
Administrator
ጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ሳምንት ብቻ 10 አዳዲስ ከፍተኛ ሹመቶች ሰጥተዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለከፍተኛ የሀላፊነት ቦታዎች የተመረጡትን አዳዲስ ተሿሚዎች ይፋ አደረጉ ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሹመት ይፋ ያደረጉት በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ተሿሚዎች የህዝብ እንደራሲዎች ምክር ቤት እንዲያፀድቅላቸው በጠየቁት መሰረት አፅድቋል፡፡ በዚህም መሰረት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ፣ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ደግሞ የማዕድን ሚኒስትር እንዲሁም ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ሹመቶችንም የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት ከጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አቶ ማሞ ምህረቱ የብሄራዊ ባንክ ገዢ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጪ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ፣ ወ/ሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ሀላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም አቶ መለሰ አለሙ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ የዘርፍ አስተባባሪ ሆነው ተሾመዋል፡፡
በሌላ በኩል፣የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ሥብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔዎችን ካስተላለፈ በኋላ የማዕድን ሚኒስትሩን ታከለ ኡማን (ኢ/ር) የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትራን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን ፣ የግብርና ሚኒስትሩን አቶ ኡመር ሁሴንና ተፈሪ ፍቅሬን በክብር ከሸኘ በኋላ ቀጣይ ጉዟቸው የተሳካ እንዲሆን ተመኝቶላቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን ረዳ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትንና ምክትል ፕሬዚደንትን ሹመት አፅድቋል፡፡ በዚሁ መሰረት ም/ቤቱ አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከበደን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አድርጎ በ3 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ ሲያፀድቅ፣ ወይዘሮ አበባ እምቢአለን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ በሙሉ ድምፅ ሹመታቸውን ማፅደቁ አይዘነጋም፡፡
የከተማዋ የትራንስፖርት ታሪፍ ምን ያህል ጨመረ?
የባቡር ታሪፍም ከ4 ብር ወደ 7 ብር ጨምሯል
በጥር ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገውን የዋጋ ማስተካከያ ከግምት ውስጥ በማስገባት የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በዚህም መሰረት ለሚኒባስ ታክሲዎች÷ እስከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 3 ብር ከ50 የነበረው በተስተካከለው ታሪፍ 4 ብር፣ ከ2 ነጥብ 6 እስከ 5 ኪሎ ሜትር 6 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ 7 ብር ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ከ5 ነጥብ 1 እስከ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 10 ብር የነበረው ታሪፍ በተመሳሳይ 10 ብር ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
የሃይገርና የቅጥቅጥ ታክሲዎች የታሪፍ ማሻሻያ ደግሞ÷ እስከ 8 ኪሎ ሜትር 5 ብር የነበረው ታሪፍ በነበረው እንዲቀጥል፣ ከ8 ነጥብ 1 እስከ 12 ኪሎ ሜትር 7 ብር ከ50 የነበረው በአዲሱ ማሻሻያ 8 ብር፣ ከ12 ነጥብ 1 እስከ 16 ኪሎ ሜትር 9ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ በሚተገበረው ማሻሻያ 10 ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም ከ16 ነጥብ 1 እስከ 20 ኪሎ ሜትር 12 ብር የነበረው ክፍያ በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ 13 ብር እንዲሁም ከ20 ነጥብ 1 እስከ 24 ኪሎ ሜትር 14 ብር ከ50 የነበረው በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ 15 ብር፣ ከ24 ነጥብ 1 እስከ 28 ኪሎ ሜትር 17 ብር የነበረው 18 ብር እንዲሆን መወሰኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ከ7 ነጥብ 6 እስከ 10 ኪሎ ሜትር 13 ብር የነበረው ታሪፍ በማሻሻያው 14 ብር፣ ከ10 ነጥብ 1 እስከ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 16 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ 17 ብር፣ ከ12 ነጥብ 6 እስከ 15 ኪሎ ሜትር 19 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ 20 ብር ከ50 እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ከ15 ነጥብ 1 እስከ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 23 ብር የነበረው 24 ብር፣ ከ17 ነጥብ 6 እስከ 20 ኪሎ ሜትር 26 ብር ከ50 የነበረው በአዲሱ ማሻሻያ 27 ብር፣ ከ20 ነጥብ 1 እስከ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 29 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ በማሻሻያው 31 ብር ሆኗል፡፡
እንዲሁም ከ22 ነጥብ 6 እስከ 25ኪሎ ሜትር 33 ብር የነበረው ታሪፍ በማሻሻያው 34 ብር፣ ከ25 ነጥብ 1 እስከ 27 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር 36 ብር የነበረው ታሪፍ 38 ብር፣ ከ27 ነጥብ 6 እስከ 30 ኪሎ ሜትር 39 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ በአዲሱ ማሻሻያ 41 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
በተሻሻለው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ታሪፍ ደግሞ እስከ 17 ኪሎ ሜትር 4 ብር የነበረው፣ በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ 7 ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡
የአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆነ
አረቄ በጫነ መኪና ምክንያት በተከሰተ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ የነበረው የአዲስ -አዳማ የክፍያ መንገድ የአዳማ ዋና መውጫ ከትናንት ጥር 12 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ 3፡30 ጀምሮ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆኖ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ፡፡
ባለፈው ሰኞ ጥር 8 ምናልባትም በክፍያ መንገዱ የመጀመሪያና ከባድ አደጋ መድረሱን በዚህም የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን የገለፀው ኢንተርፕራይዙ፣ በዚህ ምክንያት የአዲስ አደማ ዋና መውጫ መንገድ እስከ ትናንትና ድረስ ለተሽከርካሪ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ እንደነበር አስታውሷል፡፡ በኢንተርፕራይዙ የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ የሆኑት ዘሃራ መሃመድ አንዳብራሩት መንገዱ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎለት ከትናንት ጥር 12ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ 3፡30 ጀምሮ ለተሸከርካሪ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በቦስተን ማራቶን ላይ ተጠብቀዋል
በ127ኛው የቦስተን ማራቶን ላይ በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ በወቅታዊ ብቃታቸው ውጤታማና ለአሸናፊነት ተጠብቀዋል፡፡ በወንዶች ምድብ 21 አገራትን የሚወክሉ ምርጥ የማራቶን አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡ ከመካከላቸውም ከ2 ሰዓት ከሰባት ደቂቃ በታች የሚገቡ 15 አትሌቶች መኖራቸው አስደናቂ ፉክክር የሚፈጥር ይሆናል፡፡ በወንዶች ምድብ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የዓለም ሪከርድን የያዘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ መሳተፉ ነው። ሄርፓሳ ነጋሳ፤ ሹራ ኪታታ፤ አንዱአለም በላይና አንድአምላክ በሃይሉ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሮጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በቦስተን ማራቶን ላይ በሴቶች ምድብ ልዩ ትኩረት የሳበችው ደግሞ የኢትዮጵያዋ አማኔ በሬሶ ናት፡፡ በ2022 የቫሌንሽያ ማራቶን ላይ ያሸነፈችው አማኔ በወቅቱ ያስመዘገበችው 2 ሰዐት ከ14 ደቂቃዎች ከ58 ሴኮንድ በማራቶን የኢትዮጲያ ክብረወሰን እንደሆነ ይታወቃል። በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን የሆነችውና በቶኪዮ ማራቶን በሶስተኛ ደረጃ የጨረሰችው ጎይተቶም ገብረስላሴ፤ በ2021 በበርሊን ማራቶን ሁለተኛ የነበረችውና በ2022 ቶኪዮ ማራቶን በ5ኛ ደረጃ የጨረሰችው ህይወት ገብረማርያም፤ በ2019 በቺካጎ ማራቶን 2ኛ፤ በ2021 ኒውዮርክ ማራቶን 3ኛ እንዲሁም በ2022 ቦስተን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ የወሰደች አባቤል የሻነህ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ኬንያን በመወከል ደግሞ የዓለም ክብረወሰን የያዘችው ብሪጂድ ኮሴጊ፤ ያለፈው የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ፔሬስ ጄፕቺሪር፤ ሁለት ጊዜ የቦስተን ማራቶን ሻምፒዮን የሆነችው ኤድና ኪፕላጋት ይጠቀሳሉ፡፡
የቦስተን ማራቶን አሸናፊዎች በሁለቱም ፆታዎች 150ሺ ዶላር በአዘጋጆቹ የሚሸለሙ ሲሆን ለሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ 75ሺ ዶላርና 40ሺ ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ የቦታውን ሪከርድ ለሚያስመዘግብ አትሌት ደግሞ 50ሺ ዶላር ቦነስ ይበረከታል፡፡
ባለፉት 126 የቦስተን ማራቶኖች ከ27 በላይ አገራትን የወከሉ አሸናፊዎች ተገኝተዋል። 108 አሸናፊዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ አሜሪካ ስትሆን፤ ኬንያውያን 34 እንዲሁም ካናዳ 21 አሸናፊዎችን አስመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑም በወንዶች 6 ጊዜ እንዲሁም በሴቶች 8 ጊዜ ቦስተን ማራቶንን አሸንፈዋል፡፡ በወንዶች በ1989 ላይ አበበ መኮንን፤ በ2005 ላይ ሃይሉ ንጉሴ፤ በ2009 ድሪባ መርጋ፤ በ2013ና በ2015 ሌሊሳ ዴሲሳ እንዲሁም በ2015 ለሚ ብርሃኑ አሸንፈዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ1997 በ1998 እና በ1999 ለሶስት ተከታታይ ግዜያት ፋጡማ ሮባ፤፤ በ2008 ድሬ ቱኔ፤ በ2010 ጠይባ ኤርኬሶ፤ በ2014 ብዙነሽ ዳባ፤ በ2016 አፀደ ባይሳ እንዲሁም በ2019 ወርቅነሽ ደገፋ አሸንፈዋል፡፡
ፍቅር ያላት አገር፣ ሽለ - ሙቅ ናት!
በጥንት ዘመን የነበረ አንድ ንጉሥ ታላላቅ ጠበብት፣ መኳንንት፣ መሣፍንት እንዲሁም የጦር ኃይል አባላትን ጨምሮ ህዝቡን ሰበሰበና አገር ለማዳንና ህልውናዋ ተጠብቆ እንድትቆይ “ወሳኝ እኔ ነኝ” የሚል እጁን ያውጣና ምክንያቱን ያስረዳኝ አሉ፡፡
በመጀመሪያ የጦር አበጋዙ ተነስቶ፤
“አገር የማድን፣ የአገርን ህልውና የማስጠብቅ እኔ ነኝ” አለ፡፡
ሁለተኛ የተነሳው ምሁሩ ነበር፤
“ያለ እኔ ዕውቀት አገር ደህንነቷና ህልውናዋ አይጠበቅም፡፡ ምንም ነገር ስትሰሩ፣ እኔን ያማክሩ አለ፡፡ ስለ ጦር መሳሪያም ቢሆን መሰረቱ የእኔ እውቀት ነው!” አለ፡፡
ሦስተኛው ገበሬው ነው፤
“እኔ ካላመረትኩ ሁሉም ከንቱ ነው ንጉሥ ሆይ።
ስለዚህ በልተው ካላደሩ፣ ምንም አይሰሩ!” አለ፡፡
ነጋዴው ተነሳ፤
“የጦር መሳሪያውንም፣ የምሁራኑንም የምርምር ዕቃ፣ የገበሬውንም ምርት የሚያንቀሳቅሰው የእኔው የንግድ ሥራ ነው! በእኔ ኃይል ነው የአገርን ደህንነትና ህልውና የሚያቆዩት ንጉሥ ሆይ!” አለና ተቀመጠ፡፡
የቢሮ ኃላፊው እጁን አውጥቶ ተነሳና፤
“ንጉሥ ሆይ! የተናገሩት ሁሉ ዕውነት ነው፡፡ ነገር ግን የጽህፈት ሥራና የቢሮክራሲ ደም - ሥር ካልታከለበት ከንቱ ነው፡፡ የእኔን ቢሮክራሲ የማያከብር ዋጋ አይኖረውም!”
የጥበብ ሰው ተነስቶ፤
“አገርን የሚያሽር የጥበብ ሥራ ነው! ምንም ነገር ተነስቶ ጥበብ ካልተጨመረበት ዐይን አይገባም፡፡ ህይወት አይኖረውም!” አለ፡፡
የፋይናንስ ሃላፊው፤
“ንጉሥ ሆይ! ምንም አያሳስብም፡፡ ያለ ሂሳብ፣ ያለ ፋይናንስ ማንም የትም አይንቀሳቀስም! እኔ ሂሳብ ከተቆጣጠርኩ፤ አገር አማን ናት!” አለ፡፡
በመጨረሻ አንዲት ምስኪን ሴት ተነስታ፤
“ንጉሥ ሆይ! ምንም ተባለ ምን፣ ወሳኙ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ነው ገዢው!” አለች፡፡
ንጉሡ አሰቡ አሰቡና፤ “ያለ ፍቅር ምንም ነገር ከንቱ ነው፡፡ አንቺ አማካሪዬ ትሆኛለሽ” አሉና ደመደሙ፡፡
***
“እስከ ዛሬ ጥሩ ጦርነት አልነበረም፡፡ መጥፎ ሰላምም ታይቶ አያውቅም!” ይላል ፍራንክሊን፡፡ ታላቅ ጦርነት አንድ አገር ላይ ሦስት አሻራ ትቶ ያልፋል፡-
ሀ. የአካል ጉዳተኞች ሠራዊት
ለ. የሐዘንተኞች ሠራዊት
እና ሐ. የሌቦች ሠራዊት
ይሄ ሁሉ የፍቅር መጎናፀፊያ በሌላት አገር የሚከሰት ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ ህብረተሰብና እስከ ጎረቤት አገር ድረስ ፍቅር ከሌለ የሚከሰት ብዙ ጎዶሎ ሥፍራ አለ፡፡ ያንን ለመሙላት የሞቀ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ ጦር፣ ትምህርት፣ ምርት፣ ንግድ፣ ቢሮክራሲ፣ ጥበብ፣ ፋይናንስ ወዘተ … ሁሉም የፍቅር ተገዢ መሆን አለባቸው - አለዛ ሰላም አይኖርም!
የዓለም ኢንፎርሜሽን ቀን እናከብራን፡፡
የፍትሕ ቀን እናከብራለን፡፡
የፕሬስ ቀን እናከብራለን፡፡
የአረጋውያን ቀን እናከብራለን፡፡
የወጣቶች ቀን እናከብራለን፡፡
የቫላንታይን ቀንም እናከብራን፡፡
የእጅ መታጠብ ቀንም እናከብራለን!
ምኑ ቅጡ! አያሌ የምናከብራቸው ቀናት አሉ፤ ይኖራሉም። ወደንም ይሁን ሳንወድም! የዓለምም ይሁን የአገር! ወጣም ወረደ፤ ሁሉም ፍቅር ይፈልጋሉ፡፡ ፍቅሩን በዛ አድርጎ ይስጠን!
ክፉ ክፉውን በማሰብ አገር አናድንም፡፡ መግባባት፣ መናበብ፣ መቀራረብ፣ ውዝግብን ከየሆዳችን ማውጣት፣ ለመፋቀር መዘጋጀት … የአገር ፍቅር መሰረት ነው፡፡ የጀግንነት ምልክት ፍቅርን መላበስ ነው!
ለወታደሩ ፍቅር ይስጠው፡፡ ለፖለቲከኛው ፍቅር ይስጠው፡፡ ለምሁሩ ፍቅር ይስጠው፡፡ ለሂሳብ አዋቂው ፍቅር ይስጠው፡፡ ለነጋዴው ፍቅር ይስጠው! ለጥበብ ሰው ፍቅር ይስጠው! አገር በፍቅር ትድን ዘንድ ለሁላችንም ፍቅር ይስጠን፣ ብርታት እና ፅናቱን ይስጠን!
ኮስተር ብለን ካሰብን ምርት ያለ ፍቅር አይመጣም፡፡ ዕድገት ያለፍቅር አይመጣም። የመንፈስ ተሐድሶ ፍቅርን ይሻል፡፡ ለውጥ ፍቅርን ይሻል፡፡ A change is equal to rest የሚለው የአይንስታይን አባባል መለወጥ ማረፍ ነው እንደማለት ነው፤ ትርጉሙ እያደር ሊገባን ግድ ነው። እረፍት የሰላም መደላድል ነው፡፡ ለውጥ ለአዲሱ ሁኔታ ተገዢ መሆንን ይጠይቃል! Resist conservatism! እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡ “ወግ - አጥባቂነት ይውደም” የሚለው የዱሮ መፈክር ይበልጥ ይገልጠው ይሆናል! መንገዶች ሁሉ ወደ ለውጥ ያመሩ ዘንድ ዐይናችንን እንግለጥ!!
ለውጥ ፍቅር ይፈልጋል፡፡ ምነው ቢሉ? ፍቅር ያላት አገር ሽለ-ሙቅ ናት፤ (Fertile) ወላድ ናትና! ምርታማ ናትና! ለዚያ ያብቃን!
“አሳንቲ” ዛሬ በሐገር ፍቅር ይመረቃል
የደራሲ ምርት ባቦ የበኩር ሥራ የሆነው “አሳንቲ “ የተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ዛሬ ቅዳሜ ከጠዋቱ 4 ሰዓት በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡
በ212 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ አምስት አጫጭር ልብወለድ ታሪኮችን ያካተተ ነው፡፡
በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ሥራዎቻቸውን ከሚያቀርቡ ታዋቂ የሥነጽሁፍ ባለሙያዎች መካከል ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ የህግ ባለሙያው ተክለሚካኤል አበበ፣ ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ፣ ተዋናይ ፍቃዱ ከበደና ሌሎችም ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የምርቃት ፕሮግራሙን ኒው አቢሲኒያ ባንድ በሙዚቃ እንደሚያደምቀው ታውቋል፡፡
በአሜሪካ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችና አስገዳጅ ህጎች ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸው ተገለጸ
በአሜሪካ የዴሞክራት 117ኛው ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች እንዲሁም አስገዳጅ ህጎችና ረቂቅ ህጎች ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸውን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ትናንት አስታወቀ፡፡
“አዲሱ የሪፐብሊካን 118ኛው ምክር ቤት ኮንግረሱን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ላይ ወጥተው የነበሩ የዴሞክራቶች ረቂቅ ህጎች ሙሉ በሙሉ ጊዜው ያለፈባቸው ሆነዋል” ብለዋል፤ የም/ቤቱ ሰብሳቢ ዲያቆን ዮሴፍ_ተፈሪ፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግሥት የተለያዩ ማዕቀቦች በመጣልና አስገዳጅ ህጎች በማውጣት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሲጥር መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አሁን በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ እየተከሰተ ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ከአዲሱ የኮንግረሱ መሪ ኬቨን ማካርቲ ሃላፊዎች ጋር ንግግር መጀመሩን ምክር ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር በወቅቱ አገራዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ልዩ የልኡካን ቡድን ትላንት ከአሜሪካ ተነስቶ እስራኤል መግባቱ ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወራት ውስጥ 8.18 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ኢትዮ ቴሌኮም፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 33.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን 8.18 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡንም ገልጿል።
ኩባንያው በስድስት ወር አፈጻጸሙ ያገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ19.9 በመቶ እድገት እንዳለው የተጠቆመ ሲሆን፤ ዓምና በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ያገኘው ገቢ 28 ቢሊዮን ብር ነበር።
በ2014 በጀት ዓመት 61.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስመዘገበው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዘንድሮው ዓመት ገቢውን ወደ 75.05 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ እቅድ የያዘ ሲሆን፤ ባለፉት ስድስት ወራት ያገኘው ገቢ የእቅዱን 96 በመቶ ያሳካ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው ባለፉት ስድስት ወራት የደንበኞቹን ቁጥር አምስት በመቶ በማሳደግ 70 ሚሊዮን ማድረሱ ከትላንት በስቲያ በስካይ ላይት ሆቴል፣ የ2015 የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ቁጥር በዚህ ያህል መጠን ያሳደገው፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመርን ተከትሎ በተፈጠረው “የውድድር ገበያ” ውስጥ መሆኑን ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ አመልክተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ “ዱቤ አለ” የተሰኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት ጀመረ
ዳሸን ባንክ ከኤግል ላይን ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር “ዱቤ አለ” የተሰኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት ባለፈው ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዋውቋል፡፡
“ዱቤ አለ” በሀገራችን በባህላዊ መንገድ ሲከናወን የነበረውን የማህበረሰባችንን የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አስተማማኝ የባንክ አሰራር በማገዝ የቆየን እሴት የሚያስቀጥል የግብይት አገልግሎት መሆኑን የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በማስጀመሪያ ሥነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ ዳሸን ባንክ ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በመተባበር፣ ህብረተሰቡ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችንና በርካታ አገልግሎቶችን በ3 ወር፣ በ6 ወርና በ12 ወር በሚመለስ ዱቤ በወለድና ያለወለድ መግዛት የሚያስችል አማራጭ መሆኑም ተብራርቷል፡፡
“ዱቤ አለ” ሸማቾች የፈለጉትን እቃ በዱቤ ገዝተው ቆይተው መክፈል የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ አሰራርና መተግበሪያ ሲሆን፤ መተግበሪያውን በቀላሉ ከፕሌይስቶር ወይም ከአፕስቶር በማውረድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻል የኤግል ላይንስ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በእርሱ ፈቃድ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡ “ዱቤ አለ” የተሰኘው የዱቤ ግብይት አገልግሎት ህብረተሰቡ ያሻውን በዱቤ ገዝቶ ቀስ ብሎ መክፈል የሚችልበትን እፎይታ ይሰጣል የተባለ ሲሆን፤ የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና በማቅለል በኩልም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጧል፡፡
የኤግል ላይንስ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈፃሚው በእርሱ ፈቃድ ጌታቸው ቴክኖሎጂውን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት ሲደረግበት ቆይቶ በሀገር ልጆች እንዲበለፅግ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ደንበኞች መተግበሪያውን ካወረዱ በኋላ መመዝገብ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ከተመዘገቡ በኋላ ወደ ዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ የዱቤ ገደብ ማስፈቀድና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ታውቋል፡፡
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከ480 በላይ እስረኞችን ማስለቀቃቸው ተጠቆመ
ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ኦሮሚያ፣ ምዕራብ ጉጂ ዞን፣ በቡሌ ሆራ ከተማ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከ480 በላይ እስረኞችን ማስለቀቃቸው ተጠቆመ።
የመንግስት ባለሥልጣንና ነዋሪዎች ለ”አዲስ ስታንዳርድ” እንደተናገሩት፤ የአማፂ ቡድኑ አባላት በጎሮ ጉዲና ቀበሌ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር እስረኞችን አስለቅቀዋል፡፡
የቡሌ ሆራ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጊርጃ ኡራጎ እንደገለጹት፤ ታጣቂዎቹ በሥራ ላይ የነበሩ አምስት የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ አባላትን ከገደሉ በኋላ ነው እስረኞቹን ያስለቀቁት፡፡
“የአማፂ ቡድኑ አባላት አምስት የማረሚያ ቤቱን ጠባቂዎች ከገደሉ በኋላ ከ480 እስከ 500 የሚደርሱ እስረኞችን ማስለቀቅ ችለዋል” ሲሉ ከንቲባው ለ”አዲስ ስታንዳርድ” ተናግረዋል።
ከማረሚያ ማዕከሉ አቅራቢያ የሚኖሩ አንድ እማኝ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከባድ የተኩስ ልውውጥ ነበር።
“የተኩስ ልውውጡ ከምሽቱ 5፡30 ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 9፡30 ዘልቋል። በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከባድ ተኩስ ነበር። ከዚያ በኋላ ነው የአማጺው ቡድን አባላት ወደ ማረምያ ማዕከሉ ዘልቀው በመግባት እስረኞቹን ያስለቀቁት።” ብሏል፤ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የአካባቢው ነዋሪ።