Administrator

Administrator

 ከሰሞኑ ሌላ የሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው ተብሏል

     ሰሜን ከኮርያ በቅርቡ ያደረገቺው ስድስተኛው የኒውክሌር ሙከራ ባስከተለው የመሬት መንቀጥቀጥና የዋሻ መደርመስ አደጋ ሳቢያ ከ200 በላይ የኒውክሌር ጣቢያው ሰራተኞች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የጃፓኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ የአሻይ ዘገበ ሲሆን የሰሜን ኮርያ መንግስት ግን ሃሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
አገሪቱ ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ፑንጌሪ ከተባለውና በሰሜን ምዕራብ ግዛቷ ከሚገኘው የኒውክሌር ጣቢያ ካደረገቺው የኒውክሌር ሙከራ ጋር በተያያዘ በጣቢያው ዋሻ ውስጥ በሬክተር ስኬል 6.3 የመሬት መንቀጥቀጥና ፍንዳታ መፈጠሩንና 100 ያህል ሰራተኞችን ወዲያውኑ መግደሉን የዘገበው ሮይተርስ፤ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በደረሰ ሌላ አደጋም ሌሎች ከ100 በላይ ተጨማሪ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ መነገሩን አመልክቷል፡፡
የሰሜን ኮርያ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባሰራጨው ዘገባ፤ መረጃው መሰረተ ቢስና አገሪቱ በኒውክሌር ፕሮግራም ላይ እያስመዘገበች ያለውን እመርታ ለማጠልሸት ሆን ተብሎ የተሰራጨ ወሬ ነው በማለት ማስተባበሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜናም የደቡብ ኮርያ የስለላ ተቋም፣ ሰሜን ኮርያ በቅርቡ ሌላ የሚሳኤል ሙከራ ልታደርግ በዝግጅት ላይ መሆኗን የሚያመላክት መረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
የስለላ ተቋሙ በሰሜን ኮርያ የሚሳኤል ፕሮግራም ተቋማት አካባቢ አዲስ ሙከራ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተጧጧፈ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡


    ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ የሚገኘው የሞዛምቢክ መንግስት፣ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የህዝብ ገንዘብ ወጪ በማድረግ አለማቀፍ ብራንድ የሆኑ 45 እጅግ ዘመናዊ የቅንጦት መኪኖችን ለባለስልጣናት ማመላለሻ ለመግዛት ጫፍ ላይ መድረሱንና ይህም የአገሪቱን ዜጎችና የሲቪል ማህበራትን በከፍተኛ ሁኔታ ማስቆጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት መርሴድስ፣ ቶዮታ ላንድክሩዘር፣ ፎርድ ሬንጀር፣ ሃዩንዳይና ፔጆን ጨምሮ በአለማቀፍ የመኪና ገበያ የላቀ ስም ያላቸው ኩባንያዎች ምርቶች የሆኑ 45 አዳዲስ ሞዴል መኪኖችን ለመግዛት ስምምነት አድርጎ ክፍያ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም በማህበራዊ ድረገጾችና በተለያዩ መድረኮች ተቃውሞ እንደገጠመው አመልክቷል፡፡
የመንግስት ባለስልጣናትን ለማንሸራሸር የታሰቡትን እነዚህን የቅንጦት መኪኖች ለመግዛት የተመደበው ገንዘብ፤ በዘንድሮው አመት ለአገሪቱ የአደጋ መቆጣጠር ተቋም ከተያዘው በጀት በእጅጉ እንደሚበልጥና የከተማ ድህነትን ለመቀነስ ከተያዘው በጀት በጥቂቱ እንደሚያንስም ተዘግቧል፡

 የከተማው ስፋት የኒውዮርክ ሲቲን 33 እጥፍ ያክላል ተብሏል

    ሳዑዲ አረቢያ 26 ሺህ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና ከኒውዮርክ ሲቲ 33 እጥፍ ያህል የቆዳ ስፋት የሚኖረውን ኒኦም የተሰኘ እጅግ ግዙፍ ከተማ፤ በ500 ቢሊዮን. ዶላር ወጪ ልትቆረቁር መዘጋጀቷን ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች፡፡
በሰሜን ምዕራባዊ የሳዑዲ ግዛት የቀይ ባህርን ዳርቻ ታክኮ የሚቆረቆረው አዲሱ ከተማ ኒኦም፤ ለኑሮ፣ ለንግድና ለመዝናኛ በአለማቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ተመራጭ ከተማ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን የዘገበው ሮይተርስ፤ ከተማው የሚቆረቆርበት ስፍራም ለእስያ፣ አውሮፓና አፍሪካ አገራት በቀላሉ ተደራሽ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ራዕይ 2030 የተባለውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደተሻለ ለውጥ በማሸጋገር ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን የመፍጠር ግብ ያስቀመጠው ዕቅድ አካል የሆነው ይህ ግዙፍ ከተማ፤የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አስታውቀዋል፡፡
ከተማው እጅግ የተዋበ፣ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የተሟላ፣ ሙሉ ለሙሉ በታዳሽ ሃይል አቅርቦት የሚሰራ እንደሚሆንና ራሳቸውን የቻሉ በጣም ሰፋፊ የቢዝነስና የኢንዱስትሪ ዞኖች አንደሚኖሩት የጠቆመው ዘገባው፤ የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በ2015 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመትም አመልክቷል፡፡
የአለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች የሆነቺው ሳዑዲ አረቢያ፣ የነዳጅ ዋጋ ከቀነሰበት ከ2014 አንስቶ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝና የፋይናንስ እጥረት መታየቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከልም ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለማስከፈል ማቀዱ እንደሚገኝበትም አክሎ ገልጧል፡፡

ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ሶስት ወራት፣ የደቡብ ኮርያው የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ በታሪኩ ከፍተኛው የሩብ አመት ትርፍ የሆነውን የ9.8 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ሲያስመዘግብ፣ የማህበራዊ ድረገጹ ፌስቡክ በበኩሉ፤ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉ በሳምንቱ መጀመሪያ ተዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ በሩብ አመቱ ያገኘዋል ተብሎ ከተገመተው ትርፍ በእጅጉ የላቀ ትርፈ ማስመዝገቡን የዘገበው ኤቢሲ ኒውስ፤ የሩብ አመት ሽያጩም ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በ30 በመቶ ብልጫ በማስመዝገብ፣ 55.1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል፡፡ የአለማቸን ቁጥር አንድ የስማርት ፎን አምራቹ ሳምሰንግ፣ በአለማቀፍ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የሚሞሪ ቺፕስ ሽያጩ ጋር በተያያዘ በትርፋማነት አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የሚሞሪ ቺፕስ ምርቱን የበለጠ ለማስፋፋት ባለፈው አመት ብቻ 29.5 ትሪሊዮን የደቡብ ኮርያ ዎን ወጪ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
ፌስቡክ በበኩሉ፤ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ4.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን ትርፉ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገበው ጋር ሲነጻጸር የ80 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሩብ አመት አስመዘግበዋለሁ ብሎ ካቀደው ገቢ የ47 በመቶ ብልጫ ያለው የ10.33 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን ከዚህ አጠቃላይ ገቢው 98 በመቶ ያህሉን ያገኘው ከድረ-ገጽ ማስታወቂያ አገልግሎቱ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

 የኦስካር እጩው ታዋቂ የሆሊውድ ዳይሬክተርና የፊልም ጸሃፊ ጄምስ ቶባክ፣ ጾታዊ ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሶብናል በሚል በይፋ ክሳቸውን የሚያቀርቡ ሴት ተዋንያን ቁጥር 238 መድረሱን ሎሳንጀለስ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ሃርቬ ዊኒስተን የተባለው ታዋቂ የፊልም ፕሮዱዩሰር፣ “ጾታዊ ትንኮሳና የአስገድዶ መድፈር ጥቃት አድርሶብናል” በማለት ከ40 በላይ ሴት ተዋንያን ባለፉት ሳምንታት በአደባባይ ክሳቸውን ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ “እኔም” የተሰኘና “ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶብኛል” የሚሉ ሴቶች ድርጊቱን ያወገዙበት ዘመቻ፣ በማህበራዊ ድረገጾች ተጧጡፎ መቀጠሉን ያስታወሰው ዘገባው፤በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ ሌላኛው ታዋቂ የሆሊውድ ዳይሬክተር ጄምስ ቶባክ፣”ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሞብናል” የሚሉ በርካታ ሴት ተዋንያን ወደ አደባባይ እየወጡ ሲሆን ጉዳዩ ዓለማቀፍ ትኩረት እየሳበ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
“ዘ ፒክ አፕ አርቲስት”ን ጨምሮ በርካታ ተወዳጅ ፊልሞችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ዳይሬክተሩ፤በተለይ ጀማሪ ተዋንያንን ወደ ፊልሙ አለም ለማስገባት የተለያዩ ጾታዊ ትንኮሳዎችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን እንደሚያደርስባቸው የሚገልጹና “የጥቃቱ ሰለባ ነን” በሚል ምስክርነታቸውን የሚሰጡ የሆሊውድ ሴት ተዋንያን ቁጥር 238 መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የ72 አመቱ ዳይሬክተር ከተዋንያኑ የቀረበበትን ክስ፣ “መሰረተ ቢስ ውንጀላ” በማለት ያጣጣለው ሲሆን በእንዲህ አይነት ነውር ላይ ተሰማርቶ እንደማያውቅ መግለጹንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የፊልም ባለሙያው የጾታ ትንኮሳና ጥቃት ሰለባ ነን በሚል በይፋ ክሳቸውን ካቀረቡት ታዋቂ የሆሊውድ ሴት ተዋንያን መካከል፡- ጁሊያና ሙር፣ ሳሪ ካሚን፣ ስታር ሪናልዲ እና ቴሪ ኮን እንደሚገኙበትም ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡

እስካሁን 50 ሺህ አስሯል፤ 110 ሺህ ከስራ አባርሯል

    ባለፈው አመት ከተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ከ50 ሺህ በላይ ዜጎቹን ያሰረውና 110 ሺህ ያህሉንም ከስራ ገበታቸው ያባረረው የቱርክ መንግስት፤ከትናንት በስቲያ በተጨማሪ 121 የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀድሞ ሰራተኞች ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ሀሙስ እለት የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው 121 ቱርካውያን፣ ከዚህ ቀደም ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ጋር ንክኪ አላችሁ በሚል ከስራ ገበታቸው ያባረራቸው እንደሆኑ የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ፖሊስ በ30 ያህል ግዛቶች ግለሰቦቹን አድኖ ለመያዝ ዘመቻ መጀመሩን አመልክቷል፡፡ ግለሰቦቹ በሚስጥር መልዕክት መላላክ በሚያስችል የሞባይል አፕሊኬሽን አማካይነት ከመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾችና ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ይገናኙ ነበር መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የቱርክ መንግስት ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ ከሆነውና “የመፈንቅለ መንግስቱ ፊታውራሪ” ከሚላቸው ጉሌን ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የሚጠረጥራቸውን ዜጎቹን በጅምላ ማሰሩ በአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና መንግስታት ሲያስተቸው መቆየቱንም አስታውሷል፡፡

10 ዶላር ተቀጥተው ተለቅቀዋል

   በኡጋንዳ የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የግንብ አጥር ስር ሽንታቸውን በመሽናታቸው ክስ የተመሰረተባቸው የአገሪቱ ፓርላማ አባል አብራሃም አብሪጋ፤ በካምፓላ ፍርድ ቤት 10 ዶላር ቅጣት እንደተጣለባቸው ተዘግቧል፡፡
ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት የተሰኘው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ አባል የሆኑት ግለሰቡ፣ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጥር ስር ሽንታቸውን ሲሸኑ ባልታወቁ ሰዎች ፎቶ መነሳታቸውንና ፎቶግራፉም በማህበራዊ ድረ ገጾች በስፋት ተሰራጭቶ መነጋገሪያ መሆኑን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህን ተከትሎም መታሰራቸውንና ለፍርድ መቅረባቸውን ጠቁሟል፡፡
የግለሰቡ ድርጊት የመዲናዋን የአካባቢ ንጽህና ህግ የሚጥስ በመሆኑ ክስ እንደተመሰረተባቸው የጠቆመው ዘገባው፤ መሰል ድርጊቶችን የፈጸመ ሰው በሁለት ሳምንት እስር ወይም በገንዘብ እንደሚቀጣ በማስታወስ፣ ግለሰቡም ጥፋተኛነታቸውን በማመናቸው የገንዘብ ቅጣቱ እንደተጣለባቸው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም የኡጋንዳውን ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የስልጣን ዘመን ለማራዘም ያለመ ነው የሚባለውን የዕድሜ ገደብ ማሻሻያ ህግ በመደገፍ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማግባባት፣ለእያንዳንዳቸው 8 ሺህ ዶላር በሙስና መልክ ከገዢው ፓርቲ የተሰጣቸው ስምንት የፓርላማ አባላት፤”ገንዘቡን አንፈልግም” ብለው መመለሳቸውን  ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ገዢው ፓርቲ የህገ መንግስት ማሻሻያው በከፍተኛ የድምጽ ድጋፍ እንዲያልፍ ለማድረግ ለፓርላማ አባላቱ በድምሩ 3.5 ሚሊዮን ዶላር መደለያ  መስጠቱ እየተነገረ መሆኑን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የአፍሪካ ህጻናት ቁጥር ከአውሮፓ በ4 እጥፍ ይበልጣል
    የአፍሪካ አገራት የህዝብ ቁጥር ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝና፣ ፍጥነቱ በዚሁ ከቀጠለ እ.ኤ.አ በ2050 ከአለማችን አጠቃላይ ህዝብ ሩብ ያህሉ አፍሪካውያን ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው አዲስ የጥናት ውጤት እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ወቅት 1.2 ቢሊዮን የሆነው የአፍሪካ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር፣ በመጪዎቹ 30 አመታት ጊዜ ውስጥ 2.5 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 580 ሚሊዮን ያህል ህጻናት እንዳሉ የጠቆመው ጥናቱ፤ ይህ ቁጥር ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ እንደሚበልጥና በፈረንጆች አቆጣጠር በ2100 ከአለማችን አጠቃላይ ህጻናት መካከል ግማሹ አፍሪካውያን ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
አፍሪካ ከተፋጠነው የህዝብ ቁጥር እድገት ጋር የሚመጣጠን የተማረ ሃይልና ባለሙያ ካላፈራች የከፋ ችግር ውስጥ ትገባለች ያለው ጥናቱ፤ አህጉሪቱ የአለም የጤና ድርጅትንና አለማቀፍ የትምህርት ጥራት ደረጃዎችን ለማሟላት ተጨማሪ 5.6 ሚሊዮን የህክምና ባለሙያዎችንና 5.8 ሚሊዮን መምህራንን ማፍራት ይጠበቅባታል ብሏል፡፡

ሀተታ ሀ…
የዚህ ፅሁፍ መነሻ እውነት ነው…. እውነት እንደ መነሻ እንጂ ያላግባብ ምስጋና ለማቅረብ ታስቦ አይደለም፡፡ ለመተዋወቅና ዝምድና ለመፍጠርም አይደለም፡፡ ጉርሻ ቢጤ ነገር ለማግኘት ማሞካሸት የሚል እሳቤም አልያዘም፡፡ የብልጠት ምስጋና እንዲሆን ታስቦ የተደረገም አይደለም፡፡ በፍፁም፡፡ በእውነት እውቀት እንጂ በብልጣብልጥነት የኖረ… የሚቀጥል ሀገር አለ ብሎ ጸሐፊው አያምንም፡፡ በመሆኑም የብልጠት መወድስ አይደለም፡፡ እውነት ግን ምክንያት ነበር፡፡ የሰራ ስው ሊወደስና ሊመሰገን ይገባል፡፡ የሚል እውነት ነው፡፡ ቤቴ ከባልንጀሮቼ ጋር ቁጭ ብዬ የማወራው… የሚያስወራ ርዕሰ ጉዳይ ከብዙ ጊዜ በኋላ በማግኘቴ የልቤን የእውነት ምስጋና ለማቀበል ያህል ነው፡፡
 
ሀተታ ሁ…
ጠጠር በምታክል የህይወት ተሞክሮዬ ውስጥ የማይረሱ እና ሊዘነጉ የማይችሉ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ የእውነትም ነበሩ፡፡ ታዲያ ለኔ ቀድሞ የሚመጣው ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሀንስ፤ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ብለው በሬዲዮ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ በሬዲዮ ሲተላለፍ ባላዳምጠውም በመፅሀፍ መልክ በመታተሙ ለማንበብ እድል አግኝቻለሁ፡፡ ንግግሩ የተደረገበት ዋና መንስኤም አፄ ኃይለስላሴ፣ ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስትን ለዩኒቨርስቲ መገልገያ እንዲውል በማድረጋቸው ነበር፡፡ ንግግር ተባለ እንጂ ታስቦ የተፃፈ የሊቅ መፅሀፍ ነው ለኔ፡፡ ሀገሬ እንዴት ያለች የሊቅ ሀገር እንደሆነች ከሚያስረግጡ የሬዲዮ ንግግሮች መካከል እንዱ ነው ማለት ይቻላል። መፅሀፉን ያላነበባችሁት ብታነቡት መልካም ፍሬን ታገኙበታላችሁ በማለት ወደ ሚቀጥለው ሀሳቤ ልሻገር፡፡
ከሰማኋቸው እና እውቀት እውቀት ከሚሸቱ የሬዲዮ ፕሮግራሞች መካከል ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ገደማ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይቀርቡ የነበሩት የ“እሁድ ጥዋት” እና “ቅዳሜ ወጣቶች” ፕሮግራም የማይዘነጉኝ ናቸው፡፡ በአንዲት ትንሽ የገጠር መንደር…በሰፈሩ ብቸኛ በሆነችው… በመቀጥቀጥ ብዛት የቢራ ጠርሙስ በመሳሰሉ ባትሪዎች በምትንቀሳቀሰው ያላምሬ ሬዲዮ የሱማሌ፣ የትግራይና የደቡብ ወንድሜን የሕይወት ልምድ፣ ተሞክሮ ያሳወቀኝና እሩቅ ሀገር ስላለው ኢትዮጵያዊ ወንድሜ መንፈሳዊ ቅናት ይፈጥርብኝ የነበረው የቅዳሜ የወጣቶች ፕሮግራም ድንቅ ነበር፡፡ ፕሮግራሞቹ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ፣ ወጣትነትን በእጅጉ የሚገልፁና የሚያንፁም ነበሩ፡፡ ወይ ጉድ! … እኔም በዚች እድሜዬ ነበሩ ካልኩ የሆነ ቦታ የተቋረጠ ና የተረሳ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ችግር አለ እንደማለትም ያስኬዳል፡፡
ትምህርት ቤት ሰኞ ጠዋት በእረፍት ጊዜ ለ15 ደቂቃ የምንወያይበትን ርዕሰ ጉዳይ የሚሰጠን ሌላው የሬዲዮ ፕሮግራም “ከመጻህፍት ዓለም” ነበር። በሚጢጢ አንጎላችን ስለ ገፀባህሪ አሳሳል፣ ስለ ሰው ምንነት የተከራከረንበትን ጊዜ አልረሳውም። «ቃል» የተባል መጽሕፍ ሲተረክ፤ ጥጉ ይልማ ከጸሀይ ይበልጣል ብዬ በመከራከሬ፣ የቀመስኩት ቦክስ ምልክቱ ዛሬም አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን ለዛ ያላቸውና ማንነትን የሚቀርጹ ፕሮግራሞች ነበሩ፡፡ ነበሩ… ነበሩ… ብቻ፡፡

ሀተታ…..
“ከትላንት ዛሬ ይሻላል ነው ይበልጣል” የሚለውን ሀረግ ከየት እንዳነበብኩት አላስታውሰውም፡፡ ዛሬ… በኔ ጊዜ ግን አብዛኞዎቹ በሬዲዮ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ልደትን ለማክበር የተሰናዱ ይመስላሉ። በኔ ጊዜ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች በአራዳ ቋንቋ ብገልፀው … ለ‘ኢንጆይ’ የተቋቋሙ ይመስለኛል፡፡ ድረ ገፅ ላይ የተፃፈ እንግሊዘኛን ወደ አማርኛ ገልብጦ ማንበቢያ ጣቢያም ይመስሉኛል። ያልተጣራ መረጃና መረጃን ብቻ ለማስተላለፍ የተቋቋሙም ይመስሉኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ የክልል ከተማ ላይ የተቋቋመ የሬዲዮ ጣቢያ፣ ስለ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ መለፍለፍ፣ ፋይዳው ለኔ አይገባኝም፡፡ እንዲገባኝም አልገደድም። ይልቁኑስ የአካባቢውን እውነታ፣ ውበት፣ ማንነትና በራስ የመኩራት ባህል፣ በአጠቃላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነት ተኮር ስለሆነ ነገር፣በሬዲዮ ማውራት ግን ለብዙ አርቆ አሳቢዎች ይገባቸዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ግሎባላይዜሽን’ ከሚያመጣው ጣጣ አንዱ መዋዋጥ ነው፡፡ የሀገሬ የሬዲዮ ፕሮግራሞችም መነሻ አላማ መሆን የነበረበት ከዚህ መዋዋጥ የምንወጣበትን መንገድ በማመልከት፤ ጥርት ባለ ኢትዮጵያዊነት መኩራት ምን ማለት ነው የሚል ሀገራዊ አንድምታ ያለውን ሀሳብ ይዞ መቅረብ ነው፡ ነገር ግን ፕሮግራማቸው ቀድሞ ከተዋጠ ወጤቱ አስፈሪ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ የሚዲያ ተፅዕኖ ክብደትን ሳስብ መጭው ጊዜ ያስፈራኛል። የወገኛ ነገር ሆኖብኝ እንጂ የጽሁፌ አላማ ስለ ጣቢያዎች የፕሮግራም ይዘት ማውራት አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ በሰከነ አእምሮ እንዲያስቡ ጠቁሞ ማለፍ ክፋቱ አይታየኝም፡፡

ሀተታ አ…
ቀደም ብዬ ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት፤ የጽሑፌ መነሻ አላማ ስለ አንድ ብርቱ እንስት የሬድዮ ጋዜጠኛ አኮቴት ማቅረብ ነው፡፡ ብርቱ እንስት የሬዲዮ ጋዜጠኛ ብዬ መፃፍ ስጀምር፣ መዓዛ ብሩ የምትባል የሸገር በተለይ ደግሞ “የጨዋታ እንግዳ” አስተናጋጅ ጋዜጠኛ በአንባቢያን አእምሮ እንደምትከሰት እገምታለሁ፡፡ በኔ ጊዜ እየቀረቡ ካሉት የሬዲዮ ፕሮግራሞች በተለየ መልኩ ብርሀን ለመፈንጠቅ የምትታትር ጋዜጠኛ ነች፤ መዓዛ ብሩ። እውነት ነው፤ እኛ ወጣት ኢትዮጵያዊያን የሆነ ብርሀን በማጣትና የባዕድ ሀገር ተብለጭላጭ ብርሃን መሳይን ነገር በመሻት፣ ውቅያኖስ ላይ እንደተጣለ ኩበት እየዋለልን እንደሆንን እኔን እንደ ማስረጃ ማቅረብ ወይም የጎረቤቴን ልጅ መጥቀስ በቂ ነው። ዛሬ ከአድዋ ጀግኖች ይልቅ ቬትናም ላይ ጦርነት ያወጁ የአሜሪካ ‘ጀግኖች’ በልጠውብን፣ በጣም በታመምንበት ሰዓት፣ “የጨዋታ እንግዳ” የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም መኖሩ፣ እውነትም ይህች ሀገር ብዙ ተቆርቋሪ ዜጋ እንዳሏት የሚያመላክት ነው፡፡
አኮቴቴ የጨበጣ እንዳይሆን ግን ምክንያቶቼን ለመጥቀስ ልሞክር፡፡ የአዋቂ እይታ ስም ከማውጣት ይነሳልና ከስሙ ልጀምር፤ “የጨዋታ እንግዳ”:: ጨዋታ ለአብዛኛዎቻችን እንግዳ ቃል አይደለም፡፡ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለ የህይወት ምግብ ነው፡፡ ልብ ካላችሁ ደግሞ ቤተሰቦቻችን “ልጆች ጨዋታ ላይ ነን” ካሉ ቁም ነገር እየሰሩ ነው፡፡ እከሌ እኮ ጨዋታ አዋቂ ነውም ይባላል፡፡ በትያትረኛ ስንመለከተው ደግሞ በቅድመ-ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ለትያትር መኖር ወይም መፈጠር ጨዋታ አዋቂዎች እንደ መነሻ ምክንያት ይታያሉ፡፡ ጨዋታ የሚለው ቃል አስደንቆን ሳንጨርስ እንግዳ ይከተላል፡፡ እኔን፣ አንተን፣ አንችን፣ እኛን ሊገልፅ የሚችል ቃል ነው። በኢትዮጵያዊታችን ከምንኮራባቸውና የጋራ መገለጫዎቻችን ከሆኑት አንዱ እንግዳ ተቀብለን ማክበራችን ነው፡፡ እንደ “ጨዋታ እንግዳ” አይነቱ  ቀላልና ሳቢ አገላለፅ፣ የስነጥበብ አንዱ መገለጫ እንደሆነም ብዙዎች አስረግጠው ይናገራሉ። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ አብረሀም በእንግዳ ተቀባይነቱ ሶስቱ ስላሴዎችን እንዳስተናገደ ሁሉ፤ በጨዋታ እንግዳ የቀረቡ ብዙ አዋቂ፣ መርማሪ፣ አርቆ አሳቢና ሀገርኛ የሆኑ ዘመዶቼ መሆናቸውን ሳስብ እውነትም ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንድል ይስገድደኛል፡፡ ከስያሜው ወጣ ብዬ፣ መዓዛ ብሩን በአደባባይ እንዳመሰግናት ስላደረጉኝ ብዙ ነገሮች ለማውራት ትህትና የበዛው ድፍረት በቂ ይመስለኛል፡፡ መዓዛ ብሩ አብዝታ የጋዜጠኛ ስነምግባርን የተላበሰች፣ ለበቃ የጋዜጠኝነት ሙያ የተፈጠረች ብቁ ጋዜጠኛ ነች፡፡ እንዴት?
ስለ ጋዜጠኝነት ስነምግባር ሲወራ ቀድሞ የሚመጣው፣ ጋዜጠኛ እውነትን የመሻቱ ጉዳይ ነው፡፡ መዓዛ እንግዶቿን ስታጨዋውት የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ ይሄ እና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ሀቁን በራሷ እይታ ለመተንተን አትደፍርም፡፡ አንድ ጥያቄ ጠይቀው መልሱን እራሳቸው እንደሚመልሱትና በእንግዳቸው ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚታገሉ ጋዜጠኞች አይነት አይደለችም፡፡ ሀቁ እንዲወጣ ግን የበሰለ የቤት ስራዋን ሰርታ ትመጣለች። አንዳንዴ “እንግዶቿ ከየት ያገኘችው መረጃ ነው?” እስኪሉ ድረስ ጥናቷ እጅግ በጣም ጥልቀት አለው፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ፣ ልደትህ መቼ ነው የሚከበረው? የምግብ የመጠጥና የልብስ ምርጫህ ምን ይመስላል? ድመት አትወድም አሉ? ጀምስ ቦንድ የተባለው ፈረንጅ አብሮህ እንዲሰራ ጠይቆህ ነበር? የሚሉ አይነት ጥያቄዎች፣ ከመዓዛ አንደበት አልሰማሁም፡፡ ይልቁንም እውነት… በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ሊገነባ የሚችል ሀቅ እንዲወጣ እሳቷን ትለኩሳለች፡፡ ለኔ መረጃ እውቀት የሚሆነው በዚሁ ረገድ ነው ብዬ እተማመናለሁ፡፡
መዓዛ ለምታነሳው ርዕሠ ጉዳይ፣ እራሷን ከምንጩ ትነጥላለች፡፡ ከስሜታዊነት የፀዱ ጥያቄዎችን በማሰናዳትም ከሙያው የሚጠበቀውን ስነምግባር ትጠብቃለች፡፡ በመዓዛ “የጨዋታ እንግዳ” የምናውቀው አንድ እና አንድ ነገር መዓዛ ብሩ የምትባል ጋዜጠኛ እንግዳ ስትጠይቅ ብቻ፡፡ ጥያቄዎቿም ከራስ ስሜት የፀዱ ናቸው፡፡ ለአድማጭ ፍላጎትና ስሜት ቅድሚያ የምትሰጥ ጋዜጠኛ ናት። ይህ አይነቱ ስነምግባር አፍሪካ ውስጥ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ፈታኝና የማይታሰብ ነው፡፡ መዓዛ ጥቁር እንግዳ ብላ ከጋበዘች፤ እንትና የሚባል ግለሰብ፣ እነእንትና የሚባሉ ሰዎች ወይንም እንትን የሚባል መደብ ይከፋዋል የሚል የደካማ ምክንያት ተብትቦ ሲይዛት እስካሁን አልታዘብኩም፡፡ ጥያቄዎቿ የማንም ተፅዕኖ ሲያደበዝዘው አይታይም፡፡ የሀቁ ጠቀሜታ ለአድማጯ እስካመዘነ ድረስ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትልም፡፡
 
የመዓዛ ብሩ ሂስ እና የመቻቻል መድረክ
ይህ እንድፅፍ ካስገደደኝ ሁነኛ የመዓዛ ጥንካሬ መገለጫዎች፣ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ይገኛል። የምንጠያየቅበትን፣ የምንተቻችበትን ና ካለፈው ተምረን የወደፊቱን የምንተነብይበትን መድረክ በማዘጋጀት መዓዛ ትልቅ ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች፡፡ የታሪክ ክፍተቶች በበጎ እንዲሞሉ ትተጋለች፡፡ የትውልድ ቀጣይነት እንዲኖር መመኘት ብቻ ሳይሆን እውን እንዲሆን ትሮጣለች፡፡ በተለይ ደግሞ በ“ጨዋታ እንግዳ” የቀረቡ እንግዶች የዘነጋናቸው ወይንም በተዳፈነ አስተሳሰብ ከሆነ መደብ ጋር መድበን ቂም የያዝንባቸው፤ ሀቁ ሲወጣ ግን በየቤታችን ይቅር ይበሉን ያልናቸው ሊቃውንት ናቸው፡፡ እናም እንደ ሲኤንኤኑ ላሪ ኪንግ እና የሀርድ ቶኩ ስቴቨን ጆን ሳካር፣ መዓዛም ምርቱ ከገለባው የሚለይበት፣ ምክንያታዊ ዳኝነት ገዥ ሀሳብ የሚሆንብት መድረክ ነው፤ የ“ጨዋታ እንግዳ”ዋ፡፡
አቦ መዓዛ ይመችሽ! ከዚህ በላይ ስለ መዓዛ ብቁ የጋዜጠኝነት ተሰጥኦ ለመተንተን ሰፊና ጥልቅ የጋዜጠኝነት እውቀት ይፈልጋል፤ ለማድነቅ ግን ክፍት አእምሮ፣ ተራማጅ አስተሳሰብ ና ስሜት በቂ ነው ባይ ነኝ፡፡ነገ ብዙ መዓዛዎች እንዲመጡና ሌላ መዓዛ እንድናሸት ሁሌም በርችልን፡፡ በስተመጨረሻ መዓዛ “የጨዋታ እንግዳ” ብላ ሰዎችን መጋበዟ፣ አንድምታው ምን ይሆን?.... ሙያው ውስጥ ላሉ ባልንጀሮቿ ብዙ ብዙ ነው መልዕክቱ፡፡ መቸም ለብልህ ሁለቴ አይነግሩትም፡፡
ለኛ… በየትኛውም ቦታ ተሰማርተን ቀና ደፋ ለምንል ወጣቶች ደግሞ ቃሉ ሰፊ ነው፡፡
በ“ጨዋታ እንግዳ” ከቀረቡ ልሂቃን መካከል የአንዱን ሊቅ ንግግር ልውሰድና፣ እኔ እንደሚመቸኝ አድርጌ ላቅርበው። ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያ፣ የማትቀየርና ምርጫ የሌላት እጮኛው ኢትዮጵያ ናት፡፡
የዚችን ድንቅ እጮኛ ሁኔታና ያልተፈታ እውነት ለማወቅ መጠየቅ፣ ጠይቆም ደጉን ከክፉ መለየት። ምክንያቱም እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ መጠየቅ ይበልጣል፡፡ ከመጠየቅም ደግሞ እጅግ በጣም መጠየቅ ያዋጣል፡፡ እንደ ሀገርም እንደ ራስም ለመኖር ሳናስተውል “አብቅቶላቸዋል… ያዛውንት ቃል ምንተዳዬ” ብለን የዘነጋናቸውን፣ በአካባቢያችን ያሉ አዛውንትን እየጠየቅን፣ መቅረፅ፣ መሠነድ ክፍተታችንን ለመሙላት አማራጭ የሌለው ማለፊያ መንገድ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ይህ ጽሁፍ ከ5 አመታት በፊት በጋዜጣችን ላይ ለንባብ የበቃ ሲሆን፣ ሸገር ሬዲዮ ጣቢያ የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በድጋሚ ለንባብ አብቅተነዋል)

(በር ነኣ አሃ በእድ በጎዳ ነኣ ሀርግያጋ ቤአነ ቤስ)
- የወላይትኛ ምሳሌያዊ ንግግር

  በጥንት ጊዜ በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን፣ በአሜሪካው ፕሬዚዳንትና በራሺያው ፕሬዚዳንት ላይ የተቀለደ አንድ ተረት ቢጤ ዕውነት ነበር፡፡ እነሆ፡-
የሁለቱ አገሮች ፕሬዚዳንቶች፤ ወታደራዊ ኃይላቸውን ያወዳድራሉ፡፡ የእኔ ይበልጥ፣ የእኔ ይበልጥ፣ ይፎካከራሉ። በመጀመሪያ የሩሲያው ፕሬዚዳንት፣ አሜሪካንንና የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይል ሊጎበኙ ይሄዳሉ! ከዚያም አንድ ጉዳይ ያነሳሉ፡፡
“የአንድ አገር ወታደራዊ ኃይል የሚለካው፤ ወታደሩ ለፕሬዚዳንቱ ባለው ታዛዥነት መጠን ነው!”
“እርግጥ ነው!” አሉ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፡፡
“በል እንግዲያው ወታደሮችህ ምን ያህል ለአንተ ታማኝ እንደሆኑ አሳየኝ?”
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ይዘው፣ ወደ ወታደሮቻቸው ይሄዱና አንዱን ወታደር ጠርተው፤ ወደ አንድ ገደል አፋፍ ይወስዱትና፤
“በል ወደዚህ አዘቅት ገደል ተወርወር” ይሉታል፡፡
ወታደሩም፤
“አይ አላደርገውም” ይላል፡፡
“ለምን?” ይሉታል፡፡
“ጌታዬ፤ በእኔ ደሞዝ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች” አሉኝ፤ (I have a family to support!) ይላል፡፡ የሩሲያው ፕሬዚዳንት በአሜሪካኑ ወታደር ታዛዥ አለመሆን እየሳቁ፤
“ቆይ የእኔን ወታደር ታማኝነት አሳይሃለሁ!” ይሉና የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ወደ ሩሲያ ይዘውት ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም አንዱን ወታደር ጠርተው፤
“ወደዚህ አዘቅት ገደል ተወርወር!” ይሉታል፡፡
ወታደሩም፤
“ታዛዥ ነኝ ጌታዬ!” ብሎ ወደ ገደሉ ይወረወራል፡፡
እንዳጋጣሚ ግን አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ያርፍና ከሞት ይተርፋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደሳቸው እንዲመጣና ጥያቄ እንዲያቀርቡለት ይጠይቃሉ፡፡
ወታደሩ ተጠርቶ መጣ!
የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም፤
“የእኔ ወታደር ወደ ገደል ተወርወር” ብለው፣ ‹የማስተዳድረው ቤተሰብ አለኝ› አለ፡፡ አንተስ እንዴት ልትወረወር ቻልክ?” አሉና ጠየቁት፡፡
ወታደሩም፤
“I too, have a family to support (እኔም የማስተዳድረው ቤተሰብ ስላለኝ ነው)” አለ፡፡
“እንዴት?” ቢሉት፤
“እኔ አልወረወርም ብል፤ እኔንም ቤተሰቤንም ነው የሚፈጁን!” ሲል መለሰ!
*       *      *
የአንድ ሰው ጥፋት ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማድ ከሚተርፍበት ስርዓት ይሰውረን፡፡ ባለፈው ዘመን የመናገር ነፃነት ባልነበረበት ሁኔታ ውስጥ “አፍ-እላፊ” የሚባል ወንጀል ነበር - የአፍ ወለምታ! “ክብረ ነክ ንግግር” ነበር የሚባለው- ከወታደሩ ዘመን በቀደመው የንጉሱ ዘመን! አፍ - እላፊ ባለስልጣንን፣ መሪን፣ ሥርዓትን፣ አስተዳደርን ከመተቸት እስከ አገርን ማንቋሸሽ ድረስ የሚሰፋ ወንጀልን ያካትት ነበር፡፡ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው አነጋገርም ያስቀጣ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- “ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀቀኛ ኮሚኒስት ናቸው!” እያለ ቀኑን ሙሉ ይለፈልፍ የነበረ ንክ ሰው፣ ታስሮ ነበር! ወንጀሉ፤ “ማንም የሚያውቀውን ሀቅ እየደጋገምክ የምታናገረው ነገር ቢኖርህ ነው!” ተብሎ ነው! “አለፈልሽ ባሮ!” እያለም የባሮን ወንዝ አስመልክቶ መፈክር ያሰማ ሰው፤ ሽሙጥ ነው ተብሎ የታሰረበት አጋጣሚም ነበር!
ዋናው ጉዳይ ሰው ሲታፈን፤ መናገሪያ፣ መተንፈሻ…፣ ዘዴ መሻቱ አይቀሬ ነው የሚለው ዕውነታ ነው! ያሰበ ጭምር ይቀጣል በሚባልበት ሥርዓት የተናገረ፤ መወንጀሉና መቀጣቱ አይገርምም! ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብት በማይከበሩበት አገር ምሬቶች ይጠራቀማሉ፡፡ መውጫ ቀዳዳ ይፈልጋሉና ሥርዓት ወዳለው አመፅ አሊያም ወደ ሥርዓተ - አልበኝነት ሊያድጉ ይችላሉ፡፡ የገዢዎችን የመግዛት አቅም ይፈታተናሉ፡፡ ምላሽ የሌላቸው ጥያቄዎች ይበዛሉ!! ዓለም የጋዝ ታንክ ለመሙላት ሲሯሯጥ፣ ደሀ አገሮች ሆዳቸውን ለመሙላት ይፍረመረማሉ፡፡ “የምግብ ፍላጎት አለመሟላት ከነፃነት ረሀብ ጋር ከተዳመረ፤ የህዝቦች ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል” ይባላል፡፡ የኢኮኖሚ ህመምና የፖለቲካ ህመም ከተደራረቡ፣ ከማስታገሻ ያለፈ በሽታን ይፈጠራሉ! ፍትሕ-አልባ ሁኔታን ይቀፈቅፋሉ፡፡ ሌብነት እንደ ሥራ ይቆጠራል፡፡ አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር ግን፤ ሰላም -አልባ ሁኔታ ውስጥ ከገባን የሰረቅነውን የምንበላበት ጊዜም ይጠፋል! ያደለብነው ኪስ ያፈሳል! የገነባነው ቪላ ይፈርሳል! ለሌሎች የቆፈርነው ጉድጓድ፣ የእኛው መቀበሪያ ይሆናል! በድሮ ጊዜ አንድ ባለስልጣን እሥር ቤት ሲጎበኙ፣ እስር ቤቱን የማስፋፋት ሰፊ እቅድ መያዙን አስተዳዳሪው ያስረዷቸዋል፡፡ ባለስልጣኑም፤ “ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ በደምብ ገንቡና አስፋፉት፡፡ ዞሮ ዞሮ የእኛም የወደፊት ቤታችን ነው!” አሉ ይባላል፡፡ ያሉት አልቀረም - ገቡበት! ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፤ በአንድ ተውኔቱ ውስጥ ንጉሡ እሥር ቤት መርቀው ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ “የአባታችን እርስተ - ጉልት የሆነውን ይህንን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ በተለመደው ባህላችሁ እንድትተሳሰሩበት ነው” ይለናል፡፡    
ዛሬ፤ ከፊውዶ-ቡርዥዋው ስርዓት ወደ ሶሻሊዝም፤ ከዚያም ወደ ካፒታሊዝም አድገናል እያልን፤ የግሎባላይዜሽን ቅርቃር ውስጥ የገባን ይመስላል፡፡ በጥናት ያልተደገፈ ሥርዓት፣ መላ-አጥ መንገድ ላይ በትኖናል ቢባል ማጋነን አይሆንም!
ከነስማቸው እማማ ጦቢያ፤ የሚባሉ የዱሮ ሴት ወይዘሮ ነበሩ አሉ- ደርባባና ጨዋ!
“ከዚህ ከባሪያ የገላገልከኝ ለታ፣ ወዲያውኑ ብትገድለኝ ግዴለኝም” ይሉ ነበረ ሲፀልዩ፡፡
ባሪያ ያሉት ሄደና ሌላ መንግሥት መጣ!
ይሄኛውንም ማማረር ቀጠሉ፡፡
“ምነው እማማ፤ ከዚህ ከባሪያ ገላግለኝ ሲሉ ነበረ፡፡ ገላገለዎት፡፡ አሁን ደግሞ ምን ሆኑና ያማርራሉ?” ቢባሉ፤
“አሃ! ያኛውኮ ከፋም ለማም የጨዋ ባሪያ ነው! ይሄኛውኮ የረባ ጌታ እንኳ የለውም! ጌታውን ቢያውቅ የማንም መጫወቻ አያደርገንም ነበር!” አሉ ይባላል፡፡
አይ እማማ ጦቢያ፡፡ አሜሪካንን አላወቁ! እንግሊዝን አላወቁ! የረባ ጌታ ማን እንደሆነ አላወቁም! ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም መሸጋገር፣ የጌታ አማራጭ የማግኘት ጉዳይ ብቻ ቢሆን እንዴት በታደልን ነበር! ጌቶቻችንን በቅጡ አለማወቅ፣ የነገ ዕቅዳችንን በግልፅ እንዳናይ እንዳደረገን ይኖራል! ከዚህ ያውጣን!!
ለችግሮቻችን ምላሽ ፍለጋ ወደ ሹሞቻችን ማንጋጠጥ፣ ዘላቂና ሁነኛ መፍትሔ አያመጣም! ችግሮቹ የራሳችን የመሆናቸውን ያህል መፍትሔም ከእኛ መፍለቅ ይኖርበታል፡፡ በዲሞክራሲያዊና በፍትሐዊ መንገድ ያላፈራናቸው አለቆች፤ መልካም አስተዳደርን ያጎናፅፉናል ብለን ማሰብ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ነው፡፡ ለዕለት ኑሯችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንኳ ሸምተን ማደር እያቃተን፤ ነው፡፡ ያም ሆኖ ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አሀዞች ማውራት አልገደደንም፡፡ አለቆቻችን መፍትሔ-ሰጪ አካላት መሆን ካቃታቸው መሰንበታቸውን እያወቅን፣ ሁነኛ ምላሽ ካልሰጣችሁን እያልን እነሱን ደጅ እንጠናለን፡፡ እንደ ሲቪልም፣ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲም ዕሳቤያችን ያው ነው! አሌ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የቤት-ጣጣ እያለብን፤ ነቅተን፣ በቅተን፣ ተደራጅተን፣ በአንድነት ፈጥረን የበሰለ መፍትሔ ከውስጣችን ማግኘትን ትተን፣ የሌላ ደጃፍ እናንኳኳለን! የወላይታው ምሳሌያዊ አነጋገር ግንዛቤ የሚሰጠን እዚህ ላይ ነው፡- “የራሱን ልጅ አስከሬን አዝሎ፣ የታመመውን የሹም ልጅ ለመጠየቅ ይሄዳል!” ይለናል፡፡ ሹሞቹ ጤና መስለውት ነው!