መድረስና ምርመራ ማድረግ፣ ከዚያም ሪፖርት ማውጣት አለብን። ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተሰራጨ ብቻ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ሳንመረምር ሪፖርት አናወጣም፡፡ ለመዘግየቱ ትልቁ ምክንያት ቦታው ላይ በፍጥነት ለመድረስ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት የተቋማዊ አቅማችን ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የድጋፍ ሰጪ ክፍሉን ጨምሮ ጠቅላላ ሰራተኞቻችን 360 ገደማ ናቸው፡፡ በዚህ አቅም በሁሉም አካባቢዎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር፣ ለማረጋገጥና ሪፖርት ለማውጣት ይቸግረናል፤ በዚህም የተነሳ ሪፖርቶቹን እናዘገያቸዋለን፡፡
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየፈጸሙ እንደሚገኙ በርካታ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢሰመኮ ያደረገው ነገር አለ?
እዚያ መሄድ ስላልቻልን ይሄንን ጉዳይ ማረጋገጥ አልቻልንም። ስለዚህ ለጊዜው ምንም ማለት አልችልም።
ብዙዎች በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል ለተፈረመው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት፣ ውጤታማ የሽግግር ፍትህ መኖር አለበት ብለው ይሞግታሉ። ከዚህ አንጻር ምን መደረግ አለበት ብለው ያስባሉ?
በምርመራችን ላይ የሽግግር ፍትህ ስርዓት እንደ ምክረ ሃሳብ በግልጽ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር አለበት ብለን እናምናለን። ህጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በአገር አቀፍ ደረጃ መተግበር እንዳለበት ሃሳብ ተጠቁሞ ነበር፤ ይህም ሀሳብ በሰላም ስምምነቱ ላይ የተካተተ ሲሆን መንግስት እየሰራበት ነው።
የሽግግር ፍትህ ሥርዓት አራት ዋነኛ ዓላማዎች አሉት። የመጀመሪያው ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም ነው፤ ሁለተኛው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች የሚመረመሩበትና ወንጀል ፈጻሚዎች በህጉ መሰረት የሚቀጡበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፤ ሦስተኛው እውነትን ማፈላለግ ማውጣት- የችግሩን መንስኤ ማወቅ ከተጎጂዎችና ግጭቱን ከጀመረው ወገን ጋር ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ ነው። አራተኛው ደግሞ ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት አስፈላጊውን የፖሊሲ ማዕቀፍ የመቅረጽ ሂደት ነው። ከዚህ አንጻር ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ።
ኢሰመኮ ስራውን በገለልተኛነትና በውጤታማነት ለማከናወን የሚገጥሙት ትላልቅ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
የኮሚሽኑ ራዕይ ለሰብአዊ መብቶች ክብር መስጠት ባህል ሆኖ ማየት ነው። ያንን ለማድረግ ህብረተሰባችን የሰብአዊ መብት እሴቶችን ማወቅ፣ መገንዘብና መጠቀም ይኖርበታል። ይኼ ትልቅ ሥራ ነው። ሰብአዊ መብቶችን ማረጋገጥ፤ ማስተማርና የአቅም ግንባታን መስጠት፤ በዚህም ህዝቡና ባለስልጣናት ሃላፊነቶቻቸውን የሚያውቁ፣ በዚያም መሰረት ማስፈጸም ይችላሉ።
የኮሚሽኑ ሃላፊነት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በፖሊስ ጣቢያ፣ በወህኒ ቤቶችና ት/ቤቶችን ጨምሮ በሌሎች የሰብአዊ መብቶች በሚጣሱባቸው አካባቢዎች ጥሰቶቹን ለመከላከል እርምጃዎች መወሰዳቸውን ማረጋገጥ መሆኑን፣ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ማስተማር አስፈላጊ ነው።
እኛን ከሚገጥሙን ተግዳሮቶች መካከል በአንዳንድ ቦታዎች ጉብኝት እንዳናደርግና የተወሰኑ ሰዎችን እንዳናነጋግር መከልከላችን ነው። አንዳንዴ ሁኔታውን እንዲያመቻቹልን የበላይ አለቆችን እናነጋግራለን። እንዲያም ሆኖ ፈታኝ ነው። ሌላው ያወጣናቸውን ምክረ ሃሳቦችን የመተግበር ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ ስራ አስፈጻሚው አካልና ህብረተሰቡ የኮሚሽኑን ሃላፊነትና ስልጣን እንዲረዱና ምክረሃሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲሁም ምርመራ ለማድረግ ስንፈልግ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹልን ጥሪ እናቀርባለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብአዊ መብቶች ክብር መስጠት ባህል ሆኖ ለማየት እንችል ዘንድ ህብረተሰቡና ስራ አስፈጻሚው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ።
የተስፋ ቅኝት፤ ‹‹አፍላ ገጾች››
ዘውግ፡- ሥነ-ግጥም
ገጣሚ፡- ዮናስ መስፍን
የኅትመት ዘ መን፡- 2 015 ዓ .ም.
የመጽሐፍ ዓይነት፡- E-book, Afro Read
ሒሳዊ ዳሰሳ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ
1. መነሻ
ሥነ-ግጥም ውኃ ቢሆን በሊትር ወይም በሚሊ ሊትር ተለክቶ/ተሰፍሮ ይኼ ነው የሚባል ብያኔ ያገኝ ነበር። ሥነ-ግጥምን ማንበብም ሆነ መግጠም ከተመንና ከሕግጋት ያልፋል፤ ቋንቋ፣ ጭብጥ፣ ሥነ-ውበት፣ ፍካሬ፣ ሙዚቃዊነት፣ ስዕላዊነት፣ ምት፣ ምጣኔ… ጂኒ-ቋልቋል ሥነ-ግጥምን ለመግለጽም ሆነ ለመስፈር በቂ አይመስሉኝም፤ ወይም ሁነኛ መለኪያ የወጣለት አይመስለኝም፡፡ ሥነ-ግጥም፤ ከእነዚህ መሥፈርቶች እንዲዘል እሙን ነው…
…በአገራችን ‹ጥሩ›፣ ‹ዓይነተኛ› ወይም ‹ሸጋ› የሚባል ሥነ-ግጥም ድንበሩ አልለየለትም። የአገራችን ታላላቅ ገጣሚያን ‹ውበት-ዘመም› እና ‹ሀሳብ-ዘመም› ተብለው በሁለት ጎራ ቢመደቡ መልካም ነው፤ የመጀመሪያዎቹ፣ ‹ውበት-ዘመሞቹ› በሥነ-ግጥሞቻቸው የውበት ልክፍተኞች እንደሆኑ ያስተጋባሉ፤ በሥነ-ግጥሞቻቸው ብርሃንና ጽጌያትን፣ ጨረቃና ጸሐይን፣ አንጡባርና አልባብን…ወዘተ. ከእውኑ ዓለም ጋር በመፈከር ይሰናኛሉ፤ የዚህ ምድብ ቀንደኛ ተጠቃሽ ደበበ ሠይፉ ይመስለኛል፤ ገብረክርስቶስ ደስታ ጭምር፤ ግና በግጥሞቻቸው ሌጣ ውበት ላይ ብቻ ሳይሆን ሀሳብ/ጭብጥ ላይም ያተኩራሉ። ‹ሀሳብ-ዘመሞቹ› በበኩላቸው በጭብጥ መራሽ ሥነ-ግጥም የተለከፉ ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ ዮሐንስ አድማሱ እና ዮፍታሔ ንጉሴን ማንሳት ይቻላል። የግጥም ሀሳባቸው ለበቅ ነው፤ ዳግማይ ልብ መባል ያለበት ነገር በሁለቱም ጎራ የውበትና የሀሳብ ልክፍት በጉልህ መኖሩ ነው።
ሥነ-ግጥምን አውራና ብሉይ የሚያሰኙት አላባዊያኑ ብቻ አይደሉም፤ ነፍሲያን የማናወጽ አንድምታውም ነው፤ እንደ ተዐምር ዓይነት፣ ሽባ የመተርተር ከኀሊነት ቢባል መልካም ነው። ገጣሚ የዓለምን ስብጥርጥር ሃቂቃ ከእራስ ተሞክሮ ጋር አዋዶ ይትነፍሳል፤ በሥነ-ውበት እየታገዘ የተለያዩ ጉዳዮችን ይፈክራል፤ መፈከር በፈሊጣዊው ቋንቋ እየታገዙ እውነታንና ልምድን በምሳሌ ማቅረብ ነው፤ ሥነ-ግጥም ከዚህም እንዲልቅ እሙን ነው…
…አሁኔ ‹‹አፍላ ገጾች›› የተሰኘ የሥነ-ግጥም መድበል ነው። የመጽሐፉ ዓይነት E-book ሲሆን፣ ዘጠና የሚደርሱ ሥነ-ግጥሞችን በውስጡ አቅፏል። ገጣሚ ዮናስ መስፍን በዚህ መድበል ብርሃን አሳባቂ ሀሳቦችን በውብ ቋንቋ እያሸገነ ተሰናኝቷል፤ በአብዛኛው የመድበሉ ሀሳብ የተስፋ ቅኝት ነው፤ ሌሎች ገጸ-በረከቶችንም አጭቋል መድበሉ፡፡
ድኅረ-ዘመናዊ የሥነ-ጽሑፍ ኅልዮትን/ትወራን ተንተርሼ የ‹‹አፍላ ገጾች››ን ሙክርታዊ አበክሮዎች ስመረምር እንዲህ ሆነ…
2. ሥም/ርዕስ
ገጣሚ ርዕስና ሥምን ያማከለ ሀሳቡን በግጥም ገላ ውስጥ ሊያሰርጽ ይችላል፤ ርዕስና ሥም ቀዳማይ ስንኝ ደግሞ ተከታይ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፤ ሃቲት ከርዕስ ከተቃረነ የትርጉም መዛባት ይከተላል፤ ርዕስ ደግሞ ሃቲቱን መወከል መቻል አለበት። ዮናስ መስፍን ርዕሳቸውን ማዕከል ያደረጉ ግጥሞችን ለንባብ አብቅቷል ብዬ አስባለሁ።
3. ውበት (Beautiful Lines)
ገጣሚ በቃላት አጠቃቀሙ፣ በገላጭ ቃላትና ሐረጋት መረጣውና በዘይቤአዊነቱ ውበታም ስንኞችን ሊሰናኝ ይችላል። ገጣሚ ዮናስ መስፍን ውበታም ስንኞችንና ገላጭ ሐረጋትን በአብዛኛዎቹ ግጥሞች በመሰግሰግ የግጥም ሀሳቡን ውብ አድርጎ አቅርቧል ብዬ አምናለሁ። ለመተማመን እንዲበጀን ማሳያ እያጣቀስኩ ላውጋ፡- ‹‹ንጋት›› በተሰኘ ግጥም ‹‹የጸሐይ ማሾ ፍካሬ››፤ ‹‹አቅም›› በሚል ግጥም ‹‹እጄ ያለመጠኑ ከሰማይ ዳስ ደርሶ ጉም ሲዘግን አሳየኝ፤››፤ በ‹‹ፍቅርን በአበባአየሁ›› ግጥም ‹‹የልቤ ቄጠማ ላንቺ ተጎዝጉዞ ከቶ አለመድረቁ››፤ ከ‹‹ባለጠግነት›› ውስጥ ‹‹የዛሬው ሰው ለጋ የእድሜ ባለጠጋ››፤ ከ‹‹እንቆቅልሽ›› ግጥም ‹‹ከበድኖች መሀል በወጣ አንድ ቅሪት አንዲት ነፍስ ማዳኑ››፤ ‹‹ናፍቆት›› ከተሰኘ ግጥም ‹‹ናፍቆትሽን ወስዶ ጊዜን ከኔ የሚያስቀር››፤ ‹‹አዋቂ›› በሚል ርዕስ ‹‹የሀሳብ ፀሐይ መውጫ››፤ በ‹‹አጥንቴን መልሺ›› ስር ‹‹እስከ ዳግም ሔዋን አጥንቴን መልሺ››፤ ከ‹‹አንድ ብር›› ግጥም ገላ ‹‹በያኔው ዘመንህ በአዲሱ ገንዘብህ እስቲ አሁንን ግዛ›› ‹‹ጤዛ›› ከሚል ግጥም ደግሞ ‹‹ጠዋቱስ ፍካት ነው ለነፍሴ ያደረ››… እና ሌሎች በውበታቸው የሚማርኩ ሐረጋትንና ስኝኞችን መጥቀስ ይቻላል።
4. ፍካሬ
ለድኅረ-ዘመናዊነት/post-modernism ገለታ ይግባውና አንድ እውነታ ብቻ ስለሌለ፣ ገጣሚ በቋንቋ ተራዳኢነት ሀሳብ ይመረምራል፤ ሀሳብ አይዘግብም/አይናገርም። ፍካሬ፣ ወይም መፈከር ማለት ሕይወትን መተርጎም ማለት ነው፤ ገጣሚ ሀሳቡን አይዘግብም፤ የዓለምን እውነታ አዟዙሮ ይፈክራል/ይተረጉማል እንጂ፤ ይኼንን ሀሳብ ለማጦንቸት እንዲህ ልበል፡- ፈሊጣዊ-ንግግርን፣ ሥነ-ቃልን፣ አፈ-ታሪክን፣ ተረት-ተረትን፣ ድርሳነ-ደብተራን እንደ ግብዐት ተጠቅሞ ወደ ተነሱበት ሀሳብ መሰግሰግ ነው መፈከር ማለት፤ የዚህ ፋይዳ ሕይወትን በሥነ-ውበት መፈከር ነው፤ ሥነ-ግጥምና ሥነ-ውበት የተቆራኙ እንደመሆናቸው መጠን ፍካሬያዊ አንደበት ጭብጥ ያጎላል፤ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነገር አንድ ገጣሚ ሕይወትን ለመፈከር ሲተልም (ተልሞም ግብዐት ሲወሰውስ) ከተነሳበት ሀሳብ ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን ልብ ማለት አለበት፤ ይኼ ጣጣ ምናልባት ‹ግጥም እየገጠምኩ ነው› ብሎ የሚነሳ ሰው ሊያጋጥመው ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፤ እውነታው ‹ግጥም እገጥማለሁ› ብሎ ብዕር የሚጨብጥ ግለሰብ ከተነሳበት ዐውድ፣ ሀሳብ/ ጭብጥ የማይጣጣም ትርጉም ያለው ፍካሬያዊ ቃል፣ ሐረግና ስንኝ ሊያካትት ስለሚችል ነው።
ዮናስ መስፍን በ‹‹የአፍላ ገጾች›› ሥነ-ውበትንና ሥነ-ግጥምን በመጠኑም ቢሆን ፈክሯል ብዬ አምናለሁ። ለዚህ ማሳያ ‹‹አዋቂ›› ከሚል ግጥም ውስጥ ‹‹የሀሳብ ፀሐይ መውጫ›› የሚለውን ሐረግ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፤ ገጣሚው የሀሳብ/የመፍትሔ አቅጣጫ ስለ ጠፋበት ገጸ-ባሕሪይ/ባለድምጽ ያትታል፡፡ በዚህ ግጥሙ፤ አስከትሎ የብርሃንና የተስፋ ምልክት ተደርጋ የምትወሰደዋን ፀሐይንና የፀሐይ መውጫን/አቅጣጫን በተምሳሌትነት በመጠቀም ሀሳቡን ያትታል። ብሎም ባለድምጹ ሁነኛውን ዘዴ ባለመምረጡ የተነሳ ጣጣ ውስጥ ሲገባ እናስተውላለን፤ ይኼ ሙከራ ተሳክቷል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በተጨማሪ በ‹‹አጥንቴን መልሺ›› የግጥም ገላ ውስጥ ‹‹እስከ ዳግም ሔዋን አጥንቴን መልሺ›› የሚለውን ስንኝ መመልከት እንችላለን፤ ዳግም ምጽዐት እንጂ ዳግም ሔዋን አይታወቅም፤ ገጣሚው ‹‹ዳግም ምጽዐት›› የሚለውን ሐረግ ወደ ራሱ ጠምዝዞ ተገልግሏል። ገጣሚው የሚነግረን በአፍቃሪው ስለተከዳ ባተሌ ታሪክ ነው፤ ጉዳቱ ስለሰፋ ምንም ነገር እንዲቀር ስላልፈለገ የተፈጠረችበትን የጎኑን አጥንት እንድትመልስለት ቀጠሮ ይዞ ይሞግታል ታዲያ። ሁነኛ ሙከራ ነው።
ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች እንደ አንድ ሙከራ የሚደነቁ ቢሆንም ገጣሚው በቀጣይ ሥራዎቹ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ እሻለሁ!
5. የተስፋ ቅኝት
‹‹ግጥም እምባ ይፈልጋል›› ይላል ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ)። እውነት አለው፤ አዛኝ፣ ተቆጭ፣ ሒስ ወሳጅ መሆን አለበት ገጣሚ ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ሻገር ሲል የተስፋ ፋና ወጊ መሆን አለበት፤ አዛኝ ሰው ስለ ተስፋ አይሰብክም ማለቴ እንዳይደለ መዝግቡት! ሥነ-ግጥም ብርሃንን፣ ተስፋን አዲስ ንጋትንም መስበክ አለበት ባይ ነኝ፤ ገጣሚ የብርሃንን፣ የትጋትን፣ አሉታዊ መልክ ማንጸባረቅ አለበት፤ ገጣሚ ማስረጽ/Canonization የቤት ሥራው ነው።
‹‹አፍላ ገጾች›› በአብዛኛው ተስፋ የሚዘሩ የሥነ-ግጥም ሀሳቦችን ሰባስባለች ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ማሳያ ‹‹ፍጻሜ አልባ ጅምር›› እና ‹‹ጤዛ›› የሚሉ ግጥሞችን ማንሳት እንችላለን።
6. ለበቅነት
ሥነ-ግጥም በሀሳብም በቋንቋ/በቃላት አጣጣልም የጎመራ መሆን አለበት፤ ጥበቅትና ፍላት በጥብቅ ይገደዋል። ተራ ጉዳይ ላይ መዘባዘብ የለትም ገጣሚ፤ ከዚህ በተቃራኒ ገጣሚ ሀሳቡን ለማግዘፍ በመተለም ችኮ መሆንም አይጠበቅበትም፤ ከራራ አሰነኛኘት ሥነ-ውበትን ገደል ሊከተው ይችላል፤ በሥነ-ግጥም ውስጥ የሥነ-ውበትና የዓለም እውነት የማይነጣጠሉ ስለሆኑ። የዮናስ መድበል እንደተንደረከከ ፍም የሚፋጁ ሀሳቦችን አቅፏል፤ ሁነኛ ምሳሌ ‹‹ቀጣይ ክፍል›› እና ‹‹የአፈር ምስል›› የተባሉ ግጥሞች ናቸው። ዳሩ በአብዛኞቹ ግጥሞች ሀሳብን ለማጉላት ሲል ከሥነ-ውበት ሸርተት ብሏል የሚል ሥጋት አለኝ፤ ‹‹ቢያስተምሩት ኖሮ›› እና ‹‹ጀግና ማነው?›› የሚሉ ግጥሞች እማኝ ናቸው። በሌላ ጊዜ እንደሚያሻሽል ተስፋ ይዤአለሁ።
7. ድንቃይ አጨራረስ
ድንቃይ አጨራረስ/Surprise ending ራሱን የቻለ የአሰነኛኘት ይትባሃል ነው። ይኼ ነጥብ በአብዛኛው የግጥም ሀሳብ አዘጋግን ይመለከታል፤ ገጣሚ ከርዕሱ ተነስቶ ሀሳቡን የሚያትትበትን መንገድ በቤት መዝጊያው ላይ ባልተጠበቀ መልኩ ሊቀለብሰው ይችላል፤ ወይም ከተጠበቀው በተቃራኒ መልኩ ሊደመድም ይችላል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሙከራ ለመራቀቅ ፍጆታ ሳይሆን የሕይወትን ምሰላ ለማመላከት ቢውል መልካም ነው ባይ ነኝ። በዚህ ሀሳብ በመታገዝ የ‹‹አፍላ ገጾች›› ገጣሚ የዓለምን እውነታና የግሉን ምሰላ በበጎ መልኩ አመላክቷል፤ ለአብነት ያህል ‹‹መከራ ይምከረው›› እና ‹‹ጠመኔ›› በሚል ርዕስ የተነሱ ሀሳቦችን መጥቀስ ይቻላል። ‹‹ናፍቆት››፤ በሚል ግጥም ስር ‹‹ናፍቆትሽን ወስዶ ጊዜን ከኔ የሚያስቀር›› በማለት ጊዜን ይሞግታል። አሁንም ይኼ ሙከራ ለወደፊት እንዲሻሻል መጠቆም እፈልጋለሁ!
8. ድግምግሞሻዊና ገለጻዎች
ከ‹‹የሚናገርለት›› ግጥም ስር፡- ‹‹አብጠርጥሮ የሚያውቅ››፤ በ‹‹ፍቱልኝ አልልም›› ግጥም ‹‹ከርታታው ልብ››፣ በ‹‹እድሜ ማራዘሚያ›› ግጥም ‹‹አንተዬ›› … እና ሌሎችም አሰልቺ መስለውኛል። ዮናስ የገጣሚ መብቱን/Poetic-license ተጠቅሞ ውበታም ቃላትንና ሐረጋትን ተጠቅሞ መሰናኘት ነበረበት።
9. በተሃ ግጥሞች
በተሃ ማለት ያልተብላላ፣ የደነበሸ፣ ያልጎመራ…ወዘተ. ማለት ነው። ሥነ-ግጥም በተራ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሚባክንና የደነበሸ መሆን የለበትም። በግጥም የሚነሳ ሀሳብ ለሚዛን የቀለለ መሆን የለበትም፤ በተሃ ግጥም ከገጣሚው የመፈከር አቅም ማነስ የተነሳ ሊወለድ ይችላል።
የሚከተሉ ግጥሞች በተሃ ናቸው ብዬ አምናለሁ፤ ‹‹የሚናገርለት››፣ ‹‹ጀግና ማነው››፣ ‹‹ምን ኖረው ለጠቢብ›› እና ሌሎችም።
10. ተቀራራቢ ቃላት/የቃላት ድረታ
ይኼ መደብ በአንድ ግጥም ገላ ውስጥ ተደጋግመው የተነሱ ተቀራራቢ ቃላትን ይመለከታል። በአንድ ግጥም ውስጥ ተመሳሳይ ቃላትን መደጋገም በንባብ ወቅት መታከትን ሊያስከትል ይችላል። መሰልቸትንና መታከትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ በዚህ መድበል በአንድ ግጥም ውስጥ ተደጋግመው የተነሱ ተቀራራቢ ቃላትን እንመልከት…
‹‹ውዳሴ ለፍቅርሽ›› ከተሰኘ ግጥም ‹‹የሀሳብሽ›› - ‹‹ሀሳቡ››፤ በ‹‹ልዩነት›› ግጥም ውስጥ፡- ‹‹መንጋ›› - ‹‹መንጋውን›› - ‹‹ከመንጋው››፣ ‹‹ሀሳብ›› - ‹‹ሀሳቡን›› እና ሌሎችም።
11. ስልተ-ምት
ይኼ ነጥብ የሚያተኩረው አንድ ገጣሚ በሥነ-ግጥም ውስጥ የሚፈጥረውን የዜማ ቀለምና ድምጸትን ነው። ዮናስ ለእራሱ ባመቸና በተመጠነ መልኩ በበርካታ ቀለምና ድምጾች የተንቆጠቆጡ ስልተ-ምቶችን ፈጥሯል። ይኼ ሙከራ በግጥሞቹ ገላ ላይ ሙዚቃዊነት የሚዳዳው ዜማ እንዲፈጠር ረድቶቷል የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ፡-
‹‹ጠወለገ አትበል
ያ ያሸተ ቅጠል›› - ከ‹‹የታነጸበቱ›› ግጥም ገላ ውስጥ፤
አልፎ-አልፎ የተከሰቱ የቸኩ ስልተ-ምቶችንም መጥቀስ ይቻላል….
‹‹የዘመን ሽሚያ›› ከሚል ግጥም፡-
‹‹ካንቺ የልጅ ነፍስያ ከንጹህ ቅን ልብሽ
ጋራ ውሎ ገጥሞ
እርሱ አንቺን ሊመስል ወደ ዘመንሽ ጫፍ
ሲጎተት በአርምሞ›› እና ከ‹‹ልቤ›› ግጥም መካከል፡-
‹‹ያለ አቅሙ ተችሮት አድናቆት ሙገሳን
ባይጠግብ እንኳን ሰምቶ
መሸሸግ መረጠ ጫንቃው መቻል ከብዶት
ውዳሴውን ፈርቶ››
የሚሉትን ማንሳት ይቻላል።
12. መደምደሚያ
ዮናስ መስፍን ‹‹አፍላ ገጾች›› በተባለ መጽሐፉ ፈርጀ-ብዙ ሙከራዎችን ሊያሳየን ሞክሯል፤ በአብዛኛዎቹ ግጥሞች የዚህችን ዓለም ስብጥርጥር ሃቂቃ ከሥነ-ውበት ጋር በማናበብ ለመሰናኘት መጣሩ የሚበረታታ ነው። በተለያዩ መዘርዝሮችና ነጥቦች ስር የተነሱ ሀሳቦች ለቀጣይ ሥራዎቹ ግብዐት ይሆኑታል የሚል እምነት አለኝ።
ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን ምን ይዞ መጣ?
አንጋፋው ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን፣ ሦስት የሥነጥበብ አውደ ርዕዮችን በአራት ቀን ልዩነት ለተመልካች ሊያቀርብ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስታወቀ፡፡
ሰዓሊው እንደገለጸው፤ “ጤፍና ነጻነት - (GLUTEEN FREE-DOM”) በሚል ርዕስ አዳዲስ የሥነጥበብ ሥራዎቹን አውደ ርዕይ፣ አትላስ ሆቴል ተሻግሮ ወደ አውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በሚወስደው መንገድ መጀመሪያ ላይ በሚገኘው፣ ዘ ፕሌስ ህንጻ አንደኛ ፎቅ፣ በኢትዮ ሜትሮ ጋለሪ አማካይነት ለተመልካች ያቀርባል፡፡
በተመሣሣይ ምሽትና ጋለሪ “መንገዴን በጨረፍታ” (the glimpse of my journey) በሚል ርዕስ በ30 ዓመታት ውስጥ ከሰራቸው ሥራዎቹ የተሰባሰበ ተጨማሪ አውደ ርዕይ ይቀርባል:: ሁለቱም ከነገ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት ጀምሮ ለሕዝብ ክፍት ሆነው ይቆያሉ ተብሏል፡፡
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ሦስተኛው የሥነጥበብ አውደ ርዕይ ደግሞ በአራተኛው ቀን ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 “የአዘቦት ልሳን” (casual dialog) በሚል ርዕስ በብሔራዊ ሙዚየም ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ ሦስቱም አውደ ርዕዮች በኢትዮ ሜትሮ ጋለሪ አማካይነት የሚቀርቡ መሆናቸውንም አክሎ ጠቁሟል፡፡
በቀለ መኮንን (ፕሮፌሰር) በቅርቡ የሚከፈቱትን አውደርዕዮች በተመለከተ በሰጠው አስተያየት፤ ”ሦስት አውደ ርዕዮች ባንድ ጊዜ አስቦ ፈጥሮና ሰርቶ ማቅረብ ቀርቶ በቅጡ መኖር መቻል ብቻውን አርት በሆነበት ወቅትና አገር፣ የሚያስከፍለውን የበዛ መስዋዕትነት መገመት አያዳግትም፡፡
ሆኖም በምንም ዓይነት ኪሳራ መልካም ነገር ጮክ ብሎ ደምቆ የሰዎች መነጋገሪያ መሆን ከቻለ እሱ በሕይወት ትልቁ ክፍያ ነው፡፡ “ ብሏል፡፡
በድንቅ ግጥሞቹም ጭምር የሚታወቀው ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በሌሎችም በርካታ በሳልና ሸንቋጭ መጣጥፎችን ለዓመታት ሲያቀርብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላይ ያጎርሳታል!
ከሥራ መሰናበት ከባድ አይደለም፡፡ ከአንድ ሥራ ወጥቶ ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ይገባላ! ከሰው መሰናበትም አይገድም- ከሌላ ሰው ጋር መገናኘት፣መዋል ማደር ይቻላላ፡፡ ከሰፈር መሰናበትም ቀላል ነው - ሌላ ሰፈር ይኬዳላ፡፡ ችግር የሚመጣው ከሀገር ሲሰናበቱ ነው!
እርግጥ ከሁሉ ክፉ ከህይወት መሰናበት ነው፡፡ “እገሌ ህይወት በቃኝ ብሎ ስንብት ጠየቀ” አይባልማ፡፡ አንዱ ምክንያት ተጠያቂ አለመኖሩ ነው፡፡ ለቃቂው ማንን ነው መልቀቂያ ስጠኝ የሚለው? ሁለተኛ ከህይወት ቀጥሎ ሌላ መስሪያ ቤት የለምና፣ የት ይገባል? አለስ ቢባል እንዴት ነው የሚያመለክተው? በውድድር የምንገባበት እንዳይባል ፈተናው የት ነው የሚሰጠው? ማነው ፈታኙ? ት/ሚኒስቴር እንዳይባል እራሱ መች ተፈትኖ ገባና? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ባለሥልጣኑ ሁሉ ተሹዋሚ ነዋ፡፡ ያውም ሹሙ ሁሉ ባፍ አመሉ፣ ሹመት ሺ-ሞት ነው እያለ እየኮነነ ከሹመት አለመሸሹ እያስገረመን! እንዲያውም ሥነ-ተረቱ የሚለን እነሆ፡- አንድ ልዑል አባቱ፣ ማለትም ንጉሱ፣ሲሞቱ፣ ስለሚያስራቸው ባለሥልጣን ሰዎች እያዘነና እየተማረረ ፣”ቆዩ ብቻ እኔ በሰዓቴ ልንገስ ብቻ፤ ይሄ ሁሉ ግፍ ያከትማል!” ይላል፡፡ ይዝታል፡፡
ንጉሱ ሞቱ፡፡ ልዑሉ ንጉስ ሆነ፡፡ ህዝቡ “አንድ ልዑል ብቻ ነው እንዴ ያለን? ሌሎቹም ልኡላን ይወዳደሩ እንጂ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ይሄኔ ያ ልዑል፣”ይሄም አለ እንዴ?” አለና አንድ አዋጅ አወጣ፡-
“ከዛሬ ጀምሮ ማናቸውም ዓይነት ብረት ነክ ነገር ይሰብሰብ፡፡ ማረሻ፣ ዶማ፣ አካፋ፣ ድጅኖ፣ ማጭድ፣ የእጅ አምባር፣ የአንገት ሃብል፣ የአጥር ሽቦ፣ የብረት በር፣ የጦር፣ የሻምላና ጎራዴ ዘር… ወዘተ አንድም ሳይቀር ይሰብሰብ!” አለ፡፡
ያለው ሆነ፡፡ በመቀጠልም፤ “አንጥረኛ፣ ቀጥቃጭ፣ብረት አቅላጭ፣ ወዘተ… በሙሉ ተሰባስቦ ብረታ ብረቶቹን በሙሉ ያቅልጡልኝና ሁሉንም ወደ እግረ-ሙቅና ድምድማ እንዲሁም የእጅ ሰንሰለት ይቀይሩልኝ!” ሲል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ትዕዛዙ ተፈጸመ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ሌሎቹ ሦስት ታናናሽ ልዑላን ወንድሞቹ ለካ አድማ ሲጠነስሱለት ከርመው ኖሮ፣ አንድ አሳቻ ቀን ቤተ-መንግስቱን አስከብበው “እጅህን ስጥ!” አሉት። በእጁ ጦርም ሆነ ሾተል፣ ጩቤ ወይም ሌላ- ስለት የሌለው ልዑል እጁን ከመስጠት ሌላ ምርጫ ጩቤ ወይም የሆነ ሌላ ስለት የሌለው ልዑል፣ እጁን ከመስጠት ሌላ ምርጫ አልነበረውም። ፍፃሜው ይሄ ሆኖ ቀረ፡፡ ከሀገር ቀርቶ ከህይወት ስንብት ለማድረግ ጊዜ ያልነበረው ልዑል አበቃለት፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ይኼው ሥልጣንም፣ ህይወትም ከምንም በላይ አጓጊ መሆናቸውን አየ፡፡ ሁለቱንም ማጣት እርግማን መሆኑን ተገነዘበ፡፡ አንዱንም ማጣት አሰቃቂ መሆኑን ተረዳ፡፡ ያባቱን ዘመን አወደሰ፡፡ ውግዘቱን ሁሉ በፀፀት አነሳ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ እንዳለው፣ “እርግማኔን መልስልኝ!” አለ፡፡
እስካሁን ያወጋነው በፈቃደኝነት አገርን ስለመልቀቅ ነበር፡፡ ተገድደው ሀገርን መሰናበትስ ምን ይመስላል? የሚከተሉትን ስንኞች እናጢን፡-
“… መሄድ መሄድ አለኝ፤ ጎዳና ጎዳና
አልግደረደርም ዘንድሮስ እንዳምና”
ያሰኘን ይሆን!? ይሄ የምሬት አንድ እጅ ነው እንበል፡፡
“ዝናቡ ዘነበ፤ ደጁ ረሰረሰ
ቤት ያላችሁ ግቡ፤ የኛስ ቤት ፈረሰ”
ይሄ የመረረው ዜጋ ቃል ነው፡፡
“እኔ እዘጋዋለሁ፤ደጄን እንዳመሉ
የት ሄደ ቢሏችሁ፤ ከፍቶት ሄደ በሉ!”
የተከፋ ዜጋ ፍፃሜ ቃል ነው፡፡
“እሾክ ብቻ ሆነ፣ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ ፤መኸጃ ያጣል ሰው!”
አገሩን ጥሎ ለመሄድ ልቡ የሸፈተ ሰው ምሬት ነው፡፡
ሰፈራ በተጀመረ ሰሞን ደግሞ ወሎ እንዲህ ሲል ገጥሞ ነበረ፡-
“ቀና ብዬ ባየው፣ ሰማዩም ቀለለኝ
አንተንም ሰፈራ፣ ወሰዱህ መሰለኝ!”/ እግዜሩን ሰፈራ ወሰዱት መሰለኝ
አምላኩን ምነው ስቃያችንን አላይ አልከን ለማለት ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ የነበራቸው ባልና ሚስት በአንድ ሰፈር ይኖሩ ነበር። ልጃቸው በየጊዜው እያለቀሰ ያስቸግራቸው ነበረና አባትየው እንደማስፈራራት ብለው፣
“ዋ ለአያ ጅቦ ነው የምሰጥህ!” ይሉታል።
ልጅ ፀጥ ይላል። እንዲህ እያሉ እየኖሩ ሳሉ፣ አንድ ቀን ማታ ልጁ እንደተለመደው ሲያለቅስ፣ አባት፤
“ዋ! ለአያ ጅቦ ነው የምሰጥህ!! አፍህን ብትዘጋ ነው የሚሻልህ!” ይሉታል።
ለካ አያ ጅቦ በሩ ላይ ሆኖ ያዳምጥ ኖሯል። ልጅ ማልቀሱን ይቀጥላል። አባቱም ከቅድሙ በባሰ ሁኔታ፤
“ዋ ዛሬ! ነግሬሃለሁ! ለአያ ጅቦ ነው የምሰጥህ!” ይሉታል፣ ከቅድሙ በጎላ ድምጽ በጣም ጮክ ብለው።
አሁን ልጁ ፀጥ አለ። ጅብ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ፀጥታ ብቻ ሆነ የሚሰማው።
አያ ጅቦ ሲጨንቀው፤
“ኸረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” አለ፡፡
ባልና ሚስት ልጃቸውን አቅፈው ለጥ ብለው ተኙ።
ይሄኔ አያ ጅቦ፤
“ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?!” አለ፤በድጋሚ።
ድምፅ የለም።
አያ ጅቦም ተስፋ ቆርጦ ወደ ማደሪያው ሄደ! የነጋበት ጅብ ሳይሆን አመለጠ።
***
የምናደርገው ተስፋ ተጨባጭ ካልሆነ ቀቢፀ-ተስፋ ነው። ጥረታችን ሁሉ ንፋስ መዝገን ነው የሚሆነው። በመሪዎቻችን ንግግር ውስጥ የምንሰማው ቃል ሁሉ ጥብቅና የሚታመን ነው ብለን ካመንን የዋሆች ነን። ሥልጣን ላይ መቆየታቸውን እያጠናከርን ነው ማለት ነው! መሪና ተመሪ ሰላማዊ ግንኙነት ቢኖራቸው መልካም ነው ቢባልም፣ ፍትሐዊ ግንኙነት መሆኑን አስተውሎና ልብ- ገዝቶ ማጤንን ይጠይቃል!
የሀገራችንን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ምስቅልቅል ሂደት እንዲህ በዋዛ ፈትተን አንጨርሰውም። በቀላሉም አንገላገለውም። ምክንያቱም ሰንሰለታዊ ትስስሩ የኖረና ስረ መሰረት ያለው በመሆኑ ነው። እያንዳንዱ ያሳለፍነው ሥርዓት የየራሱን አሻራ አሳርፎበታል። ጠባሳው ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሯል። ስለሆነም ችግራችንም የቅብብሎሹ አካል ሆኗል። ማናቸውም ታሪካችን የመከራችን መከር ነው የምንለውም ለዚህ ነው። አያሌ ምሁራን እንዳፈራን እናውቃለን። ችግር-ፈቺና ለሀገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ ምሁራንን ግን ገና ገና አልጨበጥንም፡፡ አንድ የጥንት ድምጻዊ ከዓመታት በፊት እንዳቀነቀው፡-
“ፈረንጅ አገር ሄዶ ተምሮ ሲመጣ
ትምህርቱን ሳይሰጠን ነቀፌታው ጣጣ
በወላጁ ዛተ
በአገሩ ተረተ
ቢማር ተሳሳተ” ብሎናል።
የመማር ሁነኛ ትርጉሙ አገርን መለወጥ ሊሆን ይገባዋል። ድካማችን ሁሉ የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ነው። እንጂ በችግር ላይ ችግር ለመጨመር መሆን የለበትም። ያለፈውን መንግስት ጥፋት ይሄኛው ከደገመ፤ “ትላንትና ማታ ደጃፍህ ላይ እንቅፋት ሆኖ የመታህ ድንጋይ ዛሬም ከደገመህ፣ ድንጋዩ አንተ ነህ።” የተባለው ተረት ዕውን ሆነ ማለት ነው።
በመከራ ላይ መከራ እየደረትን መኖር የለብንም። ይልቁንም በየዕለቱ አንዳንድ ዕዳ እየቀረፍን ለማደግ መሞከር ያባት ነው። በዕዳ ላይ ዕዳ እየጨመርን ይህቺን መከረኛ አገራችንን ጣሯን ካበዛንባት፣ “የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላይ ያጎርሳታል!” የተባለው ተረት ዓይነት ሆነ ማለት ነው። መንግስታችን ይኼን ያስብ ዘንድ ልብና ልቦና ይስጠው!!