Administrator

Administrator

   *ዋና ዳይሬክተሯን ተክተው ይሰራሉ ተብሏል

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ፣ በአለማቀፍ ተቋማት የረጀም አመታት የከፍተኛ አመራርነት ልምድ ያላቸውን ኢትዮጵያዊውን አቶ ደረጀ ወርዶፋን የተመድ የስነ-ህዝብ ፈንድ የፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አድርገው መሾማቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው፤በቅርቡ የስነ-ህዝብ ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙትን የፓናማ ተወላጇን ናታንያ ካኔም ተክተው እንደሚሰሩም ነው የተገለጸው፡፡
በተለያዩ አለማቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የስራ ሃላፊነቶች ላይ ከ28 አመታት በላይ የዘለቀ ስኬታማ አመራር በመስጠት የካበተ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊው አቶ ደረጀ፣ በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን ናታሊያ ካኔምን እንደሚተኩ ተመድ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአለማቀፉ ኤስኦኤስ የህጻናት መንደር፣ የምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ አለማቀፍ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑትና 4 ሺህ 500 ያህል ሰራተኞችን በስራቸው በማስተዳደር ላይ የሚገኙት አቶ ደረጀ፣ ብቃት ባለው አመራር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ፈተናዎችን በመቋቋም፣ በአብዛኛው አፍሪካን ተደራሽ ያደረጉ በርካታ ስራዎችን በስኬታማነት እንዳከናወኑ መግለጫው አስረድቷል፡፡
አቶ ደረጀ ከዚህ ቀደምም አሜሪካን ፍሬንድስ ሰርቪስ ኮሚቴ በተባለው ተቋም በክልላዊ ዳይሬክተርነት፣ በኡጋንዳ የኦክስፋም ሃላፊ፣ በሴቭ ዘ ችልድረን በምክትል የፕሮግራም ዳይሬክተርነትና በሌሎች ታላላቅ ተቋማት በከፍተኛ የስራ ሃላፊነቶች ላይ በማገልገል ብቃታቸውን ማስመስከራቸውን አስታውሷል፡፡
ኢትዮጵያዊው አቶ ደረጀ ከኦክስፎርድ ብሩከስ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በማስተርስ፣ በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በሶሻል ፖሊሲ ኢን ዲቨሎፒንግ ካንትሪስ በማስተርስ መመረቃቸውንና፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በቢዝነስ ማኔጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን መግለጫው አክሎ ገልጧል፡፡  

  “አንቺም አባዎራ እኔም አባዎራ
                   ግራ ገባው ቤቱ በማ እንደሚመራ…”

   በኬንያ ከወራት በፊት በተካሄደው የድጋሚ ምርጫ ያሸነፉት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በይፋ ቃለ መሃላ ፈጽመው አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት መምራት ከጀመሩ ከወራት በኋላ፣ እነሆ ያልተጠበቀ ነገር ባለፈው ማክሰኞ በመዲናዋ ናይሮቢ ተከናወነ፡፡
ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ካስደገሙ በኋላ፣ ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉት የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ፤ ባለፈው ማክሰኞ ናይሮቢ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው፣ “የታላቋ ኬንያ ሪፐብሊክ  ፕሬዚዳንት ነኝ” ሲሉ በማወጅ ቃለ መሃላ ፈጸሙ፡፡
የያዘውን ስልጣን በድንገት መነጠቁ ያስደነገጠውና ጉዳዩ ወደ ከፋ ግጭት እንዳያመራ ያሰጋው የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት፤ የጎንዮሹ ቃለ መሃላ አገርን የሚያፈርስ፣ክፉ ድርጊት በመሆኑ እንዳይካሄድ ብሎ ቢያስጠነቅቅም፣ ራይላ ኦዲንጋ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው፣ መጽሃፍ ቅዱሳቸውን ከፍ አድርገው ይዘው፣ መሪነታቸውን አወጁ። ሁለተኛ ፓርላማ ማቋቋማቸውንም በድፍረት ተናገሩ፡፡
ህጋዊው የኡሁሩ መንግስት. የኦዲንጋን የጎንዮሽ በዓለ ሲመት በቀጥታ ስርጭት ለህዝቡ ለማድረስ እየተዘጋጁ የነበሩትን ኬቲኤን፣ ኤንቲቪ እና ሲቲዝን ቲቪ የተባሉ ሶስት ታላላቅ የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ስርጭት አቋርጧል፡፡
የኡሁሩ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹን መዝጋቱን ተከትሎ፣ ባለፈው ሃሙስ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ተሰይሞ ጉዳዩን ካጤነው በኋላ፣ ለ14 ቀናት ያህል በጉዳዩ ዙሪያ ቀጣይ ምርምራ አድርጎ እስከሚጨርስና የመጨረሻ ብይን እስኪሰጥ ድረስ፣ የመንግስት ውሳኔ ተሽሮ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ስርጭታቸውን እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
የኡሁሩ መንግስት ግን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብሮ፣ ጣቢያዎቹን ለመክፈት ፍላጎት አለማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ የአዲሱ ፕሬዚዳንት ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም የአገሪቱ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚጥስ ነው፣ በማለት የመንግስትን እርምጃ ማውገዛቸውን አመልክቷል፡፡
የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሁነኛ ምላሽ እስካልሰጠ ድረስ፣ ኬንያ በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ልታመራ እንደምትችል የሚናገሩት የመብት ተሟጋቾች፤ ሁለቱም ሃይሎች አገሪቱን ወደ ጥፋት ከማምራት እንዲቆጠቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ስራ ፈትተው ከሚቀለቡ 6 ሺህ ወታደሮች፣ የተወሰኑት በግድ እረፍት ይወጣሉ

   ፕሬዚዳንቱ ወጪን ለመቀነስ ሲሉ ለሰሞኑ የህብረቱ ስብሰባ፣ የግል አውሮፕላናቸውን ትተው፣ በመደበኛ አውሮፕላን ነበር የመጡት
ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት የገጠመው የናሚቢያ መንግስት፤ወጪን ለመቆጠብ በሚል ሚኒስትሮችን፣ ምክትል ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት ሃላፊዎችን ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ባለስልጣናት ወደ ውጭ አገራት እንዳይሄዱ መከልከሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ማንኛውም የአገሪቱ ባለስልጣን ለስብሰባ፣ ለስልጠናና ለሌሎች ጉዳዮች ከአገሪቱ ውጭ የሚያስወጣው ጉዞ ካለ በአፋጣኝ እንዲሰርዝ መንግስት መመሪያ ማስተላለፉን የጠቆመው ዘገባው፤ የጉዞ ክልከላው ቢያንስ እስከ ወሩ መጨረሻ ተግባራዊ ሆኖ እንደሚቆይና ይራዘማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡ በውጭ አገራት ጉዞ ሳቢያ ለባለስልጣናት ከፍተኛ ወጪ ማውጣት እንዲቆም ያሳሰቡት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀጌ ጌንቦ፤ በሰሞኑ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅትም የግል አውሮፕላናቸውን ትተው፣ የህዝብ ማመላለሻ መደበኛ አውሮፕላን መጠቀማቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የናሚቢያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በማዕድን ኤክስፖርት ገቢ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የአለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ ኢኮኖሚዋን ክፉኛ እንደጎዳውና የፋይናንስ እጥረት የገጠመው የአገሪቱ መንግስት መሰል ወጪዎችን ለመቀነስ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስረድቷል።
ስራ ፈትተው በጦር ካፕሞች ለሚኖሩ የጦር ሃይሉ አባላት ደመወዝ በአግባቡ መክፈልም ሆነ የእለት ምግብና ውሃን ጨምሮ የተለያየ ወጫቸውን መሸፈን ያቃተው የአገሪቱ መንግስት፣ ከሰሞኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን የአመት እረፍት ለማስወጣትና በእረፍት ላይ ለሚገኙትም ተመልሰው እንዳይመጡ መመሪያ ለመስጠት መወሰኑን ዘ ናሚቢያን የተባለው የአገሪቱ የግል ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መከላከያ ሚ/ር ለ2018 የበጀት አመት 5.6 ቢሊዮን የአገሪቱ ዶላር እንደተመደበለት ያስታወሰው ዘገባው፣ አገሪቱ 15 ሺህ ያህል ወታደሮች እንዳሏትና 6 ሺህ ያህሉ ስራ ፈትተው በጦር ካምፖች ውስጥ እንደሚኖሩ መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

  በየቀኑ 50 ሚሊዮን ሰዓታት ፌስቡክ ላይ ይጠፋሉ

    ታዋቂው የማህበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017፣ የመጨረሻው ሩብ አመት፣ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የ4.3 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱንና ይህም ካለፈው የሩብ አመት ትርፍ፣ በ61 በመቶ ብልጫ እንዳለው ኩባንያው ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኩባንያውን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግን ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፤ ፌስቡክ በተጠቀሰው የሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 12.7 ቢሊዮን ዶላር ያገኘ ሲሆን፣ የወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ቁጥርም 2.13 ቢሊዮን ያህል ደርሷል። ፌስቡክን በሞባይል የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር ማደጉ በሩብ ዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ እንዲያገኝ አስችሎታል ያለው ዘገባው፤ በየዕለቱ ፌስቡክን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥርም 1.4 ቢሊዮን መድረሱን አስረድቷል፡፡
ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየተሻማና ስራ እያስፈታ ነው በሚል የሚሰነዘርበትን ትችት በማጤን፣ በሩብ አመቱ ተጠቃሚዎች በየቀኑ ፌስቡክ ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ መውሰዱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአንድ ቀን ውስጥ ተጠቃሚዎች በፌስቡክ ላይ የሚያጠፉትን አጠቃላይ ድምር ጊዜ ወደ 50 ሚሊዮን ሰዓታት ዝቅ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
በአዲሱ የፈረንጆች አመት የዓለማችን የዲጂታል ማስታወቂያ ገበያ ውስጥ 266 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ይንቀሳቀሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ በዚህ ገበያ ውስጥ ፌስቡክ 18.4 በመቶ ያህል ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚገመት አመልክቷል፡፡

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የፓስፖርት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ በ140 የተለያዩ ክፍት የስራ ቦታዎች ላይ ሴቶችን ቀጥሮ ለማሰራት ባወጣው ማስታወቂያ፤ ከ107,000 በላይ አመልካቾች መቅረባቸውን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በድንበር አካባቢ መስሪያ ቤቶች መስራት ለሚፈልጉ ስራ ፈላጊዎች የወጣው የክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ፤ በድረ ገጽ አማካይነት በተሰራጨ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ107,000 በላይ አመልካቾች መቅረባቸው ያስደነገጠውና መስተንግዶው ከአቅሙ በላይ የሆነበት ዳይሬክቶሬቱ፤ በአፋጣኝ ማስታወቂያውን ማንሳቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያው ቢያንስ ሁለተኛ ደረጃን ያጠናቀቁና ከ25 እስከ 35 አመት በሚገኘው የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አመልካቾችን ብቻ መጋበዙን የጠቆመው ዘገባው፤ በሳኡዲ አረቢያ የሴቶች ስራ አጥነት 33 በመቶ ላይ እንደሚገኝም አስታውሷል፡፡

   (ጾታዊ እኩልነት ለመፍጠር)

    የካናዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከ37 አመታት በላይ በድምቀት ሲዘመር በዘለቀውና “ኦ… ካናዳ” የሚል ርዕስ ባለው የአገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር ውስጥ የሚገኙትን ጾታዊ እኩልነትን ያላማከሉ ቃላት ለመቀየር የቀረበለትን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከሰሞኑ አጽድቆታል፡፡
በካናዳውያን መካከል ጾታን መሰረት ያደረገ ልዩነት የሚፈጥርና ሁሉንም ዜጎች ያማከለ መሆን ሲገባው ለወንዶች ያደላ ነው በሚል ከ8 አመት በፊት ጀምሮ ቅሬታ ሲቀርብበትና ሲያነጋግር ቆይቷል ይላል ቢቢሲ - በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተዘጋጀው የአገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር ግጥም ውስጥ የሚገኘውን አንድ ነጠላ ሃረግ፡፡
“በሁሉም ወንድ ልጆችሽ ፈቃድ…” የሚለው ይህ የብሄራዊ መዝሙሩ ግጥም አካል የሆነ ሃረግ፣ “በእናት ካናዳ ጉዳይ የሚያገባቸው ወንድ ልጆቿ ብቻ ናቸው” የሚል የተዛባና ጾታዊ እኩልነትን ያላማከለ መልዕክት ያዘለ በመሆኑ፣ ቃላቱ ተቀይረው ከጾታ ክፍፍል በጸዳ ሌላ ስንኝ ይተካ በሚል የቀረበውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ፣ በጉዳዩ ላይ ድምጽ የሰጠው ምክር ቤቱ፣ የስንኙ ሁለት ቃላት እንዲቀየሩና “በሁላችንም ፈቃድ” የሚል ትርጉም እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
“ኦ ካናዳ” የሚለው የአገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር በይፋ ስራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1980 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶ በነበሩት ዓመታትም፣ “ወንድ ልጆችሽ” የሚለውን አገላለጽ የያዘው ይሄው አነጋጋሪ ሃረግ እንዲቀየር የሚጠይቁ የውሳኔ ሃሳቦች ለ12 ጊዜያት ያህል ለምክር ቤቱ ቀርበው እንደነበርና ሁሉም ሳይጸድቁ መቅረታቸውን አስታውሷል፡፡

    የመጀመሪያው የአክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች ሆነን ሳለ፣ ይህ ስልጣኔ መስፋት ሲገባው እንዴት ፈረሰ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት “የጠፋው አዳም” የኪነ ጥበብ ምሽት፣ የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 እስከ ምሽት 1፡45 በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሚሳተፉት ምሁራን መካከል የዘርዓያዕቆብ ዘጠነኛ የልጅ ልጅ የሆኑት ሊቀ ጠበብትና ሳይንቲስት ገ/ማሪያም ማሞ፤ ስልጣኔያችን ለምን ፈረሰ፣ እንዴት ፈረሰ፣ ማንስ አፈረሰው? በሚለውና በምርምር በደረሱባቸው ሰባት ምልክቶች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ እንደሚሰጡ የሁነቱ አዘጋጅ አቶ ቤዛ ሁነኝ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ ሊቀ ጠበብቱና ሳይንቲስቱ
ገ/ማሪያም ማሞ በበኩላቸው፤በአክሱም ስልጣኔ ላይ ባደረጓቸው ምርምሮችና ግኝቶች እንዲሁም ስልጣኔው እንዲቀጥል ምን መደረግ አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ በዚህ ውይይት ለመታደም መግቢያው 70 ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡ 

  በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ኮንሰርት ታቀርባለች

    የድምፃዊት ሄለን በርሄ “እስኪ ልየው” የተሰኘ አልበሟና “ፊት አውራሪ” ለሚለው ዘፈኗ የተሰራው ቪዲዮ ክሊፕ የፊታችን አርብ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ፣ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ማማስኪችን ይመረቃል፡፡
በምሽቱም ድምጻዊት ሄለን “ፊታውራሪ”ን ጨምሮ የተለያዩ ዘፈኖቿን የምታቀርብ ሲሆን ሌሎች ድምፃዊያንም እንደሚያቀነቅኑ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የድምጻዊቷ ማናጀር አቶ በረከት ተሾመ እንደገለጹት፤ ድምጻዊቷ ከአብይ ፆም በኋላ በአዲስ አበባና በክልሎች ትልልቅ ኮንሰርቶችን የምታቀርብ ሲሆን በቀጣይም በውጭ አገራት ተመሳሳይ ኮንሰርቶች የማቅረብ እቅድ አላት፡፡  
በአንድ የዘፈን አልበሟ ተቀባይነት፣በአንድ የዘፈኗ ቪዲዮ ላይ አነጋጋሪ ስሆነው አልበሟና ስለተሰማራችበት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአዲስ አድማስ ለቀረበላት ጥያቄ በሰጠችው ምላሽ፣ አልበሟ ጥሩ ተቀባይነት ማግነቱን፣ በህፃናት ካንሰር ከUNDP ጋር በሴቶች ዙሪያ እንደምትሰራ የገለፀች ሲሆን አለባበሷ በቪዲዮው ዳይሬክተር ስንታሁ ሲሳይ ትዕዛዝ መለበሱን ገልፃ “በዚህ አለባበስ ህዝቡንም ሆነ ሚዲውን አስቀይሜ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብላለች፡፡

 በክላስ አክት ፊልም ፕሮዳክሽን እየተሰራ ዘወትር እሁድ ከምሽቱ 1፡30 የሚቀርበው “ትርታ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነገ ምሽት በፋና ቴሌቪዥን እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡  
የድራማው ደራሲ  ሶፎንያስ ታደሰ ሲሆን ዳይሬክተሩ ልዑል ተፈሪ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በድራማው ላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የሚሳተፉበት ሲሆን ከነዚህም መካከል፡- ኤልሳቤጥ መላኩ፣ አላዛር ሳሙኤል፣ ጌታቸው ስለሺ፣ ዲበኩሉ ታፈሰ፣ እታፈራሁ መብራቱ፣ ዝናቡ ተስፋዬ፣ አበበ ባልቻ፣ ፍሬው አበበ፣ ናርዶስ እንግዳ፣ ያፌት ሄኖክ፣ ሜሮን እንግዳና ሌሎችም እንደሚተውኑበት አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡   
ወንጀል ነክ ልብ አንጠልጣይ ዘውግ ያለው ድራማው፤ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በ1950ዎቹ ዓመታት በአንድ ዘመናዊ ነጋዴና በአንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ድራማው በታሪክም ሆነ በምስል ጥራቱ ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነም አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ መንገድ ላይ ይገናኛሉ፡፡
አዋቂ፡- እንደምን ውለሃል ወዳጄ
አላዋቂ፡- እግዚሃር ይመስገን እንዴት ከርመሃል?
አዋቂ፡- እኔ ደህና ከርሜያለሁ፡፡
አላዋቂ፡- ይሄ ምሁር ነኝ ባይ ጉረኛ ሁሉ ሰፈር ውስጥ አላስቀምጥ አለን እንጂ እኛማ ደህና ነን፡፡
አዋቂ፡- እንዴት ነው ያስቸገረው?
አላዋቂ፡- አሃ አንተም ጀመርከኝ እንዴ?
አዋቂ፡- የማላውቀውን እንድታሳውቀኝ ብዬ እኮ ነው፡፡
አላዋቂ፡- ደህና፡፡ አሁን ወዴት እየሄድክ ነው?
አዋቂ፡- ወደ ገበያ
አላዋቂ፡- እንግዲያውስ አብረን እንሂድ- ግን አዋቂ ነኝ ብለህ እንዳትፈላሰፍብኝ
አዋቂ፡- እኔ እንደውም ካልጠየቅኸኝ አላስቸግርህም፡፡
ተስማምተው መንገዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ጥቂት እንደሄዱ አንድ አጥር ላይ ያለ አውራ ዶሮ አጠገብ ይደርሳሉ፡፡ አውራ ዶሮው ይጮሃል። ይሄኔ አላዋቂው፤
“ይሄ አውራ ዶሮ እዚህ ሲጮህ፣ የዚህ ዓይነት ሌላ አውራ ዶሮ መንግሥተ-ሰማይ ውስጥ ይጮሃል” አለ፡፡
አዋቂው፡- መንግሥተ-ሰማይ ንፁህ ነው፡፡ እንደ ዶሮ ያለ ባለ ኩስ እዚያ ሊኖር አይችልም፡፡
አላዋቂው፡- አይ አውራ ዶሮ‘ኮ ሲጮህ፤ አፉን ወደ ገነት ቂጡን ወደ ሲዖል አድርጎ ነው፡፡
አዋቂው፡- ሲዖል‘ኮ የሰውን እርጥብ ሥጋ እንኳን ያነዳል፡፡ የዶሮ ላባ ካገኘማ ወዲያው ነው አቀጣጥሎ የሚያጋየው!
አላዋቂው መሟገቻ ነጥብ አጣ፡፡
አላዋቂው፡- ኦዎ! እኔ ምንቸገረኝ- ያባቴ ዶሮ አደለ ቢያንበገብገው!
*    *    *
የአንድ አገር አንዱ መልካም ገፅታዋ አዋቂዎቿን መንከባከቧና ከእነሱም በቂ ምክር መቀበሏ ነው። ያልተማረ አላዋቂ እየገነነ፣ የተማረ አዋቂ እየኮሰሰ በሄደ ቁጥር የሀገር እድገት ቁልቁል ይሆናል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ የፊደል ሠራዊት እስከ ደርግ የመሀይምነትን ጥቁር መጋረጃ መቅደጃ መሠረት ትምህርት ድረስ የተለፋው አላዋቂነትን ለመቀነስ ነው፡፡ ብዙ ተጉዘንበታል፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ዛሬም ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ ጥረቱን መቀጠል ተገቢ ነው፡፡ አላዋቂነት በእርግጥ የመማር ያለመማር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሳይማር በቂ ብስለት ያለው ሰው ብዙ አለ፡፡ ተምሮ በዘር፣ በሃይማኖትና በቀለም አባዜ ውስጥ የሚዳክር አያሌ ሰው አለ፡፡ ተምሮ እንዳልተማረ እያደር የሚደነቁር፣ እንደ ሽንቁር እንሥራ የሚያፈስ በርካታ ምሁር አለ፡፡ አስተዳደግ፣ አካባቢ ተፅዕኖ፣ የአቻ ዕድሜ ግፊት፣ የማህበረሰቡ የዕድገት ደረጃ፣ የግብረገብነት ጥልቀት ወዘተ … የማንነቱ መቀረጫ ሊሆኑ ይችላሉ። የሃገራችን የዕድገት አካሄድ በማንነት መለኪያ አንፃር በተለይ አሥጊ አካሄድ ላይ ያለ ይመስላል። የሚያባብስ እንጂ የሚያሻሽል በሌለበት ሁኔታ ከገባንበት እዘቅት የመውጣት ዕድል እየጠበበ እየመጣ ነው፡፡
ይህንን ጠንቅቆ የተረዳና የራሱን ጠጠር ጥሎ ለመሻሻል አስተዋፅዖ የሚያደርግ ማንኛውም ዜጋ፤ የለውጡ ሞተር አካል ይሆናል፡፡ በተለይ ወጣቱ ዐይኑን እንዲከፍት ይጠበቅበታል፡፡ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድ ከግዴለሽነትና ከተመልካችነት ወጥቶ፣ ወደ ተዋናይነት መሸጋገሩ አይቀሬ ነው! በየትኛውም ዘመን የነበረው ወጣት፤ ቀስ በቀስ ነው ለአገር አሳቢ እየሆነ የመጣው፡፡ ግብአቶቹ አያሌ ናቸው፡፡
በንጉሡ ጊዜ የነበረው ወጣት ወደ አብዮቱ የለውጥ ሂደት እስኪገባ ድረስ የሃያና የሰላሳ ዓመት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፏል፡፡ አብዮተኛ ሆኖ የተፈጠረ ወጣት ኖሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም የ1966 ዓመተ ምህረቱ አብዮት ከመፈንዳቱ ዋዜማ “የጆሊ - ጃኪዝም” ዘመን ነበር፡፡ ቤል ቦተም (ቦላሌ-ከታቹ በጣም ሰፊ)፣ ሰፊ ቀበቶ፣ አፍሮ ፀጉር፣ ህልሙም ውኑም ሴት ጠበሳ፤ ጭሳ ጭሱን በየጥጉ ያከናውን የነበረ ትውልድ ማቆጥቆ የጀመረበት ሰዓት ነበር፡፡ እንደ ዛሬው “ሀንግ” ባይሆንም፣ የግሩፕ ፀብ ጣራ ነክቶ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ያ ሁሉ የተዛነፈ ጉዳይ ላይ የነበረውን ወጣት አብዮት ዋጠውና የለውጡ ሞተር ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡ መረሳት የሌለበት ከሞላ ጎደል የጥቂት የነቁ ወጣቶች መንቀሳቀስ ብቻ እንደነበር ነው፡፡ Change is an incremental process ለውጥ አዳጊ ሂደት ነው እንደ ማለት ነው፡፡ የሁሉም ወጣት ዐይን በአንድ ጊዜ አይከፈትም፡፡ ለውጥን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ማየት ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ትውልድ ቸኩሎ ለጥቅም ሲቆም ብዙ አገራዊ ጉዳዮችን ሊዘነጋ መቻሉ አይታበልም፡፡ ታላላቆች ታናናሾችን ለመግራት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ መናናቁ የትም አያደርስም። ምንም ያልተማሩ ወላጆች፤ ልጆቻቸውን ለፍሬና ለወግ ማዕረግ ያበቁት ከእኔ የተሻለ ልጅ ላፍራ ብለው ነው! የጊዜ ገደብ አመለካከታችን መቀየር አለበት - የአንድ ጀንበር ድል የለምና፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅድ፣ ከትዕግሥትና ከሆደ - ሰፊነት ጋር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው! ለዚህ ደግሞ ቁልፉ ዲሲፕሊን ነው፡፡ ያለ ዲስፕሊን እንኳን ዓመታት ሳምንታት መዝለቅ አይቻልም፡፡ ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ፤ የሀገራችን የጋዜጣ ሥርዓት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ተብለው ተጠይቀው - “40 ዓመት ይበቃል” ማለታቸውን አንርሳ፡፡ ሩቅ የሚያይ አዕምሮና የቅርቡን በአግባቡ የሚራመድ እግር ያስፈልጋል፡፡ የየዕለቷን ድል በማጠራቀም ከጉራ በፀዳ ንቃት መንቀሳቀስ ያሻል። ይህ ሁሉ የዲሲፕሊኑ አካል ነው፡፡ የእስከዛሬው መንገድ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” ነበር። ይህ እንዳይደገም ሁሉም የቀደምት ተዋንያን “በእኛ ይብቃ” ይበሉ፡፡ ወይም በዘመነኛው አባባል “አፉ በሉን” ይበሉ፡፡ ስህተትን አለማረም ለስህተት ደረጃ ማውጫ ካልሆነ በቀር ለማንም አይበጅም። ለተረካቢው ትውልድ የምንሰጠው የጠራ ታሪክ አይኖርም፡፡ ተረካቢውም ትውልድ ታሪክን መርማሪ፣ አመክንዮ የሚገባው፣ ከነችግሩ የነገን ብሩህነት የሚያይ፣ ትችትና ማጥላላትን ዋናዬ የማይል፣ ትምህርትን መሬት አውርዶ የት እደርስበታለሁ የሚል፣ እኔ ካልተለወጥኩ አገር አትለወጥም ብሎ የሚያስብ፣ ግብረገብነትን የዕለት ተዕለት ህይወቱ ለማድረግ የሚጣጣር፣ ከፖለቲከኝነት ይልቅ ሰው ለመሆን የሚተጋ፣ የሚማረው ከሁሉም በፊት ለራሱ መሆኑን የሚያውቅ፣ ትውልድ እንዲሆን ከመመኘት አልፈን የምናግዘው፣ የምናበረታታው፣ የምናማክረው ዜጎች መኖር አለብን፡፡ ወጣቱም ከማፈንገጥ ይልቅ አዳማጭ፣ ከአጉራ - ዘለልነት ይልቅ አደብ መግዛትን የሚመርጥ፣ ከሞቅ ሞቅ ይልቅ ላቅ ጠለቅ ማለትን የሚወድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” ይሆናል፡፡ ከዚያ ይሰውረን!!      

Page 3 of 377