Administrator

Administrator

አንዳንድ እውነት ሲያረጅ ተረት ይመስላል፡፡
“የዛሬ ዐርባ ዓመት ገደማ የበርበሬ አሻጥር ፈፅመዋል በሚል ነጋዴዎች ተገድለዋል!  ወይም እንደ ጊዜው አባባል አብዮታዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል!” ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ሲሚንቶ ጤፍ ውስጥ ቀላቅለው የሸጡ አሻጥረኛ ነጋዴዎች ታሰሩ ተባለ፡፡ ውሎ አደረና ለግንባታ የሚያገለግል ሲሚንቶ ካገር ጠፋ ተባለና በየደብሩ ለቤተ- ክርስቲያን መስሪያ በህዝብ መዋጮ የተገዛና የተከማቸ ሲሚንቶ ሳይቀር ተነጠቀ - በመንግስት፡፡ ለምሳሌ፣ ከደብረ ሊባኖስ ገዳም፡፡ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ቅቤ ተወደደ። እንደ ዛሬው ሙዝ በዳቦ ብሉ ባልተባለበት ዘመን፣ ለዩንቨርስቲ ተማሪዎች ምግብ የተገዛው ቅቤ ሙዝ ተቀላቅሎበታል ተብሎ የዕቃ-ግዢ ሠራተኞች ከነጋዴ ተመሳጥራችኋል ተብለው ታሰሩ! ደሞ ዋልን አደርንና፣ የዘይት ነጋዴዎች ታሰሩ፡፡ አንዱ የዘይት ነጋዴ ከምርመራ ክፍል አዛዡ ጋር የተነጋገረውን እንይ፡፡ መቼም እንደ ተረት ነው የምንተርከው፡-
አዛዥ፤ “ሥራህ ምንድን ነው?”
ነጋዴ፤ “ንግድ፡፡”
አዛዥ፤ “ምን ዓይነት ንግድ?”
ነጋዴ፤ “የዘይት ንግድ”
አዛዥ፤ “የት?”
ነጋዴ፤ “እዛው መርካቶ!”
አዛዥ፤ “የት አስቀምጠህ ነው ወደ መርካቶ የምታወጣው?”
ነጋዴ፤ “አሁንማ ምንም የለኝም”
አዛዥ፤ "እሺ ሸጠህ ከመጨረስህ በፊት የምታከማቸው የት ነበር?”
ነጋዴ፤ “እኔማ መጋዘን የለኝም፡፡ ዘመድ ቤት ነበር የማስቀምጠው!;
አዛዥ፤ “ይሄ በዘመድ መስራት አልቀረም ማለት ነው….? በል አሁን በአጃቢ ዘመድህ ቤት ሄደህ ቦታውን ትጠቁማለህ፤ ዘመድህን ይዛችሁ ትመጣላችሁ፡፡” አሉና ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
ዘመድ የተባለው ተይዞ መጣና አዛዡ፤ “ዘይቱን የት ነው የምታከማቸው?" ቢሉት “ዘመድ ቤት” አለ፡፡ በዚህ ዓይነት እየታሰሩ የሚመጡት ባለዘይቶች ቁጥር ከሃምሳ (50) በለጠ፡፡ (ይህንን የሚመስል ሁኔታ የዛሬ ሠላሳ ዓመት በቦንዳ ነጋዴዎች፣ በሳሙና ነጋዴዎች፣ “ከኢዲዲሲ በሚወጡ በርካታ ሸቀጣ ሸቀጦች” ዙሪያ ታይቷል፡፡) ከላይ ያነሳነውን  ዘይት ነጋዴ መጨረሻ እንይ፡፡
 አዛዥ፤ “መንግስት፣ የአንተን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ ወስኗል”
ነጋዴ፤ “ምን ተወሰነልኝ ጌታዬ?”
አዛዥ፤ “አብዮታዊ እርምጃ  እንዲወሰድብህ ወይም የሰረቅህበት እጅህ እንዲቆረጥ! የቱ ይሻልሃል?" አሉና ጠየቁት
ነጋዴ፤ “እጄ ይቆረጥ!"
አዛዥ፤ "ለምን እሱን መረጥክ? ስራ መስሪያ እጅ  የለህም ማለት ነው እኮ?”
ነጋዴ፤ “ግዴለም ጌታዬ! ንጉስ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል!” አለ ይባላል፡፡”
*   *   *
ሀገራችን የአሻጥር (የህገ-ወጥ ሌብነትና ምዝበራ) ደሃ ሆና አታውቅም፡፡ ለሆስፒታል ጥኑ ህሙማን ግሉኮስ ግዙ ሲባል እንኳን የደፈረሰ ውሃ የሚሸጡ ነጋዴዎች ያሉባት አገር ናት፡፡ ይሄ እንግዲህ የኦፕራሲዮን መቀስ እሰው ሆድ ውስጥ የሚረሱትን ዶክተሮች ሳንጨምር ነው! የንግዱ ቅጥት ማጣት፣ የዓለም-አቀፍ ሕግ ለፈረመችው አገር ከጉዳይ የሚጣፍ ነገር አለመሆኑ፣ የስር፣ የመሰረት ነውና አያስገርም ይሆናል፡፡ የትም የማይገኝ መድሐኒት፣ ዶክተሮቻችን ብቻ የሚያውቁት የነጋዴ መጋዘን ተኪዶ የሚገዛ ከሆነ፣ ለህክምና የሚያስፈልጉ ዕቃዎችና መድሀኒቶች የኮንትሮባንድ፣ ንግድ፣ እንዴት “እንደበለፀገ” መነጋገር ቢያንስ ጅልነት ነው!
በመሰረቱ መሪዎች፣ የመምሪያ ሃላፊዎች፣ የአስተዳደር ሃላፊዎች ከነጋዴዎች ጋር መመሳጠራቸው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን እንዋጋለን ሲባል ከብሔራዊ ከበርቴው (National Bourgeoisie) እና ከአቀባባዩ ከበርቴ (Compounder Bourgeoisie) ጋር መዋጋት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ መኖሩን  ያፀኸይልናል፡፡ መንግስት ንግድን የማረጋጋት ኃላፊነት አለበት ስንል እጁን አስገብቶ ነጋዴ ይሁን ማለት አይደለም፡፡ ለዚያ ለዚያማ ንግድ ሚኒስቴርስ የራሱ አይደል? አንድም፤ ከዕለታት አንድ ቀን እንደተደረገው የመርካቶዎቹን ሱቆች ሁሉ ከርችሞ ማሸግም እንዳየነው ትርፉ ፀፀት ነው! “ይሄን ብሉ፣ ይህን አትብሉ!” ማለትም “የምግብ ሥራ ድርጅትን" ሠርተህ አትብላ እንደማለት ነው! ዋናው ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ነው ብለን ደጋግመን የወተወትነው ለዚህ ነበር፡፡ አሁን ሲታሰብ ግን ለካ ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ያስነሳል፡-
1ኛ/ ትክክለኛ ሰው አለን?
2ኛ/ ትክክለኛ ቦታስ አለ?
"The Right Man at the Right Place" - ለካ ጥሩ መፈክር ወይም መርህ እንጂ የተግባር አጀንዳ ካልሆነ ዋጋ የለውም!  ያለጥርጥር መልካም ምኞት ነው፡፡ መልካም ምቾት ግን አይደለም፡፡
በትምህርት መስክም ሌብነትና የፈተና ሥርቆት መበራከቱን እየሰማን ነው! ፈተና አውጪው፣ ፈታኙ፣ ፈተና አታሚው፣ አራሚው የተሰናሰለ ሌብነት እንዳይፈፅሙ መቆጣጠር ካቃተን፣ እንደ "ሿሿ” የባስና የታክሲ የማይታረም ሌብነት ጉዳይ፣ የብዙ ሰዓት የቴሌቪዥን አየር ጊዜ ከመብላት የተሻለ ረብነት ያለው ድርጊት እየፈፀምን አይደለም፡፡
ብዙ መልካም ተግባራት የሚፈፅሙትን ያህል እስከ መዘጋት የተቃረቡ መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ከዕለት ሰርክ እየበደኑ ሲሄዱ ይታያሉ፡፡ ቸል ሊባሉ አይገባም፡፡
ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም የሀገራችን ሰላም ጉዳይ፣ የጎረቤት አገሮች ትንኮሳና ወረራ፣ የሰሜኑና የደቡቡ የሀገራችን ክፍል “መንኳኳት የማይለየው በር” መሆን እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የተቃዋሚዎችና የአማጺያን እንቅስቃሴ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ግን መንግስት የሚፈፅማቸው ውሎች፣ ውስጥ ለውስጥ የሚያካሂዳቸው ውይይቶችና ድርድሮች የአገርን ዲፕሎማሲ በማይጎዳ መልኩ ለህዝብ ማሳወቅ አለበት!
የጎረቤት አገሮች ነገር “ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” የሚለውን የአባቶች ብሂል በቅጡ ያስታውሰናል፡፡ “የግብፅና የሱዳን ጆሮ ይደፈን” እንጂ እኛስ “ምቀኛ አታሳጣኝ” ማለቱን እናውቅበታለን! ግድ ገንብተን መስኖ ጀምረንም፣ ልማት እናለምልም መሰረተ ልማት  እናበልጽግ ብለንም፤ ነገረ - ዓለሙን “ወይ አፍሪካን ወይ ፋፍሪካን?!” ብለን አልፈነዋል፡፡
እዛም ሄድሽ፣ እዛም ሄድሽ፣ ወዲህም ወዲያም አልሽ
ሰው ታዘበሽ እንጂ፣ ምንም አላፈራሽ!” ያለው ያገሬ ገጣሚ ጨርሶታል፡፡
 ምንጊዜም ቢሆን መሪው መማክርቱ፣ የካቢኔ አባላቱ፤ የየክልሉ የየወረዳውና ቀበሌ ሃላፊዎች ወሳኝ መሆናቸውን ተገንዝበውና ተጠያቂ መሆናቸውንም አውቀው፣ አመራራቸውን ማሳመር ይገባቸዋል፡፡ ያ ካልሆነ ህዝብ አንድ ቀን አራስ ነብር የሆነ እለት፣ እስከዛሬ “ንጉስ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል” እያለ ማቀርቀሩን ትቶ ቀና እንደሚል አይዘንጉ!! “ጊዜም የስልጣን እጅ ነው” ይሏልና፡፡ ሌላው  አሳሳቢ ችግር ጦርነትን ትዝታ ለማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡ ግጭትን መቀነስ አንድ መላ ነው፡፡ ወቅትን ያልጠበቀ ግጭትን መቀነሰ ግን ከባድ መስዋዕትነትን ቢጠይቅም ታላቅ መላ ነው!

    • ግብፃዊያን ከጥንት ጀምሮ ነው የኢትዮጵያን ይዞታዎች መጋፋት የጀመሩት
          • በእስራኤል ያሉ ዲፕሎማቶች ጉዳዩን በአንክሮ ሊከታተሉት ይገባል
          • አፄ ዮሐንስ ለዴር ሱልጣን ገዳም ትልቅ ባለውለታ ናቸው


          የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በእስራኤል አገር ካሏት ይዞታዎችና ገዳማት አንዱ ታላቁ የዴር ሱልጣን ገዳም ነው፡፡ በዚህ ገዳም ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያንም የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳ ሲሆን በዚህ ምክንያትም በየጊዜው ውዝግቦች የሚያስተናግድ ስፍራ ሆኗል፡፡ ከሰሞኑም ግብጻዊያን የኢትዮጵያ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃዎች ባሉት የዴር ሱልጣን ገዳም ላይ የሃገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ ቀለም በመቀባት የራሳቸው ለማስመሰል ያደረጉት ሙከራ ውዝግብ ፈጥሯል፡፡
በገዳሙ ዙሪያ የሰሞኑን ጨምሮ በየጊዜው በሚፈጠሩት ውዝግቦችና በገዳሙ ይዞታ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የትንሳኤ ጉባኤ ማተሚያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአብያተ ክርስቲያናት ገዳማት ጥናት ባለሙያ የሆኑት  ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-


                   ከሰሞኑ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር  ሱልጣን ገዳም ላይ የተከሰተው ምንድን ነው? እስቲ ስለ ዴር ሱልጣን ማብራሪያ ይስጡን?
መልካም! ዴር ሱልጣን የንጉስ ቦታ ነው የሚባለው፡፡ በእስራኤል ሃገር ኢየሩሳሌም ጎለጎታ ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ ገዳም ነው። ታሪካዊ መነሻውን በአጭሩ ስንመለከት፣ ከልደተ ክርስቶስ  በፊት ለንግስት ሳባ፣ ከንጉስ ሰለሞን የተሰጣት ቦታ ነው፡፡ ቦታው ከኢትዮጵያ ጋር የሚተሳሰረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በንግስት ሳባና በንጉስ ሰለሞን የጀመረው ታሪካዊ ግንኙነት፣ በታሪክም በባህልም በሃይማኖትም ጭምር የተሳሰረ ሆኖ ነው የዘለቀው፡፡ አብዛኛው ቤተ-እስራኤላውያን ጭምር በከፍተኛ ቁጥር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኖረዋል፣ ትስስሩ የጠለቀ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ቦታ ከልደተ ክርስቶስ በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ የነበረ ነው፡፡ ይሄን ታሪካዊ ግንኙነትም ዓለም የሚያውቀው ነው፡፡ መፅሐፍ ቅዱሳዊም ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ግንኙነት ቀጥሏል፡፡ በየአመቱ ኢትዮጵያውያን የፋሲካ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር፡፡ በሐዋርያት ስራ ላይ እንደተገለፀውም፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው ያንን ግንኙነት መነሻ በማድረግ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በጃንደረባው አማካይነት ክርስትና በ34 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ በሶስት ከፍለን ነው የምንመለከተው፤ጥንታዊ፣መካከለኛና ዘመናዊ በሚል፡፡ የዴር ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያ ለመሆኑ ማስረጃዎች በዝርዝር የሚሻ ሰው፣ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፣ ታላቁ አባት፣ በቅድስት ሃገር ይዞታችን ላይ የሰነድ ማስረጃዎች አካትተው የፃፉት መፅሐፍ አለ፡፡ እስራኤላውያን በየአገሩ በተበተኑና እስራኤል በሌላ አስተዳደር ስር በነበረችባቸው ዘመን እንኳ የኢትዮጵያ ቅርሶችና ቦታዎች፣ በአባቶች መስዋዕትነት ተጠብቀው ነው የቆዩት፡፡  ዴር ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያውያን ስለመሆኑ ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ በደንብ አድርገው በማስረጃ ሰንደው ነው ያቀረቡት፡፡
እንግዲህ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል እንደሚባለው ሆኖብናል፤ ግብፃዊያን ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ ነው የኢትዮጵያን ይዞታዎች መጋፋት የጀመሩት፡፡ በርካታ ቦታዎችን በዚህ መንገድ ቀምተውናል፡፡ በብዙ አሻጥሮች ነው ይዞታዎችን በየጊዜው ሲቀሙን  የነበረው። አባቶቻችን ግን ተጋድሎ ማድረጋቸውን አላቋረጡም፡፡ ለምሳሌ አሁን እንደዋዛ በዚያው በኢየሩሳሌም የምኒልክ በር የሚባል ቦታ አለ፡፡ ይህ የሆነው በአፄ ሚኒልክ ዘመን ግብጻውያን ልክ አሁን እንደሚያደርጉት፣ የኢትዮጵያውያኑን ይዞታ ከመጋፋት አልፈው መተላለፊያ በሮችን ሁሉ እየዘጉ፣ አስክሬን ሶስት አራት ቀን እንዲቆይ ሁሉ ያደርጉ ነበር። በወቅቱ አፄ ምኒልክ የሚፈጸመውን ደባ በብዙ ጥረት ለአለም መንግስታት እያሳወቁ ባደረጉት ትግል፣ በሩ ተከፍቶ አስክሬን ወጥቶ እንዲቀበር ስላስደረጉ፣ዛሬም ድረስ እሳቸው ያስከፈቱት በር የምኒልክ በር ተብሎ ይጠራል፡፡
ሁሉም ሰው ስለ ግብፃዊያኑ ሊያውቀው የሚገባው አንድ ነገር አለ። ግብጽ አጠቃላይ ህዝቧ 100 ሚሊዮን አይሞላም፡፡ ክርስቲያኖቹ ደግሞ ከ10 በመቶ አይበልጡም፤ ነገር ግን የግብፅ ህዝበ ሙስሊሙ በዴር ሱልጣን ገዳም ይገባኛል ክርክር፣ ልክ እንደ ክርስቲያኖቹ ሲሟገቱ ነው የምንመለከተው፡፡ በብሔራዊ መንግስት ደረጃ ነው የሚያሳስባቸው እንጂ ለአንድ እምነት ብቻ ትተው አይቀመጡም። በአጠቃላይ በቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ባላቸው ይዞታ በብሔራዊ ደረጃ ነው ጉዳዩን የሚመለከቱት፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስንመጣ ግን ይሄን አንመለከትም፡፡ እርግጥ በነገስታቱ ጊዜ ከአፄ ዮሐንስ ጀምሮ ብዙ ለፍተውበታል፡፡ አፄ ዮሐንስ ለዴር ሱልጣን ገዳም ትልቅ ባለውለታ ናቸው፤ በተለይ ለደብረ ገነት ቤተክርስቲያን፡፡ አጼ ዮሐንስ በዚህ ረገድ ትልቅ ስራ የሰሩ ናቸው፡፡ ቀጥሎ ያሉ ነገስታትም ቦታውን ከማስከበር አንፃር ትልቅ ስራ ሠርተዋል፡፡ አባቶቻችን እኮ ከዚህ ኢየሩሳሌም ድረስ በእግራቸው እየሄዱ ነበር ገዳሙን የሚሳለሙት፡፡ እኔ ከዚህ ኢየሩሳሌም ድረስ ከሄዱ አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ጣሊሞን አውቃቸዋለሁ፡፡ አባቶቻችን ያንን ይዞታ ለማቆየት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
በነገስታቱ ዘመን በምን መልኩ ነበር ይዞታው ይጠበቅ የነበረው?
እንግዲህ ነገስታቱ ፈርሃ እግዚአብሔር የነበራቸው ስለነበሩ በተለይ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ያስጠብቁ ነበር፡፡ ከደርግ ወዲህ ነው የቤተ ክርስቲያን አብዛኛው ክብሯም መብቷም እየተነፈገ የመጣው፡፡ በነገስታቱ ጊዜ ቦታዎቹ ክብራቸው ተጠብቆ፣ ይዞታቸው ተረጋግጦ ነበር የዘለቀው። በቦታዎቹ ላይም በየዘመናቱ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳንጹ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኢያሪኮ በረሃ ላይ ዮርዳኖስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን ያሳነጹት እቴጌ መነን (የቀ.አፄ ኃ/ስላሴ ባለቤት) ናቸው፡፡ በዮርዳኖስና ኢያሪኮ ላይ ያሉ ቅርሶቻችን ተጠብቀው የዘለቁት በነገስታቱ ነው፡፡ ነገስታቱና በኢየሩሳሌም ያሉ አባቶች መንፈሳዊ ግንኙነትም ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ነበር፡፡
ከደርግ መንግስት ወዲህ ግን ያ ይዞታና ቅርስ ሃገራዊ ሃብትነቱ እየቀረ መጣ፡፡  ይሄ ነው ትልቁ ስህተት፡፡ የዴር ሱልጣን ጉዳይ የብሔራዊ ጉዳያችን ሆኖ ነበር መታየት የነበረበት፡፡ ልክ እንደ አባይ መታየት ነበረበት፡፡ ግብጾች ልክ እንደ ናይል ብሔራዊ ጉዳያቸው አድርገው ነው የሚሟገቱበት። የኛ ግን በቤተ ክርስቲያኒቷም ሆነ በመንግስት በኩል የተሠጠው ትኩረት አጥጋቢ አይደለም፡፡ የአካባቢውን ቋንቋ አውቆ፣  በደንብ በሰነድና በማስረጃ  የሚሞግት ባለሙያ መመደብ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው  እዚያ ያሉ መነኮሳት የተማሩ ናቸው፡፡ አረብኛም ሌላም የአካባቢውን ቋንቋ የሚናገሩ፣ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም የሚችሉና የተለያየ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወደ ሃገር ውስጥ ስንመጣ ግን ጉዳዩን  በትኩረት ያለመከታተል  ችግር አለ፡፡ አሁን  እንዳጋጠመው አይነት ችግር ሲመጣ ብቻ የአንድ ሰሞን አይነት ወሬ ሆኖ ያልፋል፡፡ የዴር ሱልጣን ጉዳይ ከሃይማኖት ቦታነትም በላይ ሃገራዊ ገፅታ ያለው ነው። ስለዚህ ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም ካቶሊኩም፣ ፕሮቴስታንቱም፣ ዋቄፈታውም ማናቸውም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ፣ ቦታው የኢትዮጵያ ይዞታ እንደሆነ አውቆ፣ የባለቤትነት ስሜት ሊሰማውና ሊሟገት ይገባዋል፡፡ መንግስትም በዚህ ጉዳይ የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት አለበት፡፡ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ  የእስራኤል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህንጻ ላይ ነበር የተከራየው። ህንጻው በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ነበር የተሰራው፡፡ ከዚያም በኋላ በርካታ ህንጻዎች ተሰርተው የእስራኤል መንግስት ተከራይቷቸው ይገኛሉ፡፡ በአልአዛር እና ቤተልሔም በነገስታቱ የተገነቡ ህንጻዎች አሉ፡፡ እነዚህ ህንጻዎች ሃገራዊ ፋይዳቸው ትልቅ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ በቸልታና በምን አገባኝ ስሜት ማየቱ ነው፣ ዛሬ ላይ ግብፆች የራሳችን የሆነን ነገር ሊነጥቁን የታገሉት። አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው እንደሚባለው ነው ያደረጉት፡፡ እኔ ቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ከአንዴም ሶስቴ ሄጃለሁ፡፡ መሄድ ብቻ አይደለም፤ ተቀምጬም ያሉትን ቦታዎችና ታሪክ ለማጥናት ሞክሬያለሁ። "የኢየሩሳሌም ማስታወሻዎቼ" የምትል አነስተኛ መጽሐፍም ለንባብ አብቅቻለሁ፡፡ በአቶ አማከለ ገበየሁ የተዘጋጀው “ቅድስት ሃገር” የሚለው ሙሉ ይዞታዎቻችንን ያካተተው መፅሐፍም በእስራኤል ታትሞ ነበር፡፡ እዚህም እንዲታተም ተደርጎ በኢየሩሳሌም ስለሚገኙ ይዞታዎቻችን ትልቅ ግንዛቤ እንዲገኝ አድርገናል፡፡
አሁን የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው?
አሁን ወደ ተፈጠረው ችግር ስንመለስ፣ ግብጻዊያኑ ሆን ብለው፣ ጊዜ ጠብቀው ነው ይሄን ችግር የፈጠሩት፡፡ የእስራኤልን ባለህበት እርጋ የሚል ህግ (ስታተስኮ) ሽረው ነው ይሄን ችግር የፈጠሩት፡፡ ይሄ ባለህበት እርጋ የሚለው  ህግ እንዲጣስ ማን ፈቅዶላቸው ነው፣ የራሳቸውን ባንዲራ  የኛ ገዳም ግድግዳ ላይ የቀቡት? ስለዚህ ጉዳይ የእስራኤልንም መንግስት  አጥብቆ መጠየቅ ይገባል፡፡ የኛ አባቶች በዚህ ገዳም ውስጥ ሲኖሩ ባለው ህግ የተነሳ ጥገና እንኳ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው እንዲሁ ነው የሚኖሩት። ይሄ በሆነበትና የባለህበት እርጋ አዋጁ ባልተሻረበት፣ ግብፃውያኑ እንዴት ይሄንን ሊፈፅሙ ቻሉ? ብሎ መጠየቅ  ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ወቅት የፀሎት ወቅት ነው፡፡ በአለም ያለ ክርስቲያን በሙሉ ወደ እስራኤል ለመሳለም ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዛት ይጓዛሉ። እዚያ ሄደው በንጹህ ህሊናቸው መፀለይ መሳለም ሲገባቸው፣ ይሄንን የሚያሳዝን ነገር ሲያዩ፣ ለእስራኤልም ገፅታ ጥሩ አይደለም። ግብጻዊያኑ ሆን ብለው አለማቀፍ ቀልብ ለመሳብና ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ ሆነ ተብሎ ጊዜ ተጠብቆ የተጫረ እሳት ነው፡፡
የግብጻውያኑ ዓላማ ምንድን ነው?
ያው በኛ ቦታ ላይ ባንዲራቸውን የሚያመለክት ስዕል መሳላቸው፣ ይሄ የኛ ነው ማለታቸው ነው፡፡ የኛ ነው እያሉ ፎቶ እያነሱ ለዓለም ለማሳወቅ  ነው፡፡ ምንድን ነው አላማው? ይሄ እኮ ግልፅ ነው፡፡ አይን ያወጣ ትንኮሳ ነው፡፡ የእስራኤል መንግስት ይሔን ጉዳይ በትኩረት ማየት አለበት፡፡
በትክክል በቦታው ላይ የተፈጸመው ምንድን ነው?
የግብፅ ባንዲራን ቀለም ነው በገዳሙ አካባቢ የቀቡት፡፡ እንዲህ ያለ ትንኮሳ ነው የፈፀሙት፡፡ በገዳሙ በር አጠገብ ነው ይሔ ምልከት የተቀመጠው፡፡ ይሄ በግልፅ ወቅቱ በርካቶች ወደ ስፍራው የሚሄዱበት በመሆኑ "ይሄ የግብፅ ነው" ብለው እንዲረዱ ለማድረግ ነው፡፡ ይሄ በጣም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አደገኛ ስልት ነው፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም  ሊቃወሙት ይገባል፡፡
ይሄ ችግር በየጊዜው ነው የሚፈጠረውና ዘላቂው መፍትሔ ምንድን ነው?
 በኔ በኩል ሶስት መፍትሔዎች አሉ፡፡ አንደኛው በእስራኤል ያለን የይዞታና የቅርስ ጉዳይ በ,ንብረትነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ መገልገያ ይሁን እንጂ ጉዳዩ የሃገር ገፅታን የያዘ ነው፡፡ የእስራኤልና የኢትዮጵያን ግንኙነት ታሪክ የያዘ ሃብት ነው፡፡ ይሄ ሃብት የሃገር ሃብት እንደመሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ልክ እንደ ግብፆች ወይም ከዚያም በተሻለ መንገድ፣ የዴር ሱልጣን ጉዳይ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ እንደሆነ ማሳየት አለባቸው፡፡ ይሄ ገዳም ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም አሉ፡፡ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ ቅርሶችም አሉን፡፡ የእነዚህ ገዳማትና ቅርሶች ታሪክ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካትቶ ለተማሪዎች መሰጠት አለበት፡፡ ልክ ሃገር ውስጥ ያሉት ቅርሶች እንደተካተቱት ሁሉ እነዚህም የኛ ቅርሶችና ንብረቶች ስለሆኑ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተት አለባቸው፡፡ ይሄ መደረጉ አንደኛ  ጉዳዩ እንደ ሌሎች ቅርሶች ሁሉ በትውልዱ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ  ይረዳናል፡፡
ሁለተኛው መፍትሔ፣ እያንዳንዱ በመላው ዓለም የሚገኝ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሙሉ በጉዳዩ ላይ የትዊተር ዘመቻ ሊያደርጉ ይገባል። ጉዳዩ አለማቀፍ ትኩረት እንዲያገኝና ህጋዊ መብታችን እንዲከበር፣ አለም ከኛ ጎን እንዲሰለፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች አለ፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ሃገሪቷን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ መንግስት የዴር ሱልጣን ጉዳይን የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ብቻ አድርጎ አይደለም ማየት ያለበት፡፡ በእስራኤል ያሉ ዲፕሎማቶች ጉዳዩን በአንክሮ እንዲከታተሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ጉዳዬ ብሎ ትኩረት ሰጥቶ ሊይዘው ይገባል።

አዲስ አድማስ
አሁን ደግሞ በዩቲዩብ መጥተናል!!

  ትኩስ መረጃዎች፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትንተናዎች፣ የስኬታማ ሰዎች ታሪክ፣
ወቅታዊ ቃለመጠይቆች፣ ጥበባዊ ወጎች፣ ግጥሞች፣ አነቃቂ ትረካዎች፣
ድንቃድንቅ ታሪኮች፣ የኪነጥበባት ቪዲዎች --
በማራኪ አቀራረብና በጥራት!
አዲስ አድማስ
አሁን ደግሞ በዩቲዩብ መጥተናል!!
ቻናላችንን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ!!

  "ይህ ድርሰት፥ በኢትዮጵያ የክርስትና ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም፥ ጋዜጠኛ በረከት “to give voice to the voiceless”/ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ነው በመቃብር ቤት ታፍኖ ያለውን የሊቃውንቱን ሕመምና ስቃይ፤ አጥንታቸው ድረስ የዘለቀውን ሐዘንና እንባ በመረዳት በብዕሩ ድምጽ ሊሆናቸው ሲሞክር ያየነው፡፡--"
                የመጽሐፉ ርዕስ ፦ በእኔ ቤት
                የገጽ ብዛት፦ 181 (መግቢያን ሳይጨምር)
                የመጽሐፉ ደራሲ፦ በረከት ዘላለም
                ዳሰሳ አቅራቢ፡- እንደቸርነትህ


           ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ምክንያት የሆነኝ፥ ጥላሁን ግርማ አንጐ የሚሰኝ ወጣት «በእኔ ቤት» ስለተሰኘው ልብወለድ በማሕበራዊ ገጹ ላይ መጻፉ ነው፡፡ ይኸውም፥ «ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ዓለማዊው ስፍራ የገባችበትን የሙስና ድር አንድ ለ14 ዓመታት ያህል በመቃብር ቤት እየኖረ፤ ሥራ ለመቀጠር ደጅ እየጠና፤ ለሙስና የሚከፈል ገንዘብ ለማጠራቀም ስለተከፈለ ፍዳ አነበብኩ።» ሲል ጽፎ ተመለከትኩ። ወጣት ጥላሁን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው ዘር ላይ የተመሠረተ መሳሳብ ከልብወለዱ መረዳቱንና ኦርቶዶክስ ባረጀና ባፈጀ መዋቅራዊ አስተዳደር መባጀቷ እንዳሳዘነው ጨምሮ ገልጾ ነበር፡፡ ሐሳቡንም ሲቋጭ፥ እነዚህ ሲሰራባቸው የቆዩ ያፈጁ ልምዶች/Status Quo በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሣዊው ዓለም ለተጠየቅ የተፈቀዱና ሊፈተሹ የሚገባቸው መሆናቸውን ጠቁሞ ነበር፡፡ በዚህ መነሻነት መጽሐፉን ገዝቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
ከሁሉ በፊት በመጽሐፉ የመግቢያ ገጽ (IV) በጥራዙ ያለው ሀሳብ በሙሉ ልብወለድ ስለመሆኑ እና ተጨባጭ ማህበራዊ መነሻ እንዳለው መገለጹ፣ ይህ ነገር እውነተኛ ነው ወይንስ ልብወለድ የሚል ጥያቄ ላነሳንና ለምናነሳ መጠነኛ ምላሽ ለማግኘት የሚያስችለን መስሎ ይሰማኛል። የቋንቋ ጥራት፣ የሀሳብ ጥልቀትና የታሪክ አወቃቀሩን በተመለከተ ዳዊት ወንድምአገኝ (ዶ/ር)ን ጨምሮ አንጋፋ የምንላቸው አድንቀው ጨርሰዋልና ብዙ ለማለት አልደፍርም፡፡
እንደመነሻ፥ የፈጠራ ታሪኩ ከመጀመሩ በፊት ስለምን አዲስ ቅኔ ለታሪኩ እንደተቆጠረ፤ የአንጋፎች የሥነ ግጥም ሥራ ስለምን እንደገባና የእግርጌ ማብራሪያዎች ስለምን እንደተሰናዱ ተገልጿልና በዚህም ላይ ተጨማሪ ማለት አይጠበቅም፡፡
በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን የተሰጡ አስተያየቶችን በመመርኮዝ፥ በውስጡም ያለውን የሐሳብ ሰንሰለትና የቋንቋ ጥራት በማጤን ከተማ ውስጥ እንደ አደገና የመጀመሪያ ሥራው እንደሆነ ወጣት ድርሰቱ የይድረስ ይድረስ የተከወነ እንዳልሆነ መመስከር ይቻላል፤ የነገረ ፈጅ ያህል መስመር በመስመር ታስቦበት የተከተበ ነው፡፡ ምክንያቱም፥ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የት ነች? ምን እየተሠራባት ነው? ለምን? በእነማ? ቀጣይ እጣዋስ ምን ሊሆን ይሆን? ሊሉ ለወደዱ ጠቅለል ያለ ምላሽ የሚሰጥ፥ ላላሉት ወገኖች ደግሞ ጥያቄ ፈጥሮ እግረመንገዱን የምላሽ አቅጣጫ የሚያመለክት ሥራ ነው፡፡ ይኸውም፥ ሐሳብን በተሟላ መልኩ ለመረዳት በመሰረታዊነት የሚያግዘው የ5W1H (አምስቱ የደብሊው እና አንዱ የኤች መጠይቅ)፥ ከጊዜ ቦታና ሁኔታ ጋር ስምሙ ሆኖ መከተቡ የሚደነቅ ይሆናል። ለእንዲህ አይነቱ የታሪክ አይነት የሐሳብ ይዘቶችን በምክንያትና ውጤት እያጀቡ መመልከትና ማመልከት በጋዜጠኝነት እንደተመረቀና እየሰራበት እንደሚገኝ ባለሙያ፥ ከአርስቶትል ጀምሮ እስከ ቶማስ አኲናስ ድረስ የተቀመጡትን ሕጎች ለማክበር የሄደበትን ርቀት ተመልክቻለሁ፡፡ በተጨማሪ፥ አንባቢ በድርሰቱ ፍጻሜ ፈራጅነትን ተጋብዟልና፥ በወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች ዘንድ መሰረታዊው ታሪክን የማንጸሪያ ሕግ 5W1H መከበሩ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ተረድቼዋለሁ፡፡
ድርሰቱን ተመርኩዞ ዋለልኝ መንግስቴ በሚሰኝ የብዕር ስም የሚጽፍ/የምትጽፍ (ጾታ ባለመታወቁ እርሳቸው እያልን ለመቀጠል እንገደዳለን) አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት እንደሚወዱ ያተቱበት ጽሑፍ ጥሩ ዕይታ የሰነቀ ነውና ከሌሎች አስተያየቶች ጋር እየተዛነቀ ቢቀርብ መልካም ይሆናል፡፡
ዋለልኝ፥« የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጥንታዊነቷ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ያሳስበኛል። እርሷን ሊያግዙ የሚችሉ መልካምና ገንቢ ሐሳቦች እንዳይንሸራሸሩ በማወቅ ወይም ባለማወቅ አቅባለች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአዕምሯአቸው በሳል የሆኑ አባላትና ልጆቿን አውግዛለች፤ አሳዳለችም፡፡ እንደ ግለሰብ ይህ ያሳዝነኛል፡፡ በዚህ ልብወለድ ውስጥ የሚገኘው ተውሕቦ የተሰኘ ገጸ ባሕርይ እንደታዘበው በጥቅማ ጥቅም፣ በዘመድ አዝማድ፣ በወንዜ ልጅነትና በመደለያ (ጉቦ) የሚሠራው ሥራ እየተንሰራፋ መሄዱ ይህችን ድንቅ የዕምነት ቤት ምን ያህል እያዋረዳት እንዳለ እንመለከታለን።» ይላሉ፡፡ ይኸውም፥ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉትን፣ The Unresponsiveness of the Late Medieval Church: A Reconsideration መሰል ጽሁፎች ያነበበ የኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ከመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ጋር የሚያመሳስላትን ነገር ያገኛል፡፡ የሃይማኖት አባት የፈረንሳይ ይሁን የጣልያን በማለት በዘር መቧደንና ቤተ ክርስቲያንን በድሎት ለመኖርና ለሀብት መሰብሰቢያነት መጠቀም የካቶሊክን ቤት ክፉኛ አምሶ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ማለፉን ያስታውሰል፤ በማለት በማስረጃ ያስረግጣሉ፡፡
የአቶ ዋለልኝ ሐሳብ እዚህ ላይ ቢቆይ፥ አነጋጋሪ በሆነው በዚህ ልብወለድ ላይ፥ ዮሴፍ ፍስሃ ሰውነት የሚሰኝ ወጣት (የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ይመስለኛል) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚስተዋል የአስተዳደር በደል፣ የሊቃውንት ለቅሶና እንባ በሥነ ጽሑፍ እስከአሁን በአግባቡ እንዳልቀረበና ጋዜጠኛ በረከት ዘላለም ግን ገንዘብ የሌላቸው ሊቃውንት ለመቀጠር ምን ያህል አፈር እንዲበሉና እንዲለብሱ እንደተፈረደባቸው በቅርብ የሚያውቀውን ሐቅ በልብወለዱ እንዳገኘ በማሕበራዊ ገጹ ላይ አብራርቷል፡፡
በድርሰቱ ላይ ግላዊ ዳሰሳውን ያሰፈረው ዮሴፍ፥ (በገጽ 64) “አንደበተ ርቱዕ ጩሉሌዎች” የሚለውን መነሻ በማድረግ በብዙ አድባራት፥ «የፈለገ ደጅ ብትጸና፣ የአለቃ እግር ብትስም፣ የፈለገ ወድቀህ ብትነሳ፣ በፈጣሪ… በእመ ብርሃን… ባዛኝቱ እያልክ ብትለምን፤ በአምላክ ሀልዎት እናምናለን የሚሉ… ግን በተግባር ፈጽሞ በአምላክ ሀልዎት የማያምኑ ቀሚስ ለባሾችና ጠምጣሚዎች የሰው ልመናና ለቅሶ የሚሰሙበት እንጥፍጣፊ ርኅራኄ የላቸውም።» ሲል ጽፏል፡፡ “ለምን?” ከተባለም የበረከት መጽሐፍ እንደሚገልጽልን፤ «ከሌለህ የለህም!» ነው በማለት የአሠራሩን መደምደሚያ ያነሳል። በደላላ ደብተራዎች በኩል የሚተመን ገንዘብ ላዘጋጀ ግን እንደ ገንዘቡ መጠን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ፥ ከከፍተኛ አንስቶ ዝቅተኛ ደመወዝ እስከሚገኝባቸው አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ከቢሮ ሥራ እስከ ቀዳሽ አወዳሽነት አማርጦ መቀጠር መቻሉ የዘመኑ ሐቅ መሆኑን ጠቅሷል። ይኸውም፥ በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን simony እየተባለ በአውሮፓ ምድር የቤተ ክርስቲያን ሥራና ሹመት በገንዘብ እንደሚሸጥና እንደሚገዛ በ1992 በJoseph Lynch የተጻፈው The Medieval Church የሚሰኘው ድፍን አውሮፓ የሚስማማበት የታሪክ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ወደየት እየሄደች እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡
በመጽሐፉ (ገጽ 21) በአንድ መሪጌታ ተወክሎ የቀረበው ጩኸት እንደገለጸው፣ የሌብነት አሠራሩን የማያውቁትና ያልተገለጠላቸው፤ በቅንነት ተመርተው በሙያቸው የሚቀጠሩ የመሰላቸው የዋህ ሊቃውንት፣ በጩኸት "ሙስናን እናጋልጣለን" ያሉ እንደሆን “በሰርቆ አደሮች’’ ከቢሮና ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተንጠልጥለው መውጣት እጣቸው መሆኑን ዮሴፍ ያትታትል፡፡
ወደ ዋለልኝ ምልከታ ስንመለስ፥ የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባቶች ኃላፊነትና የሥራ እንቅስቃሴ ሌላው የሚያጠያይቅና ከልብወለዱ ተወስዶ ብዙ ሊያነጋግር የሚያስችል ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ቅን የቤተ-ክርስቲያን ወዳጆች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ ነገሮችን ውጠው እስከአሁን አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በአስተዳደር ለማገዝ የሚቋቋመው የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ፣ በየቦታው ያለበት ፈተና ይህ ነው፡፡ ይኸውም ተውሕቦን ሲያብከነክነው በግልጽ እናያለን፡፡
በዚህ ዘመን ያለውን የሌብነት ፈተና ለመረዳት ልብወለዱ ከተራ ፈጠራነት አለፍ እንደሚል የሚያስረዳው ዮሴፍ ፍሥኃ፥ «ስንቶች የሚገባቸውን እንዳያገኙ ገፍተናቸው ወደ ሌላ ቤተ እምነት ሄዱ? ለምንድን ይሆን የአቋቋሙ ሊቅ መሪጌታ ተውሕቦ ሥራ ለማግኘት የሌላ ቤተ እምነትን ሲቀላውጥ የነበረው? አንደ ግብዙና ወሬ አቀባዩ ዲ/ን አካሉ በአብነት ትምህርት የደከሙትን፤ ከቤተ ክርስቲያን የተገፉ፤ የሚበሉት ያጡ ምስኪን ሰዎችን በምን ሞራላችንስ “ሌላ ቤተ እምነት እየሠራችሁ ነው፤ መናፍቅ ናችሁ!” ለማለት የምንደፍረው? በችግራቸው ጊዜ ያልደረስን ሰዎች በችግር ምክንያት ለሚወስዱት ውሳኔ የመፍረድ ሞራል መሠረት ከየት አገኘነው? በቤተ ክርስቲያን የሚገባቸውን ቦታ በማጣት ስንቶቹ ሊቃውንት ጎዳና አዳሪ ሆኑ? ስንቱ በብስጭት ሰካራምና ጫት ቃሚ አጫሽ ሆኑ?» የሚሉ ጥያቄዎች እንደተነሱበት አስፍሯል፡፡ ለዚህም ይመስላል በአ.አ.ዩ የአዕምሮ ሕክምና መምህሩና የ"አለመኖር" መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ዳዊት ወንድምአገኝ፤ «በተጎዳ ማህበረሰብና በላሸቁ ተቋማት ውስጥ የራስንና ራስን ማግኘት ምን ያክል የውስጥ ሙግት እንደሆነ ያሳያል። ከሁሉ በላይ አንድ ከተሜ (ደራሲው) የሀገሬውን የእምነት ስርዓት፤ የነዋሪውን ወግና ባህል፤ የጉዳቱን ልክ፤ የመረመረበት ደርዝ ‘ይበል በረከት!’ ያስብላል፡፡» ሲል በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ ሐሳቡን ያሰፈረው፡፡
በሌላ ሐሳብ ዋለልኝ፥ (ገጽ 158) ን መነሻ በማድረግ (አከራካሪነቱ ባለበት የሚቀመጥ ሆኖ) “አባቶች ይገለገሉበት ስለነበረ ጥበብ” በልብወለዱ መነሳቱ ጥሩ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በዚህም፥ «ሥር ማሽነት እና ቅጠል በጣሽነት ከማሕበረሰብ በባሕል በኩል የሚተላለፍ መድኃኒት የመፈለግ ሂደት ሆኖ ሳለ፣ ቅኑን ከደጉ መለየት በማይችሉ ዘንድ የጅምላ ማጥላላት እየደረሰበት መንፈሣዊ ድንቁርና እንዲስፋፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድ ተውሕቦ የተሰኘ ገጸ ባሕርይ፥ የባሕል ሕክምና የፈጣሪ ጸጋ መሆኑን በግልጽ በማመን የሳትነውን ያስረዳናል፡፡» ሲሉ አረዳዳቸውን ያሰፍሩና ባሕላዊ መድኃኒትን መጥላትና ማጥላላት አላዋቂነት መሆኑን የነገረን ሥራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ምክንያቱንም፥ «ዘመኑ የሚያደንቃቸው የ Phytomedicine ባለሙያዎች ስንት ድንበር አቋርጠው የሀገራችን የመንደር መድኃኒት አዋቂዎች ደጅ አልጠፋ ማለታቸውን ማን እስኪነግረን እንጠብቃለን?» ብለው በማጠየቅ፡፡ በልብወለዱ ይኸው ምልከታ በመጉላቱ ይመስላል «በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዉስጥ ያለውን እምቅ የእውቀት ሀብት የሚያሳይ ሥራ!» ሲል ሐኪም እና የድጓ አዋቂው ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም ይርጋ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ገጹ ጽፎ የምናነበው፡፡
በሌላ በኩል፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የበርካታ መንፈሣዊ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች ባለቤት መሆን ስትችል በዚያው የቆሎ ትምህርት ቤትነት ደረጃ ላይ መገኘቷና ባሉበት የሚረግጡ የጉባኤ ቤቶች ባለቤት ሆና መቅረቷ እንዲያስቆጭ የሚያደርግ ልብወለድ መሆኑን ዋለልኝ በትንተናቸው አሳይተዋል፡፡ ይኸውም፥ «በመንፈሣዊ ትምህርት ላይ የተመረኮዙ የጤና፣ የእርሻ፣ የዕደ ጥበብ፣ ማህበራዊ እና መንፈሣዊ ጉዳዮችን የማማከር አገልግሎት በብቁና ልዩ በሆነ ደረጃ ልትሰጥ ስትችል፤ ያንን አለማድረጓ ሌላው የሚስቆጨኝ ጉዳይ ሲሆን… ተውሕቦ (በገጽ 144) ባለው አቅም ይህንን ማድረጉ፥ ልብወለድ ቢሆንም ቁጭትን የሚክስ ነው፡፡» በማለት፡፡
የመጽሐፉን የሴራ አወቃቀር በተመለከተ፥ ተውሕቦ በተደጋጋሚ የDilemma Theory ማረጋገጫ እስኪመስል ድረስ በተዘባረቀ አስጨናቂ ሀሳብ ላይ እንዲዋልል ሲገደድ እናያለን። ነገሩንም፥ «ወደ ፈተና መግባት ሰልችቶኛል፡፡ እንደመግባቴ ግን ዛሬም የመጣብኝን ፈተና በአግባቡ መወጣት ይኖርብኛል፡፡» ይላል፡፡ ይኽንኑ የሐሳብ ሰንሰለት በጥልቀት በመታዘብ ይመስላል «በመቃብር ቤት ውስጥ ከአንድ አስርት በላይ የቆየው ወጣት በዋዛ የሚሸነፍ መንፈስ አልነበረውም። ነፍስና ሥጋውን የሚያፋልም ፈተና ተፈትኖ እየወደቀና እየተነሳ ይጓዛል፡፡ የመቃብር ቤቱ ድቅድቅ ጨለማ ነገን እንዳያይ አይከለክለውም።» ሲል ስለ ገጸ-ባሕርዩ ውጣ ውረድ በአ.አ.ዩ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ረ/ፕሮፌሰር ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) ሐሳቡን ጽፎ የምናነበው፡፡
የመጽሐፉን ማጠቃለያ አስመልክቶ፥ የታሪኩ መቋጫ እንቆቅቅልሽ በመሆን ለአንባቢዎች የቤት ሥራ ተደርጎ መሰጠቱ እኔ በግል የተስማማኝ ቅርጽ ነው፤ ተውሕቦ የወሰነውን አንባቢ አይወስንለትምና፡፡ ሁሉም እንደየንቃቱ፣ ግንዛቤና አረዳዱ ምን ሊወስን እንደሚችል ለመታዘብ የሚረዳ ምዕራፍ ነው፡፡» የሚለውን የዋለልኝን ሐሳብ በመደገፍ የፍልስፍና እና የሥነ-መለኮት ተመራማሪና መምህሩ ዮናስ ዘውዴ፤ «መጽሐፉ ነገሮችን በልኬትና በአግባቡ እንድናይ የሚረዳ ነው።» ሲል የሚያሞካሸው፡፡
ወንድማችን በረከት በልብ ወለድ መልኩ ለመግለጽ የሞከረው የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ እንደ አንገብጋቢ ጉዳይ ተቆጥሮ የሊቃውንቱ የሰቆቃ ሕይወት በአግባቡ እንዳልተጠና የጻፉት በርካታ የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፥ ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም ይርጋ (ዶ/ር) ግን «አስተዳደራዊና ሥነ-ምግባራዊ ብልሽቶች የፈተና ምንጭ መሆናቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያስረዳ ሥራ ነው፡፡ ከንባብ በኋላ በልቦለዱ ውስጥ የታመቁት ሀሳቦች አደባባይ ወጥተው ለውይይት መነሻ መሆናቸው መሰረታዊ ይመስለኛል፡፡» በማለት ነገሩ ከልቦለድነት ያለፈ መሆኑን የሚጠቁም ሐሳብ አስቀምጧል፡፡
ይህ ድርሰት፥ በኢትዮጵያ የክርስትና ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም፥ ጋዜጠኛ በረከት “to give voice to the voiceless”/ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ነው በመቃብር ቤት ታፍኖ ያለውን የሊቃውንቱን ሕመምና ስቃይ፤ አጥንታቸው ድረስ የዘለቀውን ሐዘንና እንባ በመረዳት በብዕሩ ድምጽ ሊሆናቸው ሲሞክር ያየነው፡፡ መጽሐፉ በሥነ-ጽሑፍ፣ በወንጀል ምርመራ፣ በጋዜጠኝነት፣ በሥነ-መለኮት እና ሌሎችም ማሕበራዊ ዘርፎች ላይ ላሉ ተማሪዎች ለጥናትና ምርምር ሥራ እንደ መነሻ ሆኖ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልም ልንገነዘብ እንችላለን።
መጽሐፉ፥ ሁሉም ራሱን እንዲያይና እግረ-መንገዱን የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ የሚያሳስብ እንደሆነ በደራሲው የማሕበራዊ ገጽ ላይ ከሚንሸራሸሩ ሐሳቦች መመልከት የሚቻል ሲሆን እውቀት፣ ሥርዓትና ትውፊት በቸልታ ከመጥፋታቸው በፊት መገናኛ ብዙኃን በግልጽ ጉዳዩን ለውይይት ቢያቀርቡት አሁንም የረፈደ እንዳልሆነ አስተያየት ከሰጡ ሰዎች የመደምደሚያ ሀሳብ ለመታዘብ ይቻላል፡፡
ለመጠቅለል ያህል፥ ይህንን መጽሐፍ ላስነበበን ወንድማችን በረከት ዘላለም፣ ረጅም እድሜና ጤናን እመኛለሁ፡፡ ያላነበባችሁ መጽሐፉን እንድታነቡት እጋብዛለሁ። በቀጣይ ጊዜያት ማሕበረሰብን በእውቀትና በምልከታ ከፍ የሚያደርጉ የሕይወት ነጸብራቆችን በልብ-ወለዳዊም ሆነ ኢ ልብ-ወለዳዊ በሆነ መልኩ እንዲያስነብበን እንመኛለን፡፡

Saturday, 16 April 2022 15:27

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

     ከግብፅ ተነስቶ ያልደረሰው አውቶብስ ጉዳይ
                                    ፉዣዥ

            “ከከንአን ወንድ እና ሴት ጋር መጋባት ለምን ተከለከለ? መሬቱን ወዶ ህዝቡን መጥላት ነው? ማርና ወተቱን ወዶ ነዋሪውን መጥላት ነው?” ወደ እነዚህ በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ። አሁን ስለሌላ ጉዳይ ላውጋህ።
የከንአን ማርና ወተት ተራ ማርና ወተት እንዳይመስልህ።
ንብ አይደለም ማሩን የሚጋግረው። ከላም አይደለም ወተቱ የሚታለበው። የከንአን ምድር ናት ይሄን ማርና ወተት የምታፈልቀው።
እንዴት ሆኖ? እኔ ምናውቄ ወዳጄ።
ይሄንን የሰማ ሰው ለምን እና እንዴት ይላል እንዴ? ለጉዞ ይነሳል እንጂ። ጭራሽ ከመከራ ጋር ተጋብቶ ያለ ሰው።
እንግዲህ የእስራኤል ህዝብ በባርነት ቀንበር ከኖሩበት ግብፅ ተነስተው፣ ቀይ ባህርን ተሻግረው፣ በሲናይ በርሃ ጉዞ የጀመሩት ከንአን ለመድረስ ነው። መሃል ላይ የግብፅ ምስር፣ ዱባ ወጥ ይፈትናቸዋል።
የግብፅ ምስር ወጥ ግን ምን አይነት ይሆን? የግብፅ ዱባስ እንዴት ይሆን የሚሰራው?
በመከራ ነዋ። በመከራ በተያያዘ እሳት ላይ በመከራ የሰራኸውን ድስት ጥደህ፣ በመከራ በደቃቁ የተከተፈ ሽንኩርት አቁላልተህ፣ በመከራ የተገኘ በርበሬና ምስር ተጠቅመህ ነው፣ በመከራ የምትሰራው። ብቻ ግን ደም ደም፣ እንባ እንባ፣ መከራ መከራ ስለሚል ይጣፍጣል። ህዝቤ የናፈቀው ይሄን ነው። እንዴት አይናፈቅ?
ደግሞ እኮ በየቀኑ ከሰማይ መና ይወርድላቸዋል። ያለምንም መከራ። ጎንበስ ብሎ ማንሳት ነው። መጎንበስ ካልፈለክም አፍህን ከፍተህ ማንጋጠጥ ብቻ ነው። አንዳንዱ ብዙ መና ከመሬት ለቀመ። ሌላው ጥቂት አነሳ። ሁሉም መናውን በሉት። ብዙ የለቀመው ምንም አልተረፈውም። ጥቂት የለቀመውም ምንም አልጎደለውም። ሁሉም ጠገበ። ደበራቸው አይገልፀውም። መከራ የሌለበት ኑሮ። ግብፅ የሚለው ስም ራሱ እኮ ከመከራ ጋር መጋባት እንደማለት ነው። ብቸኝነቱን አልቻሉትም። መከራ ናፈቃቸው። ግብፅ ናፈቀቻቸው።
በየቀኑ የሚወርደው መና መቼ እንደሚያቆም ስለማይታወቅ አቁማዳ ወይም መክተቻ የሚመስል ነገር እየፈለጉ ከወረደው መና ጥቂት ይበሉና ብዙውን ማከማቸቱን ተያያዙት። በነጋው ሌላ መና ሲወርድም ያሳደሩትን ይጥሉና አዲሱን ጥቂት በልተው ብዙውን ለነገ ያሳድሩታል።
ያደረውን የሚጥሉት ስለሚተላ ነው። እንደሚተላም ተነግሯቸዋል። በየቀኑ መና እንደሚወርድላቸውም እንዲሁ። ግን ያከማቻሉ። ምን ያድርጉ፣ ግብፅ ስትናፍቃቸው።
አንዱ የሌላውን አቁማዳ ከነመናው ይሰርቃል። አንዱ የሌላውን ማጅራት መቶ አቁማዳውን ከነመናው ይቀማል። አንዱ ጉልበተኛ አስር ደካሞችን እያስፈራራ መና ያስለቅማቸዋል፣ ያሸክማቸዋል።
ብትነካኝ አለቅህም በሚል መንፈስ ነው፣ እያንዳንዱ በበርሃ የሚጓዘው። ምን ታየኛለህ በሚል እርስ በርስ እየተጋጨ ነው ጉዞው።
ከንአን በጣም ራቀች። እንዴት አትርቅ። ግብፅ እና ከንአን ምን ያህል ይራራቃሉ ግን?
ለማንኛውም ስለ ቃል ኪዳኗ ምድር ትንሽ ልበል። ምን አይነት ታምረኛ ምድር ብትሆን ነው፣ ማርና ወተት የምታፈልቀው?
ከንአን ከሚለው ስም ጋር የሚገናኙ የእብራይስጥ ቃላት ብዙ ትርጉም አላቸው። ሃምራዊ ወይም ራስን ዝቅ ማድረግ ወይም የላቀ የቡድን አንድነትን ለመፍጠር ሲባል ግላዊ መሻቶችንና ፍላጎቶችን መተው ማለት ይሆናል። ሃምራዊ ቀለም ከሃብት ንግስና ልእልና ጋር የተያያዘ ነበር። ብርቅና ውድ በመሆኑ።
እንዴት ሆኖ ነው ግን አንድ ቃል ከሁለት ተቃራኒ ነገሮች ጋር ሊያያዝ የቻለው? ከሃምራዊ (ንግስና ልእልና ሃብት) እና ራስን ዝቅ ከማድረግ ጋር።
ወይስ አንደኛው መንገድ ሌላኛው መዳረሻ ሆኖ ነው? ሶስተኛው አማራጭ ሁለቱን ቀላቅሎ እንዳስቀመጠው፣ ለላቀ የቡድን አንድነት ሲባል የግል መሻትን መተው። ራስን ዝቅ በማድረግ ንግስና ልእልና ከፍታ ላይ መድረስ አይነት።
ከንአን ስትደርስ ምን ታገኛለህ? ማርና ወተት የሚያፈልቅ ምድር፣ ልእልና፣ ንግስና። ከንአን ለመድረስ ምን ማድረግ አለብህ? ራስህን ዝቅ ማድረግ፣ የግል መሻትህን መተው አለብህ።
ራስህን ዝቅ ማድረግ የሞት መንገድ አይደለምን? ራሱን የተወ ራሱን ዝቅ ያደረገ ሰው ተረጋግጦ አይሞትም እንዴ? ማንም እየመጣ አይረግጠውም እንዴ? ለመኖር ብሎም ልኡል ለመሆን ራስን ከፍ ማድረግ፣ ራስን ማስቀደም፣ በየቀኑ ከፍታ ማከማቸት አያስፈልግም እንዴ? ራሱን የተው ሰው በርሃብ አይሞትም እንዴ?
ቀይ ባህርን ተሻግረው፣ በበርሃ መና እየበሉ፣ በደመና ተጠልለው አዩት። ግን ደግሞ ከመከራ ጋር ተጋብተው መኖር ናፈቃቸው። ደም ደም፣ እንባ እንባ፣ ጅራፍ ጅራፍ የሚል ምስር ወጥ፣ ዱባ ወጥ ናፈቃቸው።
ምንም እንኳ ዱባና ምስር ወጥ ከመና ባይበልጡም፣ የወጣባቸው መከራ ግን ከመና ያስበልጣቸዋል ብለው አመኑ። ስለ ራሳቸው እያሰቡ፣ ብትነካኝ አለቅህምን እየፎከሩት እየሸለሉት እየተራመዱት እየተናገሩት፣ እየተገዳደሉ እየተነጣጠቁና እየተሰራረቁ፣ እያንዳንዱ ራሱን እየተከላከለ ሌላውን እያስፈራ፣ እየፈራ፣ ቅኔ እየተቀኘ፣ ቅርፅ እየያዘ፣ እየተወጣጠረ ወደ ከንአን ነጎዱ።
እረ እነዚህን ሰዎች ማን በነገራቸው? የከንአን መንገድ እኮ እርሱ አይደለም። ይህኛው የከንአን መንገድ ሳይሆን የግብፅ መንገድ ነው። ከንአን እኮ ያን ያህል እሩቅ አይደለም። ቅርብ ነው። መንገድ ተሳስተው ባከኑ። ከአርባ ምናምን አመት ጉዞ በኋላ ከንአን ደርሰዋል የሚሉ አሉ። ሊሆን ይችላል።
የደረሱ ይኖራሉ። ግን ብዙው ሰው ገና የደረሰ አልመሰለኝም። ቢያንስ እንኳን እኔ አሁንም በመንገድ ላይ መሆኔን አውቃለሁ። ይልቅስ መንገድ ላይ ቆሜ ካንተ ጋር ሳወራ የሰበሰብኩትን መና እንዳይሰርቁኝ።

________________________________________________


                 ገበያውን የሚመራው መንፈስ ምንድነው የተወጋው?
                           መላኩ ብርሃኑ             መንግስት መኪና አሽከርካሪዎችን የራሳችሁ ጉዳይ ሊል ጫፍ ላይ ደርሷል። በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት መንግስት ለድጎማ በማወጣው ወጪ 10 ቢሊዮን ብር ከስሬያለሁ እያለ ነው። ይህ መረጃ በርግጥም እውነት ከሆነ ከባድ ነው። ነዳጅ አምራች ሃገራት እንኳን የኢትዮጵያን ያህል በረከሰ ዋጋ ነዳጅ እንደማያቀርቡ ሲነገር ሰምተን እናውቃለን። በዚህ መጠን ኪሳራ ማስተናገድ ከጀመርን ግን የሆነ ቦታ ቆም ማለት ይኖርብናል።
በርግጥ ከድጡ ወደማጡ እየተንደረደረ ባለው ኢኮኖሚያችን ላይ ይህ ሲደመር ኑሯችንን ከባድ ያደርገዋል። አዳዲስና ብዙሃኑን የማይጎዱ መንገዶችን አጥብቆ ማሰብ ይጠይቅ ይሆናል። መፍትሄ ማመንጨት በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎች ስራ ነው። ይህንን ካልሰሩ ታዲያ የማንን ጎፈሬ ያበጥራሉ?
እኔን የሚያሳስበኝ ግን በከፋ መልኩ ወደኛ እየመጣ ያለው ከባድ የኑሮ ጫና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያሳስብ ነገር ሆኖ አለመገኘቱ ነው። የሆነ ክፍል ቋጥኝ ቢወድቅበት እንኳን ቅም የማይለው፣ ‘ኪሱ ጢቅ ብሎ የሞላ’ አይነት ነው። ብዙሃኑ ደግሞ ኪሱ ጭራሽ ሳንቲም ለመያዝ እንኳን ጥንካሬ አጥቶ የሳሳ ሆኗል። ሃብታሙ የበለጠ ሃብታም እየሆነ ሲሄድ፣ ደሃው የበለጠ ደሃ እየሆነ ነው።
መንግስት በቅርብ ቀን የነዳጅ ዋጋን ምናልባት በሊትር ከ47 እስከ 52 ብር ሊያደርሰው ይችላል። አንድ ሊትር በአንድ ዶላር ከሆነ ነው እሱም። በጥቁር ገበያ እንዳታሰሉት። እንዲያ ከሆነ ‘ኦልሬዲ’ 70 ብር ገብቷል። የኛ ገበያ ‘ክሬዚነት’ እዚህ ላይ ፍጥጥ ብሏል። የአዲስ አበባ መንገዶች በመኪኖች እየሞሉ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ‘መንገድ ላይ የመኖር’ ያህል አሰልቺ ሆኗል። በተለይ ጠዋት እስከ 3 ተኩል፣ ከሰዓት ከ9 ሰዓት ጀምሮ እና ማታ ከ2 ሰዓት ጀምሮ መንገዶቻችን ‘በመኪና ጢቅ’ ይላሉ። ነዳጅ የሚያልቀው ጉዳይ በመሙላት ሳይሆን መንገድ ላይ በመንፏቀቅ ነው። አንዱ ብክነት እዚህ ላይ ነው።
የመኪና መብዛት ብቻ ሳይሆን ዋጋውስ ምን እየሆነ ነው?.
..በዓለም አቀፍ ደረጃ ነዳጅ ዋጋው ሲጨምር፣ በብዙ ሃገራት የመኪና ዋጋ ቀንሷል። በተቃራኒው ግን በኢትዮጵያ የመኪና ዋጋ በየቀኑ ሊባል በሚችል መልኩ እየጨመረ ነው። መንግስት መኪና ማስገባትን ላለማበረታታት ብሎ ቀረጡን ከፍ ቢያደርገውም፣ ሰዉ ግን አሁንም ነዳጅ በተወደደበት ጊዜ እንኳን ዋጋው ጣራ የወጣ፣ ነዳጅ በሊታ ባለከባድ ሞተር መኪና እንደቆሎ መሸመቱን አልተወም።
ለምን እንደሆነ ይገባችኋል ግን ? ....እኔ ግራ ገብቶኛል። ለነገሩ መንግስትም የመኪና ማቆሚያ ሰርቶ መሸቀሉን ሳይሆን አይቀርም እንደ ትልቅ ስኬት እየቆጠረ ያለው፡፡
እዚህ ሃገር ግን ስኳር ሲጠፋ የሻይ ቅጠል ዋጋ የሚወደደው ነገር...በግ ሲረክስ የቀይ ወጥ ዋጋ የሚጨምረው ነገር ምስጢሩ ምንድነው?
ገበያውን የሚመራው መንፈስ ግን ምንድነው የተወጋው?

_______________________________________________


                     የተሳሳተ
                         በእውቀቱ ስዩም

            ከምኡዝ ጋራ ከረጅም ጊዜ በሁዋላ ተገናኘን፥ ከመንገድ ዳር ካለ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን አቧራና ቡና እየጠጣን አላፊ አግዳሚውን እያየን እናወራለን፥ ድንገት አንዲት ሴት ብቅ አለችና ወደ ምኡዝ እያየች “አንተ አለህ?” ብላ ባድናቆት ጮኸች፤ ሁለት እጆቿን በሰፊው ዘርግታ እቅፍፍፍፍፍ አደረገችው፤ ቀጥላ እኔንም እቅፍ ታደርገኛለች ብዬ ተስፋ አደረግሁ፥
ከእቅፉ ወጣችና እንደገና እጅጌዋን እስከ ክርኗ ሰብስባ ባዲስ ጉልበት ተጠመጠመችበት፤ ወረፋው እስኪደርሰኝ ከኪሴ ዶዶራንት አውጥቼ ብብቴ ላይ ነፋሁ፤ አሁንም እንደገና ተቃቀፉ፤ ስራ ከምፈታ ብዬ ከግራ ብብቴ ላይ በላብና በዶዶራንት የፋፉ ሁለት የጸጉር ዘለላዎችን ነቀልሁ፤ በመጨረሻ ፈገግታዬን እንደ ደጋን ወጥሬ፥ እጄን እንደ በረኛ ዘርግቼ ተጠጋሁዋት። ልጂቱ ግን ጸጉር የከበደውን ራሷን ዘንበል አድርጋ ሰላምታ አቀረበችልኝና ሄደች! በቴስታ ብትነቀንቀኝ ራሱ እንደዚያ አያመኝም! ላለማፈር በዙርያዬ ባለው ማህበረሰብ ፊት የምንጠራራ መስዬ ለመታየት ሞከርኩ፥
“የት ነው የምንተዋወቁት?” አልኩት
“ከምታውቀው ሰው ጋራ ተምታትቸባት መሰለኝ” አለኝ፥
“እንደ ሀረግ እሬሳ የተጠመጠመችብህ ሳታውቅህ ነው?
“ምን ታረገዋለህ፥ እድለኛ ከሆንክ ለሌላው የተላከ እቅፍ ይደርስሀል፥ እድለቢስ ከሆንክ ደግሞ ለሌላው የተወረወረ ድንጋይ ይፈነክትሀል! እድል ነው”
ከጥቂት ቀናት በፊት የደረሰብኝ ነገር ትዝ አለኝ፥
የሆነ ቦታ ደወልኩ፥ የደወልኩት ስልክ አይነሳም፤
“ውድ አቤል! ከአሜሪካ የተላከልህ እቃ ስላለ መልሰህ ደውልልኝ” የሚል መልክት ጽፌ ሰደድሁ፤
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ስልኩ ተደወለልኝ::
“ቁጥር ተሳስተሀል” የሚል የሴት ድምጽ መጣ፤
ይቅርታ ጠይቄ ስልኩን ዘጋሁት፤ ጥቂት ቆይቼ ግን መልሼ ደወልኩ፤
“ሄሎ"
“ተሳስተሀል አልኩህኮ” አለቺኝ ሴቲቱ፥
“ገባኝ”
“ከገባህ ምን አስደወለህ?”
“ምናልባት ለምክንያት የሆናል የተሳሳትሁት የኔ እመቤት! ደሞ ማን ያውቃል፥ የተሳሳተ ቁጥር የተሳካ ትዳር መሰረት ሊሆን ይችላል”
“ተው ባክህ”
“ቁንጅናዬን ይንሳኝ!”
“ሆሆ። ለመሆኑ ማን ልበል?;
“በውቄ እባላለሁ”
“ለማቆላመጥ እስኪያበቃኝ ሙሉ ስምህን ብታስተዋውቀኝ”
“በእውቀቱ"
“እሺ አቶ በወቅቱ ፤ እስቲ ስለ ራስህ ንገረኝ”
“መልኬ በጠይም እና በቀይ መሀል ነው-ቀይም!”
“ቁመትህ? ስንት ሜትር ነው?”
“እሱን በሚሊሜትር ብንነጋገር ደስ ይለኛል የኔ እመቤት”
“ሄሎ፤ የስልኩ ድምጽ ይቆራረጣል ፥ የት ሆነህ ነው?”
“ቤንዚን እያስቀዳሁ ነው”
“ለመኪናህ?”
“በምን እድሌ! ለፋኖሴ ነው እንጂ”
የተራዘመ ዝምታ፥
“ስምሽ ማን ነው” አልኩዋት በመጨረሻ፥
“ጄሪ”
“ለማቆላመጥ እስከደርስ ሙሉ ስምሽን ብትነግሪኝ”
“ማን ይመስልሀል”
“ጀሪካን?”
ስልኩ ተዘጋ::
ምን አናደዳት? ባሁኑ ጊዜ በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ ከጀሪካን የተሻለ ፋይዳ ያለው ነገር እንደሌለ ባይገለጥላት ይሆናል፡፡
መልሼ ለመደወል ተሰናዳሁ፡፡

_________________________________


                          ምን እየሆነ ነው?
                               ጌታሁን ሔራሞ

            ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መባቻ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ በወጣችበት ዋዜማ ነጮቹ የአፓርታይድ ጠንሳሾች እነማንዴላ ለ27 ዓመታት ያህል የታሰሩበትን የሮበን ደሴትን ወደ መካነ እንስሳት(Zoo) በመቀየር ትውስታውን ለመደምሰስ ሙከራ አድርገው ነበር። የነጮቹን ሴራ ቀድመው በተረዱ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር የአካባቢ ዲዛይነሮችና አርክትክቶች ጥረት ግን የሮበን ደሴት ትውስታ ሳይሰደድ፣ የጥቁሮቹ  የነፃነት ትግል መዘከሪያ ሙዚየም ሊሆን በቃ። ዩኔስኮም እ.ኤ.አ. በ1999 የሮበን ደሴት “World Heritage Site for its importance to South Africa’s political history and development of a democratic society” እንደሆነች በመዝገቡ ከትቦ ለዓለም አሳወቀ።
ሰሞኑን በተለይም የኢትዮጵያ ሠዓሊያን፣ የታሪክ ምሁራንና አርክቴክቶች በሁለት በከተማችን እየተፈፀሙ ባሉ ሁኔታዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። የመጀመሪያው ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውና በ1887 ዓ.ም. ተመስርቶ በቅርስነት የተመዘገበው በተለምዶ ‹‹ሰይጣን ቤት›› ይባል የነበረው የጥበብ ቤት በአሁኑ ወቅት ለሱቅነት መሸንሸኑ ነው። ሁለተኛው ታላቁ ብሔራዊ ሙዚየም ለቢሮ አገልግሎት ሊሸነሸን እንደሆነ መነገሩ ነው። ነጮቹ “What is going on!” እንዲሉ፣ እኛም “ምን እየሆነ ነው?” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ያለፈውን የታሪክ አሻራ ደብዛውን አጥፍቶ በምትኩ የራስን አሻራ ማስቀመጥ? እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጮች የትናንት ትውስታን ገርስሶ አዲስ ትውስታን የመትከል እርምጃ? የምር አዲስ አበባ ውስጥ ለሱቅና ለቢሮ የሚሆን ቦታ ጠፍቶ ነው...እነዚህ ቅርሶች ኢላማ የሆኑት? ይህ ቅርሶቹን ከማፈራረስ የማይተናነስ ድፍረትና እብሪት የተጠናወተበት እርምጃ ነው።
በነገራችን ላይ ሙዚየሞች በሀገር ግንባታ (Nation building) ላይ ስላላቸው አይተኬ ሚና  በቅርቡ ሰፋ ያለ ፅሁፍ አስነብባችኋለሁ። ግን ግን...መንግስት ሀገሪቱ በየአቅጣጫው በሰላም መደፍረስና በኢኮኖሚ ድቀት ተወጥራ ባለችበት ወቅት ሌሎች ተጨማሪ የውጥረት አጀንዳዎችን እያመረተ ወደ ሕዝቡ የሚልከው ለምን ይሆን? የሕዝብን ንቃተ ሕሊና ዝቅ አድርጎ መገመትና ምክሩን መናቅ በሂደት ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ስለመሆኑ ከወዲሁ በደማቁ ማስመር ግድ ይላል። ሌላው ይቅርና እንዲመራው የመረጠውን ሕዝብ በማስከፋትና በማበሳጨት የብልፅግናን መንግስት የሚመስል በዓለም ላይ ይኖር ይሆን?

___________________________________________

                 የማርያም መንገድ
                      አበረ አያሌው


            አታውቁም እናንተ…
ከሷ የሚመዘዝ - የኑሮ ጠመኔ፥
ስንት ምልክቷን - እንዳስቀረ በኔ፤
እንከን የሚሸሸው - ቀና፥ ቀና ኑሮ - ከሩቁ ሲጠቅሳት፥
እኔን፥ እኔን ብላ - ስንት እራፊ ዘመን - እንዳለፈች በ’ሳት።
አታውቁም እናንተ…
ጫንቃዋ ላይ ጥዬ - መዝገብ ሙሉ ቀንበር፥
ላሸሼ ገዳሜ - ክጃት እንደነበር፤
የከዳኋት ጊዜ - የጎረቤት አሽሙር - ሳይበርዳት፥ ሳይሞቃት፥
እኔን ስትጠብቅ - ስንት’ዜ ‘ንዳለፋት - የ’ናቷ ምርቃት።
አታውቁም እናንተ…
ከትዝታዬ ጋር - ስለሷ ሳወጋ፥
እልፍ ቀን ቢጨልም - እልፍ ሌት ቢነጋ፤
ልክ እንደኼደችው - ቀርታ አት’ቀርም - ትመጣለች አኹን፤
ከዘገየች እንኳን - እያዘገመች ነው - ተዉ ሟርታችኹን።

_________________________________________________


                          "ሰለባዎች ጥሩ አስተዳዳሪዎች አይሆኑም?"
                               ኦሃድ ቤንዓሚ

            የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከብሔር ብሔረሰብ ተኮርነት ወደ ኢትዮጵያ ተኮርነት የመለወጥ ሂደት የተሻለው አማራጭ ነው፤ የኢሕአዴግ ፖለቲካ ትውልድ ይህን ለመቀበልና ከብሔር ውጭ ለማሰብ እንደሚቸገር ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ፍጹም የማይለወጥ ነገር የለም፤ እና እርስ በርሳችን ከመበላላታችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ አለብን፤ ትግራይ ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ያለቁት በዚህ እኩይ የማንነት ተኮር ፍልስፍና ምክንያት መሆኑን ለብሔረተኞች ማስረዳት ከባድ ነው፤ የባሰውኑ ደግሞ ሌሎቻችን እልቂቱ የክብደቱን ያክል ድንጋጤ ያልፈጠረብን ፖሊሲው ያመጣብንን ግርዶሽ ገልጠን ማየት በአለመቻላችን ምክንያት ወያኔንና የትግራይን ህዝብ አንድ አድርገን ማየት ስለለመድን ነው፡፡ (የፖሊሲው ችግር ነው)
ለጠባብ ብሔርተኞች፣ ችግሩ አጎራባቹ ክልል እንጂ የወያኔ ፍልስፍና አይደለም፤ ነገር ግን ዜጎች ተጎረባብተው በመቶ የሚቆጠሩ ክፍለዘመኖችን አስቆጥረዋል፤ የተባሉት ግን ይህ ፖሊሲ እግር አውጥቶ መሄድ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ መንግስትም ይህን የቤት ሥራ ቢጀምረው ጥሩ ነው፤ አራት አመት ቀላል ጊዜ አይደለም፤ እስካሁን የተጀመረ ነገር የለም፡፡
አገርን የማስተዳደርን እድል ማግኘት እንዴት መስተዳደር ትፈልግ እንደነበረ የምታስተዳድርበትና ለዚህም መሰጠትህን የምታስመሰክርበት አጋጣሚ ነው። አለበለዚያ መዳን ከሌላ መምጣቱ አይቀርም፡፡
የማንነት ተኮር ፖለቲካ ከጥቅሙ አደጋው ይከፋል የሚል እምነት ያለባቸውም የብሔረተኛነት ጽንፈኝነት አቀንቃኞች ለዘመናት የተዘራባቸውን የጥላቻ መርዝ መረዳት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው ሰለባ መሆናቸውን አያውቁትም፤ ችግር ነው፡፡
ሰለባዎች ጥሩ አስተዳዳሪዎች አይሆኑም የሚሉ አሉ፤ ይህንን የሚቃወሙም አሉ፤ ሁሉም እንደ አመለካከትህ ነው፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አካሄድ ልብ የሚያሳርፍ አይደለም፤ ወደ ሌላ ማንነት ተኮር ቀውስ ልናመራና ሌላ ከሰሜኑ የበለጠ አደጋ አንዣቦብን ሊሆን ይችላል፤ መዘውሩ ያለው በመሪው እጅ ነው፡፡
የትግራይ አይነት ቀውስ እንዲደገም የሚያደርግ አካሄድ የተለያዩ ሰበቦችንና የታሪክ ጥቅሻዎችን እየተመገበ ነው፤ ኃላፊነቱ በገዢው ኃይል መዳፍ ነው፤ በጊዜ ትክክለኛውን ማስተካከያ መውሰዱ መልካም ነው፡፡

   መግቢያ
ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከሚገኙ ጥቂት የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ሀገራት ውስጥ አንዷ መሆኗ እውን ነው። የረጅም ዘመን የስልጣኔ ባለቤት እንደመሆንዋ መጠን የረጅም ዘመን የሀገረ-መንግስትና አስተዳደራዊ ታሪክ ያላት መሆንዋንም መገንዘብ ያሻል። እንደሚታወቀው የሀገረ-መንግስት ምስረታውና የመንግስታዊ አስተዳደር መነሻው የአክሱም ዘመን በመሆኑ የአስተዳደር ወሰን የራሱ የሆነ ታሪክ ነበረው። በታሪክ አጋጣሚ ጎረቤት የሆኑት የትግራይና የሰሜን-በጌምድር የግዛት አስተዳደር የአካባቢን መልክዓ-ምድር፣ ተመሳሳይ ቋንቋና የዘር ሐረግ ያላቸውን ህዝቦች የሰፈሩበትን ቦታ መሰረት ያደረገ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎችና መረጃዎች ያሳያሉ።
የዚህ ምዕራፍ ዋና ዓላማ በረጅሙ የኢትዮጵያ የሀገረ-መንግስትና የአስተዳደር ታሪክ ውስጥ የወልቃይት፣ጠገዴና የጠለምት አካባቢዎች የግዛት አስተዳደር ምን ይመስል እንደነበር ማሳየት ነው። አፃፃፍና ትንታኔውም የታሪክ ሀቅ ላይ የተመሰረተና በመረጃ የተደገፈ ነው።
2.1 ወልቃይት፣ጠገዴና ጠለምት
የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ወስጥ በተለይ በሀገረ-መንግስት ግንባታ፣ በዳር ድንበርና ወሰን ጥበቃ ላይ የጎላ ድርሻ እንደነበረው በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ። የዚህ ምዕራፍ ዋና ዓላማ የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ህዝብ በሀገረ-መንግስት ግንባታ፣ በዳር ድንበርና ወሰን ጥበቃ የነበራቸውን ሚና ማሳየት ባይሆንም፣ ከ1983 ዓ.ም በኋላ በአካባቢው ላይ ለተነሳው የማንነት ጥያቄና ህወሓት በአማራ ተወላጆች ላይ የፈፀመውን እልቂት ለመረዳት ይጠቅማል።
2.1.1 በአክሱም ዘመነ መንግስት
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የብዙ ጉዳዮች መነሻ የአክሱም ዘመን ነው። በአክሱም የሀገረ-መንግስት የአስተዳደር ታሪክ ውስጥ የ14ኛው እና የ15ኛው ክፍለ ዘመን ነገስታት አጼ ኢዛናና አፄ ካሌብ ሰፊ ድርሻ አላቸው። በሁለቱ ነገስታት የታሪክ ሂደት ውስጥ የትግሬና የሰሜን-በጌምድር የወሰንና የግዛት አስተዳደርን በተመለከተ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ወልቃይት፣ጠገዴና ጠለምት በመልክዓ ምድርና በህዝብ አሰፋፈር የተለየ ነበር። ለማዕከላዊ መንግስት (ለአክሱም ነገስታት) ግብር የሚከፍለው የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢ የራሱ ማንነት ያለው ህዝብ ሆኖ የግዛት አስተዳደሩም ከትግሬው ግዛት በመልክዓ ምድራዊው አቀማመጥ የተለየ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚሁም በአርኪዮሎጂ ጥናት ላይ  የተመሰረተ የButzer Hunting Ford ጥሩ ምሳሌ ነው። እነኚህ አጥኚዎች  “The Rise and Fail of Axum, Ethiopia: A GeoArchaeological Interpretion” እንደሚያሳዩት፤ የማዕከላዊ መንግስታት ዋና መቀመጫ ከሆነው አክሱም የወልቃይትን የአስተዳደር ግዛት የሚለየው ተከዜ ወንዝ ነው። ይህም ጥንታዊ የኢትዮጵያ የግዛት አስተዳደር በመልክዓ-ምድርና የህዝብ አሰፋፈርን መዋቅር ያደረገ እንደነበር ያስገነዝባል።
በትግሬና በአማራ መካከል የነበረው የአስተዳደር ወሰን ተመሳሳይ ቋንቋና የዘር ሀረግን መሰረት ያደረገ የህዝብ አሰፋፈር ላይ የተዋቀረ እንደነበር መገንዘብ ያሻል። ይህ ሲባል ግን በተለያየ መልክዓ ምድር ላይ የሰፈሩ ህዝቦች አይገናኙም ማለት ግን አይደለም። አንድ ማህበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ ጦርነት፣በሽታና ሌላ የተፈጥሮ አደጋ ችግሮች ሲፈጠሩ ወደ ሌላ አካባቢ ፈልሶ የሌላ ማህበረሰብ የአስተዳደር ግዛት ውስጥ ይኖር ነበር። ይህ በጊዜ ሂደት በማህበረሰብ መካከል ትስስርን ፈጥሯል። ይህ የህዝቦች መስተጋብር ግን በትግሬና በአማራ መካከል የየአካባቢዎችን የግዛት አስተዳደር ወሰን አልቀየረውም። ስለዚህ በአክሱም ዘመን በአማራውና በትግሬ ማህበረሰብ አብሮ የመኖር መስተጋብርና ትስስር ቢኖርም፣ የሁለቱ ማህበረሰቦች የአስተዳደር ወሰን የሚለየው የተከዜ ወንዝ እንደሆነ ታሪካዊ ሂደቱ ያስረዳል።
የአክሱም መንግስት በሀገር ውስጥ በተፈጠረው ሽኩቻ እየተዳከመ ሄዶ በመጨረሻ አረቦች ቀይ ባህርን ሲቆጣጠሩ የፍፃሜው ውደቀት ላይ ደረሰ። የአክሱም ዘመን በ8ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ገደማ ሲያከትም ስርወ -መንግስቱ ወደ ላስታ ሮሃ በ1150 አካባቢ ተዛወረ። በላስታ ሮሃ ውስጥም የዛግዌ ስርወ -መንግስት ተመሰረተ። በዚሁ ስርወ መንግስት ዘመንም የወልቃይት፣ጠገዴና ጠለምት የግዛት የአስተዳደር ወሰን መለያ ተከዜ ወንዝ እንደነበር የታሪክ መረጃዎችና ጥናቶች ያሳያሉ። ለምሳሌ ተሰማ ሀብተ ሚካኤል በ1951 ባሳተሙት የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ እንዲህ ይላል፡- ከአክሱም መንግስት ውድቀት በኋላ ስርወ መንግስት ወደ ላስታ ሮሃ በተዛወረበት ጊዜ ከተከዜ ወንዝ ማዶ የሰሜን ግዛት አስተዳደር ክፍል ነው። በቦታው የሰፈሩትም አማሮች ናቸው ይላል። በተጨማሪም በበርካታ መረጃዎች የተደገፈው የህዝባዊ ታሪክ  ፀሀፊው አቻሜለህ ታምሩ “የወልቃት ጉዳይ” በተሰኘ መፅሐፉ የንጉስ ነአኩቶ ለአብ ገድለ-ታሪክን (Hagiography) ዋቢ አድርጎ እንዳቀረበው፤ የአይሁድ እምነት ተከታይ የሆኑት ፈላሻዎች ለንጉሱ ግብር አንገብርም በማለት በተደጋጋሚ እንደ አመፁ ያስረዳል። ስለዚህ ንጉሱ ግብር ለመሰብሰብ ዘመቻ በሚያደርግበት ጊዜ የአማራውንና የትግሬውን አሰፋፈርና የአስተዳደር ወሰን የሚለየው የተከዜ ወንዝ እንደሆነ ተጠቅሷል።
2.1.2 በዛግዌና በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ
ኢትዮጵያ ረጅም የሀገረ-መንግስት ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም፣ የስርዓት ለውጥ ግን ሁሌም በአመፅ የተደገፈ ነበር። ታሪካችን እንደሚያስረዳው፤ የስልጣን ሽኩቻና ግጭት እንደ አሁኑ ዘመን ብሔርን መሰረት ያደረገ አልነበረም። የስልጣን ሽኩቻ (Power Struggle) በዛግዌ ዘመንም ሆነ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በጎንደርና በዘመነ መሳፍንት በንጉሳዊያን ቤተሰቦች መካከል ሳይቀር እንደነበር የሚካድ አይደለም። ነገር ግን የስልጣን ሽኩቻ ብሔርንና ቋንቋን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ የአስተዳደር ወሰኑ ላይ ለውጥ የለም።
የዛግዌ ዘመን በ1270 ላይ ሲያከትም ስርወ-መንግስቱ (በትረ መንግስቱ)ወደ ሰለሞናውያን እጅ ገባ። የሰለሞናውያን ስርወ-መንግስቱ በ1270 ዳግም ካንሰራራ በኋላ ስማቸው እጅግ በጣም ጎልተው ከሚታወቁት ነገስታት መካከል አምደ ፅዮን አንዱ ናቸው። አፄ አምደ ፅዮን ከሚታወቁበት ባህሪ ውስጥ አንዱ ጠንካራ የግዛት አስተዳደር ነው። ንጉሱ የግዛት ማስፋፋት በሚያደርጉበት ጊዜ የበጌምድርና የሰሜን የትግሬው የግዛት አስተዳደር ወሰን አልቀየሩትም። በቅርቡ ከግዕዝ ወደ አማርኛ በተተረጎመው የአፄ አምደ ፅዮን “ዜና መዋዕል” ላይ የወልቃይት፣ ጠገዴና የጠለምት የአስተዳደር ወሰን (ግዛት) ከእሳቸው በፊት ይገዙ የነበሩትን ነገስታት ይመስል እንደነበር ያስረዳል። ዜና መዋዕሉ የንጉሰ ነገስቱን  ግዛቶች በተከዜ፣ በበሽሎ፣ በአዋሽና፣ በአባይ ወንዞች የተከለሉ መሆኑን ያስገነዝባል። የትግሬና የአማራውን የአስተዳደር ወሰን የሚለየውም የተከዜ ወንዝ እንደሆነ በግልፅ ያስቀምጣል።
የኢትዮጵያን የውስጥ አስተዳደር የግዛት ወሰን በተመለከተ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችና የሀይማኖት ሰባክያን የተመለከቱትንና የተገነዘቡትን ከትበው አልፈዋል። ከነገስታት በተሰጣቸው የስጦታ  መፅሐፍ ውስጥ (ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገር በውጭ ሀገር ጎብኝዎችና በሀይማኖት ሰባክያን በተወሰደው) የአስተዳደር ወሰንን ታሪክ እናገኘዋለን። ለዚሁ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የትግሬው ገዥ ራስ ልስሁል ሚካኤል፣ ለጀምስ ብሩክ ያበረከቱት “መፅሐፈ አክሱም” የተሰኘው ታሪካዊ ሰነድ ነው። ይህ መፅሐፍ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምትና ሁመራ በትግሬው ግዛት ውስጥ ያልነበሩ መሆኑን ያስገነዝባል።
በ15ኛው እና በ16ኛው ክፍለ ዘመን እነዚህ የትግሬው የግዛት አስተዳደር ክፍል እንዳልነበሩ ያስገነዝባል። በየትኛውም የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የትግሬ ግዛት እንደነበሩ የሚያሳይ መረጃ የለም። ከእሳቸው በፊት እንደነበሩት ነገስታት ሁሉ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመንም እነዚህ አካባቢዎች የሰሜን በጌምድር የአስተዳደር ግዛት ክፍል ነበሩ። በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በአክሱም ንቡረ-ዕድ የተፃፈው “መፅሐፈ አክሱም” የተሰኘው (በጀምስ ብሩስና በፈረንሳይ አርኖል ዲአባዲ አማካኝነት ወደ አውሮፓ በተወሰደው ዶክመንት እንደሚገለፀው፤ ወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት የትግሬው የአስተዳደር ክፍል አልነበሩም።
በተመሳሳይ መልኩ ዮሐንስ መኮነን “Ethiopia The Land and Its People, History and Culture”   እና John R.S “The World Through Maps: A History of Cartography” ላይ ከተዘረዘሩት የትግራይ የግዛት አስተዳደር ውስጥ ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የሉም። እነዚህ ሁለቱ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት፤ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የትግሬ ግዛቶች ተምቤን፣ ሽሬ፣ ስራየ፣ሀማሴን፣ ቡር፣ ሳማ፣ አጋሜ፣ አምባ ሰናይት፣ ገርአልታ፣ እንደርታና ሰሐራት ናቸው።
ፍራንሲስኮ አልባሬዝ የተባለ ፖርቱጋላዊ የካቶሊክ እምነት ተከታይ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በኤርትራ ትግሬና በጌምድር ለ7 ዓመት ከ1520-1527 እንደቆየ ይታወቃል። አልባሬዝ የመጣበት ዋናው ተልኮ የካቶሊክ እምነትን በድብቅ ለመስበክ ቢሆንም፣ የአካባቢውን መልክዓ ምድር ሁኔታ፣ የግዛት አስተዳደርና የህዝብ አሰፋፈርን በማስታወሻው ከትቧል። በጊዜው የነበረውን የግዛት አስተዳደር ሲገልፅ፤ በጌምድር በኢትዮጵያ ከሚገኙት የአስተዳደር ግዛቶች ውስጥ በጣም ትልቁ ነው ይላል። የበጌምድር ግዛት በኤርትራና በጎጃም መካከል ይገኛል በማለት ገልፆታል። በሌላ አገላለፅ የበጌምድር ግዛት ከጎጃም ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን እስከ ባህር ነጋሽ (ኤርትራ) ድረስ 3.2 ማይል ርቀት ይዘልቃል ሲል አስቀምጦታል። ይህም የሚያሳየው የተከዜን ወንዝ ተከትሎ ወደ ምዕራቡ አቅጣጫ የወንዙ ተፈጥሮአዊ ተፋሰስ የኤርትራ ግዛት የሆነውን “አም ሀጀር” የሚያዋስን መሆኑን ነው።--
("የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የታፈኑ እውነታዎች" ከተሰኘው መጽሐፍ የተቀነጨበ፤ታህሳስ 2014 ዓ.ም)   “ከእያንዳንዱ ኦቲዝም ካለበት ልጅ ስኬት ጀርባ፣ ከሥራና ከህይወት ወደኋላ የቀሩ ወላጆች አሉ”


           ወይዘሮ መዓዛ መንክር ይባላሉ፡፡ የአዕምሮ ህክምና ባለሙያና አማካሪ ሲሆኑ የሻምፒዮንስ አካዳሚ ት/ቤት መስራችና ሥራ አስኪያጅም ናቸው፡፡ ት/ቤቱ በተለይ ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸውንና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ተቀብሎ በማስተማር ይታወቃል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ወላጆች በእጅጉ የሚያግዝ “ሁሉም በአንድ” የተሰኘ ተግባር ተኮር መፅሐፍ አዘጋጅተው ለንባብ ያበቁ ሲሆን፤ በኦቲዝም ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በኩል በርካታ ጥረቶችንና እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡ የኦቲዝም ወር ተብሎ በተሰየመው በመጋቢት ወርም በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን ያካሄዱ ሲሆን በተለይ በኦቲዝም  ለተጠቁ ልጆች ወላጆች ባሰናዱት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በጉዳዩ ዙሪያ ወይዘሮ መዓዛ መንክርን እንደሚከተለው አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-Psych ጤና - አዲስ መጽሐፍ #ሁሉም በአንድ#... | Facebook


             በአዲስ አበባ ያሉ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ለትርፍ የተቋቋሙና መደበኛ የሚባሉ ልጆችን ብቻ ተቀብለው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ የእናንተም ሻምፒዮንስ አካዳሚ ኢንቨንስትመንት እንጂ በጎ አድራጎት አይደለም፡፡ ነገር ግን ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆችም ተቀብላችሁ ታስተምራላችሁ፡፡ እንዴት ለማስተማር ፈቃደኛ ሆናችሁ?
በእውነቱ ይሄ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ምን መሰለሽ በሀገራችን እንደ አጠቃላይ በተለይ የግል ት/ቤቶች ሲከፈቱ እንዳልሽው ቢዝነስ ሆነው ነው የሚቋቋሙት፡፡ ኢንቨስትመንት ናቸው፡፡ ያ ኢንቨስትመንት ደግሞ ውድድር አለው፡፡ ምን ዓይነት ውድድር ካልሽኝ፣  “እኔ ት/ቤት 8ኛ ክፍል ካስፈተንኳቸው 20ዎቹ  መቶ ደፍነዋል”፣ “እኔ 12ኛ ክፍል አስፈትኜ 30 ተማሪዎች ስትሬት A አምጥተዋል” እያሉ ደህና ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን እንደ መፎካከሪያነትና ት/ቤቱ እውቅና እንዲያገኝ እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል፡፡ ይህንንም በየትምህርት ቤቱ በር ላይ ተለጥፎ በግልፅ እናየዋለን፡፡ እንዲህ አይነቱ አመለካከት ወላጆች ት/ቤት ሲመርጡም ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል፡፡ በብዛት ጥሩ ውጤት ያመጡ ልጆች ያሉበት ት/ቤት ማስተማር እንዲፈልጉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ትክክልም ነው፡፡ ወላጅ ለልጁ ያስባልና፡፡ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች አካታች የትምህርት ተቋማት ይፈልጋሉ
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ፣ በራሳቸው ፍጥነት የሚጓዙና ከማንም ጋር የማይፎካከሩ፣ ምናልባት የሌሎችንም ድጋፍ የሚሹ ልጆችን አስተምራለሁ ብለሽ ስትነሺ፣ በጣም ከባድና ብዙ ዋጋ ያስከፍልሻል፡፡ ለምሳሌ የእኛን ብትጠይቂኝ፣ ብዙ ጊዜ ከወላጆች “ብር እየከፈልን እንዴት ከእንደነዚህ አይነት ልጆች ጋር ልጆቻችንን ቀላቅላችሁ ታስተምራላችሁ” በሚል በጣም ከባድ  ቁጣና ወቀሳ ይሰነዘርብናል፡፡ አንዳንዱ ወላጅ ደግሞ “አንድ ቀን ት/ቤት ስገባ አንድ ልጅ አንገቱን ሲያወዛውዝ አይቻለሁ ወይም እጁን እንዲህ ሲያደርግ አይቻለሁ፤ ስለዚህ ልጄ  ከዚህ ልጅ ጋር እንዳይቀመጥ አደራ!; ይላሉ፡፡ “የኔ ልጅ ይሄ ልጅ የሚማርበት ክፍል ውስጥ  ነው የሚማረው አይደለም!?” ብለው  አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጃቸው በጣም ጎበዝና ተፎካካሪ ከሚባለው ጋር እንዲማር እንጂ ልዩ ድጋፍ ከሚፈልግ ልጅ ጋር እንዲማር አይፈልጉም፤ እናም ፈተናው ቀላል አይደለም፡፡  እኛ ለረዥም ዓመት  ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ተቀብለን ስናስተምር፣ ልጆቻቸውን ከዚህ አስወጥተው ሌላ ት/ቤት የሚያስገቡ ገጥመውናል፡፡ ለምን ስንል “አይ ሻምፒዮን አካዳሚ እኮ በሽተኛ ልጆች ተቀብሎ ያስተምራል ብሎ ጎረቤቴ ነግሮኛል” ይሉናል። አንዳንዱ ደግሞ ይመጣና፤ “ይሄ በሽታ ይተላለፋል ወይ?” ብሎ የሚጠይቅሽም አለ፣ ብቻ ብዙ ዓይነት ጥያቄዎች ወላጆች ውስጥ ይፈጠራል፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ ስለማይሰራና ግንዛቤው ስለሌለ ነው፡፡
እኛ ይህን ችግር ለመፍታት ዛሬ እዚህ ተገኝታችሁ እንዳያችሁት ወላጆችን በማገናኘት ልምድ እንዲለዋወጡ ግንዛቤ እንዲያገኙ፣ ስለችግሩ ይበልጥ እንዲያውቁ ተደጋጋሚ መድረኮችን እያዘጋጀን  የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ እያደረግን ነው፡፡ ኦቲስቲክ ሆነው በዓለማችን ላይ ትልልቅ ስኬቶችን ያመጡ ሰዎችን ታሪክ በመንገር፣ ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ ከተደረገላቸው ልጆቻቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ እናስተምራቸዋለን፡፡ በፊልሙ በቢዝነሱ በፈጠራ ስራ ብቻ በበርካታ ዘርፎች ትልልቅ ስኬት ያስመዘገቡ ዓለም አቀፍ ሰዎች አሉ፡፡ እዚህ እኛም ት/ቤት ውስጥ በስዕል፣ በግጥም፣ በቋንቋ፣ በሳይንስና በአጠቃላይ ትምህርቱም ውጤታማና ተሸላሚ የሆኑ ልጆች አሉን፡፡ ለምሳሌ የUKG ተማሪ ሆኖ በአፍሪካ ካርታ ላይ ያሉትን ሀገራት ቦታውን ስታሳይው የሚነግርሽ ኦቲስቲክ ልጅ አለ፡፡ መደበኛ ሆኖ ግን አይደለም የአፍሪካን፣ የኢትዮጵያን የማያውቅ  ሊኖር ይችላል፡፡ እናም እነዚህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች እድል ከተሰጣቸው የበለጠ ክህሎት እንዳላቸው ስናሳይ፣ ወላጆች ግንዛቤ እያገኙ፣ ችግሩም እንደማይተላለፍ እያወቁ የእኛንም ጥረት እያደነቁ መጡ፡፡ ለምሳሌ አንድ መደበኛ ልጅ እድሜው ሲፈቅድ መናገር መጀመሩ ኖርማል ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ ስንት ተደክሞና ተለፍቶ ነው የሚናገረው ብለው ይገረማሉ፡፡
ለምሳሌ አንድ የገጠመኝ ምን መሰለሽ፣ አንድ ተማሪያችን ለእረፍት ከከተማ ውጪ ይሄዳል፡፡ እዛ ያረፉበት ሆቴል ውስጥ ሲዋኙ አንዱ ከውጭ የመጣ ኦቲስቲክ ልጅ አለ። ያ ልጅ ውሃ ውስጥ እንዳይደፍቃቸው ወላጆች ልጆቻቸውን በአይን ጥቅሻ ያስጠነቅቁ  ስለነበር፣ ሁሉም እየወጡና እየሸሹ መዋኛው ባዶ ሆነ፡፡ በዚህን ጊዜ ያ የእኛ ተማሪ ወደ ክፍሉ ሄዶ ኳስ አምጥቶ ያንን ልጅ ማጫወት ጀመረ፡፡ በዚህን ጊዜ የልጁ አባት ተደንቆ፤ “እንዴት ሌሎቹ እየሸሹ ሲሄዱ አንተ ልታጫውተው ፈለግህ?” ሲለው፤ “እሱ እኮ እብድ አይደለም! እኛ ት/ቤት እንደእሱ አይነት ልጆች ይማራሉ። እነሱም የሚፈልጉት የሚረዳቸውና የሚቀርባቸው ጓደኛ ነው” አለው፡፡ ይህን የሚለው የ7 ዓመት ሕጻን ልጅ ነው። ከዚህ በኋላ  አባትየው “እባካችሁ ይህ አስተዋይ ልጅ  የሚማርበትን ት/ቤት አድራሻ ስጡኝ; ብሎ ተቀብሎ ደውሎልኝ፤ “ትውልድ እየተቀየረ ነው፤ ትልቅ ስራ እየሰራችሁ ነው; ብሎ አመሰገነኝ። ይህ እንግዲህ አብሮ ከመዋል ባህሪያቸውን ከመረዳትና ጉዳት እንደማያደርሱ ከማወቅ የሚመጣ ነው። ችግሩ በድጋፍ፣ በክትትልና በተጨማሪ ስልጠና የሚለወጥ እንደሆነ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለውጥ በተግባር በልጆቹ ላይ እያመጣን አስተሳሰብ እየቀየርን ነው፡፡ ወላጆችም “እንኳንም ዕድል ሰጣችሁን” እያሉ  የሚያመሰግኑም ብዙ ናቸው፡፡ እኛም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥረት እየጨመርን፣ እየለፋንና እየታገልን ሌሎች ወላጆችን ለማስደሰትና ለገንዘብ ብለን ከአላማችን ዞር አንልም በማለት በመፅናታችን ሰዎችን ወደምንፈልገው መስመር እያመጣን እንገኛለን፡፡
ሻምፒዮንስ አካዳሚ መቼ ነው የተቋቋመው? ምን ያህል መደበኛ፣ ምን ያህል ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ያስተምራል?
የእኛ የአካትቶ ትግበራ ከተጀመረ 15 ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ፣ የት/ቤታችን ትልቁ ተግዳሮት ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ያስተምራል መባሉ ነው፤ ይሄ ወላጆችን ያስፈራቸዋል፡፡ ቀደም ብለው ደፍረው የገቡት ስለልጆቹ ሲያዩ ልጆቻቸው ስለነዚህ ልጆች ሲነግሯቸው፣ “እከሌ እኮ የክፍሉን ተማሪ ስም ከነአያታቸው ይሸመድዳል; ሲሏቸው "አሃ ለካ ልዩ ተሰጥኦና ኳሊቲ አላቸው" እያሉ ነው መቀበል የጀመሩት፡፡ ከውጭ ሲሆኑ ግን ደፍረው ወደ እኛ መምጣት ይቸገራሉ። ብቻ ያም ሆኖ ት/ቤታችን “ሻምፒዮንስ” በሚለው ስም ከተከፈተ 6 ዓመቱ ነው፡፡ 500 ተማሪዎች አሉን፡፡ ከእነዚህ መካከል 80ዎቹ ልዩ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው ናቸው። ልዩ ድጋፍ ከሚፈልጉት 30ዎቹ ይሄ ነው ብለሽ ከመደበኛዎቹ በማትለይው ደረጃ ውጤታማ ሆነው ከእኩዮቻቸው ጋር የሚማሩ ናቸው፡፡ ይህ ለውጥ የመጣው ባደረግንላቸው ክትትልና ድጋፍ ነው፡፡ ቀደም ሲል በዚህ የወላጆች የግንዛቤ መድረክ ላይ ሪፖርት ስናቀርብ እንደሠማችሁት፤ ከዚህ ከእኛ ወረዳ ተወዳድሮ በስዕል አንደኛ ወጥቶ ልዩ ተሸላሚ የሆነው፣ የልዩ ፍላጎት ተማሪያችን ነው፡፡ አሁንም እናቱ ልምድ ስታካፍል ነበር፡፡ ይህ ተማሪ አሁን ላይ የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ ዋጋ ብንከፍልና ብንደክምም፣ ከ80ዎቹ ውስጥ 30ዎቹን አብቅተናል፡፡ 50ዎቹ ደግሞ የሙሉ ቀን ቴራፒ የሚወስዱና በከፊልም ቴራፒ እየወሰዱ የቀጠሉ ናቸው፡፡
በሀገራችን የአካትቶ ትምህርት በህግ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ትኩረት ከማጣቱ የተነሳ የሚፈለገውን ያህል መፍትሄ እንዳላመጣና በዘርፉም የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር አናሳ በመሆኑ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ይነገራል፡፡ እርስዎ እንደ ባለሙያም ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተልም ምን ይላሉ?
በሀገራችን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ከዲፕሎማ እስከ 3ኛ ዲግሪ (PHD) ድረስ ይሰጣል፡፡ ችግሩ ምንድን ነው ካልሽኝ፣ ትምህርቱ ተግባር ተኮር አይደለም፡፡ እዛው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተምረው ተመርቀው  ወደ ሌላ ስራ ይሄዳሉ እንጂ ወርደው ድጋፉን ከሚፈልጉት ልጆች ጋር፣ ወላጅ ካለበት ጫና ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ተግዳሮቱን በተግባር የሚጋፈጥ ባለሙያ የለም፡፡ አንድ የዘርፉ ተመራቂ አንድ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ወይም ኦቲስቲክ የሆነ ልጅ ይዞ አሰልጥኖ አስተምሮ፣ ለውጥ እስኪያመጣ ድጋፍ አድርጎ አይደለም የሚመረቀው። እዛው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ንድፈ ሃሳቡን ይማራል ይመረቃል፤ አለቀ፡፡ በዚህ ምክንያት በዘርፉ የሰለጠነ፣ በተግባር የተፈተነ ባለሙያ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔም እራሴ በውጭ ሀገር የንግግር ቴራፒ፣ኦኪፔሽናል ቴራፒ (እጅና እግርን አቀናጅቶ የመጠቀም ቴራፒ)፣ባህሪ ማረቅ (ብሔቪየራል ቴራፒ) የሚባሉትን ትምህርቶች በመውሰድ፣ የትምህርት ዝግጅቴም (የስነ ልቦና እና የአዕምሮ ህክምና) ስለሆነ ነው የማሰለጥነው፡፡ ለምሳሌ ወደ 200 የሚጠጉ ቤት ለቤት የሚሰሩ፣የተለያዩ ት/ቤቶች የተቀጠሩና በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ እኛ ጋር እየመጡ ነው ስልጠና የሚወስዱት እንጂ አገሪቷ ላይ በተግባር የተደገፈ የሚሰራ ነገር  አይታይም፡፡ ነገር ግን ጠቅለል ብሎ የልዩ ፍላጎት ትምህርት እስከ 3ኛ ዲግሪ አለ። አንድ በልዩ ፍላጎት ፒኤችዲ ያለው ምሩቅ፣ እንዴት ነው አንድ  ኦቲዝም ያለበት ልጅ መናገር የሚችለው? የሚለውን በተግባር ያውቃል ብለን አናምንም::
እርስዎ ከላይ የጠቀሷቸውን ተግባር ተኮር ስራዎች ካላከናወነበት በዘርፉ ፒኤችዲ ይዞ ምንድን ነው የሚሰራበት?
እሱ ነው ዋናው አንገብጋቢው ጥያቄ፡፡ አብዛኛዎቹ ወደ ጥናት ነው የሚያዘነብሉት፤ ተመራማሪዎች (ሪሰርቸሮች) ናቸው። እኛ አሁን ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ እናወጣለን። በሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ  እንዲሁም በልዩ ፍላጎት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ስንቀጥር፤ “እኔ ዲግሪ ይዤ አንድን በሽተኛ ልጅ አጨብጭብ፣ቁጭ በል፣እየኝ ስል ልውል ነው እንዴ” ብለው ትተው ነው የሚሄዱት። ከዚያ በኋላ የህፃናት መብት፣ ቀይ መስቀል  እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ነው የምታገኚያቸው። ከአንድ ኦቲስቲክ ልጅ ጋር ተግባር ተኮር የሆነ ስራ መስራት፣ ራስን ዝቅ ማድረግ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። “እንዴት ነው እጅ መታጠብ፣ መጸዳዳት፣ መናገር የማስተምረው?” ብለው ስራውን ለቀው ይሄዳሉ፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው።  አንድ ልጅን ረድቶና አግዞ መቀየር፣ የዛን ልጅ ቤተሰብ መቀየር ማለት ነው፡፡ እዚህ 100 ሰው ቢኖር  500 ሰው መርዳት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ይህንን እገዛና ለውጥ ሳይሆን የሚያስቡት እዚህ ጋ ያለውን ልፋትና ትግል ነው፤ እና ለምን ብዬ እንገላታለሁ ይላሉ፡፡ እዚህ አገር ትልቅ ተደርጎ የሚወሰደው የቢሮ ስራ ነው።
ለምሳሌ ቀላል ምሳሌ ልንገርሽ፡፡ እኛ ለግንዛቤ ሥራ አብዛኛውን ህዝብ የምናገኘው በእናንተ በሚዲያዎች በኩል ነው፡፡ ስለዚህ  እንዲህ አይነት መርሃ ግብሮች ስናዘጋጅ ብዙ ሚዲያ መጥቶ እንዲዘግበው፣ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝና ግንዛቤ እንዲስፋፋ እንፈልጋለን፡፡ ከጠራነው በርካታ ሚዲያ ውስጥ ጉዳዬ ብላችሁ የመጣችሁት ከአንድ እጅ ጣት አትበልጡም፡፡ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው በብዙ መልኩ ለችግሩ ትኩረትና ቅድሚያ አለመሰጠቱን ነው። እኔ በልዩ  ፍላጎት ላይ ማስተርሴን ስሰራ የጥናት ፅሁፍ  የሰራሁት የሚዲያ ሽፋን ላይ ነበር። ብሔራዊ ሚዲያው ስለ ልዩ ፍላጎት ምን ያህል ዘግቧል የሚል ነበር ጥናቴ፡፡ በወቅቱ ኢቲቪና ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምን ያህል ትኩረት ሰጥተውታል የሚለውን ለማየት የአንድ ዓመት ሂደታቸውን ስፈትሽ፣ በጣም በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ 0.06 ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ይህም ቢሆን ዓመታዊ የዳውን ሲንድረም ቀን ሲከበር መግለጫ የተሰጠበት፣ ከአይነስውርነት ጋር የተያያዙ መግለጫዎች እንጂ ጉዳዩን ጉዳይ አድርጎ በስፋትና በጥልቀት የሰራ፣ የስኬት ታሪክ የፃፈ፣ እድል ካገኙ መስራት ይችላሉ የሚል አመላካች ነገር የዘገበ አንድም አላገኘሁም። ስፖርት፣ ፋሽን፣ ሙዚቃና ቢዝነስን ስንመለከት ደግሞ ምን ያህል ከሚፈለገው በላይ ሽፋን እንዳለው እንታዘባለን፡፡ የልዩ ፍላጎት ጉዳይ የሚናቅ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም አሁን የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ያለ ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡
የኦቲዝም ወይም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቁሙ የቅርብ ጥናቶች ይኖራሉ?
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ከሚወለዱት 44 ልጆች አንዱ ኦቲዝም አለበት፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ስታቲስቲክ ስንወስደው ትልቅና የሚያስደነግጥ ቁጥር ነው፡፡ ከ44 ልጆች አንዱ ኦቲስቲክ ነው ማለት እዚህ ሰፈር ውስጥ ብዙ ልጆች አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ እየተስፋፋ  በመሆኑ  ሚዲያውም ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት። ዛሬም እዚህ ቦታ በመምጣታችሁ ትልቅ አክብሮት አለኝ፤ የእውነቴን ነው የምላችሁ፡፡
እናንተ የሥራችሁን ውጤታማነት የምትለኩበት አንዱ ጉዳይ የወላጆች እፎይታ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት ሰው በጦርነትና ግጭት፣ በኑሮ ውድነትና በሌሎች በርካታ ችግሮች የተወጣጠረበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ወላጆች ኦቲስቲክ ልጆች ሲኖራቸው፣ በተለይ እናት ስራ ትታ ሙሉ ስራዋ ልጇ ይሆናል። ባለፈው በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደ የዳውን ሲንድረም ቀን ላይ ያየሁት አንድ መሪ ቃል ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ  ትንሽ ቢያወጉኝ…?
በጣም ትክክል ነሽ! ያ መሪ ቃል ከኔ መፅሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ “ከእያንዳንዱ ኦቲዝም ካለበት ልጅ ስኬት ጀርባ ከሥራና ከህይወት ወደኋላ የቀሩ ወላጆች አሉ” ይላል፡፡ እውነት ነው። ልዩ ድጋፍ የሚሹ ልጆች  በራሱ ያለባቸው እክል አለ። መሻሻል ያለበት ሊሰራ የሚገባው ማለቴ ነው። በተለይ ልጆቹ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ። አንድ ሰው አግብቼ ልጅ እወልዳለሁ ብሎ ሲያቅድ ምንም ይፈጠራል ብሎ አያስብም። እወልዳለሁ፣ አሳድጋለሁ፣ ጥሩ ት/ቤት አስተምረዋለሁ፣ ጥሩ እንዲመገብ አደርጋለሁ ብቻ  ነው የሚለው፡፡ እነዚህ ወላጆች ግን ፍፁም ከአዕምሮና እቅዳቸው ውጪ የሆነ ነገር ነው የሚገጥማቸው። ይሄ ችግር ሲከሰት ዘርፈ ብዙ ቀውስ አለ፡፡ በተለይ ወላጆች ራሳቸው ችግሩን እስኪቀበሉት ድረስ ከባድ ነው። "ለምን ለኔ ይሄ አይነት ልጅ ተሰጠኝ" በሚል ከፈጣሪና ከሁኔታዎች  ጋር ይሟገታሉ። ከዚህ ሙግት በረጅም ሂደት ከወጡ በኋላ ደግሞ እሺ መፍትሔውስ ምንድን ነው? እንደዚህ አይነት ልጅ አምኜ ለሰራተኛ ሰጥቼ፣ ለዘመድ ትቼ እንዴት ነው ስራ የምሰራው? ለተለያየ ጥቃት ይጋለጥብኛል በሚል ስራቸውን እርግፍ አድርገው ትተው፣ ሙሉ ስራቸው ልጃቸው ይሆናል። ከዛ ደግሞ ልጁን ማብቃት አለባቸው። ልጃቸውን ይዘው ወደ ውጪ ሲወጡ ማህበረሰቡ “እከሌ’ኮ ልጇ በሽተኛ ነው” እያለ ያሸማቅቃቸዋል። ይሄ ሁሉ ጫና ነው ያለው፡፡ አንድ እናት ሁለት የማይናገሩ ልጆች አሏት- ኦቲስቲኮች ናቸው፡፡ በጣም ራሳቸውን የሚጎዱ ናቸው። የእነዚህ ልጆች ወላጆች የገንዘብ አቅም ያላቸው ናቸው። ልጆቹ ከቤት አይወጡም። አንድ ቀን ሞግዚታቸው ከቤት ይዛቸው ወጣችና ጎረቤቶች “ሀይ ቤቢ ሀይ ሚጣ” ሲሏቸው ህፃናቱ መልስ አልሰጡምና “እነዚህ ልጆች ዲዳ ናቸው እንዴ?” ብለው ሲጠይቁ፣ ሞግዚታቸው “አዎ አይናገሩምኮ” አለች። ከዚያ በኋላ እናትየዋ ስትነግረኝ፤ "ልጆቼን ይዤ ከቤት ስወጣ ሰው ሙሽራ እንደሚያጀብ “ዲዳ ልጆች ናቸው” እያለ ለማየት ይወጣ ነበር ብላ እያለቀሰች ነው የነገረችኝ፡፡ ከማህበረሰቡ፣ ከፋይናንሱ፣ ከቤት አከራይ በርካታ ጫና ነው ያለው፡፡ ይህ ሁሉ ጫና ተደራርቦባቸው እኛ ጋ ሲመጡ፣ መጀመሪያ ወላጆችን እናበቃቸዋለን። "እጃችሁ ላይ መፍትሔ አለ፤ ኦቲስቲክ ልጆች የሚፈልጉት ትምህርታዊ ሥልጠና ነው” እንላቸዋለን። "ያልተቋረጠ ስልጠና ያለመታከት ከሰጣችኋቸው መፍትሔው እጃችሁ ላይ ነው” እንላለን፡፡ ይህን ሲሰሙ ጨልሞባቸው የነበረው ነገር ከላያቸው ላይ ይገፈፋል፡፡
ሁለተኛው ነገር፤ ልጆቻቸው አቅማቸው እንዲጎለብትና እንዲለወጡ ስልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሁለቱን እያቀናጀን ስንሄድ ለውጥ ይመጣል፡፡ ቅድም ሰምታችኋል “እከሌ እኮ እጁን እያውለበለበ ቻው አለ” ብለን ሰለብሬት እናደርጋለን፡፡ ለመደበኛው ሰው እጅ ማውለብለብ ከቁም ነገር የምንቆጥረው ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ኦቲስቲክ ልጅ አንድ ቃል ሲያወጣ እልል ይባላል፡፡ አዲስ እንደተወለደ ነው የምንቆጥረው፡፡ ሌላው ነገር ልጃቸው ከዚህ በፊት ትኩረት አይሰጣቸውም፤ እናቱ ትሁን፣ ግንኙነት ይኑራት የማያውቀው ልጅ ከት/ቤት ልትወስደው ስትመጣ፣ ከሰው መሃል ለይቶ ሄዶ ሲያቅፋት በደስታ ይሰክራሉ፡፡ ትምህርት ቤታችሁ “Healing School” ነው ይሉናል፡፡ በዚህ በጣም ደስ ይለናል፡፡ ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ የጠራናቸው እነዚህ ሁሉ ወላጆች ልጆቻቸው ኦቲስቲክ የሆኑ ናቸው፤ ሌሎች ወላጆች አልጠራንም። ዛሬ እነዚህ ወላጆች የሚመካከሩበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ስለ ልጆቻቸው ለውጥ ምስክር የሚሰጡበትና የበለጠ ግንዛቤ የሚያገኙበት ነው፡፡ በፊት እንደዚህ አይመጡም ነበር፤ ይፈሩና ይደበቁ ነበር፡፡ አሁን ግን ልጆቻቸው ዋጋ እንዳላቸው ሲያዩ፣ ያንን መደበቅና መፍራት አስወግደው በልበ ሙሉነት ለልጆቻቸው የበለጠ ለውጥ ይሳተፋሉ፤ ይመካከራሉ። የዚህ ሁሉ ወላጅ ለውጥ የእኛ የብዙ ጊዜ ልፋት ውጤት ነው፡፡ የዛሬ ስምንትና ዘጠኝ ዓመት ወላጅ እንደዚህ አይመጣም ነበር፡፡ ቢመጡም እንኳን ተሸፋፍነው ወይም ኮፍያ አድርገው አሊያም መኪና ውስጥ ሆነው ሰራተኛ ነበር የሚልኩት። አሁን እሱን አስቀርተናል፡፡ ውጤታችንን እንዲህ ነው የምንለካው፡፡ ለምሳሌ እኔ “ድንቅ ምክር” የተሰኘ የፌስቡክ ገፅ አለኝ፡፡ እዛ ላይ ብዙ ትምህርት እንሰጣለን፤ ኦቲስቲክ ሆኖ 7ኛ ክፍል የደረሰልንን ልጅ ስኬት ያካፈልንበት ታሪክ ይገኛል፡፡
ከመንግስት የሚደረግላችሁ ድጋፍ አለ ወይስ እንደሌላው ኢንቨስትመንት ብቻ ነው የምትታዩት?
በጣም በሚገርም ሁኔታ ለመንግስት ት/ቤት፣ በቃ ት/ቤት ነው፤ አካተትሽ አላካተትሽ የማንም ጉዳይ አይደለም። የአካል ጉዳት የአዕምሮ ጤና ችግር ምንድን ነው? ሰው ሲደርስበት ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ያልደረሰበት ሰው ነገ እኔ ላይ ይደርሳል ብሎም አያስብም፤ ጉዳዩንም ነገሬ አይልም። ትምህርት ቢሮ  ትምህርት ተደራሽ ይሁን ይላል፡፡ አካቶ ስናስተምር በግላቸው ቅን ሰዎች አሉ - በርቱ ጠንክሩ የሚሉና የሚያበረታቱ። እንደ መንግስት ግን ድጋፍ የለም፡፡ ግቢ ተከራይተን ነው የምናስተምረው፡፡ ቢያንስ ልዩ ፍላጎት ላላቸው የአስተማሪ ከፍለው የቦታ ነፃ እንዲሆንላቸው መሬት ስንጠይቅ መልስ የለም፡፡ እኛ ሶስት ቅርንጫፍ አለን፡፡ ለቤት ኪራይ በዓመት ወደ 10 ሚ. ብር እንከፍላለን። ሰራተኛም በርካታ ነው ያለን፡፡ እያንዳንዱ ልዩ ድጋፍ የሚፈልግ ልጅ አንድ አጋዥና ተንከባካቢ ይፈልጋል፡፡ ባህሪውና ፍላጎቱ የተለያየ ስለሆነ። ይህን ሁሉ አይቶ "ይህን እናግዛችሁ"  የሚለን አካል እስካሁን አላገኘንም፡፡
እስቲ በመጨረሻ በኦቲዝም ዙሪያ ስላሳተሙት መፅሐፍ ጥቂት ይንገሩን?
በ2013 ዓ.ም “ሁሉም በአንድ” የተሰኘ ተግባር ተኮር የህክምና መፅሐፍ ኦቲዝም ላለባቸው፣ የመማርና ትኩረት የማድረግ ችግር ላለባቸው፤ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸውና በአጠቃላይ ከንግግር ጋር የተያያዘ ችግር ላለባቸው ልጆች አዘጋጅቻለሁ፡፡ “ሁሉም በአንድ” ያልኩት ማንኛውም ድጋፍ የሚፈልግ ሰው ድክመቱ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡ ነገር ግን ብዙ ተሰጥኦ ብዙ ጸጋ አላቸው፡፡ እኔ ለረጅም ዓመት ከብዙ መቶዎች ልጆች ጋር አብሬ ስለቆየሁ ድክመት ብቻ አይደሉም፡፡ ልብ ብለን ካስተዋልን ለአለም የሚጠቅም ብዙ ጸጋ አላቸውና  ያንን ለመግለፅ ነው፡፡ መፅሐፉ 10 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን አስር እውነተኛ የወላጆችን ታሪኮች ይዟል፡፡ የደረሰባቸው ውጣ ውረድ፣ የትዳር መበተን፣ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት ት/ቤት ማጣት፣ ብዙ መከራ ያሳለፉ ወላጆች ታሪክ አለው፡፡ #ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆች የምታሳድጉ እኛም ይህንን ችግር አሳልፈናል፤ ነገር ግን ልጆቻችን እዚህ ስኬት ላይ ደርሰዋል; የሚል አስተማሪ ታሪክ የያዘ ነው፡፡
መፅሐፉ ማኑዋል ነው፡፡ መሬት ወርዶ በተግባር የሚሰራ  ባለሙያ ስለሌለ ወላጆች በተግባር ልጆቻቸውን ማገዝ ቢፈልጉ ምን ይስሩ፣ ከምን ይጀምሩ የሚለውን ሁሉ ያካተተ ነው፡፡ እኛ በግላችን ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ለማገዝ ዘርፈ ብዙ ስራ ለመስራት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እናንተም እንደ ሚዲያ ለጉዳዩ ሽፋን ለመስጠት ስለመጣችሁ በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡


 "--ቀደም ሲል እኮ አይደለም ውሎ አበል ጋዜጠኛው አንዲት ኩኪስ እንዳይቀምስ የሚከለክሉ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡ ውሎ አበል ካስፈለገም ራሳቸው ʻቺክንፊድʼ የሚሏት አይነት ትንሽዬ ብር ይወረውሩ ነበር፡፡ ለዚያውም ደግሞ የሂሳብ ክፍሉን አለቃና የገንዘብ ከፋዩዋን ግልምጫ ችሎ! እንደሱ አይነት ነገር ቀረ እንዴ!--"
            
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ለካስ ድራፍት ሠላሳ ብር ገባ የሚባለው ዝም ተብሎ አይደለም! አሀ...ምድረ ጋዜጠኛ ከውሎ አበል ብቻ በወር እስከ ሀያ ሺህ ብር (ትዌንቲ ታውዘንድ!) ያገኛል እየተባለ ድራፍቱ ሠላሳ ብር ላይ መቆሙም ተመስገን ነው ቂ...ቂ...ቂ...።  ኮሚክ እኮ ነው፡፡ አለ አይደል የአበል ፍራንክ በየወሩ ፔይሮል ላይ የሚፈረምበትን አልፎ ሲሄድ...ወይ የለቀቁ ክሮች  አሉ፣ ወይ ደግሞ ነገሮች በደንብ ሳይገቡን ዘመን ጥሎን እየሄደ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ እንዳልተጠራ የሰርግ ድንኳን ሰባሪ ሁሉ ውሎ አበልን በተመለከተ ጋዜጠኝነቱም ውስጥ ድንኳን ሰበራ የሚባል ነገር አለ መባሉን፣ ከተፈለገ መሀረብ እንደሚያስጨርስ ትራጄዲ፣ ከተፈለገም በሳቅ ሆድ እንደሚያቆስል ኮሜዲም መውሰድ ይቻላል፡፡ እናላችሁ... ፈረንጅ ʻኢንተረስቲንግʼ የሚላቸው እኮ እንዲህ አይነት ነገሮችን ነው፡፡
ምን ገረመኝ መሰላችሁ... መጀመሪያስ ቢሆን ድንኳን ሰበራ ብሎ ነገርን ምን አመጣው! ያው መቼም እዚችም፣ እዛችም የምንሰማቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ የመጡበት ሳይታወቅ አበል የሚወስዱ ምናምን የሚለው ትንሽ ያልጠረጠረ... ምናምን ነገር አያስብልም! አሀ...ልክ ነዋ... አበሉን የሚያከፋፍሉት ለማን እንደሰጡ፣ ፍራንክዬው ስንት ስንት እንደሆነ ምናምን ʻየሚጥፉትʼ ነገር የላቸውም እንዴ!
ጋዜጠኛ የብርወርቄ አበላቸው... ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር!
ጋዜጠኛ ሞላልኝ አበሉ....ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር!
አስተባባሪ ጋዜጠኛ አበሌ ዳር ከዳር .... ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር!
እያለ ሊቀጥል  ይችላል፡፡
ለነገሩማ...ለማሳበቅ ያህል...አንዳንድ ቦታ ውሎ አበል አዳዮቹም ʻለአምጪው እንዲሰጥ ህጉ  ያስገድዳልʼ የሚል ያልተጻፈ ህግ ያለ ይመስላል ሲባል ስንሰማ ኖረናል፡፡ እኔ የምለው ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... አለ አይደል...ያቺ ወሳኝ የነበረችው ሞዴል ስደስት ምናምን የሚሏት ነገር ቀረች ማለት ነው! ግርም የሚለው ደግሞ ጋዜጠኝነታቸው ወይም የትኛውን ድርጅት እንደሚወክሉ የማይታወቁ ሰዎች አሉ መባሉ ነው፡፡ እዚህ ሀገር እኮ በአግራሞትና አንዳንዴም በብሽቀት አለመሳቅ አይቻልም፡፡
እኔ የምለው.... ዘንድሮ የአበል ክፍያ ላለበት የፕሬስ መግለጫ ጋዜጠኞች ሲጠሩ እንደ እድር በጥሩምባ... “የሀገር ውስጥ ጋዜጠኛ ነን የምትሉ ሁሉ ከቀኑ ስምንት ሰዓት በእንትን አዳራሽ ፕሬስ መግለጫ ስለሚሰጥ በሰዓቱ እንድትገኙ። በፕሬስ መግለጫው ላይ የማይገኙ ጋዜጠኞች ወይም አርፍደው ለሚመጡ ጋዜጠኞች የቀበሌ ሰልፍ የማያስፈልግባት የውሎ አበል ... ስኳሯ እንዳማረቻቸው ትቀራለች፣” ይባላል እንዴ! ስሙኝማ...ስታንድአፕ ኮሜዲ አቅራቢዎች ...  የጋዜጠኝነት ድንኳን ሰባሪዎች የምትለዋ ነገር አሪፍ 'ኮንሴፕት' አይደለች!
እናላችሁ... የምር የተጻፉም፣ ያልተጻፉም ህጎች ተለውጠዋል ማለት ነው፡፡ ልክ ነዋ! ሊበራሊዝም ይሁን ምናምኒዝም ይሁን እንጃ እንጂ ይሄ የእውነተኛው ጋዜጠኛም የድንኳን ሰባሪውም ኪስና ቦርሳ እንዳይነፍስበት እያደረገ ላለው ʻውሎ አበልʼ ፈረንጅኛው ʻዊይርድʼ ከሚላቸው ሀገራችን--በተለይ ቦተሊካው--የተለያዩ ቡድኖች አንዱ ተነስቶ “መታሰቢያ ይታነጽለት፣” ቢል እንዳትገረሙ... “እዚች ሀገር ላይ ሊሆን አይችልም የሚባል ነገር አይኖርም!” የሚል ደረጃ ላይ ደርሰናልና! ለውጥማ አለ፣ (ቂ...ቂ...ቂ...) ቀደም ሲል እኮ አይደለም ውሎ አበል ጋዜጠኛው አንዲት ኩኪስ እንዳይቀምስ የሚከለክሉ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡ ውሎ አበል ካስፈለገም ራሳቸው ʻቺክንፊድʼ የሚሏት አይነት ትንሽዬ ብር ይወረውሩ ነበር፡፡ ለዚያውም ደግሞ የሂሳብ ክፍሉን አለቃና የገንዘብ ከፋዩዋን ግልምጫ ችሎ! እንደሱ አይነት ነገር ቀረ እንዴ!
እናላችሁ...ከዚህ በፊት የደጋገምናትን ነገር ለማስታወስ ያህል ስሙኝማ፡፡ በቀድሞ ጊዜ አንዲት በወቅቱ “ጥይት!” የምትባል ጋዜጠኛ፣ ጋሽ ይድነቃቸውን ‘እየጠየቀች’ ነበር አሉ፡፡ እናላችሁ ለደቂቃዎች ዲስኩር የምትመሳስል ነገር ካወራች በኋላ “እዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ?” የሚል ነገር ትጠይቃለች። ይሄኔ የጂብራልታሩ ዓለት ምን አሏት አሉ መሰላችሁ...“አንቺ ጨርሰሽው እኔ ምን እላለሁ!” ዘንድሮ እንዲህ የሚሉ ተጠያቂዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ ምን ይሆን ነበር መሰላችሁ... በቃ፣ የቃለ ምልልስ ስቱዲዮ ሁሉ የሸረሪቶች ʻወርልድ ካፕʼ ምናምን የሚካሄድበት ይሆን ነበር፡፡ አሀ... ለቃለ መጠይቅ የሚጋበዙ ሰዎች “እኔ እዛ የምሄደው ተቀምጬ የእነሱን ዲስኩር ለመስማት ነው እንዴ!” ብለው ድርሽ አይሏትማ!
ስሙኝማ...የምር ግን የውሎ አበልዋ ነገር እንዳለ ሆኖ...እንደው ከጊዜ ጋር የማይሻሻሉ ነገሮች መኖራቸው በዚህ ዘመን ግርም አይላችሁም! የተጠያቂውን ስም፣ ሥራ፣ በሆኑ ጉዳዮች ፈጽሟቸዋል የሚባሉ ነገሮችን ከዘረዘሩ በኋላ... “እንግዳችን ስምዎትንና የሥራ ድርሻዎትን ቢገልጹልን...; የሚሉት ምን የሚሉት ስቲፈን ሰከርነት ነው! ቂ...ቂ...ቂ... (አንተ ስቲፈን ሰከር የሚሉህ ‘እንግሊዙ’ ሰውዬ “የእንግሊዝ ሆዱ አይታወቅም...” ሲባልባት በኖረች ሀገር ውስጥ አንተን ለመምሰል ፈላጊዎች በዛንማ! “ስቲፈን ሰከርን መሆን ወይም አለመሆን...” ምናምን የሚል ወርክሾፕ ይዘጋጅልንማ! ልክ ነዋ...ከገባንበት አይቀር አንደኛውኑ እንዋኝበትና ይለይልን ብለን ነው፡፡)
እናላችሁ...ተጠያቂው እኮ “ራሱ ስሜንና የሥራ ድርሻዬን ከዘረዘረ በኋላ እንደገና ካሜራ ፊት የሚጠይቀኝ ʻፌክʼ ነው ብሎ ጠርጥሮኝ ይሆን እንዴ!” ሊል ይችላል፡፡ (ዘንድሮ የማይጠረጥርና ለመጠርጠር ምክንያት የማይሆን ነገር የለም ብለን ነው፡፡)
ታዲያላችሁ...መረጃን ይዞ ከመሞገትና አቋም ይዞ ʻከማፋጠጥʼ መሀል ያለው መስመር (ሳይኖር አይቀርም በማለት ነው!) ደመቅ ብሎ ይሰመርልን፡፡ እናማ...እኔ ተጠያቂ ብሆን አስቀድሜ የማጣራው ጠያቂዬ ወንበሩ ስር ወይ ፍልጥ ወይ ቆመጥ ደብቆ እንደሆን ነው። አሀ...ማን ሞኝ አለ! ዘንድሮʼኮ አንዳንዶቹ ቁጣቸው ያስፈራላ! የሚተማመኑበት የደበቁት ነገር ሳይኖራቸው እንደዛ መሸሻ በሌለበት ስቱድዮ ውስጥ አግተው ቴረር አይለቁብንም ነበራ! ሀሳብ አለን...ስቱድዮ ውስጥ የቦክስ ጓንት ይቀመጥልንማ! አሀ...ነገሩ ጠንከር ካለ “ወንዝ እንውረድና ይዋጣልን፣” ማለት ሳያስፈልግ እዛው የሚሆነው ሊሆን ይችላላ! “አቦ የጠራኸኝ ለቦክስ ከሆነ ጓንት ይሰጠንና እዚሁ ይለይልን፤ ይሞታል እንዴ!” ማለት ይቻላላ! ደግሞ ላይቭ መሆን አለበት!
ሀሳብ አለን ʻትዌንቲ ታውዘንድʼ ውሎ አበል ምናምን ለማያውቁት ለቀድሞ ጋዜጠኞች ሞራል መጠበቂያ ʻኮመፕንሴሽን ይሰጥልንማ! አሀ..ልከ ነዋ! እነሱ ያንን ሰማያዊ ካኪ እያስያዙ ʻመስዋእትነትʼ ባይከፍሉ ʻትዌንቲ ታውዘንድʼ ላይ አይደረስም ነበራ! ስሙኝማ... ከዚህ ቀደም ያወራናት...አንድ መሀል ከተማ የነበረች ባለመጠጥ ቤት ደንበኞቿ ጋዜጠኞች፣ በዱቤ እየላፉ እዳ አንከፍል ቢሏት፣ ያስያዟቸውን ካኪዎች ሰብስባ፣ በጊዜው የነበሩት ሚኒስትር ቢሮ ገብታለች የሚባል ወሬ አለ፡፡ (እነ እንትና... ስንትና ስንት ነገር እየታተመ በሚወጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ ምነው የዛ ዘመን የጋዜጠኝነት ‘አድቬንቸር’ መጽሐፍ ሆኖ አልወጣምሳ! ልክ ነዋ...አሁን እኮ አድቬንቸር የሚባሉ ነገሮች ለመኖራቸው፣ ቃሉ ራሱ ያለም አይመስልም፡፡)
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንድ የብሮድካስት ጋዜጠኛ እስኪበቃው ‘ሲፑ’ን በመገልበጥ ይታወቅ ነበር...በማንኛውም ሰዓት ማለት ነው፡፡ እናማ፣ ሁልጊዜ ነበር በአለቆች ማስጠንቀቂያ አልፎ፣ አልፎም ቅጣት የሚደርስበት ይባል ነበር፡፡ ነገርዬውማ ‘ሲፑዋ’ ላይ የሚበረታው እሱ ብቻ ስለነበረ ሳይሆን በቃ እድሉ ሆነና ዓይን ውስጥ ስለገባ ሳይሆን አይቀርም! ቂ...ቂ...ቂ... ታዲያማ...አንድ ጊዜ  ለ‘ሲፕ’ ያለመስነፋቸው በአደባባይ የሚታወቅላቸው ሚኒስትር ተሹመው ይመጣሉ፡፡ ይሄኔ እሱዬው ለሥራ ጓደኞቹ ምን ቢል ጥሩ... “ከእንግዲህ አንድሽ ታናግሪኝና ዋጋሽን ታገኛለሽ!” ጋዜጠኛ ቢሮ አካባቢ ሲታጣ አለቆቹ “እስቲ እንትን ባር ሄዳችሁ ፈልጉት፣ ይባልበት የነበረ ዘመን ‘ፐረሰናል ፍሪደም’ የሚከበርበት አይመስላችሁም! ቂ...ቂ...ቂ...
ያኔ ታዲያ አይደለም በየወሩ ከውሎ አበል ‘ትዌንቲ ታውዘንዷንʼ ላፍ ሊያደርግ ጋዜጠኛው አስር ሺህና ሀያ ሺህ የሚባሉ ቁጥሮችን የሚያውቃቸው በሆነ ጉዳይ ሰልፍ ስለወጣ ህዝብ ብዛት ምናምን ዜና ሲጽፍ ወይም ሲያነብ ነበር፡፡ እናማ ለውጥማ አለ የምንለው በምክንያት ነው ለማለት ነው፡፡
ስሙኝማ... እግረ መንገድ በዜናዎች አዘጋገብ የሆነ ነገር ጠቀስ አድርጎ ለማለፍ፣ ይሄ ቅጽል ማብዛት የሚሉት ነገር ትንሽ ነገሮችን እያበላሸ አይመስላችሁም! እናላችሁ...እሺ ባላየነው ነገር አንድ መቶ አንድ ቅጽል ቢደረደር አናውቅምና ሊሆን ይችላል በሚል ጭጭ ብለን እንቀበላለን። ግን አሁን በዩቲዩብና በመሳሰሉት ስለ ዩክሬይን እየዘገብን ያለነውን ልብ ብላችሁልኛል? እንደ አንዳንዶቻችን አዘጋገብ እኮ በዩክሬይን ምክንያት ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ተነስቶ ነበር፡፡ የምር!
“አለቀለት! ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የመጀመሪያ ጥይት ተተኮሰች!” ወይም ደግሞ...
“ፑቲን በማንኛውም ሰዓት ኑክሌር እንዲተኮስ ትእዛዝ ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡”
ነገርዬውማ ዘገባውን የሚያቀርቡልን ሆነ ብለው ለማሳሳት ሳይሆን አንዱ ትልቅ ችግር የሚያገኟቸውን ዜናዎች የሚተረጉሙበት መንገድ፣ እንዲሁም ዜናዎቻቸውን የሚወስዱባቸውን ሳይቶች መምረጡ ላይ ይመስለናል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ምኑንም አይነት ወሬ ሰበር ዜና የማድረግ ልማድ ነው፡፡ ፕላስ ...
ይልቅ የ‘ትዌንቲ ታውዘንዷ’ የውሎ አበል ወሬ ከድንኳን ሰባሪ አበል ተቀባዮች ጋር ‘ፕላስ’ ስትደረግ ሰበር ለመሆን ምን ይቀራታል!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

   በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ብቻ የሚንቀሳቀስና የራሱ የሆነ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያሉት ቢላን የተሰኘ አዲስ የሚዲያ ተቋም ተመስርቶ  ስራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡
ሚዲያው ሴቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራና ለሴቶች መብቶች መከበር የሚታገል እንደሆነ የዘገበው ቮይስ ኦፍ አሜሪካ፤ ከጋዜጠኞች እስከ አስተዳደር ሰራተኞች ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ብቻ የሚንቀሳቀስ እንደሆነና የተለያዩ ፈተናዎች ለሚያጋጥሟቸው የሶማሊያ ሴት ጋዜጠኞች መልካም እድል እንደሚፈጥርም አመልክቷል፡፡
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተቋቋመው ቢላን ሚዲያ፣ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭቱን ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ የሴቶች ጥቃት፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የስራ ፈጠራና የመሳሰሉ ጉዳዮችን የተመለከቱ ይዘቶችን እንደሚያቀርብም አመልክቷል፡፡


Page 6 of 602