Administrator

Administrator

 * ከ1 ቢሊዮን - $30 ቢሊዮን የሚደርስ ሃብት አላቸው
               * አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከቢሊየነሮቹ አንዱ ናቸው

1. ቢሁሚቦል አዱልያዴጅ እና ቤተሰቡ - $30 ቢሊዮን (የታይላንድ ንጉስ)
ንጉሱ በቅርቡ ቢሞቱም ሀብታቸውን  ቤተሰባቸው ወርሶታል፡፡ በዓለማችን ለረዥም ዘመን በርዕሰ ብሄርነት ያገለገሉ ሲሆን በአገራቸው መልካም ስምና ዝና ያተረፉ ንጉስ ናቸው፡፡ ንጉሱ ጠብመንጃ ይወዱ ነበር፡፡ የጃዝ ሙዚቃ ማድመጥና ጀልባ መቅዘፍ ያስደስታቸዋል፡፡ ፎርብስ፤ የንጉሱን ሀብት ሲገምት ጥቂት በማሳነሱ ታይላንዳውያን ትንሽ በስጨት ብለው ነበር፡፡ (እንዴት ተደፈርን በሚል!)
2. ሃሳናል ቦልክያህ - $20 ቢሊዮን (የብሩኔይ ሱልጣን)
ለሱልጣን ቦልክያህ ከዓለማችን ባለፀጎች አንዱ መሆን እምብዛም የሚከብድ አይደለም፡፡  ለምን? ቢባል፣ በመንግስትና በግል ካዝናቸው መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ሱልጣኑ በዓለም ትልቁ የግል መኖሪያ ቤት ባለቤት ናቸው፡፡ (1ሺ 800 ክፍሎች ያሉት) ምርጥ ሲጋር የሚወዱ ሲሆን የራሳቸውን 747-400 ጀት ያበራሉ፡፡ የተለያዩ ውድና ብርቅ የአውቶሞቢል ስብስቦች አሏቸው፡፡  
3. ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳውድ - $18 ቢሊዮን (የሳኡዲ አረቢያ ንጉስ)
ዕድሜያቸው ወደ 80 ቢገፋም፣ለረዥም ጊዜ ንጉስ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወንድማቸው በመሞቱ ነው፡፡ እንደ ሳኡዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባልነታቸው፣ የሃብት ምንጫቸው የነዳጅ ዘይት ነው፡፡
4. ካሊፋ ቢን ዛዬድ አል ናህያን - $15 ቢሊዮን (የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ፕሬዚዳንት)
5. ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም - $4 ቢሊዮን (የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጠ/ሚኒስትር)
የነዳጅ ዘይት ገንዘብን በመጠቀም ዱባይን የመካከለኛው ምስራቅ ቬጋስ አድርገዋታል። በእሳቸው ባለቤትነት ተይዘው በነበሩ ሁለት ኩባንያዎች፡- ዱባይ ወርልድ እና ዱባይ ሆልዲንግ አማካይነት በከተማዋ በርካታ ቢዝነሶችና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች የፈጠሩና የገነቡ ሰው ናቸው። ሼክ ሞሃመድ ኢምሬትስ አየር መንገድን ያስጀመሩ ሰው ናቸው፡፡ በተጨማሪም የዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያና የዱባይ ወርልድ ሴንትራል -አል ማክቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ግንባታን በበላይነት መርተዋል፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ የበረራ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጠውና ባለቤትነቱ የመንግስት ከሆነው ፍላይዱባይ ምስረታ ጀርባም ሼክ ሞሃመድ ነበሩ፡፡  
6. ሃንስ አዳም (ሁለተኛው) - $4 ቢሊዮን (የሊችቴንስቴይን ልኡል)
የአውሮፓ ቢሊዬነር ንጉስ የሆነው ሃንስ አዳም፤ በፋይናንስ ዕውቀቱ በእጅጉ ይታወቃል፡፡  በአሁኑ ጊዜ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን የቤተሰቡን ቢዝነስ ተረክቦ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ንጉሱ ከ1ሺ በላይ ውድና ምርጥ የስዕል ስብስቦች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ከራሱ ጋር የሚቃረን ቢመስልም ዲሞክራሲ ምርጡ የመንግስት ሥርዓት ነው ብሎ ያስባል፡፡
7. ዶናልድ ትራምፕ - $3.8 ቢሊዮን (ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
ቢዝነሳቸውን 7 ጊዜ ያህል ከስሯል ብለው ያመለከቱ ቢሆንም ከወደቁበት በተደጋጋሚ አንሰራርተው ለቢሊዮርነት በቅተዋል፡፡ ፎርብስ፤ የሃብቴን መጠን በእጅጉ አሳንሶታል የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ የሚያሰሙት የሪልእስቴት ከበርቴው ትራምፕ፤ እስከ $10 ቢሊዮን የሚደርስ ሃብት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዋይት ሃውስ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው መንግስት  የሚከፍላቸውን 400ሺ ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ እንደማይቀበሉ ቢሊዬነሩ በተመረጡ ማግስት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ትረምፕ እንደ ቃላቸው ከዘለቁ አሜሪካን ያለ ደሞዝ የሚያገለግሉ ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡      
8. ሞሃመድ Vi - $2.5 ቢሊዮን (የሞሮኮ ንጉስ)
የሞሮኮ ንጉሳውያን ቤተሰቦች በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ ሃብት አላቸው ተብሎ ይታመናል። ዛሬ ንጉስ ሞሃመድ በአገሪቱ ቀዳሚ የመሬትና የግብርና ምርቶች ባለቤት ናቸው፡፡ የንጉሱ ቤተመንግስት በቀን 960 ሺ ዶላር ገደማ ወጪ የተመደበለት ሲሆን፣ አብዛኛው ወጪም ለመኪና ጥገና፣ ለሰራተኞች ክፍያና ለአልባሳት የሚውል ነው፡፡
9. አልበርት (ሁለተኛው)- $1 ቢሊዮን (የሞናኮ ልኡል)
ልኡል አልበርት (ሁለተኛው)፤ በዓለም እጅግ ባለጸጋ ከሆኑ ንጉሳውያን ቤተሰቦች አንዱ ሲሆኑ ሃብታቸው በፈረንሳይና ሞናኮ የሚገኙ መሬቶችን ይጨምራል።  
10. ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ - $1 ቢሊዮን (የካዛኪስታን ፕሬዚዳንት)
የካዛኪስታኑ ፕሬዚዳንት ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ፣ ከዓለማችን ቢሊዬነር ፕሬዚዳንቶች አንዱ ሲሆኑ የሃብት መጠናቸው 1ቢ.ዶላር ይገመታል፡፡ ከታላቋ ሶቭየት ህብረት መበታተን አንስቶ በሥልጣን ላይ ሲሆኑ እንደ አለመታደል ሆኖ ስማቸው ከሙስና ጋር ይነሳል፡፡

“መረጋጋት ተፈጥሯል፤ ጉባኤውን የሚያደናቅፍ ስጋት የለም” - መንግስት
    የአፍሪካ ህብረት በመጪው ጥር ወር በአዲስ አበባ ሊያካሂደው ያቀደው ቀጣዩ የመሪዎች ጉባኤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር በሰላም የመጠናቀቁ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገልጧል፡፡
የህብረቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛ ድላሚኒ ዙማ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ባለፈው ማክሰኞ በጽህፈት ቤታቸው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ውይይት፣ ቀጣዩ የመሪዎች ጉባኤ በሰላም የመጠናቀቁ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው የገለጹ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ አገሪቱ ወደ መረጋጋት መምጣቷን በመጥቀስ፣ የጉባኤውን ሂደት የሚያደናቅፍ ችግር ይከሰታል የሚል ስጋት አለመኖሩን እንደገለፁ ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መንግስት የወጣቶችን ስራ አጥነት የመሳሰሉ ያልተፈቱ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት በማሰብ፣ ህዝቡን ሙሉ በሙሉ ባሳተፈ መልኩ እየሰራ መሆኑንና አገሪቱ ከህብረቱ ጋር በገባቺው የአስተናጋጅነት ስምምነት መሰረት ጉባኤው በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል መግባታቸውን መግለጫው አስታውቋል፡፡

በመላው ዓለም በ7 ሺህ 189 ሰዎች ላይ የሞት ወይም የመጥፋት አደጋ ተከስቷል

አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም በተገባደደው የፈረንጆች አመት፤ 2016 ብቻ 47 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተለያዩ አካባቢዎች በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ ለሞት መዳረጋቸውን የሚያመላክት መረጃ ከተለያዩ አጥኚ ተቋማትና የመረጃ ምንጮች ማግኘቱን ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በአመቱ በድምሩ ከ700 በላይ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የጅቡቲና የሱማሊያ ዜግነት ያላቸው ስደተኞች በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ በመኪና አደጋ፣ በድብደባና በሌሎች የሃይል ጥቃቶች እንዲሁም በመጠለያ፣ መድሃኒትና በውሃ እጦት ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡
አብዛኞቹ ስደተኞች ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉት በሱዳን፣ በግብጽና በሊቢያ መሆኑን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ በመንግስታትና በሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ያልተመዘገቡ ሌሎች በርካታ የሞቱ ስደተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉም ገልጧል፡፡
በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አካባቢዎች በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ወይም ጠፍተው የቀሩ ሰዎች ቁጥር 7 ሺህ 189 መሆኑንና ይህም ቁጥር እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፣ 4 ሺህ 812 ያህሉ አደጋዎች የተከሰቱት በሜዲትራንያን ባህር እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በ2016 የስደተኞች የሞትና የመጥፋት አደጋዎች ላይ የተሰሩ ጥናቶች፣ በየቀኑ በአማካይ 20 ስደተኞች ለሞት አልያም ጠፍቶ ለመቅረት አደጋ እንደሚዳረጉ የጠቆመው ተቋሙ፣ አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ሌሎች ተጨማሪ 300 ያህል ስደተኞች ይሞታሉ አልያም ይጠፋሉ ተብሎ እንደሚገመትም አክሎ ገልጧል፡፡

 “በመመረጤ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል”

     ላለፉት 90 አመታት በዓለማችን በየአመቱ በበጎም ይሁን በመጥፎ ተጽዕኖ የፈጠሩ ግለሰቦችን እየመረጠ ይፋ ሲያደርግ የቆየው ታዋቂው “ታይም” መጽሄት፣ ዘንድሮ ተመራጩን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን “የአመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው” በሚል መርጧል፡፡
በመጽሄቱ አዘጋጆች አቅራቢነት ለ2016 የታይም መጽሄት “የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው” ምርጫ ለመጨረሻው ዙር ከደረሱት 11 የአለማችን ታዋቂ ግለሰቦች መካከል፣ አነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሰኞ አሸናፊ በመሆን የተመረጡ ሲሆን በመመረጣቸው ትልቅ ኩራት እንደተሰማቸው፣ ትራምፕ ለኤንቢሲ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡
ታይም መጽሄት ትራምፕን የዘንድሮ የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው አድርጎ በመረጠበት እትሙ የፊት ገጽ ላይ እንደ ወትሮው የተመራጩን ትራምፕ ፎቶግራፍ ያወጣ ቢሆንም፣ ከስማቸው ግርጌ “PRESIDENT OF THE DIVIDED STATES OF AMERICA” የሚል ሸኝቋጭ ጽሁፍ ማስፈሩ ግን ብዙዎችን እያነጋገረ ነው ተብሏል፡፡ ለ2016 የአመቱ የታይም መጽሄት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ምርጫ በዕጩነት ከቀረቡት የአለማችን ታዋቂ ግለሰቦች መካከል፣ ተሸናፊዋ የዲሞክራት ዕጩ ሄላሪ ክሊንተን፣ ድምጻዊቷ ቢዮንሴ ኖውልስ፣ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግና የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋን ይጠቀሳሉ፡፡
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ እ.ኤ.አ በ2008 እና በ2012 ለሁለት ጊዜያት የታይም መጽሄት የአመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው ተብለው እንደነበር ያስታወሰው ሮይተርስ፤ ባለፈው አመት የታይም መጽሄት የአመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው በሚል የተመረጡት የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል እንደነበሩም አክሎ ገልጧል፡፡
ታይም መጽሄት ከዚህ ቀደም የአመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው በሚል ከመረጣቸው ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች መካከል አዶልፍ ሂትለር፣ ማህታማ ጋንዲ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ፣ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ፣ ንግስት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ ይጠቀሳሉ፡፡

ታላላቆቹ የአለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍት፣ ጎግልና ትዊተር በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት የሚሰራጩ ከሽብርተኝነት ጋር የሚገናኙ መረጃዎችን በማስቆም ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ተስማምተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ የጋራ የመረጃ ቋት በመፍጠርና የሽብር ቡድኖችን የፕሮፓጋንዳ መረጃዎችን የሚያሰራጩ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎችን በመከታተል መሰል መረጃዎች እንዳይሰራጩ ለማገድ ማቀዳቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
“ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የጽሁፍ፣ የምስልና የቪዲዮ መረጃዎች እየተከታተልን በመገምገም እንዳይሰራጩ እናግዳለን፣ የሚመለከታቸው አካላት እርምጃ እንዲወስዱም መረጃ እንሰጣለን” ብለዋል፤ ኩባንያዎቹ በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጡት የጋራ መግለጫ፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ባለፈው ጥር ወር ላይ ከአፕል፣ ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍትና ትዊተር ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ተመሳሳይ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ትዊተር ባለፈው ነሃሴ ወር ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን ከ235 ሺህ በላይ አካውንቶችን በመዝጋት ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

 ለገበያ በሚያቀርቡት የመድሃኒት ምርት ላይ የ2600 % የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የተባሉ ሁለት የአሜሪካ ኩባንያዎች፣ በድምሩ የ112.7 ሚ. ዶላር እንዲከፍሉ ባለፈው ረቡዕ በአንግሊዝ ቅጣት እንደተጣለባቸው አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ፒፋይዘር የተባለው መድሃኒት አምራች ኩባንያ እና ፍሊን ፋርማ የተባለው አከፋፋይ ኩባንያ የሚጥል በሽታ ተጠቂዎች በሚወስዱት መድሃኒት ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል በሚል በእንግሊዝ የገበያ ተወዳዳሪነት ባለስልጣን ክብረ ወሰን የተመዘገበበት የተባለውን የ112.7 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንደተጣለባቸው ዘገባው ገልጧል፡፡
ኩባንያዎቹ እ.ኤ.አ በ2013 ኢፓኑቲን በተባለውና በእንግሊዝ ብቻ ከ48 ሺህ በላይ ታማሚዎች ይወስዱታል ተብሎ በሚገመተው በዚህ መድሃኒት ላይ የስያሜ ለውጥና እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ተጠቃሚዎችን በዝብዘዋል በሚል ነው ቅጣቱ የተጣለባቸው፡፡
ኩባንያዎቹ በወቅቱ 2.83 ፓውንድ ይሸጥ በነበረውን በዚህ መድሃኒት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማድረግ በ67.5 ፓውንድ እንዲሸጥ ማድረጋቸው ተጠቃሚዎችን ያለአግባብ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንዲያወጡ አስገድዷል መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ ቅጣቱን የጣለው ባለስልጣን መስሪያ ቤት ዋጋውን እንዲቀንሱ ለኩባንያዎቹ ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸውም አመልክቷል፡፡

 ትራምፕ ስምምነቱን እንዲያፈርሱ አልፈቅድም ብላለች

        ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቡትን የኒውክሌር ስምምነት የማፍረስ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አገራቸው እንደማትፈቅድላቸው  የገለጹት የኢራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ፤ ትራምፕ ስምምነቱን የሚያፈርሱ ከሆነ ግን የከፋ ነገር እንደሚከሰት ማስጠንቀቃቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኒዩክሌር ስምምነቱን በመጣስ አሜሪካ በኢራን ላይ ከጣለቻቸው ማዕቀቦች አንዳንዶቹ ለ10 አመታት እንዲራዘሙ የሚፈቅደውን ህግ በፊርማቸው የሚያጸድቁ ከሆነ፣ አገራቸው ምላሽ እንደምትሰጥና ይህም አሜሪካን አላስፈላጊ ዋጋ እንደሚያስከፍላትም ሩሃኒ አስጠንቅቀዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አገራቸው ከፈረመቻቸው አደገኛና አክሳሪ ስምምነቶች መካከል፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2015 ከኢራን ጋር የተፈጸመው የኒውክሌር ስምምነት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፣ ስልጣን ከያዙ ለውጥ የሚያደርጉበት አንደኛው ጉዳይ ይህ ስምምነት እንደሆነ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንት ሩሃኒ ግን ባለፈው ማክሰኞ ባደረጉት ንግግር ትራምፕ ስምምነቱን ለማፍረስ ከሞከሩ፣ መንግስታቸውና ህዝባቸው በዝምታ እንደማይመለከቱ አስጠንቅቀዋል፡፡
“አሜሪካ ጠላታችን መሆኗ አንዳች እንኳን የማያጠራጥር ሃቅ ነው፣ በቻለቺው አቅም ሁሉ በእኛ ላይ ጫና ለማሳደር ትፈልጋለች” ያሉት ፕሬዚዳንት ሩሃኒ፤ ሰውዬው ወደ ስልጣን ሲመጡ የተለያዩ የለውጥ ተግባራትን የመፈጸም ፍላጎት አላቸው፣ ያም ሆኖ ግን ትራምፕ ከሚወስዱት እርምጃ ኢራንን ተጎጂ የሚያደርግ አንድ እንኳን አይኖርም ብለዋል በቴህራን ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር፡፡ ኢራን ለአለማቀፍ ሰላም ስጋት አይደለቺም፣ አለም በእኛ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ያደረገው የአሜሪካና የእስራኤል ፕሮፓጋንዳ ነው ብለዋል- ፕሬዚዳንት ሩሃኒ፡፡
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ ከአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ሩስያና ጀርመን ጋር በ2015 ስምምነት መፈጸሟ ይታወሳል፡፡

 “ጦቢያ ጃዝ” 65ኛውን የግጥም በጃዝ ምሽት የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ ያካሂዳል፡፡
በዚህ ኪነ ጥበባዊ ፕሮግራም ላይ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ‹‹ነፃ አውጭ›› በተባለው የሙዚቃ ባንድ ታጅበው ግጥሞቻቸውን ለታዳሚው እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡ የጥበብ ምሽቱ አዘጋጅ እናት የማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ በመድረኩ ከግጥሞች  በተጨማሪ ዲስኩርና መነባንብም ይቀርባሉ፡፡ 

 የመጽሐፉ ርዕስ፡- ዘፍ ያለው
                  ደራሲ፡- ሌተና ኰሎኔል ተፈራ ካሣ
                   የገጽ ብዛት፡- 340
                    ዋጋ፡- 150 ብር
             ገምጋሚ፡- ብርሃነሥላሴ ኃ/መስቀል

     ማርክ ክራመር  በቀዝቃዛው ጦርነት ዙሪያ  በኤም አይ ቲ ፕሬስ የሚዘጋጀው ‹‹ዘ ጆርናል ኦፍ ኮልድ ዎር››  የተሰኘው ጆርናል ኤዲተር ነው፡፡ “ሰፓይስ” በሚል ርዕስ በዚህ ጆርናል ላይ በተካተተው ጽሑፍ መግቢያ ላይ “Espionage and covert operations are notoriously difficult to study” ይላል- ስለላና ምሥጢራዊ ዘመቻዎችን ማጥናት የቱን ያህል አስቸጋሪ  እንደሆነ ሲያብራራ፡፡
እነዚህን ተግባራት ለማጥናትና ጽሑፎችን ለመጻፍ በድርጊቱ ውስጥ ተዋናይ መሆንንን ይጠይቃል፡፡ ያ ደግሞ ሕይወትን ሊያስከፍል ይችላል፡፡ እንደዛም ሆኖ በእንደነዚህ ዓይነት ተግባራት ላይ ምሥጢራዊነት እጅግ ስለሚበዛ በድርጊቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነውም የተሟላ መረጃ ለማግኘት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ነው የስለላና ምሥጢራዊ ዘመቻዎችን የተመለከቱ ታሪኮች “በስማ በለው!” ሳይሆን ድርጊቱ ውስጥ በነበሩ ግለሰቦች  ሲተረኩ እጅግ ጣፋጭና ተዓማኒነት ያላቸው የሚሆኑት፡፡
የስለላ ሥራ በዓለም ላይ መቼ እንደተጀመረ እስካሁን ድረስ በግልጽ ባይታወቅም ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች፤ በተለይም ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የስለላ ተግባር ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ነበር፡፡ የጦርነቱን መገባደድ ተከትሎም በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ እራሳቸውን ያገኙት ኃያላን ሀገራት፤ በምድሪቱ ላይ የኃይል ሚዛኑን የበላይነት ለመረከብ በምዕራቡና በምሥራቁ ጎራ ተሰልፈው ከባድ ወደ ሆነ መጠላለፍ ውስጥ ገብተው እንደነበር የሩቅ ጊዜ ትዝታ አይደለም፡፡
የቀዝቃዛው ጦርነት የማይረሳ ዋነኛ መለያውም በጊዜው ይከናወኑ የነበሩ “የሾተላዩ ሰላዮች” ዓይነት ለሁለት ወገን የሚሠሩ የምሥጢራዊ ወኪሎችና የበላይነቱን ለመያዝ በየቦታው የሚፈፀሙ ግድያዎች ታሪክ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ምሥጢራዊነትንና ግለሰቦችን መንታ ሰብዕና እንዲኖራቸው ያደርግ የነበረ ተግባር፣ ጠላት ተብለው የተፈረጁ ሃገራት መንግሥታዊ መዋቅርና ተቋማት ውስጥ ሰርጎ ለመግባት የሚያስችል ጥበብ የታከለበት ነበር፡፡
የወቅቱ ኃያላን ሃገራት በተለይም ደግሞ፣ አሜሪካና ሶቭየት ሕብረት በእጅጉ እዚህ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀው ነበር፡፡ የስለላን ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በረቀቁ ዘዴዎች ለመደገፍ፣ የበቁ ሰላዮችንና ምሥጢራዊ ወኪሎችን ለመመልመል  ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ ያደርጉ እንደነበርም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ ቡድን ውስጥ የተካተቱ ሃገራት እየተጣመሩ የተቃራኒን ጎራ የስለላ መዋቅር ለመበጣጠስ ጥረት አድርገዋል፡፡ አንዱ በአንዱ ቡድን ላይ የበላይነቱን ለመውሰድ በብርቱ ሲደክሙ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ጠላት በሚሏቸው ሃገሮች ላይ ሰላዮቻቸውን በመበተን የየሃገራቱን ምሥጢር ሲቦጠቡጡ፣ ወታደራዊ አቅማቸውን፣ የሚያደርጓቸውን ዝግጅቶችና የሚያራምዷቸውን ርዕዮተ ዓለሞች ሲሰልሉ፣ ፖለቲከኞችንና የተቃራኒ ጎራ ወኪሎችን ሲያስገድሉና ሲያሳፍኑ መዋል የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነበር፡፡
እነዚህ “የኢምፔርያሊስቱና የሶሻሊስቱ ጎራ” በሚል የተሰለፉ ሃገራት፣ በተለይ ከ1940ዎቹ አንስቶ በአፍሪካ ሃገራት ላይ የነበራቸውን ተቀባይነት ለማስፋፋት መረቦቻቸውን ዘርግተው የተንቀሳቀሱበት ወቅትም ነበር፡፡ በየሃገራቱ ላይ መረቦቻቸውን በመዘርጋት ሊያራምዱት የሚፈልጉትን ተግባር ለማከናወን ረቀቅ ያሉ የስለላ መዋቅሮችን በአፍሪካ ሃገራት ላይ ዘርግተው ተንቀሳቅሰዋልም፡፡    
በዚያን ወቅት ኃያላኑ ሃገራት የየጎራዎቻቸውን ርዕዮተ ዓለም በሌሎች፣ በተለይም ደግሞ አዳጊ በሚባሉት ሃገራት ላይ ለመጫን ሲጣደፉም የነበረበት ወቅት ነው። ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው እንደ ምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ቦታዎች፣ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የነበረው የሁለቱ ጎራዎች ትንቅንቅና ሽኩቻ ደግሞ እጅግ አስገራሚና ፍትጊያ የበዛበት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚህ ሽኩቻ ውስጥ ኢትዮጵያ አጭር በሚባል የጊዜ ልዩነት ውስጥ የሁለቱንም ጎራዎች ርዕዮተ ዓለም ተቀብላ ያስተናገደችበት ታሪካዊ አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር፡፡ መጀመሪያ ከምዕራቡ አለም ጋር ወግና የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ከአብዮቱ መፈንዳት በኋላ ደግሞ ወደ ምሥራቁ አለም ጠቅልላ የገባችበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነው  እ.ኤ.አ በ1977 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር አድርጋው የነበረው ጦርነት፤ የቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት ጦርነት ተደርጎ የሚወሰደው፡፡  ከ1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ እስከ አብዮቱ መባቻ ድረስ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥራ፣ ከወዲያ ወዲህ መላወስ ተስኗት የከረመችበት ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ በሹማምንቱ መካከል የነበረው የእርስ በእርስ ሹክቻ የገነገነበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህም ሃገሪቱ በሰከነ መንፈስ የውጭ ጠላቶቿን ሁኔታ እንዳትከታተል እንቅፋት ሆኖባታል፡፡ በስለላና በአፈናው መረብ ተወጥራ እንደነበር፣ የሌተናል ኮሎኔል ተፈራ ካሣ ‹‹ዘርፍ ለው የተሰኘ መፅሃፍ ይገልፃል (ገፅ 314) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች “ሃገሪቱ ለውጥ ያስፈልጋታል! መሬት ላራሹ!”። የሚለውን የትግል እንቅስቃሴያቸውን በተደራጀ ሁኔታ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በሰሜኑና ሰሜን ምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል አሰቃቂ ረሀብ ተከስቶ፣ “ገባሩ ሕዝብ በጠኔ ተመትቶ እንደ ቅጠል እየረገፈ ነው፡፡ ‹‹የሚቆረጥልን ደመወዝ አንሶናል፤›› የሚሉ ወታደሮች በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫ በጉርምርምታ ላይ ናቸው፡፡ ለንግሥና ያቆበቆቡ የቤተ መንግሥት ሰዎች፣ አፍንጫቸውን ነፍተው በንጉሡ ዙሪያ ተሰባስበው የሚሆነውን በጉጉት ይጠባበቁ ይዘዋል፡፡ ሹማምንቱና መኳንንቱ የአስተዳደር ሥራዎቻቸውን ቸል ብለው በየራሳቸው የግል የንግድ ሥራ በመጠመዳቸው በሃገሪቱ የፍትህና የአስተዳደር ተግባር እንዲዳከም ሆኖ፣ የመንግሥት መዋቅሩ በህዝብ ብሶት እየተንገጫገጨ ነው”  ከዚህም ባሻገር፣ ሹማምንቱ በተማሪ አመፅና ተቃውሞ ስም ወረቀት እያስበተኑ ንጉሡ የተሳሳተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ሊያደርጉ ሲሞክሩ ጥበበኞቹ የህዝብ ደህንነት ባለሙያዎቻችን ደርሰውበት ውርደትን እንዲከናነቡ አድርገዋቸዋል ይላል  መፅሀፉ፡፡ (ገፅ 172)
በእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች መላወሻ ያጡት ሃገሪቱና ንጉሡ በትካዜ ተውጠዋል፡፡ አዛውንቱ ንጉሥ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በአዕምሯቸው እየተመላለሱ እረፍት ቢነሷቸውም፣ አልጋቸውን ወርሶ ሃገሪቱን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚያሸጋግራት ሁነኛ ሰው የማጣታቸው ነገር ቢያብሰለስላቸውም ተስፋ ግን አልቆረጡም፡፡ በዋነኛነት ዘወትር አያሳፍረኝም በሚሉት ፈጣሪያቸው ተማምነዋል። ከፀሎትና እምነት በሻገርም ታማኝና ትጉህ ናቸው ከሚሏቸው ባለሟሎቻቸው ጋር ሆነው የጎበጠውን ለማቅናት፣ የደፈረሰውን ለማጥራት፣ የፈሰሰውን ለማፈስ፣ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አብዝተው ይደክማሉ፤ ይዘክራሉ፡፡ በአዛውንት ጉልበታቸው  ጎንበስ  ቀና ይላሉ። በዚህ መካከል ግን፣  “ሲያመጣው ልክ የለው” እንዲሉ፣  ሃገሪቱንና ንጉሠ ነገሥቱን ከሌላ አቅጣጫ የሚወጥር ክስተት ተከስቷል ይሉናል ደራሲው፡፡   
ከዚህ ሁሉ ውጥረት በስተጀርባ ከብዙሃኑ የአገሬው ሰው የተሰወረ የአፈናና የስለላ ትንቅንቅን፣ በአለም የኃይል ሚዛን ላይ በከባድ ሚዛን ምድብ ውስጥ የተመደቡ ሃገራትን የስለላ አቅም የፈተነ፣ የድሀይቱን ምሥራቅ አፍሪካዊት ሃገር፣ የኢትዮጵያን “የህዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት” አገርን ያኮራ ተግባር የሚያስቃኝ መጽሐፍ ነው- ‹‹ዘፍ ያለው››፡፡
“ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው፣ ኰሎኔሉ፣ “አስጨናቂና እንቅልፍ አልባ የአፈና እና የስለላ ትንቅንቅ” በሚል መፅሃፍ ውስጥ በገለፁት ተልዕኮ ወስጥ ተሳታፊ የነበሩ፣ የሕዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ባልደረባ መኮንን ናቸው፡፡  ደራሲው ጥብቅ ምሥጢሮችን አዋቂ እንደሆኑም ከታሪኩ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ምሥጢር አጠባበቅን በተመለከተ እንዲህ ያስረዳሉ፡- “በምሥጢር የተሠራ በግልም ሆነ የአገር ጉዳይ እስከነ አካቴው /መጨረሻው/ ድረስ ተደብቆ ምሥጢር ሆኖ አያልፍም፡፡ ምሥጢር ሽታ አለው፣ የሚተንም ነው፡፡ የተወሰነ ዕድሜም አለው…”
ማናቸውም የአገርንና የሕዝብን ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚደረጉ ምሥጢር ነክ ጉዳዮች ሁሉ ሊሸከሟቸው በሚችሉ ዜጎች አዕምሮ ውስጥ መቆለፍ እንዳለባቸው እሙን ነው፡፡ የአገርን ምሥጢርን ጠብቆ እስከ ውጤትም ማቆየት፣ ከውጤትም በኋላ ቢሆን፣ የምሥጢርን ዕድሜ በትንሹ ከሃያ እስከ ሠላሳ ዓመት ማቆየት” ጠቃሚ ነው ይሉናል፡፡ ዛሬም ልጆቻቸው ከዓመታት በኋላ መጽሐፉን ለህትመት ብርሃን ሲያበቁት፤ “የአሳታሚው ማስታወሻ” በሚለው ስር፣ ልጃቸው ቴዎድሮስ ተፈራ ከገለፀው መረዳት እንደሚቻለው፣ ከመጠነኛ አርትኦትና ከአንዲት ሃረግ በስተቀር የቀነሰውና የጨመረው የለም፡፡
የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጉዳይን ዋነኛ መሠረት አደርጎ የተዋቀረው “ዘፍ ያለው” የተሰኘው መፅሃፍ፤ “የተደገሰን የእልቂት ሽል ማጨናገፍ አስፈላጊነቱን አምነውበት ከአገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው የነበሩት የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ ኰሎኔል ጋሌብ ሐጂ ዩኒስ አሊ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመሰደዳቸው ብቻ በኢትዮጵያ ላይ ሠይጣናዊ ጠላትነት ያሳደሩ ሦስት አገሮች፡- በታሪክ ተመዝግበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር፣ የሶቪየቱ ዲፕሎማትና የኬጂቢ ሰው ጋር ሦስተኛው ዲፕሎማት፣ ‘ከአንድ አፍሪካዊት ዓረብ አገር’ የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረው ኰሎኔል አፍነው በመውሰድ፣ ኢትዮጵያን ሦስት ሆነው ብቻዋን በስለላና በአፈና ትንቅንቅ ሲገጥሟት፣ ‘አገሬ ላይ ነኝ’ ብላ ሳትንቅ የተቋቋመችው በዘዴ ነበር፡፡”   በማለት መፅሃፉ የታሪኩን አኩሪ ተልዕኮ ይዘከዝክልናል፡፡  
ሃገርን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ የሚያስችል መረጃን ያቀበለ የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረን ኰሎኔል ለመጠበቅ ሲባል የተደረገ ውጥረት የተሞላበት ትንቅንቅ ነው፡፡ መፅሃፉ የሚተርከው፡፡ የሕዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ለሃገራቸው ሲሉ፣ በኃያላን ሃገራት የስለላ ተቋማት ጣልቃ ገብነት ወደ ሶማሊያ ኤምባሲ ታፍኖ የተወሰደውን ሶማሊያዊ ኰሎኔል ከአፋኞቹ እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት “እንቅልፍ ለምኔ?” ብለው፣ ውሎና አዳራቸውን በቢሯቸው ውስጥ አድርገው የፈፀሙትን እልህ አስጨራሽ ግብግብ ያስቀኛል  የኮሎኔል ተፈራ ካሣ መፅሃፍ፡፡ “በአደገኛ ሰላይነቱ (የኬጂቢ ሰላይ) ከተሰጠው የዲፕሎማቲክ ሥራ ውጪ አልፎ ያልተፈቀደለትን በመሥራቱ /ፐርሶና ኖን ግራታ/ ተሰጥቶት ከአገር እንዲባረር ተደርጓል” (ገፅ 175) ያሉት ሰው ተባሮ ሲወጣ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ሲሳፈር፣ “ዛሬ ብታስወጡኝ ነገ በክብር ተመልሼ እንደምመጣ እንድታውቁት!” ብሎ ዝቶባቸው፤ ዳግም ተመልሶ ወደ ሃገራችን መግባቱን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? ከዲፕሎማቲክ ግኝኙነት ውጪ ሲንቀሳቀስ ተገኝቶ የተባረረ ዲፕሎማት፤ መንግስት ቢለወጥ እንኳ ዳግም ወደተባረረበት ሃገር እንዳይገባ የሚደነግገውን የቬይና ኮንቬንሽን በማንና ለምን ተጥሶ ወደ ሃገራችን ሊገባ ቻለ? ድርጊቱ በመፈፀሙ ለሃገራቸው ሲሉ የደከሙና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆኑትን የጸጥታ ባለሙያዎቻንን (ደራሲውን ጨምሮ) ያሳዘነና ያስከፋ እንደነበር በሚጋባ በቁጭት ተርኳል፡፡      
የመጽሐፉ ዓቢይ የታሪኩ ማዕከል የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ በነበረው ኰሎኔል ዙሪያ የሚያጠነጥን ቢሆንም በአጠቃላይ በወቅቱ በሃገሪቱ የነበረው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዴት በውጥረቶች የተሞላ እንደነበር ደራሲው በጥልቀት ገልፀውታል፡፡
መፅሃፉ፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ጃንሆይ) በዙሪያቸው ያጋጠማቸውን ከባድ ፈተና እያስታወሱ ሲቆዝሙ ያስቃኘናል፡፡ ንጉሡ የገጠማቸው ፈተና፤ “አይጋፉት ባላጋራ” ዓይነት ሆኖ ሲሰማቸው፣ ደግሞ መለስ ብለው “እስካሁን የጠበቀን እግዚአብሔር ነው፡፡ አሁንም እሱ ነው ተስፋችን” እያሉ ሲጽናኑ፤ በስነ ጽሑፋዊ ጥበቡ እንድንሰማው ሲያደርገን፣ ሹማምንቶቻቸው፣ መኳንንቶቹና መሳፍንቶቹ በወሬ፣ በስብቅ፣ በሸፍጥ በአሉባልታ ምን ያህል ይጠላለፉ እንደነበር መረጃን መሠረት አድርጎ፤ ምሥጢራቸውን ሲካፍለን፣ ይህም በሕዝብ አስተዳደር ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ይተነትንልናል፡፡ደራሲው የመጽሐፉ ዓቢይ ገፀ ባህሪ አድርጎ “በራሪ የሠላም አምባሳደር በሚል” የሰየመው፣ የሶማሊያው አየር ኃይል አዛዥ ኰሎኔል ጋሌብን ሕይወት ከልጅነት ጊዜው ጀምሮ በቅኝ ገዢ የእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ቤት ያሳለፈውን፣ አየር ኃይሉን የተቀላቀለበትን ሁኔታ፣ በፖለቲካዊ አመለካከቱ ሳቢያ በወጉ ሳያጣጥመው ስለከሸፈው ጅምር የፍቅር ሕይወቱ፣ በአገሩ ሶማሊያ ላይ እንደ አልቅት ተጣብቀው ሀብቷን ስለሚቦጠቡጡ ወዳጅ ነን ባይ ሃገራት ስለሚሰማው ሰሜትና ስለደረሰበት በደል፣ በሃገራችን በስደት በቆየበት ጊዜ ያሳለፋቸውን ገጠመኞች እንዲሁም በጣልያን ሃገር በሮም ከተማ ዳግም በስደት ሲኖር ባደረገው ታጋድሎ፣ የኢትዮጵያ የውጭ መረጃ /ፎሪን ኢንተልጀንስ/ ሰዎች ስላደረጉለት ድጋፍና በመጨረሻም ባደረገው ፅናትና ተጋድሎ በመገረም፤ “የሮም ከተማ ከአፍሪካ ዳግማዊ ዘርዓይ ደረስን ወይንም አብዲሳ አጋን ልትፈጥር ይሆን?! (ገፅ 310)” ስላሉበት ዝርዝር ምሥጢር በጥልቀት ይተርክልናል፡፡
የሕዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ መኮንኖችና ባልደረቦች ከ1953 መፈንቅለ መንግስት በኋላ ‹‹ተገፍተናል›› የሚል ስሜት ተሰምቷቸዋል፡፡ የእኛን ተግባር ሌሎች ታማኝ ነን ባዮች እንዲሠሩት ተደርጓል የሚል ቅሬታ ውስጣቸው ገብቷል፡፡ ከፍተኛ መኮንኖቹ በየአጋጣሚው ብሶታቸውን ይገልፃሉ (ገጽ 168)፡፡  “ደግሞስ ከእናንተ ምን ይጠበቃል? ተባልን፤ አመኔታ ከአጣን አሥር ዓመት አለፈን” ሲሉ አቤቱታቸውን እናነባለን፤ ቢሆንም ግን ስለ ሥራ ክፍላቸው አብዝተው ይጨነቃሉም ይላል- “ዘፍ ያለው”፡፡
“ስለ ኢንተለጀንስ ክፍሉ ሥራ ኃላፊነት፣ በተለይ ‘የጃንሆይንና የዘውዱን ክብርና ሞገስ ተዳፈሩ’ የምንላቸው ሰዎች ላይ ብቻ ማተኮር የለብንም፡፡ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ እንሥራ” (ገፅ 166) የሚል ሀገራዊ ስሜት በውስጣቸው የሚመላለስባቸው ስለመሆናቸውም ያስረዳናል፡፡ የተቋሙ ኃላፊ የበላይ መኮንኖችን የተከፋ ስሜት ለንጉሡ በማቅረብ የነበረውን ስሜት ለማደስ ሲውተረተሩም እናያለን፡፡ ይህም ተሳክቶላቸው ለሚካሄደው ዘመቻ መኮንኖቹን በነቃ ሁኔታ የሚያሳትፉበትን ታሪካዊ ክስተት መፍጠራቸው መጽሐፉ ይዳስሳል፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሶማሊያ አምባሳደር፣ ከዲፕሎማሲ ሥራው ባሻገር ወዳጅ ከሚላቸው ሃገራት የሰለላ መዋቅሮች ጋር አብሮ የሃገሪቱን ምሥጢር በመሰለል ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ በተለይም ደግሞ  “ከአንበሳ መንጋጋ ሥጋ ፈልቅቄ ወስጃለሁ” ብሎ ካመነ ወዲህ ኩራትና ትዕቢት ልቡን ወጥሮታል፡፡ የፈለቀቀውን ሥጋ ከኢትዮጵያ በሆነ ዘዴ አሾልኮ በሃገሩ መሬት  ከሃገሩ መሪዎች ጋር ሊያላምጠው ቋምጧል፡፡ ለዚህም በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ ሁለት ቁመተ ሎጋ ኮማንዶዎችን ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ወዲህ ደግሞ “የፈለቀቁትን ሥጋ አፋቸው ሳይከቱት መልሰን እንነጥቃቸዋለን” የሚሉት የኢትዮጵያ የሕዝብ የጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ መኮንኖችና ባልደረቦች፣ ሥራዎቻቸውን በተጠና እና ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ እያከናወኑ ነው፡፡ “/Mission Accomplished/ ተግባር ተፈፀመ!” ይሉናል። ግን እንዴት የቀረውን አንብባችሁ ድረሱበት- ከመፅሃፉ፡፡ ትገረማላችሁ፡፡ ትደመማላችሁ፡፡

Monday, 12 December 2016 12:15

ማወቅ ይጠቅማል!

መጠጦችና የአልኮል ይዘታቸው
ቢራ- 4%-6%
ወይን ጠጅ- 11.5%-13.5%
ውስኪ- 40%-46%
ጂን- 40%-50%
ቮድካ 35%-50%
ብራንዲ 35%-60%
ራም- 37.5%-80%
ኡዞ- 40%-46%
ሻምፓኝ- 12%
ተኪላ- 40%-50%
ሳምቡካ 38%
ፓስቲስ- 40%-45%
ሬሚ ማርቲኒ 40%
ማሊቡ- 21%