Administrator

Administrator

•  ስፖርቱ መስፋፋቱ በሥነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት
ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሏል


የኢትዮጵያ ሌጀንድ ኢንተርናሽና ፕሮ ቴኳንዶ ፌደሬሽን፣ የቴኳንዶና የማርሻል አርት ስፖርትን በት/ቤቶችና በመዝናኛ ቦታዎች ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ከአሴቅ ዲኮርና ኢቨንት ኦርጋናይዜሽን ጋር ትላንት ተፈራረመ፡፡

የስምምነቱ ዋና ዓላማ፤ የቴኳንዶና የማርሻል አርት ስፖርትን በት/ቤቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በሌሎችም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆነ ተቋማት ማስፋፋትና ማጠናከር ነው ተብሏል፡፡

የቴኳንዶና የማርሻል አርት ስፖርቱን የማስፋፋት ፕሮጀክቱ፤ በተለይም ት/ቤቶችና ታዳጊዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤  ጤናቸው የተጠበቀ፣ በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ እንዲሁም  በመልካም ሥነምግባር የታነፁ ብቁና አሸናፊ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም፤ የሌጀንድ ኢንተርናሽና ፕሮ ቴኳንዶ ስፖርት ውድድርን በየደረጃው በስፋት፣ በጥራትና በስርዓት በማዘጋጀት በከተማ አቀፍ፣ አገር አቀፍና ዓለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ምርጥ ስፖርተኞችን በማፍራት የአገርን ክብርና ዝና ከፍ ለማድረግ ታልሟል፡፡

በስምምነት ሰነዱ ላይ እንደተመለከተው፤ በከተማ ውስጥ የሚታየውን የማርሻል አርት ስፖርት ማሰልጠኛ ሥፍራ እጥረት ለመቅረፍ ከት/ቤቶች ጋር በትብብር የሚሰራ ሲሆን፤ የተለያዩ የሌጀንድ የማርሻል አርት ስፖርት ሌሎች ውድድሮችንና መዝናኛ ፕሮግራሞችን በተቀናጀ መልኩ በማዘጋጀት  ስፖርቱን ተደራሽ ለማድረግና ለህብረተሰቡ በስፋት ለማስተዋወቅ ታቅዷል፡፡

ሌጀንድ ኢንተርናሽና ፕሮ ቴኳንዶ ፌደሬሽን፣ ከ24 ዓመተ በፊት በዓለማቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን  በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የጠቆሙት ማስተር ሄኖክ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ላለፉት 4 ዓመታት ፈቃድ ተሰጥቶት ተደራሽነቱን ለማስፋትና ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት  እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሌጀንድ ፎር ኦል እና በአሴቅ ዲኮርና ኤቨንት ኦርጋናይዜሽን የተደረሰው ስምምነት፣ በዋናነት ተግባራዊ የሚደረገው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ ነው ተብሏል፡፡

Sunday, 19 November 2023 00:00

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

•  ማህበሩ 70 ቢሊዮን ብር ለብድር ማቅረቡ ተነግሯል

የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር የተመሰረተበትን የ25ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በመጪው ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር ተገለፀ፡፡

በዝግጅቱ ላይ በአገሪቱ በልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውና የ25 ዓመታት እድሜ ያስቆጠረው የማይክሮፋይናንስ ዘርፍ ኅዳር 18ን “የኢትዮጵያ የብድርና ቁጠባ ቀን” በማለት እንደሚሰይም ተነግሯል፡፡  

በማህበሩ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች እንደሚሳተፉ የጠቆመው የማህበሩ መግለጫ፤ ክብረ በዓሉ በፓናል ውይይትና ኤግዚቢሽን እንዲሁም ጥናቶች በሚቀርቡበት ኮንፍረንስና ሌሎች ኹነቶች እንደሚከበር አመልክቷል፡፡

ክብረ በዓሉ በመጪው ሳምንት ከህዳር 18-21 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ለአራት ተከታታይ ቀናት፣ በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ይከበራል፡፡

የ25ኛ ዓመት በዓል አከባበሩን  በተመለከተ በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ ዳሙ ሆቴል አጠገብ ወደ ፒኮክ መናፈሻ መግቢያ ላይ በሚገኘው የማህበሩ አዳራሽ ፣ የማህበሩ የቦርድና የማኔጅመንት ከፍተኛ አመራሮች ለሚዲያ ባለሙያዎች  መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዓሉ “ማይክሮፋይናንስ በዲጂታል ዘመን፣ የፋይናንስ አካታችነት ለስራ ፈጠራና ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን ያመለከተው  ማህበሩ፤ ባለፉት ዓመታት በዋናነት የዲጂታል ስርዓት በማስፋፋትና በፋይናንስ አካታችነት ረገድ ጉልህ ስኬት መቀዳጀቱን ጠቁሟል፡፡

የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የዲጂታል ሥርዓት ተጠቃሚ መሆናቸው በተጨባጭ ውጤታማ እንዳደረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በቴክኖሎጂው አማካኝነት  የተደራሽነት ሽፋናቸውን ቀድሞ ከነበረው 35 በመቶ ገደማ ወደ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ማሳደጋቸው ተጠቁሟል፡፡  

ከ50 የማህበሩ አባላት መካከል በ30 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የኮር ባንኪንግ ዲጂታል ሥርዓት መተግበሩን የገለጹት አመራሮቹ፤ በፋይናንስ አካታችነት ረገድም ከባንኮች ይልቅ ተቋማቱ የበለጠ ስኬት መቀዳጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ስድስት የሚሆኑ የማህበሩ አባላት ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን መስፈርት በማሟላት ወደ ባንክ ማደጋቸውንና በሂደት ላይ የሚገኙም እንዳሉ የጠቆሙት አመራሮቹ፤ ተቋማቱ ወደ ባንክ ሽግግር ቢያደርጉም የቀድሞ አገልግሎታቸውን የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡


ማህበሩ የሴቶች ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድም ትርጉም ያለው ሥራ ማከናወኑን የተናገሩት አመራሮቹ፤ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለሴቶች ሲቀርብ የነበረው ብድር አነስተኛ ቢሆንም፣ በሂደት እየተሻሻለ መጥቶ በአሁኑ ወቅት የብድሩ መጠን 50-50 (እኩል ለእኩል) ለመሆን መብቃቱን ጠቅሰዋል፡፡  ለሴቶች ተስማሚ የሆነ የብድር አገልግሎት ለመተግበር ጥረት መደረጉንና የሴቶች ተሳትፎም ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ  መምጣቱን አክለው ገልፀዋል፡፡

በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚቆጥቡ ደንበኞች ከ20 ሚ. በላይ እንደሚደርሱ የተነገረ ሲሆን፤ ማህበሩ  ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ለብድር  ማቅረቡን  ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር ባለፉት 25 ዓመታት ስኬት ብቻ አይደለም የተቀዳጀው፤ ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች እንዳገጠመውም የማህበሩ አመራሮች በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡

ከተግዳሮቶቹም መካከል የፋይናንስ እጥረት በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡ የተጀመረውን ኮር ባንኪንግ ተግባራዊ ለማድረግ ማህበሩ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ገጥሞት ነበር ያሉት አመራሮቹ፤ የውጭ ምንዛሬ በፈለግነው ጊዜና መጠን ባለማግኘታችንም ተቸግረን ነበር ብለዋል፡፡  ሆኖም ማህበሩ ችግሩን ከተቋማቱ  ጋር በጥምረት በመስራት ለመፍታት እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡

የመሰረተ ልማት ችግር ሌላው የገጠማቸው ተግዳሮት እንደነበር የጠቆሙት የማህበሩ አመራሮች፤ የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ሥራቸውን እያስተጓጎለባቸው ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመው፣ ከፍተኛ አቅም ያለው ጄነሬተር በመጠቀም አገልግሎታቸውን ያለማቋረጥ ማቅረብ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ትልቅ ተግዳሮት የሚያበድሩት ካፒታል ማነስ  መሆኑን በይፋ የገለፁት የማህበሩ አመራሮች፤ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኃን ስለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና አገልግሎታቸው ለህብረተሰቡ በቂ መረጃ በመስጠትና ግንዛቤ በማስጨበጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ እግረ መንገዳቸውን በመግለጫው ላይ ለተገኙት የመገናኛ ብዙሃን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Wednesday, 22 November 2023 21:26

addisadmassnews.com Issue1244

Wednesday, 22 November 2023 20:21

እነሆ ድልድዩን !

እነሆ ድልድዩን !
ይህንን መጽሐፍ አንብቤ እንዳጠናቀቅኩ በሃሳቤ " የሰው ልጅ ስልጣን ላይ ሆኖ ባበበበት ወቅት (በተወደደበት ጊዜ ) ያቺ ጊዜ ሳታልፍ ለተተኪው ትውልድ ስልጣኑን ቢያስረክብ በታሪክ ውስጥ ዘላለማዊ ይሆናል ። ታላቅነቱንም ምንጊዜም ትውልድ ይመሰክርለታል። እርሱም ካደለው ይህንን በህይወት ቆሞ ያያል ።" በማለት አብሰለሰልኩ ።
የመጽሐፉ ርእስ " ዘውድ ያልደፋው ንጉሥ " ደራሲው ደረጀ ተክሌ ወልደ ማሪያም ሲሆን በ452 ገጽ ተጠርዞ  በ500 ብር ገበያ ላይ ውሏል።
ባለታሪኩ ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ናቸው ። ከ1893 - 1968 ዓም እዚህ ምድር ላይ ያኖረዋል ።በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከፍተኛ ባለስልጣን ነበሩ ። እኝህ ድንቅ ሰው ምን እንደከወኑ ደረጄ ማለፊያ በሆነ ትረካ ያወጋናል እና መጽሐፉን ገዝቶም ሆነ ፈልጎ ማንበቡን ለእናንተ ልተው ። እኔ ስለጀግናው ቀደም ብሎ መረጃ ቢኖረኝም ደረጀ መረጃዬን ጥብስቅ ስላደሰገልኝ ላመሰግነው እወዳለሁ ። ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ለጃንሆይ ምን ብለዋቸው ነው ከላይ በጥቅስ ያስቀመጥኩትን አባባል ያልኩት ? ጸሐፌ ትእዛዝ የጥንቱን ትውልድ ከአዲስ ትውልድ ያገናኙ ድልድይ ነኝ ይላሉ ። ... የእንግሊዝን መንግስት የኢትዮጵያ ሞግዚትነት አምክነው አገራችንን ነፃነቷን እንድትጎናጸፍ ካደረጉ አርቆ አሳቢዎች መካከል አውራውም ናቸው ። ...
መልሱን ከመጽሐፉ ታገኙታላችሁ ።
ሰላም በምድራችን ላይ ይስፈን !

ከትምህርት ባሻገር ሁለንተናዊ የሰብዕና መገንቢያና የተሻለ የትምህርትና የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ባህል ማዕከሉን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በየሳምንቱ ማክሰኞ የኪነ-ጥበብ ምሽት ዳግም ማዘጋጀት እንደሚጀምር የባህል ማዕከሉ ኃላፊ ተስፋዬ እሸቱ ገልጸዋል፡፡

ቅዳሜ፣ ማክሰኞና ሐሙስ ደግሞ ፊልም የሚያሳይ ሲሆን፤ በቀረቡት ፊልሞች ላይ በወር አንድ ጊዜ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

ባህል ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር ጥምረት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርሟል።

Wednesday, 22 November 2023 11:49

ምርጥ አባባሎች:-

ምርጥ አባባሎች:-

" የትልቅ ሰውን ትልቅ ስራ ሌሎች ይናገሩለታል እንጂ እርሱ አይናገርም።"

(የህልም ዣት)

" የምትወደው ሁልጊዜ ሲለይህ የሚያስረሳህ እንጂ የሚያስታውስህ ነገር አትፈልግ፤ ያለዚያ ህይወትህ የስቃይ ህይወት ይሆናል።"

(ፍቅር አስክ መቃብር)

" ሰው ባለመብት የሚያደርገው የሚፈፅመው ተግባር ነው፤ ተግባሩን ሳይፈጽም በመብቱ የተጠቀመ ሁሉ ባለዕዳ ነው።"

(ወንጀለኛው ዳኛ)


የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

የ“ፍትሕ መጽሔት” ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዛሬ ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከጠበቆቹ ጋር ቀርቧል።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፣ በባለፈው ቀጠሮ ፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቆች፤ “የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የዐቃቤ ሕግን የይግባኝ ቅሬታና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲሰጠን ገጽ አጉድሎ ስለሆነ የተሟላ መልስ መስጠት ባለመቻላችን፣ መልሳችን እንድናሻሽል ይፈቀድልን” በሚል አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡
ዐቃቤ ሕግም በበኩሉ፤ “በዚህ አቤቱታ ላይ እኔም አስተያየት መስጠት አለብኝ” ብሎ ተከራክሯል፡፡
ጠበቆቹም፤ “እኛ ስህተት ሠራ ያልነው ፍርድ ቤትን ነው፡፡ ስህተቱን እንዲያርምም የጠየቅነው ፍርድ ቤቱን ነው፡፡ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ዐቃቤ ሕግ ስለማይመለከተው ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጥ ሊፈቀድለት አይገባም፤” በሚል ተከራክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም፤ “ዐቃቤ ሕግ አስተያየት ይስጥ ወይስ አይስጥ ብሎ ትእዛዝ ለመስጠት ዳኛ ስለሚጎድል ለህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም  ቀጠሮ ስጥተናል፤” ማለቱ ይታወሳል፡፡
በአቶ ሸምሱ ሲርጋጋ የመሀል ዳኝነት (ሰብሳቢነት)፣ በሀፊዝ አባጀማል እና መሀመድ አህመድ የግራና ቀኝ ዳኝነት ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም፣ “ዐቃቤ ሕግ አስተያየት መስጠት ይገባዋል” ሲል የሰጠው ትእዛዝ ዛሬ ህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም በችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሰጠው አስተያየት፤ “የተሰጠው ትእዛዝ  ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ይሄ የፍርድ ቤቱን ተአማኒነት ገና ከመነሻው ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡ ችሎቱ፣ ዐቃቤ ሕግ የሚጠይቀውን ሕገ-ወጥ ጥያቄ በሙሉ እየተቀበለ የሚሄድ ከሆነ ታዲያ፣ እንዴት ነው ነፃና እውነተኛ ፍትሕ የሚገኘው?” ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ  ያነጋገርናቸው አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎችም፤ “ዐቃቤ ሕግ አስተያየት ይስጥ” ተብሎ መታዘዙ አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ፣ የዐቃቤ ሕግን አስተያየት ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም  በቢሮ በኩል ከተቀበለ በኋላ፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቆች ያቀረቡት የመልስ ማሻሻያን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ለታኀሣስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

የባንኩ  የሃብት መጠን  83 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል

 ሕብረት ባንክ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን በዛሬው ዕለት በይፋ ያበሰረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የባንኩ የሃብት መጠን  83 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል።

 አጠቃላይ ካፒታሉ 9. 3 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም  60 ቢሊዮን ብር ብድር እና 64 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ እንዳለው የገለጸው ባንኩ፤ በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ እድገት እያስመዘገበ  መምጣቱንም ጠቁሟል።

ባንክ ባለፉት 25 ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መዝለቁ የተገለፀ ሲሆን፤ ከ15 ዓመታት በፊት ሞባይል ባንኪንግን፣ ኤስኤምኤስ ባንኪንግ በሚል በመጀመር ቀዳሚ ባንክ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪ ባንኩ የኮር ባንኪንግ ሲስተም በራሱ ሰራተኞች መተግበሪያ በማበልፀግ በኢትዮጵያ ብቸኛው ባንክ መሆኑም ተነግሯል፡፡  

ባንኩ የተመሠረተበት የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል፣ ዓመቱን በሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብርም ተጠቁሟል።

*ኩባንያው በቅርቡ በ3 የአፍሪካ አገራት የዳታ ማዕከሎቹን ይከፍታል

በሰባት የአፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀሰው  ራክሲዮ የዳታ ማዕከል ኩባንያ፣ በአዲስ አበባ አይሲቲ ፓርክ የገነባው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዳታ ማዕከሉ  በይፋ ሥራ መጀመሩን አበሰረ፡፡

በዓይነቱ ልዩ መሆኑ የተነገረለት የራክሲዮ ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል፣ በይፋ ሥራ መጀመሩን የማብሰሪያ ሥነስርዓት ዛሬ ጠዋት ረፋዱ ላይ በአይሲቲ ፓርክ የተከናወነ ሲሆን፤ በሥነሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ዘርፉ መሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ራክሲዮ ኢትዮጵያ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “በኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የሚገኘው አዲሱ የራክሲዮ ደረጃ III ዕውቅና የተሰጠው ዘመናዊ የዳታ ማዕከል፣ ከምንጊዜውም በላይ እያደገ ለመጣው የመንግሥትና የግል ተቋማት የዳታ ማዕከል አገልግሎት ጥያቄዎች፣ አስተማማኝና የማይቆራረጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መፍትሄ በማቅረብ መልስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡” ብሏል፡፡

ማዕከሉ፤ 800 ራኮችና እስከ 3 MW የአይቲ ሃይል፣ ደህንነቱ በተጠበቀ የዳታ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት፣ ሙሉ በሙሉ ምትክ ያለው ያለማቋረጥ የሚሰራ የአይቲ መሰረተ ልማቶች  ዝግጁ አድርጓል - ሲል አክሏል ኩባንያው በመግለጫው፡፡

በኢትዮጵያ የራክሲዮ ዳታ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በዕውቀቱ ታፈረ ባደረጉት ንግግር፤ “ይህ አገልግሎት በአዲስ አበባ መጀመሩ ለራክሲዮና ለአገራችን በዲጂታል መሰረተ ልማት ረገድ መሰረት የሚጥል ነው፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎችንና የመንግሥት ኤጀንሲዎች የሥራ እንቅስቃሴን ከማፋጠንም ባሻገር፣ አህጉራዊና ዓለማቀፍ አገልግሎትና የይዘት አቅራቢዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ አጋዥ እንደሚሆን እናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ በማከልም፤ “የማዕከላችን ደረጃ III ዓለማቀፍ የምስክር ወረቀት፣ እኛ  እየሰጠን ያለው የአገልግሎት ጥራት መጠን ማሳያ ሲሆን፤ ለደንበኞቻችን ደግሞ ለማናቸውም ንብረቶቻቸው ከፍተኛ ደህንነት አስተማማኝ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የዳታ ማዕከሉ በይፋ ሥራ መጀመሩን ያበሰሩት የራክሲዮ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮበርት ሙሊንስ በበኩላቸው፤ “ይህንን በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነ ወሳኝ መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረጋችን እጅግ ኩራት ይሰማናል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጣይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የዲጂታል አካችነት ጅምር ግቦችን የሚደግፍ እንደሆነ ሙሉ እምነታችን ነው፡፡ ብለዋል፡፡

ሮበርት ሙሊንስ አክለውም ሲናገሩ፤ “ይህ ጊዜ ለእኛ እንደ ኩባንያ እጅግ በጣም ደስተኛ የሆንበት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ እንደዚሁ ተመሳሳይ ማዕከላችንን ከጀመርን በኋላ፣ ራክሲዮ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሁለተኛው ማዕከላችን  መሆኑ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ተመሳሳይ ማዕከሎችን  በሞዛምቢክ፣ በአይቮሪኮስትና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምንከፍት ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡

ዛሬ ረፋድ ላይ በአይሲቲ ፓርክ የተገነባው የራክሲዮን ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመር ከተበሰረ በኋላ፣ የዕለቱ እንግዶችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች  የዳታ ማዕከሉን ጎብኝተዋል፡፡