
Administrator
“አገሬ በልጽጋ ከውጭ ልመና ወጥተን ማየት እሻለሁ”
• መንግስትና ህዝብን ማጭበርበር እግዚአብሔርን ማጭበርበር ነው
• ለህዝቡ መንገድ ለመሥራት ከቀበሌ አመራሮች ጉቦ ተጠይቀናል
ባለፈው ሳምንት በልጅነታቸው ከሸንኮራ አገዳ ንግድ ጀምረው ዛሬ የቢሊዮኖች ዶላር ኢንቨስትመንት ባለቤት የሆኑትን የአቶ አቶ መኩሪያ ባሳዬ ቃለምልልስ የመጀመሪያ ክፍል አቅርበናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከታሪኩ ባለቤት ጋር ያደረገችውን
ሁለተኛ ክፍል አስደማሚ ቃለምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡ ታሪኩ በራስ ጥረትና ልፋት የሚገኝ ስኬትን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነውና ትወዱታላችሁ፤ ትማሩበታላችሁ ብለን እናምናለን፡፡ የመጀመሪያውን ቃለምልልስ ያላነበባችሁ በአዲስ አድማስ ዌብሳይት
ህብረተሰብ አምድ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡
አሁን ላይ ከትዳር አጋርዎ ዶ/ር ማርጋሬት መኩሪያ እና ናኦል መኩሪያ የተባሉ ልጆችን ማፍራት ችለዋል ---
አዎ! እውነት ነው፡፡ እውነት ለመናገር በወቅቱ አባትየው እውነት ነበራቸው፡፡ እኔ እንኳን የእሳቸው ልጅ ማግባት ቀርቶ የቤት ሰራተኛቸው መሆን አይገባኝም፡፡ አንደኛ አልተማርኩም፣ ሁለተኛ የገጠር ልጅ ነኝ፤ ሶስተኛ የገበሬ ልጅ ነኝ፡፡ እሳቸው በቦሬ በጉጂና በአዲስ አበባ በጣም የታወቁ ብዙ ሀብትና መኪኖች የነበሯቸው የተከበሩ ሰው ናቸው። በሰው አይንና ሚዛን የሚሆን አልነበረም፤ እግዚአብሔር ስለፈቀደ ነው ሁሉም የሆነው። እንዳልሽው በ1987 ዓ.ም የመጀመሪያ ልጄ ማርጋሬት ተወለደችልኝ፡፡
ስሟን ግን እንዴት ማርጋሬት ብላችሁ ሰየማችኋት?
በ1987 ቦንኬ የሚባል ሰባኪ ከውጪ መጥቶ ሀዋሳ ስታዲየም ላይ እየሰበከ ነበር፡፡ በዚያን ዕለት ሰባኪው ስለ አንድ የራሽያ ወታደር ታሪክ ይነግረናል። ወታደሩ በዓለም ጦርነት ጊዜ ማርጋሬት የተባለች የሚወዳትን ሚስቱን ጥሎ ነው የሄደው፡፡ ከጦርነቱ ሲመለስ ከተማው በሙሉ ወድሞ የእሱ ቤት ብቻ ቀርቷል፡፡ “በቃ ሚስቴ አለች እድለኛ ነኝ” ብሎ በሩን አንኳኳ። በሩን ስትከፍትለት እሱ መሆኑንም ስታይ ደንግጣ በሩን ዘጋችበት። እሷ ሞቷል ብላ ሌላ አግብታለች፡፡ ይህ ሰው “ማርጋሬት ማርጋሬት” እያለ እየጮኸ፣ በሌላ አቅጣጫ ከባሏ ጋር ጠፍታ ሄደች” እያለ ታሪክ እየነገረን ባለለቤቴ ምጥ ያዛትና በ30 ደቂቃ ውስጥ ወለደች፡፡ ከዚህ ታሪክ ጋር ተያይዞ ነው ማርጋሬት ያልናት። አያቷ (የእናቷ እናት) ፋዮ ካልቻ ይባላሉ። እሳቸው ናቸው እንዲያውም ማርጋሬት ትባል ያሉት። ሁለተኛው ልጄ ናኦል ይባላል፡፡ አሜሪካ እየተማረ ይገኛል፡፡ ከዚያ ልጅ የመውለድ ፕሮግራም አቆምንና ባለቤቴን ወደ ት/ቤት መለስኳት፡፡ እንደነገርኩሽ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ከ9ኛ ክፍል ነው ጠልፌ ያገባኋትና ሀዋሳ ታቦር ሀይስኩል ጨርሳ፣3 ነጥብ 8 አምጥታ፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ገባች፡፡ በጥሩ ነጥብ ተመርቃ ወጣች። እሷ አራት ዓመት ተምራ እስክትጨርስ ልጆቼን ያሳደግኩት እኔ ነኝ፡፡ እኔ ባልማርም የሚማር ሰው እወዳለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች እንዲማሩ ደግፌያለሁ፡፡ ከዜሮ ጀምረው እስከ ከፍተኛ ትምህርት አጠናቅቀው ውጪ የሄዱም አሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በሀላፊነት የሚሰሩም አሉ፡፡ በዚህ ደስ ይለኛል፡፡ ባለቤቴ ተመርቃ ከወጣች በኋላ በሀዋሳ ማዘጋጃ ቤት እንድትቀጠር አደረግሁ፡፡ ወይዘሮ ውቤ ዮሐንስ ትባላለች፡፡ እሷ ማዘጋጃቤት መስራት ስትጀምር እኔ የኮንስትራክሽን እቃ አስመጪነት ጀመርኩኝ፡፡ እሱን አንድ አመት እንደሰራሁ ወደ ኮንስትራክሽን ገባሁ፡፡ ደረጃ አራት ተቋራጭ ድርጅት መሰረትኩ፡፡ ያን ጊዜ ሼህ አላሙዲን በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋም እየሰሩ ነበርና እሱን በግብዣ መልክ እኔ እንድገነባ ሰጡኝ፡፡ እሱን በአንድ ዓመት አጠናቅቄ ሀዋሳ መጣሁ፡፡ ሀዋሳዎች አራት የክፍለ ከተማ ፅ/ቤቶች ግንባታ ሰጡኝ፡፡ እነሱ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር እንዳስረክብ ነበር የፈለጉት፡፡ እኔ በ6 ወር ጨርሼ አስረከብኩ፡፡
በጣም አስገራሚ ነው! እስኪ በሀዋሳ ስላፈሯቸው ሀብቶች ያጫውቱኝ?
በሀዋሳ ከሰዎች የግል ይዞታ መሬት እየገዛሁ፣ ቤት እየሰራሁ እሸጣለሁ፡፡ ሀዋሳ አደባባይ ላይ በርካታ ግንባታዎች አሉ፤ ነገር ግን ከግለሰቦች መሬት እየገዛሁ እንጂ ከመንግስት ጠይቄ አይደለም የምሰራው፡፡ እኔ ከመንግስት ለመኖሪያ ቤት እንኳን መሬት ጠይቄ አላውቅም። አሁን በቅርቡ ትልቅ ሆቴል ለመገንባት አዲስ አበባ መሬት ጠይቄ ተሰጥቶኛል፡፡ ከዚያ ውጪ መሬት እየገዛሁ ነው የምገነባው፡፡
ሀዋሳ ላይ መሃል ፒያሳ “ታይም ካፌ” ፣ “ታይም የገበያ ማዕከል”፣ “ታይም የገበያ አዳራሽ”፣ “ታይም የመኝታ አገልግሎት” የተሰኙ ተቋማት ከፍተዋል፡፡ አሁንም ሀዋሳ ላይ ነው ኑሮዎን ያደረጉት ወይስ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል?
እኔ አዲስ አበባ መኖሪያ ቤት የለኝም፤ አሁንም የምኖረው ሀዋሳ ነው፡፡ ምን መሰለሽ -- የሰሜኑ ጦርነት ሲቀሰቀስ በጣም ነበር ያዘንኩት። በዚህ በኩልም ከትግራይ በኩልም የሚሞቱት ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ በዚህ ጦርነት ዱባይ ቤት ያልገዛ፣ ሀብት ያላሸሸ ባለ ሀብት የለም፡፡ አብዛኛው ማለት ይቻላል እንደዛ አድርጓል፡፡ እኔ እንኳን ዱባይ ሄጄ ቤት ልገዛ አዲስ አበባ እንኳን ቤት የለኝም። አልፈልግም። ከደሀ ማህበረሰብ መሃል ወጥተን አድገን የት ነው ጥለን የምንሄደው፡፡ ይቺ አገር እኮ እኔ አንቺ ሌሎች ወንድሞቻችን እህቶች እንጂ ሌላ የላትም’ኮ፡፡ ከዚህ ደሀ ህዝብ ጉሮሮ ነጥቄ ዱባይ ቤት የምገዛበት ምክንያት የለም፡፡ ዱባይም አሜሪካም የሚኖር ሁሉም ይሞታል። ወደ መሬት ይገባል፡፡ ስለዚህ እኔ የቅንጦት ህይወት አልፈልግም፤ መኖሪያዬ ሀዋሳ ነው። ቅድም የጠቀስሽው ታይም ካፌ ሀዋሳ ላይ በጣም ብራንድ ነው፡፡ ሻይ፣ ቡና ማኪያቶና ጭማቂ ነው የምንሸጠው፡፡ ዓመታዊ ሽያጫችን 32 ሚሊዮን ብር ገብቷል፡፡ መንግስት ከዚያ ብዙ ታክስ ያገኛል፡፡ አንዲት ሽራፊ ሳንቲም አናጭበረብርም፡፡ መንግስትና ህዝብን ማጭበርበር እግዚአብሄርን ማጭበርበር ነው፡፡ ደረሰኝ ሳንቆርጥ አንድ ውሃ አንሸጥም፡፡ በዚህ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል። እንዳልኩሽ ሀዋሳ ላይ ከ10 በላይ ግንባታዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ሁሉንም መሬት ገዝቼ ነው እየገነባሁ ያለሁት። መንግስት መሬት አመቻችቶ ሰጥቶኝ ቢሆን ለመሬት ግዢ የሚወጣው ብር ይተርፍና ሌላ ይሰራ ነበር ፤ነገር ግን ከመንፈስ እርካታዬ አይበልጥም፡፡
ኢንዱስትሪም ገንብተዋል ልበል?
አዎ ሀዋሳ ላይ የገዛሁት የዱቄት ፋብሪካ አለ፤ በዘመናዊ መንገድ አደራጅቼ አልሚ ምግብ ማምረት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ለህፃናት አልሚ ምግብ በጣም ያስፈልጋል። በእኔ አቅም ጥቂት ልጆች ከአልሚ ምግብ እጥረት ከተላቀቁና ጤናማና ብሩህ ሆነው ካደጉ ለእኔ እርካታ ነው። ሌላው ላለፉት 12 ዓመታት ስጠይቅና ስጠብቅ ቆይቼ፣ ገና አምና ነው ቦታውን የሰጡኝ፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን አመሰግናለሁ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ግዙፍ የማዕድናት ማቀነባበሪያ ልገነባ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ግንባታውን ለውጪ ተቋራጮች ነው የምንሰጠው፤ በጣም ግዙፍ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ አፍሪካ ህብረት አካባቢም የህንፃ ግንባታ ጀምረናል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ ከተማ ላይ ትልቅ የወተት ማቀነባበሪያ ልናቋቁም ከግለሰብ ኩባንያ ገዝተን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ልናደራጅ በሂደት ላይ ነን፡፡ እዚያ አካባቢ ያለው ጥሩ ያልሆነ ቢሮክራሲ ይዞን እንጂ እስካሁን ብዙ እርቀት በሄድን ነበር፡፡ እኛ የግንባታ መሳሪያ ሙሉ በሙሉ አስገብተናል፡፡ ችግሩንም ለሚመለከተው የኦሮሚያ መንግስት አቤት ብለን እየተፈታ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ይጀመራል፤ ኢንቨስትመንቱ 59 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
በአጠቃላይ ስንት ኩባንያዎች ናቸው ያሉዎት?
32 ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በስራቸው ከ3 ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉ፡፡ አሁን እዚያም እዚህም ሆነው በዝተው እኔንም እያደከሙኝ ነው፡፡ እስከ ዛሬ በቀን ከ18 ሰዓት በታች ሰርቼ አላውቅም ነበር። አሁን በቅርቡ 17 ሰዓት መስራት ጀምሬያለሁ። እነዚህን ኩባንያዎች ጠቅለል አድርገን በአንድ በሶስቱ ላይ ማተኮር እንፈልጋለን፡፡ ሻኪሶ ውስጥ ለምሳሌ የቡና እርሻ አለኝ፡፡ እኔ 160 ሄክታር የቡና እርሻ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በ35 ሚሊዮን ብር መሬቱን ገዝቼ፤ መሬቱን የሸጠልኝ ግለሰብ በ7 ሚሊዮን ብር መፈልፈያ ሸጦልኝ በድምሩ በ42 ሚሊዮን ብር ነው ወደ ቡና እርሻ ስራ የገባሁት፡፡ ነገር ግን መሬት በሊዝ ባገኝ ኖሮ፣ በ2 ሚሊዮን ብር ማለቅ ይችል ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ የቡና እርሻው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል። አንደኛ ደረጃ ኦርጋኒክ ቡና ነው፡፡ በጉጂ ዞን ኦዳ ሻኪስ ወረዳ ሀንገዲ ቀበሌ ነው የሚገኘው፡፡ እዚህ አካባቢ ደስ የሚለንን ነገር ልንገርሽ፡፡ የቡና እርሻውን እንደገዛሁ መንገድ የለም ነበር፡፡ የአካባቢው ህዝበ በመንገድ እጦት ያለቅስ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ህዝቡ ይሰቃይ ነበር፤ 14 ኪ.ሜትር መንገድ ነው ለህዝቡ የሰራሁት፤ ያንን መንገድ ስሰራው ብዙ ፈተና አይቻለሁ፤ ለህዝቡ እንባ ስል ለቀበሌ አመራሮች እጅ መንሻ ከፍያለሁ። ለምን እከፍላለሁ ባልሰራ ቢቀርስ ማለት እችል ነበር። ግን ደግሞ ህዝቡ ያሳዝናል። ማሽን ጭነን ሄደን፤ ዶዘር ኤክስካቫተር፣ ሩሎ፣ አስራምናምን ዳምፕ ትራክ ይዘን ሄድን አትሰሩም ተባልን፡፡ እኔ ለአንድ እራሴ አይደለም የምሰራው፤ ለሀገር ለወገን ነው፡፡ ላልማ ባልኩ ጉቦ ተጠየኩኝ፤ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ስንት ብር ጉቦ ከፈሉ?
እሱን ተይው፡፡ 500 ሺህ ብር ካልሰጣችሁን አሉ፤ የቀበሌ አመራሮች፡፡ ሦስት ቀን አጉላሉን። ትሮ ኡዴሳ የሚባል የኔ ስራ አስኪያጅ ነበር የመንገዱን ሥራ የሚያስተባብር፡፡ እሱ አንከፍልም፤ ማሽኖች ተጭነው ይውጡ አለ፡፡ እግዚአብሄር ያሳይሽ--- ማሽኖቹ ከአዲስ አበባ ተጭነው ነው የገቡት፤ ለሎቤድ ብቻ 700 ሺህ ብር ነው የከፈልነው፡፡ ጭነን እንውጣ ብንል ሌላ 700 ሺህ ብር ለማሽነሪዎቹ መመለሻ ከምንከፍል 500 ሺህ ብር እንስጣቸውና መንገዱን ለሚያለቅሰው ህዝብ እንስራለት ብለን ተመካከርን፡፡ መንገዱን ሰራን፤ ያንን መንገድ እንደ ሦስተኛ ልጄ ነው የማየው፤ ዋጋ ከፍዬበታለሁ፡፡ በህይወቴ ፈታኝ አጋጣሚ ዎች ከምላቸውም አንዱ ነው፡፡
አሁን የተበታተኑትን 32 ኩባንያዎች እያጠፍን በሦስቱ ላይ ለማተኮር አቅደናል። ቡና ኤክስፖርት ማድረግ፣ ወርቅና ማዕድን ማቀነባበርን በተጠናከረ መልኩ አዲስ አበባ ላይ መሥራት ፈልገናል፡፡ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ላይ የከበሩ ማዕድናትን በከፍተኛ ጥረት እያቀነባበርን መላክ እንጀምራለን፡፡ ወርቅ መላክ አይቻልም፤ ብሔራዊ ባንክ ነው የሚገባው፡፡ የሀዋሳዎቹ ካፌዎች ይቀጥላሉ። አንድ ነገር ግን ልንገርሽ፤ ታይም ካፌ ብለን የዛሬ 13 ዓመት የከፈትነው የሙስሊሙም፣ የኦርቶዶክስም የፕሮቴስታንትም ትልልቅ የሀይማኖት መሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚጠቀሙበት ቀደምት ታዋቂ ካፌ ነበር፡፡ በስሩ 116 ሰዎች ይሰራሉ። አሁን እሱን ልንዘጋው ነው፡፡
ለምንድን ነው የሚዘጋው?
አሁን አዲሱ ትልቁ ታይም ካፌም ሆነ የበፊቱ ላይ ምንም የትራፊክ መጨናነቅ በሌለበት መኪና እንዳይቆም አምጥተው ምልክት አስቀመጡ። ደንበኞቻችን መኪና ማቆሚያ ስላጡ በተለይ የበፊቱን ካፌ መጠቀም አቆሙ፤ ሽያጩ በቀን እስከ 130 ሺህ ብር ነበር፤ አሁን ስላሽቆለቆለ ልንዘጋውና ሰራተኞቹን ልናሰናብት ነው፡፡ ከዘጠኝ ዓመት እስከ አሥራ ሦስት ዓመት የሰሩ ሰዎች አሉ፤ ግን ምን እናድርግ? የግድ ማሰናበት አለብን፡፡ እኛ ለከንቲባውም ነግረናል፤ መስተካከል አለበት ብለን እናምናለን፡፡
አዲስ አበባ ላይ ጋዜቦ አደባባይ ታይም ኮፊ ከፍታችኋል አይደል?
አዎ! ታይም ኮፊ በዚህ ዓመት ብቻ በአዲስ አበባ ውስጥ 15 ይደርሳል ቁጥራቸው፡፡ ለዚህም ቦታዎችን ገዝተን አዘጋጅተናል፡፡ ብሄራዊ አካባቢ ገዝተናል፣ ስቴድየም ሁለት ገዝተናል፣ ገነት ሆቴል አካባቢ ና ሌሎችም ቦታዎች ገዝተን ወደ መክፈቱ ስራ እየገባን ነው፡፡ እቅዳችን አዲስ አበባ ላይ ብቻ 150 የታይም ኮፊ ቅርንጫፍ መክፈት ነው፡፡ ከዚያ ኬኒያ፣ ዱባይ፣ ጀርመንና አሜሪካ ታይም ኮፊ ይከፈታል፡፡ የኬኒያውን ፈቃድ አግኝተን ጨርሰናል። የአዋጭነትና የቦታ ጥናት የሚያደርጉ ከፍተኛ ባለሙያዎች አሉን። በዚህ ረገድ ተግተው እየሰሩ ነው፡፡ ከላይ የገለፅኩልሽ የውጪ ሀገራት በሙሉ የኢትዮጵያ ቡናን የሚወዱ ናቸው፡፡
እስኪ ወደ ወርቅ ማውጣቱ ስራ እንምጣ። በ2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት “ታይም ማዕድን”ን በይፋ ጀምረዋል፡፡ ወደዚህ ኢንቨስትመንት የገቡት በቁጭት መሆኑን ሰምቻለሁና ስለለሱ ይንገሩኝ..?
ወርቅ በጣም ከባድ ስራ ነው፡፡ በዚያው ልክ ጥሩ ስራም ነው፡፡ እኔ በህይወቴ የሚፈታተነኝ ስራ ከሌለ ወይም ተግዳሮት ካልገጠመኝ ስራ የሰራሁ አይመስለኝም፡፡ ያንን ተግዳሮት ማለፍ ማሸነፍ ነው ደስታ የሚሰጠኝ፡፡ ሀገራችን እንዳየሽው በዶላር ችግር እንደተሰቃየች አለች። እኔ ውስጤ ያለቅሳል፡፡ መሪዎቻችን ብድርና ልመና ፍለጋ ወደ ውጪ ይሄዳሉ። በዚህ በጣም ውስጤ ያለቅሳል፡፡ የሀገር መሪ ምልክት ነው፤ መከበር አለበት፡፡ መሪን የሚሾመው እግዚአብሄር ነው፡፡ እሱ አመፀኛ ከሆነ ያምፅ እንጂ የሚሾመው እግዚአብሄር ነው፡፡ መሪዎች ሁሉ ለማኝ ሆነው ውጪ ሲሄዱ ሀዘን ይሰብረኛል። የምሬን ነው የምልሽ፡፡ ዋናው ወደ ማዕድን ዘርፍ እንድገባ ያነሳሳኝ ይሄ ቁጭት ነው፡፡ ለምን በዚህ ዘርፍ ገብቼ የራሴን አስተዋፅኦ አላደርግም የሚል ቁጭት፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ከዚህ በፊት ከዚህ ቦታ አንድ ገበታ አፈር አውጥቼ 22 ሺህ ብር ሸጫለሁ። በዳሰሳ፣ የተማረ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ በሌለበት ይህን ያህል ካገኘሁ፣ በተማረ የሰው ሃይል በቴክኖሎጂ ተደግፈን ብንሰራ እዚህ ቦታ ላይ ሊሰራ የሚችለውን ታሪክ አስቢው፡፡ እዚህ ያለንበት አርዳጂላ፣ በኃይለስላሴ ዘመን ነው ስራ የተጀመረው። ያኔ በሰው ሀይል እየተቆፈረ ነበር የሚጠናው። በደርግም በሰው ሀይል ነበር የሚቆፈረው። በኢህአዴግም ብዙ ለውጥ የለም። አሁን የብልፅግና መንግስት መጥቷል። በዛው አይነት መቀጠል የለበትም፡፡ የተማረ የሰው ሀይል አለን፡፡
ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን ሀገራችንን ከዶላር ቆፈን፣ መሪዎቻችንን በሰው ፊት በልመና ከመገረፍ ለምን አናድንም? ደግሞ እንችላለን፡፡ ይሄ ቁጭት ነው ወደ ዘርፉ ያስገባኝ። የወርቅ ማውጣት ስራ እንደሚታሰበው አይደለም፡፡ ኢንቨስትመንቱ 2 ቢሊዮን ዶላር ነው ሲባል የተጋነነ ገንዘብ የሚመስለው አለ። ይሄ ግን ግማሹ ነው፡፡ አይበቃውም፡፡ አንድ የወርቅ ማውጫ ማሽን በ780 ሚሊዮን ብር ገዝተን ከደቡብ አፍሪካ እያስመጣ ን ነው፡፡ አንድ ማሽን ብቻ 780 ሚሊዮን ብር ! እሱም ትልቁ አይደለም፤ ዝቅተኛው ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያያችኋቸው ኤክስካቫተሮች ወርቅ አይደሉም፤ የግንባታ ማሽነሪዎች ናቸው፡፡ የማዕድን ብቻ ተብለው የተሰሩ እያንዳንዳቸው 60 እና 70 ሚሊዮን ብር የሚገዙ ማሽኖች ናቸው፡፡ ስራውን በሙሉ አቅም ስንሰራ 10 ቢሊዮን ዶላር ላይበቃ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የማዕድን ሥራ እጅግ ፈታኝ ነገር ግን ውጤቱ አስደሳች ነው፡፡ ውጤቱ ለሀገር ነው፡፡ ወርቅ አውጥተን ብሄራዊ ባንክ ነው የምናስገባው፤ የሀገር ጥቅም ነው። የእኛ ታይም ማዕድን 25 በመቶውን የወርቅ ፍላጎት ይሸፍናል ብለን እናምናለን፡፡
ሁለተኛው ቁጭቴ አካባቢው ላይ በርካታ ወጣቶች ሥራ የላቸውም፡፡ እነዚህ ልጆች የሚመራቸውና የሚያግዛቸው ነው ያጡት። በሀገራችን ትልቅ ሥራ ሆኖ የተያዘው ለፎቅ ድንጋይ መቆለል ነው፡፡ ይሄ አያዋጣም፡፡ 90 በመቶው ሳይበላ፣ 10 በመቶው የሚበላ ከሆነ የሚቆለሉ ፎቆች ይፈርሳሉ የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ኢንዱስትሪ ማብዛትና ማዕድኖቻችን ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህ ነው እኔም ከወሬ ባለፈ እያንዳንዳቸው ከ80 በላይ አባላት ያሏቸው 77 ማህበራትን አደራጅቼና ሥልጠና ወስደው፣ ከታይም ማዕድን ጋር ወርቅ በማውጣት የጥቅም ተካፋይ እንዲሆኑ ያደረግሁት። ይሄው እናንተ ባላችሁበት ከ6 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እየገቡ ነው፡፡
ሀገራችን ሀብት አላት፤ ወርቅ ላይ ተኝተን ደሀ ነን፡፡ እኛ በዘርና በሀይማኖት ስንናከስ የውጪ ዜጎች በስደተኛ መታወቂያ እየገቡ፣ ወርቅና ማዕድናትን እየተዘረፍን ነው፤ መንቃት አለብን እላለሁ፡፡
የወርቅ ስራ በጀመሩባቸው ቀበሌዎች አራት ቀበሌዎችን የሚያገናኙ 41 ኪ.ሜትር መንገድ ገንብተዋል---
አካባቢው በጣም አስቸጋሪ ነው፤ መንገድ የለም። ህዝቡ ምርቱን ወደ ከተማ አምጥቶ የሚሸጠው በሸክምና በእንስሳት ጉልበት ነው። ድሮ እህል ስነግድ ከአናሶራ ቦሬ ከተማ ድረስ 54 ኪሎ ሜትር በፈረስ ጭኜ እወስድ እንደነበር ነግሬሻለሁ፡፡ ከዚያ በላይ እናቶች በምጥ፣ በሌሎች ህመሞች ህክምና ሳያገኙ ይሞቱ ነበር፡፡ ይህንን በመመልከት 41 ኪሎ ሜትር መንገድ ሰርተናል፡፡ ለዚህ የመንገድ ሥራ 800 ሚሊዮን ብር አውጥተናል፡፡ ይሄ መንገድ አራት ቀበሌዎችን ከዋና ዋና መንገዶች ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡
ነገር ግን ነዋሪው ውስጥ ለውስጥ መንገድ ያስፈልገዋል፤ ገና 380 ኪሎ ሜትር መንገድ የመገንባት እቅድ አለን፡፡ አሁን በተገነባው መንገድ ህዝቡ ያገኘውን እፎይታ ከአንደበቱ ሰምታችኋል፡፡
በህይወት እያሉ በአገርዎ ላይ ሆኖ ማየት የሚፈልጉት ምንድን ነው?
ሀገሬ ባላት ሀብት በልፅጋ ከድህነት ወጥተን፣ መሪዎቻችን ከውጭ ልመና ወጥተው ማየት እፈልጋለሁ፡፡ይህንንም ለማየት በቀን 18 ሰዓት እየሰራሁ ነው፡፡ ይህን ሳላይ ፈጣሪ ከዚህ ምድር እንዳይወስደኝ ፀሎቴ ነው፡፡
አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን (old Wine in a new bottle)
ከእለታት አንድ ቀን ፣ አንድ ክፉ ሚስት የነበረችው ደግ ባልና ሚስቱ በአንድ መንደር ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ሚስቲቱ የፈሰሰ ውሃ የማታቀና ፣ ሁሉንም ነገር ገበሬ ቧላ ከእርሻ ሲመለስ ጠብቃ “ይሄን አድርግ፤ ይሄን አታድርግ” እያለች አልጋዋ ላይ ተጋድማ የምታዝዝ ቅምጥል ነበረች፡፡
ባል ደሞ ሁሉንም እሺ ባይ፣ ገርና ታዛዥ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ የሚያውቅ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ከመጠን በላይ ለዚያ ባል ያዝንለታል፡፡
ከፊሉ ሰው፤
“ምነው እንደ ባል ሁን እንጂ" እያለ ይመክረዋል፡፡ ይገስፀዋል፡፡
ከፊሉ ሰው ደግሞ፤
“እኛንም አሳፈርከን እኮ፤ እንደ ባል ኮስተርተር በል እንጂ" ይለዋል፡፡
አንዳንዱ ደሞ፤
“እሷ ጌታህ አንተ ሎሌዋ ነው የምትመስሉት፤ እንዲህ አገር እስከሚያውቅ እስከሚሳለቅብህ ድረስ ለምን መጫወቻ ትሆናለህ!" ይለዋል፡፡
አክስቱ እማማ ጀማዬ ግን ቀልድ አያውቁም፤
“እረዲያ ወይ ትክክለኛ ባልና ሚስት ሁኑ አልያ ተፋቱ፤ ወለም ዘለም ይብቃችሁ” ይሉታል፡፡
ይሄ ሁሉ ሆኖም ባል አመሉ ሳይቀየር ብዙ አመት ቆዩ፡፡ የፈጣሪ ስራ ታከለበትና ሚስት በጠና ታመመች፡፡ ብዙም ሳትሰነብት ህይወቷ አለፈ፡፡
ምስኪኑ ባል ሚስቱን ቀብሮ ተኮማትሮ እቤት መቀመጥ ሆነ ስራው፡፡ አመታት ካለፉ በኋላ አንድ ቀን የሰፈር አዛውንት ወደ ባል ቤት መጥተው፤
“ልጄ እስከ መቼ እንደዚህ ተኮማትረህ ትችለዋለህ፤ እኛ የሰፈር ሽማግሌዎች መክረን ዘክረን መፅናኛ የምትሆንህ ጨዋ ፀባይ ያላት ሴት ልጅ መርጠን እንድርልሀለን፤ እሺ በልና ሀዘኑንም እርሳው“ ብለው ተማፀኑት፡፡
ይሁን ብሎ ተዋወቃትና አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ይቺኛዋን ሚስት የፊተኛዋን ተቃራኒ ሆና አገኛት፡፡ እጅግ ደስተኛ አደረገችው፡፡ ሸክም ያለበት እንደሆነ እርሻው ቦታ ድረስ ተከትላ ሸክሙን ታግዘዋለች፡፡ ማታ ደክሞት ሲመለስም ውሃ አሙቃ እግሩን አጥባ፣ ጀርባውን በቅባት አሽታ፣ እራቱን አብልታ ታስተኛዋለች፡፡ ጠዋትም ገና ከአልጋው ሳይነሳ ፊቱን አስታጥባ ቁርስ አቅርባ ታጎርሰዋለች፡፡
መቼም የሰው ልጅ ነገር አስገራሚ አይደል ፤ ጠዋት ማለዳ ከእንቅልፉ ነቅቶ ፀሎት ሲያደርስ፤
“አምላኬ ሆይ፤ ያቺን ክፉ ሚስቴን ወስደህ ይቺኛይቱን ስለሰጠኸኝ አመሰግንሀለሁ፤ ጌታዬ የተሻለች የምትመጣ ከሆነ ምነው እቺም በሞተች ” አለ ይባላል፡፡
***
ከእንስሳት ይልቅ በልቶ የማይጠግብ የሰው ልጅ ነው፡፡ እድሜ ልኩን የተሻለ ፍለጋ ሲዳክር ይኖራል፡፡ የሀገራችን ነገር አሳሳቢነቱ የሰው ልጅን ፍላጎት ያህል እንደቀጠለ ነው፡፡ የማይጠግቡ ሰዎች ስላሉን ነው፡፡
ዋና ዋናዎቹንና ተደጋጋሚዎቹን እንነቁጣቸው፡-
አዳዲስ ፓርቲዎች እንደ እጭ ይፈለፈላሉ፤ አዳዲስ መሪዎችም ድንገት ብቅ ይሉና እንደ ድመት ኮርማ ይንጎማለላሉ፤ ዛሬ የተጣሉ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ነገ ይታረቃሉ፤
ወዳጅና ወዳጅ የተጣሉ እንደሆን
መታረቅም እንደ ጥንትም አይሆን
--እንደተባለው ነው፡፡ አንዱ አንዱን አጥፍቶ መጠበቁ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም
ገዴ ዞራ ዞራ በእንቁላሏ ላይ
ጊዜ የሚጠብቅ ሰው ጅል ሊባል ነው ወይ!
በኢኮኖሚውም ረገድ፡-
አሁን ኑሮ ነው ወይ የሸማኔ ኑሮ
ከጉልበቱ በታች መሬት ተቀብሮ
ሲል ይውላል፡፡
አሻግራቸውና ከብቶቹ ሳር ይብሉ
ያ ሳር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ
ምሬት የገባው ለታ ደግሞ
እረ ምረር ምረር ምረር እንደ ቅል
አልመርም ብሎ ነው ዱባ እሚቀቀል
ከዚህ ወዲያ ወደ ጫካ ባሰበ ሰዓት ደሞ
መሳሪያው ሳያብል ጥይቱ ሳያንሰው
እንዴት ልሙት ብሎ እጁን ይሰጣል ሰው
ቀጣዩ የፖለቲካ ጨዋታ ደግሞ የካሮትና የአርጩሜ ነው (carrot and stick) ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንደሚሉት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ስጋታችን የስታሊን በትር እንዳይመጣና እንደገና ቀይ ሽብር እንዳይደገም ነው፡፡ እንደ ዘመኑ አባባል በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል እንዳይባል ነው፡፡ አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን ማለት ይሄው ነው፡፡
መልካም የገና በዓል ይሁንልን!
የበዓል የሙዚቃ ኮንሰርት እየተነቃቃ ነው
ላለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ተዳክሞ የቆየው የበዓላት የሙዚቃ ኮንሰርት መነቃቃት እያሳየ መሆኑ ተነገረ። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ፣ በሸራተን አዲስ ደማቅ የሙዚቃ ኮንሰርት የቀረበ ሲሆን በዚህ ኮንሰርት አንጋፋው ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ ልጅ ሚካኤልና ሄዋን ገብረወልድ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አቅርበውበታል፡፡ በርካቶች የታደሙበት ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት መግቢያው እራትን ጨምሮ 10ሺህ ብር ነበር፡፡ ኮንሰርቱን ከ3ሺ በላይ ሰዎች እንደታደሙት አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
በነገው ዕለት ቅዳሜ የሚከበረውን የገና በዓል አስመልክቶ ዛሬ ምሽት የዋዜማ ኮንሰርት በሚሊኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቷል - በጆርካ ኢቨንትስ፡፡ በዚህ የዋዜማ ኮንሰርት ዝነኞቹ ድምፃውያን ሚካኤል በላይነህና ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ እንዲሁም የኦሮምኛ ዘፈን አቀንቃኙና የኦዳ አዋርድ ተሸላሚው ዮሳን ጌታሁንና ታዋቂው የኤርትራ ድምፃዊ ዳዊት ተ/ሰንበት (ሽላን) የሙዚቃ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ታዋቂ የከተማዋ ዲጄዎች የሙዚቃ ድግሱን ያደምቁታል ተብሏል፡፡
በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ ለመታደም መደበኛው የመግቢያ ዋጋ 300 ብር ሲሆን ቪአይፒው 900 ብር መሆኑንና ትኬቶቹንም በቴሌብር መግዛት እንደሚቻል አዘጋጁ ጆርካ ኢቨንትስ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ነገ ቅዳሜ ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ “የኔ ዜማ” በሚል የመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ፣ ሃይሉ አመርጋና ሌሎችም ድምጻዊያን የሚያቀነቅኑበት የሙዚቃ ድግስ ከኤድናሞል ወረድ ብሎ በሚገኘው “ዘ ክለብ” እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ኮንሰርት ላይ ለመታደም የመግቢያ ዋጋው 2 ሺህ ብር ሲሆን፤ ክፍያው ምግብና መጠጥን ያካትታል ተብሏል። የትኬት ሽያጩ የተጀመረ ሲሆን ትኬቱ የሚገኘው በአዘጋጁ በ “ዘ ክለብ” ውስጥ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የበዓል የሙዚቃ ኮንሰርት መነቃቃት ያሳየው በመዲናዋ ብቻ አይደለም፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው አንጋፋዋ ድምፃዊት ማሪቱ ለገሰ፣ ነገ ቅዳሜ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ ኮንሰርቷን በደሴ ከተማ እንደምታቀርብ ታውቋል። በመቀጠልም በጎንደር ባህርዳርና አዲስ አበባ ከተሞች የሙዚቃ ሥራዎቿን ለአድናቂዎቿ ታቀርባለች ተብሏል።
ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ
“ሟችም የሚሞተው ለዓላማ፤ ገዳይም የሚገድለው ለዓላማ”
ሌንጮ በዳዳ
ለምን ዓላማ እና ለማን ዓላማ ለመሞት ዝግጁ ናችሁ? ለአላማ መሞት አሪፍ ነገር ነው አይደል? አዎ! አሪፍ ነው ለብዙኀኑ፤ .... በግሌ ለኔ ግን አይደለም፡፡
በያዝኩት ነገር ምክንያት ሞት ከመጣብኝ፣ ምላሴን አውጥቼበት ላሽ እላለሁ እንጂ፣ የሞኝ ጀብደኛ ሞት አልሞትም፡፡
በመሰረቱ አላማ የለኝም፣ ቢኖረኝም ሙትልኝ የሚል አይደለም፡፡ እንዲያ ካለማ ጠላቴ እንጂ አላማዬ ስላልሆነ ዶሮ እስኪጮህ ሳልጠብቅ እክደዋለሁ፡፡ ሃይማኖትም ለጊዜው የለኝም፣ ለነገሩ እንዲያው ለጊዜው፣ ለጊዜው ብዬ ልለፈው እንጂ ለዘላቂውም አይኖረኝም፡፡ ሃይማኖትና እምነት ይለያያል አይደል ግን? ….ሀገር አለኝ በእርግጥ፡፡ ለሀገሬ ግን አልሞትላትም፡፡ ብችል እኖርላታለሁ፣ እኖርባታለሁ እንጂ ለምን ስል እሞትላታለሁ፡፡ እሷስ ምን ቆርጧት ሞቴን ትሻለች? አንድ ደረጄ ዓለማየሁ የተባለ የዛ ዘመን ሰው (የመኢሶን አባል የነበረ)፣ በእፎይታ መፅሄት ላይ ለአንድ የሕወሓት ሰው በፃፈው የመልስ ደብዳቤ ውስጥ እንዲህ ይላል፤
“ወንጀሉ የሚጀመረው መግደል ላይ ሳይሆን፣ ለመሞት ዝግጁ መሆን ላይ ነው፡፡ ለቅዱስ ዓላማ መሞት ቅዱስ ይሆንና እርኩስ የተባለን ዓላማ ተከታይ መግደል ወንጀል መሆኑ ይቀራል” ይላል፡፡ ዝቅ ብሎም፤ “እየፎከረ የሚሞት፣ እየዘፈነ ቢገድል ምን ይገርማል?”
ምስለ- ሴጣን የሆነችው ደርግ በዘመኗ ሀገሩን፣ ህይወትን እየተኛ ሞትን እንዲያልም` አድርጋው ነበር … “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!፣ አብዮት ልጆቿን ትበላለች፣ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር፣ አረንጓዴ፣ ቡራቡሬ….. ሽብር… ሞት! … ካካካ ጥይት ዷዷዷ… ጠብመንጃ!
ስንቱ ለሀገሩ ሞተ፣ ስንቱ በሀገሩ ሞተ? ስንቱ ለዓላማው ሲል ስንቱን ገደለ? ስንቱ ዓላማውን እየዘመረ ደረቱን ነፍቶ ወደ መቃብሩ ነጎደ? የስንቱ ዓላማ ትክክል ነበር? ከሞታቸው ሀገራቸው ምን አተረፈች?
በርግጥ ሞታቸውን እያቃለልኩ አይደለም። ከውድ ህይወታቸው አንፃር ግን ሞታቸው የቀለለ ነው፡፡ (ለነገሩ ስለ ህይወት ውድነት እርግጠኛ መሆንም አይቻልም)
መቼም ያ ዘመን፣ ሞት በዓላማ ወለል ላይ የሚደንስበት እየዘፈኑ መሞት የበዛበት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በግለ ታሪክ መፅሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፤...
“ለዓላማችን ነው ብለን የገባንበት የፓለቲካ ዓለም ምን እንደነበርና ከሞት ጋር ስንጫወት የነበረውን የዥዋዥዌ ጨዋታ አስታውሼ በጣም አዘንኩ” (ገፅ 72)
….ብዙ ሰው “ለሃይማኖቴ እሞታለሁ፣ ለሀገሬ እሞታለሁ” ሲል ይገርመኛል፡፡
የሃይማኖት አላማ ህይወትን መስጠት እንጂ ህይወትን ማጥፋት ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው። ሀገር የሚኖሩባት እንጂ ማገዶ የሚሆኑባት ከሆነችም ነገር ተበላሽቷል፡፡ በመሰረቱ ማንም ለማንም አይሞትም፡፡ ማንም ለማንም በመሞቱ ለማንም የተሻለ አለም አያመጣም፡፡ ለሁሉ ነገር እራሳቸውን የመስዋት በግ አድርገው ማቅረብ የሚወዱ ሰዎች የነብሳቸውን ሰንካላነት በሞታቸው ሊያቀኑ የሚሞክሩ ሰነፎች ነው የሚመስሉኝ፡፡
የሚገርመው፣ ሟችም የሚሞተው ለዓላማ፤ ገዳይም የሚገድለው ለዓላማ መሆኑ ነው!
ወዳጄ፣ ዓለም ከምናየው እጅግ የሰፋ ነው። እና በዚህ ሰፊ ዓለም ውስጥ ዓላማ በሚባል ጠባብ በረት ውስጥ የተከረቸምን መጋጃ መሆን አለብን? ... መሆን አለብን ወይ ነው እምለው?
ኧረ ለጠላቴም አልመኝም ... ለነገሩ እኔ ጠላት የለኝም
Moral of the story:- ሁልሽም ውኃ እንዳገኘች እንቁራሪት ትንሽ ነገር (ጠብታ ውኃ) ስታገኝ ትልቅ ነገር የሰራሽ ወይም ያገኘሽ መስሎሽ ከተግባርሽ በላይ ድምፅሽን ስታሰሚ ጠላትሽን በራስሽ ላይ አታንቂ፣ ጠንቀቅ በይ!
_________________________________________________
በእንተ ትግራይ
በእውቀቱ ስዩም
የሚከተለውን ልጥፍ፥ አምና በፈረንጅ አቆጣጠር ፌብሯሪ 28፥ 2021 ጽፌ ያጋራሁት ነው፤ ያኔ ጦርነት የተጧጧፈበት ወቅት የተጻፈ ቢሆንም፥ ዛሬም ትርጉም ይኖረዋል ብዬ በድጋሚ አምጥቸዋለሁ፡፡
ስለትግራይ ሲነሳ ብዙ ይነሳል ፤ እኔ ጭሮ አዳሪ ስለሆንሁ መጀመርያ የማስታውሰው የጽሁፍ ሰዎችን ነው፤ አለቃ ተወልደ መድህን፥ ደብተራ ፍስሀ ወልደጊዮርጊስ፥ ገብረህይወት ባይከዳኝ እና ስብሀት ገብረእግዚአብሄር፥ ከትግራይ ምድር የተሰጡኝ የኢትዮጵያ ገጸበረከቶች ናቸው::
የዛሬ ሶስት መቶ አመት ገደማ የተጻፈ የታሪክ ድርሳን አግኝተህ ብታነብ፥ ትግራይ በእርሻ፥ በቀንድ ከብት እና በሌላው ምርት የበለጸገች እንደነበረች ትረዳለህ:: ከዚያ ያ ሁሉ አዱኛ ምን ሆነ? ጂኦግራፊ እና ታሪክ ከኛ ምርጫ በላይ የሆኑ ነገሮች ናቸው፤ የትግራይ ምድር የኢትዮጵያ ዋናው በር ነው:: የውጭ ወራሪ የወረወረው ሁሉ ቀድሞ እዚህ በር ላይ ይወድቃል፤ በውስጥም የሀያላን መደባደቢያ መድረክ ሆኖ ቆይቷል:: በቴዎድሮስ ዘመን (1861) አገው ንጉሴ የሚባለው ሸፈተና ወደ አክሱም አፈገፈገ፤ ንጉሱ ከሸዋ ተነስተው አክሱም ድረስ ገስግሰው ገጠሙት፤ ከቴዎድሮስ ህልፈት በሁዋላ፥ የላስታው ጎበዜ፥ ተክለጊዮርጊስ ተብለው ነገሱ፤ ካሳ ምርጫ የተባለው ወደረኛቸው አልገዛም አለ፤ አድዋ ላይ ተቀጣጥረው ተፈሳፈሱ፤ ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው አልቆ ተክለጊዮርጊስ ቆስለው ተማረኩ፤ ካሳ ምርጫም” ዮሀንስ አራተኛ” ሆነው ነገሱ::
ዮሀንስ ሞተው አጼ ምኒልክ ሲነግሱ እነ መንጌ አሻፈረኝ አሉ፤ ደሞ በዚያ ዘመን መንጌ ምን ይሰራል ለሚለኝ አንባቢ መንጌ ያልኩት የአጼ ዮሀንስን ወራሽ ራስ መንገሻን ነው፤ አጤ ምኒልክ ወደ ትግራይ ወጡና ውጊያ ገጠሙ፤ ከአመታት በሁዋላ ደግሞ ጣልያን በጀልባ አቆራርጦ መጣና “በራሳችሁ ሜዳ ይዋጣልን” አለ፤ በአምባላጄ በመቀለ እና በአድዋ ጥይት ዘነበ፤ ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን ጀምሮ የነበረውን የጦርነት ታሪክ ብዙ ሰው ስለሚያውቀው ልግደፈው::
ይሄ ሁሉ በአረር ሲለበለብ፥ በመድፍ ሲታረስ የኖረ መሬት ሳር ማብቀሉም ይደንቃል፤ ባጠቃላይ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ፥ በህይወት መቆየትና ወልዶ መሳም በራሱ ቶንቦላ ነው፡፡
ለማንኛውም፥
ለአጥቂዎች የእጃቸውን ይስጣቸው፤ ጌቶችም ስራቸው ያውጣቸው፤ አርሶ ነግዶ፥ ከሞላ ጎደል ቡና እየተጠራራ የመከራና ተድላ ኑሮ እየተጋራ የሚኖር ህዝብ፥ ግፍ ሊፈጸምበት አይገባም::
በቁም ነገር የጀመርኩትን ጽሁፍ በቁጭ-ነገር እንድዘጋው ይፈቀድልኝ፥ ከአሜን ባሻገር “የተባለውን መጽሀፌን ለመጻፍ በየከተሞች ስዞር አድዋን አዲግራትን አክሱምን እና መቀለን ጎበኘሁ፤ አንድ ቀን ወዳጄ መሀመድ ሳልማን መቀለ ዩኒቨርሲቲ ጋብዞኝ፥ ውዬ ሳበቃ ወደ ሆቴሌ የሚመልሰኝን ባጃጅ ተሳፈርሁ፤ “አብርሀ ካስል“ የተባለው ሆቴል ስደርስ ወረድኩና “ሂሳብ ስንት ነው?" አልኩት ባለ ባጃጁን፤
“ዙ ብለህ ደስ ያለህን ስጠኝ” ሲል መለሰልኝ፤ ከዚያ በፊት ሌላ ባጃጅ ያስከፈለኝ አስር ብር ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህኛው ልጅ ትህትና ልቤን ስለነካው፥ መልኩም ኪሮስ አለማየሁን ስለሚመስል፥ ከባንክ የወጣ ትኩስ አምሳ ብር አውጥቼ ሰጠሁት፤ ልጁ እሳት ለብሶ፥ እሳት ተንተርሶ እንዲህ አለኝ፥ “ዋይይይ! ብር ከሌለህ የለኝም አትልም እንዴ?”
__________________________________________________________
የኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የመኪና ሙዚየም
ዋሲሁን ተስፋዬ
ማልደው መነሳትን የለመዱት ከልጅነታቸው ነው፤ በጠዋት ይነሱና የተለመደ ፀሎታቸውን አድርሰው ፡ ከተቋቋመ ከአርባ አመታት በላይ ወዳስቆጠረውና ፡ አራት መቶ ሺህ ዶሮዎች ወዳሉበት ፡ የዶሮ እርባታቸው ፡ ወይም ወደ ትልቁ ሰው ሰራሽ የአሳ እርባታ ጣቢያ ..... ወይ ደግሞ. ... ከሰፋፊ የእርሻ ስፍራቸው መሀከል ወደ አንደኛው ሄደው ፡ ግብርናው እንዴት እየሄደ እንደሆነ ጎብኝተው ፡ በማሳው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ይቆዩና..... በናይጄሪያ ውስጥ አርባ ሰዎች ብቻ በሚነዱት .. ዘመናዊ ሞዴል ሮልስ ሮይስ ፋንቶም መኪናቸው ፡ ወይም በግል ሄሊኮፕተር ....... ካሏቸው ከ18 በላይ ዘመናዊ ቪላዎች ወደ አንዱ ሄደው እረፍት ያደርጋሉ። በነገራችን ላይ እኚህ አዛውንት ከዚህ ፋርም ብቻ በቀን ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ያገኛሉ።
ይህ የቀን ገቢ የዛሬ ሀያ አመት አካባቢ የከፈቱትን እና በየእለቱ 10 ቶን የፓልም ዘይት የሚያመርተውን ግዙፍ ካምፓኒ ገቢን አይጨምርም። በነዚህ እና በሌሎች የገቢ ምንጫቸው በሚያገኙት ፡ ፎርብስ፡ ከአፍሪካውያን ቢሊየነሮች መሀከል መዝግቧቸዋል።
ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ፡ ወይም በሀገሬው አጠራር “ባባ” ....አሁን አሁን ፡ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ፡ የከሰአቱን ጊዜ የሚያሳልፉት ፡ ብዙ ሚሊዮኖችን አውጥተው፡ ከስልጣን ከተሰናበቱ በኋላ በገነቡት እጅግ እጅግ እጅግ በጣም ትልቅ በሆነው ፕሬዝደንሽያል ቤተ-መጻህፍታቸው ውስጥ ነው። ይህ በስማቸው ያሰሩት ግዙፍ ቤተ መጻህፍት ፡ በውስጡ ፡ የስብሰባ ማእከላት ፡ የወጣቶችና የህፃናት መዝናኛዎች. . እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያካተተ ሲሆን በውስጡም 42 ሚሊየን የሚሆኑ መጻህፍትና መዛግብት ተሰባስበውበታል። ( 42 ሚሊየን)
ይህ ትልቅ ቤተ መጻህፍት ካካተታቸው ነገሮች መሃል አንደኛው ፡ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ተሰባስበው ፡ ትዝታቸውን ልምዳቸውን ፡ የሚያወጉበት ፡ ብቸኝነት ሳይሰማቸው ፡ የአዛውንትነት እድሜያቸውን ያለድብርት እንዲያሳልፉ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ክበብ ነው ። ሌላው በዚሁ ላይብረሪ የሚገኘው ደግሞ ፡ የመኪና ሙዚየም ነው። ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ በተለያዩ ጊዜያት ከገዟቸው መኪናዎች ብዛት የተነሳ. .. የመኪና ሙዚየም ለመክፈት ተገደዋል።
በዚህ የመኪና ሙዚየም ውስጥም ፡ ካሉት ስብስቦች መሀከል. . በልጅነታቸው ይነዱት የነበረው ፡ ብስክሌት ፡ የመጀመሪያ መኪናቸው የሆነችው ቮልስዋገን .... የድሮ ሞዴል ፔዦ 504 ን ጨምሮ ፡ ዘመናዊዎቹ ላንድክሩዘር ፕራዶ .... መርሰዲስ S-550 .... ሌክሰስ LX570 ... የተለያየ ሞዴል ያላቸው ሮልስ ሮይስ መኪኖችና ሌሎች ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች እና ሁለት የግል ሄሊኮፕተሮች ይገኙበታል። ከነዚህ ሙዚየም ውስጥ ካሉ ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ፡ በመርሰዲስ እና በሮልስ ሮይስ ኩባንያ ፡ ለኚህ ሰው ተብለው በልዩ ትእዛዝ የተሰሩ ናቸው።
የሰማንያ አምስት አመቱ አዛውንት ፡ .የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ፡ የአሁኑ አደራዳሪያችን ፡ ናይጄሪያዊው ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ላለፉት አርባ አመታት በትላልቅ የግብርና ስራዎች ላይ ተሰማርተው ፡ ሀብት ማፍራት የቻሉ ፡ ሀገራቸውን በቅንነት አገልግለው የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ ፡ ያላንዳች ኮሽታ ስልጣናቸውን በሰላም ያስረከቡ ፡ ከዛም በኋላ በተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎት እየተሰማሩ ያሉ ፡ ከባለፈው አመት ጀምሮ ደግሞ ፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ እስከዛሬዋ እለት ድረስ የዘለቁ ሰው ናቸው።
________________________________________________
ከቅዠት ወደ መራራ ሀቅ
ሙሼ ሰሙ
ሁለት ዓመት ከፈጀ እጅግ አሰቃቂና ከፍተኛ ዋጋ ካስከፈለ አውዳሚ የቀቢጸ ተስፋ ጦርነት በኋላ በማን አህሎኝነት ተወጥሮ ማብቂያ በሌለው የጦርነት አዙሪት ውስጥ በመዳከር ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍና ንብረት ከማውደው በስተቀር አንዳችም ትርፍ እንደማይኖረው መረዳት ከቻልክ፣ በሕዝብ ላይ ተስፋ የሚያጭርን የሰላም በር የማንኳኳት እድል እንዳለህ የመቀሌውን ጉዞና ሂደቱን ለታዘበው ትልቅ ትምህርት ነው።
መነሻው ከየትኛውም ወገን መንጭቶ ወይም አንዳንዶች እንደሚገምቱት በሃያላን መንግስታት ተጽእኖ የተተገበረ ሊሆን ይችላል። ተወደደም ተጠላ የሰላም ድርድሩ፣ የመቀሌው ጉዞና በመቀሌ ከተማ የተደረገላቸው አቀባበል ለድምዳሜ እንጭጭ ቢሆንም ውጤቱ ያልተጠበቀና እያደገ ሊሄድ የሚችል አስደማሚ ክስተት መሆኑ አያጠራጥርም ።
የተንጸባረቀው የይቅር ባይነት መንፈስም ለሀገሬና ለሕዝቤ ደህንነትና ሰላም እቆረቆራለሁ የሚል ዜጋ ላይ ሁላ መጋባት የሚችልና መጋባት ያለበት ዘመን ተሻጋሪ ውሳኔ ከመሆኑም በላይ ጦር ሰባቂነትና ሟርተኝነትም ሰላም በመሻት ሊሟሽሹ የሚችሉ ስለመሆናቸው ፍንጭ የሰጠ ሂደት ነው።
በእርግጥ የጦርነቱ ሰበብም ሆነ መዘዘኞቹ ፖለቲከኞች እንጂ ሕዝቦች አልነበሩም፣ ወደፊትም ሊሆኑ አይችሉም። ዛሬ ላይ ፖለቲከኞቹ ስለታረቁ የጦርነቱ ታሪክና የቀውሱ ምዕራፍ አይዘጉም።
በፖለቲከኞች ሰበብና ቆስቋሽነት ወደ ጦርነት የተማገደና ለእርስ በእርስ ጥላቻ የተዳረገ ሕዝብ ሞልቶ ስለተረፈ በፖለቲከኞች የተጀመረው ሰላምና ይቅር ባይነት ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አድጎና ጎልብቶ ማየት ያስፈልጋል። ከገጠመን ሀገራዊ ቀውስ ለመሻርም ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ህዝብም መፈወስ መቻል አለበት።
ጦርነት ከሚፈጥረው ሰብአዊ ቀውስ፣ ከሚያደርሰው ቁሳዊ ውድመትና ከሚፈጥርብህ የማይጨበጥ የአሸናፊነት ቅዠት በኋላ ምኞትህ አለመሳካቱን ስትረዳ የምትማረው መራራ ሀቅ ቢኖር፣ ጦርነት በደረሰበት ላለመድረስ በፍርሃት በመሸሽ፣ የትኛውንም ዓይነት ግለሰባዊ ክብርህን ተራምደህ ሰላምን መናፈቅና እርቅን መሻት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውም ይኸው ነበር። ከቅዠት ወደ መራራ ሀቅ መሸጋገር።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ነገር፣ አምላካችን በከንቱ ጦርነት የሞቱ ወገኖቻችንን ነፍስ በገነት ይቀበል። በስነልቦና ለተጎዱትንና በማህበራዊ ቀውስ ለተመቱ፣ ሀብት ንብረታቸውን ላጡት ወገኖች መጽናኛን ይላክ። የሰላም ጅማሮውንም በጸና መሰረት ላይ ያቁምልን። አሜን።
ከሸንኮራ ንግድ እስከ ቢሊዮኖች ዶላር ኢንቨስትመንት
የ32 ኩባንያዎች ባለቤትና የ3 ሺ ሰራተኞች አስተዳዳሪ ሆነዋል
በኦሮሚያ ክልል ቦሬ ወረዳ፣ ኮቲኮ ቀበሌ፣ በ1964 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ አርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አባታቸው ከአራት ሚስቶቻቸው ከወለዷቸው 44 ልጆች 39ኛ ልጅ ናቸው፡፡ በቦሬ ከተማ በካቶሊክ ሚሽነሪዎች በተከፈተው “ጎሳ” የተሰኘ ት/ቤት ለመማር ከአባታቸው እርሻ ላይ ቃርሚያ እየለቀሙና ደብተር እየገዙ ለሰባት ዓመታት ትምህርት ቢጀምሩም፣ አባታቸው ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ እያደረጉ ወደ ከብት እረኝነት ስለመለሷቸው የመማር እድል ሳያገኙ እስከ 13 ዓመት እድሜያቸው በከብት እረኝነትና ቤተሰብን በማገልገል ቆይተዋል፡፡
የትምህርት እድል እንደማያገኙ ያወቁት የዛኔው ታዳጊ የአሁኑ ጎልማሳ ከመኖሪያ ቀያቸው ጠፍተው በቦሬ ከተማ የሸንኮራ አገዳ ንግድ ቢጀምሩም፣ አባታቸው በታላላቅ ልጆቻቸው አሳድደው ወደ ቤታቸው መልሰዋቸዋል፡፡ ሆኖም እምቢተኛውና አልበገር ባዩ ታዳጊ ድጋሚ ጠፍተው ወደ ሸንኮራ ንግዳቸው ተመልሰው መሥራት ጀመሩ - የዛሬው እንግዳችን ዝምተኛው ጀግና አቶ መኩሪያ ባሳዬ፡፡ ከዚያስ? አሁን የ32 ኩባንያዎች ባለቤትና የ3 ሺ ሰራተኞች አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ እንዴት? መልሱን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በጉጂ ዞን የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሥራቸውን ባስጀመሩበት አናሶራ ወረዳ ተገኝታ ካደረገችው አስደማሚ ቃለምልልስ ታገኙታላችሁ፡፡ እነሆ፡-
እንዴት ግን የሸንኮራ ንግድ ጀመሩ ማለቴ ለምን መረጡት? ከየትስ ወዴት እየወሰዱ ነበር የሚሸጡት?
ከፍተኛ የመማር ፍላጎት ነበረኝ፡፡ አባቴ ደግሞ ፍላጎቱ ከብት እንድጠብቅ ስለነበር፣ ሰባት ዓመት ሙሉ ትምህርት እየጀመርኩ አቋርጬ ወደ ከብት እረኝነት እንድመለስ አደረገኝ፡፡ ለመማር ካለኝ ጉጉት የተነሳ ከአባቴ እርሻ ላይ ቃርሚያ ለቅሜ እህል ሸጬ ነበር ደብተር የምገዛው፡፡ ይህ ሁሉ ፍላጎቴ መና ሲቀር ከቤቴ ጠፍቼ ቦሬ ከተማ ሄጄ ሸንኮራ መነገድ ጀመርኩ:: ይሁን እንጂ አባቴ በወንድሞቼ አሳድዶ ይዞ መለሰኝ፡፡ አሁንም ጠፍቼ ወጣሁ። በወቅቱ እናቴ ከሌሎቹ ልጆቿ በጣም ትወደኝ ስለነበር፣ አባቴን “ይሄ ልጅ እራቅ ወዳለ ቦታ ጠፍቶ ሄዶ ይሞትብኛል፤ እባክህ ተወው ይነግድ ትምህርትም ስራም ከልክለነዋል፤ እዚህ አይቀመጥም” በማለት ለመነችልኝ፤ አባቴም በቃ ተወኝ፡፡ እንደፈለግህ ሁን አለኝ፡፡
እናቴ ከሌሎች ልጆች በተለየ መልኩ ትወደኝ ነበር ብለውኛል፡፡ ለምን ነበር ከሌሎቹ የበለጠ የሚወዱዎት?
እናቴ እኔን በተለየ የምትወድበት ብዙ ምክንያት አላት፡፡ አንደኛ፤ የኔ ታላቅ ሞቶባት በመሪር ሀዘን ውስጥ ነበረች፡፡ ሁሌ ከቤት እየወጣች ስታለቅስ ስታዝን እየዋለች ትመለስ ነበር፡፡ አንድ ቀን በህልሟ “ሀዘን አቁሚ ወንድ ልጅ እሰጥሻለሁ፤ መኩሪያና መከታ የሆነ ልጅ ነው የምሰጥሽ” የሚል ህልም አይታ እንደነበር ነግራኛለች፡፡ አምላክ እኔን ለመካስ የሰጠኝ ልጅ ነው ብላ ስለምታምን ነው በተለየ መልኩ የምትወደኝ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት እኔ ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ ለ3 ወራት ሙሉ አልተኛችም፡፡ ምክንያቱም በጣም የማለቅስ የምረብሽ ልጅ ነበርኩ፡፡ ከፍ እያልኩ ስሄድም አስቸጋሪ ነበርኩኝ፡፡ እናቴ ሁለት ሞግዚት ተጨምሮላትም አልቻሉኝም ነበር፡፡ አባቴ እንዲያውም “ይሄ ልጅ በግ ቢሆን አርጄው እገላገል ነበር” ብሎ እስኪማረር ድረስ ነበር የማስቸግረው፡፡ በዚህ እናቴ ለእኔ መስዋዕትነት ከፍላለችና ትወደኛለች፡፡
አባትዎ ሀብት ነበራቸው?
አዎ፤ እኔ ከብት እረኝነት በጀመርኩበት ጊዜ በትንሹ ወደ አራት ሺህ ከብትና 14 ጋሻ መሬት ነበረው፡፡ ይህ 14 ጋሻ መሬት ግማሹ በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ግማሹ የከብት ማሰማሪያ፣ የግጦሽ ቦታ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ ብቻ እኔን ወደ መጥፋትና ወደ ሸንኮራ ንግድ ያስገባኝ ችግር ሳይሆን ትምህርት መከልከሌ ነበር፡፡ ንግዱን ሲከለክለኝ እናቴ ከላይ በገለፅኩልሽ መልኩ አስፈቀደችልኝና ቀጠልኩ ማለት ነው፡፡
መቼ ነበር የሸንኮራ ንግድ የጀመሩት?
በ1979 ዓ.ም ነው የጀመርኩት፡፡ ሸንኮራውን እኔ ከተወለድኩበት 14 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሱኬ ከሚባል ቦታ ገዝቼ፣ ቦሬ ከተማ ሌላ 16 ኪ.ሜ በድምሩ 30 ኪሎ ሜትር በእግሬ እየተመላለስኩ ነበር የምሸጠው፡፡ ሆኖም የሸንኮራ ንግዱ አላዋጣ አለኝና ወደ ጨው ንግድ ገባሁ፡፡ ያን ጊዜ ከተማ ውስጥ ጨው የሚነግዱ ትልልቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አሸናፊ ደርሰህ የሚባል ሰው የ10 ብር ጨው ያበድረኛል፡፡ እሱን እየቸረቸርኩ 20 ሳንቲም ሳተርፍ፣ ያን ጊዜ “ገፉማ” የሚባል ምግብ ነበር። በአምስት ሳንቲም ገፉማ በልቼ 15 ሳንቲም እቆጥባለሁ፡፡ ያላተረፍኩ ቀን ወይም 10 ሳንቲም ብቻ ያተረፍኩ ቀን ከዚህ ላይ ገፉማ ከበላሁ የምቆጥበው ያንሳል በማለት ሳልበላ በእግሬ ወደ ቤት እሄድ ነበር፡፡ በዚህ አይነት እኔን እያዩ የሰፈሬ ልጆች ከኔ ጋር ንግድ ጀመሩ፡፡ ከነዚህ መካከል ነፍሱን ይማረውና ገዳቾ የሚባል ጓደኛዬ፣ ካሳ የሚባል ታላቅ ወንድሜና በቀለ የሚባል የወንድሜ ልጅ ሆነን መነገድ ቀጠልን። ብቻ የእኔን ፈለግ እየተከተሉ በጨው ንግድ 8 ደረስን፡፡
በዚያን ጊዜ ትልቁ ችግራችን ቋንቋ ነበር። እኛ ከገጠር ወደ ከተማ ስንመጣ አማርኛ አንችልም። እሱ ትንሽ ተፅዕኖ ቢፈጥርብንም ከከተማ ልጆች ጋር ጓደኝነት መሰረትን፡፡ ከእነዚህ ጓደኞቻችን ከድር መሃመድ የሚባል የጉራጌ ልጅ ተቀብሎ ከተማ አለማመደን፡፡ አሁን ወልቂጤ ነው ያለው፡፡ ሌላው ሲዳማ ውስጥ ማንም ንግድ ሳይጀምር ነጋዴ የነበሩት፣ በአሁኑ ወቅት ባለቤቴ የሆነችው የትዳር አጋሬ አባት ሲነግዱ እያየን እየተበረታታን ቀጠልን፡፡ እኔ በቀላሉ ከሰው ጋር የመግባባት ተሰጥኦ አለኝ፡፡ በዚህ አይነት ከከተማው ሰው ጋር መግባባቴን ቀጠልኩ፤ ሰውም እየወደደኝ መጣ ማለት ነው። ጨው እየነገድኩ ያጠራቀምኩት ካፒታሌ 25 ብር ሲደርስ ወደ እህል ንግድ ገባሁ፡፡ የእህል ንግድ እናንተ ካያችሁት ከአናሶራ ወረዳ ከቲቻ ቀበሌና ጎንቢሶ ቀበሌ እየገዛሁ፣ 54 ኪሎ ሜትር ድረስ በመምጣት ቦሬ ከተማ ነበር የምሸጠው፡፡ ያን ጊዜ ፈረስም ሰውም እከራያለሁ፡፡
ፈረስ የሚከራዩት መቼስ ለእህል መጫኛ ነው፤ ሰው የሚከራዩት ለምንድን ነው?
የሚገርምሽ በወቅቱ ቁመቴ ፈረስ ላይ እህል ለመጫን ስለማልደርስ ነበር ሰው እየተከራየሁ የማስጭነው፡፡ እህሉ በአግባቡና ሚዛኑን ጠብቆ ካልተጫነ ሩቅ መንገድ ስለሚጓዝ በጣም ያስቸግራል፡፡ እና በዚህ አይነት ከጠቀስኩልሽ ቀበሌዎች እህል ወደ ቦሬ እየጫንኩ ስነግድ ከቆየሁ በኋላ በ1980 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከቦሬ ከተማ ከእኛ እየገዙ ወደ አለታ ወንዶና ወደ ነገሌ ቦረና ሲሸጡ አስተዋልኩ፡፡ አሃ እኔም በቀጥታ ወደ አለታ ወንዶና ወደ ነጌሌ መጫን እችላለሁ አልኩና፣ ሳልፈራ በድፍረት ወደዚያ ስራ ገባሁ፡፡ ይህንን ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመስራት ስድስት ፈረስ እህል ጭኜ ወደ ከተማ ስገባ፣ አንድ ሰብስቤ የሚባሉ ትልቅ ነጋዴ አዩና “በቃ እኔ ነኝ የምገዛው” አሉና እዚህ አስገባ አሉኝ፡፡ “አይ ጋሼ ራሴ ነጌሌ ልጭን ነው” ስላቸው፤ “አንተ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ነገሌ የምትጭነው” ብለው በጥፊ መቱኝ፡፡ በግራ ፊቴ በኩል በሀይል በጥፊ ሲመቱኝ በቀኝ ጆሮዬ ደም ፈሰሰ፡፡ እንዴት ለእኛ ሳታስረክብ ቀጥታ ለነገሌ ነጋዴ ታስረክባለህ፣ ብለው ነው የመቱኝ። መምታት ብቻ አይደለም፤ እህሌን ከነፈረሶቼ ቀሙኝ፡፡ እየሮጥኩ ፖሊስ ጣቢያ ሄድኩኝ፤ ደም በደም ሆኜ ፖሊስ ጣቢያ ስደርስ ሃምሳ አለቃ ክብረት የሚባሉ የጣቢያው ፖሊስ አዩኝና፤ “ማነው የመታህ?” አሉኝ፡፡ የተፈጠረውን ነገርኳቸው፡፡ በጣም ተናድደው፣ ሁለት ፖሊስ አስከትለው መጥተው፣ የመታኝ ሰው ጋ ሲደርሱ አቶ ሰብስቤ ነው፡፡ ይህ ነጋዴ በወቅቱ በአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ ስለነበር “ኦ ሰብስቤ አንተ ነህ እንዴ የመታኸው? ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ?” ብለው ብቻ ዳኝነትም ሳይሰጡኝ ተመልሰው ሄዱ፡፡ እኒህ ሰው የመቱኝ ለአስራ ምናምን ዓመት የጆሮ ታማሚ አድርጎኝ ነበር፡፡ እህሌን እንደምንም ከሰብስቤ አስመልሼ በአንድ ጥፊማ አልቆምም ብዬ ወደ ነገሌ ጫንኩኝ፡፡ ከነገሌ ወደ መጨረሻዋ የኢትዮጵያ ድንበር ወደ ዶሎ መጫን ጀመርኩኝ፡፡ ወደ ሱፍቱ ከተማና ማንኢራ ወደሚባል የኬንያ ከተማም መጫን ጀመርኩኝ፡፡ ከዚህ እህል ጭኜ ሸጬ ከዚያ ደግሞ የቆራሊዮ እቃ ይዤ እመጣለሁ፡፡ በዚህ ስራ ላይ እያለሁ በ1982 አጋማሽ ላይ ደግሞ አናሶራ ወረዳና ቦሬ ወረዳ የወርቅ ማዕድን ተገኘ ተባለ፡፡ ከዚያ በባህላዊ መንገድ ወርቅ ማውጣት ጀመርኩ፡፡ አንድ ጉድጓድ 3 ሜትር ወደ ታች ለመቆፈር ሰባት ቀን ፈጀብኝ፡፡ ልጅነትም ልፋትም ስላለ አቅም የለኝም፡፡ ልክ ቆፍሬ ወርቁ ጋ ስደርስ አሸዋው በሙሉ ወርቅ ነው፡፡ ባቢቾ ቀበሌ ልጁ ወርቅ ሲያጥብበት የነበረው ባቲያ የሚባለው ገበቴ ላይ አሸዋውን አፍሼ ሳጣራው ግማሹ ወርቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያኔ ግራሙ 40 እና 50 ብር ነበር፡፡ አወጣሁና 22 ሺህ ብር ሸጥኩት፡፡
የወርቅ ስራ ቀደም ብለው ነዋ የጀመሩት?
አዎ! ያኔ አንድ እያሱ የሚባል የደርግ ሊቀ መንበር ነበር ጉድጓዴን ቀምቶ ደብድቦ ያባረረኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ቢያንስ ከዚያ ጉድጓድ የ1 ሚሊዮን ብር ወርቅ ወጥቷል፡፡ ምን መሰለሽ? አባቴ ከአራት ሚስቶች 44 ልጅ ወልዷል፡፡ የእኔ እናት ብቻ 15 ልጆች ወልዳለች፤ የኔ ታላቅ ሲሞት 14 ልጆች ነበርን፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ብዙ ነን፡፡ ምግብ ሲቀርብልን ምግቤን ሲጋፉኝና ሲወስዱብኝ ለምን ወሰዳችሁብኝ ብዬ አልጣላም፤ ጥዬ ነው የምሄደው፡፡ ጉድጓዴን ደብድበው ሲቀሙኝ ጥዬ ሄድኩና በዚያ ብር እዚያው የወርቅ ንግድ ጀመርኩኝ፡፡ ያኔ ዘመናዊ የወርቅ ሚዛን ስላልነበር በዚህም በዚያም በኩል ቆርኪ አስረን ነበር የምንመዝነውና የምንገበያየው፡፡ የቆርኪው ሚዛን ሳይሳካ ሲቀር ሰፊ አፍንጫ ያለው ሰው እንፈልግና ለሰውየው የልኬት እንከፍላለን፡፡ ከዚያም በሰውየው አፍንጫ እንለካለን፡፡
እስኪ በሰፊ አፍንጫ ለክታችሁ እንዴት እንደምትገበያዩ በደንብ ያብራሩልኝ?
እንዴት መሰለሽ -- ያ ሰፊ አፍንጫ ያለው ሰው ይፈለግና ወርቅ ቋጥረን በሰፊው አፍንጫው ስንከተው ከገባ ይህን ያህል ብር ነው እንላለን፡፡ በሰፊው አፍንጫ ካልገባ አይ ይሄ ወርቅ ትልቅ ነው ብለን ዋጋ ጨምረን እንናገራለን፡፡ ያው ከሚዛኑ አፍንጫ ይቀድማል፡፡ እስከ መቼ በሰው አፍንጫ እንገበያያለን፤ ለምንስ ሌላ መፍትሄ አልፈልግም ብለን ሚዛን መስራት ጀመርን። ሚዛኑ ተሳካልን፡፡ እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ሁሉም ሰው በዚያ ሚዛን ነበር የሚገለገለው። ከዚያ ኢህአዴግ ሲገባ እኔ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ነበረኝ፡፡ የጦፍኩ ነጋዴ ሆንኩኝ፡፡ ኬንያ እሄዳለሁ፤ አዲስ አበባ እሄዳለሁ፤ እነግዳለሁ። በነገራችን ላይ አፍሪካ ወርቅ ቤትን እኛ ነን ያሳደግነው፡፡
የፒያሳውን?
አዎ የፒያሳውን አፍሪካ ወርቅ ቤት ነው የምልሽ፡፡ ሌላ ደግሞ ገብረ ህይወት የሚባሉ ባለወርቅ ቤት፣ በጣም ታማኝ ትግሬ ሰውዬ ነበሩ፡፡ አሁን ይኑሩ አይኑሩ አላወቅሁም። በጣም ታማኝ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ወርቅ ቤቶች ይሰርቁን ነበር፡፡ እሳቸው ግን በታማኝነት ከእኛ ይረከቡና 25 ሳንቲም አትርፈው የእኛን ብር ይመልሱልናል፡፡ በዚህ አይነት ከእሳቸው ጋር መስራት ጀመርን፡፡ ከዚያም ትልቅ ነጋዴ እየሆንኩ መጣሁ፡፡ በ1987 ዓ.ም ሚስት ማግባት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
ሚስትዎን ጠልፈው ነው ያገቧት የሚባለው እውነት ነው እንዴ?
ምን መሰለሽ --- ጠለፋ ነው አይደለም የሚለውን ለመፈረጅ እንዲመች በመጀመሪያ ሁኔታውን ልንገርሽ፡፡ የልጅቷ አባት ያኔ በሲዳማ ነጋዴ ሳይኖር ይነግዱ የነበሩ ትልቅ ባለሀብት ናቸው፡፡ ዮሃንስ ኦታቻ ይባላሉ፡፡ የኒህ ሰው ልጅ በጣም ቆንጆና በጣም ጎበዝ ተማሪ አለች፡፡ እሷን ካላገባሁ ስል “አይ አይሆንም” ተባለ፡፡ ለምን? እኔ ተራ የገበሬ ልጅ ነኝ፤ እሷ ደግሞ የሚሊየነር ልጅ ናት፡፡ እንዴት ይሆናል ሲባል፣ “እንዴት አይሆንም፤ እኔ እንዴት ከሰው አንሳለሁ?” አልኩኝ፡፡ ዋናው ነገር ልጅቷ እኔን በጣም ነው የምትወደኝ፣ እኔም እወዳታለሁ፡፡ ከዚያ ጠልፌ ወሰድኳት፡፡
በዚያን ጊዜ ሴትን መጥለፍ አያስከስስም ነበር እንዴ?
በእኛ ጊዜ አያስከስስም፤ ጉዳዩን የሚፈታው የአገር ሽማግሌ ነው፡፡ በወቅቱ የአገር ሽማግሌ ተሰብስቦ የልጅቷ አባት ጋ ሄዱ፡፡ “እንዴት የድሃ ልጅ ያልተማረ ሰው ልጄን ያገባል፤ እራሴን አጠፋለሁ” ብለው በአንድ ክፍል ውስጥ ገብተው ቆልፈው እምቢ አሉ፡፡ የመንግስት ሹማምንት ቢሄዱ የአገር ሽማግሌዎች ቢለምኑ አባትየው አሻፈረኝ አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የመካነ ኢየሱስ ቄስ የሆኑ ቄስ ዮሃንስ የሚባሉ ጓደኛ አሏቸውና እሳቸው ተጠርተው መጡና ተቆጧቸው፡፡ “ምን ማለትህ ነው ልጅህን አንተ አታገባም፤ ለወንድሞቿ አታጋባም ስለዚህ ተው” ብለው ተቆጡ፡፡ “እኔ ካናዳ ልኬ ላስተምራት ፕሮሰስ ጨርሻለሁ” ብለው ተቆጡ። ነገሩ እየተጋጋለ ሲሄድ “ለማንኛውም የልጅቷ ፍላጎት ይታወቅ፤ ካልወደደችው በግድ አፍኖ ሊያኖራት ስለማይችል እንመልሳታለን” አሉ፤ የኔ ጎሳዎች። ከዚያ በኋላ አንድ የእሷ አጎትና ሌሎች ሽማግሌዎች ተመርጠው ተላኩና እሷን ጠየቋት። “እኔ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ አግብቻለሁ ደግሞ እወደዋለሁ፤ ወደ ቤት መመለስ አልፈልግም። ለአባቴ ንገሩት፤ በጣም እንደሚወደኝ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በቃ ከምወደው ሰው ጋር ነው ያለሁት” የሚል ምላሽ ሰጠች፡፡ አባቷ ሰሙና “በቃ በትክክል ልጄ እንደዚህ አለች?” ብለው ጠየቁ፡፡ ሽማግሌዎቹ ይህንኑ አረጋገጡላቸው፡፡ ነገሩ እዚህ ላይ አበቃ፡፡
ከዚህ በኋላ በአጋጣሚ በሲዳማና በጉጂ መካከል ግጭት ተነሳ፡፡ በዚህ ግጭት አባቷ ወደ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ተዘረፉ። እነሱንም ለመጨረስ ቀለበት ውስጥ አስገቧቸው፡፡ ይህ ሲሆን ከአባቷ ጋር ገና አልታረቅንም፤ አልተገናኘንም፡፡ በወቅቱ እግዚአብሔር ከኔ ጋር ሆኖ ቦሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 560 የሲዳማ ሰዎችን ሰብስቤ ቤት አምጥቼ አዳኗቸው፡፡ በአካባቢዬ እኔም የትልቅ ቤተሰብ ልጅ ነኝ፡፡ አባቴ የተከበሩና ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ እንደነገርኩሽ ከአራት ሚስቶች 44 ልጆች የወለዱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በውጭ የተወለደ ልጅ በአካባቢው ባህል አይቆጠርም እንጂ ቢቆጠር ወደ መቶ ሳንጠጋ አንቀርም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንድ የሀዋርያት ቤተክርስቲያን መሪ “እኔ የእናንተ ወንድም ነኝ፤ አባታችሁ መቶ በመቶ የራሴ ልጅ ነህ ብሎኛል” ብሎ መጣ፡፡ እውነትም ይህ ሰው መቶ በመቶ አባቴን ነው የሚመስለው፡፡ እንደሱ በውጪ ያሉ ልጆች ሳይቆጠሩ እኛ 44 ነን፡፡ አባቴ ሲሞቱ የስጋ ዝምድና ያለን ብቻ ከ 3ሺህ በላይ ሰው ነው ለቅሶ ላይ የወጣው፡፡ ወደ ዋናው ስመለስ በአካባቢው ቤተሰቤ የተከበረ ስለሆነ፣ እነዛን 560 ሲዳማዎች ቤቴ ድረስ መጥተው ሊያጠቋቸው አልቻሉምና እኔ በሰላም ወደ ሲዳማ አሻገርኳቸው። እግዚአብሄር መቼም ሁሉንም ለበጎ ነው የሚያደርገው፡፡
(ይቀጥላል)
ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ
ከዕለታት አንድ ቀን፣ እመት ጦጢት፣ ከዛፍ ዛፍ እየዘለለች ፍሬ ትለቅም ነበር፡፡
አያ ገበሬ ደግሞ ወደ እርሻ ሄዶ ዘር ዘርቶ መመለሱ ነው፡፡
“እመት ጦጢት እንደምንድነሽ?“ አላት፡፡
“ደህና ነኝ፤ አንተስ እንደምንድ ነህ?“ ጦጢት አፀፋውን መለሰች፡፡
“እኔም በጣም ደህና ነኝ፡፡”
“ሥራ እንዴት ነው?” አለችው፡፡
“ምንም አይልም፡፡ ዝናቡ ብቻ ለዘር አልተመቸኝም”
ጦጢት አሁን ወደ ጉዳዩዋ ገባች፡፡
“ለመሆኑ ዘንድሮ ምን ዘራህ?”
ይሄ ገበሬ በትክክል የዘራውን ቢነግራት እርሻው ውስጥ ልትቦጠቡጥበት ነው፡፡ ስለዚህ የዘራውን ትቶ ለጦጢት የማይመቻትን ነው መጥራት ያለበት፡፡
“እመት ጦጢት ዘንድሮስ ተልባ ነው የዘራሁት” አላት፡፡
ጦጢትም፤
“ይሁን እስቲ ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
እመት ጦጢት ሌሊቱን ስትቦጠቡጥለት አደረች፡፡
ገበሬ ተናዶ ሲያሳድዳት ከረመ፡፡
ጦጢት ነቅታ ኖሯልና ደብዛዋን አጠፋች፡፡
ብልጥ ለብልጥ ዐይነ-ብልጥጥ ይሏል ይሄው ነው!
***
ነገርን መሬት ወርዶ ማየት ብልህነት ነው!
መሬት ሳይወርዱ ሁሌ ወንበር ላይ መቀመጥ አያዋጣም፡፡ ምናልባትም አንዳንዴ የማይቻል ነገር ነው! ሥልጣን ብዙውን ጊዜ ይሞቀናል ተብሎ ቢታሰብም አንዳንዴ ብርድ ብርድ ይላል፡፡ ያንቀጠቅጣል፡፡ አፍና ቅብቅብ ሁልጊዜ አንበላም ይባላል፡፡ አያሌ ሰዎች በንግግር ጥበብ ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ሚዲያን የሙጥኝ ሲሉ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም የምላሥ ወለምታ በቅቤ አይታሽም የሚለውን ተረት ልብ ቢሉ መልካም ነወ፡፡
ለረዥም ዓመታት በመንግስት ዙሪያ የሚሰገሰጉና በሽር-ብር የሚኖሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ከትናንትና ፖለቲከኞች አወዳደቅ አይማሩም፡፡ ምክንያቱም አድር-ባይነትን እንደ ሙያ ይዘውታል፡፡ ያለ ፍሬንና ፍሬቻ መጓዝን አደገኛነት አይሰጉበትም፡፡ ቁልቁለትና ዳገት አይመርጡም፡፡ ትላንት የሰራውን ሰው “እሰይ!” ይሉታል እንጂ ነግ በኔ አይሉም፡፡ ምክር አይሰሙም፡፡ ሁሉን እንደ ምቀኛ ይቆጥራሉ፡፡ ሲቀናቸው ለሰርገኛው ሁሉ አንደኛ ሚዜ ናቸው፡፡
ሆኖም ሁኔታዎች ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ የዕድገትና የለውጥ ህግ ያለ፣ የነበረ የሚኖር ነው፡፡ መለወጡን ማወቅና ሁሌ ለለውጥ መዘጋጀት ፣ በተለይ በመሪዎች ዘንድ ታላቅ ግዴታ ነው! አመራሮች እንደነበሩ እንደማይቆዩ፣ ሕዝብ ለውጥን መሻቱ አይቀሬ ነው፡፡
ይህን ደጋግመን ብለናል፡፡ ዛሬም እንላለን! በዚህ ረገድ ምሁራን ያላቸው ሚና በርካታ ነው፡፡ በየደረጃው የወረዳው፣ የቀበሌውና የቀጠናው ዘርፎች ሁሉ ዓላማቸውን አውቀውና ተረድተው መጓዝ አለባቸው፡፡ ያልተቀናጀ ትግል የትም አያደርስም፡፡
ከሁሉም በላይ አጥፊያችን መናናቅ ነው! ንቀት አገር ያደቅቃል፡፡ ኢኮኖሚን ይገድላል!
“ባለቤቱን ካልናቁ
አጥሩን አይነቅንቁ”
የምንለው ለዚህ ነው፡፡
ወደ አምባገነንነት ማምራት የሚመጣውም እንዲህ እያለ ነውና - እንጠንቀቅ!
የወንድ መሀንነት፡፡
በአለምአቀፍ ደረጃ 48 ሚሊዮን ጥንዶች እንዲሁም 186 ሚሊዮን ሰዎች ልጅ ያለመውለድ ችግር (መሀንነት) አለባቸው። ችግሩ 50% በወንዶች እንዲሁም 50% በሴቶች ላይ ባሉ ተፈጥሯዊ ወይም ከጊዜ በኋላ በመጡ እክሎች አማካኝነት የሚከሰት ነው። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ “ልጅ ያለመውለድ ችግር[መሀንነት] መከሰቱን በህክምና ማረጋገጥ(መመርመር) የሚያስፈልገው ጥንዶች ለ1 አመት ያህል የግብረ ስጋ ግንኙነት እየፈጸሙ እርግዝና ካልተፈጠረ ነው” ብለዋል። የመሀንነት ችግር ካልተከሰተ 85 % በሚሆኑት ጥንዶች ላይ በ1 አመት ውስጥ እርግዝና ይፈጠራል። ነገር ግን የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት የሴቷ እድሜ ከ35 አመት በላይ ከሆነ፣ የወር አበባ መዛባት ካለ እና ከዚህ ቀደም ለመሀንነት የሚያጋልጥ ሁኔታ ከነበረ ጥንዶች በተጋቡ በ6 ወር ውስጥ ወደ ህክምና ተቋም ቢሄዱ ይመከራል።
በ1 አመት ውስጥ ከ10 እስከ 15% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ ላለመውለድ ችግር ይጋለጣሉ። 85% የችግሩ መንስኤ በህክምና ይታወቃል። እንዲሁም 15% የተፈጠረው የመሀንነት ችግር ምክንያት (መንስኤ) በህክምና ምርመራ እንደማይታወቅ የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
የመሀንነት ችግር (ልጅ አለመውለድ) ለድብርት እና ለጭንቀት በመዳረግ ለስነልቦና መታወክ ሊያስከትል ይችላል። እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ ተፅእኖ በማሳደር የአይምሮ ሰላም ያናጋል። ስለሆነም የህክምና ባለሙያው “መሀንነት በሽታ ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።
መሀንነት ሁለት አይነት ሲሆን ይህም የመጀመሪያ መሀንነት (primary infertility) እና ሁለተኛ መሀንነት (secondary infertility) ተብሎ ይከፈላል።
1, የመጀመሪያ መሀንነት (primary infertility); ሙሉበሙሉ ልጅ ለመውለድ ያልቻሉ ማለትም በተለያየ ምክንያት 1 ልጅ ለመውለድ የተቸገሩ ሰዎች በዚህ ምድብ ይካተታሉ።
2, ሁለተኛ መሀንነት (secondary infertility); በዚህ ውስጥ የሚመደቡት አንድ እና ከአንድ በላይ ልጅ ወልደው በቀጣይ ልጅ ለመውለድ የተቸገሩ ሰዎች ናቸው። እንዲሁም ልጅ ባይወለድም ከማህጸን ውጪ እርግዝና ተፈጥሮ ወይም በሌላ ምክንያት ፅንስ በመሀል ከተቋረጠ እዚህ ውስጥ ይካተታል። ስለሆነም እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ‘መሀን መሆን’ በመባል ይጠራል። ሁለቱም የመሀንነት አይነት ተመሳሳይ በሆነ መንስኤ[ምክንያት] ሊፈጠር ይችላል።
በተለምዶ ሰዎች መሀን ናቸው ተብሎ የሚታሰበው አንድ ልጅ ካልወለዱ ነው። ባለሙያው እንደተናገሩት ይህ አስተሳሰብ በብዛት የሚስተዋለው ከዚህ ቀደም ልጅ ያላቸው ወንዶች (አባቶች) ላይ ነው። ከዚህ ቀደም ልጅ የወለደ አንድ አባት ልጅ የመውለድ ችግር እንደሌለበት ያስባል። የትዳር አጋሩ (ሚስቱ) በተመሳሳይ መልኩ ችግሩ የእሱ ሳይሆን የእሷ እንደሆነ ታምናለች። “ህክምና ስንሰጥ በጣም የምንቸገረው ወንዶች ‘እኔ ወልጃለው እኔ ጋር ችግር የለም’ በማለታቸው ነው። በተመሳስይ ሴቶቹ ‘እኔ ጋር ነው ችግር ያለው’ ይላሉ። ነገር ግን እንደዚህ ብለን መደምደም አንችልም” ብለዋል ዶ/ር አቤል ተሾመ። ይህ አስተሳሰብ የሚንፀባረቀው ባል አስቀድሞ ልጅ ስለወለደ ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ዘንድ የመሀንነት ችግር የሴቶች ችግር እንደሆነ ስለሚታሰብ ነው። ነገር ግን ሁለቱም የመሀንነት ችግር አይነት በሁለቱም ጾታዎች ይከሰታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ እስከ 15 በመቶ ጥንዶች የመሀንነት ችግር ያለባቸው ሲሆን ከዚህም ውስጥ 7 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ለመሀንነት እንዳተጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንድ ወንድ በተፈጥሮ (ሲወለድ) ከ15 ሚሊዮን በላይ የዘርፈሳሽ (የዘር ፍሬ) ይዞ ይወለዳል። ልጅ ለመውለድ ይህ የዘር ፍሬ መኖር አለበት። እንዲሁም የዘር ፍሬው ከ40% በላይ ተንቀሳቃሽ እና መጠኑ 1.5 ሚሊሊትር በላይ መሆን አለበት። በተጨማሪም ቅርፁ ጤነኛ መሆን እናዳለበት የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። እነዚህ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ሲጎድሉ መሀንነት ይከሰታል። ይህ መጓደል በሁለት መንገድ ሊያጋጥም ይችላል። በተፈጥሯዊ እና ከጊዜ በኋላ የተከሰተ በማለት ይከፈላል።
1, በተፈጥሮ የሚያጋጥም ሙሉ በሙሉ የዘር ፍሬ አለመኖር ወይም የዘር ፍሬ የማምረት ችግር
2, ከአንጎል(አይምሮ) ተመርተው የዘር ፍሬን የሚያነቃቁ ሆርሞኖች (pituitary hormones, hypothalamus hormones, testosterone) በአፈጣጠር ችግር ምክንያት አለመመንጨት
3, የዘር ፍሬ የሚያልፍበት መንገድ(መስመር) ችግር
4, የዘር ፍሬ በተፈጥሮ ሆድ ውስጥ ይመረታል። በሂደት የተመረተው የዘር ፍሬ ወደ ዘር ፍሬ ከረጢት ይገባል። ነገር ግን ሆድ ውስጥ ከቀረ የመሀንነት ችግር ያስከትላል።
በተፈጥሮ የሚያጋጥም የመሀንነት ችግር መቶበመቶ በሚባል መልኩ ልጅ ላለመውለድ [መሀንነት] ችግር ይዳርጋል።
ከጊዜ በኋላ ለሚከሰት ልጅ ያለመውለድ ችግር የሚያጋለጡ ምክንያቶች;
1, የጭንቅላት እጢ እና ኢንፌክሽን
2,ኢንፌሽን; ለምሳሌ በልጅነት የሚከሰት የማጅራት ገትር እና ጆሮ ደግፍ በሽታ
3, ፅኑ ህመም; እንደ ኩላሊት እና መሰል በሽታዎች ከአንጎል የሚለቀቁትን ሆርሞኖች ሊያዛቡ ይችላሉ።
4, የተለያዩ መድሀኒቶች; ለአይምሮ ህመም የሚሰጡ (ለድብርት በሽታ) መድሀኒቶች፣ የፀረ ካንሰር መድሀኒት እና ለካንሰር የሚሰጥ ህክምና (ዳሌ አከባቢ ከሆነ)
5, የአባላዘር በሽታ፤
6, ሙቀት እና አለባበስ; የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ ያለበት አካል በተፈጥሮ የተቀመጠው ለሙቀት እንዳይጋለጥ ተደርጎ ነው። ስለሆነም ሙቀታማ ቦታ ማዘውተር እና የሚያጣብቅ የውስጥ ሱሪ መልበስ ለመሀንነት ሊያጋልጥ ይችላል።
7, ከፋብሪካ የሚወጡ የተለያዩ ኬሚካሎች (ፔትሮሊየም፣ ቤንዚን) እና ብረታብረት [ሊድ] ነክ ነገሮች ላይ የሚሰሩ ሰዎች መሀንት ሊያጥማቸው ይችላል፡፡
8, የውበት መጠበቂያ የሆኑትን ስቲም እና ሳውና ባዝ አዘውትሮ መጠቀም፤
9, የሰውነት ጡንቻ ለማፈርጠም የሚወሰድ መድሀኒት (አናቦሊክ ስትሮይድ); በውስጡ የቴስቴስትሮን [testosterone) ንጥረነገር(ሆርሞን) ካለው በሰውነት ውስጥ ያለውን የሆርሞን ስርአት ያዛባል። ይህም የዘር ፍሬ በመቀነስ ወይም ሙበሙሉ በማጥፋት ለመሀንነት ሊያጋልጥ ይችላል።
የመሀንነት ምልክቶች; በተፈጥሮ ልጅ ያለመውለድ (መሀንነት) ችግር ካለ የጉርምስና እድሜ ላይ የሚታዩ ፀጉር የመብቀል፣ ድምፅ መወፈር (መጎርነን) እና መሰል ምልክቶች ላይታዩ ይችላሉ። ሌላኛው በአፈጣጠር ችግር የዘር ፍሬ ሆድ ውስጥ መቅረት ሲሆን ይህንንም እስከ 2 አመት ወደ ዘር ፍሬ ከረጢት ካልገባ ችግር እንዳለ ማወቅ ይቻላል። ስለሆነም በህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት ወደ ዘር ፍሬ ከረጢት እንዲገባ ይደረጋል።
ህክምናውን በተመለከተም የግብረስጋ ግንኙነት ለመፈጸም በተለያየ ምክንየት ፍላጎት የማጣት ችግር ሲኖር፤ የዘር ፍሬ ቁጥር ዝቅተኛ ከሆነ፤ የዘር ፈሳሽ ወደ ሴት ማህጸን ሳይሆን ወደ ሽንት ፊኛ የሚሄድ ከሆነ በህክምና መርዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪ አይ ቪ ፍኤ [IVF] የተባለ ህክምና የሚገኝ ሲሆን ይህም የወንድ ዘር እና የሴት እንቁላል በላብራቶሪ እንዲገናኝ [እንዲቀላቀል] ተደርጎ ወደ ሴቷ ማህጸን እንዲገባ እና ልጅ እንዲወለድ የሚያስችል የህክምና ዘዴ ስለሆነ የመህንነት ችግርን ለማቅለል ይረዳል፡፡
የወንዶች የመሀንነት ችግር መከላከያ መንገድ ነው ከሚባለው ውስጥ ሰፋ ያለ የውስጥ ሱሪ መልበስ፣ ስቲም እና ሳውና አለማዘውተር፣ ፋብሪካ እና ብረታብረት አከባቢ [የሚሰሩ ሰዎች[ የፊት ጭምብል በማድረግ አፍ እና አፍንጫን መሸፈን የመሳሰሉትን መጠቀም ይመከራል።
ልጅ ያለመውለድ ችግር የሴት ወይም የወንድ ብቻ ባለመሆኑ ለጋራ ችግር በጋራ መመርመር እና ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል። ስለሆነም ጥንዶች ወደ ህክምና ተቋም በጋራ እንዲመጡ በማለት የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ
(በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን በተመለከተ)
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ውሳኔውን በሚቃወሙና በሚደግፉ ተማሪዎች መካከል በተከሰተው ውዝግብና ግጭት ምክንያት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች እንድምታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ምንም እንኳን የጸጥታው ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ ጋብ ያለ ቢሆንም፤ ለወደፊቱም ይህን መሰል ሁኔታዎችንና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትልና ምርመራ የተረጋገጡ ግኝቶችን፣ ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው የሕግ ማዕቀፎች አንጻር በመተንተን ጭምር ይህን ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ይወዳል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራና ክትትል፣ የጸጥታ መደፍረስ የተከሰተባቸውን ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የሚሸፍን ምርመራ ለማካሄድ ባይቻልም፤ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን፣ መምህራንና ኃላፊዎችን፣ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የነበሩ ተማሪዎችንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም በማነጋገር፣ የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የነበሩ ምስክሮችንና የተማሪዎች ወላጆችን እንዲሁም የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሌሎች ኃላፊዎችን በማነጋገርና መረጃዎችና ማስረጃዎች በማሰባሰብ ስለ ጠቅላላ ጉዳዩ ተገቢውን ግንዛቤ ለማግኘት ተችሏል፡፡
ዋና ዋና ግኝቶችና የሰብአዊ መብቶች እንድምታዎች
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ መነሻው፣ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የክልሉ መዝሙር እንዲዘመር ማድረግን በሚመለከት የተለያየ ሃሳብና ፍላጎት ባላቸው ተማሪዎችን ጨምሮ የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በአፋን ኦሮሞ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ የመስቀልና የክልሉን መዝሙር የመዘመር መብት አላቸው በሚል መነሻ በትምህርት ቤቶቹ ግቢ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጎን በመስቀልና ጠቅላላው ተማሪዎች የክልሉን መዝሙር በመዘመር የሰንደቅ ዓላማ ሥርዓቱን እንዲያከብሩ በመደረጉ በየትምህርት ቤቶቹ በሚገኙ ከፊል የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባሎች እርምጃው ሕጋዊ መሠረት የለውም በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
በአብዛኛው ቦታዎች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ መሰቀልና የክልሉ መዝሙር መዘመርን በሚደግፉና በሚቃወሙ ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ሁከት፣ ረብሻና ግጭት፤ እንዲሁም የፖሊስ አባላት ሁኔታውን ለመቆጣጠር በወሰዱት የእስር እርምጃ የሰብአዊ መብቶች አሉታዊ እንድምታ ያስከተለ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የትምህርት ሂደት በመስተጓጎሉ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ከባድና ቀላል የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል፣ የተማሪዎችና የትምህርት ቤቶች ንብረት ወድሟል፣ ሕፃናት ተማሪዎች ለአካላዊ እንግልትና ከሕግ ውጭ ተገቢ ላልሆነ እስር ተዳርገዋል፡፡
ይሁንና በማኅበራዊ ሚዲያና በአንዳንድ ተቋሞችም የተዘገበውና ጉራራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ከፍተኛ 12 ትምህርት ቤት ውስጥ የነበረ ተማሪ ሕይወት ጠፍቷል የተባለው ትክክለኛ መረጃ አለመሆኑንና በዚህ ክስተት የደረሰ የሕይወት መጥፋት አለመኖሩን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
በንብረት ላይ የደረሰው ውድመትና በረብሻው ወቅት በተማሪዎች ላይ የደረሰው ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በተማሪዎቹ የእርስ በእርስ ግጭት የተከሰተ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ በርካታ ምስክሮች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት፤ ፖሊስ ብዙ ተማሪዎችን ከማሰሩ በስተቀር፤ አብዛኛዎቹ የፖሊስ አባላት በጥንቃቄና ተመጣጣኝ በሆነ እርምጃ ሁከቱን ለማረጋጋት ይጥሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ፖሊስ አብዛኛዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ ተማሪዎች በፍጥነት ወደ የሕፃናት ልጆች ችሎትና መደበኛ ፍርድ ቤት እያቀረበ ከፍርድ ቤት በተሰጠ የዋስትና መብት በተለያየ ጊዜ ከእስር ተለቀዋል። በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ፖሊስ በፍጥነት ወደ ሕፃናት ችሎቶች እንዲቀርቡ እያደረገ ወዲያውኑ ተለቀዋል፡፡
በአንጻሩ እጅግ ብዙ ዕድሜያቸው በአብዛኛው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች ከመነሻውም ቢሆን ለእስር መዳረጋቸውና ለተለያየ ጊዜ መጠን በእስር መቆየታቸው ተገቢ ያልሆነና ለነገሩ ሁኔታም ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ነው፡፡
የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ በሆነ እርምጃ ሁከቱን በመቆጣጠር፣ እጅግ ቢበዛ ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ተማሪዎቹን በየትምህርት ቤታቸው ግቢ ወይም ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ አድርገው፣ በቀጥታ በወንጀል ተግባር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ካሉም እንደአስፈላጊነቱ እጅግ አጭር ለሆነ ጊዜ ብቻ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይተው ሳይውል ሳያድርና እንደ አግባብነቱ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 28(1) መሰረት በፖሊስ ጣቢያ በሚሰጥ ዋስትና መልቀቅ ሲገባቸው፤ ከዚህ ውጪ ብዙ ሕፃናት ተማሪዎችን የተሟላ አገልግሎት በሌላቸውና ለአካለ መጠን የደረሱ ተጠርጣሪዎች በሚታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች አስረው ማቆየታቸው የአስፈላጊነት፣ የሕጋዊነትና የተመጣጣኝነት መርሆችን ያልተከተለ የሕፃናትን መብቶች የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
በተማሪዎች ተፈጽሟል የሚባል ጥፋት ቢኖርም እንኳን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በሚመለከተው የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና አግባብነት በአላቸው የኢትዮጵያ ሕጎች መሠረት ለሕፃናት ልጆች የሚገባው የሕግ ከለላ እንደተጠበቀ ሆኖ የማጣራት ሥራ ከማከናወን በስተቀር፤ ሕፃናት ተማሪዎችን ሊያውም በጅምላ ለእስር መዳረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊደገም የማይገባ ነው፡፡
2. የሰንደቅ ዓላማውና የብሔራዊ መዝሙር ውዝግብና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች እንድምታው
ለዚህ ሁከትና ለደረሰው የሰብአዊ መብቶች ጉዳት መነሻ ምክንያት የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ እና የብሔራዊ መዝሙር አጠቃቀም ሕጋዊ መሠረት እና ምክንያት መፈተሽም ለወደፊቱ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለመከላከል አስፈላጊ ነው፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 እንደተደነገገው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያለው፣ ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት የሆነ እና የከተማው ነዋሪዎችም በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወከሉ ሲሆኑ፤ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም የሚጠበቅለት መሆኑና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን የተገለጸ ቢሆንም፣ እስከአሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝርዝር ሕጉን ያላወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት የግዛት ወሰን ውስጥ እና የክልልና የከተማ መስተዳድሮችን ጨምሮ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ ንግድ መርከቦችና አውሮፕላኖች ላይ ተፈጻሚ በሚሆነው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ በየቀኑ ወይም ቢያንስ በብሔራዊ በዓል ቀን የሚሰቀልባቸው ቦታዎችና የሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀልና አጠቃቀም ሥነ ሥርዓት በዝርዝር ተደንግጓል፡፡
በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 3 (3) መሠረት፤ ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና አርማ ሊኖራቸው እንደሚችል በደነገገው መሠረትና በየክልሎቹ በጸደቁ የክልል ሕገ መንግሥትና የክልል ሰንደቅ ዓላማ አዋጆች መሠረትም የየክልሉ የሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀልና አጠቃቀም ሥነ ሥርዓት የሚደነግጉ ሲሆን ሁሉም የክልል ሰንደቅ ዓላማ አዋጆች በየክልሉ ከፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ጋር በአንድነት ተፈጻሚ የሚሆኑ ናቸው ፡፡
ከዚህ ውጪ የአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በሌላ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ወይም የግል ተቋሞች ውስጥ እንዲሰቀል የሚያስችል የሕግ መሠረት የለም፡፡
በአንጻሩ በየትኛውም ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የአንድ የሌላ ክልል መለያ በሆነ ተቋም ሕንጻ ላይ ወይም ግቢ ውስጥ (ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሕንጻዎች ላይ) በክልሉ ወይም በከተማው መስተዳድር ዕውቅና የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በአዋጅ ቁጥር 654/2001 በተመለከተው መሠረት መስቀል የሚከለክል የሕግ ምክንያትም የለም፡፡
ከዚህ በላይ ከተገለጹት ሕጋዊና ምክንያታዊ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ወይም የሕዝብ አገልግሎት ተቋሞች የሌላ ክልል ሰንደቅ ዓላማን በአስገዳጅነት ለመስቀል መጣር ሕጋዊ መሠረት የሌለው ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊ ውዝግብና ሁከት በመፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡
በሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ወቅት የሚዘመረውን ብሔራዊ መዝሙር በተመለከተ በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 4 በግልፅ እንደተመለከተው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አንድ ብሔራዊ መዝሙር ሲሆን፤ በአዋጅ ቁጥር 673/2002 አንቀጽ 5 እንደተመለከተው ክልሎች በሕግ በወሰኑት የሥራ ቋንቋ የብሔራዊ መዝሙሩ የግጥም ይዘትና ዜማ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ የሥራ ቋንቋ በማስተርጎምና በየክልሎቹ ምክር ቤቶች በማስፀደቅ ብሔራዊ መዝሙሩ እንዲዘመር ማድረግ አለባቸው፡፡
ከዚህ ሕጋዊና ምክንያታዊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አጠቃቀም ውጪ አላስፈላጊ ውዝግብና ሁከት መፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡
በተጨማሪም መንግሥት በሰብአዊ መብቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ውሳኔዎች፣ ደንቦች፣ ፕሮግራሞች፣ መርኃ ግብሮች ወይም አሠራሮች ሲዘጋጁ ወይም ከመተግበራቸው በፊት በሰብአዊ መብቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ውጤቶች አስቀድሞ መለየት፣ ማጤንና መከላከል ወይም መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል። ይህም የመንግሥት ደንቦች፣ ፕሮግራሞች፣ መርኃ ግብር ወይም አሠራሮች መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን ከማክበር፣ ከማስከበር እና ከማሟላት አኳያ ካሉት ግዴታዎች ጋር እንዳይቃረን ለማድረግ ያስችላል።
3. ስለ ሕፃናት ተማሪዎች ልዩ ጥበቃ
በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና በኢትዮጵያም ሕጎች መሠረት የሕፃናት ልዩ ልዩ መብቶች የተጠበቁ ሲሆን፤ በተለይ የሕፃናት ልጆች በትምህርት ቤትና አካባቢ የሚደረግ ልዩ ትኩረትና ጥበቃን በሚመለከትም ዓለም አቀፍ ግዴታዎችና መርሆች አሉ፡፡
ከእነዚህም ውስጥ፡-
በትምህርት ቤቶች ውስጥ አመጽ፣ ማስፈራራትና የኃይል እርምጃ የሕፃናት ልጆችን በምቹ ሁኔታ የመማርና የማደግ መብት የሚጎዳ፣ ለሥነ ልቦና ጉዳት የሚያጋልጥና አጠቃላይ የሆነ ፍርሀት፣ ሥጋትና ጭንቀት በማሳደር ትምህርትን፣ ዕውቀትንና ዕድገትን የሚጎዳ በመሆኑ ይህን መሰል ሥጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሙሉ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፣
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕፃናት ልጆች የሰው ልጆች ክቡርነትና እኩልነትን፣ የሃሳብ ልዩነትና መቻቻልን እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ሙሉ እሴቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚማሩበት የሚለማመዱበትና የሚያጎለብቱበት ስፍራ ስለሆነ፤ ሕፃናት ልጆችን እና ተማሪዎችን በሚመለከታቸው ጉዳይ በማማከር፣ በማሳተፍና በማድመጥ የትምህርት ቤታቸው ሕይወት ውስጥ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ማድረግ እንጂ በኃይል፣ በዛቻ፣ በማስፈራራት፣ በማስጨነቅና በሥጋት ማስተማርና ማስተዳደር ተገቢ አይሆንም፡፡
ልጆች በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ፣ ሃሳባቸውንና ተቃውሟቸውን የመግለጽ ነጻነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊ ክህሎቶችን የሚያጎለብቱበትን መብታቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ እና ድጋፍ በትምህርት ቤቶች ውስጥም ማመቻቸት ተገቢ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን:-
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደፊትም እንዳያጋጥሙ ለችግሩ መንስኤ ለሆነው የሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብ ሕፃናትን ጨምሮ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ግልጽ የሆነ የሕግ እና ፖሊሲ መፍትሔ በማበጀት ዘላቂ እልባት በመስጠት፣ እንዲሁም አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎችና የሰብአዊ መብቶች መርሆችን በማክበርና በማስከበር የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጋራ እንዲከላከሉ፤ በተጨማሪም የየትምህርት ቤቶቹና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሰላም፣ በመቻቻል እና የሃሳብ ልዩነትን በመቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመፍታት ላይ ተመሥርቶ የመፍትሔ አካል እንዲሆን አበክሮ ያሳስባል፡፡
ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ
ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ መታወቂያዎቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ማህተሞችና ወረቀቶችም በብርበራ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ አካባቢ ነው። ተጠርጣሪዎቹ ለዚሁ ህገ-ወጥ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚውሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር ጽ/ቤት እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የቀበሌ 01 አስተዳደር ጽ/ቤት የሚሉ ሃሰተኛ ክብ ማህተሞችን እንዲሁም የግለሰብ የስም ቲተር በማስቀረፅና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርማ ያረፈበትን የመታወቂያ ወረቀት አመሳስለው በማሳተም ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ማህተሞቹንና ወረቀቶቹን በአንድ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ደብቀው በማስቀመጥ የነዋሪነት መታወቂያ ለሚፈልጉ ሰዎች ሃሰተኛ መታወቂያዎችን እያዘጋጁ እንደሚሸጡ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማና ፖሊስ ባደረገው ክትትል 3 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ሲሆን፤ ሃሰተኛ መታወቂያውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ማህተሞችም ከተደበቁበት በብርበራ እንደተገኙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
የካንሰር ታካሚዎች ለህክምና እስከ ሁለት ዓመት ወረፋ ይጠብቃሉ
ለውጭ ሀገር ህክምና በየአመቱ 100 ሚሊየን ዶላር ይወጣል
– አራት የጨረር ሕክምና መሳሪያዎች በመጋዘን ተቀምጠዋል
አዲስ አበባ፡- ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፉ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ የካንሰር በሽታ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በየአመቱ 70 ሺህ ሰዎች በካንሰር የሚያዙ ሲሆን ቢያንስ 50 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችም ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያሉት የካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከላት ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የገንዘብ አቅም ያላቸው ጥቂት ዜጎች ለሕክምና ባህር ማዶ ሲሻገሩ፣ ብዙዎች ግን ወረፋ እየተጠባበቁ ለህልፈት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሌላ በኩል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውንና ጨረር በማመንጨት ካንሰርን የሚገድለውን ‹‹ሌይነር አክስለሬተር›› የተሰኘ ዘመናዊ የካንሰር ህክምና መስጫ ማሽን እአአ በ2017 ወደሃገር ውስጥ አስገብቷል፡፡
ለጎንደር፣ ለሃይደር፣ ለጅማ፣ ለጥቁር አንበሳ፣ ለጳውሎስ፣ ለሐዋሳና ለሃሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ለእያንዳንዳቸውም አንድ ደርሷቸዋል፡፡ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን እንደገለጹት፤ ሰባቱ ማሽኖች የተገዙት
በ24 ሚሊየን ዶላር ወጪ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ደነቀ፤ ባግባቡ ከተሰራ ባንከሩን ሰርቶ ማሽኑን ለማስገባት ከአንድ አመት በላይ አይፈጅም ይላሉ። ህንጻው ተገንብቶ፣ ሁለት ማሽን ተክሎ፣ ባንከሩ ተዘጋጅቶ፣ አስፈላጊ ግብአቶችን አስገብቶ ስራ ለማስጀመር እስከ አንድ ቢሊየን ብር ሊፈጅ ይችላል።
ከገቡት ማሽኖችም የጅማ፣ የጥቁር አንበሳና የሃሮማያ ስራ ሲጀምሩ፤ ቀሪዎቹ አራት ማሽኖች በየተቋማቱ እስካሁን በመጋዘን ተቀምጠዋል።
በውሉ መሰረት የማሽን ገጠማ ስራ (ኢንስታሌሽን) እና ተጨማሪ ስራዎች ማሽኑን ያቀረበው ኩባንያ ኃላፊነት ሲሆን፤ የካንሰር ማዕከል (ባንከር)፣ የህንጻ ግንባታና ባለሙያ ማብቃት ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎቹ ኃላፊነት መሆኑንም ዳይሬክተሯ ይጠቁማሉ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና ኢንስቲትዩት የካንሰር ማዕከል ኃላፊ ዶክተር አማረ አሰፋ እንደሚሉት፤ የካንሰር ህክምና መስጫ ማሽኑ ስራ ከጀመረ 15 ወራት ሆኖታል። በማዕከሉ በቀን እስከ 107 ሰው፤ በአመት እስከ ሁለት ሺ 500 ሰው ይታከማል፣ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም በጨረር ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች መታከማቸውን ይገልጻሉ።
የጥቁር አንበሳ ማሽን በብልሽት ለሶስት ወራት አገልግሎቱን በማቋረጡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተገልጋዩችን በመቀበል ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበረበት፣ እንደአገር የማሽን ህክምና ከሚፈልገው ታካሚ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑንም ይጠቁማሉ።
በሃገራችን በየአመቱ 150 ሺህ ሰው የጨረር ህክምና ይፈልጋል። ይህንን ህዝብ ለማከም ደግሞ ቢያንስ እስከ 200 ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ፣ ለህክምናውም ዜጎች በየአመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚያደርጉ ይገመታል ሲሉ ዶክተር አማረ ይናገራሉ።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ አቅም ያላቸው ህክምናውን ለማግኘት ወደ ታይላንድ ባንኮክ፣ ቱርክ፣ ሕንድ ይጓዛሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው ህንድ አገር ለመታከም ሁለት ወራት ያህል ይፈጅበታል፣ የአልጋና የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ ከ16 እስከ 20 ሺህ ዶላር ይፈጅበታል። ለጨረር ህክምናው ብቻ ደግሞ 32 ሺ ዶላር ይከፍላል።
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ኤዶም ሰይፉ እንደሚናገሩትም፤ አዲሱ ማሽን ስራ ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። በቅርቡ ለሶስት ወራት በመበላሸቱ በርካቶች ተጉላልተዋል።
ችግሩ ተደራራቢ ህክምናውም ውስብስብ ሆኗል። በቀን ከ30 እስከ 40 በወር ደግሞ ከ400 እስከ 500 የሚጠጉ አዳዲስ ታካሚዎች ይመጣሉ። አብዛኞቹ ታካሚዎች የጨረር ህክምና ስለሚያስፈልጋቸው ለጨረር የሚመዘገበው ታካሚ እየጨመረ ይገኛል። አንድ ታካሚ ለህክምናው ስድስት ወራት ይቀጠር የነበረው ዓመት፣ አሁን ዓመት ከስድስት ወራትና ሁለት ዓመታትም ደርሰናል ነው የሚሉት።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤና ህክምና ኮሌጅና በሕይወት ፋና ሁሉን አቀፍ ሆስፒታል የአስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር አቶ ፊላ አህመድ በበኩላቸው፤ የጨረር ህክምና ማዕከል ስራ ጀምሯል፣ ጎን ለጎን ከፍቃድ ጋር ተያይዞ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ ይላሉ።
እስካሁን በጨረር ህክምናው 45 ሰዎች የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል። 20 ሰዎችም ተመዝግበው ህክምና ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አንተነህ ጋዲሳም፤ የማሽን ገጠማ ስራ እያለቀ መሆኑንና ከጨረር ህክምና ውጭ ያሉ ህክምናዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበውም፤ ህክምናው የሚሰጥበት ክፍል /ባንከሩ/ ሙሉ ለሙሉ ማለቁን፣ ለመጀመር ቴክኒሽያኖችና የሰው ሃይል የማሟላት ስራ እየሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
ጨረታውን ያሸነፈው የማሽን የገጠማ ስራ (ኢንስታሌሽን) የሚሰራው ‹‹ኤልስሜድ ኸልዝ ኬር ሶሉሽን›› የኢትዮጵያ ወኪል፣ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት አቶ ዳዊት ሃይሉ ጨረታው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል እ.አ.አ በ2015 እንደወጣ ያስታውሳሉ።
በ2016/17 አካባቢ የሐዋሳና የሐረር ሳይቶች ዝግጁ መሆናቸው እንደተነገራቸው ኤልሲ ተከፍቶ ለሰባቱም አስፈላጊ እቃዎች እንዲገቡ መደረጉንም ነው የሚናገሩት።
የሐረማያ፣ የሐዋሳና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ፈጥኖ ወደ ትግበራ ለመግባት የጸጥታ ችግር፣ ከኮቪድ መከሰት ጋር ተያይዞ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ተደማምረው ጫና ማሳደራቸውንም በምክንያትነት ያነሳሉ።
አቶ ፊላ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊ ግብአቶችን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ስራው ለውጭ አካል በመሰጠቱ በራስ ጉዳይ የመጠመድና አስፈላጊ ግብአቶችን ለማስገባትም ችግር ማጋጠሙ ለመዘግየቱ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።
ዶክተር አንተነህ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ ማሽኑን እአአ በ2017/18 መረከባቸውን፣ በ2019 የገጠማ ስራው መጀመሩን፣ ገጠማውን የሚሰራው አንድ ቡድን በመሆኑ የጥቁር አንበሳንና የጅማን ጨርሶ ወደሐረር እስኪጓዝ መዘግየቱን ይገልጻሉ። ከሶስት ወራት በኋላም ወደ ትግበራ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ዘገየ የሚለውን እንደማይስማሙበት የሚናገሩት ደግሞ ዶክተር አሸናፊ ናቸው፤ በእቅዱ መሰረት በጣም ዘገየ የሚባልበት ሁኔታ ላይ አለመሆኑን፣ የተጀመረው፤ የጅማ፣ የሐዋሳና የሀሮማያ ሳይቶች ከተጀመሩ ከዓመት በኋላ የጎንደር መጀመሩንና የዲዛይን ማሻሻያዎችም መደረጋቸውን ይገልጻሉ።
ከሌሎቹ ሳይቶች በተለየም የኒኩሊየር ሕክምና መስጫ አብሮ በመገንባቱ መዘግየት መፍጠሩን፣ የኒኩሊየር ማስወገጃውና የማሽኖቹ ተከላ ተጠናቅቆ እኤአ 2023 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ስራ እንደሚጀምርም ይገልጻሉ።
እስካሁን ጎንደር ሐዋሳ፣ መቀሌና (ሀይደር) ስራ አለመጀመራቸውን የሚያስታውሱት ኤልስሜድ ኸልዝ ኬር ተወካይ አቶ ዳዊት በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ጎንደርና ሐዋሳ በወቅቱ የባንከሩ ሳይት ከተሰራ በኋላ ከፊት ለፊታቸው ትልቅ ህንጻ ስለገነቡ ማሽኑን ለመግጠም አልቻልንም።
አሁን ህንጻው ተጠናቅቆ ወደ ማሽን ገጠማ ስራ ገብተናል። የሐዋሳው በዚህ ወር፣ የጎንደሩ በሚቀጥለው ወር ይጠናቀቃል። የጳውሎስ ግን እስካሁን ገጠማ አልተካሄም። ሆስፒታሉ የካንሰር ማዕከልን ጨምሮ ሰፊ የግንባታ ስራ ላይ ይገኛል።
ስራ ያልጀመሩ ቀሪዎቹን ማሽኖች ወደትግበራ ለማስገባት ተግዳሮት የሆኑብን የሳይቶቹ ዝግጁ አለመደረግ ነው። አሁን ላሉ ለማሽኖች አስፈላጊ መለዋወጫ አስገብተናል። የግንባታ ብቻ ሳይሆን፤ የኤሌክትሪክና ማሽኑ የሚፈልጋቸው ግብአቶች መኖር ወሳኝ ነው ብለዋል አቶ ዳዊት።
መቀሌ የሚገኘው የሃይደር ሪፈራል ሆስፒታል ማሽኑን ከወሰዱ ሰባቱ ተቋማት አንዱ መሆኑንና ከሰሜኑ ግጭት ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለበትን ሁኔታ እንደማያውቁም፣ አሁን የሰላም ስምምነት በመፈጠሩ ቡድን ተዋቅሮ ያለበትን ሁኔታ እስከምንመለከት መረጃ የለንም የሚለው ምላሽ ወይዘሮ ሕይወትም አቶ ዳዊትም የሚጋሩት ምላሽ ነው።
የታካሚዎቻችንን ቁጥር በእጥፍ ማሳደግ እንፈልጋለን። አንድ ባንከር ዝግጁ አድርገናል፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልም አለን፤ ቢያንስ አንዱ ሲቆም ሁለተኛው ማሽን አገልግሎት እንዲሰጥ ተጨማሪ ማሽን ያስፈልገናል የሚሉት ደግሞ አገልግሎቱን እየሰጡ የሚገኙት የጥቁር አንበሳና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
አስጊነቱ እየጨመረ ባለው በዚህ በሽታ ‹‹በዓመት ከ60 እስከ 70 ሺህ ሰዎች በተለያዩ አዲስ የካንሰር አይነቶች ይያዛሉ። በከፍተኛ ቁጥር ተጠቂ እየሆኑ የሚገኙት ደግሞ ሴቶች ናቸው›› ይላሉ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ሕይወት ሰለሞን።
የራዲየሽን ቴክኒሽያንና የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች ቁጥራቸው መጨምር አለበት፣ በቂ መለዋወጫ በመጋዘን መኖር ይገባዋል፣ ማሽኑ ሲበላሽ የሚያድሱና የሚያስተካክሉ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ይገባል የሚለውንም ምክረ ሃሳብ ሁሉም ባለሙያዎች ይጋሩታል።
በኢትዮጵያ መዳን እየቻሉ በህክምና እጦት የሚሞቱ በርካታ የካንሰር ታማሚዎች ቢኖሩም ከዚህ በተቃረነ መልኩ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሃገር ተገዝተው የገቡ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች ሙሉ ለሙሉ ወደስራ ሳይገቡ ለአመታት ቆይተዋል። ይህ ደግሞ የሃገር ሃብት ያለአግባብ እንዲባክን ፣ ዜጎች በህክምና እጦት እንዲሞቱ፣ እንዲሁም ጥቂት አቅሙ ያላቸው ዜጎችም በሀገር ውስጥ መታከም እየቻሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አውጥተው ወደውጭ እንዲሄዱ በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የገቡት ማሽኖችም በወቅቱ ወደስራ ካልገቡ ሊበላሹና ለተጨማሪ ኪሳራ ሊዳርጉ ይችላሉ።