
Administrator
ብሬክስሩ ትሬዲንግ በዓመቱ 65 ሚ. ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ
በ20 ዓመታት ውስጥ ባለ ብዙ ፋሲሊቲ ሜትሮፖሊስ (ከተማ) ለማቋቋም አቅዷል
ብሬክስሩ ትሬዲንግ አ.ማ. ዓመታዊ የሽያጭ ዕቅዱን በ65 በመቶ በማሳካት 65 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ በተካሄደው ሦስተኛው መደበኛ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ነፃነት ዘነበ እንደተናገሩት፤ የ2014 በጀት ዓመት የሽያጭ መጠን 65 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
ጠቅላላ ጉባኤው በ2014 የበጀት ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ዕቅድ ቢያስቀምጥም፣ ድርጅቱ የዕቅዱን 65 በመቶ በማሳካት፣ 65 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የቦርድ ሰብሳቢው አስታውቀዋል።
“የባለአክሲዮኖች ድርሻ በሽያጭ ካገኘነው ገቢ 50 በመቶው ነው” ሲሉም ገልፀዋል፡፡ በ2014 የበጀት ዓመት የኩባንያውን ንግድ ለማስፋፋት የተነደፈውን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በስኬት መድረሱንም አቶ ነፃነት ተናግረዋል።
“ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ለመክፈት ባቀድነው መሰረት በአዲስ አበባና አዳማ ከተማ ሁለት ቅርንጫፎችን መክፈት ችለናል” ብለዋል፤አቶ አቶ ነፃነት። “በደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያና ካሜሩን ቢሮ ለመክፈት የምናደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ የሚያስችል በጀት መድበናል። በተጨማሪም፣ መንገዶችን ለማመቻቸት የሚረዱ ሃሳቦችን ከተወሰኑ ግለሰቦች ጋር በመለዋወጥ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ብሬክስሩ ከዚህም ባሻገር “ጆብ ክርኤሽን” ከተባለ የኬንያ ኩባንያና ከደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል” ሲሉም ገልጸዋል፤ሰብሳቢው፡፡
ጠቅላላ የባለአክሲዮኖቹ ጉባኤ ተወያይቶ የኦዲትና አጠቃላይ ሪፖርቶችን እንደሚያጸድቅ የተገለጸ ሲሆን፤ የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ድልድልና የኩባንያው የስራ ዕቅድም ለውይይት ቀርቦ እንደሚጸድቅ በበዓሉ ላይ ከተሰራጨው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
ብሬክስሩ ትሬዲንግ፤ አርቆ አስተዋይ፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድ የመገንባት ራዕይ ያለውና “ቅን” በተሰኘ ቡድን በ2019 ዓ.ም የተመሰረተ የንግድ ኩባንያ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተሻሉ አዳዲስ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ፣ የየራሳቸውን ንግድ በዲሲፕሊን እንዲያከናውኑና ከሌሎች ጋር ውጤታማ ትብብር እንዲፈጥሩ የማማከርና የስልጠና አገልግሎቶችን መስጠቱ ተጠቁሟል፡፡
ብሬክስሩ ትሬዲንግ፤ በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኩባንያዎችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የሥልጠና ማዕከሎችን፣ የስብሰባ ማዕከላትን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ሪል እስቴትን፣ ቢሮዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ጂምናዚየሞችን፣ ሙዚየሞችንና ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የሚያቅፍ ባለብዙ ፋሲሊቲ ሜትሮፖሊስ (ከተማ) ለማቋቋም ማቀዱ ታውቋል።
ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ከቢቢሲ ጋር
25 ሺ ገደማ ኢትዮጵያውን በኳታር ይኖራሉ
ግሩም ሰይፉ ጋዜጠኛ ነው። አዲስ አድማስ ለተሰኘው ጋዜጣ ስፖርታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመፃፍ ይታወቃል። ግሩም የኳታር የዓለም ዋንጫ ዝግጅትን ለመታደም ወደ ዶሃ ያቀናው ከመክፈቻው ጥቂት ቀናት ቀድሞ ነው።
ዶሃ ከአዲስ አበባ 2200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ በየቀኑ መንገደኞችን ያመላልሳሉ።
ግሩም፤ ነፋሻማዋን አዲስ አበባ ለቆ ወደ ዶሃ ሲያመራ የጠበቀው የግንቦት ሃሩር ነው። ነገር ግን ይህ ወቅት ለኳታሮች ቀዝቃዛው ወር ነው።
“ዶሃ የቀትር ፀሐይ የሚባል የለም” ይላል። ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ የዶሃን አሸዋማ መሬት የሚቀጠቅጠው ፀሐይ ሃሩር ነው።
ኳታር፤ በሜትሮሎጂ ዘገባ አገላለፅ፤ “በአብዛኛው ፀሐያማ” ናት። በአብዛኛው ከማለት ከንጋት እስከ ምሽት ማለት ሳይቀል አይቀርም። አሁን ባለው የአገሪቱ የአየር ሁኔታ ዝቅተኛው የሚባለው 23 ድግሪ ሴንትግሪድ የሚጀምረው ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ ነው።
ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው የተሰኘው ድረ-ገፅ፣ የኳታር ሕዝብ ብዛት በዚህ ዓመት 2.7 ሚሊዮን ይገመታል ይላል።
ከእነዚህ መካከል ካታሪ የሚባሉት አረቦች 15 በመቶውን ይይዛሉ። ሕንዳዊያን፣ ፊሊፒናውያን እንዲሁም ሌሎች የእስያ አገራት ዜጎች ኑሯቸውን በኳታር ይመራሉ።
ከዚህ ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና ኬንያዊያን በዋና ከተማዋ ዶሃ እንዲሁም በአር ራያን ይገኛሉ።
በነዳጅ ሃብት የበለፀገችው ኳታር፤ እነሆ በአረቡ የዓለም ሲዘጋጅ የመጀመሪያው የሆነውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።
ቶለመ
“ኢትዮጵያዊያን የሥራ ሰዎች ናቸው ይባላሉ”
ግሩም፤ ካሜሩን ከሰርቢያ የሚያደርጉትን የቀን 7 ሰዓት የምድብ ጨዋታ ታድሞ ለመዘገብ እየተጓዘ ሳለ ነው በስልክ ያገኘነው። በየገባህበት ሥፍራ ሁሉ የአየር ማጤዣ ተገጥሟል የሚለው ግሩም፣ ይህ ቴክኖሎጂ ባይኖር ኖሮ ኳታር ለኑሮ ከባድ ትሆን እንደነበር ይናገራል።
“አሁን ለምሳሌ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር 5 ሰዓት ከምናምን ነው። እኛ አገር ግንቦት ወር ላይ ያለው የሚያማርረው ሙቀት ነው አሁን እዚህ ያለው።”
ግሩም የኳታር ነዋሪዎችን ስለ አየር ሁኔታው ሲጠይቃቸው፤ “በብርድ ወቅት መጣህ” በሚል ዓይን እያዩት፤ “ኧረ እንዲያውም ይሄ እኮ ቀዝቃዛው ጊዜ ነው” ይሉታል።
ኳታር፤ ለዚህ ነው ይህንን ወቅት ለዓለም ዋንጫ የመረጠችው እንጂ ለወትሮው የዓለም ዋንጫ በሰኔ ነበር የሚዘጋጀው።
ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚነሳው ነፋስ፣ የኳታር ምሽትን ቀዝቀዝ አድርጎታል።
ኳታር፤ ይህን የዓለም ዋንጫ ስታዘጋጅ ከምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባት ነበር። አገሪቱ የሰብዓዊ መብት አይከበርባትም፣ ስታድየሞቹ ሲታነፁ በርካታ የጉልበት ሠራተኞች ሞተዋል፣ የአየር ሁኔታው ምቹ አይደለም. . . ብቻ ብዙ ነቀፋ አስተናግዳለች።
ነገር ግን ጋዜጠኛ ግሩም፤ ይህ ነቀፋ ተጋኗል የሚል እምነት አለው። “የኳታር ዜጎች በጣም ሰላምተኞች ናቸው። እንግዳ ተቀባይነታቸውን ማየት ችያለሁ። በአረቡ ዓለም መዘጋጀቱ የአረቡ የዓለም ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ልዩ አጋጣሚ ነው” ይላል።
ኻሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም
እንደሱ አመለካከት፤ ዶሃ ወደፊት ልክ እንደ ዱባይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎች የምታስናግድ መናኸሪያ እንደምትሆን አምነት አለው።
ግሩም፤ በዶሃ በተዘዋወረባቸው ቦታዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ኑሮን ለማሸነፍ በተለያየ ሥራ ተሠማርተው ሲተጉ አይቷል።
“ስታዲየሞች ውስጥ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያንን አግኝቻለሁ። አንድ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ኢትዮጵያዊም ተዋውቄያለሁ። በዓለም ዋንጫው ከትላልቅ የብሮድካስት ኩባንያዎች ጋር የሚሠራ ኢትዮጵያዊም ማግኘት ችያለሁ።”
ጋዜጠኛው ግሩም እንደሚለው፤ ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ኳታር ውስጥ ይኖራሉ።
ስለአገሪቱ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያወጣው ‘ኦንላይን ካታር’ የተሰኘው ገፅ፤ ቢያንስ 25 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ አስፍሯል።
“በቤት ሠራተኝነት የሚሠሩ አሉ። የሚማሩ አሉ። የሕንፃ ግንባታ ባለሙያዎች፤ የታክሲ ሾፌሮች አሉ። በርካታ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ያሉበት አንድ አካባቢ አለ። አዲስ አበባ የሚል ስያሜ ያለው ፀጉር ቤት አይቻለሁ። እኔ ከጎበኘኋቸው ሬስቶራንቶች በአንዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው አይቻለሁ።”
“ኢትዮጵያውያን በኳታሮች ዘንድ ይከበራሉ።” የሚለው ግሩም፤ “የሥራ ሰዎች ናቸው ይባላሉ” ብሏል።
ጋዜጠኛ ግሩም ከዚህ ቀደም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሩሲያ ተጉዞ የዓለም ዋንጫን መታደም ችሏል። ነገር ግን የዶሃው በብዙ መልኩ እንደሚለይ ይገልጻል።
አንደኛው ምክንያት፤ ስታድየሞቹ የተቀራረቡ በመሆናቸው እሱና የሙያ አጋሮቹ በአንድ ቀን የተለያዩ ጨዋታዎችን መታደም መቻላቸው ነው።
ለምሳሌ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከዋና ከተማዋ ሞስኮ ወደ ሶቺ ለመሄድ 72 ሰዓታትን በባቡር ተጉዞ ነበር።
ከዚህ በፊት ከተመለከታቸው የዓለም ዋንጫዎች በተለየ በምድብ ጨዋታዎች የታየው ፉክክር፣ የተመልካቾች ብዛትና የስታዲየሞቹ ልዩ ‘ዲዛይን’ ይህንን የዓለም ዋንጫ “ለየት አድርጎብኛል” ባይ ነው የአዲስ አድማሱ ግሩም ሰይፉ።
ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ
ልጆችን እንጂ ልጅነትን ማስቆም አይቻልም!
አሌክስ አብርሃም
ወላጆች ልጅ ሲወልዱ ድካምና ውጣውረዱን የሚችሉበት ፍቅር አብሮ ባይሰጣቸው ኖሮ … ገና በዓመታቸው ዳይፐራቸውን እያስያዙ ከቤት ያባርሯቸው ነበር፡፡ ልጅ ማሳደግ አዲስ ከዚህ በፊት ያልነበረ ሰው መስራት ሊባል ይችላል፡፡ልጅ ማሳደግ የራስን ፍላጎት አምሮትና ማንነት ጭምር መተው የሚጠይቅ ከባድ ኃላፊነት ነው። ያስደስታል፣ ያበሳጫል፣ አንዳንዴም ፀጉር ሊያስነጭና ሊያስለቅስ ይችላል! ለዛም ነው ከመውለድ በፊት ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ ወሳኝ ነው የሚባለው፡፡ እሽ አስበንም ይሁን ሳናስብ ልጅ ተወለደ ከዛስ? የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ይሄ ነው …
አንዳንድ ወላጆች ህፃናት ልጆችን ወደቤታቸው የመጡ ተጨማሪ ፍጥረቶች እንጅ ልክ እንደነሱ ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ የቤቱ ባለቤት መሆናቸውን አያስቡትም፡፡ በህፃናትና ወላጆች መካከል የሚፈጠረው ‹‹ጦርነት›› ሁሉ፣ ልጆች የባለቤትነት መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት የህፃን ጥረትና ወላጆች የልጆቹን ባለቤትነት ለመንፈግ የሚያደርጉት የአዋቂ ክልከላ ውጤት ነው፡፡
ምሳሌ:- ልጆች የፈለጉት የቤቱ ክፍል ላይ መጫወቻቸውን ማስቀመጥ (መዝረክረክ)፣ እቃዎችን መገለባበጥ፣ መንጠላጠል፣ ማቆሸሽ፣ የሚሰበር ዕቃ ካገኙ መስበር ፣እጃቸው ላይ ባገኙት እርሳስ፣ ከለር ከሰል ሊፕስቲክ ኩል ወዘተ ያገኙት ነገር ላይ መፃፍ መሳል ይፈልጋሉ! ወላጆች ደግሞ እነሱ የወሰኑላቸው ቦታ ላይ ብቻ እንዲጫወቱ ፣የፈቀዱላቸውን ዕቃ ብቻ እንዲነኩ ይፈልጋሉ …በዚህ ትግል መሃል ለቅሶው፣ ቁጣው፣ ማስፈራሪያው፣ ማስጠንቀቂያው ገፋ ካለም ቁንጥጫው ነጠላ ጫማው … ዓለም የማይዘግበው ጦርነት ሁሉ በየቤቱ ይኖራል! የወላጆችን ክልከላ ከልጆች ደህንነት እንዲሁም ከቤት ውበት አንፃር ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የሆነ ሆኖ ክልከላ የት ድረስ?
በተለይም በአበሻ ወላጆች ዘንድ በስፋት የተለመደ አንድ ጉዳይ አለ …ይሉኝታ ! እንግዳ ወደ ቤት ከመጣ ልጆች ቤት እንዳያዝረከርኩ፣ እንዳይንቀዠቀዡ ከባድ ማዕቀብ ነው የሚጣልባቸው! ይህም ከጨዋነት ይቆጠራል፡፡ እንግዳ የቤቱን ውበት፣ የልጆቹን ባህሪ መበላሸት ታዝቦን እንዳይሄድ እንፈራለን! አንዳንድ እንግዳ እንደውም አስተያየት ሁሉ ይሰጣል ‹‹አይ እነዚህን ልጆች አቅበጣችኋቸዋል፤ አሁን የእንትና ልጅ ገና እናቱ በዓይኗ ስትገለምጠው ነው እጅ በደረት አርጎ የሚቀመጠው....!›› ስለዚህ በእንግዶች ፊት ክብራችን ከፍ እንዲል፣ ከእንትናም እናት ላለማነስ፣ ልጆቹን በምንም ይሁን በምን ለጊዜው የእስር ቤት አይነት ክልከላ እንጥልባቸዋለን! የልጆች ተፈጥሮ ደግሞ አሳሽነት ነው፣ መፈለግ ነው መንካት ነው፣ መሞከር ነው! በደመነፍስ መንቀሳቀስ ነው ማዝረክረክ ነው …የፈለጉትን በፈለጉበት ጊዜ እንጅ በኋላ እንግዳ ሲሄድ የሚል ነገር አይገባቸውም! ይሄን ተፈጥሯቸውን ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውም መቋቋም አይችሉም! ልጆች ልጅነትን አይቋቋሙም!
እንግዳም ባይኖር ብዙ ወላጆች ቤታቸውን የሚያደራጁበት መንገድ ፈፅሞ ለልጆች የማይመች ነው! (የቤት ችግር እንዳለ ሆኖ) ገና ሲያረግዙ ለአራስ ጥየቃ የሚመጣውን ወዳጅ ዘመድ ታሳቢ በማድረግ፣ አልያም ራሳቸውን ስለሚያስደስታቸው፣ ወይም የሆነ ሰው ቤት ስላዩት ቆንጆ የቲቪ ማስቀመጫ ጠርዙ ከመሳሉ የተነሳ ዶሮ የሚያርድ … ጫፍና ጫፉ እንደጦር የሾለ በውድ ዋጋ ይገዛሉ፣ ትልቅ ፍላት ስክሪን ቲቪ ያስቀምጡበታል፣ ልጆች ቶሎ ያድጋሉ፣ ብዙዎቻችን እቃ የመቀየር አቅሙም ባህሉም የለንምና ቦታ እንኳን ሳይቀያየር ይደርሳሉ! በቀላሉ ስለሚደርሱበት ቲቪ ማስቀመጫው ላይ መንጠላጠል፣ ቲቪውን መንካት አስፈላጊ ከሆነም ባገኙት እቃ መኮርኮም ይፈልጋሉ! ከፈለጉ ደግሞ ያደርጉታል! ወላጅ የዕቃዎቹን ውድነት ከልጆቹ ነፃነት ያስቀድማል! በውድ ዋጋ የገዛው ሶፋ ላይ ሽንታቸውን ሊሸኑ ምግብ ሊያንጠባጥቡ …ወተት ሊደፉ ይችላሉ …ወላጅ በብስጭት ድፍት ሊል ምንም አይቀረውም! ችግሩ ከየት መጣ?
ቤታችሁ ውስጥ ከጥግ እስከ ጥግ ኤንትሬ ከነተሳቢው የሚያክል ሶፋ ትገጠግጣላችሁ፣ በዛ በኩል ብሔራዊ ሙዚየም የሚቀናበት ቡፌ በብርጭቆና ምናምን አጭቃችሁ ታቆማላችሁ... አየር አያሳልፍም እንኳን ሰው! …በዛ ላይ የአንዳንዶቻችን የቀለም ምርጫ እንኳን ልጆችን አዋቂ በድብርት የሚገድል ነው! ከዛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በልጆቻችሁ ላይ ታውጁና ሚስት ወጥ ማማሳያ፣ ባል ቀበቶ ይዛችሁ ትቆማላችሁ! የቤተሰብ “ኮማንድ ፖስት”!
ልጆች ላይ መጮህ፣ መምታት፣ ማስፈራራትን እንደ መከላከያ ይወሰዳል! የዚህ ሁሉ ችግር መነሻው ገና ከጅምሩ ልጆችን የቤቱ ባለቤት ሳይሆን ተጨማሪ እንደ ወላጆቻቸው ፍላጎት ብቻ የታዘዙትን እያደረጉ የሚኖሩ ፍጥረቶች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ልክ ባል ወይም ሚስት ለእነሱ የሚመቻቸውን የእቃ አቀማመጥ እንደሚወስኑ ሁሉ ለልጆቹንም ታሳቢ ያደረገ የእቃ፣ የከለር የአቀማመጥ ሁኔታዎችን አቅም በሚፈቅደው ማመቻቸት ግድ ይላል! ምክንያቱም …ልጆችን ማስቆም ይቻል ይሆናል፣ ልጅነትን ማስቆም ግን አይቻልም:: …ልጆች ፊታችሁ የቆሙ ትንንሽ ፍጥረቶች ሲሆኑ ልጅነት እነዚህን ትንሽ ፍጥረቶች ጦር ሰራዊት የሚያደርግ ውስጣዊ ባህሪ ነው! ዋናው ነጥብ (እንግዶች ሌላ እንግዳ ሆነው የሚሄዱበት ብዙ ቤት አላቸው…ልጆች ግን ልጅ ሆነው መኖር የሚችሉበት ብቸኛ ቤት ቤታቸው ብቻ ነው!) ያዝረክርኩ፣ ግን እንዴት እንደሚያስተካክሉ ሳትታክቱ አስተምሯቸው፣ ልጆች ዕቃዎቻችሁን እንዳያበላሹ ከምትጠነቀቁት በላይ ዕቃዎች ልጆቻችሁን እንዳይጎዱ ቀድማችሁ አስቡ ተጠንቀቁ! አመቻቹ! ሶፋ ያረጃል ይጣላል፣ ቲቪ ነገ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፤ ልጆች ግን በምንም የማይተኩ አስቸጋሪ፣ ‹ስማርት› እና ውብ ፍጥረቶች ናቸው!
ዛሬ ቀላል የሚመስላችሁ የልጆች ጨዋታ፣ ነገሮችን ለማወቅ መጓጓት፣ የነገ ማንነታቸው ላይ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አለው! መሳቢያችሁን ከፍቶ እንዳያይ፣ ቡፊያችሁን ከፍቶ የሸክላ ሰሐንና ብርጭቆ እንዳይሰብር በቁንጥጫና በጩኸት፣ በነጠላ ጫማና ቁንጥጫ እያሸማቀቃችሁ ያሳደጋችሁትን ልጅ፤ ‹‹ልጄ ሲያድግ ናሳ ነው የሚሰራው፣ ጨረቃን ነው የሚያስሰው…›› ትላላችሁ … ልጆች ማሰስን የሚጀምሩት ከጨረቃ አይደለም፤ ከቤት ነው! ዓለምም ህዋም ለልጆች ቤታቸው ነው፡፡ አዲስ ነገር መሞከርን የሚፈራ፣ ስህተትን የሚፈራ ይሄንና ያን ብነካ ጩኸትና ቅጣት ይከተለኛል በሚል ተሸማቆ ያደገ ህፃን፣ መፈለግ፣ ማሰስ፣ መሞከር ሳይሆን መደበቅ ነው የሚቀናው፡፡ ለዛ ነው አብዛኞቻችን ድብቆች ደንጋጭና ግልፅነት የሚያስፈራን፣ አዲስ ነገር ‹ነርቨስ› የሚያደርገን ሰዎች የሆነው! ሩቅ ሳትሄዱ አስተዳደጋችሁን ዙሩና አስታውሱ! አስተዳደግ!
ሳጠቃልለው (ጨዋታ ለልጆች ቀልድ አይደለም፣ ቤታችሁ መጥቶ ለሚሄድ እንግዳ ሳይሆን፣ ለልጆቻችሁ እንዲመች አድርጋችሁ አመቻቹ! ቤታችሁ የልጆቻችሁ ዓለም ነው! ዓለማቸውን ነገ ለማያስታውሳችሁ እንግዳ ይሁን ጎረቤት አትቀሟቸው!) ልጆች ያዝረከረኩትን ቤት ማየት የማይፈልግ እንግዳ ፣እዛ ፓርክ፣ ቤተ መንግስት፣ ሙዚየም ምናምን ሂዶ ይጎብኝ! አንዴ ልድገመው …ቤታችሁን ንፁህ ግን ልጆች እንዳሻቸው የሚያዝረከርኩት ይሆን ዘንድ መልካም ፈቃዳችሁ ይሁን! እናንተም እንግዳ ሆናችሁ ሰዎች ቤት ስትሄዱ ከወላጆቹ የበለጠ ለልጆች ምቹ እና ቀላል ለመሆን ሞክሩ …በሰው ዓለም አትኮፈሱ!
___________________________________________________
=================================================
ስለ “ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” (Settler Colonialism) ማን ምን አለ?
ጌታሁን ሔራሞ
የሀገራችንን የኋላ ታሪክ በተመለከተ ስለ “ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” የሚቃረኑ እሳቤዎች ከዚህኛውም ከዚያኛውም ጎራ ሲሰነዘር እንሰማለን። ለምሣሌ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ፡፡ (የምኒልክን ወደ ደቡብ አቅጣጫ መዝመትን ከ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” አገናኝተው ይተነትናሉ። በተቃራኒው ፕሮፈሰር መሳይ ከበደ፤ (በ”Survival and Modernization” መፅሐፋቸው) እና ዶ/ር ሀብታሙ መንግሥቴ ተገኘ (የ”በራራ-ቀዳሚት አዲስ አበባ” መፅሐፍ ደራሲ) የምኒልክ ዘመቻ በ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ”ነት ከተፈረጀ የኦሮሞው የሞገሳ፣ የገዳ እና የፍልሰት ታሪኮችም የ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” ይዘቶችን እንዳቀፉ ይሞግታሉ። በተለይም ሀብታሙ መንግስቴ በመፅሐፋቸው፤ (በራራ-ቀዳሚት አዲስ አበባ) ምዕራፍ ሰባት “የሰፈራ ቅኝ ግዛት፣ የባህል ድምሰሳና የዘር መሳሳት በዓለም ታሪክና በኢትዮጵያ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ስለ “ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” ያነሱት፣ እነ ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ ከሚያነሱት በተቃራኒው ነው።
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሌሎች የሀገር ውስጥም የውጭም ፀሐፍት ብዙ ብለዋል። በእኔ ዕይታ በሁለቱም ጎራ ያሉ ዕሳቤዎች ለውይይት መቅረብ አለባቸው የሚል እምነቱ አለኝ። ምክንያቱም በአካዳሚክም ሆነ በፖለቲካ ሊሂቃን የሚነገሩ ሐቲቶች ወደ ሕዝቡ ሲደርሱ፣ ትርጉማቸው እየተዛባ፣ ግጭቶችን የመቀስቀስ ዕምቅ አቅም አላቸው። እይታዎቹ ታች ወርደው ወደ ጠብ-ጫሪነት ከመቀየራቸው በፊት፣ (ተቀይረዋልም) ሚዛናዊነትን በተላበሰ መልኩ መነጋገር ወደ መፍትሔው አቅጣጫ ይወስደናል የሚል እምነቱ አለኝ።
ስለዚህም በቅርቡ “ስለ ‘ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ’ ማን ምን ብሎ ነበር?” በሚል ርዕስ፣ ከፅንሰ ሐሳቡም በመነሳት በሁለቱም ጎራዎች የተንፀባረቁ ሐሳቦችን ላስቃኛችሁ እሞክራለሁ። በነገራችን ላይ የ”ሰፈራ ቅኝ አገዛዝ” ፅንሰ ሐሳብ ከመደበኛው ቅኝ አገዛዝ ፅንሰ ሐሳብ እንደሚለይ ታምኖበት፣ በጥልቀት ጥናት መደረግ የጀመረው ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ነው።
=========================================================
ሙሰኞች፤ ”60 ለመንግስት፣ 40 ለእኛ” እያሉ ነው
ሙሼ ሰሙ
ሙስናና ሙሰኞች የመንግስትን መዋቅር መሳ ለመሳ ገጥመው፣ የራሳቸውን የአሰራር ስርዓት ዘርግተውና “ኮሚሽን” አደላድለው፣ ኪሳቸውን እያደለቡና ሀገር እያፈረሱ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው።
መፈክራቸውም 60 ለመንግስት፣ 40 ለእኛ (ሙሰኞች) እንደሆነም እየሰማን ነው። ሙስና ስጋ ለብሶ ነፍስ ገዝቶ በሕዝብና በመንግስት መሃል በኩራት መንጎማለሉ ሳያንሰው፣ የሚያከብረውና የሚፈራው ሕግ፣ የሚያሸማቅቀውና የሚያፍረው የሞራል መዳድል እንደጠፋም እየተገለጸ ነው።
ይህ እንግዲህ ቱባ ቱባ ሙሰኞች ሲዘከሩ የምንሰማው ወቅታዊ ትርክት ነው። በሙስና ከተጨማለቁትና በሕገ ወጥ መንገድ ሀብት ጠግበው ከሚተፉት ባለሃብቶችና አስፈጻሚ የመንግስት ጋሻ ጃግሬዎች የጥጋብና የፈንጠዝያ ዓለም ወረድ ሲባል፣ በአስተዳደራዊ በደልና በአገልግሎት እጦት በየእለቱ እየተንከራተቱና ደም እንባ እያለቀሱ ያሉ ዜጎች መኖራቸው ፈጽሞ የተረሳ ይመስላል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ሰዓት የማይፈጅ አንድ ተራ አስተዳደራዊ ጉዳይ ለማስፈጸምና አገልግሎት ለማግኘት ከቢሮ ቢሮ፣ ከአስፈጻሚ አስፈጻሚ መንከራተት፣ መረጃህ የለም፣ ሰነድህ ጠፍቷል፣ ነገ ተመለስ፣ አይመለከተኝም፣ የራስ ጉዳይ፣ ምን ታመጣለህ መባል፣ መንጓጠጥ፣ መገላመጥና የፈለክበት ሂድና ክሰስ መባል የእለት ከእለት ኑሯችን ሆኗል።
ሙስና በስልጣን ከመባለግና ስልጣንን ተገን አድርጎ ያልተገባ ጥቅም ከማግኘት ባሻገር ሰፊ የበደልና የግፍ ጉሮኖ መሆኑም ተዘንግቷል። የአሰራር ብልሹነት፣ አስተዳደራዊ በደል፣ ተገልጋይ ማጉላላትና ማንገላታት፣ በስራ ሰዓት አለመገኘት፣ የስራ መደብን ጥሎ መጥፋት የመሳሰሉት ኑሮህን እንድታማርርና እራስህንና ሀገርህን እንድትጠላ የሚያደርጉህ ግፎችና በደሎች የሙስና ዓይነተኛ መገለጫ መሆናቸው ከመዝገብ ተፍቋል። አስዳደራዊ በደሎችና ግፎች አብዛኛውን ሕዝብ የሚመለከቱና ከቱባ ሙሰኞችና አቀናባሪዎቻቸው ዘረፋ በላይ እጅግ የላቁ ጉዳት አድራሽና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተረስቷል ።
የሙስና ትግሉ ግብ ለቱባ ሙሰኞች አዳዲስ ኮሚቴ ከማቋቋምና መረጃ ከማሰብሰብ ባሻገር፣ ሰፋ አድርጎ ሊፈትሸውና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ አስቻይ (Enabling) ሁኔታዎቹ መታገል መሆኑ፣ ሰሚ ጆሮ ያጣ ጩኽት ነው።
ትኩረትና ትግል የሚሹ አስቻይ ( Enabling) ሁኔታዎች በጥቂቱ እንቃኝ፡
አንደኛው ለሙስና አስቻይ ሁኔታ ሳይሰሩ፣ ሳይለፉና ሳይደክሙ በዘረፋና በንጥቂያ መክበር የማያስጠይቅ መብት መሆኑ ነው። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ስር እየሰደደና ባህል እየሆነ የመጣው ሳይሰሩ፣ ሳይለፉና ሳይደክሙ ሆኖና መስሎ በመገኘት ብቻ ያዩትንና የሰሙትን ሀገራዊና ግለሰባዊ ሀብት፣ የኔ ነው በማለት መቀራመትን የሚያበረታታ አስተዳደራዊና ስነ ልቦናዊ አስቻይ ሁኔታ ስር እንዲሰድ መፈቀዱ ነው ።
ሁለተኛው አስቻይ ሁኔታ ጦርነቱ ነው። ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረትና ቀውስ ምክንያት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መዛበት፣ ጥቂት ስርዓት አልበኞች አጋጣሚውን ተጠቅመው በዘረፋና በሙስ እንዲሰማሩ፣ እንደፈለጉ እንዲፈነጩና እንዲከብሩ እድል መፍጠሩ ነው።
ሶስተኛው አስቻይ ሁኔታ የክልከላ፣ የእገዳ፣ የስርዓት መፋለስና የአሰራር መጨማለቅ የማን አለብኝነትና የቸልተኝነት ስር መስደድ ነው። ቤት መሸጥ፣ መሬት መሸጥ፣ መታወቂያና መንጃ ፈቃድ ማደስና ማውጣት፣ ንብረት ማዛወር የመሳሰሉት መሰረታዊ መብቶች መታገዳቸው በሕገ ወጥ መንገድ መታወቂያ በገፍ መታደሉ ወዘተ መገለጫዎቹ ናቸው። ይህ ተግባር ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር አቋራጭ እንዲፈልጉና መብታቸውን በጉቦ እንዲገዙ አድርጓል።
አራተኛው አስቻይ ሁኔታ :- የስልጣን ምንጭ ችሎታና ብቃት, ከመሆን ይልቅ ታማኝነት መሆኑ ነው። በታማኝነት የተገኘ ስልጣን አስተማማኝ አይደለም። የተሻለ ታማኝ እስኪመጣ ድረስ ካልሆነ በስተቀረ የስራ ዋስትናና በስልጣን ላይ መቆየት አስተማማኝ አይደለም። ለዚህ ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ሁላ በሙስና ተዘፍቆ፣ ዘርፎና አተራምሶ ነገን አስተማማኝ ማድረግ የአሽከሮች ምንዳ መሆኑ ነው።
የሙስና ትግል የትልልቆቹ አሳዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሕዝብ የሚያስመርሩና ደም የሚያስለቅሱ የትንንሾቹም ሙሰኞች ጉዳይ መሆን አለበት። የግል ዘርፉ፣ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት የተዘፈቁበት የሙስና ስፋትና ጥልቀት እንደ ሀገር የሰመጥንበትን የመበስበሰሰ ደረጃ የሚጠቁም ነው። የሙስና ትግሉ መጀመር ያለበት የትናንት ሙሰኞችን በማሳደድ ላይጨብቻ አተኩሮ ሳይሆን የነገ ሙሰኞችን ከወዲሁ ለመመከት በሚረዳ መልክ ለሙስናና ዘረፋ መንስኤ የሆነ ስነ ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አስቻይ ሁኔታዎችን በመታገል ጭምር መሆን አለበት።
ለማመን የሚያዳግቱ የዓለም ዋንጫ ታሪኮች (ከኡራጋይ የዓለም ዋንጫ እስከ ኳታር)
የአርጀንቲናው የስፖርት ሊቅ ሊቺያኖ ወርኒኪ፤ ከኳታር የዓለም ዋንጫ 2022 መክፈቺያ ጥቂት ቀደም ብሎ ባሳተመው “The Most Incredible World Cup Stories “ የተሰኘ መፅሐፉ ውስጥ ለማመን የሚያዳግቱ የዓለም ዋንጫ ታሪኮችን ብቻ አይደለም የሰነደው፡፡ ይልቁንም ከመጀመሪያው የኡራጋይ ዓለም ዋንጫ እስከ ኳታር ያሉትን አስደናቂ፤ አስደማሚ፣ አዝናኝና ትንግርት የሚመስሉ እውነታዎችንና ገጠመኞችንም ጭምር እንጂ፡፡
በ20 የተለያዩ ቋንቋዎች በታተመው በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ለማመን የሚያዳግቱ ታሪኮች መካከል፤ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ የ2010 የዓለም ዋንጫ ነፃ ትኬቶችን ለማግኘት ሲል፣ አዞዎች በሞሉበት ወንዝ ውስጥ ዘሎ መግባቱ፤ አንድ የኡራጋይ ተጫዋች በድንገተኛ የልብ ድካም ከተጠቃ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ መግባቱ፤ እንዲሁም የሩሲያ ጥንዶች “አሪፉ ተጫዋች ማነው፤ ሊዮኔል ሜሲ ወይስ ክርስቲያኖ ሮናልዶ?” በሚል ከተከራከሩ በኋላ መለያየታቸውን፤ የሚተርኩት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከሮይተርስ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ የዓለም ትልቁን የስፖርት ኹነት ከተለየ አንጻር እንደሚመለከተው የተናገረው ወርኒኪ፤ “ትናንሾቹ ታሪኮችም ቢሆኑ ዓለም ለእግር ኳስ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩ ናቸው” ብሏል።
ወርኒኪ እንዲህም ሲል ጽፏል፤ “እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም አንድ አልባኒያዊ ወደ ውርርድ ቤት ይሄድና፣ አርጀንቲና ቡልጋሪያን ታሸንፋለች ብሎ ይወራረዳል፤ሚስቱንም በቁማር ያሲዛል። የማታ ማታ ታዲያ ያቺ የተወራረደላት አገር 2ለ0 በሆነ ውጤት ተሸነፈች፤ እሱም ውርርዱን ተበላ፤ በቁማር ያስያዛትን ሚስቱንም በአሳዛኝ ሁኔታ አጣ::” ይሄ ለማመን የሚያዳግት ታሪክ ሳይሆን “ጉድ” ነው መባል ያለበት፡፡
ከ16 ዓመት በኋላ ደግሞ የአስተናጋጇ አገር የደቡብ አፍሪካ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ፤ የመጨረሻውን የዋንጫ ጨዋታ ሁለት ትኬቶች፣ ያልተለመደ የእብደት ድርጊት ለፈፀመ ሰው እንደሚሸልም ያውጃል፡፡ አሸናፊው ማን ቢሆን ጥሩ ነው? አዞዎች የሚርመሰመሱበት ወንዝ ውስጥ ዘሎ የገባ አንድ ሰውዬ ትኬቱን ወስዷል፤ይለናል ጸሃፊው፡፡
በእያንዳንዱ የአለም ዋንጫ አዲስ ምዕራፍ እየታከለበት የሚበለፅገው “The Most Incredible World Cup Stories“ መፅሐፍ፤ ያሁኑ ሦስተኛው ዕትም ሲሆን ፀሃፊው ከኳታር የዓለም ዋንጫም ገና ካሁኑ ትናንሽ ጮማ ወሬዎችን እያሰባሰበ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
“ከአድማዎችና ከሰብአዊ መብት ጉዳዮች አንስቶ አያሌ ትኩረት የሚስቡ ነገሮች አሉ” ያለው ወርኒኪ፤ “ከስፖርት ውጭ በእርግጠኝነት በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ማህበራዊ ኹነቱ በእጅጉ የሚያመዝን ይሆናል” ብሏል፡፡
የአለም እግር ኳስ አድራጊ ፈጣሪ የሆነው ፊፋ፣ በወግ አጥባቂዋ የሙስሊም አገር ስቴዲዮሞች ቢራ እንደማይሸጥ ማወጁ፣ ለወርኒኪ ቀጣይ ምዕራፍ እንደ መነሳሻ ሊያገለግለው እንደሚችል ሮይተርስ በዘገባው ጠቆም አድርጓል፡፡
የ53 ዓመቱ ሉቺያኖ ወርኒኪ የተወለደው በአርጀንቲና ቦን አይረስ ሲሆን ከሳልቫዶር ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት ተመርቋል፡፡ ለ20 ዓመት ያህልም በ”Argentine University of Enterprise (UADE)” እንዲሁም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ጋዜጠኝነትን አስተምሯል፡፡ በበርካታ አገራትም መጣጥፎችን አሳትሟል፡፡ ከ20 በላይ የእግር ኳስና የስፖርት መፃህፍት ደራሲም ነው፡፡ ከመፃህፍቱ መካከልም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-
The Most Incredible world cup Stories(2010)
The Most Incredible World cup Stories(2012)
The most Incredible World cup Stories(2013)
Doctor and Champion (Autobiography of Carlos Bilardo-2014)
The Most Incredible Copa Libertadores Stories(2015)
Round Words (2016)
Why is Football played eleven against eleven? (2017)
Matador ( Autobiography of Mario Kempes -2017)
Duel Never Seen (2019)
Inside DIego (2021)
Football Drops (2022)
Dark Goals(2022)
ሁዋዌ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና እየሰጠ ነው
• ሥልጠናው 5G፤ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን--ያካትታል
• ሴት መምህራንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሥልጠናው ተሳትፈዋል
የትምህርት ሚኒስቴር ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር፤ “ሴቶችን በዲጂታል ክህሎት ማብቃትና የሴቶች አመራርን በቴክኖሎጂ መደገፍ” በሚል መሪ ቃል፣ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና ለሴት መምህራን መሰጠቱ ተገለጸ።
የመጀመሪው ዙር ስልጠና ከህዳር 12 እስከ ህዳር 14 ቀን 2015 የተካሄደ ሲሆን ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ሴት መምህራን በስልጠናው መሳተፋቸው ታውቋል። ሁለተኛው ዙር ስልጠና ህዳር 15 የተጀመረ ሲሆን ስልጠናው በዲጂታል ክህሎት (5G፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ክላውድ) እንዲሁም በሴቶች አመራር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ፣ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሁዋዌ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የሴቶችን የኑሮ ደህንነት በማሻሻል ረገድ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለውን ፋይዳ እየመረመረ ነው ብለዋል።
“ሴቶች በቴክኖሎጂ እንዲሳተፉ ለመርዳት እንዲሁም ዕምቅ አቅማቸውን እንዲያወጡና ህብረተሰባችንን ወደላቀ ብልፅግናና ፍትሃዊ መጪ ዘመን ይመሩ ዘንድ የበለጡ ዕድሎችንና መድረኮችን ለመክፈት ቁርጠኞች ነን” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ትምህርት ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ ዘላለም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ትምህርት ሚኒስቴር በICT ዘርፍ በሰው ሃብት ልማት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የትምህርት ዘርፉን የሚያግዝ ተግባራዊ ሥልጠና ለማግኘትም ሁዋዌን ከመሳሰሉ የግል ኩባንያዎች ጋር እንደሚሰሩ በአጽንኦት ተናግረዋል። ሁዋዌ ለሴቶች መምህራን ሥልጠና በመስጠት ላደረገው ትብብርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አንዳንድ ሰልጣኞች እንደተናገሩት፤ የክፍል ውስጥ የማስተማር ሂደቱ ይበልጡኑ ንድፈ-ሃሳባዊ በመሆኑ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ተግባራዊ ስልጠና ወሳኝ ነው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2008 አንስቶ ሁዋዌ በርካታ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ መርሃ ግብሮችንና ውድድሮችን በዓለማቀፍ፣ በክልላዊና አገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የጀመረ ሲሆን ከእነሱም መካከል፡ “የስኮላርሺፕ መርሃግብሮች፤ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር፤ ሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚ፤ ሁዋዌ ዴቨሎፐርስ ትሬይኒንግ፤ ሁዋዌ ክላውድ ዴቨሎፐር ኢንስቲቲዩት፤ ውመን ቴክ እና ቴክኖሎጂ ፎር ኢጁኬሽን” ይጠቀሳሉ፡፡
በተመሳሳይ ዜና፤ የ2022 “Seeds for the Future” መርሃ ግብር በኢትዮጵያ፣ ከህዳር 12 እስከ ህዳር 19 ቀን 2015 የተካሄደ ሲሆን፤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ60 በላይ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል።
መርሃ ግብሩ የ8 ቀናት የኦንላይን ስልጠና ሲሆን ከተማሪዎቹ የ15 ሰዓታት ሙሉ ትጋትን የሚጠይቅ እንደሆነ ተጠቁሟል። ሥልጠናው በቁልፍ ቴክኖሎጂዎች (5G፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ላይ መሰረታዊና ከፍተኛ ደረጃ ኮርሶችን የሚያካትት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
“ክፉ ደጉን ያየን ነንና ጎረቤት ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” (“ማለባበስ ይቅር”)
ከዕለታት ከአንድ ቀን ዘጠኝ ጓደኛሞች ወደ አንድ ሩቅ አገር ለመሄድ መንገድ ይጀምራሉ። ብዙ ርቀት እንደሄዱ ይመሽባቸዋል።
አንደኛው፤
“ጎበዝ፤ ከዚህ ወዲያ ከቀጠልን ጨለማው ይበረታብናል። ስለዚህ እዚህ ተኝተን እንደር” አለ።
ሁለተኛው፤
“ጥሩ ሀሳብ ነው። ግን ደህንነታችን ለመጠበቁ ምን መተማመኛ ይኖረናል?”
ሦስተኛው፤
“በተራ በተራ የሚጠብቅ ሰው እንመድብና ተረኛው ሲደክመው ቀጣዩን ጠባቂ ቀስቅሶ ይተኛ” አለ።
ሁሉም በመጨረሻው ሀሳብ ተስማማና “ስለ አተኛኘት ቅደም ተከተል እጣ እናውጣ” ተባባሉ። በወጣባቸው እጣ መሰረትም ተኙ።
ሌሊት ላይ አንድ የመቆረጫጨም ድምጽ ተሰማ።
“የምንድን ነው የሚሰማው ድምጽ” ተባባሉ።
ከዳር የተኛው ሰው መለሰ፡-
“ጎበዝ ዝም ብላችሁ ተኙ፤ አያ ጅቦ እኔን እየበላ ነው!” አለ።
አያ ጅቦ ወደሚቀጥለው ተረኛ ተሸጋገረ።
በዚህ ሁኔታ ሁሉም “ዝም በሉ” እያሉ፤ ዐይናቸው እያየ ተበልተው አለቁ ይባላል!
***
በየአሮጌው መመሪያና ህግ፣ ያለ አንዳች ማሻሻያ እየተጎዳዱ መገዛት ከጀመርን ብዙ ሰነበትን። አዲስ አውጥተናል ብንልም፤”አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን” የሚባለውን አይነት ነው (Old wine in a new bottle እንዲል ፈረንጅ)
መንግስትና መንግስት፤ በተቀያየረ ቁጥር ህዝብ ቢወድም ቢጠላም፣ ያንን ተቀብሎ መገዛት እጅግ ከመለመዱ የተነሳ እንደተፈጥሮ ህግ መወሰዱ፣ እንደ ፀሀይ መውጣትና መጥለቅ ከሆነም ሰንብቷል።
በመካከል “ይሄኛው መንግስትና ህግ አይሻኝም” የሚል ግለሰብ ወይም ቡድን አሊያም ፓርቲ ቢወለድ፤ ወይ ይታሰራል፣ ወይ ይወገዳል አሊያም ስርዓተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል። ከታሪክ እስከ ዛሬ ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ ከባንዳ እስከ ዘመናዊ አድር-ባይ፣ አሸርጋጅና አቀንቃኞችን የፈሰፈልነው፣ በዚህ “ጥበብ” እና “ዘዴ” ነው። ሌላው ቢቀር በጉርሻ ወይ በንክሻ “የሚባለውን ፍልስፍና ማንም ጅል አይስተውም ( Carrot and stick እንዲሉ)። በዚህ መልኩ ሲታሰብ እያንዳንዱ መንግስት ሊፈተሽ ይገባዋል ማለት ነው።
በተለይም አሁን ከመደብ ፖለቲካ ይልቅ የብሔር ብሔረሰብና ሐይማኖት እንደ ዘመን አመጣሽ ዘፈን በሚቀነቀንበት ሰዓት፣ የፖለቲካው አካሄድ እጅግ እየተወሳሰበ መምጣቱን ከነትርፍና ኪሳራው ለማስላት ከባለኪዮስክ ትንተና (Shop-keeper’s analysis) የበለጠ ስሌት አይጠይቅም። “ማንኛውም መሪ እበልጥሃለሁ” በሚል እሳቤ ሲያምታታ፣ ቀላል የዓሳ መረብ ውስጥ ሲገባ ታገኘዋለህ ይላሉ ጸሐፍት። የእኛም አገር መሪዎች ታሪክ ይሄን የሚያጸኸይ ነው። ይሄንን ለማየት የፖለቲካ ሳይንቲስት ማማከርም፣ አዋቂ-ቤት ሄዶ መስገድም አይጠይቅም!
በኢትዮጵያ አገራችን ከተማሪና አስተማሪ ትግል ጋር መተዋወቅ ትምህርት ቤት መግባትን አይጠይቅም። እንዳሁኑ ጊዜ 13,000 ተማሪ የተንሳፈፈበት ዘመን ግን ኖሮ አያቅም። ሚኒስትሩም ያሳዝናሉ። የትምህርት ስርዓት ከተጀመረ ፊደል ከተቆጠረ ጀምሮ፣ ይህ ሁኔታ አብሮን የኖረ ነው። አንዳንድ መሪዎቻችንም “እጁን እኪሱ ከትቶ፣ ባዶ ኪስ የሚያገኝ መምህር ከእንግዲህ አይኖርም” ብለውም ነበር። ሆኖም ዛሬም ከደሞዝ ጥያቄ እስከ ሥራ ማቆም አድማ ድረስ ሲገፋ እየታዘብን ነው! የሚገርመው ይህንኑ መሰል ጥያቄ ለወቅቱ ትምህርት ሚኒስትር ቀርቦ እንደነበር መታወሱ ነው። የታሪክ አዙሪት! ጥናቱን ስጠን!
እውነቱን ለመናገር የአምባ-ገነን መሪዎች ዴማጎጂም ተለይቶን አያውቅም። እነ ሂትለርስ እንደ ጎብልስ ያሉ አማካሪዎች ነበሯቸው። የእኛስ እነማን ይሆኑ? ወጣ ወረደም ያለን አማራጭ ከዕለታት አንድ ቀን ስለ ኤች አይ ቪ እንዳስጠነቀቅነው፡-
“ክፉ ደጉን ያየን፣ ነንና ጎረቤት
ያንተ ቤት ሲንኳኳ፣ ይሰማል እኔ ቤት!”
የሚለውን ስንኝ እንደግመዋለን!
ነግ በእኔ ነው ጎበዝ!! ትምርታችንን ይግለጥልን!
አቶ ስብሐት ነጋ "ወደ ውጪ አገር እንዳልወጣ ታገድኩ” ሲሉ ፖሊስን ከሰሱ
በመንግስት ምህሪት ከእስር ተለቀው የነበሩት የህውሃት መሥራችና አመራሩ አቶ ስብሐት ነጋ ለህክምና ወደ ውጪ አገር እንዳልሄድ ከህግ ውጪ በፌደራል ፖሊስ ተከለከልኩ ሲሉ ክስ አቀረቡ።
አቶ ስብሐት ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ መሰረታዊ መብቶች ጉዳዮች ችሎት ትናንት ባቀረቡት ክስ እንዳመለከቱት፤ “ለህክምና ወደ ውጪ አገር እንዳልሄድ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከቦሌ አየር ማረፊያ እንድመለስ ተደርጌአለሁ” ብለዋል። አቶ ስብሐት ነጋ በጠበቃቸው አማካኝንነት ባቀረቡት ክስ ላይ እንዳመለከቱት፤ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመቻቸውን ህጎች ባልተከተለና በህገ-መንግስቱ የተቀመጠውን የዜጎችን በነፃነት መንቀሳቀስ መብት በሚጋፉ መልኩ ፍርድ ቤት ሳያዝ ፖሊስ ከስልጣኑ ውጪ የጉዞ እገዳ እንደጣለባቸው ተጠቁሟል።
የአቶ ስብሐት ነጋን ክስ የተቀብለው ፍ/ቤቱ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ፖሊስ መልስ ባለማቅረቡ ሳቢያ መልስ የመስጠት መብቱ እንዲታለፍ ብይን ሰጥቷል። በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠትም ለመጪው ረቡዕ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ሄርቬ ሚልሐድ፤ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ
በሥራ አመራር መስክ የካበተ ልምድ እንዳላቸው የተነገረላቸው የ60 ዓመቱ ፈረንሳዊ ሚስተር ሄርቬ ሚልሐድ፤ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በካስቴል ግሩፕ መሾማቸው ተገለጸ፡፡
ሚስተር ሚልሐድ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አህጉሮች በሚገኙ በርካታ አገራት ከሚሠሩ ዳኖኔ ግሩፕን ከመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ያዳበሩ ሲሆን፤ በዳኖን ግሩፕ ብቻ ለሃያ ዓመታት የኦፕሬሽንስ ም/ፕሬዚዳንት (WW VP Operations) እንዲሁም ለአልጀሪያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡
በመቀጠልም የl’Européenne d’Embouteillage ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ እንዲሁም የጃፓን መጠጦችና አልኮል ኩባንያ የሳንቶሪ (Suntory Group) አካል የሆነው የኦራጂና ሳንቶሪ ፈራንስ (Orangina Suntory France (OSF) የኦፕሬሽንስ ም/ፕሬዚዳንት (VP Operations) በመሆን 650 ሠራተኞችን ያቀፉ አራት ፋብሪካዎችን እንደመሩ፤ ኩባንያው ለአዲስ አድማስ የላከው መግለጫ ያመለክታል።
ሚስተር ሚልሐድ የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን እንደ አዲስ ነድፈው የተገበሩ፣ ለስኬታማ ሥራ አፈፃፀም፣ የደንበኞች አገልግሎትና ወጪ ተገቢ ትኩረት የሚሰጡ፣ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ድርጅቶች የሥራ ቅልጥፍናን ከሠራተኞች ደህንነት ጋር ባጣጣመ መልኩ አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የቻሉ የሥራ መሪ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
በሚያዝያ 2010 ዓ.ም ካስቴል ግሩፕን ከተቀላቀሉ በኋላም፣ ሶዲብራን (ኮትዲቯር)፣ ኤስኤቢሲን (ካሜሩን) እና የመካከለኛ አፍሪካውን (Centrafrique) MOCAF በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
በቅርቡ ሚስተር ሚልሃድ የካስቴል ማላዊ ሊሚትድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን ላለፉት አራት አመታት ያገለገሉ ሲሆን ለድርጅቱ ባከናወኑት ታላቅ ሥራ “ድርጅቱን ከመዘጋት ያዳነ ሥራ አስኪያጅ” የሚል ስያሜ መቀዳጀታቸው ታውቋል፡፡
በተለያዩ ባህሎች ውስጥ አልፈው ካካበቱት ልምድና ለሠራተኞች ደህንነት እንዲሁም ለማኀበራዊ ኃላፊነት ሥራ ከሚሰጡት ትኩረት አንፃር፣ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፣ የቆየውን የቢጂአይ ኢትዮጵያ ስኬታማ የንግድ ሥራ ጉዞ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የማህበረሰብ ድጋፍን ባህል አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
“አዲሱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቢጂአይን የተቀላቀሉበት የአሁኑ ወቅት በንጽጽር እጅግ ምቹ ሊባል የሚችል ነው፤ ከምክንያቶቹም መካከል ዋነኛው በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማብቃቱን ተከተሎ፣ በአገር ደረጃ የሰላም ተስፋ ማንሰራራቱ ሲሆን እንደ ድርጅትም ለዓመታት ሥራ ፈትቶ የቆየው የራያ ቢራ ፋብሪካ ሥራ የሚጀምርበት ዕድል መገኘቱ፤ እንዲሁም ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ ቢራ ፋብሪካን መግዛቱ፣ ተጠቃሽ ናቸው።” ብሏል ኩባንያው በመግለጫው፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሚስተር ሚልሃድን “እንኳን ደህና መጡ” በማለት በደስታ መቀበሉን የጠቆመው መግለጫው፤ በዓለም አቀፍ መጠጥ ንግድ ካካበቱት የረዥም ጊዜ ዘርፈ-ብዙ ልምድ ለመጠቀም መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ላለፉት 25 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ የቆየ ደርጅት ሲሆን መቶ ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ብቁና የተገባ ወራሽ መሆኑ ይታወቃል።
‹‹የፈረንጅ ሚስት››
ደራሲ፡- እስከዳር ግርማይ (የ‹‹ሰውነቷ›› ፊልም ደራሲ ተዋናዪትና ፕሮዱዩሰር እንዲሁም የ‹‹ጥቁር እንግዳ›› ፊልም ፕሮዱዩሰርና ተዋናዪት)
ሒሳዊ ዳሰሳ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ
ንቁ፣
……ብቁ፤
ቁጡ፣
…...ቅንጡ፤
ጥንቁቅ፣
……ምጡቅ፤
ድንብልቅ፣
……ፍልቅልቅ፤ (ለእስከዳር ግርማይ)
መነሻ፡-
ሪዛሙ ደራሲ በርናንድ ሾው ‹‹Major Barbara›› በሚል ድርሰቱ አንዲት ልባም ሴት አስተዋውቆናል። በበኩሌ የበዓሉ ግርማ ሴቶችም ለእኔ ጎምቱ ናቸው፤ እነ ሒሩት፣ ሉሊት፣ ፊያሜታ…
…ካለፈው ዓመት (2014 ዓ.ም.) አንስቶ የሴት ደራሲያን ቁጥር እየተበራከተ መምጣት ለሥነ-ጽሑፋችን ጉልህ አበክሮ ይኖረዋል፤ በጣም ደስ ተሰኝቼአለሁ፤ ለመሆኑ ሴት የሌለችበት ነገር ምኑ ይጥማል?...
….ከእነዚህ መካከል እስከዳር ግርማይ አንዷ ናት፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?›› በተነበበ በወራት ልዩነት ‹‹የፈረንጅ ሚስት››ን አስነበበችን፤ ለአሁን ስለ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› እናውጋ፡-
‹‹የፈረንጅ ሚስት›› በተሰኘ ድርሰት እስከዳር ግርማይ በፈረንጅ ሚስትነት - የእራስዋን ተመክሮዎች፣ ገጠመኞች አሳዛኝ ወላ አስደሳች ቀናት፣ ሞግታ የረታችባቸውን አጋጣሚዎች - ከሌሎች - ከወዳጅ ጓደኞችዋ (ከፈረንጅ ሚስቶች) ጋር እያጣቀሰች የተረከችበት ድርሰት ነው፤ ቋንቋው ግልጽ ግና ውብና ትረካው ፈጣን ድርሰት ነው፤ ሳነበው እንዲህ ሆነ፡-
1ኛ. ነገረ መቃን/Frame-work - አንድን የድርሰት ወላ የጥናታዊ ጽሑፍ ሀሳብ ለማስኬድ መቃን ሁነኛ ዘዴ ነው፤ ፎቶ በመቃን ሲሆን ውበት ይኖረዋል። እስከዳር የታላቁን ባለቅኔ የጸጋዬ ገ/መድኅንን ‹‹አድባር›› የሚል ግጥምና ከቲያትሮቹ መካከል ደግሞ ‹‹ማነው ምንትስ?›› የሚል ሴቶችን የሚያበቃ ሀሳብ ላይ ተመርኩዛ፣ ወይም መቃን አድርጋ በመገልገል ሀሳቧን ትተርካለች። በእርግጥ ድርሰቱ በተለያዩ ገጠመኞች፣ ትንታኔዎች፣ መዘርዝሮችና ምሳሌዎች የተሞላ ቢሆንም ሲቋጭ ከመቃኑ ፈቅ አይልም፤ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ አበክሮ እንዳላቸው ይጠቁማል የሚል ዕምነት አለኝ። አልቆጨኝም፤ ረክቼአለሁ!!
2ኛ. ነገረ ጥናታዊ ጽሑፋዊነት - ድርሰቱ ለቀለም ትምህርት ብሎም ለዓለም-አቀፍ ንባብ መዋል የሚችል ጥናታዊ ጽሑፍ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ደራሲዋ ተሳታፊ ቀጂ እና የጥናቱ አካል በመሆን /participant observant/ በፈረንጅ ሚስትነት የገጠማትን ዕክል፣ መድሎ፣ ኢ-ፍትሕና ሌላም ነገር ትተርካለች፤ ትረካው ደግሞ በሁኔታዎችና በሰዎች አኳኋን ላይ መሠረት ያደረገ - interpretive analysis ነው (እመለስበታለሁ)። እናም ድርሰቱ ሴቶችን በተመለከተ ለሶሾሎጂ፣ ለሥነ-ልቡና፣ ለምጣኔ-ሀብትና ለሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ሁነኛ ምንጭ በመሆን ያገለግላል ብዬ አምናለሁ። ‹‹Challenges that Hampers Yeferenj Mist›› በሚል ርዕስ ለዓለም እንደምታስነብብ አልጠራጠርም።
3ኛ. ነገረ ቁጣ - በወንዴ ጾታ በኩል ትክክል የሚመስሉ ግና መረንና መቀጮ የሆኑ ድርጊያዎች፤ በትንሹ አላስፈላጊ፣ ወይ፣ መናኛ፣ ወይ፣ ክብረ ነክ ቃላት አጣጣላችን ምን ያክል የሴትዋን መንፈስ እንደሚያስቆጣ፣ አልፎም ጫና እንደሚያሳድርባት የሚያስገነዝብ ድርሰት ነው፤ መረንና ፈር ከሳቱ አባባሎች እስካልተቆጠብን ድረስ የሴቶቹን ሥነ-ልቡና እንደምናለምሽ የሚያስጠነቅቅ ድርሰት ነው፤ ለምሳሌ፡-
በገጽ፡- 23፣ 34 እና በሌሎች የቀረቡ ተረኮችን ማየት ይቻላል።
4ኛ. ነገረ ትንተና/interpretive analysis - በqualitative research መስክ ተመራጩን የትንተና ዘዴ (interpretive analysis) በመጠቀም፣ የሰዎችን ፊት በመፈተሽ ብሎም የቃላት አጣጣልን ከግምት በማስገባትና ከሁኔታው/ከጉዳዩ በማናበብ የሚከናወን ትንተና ማለት ነው፤ ለምሳሌ፡-
በገጽ 32፣ 33 ላይ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር የምታደርገውን ውይይት፣ ትንተና እና ሌሎችንም ማየት ይቻላል፤
5ኛ. ነገረ ፍካሬ - እውነትን በሥነ-ውበት መፈከር የዚህ ድርሰት በጎ ጎኑ ነው፤ አንዳንድ ውበታም ቃላት፣ ገላጭ ሐረጋትና ዓረፍተ-ነገሮች በብዛት ይስተዋላሉ። የዓረፍተ ነገር አጀማመርዋም ቢሆን መሳጭና ሁሉን አቀፍ ነው።
ማሳያ፡- ገጽ 36 ‹‹የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ከባለቤቴ ጋር ተፋትተን ንብረት ክፍፍል ውስጥ ብንገባ፣ ባለቤቴ መቀመጫዬን ከራሱ ድርሻ ንብረት ጋር ሳይደምረው አይቀርም….››
6ኛ. ነገረ ሚዲያ እና ክብረ-ነክ ጋዜጠኞች - በድርሰቱ አንዳንድ ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያዎች ክፍተት ተቃኝቷል፤ መረንና ለሙያቸው ክብርና ግንዛቤ የሌላቸው ጋዜጠኞች ምን ያክል የሴትዋን መንፈስ እንደሚያስቆጡ ያሳስባል፤ ለምሳሌ፡-
ከገጽ 32-41 ያለውን ውይይት መመልከት ተገቢ ነው።
7ኛ. ነገረ ተጽዕኖ - ድርሰቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ (በውጭም በአገር ውስጥም) በሚገባ ያስቃኛል፤ የሞራል፣ የአካል፣ የመንፈስ፣ ኢ-ፍትሐዊነት…ወዘተ ጫናዎች በፈረንጅ ሚስቶች ላይ ሲደርሱ እናያለን።
8ኛ. ነገረ ተራ ግምት/wild-guess - የውጭ አገር ብሎም የአገራችን ሰዎች ለፈረንጅ ሚስት ያላቸውን ተራና መናኛ ግምት ከዚህ ድርሰት መገንዘብ ይቻላል፤ የፈረንጅ ሚስት በራስዋ ጥረት እንደማትኖር አድርጎ መሳል አንዱ ክፍተት እንደሆነ በመረጃ አስደግፋ ትሞግታለች።
9ኛ. ነገረ ሙግት/discourse - በዚህ ድርሰት ያልተገባ ንግግርና ተራ ግምት ሲገጥማት ከተሳሳተው ግለሰብ ጋር ቀጥተኛና ግልጽ ውይይት በማድረግ የተሳሳተ ግንዛቤን መቀየር እንደሚቻል ያሳየችበት መጽሐፍ ነው፤ ሴቶች በምክንያታዊነት ላይ ተንተርሰው ክርክርና ሙግት ሲገጥሙ ታስቃኛለች፤ ሴቶችን ማብቃት ነው ይኼ! ለአብነት፡-
ገጽ 74 ላይ ደራሲዋ/ተራኪዋ ከአንድ የአረብ ሰው ጋር ስትሞግት ወላ ስታሳምን እናገኛለን!
10ኛ. ነገረ መሰናሰል እና የፍሰት ወጥነት - ድርሰቱ ከምዕራፍ ምዕራፍ የተያያዘና በቂ መዘርዝሮችን ያቀፈ ነው። በተጨማሪም ምሳሌዎችና ምዕራፎቹ ከዋናው ሀሳብ የማይጋጩ ናቸው፤ ረክቼአለሁ!!
11ኛ. ነገረ ምክረ-ሀሳብ/recommendations - ደራሲዋ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ክስተቶች ወ ገጠመኞች ተንትና ካቀረበች በኋላ፣ ‹ከእጄ ውጪ› ብላ አትገላገልም፤ ለጠቀሰቺው ችግር መፍትሔ ይሆናሉ ብላ ያሰበችውን (ሚዛን የሚደፉ) የምክር ሀሳቦችን ትለግሳለች። እንዲያ ይሻላል!!
መውጪያ፡-
በጥናታዊ ጽሑፍ አንድ የተለመደ አባባል አለ፤ ‹‹Publish or Perish›› ይሉት ብሒል ነው ታዲያ። የምርምር ወላ የድርሰት ሥራዎች ለውጥ እንዲያመጡ ከተቻለ ለኅትመት ማብቃት፤አሊያ ወዲያ መጠቅለል። በአጠቃላይ፣ አንድ ድርሰት ወላ ጥናታዊ ጽሑፍ በተደራሲው ወይም በተጠኚው ላይ ፈጣን አሉታዊ ጫና ማሳደር ከቻለና ትክክለኛውን መንገድና መፍትሄ እንዲመርጥ ካስቻለ ግቡን መቷል ማለት ይቻላል፤ ‹‹የፈረንጅ ሚስት›› በእራሴ ላይ ፈጣን እርምጃ እንድወስድ አድርጎኛል፤ ምናልባት ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ሚስቶች ወላ ለሴቶች የነበረኝን ተራና መናኛ ግምት እንድከልስና ትክክለኛውን እሳቤ እንድፈትሽ አስችሎኛል ብዬ ብናገር ከሕሊናዬ አልጋጭም!!
ታማሚዎቿን በዳንስ የምታነቃቃዋ ነርስ
በኬንያ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የተኛ ህፃን እየደነሰች ስታነቃቃ የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ በቲክቶክ መልቀቋን ተከትሎ፣ በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆናለች፤ የ22 ዓመቷ የነርሲንግ ተማሪ ሉክሬስያ ሮባይ፡፡
ቪዲዮው በኪታሌ ካንቲ ሪፈራል ሆስፒታል በሥራ ላይ ሳለች የተቀረፀ መሆኑን ተናግራለች- ሮባይ። በሆስፒታሉ ውስጥ ህመምተኞችን እየዞረች ስትጎበኝ አንድ የተከፋና የተደበተ ህፃን ማግኘቷን የምታስረዳው ወጣቷ ነርስ፤ በተወዳጅ የህጻናት ዘፈን እየደነሰች ልታነቃቃውና ልታስደስተው መወሰኗን ትገልጻለች።
“ታማሚው እግሩ ላይ ስብራት ደርሶበት ወደ ሆስፒታሉ የገባ ሲሆን የፈራ ይመስል ነበር። ወዲያው ሙዚቃውን ከሞባይል ስልኬ ላይ በማጫወት መደነስ ጀመርኩኝ፤በዚህም ህጻኑ ተነቃቃ። እንደ ነርስ ህመምተኞቼ ደህና መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብላለች፤ ሮባይ፡፡
ወጣቷ የጤና ባለሙያ የዘየደችው መላ ሰርቶላታል። ግትር ብሎ ተቀምጦ የነበረው በሽተኛ ህፃን፤ እጆቹንና እግሮቹን ባለበት ሆኖ ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ፊቱም በፈገግታ ፈክቷል፤ ዕድሜ ለዳንሰኛዋ ነርስ፡፡
በዚህም አስደማሚ ተግባሯ የአያሌ ኬንያውያንን ልብ አሙቃለች፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት በቲክቶክ የለቀቀችው ይኼ አጭር ቪዲዮ፤ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዕይታዎችንና በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶችን አግኝቶላታል፡፡
ፎለፎሏ ነርስ፤ ዳንስ በጥልቅ ስሜት የምትወደውና በዙሪያዋ ለሚገኙ ሁሉ የተስፋ መልዕክት ለማስተላለፍ የምትጠቀምበት ጥበብ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡
“ለዳንስ ጥልቅ ፍቅር አለኝ። አብሮኝ የተፈጠረ ነው። በዚህ ህይወታችን ድንቅ ነገሮችን የሚያበረታታ ህብረተሰብ ወይም ባህል አካል መሆን ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።” ብላለች ሉክሬስያ።
የሉክሬስያ አለቃ የሆነችው ቤቲ ናልያካ፣ እቺ ተማሪ ነርስ በልምምድ ጊዜያቶቿ ላሳየችው ብቃትና ሰብአዊ ተግባር አወድሳታለች፡፡
“ሮባይ ጎበዝ ተማሪ ናት። አንድ ስራ ስንሰጣት በቅጡ እንደምታጠናቅቀው እርግጠኞች ነን። ምንጊዜም ፈታኝ ጉዳይ ሲገጥማት ጥያቄ የምትጠይቀውና ከሠራተኞቹ ጋር የምትተባበረው እሷ ናት። ለእርሷ የወደፊቱ የነርሲንግ ሙያ ብሩህ ነው።” ስትል ናልያካ መስክራለች፡፡
ነርስነት የዕድሜ ዘመኗ ጥልቅ ፍላጎት እንደነበር የምትገልጸው ሉክሬስያ፤ ሁልጊዜም ሰዎችን መርዳትና ከስቃያቸው መገላገል ትሻ እንደነበር ጠቁማለች፡፡
“ሁልጊዜም መስራት የምፈልገው ነገር ነው። ከውስጤ ነው ፈንቅሎ የወጣው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የህክምና ባለሙያ ለመሆን እፈልግ ነበር። የታመሙትን መንከባከብ እሻ ነበር። ሌላ ሙያ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም…አብሮኝ የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ” ብላለች።
ያለ ወላጅ ያደገችው ሉክሬስያ፤የትምህርት ጉዞዋ በብዙ ውጣውረዶች የተሞላ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ እዚህ ደረጃም የደረሰችው በነፃ የትምህርት ዕድልና በስፖንሰርሺፕ ነው፡፡
የትራንስ ንዞያ ካንቲ አስተዳደር የቀራትን የአምስት ወር የነርሲንግ ኮርስ ክፍያ ለመሸፈን ቃል የገባላት ሲሆን፤ ትምህርቷን ስታጠናቅቅም ለህመምተኞቿ በፍቅር በደነሰችበት ሆስፒታል ውስጥ እንደሚመድባትም አረጋግጦላታል። በዚህም የ22 ዓመቷ ወጣት ህልም እውን ይሆናል ብሏል፤የኬንያው ሲቲዝን ቴሌቪዥን።