Administrator

Administrator

  (ሁለተኛ ክፍል)
አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው “የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ፤ “የዶ/ር ዐቢይ አህመድን ህዝባዊ መሠረት የካደው መጽሐፍ” በሚል ባለፈው ሳምንት የመጀመርያውን ክፍል ሂሳዊ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ክፍል እነሆ፡
አቶ ሚካኤል ይግባቸው አይግባቸውም የኢሕዴን የቀድሞ መዝረክረክ ምንጩ፣በፓርቲው ውስጥ ያሉት ሰዎች የተወከሉበትን ብሔር ሕይወት ለመለወጥ ያልተዘጋጁና ፓርቲውም በአክሲዮን የተያዘ እንጂ ነፃ ያለመሆኑ ነው፡፡ ከጅምሩ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መታገሉን ያልወደዱት የሕወሓት አመራሮች የበታተኑትም ለራሳቸው ጥቅምና አጀንዳ፣በስሙ የሚነግዱበት የብሔር ቡድን ለመፍጠር ተመኝተው መሆኑን የቀድሞው የኢሕዴን መሥራችና አመራር አቶ ያሬድ ጥበቡ፤ “ወጥቼ አልወጣሁም” በሚለው አዲስ መጽሐፋቸው ላይ ይገልጻሉ፡፡
ኢሕአዴጋዊ ፍቅር የተጠናወተው፣ ይልቁንም ሕወሐታዊ አድናቆት የያዘው የሚካኤል መጽሐፍ እንደሚለው፤ ብሔር-ተኮር ስራ ይሰራ ዘንድ እንዳይችል ያደረገው ጨቋኝ ለተባለው አማራ መጨቆኛ ይሆናሉ ያላቸውን የራሱን ሰዎች መሰግሰጉ እንደሆነ ማንም አያጣውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየትኛውም ክልል ባልታየ ሁኔታ የክልሉ ቢሮ ኃላፊዎች ሳይቀር ከዕድለኛው ቡድን መጥተው ሲሾሙበት ለምን ነፃ አይሆንም? ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ ለመሆኑ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የነበረው የአማራ ፓርቲ ሰዎች፣ ምን ያህሎቹ የክልሉ ተወላጆች ነበሩ?
ምንም እንኳ የብሔር ፖለቲካ መዘዙ ሺህ ቢሆንም በዚሁ ቅኝት በተቃኘ አስተዳደር ውስጥ ሆኖ በማይመለከተው ሰው መተዳደር የሚያመጣውን ጣጣ አይተናል፡፡ ወጣቱ በስራ አጥነት መንገላታቱ ሳያንስ በእስራት ሲሰቃይና በጥይት ሲደበደብ፤እወክለዋለሁ የሚለው ድርጅት ጥይት አቀባይ እንዲሆን ያደረገው፣ ህዝቡን ልክ ለማስገባት የተመደበው ፓርቲ ነው፡፡
የአቶ ሚካኤል መጽሐፍ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ቢያነሳም በጣም ጥቂት በሆኑ ገፆች ሊነካ የፈለገው አዲሱን የለውጥ መንገድ ነው፡፡ ይህ የለውጥ መንገድ ብዙዎቻችን ከአሰቃቂ ግፍ፣ አድልዎ ከበዛበት አስተዳደር፣ ዐይን ካወጣ ዘረፋ፣ ከእስራትና ከግድያ የታደገን ቢሆንም ደራሲው ሚካኤል የታየው ግን ስጋቱና አደጋው ነው፡፡ ወደ ሚካኤል ጎርባቾቭ የወሰደውም ያ ነው፡፡  
“የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚለው መጽሐፉ፤ሚካኤል ጎርባቾቭ ሶቪየት ህብረትን እንደበታተኑ ዶክተር ዐቢይም አገራቸውን ሊበታትኑ ይችላሉ የሚል ስጋቱን አጋርቶናል፡፡ ለመሆኑ ዶክተር ዐቢይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከተሰሩት በደልና ግፎች የባሰ ምን ሰርቶ ነው አደጋ ያመጣብን? ይልቅስ ሰው በየአደባባዩ ሲታረድ፣ በእስር ቤት ሲታጎርና ጥፍሩ ሲነቀል፣ ሲኮላሽ-- ያልተፈጠረው ስጋት አሁን እንዴት ሊመጣ ቻለ? ..መንግሥት እንደ ተራ ወንበዴ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ሀውልት ሲሰራ፣ ሸንጎ እየጠራ ፀብ ሲቀሰቅስ---ያልነበረው ስጋት፣ ዶክተር ዐቢይ መጥቶ “እንታረቅ፣ ይቅር እንባባል፣ እንደመር” ሲል እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
ዶክተር ዐቢይ ባይመጣስ በሀገሪቱ ይፈጠር የነበረው ሁኔታ የዛሬውን ዐይነት ህዝብን የሚያረጋጋና ደስ የሚያሰኝ ይሆን ነበር? ቀጣዩን ሁኔታ የሁላችንም ልብ ያውቀዋል፡፡ ምናልባትም ቢበዛ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሀገሪቱ መያዣ መጨበጫ ወደሌለው ችግር ውስጥ ትገባ ነበር፡፡
ይህ ማለት ግን “የኛ ጥቅም ከሚነካ አገሪቱ ትበታተን!” የሚሉ ወገኖች የሉም ማለት አይደለም። የኔ ሙግት ሚካኤልን የሚያህል ትልቅ ሰው፣ ብዙ የሚያውቅና የጥበብ ልብ ያለው ሰው፣ ለምን ያንን የደምና የእንባ ዘመን ከስጋት ሳይቆጥር ቀረ? የሚል ነው፡፡
ሚካኤል በክልል ከተሞች በተለይም የአማራውንና አማርኛ ተናጋሪውን ባይተዋርነት በሚመለከት በስፋት ጽፏል፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕድል የሚለውን የኢሕአዴግ ሀሳብ ይዞ በ1999 ዓ.ም ከተደረገው የህዝብ ቆጠራ ስታቲስቲክስ በመነሳት፣ የተሻለ መንገድ ያሳየበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለመነሻ የሀገራችን ከተሞች አመሰራረትን በሚመለከት ሚካኤል እንዲህ ይለናል፡-
“የአገራችን ከተሞች አንዳንዶቹ ቀደም ሲል የገበያ ስፍራዎችና የነባሮቹ ገዢዎችና የጎሳ መሪዎች መቀመጫዎች የነበሩ ቢሆንም ባመዛኙ ግን ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ለመግዛት በተነሱት አጼ ምኒልክ አዳዲስ የተካተቱ ግዛቶችን በአንድነቱ ውስጥ አዲስ በተካተተው ህዝብ መካከል ሆነው ግዛት እንዲያስጠብቁ በተላኩ የገዢው መደብ የጦር መሪዎች፣ በአሽከሮቻቸውና በወታደሮቻቸው የተመሰረቱ የጦር ሰፈሮች ነበሩ፡፡ በመጪዎቹ ዘመናት ደግሞ ከጦር ሰፈርነታቸው ከፍ ብለው በተጨማሪ ያስተዳደርና የገበያ ማዕከሎች ሆኑ፡፡”
ጸሐፊው ስለ ሀገራችን ከተሞች የሕዝብ ስብጥርና ምስረታ ያነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ በአንዳንድ የክልል ከተሞች የሚኖሩና የክልሉን “ለባለ ክልሉ” በሚል ብሔርተኛ የፖለቲካ ቅኝት መጤዎቹን ያገለለ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስልጣን በመንሰራፋቱ ላይ የራሱን ሀሳብ ለመስጠት ነው፡፡
በቅኝቱ የሐረሪን፣ የኦሮሚያን፣ የቤኒሻንጉልን፣ የአፋርን ክልሎች ማሳያ በማድረግ በከተሞች ውስጥ የሚኖሩት አማርኛ ተናጋሪዎች በቁጥር የበዙ ሆነው ሳለ፣ በአስተዳደር ውስጥ ድምፃቸውን የሚያሰሙላቸው ወኪሎች የሏቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ፣ ኢትዮጵያውያንን በስልጣን ላይ ባሉ የክልሉ ተወላጆች የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደልና ጫና እንዳይኖር እነርሱን ወክሎ፣ መፍትሄ ለማስገኘት ዕድሉ ስለማይኖረው ውሎ አድሮ በፌደራላዊው መንግስት ላይ የሚኖረው እምነትና አመላካከት የተበላሸ ይሆናል ይለናል” መጽሐፉ፡፡
ለዚህም እንደ ማስረጃ ያቀረበው የ1999 ዓ.ም የህዝብ ቆጠራ መሰረት በማድረግ፣ ከ3.4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከክልላቸው ውጭ መሆኑን ያሳያል-ሚካኤል፡፡ በዚህ ርዕስ ሥር ባስቀመጠው አጠቃላይ ድምዳሜ፤ ኢሕአዴግን፣ ይልቁንም ብአዴንን ይወቅሳል፡፡ በሌላ በኩል በ1997 ዓ.ም ፓርቲው በከተሞች የመሸነፉ ምክንያት የነዚህ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦች ከስርአቱ መንሸራተትና ማኩረፍ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚያም አለ በዚህ፣ በከተሞ አካባቢ ተወላጅ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ችግር መዝኖ መፍትሄ ይሰጣቸው ዘንድ መጠየቁን በበጎነት አሰምርበታለሁ፡፡
ለችግሩ እንደ መፍትሄ ያስቀመጣቸው ነገሮችም በጎ ናቸው፡፡
1ኛ. ዛሬ ያለበት ምዕራፍ ያለፉትን ዘመናት ጉዞዎች በአዲስ የእይታ መነጽር መርምሮ፣ የሚመራውን የአማራ ህዝብ፣ በተለይም ከክልሉ ውጭ ባሉ ከተሞች ተሰራጭቶ የሚኖረውን የአማራ ህዝብ ፖለቲካዊ መብቶች አስከብሮ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን መልካምና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ባስተማማኝ መሰረት ላይ የሚያቆምበት፤
ሁለተኛውና ሶስተኛው ነጥብም ከክልል ውጭ የሚኖረው ህዝብ ዋስትና የሚሰጥ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው፣ በሚኖርበት ቦታ ላፈራውና ለሚያፈራው ሀብትና ንብረት ዋስትና እንደሚያገኝ፤ በሌላም በኩል ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማንነቱን አውቆ፣ የሚኖረውን የአማራ ህዝብ ፖለቲካዊ መብቶች አስከብሮ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን መልካምና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ባስተማማኝ መሰረት ላይ የሚያቆምበት፣
ሁለተኛውና ሦስተኛው ነጥብም ከክልሉ ውጭ የሚኖረው ህዝብ ዋስትና የሚሰጥ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረውና፣ በሚኖርበት ቦታ ላፈራውና ለሚያፈራው ሀብትና ንብረት ዋስትና እንዲያገኝ፤ በሌላም በኩል ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማንነቱን አውቆ፣ በጥንታዊና ነባሩ ማንነት ላይ ዲሞክራሲያዊና ብሔራዊ ማንነቱን ሳያምታታ፣ ድርጅቱን “የራሴ ነው” በሚል ተቀብሎ፣ ድርጅቱን እንደተጠሪው የሚቆጥር ሕዝብ መፍጠር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ይህ የሚካኤል ጥሩ አካሄድና ለወገን ተቆርቋሪነት ነው፡፡
ይሁንና ብዙ ነገሮቹን ስንመረምር፣ በሦስተኛው ዓለም፣ በተለይ በአፍሪካ መሪዎች አካሄድ ያየው አይመስልም፡፡ በተለይም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተሸረቡትን የፖለቲካ መንግሥታዊ ሴራዎች የሚያውቃቸው አይመስልም፡፡
ለመሆኑ ብአዴን የአማራውን ህዝብ ይወክል ነበር ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ “አዎን!” የሚልበት ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ምናልባትም ወቀሳው ከዚሁ ባይተዋርነት የመነጨ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ያ በእባብ፣ በእንቁራሪትና በጊንጥ ሊመሰል የሚችለው የፖለቲካ ባህር በውስጡ ከጥቂት ዓሳዎች በስተቀር በጨካኞችና በግፈኞች የተሞላ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአንጻራዊነት ሌሎቹ ክልሎች ጥይትና ሳንጃን ሲቀበሉ፣ አብሮ ጥቂት ልማት ይመረቅላቸዋል፡፡ በብአዴን ግዞት ሥር የነበረው ሕዝብ ግን ትምህርት ቤት እንኳ የሚሰራለት አጥቶ ቁልቁል ወደ ኋላ በመሄድ በየዛፉ ስር ፊደል ሲቆጥር መኖሩን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡
የአቶ ሚካኤል መጽሐፍ ትኩረትና ማስጠንቀቂያ፤ በብአዴን እጅ ለወደቀው ምስኪን የአማራ ህዝብ ሳይሆን፣ የኢህአዴግን የምር ቀውስ ወደ ፈጣሪው በየክልሉ ላለውና በራሱ ሰዎች ባለመወከሉ ቁጣ ጦስ ነገሮች አስጊ እየሆኑ መምጣታቸውም ይመስላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የዋለልኝን የብሔር ጥያቄ አስቀምጦ፣ ኢህአዴግ መሬት ላይ ያወረደበትን መንገድ ማሳየቱ፣ እግረመንገዱን በስስ ልምጭ መንካቱ ጥሩ ነው፡፡  
ቢሆንም ክፋት የለውም … ይሁንና ሌላው ያልተመቸንና መዝጊያው ላይ የተነገረን ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያው በማህበራዊ ሚዲያ እስኪታክተን ያነበብነው ነው፡፡ “ትግራይ ልትገነጠል ትችላለች!” የሚል፡፡
ይህ ቋንቋ በእጅጉ ይዘገንነኛል፡፡ ለመሆኑ ትግራይን የፈጠራት ማነው? … የተፈጠረችውስ መቼ ነው? … ለምንስ የትናንቱ ወያኔ ጠፍጥፎ እንደሰራት ትቆጠራለች? እውነት ለመናገር የትግራይ አባቶች ኢትዮጵያን ከፈጠሯት ሰዎች ተርታ ያሉ አይደሉም እንዴ? .. ለነፃነት በፈሰሰው፣ ለብሔራዊ አንድነት በተከፈለው ዋጋ ቁንጮ ላይ ያሉ ሰዎች ምድር ታሪክ በሚያዛቡ ሰዎች ትነጠላለች ያለውስ ማነው?
እንደኔ ከዚህ ለዘብ ያለ አስተያየትና ቅሬታ ቢነሳ ቅር አይለኝም፡፡ ከዚያ ውጭ ግን መገንጠል ያቃዠውና ከትግራይ ህዝብ ልብ ያልወጣ ጩኸት ሰሚ የለውም። ዮሐንስ የሞተው ሀገር ለመገንጠል አይደለም፣ አሉላ በየጦር ግንባሩ በእሳት የተበላው፣ የጥይት ባሩድ ሲያሸት የመኖሩ ትሩፋት ሕዝብን ለመለየት አይደለም። አንዲት ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ነው፡፡ እንደዛሬዎቹ ሀገር ለመበተን፣ ህዝብ ለመለያየት አይደለም፡፡
ከሚካኤል ሀሳቦች የምጋራው የጋራ ጉዳይ አለኝ። ያም የትግራይ ክልል ተወላጆች የጥቃት ስጋት አለባቸው የሚለነው ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ በሌሎች መገናኛ ብዙኃንም ሽንጤን ገትሬ ተሟግቻለሁ፡፡ አሁንም በእጅጉ እታገለዋለሁ፤ እቃወመዋለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ ስጋችን፣ አካላችን ነው፡፡ የአክስት ባል፣ የአጎት ልጅ ወዘተ ሆነናል፡፡ ይህንን ዝምድና ያላገናዘበ ዘረኝነትና ጥላቻ ተቀባይነት የለውም፡፡
ሚካኤል ሺፈራው (ገፅ 269 ላይ)ባሰፈረው ሃሳብ ግን አሁንም ትክክለኛ ያልሆነ ሃሳብ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድን የረጂም ታሪክ ባለቤት የሆነን ህዝብ ትናንት የተፈጠረ ፓርቲ ብቻውን ሊነዳው አይችልም፡፡
አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው ኃይል የመገንጠል አማራጭ ሊወስድ የሚችል መሆኑን ሳይረፍድ መረዳት የሚገባ ይመስለኛል” ይላል ሚካኤል፡፡ እኔ ደግሞ ትግራይን ኢትዮጵያዊ አድርጎ የፈጠራት ሕወሓት ስላይደለ የመገንጠል ሀሳቡም ሆነ ስልጣኑ የለውም ባይ ነኝ፡፡ የትግራይ ህዝብ ሀገሩ ትግራይ ብቻ አይደለም፡፡ ሀገራችን የምንለው ሁሉ ሀገሩ ነው። ህዝቡ ለኦጋዴን ሞቷል፣ ለሞያሌ ነፍሱን ሰጥቷል፡፡ በሌሎች ግንባሮችም ዋጋ ከፍሏል፡፡ አሁን ደግሜ ማንሳት ባያስፈልገኝም እንደዛሬ ወያኔ በጎጥ ሳይለየን በፊት ለዚህች ሀገር ዋጋ የከፈሉ የቅርብ ሰዎቼን የአብሮ አደጎቼን ወላጆች ማስታወስ እችላለሁ፡፡
ሳጠቃልል፤ አቶ ሚካኤል የጻፉት መጽሐፍ በተለይ መግቢያና መውጫው ላይ ችኮላ ስለነበረበት፣ የአረፍተ ነገር አጠቃቀም፣ የአንቀፅ አደረጃጀት፣ የቃላት ግድፈት ጎልቶ ይታይበታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ገፅ 217 እና 218 ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ማስፈሩን፣ በምስጋናው ገፅ እንኳ ከአምስት በላይ ግድፈቶች መኖሩ፣ ገፅ 192 እና 193 የሚታየው፣ “አይቻለሁ፣ አስተውያለሁ” የሚል የሪፖርት ቋንቋ ያለ ቅጥ መበዛት፣ ጉዳዩን የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት አስመስሎታል፡፡
በመጨረሻም ለዶክተር ዐቢይ ብሎ የጻፈውንና ያሰፈረውን ሃሳብ እጋራለሁ! አሁንም ቅር የሚለኝ ግን ያ ሁሉ ግፍ ከሀገሪቱ ሰማይ ስር ሲፈፀም ጥሩ እንቅልፍ አግኝቶ፣ አሁን በለውጡ ጅማሬ “ለማስጠንቀቂያ” መባዘኑ ነው፡፡

የደቡብ ኮርያ መንግስት ተማሪዎችንና መምህራንን ቡና አብዝቶ ከመጠቀም ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ ችግሮች ለመጠበቅ በሚል በትምህርት ቤቶች ቅጽር ግቢ ውስጥ ቡና እንዳይሸጥ የሚከለክል ህግ ሊያወጣ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱን የምግብና የመድሃኒት ደህንነት ሚኒስትር መግለጫን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በሁሉም የአገሪቱ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ቡና ሲሸጥም ሆነ ሲገዛ የተገኘ ከፍተኛ ቅጣት ይጣልበታል፡፡
መንፈሳቸውንና ዘና ለማድረግና ለመነቃቃት በማሰብ በርካታ ተማሪዎችና መምህራን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ቡና በብዛት እየተጠቀሙ የልብ ምት መጨመርና የእንቅልፍ ማጣትን ጨምሮ ለተለያዩ የጤና እና የስነልቦና ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸው አሳስቦኛል ያለው ሚኒስቴሩ፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ በቡና ሽያጭ ላይ ክልከላ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በመዲናዋ ሴኡል ከ18 ሺህ በላይ የቡና መሸጫዎች እንዳሉና አንድ ደቡብ ኮርያዊ በአመት በአማካይ 181 ሲኒ ቡና ይጠጣል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም አገሪቱን ከእስያ ከፍተኛው የቡና ተጠቃሚነት ያለባት አገር ያደርጋታል ብሏል፡፡

 ገዢው ፓርቲ ያልበሰሉ ፖለቲከኞች አገር እንዳያጠፉ ያሰጋል ብሏል

    በአወዛጋቢ ምርጫ ስልጣኑን ያስጠበቀው የዚምባቡዌ ገዢ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ፣ ምራቃቸውን ዋጥ ያላደረጉና በወጉ ያልበሰሉ ግለሰቦች ለፕሬዚዳንትነት እየተወዳደሩ አገሪቱን ለቀውስ እየዳረጓት በመሆኑ፣ ዜጎች ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የሚችሉበትን የዕድሜ ገደብ ከ40 አመት ወደ 60 አመት ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጹን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው የዚምባቡዌ አገራዊ ምርጫ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ በአብላጫ ድምጽ ቢያሸንፉም፣ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኔልሰን ቻሜሳ፤ ምርጫው በመጭበርበሩ ውጤቱ ይሰረዝልን በሚል ለፍርድ ቤት ቢከስሱም በለስ እንዳልቀናቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ የ40 አመት ዕድሜ ያላቸው ኔልሰን ቻሜሳ ምርጫውን የልጅ ጨዋታ አድርገውታልና ከአሁን በኋላ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ቢያንስ 60 አመት የሞላቸው ዜጎች ሊሆኑ ይገባል ሲል ዛኑ ፒኤፍ ማስታወቁን አመልክቷል፡፡
የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ቻሜሳ በምርጫው ሲሸነፉ እንደበሳል ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደህጻን ልጅ በማኩረፍና የማይገባ ድርጊት በመፈጸም ጉዳዩን የልጅ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አድርገውታል፤ ከአሁን በኋላ እንደ እሳቸው ያለ ያልበሰለ ሰው ዘልሎ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የለበትም ብለዋል፤ የገዢው ፓርቲ የዛኑ ፒኤፍ የብሄራዊ ደህንነት ጸሃፊ ላሞር ማቱኬ፡፡
በአገሪቱ ክምር ቤት አብላጫ ወንበር የያዘው ፓርቲያቸው፤ ዜጎች ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የሚችሉበትን የዕድሜ ገደብ ከ40 አመት ወደ 60 አመት ለማድረግ በህገ መንግስቱ ላይ ማሻሻያ መደረግ የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር ጠንክሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን አንድ የፐርሺያ ንጉሥ ሁለት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው፡፡
በመጨረሻም፤ “የሞት ፍርዱ ከመፈፀሙ በፊት የፈለጋችሁትን ተናገሩ” ሲል እድል ይሰጣቸዋል፡፡
አንደኛው፤ “ምንም የምናገረው የለኝም” አለ ሁለተኛው፤
ንጉሡ ምን ያህል ፈረሳቸውን እንደሚወዱት ስለሚያውቅ፤
“ንጉሥ ሆይ፤ የአንድ ዓመት ጊዜ ከሰጡኝ ፈረስዎ ወደ ሰማይ እየከነፈ እንዲሄድ ላስተምረው እችላለሁ” አላቸው፡፡
ንጉሡ በሰማይ ላይ የሚከንፍ ፈረስ እየጋለቡ ሲሄዱ ታያቸው፡፡ ካሁኑ ነሸጣቸውና ይቁነጠነጡ ጀመር፡፡
“ይሁን አንድ ዓመት ሰጥተንሃል፡፡ ፈረሱን አምጥተው እንዲያስረክቡህ አደርጋለሁ” አሉ፡፡
የመጀመሪያው እሥረኛ በምንም አይነት ፈረስ እንደማይበር
ስለሚያውቅ ፈረስ አስተማሪውን እሥረኛ ጓደኛውን እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“ወዳጄ፤ ፈረስ በሰማይ እንደማይበር አሳምረህ ታውቃለህ፡፡ እንዲህ ያለ የዕብድ ሀሳብ ከየት አምጥተህ ነው ቃል የገባኸው፡፡ የመሞቻችንን ጊዜ ከማራዘም በስተቀር ምን ይፈይድልሃል?”
ፈረስ አስተማሪውም፤
“አይምሰልህ ወዳጄ፤ ነፃነቴን የማገኝባቸውን አራት ዕድሎች ራሴ መስጠቴ ነው”
አንደኛው እሥረኛም፤
“አራቱ ዕድሎች ምን ምን ናቸው?” ሲል በመጓጓት ጠየቀው፡፡
ፈረስ አስተማሪው፤ እንዲህ ሲል ዘረዘረለት፡-
1ኛ ወይ በዚህ ዓመት ውስጥ ንጉሡ ሊሞቱ ይችላሉ
2ኛ እኔም ልሞት እችላለሁ
3ኛ ወይ ደሞ ፈረሱም ሊሞት ይችላል
4ኛ ደሞስ ማን ያውቃል እኔ ፈረሱ በሰማይ እንዲበር ላስተምረው እችል ይሆናል
*   *   *
አበው ጠበብት ሦስት አይነት ጊዜ አለ ይሉናል፡፡ አንደኛው ረዥም ጊዜ የሚባለው ነው፡፡ ረዥም ጊዜ በትዕግሥት በጥንቃቄ እቅዶቻችንን ሁሉ ቀምረን የምንጓዝበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ተገደን የምንገባበት ጊዜ ነው፡፡ (Forced Time የሚሉት ነው ፈረንጆች፡፡) ይሄ አጭርና ጉዳያችንን ተጣድፈን፣ ተወጥረን በግዴታ ወደ ተግባር የምናስገባበት ነው፡፡ ሦስተኛው የፍፃሜ ጊዜ ነው፡፡ እቅዶችን የምንፈፅምበትና ግባችንን የምንመታበት ነው፡፡ እነዚህን ጊዜያት ወደ አገር መንዝረን ስናያቸው “ከእቅድ በላይ አመረትን”፣ “ከታሰበው ጊዜ ቀደም ብለን ግባችንን መትተናል”፣ “ሥር-ነቀል ለውጥ አካሂደን ሰፊውን ህዝብ የአብዮቱ ተጠቃሚ አድርገነዋል”… ወዘተ በማለት አያሌ መፈክሮችን ስናሰግር መክረማችንን እንድንመረምር ግድ ይለናል፡፡ በእርግጥ ግን ያቀድነውን እቅድና ጊዜያችንን በአግባቡ አጣጥመን ለአንዳች ፋይዳ በቅተናልን? ተጀምረው የተቋረጡ “እንደ እገሌ ህንፃ አቁሞ ያስቀርሽ!” “እንደ እገሌ መንገድ ያሽመድምድህ!” “እንደ አገሬ መብራት ድፍን ያርገኝ ብለህ ማል እስቲ!” “እንደ ዛሬው ውሃ ድርቅ ያርገኝ በል እስቲ!” “እንደ ኔትወርካችን ይበጣጥሰኝ! በል…” እስከመባባል ድረስ በምፀት፣ በስላቅና፣ በለበጣ ህይወት ውስጥ የምንጓዘው ከቶም እቅዳችን በጊዜው ተከናውኖ ነውን? ያሰኘናል፡፡
ናፖሊዮን ቦናፓርት “የተነጠቅነውን ቦታ ለማስመለስ እንችላለን፣ ያጠፋነውን ጊዜ ግን በጭራሽ” ይለናል። የበለጠ የከፋው ደግሞ ስለባከነው ሰዓት በመገማገም የምናባክነው ሰዓት ነው፡፡ ባለፈው መንግሥት፤ “የኮሚቴዎችን መብዛትና እንዴት እንደሚቀነሱ የሚያጠና ኮሚቴ ፍጠሩ!!” እንደተባለው ነው፡፡
“ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው፣ የሚያውቅ ሎሌው ያረገዋል
የተጃጃለውን ግና፣ ሎሌው አርጐ ይገዛዋል” ይለናል ገጣሚው፡፡ ይህን ልብ እንበል፡፡
የሙሰኞች መናኸሪያ የሆነችው አገራችን፤ የጊዜ ሌቦችም መደበቂያ መሆኗንም አንዘንጋ፡፡ ሙስና ከየትም የሚከሰት ተዓምር ሳይሆን የሰው ልጆች ራሳቸው ጊዜን እያዩ የሚፈፅሙት እኩይ ተግባር ነው። ዞሮ ዞሮ የሚያጠፋም ሰው፣ የሚያለማም ሰው ነው፡፡ ሰው የምንለው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ነው”
“ለመቶ አምሳ ጌታ፣
ስታጠቅ ስፈታ ነጠላዬ… አለቀ በላዬ”
ካለችው የበታች አካል ጀምሮ፤
“የእባብ መርዝም እንደዚያው፤ ሁሌም የሚፈለፈለው
ንጉሡ አናት ላይ ካለው፤ ከዘውዱ ወይራ ቅጠል ነው”
እስከሚለው ቄሣራዊ አገዛዝ ድረስ፤ የሙስና ፖለቲካዊ ዘይቤ መገለጫ ነው፡፡
ሰውም እንደ ሐምሌት፤
“…በምናውቀው ስንሰቃይ፣ የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችንም ማቅማማት፣ ወኔያችንንም ተሰልበን… መሆን ወይም አለመሆን?...”
እያለ ስለ በደሉ ማውጠንጠንን ኑሮ ብሎታል፡፡ ወዳጅም ሰው፣ ባላንጣም
ሰው፣ ደጋፊም ሰው፣ ተቃዋሚም ሰው፣ የበላይም ሰው፣ የበታችም ሰው ነው….
“ሰው ይጫኑብህ ግንድ?” ቢሉት፣
ግንድ ከተጫነኝ ሰው ያነሳልኛል፤
ሰው ከተጫነኝ ማን ያነሳልኛል?!” አለ፤ የሚለው የጉራጌ ተረት፤ ይሄንኑ በብርቱ ያፀኸያል!
ከአዘጋጁ፡- (ከላይ የቀረበው ርዕሰ አንቀጽ በአዲስ አድማስ ዌብሳይት ላይ Monday, 20 October 2014 ፖስት የተደረገና በድጋሚ ያወጣነው መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን)

   በወልቃይት ጠገዴ መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል

      በወልቃይት ጠገዴ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ ነው ያለው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ብሄርተኝነት አስመላሽ ኮሚቴ፤ በአካባቢው የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ የመከላከያ ሰራዊት በማሰማራት መፍትሄ እንዲያበጅ ለጠቅላይ ሚኒስትር በፃፈው የአቤቱታ ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባስገባው የአቤቱታ ደብዳቤ፤ በወልቃይት ህዝብ ላይ በትግራይ ክልላዊ መንግስት የስነ ልቦና እና አካላዊ ጥቃቶች እየተፈፀመ ነው ብሏል፡፡
“አድርሽኝ” በሚባል የአካባቢው ባህላዊ በዓል ላይ “በአማርኛ ቋንቋ ዘፍናችኋል” የተባሉ 20 ያህል ሰዎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምስል የታተመበት ቲ-ሸርት የለበሱ ወጣቶችም አካላዊ ጥቃትና እስር እንዳጋጠማቸው የጠቀሰው ኮሚቴው፤ የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት ጥያቄን የሚያነሱም እየታሰሩ ነው ብሏል ስማቸውን በመዘርዘር፡፡
“በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ከቀን ወደ ቀን እጅግ እየከበደ መጥቷል” ያለው ኮሚቴው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ አስቸኳይ እልባት እንዲያበጁ ጠይቋል፡፡
ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ታስረው የሚገኙ እንዲፈቱ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትም ለፍርድ እንዲቀርቡ በአቤቱታው ላይ ተጠይቋል፡፡
በአካባቢው ያለውን ስጋት ለመቀነስና ማህበረሰቡን ከጥቃት ለመከላከልም በአካባቢው የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሰማሩ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡    

 ከወር በፊት በሃዋሳ ከተከሰተው የወላይታና ሲዳማ ብሄር ተወላጆች ግጭት ጋር በተያያዘ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ 100 ግለሰቦች ላይ ትናንት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባን ጨምሮ በ100 ተጠርጣሪዎች ላይ ከተመሰረተው ክስ መረዳት እንደሚቻለው፤ በከተማዋ በሲዳማና ወላይታ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ፣ ከ10 በላይ ሰዎች እንዲሞቱና በርካቶች እንዲፈናቀሉ አድርገዋል ተብሏል፡፡ ከተማዋ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ጋር ከተከሰሱ ባለስልጣናት መካከል የሃዋሳ ከተማ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ስድስት የማረሚያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በድርጊቱ ተሳትፋችኋል በሚል በአቃቢ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡  



    አንዳንድ ታሪክ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን እንድ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ድንቅ መምህር ነበሩ፡፡ ለተማሪዎቹ የሚሰጧቸው ቋሚ ትዕዛዛት ነበሩ፡፡ ተማሪዎቹም ያከብሩዋቸውና ይወዷቸው ስለነበር ለጥ ሰጥ ብለው ትዕዛዛቱን ይቀበሉና ይተገብሩ ነበር፡፡
1ኛው ትዕዛዝ - የቤት ሥራህን አትርሳ
2ኛው ትዕዛዝ - ለሂሳብ አሰራር ቦታ ተው
3ኛው ትዕዛዝ - መልሱን ጥርት አርገህ ፃፍ
4ኛው ትዕዛዝ - አትኮርጅ
5ኛው ትዕዛዝ - ከኮረጅክ በትክክል ኮርጅ ግን መልስ ብቻ አትኮርጅ፤ አሰራሩን
በትክክል እይ፡፡ ቢያንስ ሥራውን አውቀህ ትገለብጣለህ፡፡
6ኛው ትዕዛዝ - የቅሪላ ማልፊያ (የኳስ) ጊዜህን ቀንስ፡፡ የቤት ሥራህን እንዳያዘናጋህ
አስብ፡፡
7ኛው ትዕዛዝ - ግብረገብነትን ውደድ
8ኛው ትዕዛዝ - ከክፍልህ አታርፍድ
9ኛው ትዕዛዝ - የክፍል ሥራህን ቀጥ ብለህ ሥራ
10ኛው ትዕዛዝ - እኔ ሥነግርህ አጠንጥን፤ “ፈተና ሲሰጥህ ተርትር”
11ኛው ትዕዛዝ - እናት አባትህን አክብር፡፡
*   *   *
ሀገራችን ብዙ ትዕዛዛትን ትሻለች፡፡ ትዕዛዝ አክባሪ ዜጋም ሊኖራት ይገባል፡፡ ከወሬ መላቀቅ ያስፈልጋታል፡፡ ሹም ሽር፤ የሥራ ኮንትራት መሆኑን ጠንክሮ ማስረዳት፣ መቆጣጠርና መከታተል የግድ መኖር አለበት፡፡ ሥርዓተ - አልባነት የወቅቱ አደጋ መሆኑንና ፈጦ - ገጦ መምጣቱን አስተውለን - “እናቴ ዕንቁላል ስሰርቅ ዝም ባላልሺኝ፤ በሬ ስሰርቅ ባልተያዝኩኝ” ያለውን ልጅ ማስታወስ ነው፡፡
የሥራ ባህላችንን ማጠንከር ግዴታ ነው፡፡ ግዴታችንን እንወቅ፡፡ የቤት ሥራችንን ለአፍ ወረት ብቻ አናውራ፡፡ የአሠራር ቦታ እንተው፡፡ መልሶቻችንን በግልፅ እናስቀምጥ! ህዝብ “የሥርዓት - ያለህ!” ብሎ እስኪጮህ አንጠብቅ፡፡ ትናንሽ የክፍል ሥራዎች ተጠራቅመው የአገር ችግር እስኪሆኑ ድረስ ዕድል አንስጥ፡፡
ከሁሉም በላይ ልብ መባል ያለበት የአገራችንን መላ - ችግር እንፍታ ካልን እንኳን ተጣልተን፤ ተፋቅረንና ተቧድነንም በቀላሉ የምንገላገለው እንዳይደለ ነው፡፡ ብዙዎች ከውጪ አገር ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸውን አይተናል፡፡ ይሄ አንድ ሁነኛ ነገር ነው፡፡ ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ተቃዋሚ እኪሱ ውስጥ ትንሽ ዘውድ ይዞ የሚዞር ነው፡፡ መቼ እንደምነግሥ አይታወቅም ባይ ነው!” ነገሩ ግን የመንገሥ ጣጣ ሳይሆን የሀገሪቱን ችግሮች አውጠንጥኖ ማወቅና አልጋ ባልጋ አለመሆኑን ተገንዝቦ መክሮ፣ ዘክሮ፣ ተቀናጅቶ፣ በጠላትነት ሳይፈራረጁ፤ ቅራኔ አፈታት አውቆ፤ ሽንፈትንም ድልንም ተቀብሎ መጓዝን መገንዘብ ነው፡፡ ዛሬ ዳር ቆሞ ተመልካች የማትፈልግ አገር ዘንድ እየደረስን ነው፡፡ ድርሻዬን እንዴት ላዋጣ? ከማለት ጀምሮ፣ እንዴት በአንድ ልብ እንሥራ? አንድ ትልቅ የአገር ጉዳይ ውጤት ባለው መልክ ዳር ለማድረስ አንዱ እየታገለ፣ ሌላው ዳተኛ እየሆነ፣ ፍሬ እናፈራለን ብሎ ማሰብ ዘበት ነው! የግድ ሀቀኛ ተዋናይ ሆኖ መድረኩ ላይ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ውሃ ዋና፤ ዳር ቆሞ አይሳካም፡፡ ያም ብርቱ ድካምን ይጠይቃል!   
የሁሉንም ተሳትፎ በሚሻ መልኩ የሁሉንም ርብርብ የሚፈለግበት ጊዜ ነው፡፡ አለበለዚያ፤ “አዳመጠች አረገዘችን አይሆንም” የሚለውን የአባቶች ብሒል መዘንጋት ነው!  



   ብዙ ሰዎች Fungal Infection በመባል በሚታወቀው የኢንፌክሽን አይነት ይጠቃሉ። መነሻችን ከብልት ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ ለማየት ቢሆንም ሰዎች ይህ ኢንፌክሽን ወይንም የሰውነት መመረዝ የሚደርስባቸው በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ነው፡፡ ከላይ የምትመለከቱት በፊትና በምላስ ላይ በምን መልክ እንደሚወጣ ነው፡፡ በሺዎች ከሚቆጠሩ የፈንገስ አይነቶችም ጥቂቶቹ ናቸው ሰውን ለሕመም የሚዳርጉት፡፡ ብዙ ሰዎች ደግሞ በተፈጥሮ የበሽታ መቋቋም ኃይላቸው ጠንካራ ስለሚሆን በዚህ በሽታ አይጠቁም፡፡ ለምሳሌም በሕክምና ያልታገዘ የኤችአይቪ ኢንፌክሽን ያለበት ሰው ወይም የካንሰር ሕመም ላለባቸው ሰዎች የሚሰጠው እንደ ኬሞቴራፒ ያለው ሕክምና የበሽታ መቋቋም ኃይልን ሊፈታተን ይችላል፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚወሰድ የበሽታ መከላከያ መድሀኒቶች (antibiotics) ለሕመሙ ለመጋለጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ባጠቃላይም የፈንገስ ኢንፌክሽን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ እንደሚወጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በእግር ላይ የሚወጣ ፈንገስ፤ ይህ የፈንገስ አይነት Tinea Pedis በመባል ይታወቃል፡፡
ሌላው ቀይ ወይንም ብርማ መልክ ያለው በሰውት ላይ የተጉረበረበ ምልክት የሚያሳይ ነው፡፡ ባብዛኛውም ክብ ቅርጽ የሚይዝ ነው፡፡
በጭንቅላት ወይንም በራስ ቅል ላይ የሚታየው በሳይንሳዊ አጠራሩም Tinea Capitis  ይባላል፡፡
Onychomycosis የተሰኘው የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚታየው በአብዛኛው በእግር አውራ ጣት ላይ ወይንም ሌላው የእግር አካል ላይ እንዲሁም በሌሎች ጣቶች ጥፍሮች ላይ ነው፡፡ ይህ በመራመድ ወይንም በመጫማት ጊዜ ሕመም ሊኖረው ወይንም ምቾት ሊያሳጣ ይችላል፡፡
Tinea Versicolor  የተሰኘው ደግሞ ከሌላው የአካል ክፍል ቀለምን ለየት በማድረግ በትናንሽ ክቦች በተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ የሚታይ የፈንገስ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ጠቆር ወይንም ደብዘዝ፤ ቀይ ወይንም ፒንክ እንደሚባለው ቀለም ባለ መልክ ከሌላው የቆዳ ክፍል ቀለም ሊለይ ይችላል፡፡
ብዙ ጊዜ ሙቀት ባለው ወይንም እርጥበት በሚሰማው የሰውነት ክፍል ሊፈጠር የሚችለው ደግሞ በሳይንሳዊ አጠራሩ Cutaneous Candidiasis ነው፡፡ ይህ አይነቱ ኢንፌክሽን ከተለያዩ ሕክምናዎች ወይንም ውፍረት ፤የስኩዋር ሕመም፤በመሳሰሉት ሁሉ ሊከሰት የሚችል በየትኛውም የቆዳ ክፍል ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
ከላይ የተገለጸው ይህ የኢንፌክሽን ሕመም በቆዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍ በጉሮሮ አካባቢ እንዲሁም ሴቶች በብልታቸው እንደሚከሰትባቸው እሙን ነው። ሴቶች በአብዛኛው ማለትም እስከ 75% የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው በብልት አካባቢ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ያጋጥማ ቸዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወደ 90% የሚሆኑት ኢንፌክሽኖች የሚፈጠሩት ደግሞ በሳይንሳዊ አጠራሩ Candida albicans በሚባለው ዝርያ አማካኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ከ20-50% የሚሆኑት ሴቶች በተፈጥ ሮአቸው ይህ Candida የተሰኘው በተፈጥሮ በብልታቸው የሚገኝ መሆኑም ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ጤናማ የሆነ ብልት ባክቴሪያ (Bacteria) እና (Yeast) ይስት እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን   ለኢንፌክሽን መፈጠር በብልት አካባቢ የሚ ኖረው ባክቴሪያ (Bacteria) እና (Yeast) ይስት በመባል የሚጠሩት መጠናቸው ሲዛባ በተለይም (Yeast) የይስት ህዋስ በእጥፍ ስለሚባዛ ችግሩ ይፈጠራል፡፡ በእርግጥ ይህ የኢንፌክሽን አይነት ምንም እንኩዋን በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት መተላለፍ ቢችልም ነገር ግን በግብረስጋ ግን ኙነት  ምክንያት ከሚተላለፉ በሽታዎች ውስጥ የሚመደብ አይደለም። ይህ የኢንፌክሽን አይ ነት በማንኛዋም ሴት ብልት ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
የፈንገስ ኢንፌክሽን ለመከሰቱ የሚታዩ ምልክቶች፤
በወሲብ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት፤
ሽንት ሲሸና ሕመም ወይንም ማቃጠል፤
ከብልት ውስጥ ወፈር ያለ ወደ ግራጫ የሚወስደው እና መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ካለ የኢንፌክሽን ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
የማሳከክ፤ የመቅላት ወይንም የመጉረብረብ…መልክ ካለ ኢንፌክሽን ተፈጥሮአል ማለት ነው፡፡
ብልት ለኢንፌክሽን ከሚጋለጥባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
በብልት ውስጥ መገኘት የሚገባው የባክቴሪያ መጠን ሲቀንስ፤
እርግዝና፤
የህክምና ክትትል የማይደረግበት የስኩዋር ሕመም፤
የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ ፤
የተሟላ አመጋገብ አለመኖር፤
የሆርሞን መጠን መዛባት፤
ጭንቀት፤
የእንቅልፍ እጦት፤
የመሳሰሉት ለዚህ ኢንፌክሽን መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሕመም በቀላሉ ሊታከም እና ሊድን የሚችል ነው፡፡
በሴቶች ብልት የኢንፌክሽን ሕመም ከ4/ሴቶች ሶስቱ ያህል በሕይወት ዘመናቸው የመያዝ አጋጣሚው አላቸው፡፡ አብዛኞቹ ቢያንስ ቢያንስ ለሁለት ያህል ጊዜ ሊታመሙ ይችላል፡፡ ከዚህ በተለየ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወደ አራት ጊዜ የታመሙ ሰዎች ካሉ ግን ተከታታይ የሆነ የህክምና እርዳታ እደሚያስፈልጋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢንፌክሽኑን መከላከል ይቻላል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፤
እርጎ በተ ጨማሪም ምግብን የሚረዱ እንደ ቫይታሚን ቢ ኮምፕሌክ ያሉትን መውሰድ፤
ልብስን በተመለከተም ከጥጥ የተሰሩ ወይንም ሐርነት ያላቸውን ልብሶች መልበስ
የውስጥ ሱሪን ሞቅ ባለ ውሀ ማጠብ፤
ከጥቅም ላይ የዋሉ የሴት ልብሶችን በቅርብ ጊዜ ወይንም በፍጥነት መተካትወይንም መለወጥ ያስፈልጋል፡፡
ማስወገድ የሚገቡ ነገሮች፤
እንደታይት የመሳሰሉ ሰውነትን የሚያጠብቁ እና ላስቲክነት ያላቸውን ልብሶች አለመጠቀም፤
እንደ ሽቶ ወይንም ጠረን መለወጫ የመሳሰሉ ኬሚካሎችን በብልት አካባቢ መጠቀምን ማቆም፤
ገላ በመታጠብ ጊዜ  ባጠቃላይ በብልት አካባቢ እርጥብ ልብስን ከውስጥ ለብሶ መቀመጥን ማስወገድ፤
የፈላ ውሀ ውስጥ መቀመጥ ወይንም መዘፍዘፍ ወይንም በተቀራረበ ሁኔታ ሙቀት ባለው መታጠቢያ ከመታጠብ መቆጠብ፤
ከላይ የተጠቀሱትን ድርጊቶች በመፈጸም ኢንፌክሽኑን አስቀድሞውኑ መከላከል ይቻላል፡፡

  የአሸባሪው ቡድን አይሲስ ታጣቂዎች በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ በምትገኘው የፑንትላንድ ግዛት አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችና ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአይሲስ ታጣቂዎች በአካባቢው በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በላኩት አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክት፣ “ለቡድኑ በቋሚነት ቀረጥ የማትከፍሉ ከሆነ፣ ለመሞት ዝግጁ ሁኑ” የሚል ማስፈራሪያ መስጠታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ አይሲስ ቀረጡን የጣለው በሶማሊያ አንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ ቀረጥ በመጣል ገቢ ከሚያገኘው ተቀናቃኙ የአሸባሪ ቡድን አልሻባብ የወሰደውን ልምድ ተመርኩዞ ሳይሆን አይቀርም ያለው ዘገባው፤ አይሲስ በደቡባዊ ሶማሊያ መንግስት ጦር ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እያጠናከረ መምጣቱንና ከአልሻባብ ጋር የነበረው ግጭት እየተባባሰ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

 ጆርጅ ክሉኒ በ239 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ቀዳሚነቱን ይዟል

    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ወንድ የፊልም ተዋንያንን ዝርዝር ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የ57 አመቱ የሆሊውድ ኮከብ ጆርጅ ክሉኒ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 239 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
ዋይኔ ጆንሰን በ124 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የአቬንጀርሱ ተዋናይ ሮበርት ዳውኒ ጁኒየር በ81 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
ክሪስ ሄምስዎርዝ በ64.5 ሚሊዮን ዶላር፣ የቻይናው ኮከብ ተዋናይ ጃኪ ቻን በ45.5 ሚሊዮን ዶላር፣ አሜሪካዊው ዊል ስሚዝ በ42 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ከአንደኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የፊልም ተዋንያን በድምሩ ከግብር በፊት 748.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡