Administrator

Administrator

ባለፈው ረቡዕ በአለማቀፍ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ዋጋ ቅናሽ መከሰቱን ተከትሎ፣ የአለማችን 500 እጅግ ባለጸጋ ቢሊየነሮች በዕለቱ በድምሩ 99 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ተነግሯል፡፡
ከአለማችን ባለጸጎች በዕለቱ ከፍተኛውን ኪሳራ ያስተናገዱት የአማዞን ኩባንያ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ሲሆኑ፣ ባለጸጋው ረቡዕ እለት 9.1 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በአለማቀፉ የአክሲዮን ገበያ ላይ በተከሰተው በዚህ ቀውስ ሳቢያ ከተጣራ ሃብታቸው ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የቀነሰባቸው የአለማችን ቢሊየነሮች 17 ናቸው ያለው ዘገባው፤ የአለማችን የቴክኖሎጂው ዘርፍ 67 ባለጸጎችም በድምሩ 32.1 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸውን አመልክቷል፡፡
በአንድ ቀን (ረቡዕ) ቢሊየነሮቿ በከፍተኛ ሁኔታ የከሰሩባት አገር አሜሪካ ናት ያለው ዘገባው፣ የአገሪቱ ቢሊየነሮች በድምሩ 54.5 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸውንም ገልጧል፡፡



    ወላጆቿና ወዳጅ ዘመዶቿ ትዳር እንድትይዝ ነጋ ጠባ መወትወታቸው ያሰላቻት ኡጋንዳዊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሉሉ ጀሚማ፤ ከውትወታው ነጻ ለመውጣት በማሰብ ከሰሞኑ ከራሷ ጋር በይፋ ጋብቻ መፈጸሟን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በፈጠራ ጽሁፍ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ የምትገኘው ሉሉ ጀሚማ፤ ከሰሞኑ የ32ኛ አመት የልደት በአሏን ባከበረችበት ስነስርዓት ላይ በቬሎ ሽክ ብላ ከራሷ ጋር መጋባቷ ተነግሯል፡፡
ጀሚማ በጋብቻ ስነስርዓቱ ላይ ለታደሙት 30 ያህል እንግዶቿ ባደረገቺው ንግግር፣ የህይወቷ ተቀዳሚ አላማ ትምህርቷን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅና ወደ ስራ ገብታ ውጤታማ ተግባር መፈጸም እንጂ ትዳር መመስረት አለመሆኑን በመግለጽ፣ እንድታገባ የሚወተውቷትን ወላጆቿንና ወዳጅ ዘመዶቿን ለማስደሰት ስትል ከራሷ ጋር ለመጋባት መወሰኗን አስታውቃለች፡፡
“አባቴ ገና የ16 አመት ልጃገረድ እያለሁ ነበር የሰርጌ ዕለት የማደርገውን ንግግር አርቅቆ የሰጠኝ፡፡ እሱም ሆነ እናቴ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትዳር የምይዝበትን ቀን በመናፈቅ ፈጣሪ ጥሩ ባል እንዲሰጠኝ ሲጸልዩልኝ ነው የኖሩት፡፡ እኔ ግን አላማዬ ትዳር አይደለም” ብላለች ጀሚማ፡፡
ጀሚማ ከራሷ ጋር ለተጋባችበት ሰርግ ያወጣቺው ወጪ፣ በነጻ ወዳገኘቺው አዳራሽ ለሄደችበት ትራንስፖርት የከፈለቺው 2.62 ዶላርና የቬሎ መግዣ ብቻ ነው ያለው ዘገባው፤እምር ድምቅ ያለቺባቸውን ጌጣጌጦች ከእህቷ በውሰት ወስዳ መጠቀሟን፤ የማስዋብና የማሰማመር ሃላፊነቱን አንድ ጓደኛዋ በነጻ እንደከወነችላት፣ ወንድሟ ደግሞ የኬክ ወጪውን እንደሸፈነላት አክሎ ገልጧል፡፡

Sunday, 14 October 2018 00:00

ከመጠምጠም መማር ይቅደም

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ባልንጀራዎች ነበሩ፡፡ ወደ አንድ ሩቅ አገር ለመሄድ አስበው መንገድ ጀመሩ፡፡ አንደኛው በሽተኛና ለቋሳ ነው፡፡ ሁለተኛው ብርቱና ጤናማ ሰው ነው። የሚሄዱት በረሀውን አቋርጠው ነው፡፡ ፀሐዩ ያነድዳል፡፡ አሸዋው ያቃጥላል፡፡ በረሀው ረዥምና ሰፊ ነው፤ አቅምና ወኔ ይፈታተናል፡፡ በዋዛ ማለፍ አልተቻለም፡፡
በሽተኛው ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ ጤነኛውና ጠንካራው፤ በሽተኛውን ከወደቀበት አንስቶ ተሸክሞ፣ በረሀውን እስኪጨርሱ ድረስ ተጓዙ፡፡ አወረደውና ጥቂት አረፍ አሉ፡፡
አየሩ እየቀዘቀዘ፣ ጀንበሯ እያዘቀዘቀች መጣች፡፡ ጥቂት እንደሄዱ “እንተኛ?” አለ በሽተኛው፡፡
“እውነትክን ነው፡፡ በጊዜ መተኛት፣ በጠዋት መነሳት፣ የጤንነት ምንጭ ነው! የጠቢብነት መሰረት ነው፡፡ ሀብትም፡፡”
“Early to bed
and early to rise
makes a man, healthy, wealthy and wise. እንዲሉ ፈረንጆች፡፡” አለ ጤነኛውና በሳሉ ጓደኛው፡፡
ተኙ፡፡
ማታ ነው - የጅብ ሰዓት፡፡ ጅብ፤ ጓደኛሞቹ ወደተኙበት መጣ፡፡ በሽተኛው የጅቡን እንቅስቃሴ ሰምቶ፣ አወቀው፡፡ ስለዚህ ጎኑ ያለውን የበረሀ ጓደኛውን ትቶ ሮጠና ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ጅቡ ወደተኛው ሰው ተጠጋ፡፡ ጆሮው ዙሪያ ተጠግቶ አሸተተውና ምንም ሳያደርገው ሄደ፡፡ ጅብ የሞተ አይነካምና፡፡
 ይህ ሁሉ ሲሆን በሽተኛ ጓደኛው ዛፍ ላይ ሆኖ ቁልቁል ይመለከታል፡፡ ጅቡ ከራቀ በኋላ ከዛፉ ላይ ወረደና ወደ ጓደኛው ሄደ፡፡ ለካ ጓደኛው የጅብን ባህሪ ስለሚያውቅ ነው፣ ፀጥ እረጭ ብሎ የሞተ ያስመሰለው!!
በሽተኛው ጤነኛውን ጠየቀው፡- “ጅቡ አፉን በጣም ጆሮህ ላይ አቅርቦ ምን አለህ?”   
ጠንካራው ሰውም እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“ሁለተኛ፤ በክፉ ቀን የሚከዳ ባልንጀራ አትያዝ ብሎኝ ነው ያለፈው!” አለው፡፡
*   *   *
ለካ የሞተ መምሰል አንዳንዴ አሪፍ እስትራቴጂ ነው! ጊዜን የማወቅ ጉዳይ ነው፡፡ መንጋትና መምሸቱን ከማያውቅ ትውልድ ይሰወረን! ከከሀዲም ያድነን!
“ትላንቱን የማያውቅ
ዛሬን የሚያሳስቅ
 ነገን የሚደብቅ
እንደኖረ ሳይሆን እንዳይኖረው ይወቅ” -- ብሏል ገጣሚው ፀጋዬ ገብረመድህን በ”ቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ ላይ”-  ይህን መሳዩን ትውልድ፡፡
“ሽማግሌውን ባንቀልባ፣ ከምንሸከም እንኮኮ
ጎልማሳውን ከወኔ ጣር፣ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ”  
እንደ ወዶ ገባ ኮርማ፣
መጠለሉን ከሴት ታኮ
ካቀቃተን ምንድን ነን እኮ?”
 ትውልድን ማዳን ፀጋ ነው፡፡ ጥረታችን እዚያ ዙሪያ ይሁን፡፡ “ወጣት የነብር ጣት” የሁሉም ዘመን ማተብ አይደለም! “የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙ ጭራሽ አይለቁም” የሚባለው ለለውጥም ይሰራል፡፡ (ለውጡ ጅራት ይኑረውም አይኑረውም) ለማናቸውም ዓይነት ለውጥ መዘጋጀት፡፡ ከማናቸውም ዓይነት ለውጥ መነሳትና ለማጥበቅ ሀሞትን መሰነቅ እንጂ እህህም እህህም የትም አያደርስምና፡፡ “እህህን ለፈረስ ያስተማርኩ እኔ ነኝ እሱንም ቢርበው እኔን ሲቸግረኝ” (ለመሆኑ እህህ … ምን ያህል ረጅም ነው? ሳንወለድ ጀምሮ ስንሞትም እሱ ቀጣይ ነው?!) Sustainable poverty /ዘላቂ ድህነት/ መኖር አለመኖሩን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ይንገሩን፡፡
“ወጣቱማ ይማር! ቢፈልግ ደግሞ ይማረር
ሀሁውን በቅጡ ይቁጠር
ጥቁር መጋረጃ ይቅደድ
ፈተናን መሸሽ ያስወግድ
የልጅነቱን ያህል ይሂድ!
የወጣትነቱን ይንደድ
የጎልማሳነቱን ይውደድ
እንጂ በትኩሳት ብቻ፣ በጀማነትም አይንደድ!
በዚህም በዚያኛውም ስም፣
ትርፍ ፍለጋ አይሰደድ!
ለተሻለ ነገር ሁሉ፣ በራሱ መንገድ ይወደድ!”
ብቻ ለማናቸውም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር፤ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም!!

 በሳምንቱ መጀመሪያ በተካሄደው የአሜሪካን ሚዩዚክ አዋርድ፣ አራት ሽልማቶችን ያገኘቺው ታዋቂዋ አሜሪካዊ ድምጻዊት ቴለር ስዊፍት፣ ያገኘቻቸውን ሽልማቶች 23 በማድረስ፣ በሴቶች ዘርፍ አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቧ ተዘግቧል፡፡ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው አመታዊው አሜሪካን ሚዩዚክ አዋርድ ስነስርዓት ላይ የአመቱ ምርጥ አርቲስትን ጨምሮ በአራት ዘርፎች የዋንጫ ተሸላሚ በመሆን ያገኘቻቸውን ሽልማቶች 23 ያደረሰቺው ቴለር ስዊፍት፤ በዊትኒ ሆስተን ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን መስበሯን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ድምጻዊቷ በሎሳንጀለስ የማይክሮሶፍት ቴአትር በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓት ላይ ባደረገቺው ንግግር፤ በመጪው ህዳር መጀመሪያ ላይ በሚካሄደው የአሜሪካ የሚድተርም ምርጫ ላይ ዲሞክራቶችን ወክለው ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለደጋፊዎቿ ጥሪ አቅርባለች፡፡

   ዱባይ ከቱሪስቶች 29.7 ቢ. ዶላር በማግኘት ቀዳሚ ከተማ ናት


    ለሁለት ተከታታይ አመታት በብዛት በመጎብኘት ከአለማችን ከተሞች ቀዳሚነቱን ይዛ የቀጠለቺው የታይላንድ ርዕሰ መዲና ባንኮክ፣ ዘንድሮም በ20.5 ሚሊዮን አለማቀፍ ቱሪስቶች በመጎብኘት፣ የአንደኛነት ስፍራዋን ማስጠበቋ ተነግሯል፡፡
ማስተርካርድ የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን የአለማችን የአመቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች ሪፖርትን ጠቅሶ ፎርብስ እንደዘገበው፣ ባንኮክ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ በ20.5 ሚሊዮን አለማቀፍ ቱሪስቶች የተጎበኘች ሲሆን ይህ የጎብኝዎቿ ቁጥር በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2018 መጨረሻ በ9.06 በመቶ  እድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመላው አለም የሚገኙ 162 ከተሞችን የአመቱ አለማቀፍ የንግድና የቱሪዝም ጎብኝዎች ፍሰት መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት፣ ከባንኮክ ቀጥሎ ያለውን የሁለተኛነት ደረጃ የያዘቺው የእንግሊዟ ርዕሰ መዲና ለንደን ስትሆን ከተማዋ በአመቱ በ19.83 ሚሊዮን ሰዎች ተጎብኝታለች፡፡
የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በ17.44 ሚሊዮን አለማቀፍ ጎብኝዎች የሶስተኛነት ደረጃን ስትይዝ፣ ዱባይ በ15.79 ሚሊዮን ጎብኝዎች በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሲንጋፖር በ13.91 ሚሊዮን፣ ኒው ዮርክ በ13.13 ሚሊዮን፣ ኳላላምፑር በ12.58 ሚሊዮን፣ ቶኪዮ በ11.93 ሚሊዮን፣ ኢስታምቡል በ10.7 ሚሊዮን፣ ሴኡል በ9.54 ሚሊዮን ሰዎች በመጎብኘት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአምስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
በፈረንጆች አመት 2017 ከአለማቀፍ ቱሪስቶች ብዙ ገቢ በማግኘት ከአለማችን ከተሞች ቀዳሚነቱን የያዘቺው ዱባይ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ከተማዋ በአመቱ በድምሩ 29.7 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን አመልክቷል፡፡ ከአለማቀፍ ቱሪስቶች ብዙ ገቢ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን የያዘቺው የሳኡዲ አረቢያዋ መካ በአመቱ በድምሩ 18.45 ቢሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን  ለንደን 17.45 ቢሊዮን ዶላር፣ ሲንጋፖር 17.02 ቢሊዮን ዶላር፣ ባንኮክ በ16.36 ቢሊዮን ዶላር በቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡

 የ2019 የፈረንጆች አመት የታይም የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም የአንደኛነት ደረጃን መያዙ ተዘግቧል፡፡
ሌላው የእንግሊዙ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ካምብሪጅ የአምና ክብሩን በማስጠበቅ የሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የአሜሪካው ስታንፎርድ አምና በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በአመቱ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የአሜሪካዎቹ ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ሃርቫርድ፣ ፕሪንሲቶንና የል ሲሆኑ፣ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ስምንተኛ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በአመቱ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝሩ ውስጥ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን የያዘቺው አሜሪካ ስትሆን፣ በዝርዝሩ ውስጥ 172 የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካተታቸው ተነግሯል፡፡ ጃፓን 103 ዩኒቨርሲቲዎቿን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት የሁለተኛነት ደረጃን ስትይዝ፣ ቻይና በበኩሏ 72 ዩኒቨርሲቲዎቿን በዝርዝሩ አካትታ ሶስተኛነቱን ይዛለች፡፡

 ባለቤታቸው ጠ/ሚ ናጂብ ራዛቅ የተመሰረቱባቸው ክሶች 25 ደርሰዋል

   
   በስልጣን ዘመናቸው ፈጽመዋቸዋል በተባሉ የገንዘብ ማጭበርበርና በስልጣን የመባለግ ወንጀሎች 25 ክሶች የተመሰረቱባቸው የቀድሞው የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ሮሳማህ ማንሶር፣ 17 የታክስና ገንዘብ ማጭበርበር ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡
የቅንጦት ኑሮን በመውደድና በሚሊዮን ዶላሮችን እያወጡ በውድ ጌጣጌጥ በማሸብረቅ የሚታወቁት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮሳማህ ማንሶር፣ ረቡዕ በአገሪቱ የጸረ ሙስና ተቋም ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከትናንት በስቲያ በኳላላምፑር ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ66 አመቷ ሮሳማህ ማንሶር ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት ምላሽ፣የተከሰሱባቸውን ሁሉንም የወንጀል ድርጊቶች አለመፈጸማቸውን ገልጸው፣ ክሶቹን መቃወማቸውንና የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱም በግማሽ ሚሊዮን ዶላር  ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ መፍቀዱን አመልክቷል፡፡
በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሙስና ቅሌት 21 የወንጀል ክሶች ተመስርቶባቸው የነበሩት የቀድሞው የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ፤ ባለፈው ሳምንት 556 ሚሊዮን ዶላር የህዝብ ገንዘብ ያለ አግባብ ወደ ግል ካዝናቸው ከማስገባታቸውና በስልጣን ከመባለጋቸው ጋር በተያያዘ፣ አራት አዳዲስ ክሶች እንደተመሰረቱባቸው  ተዘግቧል፡፡  


የመጀመሪያው ባለ 10ጂቢ ራም ሞባይል እየመጣ ነው

   የሞባይል ቴክኖሎጂ እየተራቀቀ መምጣቱን ተከትሎ፣ ፎቶ ለመነሳት ወደ ፎቶ ቤት መሄድ ታሪክ እየሆነ መጥቷል፤ ህጻን አዋቂው ሞባይሉን ወደ ራሱ ደግኖ፣ በሰኮንዶች እድሜ ውስጥ ጥርት ኩልል ያለ የራሱን ፎቶ ማንሳት ጀምሯል፡፡
ጥራት ያላቸው ካሜራዎች በተገጠሙላቸው ሞባይሎች ተጠቅመው፣ ራሳቸውን ፎቶ በማንሳት ወይም ሰልፊ ሱስ የተጠመዱ ሰዎችን ማየት የተለመደ አለማቀፋዊ ክስተት እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ ችግሩ ግን የራሳቸውን  አስገራሚ ፎቶ ለማንሳት ከመጓጓት የተነሳ ለአደጋና ለሞት የሚጋለጡ የሰልፊ ሱሰኞች እየበዙ መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የተሰራን አንድ አለማቀፍ ጥናት ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ ባለፉት ስድስት አመታት ብቻ በአለማችን 259 ሰዎች በአደገኛ ሁኔታ ራሳቸውን ፎቶ ለማንሳት ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸው የተረጋገጠ ሲሆን በዚህ ሰበብ መሞታቸው ሳይታወቅ የቀሩ እጅግ በርካቶች እንደሚኖሩም ይገመታል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሰልፊ ምክንያት ለሞት ከተዳረጉት መካከል 72.5 በመቶው ወንዶች እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ አብዛኞቹ ከተራራና ከሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ጫፍ፣ ባህር ውስጥና በፍጥነት በሚበርሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ሆነው፣ እንዲሁም ከአደገኛ እንስሳት ጋር ፎቶ ለመነሳት ሲሞክሩ ለሞት የተዳረጉ መሆናቸውን  አመልክቷል፡፡ በአደገኛ ሁኔታ ሰልፊ ለመነሳት ከሚደረግ ሙከራ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የሞት አደጋዎች ከሚበዙባቸው የአለማችን አገራት መካከል ህንድ፣ ሩስያ፣ አሜሪካና ፓኪስታን እንደሚጠቀሱ የጠቆመው ዘገባው፣ በመሰል ሁኔታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከአመት ወደ አመት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ቴና የተባለው የቻይና ታዋቂ የሞባይል ስልኮች አምራች ኩባንያ፣ ኦፖ ፋይንድ ኤክስ የተሰኘውንና በአለማችን የመጀመሪያውን ባለ 10ጂቢ ራም የሞባይል ስልክ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን ዘ ቨርጅ የቴክኖሎጂ ድረገጽ ዘግቧል፡፡ በአለማችን የሞባይል ስልኮች ኢንዱስትሪ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ራም ወይም ውስጣዊ የመረጃ መያዝ አቅም ተብሎ ሲጠቀስ የነበረው 8 ጊጋ ባይት ራም እንደነበረ ያስታወሰው ዘገባው፤ ኦፖ ፋይድ ኤክስ የተባለው አዲሱ ሞባይል ግን ባለ ሁለት ዲጂት ጊጋ ባይት የመረጃ መያዝ አቅም ተጎናጽፎ በመምጣት በታሪክ የመጀመሪያው ሞባይል ይሆናል መባሉን ገልጧል፡፡
አዲሱ ሞባይል ከአንዳንድ መካከለኛ ዋጋ የሚያወጡ ላፕቶፖች የበለጠ መረጃ የመያዝ አቅምና ፍጥነት እንዳለውም ተነግሯል፡፡ ኦፖ ፋይድ ኤክስ ከዚህ በተጨማሪም ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ያህል ብቻ ቻርጅ ተደርጎ ግማሽ ያህል ባትሪው የሚሞላ መሆኑና ካሜራዎቹም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምስሎችና ቪዲዮዎች የመቅረጽ ብቃት ያላቸው መሆናቸው ሞባይሉን በገበያ ዘንድ ተመራጭ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ስልኩ ተመርቶ በገበያ ላይ የሚውልበትን ትክክለኛ ወቅት በተመለከተ በይፋ የተባለ ነገር አለመኖሩን ገልጧል፡፡

 በስዊዘርላንዳዊው ሳይንቲስት አልፍሬድ ኖቤል መታሰቢያነት በተለያዩ ዘርፎች በየአመቱ ሽልማት የሚሰጠውና መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ያደረገው የኖቤል የሽልማት ተቋም፣ የ2018  የኖቤል ተሸላሚዎችን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ማድረግ ጀምሯል፡፡
ተቋሙ ባለፈው ሰኞ የአመቱን የኖቤል የህክምና ዘርፍ ተሸላሚዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በካንሰር ህክምና ዘርፍ የላቀ ፈጠራ ያበረከቱት ጄምስ ፒ አሊሰንና ታሳኩ ሆንጆ የተባሉ የዘርፉ ዝነኛ ሳይንቲስቶች ሽልማቱን እንደተጋሩት ታውቋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው የፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚዎች መረጃ ደግሞ፣ በመስኩ አዲስና ፈር-ቀዳጅ የፈጠራ ውጤት ያበረከቱት አሜሪካዊቷ አርተር አሽኪን፣ ፈረንሳዊው ጄራርድ ሞሩ እና ካናዳዊቷ ዶና ስቲክላንድ በጋራ አሸናፊ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ካናዳዊቷ ዶና ስቲክላንድ፣ የኖቤል የፊዚክስ ሽልማትን ከ55 አመታት በኋላ ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ሳይንቲስት ሲሆኑ፣ ሌላኛው የዘርፉ ተሸላሚ የ96 አመቱ አሜሪካዊ አርተር አሽኪን ደግሞ በኖቤል ሽልማት ታሪክ እጅግ ካረጁ በኋላ የተሸለሙ የመጀመሪያው የእድሜ ባለጸጋ ናቸው ተብሏል፡፡
 ተቋሙ ባለፈው ረቡዕ ከስቶክሆልም ይፋ ባደረገው መረጃ፣ አሜሪካዊቷ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ኤች አርኖልድ፣ ከሌላኛው የአገሯ ልጅ ጆርጅ ፒ ስሚዝና እንግሊዛዊው ግሪጎሪ ፒ ዊንተር፣ በጋራ በኬሚስትሪ ዘርፍ የአመቱ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የኬሚካል ምህንድስና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ኤች አርኖልድ፣ በኖቤል ሽልማት ያለፉት 117 አመታት ታሪክ፣ በኬሚስትሪ ዘርፍ ተሸላሚ የሆኑ አምስተኛዋ ሴት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት በነበረውና ትናንት ይፋ የተደረገው የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ዘርፍ ውጤት ደግሞ፣  ጾታዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን ለማሰቀረት ውጤታማ ስራ ያከናወኑት ኮንጓዊው ዴኒስ ሙክዌጌ እና በአሸባሪው ቡድን አይሲስ ለወሲብ ባርነት ተዳርጋ የነበረቺው ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ ተሸላሚ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡
የዘንድሮው የኖቤል የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሸላሚዎች ከነገ በስቲያ ይፋ እንደሚደረጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የኖቤል የሽልማት ተቋም ዘንድሮ በስነጽሁፍ ዘርፍ እንደማይሸልም አስታውቋል፡፡
የኖቤል የሽልማት ተቋም ከተመሰረተበት እ.ኤ.አ ከ1901 አንስቶ 585 ሽልማቶችን ለ896 ግለሰቦችና 27 ተቋማት የሰጠ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች እስካሁን 49 ሴቶች መሸለማቸው ተነግሯል፡፡ በለጋ እድሜ የኖቤል ሽልማትን በመሸለም ቀዳሚነቱን ይዛ የምትገኘው በ2014 ላይ በ17 አመት ዕድሜዋ፣የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያገኘቺው ማላላ ዩሱፋዚ ናት፡፡

 በ”ጉዞ ሚዲያና ማስታወቂያ” በየወሩ የሚዘጋጀው “ብራና ጃዝ” የኪነ ጥበብ ምሽት የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ምሽት፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያፀኑ ልዩ ልዩ ጥበባዊ ክዋኔዎች እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን አንጋፋው ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ አስቴር በዳኔ፣ ሰለሞን ሳህለና ትዕግሥት ማሞ በመሶብ ባህላዊ ባንድ ታጅበው ግጥሞቻቸውን ያነባሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ዲስኩር የሚያቀርቡ ሲሆን በአንጋፋው አርቲስት ተስፋዬ ገ/ሃና አጭር ተውኔት፣ በወጣቷ ፀሐፊ ፅጌረዳ ጎንፋ ደግሞ  ወግ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡