Administrator

Administrator

አዲስ አበባ፤ አዲስ አስተዳደር ካገኘች ሁለት ወር አስቆጠረች፡፡ በፌደራል ደረጃ እየተካሄደ ከሚገኙት ለውጦች አንፃር በከተማችን አዲስ ለውጦችን ብንጠብቅ አይፈረድብንም፡፡ ለዛሬ ብዕሬን ያነሳሁት፣ አዲሱ አስተዳደር በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ለመገምገም ሳይሆን የኛን የከተማዋን ዜጐች ምኞት፣ተስፋና ሥጋት በመግለጽ፣ አዲሱ አስተዳደሩ ትኩረት ሊያተኩርባቸው ይገባል የምላቸውን አንዳንድ ሃሳቦች ለመሰንዘር ነው፡፡
1ኛ) አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ቀልጣፋ ማድረግ፤
አገልግሎት ሲባል በጣም በርካታ ጉዳዮች እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርት፣ ግብር አሰባሰብ ያሉትን እጅግ ሰፊና ውስብስብ ጉዳዮች የሚያካትት ነው፤ በየራሳቸዉ ርዕስ ሆነው፣ ብዙ ሊፃፍባቸው የሚችሉም ናቸው፡፡ የዛሬው ትኩረቴ በተመረጡ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ ከአካባቢ ውበትና ፅዳት ስንነሳ፣ አዲስ አበባን የፌደራል መንግስት መቀመጫ፣ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ፣የአፍሪካ መዲና ወዘተ…እያልን  እናሞካሻታለን፡፡ እውነታው  ግን አዲስ አበባ በማንኛውም መመዘኛ፣ ሊጠቀሱ ከሚችሉ የአፍሪካ ከተሞች ባነሰ ደረጃ ላይ መገኘቷ ነው። ለስብሰባ ወይም እግር ጥሎት አዲስ አበባ የተገኘን የውጪ ዜጋ - አውሮፓዊ ወይም አሜሪካዊ፣ አይደለም አፍሪካዊ፣ አንድ ተጨማሪ ቀን ለማቆየት የሚያበቃ ሰው ሰራሽ ሆነ ተፈጥሮአዊ መስህብ አላደራጀችም፡፡ አዲስ አበባ አሁንም ድረስ ሰዎችና እንስሳት አብረው የሚኖሩባት ትልቅ መንደር ነች የሚሏት አሉ፡፡ እውነት ነዉ፣  በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎችና አደባባዮች የቀንድ ከብቶች፣ አህዮች፣ በጎችና ባለቤት አልባ ውሾች ሲተረማመሱ መመልከት በጣም የተለመደ ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ የከተማዋን የገፅታ ግንባታ  ጥላሸት የሚቀባ ብቻ ሳይሆን የትራፊክ ፍሰቱን በእጅጉ የሚያስተጓጉል፣ የከተማዋን የፅዳት ሁኔታ የሚያበላሽ እንዲሁም መንገዶችንና ያሉትን ጥቂት አረንጓዴ ቦታዎች የሚያጎሳቁሉ መሆኑን መረዳት አዳጋች አይደለም።
እውን ይህን ይህን ሁኔታ መለወጥ የማይቻል ሆኖ ነው ወይስ በተለመደው ቸልተኝነታችን ተላምደው ነዉ? ዛሬ ዛሬ የገጠሩ ሕዝባችን እንኳን ቤት ሲሰራ የሰዎችንና የእንስሳቱን ለይቶ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች አያስፈልጉንም  እያልኩ አይደለም፤ ወይም በከብት እርባታና ንግድ ኑሯቸዉን የሚገፉ ዜጎች መኖራቸው ተዘንግቶኝም አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት ለምን በተሻለ መንገድ አናካሂደውም ነዉ? አዲሱ የከተማው አስተዳደር  ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ተግቶ መስራት ይኖርበታል  ብዬ አስባለሁ፡፡  አዲስ አበባ የዘመናዊነት መስታወት እንጂ የእንስሳት መራኮቻ መሆኗ ማብቃት አለበት፡፡
የማዘጋጃ ቤት አገልግሎትን ከማዘመንና ቀልጣፋ ከማድረግ ጋር ተያይዞ መጠቀስ የሚገባቸው ሌሎች በርካታ ጉዳዮችም አሉ። በተለይ የስራ ቅልጥፍናን ከመፍጠርና ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ፣ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፣ ለአገልግሎቶች ዝቅተኛውን ደረጃ መወሰንና ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች ላይ የተሰማሩ ሁሉ ሊያሟሏቸዉ የሚገቡ መሰረታዊ ደረጃዎች ተለይተው ሊነገሯቸው ይገባል፡፡ ብዙዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች፤ ንፅህናቸው በእጅጉ የተጓደለ፣ የተጎሳቆሉና ጥገና ስለማይደረግላቸው፣ በሚያወጡት ጭስ፣ የከተማዋን የአየር ብክለት በማባባስ ላይ ናቸው። አብዛኛዎቹ የከተማዋ ህንፃዎች፤ አካል ጉዳቶችን ታሳቢ አለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን የአደጋ ጊዜ መውጫ የሌላቸው ናቸው።
የህንፃው ተጠቃሚዎች እንኳ መኪኖቻቸውን የሚያቆሙበት ቦታ ስለማያዘጋጁም፣ መንገዶች ሁሉ ወደ መኪና ማቆሚያነት እየተቀየሩ ናቸዉ። የከተማ  መንገዶች  አሰራርና አስተዳደርም እንደዚሁ የተዘበራረቀና ለተጠቃሚዎች የማይመች ናቸው። እኛ ደሃ አገር ነን፤ እየሰራን እያፈረስን ልንቀጥል አንችልም፡፡ ሐብታችንን መቆጠብና በጥንቃቄ  መጠቀም አለብን፤ ይህ ደግሞ በዘመቻ ሳይሆን አቅዶ መስራትን የግድ ይላል፡፡ ከተማዋ የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሊኖራት ይገባል፡፡
የውሃ አቅርቦት ሌላዉ የአገልግሎት አይነት ነው:: በአለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ከተሞች ለመጠጥና ለሌላ ስራ (ለፋብሪካ፣ ለማጠቢያ፣ ለአትክልት) የሚውለውን ውሃ ለይተው ያቀርባሉ:: ይህም ብቻ ሣይሆን የአንድን ግለሰብ (ቤተሰብ) ዝቅተኛውንና ከፍተኛውን የፍጆታ መጠን ይወስናሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት የውሃ ሃብትን በአግባቡ አለመጠቀምና ስርጭቱንም ፍትሃዊ ለማድረግ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እንደምናውቀው፣ 24 ሰዓት ያልተቋረጠ ውሃ የሚያገኙ አካባቢዎች አሉ፤ በተቃራኒው  አንድ ወርና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ፣ እጅግ መሰረታዊ የሆነው የውሃ አቅርቦት የሚነፈጋቸው አካባቢዎችም  አሉ፡፡ ይህ በአጭር ጊዜ ባይሆን በመካከለኛ ጊዜ እንዲሻሻል መስተዳደሩ ተግቶ ሊሰራ ይገባዋል፤ በሌላ በሌላው ብንለያይ በውሃማ ሊሆን አይገባም፡፡
2ኛ) የአካባቢ ፅዳትና ውበትን ማሻሻል፤
የአዲስ አበባ የጽዳት ጉድለት ብዙ ተነግሮለታል። ለችግሩ መባባስ መስተዳደሩም ነዋሪውም አስተዋፅኦ አደርገዋል፡፡ ከተማና ከተሜነት የራሳቸው የሆነ መለያ ባህሪያት አሏቸው። እንደ ድፍረት እንዳይቆጠርብን እንጂ፣ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከተሜነት ይጎድለዋል፡፡ አዲስ አበባ እኮ ሥልጡን ነን ባዮች (ዘመናዊ መኪና የሚያሽከረክሩት ሳይቀር)፣ የበሉትን የሙዝና ብርቱካን ልጣጭ እንዲሁም  የተገለገሉበትን ዕቃ በየጎዳናው የሚጥሉ፤ ዘመናዊ  መኖሪያ ቤት ውስጥ እየኖሩ የራሳቸውን ቆሻሻ ከግቢያቸው አስወጥተው መንገድ ላይ የሚደፉ፣ ይባስ  ብሎም በየመንገዱና አጥር ስር  የሚፀዳዱ ሰዎች--የሞሉባት ከተማ ነች፡፡ ታዲያ እኛ  አዲስ አበቤዎች፣ ከተሜነት አይጎድለንም ትላላችሁ? በዓመት በዓል ሰሞን የሚታየውን በየመንገዱ የተዝረከረከ የእርድ ተረፈ ምርት ለተመለከተ፣ ለከተማው መቆሸሽና መጎሳቆል ዋናው ተጠያቂ፣ ነዋሪው መሆኑን አይጠራጠርም፡፡ እንዲያም ሆኖ የከተማው አስተዳደር፣ ተግባሩን በትክክል እየተወጣ ነው ማለት አይደለም፡፡ የህዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸውና አማካይ በሆኑ ቦታዎች፣ በበቂ መጠን መገኘት ሲኖርባቸው፣ በፍለጋ እንኳን የማይገኙ ናቸው። ጥቂቶቹም አገልግሎት ከሚሰጡበት የሚዘጉበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው አካባቢዎች፣ ቀላልና ደረቅ ቆሻሻ የሚጠራቀሙባቸው ቅርጫቶች (በአንዳንድ ድርጅቶች ተነሳሽነት የተቀመጡት ቅርጫቶች፣ በወሮበሎችና ራስ ወዳዶች እየተነቀሉ መወሰዳቸው ወይም አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ በአግባቡ ተደራጅተው አይገኙም፡፡
የሕንፃና የመንገድ ግንባታ፣ አስገዳጅ ደረጃዎች እንዳሉ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ግን ምን ያህል ተፈፃሚ ሆነዋል? ያልተተገበረ ደንብና መመሪያ ሳይኖር  አይቀርም፡፡ ከቶ ስለ ምን የምንናገረውን ፈፅመን ለመገኘት እንቸገራለን?  መጀመር እንጂ መጨረስ ዳገት እንደሆነብን ሊቀር  ነው ማለት ነው?  መስተዳደሩ፣ እነዚህን ሕፀፆች ከማስወገድ ባለፈ፣ የከተሜነት ባህልና እሴቶች እንዲስፋፉ ከመገናኛ ብዙሃንና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት፣ የተጠናከረ የትምህርት ፕሮግራም ቀርፆ ሊተገብር ይገባዋል። በቀጣይ ግን አስገዳጅ ደንብና መመሪያዎችን ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ አካባቢን የማስዋብና አረንጓዴ የማድረግ ስራ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡ አሁን ያለው የከተማ መስፋፋት ምጣኔ፣ በዚህ ከቀጠለ ከተማዋ ሩቅ በማይባል ጊዜ፣ ለከፋ የአየር ብክለት እንደምትጋለጥና የሙቀት መጠኑም በእጅጉ እንደሚጨምር አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች፣ እዚህም እዚያም የተወሰኑ ጥረቶች ቢደገረጉም ያልተደራጁ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ቀጣይነት የሌላቸው ናቸዉ። በነገራችን ላይ እንደ  አንድ ግብር ከፋይና ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ፣ በጣም ከሚያስቆጩኝ ነገሮች አንዱ፣ ምን እየሰሩ እንደሆነ እንኳ በውል የማይታወቁ የመንግስት ተቋማትን ለማስቀጠል የሚወጣው ገንዘብ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የመንግስት ተቋማት፣ በርካታ ሲሆኑ የደንብ ማስከበር አገልግሎትና የውበትና መናፈሻ ኤጀንሲ በምሳሌነት  ሊጠቀሱ ይችላሉ። የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን፣ ከዚሁ ጎራ ልትመድቧቸዉ ትችላላችሁ። እባካችሁ፤ በየወሩ ስለምትሰበስቡት ደሞዛችሁ ስትሉ ሥራችሁን በአግባቡ ስሩ፡፡
3ኛ) በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማረጋገጥ፤
ለአዲስ አበባ መንገዶች መጎሳቆል፣ ለከተማዋ ውበት ማጣትና ለነዋሪዎች መጉላላት ዋነኛ ተጠያቂ ማን ነዉ? ብትሉኝ፣ ከሶስቱ ድርጅቶች ማለትም፡- ከመብራት ኃይል፣ ቴሌኮሚኒኬሽንና ውሃና ፍሳሽ አልወርድም። እርግጥ ነው የእነዚህ ድርጅቶች አገልግሎት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ያለ እነርሱ ከተማንና ዘመናዊ አኗኗርን መመኘት አይታሰብም፡፡ ግን አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው? ስለ ምን እነዚህ ድርጅቶች አቅደውና ተቀናጅተው መስራት አቃታቸው? እውነት ይህን ያህል ሀብታም ነን ማለት ነዉ? ለጥገና ወይም ለማስፋፋት መንገድ መቁረጥ ግድ ሊሆን ይችላል፤ ግን የፈረሰውን ወደነበረበት መመለስ ለምን አይቻልም? ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያለበትስ ማነው? ይህ መስተዳደር ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ አለበት ብዬ አምናለሁ፤ እየሰሩ ማፍረስ መቆም አለበት፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ መታየት ያለበት የመንገዶች አገልግሎት ጉዳይ ነዉ። ለእግረኛ ወይም ለመኪና የተዘጋጁ መንገዶች ከታሰቡላቸው አላማ ዉጪ ለጎዳና ላይ ንግድ፣ ለግንባታ እቃዎች ማከማቻ፣ ለካፌ፣ ለወርክሾፕ አገልግሎት ሲውሉ ማየት የተለመደ ነወ፡፡ ይህን ጉዳይ ማንሳት አንዳንዶች እንደሚያስቡት ምቀኝነት አይደለም፡፡ ሰዎች ሰርተው ኑሮአቸውን ማሻሻላቸው፣ አለፍ ሲልም በግብር መልክ ለአገር አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉ የሚበረታታ ጉዳይ ሆኖ፤ ሲሰሩም ሆነ ሲያተርፉ የሌሎችን ምቾትና ደህንነት በመጋፋት፣ የከተማውን ገፅታ በማበላሸት፤ ሱቅ ከፍተው፣ ሰራተኛ ቀጥረው፣ ቤት ተከራይተው በሚሰሩት ኪሣራ መሆን የለበትም፡፡ ደንብ አስከባሪው  ተቋም ሊሠራ የሚገባው ትልቅ ተግባር ይህ ነበር። አዲሱ ከንቲባ እየሰሩ ያልሆኑ ተቋማትን መፈተሽ ሳይኖርባቸዉ አይቀርም፤ ተጠያቂነት የሚባል ነገር የለማ - በሁለቱም ወገን።
4ኛ) ከተማዋን ከማናቸውም የድምጽ ብክለት በህግ መከላከል፤
ኢትዮጵያ የእምነት አገር ነች፤ በየምክንያቱ ወደ እምነት ተቋማት የሚተመውን ሕዝብ ብዛት ለተመለከተ፣”በእውነት ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖተኞች ናቸው” ያሰኛል፡፡ የፈጣሪ መንፈስ የቀረበዉ ሆኖ ከመገኘት የላቀ ነገር የለምና፣ ይህ በጣም ጥሩ ነገር ነዉ። ስንቶቻችን የእምነቶቹን ትዕዛዝ በአግባቡ እየፈፀምን ነው? ስንቶቻችንስ የምንለውን ሆነን ተገኝተናል?--- ለጊዜው  ጥያቄዎቹ ይቆየንና ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንመለስ፡፡
ከተማችንን የሚያሳስበው ሌላው ዋና ጉዳይ የድምፅ ብክለት ነዉ፡፡ ሁሉም ቤተ-እምነቶች ማለት ይቻላል፣ ፉክክር በሚመስል ሁኔታ፣ ከተማዋን በድምፅ ማጉሊያ ሲቀውጧት ይዉላሉ፣ ያድራሉ፡፡ የዉጪ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ እንደ ማሳሰቢያ የሚነገራቸው (ወይም ከተመለሱ በኋላ፣ እንደ አሉታዊ ትውስታ የሚነሱት) ከትራፊክ አደጋና ከልመና መስፋፋት ቀጥሎ ከቤተ- እምነቶች የሚወጣው አዋኪ ድምፅ ነው፡፡ የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ  አማኝ ነው፤ ግን እውነቱን ለመናገር ይህ ገደብ ያለፈ ከእምነት ተቋማት የሚነሳ የድምፅ ብክለት መቆም አለበት ከሚሉት ወገን ነው፡፡
የድምፅ ብክለት ጉዳይ ከተነሣ፣ በአስፈሪ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለዉ ደግሞ ከጭፈራ (መሽታ) ቤቶችና ከጋራዦች የሚወጣው ድምፅ ነዉ። ዓላማው ቢለያይም ሁሉም የራሱን ፍላጎት ለማራመድ በትጋት እየሰራ ነዉ፡፡ በዚህ መሃል እየተጎዳ ያለዉ የከተማው ነዋሪና የከተማዉ ገፅታ በመሆናቸው መስተዳድሩ ከተቋማቱ ጋር ሊመክርበት ይገባል፡፡ እንደ  አንድ ዘመናዊ  ከተማ፤  አስገዳጅ የድምፅ ብክለት ደረጃ ወጥቶ፣ ሁሉም ህብረተሰብ እንዲያዉቀው ብቻ ሳይሆን የማስፈጸሚያ ስርዓት ሊዘረጋ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ አዲሱ መስተዳደር፤ ድክመቶችንና ዉስንነቶችን መሸፋፈኑን ትቶ፣ ሥኬቶችን ብቻ በማጋነን ከመኩራራት ወጥቶ፣ ከህዝቡ ጋር በመተባበር፣ ለዘላቂና ሁለንተናዊ ለዉጥ ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በመንግስት ላይ ጣት መቀሰር ቀላል ነዉ፡፡ እኛ የከተማ ነዋሪዎችም በያገባኛልና በኃላፊነት መንፈስ፣በግልና በጋራ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት መወጣት ይኖርብናል። ይህ እንዲሆን መንግስት (መስተዳደሩ) ነዋሪዎች፣ በተናጠልና በተደራጀ መልክ የሚደርጉትን ተሳትፎ ለማሳለጥ የሚያስችል፣ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ሊቀርፅ ይገባል፡፡ በዚህም ሳያበቃ፣ መሰረታዊ በሆኑ ከተማ አቀፍ ጉዳዮች፣ ከነዋሪዎቹ ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር መስራት አለበት። በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ሲኖር፣ ለጋራ ዓላማ መሥራት ይከተላል፡፡
ከአዘጋጁ፡-   (ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)




ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ከባድ የአገር ወረራ ሊካሄድ መሆኑ ይሰማና፣ ሰው ስጋት በስጋት ይሆናል፡፡ ዙሪያ ገባው ህዝብ መነጋገሪያው ይሄ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ከሽማግሌዎቹ አንዱ፤
“በሰሜን በኩል እንሂድና ወደ ታች ወደ ምሥራቅ እንውረድ”
ሁለተኛው፤
“የለም የለም፤ ከምዕራብ ወደ ደቡብ ብንከባቸው ነው የሚያዋጣን”
ሶስተኛው፤
“ኧረ ኧረረ እረረ … ያማ በጭራሽ አይታሰብም፤ መሆን ያለበት ከደቡብ እንነሳና--- ዳር ዳሩን፣ አጥር ላጥር ተጉዘን ወደ ማህል መግባት ነው፡፡ ዋናው ያካሄድ ዘዴ ማበጀት ነው፡፡”
አራተኛው፤
“ሰሜንንም፣ ደቡብንም ምሥራቅንም፣ ምዕራብንም አካለላችሁ፡፡ ጠላት ግን የት ጋ እንደሆነ እንኳ አላነሳችሁም” አሉ፡፡
ሁሉም ግራ ተጋቡና ዝም አሉ፡፡
አንደኛው፤
“ችግራችን ይሄው ነው፡፡ ጦርነቱ የት ጋ እንደሆነ እንኳን ሳናውቅ ዘመቻ እንጀምራለን! ሳንደራጅ መሳሪያ እንወለውላለን፤ ሳናስብ እናውቃለን፡፡ ሳናውቅ ማሰብ እናቆማለን። ማሰብን እንገድፋለን፡፡ ያንን ብናውቅ፣ አገርን እየበደልን መሆኑን ተገንዝበን በጭራሽ አይፀፅተንም፡፡”
ሁለተኛው፤
“አሁን ወራሪ እየመጣብን ነው፡፡ ምን እናድርግ ብንባባል አይሻልም?”
ሦስተኛው፤
“ወራሪያችንማ ነገ ራሱ ነው፡፡ ቀኑ ነው፡፡”
በዚሁ ስብሰባው ተጠናቀቀና ወደ ምርጫ ሄዱ፡፡ የሰዎች ስሞች ተጠቁሞ፣ አንድ የጎበዝ አለቃና አስራ ሶስት ጎበዛዝት ተመረጡ፡፡
ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ተፋፋመ፡፡ ከግራም ከቀኝም ብዙ ሰው ወደቀ፡፡ በቀጠሉት ቀናትም ጦርነቶች ተካሄዱና በጠላት አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ የጎበዝ አለቃውም ወደ ቀዬው ተመለሰ።
የመንደሩ ሰው የጦርነቱን ውጤት ለማወቅ ልቡ ተንጠልጥሎ ነበርና፤
“የጦርነቱ መጨረሻ ምን ሆነ?” ሲል ጠየቀው፡፡
የጎበዝ አለቃውም፤
“አይ፤ እንደፈራነው አይደለም፡፡ እኔ በሰላም ተመልሻለሁ” አለ፡፡
*   *   *
ጉዟችን ዛሬም ረጂም ነው፡፡ አውሎ ነፋሱ ረግቦ፣ አቧራው መሬት ሲወርድ፣ መጠያየቅ መጀመሩ አይቀሬ ነው፡፡
“ቀጣይ ጉዟችን ወዴት ነው?”
“የራሳችን ጥያቄ አለን ወይስ መሪዎች እንደ መሩን መነዳት ነው?”
“ስለ ፖለቲካው ብዙ አወራን፡፡ የኢኮኖሚው የታመቀ መገለጫ ነውና ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚው ምን ይዋጠው ሳንል ወዴት እንደርሳለን?”
“ሁሉን ነገር መንግሥት ላይ ላክከን አንችለውም፡፡ የተቃዋሚዎች ድርሻ ምንድን ነው? የሲቪል ተቋማትስ? የህዝብስ? የየአንዳንዱ ዜጋስ? ሁሉም የየድርሻውን እንዴት ይውሰድ?”
ሌሎችም ጥያቄዎች አሉ፡፡ እንጠይቃቸው፡፡ እንጠያየቅባቸው፡፡ እንጠየቅባቸው። ሁሉንም ነገር “ዓለም አላፊ ነው፡፡ መልክ ረጋፊ ነው፤ ፎቶግራፍ ቀሪ ነው” ብለን አንዘልቀውም፡፡ ከልብ እናስብ፡፡ እራሳችንን የምንወደውን ያህል አገራችንን እንውደድ፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ወደ ጦርነቱ እንግባ!
ብዙ ግብረ-ገብነት፤ ከመሰላቸትና ውሎ አድሮም ከመናናቅ አያልፍም፡፡ መሪ ከተናቀና ተመሪ ከናጠጠ፣ ተከታይ አደጋ አይቀሬ ነው፡፡ ለማንም የማይበጅ ሥርዓተ - አልበኝነትን አውርሶን የሚሄድ፣ አልሮ ሂያጅ ግርግር ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ አመፅም አይደለም። ሥር ነቀል አብዮትም አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ክለሳም (ሪቪዥኒዝምም) አይደለም፡፡ እዚህ ውስጥ ስለ ሪፎርም ማሰብ፣ ስለ ሊብራሊዝም ማሰብ ዘበት ይሆናል፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚለው ተረት ፣ ቤት የሚመታው እዚህ ጋ ነው፡፡ ይሄን መቼም እናስብ። “ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ”ንም ልብ እንበል!
ለአገርና ለህዝብ ወደሚበጀው  በሰላም ያሸጋግረን!!

“ከዜግነት ጋር የተያያዘው ህግ እንቅፋት ሆኖብናል”
በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ አገራት ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እስካሁን በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ህጋዊነትን ያላገኙ ሲሆን የፖለቲካ
ድርጅቶቹ እንዲመዘገቡ ምርጫ ቦርድ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቦርዱ ቀደም ሲል ለፖለቲካ ድርጅቶቹ ጥሪ በማድረግ፣ በአመዘጋገብ ስርአቱና ሂደቱ ላይ ገለፃ መስጠቱንና እንዲመዘገቡም ማስታወቁን ጠቁመው፤ እስካሁን ከ“አፋር ህዝብ ፓርቲ” በስተቀር ወደ ጽ/ቤቱ ቀርቦ አቅርቢ እውቅና ለማግኘት
ያመለከተ ፓርቲ የለም ብለዋል፡፡ የሀገሪቱ ህግ፤ “ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በሃገር ውስጥ ህጋዊ ሆኖ ነው መንቀሳቀስ አለበት” ይላል ያሉት አቶ ተስፋለም፤ ድርጅቶቹ ወደ
ምዝገባ ስርአቱ እንዲገቡ ቦርዱ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቦርድ በህጋዊነት የመዘገባቸው 22 ሀገር አቀፍና 40 ክልላዊ፣ በድምሩ 62 ፓርቲዎች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመው፡፡ ቦርዱም በሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚያውቃቸው እነዚህኑ ድርጅቶች ብቻ ነው ብለዋል - አቶ ተስፋለም፡፡ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ወደ ቦርዱ ቀርበው ህጋዊ የሚያደርጋቸውን ምዝገባ እንዲያከናውኑም ቦርዱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ ከተመለሱት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር እና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር፤ ከዜግነት ጋር የተያያዙ የህግ ድንጋጌዎች ምዝገባ እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስታውቀዋል፡፡
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር አመራር አቶ ግደይ ዘርአፅዮን “ከዜግነት ጋር በተያያዘ ያለው ህገ ደንብ ላይ ማብራሪያ እየጠየቅን ነው፤ ህጉ ተስተካክሎ ምዝገባውን እናከናውናለን
ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር አመራር አቶ አሚን ጁንደም በተመሳሳይ፤ ይህ ህግ እና ተያያዥ ጉዳዮች ምዝገባውን እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሆነባቸው ለአዲስ አድማስ
አስታውቀዋል፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በኢትዮጵያውያን ተቋቁሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው አመራሮች ብቻ እንደሚመራ በህግ ተደንግጓል፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ከ15 በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል፡፡

 መጣጥፍ

    ጠይም ጽጌረዳ ጎንፋ የት እንዳነበብኩት የማላስታውሰው የሁለት እንቁላሎች ታሪክ ነው (ቆየት ያለ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ይመስለኛል)። እንቁላሎቹ የተለያየ ቦታ ቢጣሉም፣ ንፋስ ገፍቶ ገፍቶ አጠጋጋቸው። ወንድና ሴት ናቸው፡፡ (እንቁላል ፆታ አለው እንዴ?) ገና በቅርፊት እንዳሉ ወሬ ይጀምራሉ።
“ድምፅሽ ያምራል” አላት።
“ያንተም ውብ ነው” አለችው።
“ምን እግር ጣለሽ?  ከየት መጣሽ ውዴ?” ጠየቃት።
“የእህል ውሃ ነገር፣ አንተን ሳታውቂው አትሙቺ ሲለኝ” ትመልሳለች፤ ሆድ በሚያባባ ድምጽዋ።
እንዲሁ ሳር ላይ እየተንከባለሉ፣ የረባ ያልረባውን ሲጨዋወቱ ይዋደዳሉ። ፍቅር ይጠናል። አልፈው ተርፈው ቃል ይገባባሉ።
“እኔ እንደተፈለፈልኩ፣ አንተን ነው የማገባው” ትለዋለች፡፡
“እኔስ ካላንቺ ማን አለኝ!” ይላታል።
እንዲያውም ለጫጉላ ሽርሽር በሰዓታት በረራ ተጉዘው፣ አሰብና ምፅዋ ለመዝናናት ሁሉ ተመኝተዋል። (በረራው በክንፍ ይሁን በአውሮፕላን አንድዬ ይወቀው!)
በፍቅሩ ጥናትና ጊዜዋም ደርሶ ሴቷ ቀድማ እንቁላሏን በርቅሳ ወጣች - ርግብ ነበረች።
የውጪው አለም እንዴት እንደሚያምር ...
ስለ ፀሐይ ድምቀት ...ስለ ነፋሻው አየር...መብረር እንዴት ደስ እንደሚል-- ሁሉንም እየተረከች ገና በቅርፊት ያለውን ወዳጇን አጓጓችው።
ቶሎ እንዲፈለፈልላት በላባዎቿ አቅፋ፣ ሙቀት በመስጠት ትዘምራለች... “የጓሮዬ አባሎ - አብብ ቶሎ
የጓሮዬ ጦስኝ - አብብልኝ” እያለች።
ውብ ዜማዋ ልቡን ሰውሮታል ... ሙቀቷ የልብ ልብ ሰጥቶታል ... ፍቅሯ ጉልበት ሆኖት፣ ቅርፊቱን ሰብሮ ተጠመጠመባት - እባብ ነበር።
“ዘመኑ ምናለኝ ዘመኑ ወርቅ ነው፤ ፍቅር ያለቀ ዕለት...”
እፈራለሁ...
በፍቅርና በይቅርታ፣ “ከእነ ቅርፊታቸው” የታቀፉት ሁሉ ሲፈለፈሉ፣ ርግብ ወይም ዶሮ ባይወጣቸውስ? እላለሁ።
እባብም ቢኖርስ?..
ፍቅር ባያልቅ እንኳ፣ እንደ አስራ ሦስት ወር ፀጋ፣ ከአመት አመት የአገራችን ሰማይ በፍቅር ቢሸፈን እንኳ ... አብሮ የማያዛልቅ ስንት አይነት ማንነት አለ?... “በእንቁላሉ ጊዜ...”ንም ለመተረት’ኮ፣ ከመነደፍ መትረፍና መሰንበት ያስፈልጋል፤ ወገኖቼ።
..እንዲህ አምናለሁ...
ሁሉም እጅ ተዘርግቶ አይታቀፍም። አገር በገራገር ፈገግታ ብቻ አትመራም። በኮስታራ ግንባርና በአርጩሜም ጭምር እንጂ። በየመድረኩ እየተቃቀፉ መሳሳቁን ለበላቸው ግርማ ተውለት- እስቲ ‘ጊነስ ወርልድ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ’ ላይ ይመዝገብበት። በሰው እንጀራ አትግቡ። ፈገግታ ጥሩ ነው፤ ከበሽታ ይከላከላል፣ ረዥም ዕድሜንም ያጎናፅፋል ... በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትንም ይቸራል ... (ይላሉ ተመራማሪዎቹ)፡፡
ሱፍ ገበርዲን ለብሶ .... ሱፉን ግጥም አርጎ፣ ፀጉሩን ተከረክሞ-- የመጣው ሁሉ “መልዓክ” መስሎ ከታየን፣ (አይ ያለው ማማሩ¡) አስቴር አወቀን መሆናችን ነውና፣ ድምፃችንን ሞርደን፣ ከቴዲ አፍሮ ቀጥሎ ባለው ሳምንት ኮንሰርት ብናዘጋጅስ?
አብሮ ለመቀጠል፣ አብሮ ለመሰንበት ግን “ከሱፉ ስር ማነው?” ነው ጥያቄው። ኧረ የምን ሱፍ፣ ከቆዳው ስር ራሱ ማነው?
እንደ አንድዬ ልብንና ኩላሊትን መመርመር ባይሆንል፣ “ጊዜው ደርሶ እንቁላሉ ሲፈለፈል ምን ይወጣል?” ብንል ደግ ነው። “አስኳሉ ጤነኛ ነው ወይ?” ማለትም አይከፋም ።
መፈልፈሉ ይቅር ... ለመብልነት እንኳ ስንገዛ፣ በአውራ ጣታችንና በሌባ ጣታችን መሐል ይዘን ፤ አንድ አይናችንን ጨፍነን ፤ ወደ ፀሐይ አንጋጠን፤ በአንድ አይናችን አጮልቀን አይተን አይደል እንቁላል የምንገዛው? ውስጡ ቢጫ ፣ብርሐን ፣ ንፁህ መሆኑን ፈትሸን...!
አንዳንድ ሰው አለ፤ ልክ እንደ እንቁላል ወገቡን ይዛችሁ፣ ወደ ፀሐይ በአናቱ በኩል ቀና አድርጋችሁ ስትፈትሹት፣ በተረከዙ በኩል ፀሐይዋን ካላያችሁ የማትቀበሉት፣ የማታምኑት፣ የማታቅፉት።
ለምግብነትም ለዘርም፣ ለምንም የማይሆን...!
..እንዲህ እመኛለሁ…
ያ በየኤርፖርቱና በየሆቴሉ ደጃፍ ያደፈጠው ማሽን፤ ጫማና ጃኬት ሳይቀር አስወልቀው የሚፈትሹበት ግድግዳ አልባ፣ መዝጊያ አልባ፣ የብረት ጉበን ... ለአምስት ሳንቲምና ለፀጉር ማስያዣ ቢም እንደዚያ “እሪሪሪሪሪ” ከሚል፣ ምነው የየሰውን አመል እየጮኸ ቢያጋልጥ...!
አለ አይደል…
“ክፋት- እሪሪሪሪሪ”
“እባክዎ ጌታዬ፤ ወደ ሐገር ከመግባትዎ በፊት ክፋትዎን ያውልቁ?”
ክፋት- ውልቅ… ቁጭ - ልክ እንደ ጃኬት!
እለፍ ቀጣይ ተረኛ...
“ዘረኝነት- እሪሪሪሪሪሪ”
“እባክዎ ጌታዬ፤ ወደ ሐገር ከመግባትዎ በፊት ዘረኝነትዎን ያውልቁ?”
ዘረኝነት ውልቅ… ቁጭ - ልክ እንደ ባርኔጣ!...
እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ..
ቅርፊቱ፣ ሱፉ፣ ቦዲው ካራሶሪያው ... ምናምኑ እያማለለን፣ የመጣውን ሁሉ ተንሰፍስፈን ባላቀፍን።

ከአንድ ጋዜጣ ያገኘነው ተረት የሚከተለውን ይመስላል፡- ተረቱ በተለያየ አገር የሚነገር ቢሆንም በዚህ መልኩ የተነገረው እኛ ጋ ነው፡፡ እንደሚያመች አድርገን አቅርበነዋል፡፡
እነሆ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን ጅብና ቀበሮ ቤት ፍለጋ ይሄዳሉ፡፡ ጅብ ትልቅ ቤት ሲያገኝ፣ ቀበሮዋ ብዙ ቀዳዳዎች ያሉት ትንሽ ቤት አገኘች፡፡
ቀበሮዋም፤
 “አንበሳ ቢመጣብህ በየት በኩል ታመልጣለህ? እኔ በቀዳዳዎቹ ለማምለጥ እችላለሁ” ትለዋለች ለጅቡ፡፡
 ጅብ ብዙም አርቆ ሳያስተውል፣
 “እባክሽ እንቀያየር?” ይላታል፡፡
 እሺ፤ ብላው ተቀያየሩ፡፡
ሌላ ቀን ጅቡና ቀበሮዋ ምግብ እንፈልግ ተባባሉ፡፡
ጅብ፤ “ወፍራም በሬ አግኝቻለሁ፤ አንቺስ?” አላት፡፡
ቀበሮ ያገኘችው ተባይ የሞላው አህያ ነው፡፡
“እኔ ያገኘሁት አህያ ነው፡፡ ግን ተመልከት ጮማ ነች! እንቀያየር” አለችው፡፡
ተቀያየሩ፡፡
የማረጃ ቢላዋ ፍለጋ ተሰማሩ፡፡
ጅብ ቢላ አገኘ፡፡ ቀበሮ ዶሮ ላባ አገኘች፡፡
 “ዶሮ ላባ በጣም ጠቃሚ መሳሪያ ነው፡፡ ቢጠፋብኝ በቀላሉ እተካዋለሁ፡፡ ያንተ ቢላ ግን ቢሰበር መተኪያ የለህም፤እንቀያየር” አለችው፡፡
ጅብ ተስማማ፡፡ ተቀያየሩ፡፡
በሬውን ለማረድ ጅቡ አልቻለም፡፡ ቀበሮ ግን ቢላውን በላባ ሸፍና በሬውን አረደችና አብረው በሉ፡፡ ቆይተው በመንገድ ላይ ማርና ቅቤ የተሸከመ ግመል አዩ፡፡
 ቀበሮ፣ ግመሉን ለሚነዱት ሐማሎች፤
“ደክሞኛል፤ እባካችሁ ግመሉ ላይ ጫኑኝ” አለች፡፡ ጫኗት፡፡
ማሩንና ቅቤውን ግጥም አድርጋ በላች፡፡
“አውርዱኝ ቤቴ ደርሻለሁ” አለች፤ጥግብ ስትል፡፡
አወረዷትና ወደ ገበያ ሄዱ፡፡
እዚያ ሲደርሱ “ጉድ!” አሉ። የተሰሩት ገባቸው፡፡ በቁጭትና በንዴት የአካባቢውን ቀበሮዎች ሁሉ ሰበሰቡና፤ “ዝለሉ!” አሉ፡፡ ያቺ ቀበሮ ቅቤና ማሩ ስለሚከብዳት እንደ ልቧ ስለማትዘል በቀላሉ ሊለይዋት ነው! እውነትም እመት ቀበሮ መዝለል አቅቷት ተያዘች። ታሰረች፡፡
“በኋላ እንገርፋታለን” ብለው ወደ ገበያው ሄዱ፡፡
ያ ጅብ መጣና አገኛት፤
“ለምንድነው የታሰርሺው?” ሲል ጠየቃት፡፡
“ቅቤና ማር ብይ ሲሉኝ እምቢ ብዬ!” አለችው፡፡
ጅቡም፤ ብልጥ የሆነ መስሎት፤
“በይ ቦታ እንለዋወጥ!” አላት፡፡ ፈታትና ቦታ ተለዋወጡ፡፡
ነጋዴዎቹ ሲመለሱ፣ በቀበሮዋ ቦታ ጅቡን አገኙ፡፡
“ምን ልትሰራ መጣህ?” አሉት፡፡
“ቀበሮ ቅቤና ማር ታገኛለህ ብላኝ ነው!” አላቸው፡፡
ቀበሮ ዛፍ ላይ ሆና፣
“ዐይኑን አትግረፉት! ጆሮውን አትንኩት! ሌላ ቦታ ላይ ግን ግረፉት” ትላለች፡፡
 ሰዎቹ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ገረፉት፡፡ ቆዳው ተልጦ ሥጋው ይታይ ጀመር፡፡
ከዚያ ጥለውት ሄዱ፡፡
 ጅቡ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤት ሲደርስ ልጆቹ ሲያዩት፤
“አባታችን ስጋ ይዞልን መጣ” ብለው ራሱን ተቀራመቱት!
*       *       *
ከላይኛው ተረት የቤትን ችግር ማስተዋል አያዳግተንም፡፡ ነገ ጠላት ቢያጋጥም ለማምለጥ ማስተዋል እንዳለብን ልብ እንላለን፡፡ ቦታ በመቀያየር ዙሪያ ብዙ ጅልነት እንደሚኖር እናጤናለን፡፡ ምግባችንን መለዋወጥም የራሱ ጣጣ እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ ማረጃችን ቢላ ወይስ ዶሮ - ላባ? የሚለውንም እናሰምርበታለን፡፡ ቢላ በላባ ሸፍነው ማረድ ግን ማኬቬሊያዊ አካሄድ ነው! የማርና ቅቤ ተሸካሚ ግመል፣ ግመሉንም የሚነዱ ነጋዴዎች ብዙ ናቸው፡፡ ግመሉ ላይ የሚጫኑ ብልጣ - ብልጦች ግን አያሌ ናቸው፡፡ ያም ሳይበቃቸው እንደ ጅቡ ሁሉ ለብዙዎች መታሰር ምክንያት የሚሆኑ አያሌ ናቸው! በልተው፣ መብላታቸው ተነቅቶባቸውም በአፋቸው ሌሎችን አስቀፍድደው፤ ዛፍ ጫፍ ላይ ሆነው የሚያላግጡ በርካቶች ናቸው! ለማን አቤት ይባላል?! ጅልነት በራስ ወገን እስከ መበላት ያደርሳል!
“አብዮት ልጇን ትበላለች!” ይሉ ነበር የዱሮ ገዢዎቻችን፡፡
 ሎሬት ፀጋዬ እንዳለው፤
 “አንዲት የዱር አውሬ፣ በአንዳንድ የመከራዋ ሰሞን
 ልጇን ትበላለች አሉ፣ ምጥ የጠናባት እንደሆን!
ዕውነቱ ሁሌም አይቀሬ ነው፡፡ ዩኒቨርሳል እንደሆነው ሁሉ “የቤት - ጣጣም” አለበት፡፡
 ዲበ - ኩሉ ይሰውረን እንጂ በሹም - ሽር የምንገላገለውስ አይደለም! “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ
 አያጣፍጥም” የሚለው ተረት ዱሮ ይሰራ ነበር፡፡
 አሁን ግን፤
‹‹የጣፈጠ ወጥ በጉልቻ መቀያየር የሚበላሽበት ዘመን መጣ›› በሚለው መተካት ሳያሻው አይቀርም፡፡ ሁሉን ነገር በሙከራ ብቻ አንዘልቀውም፡፡ ከወገናዊነት ነፃ እንሁን፡፡ ከልባችን ወደፊት እንጓዝ!!  አገሪቱ ከቤተ ሙከራነት መውጣት አለባት፡፡ በመካከለኛው የቢሮክራሲ ማዕድ የሚነሳውን ቢሮክራሲያዊ ሙስና አባዜ መላቀቅ ያሻል! ግምገማ ዕውነተኛ መሆኑ መፈተሽ አለበት፡፡ ባጠፉ አመራሮች ላይ እርምጃ እንወስዳለን ሲባል፣ ሁለት ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ አንደኛው ገምጋሚዎቹ ምን ያህል ንፁሀን ናቸው? ሁለተኛ የሚወሰደው እርምጃ ምን ያህል ሥር ነቀል ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ወሳኝ መሆኑን አንዘንጋ! ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ በቦታቸው የሚተካውስ ማነው? አስተማማኝ ነውን? ብሎ መጠየቅም ያባት ነው! ዞሮ ዞሮ ከሥርዓቱ መመሪያ ውጪ አዲስ ነገር የለም! ጆርጅ ፍሪድማን፤ ‹‹ቀጣዮቹ መቶ ዓመታት›› (The next 100 years ) በሚለው መጽሐፉ፤
‹‹ኦባማ የቡሽን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አራማጅ ነው፡፡ ቡሽ በኢራቅ ላይ ያወጣው መመሪያ እንዳለ አለ። ከአውሮፓውያን በተለይም ከጀርመን ያለው ግንኙነት ያው ነው፡፡ ከኢራንና ከኩባ ጋር ለመግባባት የሞከረው ውጤቱ ፍሬ ቢስ ነበር፡፡ ከሩሲያ ጋር ያለውም ዝምድና የቡሽ እንደነበረው ነው፡፡ ከጆርጂያ፣ ከዩክሬን.. ከፖላንድም ያለውን ዝምድና ማዝለቅ ነው፡፡ ኦባማ ለፕሬዚዳንትነት በመወዳደርና ፕሬዚዳንት በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ጥርት አድርጎ ያውቃል፡፡ እንደ ተመራጭ ብዙ ነገር ትናገራለህ፡፡ እንደ መሪ ግን ከነባራዊው ዕውነታ ጋር ትጋፈጣለህ። እንደ ቼዝ ተጫዋች የምትሄድበት አቅጣጫ ይጠፋሃል፡፡ መሪነት የዋዛ ነገር አይደለም፡፡”
ዶናልድ ትራምፕም ከመመሪያው ውጪ እንዳይደለ ከላይ ካነሳነው ሁኔታ መገንዘብ አያዳግተንም፡፡ የሀገራችንን አመራሮችም ሆነ የመካከለኛ ቢሮክራሲ ሹማምንት በዚህ ረገድ መገምገም አዳጋች አይደለም፡፡
 እንደ ፀሀፊው አሪፍ አገላለፅ፤
‹‹United States is a bizarre mixture of overconfidence and insecurity›› (አሜሪካ ከመጠን ያለፈ ልበሙሉነትና ደህነነቷን የማጣት ሥጋት ቅልቅል የሆነች አገር ናት እንደ ማለት ነው) ይላታል፡፡ እኛስ ብንሆን? ብሎ መጠየቅ አስማታዊነትን አይጠይቅም፡፡ የትኛውም መሪ፣ መካከለኛ መሪ፤ ወይም ታህታይ መሪ፤ በፓይለቶች ቋንቋ፡-
‹‹Soft-Landing›› በሰላም መሬት መድረስ ካጋጠመው ዕድለኛ ወይም የበቃ ሰው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አያጋጥምም፡፡ እጅግ ወደ ፅርሃ-አርያም ለወጣ ምድር ሩቅ ናት፡፡
ስለዚህ አዕምሮውን ማዘጋጀት አለበት - ለመውረድ። አለበለዚያ ዐረቦች፤
‹‹ንጉሥ ሆኖ ሳይከሳ የሚሰናበት የለም!” የሚሉትን ተረትና ምሣሌ ልብ እንድንል እንገደዳለን!

Saturday, 29 September 2018 13:46

ሴቶች በግላቸው እራሳቸውን…

 ሴቶች በተፈጥሮአቸው ከሚኖራቸው የስነተዋልዶ ባህርይ አንዱ የወር አበባ ነው፡፡ ሴት ልጆች በአስራዎቹ እድሜ ክልል ሲደርሱ የሚያዩት የወር አበባ የሚፈጠረው የማህጸን ግድግዳ ጽንስ ይፈጠራል ከሚል ከተዘጋጀ በሁዋላ ጽንሱ መፈጠሩ ሲቀር ይፈራ ርስና ወደፈሳሽነት ተለውጦ ንጹህ ያልሆነ ደም ይፈሳል፡፡ የወር አበባ የሚቆየው ከ3-5 ቀን ድረስ ነው፡፡ የወር አበባ ተፈጥ ሮአዊ ሲሆን በመፍሰሱ ምክንያት በሰውነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የሌለው ሲሆን በትክክ ለኛው ሁኔታ ካልፈሰሰ ግን በመጠኑ ያለመመቸትና የሕመም ስሜት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በእ ርግጥ አንዳንድ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ የሕመም ስሜት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
የወር አበባ በሚመጣበት ወቅት የሚከሰተው የህመም ስሜት በሁለት ይከፈላል፡፡
primary dysmenorrhea፡- ይህ አይነቱ የህመም ስሜት በ90% ያህል ሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ይህ በአብዛኛው ሴቶቹ ሲያገቡ ወይም ልጅ ሲወልዱ መፍትሔ የሚያገኝ ነው፡፡
secondary dysmenorrhea ፡- ይህ ሁለተኛው የሕመም አይነት ሲሆን በዳሌ አካባቢና ከማህጸን ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሕመም ነው፡፡ በእርግጥ መፍትሔው የሚገኘው የሚያማቸው ሴቶች በሕክምና ከተረዱ ነው፡፡
አንዳድ ሴቶች የወር አበባ በወር ሲመጣ ቀኑን ሳያስተካክል የሚመጣ መሆኑን ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ በፍሰቱ የማነስና የመብዛት ሁኔታን ያስተውላሉ፡፡ ነገር ግን የወር አበባ የሚበዛባቸው ሴቶች ልብ ሊሉት የሚገባቸው ነገር አለ፡፡
በተፈጥሮ ጭንቀታም መሆን፤
በማህጸን ዙሪያ እጢ ወይንም ኢንፌክሽን ካለ እና ሌሎች ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች የወር አበባ በሚመጣበት ጊዜ መብዛትንና ሕመምን ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ነው፡፡
ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ሕመም ይሰማናል የሚሉ ሴቶች የሚገልጹትን ስሜት ከአንዲት ሴት በደረሰን መልእክት መመልት ይቻላል፡፡
‹‹…እኔ በእድሜዬ ወደ 32/ሰላሳ ሁለት አመት ይሆነኛል። የወር አበባ ከመጀመሪያውም እንደሌሎች ሴቶች በወቅቱ ወይንም በቶሎ ያላየሁ ሲሆን መምጣት የጀመረው በ18/አመት እድሜዬ ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ልክ በወር አንድ ጊዜ ታማሚ ሆኛለሁ፡፡ አስቀድሞውኑ የሚጀምረኝ ሕመም አለ፡፡ ወገቤን ይከተክተኛል፤ማህጸኔ አካባቢ ጨምድዶ ይይዘኛል፤ የእራስ ምታት ጭምር ስለሚያመኝ በዚህ ጊዜ ሰው ባያናግረኝ እመርጣለሁ፡፡ ይህንን ሁኔታ ባለቤቴ ለረጅም ጊዜ ሊረዳው አልቻለም ነበር፡፡ እንዲያው አመልሽ ተለውጦ እንጂ የወር አበባ መም ጣት ባንቺ ብቻ አልተጀመረም ይለኝ ነበር። ነገር ግን አንድ ጊዜ …ተነሽና ወደሐኪም ቤት እንሂድ አለኝ፡፡ እኔም እሺ ብዬ ሔድኩ፡፡ ሐኪሙ እሱንም እኔንም አስቀምጦ ሁኔታውን ሲያ ስረዳ እዚያው ሐኪሙ ፊት ነበር ይቅርታ የጠየቀኝ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ባለቤቴ በደንብ ይረዳኝ ጀመር፡፡ ባል አግብቼም ሆነ ልጅ ወልጄ ሕመሙ ግን አልተሻለኝም፡፡››
    ቤተልሔም ብስራት ከቤተል
በአንድ ወቅት ያነጋገርናቸው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡
…ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የህመም ስሜት በተለያየ መንገድ መግለጽ ይቻላል፡፡ ለሕክምና የሚመጡት ሴቶች እንደሚገልጹት ከሆነ የጡት ሕመም፤ የእራስ ምታት፤ የእግር ማበጥ፤ በወገብና በማህጸን አካባቢ የሚሰሙ ሕመሞች የመሳሰሉትቸ  ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌም የማህጸን በር ጠባብ ከሆነ የሚፈሰውን ደም እንደልብ ስለማያስተላልፍ ማህጸን ደሙን ለማስወጣት ሲል በሚያደርገው ትግል በሴቶቹ ላይ ሕመም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ አይነቱ ሕመም ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖር የሚፈጠር የህመም ስሜት ሲሆን እንደእጢ የመሳሰሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ግን ምክንያታዊ የሆነ ሕመም ነው፡፡ በእርግጥ ብዙውን ጊዜ ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ችግር በጋብቻ እና ልጅ በመውለድ ምክንያት ሊወገድ የሚችል ሲሆን አንዳንድ ሴቶች ላይ ያለው አጋጣሚ ግን መድሀኒት ከመውሰድ እስከ ቀዶ ሕክምና የሚያደርስ ሕክምና ሊያስፈልጋቸው የሚችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የወር አበባን ለማስወገድ ሲባል ብቻ ጋብቻ እና ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይኖር መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ በወቅቱ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር ገልጸው ነበር፡፡
በወር አበባ ጊዜ ለሚከሰት ሕመም እንደማስታገሻ ከሚታሰቡት መካከል የአመጋገብ ሁኔታዎ ችም ቸል የማይባሉ ናቸው፡፡ አንዳድ ሴቶች እንደሚመሰክሩት የአመጋገብ ሁኔታን በመለወጣ ቸው ምክንያት ሕመሙ እንደታገሰላቸው ያሳያል፡፡ የአስተሳሰብ ሁኔታን ለማስተካከል የሚረዱ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌም እንደ ዮጋ የመሳሰሉት ሊረዱ ይችላሉ፡፡
አመጋገብ፡-
በካልሲየም የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ… ባቄላ፤ ጥቁር አረንጉዋዴ ቀለም ያላቸው አትክልቶች እንደ..ጎመን የመሳሰሉ ..ወዘተ…
ከሰውነት ውስጥ መመረዝን የሚያስወግዱ ምግቦችን መመገብ…ፍራፍሬዎች… ቲማቲም…ወዘተ…
ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን የለወጡ… እንደ የተፈተገ ስንዴ ከመሳሰሉ የሚሰሩ ምግቦችን … ነጭ ዳቦ… ፓስታ እና ስኩዋር የመሳሰሉትን አለመመገብ…
ቀይ ስጋን መመገብ አለማብዛት እና በቀዝቃዛ ውሀ ውስጥ የሚገኝ አሳን እንዲሁም ፕሮቲን ለማግኘት የሚረዳውን እንደ ባቄላ የመሳሰሉትን መመገብ…
ጤናማ የሆኑ የአትክልትና የወይራ ዘይት መጠቀም…
በአመጋገብ ውስጥ የአኩሪ አተር ወተትን ማካተት፤ ስብ ያላቸውን ምግቦች መቀነስ፤
በንግድ ሱቆች የተደረደሩ …ተዘጋጅተው የሚሸጡ እንደ ኩኪስ፤ ኬኮች፤ የተጠበሰ ድንች፤ እና ባጠቃላይም በኢንደስትሪ ተሰርተው የሚቀርቡ ምግቦችን እና ቅቤ የመሳሰሉ ትን ነገሮች አለመመገብ…
እንደ ቡና ያሉ፤ አልኮሆል እና ሲጋራ ማጤስ የመሳሰሉትን ከልምድ ማስወገድ…
በቀን ከ6-8/ብርጭቆ የተጣራ ውሀ መጠጣት…
በቀን ውስጥ ለ30/ደቂቃ ያህል በሳምንት ለ5/ቀናት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት፤
ከላይ የተጠቀሰው የአመጋገብ ልማድ ለማንኛውም ሰው የሚመከር ሲሆን በተለይም የወር አበባ በሚመጣበት ወቅት ሕመም የሚሰማቸው ሴቶች አመጋገባ ቸውን በተቻለ መጠን በተጠቀሰው መልክ ማስተካከል ቢችሉ ሕመሙ እንደሚቀንስላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በተጨ ማሪም አመጋገብን ለመደገፍ ሲባል ከሚወሰዱ መካከል የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ኦሜጋ -3/ ለምሳሌ የአሳ ዘይት በቀን 6/ግራም ቢወሰድ በወር አበባ ጊዜ የሚሰማውን ሕመም ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ እንደ ደም ማቅጠኛ ያሉ መድሀኒቶችን ለሚወስዱ ሰዎች አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ሐኪምን አስቀድሞ ማማከር ይገባል፡፡  
ካልሲየም በወር አበባ ጊዜ የሚከሰትን ሕመም ከማስታገስ በተጨማሪ ለጤናማ አጥንት እና ጡንቻዎች መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ካልሲየም ሲትሬት ማለትም በካልሲየም መልክ የተሰራው ሰውነት በቀላሉ የሚቀበለው ስለሆነ የወር አበባ ሕመምን ለማስታገስ ይረዳል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ግን የወር አበባው ከጀመረ በሁዋላ ቢወሰድ ጥቅም ላይሰጥ ይችላል፡፡
በአጠቃላይም ቫይታን ዲ፤ ቫይታሚን ኢ፤ እና ማግኔዥየም የወር አበባ ከመጀመሩ አስቀድሞ ቢወሰድ የህመም ስሜትን ሊቀንሱ እንደሚችሉ መረጃው የሚጠቁም ሲሆን ለማንኛውም ግን ሐኪምን ማማከር እንደሚጠቅም ይገልጻል፡፡
የወር አበባ ሕመም የሚሰማቸው ሴቶች በግላቸው እራሳቸውን መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሙቀት እንዲሰማቸው ማድረግ፤ጀርባን ጫን ጫን እያሉ መግፋት ወይንም እንደመታሸት ማድረግ፤ ሴትየዋ የህመሙ ስሜት እንዳይሰማት ማረሳሳት፤ሕመሙን እረስታ እንድትረጋጋ ማድረግ፤ የመሳሰሉት ዘዴዎች ይጠቅማሉ፡፡
ከዚህ ውጭ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በወር አበባ ወቅት ለሚሰማ ሕመም ማስታገ ሻነት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ወቅት የሚጠቅም በመሆኑ የእግር ጉዞን ጨምሮ ሌሎች እንቅ ስቃሴዎችን ማድረግ ለጤናማነት ይረዳል፡፡

 ጃማይካዊቷ ዜላ ግሪፍትስ ጌይል  ከክሁል ሆሊስቲክ ዴቨሎፕመንት ማዕከል ጋር በመተባበር ‹‹ኢነር ዚል ሬጌ ሮቢክስ›› የሚባለውን ልዩ የዳንስና ኤሮቢክስ እንቅስቃሴ ልታሰለጥን ነው፡፡ ልዩ የዳንስና ኤሮቢክስ እንቅስቃሴ  ስልጠናው ደምበል አካባቢ በሚገኘው ሬቲና ህንፃ 9ኛ ፎቅ ላይ ነገ በ10 ሰዓት የሚጀመር ሲሆን በየሳምንቱ እሁድ እንደሚቀጥል የዳንስ አሰልጣኟ ዜላ ግሪፍትስ ጌይል ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡
 ነገ በክሁል ሆሊስቲክ ዴቨሎፕመንት ማዕከል ለስልጠናው በተዘጋጀው የመክፈቻ ስነስርዓት የአፍሮ ቢትና የአፍሮ ሬጌ ዳንስ አሰልጣኞች እንዲሁም የዮጋ ኢንስትራክተር በተጋባዥነት ይሳተፉበታል፡፡ የ‹‹ኢነር ዚል ሬጌ ሮቢክስ›› ስልጠናው ለሁሉም የእድሜ ደረጃ እና ፆታ እንደሚሆን ሲታወቅ ክፍያው በግለሰብ ለአንድ ቀን 200 ብር እንዲሁም ለአንድ ወር 600 ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡  ዜላ ግሪፍትስ ጌይል  በእንግሊዝ ሳውዝሃምፐተን ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዊንቸስተር በዳንስ ሙያ ማሰትሬት ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን ‹‹ኢነር ዚል ሬጌ ሮቢክስ›› የምትለውን ልዩ አይነት የዳንስ እንቅስቃሴ በመፍጠር ስትንቀሳቀስ ከ15 ዓመታት በላይ ሆኗታል፡፡ ‹‹ኢነር ዚል ሬጌ ሮቢክስ›› በዳንስ ችሎታ እያንዳንዱ ሰው ያለውን ውስጣዊ  ኃይልና ፈጠራ ከኤሮቢክስ በማጣመር እየተዝናና የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ መኖር ከጀመረች ከ8 ዓመታት በላይ የሆናት ዜላ ግሪፍትስ ጌይል፤ በዳንስ አሰልጣኝነት እና አስተማሪነት በሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ስኩል፤ በላዮንሃርት፡ በማያ እና በአንድነት አካዳሚዎች ስታገለግል ቆይታለች፡፡

  • ድርጊቱ አሳፋሪና የኢትዮጵያውያን የውርደት ታሪክ ነው
       - ጠ/ሚ ዐቢይ
     • በተፈጸመው ጥቃት እንደ ኢትዮጵያዊነቴ አፍሬአለሁ
       - ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ
     • ከኢትዮጵያዊነት ባህል የዘለለና ከሰው ልጅ ሞራል ያፈነገጠ ነው
        - ቴዲ አፍሮ
     • ኢትዮጵያውያን የተፈተንበት ነው፤አይዟችሁ እናልፈዋለን
       - አርቲስት ታማኝ
 

     በቡራዩ በዜጐች ላይ ለደረሰው አሠቃቂ ግድያ፣ ዘረፋና መፈናቀል መንግሥት የማያዳግም ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ የፖለቲካ መሪዎች፣ዝነኛ አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች የጠየቁ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የጥቃት ተጎጂዎችንና ተፈናቃዮችን ሲጎበኙና ሲያጽናኑ ሰንብተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ከተፈናቃዮቹ ሳይለዩ ላሳዩት ኢትዮጵያዊ ፍቅርና ሰብአዊነት ከተጎጂዎቹም ሆነ ከጎብኚዎች ከፍተኛ ምስጋና ጎርፎላቸዋል፡፡
ወትሮም ኢትዮጵያዊነት ሲመቱት እንደሚጠብቀው ምስማር፣ በመከራ የሚጸና ነው፡፡ በቡራዩና አካባቢው የተፈጸመው ግፍ አሳዛኝ ቢሆንም የታየው የወገናዊነትና የብርታት መንፈስ ኢትዮጵያዊነት በመከራ የሚጸና መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ተጎጂዎቹን በተጠለሉበት ሥፍራዎች ተገኝተው የጎበኙት የፖለቲካ መሪዎችና የጥበብ ባለሙያዎች የተንጸባረቀው ስሜትና መልዕክትም ይኸው ነው፡፡ ኅዙነ ልብ ቁፅረ ገጽ ሆነው ተጎጂዎችን በመድሃኔአለም ት/ቤት የጎበኙት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “ድርጊቱ አሳፋሪና የኢትዮጵያውያን የውርደት ታሪክ ነው፤” ብለዋል፡፡ መንግሥታቸው ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከእንግዲህ ጉልበተኞችን እንደማይታገሥም አስጠንቅቀዋል፡፡
በአካባቢው ለተፈጠረው ግጭትና ጥቃት መነሻ ምክንያቱ የአንዲት የ6 ዓመት ሕፃን በአሠቃቂ ሁኔታ ተገድላ መገኘት መሆኑን የጠቆሙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፤ ይህን አጋጣሚ ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች ተጠቅመውበታል፤ ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ከእንግዲህ ለእንዲህ ያለው ብሔር ተኮር ጥቃት ትዕግሥት እንደሌለው የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ለማ፤ ድርጊቱም የኦሮሞን ሕዝብ አይወክልም፤ ብለዋል፡፡
ተጐጂዎችን በርካታ የፖለቲካ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተጠለሉበት ተገኝተው የጐበኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኙበታል፡፡ ድርጊቱ ዲሞክራሲን ያለ አግባብ መጠቀም በመሆኑ፣በኢትዮጵያዊነቴ አፍሬአለሁ፤ ብለዋል፡፡ በአጥፊዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበው፤ለዚህም መንግስት የሚከፍለው መስዋዕት ካለ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነም በተጎጂዎቹ መጠለያ ተገኝቶ እያነባ ሃዘኑን ከገለጸ በኋላ “አሁን ኢትዮጵያውያን የተፈተንበት ወቅት ላይ ነን፤ አይዟችሁ እናልፈዋለን” በማለት ተጎጂዎቹን ያጽናና ሲሆን ኢትዮጵያውያን Go Fund me በተሰኘው የማኅበራዊ ድረ ገፅ የእርዳታ ማሰባሰቢያ አማካኝነት ወገኖቻቸውን እንዲያቋቁሙ በተማጸነው መሰረት፣በ24 ሰዓት ውስጥ ከ2 መቶ ሺህ ዶላር በላይ (9 ሚ. ብር ገደማ) ማሰባሰብ መቻሉ ታውቋል፡፡  
አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በበኩሉ፤በተጎጂዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘኑን ገልጾ፤ድርጊቱ ከኢትዮጵያዊነት ባህል የዘለለና ከሰው ልጅ የሞራል ህግም ያፈነገጠ ነው፤ከዚህ በኋላ መደገም የለሌበት” ብሏል፡፡ ከባለቤቱና ጓደኞቹ ጋር ተጎጂዎቹን የጎበኘው አርቲስቱ፤ለጥቃቱ ተጎጂዎች ማቋቋምያ ይሆን ዘንድ የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ለዚህ ሳምንት ተላልፎ የነበረውን የሙዚቃ ኮንሰርቱንም እንደሰረዘ አስታውቋል - “ወገኖቼ ባዘኑበት ሁኔታ ኮንሰርት የማቀርብበት አንጀት የለኝም” በማለት፡፡
ፖሊስ በበኩሉ፤ እስካሁን ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ ከ500 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ፤ ከዚህ በኋላ ለሚፈጠር ተመሳሳይ ችግር ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን ጅቦች በጠፍ ጨረቃ ተርበው የሚበላ ፍለጋ ሲዘዋወሩ አንድ ግዙፍ ዝሆን ገደል ገብቶ ሞቶ አዩ፡፡
አንደኛው ጅብ - በረሀብ ከምንሞት እንግባና እንብላው
ሁለተኛው ጅብ - ገደሉ በጣም ሩቅ ነው፡፡ እንኳን ገብተን ሆዳችን ሞልቶ እንዲሁም ለመውጣት አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ መዘዋወራችንን እንቀጥልና የረፈደበት አህያ እንፈልግ፡፡
ሦስተኛው ጅብ - እንግባና ከበላን በኋላ እንደጋገፍና አንዳችን አንዳችን ትከሻ ላይ እየወጣን ከገደሉ እንወጣለን፡፡
አራተኛው ጅብ - ከገባን በኋላ እናስብበታለን
አንደኛው ጅብ - በድምፅ ብልጫ እንለየው
ሁሉም በድምፅ ብልጫ ይሁን በሚለው ሀሳብ ተስማሙ፡፡
አንደኛው ጅብ - እሺ፤ እንግባና በልተን እናስብበታለን የምትሉ?
ሁሉም እጃቸውን አወጡ፡፡
በሙሉ ድምፅ እንብላው አሉና ተግተልትለው ገቡ፡፡
ለአንድ ሁለት ሦስት ቀን ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ዋለ አደረና የዝሆን መቀራመቱ ጥጋብ አበቃና፣ ረሀብ በተራው ይሞረሙራቸው ጀመር፡፡
እንደተገመተውም ከገደሉ መውጫው ዘዴ ሊገኝ አልተቻለም፡፡
እየተራቡ መተኛትም ሆነ ዕጣ-ፈንታቸው፡፡ አንድ ሌሊት አንደኛው ጅብ ጐኑ ላለው ጅብ፤ “በጣም የተኛውንና ዳር ያለውን ጅብ ለምን አንበላውም?” ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ አንዱ ለአንዱ እያማከረ፣ ዳር ላይ ለጥ ያለው ላይ ሰፈሩበት፡፡ ለአንድ ሁለት ቀን ፈንጠዝያ ሆነ፡፡
እንደገና ረሀብ ሆነ፡፡ በዚያው ተዘናግቶ በተኛው ተረኛ ጅብ ላይ እየፈረዱ፣ በመጨረሻው ሁለት ቀሩ፡፡ ብዙ ለሊት እየተፋጠጡ አደሩ፡፡ ሆኖም መድከም አይቀርምና አንዱ ደክሞት ተኛ። የነቃው በላው፡፡ ጥቂት ሰነበተና እራሱም በረሀብ ሞተ!
*   *   *
የሀገራችን የሙስና ደረጃ ገና ያልተጠረገ በረት ነው፡፡ “አህያም የለኝ ከጅብም አልጣላ” ብለን የምንዘልቀው እንዳልሆነ ካወቅነው ውለን አድረናል፡፡ “ሙስናው በአዲስ መልክ ሥራ ቀጥሏል፡፡” እንዳንል፣ መረር ከረር ብሎ መገታት እንዳለበት መገንዘብ ያሻል፡፡ ብርቱ ጥንቃቄና ብርቱ እርምጃ ግድ ነው፡፡ “ግርግር ለሌባ ያመቻልና” የህዝቡን ፀጥታ የሚያደፈርስን ሁኔታ በችኮላም ሳንደናገር፣ በመኝታም ሳንዘናጋ በአስተውሎት መጓዝና ፍሬ ያለው ሥራ መስራት ያሻል፡፡ በየትኛውም አገር ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ አደናጋሪ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ መንጣጣቱም” ሆነ፤ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” መባሉ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር በመሆኑ፤ ነፃ አስተሳሰቡን እጅግ ልቅ ሳናደርግ፣ ግትርነቱንም (die-hardism) እጅጉን ሳናከርረው፣ በሥነ ሥርዓትና በዲሲፕሊን መራመድ ብቻ ነው የሚጠበቅብን። የረፈደ ነገር ያለ ቢመስለን አይገርምም! የአጭር ጊዜ ለውጥ ነውና! አመለካከታችን እስኪጠራ፣ በሀገራችን ህዝብ ዘንድ ብትሰራም ትኮነናለህ - ባትሰራም ትኮነናለህ (Do, damned! Don’t damned) ነውና፣ የያዝነውን መንገድ አለመልቀቅ ረብ ያለው እርምጃ ነው፡፡ ሰላምን ማደፍረስም ለሙስና ማራመጃም መከላከያም ሊሆን የሚችል አደገኛ መሣሪያ ነው! ዞሮ ዞሮ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው - ልብላው ነው” ከሚለው ተረት አይዘልም! ወንጀሎችን እንቆጣጠር! የመሣሪያ ዝውውርን በሕግ የበላይነት ሥር እናድርግ! “ጦር ሜዳ ማህል ግጥም አታነብም” እንደሚባል አንዘንጋ! ዘረፋን እንቋቋም! ያለ መስዋዕትነት ድል የለም! ከመጠምጠም መማር ይቅደም! የዕውቀትንና የባለሙያን ግብዓት በየፕሮግራሞቻችን ውስጥ ቀዳሚ እናድርግ፣ ከዘርና ከጐሣ ግጭት ወጥተን፣ በዲሞክራሲና በሕግ የበላይነት ራሳችንን እንገንባ! የዴሞክራሲያዊነት እንጂ የገዥነትና የተረኝነት ስሜት የትም አያደርሰንም!

 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር በአሜሪካ ከሚገኘው የአሜሪካን የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ደጋፍ በሚያደርጉ ድርጅቶች አጋዥነት ስራ ከጀመረ እነሆ ሁለት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ የተሰሩ ስራዎችን በሚመለከት አንዳንዶቹን እንደሚከተለው ለንባብ ብለናል፡፡
RESIDENCY: -
ከጠቅላላ ሐኪምነት ወደ ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ የትምርት መመሪያ እንዲሰለጥኑና ብቃት እና ጥራት ባለው መንገድ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ስራ ከጤና ጥበቃ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጋራ ስራ ተሰርቶአል፡፡ ለሚማሩ ሰዎች ጥሩ ትምህርት መስጠት፤ ጥሩ ጥናትና ምርምር ማድረግ ፤የተሻለና ጥሩ የሆነ ሕክምና መስጠት የሚሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልግበት ምክንያትም የድህረ ምረቃ ትምህርቶቹ ከበሽተኛ ጋር የተገናኙ በመሆናቸውና ሐኪሙ ብዙ እናቶችን በሕክምናው አገልግሎት የመርዳት ኃላፊነት ስለአለበት በጥሩ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት ስለታመነ ነው፡፡
ETHICS: -  
ሌላው የፕሮጀክቱ ዘርፍ የጽንስና ማህጸን ህክምና ባለሙያዎች የስነምግባር መመሪያን መቅረጽ ነው፡፡ የማህጸን እና ጽንስ ሐኪሞች ለሕመምተኛው መደረግ ያለበት የትኛው ነው ?የሚለውን ለመወሰን የሕመም ተኛው ፈቃድ፤ የሚኖረው አቅም የመሳሰሉት ሁሉ የሚያስፈልጉ ሲሆን ይህንን በትክክ ለኛው መን ገድ ለመምራት የሚያስችል የስነ ምግባር መመሪያ  በመዘጋጀት ላይ ነው ፡፡
CME: -
የህክምና ባለሙያዎች በስራ ላይ ባሉባቸው ጊዜያት እውቀታቸውን ከተለያዩ ሳይንሳዊ ግኝቶች እና አሰራሮች አንጻር የሚፈትሹባቸው ቀጣይነት ያለው ስልጠና እንዲያገኙ ማገዝ አንዱ  የESOG_ACOG ፕሮጀክት አቅጣጫ ነው፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች በዚህ ዘርፍ ጊዜው በሚፈቅደው የአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ እንዲያልፉ የሚያስችል አሰራር ነው፡፡
LEADERSHIP: -
የአመራር ብቃትን ማጎልበት ለጽንስና ማህጸን ሐኪሙ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑና በስራ ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል የሚረዳ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በተወሰኑ ጊዜያት ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡ Transformational leadership በሚል የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለ ሙያዎች መሰልጠናቸው በተለይም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ሙያን በማስተማር ላይ ለሚገኙት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
ከተጠቀሱት በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ቀደም ብሎ የጀመራ ቸውን ሳይንሳዊ ምርም ሮችን የሚያሳትምበት ጆርናልና ፤በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ለህብረ ተሰቡ ስለጤንነቱ እንዲያ ውቅና አስቀድሞ እራሱን እንዲከላከል የሚያስችል ስራ የሚሰራባ ቸውን የመገናኛ ብዙሀን ስራዎች ማሳደግና የተሻለ ጥራት እንዲኖራቸው እገዛ ከማድረግ ባሻገር ሐኪሞች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት አማካኝነት ትምህርትና መረጃዎችን እንዲያገኙ የማድረግ እና ሌሎችንም ተያያዥነት ያላቸውን ስራዎችን በመተግበር ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ (CIRHT) The Central For International Reproductive Health Training Of The University of Michigan ) በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ለአምስት አመት ሊተገብረው የታሰበው ፕሮጀክት በሁለት አመቱ ወደ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲዛወር የመደረጉን ምክንያት ፕሮጀክቱ ስራውን ሲጀምር የኢሶግ ቦርድ ፕሬዝዳንት የነበሩት የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት  የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ ለዚህ እትም አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ እንደገለጹት ‹‹… ከአሜሪካ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር  ጋር የተጀመረው ፕሮጀክት ጽንሰ ሐሳብ ኢሶግ  ከነበሩት ስትራቴጂክ ዶክመንቶች ውስጥ አንዱ በተለይም እንደውጭው አቆጣጠር ከ2012-2016/ የነበረውን የአምስት አመት ተግባራት በሚያመላክተው ውስጥ ማህበሩ በዚህ ፕሮጀክት ስንፈጽማቸው የነበሩትን ተግባራት እና ሌሎችንም ማህበሩ ከነበረው ራእይና ተልእኮ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ይህንን ተግባር ዋነኛ ማድረግ ይገባል የሚል እቅድ ነበረ፡፡ስለዚህም እኔ የቦርድ ፕሬዝዳንት ሆኜ ስመረጥ ከ2014/እንደውጭው አቆጣጠር ጀምሮ ዶክመንቱን በመፈተሸ ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ለመምራት የሚያስችለን የኢትዮ ጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ኮሌጅ መመስረት ያስፈልጋል የሚል እምነት አደረብን፡፡ ስለዚ ህም ሶስት ልምድ ያላቸው ሐኪሞች ተመድበው ስራውን እንዲከታተሉ ሲደረግ እኔም ነበርኩ በት፡፡ ይህንን ጉዳይ በስራ ከምናገኛቸው የተለያዩ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች  ጋር በመመካከር ስራው ከአሜሪካ የማህጸንና ጽንስ ኮሌጅ ጋር የምንሰራበት መንገድ ስለተመቻቸ June/ 2016/  የመግባቢያ ሰነዱ ተፈርሞአል፡፡
ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ አስከትለው እንደተናገሩትም በኢሶግ ስትራቴጂክ ዶክመንት ላይ የተገለጸው በውጭው አቆጣጠር በ2020/ የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ኮሌጅ እንደሚመሰረት ነው፡፡ የተጀ መሩት ስራዎች በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ሲያልቁ እራሱን የቻለ ኮሌጅ ተመዝግቦ ስራ ይጀምራል የሚል እቅድ ተነድፎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከድጋፍ አድራጊዎች ወገን ባልታሰበ ሁኔታ የሚገኘው እገዛ በውጭው አቆጣጠር ከሴፕቴምር 30/2018/በሁዋላ እንደማይቀጥል ስለተነገረን ይህ ዱብእዳ እንደሚባለው አስደንጋጭ ዜና ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአለምአቀፍ ደረጃ ካለው ድጋፍ የማድረግ እንዲሁም የገንዘብ አሰጣጥ ፍሰትና በተወሰነ መልኩም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ከአሁን በሁዋላ ስራውን እየመራ መቀጠል ይችላል ከሚል እምነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለ ዚህም የአሜሪካው የማህጸንና ጽንስ ኮሌጅ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ስለሚቋረጥ በቀጣይነት ከኢሶግ ጋር ለመስራት ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ተነግሮን ፕሮጀክቱ እንዲቋረጥ ተገድዶአል፡፡›› ብለዋል፡፡
የተጀመሩት ስራዎችን ቀጣይነት በሚመለከት ዶ/ር ደረጀ እንዳሉት‹‹…ኢሶግ ላለፉት 27/ አመ ታት በኢትዮጵያ የስነተዋልዶ ጤና ላይ ብዙ ሰርቶአል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ የስነተ ዋልዶ ጤና ዙሪያ ከተለያዩ ድጋፍ አድራጊዎች ጋር የሰራ በመሆኑ ጥሩ አጋር መሆኑን ማሳ የት የቻለ ማህበር ነው፡፡ ስለዚህም አሁን የተጀመሩትን በጎ ስራዎች ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን መቀጠል ይቻላል፡፡ አሁን ፕሮጀክቱ ተቋርጦአል ቢባልም ለተወሰኑ ወራት ድጋፉ እንደሚቀጥል ቃል የገቡ በመሆኑ ለወደፊትም ከእነሱው ጋር ይቀጥል ወይንም ስራውን እየሰራን ሌሎች ድጋፍ አድራጊዎችን ማፈላለግ ያስፈልጋል የሚለውን የምናየው ይሆናል፡፡ ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ በስተመጨረሻው እንደገለጹት በኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ በተለይም ሙያውን በልዩ ደረጃ በማሰልጠን ረገድ የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር ባለፉት ሁለት አመታት በተደረገለት የገንዘብም ሆነ የሙያ ድጋፍ የሰራው ስራ የመጀመሪያ ነው፡፡  
ኢትዮጵያ ውስጥ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ትምህርትን የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ አንድ አይነት የሆነ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲኖራቸው ለማስቻል ከጤና ጥበቃ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ስራ ተሰርቶአል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ፈተናን መስጠትን በተመለከተም ተሳክቶ ተካሂዶአል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ተከታታይ የህክምና ትምህርት መስጠትን በተመለከተም ባለሙያዎችን ለልዩ ሙያ በማሰልጠን ረገድ ካሉ ሌሎች ተቋማት በተሻለ መስራት ተችሎአል፡፡ የህክምና ስነምግባርን በተመለከተም ዶክመንት እየተዘጋጀ ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ጠቃሚ ስራዎች በማህበሩ እየተሰሩ በመሆናቸው እና የተሰሩም በመኖራቸው ማህበረሰቡን በበቂ ሁኔታ ለማገልገል ዝግጁ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ወደፊትም የማህበሩ አባላት በተሰለፍንባቸው የተለያዩ መስኮች የተሻለ ስራ በመስራት ህብረተሰቡን በተሻለ ሁኔታ ማገልገል ይጠበቅብናል ብዬ አምናለሁ ብለዋል ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ፡፡››